ሰኔ
ሰኞ፣ ሰኔ 1
አብ በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ [ይሰጣችኋል]።—ዮሐ. 15:16
ይህ ቃል ሐዋርያቱን በጣም አበረታቷቸው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም! ሐዋርያቱ በወቅቱ ባይገነዘቡትም መሪያቸው የሚሞትበት ጊዜ ተቃርቦ ነበር፤ ያም ቢሆን እርዳታ የሚያገኙበት ዝግጅት ተደርጎላቸዋል። የመንግሥቱን መልእክት እንዲሰብኩ የተሰጣቸውን ተልእኮ ለመወጣት የሚያስፈልጋቸውን ማንኛውንም እርዳታ ለማግኘት የሚያቀርቡትን ጸሎት፣ ይሖዋ እንደሚሰማ መተማመን ይችሉ ነበር። ደግሞም ከዚያ ብዙም ሳይቆይ፣ እርዳታ ለማግኘት ያቀረቡትን ጸሎት ይሖዋ እንደመለሰላቸው ተመልክተዋል። (ሥራ 4:29, 31) ዛሬም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በጽናት ፍሬ ስናፈራ የኢየሱስ ወዳጆች የመሆን መብት እናገኛለን። በተጨማሪም የመንግሥቱን ምሥራች ስንሰብክ የሚያጋጥሙንን እንቅፋቶች ለመወጣት እንዲረዳን የምናቀርበውን ጸሎት ይሖዋ እንደሚመልስልን መተማመን እንችላለን። (ፊልጵ. 4:13) ለጸሎታችን ምላሽ ማግኘትና ከኢየሱስ ጋር ወዳጅነት መመሥረት በመቻላችን ምንኛ አመስጋኞች ነን! ከይሖዋ ያገኘናቸው እነዚህ ስጦታዎች ፍሬ ማፍራታችንን እንድንቀጥል ያበረታቱናል።—ያዕ. 1:17፤ w18.05 21 አን. 17-18
ማክሰኞ፣ ሰኔ 2
እርስ በርስ እንበረታታ፤ ደግሞም ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን እናድርግ።—ዕብ. 10:24, 25
በኢየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩት አይሁዳውያን ክርስቲያኖች፣ ከአምስት ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ “የይሖዋ ቀን” መቅረቡን የሚያሳዩ ማስረጃዎችን ይመለከታሉ፤ እንዲሁም ኢየሱስ በሰጣቸው ምልክት መሠረት ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሲሉ ከተማዋን ለቀው የሚወጡበት ጊዜ መድረሱን ይገነዘባሉ። (ሥራ 2:19, 20፤ ሉቃስ 21:20-22) በዚያን ወቅት የይሖዋ ቀን የመጣው በ70 ዓ.ም. ማለትም ሮማውያን ይሖዋ በኢየሩሳሌም ላይ ያስተላለፈውን የቅጣት ፍርድ ባስፈጸሙበት ጊዜ ነው። በዛሬው ጊዜም የይሖዋ “ታላቅና እጅግ የሚያስፈራ” ቀን እንደቀረበ እንድናምን የሚያደርጉ በቂ ማስረጃዎች አሉን። (ኢዩ. 2:11) ነቢዩ ሶፎንያስ “ታላቁ የይሖዋ ቀን ቅርብ ነው! ቅርብ ነው፤ ደግሞም በፍጥነት እየቀረበ ነው!” ብሏል። (ሶፎ. 1:14) ይህ ትንቢታዊ ማስጠንቀቂያ ለዘመናችንም ይሠራል። የይሖዋ ቀን በቀረበበት ጊዜ ላይ ስለምንኖር ጳውሎስ “እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ” በማለት የሰጠው ምክር እኛንም ይመለከታል። (ዕብ. 10:24) በመሆኑም አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ጊዜ ሁሉ ወንድሞቻችንን ማበረታታት እንድንችል ለእነሱ ይበልጥ ትኩረት መስጠት ይኖርብናል። w18.04 20 አን. 1-2
ረቡዕ፣ ሰኔ 3
ደፋርና ብርቱ ሁን . . . አምላክህ ይሖዋ በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር ስለሆነ አትሸበር፤ አትፍራ።—ኢያሱ 1:9
ይሖዋ፣ የአምላክን ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር የማስገባት ኃላፊነት ለተጣለበት ለኢያሱ እንዴት ያለ ግሩም ማበረታቻ ሰጥቶታል! ይሖዋ አገልጋዮቹን በግለሰብ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በቡድን ደረጃም አበረታቷቸዋል። ወደፊት በባቢሎን በግዞት ለሚኖረው ሕዝቡ የሚከተለውን የሚያጽናና ሐሳብ አስቀድሞ ተናግሯል፦ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ። እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ። አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ፤ በጽድቅ ቀኝ እጄ አጥብቄ እይዝሃለሁ።” (ኢሳ. 41:10) ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ ክርስቲያኖችም ሆነ በዛሬው ጊዜ ላሉ ሕዝቦቹ ተመሳሳይ ማረጋገጫ ሰጥቷቸዋል። (2 ቆሮ. 1:3, 4) ኢየሱስም ከአባቱ ማበረታቻ አግኝቷል። በተጠመቀበት ወቅት “በጣም የምደሰትበት የምወደው ልጄ ይህ ነው” የሚል ድምፅ ከሰማይ ሰምቷል። (ማቴ. 3:17) እነዚህ ቃላት ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነባቸው ጊዜያት ሁሉ ምንኛ አበረታተውት ይሆን! w18.04 16 አን. 3-5
ሐሙስ፣ ሰኔ 4
ከመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ ግን አትብላ።—ዘፍ. 2:17
በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ብዙ ሰዎች፣ ይሖዋ ለአዳም የሰጠውን ትእዛዝ ሲያነቡ አዳም የፈለገውን የማድረግ ነፃነት እንደተነፈገ ሆኖ ይሰማቸዋል። እንዲህ የሚሰማቸው፣ በመምረጥ ነፃነት እና መልካም ወይም ክፉ የሆነውን ነገር በመወሰን መብት መካከል ልዩነት እንዳለ ስላልተገነዘቡ ሊሆን ይችላል። አዳምና ሔዋን፣ አምላክን ለመታዘዝ ወይም ላለመታዘዝ የመምረጥ ነፃነት ነበራቸው። ይሁንና የትኛው መልካም፣ የትኛው ደግሞ ክፉ እንደሆነ የመወሰን መብት ያለው ይሖዋ ብቻ ነው፤ በኤደን ገነት ውስጥ የነበረው “የመልካምና ክፉ እውቀት ዛፍ” የሚያመለክተውም ይህን ነበር። (ዘፍ. 2:9) ይሖዋ ከዛፉ ፍሬ እንዳይበሉ ለአዳምና ለሔዋን ትእዛዝ የሰጣቸው፣ እውነተኛ ነፃነት ለማግኘት እሱን መታዘዝ እንዳለባቸው ለማስተማር ነው። ነገር ግን የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን አምላክን ላለመታዘዝ መረጡ። ታዲያ አዳምና ሔዋን ያደረጉት ምርጫ ውሎ አድሮ የበለጠ ነፃነት አስገኘላቸው? በጭራሽ። ራሳቸውን በራሳቸው ለመምራት ያደረጉት ጥረት የነበራቸውን እውነተኛ ነፃነት አሳጥቷቸዋል። w18.04 5-6 አን. 9-12
ዓርብ፣ ሰኔ 5
በጭንቃቸው ሁሉ እሱ ተጨነቀ።—ኢሳ. 63:9
ይሖዋ መከራ እየደረሰባቸው ላሉ አገልጋዮቹ ከመራራት ባለፈ እነሱን ለመርዳት ሲል እርምጃ ይወስዳል። ለምሳሌ እስራኤላውያን በግብፅ ባርነት እየማቀቁ በነበሩበት ወቅት ሥቃያቸው የተሰማው ሲሆን ችግራቸውን ለማስወገድ እርምጃ ወስዷል። ይሖዋ ሙሴን እንዲህ ብሎታል፦ “የሕዝቤን መከራ በእርግጥ አይቻለሁ፤ . . . የሚያሰሙትን ጩኸት ሰምቻለሁ፤ እየደረሰባቸው ያለውንም ሥቃይ በሚገባ አውቃለሁ። እኔም ከግብፃውያን እጅ ልታደጋቸው . . . እወርዳለሁ።” (ዘፀ. 3:7, 8) ይሖዋ ሕዝቡ ለሆኑት እስራኤላውያን ስለራራ ከባርነት ነፃ አውጥቷቸዋል። ከብዙ ዘመናት በኋላ ደግሞ እስራኤላውያን በተስፋይቱ ምድር ሳሉ ጠላት ጥቃት ሰንዝሮባቸው ነበር። በዚህ ጊዜ ይሖዋ ምን አደረገ? “በሚጨቁኗቸውና በሚያንገላቷቸው ሰዎች የተነሳ ሲቃትቱ” በማየቱ ‘አዝኗል።’ ለሕዝቡ የነበረው ርኅራኄ አሁንም እነሱን ለመርዳት ሲል እርምጃ እንዲወስድ ማለትም እስራኤላውያንን ከጠላቶቻቸው የሚታደጓቸው መሳፍንት እንዲያስነሳ አድርጎታል።—መሳ. 2:16, 18፤ w19.03 15 አን. 4-5
ቅዳሜ፣ ሰኔ 6
እናት የምታጠባውን ልጇን ልትረሳ ትችላለች? ከማህፀኗ ለወጣውስ ልጅ አትራራም? እነዚህ ሴቶች ቢረሱ እንኳ እኔ ፈጽሞ አልረሳሽም።—ኢሳ. 49:15
ከአሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ የመጀመሪያዎቹ ሁለት ትእዛዛት፣ እስራኤላውያን ይሖዋን ብቻ እንዲያመልኩና ከጣዖት አምልኮ እንዲርቁ የሚያሳስቡ ናቸው። (ዘፀ. 20:3-6) ይሖዋ እነዚህን ትእዛዛት የሰጠው ለራሱ ጥቅም ሳይሆን ለሕዝቡ ጥቅም ሲል ነው። ሕዝቡ ሌሎች ብሔራት የሚያመልኳቸውን አማልክት ሲያመልኩ መከራ ይደርስባቸው ነበር። በተቃራኒው ደግሞ ሕዝቦቹ ለእሱ ታማኝ ሲሆኑና እርስ በርስ ባላቸው ግንኙነት ፍትሐዊ ሲሆኑ ይባርካቸው ነበር። (1 ነገ. 10:4-9) ይሖዋ እሱን እንደሚያመልኩ የሚናገሩ አንዳንድ ሰዎች መሥፈርቶቹን ችላ በማለት በሕዝቡ ላይ ለሚያደርሱት ጉዳት ተጠያቂ አይደለም። ሆኖም ይሖዋ እንደሚወደንና የሚፈጸምብንን ፍትሕ የጎደለው ድርጊት እንደሚመለከት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። አንዲት እናት የልጇ ሥቃይ ከሚሰማት በላይ ይሖዋ ሥቃያችን ይሰማዋል። ወዲያውኑ ጣልቃ ገብቶ እርምጃ ባይወስድ እንኳ ንስሐ የማይገቡ ኃጢአተኞችን በሌሎች ላይ ለፈጸሙት በደል ተገቢ ነው ባለው ጊዜ ተጠያቂ ያደርጋቸዋል። w19.02 22 አን. 13-15
እሁድ፣ ሰኔ 7
የእኔ ሳይሆን የአንተ ፈቃድ ይፈጸም።—ሉቃስ 22:42
ከመታሰቢያው በዓል በፊት ባሉት ሳምንታት የምናደርጋቸው ስብሰባዎች አብዛኛውን ጊዜ ኢየሱስ በተወው ምሳሌ እንዲሁም ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ባሳየው ትሕትና ላይ ያተኮሩ ናቸው። እነዚህ ስብሰባዎች በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ብንሆንም እንኳ ልክ እንደ ኢየሱስ ትሑት እንድንሆንና የይሖዋን ፈቃድ እንድንፈጽም ያነሳሱናል። ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት ባሉት ቀናት ድፍረት ያሳየው እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክሩ። ተቃዋሚዎቹ ብዙም ሳይቆይ እንደሚያዋርዱት፣ እንደሚገርፉትና እንደሚገድሉት ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። (ማቴ. 20:17-19) ያም ቢሆን ሞትን ለመጋፈጥ ፈቃደኛ ሆኗል። አልፎ የሚሰጥበት ጊዜ ሲደርስ፣ በጌትሴማኒ ከእሱ ጋር አብረው ለነበሩት ታማኝ ሐዋርያቱ “ተነሱ፣ እንሂድ። እነሆ፣ አሳልፎ የሚሰጠኝ ቀርቧል” ብሏቸዋል። (ማቴ. 26:36, 46) ከዚያም መሣሪያ የያዙ ሰዎች ሊያስሩት ሲመጡ ወደፊት ራመድ ብሎ የሚፈልጉት ሰው እሱ እንደሆነ የነገራቸው ከመሆኑም ሌላ ሐዋርያቱን እንዲተዉአቸው አዟቸዋል። (ዮሐ. 18:3-8) ኢየሱስ ያሳየው ድፍረት እንዴት አስደናቂ ነው! በዛሬው ጊዜ ያሉ ቅቡዓን ክርስቲያኖችና የሌሎች በጎች አባላት ድፍረት በማሳየት ረገድ ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት ያደርጋሉ። w19.01 27-28 አን. 7-8
ሰኞ፣ ሰኔ 8
የዋህነትን ፈልጉ።—ሶፎ. 2:3
አንድ ሠዓሊ የተለያዩ ማራኪ ቀለሞችን ተጠቅሞ አንድ ሥዕል እንደሚሥል ሁሉ እኛም የዋህ ለመሆን የተለያዩ ማራኪ ባሕርያትን ማዳበር ይኖርብናል። ከእነዚህ ባሕርያት መካከል ዋና ዋናዎቹ ትሕትና፣ ታዛዥነት፣ ገርነትና ድፍረት ናቸው። የአምላክን ፈቃድ ለመታዘዝ የሚፈልጉት ትሑት የሆኑ ሰዎች ብቻ ናቸው። ከአምላክ ፈቃድ መካከል አንዱ ደግሞ ገር እንድንሆን ነው። (ማቴ. 5:5፤ ገላ. 5:23) የአምላክን ፈቃድ ማድረጋችን ሰይጣንን ያስቆጣዋል። ስለዚህ ትሑትና ገር ብንሆንም በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያሉ በርካታ ሰዎች ይጠሉናል። (ዮሐ. 15:18, 19) በመሆኑም ሰይጣንን ለመቋቋም ድፍረት ያስፈልገናል። የየዋህነት ተቃራኒ ኩራት፣ ቁጣን አለመቆጣጠርና ይሖዋን አለመታዘዝ ነው። እነዚህ ባሕርያት ሰይጣንን ጥሩ አድርገው ይገልጹታል። በእርግጥም ሰይጣን የዋህ የሆኑ ሰዎችን የሚጠላ መሆኑ ምንም አያስገርምም! እነዚህ ሰዎች ሰይጣን የሌሉትን ግሩም ባሕርያት ስለሚያንጸባርቁ የእሱ ክፋት በግልጽ እንዲታይ ያደርጋሉ። ከዚህም በላይ ውሸታም እንደሆነ ያጋልጣሉ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሰይጣን ምንም ነገር ቢናገር ወይም ቢያደርግ፣ የዋህ የሆኑ ሰዎች ይሖዋን ማገልገላቸውን እንዲያቆሙ ማድረግ አይችልም!—ኢዮብ 2:3-5፤ w19.02 8-9 አን. 3-5
ማክሰኞ፣ ሰኔ 9
እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ።—ኢሳ. 41:10
ይሖዋ የባቢሎን ነዋሪዎች ፍርሃት እንደሚያድርባቸው ያውቅ ነበር። ባቢሎን በኃያሉ የሜዶ ፋርስ ሠራዊት ጥቃት ይሰነዘርባታል። ይሖዋ ሕዝቡን ከባቢሎን ምርኮ ነፃ ለማውጣት ይህን ሠራዊት ይጠቀምበታል። (ኢሳ. 41:2-4) ባቢሎናውያንና በዚያ የሚኖሩት ሌሎች ሕዝቦች ጠላት እየተቃረበ መሆኑን ሲያውቁ እርስ በርስ “አይዞህ፣ በርታ” በመባባል አንዳቸው ሌላውን ለማደፋፈር ይሞክራሉ። ከዚህም ሌላ ጥበቃ እንደሚያደርጉላቸው ተስፋ በማድረግ ተጨማሪ ጣዖታትን ይሠራሉ። (ኢሳ. 41:5-7) በሌላ በኩል ግን ይሖዋ እንደሚከተለው በማለት በግዞት ያሉትን አይሁዳውያን አረጋግቷቸዋል፦ “እስራኤል ሆይ፣ አንተ ግን [በዙሪያህ ካሉት ሕዝቦች በተለየ] አገልጋዬ ነህ . . . እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ።” (ኢሳ. 41:8-10) ይሖዋ “እኔ አምላክህ ነኝ” እንዳለ ልብ በሉ። ይሖዋ እነዚህን ቃላት በመናገር ታማኝ አገልጋዮቹን እንዳልረሳቸውና አሁንም ሕዝቦቹ እንደሆኑ አረጋግጦላቸዋል። “እሸከማችኋለሁ . . . እንዲሁም እታደጋችኋለሁ” ብሏቸዋል። እነዚህ የሚያጽናኑና የሚያበረታቱ ቃላት በግዞት የተወሰዱትን አይሁዳውያን እንዳጠናከሯቸው ምንም ጥርጥር የለውም።—ኢሳ. 46:3, 4፤ w19.01 4 አን. 8
ረቡዕ፣ ሰኔ 10
“አንተ የምወድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” የሚል ድምፅ ከሰማያት መጣ።—ማር. 1:11
ይሖዋ ከሰማይ እንደተናገረ ከሚገልጹት ሦስት ዘገባዎች መካከል የመጀመሪያው የሚገኘው በማርቆስ 1:9-11 ላይ ነው። ይሖዋ “አንተ የምወድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ ደስ ይለኛል” በማለት ተናግሯል። ኢየሱስ አባቱ ለእሱ ያለውን ፍቅርና በእሱ ላይ ያለውን እምነት ሲገልጽ ሲሰማ ልቡ ምን ያህል ተነክቶ ይሆን! ይሖዋ የተናገራቸው ቃላት ስለ ኢየሱስ ሦስት አስፈላጊ እውነታዎችን ያረጋግጣሉ። አንደኛ፣ ኢየሱስ የይሖዋ ልጅ ነው። ሁለተኛ፣ ይሖዋ ልጁን ይወደዋል። ሦስተኛ፣ ይሖዋ በልጁ ደስ ይሰኛል። ይሖዋ ‘አንተ ልጄ ነህ’ ብሎ በመናገር ከሚወደው ልጁ ከኢየሱስ ጋር አዲስ ዓይነት ዝምድና እንደመሠረተ አሳይቷል። ኢየሱስ ሰማይ ላይ ሳለ የአምላክ መንፈሳዊ ልጅ ነበር። በተጠመቀበት ወቅት ግን በመንፈስ ቅዱስ ተቀብቷል። በዚህ ወቅት ይሖዋ በመንፈስ የተቀባው ልጁ ኢየሱስ ወደ ሰማይ በመመለስ ንጉሥና ሊቀ ካህናት ሆኖ የማገልገል ተስፋ እንዳለው ጠቁሟል። (ሉቃስ 1:31-33፤ ዕብ. 1:8, 9፤ 2:17) ስለዚህ ኢየሱስ ሲጠመቅ አባቱ ‘አንተ ልጄ ነህ’ ያለበት በቂ ምክንያት ነበረው።—ሉቃስ 3:22፤ w19.03 8 አን. 3-4
ሐሙስ፣ ሰኔ 11
ይሖዋን የሚጻረር ጥበብ . . . ከንቱ ነው።—ምሳሌ 21:30
በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ መጥፎ ምክር የሰጠው አካል ሰይጣን ነው። ሰይጣን በእብሪተኝነት ተነሳስቶ ራሱን አማካሪ አድርጎ በመሾም ለሔዋን አንድ ምክር ሰጣት፤ እሷና ባሏ ሕይወታቸውን በራሳቸው መንገድ ቢመሩ ይበልጥ ደስተኞች እንደሚሆኑ ነገራት። (ዘፍ. 3:1-6) ሰይጣን ይህን ምክር የሰጣት በራስ ወዳድነት ተነሳስቶ ነው። አዳምና ሔዋን እንዲሁም ወደፊት የሚወልዷቸው ልጆች ከይሖዋ ይልቅ እሱን እንዲያመልኩትና ለእሱ እንዲገዙለት ፈልጎ ነበር። ሆኖም አዳምና ሔዋን ያላቸውን ነገር ሁሉ የሰጣቸው ይሖዋ ነው፤ ይሖዋ የትዳር አጋር፣ ውብ የሆነ መኖሪያና ለዘላለም ሊኖር የሚችል ፍጹም አካል ሰጥቷቸዋል። የሚያሳዝነው ግን አዳምና ሔዋን አምላክን ባለመታዘዛቸው ራሳቸውን ከእሱ ጋር አቆራረጡ። እንደምናውቀው ይህ ውሳኔያቸው አሳዛኝ ውጤት አስከትሏል። ከዋናው ግንድ ላይ እንደተቆረጠ አበባ ቀስ በቀስ እየጠወለጉ መሄድና ወደ ሞት ማዝገም ጀመሩ። ልጆቻቸውም የኃጢአትና ኃጢአት የሚያስከትለው ውጤት ሰለባ ሆኑ። (ሮም 5:12) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ በርካታ ሰዎች ልክ እንደ አዳምና ሔዋን ለአምላክ ለመገዛት አሻፈረኝ ብለዋል። ሕይወታቸውን በራሳቸው መንገድ መምራት ይፈልጋሉ። (ኤፌ. 2:1-3) ይህ አካሄዳቸው ያስከተለው ውጤት የዛሬው የዕለት ጥቅስ የሚናገረው ሐሳብ እውነት እንደሆነ በግልጽ ያሳያል። w18.12 20 አን. 3-4
ዓርብ፣ ሰኔ 12
የምንናገረው . . . ከሰው ጥበብ በተማርነው ቃል አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ መንፈሳዊ ጉዳዮችን በመንፈሳዊ ቃል ስናብራራ ከመንፈስ በተማርነው ቃል እንናገራለን።—1 ቆሮ. 2:13
ሐዋርያው ጳውሎስ ብሩሕ አእምሮ ያለው፣ የተማረና ቢያንስ ሁለት ቋንቋዎችን መናገር የሚችል ሰው ነበር። (ሥራ 5:34፤ 21:37, 39፤ 22:2, 3) ሆኖም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር መወሰን ሲያስፈልገው በዓለማዊ ጥበብ ከመመራት ይልቅ በቅዱሳን መጻሕፍት ለመመራት መርጧል። (ሥራ 17:2፤ 1 ቆሮ. 2:6, 7) በመሆኑም በአገልግሎቱ ስኬታማ ሊሆንና ዘላለማዊ ሽልማት እንደሚያገኝ ተስፋ ሊያደርግ ችሏል። (2 ጢሞ. 4:8) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው የአምላክ አስተሳሰብ ከዓለም አስተሳሰብ የላቀ ነው። በአምላክ አስተሳሰብ መመራት እውነተኛ ደስታና ስኬት ያስገኝልናል። ሆኖም ይሖዋ የእሱን አስተሳሰብ እንድንቀበል አያስገድደንም። ‘ታማኝና ልባም ባሪያም’ ሆነ ሽማግሌዎች የሌሎችን አስተሳሰብ ለመቆጣጠር አይሞክሩም። (ማቴ. 24:45፤ 2 ቆሮ. 1:24) ከዚህ ይልቅ እያንዳንዳችን አስተሳሰባችንን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር የማስማማት ኃላፊነት አለብን። w18.11 20-21 አን. 12-13
ቅዳሜ፣ ሰኔ 13
ሐዘንና ሲቃም ከዚያ ይርቃሉ።—ኢሳ. 35:10
አምላክ ሕዝቦቹ ወደ ትውልድ አገራቸው ከተመለሱ በኋላ ከባድና አደገኛ ሁኔታዎች እንደማያጋጥሟቸው እንዲሁም አራዊት ወይም የአውሬነት ባሕርይ ያላቸው ሰዎች ጥቃት ይሰነዝሩብኛል የሚል ስጋት ሊያድርባቸው እንደማይገባ በኢሳይያስ በኩል አስቀድሞ ነግሯቸው ነበር። ልጆችም ሆኑ አዋቂዎች የሚያሰጋቸው ምንም ነገር አይኖርም። (ኢሳ. 11:6-9፤ 35:5-10፤ 51:3) በተጨማሪም ኢሳይያስ “ውኃ ባሕርን እንደሚሸፍን ምድርም በይሖዋ እውቀት ትሞላለች” ብሏል፤ በይሖዋ እውቀት የሚሞላው የእስራኤል ብሔር ብቻ ሳይሆን መላዋ ምድር እንደሆነች ልብ በል። ኢሳይያስ ከግዞት የተመለሱት ሰዎች ከእንስሳትም ሆነ ከሰዎች ጥቃት እንደማይሰነዘርባቸው በድጋሚ ተናግሯል። የሚኖሩበት ምድር ልክ እንደ ኤደን ገነት በቂ ውኃ ስለሚያገኝ የተትረፈረፈ ምርት ይሰጣል። (ዘፍ. 2:10-14፤ ኤር. 31:12) ሆኖም የዚህ ትንቢት ፍጻሜ ይህ ብቻ ነው? ከግዞት የተመለሱት ሰዎች ተአምራዊ በሆነ መንገድ ከሕመማቸው እንደተፈወሱ የሚያሳይ ማስረጃ የለም። ለምሳሌ ዓይነ ስውራን ዓይናቸው አልበራም። በመሆኑም አምላክ ይህን ተስፋ የሰጠው የታመሙ ሰዎችን ቃል በቃል የሚፈውስበት ጊዜ እንደሚመጣ ለመጠቆም ነበር። w18.12 5 አን. 11-12
እሁድ፣ ሰኔ 14
በእውነት ውስጥ [ተመላለሱ]።—3 ዮሐ. 3
በእውነት ጎዳና ላይ የምናደርገው ጉዞ ቀጣይ የሆነ ሂደት ነው፤ ለዘላለም በዚህ ጎዳና ላይ መጓዛችንን መቀጠል እንፈልጋለን። ታዲያ በእውነት ጎዳና ላይ ለመሄድ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙትን ውድ እውነቶች አጥኑ እንዲሁም ባጠናችሁት ነገር ላይ አሰላስሉ። አዎ፣ እነዚህን ውድ እውነቶች የምትመገቡበት ቋሚ ጊዜ በመመደብ እውነትን ግዙ። እንዲህ ማድረጋችሁ ለእውነት ያላችሁን አድናቆት ለማሳደግና እውነትን ፈጽሞ ላለመሸጥ ያደረጋችሁትን ቁርጥ ውሳኔ ለማጠናከር ይረዳችኋል። ምሳሌ 23:23 እውነትን ከመግዛት በተጨማሪ “ጥበብን፣ ተግሣጽንና ማስተዋልን” መግዛት እንዳለብን ይናገራል። እውቀት ብቻውን በቂ አይደለም። ያወቅነውን እውነት በሕይወታችን ውስጥ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። ማስተዋል ካለን ይሖዋ ባስተማረን ትምህርቶች መካከል ያለውን ተያያዥነት እንገነዘባለን። ጥበብ የተማርነውን ነገር በሥራ ላይ እንድናውል ያነሳሳናል። አንዳንድ ጊዜ እውነት በየትኛው አቅጣጫ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚያስፈልገን በመጠቆም ይገሥጸናል። እንግዲያው እንዲህ ላለው መመሪያ ምንጊዜም አዎንታዊ ምላሽ እንስጥ። ምክንያቱም ተግሣጽ ከብር የበለጠ ዋጋ አለው።—ምሳሌ 8:10፤ w18.11 9 አን. 3፤ 11 አን. 13-14
ሰኞ፣ ሰኔ 15
እውነትን . . . ግዛ፤ ፈጽሞም [አትሽጠው]።—ምሳሌ 23:23
በሕይወትህ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የምትሰጠው ነገር ምንድን ነው? ይህን ነገር አነስተኛ ዋጋ ባለው ሌላ ነገር ለመለወጥ ፈቃደኛ ትሆናለህ? ራሳቸውን ለወሰኑ የይሖዋ አገልጋዮች የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ግልጽ ነው። በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ የምንሰጠው ከይሖዋ ጋር ላለን ዝምድና ሲሆን ይህን በምንም ነገር መለወጥ አንፈልግም። በተጨማሪም በሰማይ ካለው አባታችን ጋር ዝምድና ለመመሥረት ያስቻለንን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ከፍ አድርገን እንመለከታለን። (ቆላ. 1:9, 10) እስቲ ታላቁ አስተማሪያችን ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የሚያስተምረንን ውድ እውነቶች ለማሰብ እንሞክር! ትልቅ ትርጉም ስላለው ስሙ እንዲሁም ማራኪ ስለሆኑት ባሕርያቱ አስተምሮናል። በፍቅር ተነሳስቶ በልጁ በኢየሱስ በኩል ስላደረገልን አስደናቂ የሆነ የቤዛ ዝግጅት ገልጾልናል። በተጨማሪም ስለ መሲሐዊው መንግሥት ያሳወቀን ከመሆኑም ሌላ ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የመኖር ተስፋ ሰጥቶናል። ከዚህም በላይ ምን ዓይነት ምግባር ማሳየት እንዳለብን አስተምሮናል። ወደ ፈጣሪያችን መቅረብ እንድንችል የሚረዱንን እነዚህን እውነቶች ከፍ አድርገን እንመለከታቸዋለን። ምክንያቱም እነዚህ እውነቶች ሕይወታችን ትርጉም ያለው እንዲሆን አድርገዋል። w18.11 3 አን. 1-2
ማክሰኞ፣ ሰኔ 16
አንዳችሁ ሌላውን አትዋሹ።—ቆላ. 3:9
አታላይ ሰዎች ከይሖዋ ምንም ነገር መደበቅ እንደማይችሉ ማስታወስ ይኖርብናል፤ ምክንያቱም “በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው።” (ዕብ. 4:13) ለምሳሌ፣ ሐናንያና ሰጲራ የተባሉት ባልና ሚስት ሐዋርያትን ለማታለል ሞክረው ነበር። መሬት ከሸጡ በኋላ፣ ካገኙት ገንዘብ ላይ የተወሰነውን ብቻ ወደ ሐዋርያት ይዘው ሄዱ። ባልና ሚስቱ፣ ከሆኑት በላይ ለጋስ መስለው በመታየት በጉባኤው ዘንድ ለየት ያለ ክብር ማግኘት ፈልገው ነበር። ሆኖም ይሖዋ ድርጊታቸውን የተመለከተ ሲሆን ለዚህም ተገቢውን ቅጣት እንዲቀበሉ አድርጓል። (ሥራ 5:1-10) ይሖዋ ለውሸት ምን አመለካከት አለው? ሰይጣንም ሆነ የእሱን አርዓያ በመከተል ከክፋት የመነጨ ውሸት የሚዋሹና ንስሐ የማይገቡ ሰዎች የሚጠብቃቸው ወደ ‘እሳት ሐይቅ’ መወርወር ነው። (ራእይ 20:10፤ 21:8፤ መዝ. 5:6) ይሖዋ “እንደ ሰው [እንደማይዋሽ]” እናውቃለን። እንዲያውም ‘አምላክ ሊዋሽ አይችልም።’ (ዘኁ. 23:19፤ ዕብ. 6:18) ይሖዋ ‘ውሸታም ምላስን ይጠላል።’ (ምሳሌ 6:16, 17) የእሱን ሞገስ ማግኘት ከፈለግን ምንጊዜም እውነት መናገር ይኖርብናል። w18.10 8 አን. 10-13
ረቡዕ፣ ሰኔ 17
በእነዚህ ነገሮች ላይ አሰላስል።—1 ጢሞ. 4:15
አሠሪያችሁ ከሐሰት ሃይማኖት ጋር ንክኪ ላለው በቅርቡ የሚከበር አንድ በዓል የገንዘብ መዋጮ እንድታደርጉ ጠየቃችሁ እንበል። በዚህ ጊዜ ምን ታደርጋላችሁ? እንዲህ ያሉ ሁኔታዎች እስኪያጋጥሟችሁ ድረስ ከመጠበቅ ይልቅ ይሖዋ ስለ ጉዳዩ ያለውን አመለካከት ለማወቅ ለምን ከወዲሁ ጥረት አታደርጉም? ይህም ተመሳሳይ ሁኔታ በሚያጋጥማችሁ ጊዜ ትክክለኛውን ነገር ማድረግም ሆነ መናገር ቀላል እንዲሆንላችሁ ይረዳችኋል። ለይሖዋ ታማኝ የመሆንን አስፈላጊነት አስቀድመን ማሰባችን ድንገተኛ ሕክምና በሚያስፈልገን ጊዜም ይረዳናል። ሙሉውን ደም ወይም ከአራቱ ዋና ዋና የደም ክፍልፋዮች አንዱን ፈጽሞ እንደማንወስድ የታወቀ ነው፤ ሆኖም የደም ንዑስ ክፍልፋዮችን መውሰድ ከሚጠይቁ ሕክምናዎች ጋር በተያያዘ እያንዳንዱ ክርስቲያን የይሖዋን አስተሳሰብ በሚያንጸባርቁ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ ተመሥርቶ የራሱን ውሳኔ ማድረግ ይኖርበታል። (ሥራ 15:28, 29) እንዲህ ስላሉ ጉዳዮች ማሰብ ያለብን ሆስፒታል ውስጥ በሕመም ላይ ሳለን ወይም በአፋጣኝ እንድንወስን ጫና በሚደረግብን ጊዜ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ምርምር የምናደርግበት፣ የምንቀበለውን የሕክምና ዓይነት የሚገልጽ ሕጋዊ ሰነድ የምንሞላበትና ከሐኪማችን ጋር የምንነጋገርበት ከሁሉ የተሻለ ጊዜ አሁን ነው። w18.11 24 አን. 5፤ 26 አን. 15-16
ሐሙስ፣ ሰኔ 18
እኔን የሚሰማ ሰው . . . ተረጋግቶ ይኖራል።—ምሳሌ 1:33
ይሖዋ ሕዝቡን የሚንከባከብ አፍቃሪ እረኛ ነው፤ ሕዝቡን ከጠላቶቻቸው ጥቃት ይከልላቸዋል እንዲሁም ይጠብቃቸዋል። ይህን ማወቃችን፣ ወደዚህ ሥርዓት ፍጻሜ ይበልጥ እየተቃረብን በሄድን መጠን በእጅጉ ያበረታታናል! ይሖዋ በቅርቡ በሚመጣው ታላቅ መከራ ወቅትም እንዲህ ዓይነት ጥበቃ ማድረጉን ይቀጥላል። (ራእይ 7:9, 10) በመሆኑም ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን እንዲሁም ጤነኞችም ሆኑ የአካል ጉዳት ያለባቸው የአምላክ አገልጋዮች በታላቁ መከራ ወቅት በፍርሃት የሚርበደበዱበት ምክንያት የለም። እንዲያውም ኢየሱስ ክርስቶስ “መዳናችሁ እየቀረበ ስለሆነ ቀጥ ብላችሁ ቁሙ፤ ራሳችሁንም ቀና አድርጉ” በማለት የሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ ያደርጋሉ። (ሉቃስ 21:28) ጎግ ማለትም ግንባር የፈጠሩ ኃያል ብሔራት፣ ጥቃት በሚሰነዝሩባቸው ጊዜም እንኳ የአምላክ ሕዝቦች ይሖዋ ጥበቃ እንደሚያደርግላቸው ሙሉ በሙሉ ይተማመናሉ። (ሕዝ. 38:2, 14-16) የአምላክ አገልጋዮች በዚያ ወቅት በልበ ሙሉነት የሚቆሙት ለምንድን ነው? ይሖዋ እንደማይለወጥ ስለሚያውቁ ነው። ምንጊዜም ቢሆን ይሖዋ አሳቢ አዳኝ መሆኑን ያረጋግጣል።—ኢሳ. 26:20፤ w18.09 26 አን. 15-16
ዓርብ፣ ሰኔ 19
አንተ በዓይኔ ፊት ውድ ሆነሃልና፤ . . . እኔም ወድጄሃለሁ።—ኢሳ. 43:4
ታማኝ የሆኑት እስራኤላውያን፣ ይሖዋ በተናገረው ሐሳብ በእጅጉ ተበረታተው መሆን አለበት። አንተም የይሖዋ አገልጋይ እንደመሆንህ መጠን ይሖዋ አጥብቆ እንደሚወድህ ቅንጣት ታክል አትጠራጠር። ይሖዋ ንጹሑን አምልኮ የሚከተሉ ሰዎችን ‘እንደ ኃያል ተዋጊ እንደሚያድናቸው እንዲሁም በታላቅ ደስታ በእነሱ ሐሴት እንደሚያደርግ’ ቃል ገብቷል። (ሶፎ. 3:16, 17) ይሖዋ፣ ሕዝቦቹ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥማቸው እንደሚንከባከባቸውና እንደሚያጽናናቸው ቃል ገብቷል። አገልጋዮቹን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እናንተም ትጠባላችሁ፤ ጀርባዋም ላይ ታዝላችኋለች፣ ጭኗም ላይ ሆናችሁ ትዘላላችሁ። እናት ልጇን እንደምታጽናና፣ እኔም እናንተን ሁልጊዜ አጽናናችኋለሁ።” (ኢሳ. 66:12, 13) ይህ ምንኛ የሚያበረታታ ሐሳብ ነው! አንዲት አፍቃሪ እናት ልጇን በጀርባዋ ስታዝል ወይም ጭኗ ላይ አድርጋ ስታጫውት በዓይነ ሕሊናህ ይታይህ። ጥቅሱ፣ ይሖዋ ለእውነተኛ አገልጋዮቹ ያለውን ጥልቅ ፍቅርና አሳቢነት ግሩም አድርጎ ይገልጻል። ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ እንደሚወድህና ከፍ አድርጎ እንደሚመለከትህ ጨርሶ ጥርጣሬ አይግባህ።—ኤር. 31:3፤ w18.09 13 አን. 6-7
ቅዳሜ፣ ሰኔ 20
ዛሬ ለይሖዋ የሚሰጥ ስጦታ በእጁ ይዞ ለመቅረብ ፈቃደኛ የሆነ ማን ነው?—1 ዜና 29:5
በጥንቷ እስራኤል ፈቃደኛ ሠራተኞች ያስፈለጉባቸው የተለያዩ አጋጣሚዎች ነበሩ። (ዘፀ. 36:2፤ ነህ. 11:2) ዛሬም ቢሆን ጊዜያችንን፣ ገንዘባችንን ብሎም ችሎታችንን ተጠቅመን ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን በፈቃደኝነት መርዳት የምንችልባቸው በርካታ አጋጣሚዎች አሉ። በዚህ መልኩ ራሳችንን ማቅረባችን ታላቅ ደስታና ብዙ በረከት ያስገኝልናል። በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ሥራዎች ላይ የሚካፈሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች አዳዲስ ጓደኞች ማፍራት ችለዋል። ከስብሰባ አዳራሾች ግንባታ ጋር በተያያዙ ሥራዎች ላይ ለ18 ዓመታት የተካፈለችውን ማርጂን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ይህች እህት ባለፉት ዓመታት ውስጥ በርካታ ወጣት እህቶችን አሠልጥናለች። ማርጂ በእነዚህ የግንባታ ሥራዎች ላይ የሚካፈሉ ፈቃደኛ ሠራተኞች፣ እርስ በርስ በመንፈሳዊ ለመበረታታት የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ እንደሚያገኙ ተናግራለች። (ሮም 1:12) ማርጂ በሕይወቷ ውስጥ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ባጋጠሟት ወቅት፣ በግንባታ ሥራዎች ላይ ስትካፈል ያፈራቻቸው ወዳጆቿ አበረታተዋታል። አንተስ በቲኦክራሲያዊ የግንባታ ሥራዎች ላይ ለመካፈል ራስህን በፈቃደኝነት አቅርበህ ታውቃለህ? w18.08 25 አን. 9, 11
እሁድ፣ ሰኔ 21
ወጣት በመሆንህ ማንም ሰው ሊንቅህ አይገባም። ከዚህ ይልቅ ታማኞች ለሆኑት በንግግር፣ በምግባር፣ በፍቅር፣ በእምነትና በንጽሕና አርዓያ ሁን።—1 ጢሞ. 4:12
ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት ጢሞቴዎስ በ30ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ ሳይሆን አይቀርም። ያም ሆኖ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ከባድ ኃላፊነቶችን ሰጥቶት ነበር። ጳውሎስ ይህን ምክር የሰጠበት ምክንያት ምንም ይሁን ምን ከተናገረው ሐሳብ የምናገኘው ትምህርት አለ። ወጣት ወንድሞችን ዕድሜያቸውን በማየት ብቻ ልንገመግማቸው አይገባም። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎቱን በሙሉ ያከናወነው በ30ዎቹ ዕድሜ መጀመሪያ ላይ እያለ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። በአንዳንድ ባሕሎች ውስጥ ሰዎች ለወጣት ወንዶች አክብሮት ማሳየት ይከብዳቸዋል። እንዲህ ባሉት ባሕሎች ውስጥ የሚገኙ የጉባኤ ሽማግሌዎች፣ ብቃቱን የሚያሟሉ ወጣት ወንድሞች የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆነው እንዲሾሙ የድጋፍ ሐሳብ ለማቅረብ ያመነቱ ይሆናል። ይሁን እንጂ ሁሉም ሽማግሌዎች ልብ ሊሉት የሚገባ ነገር አለ፤ ይኸውም መጽሐፍ ቅዱስ አንድ ወንድ የጉባኤ አገልጋይ ወይም ሽማግሌ ሆኖ ለመሾም የሆነ ዕድሜ ላይ መድረስ እንዳለበት የማይናገር መሆኑን ነው።—1 ጢሞ. 3:1-10, 12, 13፤ ቲቶ 1:5-9፤ w18.08 11-12 አን. 15-16
ሰኞ፣ ሰኔ 22
በውሸት “እውቀት” ተብለው ከሚጠሩ . . . ሐሳቦች [ራቅ]።—1 ጢሞ. 6:20
ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ አስተማማኝ የሆነ መረጃ ማግኘት ያስፈልገናል። በመሆኑም የምናነባቸውን ነገሮች በጥንቃቄ መምረጥ አለብን። (ፊልጵ. 4:8, 9) ተአማኒ ያልሆኑ የኢንተርኔት የዜና ድረ ገጾችን በመቃኘት ወይም በኢ-ሜይል አሊያም በጽሑፍ መልእክት አማካኝነት የተላኩልንን ያልተረጋገጡ ዘገባዎች በማንበብ ጊዜያችንን ልናባክን አይገባም። በተለይ ደግሞ የከሃዲዎችን ሐሳብ የሚያስፋፉ ድረ ገጾችን ከመመልከት መቆጠብ ይኖርብናል። የከሃዲዎች ዋነኛ ዓላማ የአምላክን ሕዝቦች እምነት ማዳከምና እውነታውን ማዛባት ነው። አስተማማኝ ያልሆነ መረጃ፣ የተሳሳተ ውሳኔ ወደ ማድረግ ይመራል። የተሳሳተ መረጃ ምን ያህል መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድርብን እንደሚችል መዘንጋት አይኖርብንም። በሙሴ ዘመን፣ ተስፋይቱን ምድር እንዲቃኙ ከተላኩት አሥራ ሁለት ሰላዮች መካከል አሥሩ መጥፎ ወሬ ይዘው መምጣታቸው ምን ውጤት እንዳስከተለ እንመልከት። (ዘኁ. 13:25-33) እስራኤላውያን እነዚህ ሰላዮች ያመጡትን የተጋነነና አስደንጋጭ የሆነ ዜና ሲሰሙ ወኔ ከዳቸው። (ዘኁ. 14:1-4, 6-10) እስራኤላውያን እውነታውን ከመስማትና በይሖዋ ከመታመን ይልቅ የተሳሳተውን ዜና ለማመን መረጡ። w18.08 4 አን. 4-5
ማክሰኞ፣ ሰኔ 23
አትታለሉ። መጥፎ ጓደኝነት መልካሙን አመል ያበላሻል።—1 ቆሮ. 15:33
አብዛኞቹ ሰዎች አንዳንድ ጥሩ ባሕርያት ይኖሯቸው ይሆናል፤ ደግሞም ዓይን ያወጣ መጥፎ ድርጊት የማይፈጽሙ የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ በርካታ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እንዲህ ሲባል ታዲያ እነዚህ ሰዎች ጥሩ ወዳጆች ሊሆኑህ ይችላሉ ማለት ነው? ከእነሱ ጋር ጊዜ ማሳለፍህ ከይሖዋ ጋር ባለህ ዝምድና ላይ ምን ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ለማሰብ ሞክር። ከይሖዋ ጋር ያለህ ዝምድና እንዲጠናከር ይረዱሃል? በልባቸው ውስጥ ያለው ነገር ምንድን ነው? ለምሳሌ ያህል፣ ወሬያቸው ሁሉ ስለ ፋሽን፣ ስለ ገንዘብ፣ ስለ ኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎች፣ ስለ መዝናኛ ወይም ሌሎች ቁሳዊ ነገሮችን ስለማሳደድ ነው? ሌሎችን የሚያንቋሽሽ ነገር መናገር ወይም የብልግና ቀልዶችን መቀለድ ይቀናቸዋል? በእርግጥም ኢየሱስ “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው” በማለት የተናገረው ያለምክንያት አይደለም። (ማቴ. 12:34) ጓደኞችህ በይሖዋ ፊት ያለህን ጥሩ አቋም አደጋ ላይ እየጣሉት እንዳሉ ከተገነዘብክ ከእነሱ ጋር ባለህ ግንኙነት ላይ ገደብ በማበጀት፣ አስፈላጊ ከሆነም ከነጭራሹ ግንኙነትህን በማቆም ቆራጥ እርምጃ ውሰድ።—ምሳሌ 13:20፤ w18.07 19 አን. 11
ረቡዕ፣ ሰኔ 24
ሙሴ በምድር ላይ ከነበሩ ሰዎች ሁሉ ይልቅ በጣም የዋህ ነበር።—ዘኁ. 12:3
ሙሴ 80 ዓመት ሲሆነው ይሖዋ እስራኤላውያንን ከግብፅ ባርነት ነፃ እንዲያወጣቸው አዘዘው። (ዘፀ. 3:10) ሙሴ የተሰጠውን ተልእኮ መቀበል እንደማይችል ለመግለጽ በተደጋጋሚ ሞክሮ ነበር። ይሁን እንጂ ይሖዋ በሙሴ ላይ አልተቆጣም፤ እንዲያውም ተአምራት መፈጸም እንዲችል ለሙሴ ኃይል ሰጠው። (ዘፀ. 4:2-9, 21) ይሖዋ፣ ሙሴ ፈርቶት ወዲያውኑ እንዲታዘዘው ማድረግ ይችል ነበር። ሆኖም ትሑት የሆነውን አገልጋዩን በማበረታታት ትዕግሥትና ደግነት አሳይቶታል። እንዲህ ያለ አሳቢነት ማሳየቱ ያስገኘው ጥቅም ይኖር ይሆን? በሚገባ! ሙሴ ታላቅ መሪ መሆን ችሏል፤ በተጨማሪም ሌሎችን በገርነትና በአሳቢነት በመያዝ የይሖዋን ምሳሌ ተከትሏል። በሌሎች ላይ በተወሰነ መጠን ሥልጣን ካላችሁ በሥልጣናችሁ ሥር ላሉት ሰዎች አሳቢነት፣ ደግነትና ትዕግሥት በማሳየት የይሖዋን ምሳሌ መከተላችሁ ምንኛ አስፈላጊ ነው! (ቆላ. 3:19-21፤ 1 ጴጥ. 5:1-3) ይሖዋንና ታላቁን ሙሴ ኢየሱስን ለመምሰል ጥረት የምታደርጉ ከሆነ በቀላሉ የምትቀረቡ ትሆናላችሁ፤ አልፎ ተርፎም ለሌሎች የእረፍት ምንጭ መሆን ትችላላችሁ።—ማቴ. 11:28, 29፤ w18.09 24-25 አን. 7-10
ሐሙስ፣ ሰኔ 25
ወንድሞች በአንድነት አብረው ቢኖሩ ምንኛ መልካም ነው! ምንኛስ ደስ ያሰኛል!—መዝ. 133:1
ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ደግነትና ወዳጃዊ ስሜት በማሳየት መንፈሳቸው እንዲታደስ ማድረግ እንችላለን። ይህም የጉባኤው አንድነት እንዲጠናከር አስተዋጽኦ ያበረክታል። በዚህ ረገድ ለምታደርገው ጥረት ልትመሰገን ይገባሃል። ‘ልብህን ወለል አድርገህ በመክፈት’ ይህን ልማድህን ይበልጥ ማጠናከር ትችል ይሆን? (2 ቆሮ. 6:11-13) በምትኖርበት አካባቢ የእውነት ብርሃን ይበልጥ ደምቆ እንዲበራ ማድረግ የምትችለውስ እንዴት ነው? ደግነት የሚንጸባረቅበት አነጋገርህ እንዲሁም ምግባርህ ጎረቤቶችህ ወደ እውነት እንዲሳቡ ሊያደርግ ይችላል። ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ጎረቤቶቼ ለእኔ ምን አመለካከት አላቸው? ቤቴንና አካባቢዬን ንጹሕና ያልተዝረከረከ በማድረግ ሰፈሩ ያማረ እንዲሆን አስተዋጽኦ አበረክታለሁ? ቅድሚያውን ወስጄ ሌሎችን እረዳለሁ?’ ከሌሎች የይሖዋ ምሥክሮች ጋር በምትጨዋወትበት ጊዜ፣ ደግነትና ጥሩ ምግባር ማሳየታቸው በዘመዶቻቸው፣ በጎረቤቶቻቸው፣ በሥራ ባልደረቦቻቸው ወይም አብረዋቸው በሚማሩ ልጆች ላይ ምን በጎ ተጽዕኖ እንዳሳደረ ብትጠይቃቸው ግሩም ተሞክሮዎችን ትሰማለህ።—ኤፌ. 5:9፤ w18.06 24 አን. 13-14
ዓርብ፣ ሰኔ 26
እናንተን የሚገድል ሁሉ ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት እንዳቀረበ አድርጎ የሚያስብበት ሰዓት ይመጣል።—ዮሐ. 16:2
ደቀ መዝሙሩን እስጢፋኖስን የገደሉት ሰዎች እንዲህ ዓይነት አመለካከት ነበራቸው፤ የይሖዋን አገልጋዮች ከሚያሳድዱ ሌሎች ሰዎች ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። (ሥራ 6:8, 12፤ 7:54-60) ጽንፈኛ አመለካከት ያላቸው ሃይማኖተኛ ሰዎች እንደ ነፍስ ማጥፋት ያሉ አሰቃቂ የክፋት ድርጊቶችን በመፈጸም፣ እናመልካለን የሚሉት አምላክ ያወጣቸውን ሕጎች መጣሳቸው ምንኛ የሚያስገርም ነው! (ዘፀ. 20:13) የእነዚህ ሰዎች ሕሊና እያታለላቸው እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም! ሕሊናችን በተገቢው መንገድ እንዲሠራ ምን ሊረዳን ይችላል? በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች “ለማስተማር፣ ለመውቀስ፣ ነገሮችን ለማቅናትና በጽድቅ ለመገሠጽ ይጠቅማሉ።” (2 ጢሞ. 3:16) በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማጥናት፣ ባጠናነው ነገር ላይ ማሰላሰልና የተማርነውን በሕይወታችን ውስጥ በተግባር ማዋል ይኖርብናል፤ ይህም የአምላክን ዓይነት አስተሳሰብ ይበልጥ እንድናዳብር ይረዳናል። እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ በማዳበር ሕሊናችንን ካሠለጠንነው አስተማማኝ መሪ ይሆንልናል። w18.06 16-17 አን. 3-4
ቅዳሜ፣ ሰኔ 27
የመንፈስን ሰይፍ ይኸውም የአምላክን ቃል ያዙ።—ኤፌ. 6:17
ጳውሎስ ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት የነበሩት የሮም ወታደሮች የሚይዙት ሰይፍ፣ ርዝመቱ 50 ሴንቲ ሜትር ገደማ ሲሆን ለጨበጣ ውጊያ የተዘጋጀ ነበር። የሮም ወታደሮች ጎበዝ ተዋጊዎች እንዲሆኑ የረዳቸው አንዱ ነገር በጦር መሣሪያዎቻቸው በየዕለቱ ልምምድ ማድረጋቸው ነው። ጳውሎስ የአምላክን ቃል ከሰይፍ ጋር አመሳስሎታል፤ ይህን ሰይፍ ያገኘነው ከይሖዋ ነው። ይሁንና ለምናምንባቸው ነገሮች ጥብቅና ለመቆምም ሆነ አስተሳሰባችንን ለማስተካከል የአምላክን ቃል ጥሩ አድርገን የመጠቀም ችሎታ ልናዳብር ይገባል። (2 ቆሮ. 10:4, 5፤ 2 ጢሞ. 2:15) ሰይጣንን እና አጋንንቱን ከልክ በላይ መፍራት አያስፈልገንም። እነዚህ ጠላቶቻችን ኃያል ቢሆኑም የማይበገሩ ናቸው ማለት አይደለም። በዚያ ላይ ደግሞ ለዘላለም አይኖሩም። በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ሰይጣንና አጋንንቱ ምንም ዓይነት ተጽዕኖ ማሳደር እንዳይችሉ ይደረጋሉ፤ ከዚያ በኋላ ደግሞ ከናካቴው ይጠፋሉ። (ራእይ 20:1-3, 7-10) የጠላታችንን ማንነት፣ የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎችና ዓላማውን አውቀናል። በይሖዋ እርዳታ ደግሞ ይህን ጠላታችንን መቋቋም እንችላለን! w18.05 30 አን. 15፤ 31 አን. 19-21
እሁድ፣ ሰኔ 28
በዚህ ጊዜ እባቡ ሴቲቱን እንዲህ አላት፦ “መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም።”—ዘፍ. 3:4
አዳም፣ እባብ ማውራት እንደማይችል ያውቅ ነበር። በመሆኑም በእባብ ተጠቅሞ ሔዋንን ያነጋገራት አንድ መንፈሳዊ ፍጡር እንደሆነ ሳይገምት አልቀረም። (ዘፍ. 3:1-6) አዳምና ሔዋን ስለዚህ መንፈሳዊ ፍጡር ምንም የሚያውቁት ነገር አልነበረም ማለት ይቻላል። ያም ቢሆን አዳም፣ አፍቃሪ ለሆነው ሰማያዊ አባቱ ጀርባውን በመስጠት ጨርሶ ከማያውቀው አካል ጋር ተባብሮ የአምላክን ፈቃድ ለመቃወም መረጠ። (1 ጢሞ. 2:14) አዳምና ሔዋን እንዲያምፁ ያደረጋቸውን ይህን ጠላት በተመለከተ ይሖዋ ወዲያውኑ አንዳንድ ነገሮችን የገለጸ ሲሆን ይህ ክፉ አካል ውሎ አድሮ እንደሚጠፋ ቃል ገባ። ይሁን እንጂ በእባቡ አማካኝነት የተናገረው ይህ መንፈሳዊ ፍጡር ለተወሰነ ጊዜ ያህልም ቢሆን የአምላክን ወዳጆች ሁሉ እንደሚቃወም ይሖዋ ገልጾ ነበር። (ዘፍ. 3:15) ይሖዋ በእሱ ላይ ያመፀውን መልአክ ስም አልነገረንም፤ ይህም ጥበቡን የሚያሳይ ነው። ይህ ጠላት በፈጸመው ተግባር ምክንያት የተሰጠውን መጠሪያ እንኳ አምላክ ያሳወቀን የመጀመሪያው ዓመፅ ከተቀሰቀሰ ወደ 2,500 ከሚጠጉ ዓመታት በኋላ ነው።—ኢዮብ 1:6፤ w18.05 22 አን. 1-2
ሰኞ፣ ሰኔ 29
[እነዚህ] በጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።—ሉቃስ 8:15
የምትሰብኩት አብዛኞቹ ሰዎች ምሥራቹን በማይቀበሉበት ክልል ውስጥ መሆኑ ተስፋ አስቆራጭ ከሆነባችሁ ሐዋርያው ጳውሎስ የተሰማውን ስሜት መረዳት ላይከብዳችሁ ይችላል። ጳውሎስ ወደ 30 ለሚጠጉ ዓመታት ባከናወነው አገልግሎት በርካታ ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ረድቷል። (ሥራ 14:21፤ 2 ቆሮ. 3:2, 3) ሆኖም ብዙ አይሁዳውያን እውነተኛውን አምልኮ እንዲቀበሉ ለመርዳት ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም። አብዛኞቹ፣ ጳውሎስን ለመስማት አሻፈረን ብለዋል፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ ስደት አድርሰውበታል። (ሥራ 14:19፤ 17:1, 4, 5, 13) ታዲያ ይህ በጳውሎስ ላይ ምን ዓይነት ስሜት ፈጥሮበታል? “የክርስቶስ ተከታይ እንደመሆኔ መጠን የምናገረው እውነት ነው፤ . . . ታላቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ሥቃይ በልቤ ውስጥ አለ” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (ሮም 9:1-3) ጳውሎስ እንዲህ የተሰማው ለምንድን ነው? ለስብከቱ ሥራ እና ለሰዎች ፍቅር ስለነበረው ነው። ለአይሁዳውያን የሰበከው ከልብ ስለሚያስብላቸው ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ፣ አይሁዳውያን የአምላክን ምሕረት ለመቀበል ፈቃደኞች አለመሆናቸውን ሲመለከት በጣም አዝኗል። እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም ለሰዎች የምንሰብከው ከልባችን ስለምናስብላቸው ነው።—ማቴ. 22:39፤ 1 ቆሮ. 11:1፤ w18.05 13 አን. 4-5
ማክሰኞ፣ ሰኔ 30
በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።—ምሳሌ 12:25
ጳውሎስ ሌሎችን የሚያበረታቱ ሰዎችም እንኳ ማበረታቻ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጿል። በሮም ለሚኖሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለመጽናት የሚያስችላችሁን መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችሁ ላያችሁ እጓጓለሁና፤ ይህን ስል እኔ በእናንተ እምነት እናንተም በእኔ እምነት እርስ በርሳችን እንድንበረታታ ነው።” (ሮም 1:11, 12) አዎ፣ ለሌሎች ግሩም ማበረታቻ ይሰጥ የነበረው ጳውሎስ እንኳ ማበረታቻ ማግኘት ያስፈለገው ጊዜ ነበር። (ሮም 15:30-32) የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉ ክርስቲያኖች አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል። “በጌታ ብቻ” እንዲያገቡ ለክርስቲያኖች የተሰጠውን መመሪያ ለመታዘዝ ሲሉ ሳያገቡ የሚኖሩ ወንድሞችና እህቶችም ማበረታቻ ሊሰጣቸው ይገባል። (1 ቆሮ. 7:39) ከዚህም ሌላ የሚደርስባቸውን ስደት ተቋቁመው ወይም ያለባቸውን ሕመም ችለው በታማኝነት የሚያገለግሉ ክርስቲያኖች ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል።—2 ተሰ. 1:3-5፤ w18.04 21 አን. 3-5