የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es20 ገጽ 78-88
  • ነሐሴ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ነሐሴ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2020
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 1
  • እሁድ፣ ነሐሴ 2
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 3
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 4
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 5
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 6
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 7
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 8
  • እሁድ፣ ነሐሴ 9
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 10
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 11
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 12
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 13
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 14
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 15
  • እሁድ፣ ነሐሴ 16
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 17
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 18
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 19
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 20
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 21
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 22
  • እሁድ፣ ነሐሴ 23
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 24
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 25
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 26
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 27
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 28
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 29
  • እሁድ፣ ነሐሴ 30
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2020
es20 ገጽ 78-88

ነሐሴ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 1

አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ እንዲሞትልን በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል።—ሮም 5:8

በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይሖዋና ኢየሱስ ስላደረጉልን ነገር አዘውትረን እንማራለን። ይህን መገንዘባችን በአመስጋኝነት ስሜት እንድንሞላ ስለሚያደርገን በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ኢየሱስን ለመምሰል እንጣጣራለን። (2 ቆሮ. 5:14, 15) በተጨማሪም ቤዛውን ያዘጋጀልንን ይሖዋን ለማወደስ እንነሳሳለን። እሱን ማወደስ የምንችልበት አንዱ መንገድ ደግሞ በስብሰባዎች ላይ ከልብ የመነጨ ሐሳብ መስጠት ነው። ለይሖዋና ለልጁ ያለን ፍቅር ምን ያህል ጥልቅ እንደሆነ ማሳየት የምንችለው ለእነሱ ስንል መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ በመሆን ነው። አብዛኛውን ጊዜ በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የተለያዩ መሥዋዕቶችን እንከፍላለን። በርካታ ጉባኤዎች አንደኛውን ስብሰባ የሚያደርጉት በሥራ ቀናት አመሻሹ ላይ ስለሆነ አብዛኞቻችን ድካም እንደሚሰማን አያጠራጥርም። ሌላኛው ስብሰባ የሚደረገው ደግሞ ብዙዎች እረፍት ላይ በሚሆኑበት የሳምንቱ የመጨረሻ ቀን ላይ ነው። ታዲያ ድካም እየተሰማንም በስብሰባዎች ላይ ለመገኘት የምናደርገውን ጥረት ይሖዋ ያስተውላል? እንዴታ! እንዲያውም በዚህ ረገድ ይበልጥ ትግል ባደረግን መጠን ይሖዋም ለእሱ የምናሳየውን ፍቅር ይበልጥ ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል።—ማር. 12:41-44፤ w19.01 29 አን. 12-13

እሁድ፣ ነሐሴ 2

ጌታ ባያት ጊዜ በጣም አዘነላት።—ሉቃስ 7:13

ሰዎች ከሚያጋጥሟቸው ተፈታታኝ ሁኔታዎች መካከል አንዳንዶቹ ኢየሱስንም አጋጥመውታል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ያደገው በድሃ ቤተሰብ ውስጥ እንደሆነ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። አሳዳጊ አባቱ ከሆነው ከዮሴፍ ጋር ይሠራ ስለነበር የጉልበት ሥራ ምን ያህል አድካሚ እንደሆነ ያውቃል። (ማቴ. 13:55፤ ማር. 6:3) ዮሴፍ የሞተው ኢየሱስ አገልግሎቱን ከመጀመሩ ከተወሰነ ጊዜ በፊት ሳይሆን አይቀርም። በመሆኑም ኢየሱስ የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት የሚያስከትለውን ሥቃይ በገዛ ሕይወቱ ተመልክቷል ማለት እንችላለን። በተጨማሪም ኢየሱስ ከእሱ የተለየ ሃይማኖታዊ አመለካከት ባለው ቤተሰብ ውስጥ መኖር ምን ሊመስል እንደሚችል ያውቃል። (ዮሐ. 7:5) ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ያጋጠሙት እነዚህና ሌሎች ሁኔታዎች ሰዎች የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች እንዲያውቅና ስሜታቸውን እንዲረዳ አስችለውታል። ኢየሱስ ለሌሎች ያለው አሳቢነት በተለይ ተአምር በሚፈጽምበት ወቅት በግልጽ ይታይ ነበር። ኢየሱስ ተአምር ይፈጽም የነበረው እንደዚያ የማድረግ ግዴታ እንዳለበት ስለተሰማው አልነበረም። ከዚህ ይልቅ መከራ እየደረሰባቸው ላሉት ሰዎች ‘በጣም ስላዘነላቸው’ ነው። (ማቴ. 20:29-34፤ ማር. 1:40-42) ኢየሱስ ለእነዚህ ሰዎች ያዘነላቸው ከመሆኑም ሌላ ሊረዳቸው ፈልጎ ነበር።—ማር. 7:32-35፤ ሉቃስ 7:12-15፤ w19.03 16 አን. 10-11

ሰኞ፣ ነሐሴ 3

እርስ በርስ መቻቻላችሁን . . . ቀጥሉ።—ቆላ. 3:13

ኢየሱስ ምድር ላይ ባሳለፈው የመጨረሻ ምሽት ምን ያህል ውጥረት ውስጥ ገብቶ እንደሚሆን ለማሰብ ሞክሩ። እስከ ሞት ድረስ ፍጹም ታማኝነቱን የመጠበቁ ጉዳይ አሳስቦት እንደሚሆን የታወቀ ነው። ደግሞም እሱ የሚወስደው እርምጃ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል። (ሮም 5:18, 19) ከሁሉ በላይ ደግሞ የአባቱን መልካም ስም ይነካል። (ኢዮብ 2:4) ሆኖም የቅርብ ወዳጆቹ ከሆኑት ሐዋርያቱ ጋር በተመገበው የመጨረሻ ማዕድ ላይ “ከመካከላችን ታላቅ የሆነው ማን ነው?” በሚል በሐዋርያቱ መካከል “የጦፈ ክርክር” ተነሳ። የሚገርመው ግን ኢየሱስ በሐዋርያቱ ላይ አልተበሳጨም። ከዚህ ይልቅ ገርነት በሚንጸባረቅበት መንገድ አነጋገራቸው። በደግነት ሆኖም ጠንከር ባለ መንገድ በድጋሚ ምክር ሰጣቸው። ምን ዓይነት ዝንባሌ ሊኖራቸው እንደሚገባ ነገራቸው። ከዚያም እስከ መጨረሻው ከጎኑ ስላልተለዩ አመሰገናቸው። (ሉቃስ 22:24-28፤ ዮሐ. 13:1-5, 12-15) ሁላችንም ሌሎችን የሚያበሳጭ ነገር እንደምንናገርና እንደምናደርግ ካስታወስን ውጥረት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜም እንኳ ገርነት በማሳየት ኢየሱስን መምሰል እንችላለን። (ምሳሌ 12:18፤ ያዕ. 3:2, 5) በተጨማሪም ሌሎች ያላቸውን መልካም ነገር ጠቅሰን ለማመስገን ጥረት እናድርግ።—ኤፌ. 4:29፤ w19.02 11-12 አን. 16-17

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 4

ይሖዋ . . . [ዙፋኑን] ለፍትሕ ሲል አጽንቷል።—መዝ. 9:7

የሙሴ ሕግ አንድ ሰው በሐሰት የሚወነጀልበት አጋጣሚ ጠባብ እንዲሆን ያደርግ ነበር። አንድ ሰው ክስ ከተሰነዘረበት ከሳሹን የማወቅ መብት ነበረው። (ዘዳ. 19:16-19፤ 25:1) በተጨማሪም ግለሰቡ ጥፋተኛ ነው የሚል ፍርድ ከመተላለፉ በፊት ቢያንስ ሁለት ምሥክሮች ቀርበው መመሥከር ነበረባቸው። (ዘዳ. 17:6፤ 19:15) አንድ ሰው ብቻ የመሠከረበትን ወንጀለኛ በተመለከተስ ምን ማለት ይቻላል? እንዲህ ያለው ሰውም ቢሆን ከቅጣት እንደሚያመልጥ ሊሰማው አይገባም። ያደረገውን ነገር ይሖዋ አይቶታል። አዎ፣ ይሖዋ ፍትሐዊ በመሆን ረገድ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል፤ እሱ ፍትሕ የጎደለው አንዳች ነገር አያደርግም። የእሱን መሥፈርቶች በታማኝነት ለሚጠብቁ ሰዎች ወሮታቸውን ይከፍላቸዋል፤ ሥልጣናቸውን አላግባብ የሚጠቀሙትን ግን ይቀጣቸዋል። (2 ሳሙ. 22:21-23፤ ሕዝ. 9:9, 10) አንዳንዶች የክፋት ድርጊት ፈጽመው ከቅጣት ያመለጡ ይመስሉ ይሆናል፤ ሆኖም ይሖዋ ተገቢ ነው ባለው ጊዜ እነዚህ ሰዎች የእጃቸውን እንዲያገኙ ያደርጋል። (ምሳሌ 28:13) ንስሐ ለመግባት ፈቃደኞች ካልሆኑ “በሕያው አምላክ እጅ መውደቅ የሚያስፈራ ነገር” እንደሆነ መገንዘባቸው አይቀርም።—ዕብ. 10:30, 31፤ w19.02 23-24 አን. 20-21

ረቡዕ፣ ነሐሴ 5

ይሖዋ ፊት ለፊት እንዳወቀው እንደ ሙሴ ያለ ሌላ ነቢይ እስካሁን በእስራኤል ተነስቶ አያውቅም።—ዘዳ. 34:10

ሙሴ ምክርና መመሪያ ለማግኘት ወደ ይሖዋ የሚመለከት ሰው ነበር። እንዲያውም “የማይታየውን አምላክ እንደሚያየው አድርጎ በጽናት ቀጥሏል” ተብሎለታል። (ዕብ. 11:24-27) እስራኤላውያን ከግብፅ ከወጡ ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ ገና ሲና ተራራ እንኳ ሳይደርሱ አንድ ከባድ ችግር ተከሰተ። ሕዝቡ ውኃ በማጣቱ ማማረርና በሙሴ ላይ ማጉረምረም ጀመረ። ሁኔታው በጣም እየተባባሰ ከመሄዱ የተነሳ ሙሴ “ይህን ሕዝብ ምን ባደርገው ይሻለኛል? ትንሽ ቆይተው እኮ ይወግሩኛል!” በማለት ወደ ይሖዋ ጮኸ። (ዘፀ. 17:4) ይሖዋም ግልጽ መመሪያዎችን ሰጠው። በትሩን ወስዶ በኮሬብ የሚገኘውን ዓለት ሲመታው ውኃ ከውስጡ እየተንዶለዶለ እንደሚወጣ ነገረው። ዘገባው “ሙሴም የእስራኤል ሽማግሌዎች እያዩ እንደተባለው አደረገ” ይላል። እስራኤላውያን እስኪበቃቸው ድረስ የጠጡ ሲሆን ችግሩም በዚህ መንገድ ተፈታ።—ዘፀ. 17:5, 6፤ w18.07 13 አን. 4-5

ሐሙስ፣ ነሐሴ 6

ፍቅር . . . ያንጻል።—1 ቆሮ. 8:1

ይሖዋ ፍቅር በማሳየት እኛን ለማነጽ ከሚጠቀምባቸው መንገዶች አንዱ የክርስቲያን ጉባኤ ነው። የእምነት ባልንጀሮቻችንን በመውደድ እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊና ስሜታዊ ድጋፍ በማድረግ ይሖዋ ላሳየን ፍቅር ምላሽ መስጠት እንችላለን። (1 ዮሐ. 4:19-21) ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያኖችን “አሁን እያደረጋችሁት እንዳለው እርስ በርስ ተበረታቱ እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ” በማለት መክሯቸዋል። (1 ተሰ. 5:11) በእርግጥም ሽማግሌዎች ብቻ ሳይሆኑ ሁሉም የጉባኤው አባላት፣ ወንድሞቻቸውንና እህቶቻቸውን በማጽናናት ብሎም በማነጽ የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። (ሮም 15:1, 2) የመንፈስ ጭንቀት ያለባቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች የሕክምና እርዳታ ማግኘት ሊያስፈልጋቸው ይችላል። (ሉቃስ 5:31) ሽማግሌዎችም ሆኑ ሌሎች የጉባኤው አባላት የሥነ አእምሮ ባለሙያዎች የሚሰጡት ዓይነት የሕክምና እርዳታ መስጠት እንደማይችሉ ያውቃሉ። ያም ቢሆን “የተጨነቁትን አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ” የሚለውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ጠቃሚ እገዛ ማበርከት ይችላሉ።—1 ተሰ. 5:14፤ w18.09 14 አን. 10-11

ዓርብ፣ ነሐሴ 7

እኔ አምላክህ ነኝና አትጨነቅ።—ኢሳ. 41:10

በይሖዋ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር የምንችለው እሱን ይበልጥ በማወቅ ነው። አምላክን በሚገባ ማወቅ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት ማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ከዚህ በፊት ለሕዝቦቹ ጥበቃ ያደረገው እንዴት እንደሆነ የሚገልጹ አስተማማኝ ዘገባዎችን ይዟል። እነዚህ ዘገባዎች ይሖዋ በዛሬው ጊዜም እንደሚንከባከበን ያለንን እምነት ያጠናክሩልናል። ኢሳይያስ፣ ይሖዋ ለእኛ ጥበቃ የሚያደርገው እንዴት እንደሆነ ለማሳየት ግሩም የሆነ አገላለጽ ተጠቅሟል። ይሖዋን እንደ እረኛ፣ አገልጋዮቹን ደግሞ እንደ ግልገሎች አድርጎ ገልጿቸዋል። ኢሳይያስ ይሖዋን አስመልክቶ ሲናገር “ግልገሎቹን በክንዱ ይሰበስባል፤ በእቅፉም ይሸከማቸዋል” ብሏል። (ኢሳ. 40:11) ይሖዋ በኃያል ክንዶቹ እቅፍ እንዳደረገን ስናስብ የደህንነትና የመረጋጋት ስሜት አይሰማንም? የተለያዩ ችግሮች ቢያጋጥሟችሁም ተረጋግታችሁ መኖር እንድትችሉ ይረዳችሁ ዘንድ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ አሰላስሉበት። ይህ ሐሳብ ወደፊት የሚያጋጥሟችሁን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመጋፈጥ ብርታት ይሰጣችኋል። w19.01 7 አን. 17-18

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 8

አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል።—መዝ. 40:8

ልትደርሱባቸው የምትጣጣሯቸው መንፈሳዊ ግቦች አሏችሁ? ለምሳሌ በየዕለቱ ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተወሰነ ክፍል የማንበብ ግብ ይኖራችሁ ይሆናል። አሊያም ደግሞ የንግግርና የማስተማር ችሎታችሁን ለማሻሻል ጥረት እያደረጋችሁ ሊሆን ይችላል። ያወጣችሁት ግብ ምንም ይሁን ምን፣ ጥሩ ውጤት ስታገኙ ወይም ሌሎች የምታደርጉትን ጥረት አይተው ሲያመሰግኗችሁ ምን ይሰማችኋል? ደስታና እርካታ እንደሚሰማችሁ ምንም ጥርጥር የለውም። ደግሞም እንዲህ የሚሰማችሁ መሆኑ ተገቢ ነው። ምክንያቱም ይህ፣ የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ከራሳችሁ ፈቃድ ይልቅ የአምላክን ፈቃድ እያስቀደማችሁ እንዳላችሁ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (ምሳሌ 27:11) መንፈሳዊ ግቦች ላይ ለመድረስ መጣጣራችሁ እውነተኛ እርካታ ያስገኝላችኋል የምንልበት ሌላው ምክንያት ደግሞ የምታከናውኑት ሥራ በምንም ዓይነት ከንቱ አለመሆኑ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ጸንታችሁ ቁሙ፤ አትነቃነቁ፤ እንዲሁም ከጌታ ጋር በተያያዘ በትጋት የምታከናውኑት ሥራ ከንቱ አለመሆኑን አውቃችሁ ምንጊዜም የጌታ ሥራ የበዛላችሁ ሁኑ።” (1 ቆሮ. 15:58) በአንጻሩ ግን ዓለማዊ ግቦችን በመከታተልና ትልቅ ቦታ ላይ ለመድረስ በመጣጣር ላይ ያተኮረ ሕይወት ስኬታማ ሊመስል ቢችልም የኋላ ኋላ ከንቱ መሆኑ አይቀርም።—ሉቃስ 9:25፤ w18.12 22 አን. 12-13

እሁድ፣ ነሐሴ 9

ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ።—መዝ. 37:29

ዳዊት ምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሕይወታቸውን ከአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር አስማምተው ስለሚመሩበት ጊዜ መናገሩ ነበር። (2 ጴጥ. 3:13) በኢሳይያስ 65:22 ላይ ያለው ትንቢት “የሕዝቤ ዕድሜ እንደ ዛፍ ዕድሜ ይሆናል” ይላል። ይህም ሰዎች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት እንደሚኖሩ ያመለክታል። በራእይ 21:1-4 መሠረት አምላክ ትኩረቱን ወደ ሰዎች ያዞራል፤ በተጨማሪም አምላክ ጽድቅ በሰፈነበት አዲስ ዓለም ውስጥ ለሚኖሩ አገልጋዮቹ ከሰጣቸው ተስፋዎች መካከል አንዱ “ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም” የሚለው ነው። አዳምና ሔዋን በኤደን ገነት ውስጥ ለዘላለም የመኖር መብታቸውን ቢያጡም ምድር ዳግመኛ ገነት ትሆናለች። አምላክ ቃል በገባው መሠረት ወደፊት የምድር ሕዝቦች ይባረካሉ። ዳዊት የዋሆችና ጻድቃን ምድርን እንደሚወርሱና በእሷም ለዘላለም እንደሚኖሩ በመንፈስ መሪነት ተናግሯል። (መዝ. 37:11) በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ያሉት ትንቢቶች በገነት ውስጥ የሚኖረውን አስደሳች ሁኔታ በጉጉት እንድንጠባበቅ ያደርጉናል። (ኢሳ. 11:6-9፤ 35:5-10፤ 65:21-23) ሆኖም ይህ የሚሆነው መቼ ነው? ኢየሱስ ለአይሁዳዊው ወንጀለኛ የሰጠው ተስፋ በሚፈጸምበት ጊዜ ነው። (ሉቃስ 23:43) አንተም በዚያ ጊዜ መኖር ትችላለህ። w18.12 7 አን. 22-23

ሰኞ፣ ነሐሴ 10

ከምንም ነገር በላይ ልብህን ጠብቅ።—ምሳሌ 4:23

ከዓለም አስተሳሰብ ጋር ምንም ዓይነት ንክኪ እንዳይኖረን ማድረግ ይቻላል? አይቻልም፤ ቃል በቃል ከዓለም መውጣት የማይቻል ነገር ነው። በተወሰነ መጠንም ቢሆን ለዓለም አስተሳሰብ መጋለጣችን አይቀርም። (1 ቆሮ. 5:9, 10) ሌላው ቀርቶ በስብከቱ ሥራችን ስንካፈል እንኳ አንዳንድ የተሳሳቱ አስተሳሰቦችን እንሰማለን። ሆኖም ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ከሚጋጩ ሐሳቦች መራቅ በማንችልባቸው ሁኔታዎች ሥር ስንሆን እነዚህን ሐሳቦች ላለማውጠንጠን ወይም ላለመቀበል እንጠነቀቃለን። የሰይጣንን ዓላማ የሚያራምዱ አስተሳሰቦችን ውድቅ ለማድረግ ልክ እንደ ኢየሱስ ፈጣኖች እንሆናለን። በተጨማሪም ሳያስፈልግ ለዓለም አስተሳሰብ እንዳንጋለጥ በመጠንቀቅ ራሳችንን መጠበቅ እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ የቅርብ ወዳጆቻችንን ስንመርጥ ጠንቃቆች መሆን አለብን። ይሖዋን ከማያመልኩ ሰዎች ጋር የምንቀራረብ ከሆነ አስተሳሰባቸው እንደሚጋባብን መጽሐፍ ቅዱስ ያስጠነቅቃል። (ምሳሌ 13:20፤ 1 ቆሮ. 15:12, 32, 33) የዝግመተ ለውጥን ጽንሰ ሐሳብ ከሚያራምዱ አሊያም ዓመፅ ወይም የፆታ ብልግና ከሚታይባቸው መዝናኛዎች በመራቅም አስተሳሰባችን “ስለ አምላክ የሚገልጸውን እውቀት [በሚጻረሩ]” ሐሳቦች እንዳይመረዝ መከላከል እንችላለን።—2 ቆሮ. 10:5፤ w18.11 21 አን. 16-17

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 11

በእውነትህ እሄዳለሁ።—መዝ. 86:11

በእውነት ጎዳና ለመጓዝ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለሌሎች በማስተማሩ ሥራ የተቻለንን ያህል ተሳትፎ በማድረግ ነው። እንዲህ ማድረጋችን መንፈሳዊውን ሰይፍ ማለትም “የአምላክን ቃል” አጥብቀን ለመያዝ ይረዳናል። (ኤፌ. 6:17) ሁላችንም “የእውነትን ቃል በአግባቡ በመጠቀም” የማስተማር ችሎታችንን ለማሻሻል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። (2 ጢሞ. 2:15) መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመን ሌሎች እውነትን እንዲገዙና የሐሰት ትምህርቶችን እንዲተዉ ስንረዳ እውነት በራሳችን ልብና አእምሮ ውስጥ ይቀረጻል። ይህም በእውነት ጎዳና ለመጓዝ ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ለማጠናከር ይረዳናል። እውነት ከይሖዋ ያገኘነው ውድ ስጦታ ነው። ይህ ስጦታ በሕይወታችን ውስጥ ከሁሉ የላቀ ቦታ የምንሰጠውን ነገር ለማግኘት ማለትም በሰማይ ካለው አባታችን ጋር የቀረበ ዝምድና ለመመሥረት አስችሎናል። ይሖዋ እስካሁን ብዙ ነገር ያስተማረን ቢሆንም ወደፊት ከሚያስተምረን ጋር ሲወዳደር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም! ገና ለዘላለም ተጨማሪ እውነቶችን እንደሚያስተምረን ቃል ገብቶልናል። እንግዲያው እውነትን እንደ ውድ ዕንቁ እንመልከተው። ‘እውነትን መግዛታችንን’ ለመቀጠልና ‘ፈጽሞ ላለመሸጥ’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ምሳሌ 23:23፤ w18.11 8 አን. 2፤ 12 አን. 15-17

ረቡዕ፣ ነሐሴ 12

[ኖኅ] የጽድቅ ሰባኪ [ነበር]።—2 ጴጥ. 2:5

ኖኅ የጥፋት ውኃው ከመምጣቱ በፊት ያከናወነው የስብከት ሥራ ሰዎችን ስለሚመጣው ጥፋት ማስጠንቀቅን የሚያካትት መሆን አለበት። ኢየሱስ ምን እንዳለ ልብ እንበል፦ “ከጥፋት ውኃ በፊት በነበረው ዘመን ኖኅ ወደ መርከቡ እስከገባበት ቀን ድረስ ሰዎች ይበሉና ይጠጡ እንዲሁም ወንዶች ያገቡ፣ ሴቶችም ይዳሩ ነበር፤ የጥፋት ውኃ መጥቶ ሁሉንም ጠራርጎ እስከወሰዳቸው ጊዜ ድረስ ምንም አላስተዋሉም፤ የሰው ልጅ መገኘትም እንደዚሁ ይሆናል።” (ማቴ. 24:38, 39) ሰዎቹ ለሚሰብከው መልእክት ግድየለሽ ቢሆኑም ኖኅ የተሰጠውን የማስጠንቀቂያ መልእክት በታማኝነት አውጇል። ዛሬም ለሰዎች የመንግሥቱን ምሥራች የምንሰብከው፣ አምላክ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ የማወቅ አጋጣሚ እንዲያገኙ ስለምንፈልግ ነው። እኛም እንደ ይሖዋ፣ ሰዎች መልእክቱን ተቀብለው ‘በሕይወት እንዲኖሩ’ ከልብ እንፈልጋለን። (ሕዝ. 18:23) በሌላ በኩል ደግሞ ከቤት ወደ ቤትም ይሁን በአደባባይ በመስበክ፣ የአምላክ መንግሥት እንደሚመጣና ይህን ክፉ ዓለም እንደሚያጠፋ ለሰዎች ሁሉ ማስጠንቀቂያ እንሰጣለን።—ሕዝ. 3:18, 19፤ ዳን. 2:44፤ ራእይ 14:6, 7፤ w18.05 19 አን. 8-9

ሐሙስ፣ ነሐሴ 13

ታማኝ ምሥክር እውነቱን ይናገራል።—ምሳሌ 12:17

የምትኖረው ባለሥልጣናት በስብከቱ ሥራ ላይ እገዳ በጣሉበት አገር ውስጥ ቢሆንና ስለ ወንድሞችህ መረጃ እንድትሰጥ ብትጠየቅ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? የምታውቀውን ሁሉ መናገር አለብህ? ኢየሱስ የሮም አገረ ገዢ ጥያቄዎችን ባቀረበለት ወቅት ያደረገው ምንድን ነው? “ዝም ለማለት ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው” ከሚለው መሠረታዊ ሥርዓት ጋር በሚስማማ መልኩ ለአንዳንዶቹ ጥያቄዎች ምንም መልስ ከመስጠት ተቆጥቧል! (መክ. 3:1, 7፤ ማቴ. 27:11-14) እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ወንድሞቻችንን አደጋ ላይ ላለመጣል አስተዋዮች መሆናችን አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 10:19፤ 11:12) የቅርብ ጓደኛህ ወይም ዘመድህ ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ብታውቅ ምን ታደርጋለህ? ‘እውነቱን ተናገር።’ ለሽማግሌዎች ከፊሉን ሳይሆን ሙሉውን እውነት የመናገር እንዲሁም ምንም ያልተዛባ መረጃ የመስጠት ኃላፊነት አለብህ። ደግሞም ሽማግሌዎች ስለ ጉዳዩ የተሟላ መረጃ የማግኘት መብት አላቸው፤ ምክንያቱም ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና እንዲያድስ ሊረዱት የሚችሉት ሙሉ መረጃ ሲኖራቸው ብቻ ነው።—ያዕ. 5:14, 15፤ w18.10 10 አን. 17-18

ዓርብ፣ ነሐሴ 14

እርስ በርስ ተበረታቱ እንዲሁም እርስ በርስ ተናነጹ።—1 ተሰ. 5:11

ለሰዎች ፍቅር በማሳየት እነሱን ማነጽ የምንችለው እንዴት ነው? አንዱ መንገድ ጥሩ አዳማጭ መሆን ነው። (ያዕ. 1:19) የሌሎችን ስሜት እንደምትረዱ በሚያሳይ መንገድ ማዳመጣችሁ ለእነሱ ፍቅር እንዳላችሁ ያረጋግጣል። በመንፈስ ጭንቀት የሚሠቃየውን ክርስቲያን ስሜት ለመረዳት የሚያስችሉ ጥያቄዎችን በደግነት መጠየቅ ትችላላችሁ። ይህም ያለበትን ሁኔታ ለመገንዘብና እሱን ለማነጽ ያስችላችኋል። ለግለሰቡ ያላችሁ ልባዊ አሳቢነትና ፍቅር በፊታችሁ ላይ ሊነበብ ይገባል። ግለሰቡ ረዘም ላለ ጊዜ ሊያዋራችሁ ከፈለገ ጣልቃ ሳትገቡ በትዕግሥት አዳምጡት። በትዕግሥት ማዳመጣችሁ የግለሰቡን ስሜት በሚገባ ለመረዳት ያስችላችኋል። በተጨማሪም በጭንቀት የተዋጠው ክርስቲያን እምነት እንዲጥልባችሁና እሱን ለማነጽ የምትናገሩትን ነገር ለማዳመጥ ይበልጥ እንዲነሳሳ ሊያደርገው ይችላል። የምታሳዩት ልባዊ አሳቢነት ሌሎችን በእጅጉ ያጽናናቸዋል። w18.09 14 አን. 10፤ 15 አን. 13

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 15

እውነትን . . . ግዛ።—ምሳሌ 23:23

እውነትን መግዛት የሚፈልግ ሁሉ ጊዜውን መሥዋዕት ማድረግ አለበት። የመንግሥቱን መልእክት ለመስማት፣ መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ለማንበብ፣ የግል የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ለማድረግ እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ጥሩ ዝግጅት አድርጎ ለመገኘት ጊዜ ያስፈልጋል። ለእነዚህ ነገሮች የሚሆን ጊዜ ለማግኘት እምብዛም አስፈላጊ ካልሆኑ እንቅስቃሴዎች ላይ ‘ጊዜ መግዛት’ ወይም መውሰድ ይኖርብናል። (ኤፌ. 5:15, 16 ግርጌ) መሠረታዊ ስለሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ትክክለኛውን እውቀት ለመቅሰም ምን ያህል ጊዜ ያስፈልገናል? ይህ እንደ ግለሰቡ ሁኔታ ይለያያል። ይሖዋ ስላለው ጥበብ፣ ስለ መንገዶቹና ስለ ሥራዎቹ መቼም ቢሆን ተምረን መጨረስ አንችልም። (ሮም 11:33) የመጀመሪያው የመጠበቂያ ግንብ እትም እውነትን ከአንድ “ትንሽ አበባ” ጋር ያመሳሰለው ሲሆን የሚከተለውን ሐሳብ ይዟል፦ “አንድ የእውነት አበባ ስላገኘህ ብቻ አትርካ። አንድ ብቻ በቂ ቢሆን ኖሮ ተጨማሪ አበቦች ባልኖሩ ነበር። መሰብሰብህን አታቋርጥ፤ ፍለጋህን ቀጥል።” ለዘላለም ብንኖር እንኳ ሁልጊዜ ስለ ይሖዋ የምንማረው አዲስ ነገር ይኖራል። በዛሬው ጊዜ ግን ጊዜያችንን በጥበብ በመጠቀም ሁኔታችን የሚፈቅደውን ያህል ብዙ እውነት መግዛታችን አስፈላጊ ነው። w18.11 4 አን. 7

እሁድ፣ ነሐሴ 16

ባሎች ሆይ፣ . . . ሚስቶቻችሁን መውደዳችሁን ቀጥሉ።—ኤፌ. 5:25

ባሎች ከሚስቶቻቸው ጋር “በእውቀት” እንዲኖሩ ተመክረዋል፤ ይህ አገላለጽ “ለእነሱ አሳቢነት በማሳየት፤ ሁኔታቸውን በመረዳት” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። (1 ጴጥ. 3:7 ግርጌ) የሌሎችን ሁኔታ መረዳት፣ አሳቢነት ለማሳየት ቁልፍ ነው። ለምሳሌ የሚስቱን ሁኔታ የሚረዳ ባል፣ ማሟያ የሆነችው ሚስቱ በብዙ መንገዶች ከእሱ የተለየች ብትሆንም ከእሱ እንደማታንስ ይገነዘባል። (ዘፍ. 2:18) በመሆኑም ስሜቷን ከግምት ያስገባል እንዲሁም በአክብሮት ይይዛታል። አሳቢ የሆነ ባል ከሌሎች ሴቶች ጋር ባለው ግንኙነትም የሚስቱን ስሜት ከግምት ያስገባል። ሌሎች ሴቶችን አያሽኮረምምም ወይም ለእነሱ ተገቢ ያልሆነ ትኩረት አይሰጥም። ማኅበራዊ ድረ ገጾችን ሲጠቀምም ሆነ ሌሎች ድረ ገጾችን ሲቃኝም ቢሆን እንዲህ ከማድረግ ይቆጠባል። (ኢዮብ 31:1) በእርግጥም ለሚስቱ ታማኝ ለመሆን ጥረት ያደርጋል፤ ይህን የሚያደርገውም ሚስቱን ስለሚወዳት ብቻ ሳይሆን አምላክን ስለሚወድና ክፉ የሆነውን ነገር ስለሚጠላ ጭምር ነው።—መዝ. 19:14፤ 97:10፤ w18.09 29 አን. 3-4

ሰኞ፣ ነሐሴ 17

ታላቅ የሚባለው ራሱን ከሁላችሁ እንደሚያንስ አድርጎ የሚቆጥር ነው።—ሉቃስ 9:48

ከአምላክ ቃል የምንማረውን ነገር በተግባር ማዋል ተፈታታኝ የሆነው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት፣ ትክክል የሆነውን ማድረግ ትሕትና የሚጠይቅ መሆኑ ነው። ትሑት መሆን ደግሞ ቀላል አይደለም፤ ምክንያቱም የምንኖረው “ራሳቸውን የሚወዱ፣ ገንዘብ የሚወዱ፣ ጉረኞች፣ ትዕቢተኞች” እንዲሁም “ራሳቸውን የማይገዙ” ሰዎች በሞሉባቸው “በመጨረሻዎቹ ቀናት” ነው። (2 ጢሞ. 3:1-3) የአምላክ አገልጋዮች እንደመሆናችን መጠን ከላይ የተጠቀሱት ባሕርያት መጥፎ መሆናቸውን እናውቃለን፤ ሆኖም እነዚህን ባሕርያት የሚያንጸባርቁ ሰዎች በሕይወታቸው ሲሳካላቸው ስናይ ቅናት ሊያድርብን ይችላል። (መዝ. 37:1፤ 73:3) እንዲያውም ‘ከራሴ ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት ማስቀደሜ ምን ፋይዳ አለው? “ራሴን ከሁሉ እንደማንስ” አድርጌ መቁጠሬ ሌሎች ለእኔ አክብሮት እንዲያጡ ያደርጋቸው ይሆን?’ እንደሚሉት ያሉ ጥያቄዎች ይፈጠሩብን ይሆናል። በዓለም ላይ ያለው የራስ ወዳድነት ዝንባሌ እንዲጋባብን ከፈቀድን ከወንድሞቻችን ጋር ያለን መልካም ግንኙነት ሊበላሽ አልፎ ተርፎም ክርስቲያናዊ ማንነታችንን ልናጣ እንችላለን። በሌላ በኩል ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን ትሑት ሰዎች ምሳሌ መመርመራችንና አርዓያቸውን መከተላችን ይጠቅመናል። w18.09 3 አን. 1

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 18

መስጠት . . . ደስታ ያስገኛል።—ሥራ 20:35

ይሖዋ መፍጠር ከመጀመሩ በፊት የሚኖረው ብቻውን ነበር። ሆኖም ለሌሎች የሕይወትን ስጦታ መስጠት ስለፈለገ መንፈሳዊና ሰብዓዊ ፍጡራንን ወደ ሕልውና አመጣ። ‘ደስተኛ አምላክ’ የሆነው ይሖዋ ለሌሎች መልካም ነገሮችን መስጠት ይወዳል። (1 ጢሞ. 1:11፤ ያዕ. 1:17) እኛም ደስተኞች እንድንሆን ስለሚፈልግ ለጋሶች እንድንሆን ያስተምረናል። (ሮም 1:20) አምላክ ሰውን የፈጠረው በራሱ መልክ ነው። (ዘፍ. 1:27) ይህም ሲባል የተፈጠርነው የእሱን ባሕርይ ማንጸባረቅ እንድንችል ተደርገን ነው ማለት ነው። በመሆኑም ሕይወታችን ደስታና እርካታ ያለው እንዲሆን ከፈለግን የይሖዋን ምሳሌ በመከተል ለሌሎች ሰዎች ፍላጎት ትኩረት መስጠትና ለጋስ መሆን ያስፈልገናል። (ፊልጵ. 2:3, 4፤ ያዕ. 1:5) እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በአጭሩ፣ ይሖዋ የፈጠረን በዚህ መልኩ ስለሆነ ነው። ፍጹማን ባንሆንም ለጋስ በመሆን ረገድ ይሖዋን መምሰል እንችላለን። ይሖዋ የሰው ልጆች እሱን እንዲመስሉት ይፈልጋል፣ በመሆኑም ለጋስ ስንሆን ይደሰታል።—ኤፌ. 5:1፤ w18.08 18 አን. 1-2፤ 19 አን. 4

ረቡዕ፣ ነሐሴ 19

በጎቼ ድምፄን ይሰማሉ።—ዮሐ. 10:27

የክርስቶስ ተከታዮች ቃሉን በማዳመጥ ብቻ ሳይሆን ተግባራዊ በማድረግ ጭምር ኢየሱስን እንደሚሰሙ ያሳያሉ። ‘የኑሮ ጭንቀት’ ትኩረታቸውን እንዲከፋፍለው አይፈቅዱም። (ሉቃስ 21:34) ከዚህ ይልቅ በተፈታታኝ ሁኔታዎች ሥር እንኳ በሕይወታቸው ውስጥ ቅድሚያ የሚሰጡት የኢየሱስን ትእዛዛት ለመፈጸም ነው። ወንድሞቻችን ምንም ያህል ዋጋ ቢያስከፍላቸው ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት ለመጠበቅ ቆርጠዋል። ኢየሱስን እንደምንሰማ የምናሳይበት ሌላ መንገድ ደግሞ በመካከላችን ሆነው አመራር እንዲሰጡ ከሾማቸው ጋር በመተባበር ነው። (ዕብ. 13:7, 17) የአምላክ ድርጅት ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ በርካታ ማስተካከያዎችን አድርጓል፤ ከእነዚህ መካከል ለአገልግሎት በምንጠቀምባቸው መሣሪያዎችና ዘዴዎች ላይ፣ በሳምንቱ መካከል በምናደርገው ስብሰባ ይዘት ላይ እንዲሁም የስብሰባ አዳራሾችን በምንገነባበት፣ በምናድስበትና በምንጠግንበት መንገድ ላይ የተደረጉት ለውጦች ይገኙበታል። በዚህ ረገድ ለተሰጠን ፍቅር የሚንጸባረቅበትና በሚገባ የታሰበበት መመሪያ ምንኛ አመስጋኞች ነን! ድርጅቱ የሚሰጠንን ወቅታዊ አመራር ለመከተል የምናደርገውን ጥረት ይሖዋ እንደሚባርክልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። w19.03 10-11 አን. 11-12

ሐሙስ፣ ነሐሴ 20

ከእንግዲህ . . . በሰዎች የማታለያ ዘዴ . . . ወዲያና ወዲህ የምንል መሆን የለብንም።—ኤፌ. 4:14

በተወሰነ ደረጃ ብቻ እውነት የሆነ መረጃ በጣም አሳሳች ነው። ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተ ምዕራብ የሚኖሩት እስራኤላውያን በኢያሱ ዘመን ያጋጠማቸውን ሁኔታ እንመልከት። (ኢያሱ 22:9-34) እነዚህ እስራኤላውያን፣ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ የሚኖሩት ወንድሞቻቸው ግዙፍ የሆነ አስደናቂ መሠዊያ መሥራታቸውን ሰሙ። በስተ ምሥራቅ የሚኖሩት እስራኤላውያን መሠዊያ መሥራታቸው እውነት ቢሆንም መረጃው የተሟላ አልነበረም። በስተ ምዕራብ ያሉት እስራኤላውያን ይህን ወሬ ሲሰሙ ወንድሞቻቸው በይሖዋ ላይ እንዳመፁ ተሰማቸው። (ኢያሱ 22:9-12) ደግነቱ፣ ጥቃት ከመሰንዘራቸው በፊት ጉዳዩን እንዲያጣሩ እምነት የሚጣልባቸው ሰዎችን ላኩ። ታዲያ እውነታው ምን ሆኖ ተገኘ? በስተ ምሥራቅ የነበሩት እስራኤላውያን መሠዊያውን የሠሩት መሥዋዕት ለማቅረብ ሳይሆን መታሰቢያ ሆኖ እንዲያገለግል ብለው ነበር። የወደፊቱ ትውልድ፣ እነሱም ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች መሆናቸውን እንዳይጠራጠር የሚያደርግ ምሥክር ለማቆም ፈልገው ነበር። ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያሉት እስራኤላውያን፣ በደረሳቸው ያልተሟላ መረጃ ላይ ተመሥርተው ወንድሞቻቸውን ከማጥቃት ይልቅ ጊዜ ወስደው ጉዳዩን ለማጣራት በመሞከራቸው ተደስተው መሆን አለበት! w18.08 5 አን. 9-10

ዓርብ፣ ነሐሴ 21

የቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።—1 ቆሮ. 10:12

ጳውሎስ እንደጠቆመው እውነተኛ አምላኪዎችም የተሳሳተ ጎዳና መከተል ሊጀምሩ ይችላሉ። በፈተናዎች ተሸንፈው መጥፎ ድርጊት የሚፈጽሙ አንዳንድ ክርስቲያኖች አሁንም በይሖዋ ፊት ጥሩ አቋም እንዳላቸው አድርገው ያስቡ ይሆናል። ሆኖም አንድ ሰው የይሖዋ ወዳጅ መሆን ስለፈለገ ወይም ለእሱ ታማኝ እንደሆነ ስለተናገረ ብቻ ይሖዋ ሞገሱን ያሳየዋል ማለት ላይሆን ይችላል። (1 ቆሮ. 10:1-5) እስራኤላውያን ሙሴ ከሲና ተራራ ሳይወርድ እንደቆየ ባዩ ጊዜ እንደተጨነቁ ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችም የይሖዋ የፍርድ ቀን እንዲሁም አዲሱ ዓለም የሚመጣበት ጊዜ እንደዘገየ አድርገው በማሰብ ሊጨነቁ ይችላሉ። እነዚህ ተስፋዎች የሚፈጸሙበት ጊዜ በጣም ሩቅ እንደሆነ ወይም ተስፋዎቹ የሕልም እንጀራ እንደሆኑ አድርገን ማሰብ እንጀምር ይሆናል። እንዲህ ያለውን አስተሳሰብ ካላስተካከልን ሥጋዊ ምኞቶቻችንን ከይሖዋ ፈቃድ ማስቀደም ልንጀምር እንችላለን። ይህ ደግሞ ቀስ በቀስ ከይሖዋ እንድንርቅና ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ላይ በነበርንበት ጊዜ እናደርገዋለን ብለን ፈጽሞ አስበን የማናውቀውን ነገር ወደማድረግ ሊመራን ይችላል። w18.07 21 አን. 17-18

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 22

በፊቴ ሞገስ ስላገኘህና በስም ስላወቅኩህ የጠየቅከውን ይህን ነገር እፈጽማለሁ።—ዘፀ. 33:17

ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ሊያውቀን የሚችል ሲሆን ይህ ደግሞ ብዙ በረከቶች ያስገኝልናል። ሆኖም በይሖዋ ዘንድ እውቅና ለማግኘት ከእኛ ምን ይጠበቃል? እሱን መውደድና ሕይወታችንን ለእሱ መወሰን ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 8:3) ይሁንና በሰማይ ካለው አባታችን ጋር የመሠረትነውን ውድ ዝምድና ጠብቀን መኖር ያስፈልገናል። ጳውሎስ እንደጻፈላቸው የገላትያ ክርስቲያኖች ሁሉ እኛም ዓለም ለሚያቀርባቸው “ደካማና ከንቱ [የሆኑ] ተራ ነገሮች” ባሪያ እንዳንሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል፤ ይህም በዓለም ዘንድ አድናቆት ለማትረፍ ከመጣጣር መቆጠብን ይጨምራል። (ገላ. 4:9) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት የገላትያ ክርስቲያኖች በአምላክ ለመታወቅ በቅተው ነበር። ሆኖም ጳውሎስ እንደተናገረው እነዚሁ ወንድሞች ከንቱ ወደሆኑ ነገሮች “መመለስ” ጀምረው ነበር። በሌላ አነጋገር ጳውሎስ “እድገት አድርጋችሁ እዚህ ደረጃ ላይ ከደረሳችሁ በኋላ፣ ትታችኋቸው ወደመጣችኋቸው ዋጋ የሌላቸውና የማይረቡ ነገሮች እንዴት ትመለሳላችሁ?” እያላቸው ነበር። w18.07 8 አን. 5-6

እሁድ፣ ነሐሴ 23

ጥበበኛ ሰው ያዳምጣል፤ ደግሞም ተጨማሪ ትምህርት ይቀስማል።—ምሳሌ 1:5

ትክክል ወይም ስህተት የሆነውን አካሄድ ለማወቅ፣ የአምላክን ሕጎች መጣስ የሚያስከትለውን መዘዝ በራሳችን ሕይወት ማየት አያስፈልገንም። በአምላክ ቃል ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች ከሠሩት ስህተት መማር እንችላለን። ከሁሉ የተሻለ ትምህርት መቅሰም የምንችለው ከአምላክ ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱትን እውነተኛ ታሪኮች ስናነብና ስናሰላስልባቸው ትልቅ ትምህርት እናገኛለን። የንጉሥ ዳዊትን ታሪክ እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ዳዊት የይሖዋን ትእዛዝ በመጣስ ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር መፈጸሙ ከፍተኛ ሥቃይ አስከትሎበታል። (2 ሳሙ. 12:7-14) ይህን ዘገባ ስናነብ በሚከተሉት ጥያቄዎች ላይ ማሰላሰል እንችላለን፦ ‘ዳዊት እንዲህ ዓይነት መዘዝ ውስጥ ላለመግባት ምን ማድረግ ይችል ነበር? እኔስ እንደ ዳዊት ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመኝ ምን አደርጋለሁ? እንደ ዳዊት ኃጢአት እፈጽማለሁ ወይስ እንደ ዮሴፍ እሸሻለሁ?’ (ዘፍ. 39:11-15) ኃጢአት በሚያስከትላቸው መጥፎ ውጤቶች ላይ ማሰላሰላችን ‘ክፉ የሆነውን ለመጥላት’ ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክርልናል።—አሞጽ 5:15፤ w18.06 17 አን. 5, 7

ሰኞ፣ ነሐሴ 24

የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ።—ማቴ. 22:21

ሰዎች በፖለቲካዊ ጉዳዮች ውስጥ ለመግባት እንዲነሳሱ የሚያደርጋቸው አንዱ ነገር በአካባቢያቸው የሚፈጸመው የፍትሕ መጓደል እየተባባሰ መሄዱ ነው። በኢየሱስ ዘመን ግብር የመክፈል ጉዳይ በጣም አወዛጋቢ ነበር። እንዲያውም ቀደም ሲል የተጠቀሰው የገሊላው ይሁዳ ለማመፅ እንዲነሳሳ ያደረገው፣ የሮም መንግሥት ሁሉም ሰው ግብር እንዲከፍል ለማድረግ ሲል ሕዝቡ እንዲመዘገብ ትእዛዝ ማስተላለፉ ነው። የኢየሱስን አድማጮች ጨምሮ የሮም ተገዢዎች ለመሬት፣ ለቤትና ለሌሎች ብዙ ነገሮች ግብር እንዲከፍሉ ይጠበቅባቸው ነበር። በዚያ ላይ ደግሞ ቀረጥ ሰብሳቢዎቹ በሙስና የተጠላለፉ መሆናቸው ሕዝቡ ከባድ ሸክም እንደተጫነበት እንዲሰማው አድርጎታል። እነዚህ ቀረጥ ሰብሳቢዎች ለመንግሥት ባለሥልጣናት ገንዘብ በመክፈል ሥልጣን የሚያገኙ ሲሆን በሥልጣናቸው ተጠቅመው ሕዝቡን ይመዘብሩ ነበር። ለምሳሌ በኢያሪኮ የሚኖረው ዘኬዎስ የተባለ የቀረጥ ሰብሳቢዎች አለቃ ሕዝቡን በመበዝበዝ ሀብት አካብቶ ነበር። (ሉቃስ 19:2, 8) ሌሎች ቀረጥ ሰብሳቢዎችም ተመሳሳይ ነገር ያደርጉ የነበረ ይመስላል። የኢየሱስ ጠላቶች፣ ከግብር ጋር በተያያዘ አንዱን ጎራ ደግፎ እንዲናገር የሚያደርግ ጥያቄ በማቅረብ ኢየሱስን ሊያጠምዱት ሞክረው ነበር። ጥያቄው የተነሳው በሮም ተገዢዎች ላይ የሚጣለውን የአንድ ዲናር ግብር በተመለከተ ነው። (ማቴ. 22:16-18) ይህ ግብር በሮም አገዛዝ ሥር መሆናቸውን ስለሚያስታውሳቸው አይሁዳውያን በጣም ይጠሉት ነበር። w18.06 5-6 አን. 8-10

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 25

አንድ ሰው ምንም ዘራ ምን ያንኑ መልሶ ያጭዳል።—ገላ. 6:7

ከሰይጣን ጎን መሰለፍ ምንጊዜም ቢሆን ጉዳቱ ያመዝናል፤ ምንም ዓይነት እውነተኛ ጥቅም አያስገኝም። (ኢዮብ 21:7-17፤ ገላ. 6:8) ሰይጣን ምን ያህል ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ማወቃችን ምን ጥቅም አለው? ሰብዓዊ ባለሥልጣናትን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን የሚረዳን ከመሆኑም ሌላ ምሥራቹን እንድንሰብክ ያነሳሳናል። ይሖዋ የመንግሥት ባለሥልጣናትን እንድናከብር እንደሚፈልግ እናውቃለን። (1 ጴጥ. 2:17) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ሰብዓዊ መንግሥታት የሚያወጧቸው ሕጎች ከእሱ መሥፈርቶች ጋር እስካልተጋጩ ድረስ እነዚህን ሕጎች እንድንታዘዝ ይጠብቅብናል። (ሮም 13:1-4) ያም ቢሆን ምንጊዜም የገለልተኝነት አቋማችንን መጠበቅ እንደሚገባን ይኸውም የትኛውንም የፖለቲካ ፓርቲ ወይም ሰብዓዊ መሪ ከሌላው ማስበለጥ እንደሌለብን እንገነዘባለን። (ዮሐ. 17:15, 16፤ 18:36) በሌላ በኩል ደግሞ ሰይጣን የይሖዋ ስም እንዳይታወቅ ለማድረግና ስሙን ለማጉደፍ እንደሚጥር ስለምናውቅ ለሰዎች ስለ አምላካችን እውነቱን ለማስተማር ይበልጥ እንነሳሳለን። በይሖዋ ስም በመጠራታችንና በስሙ በመጠቀማችን እንኮራለን። ምክንያቱም ይሖዋን መውደድ፣ ገንዘብን ወይም ንብረትን ከመውደድ እጅግ የላቀ በረከት ያስገኛል።—ኢሳ. 43:10፤ 1 ጢሞ. 6:6-10፤ w18.05 24 አን. 8-9

ረቡዕ፣ ነሐሴ 26

ሚስት ከባሏ አትለያይ።—1 ቆሮ. 7:10

በትዳር ውስጥ ችግር በሚያጋጥምበት ጊዜ መለያየት ተገቢ ነው? ቅዱሳን መጻሕፍት ለመለያየት መሠረት ሊሆኑ የሚችሉት የትኞቹ ምክንያቶች እንደሆኑ አይዘረዝሩም። ጳውሎስ “አንዲት ሴት አማኝ ያልሆነ ባል ካላትና ባሏ አብሯት ለመኖር ከተስማማ አትተወው” ሲል ጽፏል። (1 ቆሮ. 7:12, 13) ይህ ምክር ለዘመናችንም ይሠራል። አንዳንድ ጊዜ ግን አንድ “አማኝ ያልሆነ ባል” ከሚስቱ ጋር ‘አብሮ ለመኖር እንደማይስማማ’ የሚያሳይ ነገር ሊያደርግ ይችላል። ለምሳሌ በሚስቱ ላይ ከባድ አካላዊ ጥቃት ከማድረሱ የተነሳ ሚስቱ ጤንነቷ ወይም ሕይወቷ አደጋ ላይ እንደወደቀ ሊሰማት ይችላል። አሊያም ደግሞ ባልየው ለእሷም ሆነ ለቤተሰቡ ቁሳዊ ድጋፍ ለማድረግ ፈቃደኛ ላይሆን ወይም መንፈሳዊነቷን ከፍተኛ አደጋ ላይ የሚጥል ነገር ሊያደርግ ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ያጋጠማቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች የትዳር ጓደኛቸው አብሮ መኖር እንደሚፈልግ ቢናገርም ድርጊቱ ‘አብሮ ለመኖር እንዳልተስማማ’ ስለሚያሳይ ለመለያየት የራሳቸውን ውሳኔ አድርገዋል። ሌሎች ክርስቲያኖች ግን በአንጻራዊ ሁኔታ ከባድ ችግር ቢያጋጥማቸውም ከመለያየት ይልቅ ችግሩን ተቋቁመው መኖርና ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ያላቸውን ግንኙነት ለማሻሻል ጥረት ማድረግ የተሻለ እንደሆነ ወስነዋል። w18.12 13 አን. 14, 16፤ 14 አን. 17

ሐሙስ፣ ነሐሴ 27

[እነዚህ] በጽናት ፍሬ የሚያፈሩ ናቸው።—ሉቃስ 8:15

በሉቃስ 8:5-8, 11-15 ላይ በሚገኘው ስለ ዘሪው በሚናገረው ምሳሌ ላይ ዘሩ የሚያመለክተው ‘የአምላክን ቃል’ ወይም የመንግሥቱን መልእክት ነው። አፈሩ ደግሞ የሰዎችን ምሳሌያዊ ልብ ያመለክታል። ጥሩ አፈር ላይ የወደቀው ዘር ሥር ሰድዶ በቀለ፤ ‘100 እጥፍም አፈራ።’ በኢየሱስ ምሳሌ ላይ የተጠቀሰው ጥሩ አፈር፣ ዘሩ ተመችቶት እንዲያድግ እንዳስቻለ ሁሉ እኛም መልእክቱን ተቀብለን በልባችን ውስጥ አኖርነው። እንዲህ በማድረጋችን፣ በዘር የተመሰለው የመንግሥቱ መልእክት በልባችን ውስጥ ሥር ሰድዶ በማደግ በምሳሌያዊ አነጋገር ቡቃያ ሆነ፤ ውሎ አድሮም ቡቃያው ፍሬ ለማፍራት ደረሰ። ቀደም ሲል እንደተመለከትነው የስንዴ ቡቃያ አድጎ ፍሬ አፈራ የሚባለው ሌሎች ቡቃያዎችን ሲያወጣ ሳይሆን አዲስ ዘር ሲይዝ ነው፤ በተመሳሳይ እኛም ፍሬ አፈራን የሚባለው አዳዲስ ደቀ መዛሙርት ስናስገኝ ሳይሆን አዳዲስ የመንግሥቱን ዘሮች ስናፈራ ነው። ለመሆኑ አዲስ የመንግሥቱን ዘር ማፍራት ሲባል ምን ማለት ነው? የመንግሥቱን መልእክት ለሌሎች በተናገርን ቁጥር በልባችን ውስጥ ያለውን ዘር እየዘራነው ወይም እያሰራጨነው ነው ሊባል ይችላል። (ሉቃስ 6:45፤ 8:1) በመሆኑም የመንግሥቱን መልእክት ማወጃችንን እስከቀጠልን ድረስ ‘በጽናት ፍሬ እያፈራን’ እንዳለ ከዚህ ምሳሌ እንማራለን። w18.05 14 አን. 10-11

ዓርብ፣ ነሐሴ 28

እኔ፣ የምወዳቸውን ሁሉ እወቅሳለሁ እንዲሁም እገሥጻለሁ።—ራእይ 3:19

ጳውሎስ ወንድሞቹን ከማበረታታት ባለፈ ለእነሱ ሲል ‘ያለውን ሁሉ’ እንዲያውም ‘ራሱንም ጭምር ለመስጠት’ ፈቃደኛ ነበር። (2 ቆሮ. 12:15) ሽማግሌዎችም ወንድሞቻቸውን በቃላት ከማበረታታትና ከማጽናናት አልፈው በግለሰብ ደረጃ ከልብ የመነጨ አሳቢነት በማሳየት ሊያንጿቸው ይገባል። (1 ቆሮ. 14:3) ሌሎችን ማነጽ ምክር መስጠትን የሚጨምርበት ጊዜ ይኖራል፤ በዚህ ጊዜም ቢሆን ሽማግሌዎች በሚያበረታታ መንገድ ምክር መስጠት የሚቻለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳዩ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎችን መከተል ይኖርባቸዋል። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ የሰጠው ምክር በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆናል። በትንሿ እስያ ለነበሩ አንዳንድ ጉባኤዎች ጠንከር ያለ ምክር መስጠት ባስፈለገው ጊዜ ይህን ያደረገው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። በኤፌሶን፣ በጴርጋሞንና በትያጥሮን ለነበሩት ጉባኤዎች ምክር ከመስጠቱ በፊት ከልብ አመስግኗቸዋል። (ራእይ 2:1-5, 12, 13, 18, 19) ሽማግሌዎች ምክር በሚሰጡበት ጊዜ የክርስቶስን ምሳሌ መከተላቸው ተገቢ ነው። w18.04 22 አን. 8-9

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 29

አባቶች ሆይ፣ ልጆቻችሁን . . . በይሖዋ ተግሣጽና ምክር አሳድጓቸው።—ኤፌ. 6:4

ወላጆች፣ ልጆቻችሁን ቃል በቃል ከበሽታ ለመጠበቅ የተቻላችሁን ያህል ጥረት እንደምታደርጉ ምንም ጥርጥር የለውም። ለዚህ ስትሉ ቤታችሁን በንጽሕና የምትይዙ ከመሆኑም ሌላ እናንተንም ሆነ ልጆቻችሁን ለበሽታ ሊያጋልጡ የሚችሉ ነገሮችን ታስወግዳላችሁ። በተመሳሳይም ልጆቻችሁን ለሰይጣን አስተሳሰብ ሊያጋልጧቸው ከሚችሉ ፊልሞች፣ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎችና ድረ ገጾች ልትጠብቋቸው ይገባል። ይሖዋ የልጆቻችሁን መንፈሳዊ ደህንነት የመጠበቅ ሥልጣን ሰጥቷችኋል። (ምሳሌ 1:8) በመሆኑም በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ላይ የተመሠረቱ ሕጎችን ለቤተሰባችሁ ማውጣት ሊይስፈራችሁ አይገባም። የትኞቹን ነገሮች ማየት እንደሚፈቀድላቸውና የትኞቹን ነገሮች ማየት እንደማይፈቀድላቸው ለትናንሽ ልጆቻችሁ ንገሯቸው፤ እንዲሁም ይህን ውሳኔ ያደረጋችሁበትን ምክንያት አስረዷቸው። (ማቴ. 5:37) ከፍ እያሉ ሲሄዱ ደግሞ በይሖዋ መሥፈርት ላይ ተመሥርተው ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በራሳቸው መለየት እንዲችሉ አሠልጥኗቸው። (ዕብ. 5:14) ልጆቻችሁ ይበልጥ ትምህርት የሚያገኙት የምታደርጉትን ነገር በማየት እንደሆነ አስታውሱ።—ዘዳ. 6:6, 7፤ ሮም 2:21፤ w19.01 16 አን. 8

እሁድ፣ ነሐሴ 30

ሽማግሌዎችና ልጆች በኅብረት . . . የይሖዋን ስም ያወድሱ።—መዝ. 148:12, 13

ወጣት ክርስቲያን ከሆንክ በዕድሜ ለገፉ የጉባኤው አባላት ትኩረት ለመስጠት ለምን ግብ አታወጣም? በእውነት ውስጥ ባሳለፏቸው ዓመታት ስላገኙት ተሞክሮ እንዲነግሩህ በአክብሮት ልትጠይቃቸው ትችላለህ። እንዲህ በማድረግህ እንደምትበረታታ ጥያቄ የለውም፤ ከዚህም ሌላ አንተም ሆንክ እነሱ የእውነትን ብርሃን ይበልጥ ለማብራት ትነሳሳላችሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ሁላችንም ወደ ስብሰባ አዳራሻችን የሚመጡ ሰዎችን ጥሩ አድርገን ለመቀበል ጥረት ማድረግ እንችላለን። የመስክ አገልግሎት ስምሪት ስብሰባ እንድትመራ ከተመደብክ፣ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች በአገልግሎት እንዲካፈሉ በመርዳት ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከት ትችላለህ። አረጋውያኑ ለእነሱ አመቺ የሆነ የአገልግሎት ክልል እንዲኖራቸው ልታደርግ እንዲሁም በአገልግሎት ላይ ሊያግዟቸው ከሚችሉ ወጣቶች ጋር ልትመድባቸው ትችል ይሆናል። በጤንነታቸው ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ በአገልግሎት ብዙ ማከናወን ለማይችሉ ክርስቲያኖችም አሳቢነት ማሳየት ያስፈልጋል። በእርግጥም አስተዋይ መሆንህና አሳቢነት ማሳየትህ፣ ወጣቶችም ሆኑ አረጋውያን እንዲሁም አዲሶችም ሆኑ በእውነት ውስጥ የቆዩ ክርስቲያኖች ምሥራቹን በቅንዓት እንዲሰብኩ ሊረዳቸው ይችላል።—ዘሌ. 19:32፤ w18.06 23-24 አን. 10-12

ሰኞ፣ ነሐሴ 31

ነፃነታችሁን እንደ አምላክ ባሪያዎች ሆናችሁ ተጠቀሙበት።—1 ጴጥ. 2:16

እኛም የጳውሎስን ምሳሌ መከተላችን ተገቢ ነው፤ ይሖዋ ከኃጢአትና ከሞት ባርነት ነፃ በማውጣት ያሳየንን ደግነት ፈጽሞ አቅልለን ልንመለከተው አይገባም። ቤዛው፣ በንጹሕ ሕሊና አምላካችንን እንድናገለግልና የእሱን ፈቃድ በደስታ እንድንፈጽም መንገድ ከፍቶልናል። (መዝ. 40:8) ላገኘነው ነፃነት አመስጋኝነታችንን መግለጻችን ብቻ በቂ አይደለም፤ ይህን ውድ ነፃነታችንን ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንዳንጠቀምበት መጠንቀቅ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጴጥሮስ የመምረጥ ነፃነታችንን ሥጋዊ ፍላጎታችንን ለማርካት ሰበብ እንዳናደርገው ማስጠንቀቂያ ሰጥቶናል። ይህ ማሳሰቢያ እስራኤላውያን በምድረ በዳ ሳሉ ያጋጠማቸውን ነገር ያስታውሰናል። ማስጠንቀቂያው በዛሬው ጊዜ ለምንኖር ክርስቲያኖችም ይሠራል፤ እንዲያውም ከእነሱ የባሰ ፈታኝ ሁኔታ ያጋጥመናል። ሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ዓለም ከአለባበስና ከአጋጌጥ፣ ከምግብና ከመጠጥ፣ ከመዝናኛ እንዲሁም ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ስፍር ቁጥር የሌላቸው አጓጊ ምርጫዎች ያቀርቡልናል። ማስታወቂያ የሚያዘጋጁ ሰዎች መልከ መልካም የሆኑ አስተዋዋቂዎችን በመጠቀም፣ የማያስፈልጉንን ነገሮች የግድ እንደሚያስፈልጉን አድርገው ሲያቀርቡ ይታያል። በእርግጥም እንደነዚህ ያሉት ዘዴዎች በቀላሉ ሊያታልሉንና ነፃነታችንን ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንድንጠቀምበት ሊያደርጉን ይችላሉ! w18.04 10 አን. 7-8

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ