የካቲት
ማክሰኞ፣ የካቲት 1
ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ።—ፊልጵ. 2:3
ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን በደንብ እወቋቸው። ከስብሰባ በፊትና በኋላ ከእነሱ ጋር ተጨዋወቱ፤ አብራችሁ አገልግሉ፤ እንዲሁም የሚቻል ከሆነ ቤታችሁ ጋብዟቸው። እንዲህ ስታደርጉ፣ የማትቀረብ የምትመስላችሁ እህት ዓይን አፋር እንደሆነች፣ ቁሳዊ ነገር እንደሚወድ የሚሰማችሁ ወንድም ለጋስ እንደሆነ ወይም ደግሞ ብዙ ጊዜ ስብሰባ ላይ አርፍዶ የሚገኝ አንድ ቤተሰብ ተቃውሞን እየተቋቋመ እንደሆነ ልትገነዘቡ ትችላላችሁ። (ኢዮብ 6:29) እርግጥ ነው፣ ‘በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ መግባት’ የለብንም። (1 ጢሞ. 5:13) ያም ቢሆን ስለ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንዲሁም በባሕርያቸው ላይ ተጽዕኖ ስላሳደሩት ነገሮች በተወሰነ መጠንም ቢሆን ማወቃችን ጠቃሚ ነው። አንድ የእምነት አጋራችሁ የሚያበሳጫችሁ ከሆነ ስለ አስተዳደጉና ስለ ቀድሞ ሕይወቱ ማወቃችሁ እንድታዝኑለት ሊረዳችሁ ይችላል። ወንድሞቻችሁን በደንብ ማወቅ የምትችሉት ጥረት ካደረጋችሁ ብቻ እንደሆነ አይካድም። ሆኖም መጽሐፍ ቅዱስ ልባችንን ወለል አድርገን እንድንከፍት የሚሰጠውን ምክር ተግባራዊ የምታደርጉ ከሆነ ‘ሁሉንም ዓይነት ሰዎች’ የሚወደውን ይሖዋን መምሰል ትችላላችሁ።—1 ጢሞ. 2:3, 4፤ 2 ቆሮ. 6:11-13፤ w20.04 16-17 አን. 10-12
ረቡዕ፣ የካቲት 2
ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ ከሚሰጥ ሰው የበለጠ ፍቅር ያለው ማንም የለም።—ዮሐ. 15:13
ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ደቀ መዛሙርቱን እርስ በርሳቸው እንዲዋደዱ አሳስቧቸዋል። ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማዳበራቸው አንድነታቸውን ለመጠበቅና የዓለምን ጥላቻ ለመቋቋም እንደሚረዳቸው ያውቅ ነበር። በተሰሎንቄ የነበረውን ጉባኤ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ጉባኤው ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ የጉባኤው አባላት ስደት ይደርስባቸው ነበር። ሆኖም በዚያ የነበሩት ወንድሞችና እህቶች፣ በሚያሳዩት ጽናትና ፍቅር ምሳሌ ሆነዋል። (1 ተሰ. 1:3, 6, 7) ጳውሎስ እነዚህን ክርስቲያኖች “ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ” ፍቅር ማሳየታቸውን እንዲቀጥሉ አበረታቷቸዋል። (1 ተሰ. 4:9, 10) ፍቅር የተጨነቁትን ለማጽናናትና ደካሞችን ለመደገፍ ያነሳሳቸዋል። (1 ተሰ. 5:14) እነዚህ ክርስቲያኖች የጳውሎስን ምክር በተግባር አውለዋል። በመሆኑም ጳውሎስ ከአንድ ዓመት ገደማ በኋላ በጻፈላቸው ሁለተኛ ደብዳቤ ላይ “ሁላችሁም እርስ በርስ የምታሳዩት ፍቅር እየጨመረ [መጥቷል]” ሊላቸው ችሏል። (2 ተሰ. 1:3-5) ፍቅራቸው መከራንና ስደትን ለመቋቋም ረድቷቸዋል። w21.03 22 አን. 11
ሐሙስ፣ የካቲት 3
ከፊታችን የሚጠብቀንን ሩጫ . . . በጽናት እንሩጥ።—ዕብ. 12:1
የዘላለም ሕይወት ሽልማት ማግኘት ከፈለግን የክርስትናን ጎዳና ወይም አኗኗር መከተል አለብን። (ሥራ 20:24፤ 1 ጴጥ. 2:21) ይሁን እንጂ ሰይጣንና የእሱን ጎዳና የሚከተሉ ሰዎች በዚህ ውሳኔያችን አይደሰቱም፤ ‘ከእነሱ ጋር መሮጣችንን እንድንቀጥል’ ይፈልጋሉ። (1 ጴጥ. 4:4) እኛ የምንከተለውን የሕይወት ጎዳና የሚያጣጥሉ ሲሆን የእነሱ መንገድ የተሻለ እንደሆነና ወደ ነፃነት እንደሚመራ ይናገራሉ። ሆኖም ይህ ውሸት ነው። (2 ጴጥ. 2:19) በእርግጥም ትክክለኛውን ጎዳና ለመከተል መምረጣችን በጣም አስፈላጊ ነው! ሰይጣን ሁላችንም ‘ወደ ሕይወት በሚወስደው’ ቀጭን መንገድ ላይ መሮጣችንን አቁመን አብዛኛው የዓለም ሕዝብ ወደሚሄድበት ሰፊ መንገድ እንድንገባ ይፈልጋል። ሰፊው መንገድ በብዙዎች ዘንድ የሚመረጥና ምቹ ነው። ሆኖም ‘የሚወስደው ወደ ጥፋት’ ነው። (ማቴ. 7:13, 14) በትክክለኛው ጎዳና ላይ መሮጣችንን መቀጠልና ወደ ሌላኛው ጎዳና እንዳንሳብ ከፈለግን በይሖዋ መታመንና እሱን ማዳመጥ ይኖርብናል። w20.04 26 አን. 1፤ 27 አን. 5, 7
ዓርብ፣ የካቲት 4
ምልጃ፣ [ጸሎትና] ልመና . . . እንዲቀርብ አሳስባለሁ፤ . . . ይህም ሙሉ በሙሉ ለአምላክ በማደርና ሁሉንም ነገር በትጋት በማከናወን በጸጥታና በተረጋጋ ሁኔታ መኖራችንን እንቀጥል ዘንድ ነው።—1 ጢሞ. 2:1, 2
ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ሩሲያ እና አጋሮቿ ‘ውብ ወደሆነችው ምድር’ ገብተዋል። (ዳን. 11:41) ይህን ያደረጉት እንዴት ነው? በ2017 ይህ የሰሜን ንጉሥ፣ በይሖዋ ሕዝቦች ሥራ ላይ እገዳ የጣለ ከመሆኑም ሌላ አንዳንድ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን አስሯል። ከዚህም ሌላ አዲስ ዓለም ትርጉምን ጨምሮ ጽሑፎቻችንን አግዷል። በተጨማሪም በሩሲያ የሚገኘውን ቅርንጫፍ ቢሯችንን እንዲሁም የጉባኤ ስብሰባና የትላልቅ ስብሰባ አዳራሾችን ወርሷል። ይህ ከሆነ በኋላ በ2018 የበላይ አካሉ፣ ሩሲያና አጋሮቿ የሰሜኑ ንጉሥ መሆናቸውን ግልጽ አደረገ። የይሖዋ ሕዝቦች፣ ከባድ ስደት ቢደርስባቸውም በሰብዓዊ መንግሥታት ላይ ለማመፅ ወይም እነሱን ለመገልበጥ በሚደረግ እንቅስቃሴ ለመካፈል ፈቃደኛ አይሆኑም። ከዚህ ይልቅ ‘በሥልጣን ላይ ላሉት ሁሉ’ እንድንጸልይ የሚያበረታታውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ይከተላሉ፤ በተለይም እነዚህ መንግሥታት የአምልኮ ነፃነታችንን ሊነኩ የሚችሉ ውሳኔዎች በሚያደርጉበት ወቅት እንዲህ ማድረግ አለብን። w20.05 14 አን. 9
ቅዳሜ፣ የካቲት 5
ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ።—1 ጢሞ. 4:16
ወላጆች፣ ልጆቻችሁ እውነትን እንዳገኙ እርግጠኛ እንዲሆኑ ከተፈለገ በግለሰብ ደረጃ ከአምላክ ጋር ዝምድና መመሥረት እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረው ነገር እውነት መሆኑን ማመን አለባቸው። ለልጆቻችሁ ስለ አምላክ እውነቱን ማስተማር የምትችሉት እናንተ ራሳችሁ ጥሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በመሆን ረገድ ምሳሌ ስትሆኑ ነው። በተማራችሁት ነገር ላይ ጊዜ ወስዳችሁ ማሰላሰል አለባችሁ። እንዲህ ካደረጋችሁ ልጆቻችሁም የእናንተን ምሳሌ እንዲከተሉ ማስተማር ትችላላችሁ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችሁን እንደምታሠለጥኑት ሁሉ ለልጆቻችሁም የምርምር መሣሪያዎችን አጠቃቀም ልታሠለጥኗቸው ይገባል። በዚህ መልኩ ልጆቻችሁ ለይሖዋ ፍቅር እንዲያድርባቸውና ይሖዋ መንፈሳዊ ምግብ ለማቅረብ በሚጠቀምበት መስመር ማለትም ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ እንዲተማመኑ መርዳት ትችላላችሁ። (ማቴ. 24:45-47) ለልጆቻችሁ መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶችን ብቻ በማስተማር ልትረኩ አይገባም። ዕድሜያቸውና ችሎታቸው በሚፈቅደው መጠን “የአምላክን ጥልቅ ነገሮች” በማስተማር ጠንካራ እምነት እንዲያዳብሩ እርዷቸው።—1 ቆሮ. 2:10፤ w20.07 11 አን. 10, 12-13
እሁድ፣ የካቲት 6
ይሖዋ ተንኮለኛን ሰው ይጸየፋል . . . ከቅኖች ጋር ግን የጠበቀ ወዳጅነት አለው።—ምሳሌ 3:32
በዛሬው ጊዜ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የመሠረቱ ምን ያህል ሰዎች አሉ? በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ፍጽምና የጎደላቸው ሰዎች ይህን ማድረግ ችለዋል። እነዚህ ሰዎች ከይሖዋ ጋር መወዳጀት የቻሉት በኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ላይ እምነት ስላላቸው ነው። ይሖዋ ቤዛውን መሠረት በማድረግ፣ ራሳቸውን ለእሱ ወስነው የሚጠመቁ ሁሉ ወዳጆቹ እንዲሆኑ ፈቅዷል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ራሳቸውን ወስነው በመጠመቅ በጽንፈ ዓለም ውስጥ ከሁሉ ከሚበልጠው አካል ጋር “የጠበቀ ወዳጅነት” መመሥረት ችለዋል፤ እኛም እነዚህን አስፈላጊ እርምጃዎች በመውሰድ ይህን መብት ማግኘት እንችላለን። ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ወዳጅነት ከፍ አድርገን እንደምንመለከተው ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ከመቶ ዓመት በላይ አምላክን በታማኝነት እንዳገለገሉት እንደ አብርሃምና እንደ ኢዮብ ሁሉ እኛም በታማኝነት መጽናት ይኖርብናል፤ በዚህ አሮጌ ሥርዓት ውስጥ ይሖዋን ለበርካታ ዓመታት ስናገለግል ብንቆይም እንኳ በታማኝነት መጽናታችን አስፈላጊ ነው። እንደ ዳንኤል ሁሉ እኛም ከሕይወታችን ይልቅ ከአምላክ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ልናስቀድም ይገባል። (ዳን. 6:7, 10, 16, 22) ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥመን ሁኔታውን በይሖዋ እርዳታ በመወጣት ከእሱ ጋር የመሠረትነውን ዝምድና ጠብቀን መኖር እንችላለን።—ፊልጵ. 4:13፤ w20.05 27 አን. 5-6
ሰኞ፣ የካቲት 7
ልቤን አንድ አድርግልኝ።—መዝ. 86:11
ንጉሥ ዳዊት የሌላ ሰው ሚስት ሰውነቷን ስትታጠብ አየ። ዳዊት “የባልንጀራህን ሚስት . . . አትመኝ” የሚለውን የይሖዋ ሕግ ያውቅ ነበር። (ዘፀ. 20:17) ያም ሆኖ ሴቲቱን መመልከቱን የቀጠለ ይመስላል። በአንድ በኩል ይሖዋን ማስደሰት ቢፈልግም በሌላ በኩል ደግሞ ቤርሳቤህን ስለተመኘ ልቡ ተከፈለ። ዳዊት ሕይወቱን በሙሉ ይሖዋን የሚወድና የሚፈራ ሰው ቢሆንም ለራስ ወዳድነት ምኞቱ ተሸነፈ። በመሆኑም በጣም መጥፎ ድርጊት ፈጸመ። በዚህም ምክንያት በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ አመጣ። ከዚህም ሌላ ቤተሰቡን ጨምሮ ሌሎች ንጹሐን ሰዎች እንዲጎዱ አደረገ። (2 ሳሙ. 11:1-5, 14-17፤ 12:7-12) ይሖዋ ለዳዊት ተግሣጽ የሰጠው ሲሆን እሱም ከይሖዋ ጋር ያለውን ግንኙነት ማደስ ቻለ። (2 ሳሙ. 12:13፤ መዝ. 51:2-4, 17) ዳዊት ልቡ እንዲከፈል መፍቀዱ ያስከተለውን መከራና ሥቃይ አልረሳም። በመዝሙር 86:11 ላይ የሚገኘው እሱ የተናገረው ሐሳብ “ያልተከፋፈለ ልብ ስጠኝ” ተብሎም ሊተረጎም ይችላል። ታዲያ ይሖዋ፣ ልቡ ሙሉ ወይም ያልተከፋፈለ እንዲሆን ዳዊትን ረድቶት ነበር? አዎ፣ ከጊዜ በኋላ የአምላክ ቃል ስለ ዳዊት ሲናገር ‘ልቡ በአምላኩ በይሖዋ ዘንድ ሙሉ እንደነበር’ ይገልጻል።—1 ነገ. 11:4፤ 15:3፤ w20.06 11 አን. 12-13
ማክሰኞ፣ የካቲት 8
በፍቅር . . . ማሰሪያ ሳብኳቸው።—ሆሴዕ 11:4
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ለሕዝቡ ያለውን ፍቅር ከገመድ ወይም ከማሰሪያ ጋር ያመሳስለዋል። የአምላክ ፍቅር ከገመድ ጋር ሊመሳሰል የሚችለው እንዴት ነው? አንድ ምሳሌ እንመልከት፦ በማዕበል በሚናወጥ ባሕር ውስጥ ላለመስመጥ እየታገልክ ሳለ አንድ ሰው የሚያንሳፍፍ ጃኬት ወረወረልህ። ጃኬቱ ለመንሳፈፍ የምታደርገውን ትግል ስለሚያቀልልህ ግለሰቡ ያደረገልህን እርዳታ እንደምታደንቅ ጥያቄ የለውም። ይሁንና ጃኬቱ ብቻውን ሕይወትህን ያተርፍልሃል ማለት አይደለም። ውኃው ቀዝቃዛ ነው፤ በመሆኑም ወደ ሕይወት አድን ጀልባ መድረስ ካልቻልክ በሕይወት አትተርፍም። ከጀልባው ላይ ሆኖ ገመድ የሚወረውርልህና ስቦ የሚያወጣህ ሰው ያስፈልግሃል። ይሖዋ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ እንደተናገረው ከእሱ ርቀው የነበሩትን እስራኤላውያን ‘በፍቅር ማሰሪያ ስቧቸዋል።’ በዛሬው ጊዜም አምላክ እሱን ማገልገላቸውን ያቆሙ እንዲሁም በተለያዩ ችግሮችና ጭንቀቶች የተዋጡ አገልጋዮቹን በተመለከተ እንዲህ ይሰማዋል። እንደሚወዳቸው እንዲገነዘቡ ይፈልጋል፤ እንዲሁም ወደ ራሱ ሊስባቸው ይፈልጋል። ደግሞም ይሖዋ ለእነሱ ያለውን ፍቅር ለመግለጽ በአንተ ሊጠቀም ይችላል። ለቀዘቀዙ ሰዎች፣ ይሖዋም ሆነ እኛ እንደምንወዳቸው ማረጋገጣችን አስፈላጊ ነው። w20.06 27 አን. 12-13
ረቡዕ፣ የካቲት 9
ፈተናን በጽናት ተቋቁሞ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው።—ያዕ. 1:12
ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስ ሲገደል ብዙ ክርስቲያኖች ኢየሩሳሌምን ጥለው በመውጣት “በይሁዳና በሰማርያ ክልሎች ሁሉ ተበተኑ”፤ እንዲያውም አንዳንዶቹ እስከ ቆጵሮስና አንጾኪያ ድረስ ርቀው ሄደዋል። (ሥራ 7:58–8:1፤ 11:19) እነዚህ ደቀ መዛሙርት ምን ያህል ከባድ ሁኔታ እንደገጠማቸው መገመት እንችላለን። ያም ቢሆን ምሥራቹን በሄዱበት ሁሉ በቅንዓት ሰብከዋል፤ እንዲሁም በመላው የሮም ግዛት ጉባኤዎች ተቋቁመዋል። (1 ጴጥ. 1:1) ሆኖም እነዚህ ክርስቲያኖች ከዚህም የከፉ ፈተናዎች ይጠብቋቸው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በ50 ዓ.ም. ገደማ የሮም ንጉሠ ነገሥት ቀላውዴዎስ አይሁዳውያን ሁሉ ሮምን ለቀው እንዲወጡ አዘዘ። ስለዚህ ክርስቲያን የሆኑ አይሁዳውያን ቤት ንብረታቸውን ጥለው ወደ ሌላ አካባቢ ለመሰደድ ተገደዱ። (ሥራ 18:1-3) በ61 ዓ.ም. ገደማ ሐዋርያው ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹ በአደባባይ እንደተነቀፉ፣ እንደታሰሩና እንደተዘረፉ ጽፎ ነበር። (ዕብ. 10:32-34) እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ ደግሞ እነዚያ ክርስቲያኖች ከድህነት ወይም ከህመም ጋር መታገል ነበረባቸው።—ሮም 15:26፤ ፊልጵ. 2:25-27፤ w21.02 26-27 አን. 2-4
ሐሙስ፣ የካቲት 10
ዲያብሎስ ጥቂት ጊዜ እንደቀረው ስላወቀ በታላቅ ቁጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዷል።—ራእይ 12:12
እምነቱን ለማጠናከር ጥረት የሚያደርግ ክርስቲያን ሰይጣንም ሆነ ግብረ አበሮቹ በሚሰነዝሩት ጥቃት አይናወጥም። (2 ዮሐ. 8, 9) ዓለም እንደሚጠላን መጠበቅ ይኖርብናል። (1 ዮሐ. 3:13) ዮሐንስ ‘መላው ዓለም በክፉው ቁጥጥር ሥር እንደሆነ’ ተናግሯል። (1 ዮሐ. 5:19) ይህ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው በተቃረበ መጠን የሰይጣን ቁጣም እየጨመረ ይሄዳል። በመሆኑም ዲያብሎስ እንደ ሥነ ምግባር ፈተናና እንደ ከሃዲዎች ትምህርት ያሉ ስውር ጥቃቶችን በመሰንዘር ብቻ አይወሰንም። የኃይል ጥቃትም ይሰነዝራል። ሰይጣን የስብከቱን ሥራ ለማስቆም ወይም እምነታችንን ለማዳከም መሞከር የሚችልበት ጊዜ እያለቀ እንደሆነ ያውቃል። ከዚህ አንጻር በተለያዩ አገሮች ውስጥ ሥራችን የታገደ ወይም ገደብ የተጣለበት መሆኑ አያስገርምም። ያም ቢሆን በእነዚህ አገሮች ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጸንተው ቆመዋል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች ክፉው ምንም ዓይነት ጥቃት ቢሰነዝር ድል ማድረግ እንደምንችል የሚያሳዩ ማስረጃዎች ናቸው። w20.07 24 አን. 12-13
ዓርብ፣ የካቲት 11
አምላክ የሚሰጠው ስጦታ . . . በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።—ሮም 6:23
የይሖዋ ዓላማ፣ የሰው ልጆች እሱ በፈጠራት ውብ ፕላኔት ላይ ለዘላለም በደስታ እንዲኖሩ ነበር። አዳምና ሔዋን በአፍቃሪ አባታቸው ላይ ሲያምፁ ግን ኃጢአትና ሞት በሰው ዘር ላይ አጠላ። (ሮም 5:12) ታዲያ ይሖዋ ምን አደረገ? የሰውን ዘር ለመታደግ የሚያደርገውን ዝግጅት ወዲያውኑ ገለጸ። (ዘፍ. 3:15) ይሖዋ የአዳምንና የሔዋንን ልጆች ከኃጢአትና ከሞት ነፃ የሚያወጣ ቤዛ ለማዘጋጀት አሰበ። ይህን ቤዛ መሠረት በማድረግም፣ እሱን ለማገልገል የሚመርጥ ማንኛውም ግለሰብ የዘላለም ሕይወት እንዲያገኝ መንገድ ከፈተ። (ዮሐ. 3:16፤ 1 ቆሮ. 15:21, 22) ይሖዋ በልጁ አማካኝነት ስፍር ቁጥር የሌላቸው ሰዎችን ከሞት በሚያስነሳበት ወቅት ሁሉም በአንድ ጊዜ ትንሣኤ ያገኛሉ ብለን አንጠብቅም። ለምን? ምክንያቱም የምድር ሕዝብ ቁጥር በአንድ ጊዜ ከጨመረ ትርምስ ይፈጠራል። ይሖዋ ደግሞ ባልተደራጀና በተተራመሰ መንገድ ምንም ነገር አያደርግም። ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን ሥርዓት ሊኖር እንደሚገባ ያውቃል።—1 ቆሮ. 14:33፤ w20.08 14 አን. 3፤ 15 አን. 5
ቅዳሜ፣ የካቲት 12
ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ።—1 ጢሞ. 4:16
አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ የጥናቱ ዓላማ ግልጽ ሊሆንለት ይገባል፤ መጽሐፍ ቅዱስን የምናስጠናው የይሖዋ ምሥክር እንዲሆን ነው። ቅን ልብ ያለው የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ ለጥምቀት ብቁ ለመሆን ደረጃ በደረጃ ሊወስዳቸው የሚገቡ እርምጃዎች አሉ። በመጀመሪያ ተማሪው ይሖዋን ማወቅና መውደድ እንዲሁም በእሱ ላይ እምነት ማሳደር ይኖርበታል። (ዮሐ. 3:16፤ 17:3) ከዚያም ተማሪው ከይሖዋ እና በጉባኤው ውስጥ ካሉ ክርስቲያኖች ጋር ወዳጅነት ይመሠርታል። (ዕብ. 10:24, 25፤ ያዕ. 4:8) ውሎ አድሮም ተማሪው ከኃጢአቱ ንስሐ ገብቶ መጥፎ ልማዶቹን ያስወግዳል። (ሥራ 3:19) በተጨማሪም እምነቱ የተማረውን ነገር ለሌሎች እንዲናገር ያነሳሳዋል። (2 ቆሮ. 4:13) ከዚያም ራሱን ለይሖዋ ይወስናል፤ ይህን ውሳኔውን ለማሳየትም ይጠመቃል። (1 ጴጥ. 3:21፤ 4:2) ግለሰቡ ይህን እርምጃ የሚወስድበት ቀን ምንኛ አስደሳች ይሆናል! ተማሪው እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ የሚያስችለውን እያንዳንዱን እርምጃ ሲወስድ ከልብ አመስግነው፤ እንዲሁም እድገት ማድረጉን እንዲቀጥል አበረታታው። w20.10 18 አን. 12-13
እሁድ፣ የካቲት 13
እግር “እኔ እጅ ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ አይቀርም።—1 ቆሮ. 12:15
በጉባኤው ውስጥ ካሉ ሌሎች ክርስቲያኖች ጋር ራስህን የምታወዳድር ከሆነ አንተ የምታበረክተውን ድርሻ ዝቅ አድርገህ ልትመለከት ትችላለህ። በጉባኤው ውስጥ ያሉ አንዳንዶች በማስተማር፣ በማደራጀት ወይም እረኝነት በማድረግ ረገድ የተዋጣላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። አንተ ግን በዚህ ረገድ የእነሱን ያህል ችሎታ እንደሌለህ ይሰማህ ይሆናል። እንዲህ ማሰብህ ትሑትና ልክህን የምታውቅ እንደሆንክ ያሳያል። (ፊልጵ. 2:3) ሆኖም ልትጠነቀቅ ይገባል። የላቀ ተሰጥኦ ካላቸው ሰዎች ጋር ሁልጊዜ ራስህን የምታወዳድር ከሆነ በራስህ ተስፋ ልትቆርጥ ትችላለህ። እንዲያውም ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው በጉባኤው ውስጥ ምንም ቦታ እንደሌለህ ሊሰማህ ይችላል። ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች የመንፈስ ቅዱስ ተአምራዊ ስጦታዎችን ሰጥቷቸው ነበር፤ ሆኖም ሁሉም ክርስቲያኖች ተመሳሳይ ስጦታዎች አልተቀበሉም። (1 ቆሮ. 12:4-11) ሆኖም እያንዳንዱ ክርስቲያን ጠቃሚ ድርሻ ነበረው። በዛሬው ጊዜ የመንፈስ ቅዱስ ተአምራዊ ስጦታዎች የሉንም። መሠረታዊ ሥርዓቱ ግን ዛሬም ይሠራል። ሁላችንም ተመሳሳይ ተሰጥኦዎች አይኖሩን ይሆናል፤ ያም ቢሆን ሁላችንም በይሖዋ ፊት ዋጋ አለን። w20.08 23 አን. 13-15
ሰኞ፣ የካቲት 14
ይሖዋ ከጎኔ ነው፤ አልፈራም።—መዝ. 118:6
ድፍረት እንዲሰጥህ ወደ ይሖዋ ከጸለይክ ይሖዋ የጠየቅከውን ይሰጥሃል፤ ደግሞም አንተን መደገፉን አያቆምም። (ሥራ 4:29, 31) ምንጊዜም ከጎንህ ነው። ያጋጠሙህን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንድትወጣ የረዳህና በሕይወትህ ውስጥ ለውጥ እንድታደርግ ኃይል የሰጠህ እንዴት እንደሆነ አስብ። ሕዝቡን እየመራ ቀይ ባሕርን ያሻገረው አምላክ አንተንም የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንድትሆን መርዳት አይሳነውም። (ዘፀ. 14:13) በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሰፈረውን ሐሳብ የተናገረው መዝሙራዊ የነበረው ዓይነት እምነት ይኑርህ። ይሖዋ አዳዲስ አስፋፊዎችንም ደፋር እንዲሆኑ ይረዳቸዋል። ቶሞዮ የተባለች እህት ያጋጠማትን ሁኔታ እንመልከት። ቶሞዮ ከቤት ወደ ቤት መስበክ በጀመረችበት ወቅት መጀመሪያ ያገኘቻት ሴት “የይሖዋ ምሥክሮችን ማነጋገር አልፈልግም!” ብላ ከጮኸችባት በኋላ በሩን ላይዋ ላይ ዘጋችባት። ቶሞዮ በዚህ አልተደናገጠችም፤ እንዲያውም ለአገልግሎት ጓደኛዋ “አይገርምም? አንዲት ቃል እንኳ ሳልተነፍስ የይሖዋ ምሥክር መሆኔን አውቃለች። ደስ አይልም?” አለቻት። በአሁኑ ወቅት ቶሞዮ የዘወትር አቅኚ ሆና እያገለገለች ነው። w20.09 6 አን. 13-14
ማክሰኞ፣ የካቲት 15
አሳ በአምላኩ በይሖዋ ፊት መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።—2 ዜና 14:2
አሳ ‘በዙሪያቸው ካሉት ጠላቶቻቸው ሁሉ እረፍት የሰጣቸው’ ይሖዋ መሆኑን ለሕዝቡ ነግሯቸዋል። (2 ዜና 14:6, 7) አሳ ሰላም የሰፈነበት ይህ ጊዜ ዘና የሚሉበት ወቅት እንዳልሆነ ተሰምቶታል። እንዲያውም ከተሞች፣ ቅጥርና ማማዎች እንዲሁም በሮች መሥራት ጀመረ። የይሁዳን ሕዝብ “ምድሪቱ አሁንም በእጃችን ናት” አላቸው። አሳ ምን ማለቱ ነበር? ሕዝቡ የጠላቶቻቸው ተቃውሞ ስለሌለባቸው አምላክ በሰጣቸው ምድር ላይ በነፃነት መንቀሳቀስና መገንባት እንደሚችሉ መግለጹ ነበር። ይህን የሰላም ጊዜ በጥበብ እንዲጠቀሙበት ሕዝቡን አሳስቧቸዋል። አሳ የሰላሙን ጊዜ ወታደራዊ ኃይሉን ለማጠናከርም ተጠቅሞበታል። (2 ዜና 14:8) ይህ በይሖዋ እንዳልታመነ የሚያሳይ ነው? አይደለም። ከዚህ ይልቅ አሳ ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ሕዝቡን ወደፊት ሊመጣ ለሚችለው ችግር የማዘጋጀት ኃላፊነት እንዳለበት መገንዘቡን የሚጠቁም ነው። አሳ የይሁዳ ሕዝብ ያገኘው የሰላም ጊዜ ለዘለቄታው እንደማይቀጥል ተሰምቶት ነበር፤ ደግሞም ትክክል ነበር። w20.09 15 አን. 4-5
ረቡዕ፣ የካቲት 16
ከተጻፈው አትለፍ።—1 ቆሮ. 4:6
አንድ ሽማግሌ የአምላክን መንጋ ለመጠበቅ ይረዳሉ ብሎ የሚያስባቸውን ደንቦች በቅንነት ሊያወጣ ይችላል። ይሁንና ሽማግሌዎችና የቤተሰብ ራሶች ባላቸው ሥልጣን መካከል ጉልህ ልዩነቶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ለሽማግሌዎች የመፍረድ ኃላፊነት ሰጥቷቸዋል፤ በመሆኑም ንስሐ የማይገባን ኃጢአተኛ ከጉባኤው የማስወገድ ሥልጣን አላቸው። (1 ቆሮ. 5:11-13) በሌላ በኩል ግን ይሖዋ ለቤተሰብ ራሶች ለሽማግሌዎች ያልሰጠው ዓይነት ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። ለምሳሌ አንድ የቤተሰብ ራስ ለቤተሰቡ መመሪያ የማውጣትና ያንን የማስፈጸም ሥልጣን አለው። (ሮም 7:2) ለአብነት ያህል፣ አንድ የቤተሰብ ራስ ልጆቹ ማታ ቤት የሚገቡበትን ሰዓት የመወሰን መብት አለው። ልጆቹ መመሪያውን ሳይታዘዙ ቢቀሩ ለእነሱ ተግሣጽ የመስጠት ሥልጣንም አለው። (ኤፌ. 6:1) እርግጥ ነው፣ አንድ አፍቃሪ የቤተሰብ ራስ ለቤተሰቡ መመሪያ ከማውጣቱ በፊት ሚስቱን ያማክራል፤ ምክንያቱም ሁለቱ “አንድ ሥጋ ናቸው።”—ማቴ. 19:6፤ w21.02 16-18 አን. 10-13
ሐሙስ፣ የካቲት 17
[ጥበብ] ከዛጎል ይበልጥ ውድ ናት፤ አንተ የምትመኘው ማንኛውም ነገር ሊተካከላት አይችልም።—ምሳሌ 3:15
በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙት እውነቶች ውድ የሆኑበት አንዱ ምክንያት ይሖዋ እነዚህን እውነቶች የሚገልጠው “ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ” ላላቸው ትሑት ሰዎች ብቻ መሆኑ ነው። (ሥራ 13:48) እነዚህ ሰዎች ይሖዋ በዛሬው ጊዜ እውነትን የሚያስተምረው በታማኝና ልባም ባሪያ በኩል መሆኑን ይቀበላሉ። (ማቴ. 11:25፤ 24:45) እነዚህን እውነቶች በራሳችን ልናውቃቸው አንችልም፤ ደግሞም የእነዚህን እውነቶች ያህል ውድ የሆነ ሌላ ምንም ነገር የለም። (ምሳሌ 3:13) ይሖዋ፣ ስለ እሱና ስለ ዓላማዎቹ ለሰዎች የማስተማር መብትንም በአደራ ሰጥቶናል። (ማቴ. 24:14) የምንሰብከው መልእክት በጣም ውድ ነው፤ ምክንያቱም ሰዎች የይሖዋ ቤተሰብ አባላት እንዲሆኑና የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ እንዲኖራቸው ያደርጋል። (1 ጢሞ. 4:16) እያንዳንዳችን በአገልግሎቱ የምናደርገው ተሳትፎ ትንሽም ይሁን ትልቅ በዚህ ዘመን ከሚከናወኑ ሥራዎች ሁሉ ይበልጥ አስፈላጊ የሆነውን ሥራ እየደገፍን ነው። (1 ጢሞ. 2:3, 4) ከአምላክ ጋር አብሮ መሥራት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው!—1 ቆሮ. 3:9፤ w20.09 26-27 አን. 4-5
ዓርብ፣ የካቲት 18
ወንድሞችን አገኘን፤ እነሱም . . . አብረናቸው እንድንቆይ ለመኑን።—ሥራ 28:14
ሐዋርያው ጳውሎስ ወደ ሮም ሲጓዝ ይሖዋ በእምነት ባልንጀሮቹ አማካኝነት በተደጋጋሚ ረድቶታል። ለምሳሌ ያህል፣ ጳውሎስ ወደ ሮም ሲጓዝ ሁለት ታማኝ ወዳጆቹ ማለትም ሉቃስና አርስጥሮኮስ አብረውት ለመሄድ ወሰኑ። እነዚህ ክርስቲያኖች ሮም በሰላም እንደሚደርሱ ከኢየሱስ ማረጋገጫ ያገኙ አይመስልም፤ ስለዚህ ከጳውሎስ ጋር ለመሄድ የወሰኑት ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ነበር። ሕይወታቸው እንደሚተርፍ ያወቁት አስቸጋሪውን ጉዞ ከጀመሩ በኋላ ነበር። ሲዶና ወደተባለች የወደብ ከተማ ሲደርሱ ጳውሎስ “ወደ ወዳጆቹ እንዲሄድና እንክብካቤ እንዲያደርጉለት” ዩልዮስ ፈቅዶለት ነበር። (ሥራ 27:1-3) በኋላ ላይ ደግሞ ፑቲዮሉስ የተባለችው ከተማ ሲደርሱ ጳውሎስና የጉዞ ጓደኞቹ ‘ወንድሞችን አገኙ፤ እነሱም ሰባት ቀን አብረዋቸው እንዲቆዩ ለመኗቸው።’ ጳውሎስና ጓደኞቹ በእነዚህ ቦታዎች ያሉ ክርስቲያኖች ካደረጉላቸው እንክብካቤ ተጠቅመዋል፤ ያስተናገዷቸው ወንድሞች ደግሞ የጳውሎስን የሚያበረታቱ ተሞክሮዎች በመስማት በእጅጉ ተደስተው መሆን አለበት።—ከሐዋርያት ሥራ 15:2, 3 ጋር አወዳድር፤ w20.11 15-16 አን. 15-17
ቅዳሜ፣ የካቲት 19
ለአምላክ ማደር . . . ለአሁኑም ሆነ ለወደፊቱ ሕይወት ተስፋ [ይሰጣል]።—1 ጢሞ. 4:8
ወላጆች፣ በቃልም ሆነ በድርጊት ለይሖዋ ያላችሁን ጥልቅ ፍቅር ልጆቻችሁ እንዲያዩ አድርጉ። ለልጆቻችሁ ልትሰጡ የምትችሉት ትልቁ ስጦታ ይሖዋን እንዲወዱ መርዳት እንደሆነ አትርሱ። በተጨማሪም ልጆቻችሁ ጥሩ የጥናት፣ የጸሎት፣ የስብሰባና የአገልግሎት ልማድ ማዳበር የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንዲገነዘቡ እርዷቸው፤ ይህ ለልጆቻችሁ ልታስተምሩ ከምትችሏቸው በጣም አስፈላጊ ትምህርቶች መካከል አንዱ ነው። (1 ጢሞ. 6:6) እርግጥ ነው፣ ለልጆቻችሁ የሚያስፈልጓቸውን ቁሳዊ ነገሮች ማሟላት ይኖርባችኋል። (1 ጢሞ. 5:8) ሆኖም ከዚህ አሮጌ ሥርዓት በሕይወት ተርፈው አምላክ ወዳዘጋጀው አዲስ ዓለም እንዲገቡ የሚያስችላቸው ከይሖዋ ጋር ያላቸው የጠበቀ ዝምድና እንጂ ቁሳዊ ሀብት እንዳልሆነ አስታውሱ። (ሕዝ. 7:19) በርካታ ክርስቲያን ወላጆች ለልጆቻቸው መንፈሳዊነት የሚጠቅሙ ጥሩ ምርጫዎችን እያደረጉ እንዳሉ ማየት ምንኛ የሚያስደስት ነው! እንዲህ ባሉ ቤተሰቦች ውስጥ የሚያድጉ ልጆች አብዛኛውን ጊዜ በልጅነታቸው ያዳበሯቸውን ጥሩ ልማዶች ይዘው የሚቀጥሉ ከመሆኑም ሌላ ወላጆቻቸው በዚህ መንገድ ስላሳደጓቸው ደስተኞች ናቸው!—ምሳሌ 10:22፤ w20.10 28-29 አን. 10-11
እሁድ፣ የካቲት 20
በምንም ዓይነት እንዲህ ያለ ነገር አይደርስብህም።—ማቴ. 16:22
ሐዋርያው ጴጥሮስ የኋላ ኋላ የተቆጨባቸውን ነገሮች የተናገረበት ወይም ያደረገበት ጊዜ ነበር። ለምሳሌ ኢየሱስ መከራ እንደሚቀበልና እንደሚገደል ለሐዋርያቱ በነገራቸው ጊዜ ጴጥሮስ የዕለቱ ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ በመናገር ኢየሱስን ገሥጾታል። (ማቴ. 16:21-23) በዚህም ምክንያት ኢየሱስ ለጴጥሮስ እርማት ሰጠው። ብዙ ሰዎች ኢየሱስን ሊያስሩት በመጡበት ወቅት፣ ጴጥሮስ የሊቀ ካህናቱን ባሪያ መትቶ ጆሮውን በመቁረጥ የችኮላ እርምጃ ወሰደ። (ዮሐ. 18:10, 11) በዚህ ወቅትም ኢየሱስ ለሐዋርያው እርማት ሰጥቶታል። በተጨማሪም ጴጥሮስ ሌሎቹ ሐዋርያት ሁሉ በኢየሱስ ምክንያት ቢሰናከሉ እንኳ እሱ ፈጽሞ እንደማይሰናከል በመግለጽ ጉራውን ነዝቷል! (ማቴ. 26:33) ጴጥሮስ ከልክ በላይ በራሱ ተማምኖ ነበር፤ ሆኖም ለሰው ፍርሃት እጅ በመስጠት ጌታውን ሦስት ጊዜ ካደው። ጴጥሮስ በዚህ ቅስሙ ስለተሰበረ “ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።” (ማቴ. 26:69-75) ምናልባትም ጴጥሮስ፣ ኢየሱስ ጨርሶ ይቅር እንደማይለው ተሰምቶት ሊሆን ይችላል። ያም ቢሆን ጴጥሮስ ተስፋ ቆርጦ ይሖዋን ማገልገሉን አላቆመም። ተደናቅፎ የነበረ ቢሆንም ከሌሎቹ ሐዋርያት ጋር ሆኖ ይሖዋን ማገልገሉን ቀጥሏል።—ዮሐ. 21:1-3፤ ሥራ 1:15, 16፤ w20.12 20 አን. 17-18
ሰኞ፣ የካቲት 21
እናንተ ባሎች ከእነሱ ጋር በእውቀት አብራችሁ ኑሩ። . . . ከእናንተ ይበልጥ እንደ ተሰባሪ ዕቃ የሆኑትን ሴቶችን አክብሯቸው።—1 ጴጥ. 3:7
አንድ የቤተሰብ ራስ ትሕትናውን የሚያሳይባቸው የተለያዩ መንገዶች አሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ከሚስቱና ከልጆቹ ፍጽምና አይጠብቅም። ከእሱ የተለየ አመለካከት በሚኖራቸው ጊዜም እንኳ የቤተሰቡ አባላት የሚሰጡትን ሐሳብ ለማዳመጥና ግምት ውስጥ ለማስገባት ፈቃደኛ ነው። በተጨማሪም አንድ ትሑት ባል የቤት ውስጥ ሥራዎችን ለማከናወን ፈቃደኛ ነው፤ በሚኖርበት ማኅበረሰብ ውስጥ እነዚህ ሥራዎች የሴት ሥራ እንደሆኑ ተደርገው ቢታዩም ይህ ተጽዕኖ አያሳድርበትም። በእርግጥ ማኅበረሰቡ የሚያሳድረውን እንዲህ ያለውን ተጽዕኖ መቋቋም ቀላል ላይሆን ይችላል። ለምን? ሪቼል የተባለች አንዲት እህት እንዲህ ብላለች፦ “በአካባቢያችን አንድ ባል ዕቃ በማጠብ ወይም ቤት በማጽዳት ሚስቱን ካገዘ ጎረቤቶቹና ዘመዶቹ ሴታ ሴት አድርገው ሊያስቡት ይችላሉ። ሚስቱን መቆጣጠር እንደማይችል ይሰማቸዋል።” በምትኖርበት አካባቢ ሰዎች እንዲህ ዓይነት አመለካከት ካላቸው የኢየሱስን ምሳሌ አስታውስ፤ ኢየሱስ የባሪያ ሥራ ተደርጎ ቢቆጠርም የደቀ መዛሙርቱን እግር አጥቧል። አንድ ጥሩ የቤተሰብ ራስ የሚያሳስበው ሌሎች ለእሱ ያላቸው አመለካከት ሳይሆን የሚስቱና የልጆቹ ስሜት ነው። w21.02 2 አን. 3፤ 4 አን. 11
ማክሰኞ፣ የካቲት 22
ስለ አንድ ነገር እርግጠኛ ነኝ፦ ከኋላዬ ያሉትን ነገሮች እየረሳሁ ከፊቴ ወዳሉት ነገሮች እንጠራራለሁ፤ . . . ግቡ ላይ ለመድረስ እየተጣጣርኩ ነው።—ፊልጵ. 3:13, 14
ጥሩ ትዝታ የይሖዋ ስጦታ ነው፤ ሆኖም ያሳለፍነው ሕይወት ምንም ያህል አስደሳች ቢሆን ወደፊት በአዲሱ ዓለም የምናገኘው ሕይወት እጅግ የላቀ ነው። ሌሎች ይበድሉን ይሆናል፤ ሆኖም በይሖዋ አገልግሎት ወደ ፊት መግፋት የምንችለው ይቅር ለማለት ስንመርጥ ነው። ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ይሖዋን በደስታ እንዳናገለግለው እንቅፋት ይሆንብናል። ሆኖም እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ይሖዋ ይቅር እንዳለን ማመን ያስፈልገናል። (1 ጢሞ. 1:12-15) ለዘላለም የመኖር ተስፋ ተዘርግቶልናል። በአምላክ አዲስ ዓለም ውስጥ ደግሞ ያለፈውን ሕይወታችንን እያሰብን በጸጸት አንብሰለሰልም። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚያ ጊዜ ሲናገር “የቀድሞዎቹ ነገሮች አይታሰቡም” ይላል። (ኢሳ. 65:17) እስቲ አስበው፦ ይሖዋን ለበርካታ ዓመታት ያገለገልን አንዳንዶቻችን ዕድሜያችን ገፍቷል፤ በአዲሱ ዓለም ግን እንደገና ወጣት እንሆናለን። (ኢዮብ 33:25) እንግዲያው ስላለፈው ጊዜ ከልክ በላይ ላለማሰብ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። በወደፊቱ ተስፋ ላይ ትኩረት በማድረግ ለዚያ የምንበቃ ሰዎች ለመሆን የምንችለውን ሁሉ እናድርግ! w20.11 24 አን. 4፤ 29 አን. 18-19
ረቡዕ፣ የካቲት 23
እጅግ ብዙ ሕዝብ [አየሁ]፤ በታላቅም ድምፅ እየጮኹ “መዳን ያገኘነው . . . ከአምላካችን እንዲሁም ከበጉ ነው” ይሉ ነበር።—ራእይ 7:9, 10
ወደፊት ምን ይጠብቀናል? በታላቁ መከራ ወቅት ይሖዋ በሁለት አስደናቂ መንገዶች ያድነናል። አንደኛ፣ ይሖዋ የዓለም ነገሥታት ታላቂቱ ባቢሎንን ማለትም በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን በሙሉ እንዲያጠፉ በሚያደርግበት ወቅት ታማኝ አገልጋዮቹን ያድናቸዋል። (ራእይ 17:16-18፤ 18:2, 4) ቀጥሎም በአርማጌዶን ቀሪዎቹን የሰይጣን ዓለም ክፍሎች ጠራርጎ ሲያጠፋ ሕዝቦቹን ያድናቸዋል። (ራእይ 16:14, 16) ከይሖዋ ጋር ተቀራርበን ከኖርን ሰይጣን ምንም ዓይነት ዘላቂ ጉዳት ሊያደርስብን አይችልም። እንዲያውም ለዘለቄታው የሚደመሰሰው እሱ ነው። (ሮም 16:20) እንግዲያው ሙሉውን የጦር ትጥቅ ልበሱ፤ እንዲሁም ፈጽሞ አታውልቁት! ብቻችሁን ለመዋጋት አትሞክሩ። ወንድሞቻችሁንና እህቶቻችሁን ደግፉ። የይሖዋን አመራርም ተከተሉ። እንዲህ ካደረጋችሁ በሰማይ ያለው አፍቃሪ አባታችሁ እንደሚያጠነክራችሁና እንደሚጠብቃችሁ እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ።—ኢሳ. 41:10፤ w21.03 30 አን. 16-17
ሐሙስ፣ የካቲት 24
ሳትረበሹ፣ ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ።—ኢሳ. 30:15
በይሖዋ እንደምንታመን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ የሚሰጠንን መመሪያ በመታዘዝ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ አለመረበሽና በይሖዋ መታመን ያለውን አስፈላጊነት የሚያጎሉ ብዙ ታሪኮች ይዟል። እነዚህን ታሪኮች ስታጠኑ የአምላክ አገልጋዮች ከባድ ተቃውሞ ሲያጋጥማቸው እንዳይረበሹ የረዳቸው ምን እንደሆነ ለማስተዋል ሞክሩ። ለምሳሌ ያህል፣ የአይሁድ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሐዋርያቱን እንዳይሰብኩ አዟቸው ነበር፤ ሐዋርያቱ ግን በፍርሃት አልራዱም። ከዚህ ይልቅ በድፍረት “ከሰው ይልቅ አምላክን እንደ ገዢያችን አድርገን ልንታዘዝ ይገባል” በማለት መልስ ሰጥተዋል። (ሥራ 5:29) ከተገረፉ በኋላም እንኳ ሐዋርያቱ አልተሸበሩም። ለምን? ይሖዋ ከጎናቸው እንደሆነ ስለሚያውቁ ነው። በእነሱ እንደተደሰተ እርግጠኞች ነበሩ። በመሆኑም ምሥራቹን መስበካቸውን ቀጠሉ። (ሥራ 5:40-42) በተመሳሳይም ደቀ መዝሙሩ እስጢፋኖስ፣ ሊገደል በተወሰደበት ወቅት በጣም ከመረጋጋቱ የተነሳ ፊቱ “እንደ መልአክ ፊት ሆኖ” ታይቷቸው ነበር። (ሥራ 6:12-15) እንዲህ እንዲረጋጋ የረዳው ምንድን ነው? በይሖዋ ፊት ሞገስ እንዳገኘ እርግጠኛ መሆኑ ነው። w21.01 4 አን. 10-11
ዓርብ፣ የካቲት 25
ልብሳቸውን . . . በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል።—ራእይ 7:14
ይህ አገላለጽ ንጹሕ ሕሊናና በይሖዋ ፊት የጽድቅ አቋም እንዳላቸው ይጠቁማል። (ኢሳ. 1:18) ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑና የተጠመቁ ክርስቲያኖች ናቸው፤ በኢየሱስ መሥዋዕት ላይ ጠንካራ እምነት ያላቸው ከመሆኑም ሌላ ከይሖዋ ጋር ዝምድና መሥርተዋል። (ዮሐ. 3:36፤ 1 ጴጥ. 3:21) በአምላክ ዙፋን ፊት ለመቆምና በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ምድራዊ አደባባይ ላይ ሆነው ‘ቀንና ሌሊት ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት’ ለማቅረብ ብቁ የሆኑት በዚህ የተነሳ ነው። (ራእይ 7:15) በአሁኑ ጊዜ በሚከናወነው የመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ትልቁን ድርሻ እየተወጡ ያሉትም እነሱ ናቸው፤ እንዲህ በማድረግም ከራሳቸው ጥቅም ይበልጥ ለአምላክ መንግሥት ቅድሚያ እንደሚሰጡ እያሳዩ ነው። (ማቴ. 6:33፤ 24:14፤ 28:19, 20) እጅግ ብዙ ሕዝብ፣ ታላቁን መከራ ካለፉ በኋላም ይሖዋ እንደሚንከባከባቸው ማረጋገጫ ተሰጥቷቸዋል፤ ምክንያቱም ጥቅሱ “በዙፋኑ ላይ የተቀመጠውም ድንኳኑን በላያቸው ይዘረጋል” ይላል። የሌሎች በጎች አባላት ለረጅም ጊዜ ሲጓጉለት የነበረው የሚከተለው ተስፋ ሙሉ በሙሉ ፍጻሜውን ያገኛል፦ “[አምላክ] እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል።”—ራእይ 21:3, 4፤ w21.01 16 አን. 9-10
ቅዳሜ፣ የካቲት 26
በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ ከመንፈሴ አፈሳለሁ፤ ወንዶች ልጆቻችሁና ሴቶች ልጆቻችሁም ትንቢት ይናገራሉ።—ሥራ 2:17
የይሖዋ ቤተሰብ ክፍል በመሆናችን ደስተኛ ነን፤ እንዲሁም ይሖዋ ያቋቋመውን የራስነት ሥርዓት ለማክበር የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። ይሖዋ ወንዶችንም ሴቶችንም እኩል ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይጠቁማል። ለምሳሌ ያህል፣ በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን ለወንዶች ብቻ ሳይሆን ለሴቶችም እንደሰጠ እናነባለን፤ ይህ መንፈስ በተለያዩ ቋንቋዎች መናገርን ጨምሮ ተአምራት እንዲፈጽሙ አስችሏቸዋል። (ሥራ 2:1-4, 15-18) ወንዶችም ሆኑ ሴቶች በሰማይ ከክርስቶስ ጋር እንዲገዙ በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተዋል። (ገላ. 3:26-29) በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ሽልማት የሚሰጣቸው ወንዶችም ሴቶችም ናቸው። (ራእይ 7:9, 10, 13-15) ምሥራቹን የመስበክና የማስተማር ተልእኮ የተሰጠውም ለወንዶችም ለሴቶችም ነው። (ማቴ. 28:19, 20) እንዲያውም የሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ጵርስቅላ የተባለችው እህት ስላከናወነችው ሥራ ይገልጻል፤ ከባሏ ከአቂላ ጋር ሆና አጵሎስ የተባለን አንድ የተማረ ሰው ስለ እውነት ይበልጥ ትክክለኛ ግንዛቤ እንዲያገኝ መርዳት ችላለች።—ሥራ 18:24-26፤ w21.02 14 አን. 1፤ 15 አን. 4
እሁድ፣ የካቲት 27
ለራሳችሁም ሆነ . . . እረኛ ሆናችሁ [ለምትጠብቁት] መንጋ ሁሉ ትኩረት ስጡ።—ሥራ 20:28
ሽማግሌዎች፣ አስፋፊዎች በአገልግሎታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ የመርዳት ከባድ ኃላፊነት አለባችሁ፤ ይህም የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የመምራትን ሥራ ይጨምራል። አንድ አስፋፊ አንተ በተገኘህበት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምራት ካስፈራው ጥናቱን አንተ ልትመራ እንደምትችል ግለጽለት። ሽማግሌዎች አስጠኚዎችን ለማበረታታትና ተስፋ እንዳይቆርጡ ለመርዳት ብዙ ነገር ማድረግ ይችላሉ። (1 ተሰ. 5:11) በአሁኑ ወቅት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ባይኖረንም እንኳ ጥናቶች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ መርዳት እንችላለን። በጥናቱ ወቅት፣ በደንብ የታሰበባቸው ሐሳቦች በመስጠት አስጠኚውን ማገዝ እንችላለን፤ እርግጥ ብዙ እንዳናወራ መጠንቀቅ ይኖርብናል። ጥናቶች ወደ ስብሰባ ሲመጡ ጓደኛ ልናደርጋቸው እንዲሁም ጥሩ ምሳሌ ልንሆንላቸው እንችላለን። በተጨማሪም ሽማግሌዎች ለጥናቶች ጊዜ በመስጠት ሊያበረታቷቸው ይችላሉ፤ ለአስጠኚዎች ደግሞ ሥልጠናና ማበረታቻ መስጠት ይኖርባቸዋል። አንድ ሰው አባታችንን ይሖዋን እንዲወድና እንዲያገለግል አነስተኛም ቢሆን አስተዋጽኦ ከማበርከት ይበልጥ የሚያስደስት ምን ነገር ይኖራል! w21.03 13 አን. 18-19
ሰኞ፣ የካቲት 28
ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት የሚኖራቸው እሱን የሚፈሩ ሰዎች ናቸው።—መዝ. 25:14
ዳዊት ኃላፊነት የሚሰማውና እምነት የሚጣልበት ሰው መሆኑን አሳይቷል። ለምሳሌ ወጣት ሳለ የአባቱን በጎች በትጋት ይንከባከብ ነበር። ይህ አደገኛ ሥራ ነበር። ከጊዜ በኋላ ዳዊት ንጉሥ ሳኦልን እንዲህ ብሎት ነበር፦ “አገልጋይህ የአባቱን መንጋ በሚጠብቅበት ጊዜ አንበሳ እንዲሁም ድብ ይመጣና ከመንጋው መካከል አንድ በግ ነጥቆ ይወስድ ነበር። እኔም ተከትዬው በመሄድ እመታውና በጉን ከአፉ አስጥለው ነበር።” (1 ሳሙ. 17:34, 35) ዳዊት ከበጎቹ ደህንነት ጋር በተያያዘ ኃላፊነት ይሰማው ነበር። ወጣት ወንድሞች የተሰጣቸውን ማንኛውንም ኃላፊነት በትጋት በመወጣት የዳዊትን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። ወጣቱ ዳዊት ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መሥርቶ ነበር። ከዳዊት ድፍረት ወይም በገና ከመጫወት ችሎታው የበለጠ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ከይሖዋ ጋር ያለው ዝምድና ነው። ይሖዋ ለዳዊት አምላኩ ብቻ ሳይሆን የቅርብ ወዳጁም ነበር። ወጣት ወንድሞች፣ ልታደርጉ የሚገባው ዋነኛው ነገር በሰማይ ከሚኖረው አባታችሁ ጋር ያላችሁን ዝምድና ማጠናከር ነው። w21.03 3 አን. 4-5