የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es20 ገጽ 67-77
  • ሐምሌ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሐምሌ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2020
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 1
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 2
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 3
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 4
  • እሁድ፣ ሐምሌ 5
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 6
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 7
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 8
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 9
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 10
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 11
  • እሁድ፣ ሐምሌ 12
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 13
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 14
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 15
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 16
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 17
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 18
  • እሁድ፣ ሐምሌ 19
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 20
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 21
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 22
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 23
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 24
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 25
  • እሁድ፣ ሐምሌ 26
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 27
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 28
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 29
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 30
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2020
es20 ገጽ 67-77

ሐምሌ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 1

የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ።—ኤፌ. 5:17

የምንኖረው “ለመቋቋም [በሚያስቸግር] በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመን” ውስጥ ሲሆን በምድራችን ላይ እውነተኛ ሰላም የሚሰፍንበት ብሩሕ ቀን ከመምጣቱ በፊት ሕይወት ይበልጥ እየከበደ እንደሚሄድ እናውቃለን። (2 ጢሞ. 3:1) በመሆኑም ‘እርዳታና መመሪያ ለማግኘት ዓይኖቼ የሚመለከቱት ወዴት ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት አንድ መዝሙራዊ፣ እርዳታ ለማግኘት ዓይናችንን አንስተን ወደ ይሖዋ የመመልከትን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። (መዝ. 123:1-4) እኛ ወደ ይሖዋ የምንመለከትበትን ሁኔታ አንድ አገልጋይ ወደ ጌታው ከሚመለከትበት ሁኔታ ጋር አመሳስሎታል። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ምን ማለቱ ነበር? አንድ አገልጋይ ወደ ጌታው የሚመለከተው ምግብ እንዲሰጠውና ጥበቃ እንዲያደርግለት ብቻ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ ጌታው የሚፈልገውን ነገር ለማወቅና የጌታውን ፍላጎት ለመፈጸም ምንጊዜም ዓይኑ ወደ ጌታው መመልከት ይኖርበታል። እኛም በተመሳሳይ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ለእኛ ያለውን ፈቃድ ለማወቅና ከዚያ ጋር የሚስማማ እርምጃ ለመውሰድ በየዕለቱ የአምላክን ቃል መመርመር ያስፈልገናል። ይሖዋ እርዳታ በሚያስፈልገን ጊዜ ሞገሱን እንደሚያሳየን እርግጠኞች መሆን የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። w18.07 12 አን. 1-2

ሐሙስ፣ ሐምሌ 2

ወልድ ነፃ ካወጣችሁ፣ በእርግጥ ነፃ ትሆናላችሁ።—ዮሐ. 8:36

ኢየሱስ እንዲህ ሲል ከሁሉ ከከፋው ባርነትና ጭቆና ይኸውም “የኃጢአት ባሪያ” ከመሆን ነፃ ስለመውጣት መናገሩ ነበር። (ዮሐ. 8:34) ኃጢአት፣ መጥፎ ነገር መፈጸም እንዲቀናን የሚያደርገን ከመሆኑም ሌላ ትክክል እንደሆነ የምናውቀውን ነገር እንዳናደርግ አሊያም የአቅማችንን ያህል እንዳንሠራ ያግደናል። በመሆኑም የኃጢአት ባሪያዎች ነን ማለት ይቻላል፤ ይህ ደግሞ ብስጭት፣ ሥቃይ፣ መከራ በመጨረሻም ሞት ያስከትልብናል። (ሮም 6:23) የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን የነበራቸው ዓይነት እውነተኛ ነፃነት ማግኘት የምንችለው እንደ ካቴና ጠፍሮ ከያዘን ከኃጢአት ነፃ ስንወጣ ብቻ ነው። ኢየሱስ “ቃሌን ጠብቃችሁ ብትኖሩ” ማለቱ፣ እሱ ነፃ እንዲያወጣን ከፈለግን ልናሟላቸው የሚገቡ ብቃቶች እንዳሉ ይጠቁማል። (ዮሐ. 8:34) ሕይወታችንን ለይሖዋ የወሰንን ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ራሳችንን ክደናል፤ እንዲሁም የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ከሚያስከትላቸው ገደቦች ሳንወጣ ለመኖር መርጠናል። (ማቴ. 16:24) ከኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ሙሉ በሙሉ ተጠቃሚ ስንሆን እሱ ቃል በገባው መሠረት እውነተኛ ነፃነት እናገኛለን። w18.04 7 አን. 14-16

ዓርብ፣ ሐምሌ 3

የሰውን ልብ በሚገባ የምታውቀው አንተ ብቻ ነህ።—2 ዜና 6:30

ይሖዋ ምንጊዜም ለሕዝቡ ስሜት ያስባል፤ አገልጋዮቹ የተሳሳተ ጎዳና በሚከተሉበት ጊዜም እንኳ ለስሜታቸው እንደሚያስብ አሳይቷል። እስቲ የዮናስን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ይሖዋ በነነዌ ነዋሪዎች ላይ የፍርድ መልእክት እንዲያውጅ ይህን ነቢይ ልኮት ነበር። ነዋሪዎቹ ንስሐ ሲገቡ ግን አምላክ ሊያመጣባቸው ያሰበውን ጥፋት ተወው። ሆኖም ዮናስ በዚህ ውሳኔ አልተደሰተም። ጥፋት እንደሚመጣ የተናገረው ትንቢት ሳይፈጸም በመቅረቱ “እጅግ ተቆጣ።” ይሁንና ይሖዋ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክል በትዕግሥት ረድቶታል። (ዮናስ 3:10 እስከ 4:11) ዮናስ በጊዜ ሂደት የይሖዋን እርማት ተቀብሏል፤ ይሖዋም ጠቃሚ ትምህርት የያዘውን ይህን ዘገባ ለማጻፍ ዮናስን ተጠቅሞበታል። (ሮም 15:4) ይሖዋ ሕዝቡን የያዘበትን መንገድ ስንመለከት አምላክ ለአገልጋዮቹ ርኅራኄ እንዳለው እርግጠኞች እንሆናለን። እያንዳንዳችን እየደረሰብን ያለውን ሥቃይና መከራ ይገነዘባል። የውስጥ ሐሳባችንን፣ ስሜታችንንና ያለብንን የአቅም ገደብ ይረዳል። ደግሞም ‘ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ፈተና እንዲደርስብን አይፈቅድም።’ (1 ቆሮ. 10:13) ይህ ማረጋገጫ ምንኛ የሚያጽናና ነው! w19.03 16 አን. 6-7

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 4

ተጠያቂዎች በሆንበት በእሱ ዓይኖች ፊት ሁሉም ነገር የተራቆተና ገሃድ የወጣ ነው።—ዕብ. 4:13

በሙሴ ሕግ ሥር የተሾሙ ሽማግሌዎች መንፈሳዊ ጉዳዮችን ብቻ ሳይሆን የፍትሐ ብሔርና የወንጀል ጉዳዮችን ጭምር የመመልከት ኃላፊነት ነበረባቸው። እስቲ የተወሰኑ ምሳሌዎች እንመልከት። አንድ እስራኤላዊ ነፍስ ቢያጠፋ በቀጥታ የሞት ፍርድ አይፈረድበትም ነበር። የከተማው ሽማግሌዎች ግለሰቡ በሞት ሊቀጣ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለውን ከመወሰናቸው በፊት በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ በሚገባ ይመረምራሉ። (ዘዳ. 19:2-7, 11-13) በተጨማሪም ሽማግሌዎቹ በዕለት ተዕለት ሕይወት በሚያጋጥሙ የተለያዩ ጉዳዮች ላይ ፍርድ ይሰጡ ነበር፤ እነዚህ ጉዳዮች ከንብረት ጋር ከተያያዙ ውዝግቦች አንስቶ በባልና ሚስት መካከል እስከሚፈጠሩ አለመግባባቶች ድረስ ያሉ ክሶችን የሚጨምሩ ሊሆኑ ይችላሉ። (ዘፀ. 21:35፤ ዘዳ. 22:13-19) ሽማግሌዎቹ ፍትሐዊ ሲሆኑና ሕዝቡ ሕጉን ሲታዘዝ ሁሉም የሚጠቀም ከመሆኑም በላይ ብሔሩ ለይሖዋ ክብር ያመጣ ነበር። (ዘሌ. 20:7, 8፤ ኢሳ. 48:17, 18) ከዚህ እንደምንመለከተው ይሖዋ እያንዳንዱን የሕይወታችንን ክፍል ይመለከታል። ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ፍትሐዊና አፍቃሪ እንድንሆን ይፈልጋል። ከዚህም በላይ ከሌሎች እይታ ውጭ ሆነን ቤታችን ውስጥ የምንናገረውንም ሆነ የምናደርገውን ነገር ጭምር ትኩረት ሰጥቶ ያያል። w19.02 23 አን. 16-18

እሁድ፣ ሐምሌ 5

መከራም ለመቀበል ፈቃደኛ ሆነ፤ ነገር ግን አፉን አልከፈተም።—ኢሳ. 53:7

ውጥረት ውስጥ ስንሆን የዋህ መሆን ይከብደናል። ደግነት በጎደለውና ሌሎችን ቅር በሚያሰኝ መንገድ ልንናገር እንችላለን። አንተም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሞህ የሚያውቅ ከሆነ የኢየሱስን ምሳሌ መመርመርህ ይጠቅምሃል። ኢየሱስ ምድር ላይ ባሳለፋቸው የመጨረሻ ወራት ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ነበር። ከጥቂት ጊዜ በኋላ እንደሚገደልና ብዙ መከራ እንደሚደርስበት ያውቃል። (ዮሐ. 3:14, 15፤ ገላ. 3:13) ከመሞቱ ከተወሰኑ ወራት በፊት፣ በጣም እንደተጨነቀ ተናግሯል። (ሉቃስ 12:50) ሊሞት ጥቂት ቀናት ሲቀረውም “ተጨንቄአለሁ” ብሏል። ኢየሱስ ስሜቱን አውጥቶ ወደ አምላክ ያቀረበው ጸሎት ምን ያህል ትሑትና ታዛዥ እንደሆነ ያሳያል። (ዮሐ. 12:27, 28) ጊዜው ሲደርስ፣ ኢየሱስ ራሱን ለአምላክ ጠላቶች አሳልፎ የሰጠ ሲሆን እነዚህ ሰዎች እጅግ አሰቃቂ በሆነና በሚያዋርድ መንገድ ገድለውታል። ኢየሱስ ከፍተኛ ውጥረትና ከባድ መከራ ቢያጋጥመውም የዋህ በመሆን የአምላክን ፈቃድ አድርጓል። በእርግጥም ውጥረት በሚፈጥሩ ሁኔታዎች ሥር የዋህ በመሆን ረገድ ኢየሱስ ከሁሉ የላቀ ምሳሌ ትቶልናል ቢባል ማጋነን አይሆንም!—ኢሳ. 53:10፤ w19.02 11 አን. 14-15

ሰኞ፣ ሐምሌ 6

እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ።—ዕብ. 10:24

በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ሥር በስብሰባዎች ላይ አዘውትረን ለመገኘት ድፍረት ማሳየት ሊያስፈልገን ይችላል። አንዳንድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በስብሰባዎች ላይ የሚገኙት የደረሰባቸውን ሐዘን፣ የሚሰማቸውን የተስፋ መቁረጥ ስሜት አሊያም ያለባቸውን የጤና ችግር ተቋቁመው ነው። ሌሎች ደግሞ የቤተሰባቸው አባላት ወይም የመንግሥት ባለሥልጣናት ከባድ ተቃውሞ ቢያደርሱባቸውም በድፍረት በስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። በዚህ ረገድ የምንተወው ምሳሌ በእምነታቸው ምክንያት የታሰሩ ወንድሞቻችንን እንዴት እንደሚረዳ ለማሰብ ሞክሩ። (ዕብ. 13:3) እነዚህ ወንድሞች የሚደርስብንን መከራ ተቋቁመን ይሖዋን ማገልገላችንን እንደቀጠልን ሲሰሙ እምነታቸው ይጠናከራል፤ ይበልጥ ደፋር ይሆናሉ እንዲሁም እስከ መጨረሻው ንጹሕ አቋማቸውን ለመጠበቅ የሚያስችል ብርታት ያገኛሉ። ጳውሎስ ሮም ውስጥ ታስሮ በነበረበት ወቅት ወንድሞቹ አምላክን በታማኝነት እያገለገሉ እንደሆኑ በሰማ ቁጥር ይደሰት ነበር። (ፊልጵ. 1:3-5, 12-14) ከእስር እንደተፈታ ወይም ሊፈታ ጥቂት ጊዜ ሲቀረው ለዕብራውያን ክርስቲያኖች ደብዳቤ ጽፎ ነበር። በዚህ ደብዳቤ ላይ እነዚያን ታማኝ ክርስቲያኖች መሰብሰባቸውን ቸል እንዳይሉ አሳስቧቸዋል።—ዕብ. 10:25፤ w19.01 28 አን. 9

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 7

መላው ዓለም ግን በክፉው ቁጥጥር ሥር ነው።—1 ዮሐ. 5:19

ሰይጣን ልክ እንደ እሱ የይሖዋን መሥፈርቶች የምናቃልልና በራስ ወዳድነት ምኞት የምንመራ ዓመፀኞች እንድንሆን ይፈልጋል። በእሱ አስተሳሰብ በተበከሉ ሰዎች እንድንከበብ ያደርጋል። ይህን የሚያደርገው እነዚህ ሰዎች አስተሳሰባችንንና ድርጊታችንን ‘እንዲያበላሹት’ ወይም እንዲበክሉት ስለሚፈልግ ነው። (1 ቆሮ. 15:33) በተጨማሪም ሰይጣን ከይሖዋ አስተሳሰብ ይልቅ በሰዎች ጥበብ እንድንታመን በማድረግ ልባችንን ለመበከል ይሞክራል። (ቆላ. 2:8) ሰይጣን ከሚያስፋፋቸው ሐሳቦች መካከል አንዱን ማለትም ‘በሕይወት ውስጥ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ነገር ቁሳዊ ሀብት ማካበት ነው’ የሚለውን ሐሳብ እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ያላቸው ሰዎች ሀብታም ሊሆኑም ላይሆኑም ይችላሉ። የሆነው ሆኖ ግን ራሳቸውን አደጋ ላይ መጣላቸው አይቀርም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ቁሳዊ ሀብትን በማካበት ላይ ከማተኮራቸው የተነሳ እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ ሲሉ ጤናቸውን፣ ከቤተሰባቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት፣ አልፎ ተርፎም ከአምላክ ጋር የመሠረቱትን ወዳጅነት መሥዋዕት ሊያደርጉ ይችላሉ። (1 ጢሞ. 6:10) ጥበበኛ የሆነው ሰማያዊ አባታችን ለገንዘብ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ስለሚረዳን አመስጋኝ ልንሆን ይገባል።—መክ. 7:12፤ ሉቃስ 12:15፤ w19.01 15 አን. 6፤ 17 አን. 9

ረቡዕ፣ ሐምሌ 8

ጎበዝ፣ አንተ ጥሩና ታማኝ ባሪያ! በጥቂት ነገሮች ታማኝ ሆነህ ተገኝተሃል። ስለዚህ በብዙ ነገሮች ላይ እሾምሃለሁ። ወደ ጌታህ ደስታ ግባ።—ማቴ. 25:21

የይሖዋ ልጅ ወደ ምድር ከመምጣቱና ሌሎችን በማበረታታት ረገድ ፍጹም ምሳሌ ከመተዉ በፊትም እንኳ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች ማበረታቻ የመስጠትን አስፈላጊነት ተገንዝበው ነበር። አሦራውያን ዛቻ በሰነዘሩበት ወቅት ሕዝቅያስ የጦር አለቆቹንና የይሁዳን ሕዝብ ሰብስቦ አበረታቷል። “ሕዝቡም [እሱ] በተናገረው ቃል ተበረታታ።” (2 ዜና 32:6-8) ኢዮብ እሱ ራሱ ማጽናኛ ያስፈልገው የነበረ ቢሆንም ‘የሚያስጨንቁ አጽናኞች’ ለነበሩት ሦስት ጓደኞቹ ሌሎችን ማበረታታት የሚቻልበትን መንገድ በተመለከተ ጠቃሚ ትምህርት ሰጥቷቸዋል። እሱ በእነሱ ቦታ ቢሆን ኖሮ ‘በአፉ ቃል ያበረታቸውና በከንፈሮቹ ማጽናኛ ያሳርፋቸው እንደነበር’ ገልጾላቸዋል። (ኢዮብ 16:1-5) በመጨረሻም ኢዮብ ከኤሊሁ እንዲሁም ከይሖዋ ከራሱ ማበረታቻ አግኝቷል።—ኢዮብ 33:24, 25፤ 36:1, 11፤ 42:7, 10፤ w18.04 16 አን. 6፤ 17 አን. 8-9

ሐሙስ፣ ሐምሌ 9

አበረታሃለሁ፤ አዎ እረዳሃለሁ።—ኢሳ. 41:10

ኢሳይያስ “ይሖዋ በኃይል ይመጣል፤ ክንዱም ስለ እሱ ይገዛል” በማለት ይሖዋ ሕዝቡን የሚያበረታው ወይም የሚያጠነክረው እንዴት እንደሆነ ቀደም ብሎ ገልጿል። (ኢሳ. 40:10) አብዛኛውን ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስ “ክንድ” የሚለውን ቃል ኃይልን ለማመልከት በምሳሌያዊ ሁኔታ ይጠቀምበታል። በመሆኑም የይሖዋ ‘ክንድ እንደሚገዛ’ የሚገልጸው ሐሳብ ይሖዋ ኃያል ንጉሥ እንደሆነ ይጠቁማል። በጥንት ጊዜ ለነበሩ አገልጋዮቹ ድጋፍና ጥበቃ ለማድረግ ወደር የለሽ ኃይሉን እንደተጠቀመበት ሁሉ በዛሬው ጊዜም በእሱ የሚታመኑ አገልጋዮቹን ለማጠናከርና ለመጠበቅ ኃይሉን ይጠቀማል። (ዘዳ. 1:30, 31፤ ኢሳ. 43:10 ግርጌ) በተለይ ተቃዋሚዎች ስደት በሚያደርሱብን ጊዜ ይሖዋ “አበረታሃለሁ” በማለት የገባውን ቃል ይጠብቃል። በዛሬው ጊዜ በአንዳንድ የዓለማችን ክፍሎች ተቃዋሚዎች የስብከቱ ሥራችንን ለማስቆምና በድርጅታችን ላይ እገዳ ለመጣል ከፍተኛ ጥረት እያደረጉ ነው። ሆኖም እንዲህ ያለ ጥቃት ሲሰነዘርብን ከልክ በላይ አንጨነቅም። ይሖዋ የሰጠን ዋስትና ጠንካራና ልበ ሙሉ እንድንሆን ይረዳናል። “አንቺን ለማጥቃት የተሠራ ማንኛውም መሣሪያ ይከሽፋል” በማለት ቃል ገብቶልናል።—ኢሳ. 54:17፤ w19.01 5-6 አን. 12-13

ዓርብ፣ ሐምሌ 10

መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ደስተኞች ናቸው።—ማቴ. 5:3

የሰው ልጆች ከእንስሳት በተለየ መልኩ መንፈሳዊ ፍላጎት አላቸው፤ ይህን ፍላጎታቸውን ሊያሟላላቸው የሚችለው ደግሞ ፈጣሪ ብቻ ነው። (ማቴ. 4:4) ይሖዋ የሚላችሁን የምትሰሙ ከሆነ ማስተዋል፣ ጥበብና ደስታ ታገኛላችሁ። አምላክ በቃሉ እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” በሚያቀርበው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ አማካኝነት መንፈሳዊ ፍላጎታችሁን ያሟላላችኋል። (ማቴ. 24:45) ደግሞም ይህ መንፈሳዊ ምግብ ገንቢና ፈጽሞ የማይሰለች ነው! (ኢሳ. 65:13, 14) አምላክ የሚያቀርብላችሁ መንፈሳዊ ምግብ ጥበብና የማመዛዘን ችሎታ እንድታዳብሩ ይረዳችኋል፤ እነዚህ ባሕርያት ደግሞ በብዙ መንገድ ጥበቃ ያስገኙላችኋል። (ምሳሌ 2:10-14) ለምሳሌ ያህል፣ ጥበብና የማመዛዘን ችሎታ ‘ፈጣሪ የለም’ እንደሚሉት ያሉ የሐሰት ትምህርቶችን መለየት እንድትችሉ ዓይናችሁን ያበሩላችኋል። ‘ደስተኛ ለመሆን ቁልፉ ገንዘብና ቁሳዊ ንብረት ማካበት ነው’ ከሚለው የተሳሳተ አመለካከትም ይጠብቋችኋል። በተጨማሪም መጥፎ ምኞቶችንና ጎጂ ልማዶችን ለይታችሁ ማወቅና መከላከል እንድትችሉ ይረዷችኋል። እንግዲያው አምላካዊ ጥበብንና የማመዛዘን ችሎታን መፈለጋችሁን እንዲሁም እንደ ውድ ሀብት መመልከታችሁን ቀጥሉ! w18.12 20 አን. 6-7

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 11

የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናል።—ኢሳ. 65:22

ዕድሜያችን “እንደ ዛፍ ዕድሜ” የሚሆንበት ጊዜ ይመጣ ይሆን? አንዳንድ ዛፎች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ይኖራሉ። የሰው ልጆች እንዲህ ያለ ዕድሜ እንዲኖራቸው ጤነኞች ሊሆኑ ይገባል። ኢሳይያስ በትንቢቱ ላይ የገለጸው ዓይነት ሕይወት መኖር ከቻሉ ሕይወታቸው እጅግ አስደሳች ይሆናል! ደግሞስ ገነት ማለት ይህ አይደል? በዚያን ጊዜ ትንቢቱ ፍጻሜውን ያገኛል! የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ወደፊት ምድር ገነት እንደምትሆን የሚጠቁሙት እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክሩ፦ የምድር ሕዝቦች ሁሉ በአምላክ የተባረኩ ይሆናሉ። ማንም ከአውሬዎች ወይም የአውሬ ባሕርይ ካላቸው ሰዎች ጥቃት ይሰነዘርብኛል ብሎ አይሰጋም። ዓይነ ስውራን፣ መስማት የተሳናቸውና አንካሶች ይፈወሳሉ። ሰዎች የራሳቸውን ቤት የሚሠሩ ከመሆኑም ሌላ እህል ማምረትና የተትረፈረፈ ምርት መሰብሰብ ይችላሉ። ዕድሜያቸው ከዛፍ ዕድሜ የበለጠ ይሆናል። አዎ፣ መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ያለ ጊዜ እንደሚመጣ ይጠቁማል። ሆኖም አንዳንዶች እነዚህን ትንቢቶች በዚህ መልኩ ለመረዳት የሚያስችል በቂ ማስረጃ እንደሌለ ይሰማቸዋል። ምድር ገነት እንደምትሆን ተስፋ ለማድረግ የሚያስችል ምን አሳማኝ ማስረጃ አለህ? በምድር ላይ ከኖሩት ሁሉ የሚበልጠው ታላቁ ሰው አስተማማኝ ማስረጃ ሰጥቶናል።—ሉቃስ 23:43፤ w18.12 5 አን. 13-15

እሁድ፣ ሐምሌ 12

አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።—ሮም 12:2

አእምሯችን በተፈለገው መንገድ የመቀረጽና የመለዋወጥ ችሎታ አለው። ይህ ለውጥ በአብዛኛው የተመካው ወደ አእምሯችን በምናስገባውና በምናውጠነጥነው ነገር ላይ ነው። የይሖዋን አስተሳሰብ ማውጠንጠናችን ወይም በእሱ አስተሳሰብ ላይ ማሰላሰላችን የእሱ አመለካከት ትክክል መሆኑን አምነን እንድንቀበል ያደርገናል። ይህም አስተሳሰባችንን ከእሱ አስተሳሰብ ጋር የማስማማት ውስጣዊ ፍላጎት እንዲያድርብን ይረዳናል። ይሁንና አእምሯችንን በማደስ የይሖዋን አስተሳሰብ ለመቀበል “ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንዳለብን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር የሚጋጩ ሐሳቦችን ወይም አመለካከቶችን ወደ አእምሯችን ማስገባታችንን ማቆም አለብን። ይህን የመጀመሪያ እርምጃ መውሰድ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። አንድ ሰው ጤንነቱን ለማሻሻል ገንቢ ምግቦችን መመገብ ጀመረ እንበል። ሆኖም ይህ ሰው ጎን ለጎን የተበላሸ ምግብም የሚመገብ ከሆነ ገንቢ ምግብ መመገቡ ምን ጥቅም ይኖረዋል? በተመሳሳይም የተበላሹ ዓለማዊ ሐሳቦችን ወደ አእምሯችን የምናስገባ ከሆነ አእምሯችንን በይሖዋ አስተሳሰብ ለመሙላት መሞከራችን እምብዛም ጥቅም አይኖረውም። w18.11 21 አን. 14-15

ሰኞ፣ ሐምሌ 13

ወገባችሁን በእውነት ቀበቶ ታጥቃችሁ . . . ጸንታችሁ ቁሙ።—ኤፌ. 6:14

በየዕለቱ ከእውነት ጋር በሚስማማ መንገድ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ ይኖርብናል። ወገባችሁን በእውነት ቀበቶ ታጠቁ። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን አንድ ወታደር የሚታጠቀው ቀበቶ ወገቡን ለመደገፍና ሆድ ዕቃውን ከአደጋ ለመጠበቅ ይረዳዋል። ሆኖም ቀበቶው ጥበቃ እንዲያስገኝ ከተፈለገ ጥብቅ ተደርጎ መታሰር አለበት። ላላ ተደርጎ የታሰረ ቀበቶ ለወታደሩ ያን ያህል ድጋፍ ሊሰጥ አይችልም። መንፈሳዊው የእውነት ቀበቶስ ጥበቃ የሚያስገኝልን እንዴት ነው? እውነትን ልክ እንደ ቀበቶ ጥብቅ አድርገን ከታጠቅነው ከተሳሳተ አስተሳሰብ የሚጠብቀን ከመሆኑም ሌላ ትክክለኛ ውሳኔዎችን እንድናደርግ ይረዳናል። ፈተና ወይም ስደት ሲያጋጥመን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ትክክለኛ እርምጃ ለመውሰድ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ያጠናክርልናል። አንድ ወታደር ቀበቶውን ሳይታጠቅ ወደ ጦር ሜዳ ለመሄድ ፈጽሞ እንደማያስብ ሁሉ እኛም የእውነትን ቀበቶ ፈጽሞ ላለማላላት ወይም ላለማውለቅ ቁርጥ ውሳኔ ማድረግ አለብን። ከዚህ ይልቅ ከእውነት ጋር ተስማምተን በመኖር፣ የታጠቅነው የእውነት ቀበቶ ምንጊዜም ጥብቅ እንዲሆን የቻልነውን ሁሉ እናደርጋለን። w18.11 12 አን. 15

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 14

እውነትን . . . ግዛ፤ ፈጽሞም [አትሽጠው]።—ምሳሌ 23:23

በአምላክ ቃል ውስጥ ያለውን እውነት ያለምንም ጥረት ማግኘት አንችልም። ይህን እውነት ለማግኘት አስፈላጊ የሆነውን መሥዋዕትነት ሁሉ ለመክፈል ፈቃደኞች መሆን አለብን። ጠቢብ የሆነው የምሳሌ መጽሐፍ ጸሐፊ እንደተናገረው “እውነትን” አንዴ ‘ከገዛን’ ወይም ካገኘን በኋላ ‘እንዳንሸጠው’ ወይም እንዳናጣው መጠንቀቅ ይኖርብናል። ነፃ የሆነን ነገር ለማግኘት እንኳ ዋጋ መክፈል ሊያስፈልገን ይችላል። በምሳሌ 23:23 ላይ ‘መግዛት’ ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ቃል ‘ማግኘት’ የሚል ትርጉምም ሊኖረው ይችላል። ሁለቱም ቃላት ከፍተኛ ጥረት ማድረግን ወይም ውድ ዋጋ ያለውን ነገር የራስ ለማድረግ ሲባል በምትኩ ሌላ ነገር መስጠትን ያመለክታሉ። ‘እውነትን መግዛት’ የሚለውን ሐሳብ ግልጽ ለማድረግ አንድ ምሳሌ እንመልከት። በአንድ የገበያ ቦታ “ሙዝ በነፃ ውሰዱ” የሚል ማስታወቂያ ተሰቅሏል እንበል። ይህ ሲባል ታዲያ ሙዙ ተአምራዊ በሆነ መንገድ ወደ ቤታችሁ ይመጣል ማለት ነው? በፍጹም። ወደ ገበያ ቦታ ሄዳችሁ ሙዙን ይዛችሁ መምጣት ይኖርባችኋል። እርግጥ ሙዙን ያገኛችሁት በነፃ ነው። ሆኖም ወደ ገበያ ቦታው ለመሄድ ጊዜያችሁንና ጉልበታችሁን መሥዋዕት ማድረግ ያስፈልጋችኋል። በተመሳሳይም እውነትን ለመግዛት ገንዘብ መክፈል አይጠበቅብንም፤ ጥረት ማድረግ ግን ያስፈልገናል። w18.11 4 አን. 4-5

ረቡዕ፣ ሐምሌ 15

ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም እንደ ብርሃን አንጸባረቀ።—ማቴ. 17:2

ኢየሱስ ከጴጥሮስ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ወደ አንድ ከፍ ያለ ተራራ ሄደ። በዚያም እነዚህ ሐዋርያት አስደናቂ ራእይ ተመለከቱ። የኢየሱስ ፊት በደማቁ አበራ፤ ልብሱም ማንጸባረቅ ጀመረ። ከዚያም ሙሴንና ኤልያስን የሚወክሉ ሁለት ሰዎች ተገልጠው ከኢየሱስ ጋር ከፊቱ ስለሚጠብቀው ሞትና ስለ ትንሣኤው ይነጋገሩ ጀመር። (ሉቃስ 9:29-32) ከዚያም ብሩህ ደመና ከጋረዳቸው በኋላ ከደመናው ውስጥ አንድ ድምፅ ሰሙ። ይህ ድምፅ የአምላክ ድምፅ ነበር! ይህ ራእይ ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ ሲሾም ምን ያህል ክብርና ኃይል እንደሚኖረው ያሳያል። ራእዩ ኢየሱስ ከፊቱ የሚጠብቀውን መከራና አሰቃቂ ሞት በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል ብርታትና ጥንካሬ እንዲያገኝ እንደረዳው ምንም ጥርጥር የለውም። በተጨማሪም የደቀ መዛሙርቱን እምነት አጠናክሮላቸዋል። ወደፊት በንጹሕ አቋማቸው ላይ የሚደርሰውን ፈተና ለመቋቋምና ለበርካታ ዓመታት ሊያከናውኑት የሚገባውን ሥራ ለመወጣት የሚያስችል ጥንካሬ ሰጥቷቸዋል። ከ30 ዓመታት ገደማ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ በተአምራዊ ሁኔታ ስለተለወጠበት ራእይ የጠቀሰ ሲሆን ይህም ራእዩን እስከዚያ ጊዜ ድረስ በሚገባ እንደሚያስታውሰው ያሳያል።—2 ጴጥ. 1:16-18፤ w19.03 10 አን. 7-8

ሐሙስ፣ ሐምሌ 16

[እውነት የሆነውን በመናገር] ራሳችንን ብቁ የአምላክ አገልጋዮች አድርገን እናቀርባለን።—2 ቆሮ. 6:4, 7

እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሐሰት ሃይማኖት ተከታዮች የሚለዩበት አንዱ መንገድ ምንድን ነው? ‘እርስ በርሳቸው እውነትን መነጋገራቸው’ ነው። (ዘካ. 8:16, 17) ለማያውቋቸው ሰዎች፣ ለሥራ ባልደረቦቻቸው፣ ለጓደኞቻቸው ወይም ለሚወዷቸው ሰዎች ቀላልም ሆነ ከባድ በሆኑ ጉዳዮች እውነቱን ይናገራሉ። በእኩዮችህ ዘንድ ተቀባይነት የማግኘት ጉዳይ የሚያሳስብህ ወጣት ነህ? እንግዲያው አንዳንድ ወጣቶች እንደሚያደርጉት ሁለት ዓይነት ሕይወት እንዳትመራ ተጠንቀቅ። እነዚህ ወጣቶች ከቤተሰባቸው ወይም ከጉባኤው አባላት ጋር ሲሆኑ ንጹሕ ሥነ ምግባር ያላቸው መስለው ለመታየት ይሞክራሉ፤ ዓለማዊ ከሆኑ እኩዮቻቸው ጋር ሲሆኑ አሊያም ማኅበራዊ ድረ ገፆችን ሲጠቀሙ ግን ፈጽሞ የተለየ ሰው ይሆናሉ። እነዚህ ወጣቶች ሕይወታቸው በሙሉ በውሸት የተሞላ ነው፤ ወላጆቻቸውን፣ የእምነት ባልንጀሮቻቸውንና አምላክን እየዋሹ ነው። (መዝ. 26:4, 5) ይሖዋ ‘ልባችን ከእሱ እጅግ የራቀ ሆኖ’ በከንፈራችን ብቻ ስናከብረው ያውቃል። (ማር. 7:6) እንግዲያው “ልብህ በኃጢአተኞች አይቅና፤ ከዚህ ይልቅ ቀኑን ሙሉ ይሖዋን በመፍራት ተመላለስ” የሚለውን በምሳሌ መጽሐፍ ላይ የሚገኘውን ምክር መከተላችን ምንኛ የተሻለ ነው!—ምሳሌ 23:17፤ w18.10 9 አን. 14-15

ዓርብ፣ ሐምሌ 17

አምላክ ፍቅር ነው፤ በፍቅር የሚኖር ከአምላክ ጋር ያለውን አንድነት ጠብቆ ይኖራል፤ አምላክም ከእሱ ጋር አንድነት ይኖረዋል።—1 ዮሐ. 4:16

በመላው ዓለም ያሉት የአምላክ አገልጋዮች እንደ አንድ ቤተሰብ ናቸው፤ ተለይተው የሚታወቁትም በመካከላቸው ባለው ፍቅር ነው። (1 ዮሐ. 4:21) ክርስቲያኖች ለወንድሞቻቸው ሲሉ ከፍተኛ መሥዋዕት የሚከፍሉባቸው ጊዜያት አሉ፤ ሆኖም አብዛኛውን ጊዜ ፍቅራቸውን የሚገልጹት፣ ለወንድሞቻቸው በሚያከናውኗቸው ትናንሽ የደግነት ድርጊቶች እንዲሁም በሚናገሯቸው አሳቢነት የሚንጸባረቅባቸው ቃላት ነው። ለሌሎች ደግነትና አሳቢነት ስናሳይ ‘የተወደድን ልጆቹ በመሆን አምላክን መምሰል’ እንችላለን። (ኤፌ. 5:1) ኢየሱስ አባቱን ፍጹም በሆነ መንገድ መስሏል። “እናንተ የደከማችሁና ሸክም የከበዳችሁ ሁሉ ወደ እኔ ኑ፤ እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ። . . . እኔ ገርና በልቤ ትሑት ነኝ” በማለት ተናግሯል። (ማቴ. 11:28, 29) ‘ለተቸገረ ሰው አሳቢነት በማሳየት’ የክርስቶስን ምሳሌ ስንከተል በሰማይ ያለውን አባታችንን ሞገስ እንዲሁም ታላቅ ደስታ እናገኛለን። (መዝ. 41:1) ስለዚህ በቤተሰባችንና በጉባኤ ውስጥ እንዲሁም በአገልግሎት ላይ ለሌሎች አሳቢነት በማሳየት ፍቅርን እናንጸባርቅ። w18.09 28 አን. 1-2

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 18

እኛ ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን።—1 ቆሮ. 3:9

አደጋ በሚከሰትበት ጊዜ የአምላክ ሕዝቦች ወንድሞቻቸውን በመርዳት ከአምላክ ጋር የመሥራት አጋጣሚ ያገኛሉ። ለምሳሌ ያህል፣ በአደጋው ለተጎዱት የገንዘብ ድጋፍ ማድረግ እንችላለን። (ዮሐ. 13:34, 35፤ ሥራ 11:27-30) ወንድሞቻችንን መርዳት የምንችልበት ሌላው መንገድ ደግሞ በጽዳት ወይም በመልሶ ግንባታ ሥራ መካፈል ነው። ጋብርኤላ የተባለች በፖላንድ የምትኖር አንዲት እህት በጎርፍ ምክንያት ቤቷ ከፍተኛ ጉዳት ደርሶበት ነበር፤ ይህች እህት በአቅራቢያዋ በሚገኙ ጉባኤዎች ውስጥ ያሉ ወንድሞች ሊረዷት ሲመጡ በጣም ተደሰተች። ጋብርኤላ ስላጣቻቸው ቁሳዊ ነገሮች ከመጨነቅ ይልቅ ባገኘቻቸው ነገሮች ላይ ትኩረት ታደርጋለች። እንዲህ ብላለች፦ “ይህ አጋጣሚ፣ የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆን ልዩ መብት እንደሆነና ታላቅ ደስታ እንደሚያስገኝ እንዳስታውስ ረድቶኛል።” አደጋ አጋጥሟቸው የወንድሞችን እርዳታ ያገኙ በርካታ ክርስቲያኖች፣ ካጡት የበለጠ እንዳገኙ ተሰምቷቸዋል። እንዲህ ዓይነቱን እርዳታ በማበርከት ከይሖዋ ጋር የሚሠሩ ወንድሞችም ይህን ማድረጋቸው ላቅ ያለ እርካታ ያስገኝላቸዋል።—ሥራ 20:35፤ 2 ቆሮ. 9:6, 7፤ w18.08 26 አን. 12

እሁድ፣ ሐምሌ 19

ልብህን ጠብቅ።—ምሳሌ 4:23

ልባችንን በመጠበቅ ረገድ እንዲሳካልን ከፈለግን አደጋዎችን ለይተን ማወቅና ራሳችንን ለመጠበቅ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። “ጠብቅ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ጠባቂዎች የሚያከናውኑትን ሥራ ያስታውሰናል። በንጉሥ ሰለሞን ዘመን የነበሩ ጠባቂዎች በከተማዋ ቅጥር ላይ የሚቆሙ ሲሆን አደጋ መቅረቡን ሲያዩ የማስጠንቀቂያ ድምፅ ያሰሙ ነበር። ይህን ሁኔታ በአእምሯችን መሣላችን ሰይጣን አስተሳሰባችንን እንዳያበላሸው ለመከላከል ምን ማድረግ እንዳለብን እንድንገነዘብ ይረዳናል። በጥንት ዘመን የነበሩ ጠባቂዎች፣ ከከተማዋ በር ጠባቂዎች ጋር ተባብረው ይሠሩ ነበር። (2 ሳሙ. 18:24-26) ሁለቱ ጠባቂዎች፣ ጠላት በሚቃረብበት ጊዜ ሁሉ የከተማዋ በሮች መዘጋታቸውን በማረጋገጥ የከተማዋን ደህንነት በጋራ ይጠብቁ ነበር። (ነህ. 7:1-3) ሰይጣን ልባችንን ለመውረር በሌላ አባባል በአስተሳሰባችን፣ በስሜታችን፣ በዝንባሌያችን ወይም በምኞታችን ላይ ተጽዕኖ ለማድረግ ሲሞክር በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነው ሕሊናችን እንደ ጠባቂ በመሆን ያስጠነቅቀናል። ሕሊናችን የማስጠንቀቂያ ድምፅ በሚያሰማበት ጊዜ ሁሉ ማስጠንቀቂያውን መስማትና ምሳሌያዊ በሮቻችንን መዝጋት ይኖርብናል። w19.01 17 አን. 10-11

ሰኞ፣ ሐምሌ 20

ከክስ ነፃ ሆነው ከተገኙ አገልጋይ ሆነው ያገልግሉ።—1 ጢሞ. 3:10

ሽማግሌዎች ወጣት ወንዶችን የሚገመግሙት፣ በአምላክ ቃል ውስጥ በሚገኙት መሥፈርቶች መሠረት እንጂ በግል አመለካከታቸው ወይም በባሕላቸው ላይ ተመሥርተው ሊሆን አይገባም። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ አመለካከት፣ ብቃት ያላቸው ወንድሞች አንዳንድ መብቶችን እንዳያገኙ እንቅፋት ሊሆን ይችላል። አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ በአንድ አገር ያለ ጥሩ ብቃት ያለው የጉባኤ አገልጋይ ከበድ ያሉ ኃላፊነቶች ተሰጥተውት ነበር። የጉባኤው ሽማግሌዎች ይህ ወጣት ወንድም፣ ሽማግሌ ለመሆን የሚያስፈልጉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶች ምክንያታዊ በሆነ ደረጃ እንዳሟላ ቢስማሙም ይህ ወንድም እንዲሾም የድጋፍ ሐሳብ አላቀረቡም። በዕድሜ የገፉ አንዳንድ ሽማግሌዎች፣ ወንድም በጣም ወጣት ስለሚመስል እንደ ሽማግሌ ላይታይ እንደሚችል ተሰምቷቸው ነበር። ወንድም፣ ወጣት በመምሰሉ ምክንያት ብቻ የጉባኤ ሽማግሌ ሆኖ አለመሾሙ ያሳዝናል። ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች የተገኙ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ብዙዎች እንዲህ ያለ አመለካከት አላቸው። በግል አመለካከታችን ሳይሆን በቅዱሳን መጻሕፍት መመራታችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ኢየሱስ የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት እንዳንፈርድ የሰጠንን ምክር የምንታዘዘው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው።—ዮሐ. 7:24፤ w18.08 12 አን. 16-17

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 21

እውነታውን ከመስማቱ በፊት መልስ የሚሰጥ ሰው፣ ሞኝነት ይሆንበታል፤ ውርደትም ይከናነባል።—ምሳሌ 18:13

የሚደርሱንን ኢ-ሜይሎች እና የጽሑፍ መልእክቶች ለሌሎች በችኮላ መላክ አደጋ አለው። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ የይሖዋ ምሥክሮች በነፃነት መስበክ አይችሉም፤ በሌሎች አገሮች ደግሞ ሥራችን ሙሉ በሙሉ ታግዷል። እንደነዚህ ባሉት አገሮች ውስጥ ያሉ ተቃዋሚዎች፣ ፍርሃት እንዲያድርብን ወይም ከወንድሞቻችን ጋር በጥርጣሬ ዓይን እንድንተያይ የሚያደርጉ ወሬዎችን ሆን ብለው ይነዛሉ። በቀድሞዋ ሶቪየት ኅብረት የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ኬ ጂ ቢ ተብለው የሚጠሩት የሚስጥር ፖሊሶች፣ ኃላፊነት ያላቸው በርካታ ወንድሞች የይሖዋን ሕዝብ እንደካዱ የሚገልጽ ወሬ አናፈሱ። ብዙዎች ይህን የሐሰት ወሬ በማመናቸው ራሳቸውን ከይሖዋ ድርጅት አገለሉ። ይህ እንዴት የሚያሳዝን ነው! ደስ የሚለው ነገር፣ ከጊዜ በኋላ ብዙዎቹ ተመልሰዋል፤ አንዳንዶቹ ግን ሳይመለሱ ቀርተዋል። እነዚህ ሰዎች ባሕር ላይ አደጋ ደርሶበት እንደተሰባበረ መርከብ እምነታቸው ጠፍቷል። (1 ጢሞ. 1:19) እንዲህ ያለ አሳዛኝ ነገር እንዳይደርስ መከላከል የምንችለው እንዴት ነው? አሉታዊ የሆኑ ወይም ያልተረጋገጡ ዘገባዎችን ከማሰራጨት በመቆጠብ ነው። በቀላሉ ላለመሞኘት ወይም ላለመታለል እንጠንቀቅ። የሰማነውን ሁሉ ከማመናችን በፊት የተሟላ መረጃ ለማግኘት ጥረት እናድርግ። w18.08 4 አን. 8

ረቡዕ፣ ሐምሌ 22

እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ።—ሉቃስ 23:43

ጥንታዊ የሚባሉት በእጅ የተገለበጡ የግሪክኛ ቅዱሳን መጻሕፍት ቅጂዎች ሥርዓተ ነጥቦችን ወጥ በሆነ መንገድ አይጠቀሙም። ይህም የሚከተለውን ጥያቄ ያስነሳል፦ ኢየሱስ ያለው “እውነት እልሃለሁ፣ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ” ነው ወይስ “እውነት እልሃለሁ ዛሬ፣ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ”? ኢየሱስ ቀደም ሲል ተከታዮቹን “የሰው ልጅ . . . በምድር ልብ ውስጥ ሦስት ቀንና ሦስት ሌሊት ይቆያል” እንዳላቸው ማስተዋል ያስፈልጋል። (ማቴ. 12:40፤ 16:21፤ 17:22, 23፤ ማር. 10:34፤ ሥራ 10:39, 40) በመሆኑም ኢየሱስ በሞተበት ዕለት ወደ ገነት አልገባም። ከዚህ ይልቅ አምላክ ከሞት እስኪያስነሳው ድረስ “በመቃብር [ወይም “በሐዲስ”]” ውስጥ ነበር። (ሥራ 2:31, 32 ግርጌ) ሞት አፋፍ ላይ የነበረው ያ ወንጀለኛ ኢየሱስ ለታማኝ ሐዋርያቱ በመንግሥተ ሰማያት ከእሱ ጋር አብረው እንደሚሆኑ የገባላቸውን ቃል እንደማያውቅ ግልጽ ነው። (ሉቃስ 22:29) ከዚህም በላይ ይህ ወንጀለኛ ገና ለመጠመቅ እንኳ አልበቃም ነበር። (ዮሐ. 3:3-6, 12) በመሆኑም ኢየሱስ ቃል የገባለት ስለ ምድራዊ ገነት መሆን አለበት። w18.12 6 አን. 17-18, 20-21

ሐሙስ፣ ሐምሌ 23

ያ ሙሴ ምን እንደደረሰበት ስለማናውቅ በል ተነስተህ ከፊት ከፊታችን የሚሄድ አምላክ ሥራልን።—ዘፀ. 32:1

ብዙም ሳይቆይ እስራኤላውያን የወርቅ ጥጃ ማምለክ ጀመሩ! እስራኤላውያን እንዲህ ባለ ግልጽ የሆነ መንገድ የይሖዋን ትእዛዝ ቢጥሱም አሁንም ከይሖዋ ጎን እንደሆኑ አድርገው በማሰብ ራሳቸውን አታለው ነበር። እንዲያውም አሮን የጥጃ አምልኳቸውን “ለይሖዋ የሚከበር በዓል” በማለት ጠርቶታል! ይሖዋ ምን ተሰማው? ሕዝቡ የፈጸመውን ድርጊት እንደ ክህደት ቆጥሮታል። እስራኤላውያን “ምግባረ ብልሹ [እንደሆኑ]” እንዲሁም ‘እንዲሄዱበት ካዘዛቸው መንገድ ዞር እንዳሉ’ ለሙሴ ነግሮታል። ይሖዋ ‘ቁጣው ከመንደዱ’ የተነሳ አዲስ የተቋቋመውን የእስራኤልን ብሔር ሙሉ በሙሉ ለማጥፋት አስቦ ነበር። (ዘፀ. 32:5-10) ሆኖም ይሖዋ እስራኤላውያንን ላለማጥፋት ወሰነ። (ዘፀ. 32:14) ምንም እንኳ አሮን መጀመሪያ ላይ ከሕዝቡ ጋር ተባብሮ ጣዖት የሠራ ቢሆንም በኋላ ላይ ንስሐ በመግባት እንደ ሌሎቹ ሌዋውያን ከይሖዋ ጎን ቆሟል። በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በጣዖት አምልኮ በመካፈላቸው ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከይሖዋ ጎን የቆሙት ሰዎች ግን በረከት እንደሚያገኙ ቃል ተገብቶላቸዋል።—ዘፀ. 32:26-29፤ w18.07 20 አን. 13-16

ዓርብ፣ ሐምሌ 24

በገበያ ቦታ ሰዎች እጅ እንዲነሷቸው ከሚሹ እንዲሁም . . . በራት ግብዣ ላይም የክብር ቦታ መያዝ ከሚፈልጉ ከጸሐፍት ተጠንቀቁ።—ሉቃስ 20:46

ልንጣጣርለት የሚገባው ከሁሉ የላቀ እውቅና የትኛው ነው? ይህ እውቅና ሰዎች በትምህርት፣ በንግድ ወይም በመዝናኛው መስክ ለማግኘት የሚጣጣሩት ዓይነት እውቅና አይደለም። ጳውሎስ የተናገራቸው የሚከተሉት ቃላት ከሁሉ የላቀው እውቅና የትኛው እንደሆነ ያሳያሉ፦ “አሁን . . . አምላክን አውቃችኋል፤ እንዲያውም አምላክ እናንተን አውቋችኋል፤ ታዲያ ደካማና ከንቱ ወደሆኑ ተራ ነገሮች መመለስና እንደገና ለእነዚህ ነገሮች ባሪያ መሆን ትፈልጋላችሁ?” (ገላ. 4:9) የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ገዢ በሆነው አምላክ መታወቅ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! አምላክ ከእኛ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት ፈቃደኛ ነው። አንድ ምሁር እንደገለጹት “እሱ በሞገስ ዓይኑ የሚመለከተን ሰዎች እንሆናለን” ማለት ነው። ይሖዋ እኛን እንደ ወዳጆቹ አድርጎ ሲቆጥረን በሕይወት የምንኖርበትን ዓላማ እናሳካለን።—መክ. 12:13, 14፤ w18.07 8 አን. 3-4

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 25

በማሳሰቢያዎችህ ላይ [አሰላስላለሁ]።—መዝ. 119:99

የአምላክ ሕጎች ሕሊናችንን እንዲያሠለጥኑት፣ ለሕጎቹ ፍቅርና አክብሮት ማዳበር ይኖርብናል። (አሞጽ 5:15) ይሁንና እንዲህ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ቁልፉ፣ ይሖዋ ለነገሮች ያለው ዓይነት አመለካከት ማዳበር ነው። ነጥቡን በምሳሌ ለማስረዳት፦ እንቅልፍ አልወስድ ብሎህ ተቸግረሃል እንበል። ሐኪምህ ጤናማ የአመጋገብ ልማድ እንዲኖርህ፣ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ እንድታደርግና በሕይወትህ ውስጥ ሌሎች አስፈላጊ ለውጦችን እንድታደርግ የሚረዳህ ጠቃሚ ምክር ሰጠህ። ምክሩን በተግባር ስታውል ጥሩ እንቅልፍ መተኛት ቻልክ! ሐኪሙ ላደረገልህ እርዳታ በጣም አመስጋኝ እንደምትሆን ጥርጥር የለውም። በተመሳሳይም ፈጣሪያችን የሰጠን ሕጎች ኃጢአት መሥራት ከሚያስከትለው መዘዝ ይጠብቁናል፤ እንዲሁም የተሻለ ሕይወት እንድንመራ ይረዱናል። ለምሳሌ ከውሸት፣ ከማጭበርበር፣ ከስርቆት፣ ከፆታ ብልግና፣ ከዓመፅ እንዲሁም ከመናፍስታዊ ድርጊቶች እንድንርቅ የሚመክሩንን የመጽሐፍ ቅዱስ ሕጎች መታዘዛችን ምን ያህል እንደሚጠቅመን እናስብ። (ምሳሌ 6:16-19፤ ራእይ 21:8) የይሖዋን መመሪያዎች መከተል የሚያስገኘውን ታላቅ ጥቅም በሕይወታችን ውስጥ ስንመለከት ለይሖዋም ሆነ ለሕጎቹ ያለን ፍቅርና አድናቆት እየጨመረ እንደሚሄድ ጥርጥር የለውም። w18.06 17 አን. 5-6

እሁድ፣ ሐምሌ 26

አንተ የአይሁዳውያን ንጉሥ ነህ?—ዮሐ. 18:33

አገረ ገዢው ይህን ጥያቄ ያቀረበው ኢየሱስ ፖለቲካዊ አለመረጋጋት እንዳይፈጥር ስለሰጋ ሊሆን ይችላል፤ ደግሞም በጲላጦስ ዘመን ይህ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነበር። ኢየሱስ ግን “መንግሥቴ የዚህ ዓለም ክፍል አይደለም” በማለት መልሶለታል። (ዮሐ. 18:36) ኢየሱስ፣ መንግሥቱ የሚቋቋመው በሰማይ ስለሆነ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ እንደማይገባ ገልጿል። ወደ ምድር የመጣው “ስለ እውነት ለመመሥከር” እንደሆነ ለጲላጦስ ነግሮታል። (ዮሐ. 18:37) እኛም እንደ ኢየሱስ ተልዕኳችን ምን እንደሆነ ሁልጊዜ የምናስታውስ ከሆነ ፖለቲካዊ ነፃነት ለማግኘት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎችን በልባችንም ቢሆን አንደግፍም። በእርግጥ ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም። አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች እንዲህ ብሏል፦ “በአካባቢያችን ያሉ ሰዎች ለውጥ እንደሚያስፈልግ ይበልጥ እየተሰማቸው ነው። ብሔራዊ ስሜት እየተስፋፋ ሲሆን ብዙዎች ሕይወታቸውን የሚያሻሽለው ፖለቲካዊ ነፃነት ማግኘታቸው እንደሆነ ያስባሉ። ደስ የሚለው ነገር፣ ወንድሞች የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩ ሥራ በመጠመድ ክርስቲያናዊ አንድነታቸውን ጠብቀው መኖር ችለዋል። ለፍትሕ መጓደልም ሆነ ለሚያጋጥሙን ሌሎች ችግሮች መፍትሔ ማስገኘት የሚችለው አምላክ ብቻ እንደሆነ ይተማመናሉ።” w18.06 4-5 አን. 6-7

ሰኞ፣ ሐምሌ 27

ዲያብሎስን ግን ተቃወሙት፤ እሱም ከእናንተ ይሸሻል።—ያዕ. 4:7

“ተቃዋሚ” የሚል ትርጉም ያለው ሰይጣን የሚለው መጠሪያ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ የሚገኘው በሦስት መጻሕፍት ይኸውም በ1 ዜና መዋዕል፣ በኢዮብና በዘካርያስ ላይ ብቻ ነው። ለመሆኑ መሲሑ ከመምጣቱ በፊት ስለ ጠላታችን የሚገልጽ ብዙ መረጃ ያልሰፈረው ለምንድን ነው? ይሖዋ ስለ ሰይጣንና ስለ ሥራዎቹ በዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ሰፋ ያለ ማብራሪያ በማስፈር ለዚህ ጠላት አላስፈላጊ እውቅና መስጠት የፈለገ አይመስልም። ይሖዋ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት እንዲጻፉ ያደረገበት ዋነኛ ዓላማ፣ ሰዎች መሲሑን ማወቅና መከተል እንዲችሉ ለመርዳት ነው። (ሉቃስ 24:44፤ ገላ. 3:24) መሲሑ መጥቶ ይህ ዓላማ ከዳር ሲደርስ፣ ይሖዋ በመሲሑና በደቀ መዛሙርቱ በመጠቀም ስለ ሰይጣንና ግብረ አበሮቹ ስለሆኑት መላእክት ተጨማሪ መረጃ ሰጠ፤ ሰይጣንና አጋንንቱን በተመለከተ ከምናውቀው መረጃ አብዛኛውን ያገኘነው በዚህ መንገድ ነው። ይህ መሆኑም ተገቢ ነው፤ ምክንያቱም ሰይጣንን እና ተከታዮቹን ለመጨፍለቅ ይሖዋ የሚጠቀመው በኢየሱስና አብረውት በሚገዙት ቅቡዓን ነው። (ሮም 16:20፤ ራእይ 17:14፤ 20:10) ሰይጣን ያለው ኃይል ገደብ የለሽ እንዳልሆነ አስታውስ። ይሖዋ፣ ኢየሱስ እንዲሁም ታማኝ መላእክት ከጎናችን ናቸው። በእነሱ እርዳታ ጠላታችንን መቋቋም እንችላለን። w18.05 22-23 አን. 2-4

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 28

ፍሬ የማያፈራውን ቅርንጫፍ ሁሉ ቆርጦ ይጥለዋል።—ዮሐ. 15:2

ይሖዋ እንደ አገልጋዮቹ አድርጎ የሚመለከተን ፍሬ የምናፈራ ከሆነ ብቻ ነው። (ማቴ. 13:23፤ 21:43) ስለሆነም በዮሐንስ 15:2 ላይ በሚገኘው ምሳሌ ላይ እያንዳንዱ ክርስቲያን ማፍራት እንዳለበት የተጠቀሰው ፍሬ፣ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ማስገኘትን የሚያመለክት ሊሆን አይችልም። (ማቴ. 28:19) ይህ ባይሆን ኖሮ አብዛኞቹ ሰዎች ምሥራቹን በማይቀበሉበት ክልል ውስጥ የሚያገለግሉ ታማኝ ክርስቲያኖች፣ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ማስገኘት ባለመቻላቸው ምክንያት በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተጠቀሱት ፍሬ የማያፈሩ ቅርንጫፎች ይቆጠሩ ነበር። ይሁንና ይህ ጨርሶ ሊሆን የማይችል ነገር ነው! ለምን? ምክንያቱም ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ማስገደድ አንችልም። ይህ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ የሆነ ነገር ነው፤ አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ይሖዋ ደግሞ ከአቅማችን በላይ የሆነውን ነገር ባለማድረጋችን ምክንያት አገልጋዮቹ ለመሆን ብቁ እንዳልሆንን አድርጎ ይመለከተናል ብሎ ማሰብ የማይመስል ነገር ነው። ይሖዋ ምንጊዜም ቢሆን ማድረግ የማንችለውን ነገር አይጠብቅብንም። (ዘዳ. 30:11-14) ለመሆኑ ልናፈራው የሚገባው ፍሬ ምንድን ነው? ፍሬው፣ ሁላችንም ልናከናውን የምንችለውን ሥራ የሚያመለክት መሆን አለበት። ታዲያ ይህ ሥራ የትኛው ነው? የአምላክን መንግሥት ምሥራች መስበክ ነው።—ማቴ. 24:14፤ w18.05 14 አን. 8-9

ረቡዕ፣ ሐምሌ 29

እናንተ ከአባታችሁ ከዲያብሎስ ናችሁ፤ [እሱ] ውሸታምና የውሸት አባት [ነው]።—ዮሐ. 8:44

በዛሬው ጊዜ ፓስተር፣ ቄስና ረቢ ተብለው የሚጠሩትን ጨምሮ በርካታ የሃይማኖት መሪዎች አሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደነበሩት የሃይማኖት መሪዎች ሁሉ እነዚህ የሃይማኖት መሪዎችም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ‘እውነት የሚያፍኑ’ ከመሆኑም ሌላ “የአምላክን እውነት በሐሰት [ይለውጣሉ]።” (ሮም 1:18, 25) ‘አንዴ የዳነ ለሁልጊዜው ድኗል፣’ ‘ነፍስ አትሞትም፣’ ‘የሞተ ሰው በሌላ አካል ተመልሶ ይወለዳል’ እንዲሁም ‘አምላክ ግብረ ሰዶማዊነትንና በተመሳሳይ ፆታ መካከል የሚደረገውን ጋብቻ አይቃወምም’ እንደሚሉት ያሉ የሐሰት ትምህርቶችን ያስተምራሉ። የፖለቲካ መሪዎችም ውሸት በመናገር ሰዎችን ያሳስታሉ። እነዚህ መሪዎች እስከዛሬ ከተናገሯቸው ውሸቶች ሁሉ የሚከፋው “ሰላምና ደህንነት ሆነ!” በማለት በቅርቡ የሚናገሩት አዋጅ ነው። ሆኖም ይህን አዋጅ ሲናገሩ “ያልታሰበ ጥፋት ድንገት ይመጣባቸዋል።” የፖለቲካ መሪዎች ይህ ሥርዓት በአስተማማኝ ሁኔታ ላይ እንዳለ ለማስመሰል በሚያደርጉት ጥረት እንዳንታለል እንጠንቀቅ! እንደ እውነቱ ከሆነ “የይሖዋ ቀን የሚመጣው ሌባ በሌሊት በሚመጣበት መንገድ መሆኑን . . . በሚገባ [እናውቃለን]።”—1 ተሰ. 5:1-4፤ w18.10 7-8 አን. 6-8

ሐሙስ፣ ሐምሌ 30

ደካማ የሆኑትን መርዳት [አለባችሁ]፤ እንዲሁም ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል’ በማለት ጌታ ኢየሱስ ራሱ የተናገረውን ቃል ማስታወስ ይኖርባችኋል።—ሥራ 20:35

ኢየሱስ ክርስቶስ በቅቡዓን ወንድሞቹና የሌሎች በጎች ክፍል በሆኑ አጋሮቻቸው ማለትም “መኳንንት” ተብለው በተጠሩት ሽማግሌዎች አማካኝነት ማበረታቻ ይሰጠናል። እነዚህ ሽማግሌዎች በእምነታችን ላይ ‘የሚያዝዙ’ ሳይሆኑ ‘ለደስታችን ከእኛ ጋር የሚሠሩ’ በመሆናቸው የሚያስፈልገንን ማበረታቻ እንደሚሰጡን መጠበቅ እንችላለን። (ኢሳ. 32:1, 2፤ 2 ቆሮ. 1:24) ሐዋርያው ጳውሎስ ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። በተሰሎንቄ ስደት እየደረሰባቸው ለነበሩት ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ለእናንተ ጥልቅ ፍቅር ስላለን የአምላክን ምሥራች ለማካፈል ብቻ ሳይሆን ራሳችንን ጭምር ለእናንተ ለመስጠት ቆርጠን ነበር፤ ምክንያቱም እናንተ በእኛ ዘንድ እጅግ የተወደዳችሁ ነበራችሁ።” (1 ተሰ. 2:8) ጳውሎስ የሚያበረታቱ ቃላትን መናገር ብቻ በቂ እንዳልሆነ ለማሳየት በኤፌሶን ለነበሩት ሽማግሌዎች በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ ነግሯቸዋል። w18.04 21-22 አን. 6-8

ዓርብ፣ ሐምሌ 31

ይሖዋ መንፈስ ነው፤ የይሖዋ መንፈስ ባለበት ደግሞ ነፃነት አለ።—2 ቆሮ. 3:17

እንዲህ ያለ ነፃነት ለማግኘት ‘ወደ ይሖዋ መመለስ’ ይኸውም በግለሰብ ደረጃ ከእሱ ጋር ዝምድና መመሥረት ያስፈልገናል። (2 ቆሮ. 3:16) በምድረ በዳ የነበሩት እስራኤላውያን ይሖዋ ስላደረገላቸው ነገር ሰብዓዊ አመለካከት አዳብረው ነበር። ልባቸው ደንድኖ እንዲሁም አእምሯቸው ተጋርዶ ነበር፤ በመሆኑም ትኩረታቸው ያረፈው ከግብፅ ባርነት ነፃ መውጣታቸው ያስገኘላቸውን ነፃነት ተጠቅመው ሥጋዊ ፍላጎታቸውን በማርካት ላይ ነበር። (ዕብ. 3:8-10) ይሁን እንጂ የይሖዋ መንፈስ የሚያስገኘው ነፃነት ቃል በቃል ከባርነት ነፃ ከመውጣት የላቀ ነው። ሰዎች ሊያስገኙ ከሚችሉት ነፃነት በተለየ የይሖዋ መንፈስ የሰው ልጆችን ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ ያወጣቸዋል፤ እንዲሁም የሐሰት ሃይማኖትና ልማዶቹ ከሚጭኑባቸው ቀንበር ያላቅቃቸዋል። (ሮም 6:23፤ 8:2) ይህ እንዴት ያለ ክብራማ ነፃነት ነው! አንድ ሰው እስር ቤት ውስጥ ወይም በባርነት ሥር ቢሆንም እንኳ እንዲህ ዓይነቱን ነፃነት ማግኘት ይችላል።—ዘፍ. 39:20-23፤ w18.04 9 አን. 3-5

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ