መጋቢት
ማክሰኞ፣ መጋቢት 1
ሰዎች . . . በሚጠሏችሁ . . . ጊዜ ሁሉ ደስተኞች ናችሁ።—ሉቃስ 6:22
ሰዎች እንዲጠሉን አንፈልግም። ሰማዕታት የመሆን ምኞትም የለንም። ታዲያ ሰዎች ሲጠሉን የምንደሰተው ለምንድን ነው? ሦስት ምክንያቶችን እንመልከት። አንደኛ፣ በታማኝነት ስንጸና የአምላክን ሞገስ እናገኛለን። (1 ጴጥ. 4:13, 14) ሁለተኛ፣ እምነታችን ተፈትኖ ይጠራል እንዲሁም ይጠናከራል። (1 ጴጥ. 1:7) ሦስተኛ፣ ውድ የሆነውን የዘላለም ሕይወት ሽልማት እናገኛለን። (ሮም 2:6, 7) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ሐዋርያቱ እሱ የተናገረለትን ደስታ ማጣጣም ችለዋል። ሐዋርያቱ ከተገረፉና መስበካቸውን እንዲያቆሙ ከታዘዙ በኋላ ደስ ብሏቸዋል። ለምን? የተደሰቱት “ስለ [ኢየሱስ ስም] ውርደት ለመቀበል ብቁ ሆነው በመቆጠራቸው” ነው። (ሥራ 5:40-42) ለጌታቸው ያላቸው ፍቅር ለጠላቶቻቸው ካላቸው ፍርሃት ይበልጥ ነበር። ይህን ፍቅራቸውንም ምሥራቹን “ያለማሰለስ” በመስበክ አሳይተዋል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ወንድሞቻችንም ብዙ መከራ ቢደርስባቸውም በታማኝነት ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። ይሖዋ ሥራቸውንና ለስሙ ያሳዩትን ፍቅር እንደማይረሳ እርግጠኞች ናቸው። w21.03 25 አን. 18-19
ረቡዕ፣ መጋቢት 2
ዘላለማዊነትን በልባቸው ውስጥ አኑሯል።—መክ. 3:11
ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሰማያዊ ተስፋን ይዘው አይወለዱም። ይህን ተስፋ በውስጣቸው የሚያኖረው አምላክ ነው። ስለ ተስፋቸው ያስባሉ፣ ይጸልያሉ እንዲሁም ይህን ሽልማታቸውን በሰማይ የሚያገኙበትን ጊዜ በጉጉት ይጠባበቃሉ። ሰማይ ሲሄዱ ምን ዓይነት መንፈሳዊ አካል እንደሚኖራቸው የሚያውቁት ነገር የለም። (ፊልጵ. 3:20, 21፤ 1 ዮሐ. 3:2) ያም ቢሆን በሰማያዊው መንግሥት የተዘጋጀላቸውን ቦታ ለመቀበል ይጓጓሉ። ሌሎች በጎች በምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩበትን ጊዜ ይናፍቃሉ፤ ይህ የሰው ልጆች ተፈጥሯዊ ፍላጎት ነው። መላዋን ምድር ገነት ለማድረግ በሚከናወነው ሥራ የሚካፈሉበትን ጊዜ በጉጉት ይጠብቃሉ። ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ቤት የሚሠሩበትን፣ መሬት የሚያለሙበትንና ፍጹም ጤናማ የሆኑ ልጆች የሚያሳድጉበትን ጊዜ በናፍቆት ይጠባበቃሉ። (ኢሳ. 65:21-23) በምድር ላይ እየተዘዋወሩ ተራራውን፣ ደኑንና ባሕሩን ለመጎብኘት እንዲሁም ስፍር ቁጥር ስለሌላቸው የይሖዋ ፍጥረታት ለማጥናት ይጓጓሉ። ስለ ተስፋቸው ሲያስቡ ከምንም ነገር በላይ የሚያስደስታቸው ግን ከይሖዋ ጋር ያላቸው ዝምድና ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተጠናከረ እንደሚሄድ ማወቃቸው ነው። w21.01 18-19 አን. 17-18
ሐሙስ፣ መጋቢት 3
የእውነተኛውን አምላክ ቤት አቃጠለ፤ . . . እንዲሁም ውድ የሆኑትን ዕቃዎች በሙሉ አወደመ።—2 ዜና 36:19
ባቢሎናውያን ካደረሱት ውድመት በኋላ ምድሪቱን የተመለከቱ ሰዎች “ሰውም ሆነ እንስሳ የማይኖርባት ጠፍ መሬት ናት፤ ለከለዳውያንም ተሰጥታለች” ማለታቸው አያስገርምም። (ኤር. 32:43) የኢዩኤል ትንቢት ከተነገረ ከ200 ዓመት ገደማ በኋላ ይሖዋ፣ ነቢዩ ኤርምያስ ስለዚህ ጥቃት ሌላ መረጃ እንዲጽፍ አድርጓል። ኤርምያስ፣ ወራሪዎቹ በክፉ ድርጊቶች የሚካፈሉ እስራኤላውያንን ለማግኘት አሰሳ እንደሚያደርጉና ሁሉንም አድነው እንደሚይዟቸው ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “‘እነሆ፣ እኔ ብዙ ዓሣ አጥማጆችን እሰዳለሁ’ ይላል ይሖዋ፤ ‘እነሱንም ያጠምዷቸዋል። ከዚያም በኋላ ብዙ አዳኞችን እሰዳለሁ፤ እነሱም ከየተራራው፣ ከየኮረብታውና ከየቋጥኙ ስንጣቂ አድነው ይይዟቸዋል። . . . ለሠሩት በደልና ኃጢአት የሚገባቸውን ሙሉ ዋጋ እከፍላቸዋለሁ።’” ንስሐ ለመግባት ፈቃደኛ ያልሆኑት እስራኤላውያን ከባቢሎናውያን ወራሪዎች መሸሸግ የሚችሉበት ባሕርም ሆነ ጫካ አይኖርም።—ኤር. 16:16, 18፤ w20.04 5 አን. 12-13
ዓርብ፣ መጋቢት 4
ሎጥ [ዘገየ]።—ዘፍ. 19:16
ሎጥ በሕይወቱ ወሳኝ በሆነ ወቅት ላይ የይሖዋን መመሪያ ለመታዘዝ ዘግይቶ ነበር። ሎጥ ለይሖዋ ትእዛዝ ግድ እንደሌለው እንዲያውም ታዛዥ እንዳልሆነ ይሰማን ይሆናል። ይሖዋ ግን ተስፋ አልቆረጠበትም። “ይሖዋ ስለራራለት” መላእክቱ የእሱንና የቤተሰቡን እጅ ይዘው ከከተማዋ እንዲያስወጧቸው አደረገ። (ዘፍ. 19:15, 16) ይሖዋ ለሎጥ እንዲራራ ያነሳሱት አንዳንድ ምክንያቶች ሊኖሩ ይችላሉ። ሎጥ ቤቱን ለቆ ለመውጣት ያመነታው ከከተማዋ ውጭ የሚኖሩ ሰዎችን ስለፈራ ሊሆን ይችላል። ሎጥን ሊያሰጉት የሚችሉ ሌሎች ነገሮችም ነበሩ። ሎጥ፣ በሰዶም አቅራቢያ ባለ አንድ ሸለቆ ውስጥ በቅጥራን ጉድጓዶች ውስጥ ስለወደቁት ሁለት ነገሥታት ሳይሰማ አይቀርም። (ዘፍ. 14:8-12) ሎጥ ባልና አባት እንደመሆኑ መጠን የቤተሰቡ ሁኔታ አሳስቦት መሆን አለበት። በተጨማሪም ሎጥ ባለጸጋ ሆኖ ነበር፤ በመሆኑም ሰዶም ውስጥ ጥሩ ቤት ሠርቶ ሊሆን ይችላል። (ዘፍ. 13:5, 6) በእርግጥ ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች በሙሉ ሎጥ ይሖዋ የሰጠውን መመሪያ ወዲያውኑ እንዳይታዘዝ ሰበብ ሊሆኑ አይችሉም። ይሁንና ይሖዋ፣ ሎጥ በሠራው ስህተት ላይ አላተኮረም፤ ከዚህ ይልቅ ሎጥን “ጻድቅ ሰው” አድርጎ ቆጥሮታል።—2 ጴጥ. 2:7, 8፤ w20.04 18 አን. 13-14
ቅዳሜ፣ መጋቢት 5
[እንደ] ጤዛ ያለ የወጣቶች ሠራዊት ከጎንህ ይሰለፋል።—መዝ. 110:3
ወጣት ወንዶች፣ ከልጅነታችሁ ጀምሮ የሚያውቋችሁ ሰዎች እናንተን እንደ አዋቂ ለመመልከት ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። ይሖዋ ግን ከውጫዊ ገጽታችሁ አልፎ እንደሚመለከት መተማመን ትችላላችሁ። ምን ዓይነት ሰው እንደሆናችሁና ምን የማድረግ ብቃት እንዳላችሁ ያውቃል። (1 ሳሙ. 16:7) በተጨማሪም ከአምላክ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት አጠናክሩ። ዳዊት እንዲህ ያደረገው የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች በትኩረት በመመልከት ነው። የፍጥረት ሥራዎች ስለ ይሖዋ ምን እንደሚያስተምሩት ቆም ብሎ ያሰላስል ነበር። (መዝ. 8:3, 4፤ 139:14፤ ሮም 1:20) ማድረግ የምትችሉት ሌላው ነገር ደግሞ ይሖዋ ብርታት እንዲሰጣችሁ መጠየቅ ነው። ለምሳሌ አብረዋችሁ የሚማሩ ልጆች የይሖዋ ምሥክር በመሆናችሁ ያሾፉባችኋል? እንዲህ ያለ ሁኔታ የሚያጋጥማችሁ ከሆነ ይሖዋ ይህንን ተፈታታኝ ሁኔታ ለመወጣት እንዲረዳችሁ ጸልዩ። እንዲሁም በአምላክ ቃል፣ በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን እና በቪዲዮዎቻችን ውስጥ የሚገኘውን ምክር በሥራ ላይ አውሉ። ይሖዋ አንድን ተፈታታኝ ሁኔታ እንድትወጡ የረዳችሁ እንዴት እንደሆነ በተመለከታችሁ ቁጥር በእሱ ይበልጥ እየተማመናችሁ ትሄዳላችሁ። ከዚህም በተጨማሪ ሌሎች በይሖዋ እንደምትተማመኑ ሲመለከቱ እምነት ይጥሉባችኋል። w21.03 4 አን. 7
እሁድ፣ መጋቢት 6
የቅኖች ጸሎት [ይሖዋን] ደስ ያሰኘዋል።—ምሳሌ 15:8
የቅርብ ጓደኛሞች ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን አውጥተው ይነጋገራሉ። እኛስ ከይሖዋ ጋር እንዲህ ዓይነት ወዳጅነት ሊኖረን ይችላል? በሚገባ! ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ያነጋግረናል፤ በቃሉ ላይ ሐሳቡንና ስሜቱን አስፍሮልናል። እኛ ደግሞ በጸሎት አማካኝነት እሱን ልናነጋግረው እንዲሁም ውስጣዊ ሐሳባችንንና ስሜታችንን ልናካፍለው እንችላለን። አፍቃሪ ወዳጅ የሆነው ይሖዋ ጸሎታችንን በመስማት ብቻ ሳይወሰን ምላሽም ይሰጠናል። አንዳንድ ጊዜ ለጸሎታችን ፈጣን ምላሽ እናገኛለን። በሌሎች ጊዜያት ግን ለጸሎታችን መልስ ለማግኘት ስለ ጉዳዩ ደጋግመን መጸለይ ሊያስፈልገን ይችላል። ያም ቢሆን ይሖዋ ለጸሎታችን በትክክለኛው ጊዜና ከሁሉ በተሻለው መንገድ ምላሽ እንደሚሰጥ መተማመን እንችላለን። እርግጥ ነው፣ አምላክ የሚሰጠን ምላሽ እኛ ከጠበቅነው የተለየ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ ያጋጠመንን ችግር ከማስወገድ ይልቅ ችግሩን “በጽናት መቋቋም” የምንችልበትን ጥበብና ብርታት ይሰጠን ይሆናል። (1 ቆሮ. 10:13) በዋጋ ሊተመን ለማይችለው የጸሎት መብት አድናቆት እንዳለን ማሳየት የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ “ዘወትር ጸልዩ” የሚለውን መለኮታዊ ማሳሰቢያ ተግባራዊ ማድረግ ነው።—1 ተሰ. 5:17፤ w20.05 27-28 አን. 7-8
ሰኞ፣ መጋቢት 7
እስከ መጨረሻው የጸና . . . ይድናል።—ማቴ. 24:13
በረጅም ርቀት ውድድር የሚሳተፉ ሯጮች ትኩረት የሚያደርጉት ከፊት ለፊታቸው ባለው መንገድ ላይ ነው፤ ይህን የሚያደርጉት እንዳይደናቀፉ ነው። እነዚህ ሯጮች ቢወድቁም ተነስተው ሩጫቸውን ይቀጥላሉ። ትኩረት የሚያደርጉት ባደናቀፋቸው ነገር ላይ ሳይሆን በመጨረሻው መስመርና ሲያሸንፉ በሚያገኙት ሽልማት ላይ ነው። እኛም በሩጫችን ላይ ብዙ ጊዜ ልንደናቀፍ ይኸውም በምንናገረውና በምናደርገው ነገር ስህተት ልንሠራ እንችላለን። ወይም ደግሞ አብረውን የሚሮጡ ሰዎች በሚፈጽሙት ስህተት እንጎዳ ይሆናል። ይህ የሚጠበቅ ነገር ነው። ምክንያቱም ሁላችንም ፍጹም አይደለንም፤ እንዲሁም ሁላችንም የምንሮጠው ቀጭን በሆነው የሕይወት መንገድ ላይ ነው። ስለዚህ አንዳንድ ጊዜ ልንጋጭና ሌሎችን ‘ቅር የሚያሰኝ’ ነገር ልናደርግ እንችላለን። (ቆላ. 3:13) ሆኖም ባደናቀፈን ነገር ላይ ትኩረት ከማድረግ ይልቅ ከፊታችን በሚጠብቀን ሽልማት ላይ በማተኮር መሮጣችንን እንቀጥል። ባጋጠመን ነገር ተበሳጭተን ወይም ተመርረን ከወደቅንበት ለመነሳት ፈቃደኞች ካልሆንን የመጨረሻውን መስመር አልፈን ሽልማቱን ማግኘት አንችልም። ከዚህም ሌላ ቀጭን በሆነው የሕይወት ጎዳና ላይ ለመሮጥ ጥረት ለሚያደርጉ ሌሎች ሰዎች መሰናክል ልንሆን እንችላለን። w20.04 26 አን. 1፤ 28 አን. 8-9
ማክሰኞ፣ መጋቢት 8
[ይህ] መንግሥት . . . እነዚህን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል።—ዳን. 2:44
ነቢዩ ዳንኤል፣ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላላቸውና በተከታታይ ስለሚነሱ ሰብዓዊ መንግሥታት ገልጿል። እነዚህ መንግሥታት፣ በግዙፉ ምስል የተለያዩ ክፍሎች ተመስለዋል። ከእነዚህ ሰብዓዊ መንግሥታት የመጨረሻው፣ የብረትና የሸክላ ቅልቅል በሆነው የምስሉ እግር ተመስሏል። የምስሉ እግር፣ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትን ያመለክታል። የአምላክ መንግሥት ሰብዓዊ መንግሥታትን ለማጥፋት እርምጃ በሚወስድበት ወቅት ይህ ኃያል መንግሥት በሥልጣን ላይ እንደሚሆን ትንቢቱ ይጠቁማል። ሐዋርያው ዮሐንስም በይሖዋ ሕዝቦች ላይ ተጽዕኖ ስላሳደሩና በተከታታይ ስለሚነሱ የዓለም ኃያል መንግሥታት ገልጿል። ዮሐንስ፣ እነዚህን መንግሥታት ሰባት ራስ ባለው አውሬ መስሏቸዋል። የዚህ አውሬ ሰባተኛ ራስ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥትን ያመለክታል። ይህ ትኩረት የሚስብ ነው፤ ምክንያቱም አውሬው ሌላ ራስ እንደሚያወጣ የሚገልጽ ሐሳብ አናገኝም። ክርስቶስና ሰማያዊ ሠራዊቱ ይህን ሰባተኛ ራስ ጨምሮ አውሬውን ለማጥፋት እርምጃ በሚወስዱበት ወቅት ሰባተኛው ራስ በሥልጣን ላይ ይሆናል።—ራእይ 13:1, 2፤ 17:13, 14፤ w20.05 14 አን. 11-12
ረቡዕ፣ መጋቢት 9
አምላክ ፍቅር ነው።—1 ዮሐ. 4:8
ይህ አጭር ዓረፍተ ነገር አንድ መሠረታዊ እውነታ ያስገነዝበናል፤ ይኸውም የሕይወት ምንጭ የሆነው አምላክ የፍቅርም ምንጭ ነው። ይሖዋ ይወደናል! ፍቅሩ ደህንነት እንዲሰማን፣ ደስተኛ እንድንሆንና አርኪ ሕይወት እንዲኖረን ያደርጋል። ፍቅር ማሳየት ለክርስቲያኖች ለምርጫ የተተወ ጉዳይ አይደለም። ትእዛዝ ነው። (ማቴ. 22:37-40) ይሖዋን ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ የመጀመሪያውን ትእዛዝ መፈጸም ቀላል ይሆንልናል። ምክንያቱም ይሖዋ ፍጹም ነው፤ እኛን የሚይዘንም በአሳቢነትና በደግነት ነው። ሁለተኛውን ትእዛዝ መፈጸም ግን አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል። ለምን? ምክንያቱም የቅርብ ባልንጀሮቻችን የሆኑት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍጹማን አይደሉም። አንዳንድ ጊዜ አሳቢነትና ደግነት የጎደለው ነገር ሊናገሩን ወይም ሊያደርጉብን ይችላሉ። ይሖዋ ይህ ተፈታታኝ ሁኔታ እንዳለብን ያውቃል፤ ስለዚህ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች እርስ በርስ መዋደድ ያለብን ለምን እና እንዴት እንደሆነ የሚገልጽ ቀጥተኛ ምክር እንዲጽፉልን አድርጓል። ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች አንዱ ሐዋርያው ዮሐንስ ነው።—1 ዮሐ. 3:11, 12፤ w21.01 8 አን. 1-2
ሐሙስ፣ መጋቢት 10
ሰይጣን መግቢያ ቀዳዳ እንዳያገኝ።—2 ቆሮ. 2:11
ይሖዋን ማገልገል የጀመርነው በቅርቡም ይሁን ከረጅም ዓመታት በፊት ‘ሰይጣን ልቤን ለመከፋፈል የሚያደርገውን ጥረት እየተቃወምኩ ነው?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ ያስፈልገናል። ለምሳሌ ያህል፣ የፆታ ስሜት ሊቀሰቅስ የሚችል ምስል በቴሌቪዥን ወይም በኢንተርኔት ቢገጥምህ ምን ታደርጋለህ? ምስሉ ወይም ፊልሙ ፖርኖግራፊ ሊባል እንደማይችል ሰበብ ማቅረብ ቀላል ሊሆን ይችላል። ሆኖም ሰይጣን ይህን አጋጣሚ ተጠቅሞ ልብህን ለመክፈል እየጣረ ይሆን? ምስሉ አንድ ሰው እንጨት ሲጠርብ ከሚጠቀምበት ሽብልቅ ወይም ትንሽ ሹል ብረት ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ሰውየው መጀመሪያ ላይ የብረቱን ሹል ጫፍ እንጨቱ ውስጥ ያስገባዋል። ሰውየው ብረቱን ይበልጥ ወደ ውስጥ እያስገባው ሲሄድ እንጨቱ ይሰነጠቃል። በቴሌቪዥን ወይም በኢንተርኔት ላይ የሚቀርብ አጠያያቂ ምስል እንደ ሽብልቁ ሹል ጫፍ ይሆን? አንድ ሰው መጀመሪያ ላይ ትንሽ እንደሆነ ወይም ጉዳት እንደሌለው የሚሰማው ነገር እንኳ ብዙም ሳይቆይ ልቡ እንዲከፈል ሊያደርግ ይችላል፤ ይህም ንጹሕ አቋሙን እንዲያጎድፍ የሚያደርግ ኃጢአት ወደ መፈጸም ሊመራው ይችላል። እንግዲያው ተገቢ ያልሆነ ማንኛውም ነገር ወደ ልብህ እንዲገባ አትፍቀድ! ልብህ ምንጊዜም የይሖዋን ስም እንዲፈራ አንድ አድርገው! w20.06 11-12 አን. 14-15
ዓርብ፣ መጋቢት 11
ጠንካሮች ያልሆኑትን ሰዎች ድክመት [እንሸከም]።—ሮም 15:1
ለቀዘቀዙ አስፋፊዎች ቀጣይ የሆነ ድጋፍ ልናደርግላቸው ይገባል። በኢየሱስ ምሳሌ ላይ እንደተገለጸው የጠፋ ልጅ ሁሉ እነዚህ ሰዎችም ስሜታቸው በጣም ስለተጎዳ ለማገገም ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። (ሉቃስ 15:17-24) ከዚህም ሌላ በሰይጣን ዓለም ውስጥ ባጋጠማቸው ነገር የተነሳ በመንፈሳዊ መዳከማቸው አይቀርም። ስለዚህ በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩ መርዳት ያስፈልገናል። ስለጠፋችው በግ በሚናገረው ምሳሌ ላይ ኢየሱስ፣ እረኛው በጓን በጫንቃው ላይ ተሸክሞ ወደ መንጋው እንደሚወስዳት ገልጿል። እረኛው የጠፋችውን በግ ፈልጎ ለማግኘት ብዙ ጊዜና ጥረት እንደጠየቀበት የታወቀ ነው። ካገኛትም በኋላ ግን በጓን ተሸክሞ ወደ መንጋው መውሰድ እንደሚያስፈልገው ይገነዘባል፤ ምክንያቱም በጓ ወደ መንጋው ለመመለስ አቅም አይኖራትም። (ሉቃስ 15:4, 5) አንዳንድ የቀዘቀዙ አስፋፊዎች ያሉባቸውን ድክመቶች እንዲያሸንፉ ለመርዳት ብዙ ጊዜና ጥረት ሊጠይቅብን ይችላል። ሆኖም የይሖዋ መንፈስ፣ ቃሉ እንዲሁም በጉባኤው አማካኝነት የምናገኛቸው ጽሑፎች በሚሰጡን እርዳታ ተጠቅመን በመንፈሳዊ እንዲያገግሙ ልናግዛቸው እንችላለን። ታዲያ አንድን የቀዘቀዘ ሰው እንድታስጠና ብትጠየቅ የተሰጠህን መብት በደስታ ትቀበላለህ? w20.06 28 አን. 14-15
ቅዳሜ፣ መጋቢት 12
እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ።—ዮሐ. 13:35
እያንዳንዳችን የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ የሆነውን ፍቅር ማሳየት ይኖርብናል። ይሁንና “ትክክለኛ እውቀትና ጥልቅ ግንዛቤ” ማግኘትም ያስፈልገናል። (ፊልጵ. 1:9) ካልሆነ የከሃዲዎችን ትምህርት ጨምሮ “በማንኛውም የትምህርት ነፋስ፣ በሰዎች የማታለያ ዘዴና በተንኮል በተወጠነ አሳሳች ሐሳብ” ልንታለል እንችላለን። (ኤፌ. 4:14) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. በርካታ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስን መከተል ባቆሙበት ወቅት ሐዋርያው ጴጥሮስ ኢየሱስ “የዘላለም ሕይወት ቃል” እንዳለው እንደሚተማመን ገልጿል። (ዮሐ. 6:67, 68) በወቅቱ ጴጥሮስ ኢየሱስ የተናገረውን ነገር ሙሉ በሙሉ ባይረዳም ስለ ክርስቶስ እውነቱን ማወቁ በታማኝነት እንዲጸና ረድቶታል። እናንተም በመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ላይ ያላችሁን የመተማመን ስሜት ማጠናከር ትችላላችሁ። እንዲህ ካደረጋችሁ ማንኛውንም ፈተና የሚቋቋም እምነት ይኖራችኋል፤ እንዲሁም ሌሎችም ጠንካራ እምነት እንዲገነቡ መርዳት ትችላላችሁ።—2 ዮሐ. 1, 2፤ w20.07 8 አን. 2፤ 13 አን. 18
እሁድ፣ መጋቢት 13
ልጆቼ ሆይ፣ በተግባርና በእውነት እንጂ በቃልና በአንደበት ብቻ አንዋደድ።—1 ዮሐ. 3:18
ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እውነት ውስጥ እንዲጸኑ ለመርዳት ርኅራኄ ማሳየት ያስፈልገናል። (1 ዮሐ. 3:10, 11, 16, 17) ሁሉ ነገር በተመቻቸበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ችግሮች በሚያጋጥሙበት ጊዜም ጭምር እርስ በርስ መዋደድ ይኖርብናል። ለምሳሌ ያህል፣ የሚወደውን ሰው በሞት በማጣቱ ምክንያት ማጽናኛ ወይም ሌላ ዓይነት እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው ታውቃለህ? አሊያም ደግሞ አንዳንድ ወንድሞች በተፈጥሮ አደጋ ምክንያት ንብረታቸውን እንዳጡ እንዲሁም የስብሰባ አዳራሻቸው ወይም ቤታቸው ጥገና እንደሚያስፈልገው ሰምተህ ይሆን? ለወንድሞቻችን ያለን ፍቅርና ርኅራኄ ጠንካራ መሆኑ በዋነኝነት የሚታየው በንግግራችን ሳይሆን በተግባራችን ነው። እርስ በርስ በመዋደድ በሰማይ የሚኖረውን አፍቃሪ አባታችንን መምሰል እንችላለን። (1 ዮሐ. 4:7, 8) ፍቅር ማሳየት የምንችልበት አንዱ ወሳኝ መንገድ እርስ በርስ ይቅር መባባል ነው። ለምሳሌ ያህል አንድ ሰው ስሜታችንን ከጎዳው በኋላ ይቅርታ ሊጠይቀን ይችላል። ይህን ሰው ይቅር በማለትና በደሉን በመርሳት ፍቅር ማሳየት እንችላለን።—ቆላ. 3:13፤ w20.07 24 አን. 14-15
ሰኞ፣ መጋቢት 14
ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት [ይነሳሉ]።—ሥራ 24:15
ከሞት የሚነሳ እያንዳንዱ ሰው አስጠኚ ይመደብለት ይሆን? እነዚህ ሰዎች እውነትን ከተማሩ በኋላ በጉባኤዎች ውስጥ የሚታቀፉበትና ከእነሱ በኋላ የሚነሱ ሰዎችን እንዲያስተምሩ ሥልጠና የሚያገኙበት ዝግጅት ይደረግ ይሆን? ይህ ጊዜው ሲደርስ የምናየው ነገር ይሆናል። ይሁንና አንድ የምናውቀው ነገር አለ፤ በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ “[ምድር] በይሖዋ እውቀት ትሞላለች።” (ኢሳ. 11:9) በእርግጥም ያ ሺህ ዓመት በሥራ የምንጠመድበት ሆኖም አስደሳች ወቅት ይሆናል! በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት የአምላክ ምድራዊ ልጆች በሙሉ ይሖዋን ለማስደሰት ሲሉ ማስተካከያዎች ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ስለዚህ የአምላክ ሕዝቦች፣ ከሞት የሚነሱ ሰዎችን የኃጢአት ዝንባሌዎቻቸውን እንዲያሸንፉና የይሖዋን መሥፈርቶች እንዲከተሉ በሚረዱበት ወቅት የእነሱን ስሜት መረዳት አይከብዳቸውም። (1 ጴጥ. 3:8) ትንሣኤ ያገኙት ሰዎች፣ ትሑት በሆኑትና ‘የራሳቸውን መዳን ከፍጻሜ ለማድረስ ተግተው’ በሚሠሩት የይሖዋ ሕዝቦች ባሕርይ መማረካቸው አይቀርም።—ፊልጵ. 2:12፤ w20.08 16 አን. 6-7
ማክሰኞ፣ መጋቢት 15
እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤ . . . ራሱን ከሌላ ሰው ጋር [አያወዳድር]።—ገላ. 6:4
ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የሰጠውን ምክር በመከተል የራሳችንን ተግባር ከመረመርን፣ ሌሎች የሌሏቸው ተሰጥኦዎችና ችሎታዎች እንዳሉን እናስተውላለን። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ከመድረክ የማስተማር ችሎታው ያን ያህል ላይሆን ይችላል፤ ሆኖም ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በጣም ውጤታማ ሊሆን ይችላል። አሊያም ደግሞ በጉባኤው ያሉ ሌሎች ሽማግሌዎችን ያህል በሚገባ የተደራጀ ላይሆን ይችላል፤ ይሁን እንጂ አስፋፊዎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክር ሲፈልጉ በነፃነት የሚቀርቡት አፍቃሪ እረኛ ሊሆን ይችላል። ወይም ደግሞ እንግዳ ተቀባይ በመሆኑ ይታወቅ ይሆናል። (ዕብ. 13:2, 16) ጠንካራ ጎናችን እና ያሉን ስጦታዎች ግልጽ ሆነው ሲታዩን ለጉባኤው በምናበረክተው አስተዋጽኦ ረክተን እንኖራለን። ከእኛ የተለየ ስጦታ ባላቸው ወንድሞችም አንቀናም። በጉባኤው ውስጥ ያለን ድርሻ ምንም ይሁን ምን፣ ሁላችንም አገልግሎታችንን ለማሻሻልና ችሎታዎቻችንን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። w20.08 24 አን. 16-18
ረቡዕ፣ መጋቢት 16
አንድም ሰው ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሕዝብ [አየሁ]።—ራእይ 7:9
በ1935 በዋሽንግተን ዲሲ፣ ዩናይትድ ስቴትስ በተካሄደ ትልቅ ስብሰባ ላይ ወንድም ራዘርፎርድ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” የሚል ርዕስ ያለው ታሪካዊ ንግግር አቅርቦ ነበር። ወንድም ራዘርፎርድ በራእይ 7:9 ላይ የተገለጹትን ‘የእጅግ ብዙ ሕዝብ’ ማንነት በንግግሩ ላይ አብራራ። እስከዚያ ጊዜ ድረስ እጅግ ብዙ ሕዝብ በቂ ታማኝነት ባለማሳየታቸው በሰማይ ሁለተኛ ደረጃ የሚሰጣቸው ክርስቲያኖችን እንደሚያመለክት ይታሰብ ነበር። ወንድም ራዘርፎርድ እጅግ ብዙ ሕዝብ ለሰማያዊ ሕይወት የተመረጡ ሰዎችን እንደማያመለክት ጥቅሶችን ተጠቅሞ አብራራ፤ ከዚህ ይልቅ “ታላቁን መከራ” በሕይወት አልፈው በምድር ላይ ለዘላለም የሚኖሩ የክርስቶስ ሌሎች በጎችን እንደሚያመለክት ገለጸ። (ራእይ 7:14) ኢየሱስ “ከዚህ ጉረኖ ያልሆኑ ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነሱንም ማምጣት አለብኝ፤ ድምፄንም ይሰማሉ፤ ሁሉም አንድ መንጋ ይሆናሉ፤ አንድ እረኛም ይኖራቸዋል” ሲል ቃል ገብቷል። (ዮሐ. 10:16) እነዚህ በግ መሰል ሰዎች ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ለዘላለም የመኖር ተስፋ ያላቸው ታማኝ የይሖዋ ምሥክሮች ናቸው።—ማቴ. 25:31-33, 46፤ w21.01 14 አን. 1-2
ሐሙስ፣ መጋቢት 17
በስሜ [የተነሳ] ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል፤ እስከ መጨረሻው የጸና ግን ይድናል።—ማቴ. 10:22
ለመጽናትና የስብከት ሥራችንን ለማጠናቀቅ ራሳችንን መገሠጽ ይኖርብናል። (ማቴ. 28:19, 20) ራስን የመገሠጽ ችሎታ በውርስ የሚገኝ ነገር አይደለም። እንዲያውም በተፈጥሯችን የሚቀናን ብዙም ጥረት የማይጠይቅብንን ነገር ማድረግ ነው። ራስን የመገሠጽ ችሎታ ለማዳበር ራስን መግዛት ያስፈልጋል። በመሆኑም የሚከብዱንን ነገሮች ለማድረግ ራሳችንን ማሠልጠን እንድንችል እርዳታ ያስፈልገናል። ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ይህን እርዳታ ይሰጠናል። (ገላ. 5:22, 23) ሐዋርያው ጳውሎስ ራሱን የሚገሥጽ ሰው ነበር። ጳውሎስ፣ ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ ‘ሰውነቱን መጎሰም’ እንዳስፈለገው በሐቀኝነት ተናግሯል። (1 ቆሮ. 9:25-27) ሐዋርያው፣ ሌሎችም ራሳቸውን እንዲገሥጹ እንዲሁም ሁሉን ነገር “በአግባብና በሥርዓት” እንዲያከናውኑ አሳስቧል። (1 ቆሮ. 14:40) እኛም ጥሩ መንፈሳዊ ልማድ ይዘን ለመቀጠል ራሳችንን መገሠጽ ይኖርብናል፤ እንዲህ ያለው ልማድ በስብከቱ ሥራ አዘውትሮ መካፈልን ይጨምራል።—ሥራ 2:46፤ w20.09 6-7 አን. 15-17
ዓርብ፣ መጋቢት 18
ምሥራቹ ለብሔራት ሁሉ መሰበክ አለበት።—ማር. 13:10
በዛሬው ጊዜ በብዙ አገሮች ውስጥ ያለገደብ መስበክ እንችላለን። አንተስ የምትኖረው የአምልኮ ነፃነት ባለበት አገር ውስጥ ነው? ከሆነ ‘ይህን ነፃነት እንዴት እየተጠቀምኩበት ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ብዙ ሥራ ባለበት በዚህ የመጨረሻ ዘመን የይሖዋ ድርጅት፣ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ የስብከትና የማስተማር ዘመቻ እያካሄደ ነው። የይሖዋ ሕዝቦች ብዙ አጋጣሚዎች ተከፍተውላቸዋል። የሰላሙን ጊዜ በጥበብ ልትጠቀምበት የምትችለው እንዴት ነው? (2 ጢሞ. 4:2) ለምን ያለህበትን ሁኔታ አትገመግምም? አንተ ወይም ከቤተሰብህ አባላት አንዱ በስብከቱ ሥራ የምታደርጉትን ተሳትፎ መጨመር ምናልባትም አቅኚ ሆናችሁ ማገልገል ትችሉ ይሆን? አሁን ያለንበት ወቅት ሀብትና ቁሳዊ ንብረት የምናካብትበት አይደለም፤ እነዚህ ነገሮች ታላቁን መከራ አያልፉም። (ምሳሌ 11:4፤ ማቴ. 6:31-33፤ 1 ዮሐ. 2:15-17) በርካታ አስፋፊዎች ለስብከቱና ለማስተማሩ ሥራ እንዲረዳቸው ሲሉ አዲስ ቋንቋ ተምረዋል። የአምላክ ድርጅትም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች በማዘጋጀት ለእነዚህ አስፋፊዎች እገዛ እያደረገላቸው ነው! w20.09 16 አን. 9-11
ቅዳሜ፣ መጋቢት 19
መልካሙን ውጊያ መዋጋትህን [ቀጥል]።—1 ጢሞ. 1:18
ጎበዝ ወታደር ታማኝ ነው። የሚወደውን ሰው ወይም ከፍ አድርጎ የሚመለከተውን ነገር ለመጠበቅ ሲል ይፋለማል። ጳውሎስ ጢሞቴዎስን ለአምላክ ማደርን እንዲያዳብር አበረታቶታል፤ ይህ ባሕርይ አምላክን መውደድን እና ለእሱ ታማኝ መሆንን የሚያመለክት ነው። (1 ጢሞ. 4:7) ለአምላክ ያለን ፍቅርና ታማኝነት እየጨመረ ሲሄድ እውነትን አጥብቀን ለመያዝ ያለን ፍላጎት ያድጋል። (1 ጢሞ. 4:8-10፤ 6:6) ጎበዝ ወታደር ምንጊዜም ለውጊያ ብቁ እንዲሆን ራሱን መገሠጽም ያስፈልገዋል። ጢሞቴዎስ መንፈሳዊ ብቃቱን ጠብቆ መመላለስ ችሏል፤ ለዚህ የረዳው ከክፉ ምኞቶች እንዲሸሽ፣ አምላካዊ ባሕርያትን እንዲከታተል እንዲሁም ከእምነት አጋሮቹ ጋር እንዲሆን ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረጉ ነው። (2 ጢሞ. 2:22) ይህን ለማድረግ ደግሞ ራሱን መገሠጽ ጠይቆበት ነበር። እኛም ከሥጋ ምኞቶቻችን ጋር በምናደርገው ውጊያ ድል ለመቀዳጀት ራሳችንን መገሠጽ ያስፈልገናል። (ሮም 7:21-25) አሮጌውን ስብዕና አውልቀን ለመጣልና አዲሱን ስብዕና ለመልበስ የምናደርገው ያልተቋረጠ ጥረትም ራስን መገሠጽ ይጠይቃል። (ኤፌ. 4:22, 24) በተጨማሪም ቀኑን ሙሉ ስንደክም ውለን ምሽት ላይ ስብሰባ ለመገኘት ራሳችንን ማስገደድ ይኖርብናል።—ዕብ. 10:24, 25፤ w20.09 28 አን. 9-11
እሁድ፣ መጋቢት 20
ሥርዓትህን በሕይወቴ ዘመን ሁሉ፣ እስከ መጨረሻው ለመጠበቅ ቆርጫለሁ።—መዝ. 119:112
ተማሪው እድገት አድርጎ ራሱን እንዲወስንና እንዲጠመቅ በምንረዳበት ወቅት ታጋሽ መሆን ያስፈልገናል። ሆኖም ግለሰቡ ይሖዋ አምላክን የማገልገል ፍላጎት እንዳለው መገምገም የሚያስፈልገን ጊዜ አለ። ተማሪው የኢየሱስን ትእዛዛት ለመከተል እየሞከረ እንደሆነ የሚጠቁም ነገር አለ? ወይስ ፍላጎቱ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ማግኘት ብቻ ነው? ተማሪው የሚያደርገውን እድገት በየጊዜው ገምግም። ለምሳሌ፣ ተማሪው ለይሖዋ ያለውን ፍቅር ይገልጻል? ወደ ይሖዋ ይጸልያል? (መዝ. 116:1, 2) መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ያስደስተዋል? (መዝ. 119:97) ስብሰባዎች ላይ አዘውትሮ ይገኛል? (መዝ. 22:22) በሕይወቱ ውስጥ አንዳንድ አስፈላጊ ማስተካከያዎችን እያደረገ ነው? የሚማረውን ነገር ለቤተሰቡና ለጓደኞቹ መናገር ጀምሯል? (መዝ. 9:1) ከሁሉ በላይ ደግሞ የይሖዋ ምሥክር መሆን ይፈልጋል? (መዝ. 40:8) ተማሪው ከላይ ከተጠቀሱት ነገሮች መካከል በየትኛውም አቅጣጫ እድገት እያደረገ ካልሆነ ምክንያቱን በዘዴ ለማወቅ ጥረት አድርግ፤ ከዚያም ስለ ጉዳዩ በደግነት ሆኖም በግልጽ አነጋግረው። w20.10 18 አን. 14-15
ሰኞ፣ መጋቢት 21
እኔን የላከኝ ከእኔ ጋር ነው፤ ሁልጊዜ እሱን ደስ የሚያሰኘውን ስለማደርግ ብቻዬን አልተወኝም።—ዮሐ. 8:29
በሰማይ የሚኖረው የኢየሱስ አባት ሁሌም ጥሩ ምርጫዎችን ያደርጋል፤ የኢየሱስ ሰብዓዊ ወላጆችም ጥበብ የሚንጸባረቅባቸው ውሳኔዎችን አድርገዋል። ኢየሱስ ካደገ በኋላ ግን የራሱን ምርጫዎች ማድረግ ነበረበት። (ገላ. 6:5) እኛ የመምረጥ ነፃነት እንዳለን ሁሉ እሱም የመምረጥ ነፃነት ነበረው። የራሱን ፍላጎት ለማስቀደም መምረጥ ይችል ነበር። እሱ ግን ከይሖዋ ጋር ያለውን ጥሩ ዝምድና ጠብቆ ለመኖር መርጧል። ኢየሱስ በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ስለሚጫወተው ሚና ካወቀ በኋላ ይህን ኃላፊነት ለመቀበል መርጧል። (ዮሐ. 6:38) በብዙዎች ዘንድ እንደሚጠላ ማወቁ የተሰጠው ኃላፊነት ምን ያህል ከባድ እንደሆነ እንዲያስብ ሳያደርገው አልቀረም። ያም ሆኖ ራሱን ለይሖዋ ለማስገዛት መርጧል። ኢየሱስ በ29 ዓ.ም. ሲጠመቅ በሕይወቱ ውስጥ ዋነኛው ትኩረቱ የይሖዋን ፈቃድ መፈጸም ነበር። (ዕብ. 10:5-7) በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ ለመሞት እያጣጣረ በነበረበት ጊዜም እንኳ የአባቱን ፈቃድ ለመፈጸም ያለውን ቁርጠኝነት አላላላም።—ዮሐ. 19:30፤ w20.10 29 አን. 12፤ 30 አን. 15
ማክሰኞ፣ መጋቢት 22
ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም።—ዕብ. 13:5
በሕመም ወይም በሌሎች ተፈታታኝ ሁኔታዎች የተነሳ የተጨነቁ ወንድሞችና እህቶች በጉባኤ ውስጥ አሉ? ወይም ደግሞ የሚወዱትን ሰው በሞት ያጡ ይኖሩ ይሆናል። እርዳታ የሚያስፈልገው ሰው እንዳለ ካወቅን ግለሰቡን የሚጠቅም ነገር መናገር ወይም ማድረግ እንድንችል የይሖዋን እርዳታ እንጠይቅ። የምንናገረው ወይም የምናደርገው ነገር የእምነት ባልንጀራችን በዚያ ወቅት የሚያስፈልገውን ማበረታቻ እንዲያገኝ ሊያደርግ ይችላል። (1 ጴጥ. 4:10) ይሖዋ አብሮን እንደሆነ ስለምናውቅ አንፈራም። በኢየሱስና በመላእክቱ አማካኝነት ይረዳናል። በተጨማሪም ከዓላማው ጋር የሚስማማ በሚሆንበት ወቅት ይሖዋ በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ተጠቅሞ ይረዳናል። እንዲሁም ብዙዎቻችን በሕይወታችን እንዳየነው ይሖዋ፣ ቅዱስ መንፈሱን ተጠቅሞ የአገልጋዮቹን ልብ በማነሳሳት ለክርስቲያን ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው እንዲደርሱላቸው ያደርጋል። በእርግጥም እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “ይሖዋ ረዳቴ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?” ብለን በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን።—ዕብ. 13:6፤ w20.11 17 አን. 19-20
ረቡዕ፣ መጋቢት 23
ሳትረበሹ፣ ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ።—ኢሳ. 30:15
ሐዋርያት ይሖዋ ከእነሱ ጋር እንደሆነ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ አግኝተዋል። ተአምራት እንዲፈጽሙ ኃይል ሰጥቷቸው ነበር። (ሥራ 5:12-16፤ 6:8) በእርግጥ፣ እኛ ተአምራት የመፈጸም ችሎታ የለንም። ያም ቢሆን ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት ማረጋገጫ ሰጥቶናል፤ ለጽድቅ ስንል መከራ በሚደርስብን ወቅት በእኛ ደስ እንደሚሰኝና መንፈሱን እንደሚሰጠን አረጋግጦልናል። (1 ጴጥ. 3:14፤ 4:14) እንግዲያው ‘ወደፊት ከባድ ስደት ቢደርስብኝ ታማኝነቴን አጎድል ይሆን?’ እያልን መጨነቅ አያስፈልገንም፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እኛን ለመደገፍና ለማዳን ባለው ችሎታ ላይ ያለንን እምነት ከአሁኑ ማጠናከራችን የተሻለ ነው። ኢየሱስ በገባው ቃል ላይ እምነት እንጣል፤ ኢየሱስ “ተቃዋሚዎቻችሁ ሁሉ በአንድነት ሆነው ሊቋቋሙት ወይም ሊከራከሩት የማይችሉት አንደበትና ጥበብ እሰጣችኋለሁ” በማለት ቃል ገብቷል። በተጨማሪም “ከጸናችሁ ሕይወታችሁን ታተርፋላችሁ” የሚል ዋስትና ተሰጥቶናል። (ሉቃስ 21:12-19) እንዲሁም ይሖዋ፣ ታማኝ አገልጋዮቹ ቢሞቱም እንኳ ስለ እነሱ እያንዳንዱን ጥቃቅን ነገር ያስታውሳል። በመሆኑም ከሞት ሊያስነሳቸው ይችላል። w21.01 4 አን. 12
ሐሙስ፣ መጋቢት 24
ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ በአምላክ ተስፋ አደርጋለሁ።—ሥራ 24:15
ስለ ትንሣኤ ተስፋ የተናገረው የመጀመሪያው ሰው ሐዋርያው ጳውሎስ አልነበረም። በጥንት ዘመን የኖረው ኢዮብም ስለ ትንሣኤ ተናግሯል። ኢዮብ አምላክ እንደሚያስታውሰውና ከሞት እንደሚያስነሳው እርግጠኛ ነበር። (ኢዮብ 14:7-10, 12-15) ‘የሙታን ትንሣኤ’ ለክርስትና “መሠረት” ከሆኑት ትምህርቶች አንዱ ነው። (ዕብ. 6:1, 2) ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ ምዕራፍ 15 ላይ ስለ ትንሣኤ ማብራሪያ ሰጥቷል። የጳውሎስ መልእክት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች አበረታቷቸው መሆን አለበት። ይህ ምዕራፍ እኛንም ሊያበረታታን እና ለረጅም ጊዜ የነበረንን ተስፋ ሊያጠናክርልን ይችላል። የኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ፣ በሞት ያጣናቸው ሰዎች እንደሚነሱ ዋስትና ይሰጠናል፤ እንዲሁም እኛ ራሳችን እንኳ ብንሞት ትንሣኤ እንደምናገኝ ያረጋግጥልናል። የክርስቶስ ትንሣኤ፣ ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች የሰበከው “ምሥራች” ክፍል ነበር። (1 ቆሮ. 15:1, 2) እንዲያውም ጳውሎስ፣ አንድ ክርስቲያን በኢየሱስ ትንሣኤ ካላመነ እምነቱ ከንቱ እንደሆነ ተናግሯል።—1 ቆሮ. 15:17፤ w20.12 2 አን. 2-4
ዓርብ፣ መጋቢት 25
[ጴጥሮስ] ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አስታወሰ። ከዚያም ወደ ውጭ ወጥቶ ምርር ብሎ አለቀሰ።—ማቴ. 26:75
ሐዋርያው ጴጥሮስን ተስፋ እንዳይቆርጥ የረዳው ምንድን ነው? በመጀመሪያ ደረጃ፣ ቀደም ሲል ኢየሱስ የጴጥሮስ እምነት እንዳይጠፋ ጸልዮ ነበር። ይሖዋ የኢየሱስን ልባዊ ጸሎት መልሶለታል። በኋላም ኢየሱስ ለጴጥሮስ ብቻውን ተገልጦለታል፤ ይህን ያደረገው እሱን ለማበረታታት መሆን አለበት። (ሉቃስ 22:32፤ 24:33, 34፤ 1 ቆሮ. 15:5) ከዚህም ሌላ ሐዋርያቱ ሌሊቱን ሙሉ ዓሣ ለማጥመድ ሲሞክሩ አድረው ምንም ዓሣ ባልያዙበት ወቅት ኢየሱስ ተገልጦላቸው ነበር። በዚህ ወቅት ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ለእሱ ያለውን ፍቅር የሚገልጽበት አጋጣሚ ሰጥቶታል። ኢየሱስ የቅርብ ወዳጁን ይቅር ብሎት ነበር፤ እንዲሁም ተጨማሪ ሥራ በአደራ ሰጥቶታል። (ዮሐ. 21:15-17) ኢየሱስ ጴጥሮስን የያዘበት መንገድ የኢየሱስን ምሕረት ያሳያል፤ ኢየሱስ ደግሞ የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ ነው። በመሆኑም ስህተት በምንሠራበት ወቅት፣ ይሖዋ መቼም ይቅር እንደማይለን ሊሰማን አይገባም። ሰይጣን እንዲህ ያለ ስሜት እንዲያድርብን እንደሚፈልግ መዘንጋት አይኖርብንም። ከዚህ ይልቅ ራሳችንንም ሆነ የበደሉንን ሰዎች በተመለከተ፣ ሩኅሩኅና አፍቃሪ የሆነውን የሰማዩን አባታችንን ዓይነት አመለካከት ለመያዝ ጥረት እናድርግ።—መዝ. 103:13, 14፤ w20.12 20-21 አን. 17-19
ቅዳሜ፣ መጋቢት 26
በልበ ሙሉነት እመላለሳለሁ።—መዝ. 27:3
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሳይረበሹ በይሖዋ ተማምነው መኖር ሲገባቸው እንዲህ ሳያደርጉ የቀሩ ሰዎች ምሳሌ ተጠቅሷል፤ የእነዚህን ሰዎች ታሪክ በመመርመር ትምህርት ማግኘት እንችላለን። የእነሱን ታሪክ ማጥናታችን የሠሩትን ስህተት እንዳንደግም ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ ንጉሥ አሳ መጀመሪያ ላይ ችግር ሲያጋጥመው በይሖዋ ታምኖ ነበር። በኋላ ላይ ግን የይሖዋን እርዳታ ከመጠየቅ ይልቅ ችግሩን በራሱ መንገድ ለመፍታት ሞከረ። (2 ዜና 16:1-3, 12) መጀመሪያ ላይ ሲታይ፣ አሳ የእስራኤልን ሠራዊት ለመመከት የሶርያውያንን እርዳታ መጠየቁ የጥበብ አካሄድ ይመስል ይሆናል። ያገኘው ስኬት ግን ዘላቂ አልነበረም። ይሖዋ አንድ ነቢይ ልኮ “በአምላክህ በይሖዋ ከመታመን ይልቅ በሶርያ ንጉሥ ስለታመንክ የሶርያ ንጉሥ ሠራዊት ከእጅህ አምልጧል” አለው። (2 ዜና 16:7) እንግዲያው ይሖዋ በቃሉ አማካኝነት የሰጠውን መመሪያ ሳንፈልግ ችግሮቻችንን በራሳችን መፍታት እንችላለን ብለን እንዳናስብ እንጠንቀቅ። አፋጣኝ ውሳኔ የሚጠይቅ ነገር ቢያጋጥመን እንኳ ተረጋግተን የይሖዋን እርዳታ መጠየቅ ይኖርብናል፤ እሱም እንዲሳካልን ይረዳናል። w21.01 6 አን. 13-15
እሁድ፣ መጋቢት 27
ከእንግዲህ ወዲህ አይራቡም።—ራእይ 7:16
ከባድ የኢኮኖሚ ጫና ወይም አለመረጋጋትና ጦርነት ባለባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች በረሃብ እየተጠቁ ነው። ሌሎች ደግሞ በእምነታቸው ምክንያት ታስረዋል። ያም ቢሆን የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት፣ ይህ ክፉ ሥርዓት ከጠፋ በኋላ ምንጊዜም የተትረፈረፈ ቁሳዊና መንፈሳዊ ምግብ እንደሚያገኙ ስለሚያውቁ ደስተኞች ናቸው። የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት፣ የሰይጣን ሥርዓት በሚጠፋበት ወቅት ይሖዋ በብሔራት ላይ የሚያፈሰው እንደ ‘ሐሩር’ የሚያቃጥል ቁጣ አይነካቸውም። ታላቁ መከራ ካበቃ በኋላ ኢየሱስ ከጥፋቱ የተረፉትን እነዚህን ሰዎች “ወደ [ዘላለም] ሕይወት ውኃ” ይመራቸዋል። (ራእይ 7:17) የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ምን ዓይነት አስደሳች ተስፋ እንዳላቸው እስቲ አስበው። በምድር ላይ ከኖሩት በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል ሞትን የማይቀምሱት እነሱ ናቸው። (ዮሐ. 11:26) በእርግጥም የሌሎች በጎች አባላት ለይሖዋና ለኢየሱስ አመስጋኝ እንዲሆኑ የሚያነሳሳ አስደናቂ ተስፋ አላቸው! w21.01 16-17 አን. 11-12
ሰኞ፣ መጋቢት 28
ጌታ . . . ታማኝ ነው፤ እሱ ያጠነክራችኋል፤ እንዲሁም . . . ይጠብቃችኋል።—2 ተሰ. 3:3
ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ደቀ መዛሙርቱ ወደፊት ስለሚያጋጥሟቸው ችግሮች እያሰበ ነበር። ለወዳጆቹ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ አባቱን ‘ከክፉው እንዲጠብቃቸው’ ጠይቆታል። (ዮሐ. 17:14, 15) ኢየሱስ እሱ ወደ ሰማይ ከሄደ በኋላ ሰይጣን ዲያብሎስ ይሖዋን ማገልገል በሚፈልጉ ሰዎች ሁሉ ላይ ጥቃት መሰንዘሩን እንደሚቀጥል ያውቅ ነበር። በእርግጥም የይሖዋ ሕዝቦች ጥበቃ ያስፈልጋቸዋል። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በአሁኑ ወቅት የይሖዋ ጥበቃ ያስፈልገናል። ሰይጣን ከሰማይ የተወረወረ ሲሆን “በታላቅ ቁጣ” ተሞልቷል። (ራእይ 12:12) አንዳንዶች እኛን ሲያሳድዱ “ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት” እያቀረቡ እንዳሉ እንዲያስቡ አድርጓቸዋል። (ዮሐ. 16:2) በአምላክ የማያምኑ ሌሎች ሰዎች ደግሞ ከዚህ ዓለም የተለየን በመሆናችን ምክንያት ያሳድዱናል። ሰዎች እንዲያሳድዱን የሚያነሳሳቸው ምክንያት ምንም ሆነ ምን መፍራት አይኖርብንም። ለምን? የዛሬው የዕለት ጥቅስ መልሱን ይሰጠናል። w21.03 26 አን. 1, 3
ማክሰኞ፣ መጋቢት 29
ማንኛውም [ነገር] በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ አማካኝነት ከተገለጸው የአምላክ ፍቅር ሊለየን [አይችልም]።—ሮም 8:39
ይሖዋ ሁሉንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ ነው። በፍቅር ተነሳስቶ ፍላጎታችንን ሁሉ ያሟላልናል። ይሖዋ ለእኛ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ ቤዛውን አዘጋጅቶልናል። ኢየሱስም ቢሆን ሕይወቱን ለእኛ የሰጠው በጣም ስለሚወደን ነው። (ዮሐ. 3:16፤ 15:13) ይሖዋና ኢየሱስ ታማኝ ለሆኑ ሰዎች ያላቸውን ፍቅር የሚበጥሰው ምንም ነገር የለም። (ዮሐ. 13:1፤ ሮም 8:35) በተመሳሳይም አንድ የቤተሰብ ራስ ማንኛውንም ነገር የሚያደርገው በፍቅር ተነሳስቶ መሆን አለበት። ይህ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ የጻፈው ሐሳብ መልሱን ይሰጠናል፤ እንዲህ ብሏል፦ “ያየውን ወንድሙን [ወይም ቤተሰቡን] የማይወድ ያላየውን አምላክ ሊወድ አይችልም።” (1 ዮሐ. 4:11, 20) ቤተሰቡን የሚወድ እንዲሁም ይሖዋንና ኢየሱስን መምሰል የሚፈልግ አንድ ባል የቤተሰቡን መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና ቁሳዊ ፍላጎት ለማሟላት የተቻለውን ሁሉ ያደርጋል። (1 ጢሞ. 5:8) ለልጆቹ ሥልጠናና ተግሣጽ ይሰጣል። በተጨማሪም ይሖዋን የሚያስከብርና ቤተሰቡን የሚጠቅም ውሳኔ ለማድረግ ጥረት ያደርጋል። w21.02 5 አን. 12-13
ረቡዕ፣ መጋቢት 30
ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል።—መዝ. 55:22
አፍቃሪው አባታችን በሕይወታችን ውስጥ ያጋጠሙን ነገሮች ስለ ራሳችን መጥፎ ስሜት እንዲያድርብን እንደሚያደርጉ ያውቃል። እንዲሁም ይሖዋ በልባችን ውስጥ ያለውን መልካም ነገር ያያል፤ በሌላ አባባል እኛ ስለ ራሳችን የማናውቃቸውን መልካም ባሕርያትም ጭምር ይመለከታል። (1 ዮሐ. 3:19, 20) ሥር የሰደደ መጥፎ ልማድን ለማሸነፍ እየሞከረ ያለ አንድ ክርስቲያን ልማዱ ያገረሽበት ይሆናል፤ በዚህም የተነሳ በራሱ ተስፋ ሊቆርጥ ይችላል። እርግጥ ነው፣ ኃጢአት በምንፈጽምበት ጊዜ በተወሰነ መጠን የበደለኝነት ስሜት እንደሚሰማን የታወቀ ነው። (2 ቆሮ. 7:10) ሆኖም ወደ ሌላኛው ጽንፍ በመሄድ ‘እኔ የማልረባ ሰው ነኝ፤ ይሖዋ ፈጽሞ ይቅር ሊለኝ አይችልም’ ብለን ራሳችንን ልንኮንን አይገባም። እንዲህ ያለው አሉታዊ አመለካከት፣ ከእውነታው የራቀ ከመሆኑም ሌላ ይሖዋን ማገልገላችንን እንድናቆም ሊያደርገን ይችላል። ከዚህ ይልቅ ወደ ይሖዋ በመጸለይና ምሕረት እንዲያደርግልን በመለመን ችግሩን ‘መፍታታችን’ የተሻለ ነው። (ኢሳ. 1:18) ይሖዋ ከልብ ንስሐ መግባታችንን ሲመለከት ይቅር ይለናል። በተጨማሪም ሽማግሌዎችን ልናነጋግር ይገባል። ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ እንድናገግም በትዕግሥት ይረዱናል።—ያዕ. 5:14, 15፤ w20.12 23 አን. 5-6
ሐሙስ፣ መጋቢት 31
አሮጊቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት ሴቶችን ደግሞ እንደ እህቶች . . . ያዛቸው።—1 ጢሞ. 5:2
ኢየሱስ ለሴቶች አክብሮት ነበረው። ሴቶችን ይንቁ የነበሩትን የፈሪሳውያንን ልማድ አልተከተለም፤ ፈሪሳውያን ከሴቶች ጋር ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት መወያየት ቀርቶ በአደባባይ ከሴቶች ጋር ሲነጋገሩ መታየት እንኳ አይፈልጉም ነበር። ኢየሱስ ግን ለደቀ መዛሙርቱ ጥልቅ መንፈሳዊ እውነቶችን ባብራራበት ወቅት ወንዶችም ሴቶችም ይገኙ ነበር። (ሉቃስ 10:38, 39, 42) በተጨማሪም ኢየሱስ ለስብከት በሚሄድበት ወቅት ሴቶችም አብረውት እንዲጓዙ ፈቅዷል። (ሉቃስ 8:1-3) እንዲሁም ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን ለሐዋርያቱ የማብሰር መብት የሰጠው ለሴቶች ነው። (ዮሐ. 20:16-18) ሐዋርያው ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሴቶችን እንዲያከብር በቀጥታ ምክር ሰጥቶታል። ጳውሎስ መጀመሪያ ለጢሞቴዎስ ‘ቅዱሳን መጻሕፍትን’ ያስተማሩት እናቱና አያቱ እንደሆኑ በመጥቀስ ለእነሱ እውቅና ሰጥቷል። (2 ጢሞ. 1:5፤ 3:14, 15) ጳውሎስ ለሮም ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ እህቶችን በስም ጠቅሶ ሰላምታ ልኮላቸዋል። የእህቶችን ሥራ እንዲሁ ማስተዋል ብቻ ሳይሆን በክርስቲያናዊ አገልግሎት ላከናወኑት ነገር ያለውን አድናቆት ገልጿል።—ሮም 16:1-4, 6, 12፤ ፊልጵ. 4:3፤ w21.02 15 አን. 5-6