መስከረም
ማክሰኞ፣ መስከረም 1
አይታችሁት ባታውቁም ትወዱታላችሁ።—1 ጴጥ. 1:8
ኢየሱስ የማርታንና የማርያምን ስሜት ተረድቶላቸዋል። በወንድማቸው በአልዓዛር ሞት እንዳዘኑ ሲመለከት ‘እንባውን አፍስሷል።’ (ዮሐ. 11:32-35) ኢየሱስ ያለቀሰው የቅርብ ጓደኛው ስለተለየው ብቻ አልነበረም። ምክንያቱም አልዓዛርን ከሞት ሊያስነሳው እንደሆነ ያውቃል። ኢየሱስ ያለቀሰው ወዳጆቹ ምን ያህል ሐዘን እንደደረሰባቸው ስለተረዳና በዚህም ምክንያት ስሜቱ በጥልቅ ስለተነካ ነው። ኢየሱስ የሌሎችን ስሜት እንደሚረዳ ማወቃችን በጣም ይጠቅመናል። እርግጥ እኛ እንደ እሱ ፍጹም አይደለንም። ሆኖም ሌሎችን የያዘበትን መንገድ ማሰባችን እሱን እንድንወደው ያደርገናል። በአሁኑ ጊዜ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ እየገዛ መሆኑን ማወቃችን ያበረታታናል። በቅርቡ ደግሞ መከራን ሁሉ ያስወግዳል። ኢየሱስም በአንድ ወቅት ሰው ሆኖ ይኖር ስለነበር የሰይጣን አገዛዝ በሰው ልጆች ላይ ያስከተለውን ሥቃይ ለማስወገድ ከማንም የተሻለ ብቃት አለው። በእርግጥም “በድካማችን ሊራራልን” የሚችል ገዢ ያለን በመሆኑ በጣም ደስተኞች ነን።—ዕብ. 2:17, 18፤ 4:15, 16፤ w19.03 17 አን. 12-13
ረቡዕ፣ መስከረም 2
የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም።—ዮሐ. 6:44
ሰዎች ስለ አምላክ እንዲማሩ በመርዳት ረገድ የተወሰነ አስተዋጽኦ የምናበረክት ቢሆንም ዋናውን ሚና የምንጫወተው ግን እኛ አይደለንም። (1 ቆሮ. 3:6, 7) ሰዎችን ወደ ራሱ የሚስበው ይሖዋ ነው። ደግሞም እያንዳንዱ ግለሰብ ምሥራቹን የመቀበሉ ወይም ያለመቀበሉ ጉዳይ የተመካው በራሱ የልብ ሁኔታ ላይ ነው። (ማቴ. 13:4-8) ኢየሱስ በምድር ላይ ከኖሩ ሰዎች ሁሉ የበለጠ የማስተማር ችሎታ ቢኖረውም በርካታ ሰዎች መልእክቱን እንዳልተቀበሉ ማስታወስ ይኖርብናል። እንግዲያው በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸው ሰዎች ለመልእክታችን በጎ ምላሽ ባይሰጡ ተስፋ ልንቆርጥ አይገባም። በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸውን ሰዎች ስሜት መረዳታችን ብዙ ጥቅም ያስገኛል። የስብከቱ ሥራችን ይበልጥ አስደሳች ይሆንልናል። ከመስጠት የሚገኘውን የላቀ ደስታ ማጣጣም እንችላለን። እንዲሁም “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ” ምሥራቹን መቀበል ቀላል እንዲሆንላቸው እናደርጋለን። (ሥራ 13:48) እንግዲያው “[አጋጣሚውን] እስካገኘን ድረስ ለሁሉም . . . መልካም እናድርግ።” (ገላ. 6:10) እንዲህ የምናደርግ ከሆነ በሰማይ ያለውን አባታችንን ስለምናስከብር ደስተኞች እንሆናለን።—ማቴ. 5:16፤ w19.03 25 አን. 18-19
ሐሙስ፣ መስከረም 3
በጉባኤ መካከል . . . አወድስሃለሁ።—መዝ. 22:22
ንጉሥ ዳዊት “ይሖዋ ታላቅ ነው፤ እጅግ ሊወደስም ይገባዋል” በማለት ጽፏል። (መዝ. 145:3) ዳዊት ይሖዋን ይወደው ነበር፤ ይህም “በጉባኤ መካከል” እሱን ለማወደስ አነሳስቶታል። (1 ዜና 29:10-13፤ መዝ. 40:5) በዛሬው ጊዜ ይሖዋን ማወደስ የምንችልበት አንዱ መንገድ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ሐሳብ መስጠት ነው። ሁላችንም በስብሰባዎች ላይ የሚሰጡትን የተለያዩ ሐሳቦች ስንሰማ እንበረታታለን። ለምሳሌ አንድ ትንሽ ልጅ አጭር ሆኖም ከልብ የመነጩ ቃላትን ተጠቅሞ የሚሰጠውን ሐሳብ መስማት ያስደስተናል። በቅርቡ እውነትን የሰሙ አዲስ ክርስቲያኖች በደስታ ተሞልተው ስሜታቸውን ሲገልጹ ስንሰማ ልባችን በጥልቅ ይነካል። ዓይናፋር የሆኑ ወይም የእኛን ቋንቋ ገና መማር የጀመሩ ወንድሞችና እህቶች ‘እንደ ምንም ብለው ድፍረት’ በማሰባሰብ የሚሰጡትን ሐሳብ ስናዳምጥ ልባችን በአድናቆት ይሞላል። (1 ተሰ. 2:2) ታዲያ እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ለሚያደርጉት ጥረት አድናቆታችንን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ስብሰባው ካበቃ በኋላ፣ ለሰጡት የሚያበረታታ ሐሳብ ልናመሰግናቸው እንችላለን። በተጨማሪም እኛ ራሳችን በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ በመስጠት ለእነሱ ያለንን አድናቆት እናሳያለን። እንዲህ ማድረጋችን በስብሰባዎች ላይ እኛ ብቻ ተበረታተን ከመሄድ ይልቅ ሌሎችንም እንድናበረታታ ያስችለናል።—ሮም 1:11, 12፤ w19.01 8 አን. 1-2፤ 9 አን. 6
ዓርብ፣ መስከረም 4
አመስጋኝ መሆናችሁን አሳዩ።—ቆላ. 3:15
አሥሩ ሰዎች ያሉበት ሁኔታ በጣም አስከፊ ነው። እነዚህ ሰዎች የሥጋ ደዌ በሽተኞች ሲሆኑ ከዚህ በሽታ የመላቀቅ ተስፋ የላቸውም። አንድ ቀን ግን ታላቁ አስተማሪ ኢየሱስ ሲመጣ ከሩቅ ተመለከቱ። ኢየሱስ ማንኛውንም ዓይነት ሕመም እንደሚፈውስ ሰምተዋል። በመሆኑም “ኢየሱስ፣ መምህር፣ ምሕረት አድርግልን!” በማለት ጮኹ። ከዚያም አሥሩ ሰዎች ሙሉ በሙሉ ከሕመማቸው ተፈወሱ። ሁሉም ኢየሱስ ላሳያቸው ደግነት የአመስጋኝነት ስሜት እንደተሰማቸው ምንም ጥርጥር የለውም። ከመካከላቸው አንዱ ግን አመስጋኝነቱን በውስጡ ከመያዝ ይልቅ ወደ ኢየሱስ ሄዶ ለተደረገለት ነገር ያለውን አድናቆት ገልጿል። ከበሽታው የተፈወሰው ይህ ሳምራዊ “አምላክን በታላቅ ድምፅ [ለማመስገን]” ተገፋፍቷል። (ሉቃስ 17:12-19) እኛም ልክ እንደዚህ ሳምራዊ፣ ደግነት ላሳዩን ሰዎች አመስጋኝነታችንን መግለጽ እንፈልጋለን። ይሖዋ አድናቆትን በመግለጽ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። ይህን ያደረገበት አንዱ መንገድ ደስ ለሚያሰኙት አገልጋዮቹ ወሮታ በመክፈል ነው። (2 ሳሙ. 22:21፤ መዝ. 13:6፤ ማቴ. 10:40, 41) ቅዱሳን መጻሕፍት ደግሞ “የተወደዳችሁ ልጆቹ በመሆን አምላክን የምትመስሉ ሁኑ” የሚል ማበረታቻ ይሰጡናል። (ኤፌ. 5:1) በመሆኑም አድናቆታችንን የምንገልጽበት ዋነኛው ምክንያት ይሖዋ የተወልንን ምሳሌ መከተል ስለምንፈልግ ነው። w19.02 14 አን. 1-2፤ 15 አን. 4
ቅዳሜ፣ መስከረም 5
እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!—ኢዮብ 27:5
አንዲት ትንሽ ልጅ ትምህርት ቤት ውስጥ ሳለች አምላክን በማያስደስት አንድ በዓል ላይ እንደማትሳተፍ ለአስተማሪዋ በአክብሮት ነገረቻት። ዓይናፋር የሆነ አንድ ወጣት ከቤት ወደ ቤት እያገለገለ ሳለ አንድ አብሮት የሚማር ልጅ ቤት አንኳኳ፤ ይህ ልጅ በይሖዋ ምሥክሮች ላይ እንደሚያሾፍ ትዝ ይለዋል። ለቤተሰቡ የሚያስፈልገውን ነገር ለማቅረብ ተግቶ የሚሠራ አንድ የቤተሰብ ራስ አለቃው ሐቀኝነት የጎደለው ወይም ሕገ ወጥ የሆነ ነገር እንዲያደርግ ይጠይቀዋል። ይህ የቤተሰብ ራስ ሥራውን ሊያሳጣው እንደሚችል ቢያውቅም አምላክ አገልጋዮቹ ሐቀኛና ሕግ አክባሪ እንዲሆኑ ስለሚጠብቅባቸው እንዲህ ዓይነት ነገር እንደማያደርግ ለአለቃው ገለጸለት። (ሮም 13:1-4፤ ዕብ. 13:18) በእነዚህ ሦስት ሰዎች ላይ የትኛውን ባሕርይ አስተውላችኋል? ድፍረትንና ሐቀኝነትን ጨምሮ የተለያዩ ባሕርያትን አስተውላችሁ ይሆናል። ሆኖም ከሁሉ በላይ ጎላ ብሎ የሚታይ አንድ ባሕርይ አለ፤ ይህም ንጹሕ አቋም ነው። እነዚህ ሰዎች ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት ጠብቀዋል። የአምላክን መሥፈርቶች ለድርድር ለማቅረብ ፈቃደኞች እንዳልሆኑ አሳይተዋል። ሦስቱም እንዲህ ያለ እርምጃ ለመውሰድ የተነሳሱት ንጹሕ አቋም ስላላቸው ነው። ይሖዋ እነዚህ ሰዎች ይህን ባሕርይ በማንጸባረቃቸው እንደሚኮራባቸው ምንም ጥርጥር የለውም። እኛም በተመሳሳይ በሰማይ ያለው አባታችን እንዲኮራብን እንፈልጋለን። w19.02 2 አን. 1-2
እሁድ፣ መስከረም 6
ሕጉ ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ ነው።—ዕብ. 10:1
ሕጉ በተለይ ራሳቸውን መከላከል ለማይችሉ ሰዎች ለምሳሌ ወላጅ አልባ ለሆኑ ልጆች፣ ለመበለቶችና ለባዕድ አገር ሰዎች ጥበቃ ያደርግ ነበር። በእስራኤል የነበሩ ዳኞች “የባዕድ አገሩን ሰው ወይም አባት የሌለውን ልጅ ፍርድ አታዛባ፤ የመበለቲቱን ልብስ የብድር መያዣ አድርገህ አትውሰድ” የሚል መመሪያ ተሰጥቷቸው ነበር። (ዘዳ. 24:17) ይሖዋ በማኅበረሰቡ ውስጥ ላሉ ይበልጥ ለጥቃት የተጋለጡ ሰዎች ልዩ ትኩረት ይሰጥ ነበር። ከዚህም በላይ በእነሱ ላይ በደል የሚፈጽሙ ሰዎችን ተጠያቂ ያደርጋቸው ነበር። (ዘፀ. 22:22-24) ይሖዋ በኃላፊነት ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች በሥራቸው ላሉት ሁሉ ፍቅራዊ አሳቢነት እንዲያሳዩ ይጠብቅባቸዋል። ፆታዊ ጥቃቶችን የሚጠላ ከመሆኑም ሌላ ሁሉም ሰው በተለይም ይበልጥ ለጥቃት የተጋለጡ ሰዎች ፍትሕና ጥበቃ እንዲያገኙ ይፈልጋል። (ዘሌ. 18:6-30) ይሖዋ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንደሚይዘን እርግጠኞች ስንሆን ለእሱ ያለን ፍቅር ያድጋል። ለአምላክና ለጽድቅ መሥፈርቶቹ ፍቅር ካለን ደግሞ ሌሎችን ለመውደድና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ለመያዝ እንነሳሳለን። w19.02 24-25 አን. 22-26
ሰኞ፣ መስከረም 7
ፈሪሃ አምላክ በጎደለው መንገድ መኖርና ዓለማዊ ምኞቶችን መከተል [እንተው]።—ቲቶ 2:12
የሰይጣን አስተሳሰብ ተጽዕኖ እንዳያሳድርብን መከላከል የምንችለው እንዴት እንደሆነ የሚያሳይ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ይሖዋ ‘የፆታ ብልግናና ማንኛውም ዓይነት ርኩሰት በመካከላችን ከቶ መነሳት’ እንደሌለበት አስተምሮናል። (ኤፌ. 5:3) ሆኖም የሥራ ባልደረቦቻችን ወይም አብረውን የሚማሩ ልጆች የብልግና ወሬዎችን ማውራት ቢጀምሩ ምን እናደርጋለን? ጠባቂ የሆነው ሕሊናችን በዚህ ጊዜ የማስጠንቀቂያ ድምፅ ሊያሰማ ይችላል። (ሮም 2:15) ታዲያ ማስጠንቀቂያውን እንሰማለን? አንዳንድ ጊዜ፣ እኩዮቻችን የሚያወሩትን ወሬ ለመስማት ወይም የሚላላኩትን ምስል ለማየት እንፈተን ይሆናል። ሆኖም ምሳሌያዊ በሮቻችንን መዝጋት የሚገባን በዚህ ጊዜ ነው፤ ይህን ለማድረግ ርዕሱን መቀየር ወይም ከአካባቢው ዞር ማለት እንችላለን። እኩዮቻችን መጥፎ ነገሮችን እንድናስብ ወይም የተሳሳተ እርምጃ እንድንወስድ የሚያሳድሩብንን ተጽዕኖ መቋቋም ድፍረት ይጠይቃል። ሆኖም ይሖዋ የምናደርገውን ጥረት እንደሚመለከት እንዲሁም ሰይጣናዊ አስተሳሰቦችን ለመቋቋም የሚያስፈልገንን ብርታትና ጥበብ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—2 ዜና 16:9፤ ኢሳ. 40:29፤ ያዕ. 1:5፤ w19.01 17-18 አን. 12-13
ማክሰኞ፣ መስከረም 8
እጆቼ የሠሩትን ሥራ ሁሉ . . . መለስ ብዬ ሳስብ፣ ሁሉ ነገር ከንቱ . . . መሆኑን አስተዋልኩ፤ እውነተኛ ፋይዳ ያለው አንዳች ነገር አልነበረም።—መክ. 2:11
እጅግ በጣም ሀብታምና ኃያል የነበረው ንጉሥ ሰለሞን ‘ደስታን ለመፈተንና ምን መልካም ነገር እንደሚገኝ ለማየት’ ቆርጦ ተነስቶ ነበር። (መክ. 2:1-10) በመሆኑም ቤቶችን ገነባ፣ የአትክልት ቦታዎችንና መናፈሻዎችን አዘጋጀ እንዲሁም የተመኘውን ሁሉ አደረገ። ከዚያስ ምን ተሰማው? ያከናወናቸው ነገሮች ደስታና እርካታ አስገኝተውለት ይሆን? በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ሰለሞን ራሱ መልሱን ሰጥቶናል። ይህ እንዴት ያለ ትልቅ ትምህርት ነው! እናንተስ ከሰለሞን ታሪክ በመማር ጥበበኛ እንደሆናችሁ ታሳያላችሁ? ይሖዋ፣ ከሚደርስባችሁ መከራ እንድትማሩ አይፈልግም። እርግጥ ነው፣ አምላክን ለመታዘዝና በሕይወታችሁ ውስጥ የእሱን ፈቃድ ለማስቀደም እምነት ያስፈልጋችኋል። እንዲህ ያለው እምነት በዋጋ ሊተመን የማይችልና ፈጽሞ ለቁጭት የማይዳርግ ነው። አዎ፣ ይሖዋ “ለስሙ ያሳያችሁትን ፍቅር” ፈጽሞ አይረሳም። (ዕብ. 6:10) እንግዲያው ጠንካራ እምነት ለመገንባት ብርቱ ጥረት አድርጉ፤ እንዲህ ማድረጋችሁ በሰማይ ያለው አባታችሁ ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንድታገኙ እንደሚፈልግ በገዛ ሕይወታችሁ ለመመልከት ያስችላችኋል።—መዝ. 32:8፤ w18.12 22 አን. 14-15
ረቡዕ፣ መስከረም 9
አምላክ ገና ኃጢአተኞች ሳለን ክርስቶስ እንዲሞትልን በማድረግ ለእኛ ያለውን የራሱን ፍቅር አሳይቷል።—ሮም 5:8
መንፈሳዊ ሰው በአምላክ ላይ እምነት ያለው ከመሆኑም ሌላ ነገሮችን የሚመለከተው በአምላክ ዓይን ነው። የአምላክን አመራር ለማግኘትና በማንኛውም ሁኔታ ሥር እሱን ለመታዘዝ ጥረት ያደርጋል። (1 ቆሮ. 2:12, 13) ዳዊት በዚህ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። “ይሖዋ ድርሻዬ፣ ዕጣ ፋንታዬና ጽዋዬ ነው” በማለት ዘምሯል። (መዝ. 16:5) የዳዊት “ድርሻ” መጠጊያው ከሆነው ከይሖዋ ጋር የመሠረተውን ጥሩ ዝምድና ያካትታል። (መዝ. 16:1) ዳዊት ከአምላክ ጋር እንዲህ ያለ ዝምድና መመሥረቱ ምን ጥቅም አስገኝቶለታል? “ሁለንተናዬ ደስ ይለዋል” በማለት ጽፏል። አዎ፣ ለዳዊት ከምንም በላይ ደስታ የሚሰጠው ነገር ከአምላክ ጋር የመሠረተው የቀረበ ዝምድና ነበር። (መዝ. 16:9, 11) ሥጋዊ ደስታን በማሳደድና ቁሳዊ ሀብትን በማካበት ላይ ያተኮረ ሕይወት የሚመሩ ሰዎች ዳዊት የነበረው ዓይነት ደስታ ሊኖራቸው አይችልም። (1 ጢሞ. 6:9, 10) በይሖዋ ላይ እምነት ማዳበራችሁ እንዲሁም እሱን ማገልገላችሁ ዓላማ ያለው ሕይወት ለመምራትና እርካታ ለማግኘት ይረዳችኋል። ታዲያ በይሖዋ ላይ ያላችሁን እምነት ማሳደግ የምትችሉት እንዴት ነው? ከእሱ ጋር ጊዜ በማሳለፍ ማለትም ቃሉን በማንበብ፣ የፍጥረት ሥራዎቹን በመመልከትና ለእናንተ ያሳየውን ፍቅር ጨምሮ በተለያዩ ባሕርያቱ ላይ በማሰላሰል ነው።—ሮም 1:20፤ w18.12 25 አን. 7-8
ሐሙስ፣ መስከረም 10
ጋብቻ በሁሉ ዘንድ ክቡር . . . ይሁን።—ዕብ. 13:4
ጳውሎስ ይህን ሐሳብ የጻፈው ስለ ጋብቻ ያለውን አስተያየት ለመናገር ያህል ብቻ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ክርስቲያን ለጋብቻ ዝግጅት አክብሮት ማሳየት እንዳለበት ማለትም ይህን ዝግጅት እንደ ውድ ነገር ሊመለከተው እንደሚገባ ለማሳሰብ ነው። እናንተስ ለጋብቻ ዝግጅት እንዲህ ዓይነት አመለካከት አላችሁ? ባለትዳር ከሆናችሁ ደግሞ ለራሳችሁ ትዳር አክብሮት ታሳያላችሁ? ለጋብቻ ዝግጅት አክብሮት በማሳየት ረገድ ኢየሱስ ግሩም ምሳሌ ትቷል። ፈሪሳውያን ስለ ፍቺ በጠየቁት ጊዜ አምላክ የመጀመሪያውን ጋብቻ አስመልክቶ “ከዚህ የተነሳ ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ” እንዳለ ነግሯቸዋል። አክሎም ኢየሱስ “አምላክ ያጣመረውን ማንም ሰው አይለያየው” ብሏቸዋል። (ማር. 10:2-12፤ ዘፍ. 2:24) በመሆኑም ኢየሱስ የጋብቻ መሥራች አምላክ እንደሆነና ይህ ጥምረት ዘላቂ ሊሆን እንደሚገባ ጎላ አድርጎ ገልጿል። አምላክ ጋብቻ በፍቺ ሊፈርስ እንደሚችል ለአዳምና ለሔዋን አልነገራቸውም። በኤደን ገነት ያቋቋመው ጋብቻ፣ ትዳር ሊመሠረት የሚገባው በሁለት ሰዎች መካከል ብቻ እንደሆነና ‘የሁለቱ’ ጥምረት እስከ መጨረሻው ሊዘልቅ እንደሚገባ ያሳያል። w18.12 10-11 አን. 2-4
ዓርብ፣ መስከረም 11
አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።—ሮም 12:2
እውነትን ስንሰማ፣ ይሖዋ ያወጣቸውን መሠረታዊ ብቃቶች ማሟላት አስፈላጊ እንደሆነ ተምረናል። በመንፈሳዊ እያደግን ስንሄድ ግን የይሖዋን አስተሳሰብ ማለትም እሱ የሚወዳቸውንና የሚጠላቸውን ነገሮች እንዲሁም ስለተለያዩ ጉዳዮች ያለውን አመለካከት ይበልጥ ማወቅ ችለናል። ይህ ደግሞ በድርጊታችንና በግል ምርጫችን ላይ ተጽዕኖ ያደርጋል። የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብ ለማዳበር ጥረት ማድረግ አስደሳች ቢሆንም ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ጊዜ፣ ፍጽምና የጎደለው አእምሯችን የሚያመነጫቸው ሐሳቦች እንቅፋት ሊፈጥሩብን ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ከሥነ ምግባር ንጽሕና፣ ከፍቅረ ንዋይ፣ ከስብከቱ ሥራ፣ ከደም አጠቃቀም ወይም ከሌሎች ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ያለውን አመለካከት መቀበል ሊከብደን ይችላል። በዚህ ጊዜ ምን ማድረግ እንችላለን? አስተሳሰባችን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ይበልጥ የሚስማማ እንዲሆን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? የአምላክን አስተሳሰብ መረዳትን ግብ አድርገን ቃሉን በማጥናት፣ ባጠናነው ነገር ላይ በማሰላሰልና አስተሳሰባችንን ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር ለማስማማት ጥረት በማድረግ አእምሯችንን ማደስ ይኖርብናል። w18.11 23-24 አን. 2-4
ቅዳሜ፣ መስከረም 12
ከግፍ እንድታስጥለኝ ስለምን ጣልቃ የማትገባው እስከ መቼ ነው?—ዕን. 1:2
ዕንባቆም የኖረው በጣም ከባድና ተፈታታኝ በሆነ ወቅት ላይ ነው። ክፉና ዓመፀኛ በሆኑ ሰዎች መካከል መኖሩ በጥልቅ ሐዘን እንዲዋጥ አድርጎታል። የእነዚህ ሰዎች ክፋት የሚያበቃው መቼ ነው? ይሖዋ እርምጃ ለመውሰድ ይህን ያህል የዘገየው ለምንድን ነው? ዕንባቆም የሚያየው ሁሉ የገዛ አገሩ ሰዎች የሚፈጽሙትን ግፍና ጭቆና ብቻ ነው። ብቻውን እንደተተወ ሳይሰማው አልቀረም። ዕንባቆም ወደ ይሖዋ በመጮኽ ጣልቃ እንዲገባ የጠየቀው እንዲህ ባለ አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ ነው። ምናልባትም ይህ ነቢይ ይሖዋ ጉዳዩ እንደማያሳስበውና በቅርቡ እርምጃ እንደማይወስድ ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። አንተስ እንደዚህ ታማኝ የአምላክ አገልጋይ ተሰምቶህ ያውቃል? ዕንባቆም በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት አጥቶ ይሆን? አምላክ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ ያለው እምነትስ ጠፍቶ ይሆን? በፍጹም! ችግሮቹንና ያሳሰቡትን ነገሮች ለሰዎች ሳይሆን ለይሖዋ መናገሩ በራሱ፣ ተስፋ እንዳልቆረጠ ያሳያል። አምላክ እርምጃ ሳይወስድ የቆየውና አገልጋዩ እንዲህ ያለ አስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንዲኖር የፈቀደው ለምን እንደሆነ አለማወቁ አስጨንቆት እንደሚሆን ግልጽ ነው። w18.11 14 አን. 4-5
እሁድ፣ መስከረም 13
በምድር ላይ ለራሳችሁ ሀብት አታከማቹ።—ማቴ. 6:19
ኢየሱስ ዓሣ አጥማጆች ለነበሩት ለጴጥሮስና ለእንድርያስ “ሰው አጥማጆች” እንዲሆኑ ግብዣ ሲያቀርብላቸው ሁለቱም “መረቦቻቸውን ትተው” ተከትለውታል። (ማቴ. 4:18-20) እርግጥ ነው፣ በዛሬው ጊዜ እውነትን የሚሰሙ በርካታ ሰዎች ሥራቸውን እርግፍ አድርገው መተው አይችሉም። ምክንያቱም ሊወጧቸው የሚገቡ ቅዱስ ጽሑፋዊ ኃላፊነቶች አሉባቸው። (1 ጢሞ. 5:8) ሆኖም እውነትን የሚሰሙ ሰዎች አብዛኛውን ጊዜ ለቁሳዊ ነገሮች ያላቸውን አመለካከት መለወጥና ቅድሚያ የሚሰጧቸውን ነገሮች ማስተካከል ይኖርባቸዋል። እስቲ ማሪያ ያደረገችውን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ማሪያ ጎልፍ መጫወት ትወድ ነበር። በሕይወቷ ውስጥ ከምንም በላይ ቅድሚያ የምትሰጠው ለዚህ ስፖርት ነበር። የወደፊት ግቧም በዚህ መስክ ትልቅ ደረጃ ላይ መድረስ ነበር። በኋላ ግን ማሪያ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት የጀመረች ሲሆን እውነትን ስትማር ባደረገቻቸው ለውጦችም በጣም ደስተኛ ሆነች። ማሪያ ቁሳዊ ሀብት እያሳደደች መንፈሳዊ ሀብት ማካበት እንደማትችል ተገነዘበች። (ማቴ. 6:24) በመሆኑም ከልጅነቷ ጀምሮ ትመኘው የነበረውን የጎልፍ ተጫዋች የመሆን ግብ መሥዋዕት አደረገች። በአሁኑ ጊዜ በአቅኚነት እያገለገለች ነው። ማሪያ ይህን ሕይወት “እጅግ አስደሳችና ከሁሉ በላይ ትርጉም ያለው ሕይወት” በማለት ገልጻዋለች። w18.11 5 አን. 9-10
ሰኞ፣ መስከረም 14
ይህ አናጺው የማርያም ልጅ [ነው]።—ማር. 6:3
ኢየሱስ 30 ዓመት ሲሞላው የአናጺነት መሣሪያዎቹን ትቶ ትኩረቱን ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ በሆነው የማስተማሩ ሥራ ላይ አደረገ። አምላክ እሱን ወደ ምድር ከላከበት ምክንያቶች መካከል አንዱ የመንግሥቱን ምሥራች እንዲያውጅ መሆኑን ተናግሯል። (ማቴ. 20:28፤ ሉቃስ 3:23፤ 4:43) ኢየሱስ አገልግሎቱ በሕይወቱ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ቦታ እንዲይዝ ያደረገ ከመሆኑም በላይ ሌሎችም በዚህ ሥራ አብረውት እንዲካፈሉ ይፈልግ ነበር። (ማቴ. 9:35-38) አብዛኞቻችን አናጺዎች አይደለንም፤ ሆኖም ሁላችንም የምሥራቹ አገልጋዮች ነን። ይህ ሥራ በጣም አስፈላጊ ከመሆኑ የተነሳ አምላክ ራሱ በሥራው ይካፈላል፤ እኛም “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን።” (1 ቆሮ. 3:9፤ 2 ቆሮ. 6:4) “[የይሖዋ ቃል] ፍሬ ነገር እውነት” እንደሆነ እናውቃለን። (መዝ. 119:159, 160) በመሆኑም በአገልግሎት ስንካፈል “የእውነትን ቃል በአግባቡ [መጠቀማችን]” በጣም አስፈላጊ እንደሆነ እንገነዘባለን። (2 ጢሞ. 2:15) ከዚህ አንጻር ዋነኛ መሣሪያችን የሆነውን መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅመን ለሰዎች ስለ ይሖዋ፣ ስለ ኢየሱስና ስለ አምላክ መንግሥት እውነቱን የማስተማር ችሎታችንን እያሻሻልን መሄድ እንፈልጋለን። w18.10 11 አን. 1-2
ማክሰኞ፣ መስከረም 15
ደካማ የሆኑትን [እርዱ]፤ . . . ጌታ ኢየሱስ ራሱ የተናገረውን ቃል [አስታውሱ]።—ሥራ 20:35
አንድ ባል፣ ራሱ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን አርዓያ የሚከተል ከሆነ ሚስቱ እሱን ‘በጥልቅ ማክበር’ አይከብዳትም። (ኤፌ. 5:22-25, 33) ሚስትም ብትሆን ለባሏ ያላት አክብሮት ለእሱ አሳቢነት ለማሳየት ያነሳሳታል። አንዳቸው ለሌላው አሳቢነት የሚያሳዩ ወላጆች ለልጆቻቸው ግሩም ምሳሌ መሆን ይችላሉ። ልጆች ለሌሎች አሳቢነት እንዲያሳዩ የማሠልጠኑ ኃላፊነት በዋነኝነት የሚወድቀው በወላጆች ላይ እንደሆነ ጥያቄ የለውም። ለምሳሌ ያህል፣ ወላጆች ልጆቻቸውን በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ እንዳይሯሯጡ ማስተማራቸው አስፈላጊ ነው። ወይም ደግሞ በግብዣዎች ላይ ምግብ ሲወስዱ ትላልቅ ሰዎችን እንዲያስቀድሙ ሊነግሯቸው ይችላሉ። አንድ ልጅ አሳቢነት የሚንጸባረቅበት ነገር ቢያደርግ ለምሳሌ በር ቢከፍትልን ልናመሰግነው ይገባል። እንዲህ ማድረጋችን ልጁ “ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ [እንደሚያስገኝ]” እንዲገነዘብ ስለሚረዳው አሳቢነት ማሳየቱን ለመቀጠል ይነሳሳል። w18.09 29 አን. 5-6
ረቡዕ፣ መስከረም 16
መሪያችሁ አንድ እሱም ክርስቶስ [ነው]።—ማቴ. 23:10
በመግዛት ላይ ያለው ንጉሣችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሚሰጠው መመሪያ የወደፊቱን ጊዜ ግምት ውስጥ ያስገባ ነው። እንግዲያው በቅርቡ ከተደረጉት ለውጦች ጋር ራሳችንን ማስማማታችን ባስገኘልን ጥቅም ላይ ለማተኮር ጥረት እናድርግ። ለምሳሌ በቤተሰብ አምልኳችሁ ላይ ከሳምንታዊ ስብሰባዎች ወይም ከአገልግሎት ጋር በተያያዘ የተደረጉት ለውጦች ምን ጥቅም እንዳስገኙላችሁ ልትወያዩ ትችላላችሁ። የይሖዋ ድርጅት ከሚሰጠን መመሪያዎች በስተጀርባ ያለውን መንፈስና እነዚህን መመሪያዎች መከተል በሚያስገኘው ጥቅም ላይ ማሰላሰላችን መመሪያዎቹን በደስታ እንድንታዘዝ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ የሚታተሙ ጽሑፎች ቁጥር እንዲቀንስ መደረጉ የድርጅቱ ወጪ እንዲቀንስ አድርጓል፤ በተጨማሪም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀማችን በዓለም ዙሪያ የሚከናወነውን የስብከቱን ሥራ ይበልጥ ለማስፋፋት አስችሏል። እንግዲያው ሁኔታችን የሚፈቅድ ከሆነ የሕትመት ውጤቶችንና ሚዲያዎችን በኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻችን ለመጠቀም ጥረት እናድርግ። ይህ ክርስቶስን መደገፍ የምንችልበት አንዱ መንገድ ነው፤ ክርስቶስ የድርጅቱን ሀብት ከሁሉ በተሻለ መንገድ እንድንጠቀምበት ይፈልጋል። የክርስቶስን አመራር ከልብ መደገፋችን የሌሎችን እምነት የሚያጠናክር ከመሆኑም ሌላ ለአንድነታችን አስተዋጽኦ ያበረክታል። w18.10 25-26 አን. 17-19
ሐሙስ፣ መስከረም 17
ለእናንተ ጥልቅ ፍቅር ስላለን የአምላክን ምሥራች ለማካፈል ብቻ ሳይሆን ራሳችንን ጭምር ለእናንተ ለመስጠት ቆርጠን ነበር።—1 ተሰ. 2:8
እኛም እንደ አምላካችን ለሌሎች አሳቢነት የምናሳይ ከሆነ፣ ይሖዋ በጭንቀት የተዋጠ ሰው ለሚያቀርበው ጸሎት መልስ ለመስጠት ሊጠቀምብን ይችላል። (2 ቆሮ. 1:3-6) ከወንድሞቻችሁና እህቶቻችሁ ፍጽምና አትጠብቁ። ምንጊዜም ለእነሱ ሚዛናዊ አመለካከት ሊኖራችሁ ይገባል። እንከን የለሽ እንዲሆኑ መጠበቅ ምክንያታዊ አይሆንም፤ ደግሞም እንዲህ ያለው አመለካከት ለብስጭት ይዳርጋል። (መክ. 7:21, 22) ይሖዋ ከአገልጋዮቹ በሚጠብቀው ነገር ረገድ ምክንያታዊ እንደሆነ እናስታውስ። እኛም የእሱን ምሳሌ የምንከተል ከሆነ የሌሎችን አለፍጽምና ችለን መኖር አይከብደንም። (ኤፌ. 4:2, 32) ወንድሞቻችሁ የሚያደርጉት ነገር በቂ እንዳልሆነ እንዲሰማቸው ከማድረግ ይልቅ ላከናወኑት ነገር አመስግኗቸው። ይህ በጣም ያበረታታቸዋል። ወንድሞቻችንን ከልብ ማመስገናችን እነሱን በፍቅር ለማነጽ የሚያስችለን ከመሆኑም ሌላ በቅዱስ አገልግሎታቸው ‘እጅግ የሚደሰቱበት ነገር እንዲያገኙ’ ያደርጋል። የእምነት ባልንጀሮቻችንን ከሌሎች ጋር በማወዳደር ተስፋ ከማስቆረጥ ይልቅ በዚህ መንገድ ማበረታታቱ ምንኛ የተሻለ ነው!—ገላ. 6:4፤ w18.09 16 አን. 16-17
ዓርብ፣ መስከረም 18
የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና እንዳከናውነው የሰጠኝን ሥራ መፈጸም ነው።—ዮሐ. 4:34
ኢየሱስ፣ የአምላክን ፈቃድ ማድረግን እንደ መንፈሳዊ ምግብ ተመልክቶታል። ሆኖም የአምላክን ፈቃድ ማድረግ እንደ ምግብ የተቆጠረው እንዴት ነው? ጥሩ ምግብ ስንመገብ እንደምንረካና ሰውነታችን እንደሚጠናከር ሁሉ የአምላክን ፈቃድ ስንፈጽምም ደስታ እናገኛለን፤ እምነታችንም ይጠናከራል። ጥበበኛ መሆን ሲባል ከአምላክ ያገኘነውን ትምህርት በተግባር ማዋልን ያመለክታል። (ያዕ. 3:13) ጥበብ ለማግኘት ስንል የምናደርገው ጥረት መልሶ የሚክስ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ጥበብን በተመለከተ እንዲህ ይላል፦ “አንተ የምትመኘው ማንኛውም ነገር ሊተካከላት አይችልም። . . . ለሚይዟት የሕይወት ዛፍ ናት፤ አጥብቀው የሚይዟትም ደስተኞች ይባላሉ።” (ምሳሌ 3:13-18) ኢየሱስም “እነዚህን ነገሮች ስለምታውቁ ብትፈጽሟቸው ደስተኞች ናችሁ” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 13:17) ደቀ መዛሙርቱ ደስተኛ ሆነው መኖር የሚችሉት ኢየሱስ ያስተማራቸውን ነገሮች መፈጸማቸውን ከቀጠሉ ነው። የኢየሱስን ትምህርትና ምሳሌ መከተል በሕይወታቸው ሙሉ ሊያደርጉት የሚገባ ነገር ነው። w18.09 4 አን. 4-5
ቅዳሜ፣ መስከረም 19
አምላክም ሰውን በራሱ መልክ ፈጠረው።—ዘፍ. 1:27
አምላክ ለመጀመሪያዎቹ ባልና ሚስት ስለ ሌሎች ማሰብ እንዳለባቸው የሚጠቁም መመሪያ የሰጣቸው ገና በኤደን ገነት ውስጥ ብቻቸውን እያሉ ነበር። ይሖዋ አዳምንና ሔዋንን የባረካቸው ሲሆን እንዲባዙ፣ ምድርን እንዲሞሏትና እንዲገዟትም ነግሯቸዋል። (ዘፍ. 1:28) ፈጣሪያችን የፍጥረታቱ ደህንነት በጥልቅ እንደሚያሳስበው ሁሉ የመጀመሪያዎቹ ወላጆችም ወደፊት ስለሚወልዷቸው ልጆች ደስታ ማሰብ ነበረባቸው። ምድር ለአዳም ዘሮች ምቹ መኖሪያ እንድትሆን ለማድረግ ገነትን በመላው ምድር ላይ ማስፋፋት ይጠበቅባቸው ነበር። ቁጥሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚመጣው የአዳም ቤተሰብ ይህን መጠነ ሰፊ ሥራ ለማከናወን ተባብሮ መሥራት ነበረበት። ፍጹም የሆኑ የሰው ልጆች መላዋን ምድር ገነት ለማድረግና የይሖዋን ዓላማ ለመፈጸም ከእሱ ጋር በቅርበት መሥራት ያስፈልጋቸው ነበር፤ ይህን ካደረጉ ወደ አምላክ እረፍት መግባት ይችላሉ። (ዕብ. 4:11) ይህ ሥራ ምን ያህል አስደሳችና አርኪ ይሆን እንደነበር መገመት አያዳግትም! የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት በማድረግ ለሌሎች ደህንነት ማሰባቸው የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከት ያስገኝላቸው ነበር። w18.08 18 አን. 2፤ 20 8-9
እሁድ፣ መስከረም 20
እሱ በጌታዬ በንጉሡ ፊት የእኔን የአገልጋይህን ስም አጥፍቷል።—2 ሳሙ. 19:27
ሌሎች፣ የተሳሳተ መረጃ በማሰራጨት ስምህን ቢያጠፉ ምን ማድረግ ይኖርብሃል? ኢየሱስና አጥማቂው ዮሐንስ እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። (ማቴ. 11:18, 19) ኢየሱስ፣ ሰዎች ስለ እሱ የሐሰት ወሬ ሲያናፍሱ ምን አደረገ? ወሬውን ለማስተባበል በመሞከር ጊዜውንና ጉልበቱን አላባከነም። ከዚህ ይልቅ ሰዎች ተግባሩንና ያስተማረውን ነገር በማየት እውነቱን ራሳቸው እንዲፈርዱ አበረታቷል። ኢየሱስ “ጥበብ ትክክል መሆኗ በሥራዋ ተረጋግጧል” ብሏል። (ማቴ. 11:19 ግርጌ) ከዚህ ግሩም ትምህርት እናገኛለን። አንዳንድ ጊዜ ሰዎች ስለ እኛ ተገቢ ያልሆነ ወይም ነቀፋ ያዘለ ነገር ይናገሩ ይሆናል። በዚህ ወቅት፣ ነገሩ እንዲስተካከል እንመኝ እንዲሁም የጎደፈውን ስማችንን ለማጽዳት ስንል አንድ እርምጃ ለመውሰድ እንፈልግ ይሆናል። ይሁንና ከዚህ የተሻለ ነገር ማድረግ እንችላለን። አንድ ሰው ስለ እኛ የሐሰት ወሬ ቢያሰራጭ ወሬው ውሸት መሆኑን በአኗኗራችን ማሳየት እንችላለን፤ እንዲህ ካደረግን ሌሎች ሰዎች የግለሰቡን ውሸት አያምኑም። በእርግጥም ከኢየሱስ ምሳሌ መመልከት እንደሚቻለው ጥሩ ክርስቲያናዊ ምግባር ካለን ስለ እኛ የሚወሩ ባልተሟላ መረጃ ላይ የተመሠረቱ ወሬዎችና የሐሰት ውንጀላዎች ተአማኒነት እንዳያገኙ ማድረግ እንችላለን። w18.08 6 አን. 11-13
ሰኞ፣ መስከረም 21
አምላክህን ይሖዋን ፍራ፤ አገልግለው፤ ከእሱም ጋር ተጣበቅ።—ዘዳ. 10:20
ታዛዥ ስላልነበሩት ስለ ቃየን፣ ስለ ሰለሞንና በሲና ተራራ ስለነበሩት እስራኤላውያን የሚናገሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ትኩረት የሚስብ የጋራ ነጥብ አላቸው። በሦስቱም ዘገባዎች ላይ የተጠቀሱት ሰዎች ‘ንስሐ የሚገቡበትና የሚመለሱበት’ አጋጣሚ ነበራቸው። (ሥራ 3:19) በግልጽ ማየት እንደሚቻለው ይሖዋ የተሳሳተ ጎዳና በሚከተሉ አገልጋዮቹ ላይ ቶሎ ተስፋ አይቆርጥም። ለምሳሌ አሮንን ይቅር ብሎታል። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ በተመሠረቱ ጽሑፎች አሊያም የእምነት ባልንጀሮቻችን በሚሰጡን ደግነት የሚንጸባረቅበት ምክር አማካኝነት ያስጠነቅቀናል። እነዚህን ማስጠንቀቂያዎች የምንቀበል ከሆነ ይሖዋ ምሕረቱን እንደሚያሳየን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ይሖዋ ጸጋውን የሚያሳየው በዓላማ ነው። (2 ቆሮ. 6:1) የአምላክ ጸጋ “ፈሪሃ አምላክ በጎደለው መንገድ መኖርና ዓለማዊ ምኞቶችን መከተል [እንድንተው]” አጋጣሚ ይሰጠናል። (ቲቶ 2:11-14) “አሁን ባለው በዚህ ሥርዓት ውስጥ” እስከኖርን ድረስ ለይሖዋ የምናቀርበውን የሙሉ ልብ አምልኮ ፈተና ላይ የሚጥሉ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። እንግዲያው ምንጊዜም ከይሖዋ ጎን ለመቆም ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ! w18.07 21 አን. 20-21
ማክሰኞ፣ መስከረም 22
ይሖዋ የእሱ የሆኑትን ያውቃል።—2 ጢሞ. 2:19
በዓለም ሳይሆን በይሖዋ ዘንድ እውቅና ለማግኘት ያደረግነውን ቁርጥ ውሳኔ ማጠናከር የምንችለው እንዴት ነው? ሁለት አስፈላጊ እውነታዎችን ማስታወስ ይኖርብናል። አንደኛ፣ ይሖዋ በታማኝነት ለሚያገለግሉት ምንጊዜም እውቅና ይሰጣል። (ዕብ. 6:10፤ 11:6) አገልጋዮቹን በግለሰብ ደረጃ የሚያደንቃቸው ከመሆኑም ሌላ ታማኞቹን ችላ ማለት ለእሱ ‘ፍትሕ እንደማዛባት’ ነው። በተጨማሪም ‘የጻድቃንን መንገድም’ ሆነ እነሱን ከፈተና እንዴት እንደሚያድን ያውቃል። (መዝ. 1:6፤ 2 ጴጥ. 2:9) ሁለተኛ፣ ይሖዋ ፈጽሞ ባልጠበቅነው መንገድ እውቅና ሊሰጠን ይችላል። በሌሎች ለመታየት ሲሉ ብቻ መልካም ነገሮችን የሚያደርጉ ሰዎች ከይሖዋ ምንም ብድራት እንደማያገኙ ተነግሯቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ሙሉ ብድራታቸውን ተቀብለዋል። (ማቴ. 6:1-5) በሌላ በኩል ግን ኢየሱስ ሌሎችን የሚጠቅም ተግባር ቢያከናውኑም ለዚህ ተገቢውን እውቅና ያላገኙ ሰዎችን አባቱ ‘በስውር እንደሚያያቸው’ ተናግሯል። ይሖዋ እንዲህ ያሉ ተግባሮችን ትኩረት ሰጥቶ የሚያይ ሲሆን ለእያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው ወሮታ ይከፍለዋል። w18.07 9 አን. 8, 10
ረቡዕ፣ መስከረም 23
አምላክ ንጹሕ ያደረገውን ነገር ርኩስ ነው ማለትህን ተው።—ሥራ 10:15
ጴጥሮስ፣ የሰማው ድምፅ ምን ሊነግረው እንደፈለገ ግራ ተጋብቶ እያለ ቆርኔሌዎስ የላካቸው መልእክተኞች መጡ። ጴጥሮስም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት የተሰጠውን መመሪያ በመከተል ከመልእክተኞቹ ጋር ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት ሄደ። ጴጥሮስ “የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት” ቢፈርድ ኖሮ በምንም ዓይነት ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት አይገባም ነበር። ምክንያቱም ለአይሁዳውያን ወደ አሕዛብ ቤት መግባት ጨርሶ የማይታሰብ ነገር ነበር። ታዲያ ጴጥሮስ በወቅቱ ሰፍኖ የነበረውን ሥር የሰደደ ጭፍን ጥላቻ አሸንፎ ወደ ቆርኔሌዎስ ቤት የገባው ለምንድን ነው? ቀደም ሲል ያየው ራእይ እንዲሁም መንፈስ ቅዱስ የሰጠው ማረጋገጫ አመለካከቱን እንዲቀይር ስለረዳው ነው። ጴጥሮስ፣ ቆርኔሌዎስ የተናገረውን ከሰማ በኋላ በጣም ስለተገረመ በመንፈስ መሪነት እንዲህ ሲል ተናገረ፦ “እነሆ፣ አምላክ እንደማያዳላ በእርግጥ አስተዋልኩ፤ ከዚህ ይልቅ ከየትኛውም ብሔር ቢሆን እሱን የሚፈራና ትክክል የሆነውን ነገር የሚያደርግ ሰው በእሱ ዘንድ ተቀባይነት አለው።” (ሥራ 10:34, 35) ጴጥሮስ በዚህ ወቅት ያገኘው አዲስ ግንዛቤ ልቡን ነክቶት መሆን አለበት፤ ደግሞም ይህ ሁሉንም ክርስቲያኖች የሚመለከት ጉዳይ ነው! w18.08 9 አን. 3-4
ሐሙስ፣ መስከረም 24
ክፉ የሆነውን ጥሉ።—አሞጽ 5:15
አምላክ የሚጠላቸውን ድርጊቶች ላለመፈጸም እንደምንጠነቀቅ የታወቀ ነው። ይሁን እንጂ ቅዱሳን መጻሕፍት ቀጥተኛ ትእዛዝ የማይሰጡባቸው አንዳንድ ሁኔታዎች በሕይወታችን ውስጥ ያጋጥሙናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን አምላክን የሚያስደስተውንና በእሱ ዘንድ ተቀባይነት ያለውን አካሄድ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናችን በዚህ ረገድ ይረዳናል። ይሖዋ ስለሚወደን ሕሊናችንን ለመቅረጽ የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ሰጥቶናል። “የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ፣ ልትሄድበትም በሚገባህ መንገድ የምመራህ እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ” ብሏል። (ኢሳ. 48:17, 18) በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ላይ በጥሞና የምናሰላስልና ወደ ልባችን ጠልቀው እንዲገቡ የምናደርግ ከሆነ ሕሊናችንን ማሠልጠን፣ ማስተካከልና መቅረጽ እንችላለን። ይህ ደግሞ ጥበብ የተንጸባረቀባቸው ውሳኔዎች ለማድረግ ያስችለናል። መሠረታዊ ሥርዓት የሚለው አገላለጽ ለአንድ ዓይነት አስተሳሰብ ወይም ድርጊት መሠረት የሚሆነውን እውነታ አሊያም አስተምህሮት ያመለክታል። የይሖዋን መሠረታዊ ሥርዓቶች መረዳታችን የእሱን አስተሳሰብ እንዲሁም አንዳንድ ሕጎችን ያወጣበትን ምክንያት ለመገንዘብ ያስችለናል። w18.06 17 አን. 5፤ 18 አን. 8-10
ዓርብ፣ መስከረም 25
ለቄሳር ግብር መክፈል ይገባል ወይስ አይገባም?—ማቴ. 22:17
‘የሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች’ ይህን ጥያቄ ያነሱት፣ ኢየሱስ ግብር መክፈል ተገቢ እንዳልሆነ ቢናገር በመንግሥት ላይ ዓመፅ በማነሳሳት ወንጀል ሊከሱት እንደሚችሉ አስበው ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ ግብር መክፈል ተገቢ እንደሆነ ቢናገር የተከታዮቹን ድጋፍ ሊያጣ ይችላል። ኢየሱስ በዚህ ጉዳይ ላይ የትኛውንም ወገን ላለመደገፍ ጥንቃቄ አድርጓል። “የቄሳር የሆነውን ለቄሳር፣ የአምላክ የሆነውን ደግሞ ለአምላክ ስጡ” ብሏቸዋል። (ማቴ. 22:21) ኢየሱስ ቀረጥ ሰብሳቢዎቹ አጭበርባሪዎች እንደሆኑ ያውቅ ነበር፤ ያም ቢሆን በዚህ ላይ ትኩረት አላደረገም። ከዚህ ይልቅ ትኩረቱ ያረፈው ለሰው ልጆች ችግሮች እውነተኛ መፍትሔ ሊያመጣ በሚችለው በአምላክ መንግሥት ላይ ነው። በዚህ ረገድ ለሁሉም ተከታዮቹ ጥሩ ምሳሌ ትቷል። የኢየሱስ ተከታዮች፣ ከፖለቲካ ጋር የተያያዘ አንድ ጉዳይ ምንም ያህል ተገቢ ወይም ትክክል ቢመስልም የትኛውንም ወገን አይደግፉም። ክርስቲያኖች ትኩረት የሚያደርጉት በአምላክ መንግሥትና ጽድቅ ላይ ነው። በመሆኑም የትኛውንም ወገን በተመለከተ ትክክል ነው ወይም አይደለም የሚል አቋም አይዙም፤ እንዲሁም ኢፍትሐዊ ድርጊቶችን አስመልክቶ የተቃውሞ ሐሳብ አይሰነዝሩም። (ማቴ. 6:33) ብዙዎች የይሖዋ ምሥክር ከመሆናቸው በፊት አጥብቀው የሚያምኑበት ፖለቲካዊ አስተሳሰብ ነበራቸው፤ አሁን ግን ይህን አመለካከታቸውን ማስተካከል ችለዋል። w18.06 6 አን. 9-11
ቅዳሜ፣ መስከረም 26
የእውነተኛው አምላክ ልጆችም የሰዎች ሴቶች ልጆች ውብ እንደሆኑ አስተዋሉ።—ዘፍ. 6:2
ሰይጣን ለይሖዋ ታማኝ ያልሆኑትን መላእክት ለማባበል የተጠቀመው የፆታ ብልግናን ብቻ ላይሆን ይችላል፤ ምናልባትም በሰው ልጆች ላይ ሥልጣን እንደሚኖራቸው ቃል ገብቶላቸው ይሆናል። የሰይጣን ዓላማ፣ ይሖዋ ‘የሴቲቱ ዘር’ እንደሚመጣ የተናገረው ትንቢት እንዳይፈጸም ማስተጓጎል ሊሆን ይችላል። (ዘፍ. 3:15) ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ የጥፋት ውኃውን በማምጣት የሰይጣንና የዓመፀኞቹ መላእክት ዕቅድ እንዲከሽፍ አድርጓል። የሥነ ምግባር ብልግና እና ተገቢ ያልሆነ ኩራት አደገኛ ማታለያዎች መሆናቸውን ፈጽሞ መዘንጋት የለብንም። ከሰይጣን ጋር ያበሩት መላእክት ሕልቆ መሳፍርት ለሌላቸው ዘመናት በአምላክ ፊት ያገለግሉ ነበር። ይሁን እንጂ መጥፎ ምኞቶች በውስጣቸው እንዲያቆጠቁጡና ሥር እንዲሰዱ ፈቅደዋል። እኛም በተመሳሳይ በይሖዋ ድርጅት ምድራዊ ክፍል ውስጥ ለበርካታ አሥርተ ዓመታት ስናገለግል ቆይተን ይሆናል። ይሁንና በመንፈሳዊ ሁኔታ ንጹሕ በሆነው በዚህ ቦታ እያገለገልንም እንኳ ንጹሕ ያልሆኑ ሐሳቦች በልባችን ሥር ሊሰዱ ይችላሉ። (1 ቆሮ. 10:12) በእርግጥም አዘውትረን ልባችንን መፈተሻችን እንዲሁም ሥነ ምግባር የጎደላቸውን ሐሳቦችና ተገቢ ያልሆነ ኩራትን ማስወገዳችን በጣም አስፈላጊ ነው!—ገላ. 5:26፤ ቆላ. 3:5፤ w18.05 25 አን. 11-12
እሁድ፣ መስከረም 27
ታላቅ ሐዘንና የማያቋርጥ ሥቃይ በልቤ ውስጥ አለ።—ሮም 9:2
አይሁዳውያን የመንግሥቱን ምሥራች አለመቀበላቸው ለጳውሎስ ተስፋ አስቆራጭ ሆኖበት ነበር። ያም ቢሆን ለእነሱ መስበኩን አላቆመም። ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ ለእነዚህ አይሁዳውያን ያለውን ስሜት ሲገልጽ ምን እንዳለ እንመልከት፦ “ለእስራኤላውያን ከልቤ የምመኘውና ስለ እነሱ ለአምላክ ምልጃ የማቀርበው እንዲድኑ ነው። ለአምላክ ቅንዓት እንዳላቸው እመሠክርላቸዋለሁና፤ ሆኖም ቅንዓታቸው በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ አይደለም።” (ሮም 10:1, 2) ጳውሎስ ለአይሁዳውያን ለመስበክ ያነሳሳው ነገር ‘የልቡ ምኞት’ እንደሆነ ገልጿል። አይሁዳውያን እንዲድኑ ከልቡ ይጓጓ ነበር። (ሮም 11:13, 14) ሐዋርያው ቢያንስ አንዳንድ አይሁዳውያን የመንግሥቱን መልእክት እንዲቀበሉ ይሖዋን ተማጽኗል። በተጨማሪም አይሁዳውያን “ለአምላክ ቅንዓት እንዳላቸው” ገልጿል። እነዚህ ሰዎች መልካም ጎን እንዳላቸውና አምላክን ሊያገለግሉ እንደሚችሉ አስተውሏል። ጳውሎስ፣ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ቅንዓታቸው በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ካደረጉ ቀናተኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆን እንደሚችሉ ያውቅ ነበር፤ የራሱ ተሞክሮም ለዚህ ምሥክር ይሆናል። w18.05 13 አን. 4፤ 15-16 አን. 13-14
ሰኞ፣ መስከረም 28
እንደ አስፈላጊነቱ ሌሎችን የሚያንጽና ሰሚዎቹን ሊጠቅም የሚችል መልካም ቃል [ተናገሩ]።—ኤፌ. 4:29
እያንዳንዳችን ሌሎችን “እንደ አስፈላጊነቱ” ለማበረታታት ንቁዎች መሆን አለብን። ጳውሎስ ለዕብራውያን ክርስቲያኖች የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “የዛሉትን እጆችና የተብረከረኩትን ጉልበቶች አበርቱ፤ የተጎዳው የአካል ክፍል እንዲፈወስ እንጂ እንዳይናጋ እግራችሁ ዘወትር ቀና በሆነ መንገድ እንዲጓዝ አድርጉ።” (ዕብ. 12:12, 13) ልጆችን ጨምሮ ሁላችንም የሚያበረታቱ ቃላት በመናገር ሌሎችን ማነጽ እንችላለን። ጳውሎስ የሚከተለውን ምክር ሰጥቷል፦ “እንግዲህ ከክርስቶስ ጋር ባላችሁ አንድነት በመካከላችሁ ማንኛውም ዓይነት ማበረታቻ፣ ማንኛውም ዓይነት ፍቅራዊ ማጽናኛ፣ ማንኛውም ዓይነት መንፈሳዊ ኅብረት፣ ማንኛውም ዓይነት ጥልቅ ፍቅርና ርኅራኄ ካለ፣ ፍጹም አንድነት ኖሯችሁና አንድ ዓይነት አስተሳሰብ ይዛችሁ በአንድ ሐሳብና በአንድ ፍቅር በመኖር ደስታዬን የተሟላ አድርጉልኝ። ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ እንጂ በጠበኝነት መንፈስ ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ፤ ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።”—ፊልጵ. 2:1-4፤ w18.04 22 አን. 10፤ 23 አን. 12
ማክሰኞ፣ መስከረም 29
እንደ ነፃ ሰዎች ኑሩ፤ ነፃነታችሁን እንደ አምላክ ባሪያዎች ሆናችሁ ተጠቀሙበት።—1 ጴጥ. 2:16
ይሖዋ በኢየሱስ አማካኝነት ከኃጢአትና ከሞት ሕግ ነፃ እንድንወጣ ያደረገበት ዋነኛ ዓላማ ሕይወታችንን ለእሱ ወስነን “እንደ አምላክ ባሪያዎች” እንድንኖር ስለሚፈልግ ነው። ነፃነታችንን ተገቢ ባልሆነ መንገድ እንዳንጠቀምበት ብሎም ለዓለማዊ ግቦችና ለሥጋዊ ምኞቶች ዳግም ባሪያ እንዳንሆን የሚረዳን ከሁሉ የተሻለው መከላከያ በመንፈሳዊ ነገሮች መጠመድ ነው። (ገላ. 5:16) ኖኅንና ቤተሰቡን እንደ ምሳሌ እንመልከት። እነዚህ ሰዎች ይኖሩ የነበረው ዓመፀኛ በሆነና ሥነ ምግባር በጎደለው ዓለም ውስጥ ነበር። ይሁንና በዙሪያቸው የሚኖሩ ሰዎች በሚያሳድዷቸው ነገሮች አልተጠላለፉም። ለዚህ የረዳቸው ምንድን ነው? ይሖዋ በሰጣቸው ሥራ ለመጠመድ መምረጣቸው ነው፤ ኖኅና ቤተሰቡ መርከብ ይሠሩ፣ ለራሳቸውና ለእንስሳቱ የሚሆን ምግብ ያከማቹ እንዲሁም የማስጠንቀቂያ መልእክት ያውጁ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ “ኖኅም አምላክ ያዘዘውን ሁሉ በተባለው መሠረት አከናወነ። ልክ እንደዚሁ አደረገ” ይላል። (ዘፍ. 6:22) ይህን ማድረጋቸው ምን ውጤት አስገኘ? በወቅቱ የነበረው ዓለም ሲጠፋ ኖኅና ቤተሰቡ በሕይወት መትረፍ ችለዋል።—ዕብ. 11:7፤ w18.04 10 አን. 8፤ 11 አን. 11-12
ረቡዕ፣ መስከረም 30
ይህ ሁሉ ሥልጣንና የእነዚህ መንግሥታት ክብር ተሰጥቶኛል፤ እኔ ደግሞ ለፈለግኩት መስጠት ስለምችል ለአንተ እሰጥሃለሁ።—ሉቃስ 4:6
ሰይጣንና አጋንንቱ “መላውን ዓለም” ለማሳሳት ሰብዓዊ መንግሥታትን ብቻ ሳይሆን የሐሰት ሃይማኖትንና የንግዱን ሥርዓትም ይጠቀማሉ። (ራእይ 12:9) ሰይጣን በሐሰት ሃይማኖት አማካኝነት ስለ ይሖዋ የተሳሳቱ ትምህርቶችን ያስፋፋል። ከዚህም በተጨማሪ ዲያብሎስ በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች የአምላክን ስም እንዲረሱ ለማድረግ ቆርጦ ተነስቷል። (ኤር. 23:26, 27) ይህም ቅን ልብ ያላቸው አንዳንድ ሰዎች አምላክን እያመለኩ እንዳለ ቢሰማቸውም ተታልለው አጋንንትን እንዲያመልኩ አድርጓቸዋል። (1 ቆሮ. 10:20፤ 2 ቆሮ. 11:13-15) ሰይጣን በንግዱ ሥርዓት አማካኝነትም ውሸት ያስፋፋል። ለምሳሌ የንግዱ ሥርዓት፣ ደስታ የሚያስገኘው ከሁሉ የተሻለ አካሄድ ሀብት ማሳደድና ንብረት ማካበት እንደሆነ ሰዎችን ለማሳመን ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። (ምሳሌ 18:11) ይህን ውሸት የሚያምኑ ሰዎች ለአምላክ ሳይሆን “ለሀብት” ባሪያ ሆነው ይኖራሉ። (ማቴ. 6:24) ለቁሳዊ ነገሮች ያላቸው ፍቅር ለአምላክ የነበራቸውን ፍቅር ውሎ አድሮ ያንቀዋል።—ማቴ. 13:22፤ 1 ዮሐ. 2:15, 16፤ w18.05 23 አን. 6-7