የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es20 ገጽ 98-108
  • ጥቅምት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ጥቅምት
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2020
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሐሙስ፣ ጥቅምት 1
  • ዓርብ፣ ጥቅምት 2
  • ቅዳሜ፣ ጥቅምት 3
  • እሁድ፣ ጥቅምት 4
  • ሰኞ፣ ጥቅምት 5
  • ማክሰኞ፣ ጥቅምት 6
  • ረቡዕ፣ ጥቅምት 7
  • ሐሙስ፣ ጥቅምት 8
  • ዓርብ፣ ጥቅምት 9
  • ቅዳሜ፣ ጥቅምት 10
  • እሁድ፣ ጥቅምት 11
  • ሰኞ፣ ጥቅምት 12
  • ማክሰኞ፣ ጥቅምት 13
  • ረቡዕ፣ ጥቅምት 14
  • ሐሙስ፣ ጥቅምት 15
  • ዓርብ፣ ጥቅምት 16
  • ቅዳሜ፣ ጥቅምት 17
  • እሁድ፣ ጥቅምት 18
  • ሰኞ፣ ጥቅምት 19
  • ማክሰኞ፣ ጥቅምት 20
  • ረቡዕ፣ ጥቅምት 21
  • ሐሙስ፣ ጥቅምት 22
  • ዓርብ፣ ጥቅምት 23
  • ቅዳሜ፣ ጥቅምት 24
  • እሁድ፣ ጥቅምት 25
  • ሰኞ፣ ጥቅምት 26
  • ማክሰኞ፣ ጥቅምት 27
  • ረቡዕ፣ ጥቅምት 28
  • ሐሙስ፣ ጥቅምት 29
  • ዓርብ፣ ጥቅምት 30
  • ቅዳሜ፣ ጥቅምት 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2020
es20 ገጽ 98-108

ጥቅምት

ሐሙስ፣ ጥቅምት 1

ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ።—ሮም 12:15

እርግጥ ነው፣ እንደ ይሖዋና እንደ ኢየሱስ ልብን የማንበብ ችሎታ የለንም። ያም ቢሆን ሌሎች ምን እንደሚሰማቸውና ምን እንደሚያስፈልጋቸው ለመገንዘብ ጥረት ማድረግ እንችላለን። (2 ቆሮ. 11:29) በዙሪያችን ያለው ራስ ወዳድ የሆነ ዓለም፣ ተጽዕኖ እንዲያሳድርብን አንፈቅድም፤ በመሆኑም ‘ስለ ራሳችን ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት እንሰጣለን።’ (ፊልጵ. 2:4) በተለይም የጉባኤ ሽማግሌዎች የሌሎችን ስሜት ለመረዳት ጥረት ማድረግ አለባቸው። በአደራ የተሰጧቸውን በጎች የሚይዙበት መንገድ በአምላክ ዘንድ ተጠያቂ እንደሚያደርጋቸው ያውቃሉ። (ዕብ. 13:17) ሽማግሌዎች የእምነት ባልንጀሮቻቸውን መርዳት እንዲችሉ የሌሎችን ስሜት የሚረዱ መሆን ይኖርባቸዋል። ታዲያ ሽማግሌዎች ይህን ባሕርይ ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው? አሳቢ የሆነ ሽማግሌ ከክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር ጊዜ ያሳልፋል። ጥያቄዎችን ይጠይቃቸዋል፤ ከዚያም የሚሰጡትን መልስ በትኩረትና በትዕግሥት ያዳምጣል። በተለይ ደግሞ ውድ ከሆኑት በጎች መካከል አንዱ የልቡን አውጥቶ መናገር ቢፈልግም ስሜቱን እንዴት እንደሚገልጽ ግራ በሚጋባበት ጊዜ እንዲህ ማድረግ አስፈላጊ ነው። (ምሳሌ 20:5) አንድ ሽማግሌ ጊዜውን በልግስና የሚሰጥ ከሆነ ወንድሞቹ ይበልጥ እምነት ይጥሉበታል፣ ከእሱ ጋር ያላቸው ወዳጅነት ይጠናከራል እንዲሁም ለእሱ ያላቸው ፍቅር ይጨምራል።—ሥራ 20:37፤ w19.03 17 አን. 14-17

ዓርብ፣ ጥቅምት 2

በተገቢው ጊዜ የተነገረ ቃል ከብር በተሠራ ዕቃ ላይ እንዳለ የወርቅ ፖም ነው።—ምሳሌ 25:11

አድናቆት ልክ እንደ ጣፋጭ ምግብ ነው፤ አንድን ጣፋጭ ምግብ ከሌሎች ጋር ተካፍለን ስንበላው ይበልጥ ደስ ይለናል። በተመሳሳይም ሌሎች ላደረግነው ነገር አድናቆታቸውን ሲገልጹልን እኛ እንደሰታለን። ሌሎች ላደረጉልን ነገር አድናቆታችንን ስንገልጽ ደግሞ እነሱ ይደሰታሉ። አድናቆታችንን የምንገልጽለት ሰው እኛን ለመርዳት ወይም የሚያስፈልገንን ነገር ለማሟላት ያደረገው ጥረት ምን ያህል እንደጠቀመን ይገነዘባል። በውጤቱም በእኛና በዚያ ሰው መካከል ያለው ወዳጅነት ይጠናከራል። ለሌሎች የምንናገራቸው የአድናቆት መግለጫዎች በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ እንደተገለጸው ትልቅ ዋጋ አላቸው። በብር መደብ ላይ ያለ ከወርቅ የተሠራ ፖም ምን ያህል ውብ ሊሆን እንደሚችል ለማሰብ ሞክር! ደግሞም ከፍተኛ ዋጋ እንደሚኖረው ምንም ጥርጥር የለውም! እንዲህ ያለ ስጦታ ቢሰጥህ ምን ይሰማሃል? ለሌሎች የምትናገራቸው የምስጋና ቃላትም የዚህን ያህል ዋጋ አላቸው። በተጨማሪም የሚከተለውን አስብ፦ ከወርቅ የተሠራ ፖም ለረጅም ጊዜ ሊቆይ ይችላል። በተመሳሳይም አድናቆታችንን የገለጽንለት ሰው የተናገርናቸውን ቃላት ዕድሜ ልኩን ሊያስታውሳቸውና ከፍ አድርጎ ሊመለከታቸው ይችላል። w19.02 15 አን. 5-6

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 3

ሰውየው መልካምና ክፉን በማወቅ ረገድ ከእኛ እንደ አንዱ ሆኗል።—ዘፍ. 3:22

አዳምና ሔዋን መልካምና ክፉን ከሚያሳውቀው ዛፍ ፍሬ በበሉ ጊዜ በዚህ ረገድ ያላቸውን አቋም በግልጽ አሳይተዋል፦ ሁለቱም በይሖዋም ሆነ እሱ ባወጣቸው መሥፈርቶች ላይ እምነት አልነበራቸውም። መልካምና ክፉ ከሆነው ነገር ጋር በተያያዘ የራሳቸውን መሥፈርት ለማውጣት መርጠዋል። (ዘፍ. 3:22) ሆኖም ይህ ምን ኪሳራ እንዳስከተለባቸው ተመልከት። ከይሖዋ ጋር ያላቸውን ወዳጅነት አጥተዋል። በተጨማሪም ለዘላለም የመኖር አጋጣሚያቸውን ያጡ ከመሆኑም ሌላ ኃጢአትንና ሞትን ለልጆቻቸው አስተላልፈዋል። (ሮም 5:12) አዳምና ሔዋን ያደረጉትን ነገር ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ፣ ፊልጶስ በሰበከለት ጊዜ ከሰጠው ምላሽ ጋር ለማወዳደር ሞክር። ጃንደረባው፣ ይሖዋና ኢየሱስ ላደረጉለት ነገር ከፍተኛ አድናቆት ስለነበረው ወዲያውኑ ለመጠመቅ ተነሳስቷል። (ሥራ 8:34-38) ራሳችንን ለአምላክ ስንወስንና ልክ እንደዚያ ጃንደረባ ስንጠመቅ አቋማችን በግልጽ እንዲታይ እናደርጋለን። ይሖዋና ኢየሱስ ላደረጉልን ነገር አድናቆት እንዳለን እናሳያለን። በተጨማሪም ይህን እርምጃ መውሰዳችን በይሖዋ እንደምንታመን እንዲሁም መልካምና ክፉ የሆነውን ነገር በተመለከተ መሥፈርት የማውጣት መብት ያለው እሱ እንደሆነ እንደተገነዘብን ያሳያል። w19.03 2 አን. 1-2

እሁድ፣ ጥቅምት 4

ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!—ኢዮብ 27:5

ንጹሕ አቋም የሚለው አገላለጽ ከአምላክ አገልጋዮች ጋር በተያያዘ ሲሠራበት ይሖዋን እንደ እውን አካል በማየት እሱን በሙሉ ልብ መውደድንና ምንጊዜም ለእሱ ማደርን ያመለክታል፤ ይህም በምናደርጋቸው ውሳኔዎች ሁሉ የአምላክን ፈቃድ እንድናስቀድም ያነሳሳናል። ንጹሕ አቋም የሚለው አገላለጽ ከሚያስተላልፋቸው መሠረታዊ ትርጉሞች መካከል አንዱ ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ የሚል ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ለይሖዋ መሥዋዕት ተደርገው የሚቀርቡት እንስሳት እንከን የሌለባቸው መሆን ነበረባቸው። (ዘሌ. 22:21, 22) የአምላክ ሕዝቦች እግሩ፣ ጆሮው ወይም ዓይኑ ላይ ችግር ያለበት አሊያም በበሽታ የተጠቃ እንስሳ እንዲያቀርቡ አይፈቀድላቸውም ነበር። ይሖዋ እንስሳው ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ እንዲሆን ይፈልግ ነበር። (ሚል. 1:6-9) ይሖዋ የሚቀርብለት መሥዋዕት እንከን የለሽ ወይም ሙሉ እንዲሆን የሚፈልገው ለምን እንደሆነ መረዳት አይከብደንም። ለምሳሌ የበሰበሰ ፍራፍሬ፣ ገጾቹ ያልተሟሉ መጽሐፍ ወይም የሆነ ዕቃ የጎደለው መሣሪያ መግዛት አንፈልግም። የምንገዛው ነገር ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ እንዲሆን እንፈልጋለን። ይሖዋም ለእሱ ከምናሳየው ፍቅርና ታማኝነት ጋር በተያያዘ ተመሳሳይ ነገር ይጠብቃል። ፍቅራችንና ታማኝነታችን ጉድለት የሌለበት፣ እንከን የለሽ ወይም ሙሉ መሆን ይኖርበታል። w19.02 3 አን. 3

ሰኞ፣ ጥቅምት 5

ሕግህን ምንኛ ወደድኩ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ።—መዝ. 119:97

ልባችንን ለመጠበቅ በምሳሌያዊ ሁኔታ የልባችንን በር በመዝጋት መጥፎ ተጽዕኖዎችን መከላከላችን ብቻ በቂ አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የልባችንን በር በመክፈት በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድሩብንን ነገሮች ማስገባትም ይኖርብናል። ዙሪያቸውን በታጠሩ ጥንታዊ ከተማዎች ውስጥ በር ጠባቂዎቹ የጠላት ወረራን ለመከላከል የከተማዋን በሮች ይዘጉ ነበር፤ ሆኖም በሌሎች ጊዜያት የከተማዋን በሮች ከፍተው ምግብና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ማስገባት ይኖርባቸዋል። በሮቹ ሁሌም ዝግ ከሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ለረሃብ መዳረጋቸው አይቀርም። እኛም በተመሳሳይ የአምላክ አስተሳሰብ ለሚያሳድረው በጎ ተጽዕኖ ምንጊዜም ልባችንን ክፍት ማድረግ ይኖርብናል። መጽሐፍ ቅዱስ የይሖዋን አስተሳሰብ ይዟል፤ በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ባነበብን ቁጥር የይሖዋ አስተሳሰብ በእኛ አስተሳሰብ፣ ስሜትና ድርጊት ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ እንፈቅድለታለን። ታዲያ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን የተሻለ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ጸሎት በይሖዋ ቃል ውስጥ ያሉትን አስደናቂ ነገሮች አጥርተን ለማየት ያስችለናል። (መዝ. 119:18) በተጨማሪም ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል ይኖርብናል። ስንጸልይ፣ ስናነብና ስናሰላስል የአምላክ ቃል ‘ልባችን ውስጥ’ ዘልቆ ስለሚገባ የይሖዋን አስተሳሰብ ይበልጥ እየወደድነው እንሄዳለን።—ምሳሌ 4:20-22፤ w19.01 18 አን. 14-15

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 6

የውዳሴ መሥዋዕት ዘወትር ለአምላክ እናቅርብ።—ዕብ. 13:15

ይሖዋ እያንዳንዳችን ያለንበት ሁኔታና ችሎታችን እንደሚለያይ ያውቃል፤ በመሆኑም እንደ አቅማችን የምናቀርበውን መሥዋዕት ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። አምላክ እስራኤላውያን እንዲያቀርቡ ይጠብቅባቸው የነበረውን መሥዋዕት እንደ ምሳሌ እንመልከት። አንዳንድ እስራኤላውያን የበግ ጠቦት ወይም ፍየል የማቅረብ አቅም ነበራቸው። ሆኖም አንድ ድሃ እስራኤላዊ “ሁለት ዋኖሶችን ወይም ሁለት የርግብ ጫጩቶችን” መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ይችል ነበር። ሁለት ወፎችን ማቅረብ የማይችል እስራኤላዊ ደግሞ “አንድ አሥረኛ ኢፍ የላመ ዱቄት” እንዲያቀርብ ይፈቀድለት ነበር። (ዘሌ. 5:7, 11) የዱቄት መሥዋዕት ከሌሎቹ መሥዋዕቶች አንጻር ሲታይ ዋጋው ዝቅተኛ ነው፤ ሆኖም ዱቄቱ “የላመ” ማለትም ምርጥ ተደርጎ የሚቆጠር የዱቄት ዓይነት እስከሆነ ድረስ መሥዋዕቱ በይሖዋ ዘንድ ከፍ ተድርጎ ይታይ ነበር። ደግ የሆነው አምላካችን ዛሬም በዚህ ረገድ ያለው አመለካከት አልተቀየረም። ሐሳብ በምንሰጥበት ወቅት ሁላችንም እንደ አጵሎስ ጥሩ የመናገር ተሰጥኦ ወይም እንደ ጳውሎስ ሌሎችን የማሳመን ችሎታ እንዲኖረን አይጠብቅብንም። (ሥራ 18:24፤ 26:28) ይሖዋ የሚጠብቅብን የአቅማችንን ያህል ሆኖም ምርጣችንን እንድንሰጠው ብቻ ነው። ሁለት ትናንሽ ሳንቲሞች የሰጠችውን መበለት አስታውሱ። በይሖዋ ዓይን ከፍ ተደርጋ የታየችው ምርጧን ስለሰጠች ነው።—ሉቃስ 21:1-4፤ w19.01 8-9 አን. 3-5

ረቡዕ፣ ጥቅምት 7

በስሜ የተነሳም ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል።—ማቴ. 10:22

የክርስቶስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን ሰዎች እንደሚጠሉን እንጠብቃለን። ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት ደቀ መዛሙርቱ ከባድ ስደት እንደሚደርስባቸው አስቀድሞ ተናግሯል። (ማቴ. 24:9፤ ዮሐ. 15:20) የኢሳይያስ ትንቢት ተቃዋሚዎቻችን እኛን በመጥላት ብቻ እንደማይመለሱ ከዚህ ይልቅ እኛን ለማጥቃት የተለያዩ መሣሪያዎችን እንደሚጠቀሙ አስጠንቅቋል። እነዚህ መሣሪያዎች መሠሪ ማታለያዎችን፣ ዓይን ያወጡ ውሸቶችንና ከባድ ስደትን ያካትታሉ። (ማቴ. 5:11) ጠላቶቻችን እኛን ለመውጋት እነዚህን መሣሪያዎች እንዳይጠቀሙ ይሖዋ አይከለክላቸውም። (ኤፌ. 6:12፤ ራእይ 12:17) ሆኖም መፍራት አይኖርብንም። ይሖዋ እኛን ለማጥቃት የተሠራ ‘ማንኛውም መሣሪያ እንደሚከሽፍ’ ተናግሯል። (ኢሳ. 54:17) አንድ ግንብ፣ አውዳሚ ከሆነ ውሽንፍር እንደሚከልል ሁሉ ይሖዋም ‘ከጨቋኞች ቁጣ’ ይከልለናል። (ኢሳ. 25:4, 5) ጠላቶቻችን በእኛ ላይ ዘላቂ ጉዳት ለማድረስ የሚያደርጉት ጥረት ሁሉ ይከሽፋል። (ኢሳ. 65:17) የአምላክን ሕዝቦች የሚቃወሙ ሁሉ “እንዳልነበሩ ይሆናሉ፤ ይጠፋሉም።”—ኢሳ. 41:11, 12፤ w19.01 6-7 አን. 13-16

ሐሙስ፣ ጥቅምት 8

የይሖዋ መንፈስ ባለበት ደግሞ ነፃነት አለ።—2 ቆሮ. 3:17

ወጣቶች፣ ይሖዋ ነፃነትን ይወዳል፤ እናንተንም የፈጠራችሁ ነፃነትን እንድትወዱ አድርጎ ነው። ያም ቢሆን ነፃነታችሁን ኃላፊነት እንደሚሰማችሁ በሚያሳይ መንገድ እንድትጠቀሙበት ይፈልጋል፤ ይህ ደግሞ ለእናንተም ጥበቃ ያስገኝላችኋል። የብልግና ምስሎችን የሚመለከቱ፣ የፆታ ብልግና የሚፈጽሙ፣ አደገኛ በሆኑ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች የሚካፈሉ ወይም አደንዛዥ ዕፆችንና የአልኮል መጠጦችን አላግባብ የሚጠቀሙ ሌሎች ወጣቶችን ታውቁ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ እነዚህ ወጣቶች ለአጭር ጊዜ ያህል ደስታ ሊያገኙ ይችላሉ። ሆኖም በዚህ መልኩ የሚገኘው ደስታ አብዛኛውን ጊዜ ከፍተኛ ዋጋ ያስከፍላቸዋል፤ ለበሽታ፣ ለሱስ አልፎ ተርፎም ለሞት ሊዳረጉ ይችላሉ። (ገላ. 6:7, 8) አዎ፣ እነዚህ ሰዎች ነፃነት ያገኙ ይምሰላቸው እንጂ ራሳቸውን እያታለሉ ነው። (ቲቶ 3:3) በአንጻሩ ደግሞ በመጽሐፍ ቅዱስ መሥፈርቶች ለመመራት ጥረት በማድረጋቸው ምክንያት የታመሙ ምን ያህል ሰዎች ታውቃላችሁ? ይሖዋን መታዘዝ ጤናማ ሕይወት ለመምራትና ነፃነት ለማግኘት እንደሚያስችል ምንም ጥርጥር የለውም። (መዝ. 19:7-11) በተጨማሪም ነፃነታችሁን በጥበብ ስትጠቀሙበት ማለትም ፍጹም በሆኑት የአምላክ ሕጎችና መሠረታዊ ሥርዓቶች ስትመሩ እምነት የሚጣልባችሁ ሰዎች እንደሆናችሁ እንዲሁም ተጨማሪ ነፃነት ሊሰጣችሁ እንደሚችል ለአምላክም ሆነ ለወላጆቻችሁ ታሳያላችሁ።—ሮም 8:21፤ w18.12 22-23 አን. 16-17

ዓርብ፣ ጥቅምት 9

ሰው ከአባቱና ከእናቱ ይለያል፤ ከሚስቱም ጋር ይጣበቃል። ሁለቱም አንድ ሥጋ ይሆናሉ።—ዘፍ. 2:24

አዳም የሠራው ኃጢአት በጋብቻ ዝግጅት ላይ አንዳንድ ለውጦችን እንዳስከተለ እናውቃለን። ከእነዚህ ለውጦች መካከል አንዱ ሞት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ክርስቲያኖች በሙሴ ሕግ ሥር እንዳልሆኑ ባብራራበት ወቅት የጻፈው ሐሳብ እንደሚያሳየው ሞት የጋብቻ ጥምረት እንዲፈርስ ያደርጋል። በመሆኑም በሕይወት ያለው ወገን ድጋሚ የማግባት ነፃነት ይኖረዋል። (ሮም 7:1-3) አምላክ ለእስራኤል ብሔር የሰጠው ሕግ ጋብቻን አስመልክቶ ዝርዝር ጉዳዮችን ይዟል። ለምሳሌ አምላክ ለእስራኤላውያን ሕጉን ከመስጠቱ በፊትም እንኳ ከአንድ በላይ የማግባት ልማድ ተስፋፍቶ ነበር። ሕጉ ይህ ልማድ እንዲቀጥል ቢፈቅድም እንዲህ ባሉ ትዳሮች ውስጥ ሴቶችና ልጆች ጥቃት እንዳይደርስባቸው ከለላ ያደርግ ነበር። ለምሳሌ አንድ እስራኤላዊ አንዲትን ባሪያ ሚስቱ አድርጎ ቢወስድና ከጊዜ በኋላ ሁለተኛ ሚስት ቢያገባ የመጀመሪያ ሚስቱ ምግቧ፣ ልብሷና የጋብቻ መብቷ እንዳይጓደልባት የማድረግ ግዴታ ነበረበት። አምላክ፣ ጥበቃ እንዲያደርግላትና እንዲንከባከባት ይጠብቅበት ነበር። (ዘፀ. 21:9, 10) እኛ በሕጉ ሥር ባንሆንም ይሖዋ ለጋብቻ ያለውን አመለካከት ከዚህ መረዳት እንችላለን። ይህን ማወቃችን ለጋብቻ ዝግጅት አክብሮት እንድናሳይ አያደርገንም? w18.12 10 አን. 3፤ 11 አን. 5-6

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 10

እናንተ ቢነገራችሁም እንኳ [አታምኑትም]።—ዕን. 1:5

ዕንባቆም ያስጨነቀውንና ያሳሰበውን ነገር ለይሖዋ ከተናገረ በኋላ ይሖዋ ምን እርምጃ እንደሚወስድ ለማወቅ ጓጉቶ መሆን አለበት። ይሖዋ ልክ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት ስሜታችንን ስለሚረዳ ዕንባቆም የተሰማውን ቅሬታ በመግለጹ አልገሠጸውም። ዕንባቆም ይህን ጩኸት ያሰማው ከደረሰበት ሥቃይና ሐዘን የተነሳ እንደሆነ ተረድቶለት ነበር። በተጨማሪም ይሖዋ ታማኝ ያልሆኑት አይሁዳውያን በቅርቡ ምን እንደሚያጋጥማቸው ለዕንባቆም ገለጸለት። እንዲያውም በወቅቱ የነበሩት ዓመፀኛ ሰዎች በቅርቡ እንደሚጠፉ ለመጀመሪያ ጊዜ የነገረው ለዕንባቆም ሳይሆን አይቀርም። ይሖዋ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁ እንደሆነ ለዕንባቆም ገልጾለታል። ያ ዓመፀኛና ክፉ ትውልድ ከቅጣት አያመልጥም። ይሖዋ “በዘመናችሁ” የሚለውን አገላለጽ በመጠቀም ፍርዱ በዕንባቆም አሊያም በወቅቱ በነበሩት እስራኤላውያን ዘመን መፈጸሙ እንደማይቀር ጠቁሟል። ይሁንና ይሖዋ የሚወስደው እርምጃ ዕንባቆም ከጠበቀው ፈጽሞ የተለየ ነበር። ይሖዋ የነገረው ነገር በመላው ይሁዳ ላይ የከፋ መከራ እንደሚመጣ የሚጠቁም ነበር። w18.11 15 አን. 7-8

እሁድ፣ ጥቅምት 11

[የአምላክ] ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።—1 ጢሞ. 2:4

አንተስ እውነትን ገና ላልሰሙት የተለያዩ ዓይነት ሰዎች ምን አመለካከት አለህ? ሐዋርያው ጳውሎስ ምን እንዳደረገ እስቲ እንመልከት፤ ጳውሎስ ስለ አምላክ መጠነኛ እውቀት ላላቸው ሰዎች ለመስበክ ወደ ምኩራቦች የሄደ ቢሆንም ምሥራቹን የተናገረው ለአይሁዳውያን ብቻ አልነበረም። ለምሳሌ በመጀመሪያው የሚስዮናዊ ጉዞው ወቅት ሊቃኦናውያን እሱና በርናባስ ያከናወኑትን ነገር ሲያዩ፣ ሄርሜስና ዙስ የተባሉት የሐሰት አምላኮቻቸው በሰው አምሳል ሆነው እንደወረዱ ተሰምቷቸው ነበር። ታዲያ ጳውሎስና በርናባስ እንዲህ ያለ ክብር ሲሰጣቸው ምን አደረጉ? ከዚያ በፊት በሰበኩባቸው ሁለት ከተሞች ካጋጠማቸው ስደት ትንሽ እፎይ የሚሉበት አጋጣሚ እንዳገኙ ተሰምቷቸው ይሆን? እንዲህ ያለ ትኩረት የተሰጣቸው መሆኑ ምሥራቹን ይበልጥ ለማስፋፋት እንደሚረዳቸው አስበው ይሆን? በጭራሽ! ልብሳቸውን ቀደው እየሮጡ ወደ ሕዝቡ መሃል በመግባት “እንዲህ የምታደርጉት ለምንድን ነው? እኛም እንደ እናንተው ድክመት ያለብን ሰዎች ነን” በማለት ተቃውሟቸውን አሰሙ።—ሥራ 14:8-15፤ w18.09 4-5 አን. 8-9

ሰኞ፣ ጥቅምት 12

ዓመፀኞች የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁም? . . . አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ። ሆኖም . . . ታጥባችሁ ነጽታችኋል፣ ተቀድሳችኋል እንዲሁም ጻድቃን ተብላችኋል።—1 ቆሮ. 6:9, 11

እውነትን መቀበልና በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባሉት የሥነ ምግባር መሥፈርቶች መመራት ከፈለግን በአስተሳሰባችንና በምግባራችን ላይ ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኞች መሆን አለብን። ጴጥሮስ እንዲህ ያለውን ለውጥ አስመልክቶ እንደሚከተለው ብሏል፦ “ታዛዥ ልጆች እንደመሆናችሁ መጠን ቀድሞ እውቀት ባልነበራችሁ ጊዜ ትከተሉት በነበረው ምኞት መሠረት መቀረጻችሁን አቁሙ፤ ከዚህ ይልቅ . . . በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።” (1 ጴጥ. 1:14, 15) በሥነ ምግባር ባዘቀጠችው በቆሮንቶስ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች እውነትን ለመግዛት ሲሉ በአኗኗራቸው ላይ ትልቅ ለውጥ ማድረግ አስፈልጓቸው ነበር። በዛሬው ጊዜም ቢሆን በርካታ ሰዎች እውነትን ለመግዛት ሲሉ አምላክን የማያስደስቱ ምግባሮችን መተው አስፈልጓቸዋል። ጴጥሮስ በዘመኑ ለነበሩ ክርስቲያኖች የሚከተለውን ማሳሰቢያም ሰጥቷቸዋል፦ “ዓይን ባወጣ ምግባር፣ ልቅ በሆነ የሥጋ ፍላጎት፣ ከልክ በላይ በመጠጣት፣ መረን በለቀቀ ድግስ፣ በመጠጥ ግብዣዎችና በአስጸያፊ የጣዖት አምልኮ በመካፈል የአሕዛብን ፈቃድ የፈጸማችሁበት ያለፈው ጊዜ ይበቃል።”—1 ጴጥ. 4:3፤ w18.11 6 አን. 13

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 13

ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው ሁሉ አማኞች ሆኑ።—ሥራ 13:48

“ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” እነማን እንደሆኑ ማወቅ የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማወቅ የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች ያደርጉ እንደነበረው ምሥክርነት መስጠት ነው። በመሆኑም ኢየሱስ “በምትገቡበት ማንኛውም ከተማ ወይም መንደር መልእክቱን መስማት የሚገባውን ሰው ፈልጉ” በማለት የሰጠውን ትእዛዝ ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። (ማቴ. 10:11) ቅን ልቦና የሌላቸው፣ ኩሩ ወይም መንፈሳዊ ፍላጎት የሌላቸው ሰዎች ለምሥራቹ በጎ ምላሽ እንዲሰጡ አንጠብቅም። የምንፈልገው ሐቀኛ፣ ትሑትና መንፈሳዊ ነገሮችን የተጠሙ ሰዎችን ነው። ይህን ፍለጋ ኢየሱስ የአናጺነት ሥራውን ሲያከናውን አድርጎት ሊሆን ከሚችለው ነገር ጋር ልናመሳስለው እንችላለን፤ በመጀመሪያ የቤት ዕቃ፣ በር፣ ቀንበር ወይም ሌሎች ነገሮችን ለመሥራት ተስማሚ የሆነውን የእንጨት ዓይነት ይፈልጋል። ከዚያ በኋላ መሣሪያዎቹንና የእንጨት ሥራ ችሎታውን ተጠቅሞ የፈለገውን ዕቃ ይሠራል። እኛም ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት ስንጥር ተመሳሳይ ነገር ማድረግ አለብን።—ማቴ. 28:19, 20፤ w18.10 12 አን. 3-4

ረቡዕ፣ ጥቅምት 14

ፊልጶስ ወደ ሰማርያ ከተማ ሄዶ ስለ ክርስቶስ ይሰብክላቸው ጀመር።—ሥራ 8:5

ወንጌላዊው ፊልጶስ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ቢኖሩም ምንጊዜም በአገልግሎት ላይ ትኩረት በማድረግ ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። ፊልጶስ በኢየሩሳሌም አዲስ የአገልግሎት መብት ተሰጥቶት ነበር። (ሥራ 6:1-6) ከዚያ ግን ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ ተለዋወጡ። የእስጢፋኖስን መገደል ተከትሎ በክርስቲያኖች ላይ ከባድ ስደት ተነሳ። በስደቱ ምክንያት የክርስቶስ ተከታዮች ከኢየሩሳሌም ወደተለያዩ ቦታዎች ተበተኑ። በዚህ ወቅት ፊልጶስ እጁን አጣጥፎ ከመቀመጥ ይልቅ በወቅቱ ምሥራቹ እምብዛም ወዳልተሰበከባት ወደ ሰማርያ ሄዶ መስበክ ጀመረ። (ማቴ. 10:5፤ ሥራ 8:1) ፊልጶስ የአምላክ መንፈስ ወደመራው ቦታ ሁሉ ለመሄድ ፈቃደኛ ስለነበር ይሖዋ አዳዲስ ክልሎችን ለመክፈት ተጠቅሞበታል። ፊልጶስ የነበረው ከአድልዎ ነፃ የሆነ አቀራረብ ሳምራውያንን ሳይማርካቸው አልቀረም፤ ምክንያቱም አይሁዳውያን ሳምራውያንን ይንቋቸው ነበር። ከዚህ አንጻር ሕዝቡ ፊልጶስን “በአንድ ልብ” ይሰማው የነበረ መሆኑ አያስገርምም! (ሥራ 8:6-8) ፊልጶስ ተለዋዋጭ ሁኔታዎች ቢኖሩም ትኩረቱ ምንጊዜም በአገልግሎቱ ላይ እንዲያርፍ አድርጎ ነበር፤ ይሖዋም እሱንና ቤተሰቡን አብዝቶ ባርኳቸዋል።—ሥራ 21:8, 9፤ w18.10 30 አን. 14-16

ሐሙስ፣ ጥቅምት 15

እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ።—ዕብ. 10:24

በአንድ ወቅት ኢየሱስ ዲካፖሊስ በተባለው ክልል እያለ ሰዎች “መስማት የተሳነውና የመናገር እክል ያለበት አንድ ሰው ወደ እሱ [አመጡ]።” (ማር. 7:31-35) ኢየሱስ ግለሰቡን የፈወሰው ሰዎቹ መሃል እያለ ሳይሆን ‘ከሕዝቡ ለይቶ ለብቻው ከወሰደው’ በኋላ ነው። እንዲህ ያደረገው ለምንድን ነው? ግለሰቡ መስማት የተሳነው በመሆኑ ብዙ ሰዎች መሃል ሲሆን ሊጨንቀው ይችላል። ኢየሱስ ሰውየውን ለብቻው ወስዶ የፈወሰው ይህን ስላስተዋለ ይሆናል። እርግጥ ነው፣ እኛ እንደ ኢየሱስ ሰዎችን በተአምር መፈወስ አንችልም። ይሁን እንጂ የእምነት አጋሮቻችን ለሚያስፈልጓቸው ነገሮችና ለስሜታቸው ትኩረት መስጠት እንችላለን፤ ደግሞም እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል። ኢየሱስ፣ መስማት የተሳነው ሰው ምን ሊሰማው እንደሚችል ስለተረዳ አሳቢነት አሳይቶታል። እኛም ለአረጋውያንና አቅመ ደካማ ለሆኑት አሳቢነት ማሳየት ይኖርብናል። የክርስቲያን ጉባኤ መለያ፣ አባላቱ ውጤታማ በሆነ መንገድ ነገሮችን ማከናወን መቻላቸው ሳይሆን በመካከላቸው ያለው ፍቅር ነው። (ዮሐ. 13:34, 35) እንዲህ ያለው ፍቅር አረጋውያንንም ሆነ የአካል ጉዳት ያለባቸውን ወንድሞቻችንን በስብሰባዎች ላይ እንዲገኙና በስብከቱ ሥራ እንዲካፈሉ ለመርዳት የራሳችንን ጥቅም መሥዋዕት እንድናደርግ ያነሳሳናል። እነዚህ ወንድሞቻችን ማከናወን የሚችሉት ነገር ውስን መሆኑ እንዲህ ከማድረግ አያግደንም።—ማቴ. 13:23፤ w18.09 29-30 አን. 7-8

ዓርብ፣ ጥቅምት 16

እያንዳንዳችን ባልንጀራችንን የሚጠቅመውንና የሚያንጸውን ነገር በማድረግ እናስደስተው።—ሮም 15:2

ይሖዋም ሆነ ኢየሱስ እያንዳንዱን በግ እጅግ ውድ እንደሆነ አድርገው ይመለከቱታል፤ ኢየሱስ ሕይወቱን እንኳ ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቶናል። (ገላ. 2:20) እኛም ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ከልባችን እንወዳቸዋለን። ርኅራኄና ፍቅር ልናሳያቸውም እንፈልጋለን። ለወንድሞቻችን የብርታት ምንጭ መሆን እንድንችል “ሰላም የሚገኝበትንና እርስ በርሳችን የምንተናነጽበትን ነገር ለማድረግ የተቻለንን ሁሉ ጥረት እናድርግ።” (ሮም 14:19) ሁላችንም ወደፊት ምድር ገነት የምትሆንበትንና ተስፋ የሚያስቆርጥ ምንም ነገር የማይኖርበትን ጊዜ እንናፍቃለን! በዚያ ጊዜ ሕመም፣ ጦርነት፣ ከአዳም የወረስነው ሞት፣ ስደት፣ የቤተሰብ ችግር እንዲሁም ሌሎች የሚያሳዝኑን ነገሮች አይኖሩም። ከሺው ዓመት በኋላ ደግሞ የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና ይደርሳሉ። የመጨረሻውን ፈተና የሚያልፉ ሰዎችን ይሖዋ አምላክ እንደ ምድራዊ ልጆቹ አድርጎ የሚቀበላቸው ከመሆኑም ሌላ “የአምላክ ልጆች የሚያገኙት ዓይነት ክብራማ ነፃነት” ያገኛሉ። (ሮም 8:21) እንግዲያው ፍቅር በማሳየት ሌሎችን ማነጻችንን እንዲሁም ይህን አስደሳች ሽልማት ሁላችንም ማግኘት እንድንችል እርስ በርስ መተጋገዛችንን እንቀጥል። w18.09 14 አን. 10፤ 16 አን. 18

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 17

ሕግህን ምንኛ ወደድኩ! ቀኑን ሙሉ አሰላስለዋለሁ።—መዝ. 119:97

የአምላክን ቃል ማጥናት፣ ላይ ላዩን ከማንበብ ወይም በጥያቄዎች መልስ ላይ ከማስመር ያለፈ ነገር ማድረግን ይጠይቃል። በምናጠናበት ወቅት ጽሑፉ ስለ ይሖዋ፣ ስለ መንገዶቹና ስለ አስተሳሰቡ ምን እንደሚያስተምረን ለመረዳት እንሞክራለን። አምላክ አንድን ነገር እንድናደርግ ያዘዘውም ሆነ እንዳናደርግ የከለከለው ለምን እንደሆነ ለማስተዋል ጥረት እናደርጋለን። በተጨማሪም በአኗኗራችንና በአስተሳሰባችን ላይ ምን ለውጥ ማድረግ እንደሚያስፈልገን እናስባለን። እርግጥ በእያንዳንዱ የጥናት ፕሮግራማችን ላይ እነዚህን ሁሉ ነጥቦች እያነሳን አናሰላስል ይሆናል፤ ሆኖም ለጥናት ከመደብነው ጊዜ ላይ ምናልባት ግማሹን፣ ባነበብነው ነገር ላይ ለማሰላሰል ብንጠቀምበት ብዙ በረከት እናገኛለን። (1 ጢሞ. 4:15) በአምላክ ቃል ላይ አዘውትረን ስናሰላስል ይሖዋ ስለተለያዩ ነገሮች ያለው አስተሳሰብ ፍጹም መሆኑን ለራሳችን ‘እናረጋግጣለን።’ ነገሮችን እሱ በሚያይበት መንገድ ማየት እንጀምራለን፤ እንዲሁም የእሱ አመለካከት ትክክል መሆኑን አምነን እንቀበላለን። አእምሯችን ‘ስለሚታደስ’ አዲስ ዓይነት አስተሳሰብ እያዳበርን እንሄዳለን። (ሮም 12:2) ቀስ በቀስ የይሖዋ ዓይነት አስተሳሰብ ይኖረናል። w18.11 24 አን. 5-6

እሁድ፣ ጥቅምት 18

እኛ ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን።—1 ቆሮ. 3:9

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ጳውሎስ ራሱንና የእምነት አጋሮቹን አስመልክቶ ሲናገር “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን” ብሏል፤ ይህን ያለው የመንግሥቱን እውነት ዘር የመዝራትና የማጠጣት ኃላፊነት ተሰጥቷቸው ስለነበር ነው። (1 ቆሮ. 3:6) እኛም በተመሳሳይ አምላክ ከሰጠን የስብከት ሥራ ጋር በተያያዘ ጊዜያችንን፣ ሀብታችንንና ኃይላችንን ምንም ሳንሰስት በልግስና በመስጠት ‘ከአምላክ ጋር አብረን መሥራት’ እንችላለን። ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ጊዜያችንንና ጉልበታችንን በልግስና መስጠታችን ታላቅ ደስታ ያስገኝልናል። ጥሩ እድገት የሚያደርጉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን የመምራት አጋጣሚ ያገኙ በርካታ ወንድሞችና እህቶች በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። ሰዎች መንፈሳዊውን እውነት ሲረዱ፣ እምነታቸው እየተጠናከረ ሲሄድ፣ በሕይወታቸው ውስጥ ለውጥ ሲያደርጉና ያገኙትን እውነት ለሌሎች ሲያካፍሉ የማየትን ያህል በጣም የሚያስደስት ነገር የለም። ኢየሱስም ቢሆን፣ እንዲሰብኩ የላካቸው 70 ደቀ መዛሙርት ባገኙት መልካም ውጤት የተነሳ ‘ደስ እያላቸው ሲመለሱ’ በማየቱ ሐሴት አድርጓል።—ሉቃስ 10:17-21፤ w18.08 20 አን. 11-12

ሰኞ፣ ጥቅምት 19

በገዛ ልቡ የሚታመን ሁሉ ሞኝ ነው።—ምሳሌ 28:26

በራሳችን ማስተዋል ከልክ በላይ መተማመን ወጥመድ ሊሆንብን ይችላል። ስለ አንድ ጉዳይ የተሟላ መረጃ ባይኖረንም እንኳ ጉዳዩን ጠንቅቀን ማወቅ እንደምንችል ይሰማን ይሆናል። የሚደርሰንን መረጃ በትክክል እንዳንገመግም እንቅፋት የሚሆንብን ሌላም ነገር አለ። በጉባኤ ውስጥ ካለ አንድ ወንድም ጋር ብዙም አንጣጣም ይሆናል። ባሉን ልዩነቶች ላይ የምናተኩር ከሆነ ወንድማችንን በጥርጣሬ ዓይን መመልከት ልንጀምር እንችላለን። በመሆኑም ይህን ወንድም በተመለከተ አንድ መጥፎ ነገር ብንሰማ፣ ምንም ሳናጣራ ወሬውን ለማመን እንፈተን ይሆናል። ነጥቡ ምንድን ነው? ስለ ወንድሞቻችን መጥፎ አመለካከት መያዛችን፣ በእውነታው ላይ ያልተመሠረተ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ እንድንደርስ ሊያደርገን ይችላል። (1 ጢሞ. 6:4, 5) ቅናትና ምቀኝነት በልባችን ውስጥ ሥር እንዲሰዱ ባለመፍቀድ የማመዛዘን ችሎታችን እንዳይዛባ መከላከል እንችላለን። እንግዲያው ለወንድሞቻችን እንዲህ ያለ መጥፎ አመለካከት ከማዳበር ይልቅ እንድንወዳቸውና ከልባችን ይቅር እንድንላቸው የተሰጠንን መመሪያ ተግባራዊ እናድርግ።—ቆላ. 3:12-14፤ w18.08 6 አን. 15፤ 7 አን. 18

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 20

ሰማያት እንዲሁም ምድርና በውስጧ ያለው ነገር ሁሉ የአምላክህ የይሖዋ ናቸው።—ዘዳ. 10:14

ሁሉም ሰዎች ወደ ሕልውና የመጡት በይሖዋ ስለሆነ የእሱ ንብረት ናቸው። (መዝ. 100:3፤ ራእይ 4:11) ሆኖም በታሪክ ዘመናት ሁሉ እንደታየው አምላክ ከሰው ልጆች መካከል ለየት ባለ መንገድ የእሱ ንብረት የሚሆኑ የተወሰኑ ሰዎችን መርጧል። ለምሳሌ ያህል፣ መዝሙር 135 በጥንቷ እስራኤል የነበሩትን ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች “ልዩ ንብረቱ” በማለት ይጠራቸዋል። (መዝ. 135:4) በተጨማሪም የሆሴዕ መጽሐፍ እስራኤላዊ ያልሆኑ አንዳንድ ሰዎች የይሖዋ ሕዝብ እንደሚሆኑ የሚገልጽ ትንቢት ይዟል። (ሆሴዕ 2:23) ይሖዋ አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰዎች ወደፊት ከክርስቶስ ጋር አብረው ከሚገዙት ሰዎች መካከል እንዲካተቱ ሲያደርግ የሆሴዕ ትንቢት ፍጻሜውን አግኝቷል። (ሥራ 10:45፤ ሮም 9:23-26) ይህ “ቅዱስ ብሔር” የይሖዋ “ልዩ ንብረት” ነው ሊባል ይችላል፤ ምክንያቱም አባላቱ በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ከመሆናቸውም ሌላ ሰማይ ላይ እንዲኖሩ የተመረጡ ናቸው። (1 ጴጥ. 2:9, 10) በዛሬው ጊዜ ካሉት ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች መካከል አብላጫውን ቁጥር ስለሚይዙት ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችስ ምን ማለት ይችላል? እነሱንም ቢሆን ይሖዋ “ሕዝቤ” እንዲሁም “የመረጥኳቸው” በማለት ጠርቷቸዋል።—ኢሳ. 65:22፤ w18.07 22 አን. 1-2

ረቡዕ፣ ጥቅምት 21

ክርስቶስ ኢየሱስ የነበረው ይህ አስተሳሰብ በእናንተም ዘንድ ይኑር፤ . . . [እሱ] ራሱን ባዶ በማድረግ የባሪያን መልክ ያዘ።—ፊልጵ. 2:5, 7

እውነተኛ ክርስቲያኖች ልግስና በማሳየት ረገድ ለሰው ልጆች ፍጹም ምሳሌ የሆነውን የክርስቶስን አርዓያ ይከተላሉ። (ማቴ. 20:28) ‘የኢየሱስን ምሳሌ በጥብቅ በመከተል ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እችላለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። (1 ጴጥ. 2:21) ስለ ሌሎች ደህንነት በማሰብና የሚያስፈልጋቸውን እርዳታ በመስጠት የይሖዋንና የክርስቶስን አርዓያ የምንከተል ከሆነ የአምላክን ሞገስ ማግኘት እንችላለን። ኢየሱስ ስለ ደጉ ሳምራዊ የተናገረው ምሳሌ፣ ተከታዮቹ ከሚጠበቅባቸው አልፈው በመሄድ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች እርዳታ እንዲያደርጉ እንደሚፈልግ በግልጽ የሚጠቁም ነው። (ሉቃስ 10:29-37) ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው ለምንድን ነው? አንድ አይሁዳዊ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” የሚል ጥያቄ ስላቀረበለት ነው። ኢየሱስ የሰጠው መልስ እኛም የአምላክን ሞገስ ማግኘት የምንፈልግ ከሆነ ልክ እንደ ሳምራዊው በልግስና ለመስጠት ፈቃደኞች መሆን እንዳለብን ያስገነዝበናል። w18.08 19 አን. 5-6

ሐሙስ፣ ጥቅምት 22

መልአኩም ገብቶ “እጅግ የተባረክሽ ሆይ፣ ሰላም ለአንቺ ይሁን፤ ይሖዋ ከአንቺ ጋር ነው” አላት።—ሉቃስ 1:28

ይሖዋ ለማርያም ቀደም ሲል እውቅና እንደሰጣት ሁሉ ልጁን በመንከባከብና በማሳደግ ላሳየችው ታማኝነትስ ተገቢውን እውቅና ይሰጣት ይሆን? እንዴታ። አምላክ፣ ማርያም ያከናወነችው ተግባርና የተናገረቻቸው ቃላት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንዲመዘገቡ አድርጓል። ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ኢየሱስ አገልግሎቱን ባከናወነበት ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ማርያም አብራው ልትጓዝ አልቻለችም። ምናልባትም መበለት ስለሆነች ከናዝሬት መውጣት አልቻለች ይሆናል። በዚህ ምክንያት ብዙ አጋጣሚዎች ያመለጧት ቢሆንም ኢየሱስ በሞተበት ጊዜ ግን ከጎኑ ነበረች። (ዮሐ. 19:26) በኋላም ከጴንጤቆስጤ ዕለት በፊት በነበሩት ቀናት በኢየሩሳሌም ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ነበረች። (ሥራ 1:13, 14) በመሆኑም በጴንጤቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ በወረደ ጊዜ እሷም በመንፈስ ተቀብታ እንደሚሆን መጠበቅ እንችላለን። ይህ ማለት ደግሞ ከኢየሱስ ጋር ለዘላለም በሰማይ አብራ የመሆን አጋጣሚ አግኝታለች ማለት ነው። በእርግጥም ማርያም በታማኝነት ላከናወነችው አገልግሎት አስገራሚ በሆነ መንገድ ወሮታ አግኝታለች! w18.07 9 አን. 11፤ 10 አን. 14

ዓርብ፣ ጥቅምት 23

ሁሉንም ነገር ለአምላክ ክብር አድርጉ።—1 ቆሮ. 10:31

ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ አንዳንድ ዝንባሌዎች ወይም ድርጊቶች የሚያስከትሉትን ውጤት እንዲገነዘቡ ለመርዳት ሲል የተለያዩ መሠረታዊ ሥርዓቶችን አስተምሯቸዋል። ለምሳሌ ቂም መያዝ የዓመፅ ድርጊት ወደመፈጸም፣ የፍትወት ስሜት ደግሞ ምንዝር ወደመፈጸም ሊመራ እንደሚችል አስተምሯል። (ማቴ. 5:21, 22, 27, 28) ሕሊናችንን በሚገባ ለማሠልጠን በአምላክ መሠረታዊ ሥርዓቶች መመራት ይኖርብናል፤ ይህም ለይሖዋ ክብር የሚያመጡ ውሳኔዎች ለማድረግ ያስችለናል። በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊና ያላቸው ሁለት ክርስቲያኖች ስለ አንድ ጉዳይ ያላቸው አመለካከት በጣም የተለያየ ሊሆን ይችላል። የአልኮል መጠጥን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። መጽሐፍ ቅዱስ በተገቢው መጠን አልኮል መጠጣትን አይከለክልም። ሆኖም ከመጠን በላይ መጠጣትንና ስካርን ያወግዛል። (ምሳሌ 20:1፤ 1 ጢሞ. 3:8) ታዲያ አንድ ክርስቲያን የአልኮል መጠጥን በተመለከተ ሊያሳስበው የሚገባው ጉዳይ ከመጠኑ አለማለፉ ብቻ ነው? በፍጹም። አንድ ክርስቲያን ሕሊናው አልኮል እንዲጠጣ ቢፈቅድለትም እንኳ የሌሎችን ሕሊና ከግምት ማስገባት ይኖርበታል። w18.06 18 አን. 10-11

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 24

ከፈሪሳውያን እርሾና ከሄሮድስ እርሾ ተጠበቁ።—ማር. 8:15

ኢየሱስ ፈሪሳውያን፣ ሰዱቃውያንና የሄሮድስ ሥርወ መንግሥት ደጋፊዎች ከሚያስፋፉት ትምህርት ወይም እርሾ እንዲጠበቁ ደቀ መዛሙርቱን አበክሮ አሳስቧቸዋል። (ማቴ. 16:6, 12) ኢየሱስ ይህን የተናገረው፣ ሕዝቡ ሊያነግሡት ከሞከሩ ብዙም ሳይቆይ መሆኑ ትኩረት የሚስብ ነው። ሃይማኖታዊ ቡድኖች በፖለቲካ ውስጥ ጣልቃ መግባታቸው በቀላሉ ዓመፅ እንዲቀሰቀስ ሊያደርግ ይችላል። ኢየሱስ፣ ደቀ መዛሙርቱ ገለልተኛ መሆን እንዳለባቸው አስተምሯል። የካህናት አለቆችና ፈሪሳውያን፣ ኢየሱስን ለመግደል እንዲነሱ ያደረጋቸው አንዱ ምክንያት ይህ ነው። እነዚህ ሰዎች፣ ሕዝቡ የኢየሱስን ትምህርት በመስማት እነሱን መከተሉን እንዳያቆም ብሎም በፖለቲካና በሃይማኖት ረገድ ያላቸውን ተሰሚነት እንዳያጡ ሰግተው ነበር። “እንዲሁ ብንተወው ሁሉም በእሱ ያምናሉ፤ ሮማውያንም መጥተው ቦታችንንና ሕዝባችንን ይወስዱብናል” በማለት ተናግረዋል። (ዮሐ. 11:48) በመሆኑም ሊቀ ካህናት የነበረው ቀያፋ፣ ኢየሱስ እንዲገደል ሴራ ጠነሰሰ።—ዮሐ. 11:49-53፤ 18:14፤ w18.06 6-7 አን. 12-13

እሁድ፣ ጥቅምት 25

ፍቅራችሁ ግብዝነት የሌለበት ይሁን።—ሮም 12:9

ሰይጣን የሚጠቀምበት አንዱ ውጤታማ ማጥመጃ፣ ሰዎች ምትሃታዊ ኃይል ስላላቸው ነገሮች የማወቅ ጉጉት እንዲያድርባቸው ማድረግ ነው። በዛሬው ጊዜ ሰይጣን፣ ሰዎች ከአጋንንት ጋር ንክኪ እንዲኖራቸው ለማድረግ በሐሰት ሃይማኖት ብቻ ሳይሆን በመዝናኛው ኢንዱስትሪም ይጠቀማል። ፊልሞች፣ የኤሌክትሮኒክ ጨዋታዎች እንዲሁም ሌሎች መዝናኛዎች መናፍስታዊ ነገሮችን አጓጊ አስመስለው ያቀርባሉ። በዚህ ወጥመድ ላለመያዝ ምን ማድረግ እንችላለን? የይሖዋ ድርጅት፣ ተቀባይነት ያላቸውንና የሌላቸውን መዝናኛዎች ዝርዝር እንዲያቀርብልን መጠበቅ የለብንም። እያንዳንዳችን ከአምላክ መሥፈርቶች ጋር የሚስማማ ምርጫ ለማድረግ ሕሊናችንን ማሠልጠን ይኖርብናል። (ዕብ. 5:14) ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠንን ከላይ የሚገኘውን ምክር በተግባር ካዋልን ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ምርጫዎች ማድረግ እንችላለን። ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን እንጠይቅ፦ ‘የመዝናኛ ምርጫዬ ግብዝ እንደሆንኩ የሚያሳይ ነው? መጽሐፍ ቅዱስን የማስጠናቸው አሊያም ተመላልሶ መጠየቅ የማደርግላቸው ሰዎች የመዝናኛ ምርጫዬን ቢያዩ ምን ይሰማቸዋል? የማስተምረውን ነገር ተግባራዊ እንደማደርግ ያስባሉ?’ የምናስተምረውን ነገር ይበልጥ በተግባር ባዋልን መጠን በሰይጣን ወጥመድ የመውደቃችን አጋጣሚ ጠባብ ይሆናል።—1 ዮሐ. 3:18፤ w18.05 25 አን. 13

ሰኞ፣ ጥቅምት 26

ከልቤ የምመኘውና ስለ እነሱ ለአምላክ ምልጃ የማቀርበው እንዲድኑ ነው።—ሮም 10:1

እኛስ የጳውሎስን አርዓያ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎችን የማግኘት ልባዊ ምኞት ለማዳበር እንጥራለን። ሁለተኛ፣ ይሖዋ ቀና አመለካከት ያላቸውን ሰዎች ልብ እንዲከፍት በጸሎት እንማጸነዋለን። (ሥራ 13:48፤ 16:14) ወደ 30 ለሚጠጉ ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለች ሲልቫና የምትባል እህት “በክልሌ ውስጥ አንድን ቤት ከማንኳኳቴ በፊት አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝ እንዲረዳኝ ወደ ይሖዋ እጸልያለሁ” ብላለች። በተጨማሪም አምላክ በመላእክቱ ተጠቅሞ ቅን ልብ ወዳላቸው ሰዎች እንዲመራን እንጸልያለን። (ማቴ. 10:11-13፤ ራእይ 14:6) ከ30 ለሚበልጡ ዓመታት በአቅኚነት ያገለገለው ሮበርት እንዲህ ብሏል፦ “ከመላእክት ጋር አብሮ መሥራት በጣም የሚያስደስት ነገር ነው፤ ምክንያቱም መላእክት፣ በምንሰብክላቸው ሰዎች ሕይወት ውስጥ ምን እየተከናወነ እንዳለ ያውቃሉ።” ሦስተኛ ደግሞ የምንሰብክላቸውን ሰዎች መልካም ጎን ለማየት ብሎም የይሖዋ አገልጋዮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ለማሰብ እንጥራለን። ካርል የተባለ የጉባኤ ሽማግሌ እንዲህ ሲል ተናግሯል፦ “አንድ ሰው ቅን ልብ እንዳለው የሚጠቁሙ ትናንሽ ነገሮችን ለምሳሌ ፊቱ ላይ ፈገግታ የሚነበብ መሆኑን፣ ወዳጃዊ ስሜት ማሳየቱን አሊያም ጥሩ ጥያቄዎችን የሚያነሳ መሆኑን ለማስተዋል እሞክራለሁ።” በእርግጥም እንደ ጳውሎስ ሁሉ እኛም በጽናት ፍሬ ማፍራት እንችላለን። w18.05 15 አን. 13፤ 16 አን. 15

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 27

እርስ በርስ እንበረታታ፤ ደግሞም ቀኑ እየቀረበ መምጣቱን ስናይ ከበፊቱ ይበልጥ ይህን እናድርግ።—ዕብ. 10:24, 25

ከዚህ ቀደም የረዳናቸው ሰዎች ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ እንዳሉ መስማታችን ከፍተኛ የብርታት ምንጭ ሊሆነን ይችላል። ሐዋርያው ዮሐንስም ተመሳሳይ ስሜት ተሰምቶት ነበር፤ “ልጆቼ በእውነት ውስጥ እየተመላለሱ መሆናቸውን ከመስማት የበለጠ ደስታ የለኝም” በማለት ጽፏል። (3 ዮሐ. 4) በርካታ አቅኚዎች ይህ እውነት መሆኑን ይመሠክራሉ፤ ከዓመታት በፊት ወደ እውነት እንዲመጡ የረዷቸው ሰዎች አሁንም ይሖዋን በታማኝነት እያገለገሉ እንዳሉ አልፎ ተርፎም አቅኚዎች እንደሆኑ መስማታቸው በጣም አበረታቷቸዋል። በተስፋ መቁረጥ ስሜት የተዋጠን አንድ አቅኚ ከዚህ በፊት በይሖዋ አገልግሎት ስላሳለፈው አስደሳች ሕይወት ማስታወሳችን በራሱ የብርታት ምንጭ ሊሆነው ይችላል። በርካታ የወረዳ የበላይ ተመልካቾችና ሚስቶቻቸው አንድን ጉባኤ ከጎበኙ በኋላ ወንድሞች የጻፉላቸው አጭር የምስጋና ደብዳቤ እንኳ ምን ያህል እንዳበረታታቸው ገልጸዋል። ሽማግሌዎች፣ ሚስዮናውያን፣ አቅኚዎችና የቤቴል ቤተሰብ አባላትም ለሚያከናውኑት የታማኝነት አገልግሎት አድናቆት ሲቸራቸው ተመሳሳይ ስሜት ይሰማቸዋል። w18.04 23 አን. 14-15

ረቡዕ፣ ጥቅምት 28

[ንጉሡ] ልቡ ከትክክለኛው መንገድ ዞር እንዳይል ለራሱ ሚስቶች አያብዛ።—ዘዳ. 17:17

ሰለሞን ይህን መመሪያ በመጣስ 700 ሴቶችን አገባ፤ በተጨማሪም 300 ቁባቶችን ለራሱ ወሰደ። (1 ነገ. 11:3) ከሚስቶቹ መካከል አብዛኞቹ እስራኤላውያን ያልሆኑና የሐሰት አማልክትን የሚያመልኩ ነበሩ። በመሆኑም ሰለሞን እስራኤላውያን የባዕድ አገር ሴቶችን እንዳያገቡ የሚከለክለውን የአምላክ ሕግም ጥሷል። (ዘዳ. 7:3, 4) ሰለሞን ቀስ በቀስ ከይሖዋ መሥፈርቶች እየራቀ መሄዱ የከፋ ኃጢአት ወደመፈጸም መርቶታል። አስታሮት ለተባለችው እንስት አምላክና ከሞሽ ለተባለው ጣዖት መሠዊያዎችን የሠራ ሲሆን በዚያም ከሚስቶቹ ጋር በጣዖት አምልኮ ተካፍሏል። ደግሞም ካልጠፋ ቦታ እነዚህን መሠዊያዎች የሠራው የይሖዋን ቤተ መቅደስ ከገነባበት ከኢየሩሳሌም ፊት ለፊት ባለ ተራራ ላይ ነው! (1 ነገ. 11:5-8፤ 2 ነገ. 23:13) ምናልባትም ሰለሞን በቤተ መቅደሱም መሥዋዕት ማቅረቡን እስከቀጠለ ድረስ ይሖዋ መጥፎ ድርጊቱን ችላ ብሎ እንደሚያልፍለት በማሰብ ራሱን አታልሎ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ይሖዋ መጥፎ ድርጊትን ፈጽሞ በቸልታ አያልፍም። w18.07 18-19 አን. 7-9

ሐሙስ፣ ጥቅምት 29

የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ማምከን የምትችሉበትን ትልቅ የእምነት ጋሻ አንሱ።—ኤፌ. 6:16

ሰይጣን ከሚያስወነጭፋቸው ‘የሚንበለበሉ ፍላጻዎች’ መካከል ስለ ይሖዋ የሚነገሩ ውሸቶች ይገኙበታል፤ ሰይጣን ይሖዋ እንደማይወዳችሁና ማንም ስለ እናንተ ግድ እንደሌለው ሊያሳምናችሁ ይፈልጋል። የአሥራ ዘጠኝ ዓመቷን ኢዳን እንደ ምሳሌ እንውሰድ፤ ኢዳ ዋጋ ቢስ እንደሆነች ይሰማታል። “ይሖዋ እንደማይቀርበኝና ወዳጄ መሆን እንደማይፈልግ ብዙ ጊዜ ይሰማኛል” ብላለች። ኢዳ፣ ሰይጣን የሚሰነዝረውን ይህን ጥቃት የምትቋቋመው እንዴት ነው? እንዲህ ስትል ተናግራለች፦ “ስብሰባዎች እምነቴን በጣም ያጠናክሩልኛል። ማንም ሰው እኔ የምሰጠውን ሐሳብ መስማት እንደማይፈልግ ስለማስብ በስብሰባዎች ላይ ምንም መልስ አልመልስም ነበር። አሁን ግን ለስብሰባዎች እዘጋጃለሁ፤ እንዲሁም ሁለት ወይም ሦስት መልስ ለመስጠት እሞክራለሁ።” የኢዳ ተሞክሮ አንድ መሠረታዊ እውነት ያስገነዝበናል፦ ወታደሮች የሚይዙት ጋሻ ቁመቱና ስፋቱ የተወሰነ ነው፤ የእምነት ጋሻችን ግን መጠኑ ሊቀንስ ወይም ሊጨምር ይችላል። ይህ እኛ በምናደርገው ጥረት ላይ የተመካ ነው። (ማቴ. 14:31፤ 2 ተሰ. 1:3) በእርግጥም እምነታችንን ለመገንባት ጥረት ማድረጋችን በጣም አስፈላጊ ነው! w18.05 29-30 አን. 12-14

ዓርብ፣ ጥቅምት 30

ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብኛል?—ሥራ 16:30

የእስር ቤቱ ጠባቂ አመለካከቱን ቀይሮ ጳውሎስና ሲላስ እንዲረዱት የጠየቀው የምድር ነውጡ ከተከሰተ በኋላ መሆኑን ልብ እንበል። (ሥራ 16:25-34) በተመሳሳይም በዛሬው ጊዜ ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ለመስማት ፈቃደኛ ያልነበሩ አንዳንድ ሰዎች፣ ሕይወታቸውን የሚያናውጥ ነገር ሲገጥማቸው አመለካከታቸውን ይቀይሩና እርዳታ ይሹ ይሆናል። ምናልባትም ለብዙ ዓመታት ከቆዩበት ሥራቸው በድንገት በመፈናቀላቸው ተደናግጠው ሊሆን ይችላል። ከባድ የጤና እክል እንዳለባቸው በማወቃቸው ግራ የተጋቡ አሊያም የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣታቸው በሐዘን የተደቆሱ ሰዎችም ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች ስለ ሕይወት ዓላማ ጥያቄ ማንሳት ሊጀምሩ ይችላሉ፤ እነዚህ ሰዎች ከዚያ በፊት ይህ ጉዳይ አሳስቧቸው አያውቅ ይሆናል። አሁን ግን ‘ለመዳን ምን ማድረግ ይኖርብኛል?’ ብለው እስከመጠየቅ ሊደርሱ ይችላሉ። እንዲህ ያሉት ሰዎች ከእኛ ጋር ሲገናኙ፣ የምንነግራቸውን ተስፋ ያዘለ መልእክት ለማዳመጥ በሕይወታቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ፈቃደኛ ሊሆኑ ይችላሉ። በስብከቱ ሥራችን በታማኝነት መቀጠላችን ሰዎች ምሥራቹን ለመስማት ፈቃደኛ በሚሆኑበት ጊዜ ማጽናኛ ለመስጠት ያስችለናል።—ኢሳ. 61:1፤ w18.05 19-20 አን. 10-12

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 31

የይሖዋ መንፈስ በእኔ ላይ ነው፤ ምክንያቱም ለድሆች ምሥራች እንድናገር ቀብቶኛል።—ሉቃስ 4:18

በዘመናችን ያሉትን አብዛኞቹን ሰዎች የዚህ ዓለም አምላክ ስላሳወራቸው የሐሰት ሃይማኖት፣ የቁሳዊ ነገሮች ምኞትና የፖለቲካው ሥርዓት ባሪያ መሆናቸውን አያስተውሉም። (2 ቆሮ. 4:4) የኢየሱስ ተከታዮች እንደመሆናችን መጠን የእሱን ምሳሌ በመከተል፣ እነዚህ ሰዎች የነፃነት አምላክ የሆነውን ይሖዋን እንዲያውቁና እንዲያመልኩ የመርዳት መብት ተሰጥቶናል። (ማቴ. 28:19, 20) በእርግጥ ይህን ተልእኮ ስንወጣ በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ስለሚያጋጥሙን ሥራው ቀላል አይደለም። በአንዳንድ አገሮች ሰዎች ለምሥራቹ ይበልጥ ግድየለሽ እየሆኑ መጥተዋል፤ ይባስ ብሎም አንዳንዶች ለመልእክቱ ጥላቻ ያሳያሉ። ያም ቢሆን ይሖዋ ምሥራቹን እንድንሰብክ ስላዘዘን ‘ነፃነቴን በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ ለመካፈል ልጠቀምበት እችላለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። በርካታ ክርስቲያኖች የዚህ ሥርዓት መጨረሻ በጣም እንደቀረበ በማስተዋላቸው በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመካፈል እንደተነሳሱ ስንመለከት ታላቅ ደስታ ይሰማናል፤ እነዚህ ክርስቲያኖች ወደ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ለመግባት ሲሉ አኗኗራቸውን ቀላል አድርገዋል። (1 ቆሮ. 9:19, 23) ብዙዎች ነፃነታቸውን በጥበብ በመጠቀም ይሖዋን በዚህ መንገድ እያገለገሉ መሆኑ ምንኛ የሚያስደስት ነው!—መዝ. 110:3፤ w18.04 11-12 አን. 13-14

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ