ጥር
ቅዳሜ፣ ጥር 1
በክርስቶስ ኢየሱስ በማመን ለመዳን የሚያበቃ ጥበብ እንድታገኝ የሚያስችሉህን ቅዱሳን መጻሕፍት ከጨቅላነትህ ጀምሮ አውቀሃል።—2 ጢሞ. 3:15
የጢሞቴዎስ እምነት የተገነባው ወደ ይሖዋ እንዲቀርብ በሚረዱት ትምህርቶች ላይ ነበር። አንተም መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ይሖዋ የሚያስተምረውን ነገር በማገናዘብ አሳማኝ መደምደሚያ ላይ መድረስ ይኖርብሃል። በመጀመሪያ ቢያንስ ሦስት መሠረታዊ እውነቶችን ለራስህ ማረጋገጥ ይኖርብሃል። አንደኛ፣ ይሖዋ አምላክ የሁሉም ነገር ፈጣሪ እንደሆነ እርግጠኛ መሆን ይኖርብሃል። (ዘፀ. 3:14, 15፤ ዕብ. 3:4፤ ራእይ 4:11) ሁለተኛ፣ መጽሐፍ ቅዱስ አምላክ በቅዱስ መንፈሱ መሪነት ለሰዎች ያስጻፈው መጽሐፍ መሆኑን ለራስህ ማረጋገጥ አለብህ። (2 ጢሞ. 3:16, 17) ሦስተኛ፣ ይሖዋ በክርስቶስ አመራር ሥር ሆነው እሱን የሚያመልኩ የተደራጁ ሕዝቦች እንዳሉትና እነሱም የይሖዋ ምሥክሮች እንደሆኑ እርግጠኛ መሆን አለብህ። (ኢሳ. 43:10-12፤ ዮሐ. 14:6፤ ሥራ 15:14) እንዲህ ለማድረግ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉንም ነገር ማወቅ አይጠበቅብህም። ዓላማህ ‘የማሰብ ችሎታህን’ ተጠቅመህ፣ እውነትን ማግኘትህን ማረጋገጥ ሊሆን ይገባል።—ሮም 12:1፤ w20.07 10 አን. 8-9
እሁድ፣ ጥር 2
አንበጦቹም ሰዎቹን እንዲገድሏቸው ሳይሆን ለአምስት ወር እንዲያሠቃዩአቸው ተፈቀደላቸው።—ራእይ 9:5
በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ትንቢት የሰው ፊት ስላላቸውና “የወርቅ አክሊሎች የሚመስሉ ነገሮች” በራሳቸው ላይ ስለጫኑ አንበጦች ይናገራል። (ራእይ 9:7) አንበጦቹ “የአምላክ ማኅተም በግንባራቸው ላይ የሌላቸውን ሰዎች” ማለትም የአምላክን ጠላቶች ለአምስት ወር (የአንድ አንበጣ አማካይ ዕድሜ ያህል ማለት ነው) እንዲያሠቃዩ ተፈቀደላቸው። (ራእይ 9:4) ይህ ትንቢት የሚገልጸው በመንፈስ ስለተቀቡት የይሖዋ አገልጋዮች መሆን አለበት። አምላክ በዚህ ክፉ ሥርዓት ላይ ያስተላለፈውን የፍርድ መልእክት በድፍረት ስለሚያውጁ የሥርዓቱን ደጋፊዎች አሠቃይተዋቸዋል ሊባል ይችላል። ታዲያ በኢዩኤል 2:7-9 ላይ የተጠቀሱት አንበጦች በራእይ መጽሐፍ ላይ ከተገለጹት አንበጦች ጋር አንድ እንዳልሆኑ እየገለጽን ነው? አዎ። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምሳሌያዊ ትርጉም ያለው አንድ ነገር በተለያዩ ሁኔታዎች ሥር የተለያዩ ነገሮችን ሊያመለክት ይችላል። ለምሳሌ፣ በራእይ 5:5 ላይ ኢየሱስ “ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ” ተብሎ የተጠራ ሲሆን በ1 ጴጥሮስ 5:8 ላይ ደግሞ ዲያብሎስ “እንደሚያገሳ አንበሳ” ተደርጎ ተገልጿል። w20.04 3 አን. 8፤ 5 አን. 10
ሰኞ፣ ጥር 3
የይሖዋ ዓይኖች በሁሉም ቦታ ናቸው፤ ክፉዎችንም ሆነ ጥሩ ሰዎችን ይመለከታሉ።—ምሳሌ 15:3
የሦራ አገልጋይ የሆነችው አጋር፣ የአብራም ሚስት ከሆነች በኋላ የሞኝነት ድርጊት ፈጽማለች። አጋር ከፀነሰች በኋላ መሃን የሆነችውን ሦራን መናቅ ጀመረች። ሁኔታዎች እየተባባሱ ሲሄዱ አጋር፣ ሦራ ባደረሰችባት ነገር የተነሳ ኮበለለች። (ዘፍ. 16:4-6) ፍጹማን ባለመሆናችን አጋር ትዕቢተኛ ሴት እንደሆነችና የእጇን እንዳገኘች ይሰማን ይሆናል። ይሖዋ ግን ስለ አጋር እንዲህ አልተሰማውም። እንዲያውም መልአኩን ላከላት። መልአኩ ወደ አጋር መጥቶ አመለካከቷን እንድታስተካክል ረዳት፤ እንዲሁም ባረካት። አጋር፣ ይሖዋ እንደሚመለከታትና ያለችበትን ሁኔታ ሙሉ በሙሉ እንደሚያውቅ ተገንዝባለች። በመሆኑም ስለ ይሖዋ “አንተ የምታይ አምላክ ነህ” ብላ ለመናገር ተገፋፍታለች። (ዘፍ. 16:7-13) ይሖዋ ስለ አጋር ያስተዋለው ነገር ምንድን ነው? አስተዳደጓንና የቀድሞ ሕይወቷን እንዲሁም ያጋጠማትን ነገር ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። ይሖዋ፣ አጋር ለሦራ ያሳየችውን ንቀት ችላ ብሎ ባያልፍም የአጋርን አስተዳደግና የቀድሞ ሕይወት እንዲሁም ሁኔታዋን ግምት ውስጥ እንዳስገባ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። w20.04 16 አን. 8-9
ማክሰኞ፣ ጥር 4
ሩጫውን ጨርሻለሁ።—2 ጢሞ. 4:7
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ሁሉም እውነተኛ ክርስቲያኖች በሩጫ ላይ እንዳሉ ተናግሯል። (ዕብ. 12:1) ደግሞም ወጣትም ሆንን አረጋዊ፣ ጠንካራም ሆንን ደካማ ሁላችንም ይሖዋ ያዘጋጀልንን ሽልማት ለማግኘት እስከ መጨረሻው መጽናት ይጠበቅብናል። (ማቴ. 24:13) ጳውሎስ በተሳካ ሁኔታ ‘ሩጫውን ስለጨረሰ’ የመናገር ነፃነት ነበረው። (2 ጢሞ. 4:7, 8) ይሁንና ጳውሎስ የተናገረው ስለ ምን ዓይነት ውድድር ነው? ጳውሎስ አንዳንድ አስፈላጊ ትምህርቶችን ለማስተላለፍ በጥንቷ ግሪክ የሚካሄዱ ስፖርቶችን እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። (1 ቆሮ. 9:25-27፤ 2 ጢሞ. 2:5) በአንዳንድ ቦታዎች ላይ፣ የክርስትና ሕይወትን ከሩጫ ውድድር ጋር አመሳስሎታል። (1 ቆሮ. 9:24፤ ገላ. 2:2፤ ፊልጵ. 2:16) አንድ ሰው በዚህ “ውድድር” ላይ መሳተፍ የሚጀምረው ራሱን ለይሖዋ ወስኖ ሲጠመቅ ነው። (1 ጴጥ. 3:21) ሩጫውን የሚያጠናቅቀው ደግሞ ይሖዋ የዘላለም ሕይወት ሽልማት ሲሰጠው ነው።—ማቴ. 25:31-34, 46፤ 2 ጢሞ. 4:8፤ w20.04 26 አን. 1-3
ረቡዕ፣ ጥር 5
ከአምላክ የሚገኘውን ሙሉ የጦር ትጥቅ አንሱ።—ኤፌ. 6:13
“ጌታ . . . ታማኝ ነው፤ እሱ ያጠነክራችኋል፤ እንዲሁም ከክፉው ይጠብቃችኋል።” (2 ተሰ. 3:3) ይሖዋ የሚጠብቀን እንዴት ነው? ይሖዋ ከሰይጣን ጥቃቶች ሊጠብቀን የሚችል የጦር ትጥቅ አዘጋጅቶልናል። (ኤፌ. 6:13-17) ይህ መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ ጠንካራና ውጤታማ ነው! ሆኖም የጦር ትጥቁ ጥበቃ የሚያደርግልን እያንዳንዱን ክፍል ከለበስነው እና ካላወለቅነው ነው። ለምሳሌ ያህል፣ የእውነት ቀበቶ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች ያመለክታል። ይህን ቀበቶ መታጠቅ ያለብን ለምንድን ነው? ምክንያቱም ሰይጣን “የውሸት አባት” ነው። (ዮሐ. 8:44) በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲዋሽ ስለኖረ በውሸት የተካነ ነው፤ ‘መላውን ዓለምም አሳስቷል!’ (ራእይ 12:9) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውነት ግን እንዳንታለል ይጠብቀናል። ታዲያ ይህን ምሳሌያዊ ቀበቶ መታጠቅ የምንችለው እንዴት ነው? ስለ ይሖዋ እውነቱን በመማር፣ እሱን “በመንፈስና በእውነት” በማምለክ እንዲሁም በሁሉም ነገር በሐቀኝነት በመኖር ነው።—ዮሐ. 4:24፤ ኤፌ. 4:25፤ ዕብ. 13:18፤ w21.03 26-27 አን. 3-5
ሐሙስ፣ ጥር 6
ውብ ወደሆነችውም ምድር ይገባል።—ዳን. 11:41
ይህችን ምድር ልዩ ያደረጋት የእውነተኛው አምልኮ ማዕከል የነበረች መሆኗ ነው። በ33 ዓ.ም. ከተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ወዲህ ግን ይህች “ምድር” ቃል በቃል አንድን ቦታ ልታመለክት አትችልም፤ ምክንያቱም የይሖዋ ሕዝቦች የሚገኙት በመላው ዓለም ነው። በዛሬው ጊዜ፣ ‘ውብ የሆነችው ምድር’ የሚለው አገላለጽ የይሖዋን ሕዝቦች መንፈሳዊ ግዛት የሚያመለክት ነው፤ ይህ መንፈሳዊ ግዛት፣ የይሖዋ ሕዝቦች በስብሰባዎችና በመስክ አገልግሎት ላይ ለይሖዋ የሚያቀርቡትን አምልኮ ያጠቃልላል። በመጨረሻዎቹ ቀናት፣ የሰሜኑ ንጉሥ በተደጋጋሚ ጊዜያት ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ ገብቷል። በናዚዎች ይመራ የነበረው የጀርመን መንግሥት የሰሜን ንጉሥ በነበረበት ወቅት የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ መመልከት ይቻላል፤ ይህ የሰሜን ንጉሥ በተለይ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የአምላክን ሕዝቦች በማሳደድና በመግደል ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ ገብቷል። ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ የሰሜን ንጉሥ የሆነው ሶቪየት ኅብረትም ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ ገብቷል፤ ይህን ያደረገው የአምላክን ሕዝቦች በማሳደድ እና በግዞት እንዲሄዱ በማድረግ ነው። w20.05 13 አን. 7-8
ዓርብ፣ ጥር 7
ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የሚኖራቸው እሱን የሚፈሩ ሰዎች ናቸው፤ ቃል ኪዳኑንም ያሳውቃቸዋል።—መዝ. 25:14
በቅድመ ክርስትና ዘመን የኖሩ አንዳንድ የአምላክ ወዳጆችን እስቲ እንመልከት። አብርሃም አስደናቂ እምነት ያሳየ ሰው ነበር። አብርሃም ከሞተ ከ1,000 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ይሖዋ ስለ እሱ ሲናገር “ወዳጄ” ብሎታል። (ኢሳ. 41:8) ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ሞትም እንኳ ቢሆን ይሖዋን ከቅርብ ወዳጆቹ ሊለየው አይችልም። በይሖዋ ፊት አብርሃም ሕያው ነው። (ሉቃስ 20:37, 38) ሌላው ምሳሌ ደግሞ ኢዮብ ነው። መላእክት በሰማይ በተሰበሰቡበት ጉባኤ ፊት ይሖዋ ስለ ኢዮብ በልበ ሙሉነት ተናግሯል። ይሖዋ ኢዮብን “በንጹሕ አቋም የሚመላለስ ቅን ሰው እንዲሁም አምላክን የሚፈራና ከክፋት የራቀ” በማለት ጠርቶታል። (ኢዮብ 1:6-8) ዳንኤል ደግሞ ባዕድ አምልኮ በተስፋፋበት አገር ወደ 80 ለሚጠጉ ዓመታት አምላክን በታማኝነት አገልግሏል። ታዲያ ይሖዋ እሱን በተመለከተ ምን ተሰምቶታል? መላእክት በዕድሜ ለገፋው ለዳንኤል ተገልጠው በአምላክ ዘንድ ‘እጅግ የተወደደ’ እንደሆነ ሦስት ጊዜ ነግረውታል። (ዳን. 9:23፤ 10:11, 19) ይሖዋ በሞት ያንቀላፉ ወዳጆቹን የሚያስነሳበትን ጊዜ እንደሚናፍቅ በእርግጠኝነት መናገር እንችላለን።—ኢዮብ 14:15፤ w20.05 26-27 አን. 3-4
ቅዳሜ፣ ጥር 8
ሥርዓትህን አስተምረኝ።—መዝ. 119:68
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ስለ አምላክ ሕግጋት ጥሩ ግንዛቤ ሊኖረው ሌላው ቀርቶ ለእነዚህ ሕግጋት አድናቆት ሊያዳብር ይችላል። ይሁንና ተማሪው ለይሖዋ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ እሱን ይታዘዛል? ሔዋን የአምላክን ሕግ ታውቅ እንደነበር እናስታውስ፤ ሆኖም እሷም ሆነች አዳም ሕጉን ለሰጣቸው አምላክ እውነተኛ ፍቅር አልነበራቸውም። (ዘፍ. 3:1-6) ይህ ሁኔታ እኛም ስለ አምላክ የጽድቅ መሥፈርቶችና ደንቦች ከማስተማር ያለፈ ነገር ማድረግ እንደሚጠበቅብን ይጠቁማል። የይሖዋ መሥፈርቶችና ደንቦች ተወዳጅና ጠቃሚ ናቸው። (መዝ. 119:97, 111, 112) ይሁን እንጂ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን ለአምላክ ትእዛዛት እንዲህ ያለ አመለካከት እንዲያዳብሩ ይሖዋ ሕጎቹን የሰጠን በፍቅር ተነሳስቶ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። ስለዚህ ጥናቶቻችንን እንዲህ ብለን ልንጠይቃቸው እንችላለን፦ “አምላክ አገልጋዮቹን እንዲህ እንዲያደርጉ ያዘዛቸው ወይም እንዲህ እንዳያደርጉ የከለከላቸው ለምን ይመስልሃል? ይህስ ስለ አምላክ ባሕርይ ምን ያስተምረናል?” ጥናቶቻችንን ስለ ይሖዋ እንዲያስቡ እንዲሁም ለክብራማ ስሙ እውነተኛ ፍቅር እንዲያድርባቸው ከረዳናቸው ልባቸውን መንካት እንችል ይሆናል። በዚህ መንገድ የአምላክን ሕግጋት ብቻ ሳይሆን ሕጉን የሰጠውን አካልም እንዲወዱት መርዳት እንችላለን። እምነታቸው እየተጠናከረ እንዲሄድና እንደ እሳት ያሉ ፈተናዎችን በጽናት መቋቋም እንዲችሉ እንረዳቸዋለን።—1 ቆሮ. 3:12-15፤ w20.06 10 አን. 10-11
እሁድ፣ ጥር 9
ሰው ሁሉ ለመስማት የፈጠነ፣ ለመናገር የዘገየ . . . መሆን አለበት።—ያዕ. 1:19
የቀዘቀዘ ሰው በመንፈሳዊ ለማገገም ጊዜ ስለሚወስድበት ትዕግሥተኛ መሆን ይጠበቅብናል። ቀዝቅዘው የነበሩ በርካታ ወንድሞችና እህቶች፣ ወደ ጉባኤው መመለስ የቻሉት ሽማግሌዎችና ሌሎች የጉባኤው አስፋፊዎች በተደጋጋሚ ከረዷቸው በኋላ እንደሆነ ተናግረዋል። በደቡብ ምሥራቅ እስያ የምትኖር ናንሲ የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “በጉባኤ ውስጥ ያለች አንዲት የቅርብ ወዳጄ በጣም ረድታኛለች። እንደ ታላቅ እህቷ በማየት ፍቅር አሳይታኛለች። ከዚህ ቀደም ያሳለፍናቸውን አስደሳች ጊዜያት እንዳስታውስ ረዳችኝ። ስሜቴን አውጥቼ ስናገር በትዕግሥት ታዳምጠኝ ነበር፤ ምክር በሚያስፈልገኝ ጊዜ ደግሞ ይህን ከማድረግ ወደኋላ አትልም። እውነተኛ ወዳጅ ሆናልኛለች፤ በማንኛውም ጊዜ እኔን ለመርዳት ዝግጁ ነበረች።” ቁስልን እንደሚጠግን ቅባት ሁሉ የሌሎችን ስሜት መረዳትም የተጎዳ ልብን ይፈውሳል። አንዳንድ የቀዘቀዙ አስፋፊዎች በጉባኤ ውስጥ ባለ ሰው ቅር ተሰኝተው ሊሆን ይችላል፤ ከዓመታት በኋላም ይህ ስሜት አልጠፋ ይሆናል። ይህም ወደ ይሖዋ እንዳይመለሱ እንቅፋት ሆኖባቸዋል። ሌሎች ደግሞ ፍትሕ የጎደለው ድርጊት እንደተፈጸመባቸው ይሰማቸው ይሆናል። በመሆኑም የሚያዳምጣቸውና ስሜታቸውን የሚረዳላቸው ሰው ይፈልጋሉ። w20.06 26 አን. 10-11
ሰኞ፣ ጥር 10
ክፉውን [አሸንፋችሁታል]።—1 ዮሐ. 2:14
የሚያጋጥመንን ፈተና በተቋቋምን ቁጥር ትክክለኛውን ነገር ማድረግ ቀላል እየሆነልን ይሄዳል። ደግሞም ዓለም ስለ ፆታ ሥነ ምግባር ያለው የተዛባ አመለካከት የሚመነጨው ከሰይጣን እንደሆነ አንርሳ። በመሆኑም የዓለምን አመለካከት ስንቃወም ‘ክፉውን እያሸነፍን’ ነው። ይሖዋ የትኞቹ ድርጊቶች ኃጢአት እንደሆኑ የመወሰን መብት እንዳለው እንገነዘባለን። እንዲሁም ኃጢአት ላለመሥራት የቻልነውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን። ሆኖም ኃጢአት ከሠራን በደላችንን ለይሖዋ በጸሎት እንናዘዛለን። (1 ዮሐ. 1:9) ከባድ ኃጢአት ከፈጸምን ደግሞ ይሖዋ እኛን እንዲንከባከቡ የሾማቸውን ሽማግሌዎች እርዳታ እንጠይቃለን። (ያዕ. 5:14-16) ያም ቢሆን ቀደም ሲል በሠራናቸው ስህተቶች የተነሳ በጥፋተኝነት ስሜት መዋጥ አይኖርብንም። ለምን? ምክንያቱም አፍቃሪ አባታችን የኃጢአት ይቅርታ እንድናገኝ ሲል ልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቶናል። ይሖዋ ንስሐ የገቡ ኃጢአተኞችን ሙሉ በሙሉ ይቅር ይላል። በመሆኑም ይሖዋን በንጹሕ ሕሊና ከማገልገል ሊያግደን የሚችል አንድም ነገር የለም።—1 ዮሐ. 2:1, 2, 12፤ 3:19, 20፤ w20.07 22-23 አን. 9-10
ማክሰኞ፣ ጥር 11
የሕይወት ምንጭ ከአንተ ዘንድ ነው።—መዝ. 36:9
ይሖዋ ብቻውን የሚኖርበት ወቅት ነበር። ሆኖም ብቸኝነት ይሰማው ነበር ማለት አይደለም። ይሖዋ ምንም የሚጎድለው ነገር የለም። ያም ሆኖ አምላክ፣ በሕይወት መኖር የሚያስገኘውን ደስታ ሌሎችም እንዲቀምሱ ፈለገ። ስለዚህ በፍቅር ተነሳስቶ መፍጠር ጀመረ። (1 ዮሐ. 4:19) ይሖዋ መጀመሪያ የፈጠረው ልጁን ኢየሱስን ነው። ከዚያም በበኩር ልጁ አማካኝነት፣ የማሰብ ችሎታ ያላቸውን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መንፈሳዊ ፍጥረታት ጨምሮ ‘ሌሎች ነገሮችን በሙሉ’ ፈጠረ። (ቆላ. 1:16) ኢየሱስ ከአባቱ ጋር አብሮ የመሥራት መብት በማግኘቱ ደስተኛ ነበር። (ምሳሌ 8:30) የአምላክ ልጆች የሆኑት መላእክትም ደስተኛ እንዲሆኑ የሚያደርጋቸው ነገር ነበረ። ይሖዋ እና ዋና ሠራተኛው የሆነው ኢየሱስ፣ ሰማያትንና ምድርን ሲፈጥሩ መላእክት በቀጥታ የመመልከት አጋጣሚ አግኝተዋል። ታዲያ ይህን ሲያዩ ምን ተሰማቸው? ምድር ስትፈጠር ‘በደስታ ጮኸዋል’፤ ይሖዋ የፍጥረት ሥራው ቁንጮ የሆነውን የሰው ልጅን ጨምሮ ሌሎች ነገሮችን ሲፈጥርም ደስታቸውን ገልጸው እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። (ኢዮብ 38:7፤ ምሳሌ 8:31) እያንዳንዱ የይሖዋ የፍጥረት ሥራ የእሱን ፍቅርና ጥበብ ያሳያል።—መዝ. 104:24፤ ሮም 1:20፤ w20.08 14 አን. 1-2
ረቡዕ፣ ጥር 12
በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።—ማቴ. 24:9
ይሖዋ የፈጠረን ለሌሎች ፍቅር እንድናሳይና የመወደድ ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ነው። ስለዚህ ሌሎች ሲጠሉን ስሜታችን ይጎዳል፤ ምናልባትም ፍርሃት ሊያድርብን ይችላል። አንድ ወንድም እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የይሖዋ ምሥክር በመሆኔ ምክንያት ወታደሮች ሲደበድቡኝ፣ ሲሰድቡኝና ሲያስፈራሩኝ ፍርሃት አደረብኝ፤ እንደተዋረድኩም ተሰማኝ።” እንዲህ ያለ ጥላቻ ሲደርስብን ስሜታችን እንደሚጎዳ የታወቀ ነው። ሆኖም ዓለም የሚጠላን መሆኑ አያስገርመንም። ኢየሱስ ሰዎች እንደሚጠሉን በትንቢት ተናግሯል። ዓለም የኢየሱስን ተከታዮች የሚጠላቸው ለምንድን ነው? ምክንያቱም እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም ‘የዓለም ክፍል አይደለንም።’ (ዮሐ. 15:17-19) በመሆኑም መንግሥታትን ብናከብርም ለእነሱም ሆነ እነሱን ለሚወክሉ ምልክቶች አምልኮ አከል ክብር ለመስጠት ፈቃደኛ አይደለንም። የምናመልከው ይሖዋን ብቻ ነው። የሰው ዘርን የመግዛት መብት ያለው ይሖዋ መሆኑን እንደምንቀበል እናሳያለን፤ ሰይጣንና የእሱ ‘ዘር’ ግን አምላክ እንዲህ ያለ መብት ያለው መሆኑን አጥብቀው ይቃወማሉ። (ዘፍ. 3:1-5, 15) የሰው ልጆች ብቸኛ ተስፋ የአምላክ መንግሥት መሆኑን እንዲሁም ይህ መንግሥት በቅርቡ ተቃዋሚዎቹን በሙሉ እንደሚያደቅ እንሰብካለን። (ዳን. 2:44፤ ራእይ 19:19-21) ይህ መልእክት ለየዋሆች ምሥራች ቢሆንም ለክፉዎች ግን መጥፎ ዜና ነው። w21.03 20 አን. 1-2
ሐሙስ፣ ጥር 13
እኛ ከአምላክ ወገን መሆናችንን እናውቃለን።—1 ዮሐ. 5:19
ይሖዋ በጉባኤው ውስጥ ለክርስቲያን ሴቶች የተከበረ ቦታ ሰጥቷቸዋል። እነዚህ ሴቶች ጥበብ፣ እምነት፣ ቅንዓት፣ ድፍረትና ልግስና በማሳየት እንዲሁም መልካም ሥራዎችን በማከናወን ግሩም ምሳሌ ናቸው። (ሉቃስ 8:2, 3፤ ሥራ 16:14, 15፤ ሮም 16:3, 6፤ ፊልጵ. 4:3፤ ዕብ. 11:11, 31, 35) በተጨማሪም በየጉባኤዎቻችን በዕድሜ የገፉ በርካታ ክርስቲያኖች በመኖራቸው ደስተኞች ነን። እነዚህ በዕድሜ የገፉ ክርስቲያኖች በዕድሜ ምክንያት ከሚመጡ የተለያዩ የጤና እክሎች ጋር ይታገሉ ይሆናል። ያም ቢሆን በመስክ አገልግሎት የቻሉትን ያህል ይካፈላሉ፤ እንዲሁም አቅማቸው በፈቀደው መጠን ሌሎችን ለማበረታታትና ለማሠልጠን ጥረት ያደርጋሉ። በተጨማሪም ካካበቱት ተሞክሮ ብዙ ትምህርት ማግኘት ይቻላል። በእርግጥም እነዚህ ክርስቲያኖች በይሖዋም ሆነ በእኛ ዘንድ ውብ ናቸው። (ምሳሌ 16:31) ስለ ወጣቶቻችንም እናስብ። ሰይጣን ዲያብሎስ በሚቆጣጠረውና የእሱ የክፋት ፍልስፍናዎች በነገሡበት ዓለም ውስጥ ስለሚያድጉ ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። ሆኖም እነዚህ ወጣት ክርስቲያኖች በስብሰባዎች ላይ ሐሳብ ሲሰጡ፣ በአገልግሎት ሲካፈሉና ለሚያምኑባቸው ነገሮች በድፍረት ጥብቅና ሲቆሙ ስናይ ሁላችንም እንበረታታለን። በእርግጥም እናንተ ወጣቶች በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ አስፈላጊ ቦታ አላችሁ!—መዝ. 8:2፤ w20.08 21-22 አን. 9-11
ዓርብ፣ ጥር 14
በተኩላዎች መካከል እንዳሉ በጎች እልካችኋለሁ።—ማቴ. 10:16
መስበክ ስንጀምርና የይሖዋ ምሥክሮች መሆናችንን ስንናገር የቤተሰባችን አባላት ሊቃወሙን፣ ሌሎች የምናውቃቸው ሰዎች ሊያፌዙብን እንዲሁም ሰዎች መልእክታችንን ለመቀበል እንቢተኞች ሊሆኑ ይችላሉ፤ እነዚህ ሁኔታዎች ከማዕበል ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ታዲያ ድፍረት ማዳበር የምትችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ፣ ኢየሱስ ይህን ሥራ ከሰማይ ሆኖ መምራቱን እንደቀጠለ እርግጠኛ ሁን። (ዮሐ. 16:33፤ ራእይ 14:14-16) ሁለተኛ፣ ይሖዋ እንደሚንከባከብህ በገባው ቃል ላይ ያለህን እምነት አጠናክር። (ማቴ. 6:32-34) እምነትህ እየተጠናከረ በሄደ መጠን ይበልጥ ደፋር ትሆናለህ። ከይሖዋ ምሥክሮች ጋር መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በስብሰባዎቻቸው ላይ መገኘት እንደጀመርክ ለምታውቃቸው ሰዎችና ለቤተሰብህ አባላት ስትናገር ትልቅ እምነት አሳይተሃል! የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች ለመከተል ስትል በምግባርህና በባሕርይህ ላይ ትልቅ ለውጥ እንዳደረግክም ጥያቄ የለውም። ይህም ቢሆን እምነትና ድፍረት ጠይቆብሃል። ድፍረት ማዳበርህን ስትቀጥል “አምላክህ ይሖዋ በምትሄድበት ሁሉ ከአንተ ጋር [እንደሚሆን]” መተማመን ትችላለህ።—ኢያሱ 1:7-9፤ w20.09 5 አን. 11-12
ቅዳሜ፣ ጥር 15
ይሖዋ እረፍት [ሰጠው]።—2 ዜና 14:6
ንጉሥ አሳ በይሖዋ ሙሉ በሙሉ ታምኖ የጥበብ እርምጃ በመውሰድ ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆነናል። አሳ በአስቸጋሪ ጊዜም ሆነ በሰላሙ ጊዜ ይሖዋን አገልግሏል። አሳ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ “ሙሉ በሙሉ ለይሖዋ ያደረ” ሰው ነበር። (1 ነገ. 15:14 ግርጌ) አሳ ለይሖዋ ያደረ መሆኑን ያሳየበት አንዱ መንገድ የሐሰት አምልኮን ከይሁዳ ማስወገዱ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ “የባዕድ አማልክቱን መሠዊያዎችና ከፍ ያሉትን የማምለኪያ ቦታዎች አስወገደ፤ የማምለኪያ ዓምዶቹንም ሰባበረ፤ እንዲሁም የማምለኪያ ግንዶቹን ቆራረጠ” ይላል። (2 ዜና 14:3, 5) ሌላው ቀርቶ አያቱን ማአካን ከእመቤትነቷ ሽሯታል። ለምን? የጣዖት አምልኮ ታስፋፋ ስለነበር ነው። (1 ነገ. 15:11-13) አሳ የሐሰት አምልኮን በማስወገድ ብቻ አልተወሰነም። የይሁዳ ሕዝብ ወደ ይሖዋ እንዲመለስ በመርዳት ንጹሑን አምልኮ አስፋፍቷል። ይሖዋም አሳን እና እስራኤላውያንን ሰላም በመስጠት ባርኳቸዋል። በአሳ የግዛት ዘመን ለአሥር ዓመት ያህል “ምድሪቱ እረፍት አግኝታ [ነበር]።”—2 ዜና 14:1, 4, 6፤ w20.09 14 አን. 2-3
እሁድ፣ ጥር 16
ጢሞቴዎስ ሆይ፣ . . . በአደራ የተሰጠህን ነገር ጠብቅ።—1 ጢሞ. 6:20
ውድ የሆኑ ንብረቶቻችንን ለሌሎች በአደራ የምንሰጥበት ጊዜ አለ። ለምሳሌ ያህል፣ ገንዘባችንን ባንክ እናስቀምጥ ይሆናል። ይህን የምናደርገው ገንዘባችን አስተማማኝ ቦታ እንደሚቀመጥ እንዲሁም እንደማይጠፋ ወይም እንደማይሰረቅ ተማምነን ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስን ውድ የሆነ ነገር እንደተቀበለ አስታውሶታል፤ ይህ ውድ ነገር አምላክ ለሰው ልጆች ስላለው ዓላማ የሚገልጸው ትክክለኛ እውቀት ነው። በተጨማሪም ጢሞቴዎስ ‘ቃሉን የመስበክ’ እንዲሁም ‘የወንጌላዊነትን ሥራ የማከናወን’ መብት በአደራ ተሰጥቶት ነበር። (2 ጢሞ. 4:2, 5) ጢሞቴዎስ በአደራ የተሰጠውን ነገር እንዲጠብቅ ጳውሎስ ማሳሰቢያ ሰጥቶታል። እንደ ጢሞቴዎስ ሁሉ እኛም ውድ ነገሮች በአደራ ተሰጥተውናል። ይሖዋ በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለሚገኙት ውድ እውነቶች ትክክለኛ እውቀት እንድናገኝ በማድረግ ደግነት አሳይቶናል። የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ውድ ናቸው፤ ምክንያቱም ከይሖዋ ጋር ጥሩ ወዳጅነት መመሥረት የምንችለው እንዴት እንደሆነና በሕይወታችን ውስጥ እውነተኛ ደስታ ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለብን ያስተምሩናል። እነዚህን እውነቶች ስንቀበልና በሕይወታችን ውስጥ መመሪያ አድርገን ስንጠቀምባቸው፣ ባሪያ ከሚያደርጉ የሐሰት ትምህርቶችና ሥነ ምግባር የጎደላቸው ድርጊቶች ነፃ እንወጣለን።—1 ቆሮ. 6:9-11፤ w20.09 26 አን. 1-3
ሰኞ፣ ጥር 17
ለእናንተ ስንል በመካከላችሁ ምን ዓይነት ሰዎች ሆነን እንደኖርን ታውቃላችሁ።—1 ተሰ. 1:5
ጥናትህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች እንደምትወዳቸውና እንደምታምንባቸው መመልከቱ ይጠቅመዋል። ይህ እሱም የሚማረውን ነገር ይበልጥ እንዲወደው ሊረዳው ይችላል። የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ተግባራዊ ማድረግ በሕይወትህ ውስጥ እንዴት እንደጠቀመህ ልትነግረው ትችላለህ። እንዲህ ማድረግህ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው ጠቃሚ ምክር እሱንም እንደሚረዳው እንዲገነዘብ ያስችለዋል። መጽሐፍ ቅዱስን በምታጠኑበት ወቅት፣ ለጥናትህ እንደ እሱ ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጠሟቸውና እነዚህን ሁኔታዎች መቋቋም የቻሉ ሰዎችን ተሞክሮ ንገረው። በጉባኤህ ውስጥ ጥናትህን የሚጠቅም ተሞክሮ ያለው አስፋፊ ካለ በጥናቱ ላይ እንዲገኝ ጋብዘው። ጥናትህ የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወቱ ውስጥ ተግባራዊ ማድረጉ የጥበብ እርምጃ መሆኑን እንዲያስተውል እርዳው። ጥናትህ ባለትዳር ከሆነ የትዳር ጓደኛውም እያጠናች ነው? ካልሆነ ባለቤቱን በጥናቱ ላይ እንድትገኝ ጋብዛት። ጥናትህ የተማረውን ነገር ለቤተሰቦቹና ለጓደኞቹ እንዲናገር አበረታታው።—ዮሐ. 1:40-45፤ w20.10 16 አን. 7-9
ማክሰኞ፣ ጥር 18
በልጆችህ . . . ውስጥ ቅረጻቸው።—ዘዳ. 6:7
የኢየሱስ ሰብዓዊ ወላጆች ኢየሱስን የአምላክን ሞገስ በሚያስገኝለት መንገድ አሳድገውታል፤ እንዲህ ለማድረግ የረዳቸው ይሖዋ ለወላጆች የሰጠውን መመሪያ መታዘዛቸው ነው። (ዘዳ. 6:6, 7) ዮሴፍና ማርያም ለይሖዋ ጥልቅ ፍቅር ነበራቸው፤ ደግሞም ልጆቻቸው ለይሖዋ እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር እንዲያዳብሩ ለመርዳት ትልቅ ቦታ ይሰጡ ነበር። ዮሴፍና ማርያም በቤተሰብ ደረጃ ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ይዘው ለመቀጠል መርጠዋል። ቤተሰቡ በናዝሬት ባለው ምኩራብ በሚደረጉት ሳምንታዊ ስብሰባዎች ላይም ሆነ በኢየሩሳሌም በሚከበረው ዓመታዊ የፋሲካ በዓል ላይ ይገኝ እንደነበር ጥርጥር የለውም። (ሉቃስ 2:41፤ 4:16) ዮሴፍና ማርያም፣ በቤተሰብ አንድ ላይ ሆነው ወደ ኢየሩሳሌም ሲጓዙ አጋጣሚውን ለልጆቻቸው ስለ ይሖዋ ሕዝቦች ታሪክ ለማስተማር ሳይጠቀሙበት አልቀሩም፤ ምናልባትም በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ወደተጠቀሱት ቦታዎች ሲደርሱ በዚያ ስለተከናወኑት ነገሮች ነግረዋቸው ሊሆን ይችላል። የቤተሰባቸው ቁጥር እያደገ ሲሄድ ዮሴፍና ማርያም መንፈሳዊ ልማዳቸውን ይዘው መቀጠል ሊከብዳቸው እንደሚችል የታወቀ ነው። ሆኖም እንዲህ ማድረጋቸው ያስገኘላቸውን ጥቅም አስቡ! ለይሖዋ አምልኮ ቅድሚያ መስጠታቸው የቤተሰባቸው መንፈሳዊነት ተጠብቆ እንዲቀጥል ረድቷቸዋል። w20.10 28 አን. 8-9
ረቡዕ፣ ጥር 19
ዕዝራ የይሖዋን ሕግ ለመመርመር . . . እንዲሁም ሥርዓቱን . . . ለማስተማር ልቡን አዘጋጅቶ ነበር።—ዕዝራ 7:10
በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ከተጋበዝክ የምታጠኑትን ትምህርት አስቀድመህ መዘጋጀትህ ጥሩ ይሆናል። ዶሪን የተባለ ልዩ አቅኚ እንዲህ ብሏል፦ “ጥናት የጋበዝኩት ሰው ለጥናቱ ተዘጋጅቶ ሲመጣ ደስ ይለኛል። እንዲህ ማድረጉ በጥናቱ ላይ ጠቃሚ ሐሳቦችን ለመስጠት ይረዳዋል።” በተጨማሪም ጥናቱ ሁለታችሁም በደንብ እንደተዘጋጃችሁ ማስተዋሉ አይቀርም፤ ይህ ደግሞ ለእሱም ጥሩ ምሳሌ ይሆነዋል። ትምህርቱን በጥልቀት መዘጋጀት ባትችልም እንኳ ጥቂት ጊዜ ወስደህ ዋና ዋናዎቹን ነጥቦች ለማግኘት መሞከርህ ጠቃሚ ነው። ጸሎት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ወሳኝ ክፍል ነው። ስለዚህ አስጠኚው እንድትጸልይ ቢጠይቅህ ምን ብለህ እንደምትጸልይ አስቀድመህ አስብ። እንዲህ ካደረግክ ጸሎትህ ይበልጥ ትርጉም ያለው ይሆናል። (መዝ. 141:2) በጃፓን የምትኖረው ሃናኤ ከአስጠኚዋ ጋር አብራ ትመጣ የነበረች እህት ታቀርበው የነበረውን ጸሎት ታስታውሳለች። እንዲህ ብላለች፦ “ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዳላት ስላስተዋልኩ እኔም እንደ እሷ ለመሆን ፈለግኩ። ስሜን እየጠቀሰች መጸለይዋም እንደምወደድ እንዲሰማኝ ያደርገኝ ነበር።” w21.03 9-10 አን. 7-8
ሐሙስ፣ ጥር 20
አትፍራ! . . . በሮምም ልትመሠክርልኝ ይገባል።—ሥራ 23:11
ኢየሱስ፣ በሰላም ሮም እንደሚደርስ ለሐዋርያው ጳውሎስ አረጋግጦለት ነበር። ሆኖም በኢየሩሳሌም ያሉ አንዳንድ አይሁዳውያን አድብተው በጳውሎስ ላይ ጥቃት ለመሰንዘርና እሱን ለመግደል አሲረው ነበር። የሮም ሠራዊት ሻለቃ የሆነው ቀላውዴዎስ ሉስዮስ ሴራቸውን ሲሰማ ጳውሎስን ለማዳን እርምጃ ወሰደ። ቀላውዴዎስ ወዲያውኑ ጳውሎስን ከኢየሩሳሌም ወደ ቂሳርያ ላከው፤ እሱን እንዲጠብቁትም ብዙ ወታደሮች አብረውት እንዲሄዱ አደረገ። እዚያም አገረ ገዢው ፊሊክስ፣ ጳውሎስ “[በሄሮድስ] ቤተ መንግሥት ውስጥ በጥበቃ ሥር ሆኖ እንዲቆይ አዘዘ።” በዚህ መንገድ ጳውሎስ ሊገድሉት ከሚፈልጉት ሰዎች አመለጠ። (ሥራ 23:12-35) ሆኖም አገረ ገዢው ፊሊክስ በፊስጦስ ተተካ። “በአይሁዳውያን ዘንድ ተወዳጅነት ማትረፍ [የሚፈልገው]” ፊስጦስ ጳውሎስን “ወደ ኢየሩሳሌም ወጥተህ ስለዚህ ጉዳይ እዚያ እኔ ባለሁበት መዳኘት ትፈልጋለህ?” ሲል ጠየቀው። ጳውሎስ ወደ ኢየሩሳሌም ቢሄድ ሊገደል እንደሚችል ያውቃል። ስለዚህ “ወደ ቄሳር ይግባኝ ብያለሁ!” አለ። በዚህ ጊዜ ፊስጦስ “ወደ ቄሳር ይግባኝ ስላልክ ወደ ቄሳር ትሄዳለህ” ሲል መለሰለት። ብዙም ሳይቆይ ጳውሎስ ሮም ይደርሳል፤ በመሆኑም ሊገድሉት የሚፈልጉት አይሁዳውያን ሊያገኙት አይችሉም።—ሥራ 25:6-12፤ w20.11 13 አን. 4፤ 14 አን. 8-10
ዓርብ፣ ጥር 21
ልባችን እኛን [ይኮንነናል]።—1 ዮሐ. 3:20
ሁላችንም አልፎ አልፎ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማናል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች እውነትን ከመስማታቸው በፊት ባደረጓቸው ነገሮች የተነሳ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማቸዋል። ሌሎች ደግሞ እንዲህ የሚሰማቸው ከተጠመቁ በኋላ በፈጸሟቸው ስህተቶች የተነሳ ነው። (ሮም 3:23) ማናችንም ብንሆን ትክክለኛውን ነገር ማድረግ እንደምንፈልግ የታወቀ ነው። ሆኖም “ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን።” (ያዕ. 3:2፤ ሮም 7:21-23) የጥፋተኝነት ስሜት ደስ የሚል ነገር ባይሆንም ጠቃሚ የሚሆንበት ጊዜ አለ። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? የጥፋተኝነት ስሜት አካሄዳችንን እንድናስተካክልና ስህተታችንን ላለመድገም እንድንጥር ስለሚያነሳሳን ነው። (ዕብ. 12:12, 13) በሌላ በኩል ግን ንስሐ ከገባንና ይሖዋ ይቅር እንዳለን ካሳየን በኋላም እንኳ የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማን ይሆናል፤ ይህ ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ነው። እንዲህ ያለው የጥፋተኝነት ስሜት ጎጂ ነው። (መዝ. 31:10፤ 38:3, 4) ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ወጥመድ እንዳይሆንብን እንጠንቀቅ። ደግሞም ይሖዋ በእኛ ተስፋ ሳይቆርጥ እኛ በራሳችን ተስፋ ቆርጠን እሱን ማገልገላችንን ብናቆም ሰይጣን ምን ያህል እንደሚደሰት አስበው!—ከ2 ቆሮንቶስ 2:5-7, 11 ጋር አወዳድር፤ w20.11 27 አን. 12-13
ቅዳሜ፣ ጥር 22
በእርግጥም ልቤን ያነጻሁት፣ ንጹሕ መሆኔንም ለማሳየት እጄን የታጠብኩት በከንቱ ነው።—መዝ. 73:13
ሌዋዊው መዝሙራዊ በክፉዎችና በእብሪተኞች መቅናት ጀምሮ ነበር፤ የቀናው በክፋታቸው ሳይሆን የተሻለ ሕይወት ያላቸው ስለመሰለው ነው። (መዝ. 73:2-9, 11-14) ሀብትና ጥሩ ሕይወት ያላቸው እንዲሁም ምንም ጭንቀት የሌለባቸው፣ በአጭር አነጋገር ሁሉ ነገር የተሳካላቸው ይመስላሉ። ሌዋዊው ያደረበትን ቅናትና የተስፋ መቁረጥ ስሜት ለማስወገድ ጉዳዩን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ማየት ነበረበት። እንዲህ ሲያደርግ ውስጣዊ ሰላሙንና ደስታውን መልሶ ማግኘት ችሏል። ‘በምድር ላይ ከይሖዋ ሌላ የምሻው የለም’ በማለት ተናግሯል። (መዝ. 73:25) እኛም የተሳካላቸው በሚመስሉ ክፉ ሰዎች ፈጽሞ መቅናት አይኖርብንም። ደስታቸው ዘላቂና እውነተኛ አይደለም፤ እንዲሁም የዘላለም ሕይወት አያገኙም። (መክ. 8:12, 13) በእነሱ መቅናት፣ ተስፋ እንድንቆርጥና ለመንፈሳዊ አደጋ እንድንዳረግ ያደርገናል። በመሆኑም ክፉዎች ስኬታማ በመምሰላቸው ምክንያት መቅናት ከጀመርን ሌዋዊው የወሰደውን ዓይነት እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ፍቅር የሚንጸባረቅበትን የአምላክን ምክር መታዘዝና የይሖዋን ፈቃድ ከሚያደርጉ ሰዎች ጋር መቀራረብ አለብን። ከምንም ነገር በላይ ይሖዋን የምንወደው ከሆነ እውነተኛ ደስታ እናገኛለን። እንዲሁም “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” በሚያስገኝልን ጎዳና ላይ መጓዛችንን እንቀጥላለን።—1 ጢሞ. 6:19፤ w20.12 19 አን. 14-16
እሁድ፣ ጥር 23
ምን ብለን መጸለይ እንዳለብን ግራ የምንጋባበት ጊዜ ሊኖር ይችላል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመንና ስሜታችንን በቃላት መግለጽ ተስኖን ስንቃትት መንፈስ ራሱ ስለ እኛ ይማልዳል።—ሮም 8:26
ለይሖዋ በጸሎት የሚያስጨንቃችሁን ነገር ስትገልጹ እሱን ማመስገንም አትርሱ። አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ባለንበት ወቅትም እንኳ ይሖዋ ያደረገልንን ነገር መቁጠራችን ይጠቅመናል። አንዳንድ ጊዜ በጣም ከመጨነቃችሁ የተነሳ ስሜታችሁን አውጥታችሁ መግለጽ ያቅታችሁ ይሆናል፤ በዚህ ጊዜ ‘ይሖዋ፣ እባክህ እርዳኝ!’ ብላችሁ ብቻ እንኳ ብትጸልዩ መልስ እንደሚሰጣችሁ አትርሱ። (2 ዜና 18:31) በራሳችሁ ሳይሆን በይሖዋ ጥበብ ታመኑ። በስምንተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ዓ.ዓ. የይሁዳ ነዋሪዎች አሦራውያን ጥቃት ይሰነዝሩብናል ብለው ሰግተው ነበር። በአሦራውያን ቀንበር ሥር ላለመውደቅ ሲሉ አረማዊ የሆነችውን የግብፅን እርዳታ ጠየቁ። (ኢሳ. 30:1, 2) ሆኖም ይሖዋ፣ ይህ አካሄዳቸው ለጥፋት እንደሚዳርጋቸው አስጠንቅቋቸው ነበር። (ኢሳ. 30:7, 12, 13) ይሖዋ እውነተኛ ደህንነት ሊያገኙ የሚችሉበትን መንገድ በኢሳይያስ በኩል ጠቆማቸው። “ሳትረበሹ፣ [በይሖዋ] ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ” አላቸው።—ኢሳ. 30:15ለ፤ w21.01 3-4 አን. 8-9
ሰኞ፣ ጥር 24
የታተሙትን ሰዎች ቁጥር ሰማሁ፤ ቁጥራቸው 144,000 [ነበር]።—ራእይ 7:4
የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች በሰማይ ከእሱ ጋር ነገሥታትና ካህናት ሲሆኑ፣ ላሳዩት ታማኝነት ወሮታ ያገኛሉ። (ራእይ 20:6) በሰማይ ያሉት የይሖዋ ቤተሰብ አባላት በሙሉ 144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ሽልማታቸውን የሚያገኙበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ፣ ነገሥታትና ካህናት ስለሚሆኑት 144,000 ሰዎች ከተናገረ በኋላ አንድ አስደናቂ ነገር ይኸውም አርማጌዶንን በሕይወት የሚያልፉትን “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ተመለከተ። ይህ ቡድን፣ ዮሐንስ መጀመሪያ ካየው ቡድን በቁጥር በጣም ይበልጣል፤ ቁጥሩም የተገደበ አይደለም። (ራእይ 7:9, 10) የዚህ ቡድን አባላት “ነጭ ልብስ” ለብሰዋል፤ ይህም ‘ከሰይጣን ዓለም እድፍ ራሳቸውን እንደጠበቁ’ እንዲሁም ለአምላክና ለክርስቶስ ታማኝ ሆነው እንደኖሩ የሚጠቁም ነው። (ያዕ. 1:27) በታላቅ ድምፅ እየጮሁ፣ መዳን ያገኙት ይሖዋና የአምላክ በግ የሆነው ኢየሱስ ባደረጉላቸው ነገር የተነሳ እንደሆነ ተናግረዋል። በተጨማሪም የዘንባባ ዝንጣፊዎች ይዘዋል፤ ይህም ኢየሱስ በይሖዋ የተሾመ ንጉሥ እንደሆነ በደስታ መቀበላቸውን ያሳያል።—ከዮሐንስ 12:12, 13 ጋር አወዳድር። w21.01 15-16 አን. 6-7
ማክሰኞ፣ ጥር 25
ትሕትናህ . . . ታላቅ ያደርገኛል።—2 ሳሙ. 22:36
አንድ ወንድ፣ ይሖዋና ኢየሱስ የራስነት ሥልጣናቸውን በመጠቀም ረገድ የተዉትን ግሩም ምሳሌ በመከተል ጥሩ የቤተሰብ ራስ መሆን ይችላል። የይሖዋን ትሕትና እንደ ምሳሌ እንመልከት። ይሖዋ ከማንም በላይ ጥበበኛ ነው፤ ያም ቢሆን የአገልጋዮቹን ሐሳብ ያዳምጣል። (ዘፍ. 18:23, 24, 32) ይሖዋ ፍጹም ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ከእኛ ፍጽምናን አይጠብቅም። ከዚህ ይልቅ ፍጹማን ያልሆንን የሰው ልጆች እንዲሳካልን ይረዳናል። (መዝ. 113:6, 7) እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ይሖዋ ‘ረዳት’ ተብሎ ተገልጿል። (መዝ. 27:9፤ ዕብ. 13:6) ንጉሥ ዳዊት፣ ታላቅ ነገር ማከናወን የቻለው በይሖዋ ትሕትና እንደሆነ ተናግሯል። ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ እንመልከት። ለደቀ መዛሙርቱ ጌታቸው ቢሆንም እግራቸውን አጥቧል። ኢየሱስ ራሱ “እኔ እንዳደረግኩላችሁ እናንተም እንደዚሁ እንድታደርጉ አርዓያ ሆኜላችኋለሁ” ብሏል። (ዮሐ. 13:12-17) ኢየሱስ ከፍተኛ ሥልጣን የነበረው ቢሆንም ሌሎች እንዲያገለግሉት አልጠበቀም። እንዲያውም እሱ ራሱ ሌሎችን አገልግሏል።—ማቴ. 20:28፤ w21.02 3-4 አን. 8-10
ረቡዕ፣ ጥር 26
የወጣቶች ክብር ጉልበታቸው ነው።—ምሳሌ 20:29
ወጣት ወንድሞች፣ በጉባኤ ውስጥ ልታከናውኑ የምትችሉት ብዙ ነገር አለ። ብዙዎቻችሁ ጥንካሬና ጉልበት አላችሁ። ለጉባኤያችሁ ውድ ሀብት ናችሁ። ምናልባትም የጉባኤ አገልጋይ ሆናችሁ ለመሾም ትጓጉ ይሆናል። ሆኖም ሌሎች እንደ ልጅ አድርገው እንደሚመለከቷችሁ ሊሰማችሁ ይችላል፤ ወይም ደግሞ ‘ኃላፊነት ለመቀበል እንዳልደረስኩ አድርገው ይመለከቱኛል’ ብላችሁ ታስቡ ይሆናል። ይሁንና ገና ልጅ ብትሆኑም እንኳ በጉባኤያችሁ ውስጥ ያሉትን ወንድሞችና እህቶች አመኔታና አክብሮት ለማትረፍ በአሁኑ ወቅት ልታደርጉ የምትችሏቸው ነገሮች አሉ። ወጣቶች፣ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ወንድሞችንና እህቶችን የሚጠቅም ክህሎት አላችሁ? ብዙዎቻችሁ እንዲህ ያለ ችሎታ አላችሁ። ለምሳሌ አንዳንድ አረጋውያን ለግል ጥናት ወይም ለጉባኤ ስብሰባዎች ታብሌታቸውን ወይም የኤሌክትሮኒክ መሣሪያዎቻቸውን እንዴት መጠቀም እንደሚችሉ የሚያሳያቸው ቢያገኙ ደስ ይላቸዋል። ከእነዚህ መሣሪያዎች ጋር በተያያዘ ያላችሁ እውቀት አረጋውያን ወንድሞቻችንን በጣም ይጠቅማቸዋል። በምታደርጉት ነገር ሁሉ የሰማዩ አባታችሁ የሚኮራባችሁ ሰዎች ለመሆን ጥረት አድርጉ። w21.03 2 አን. 1, 3፤ 7 አን. 18
ሐሙስ፣ ጥር 27
እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል።—ገላ. 6:5
አንዲት ሚስት ከባሏ የበለጠ እውቀት ቢኖራትም እንኳ በቤተሰብ አምልኮና በሌሎች ቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ቤተሰቡን የመምራት ኃላፊነት የባልየው ነው። (ኤፌ. 6:4) አንዲት ሚስት ለባሏ መገዛት ቢጠበቅባትም መንፈሳዊነቷን መንከባከብ የራሷ ኃላፊነት ነው። ይህን ለማድረግ ደግሞ ለግል ጥናትና ለማሰላሰል የሚሆን ጊዜ መመደብ ይኖርባታል። ይህም ለይሖዋ ያላትን ፍቅርና አክብሮት ጠብቃ ለመኖር እንዲሁም ለባሏ በደስታ ለመገዛት ይረዳታል። ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው ምንጊዜም ለባሎቻቸው ለመገዛት ጥረት የሚያደርጉ ሚስቶች ደስታና እርካታ ይኖራቸዋል፤ ይሖዋ ላቋቋመው የራስነት ሥርዓት አክብሮት የሌላቸው ሰዎች ግን እንዲህ ዓይነት ደስታ የላቸውም። ለባሎቻቸው የሚገዙ ሚስቶች ለወጣት ወንዶችም ሆነ ለወጣት ሴቶች ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። በቤተሰባቸው ውስጥ ብቻ ሳይሆን በጉባኤው ውስጥም ፍቅርና ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። (ቲቶ 2:3-5) በዛሬው ጊዜ ካሉት የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች መካከል አብላጫውን ቦታ የሚይዙት ሴቶች ናቸው።—መዝ. 68:11፤ w21.02 13 አን. 21-23
ዓርብ፣ ጥር 28
ወደ አምላክ ቅረቡ፤ እሱም ወደ እናንተ ይቀርባል።—ያዕ. 4:8
ሐዋርያው ጳውሎስ ድፍረትና ጽናት በማሳየት ረገድ ግሩም ምሳሌ ትቷል። ድካም የተሰማው ጊዜ ነበር። ሆኖም ይሖዋ የሚያስፈልገውን ኃይል እንደሚሰጠው ይተማመን ነበር፤ በመሆኑም ይሖዋ በሰጠው ኃይል መጽናት ችሏል። (2 ቆሮ. 12:8-10፤ ፊልጵ. 4:13) እኛም የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልገን በትሕትና አምነን ከተቀበልን እንዲህ ዓይነቱን ጥንካሬና ድፍረት ማግኘት እንችላለን። (ያዕ. 4:10) የሚደርሱብን ፈተናዎች ይሖዋ እየቀጣን እንዳለ የሚያሳዩ ነገሮች እንዳልሆኑ እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ እንዲህ የሚል ዋስትና ሰጥቶናል፦ “ማንም ሰው ፈተና ሲደርስበት ‘አምላክ እየፈተነኝ ነው’ አይበል። አምላክ በክፉ ነገር ሊፈተን አይችልምና፤ እሱ ራሱም ማንንም በክፉ ነገር አይፈትንም።” (ያዕ. 1:13) ይህን እውነታ አምነን ከተቀበልን አፍቃሪ ወደሆነው የሰማዩ አባታችን ይበልጥ እንቀርባለን። ይሖዋ “አይለዋወጥም።” (ያዕ. 1:17) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችን ፈተናዎችን እንዲቋቋሙ እንደረዳቸው ሁሉ በዛሬው ጊዜም እያንዳንዳችንን ይረዳናል። እንግዲያው ጥበብ፣ እምነትና ድፍረት እንዲሰጣችሁ ይሖዋን አጥብቃችሁ ለምኑት። ለጸሎታችሁ መልስ ይሰጣችኋል። w21.02 31 አን. 19-21
ቅዳሜ፣ ጥር 29
ብረት ብረትን እንደሚስል ሁሉ ሰውም ጓደኛውን ይስለዋል።—ምሳሌ 27:17
በስብሰባዎች ላይ ለሚገኝ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ትኩረት በመስጠት ጥናቱን ልታበረታታው ትችላለህ። (ፊልጵ. 2:4) እስካሁን ላደረጋቸው ለውጦች አመስግነው፤ እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ እንዴት እየሄደ እንዳለ፣ ስለ ቤተሰቡና ስለ ሥራው ጠይቀው፤ እርግጥ እንዲህ ስታደርግ በግል ጉዳዩ ውስጥ ጣልቃ መግባት የለብህም። ከጥናቱ ጋር የምታደርገው ጭውውት ይበልጥ እንድትቀራረቡ ሊረዳችሁ ይችላል። ጥናቱን ጓደኛ ማድረግህ እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ ሊረዳው ይችላል። ተማሪው እድገትና ለውጥ ማድረጉን ሲቀጥል የጉባኤው ክፍል እንደሆነ እንዲሰማው ልንረዳው ይገባል። ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ እንግዳ ተቀባይ መሆን ነው። (ዕብ. 13:2) ጥናቱ አስፋፊ ከሆነ በኋላ ደግሞ አብሮን እንዲያገለግል ልንጋብዘው እንችላለን። በብራዚል የሚኖር ዲዬጎ የተባለ አስፋፊ እንዲህ ብሏል፦ “ብዙ ወንድሞች አብሬያቸው እንዳገለግል ጋብዘውኛል። ይህም ከእነሱ ጋር በደንብ ለመተዋወቅ የሚያስችል ጥሩ አጋጣሚ ፈጥሮልኛል። ይበልጥ በተዋወቅኳቸው መጠን ከእነሱ ብዙ ትምህርት አገኘሁ። ከይሖዋና ከኢየሱስ ጋርም ይበልጥ እንደተቀራረብኩ ተሰማኝ።” w21.03 12 አን. 15-16
እሁድ፣ ጥር 30
ለማንም በክፉ ፋንታ ክፉ አትመልሱ።—ሮም 12:17
ኢየሱስ ለተከታዮቹ ጠላቶቻቸውን እንዲወዱ አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 5:44, 45) ይሁንና እንዲህ ማድረግ ቀላል ነው? በፍጹም! ሆኖም በአምላክ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ ጠላቶቻችንን መውደድ እንችላለን። የአምላክ መንፈስ የሚያፈራው ፍሬ ፍቅርን እንዲሁም ትዕግሥትን፣ ደግነትን፣ ገርነትንና ራስን መግዛትን ያካትታል። (ገላ. 5:22, 23) እነዚህ ባሕርያት ጥላቻን ለመቋቋም ይረዱናል። ብዙ ተቃዋሚዎች የይሖዋ ምሥክር የሆነው የትዳር ጓደኛቸው፣ ልጃቸው ወይም ጎረቤታቸው እነዚህን ግሩም ባሕርያት በማሳየቱ የተነሳ አመለካከታቸውን ቀይረዋል። እንዲያውም ብዙ ተቃዋሚዎች ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሆነዋል። ስለዚህ የይሖዋ አገልጋይ በመሆንህ ብቻ የሚጠሉህን ሰዎች መውደድ ከከበደህ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት ጸልይ። (ሉቃስ 11:13) እንዲሁም አምላክን መታዘዝ ምንጊዜም ከሁሉ የተሻለው አካሄድ እንደሆነ ሙሉ እምነት ይኑርህ። (ምሳሌ 3:5-7) ጥላቻ ኃይል እንዳለውና ጎጂ እንደሆነ ግልጽ ነው። ሆኖም የፍቅር ኃይል በእጅጉ ይበልጣል። ፍቅር የሰዎችን ልብ ይገዛል። እንዲሁም የይሖዋን ልብ ያስደስታል። ይሁንና ተቃዋሚዎች እኛን መጥላታቸውን ባያቆሙም ደስተኞች መሆን እንችላለን። w21.03 23 አን. 13፤ 24 አን. 15, 17
ሰኞ፣ ጥር 31
ኃያል የሆነና የሕዝቡ ብዛት ስፍር ቁጥር የሌለው ብሔር ምድሬን ወሮታል።—ኢዩ. 1:6
ነቢዩ ኢዩኤል ትንቢት የተናገረው ስለ ወታደራዊ ጥቃት ነው። (ኢዩ. 2:1, 8, 11) ይሖዋ ‘ታላቅ ሠራዊቱን’ (የባቢሎን ወታደሮችን) ተጠቅሞ ዓመፀኛ የሆኑ እስራኤላውያንን እንደሚቀጣ ገልጾ ነበር። (ኢዩ. 2:25) ወራሪው ኃይል ‘የሰሜኑ ሠራዊት’ መባሉ የተገባ ነው፤ ምክንያቱም ባቢሎናውያኑ እስራኤልን የሚወሩት ከሰሜን መጥተው ነው። (ኢዩ. 2:20) ይህ ሠራዊት በደንብ ከተደራጀ የአንበጣ መንጋ ጋር ተመሳስሏል። ኢዩኤል ስለ ሠራዊቱ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እያንዳንዱ [ወታደር] መንገዱን ይዞ ይገሰግሳል። . . . ወደ ከተማዋ እየተጣደፉ ይገባሉ፤ . . . ቤቶችም ላይ ይወጣሉ፤ እንደ ሌባ በመስኮት ይገባሉ።” (ኢዩ. 2:8, 9) እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሳል ሞክር። ሁሉም ቦታ ወታደሮች አሉ። ከእነሱ መደበቅ የሚቻልበት ቦታ የለም። ከባቢሎናውያን ሰይፍ የሚያመልጥ አንድም ሰው የለም! ባቢሎናውያን (ወይም ከለዳውያን) በ607 ዓ.ዓ. ልክ እንደ አንበጣ ኢየሩሳሌምን ወረሯት። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የሚገኘው ዘገባ እንዲህ ይላል፦ “[የከለዳውያን] ንጉሥ . . . ለወጣቱም ሆነ ለድንግሊቱ፣ ለሽማግሌውም ሆነ ለአቅመ ደካማው አልራራም።”—2 ዜና 36:17፤ w20.04 5 አን. 11-12