የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es22 ገጽ 37-46
  • ሚያዝያ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሚያዝያ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2022
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 1
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 2
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 3
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 4
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 5
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 6
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 7
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 8
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 9
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 10
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 11
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 12
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 13
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 14
  • የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ዕለት
    ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ
    ዓርብ፣ ሚያዝያ 15
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 16
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 17
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 18
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 19
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 20
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 21
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 22
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 23
  • እሁድ፣ ሚያዝያ 24
  • ሰኞ፣ ሚያዝያ 25
  • ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 26
  • ረቡዕ፣ ሚያዝያ 27
  • ሐሙስ፣ ሚያዝያ 28
  • ዓርብ፣ ሚያዝያ 29
  • ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2022
es22 ገጽ 37-46

ሚያዝያ

ዓርብ፣ ሚያዝያ 1

ቀደም ብሎ የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏል።—ሮም 15:4

ከባድ ፈተና አጋጥሞሃል? ምናልባት በጉባኤህ ውስጥ ያለ አንድ ክርስቲያን ስሜትህን ጎድቶት ይሆናል። (ያዕ. 3:2) ወይም ደግሞ ይሖዋን በማገልገልህ ምክንያት የሥራ ባልደረቦችህ ወይም አብረውህ የሚማሩ ልጆች ያሾፉብህ ይሆናል። (1 ጴጥ. 4:3, 4) አሊያም ደግሞ ቤተሰቦችህ በስብሰባዎች ላይ እንዳትገኝ ወይም ስለ እምነትህ እንዳትመሠክር ሊከለክሉህ እየሞከሩ ይሆናል። (ማቴ. 10:35, 36) የገጠመህ ፈተና በጣም ከባድ ከሆነብህ ይሖዋን ማገልገልህን ለማቆም ትፈተን ይሆናል። ሆኖም ያጋጠመህ ፈተና ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ጥበብና ፈተናውን በጽናት ለመቋቋም የሚረዳ ብርታት እንደሚሰጥህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። ይሖዋ ፍጹማን ያልሆኑ ሰዎች ከባድ ፈተናዎችን የተቋቋሙት እንዴት እንደሆነ የሚገልጹ ዝርዝር ሐሳቦችን በቃሉ ውስጥ አስፍሮልናል። ይህን ያደረገው ለምንድን ነው? ለእኛ ትምህርት እንዲሆን አስቦ ነው። ይሖዋ በሐዋርያው ጳውሎስ አማካኝነት የነገረን ይህንን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን ዘገባዎች ማንበባችን መጽናኛና ተስፋ ሊሰጠን ይችላል። ሆኖም የተሟላ ጥቅም ማግኘት ከፈለግን መጽሐፍ ቅዱስን ማንበባችን ብቻውን በቂ አይደለም። ከመጽሐፍ ቅዱስ የምናነበው ነገር አስተሳሰባችንን እንዲቀርጸው እና ልባችንን እንዲነካው መፍቀድ ይኖርብናል። w21.03 14 አን. 1-2

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 2

አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ።—ዮሐ. 4:35

ምሥራቹን የምትሰብኩላቸውን ሰዎች ለአጨዳ እንደደረሰ አዝመራ አድርጋችሁ ትመለከቷቸዋላችሁ? እንዲህ ያለ አመለካከት መያዛችሁ በሦስት መንገዶች ይጠቅማችኋል። አንደኛ፣ በጥድፊያ ስሜት ትሰብካላችሁ። የመከር ወቅት የሚቆየው ለተወሰነ ጊዜ ስለሆነ ሥራው ቶሎ መከናወን አለበት። ሁለተኛ፣ ሰዎች ምሥራቹን ሲቀበሉ በማየት ትደሰታላችሁ። ደግሞም ሰዎች “መከር በሚሰበሰብበት ጊዜ ሐሴት እንደሚያደርጉ” መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ኢሳ. 9:3) ሦስተኛ፣ የምትሰብኩለት እያንዳንዱ ሰው ደቀ መዝሙር ሊሆን እንደሚችል ስለምታስቡ በግለሰብ ደረጃ የእሱን ትኩረት የሚስብ አቀራረብ ለመጠቀም ጥረት ታደርጋላችሁ። አንዳንድ የኢየሱስ ተከታዮች፣ ሳምራውያን የእሱ ደቀ መዝሙር ሊሆኑ እንደማይችሉ አስበው ይሆናል፤ ኢየሱስ ግን እንዲህ ያለ አመለካከት አልነበረውም። ከዚህ ይልቅ ወደፊት ደቀ መዝሙር ሊሆኑ እንደሚችሉ አስቧል። እኛም በክልላችን ውስጥ ያሉ ሰዎች ወደፊት የክርስቶስ ደቀ መዝሙር እንደሚሆኑ አድርገን ማሰብ ይኖርብናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ልንከተለው የሚገባ ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። የሚሰብክላቸው ሰዎች የሚያምኑባቸውን ነገሮች ያውቅ፣ ትኩረታቸውን የሚስቡትን ነገሮች ያስተውል እንዲሁም ወደፊት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደሚሆኑ ያስብ ነበር። w20.04 8-9 አን. 3-4

እሁድ፣ ሚያዝያ 3

መቃብርና የጥፋት ቦታ በይሖዋ ፊት ወለል ብለው ይታያሉ። የሰዎች ልብማ በፊቱ ምንኛ የተገለጠ ነው!—ምሳሌ 15:11

አንድን ሰው በፈጸመው ድርጊት የተነሳ በእሱ ላይ ከመፍረድ ይልቅ ስሜቱን ለመረዳት የምትችሉትን ሁሉ አድርጉ። ሙሉ በሙሉ ስሜታችንን ሊረዳ የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። በመሆኑም ሌሎችን እሱ በሚያይበት መንገድ መመልከትና ለእነሱ ርኅራኄ ማሳየት የምትችሉበትን መንገድ ማስተዋል እንድትችሉ የእሱን እርዳታ ጠይቁ። ማንንም ሳንመርጥ ለሁሉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ርኅራኄ የማሳየት ግዴታ አለብን። ሁሉም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ችግር የሚደርስባቸው ሲሆን አብዛኞቹ ከዮናስ፣ ከኤልያስ፣ ከአጋርና ከሎጥ ጋር ተመሳሳይ የሆኑ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። አንዳንድ ጊዜ እነዚህ ችግሮች የሚደርሱባቸው በራሳቸው ስህተት የተነሳ ሊሆን ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሁላችንም እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ የምንገባበት ጊዜ አለ። በመሆኑም ይሖዋ አንዳችን የሌላውን ስሜት እንድንረዳ መጠየቁ ምክንያታዊ ነው። (1 ጴጥ. 3:8) በዚህ ረገድ ይሖዋን የምንታዘዝ ከሆነ ከተለያየ ቦታ ለተሰባሰበውና አስደናቂ ለሆነው ዓለም አቀፋዊ ቤተሰባችን አንድነት አስተዋጽኦ እናደርጋለን። እንግዲያው ከወንድሞቻችን ጋር ባለን ግንኙነት እነሱን ለማዳመጥ፣ ይበልጥ ለማወቅና ለእነሱ ርኅራኄ ለማሳየት ጥረት እናድርግ። w20.04 18-19 አን. 15-17

ሰኞ፣ ሚያዝያ 4

ክርስቶስ . . . የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራ ተቀብሏል።—1 ጴጥ. 2:21

ይሖዋን በመታዘዝ ረገድ ኢየሱስ ፍጹም ምሳሌ ትቶልናል። በመሆኑም ይሖዋን መታዘዝ የምንችልበት አንዱ ወሳኝ መንገድ የኢየሱስን ፈለግ በጥብቅ መከተል ነው። (ዮሐ. 8:29) በእውነት ውስጥ መመላለሳችንን ለመቀጠል ይሖዋ የእውነት አምላክ መሆኑንና በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት የሚነግረን ነገር በሙሉ እውነት መሆኑን እርግጠኛ መሆን ይኖርብናል። በተጨማሪም ኢየሱስ ተስፋ የተሰጠበት መሲሕ መሆኑን እርግጠኛ መሆን አለብን። በዛሬው ጊዜ ብዙዎች ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ ሆኖ መሾሙን ይጠራጠራሉ። ዮሐንስ ስለ ይሖዋና ስለ ኢየሱስ በሚገልጸው እውነት ላይ ጠንካራ እምነት የሌላቸውን ሰዎች ሊያታልሉ የሚችሉ “ብዙ አሳቾች” እንዳሉ ተናግሮ ነበር። (2 ዮሐ. 7-11) “ኢየሱስን፣ ክርስቶስ አይደለም ብሎ ከሚክድ በቀር ውሸታም ማን ነው?” በማለት ዮሐንስ ጽፏል። (1 ዮሐ. 2:22) ራሳችንን ከእነዚህ አሳቾች መጠበቅ የምንችልበት ብቸኛው መንገድ የአምላክን ቃል ማጥናት ነው። ይሖዋንና ኢየሱስን ማወቅ የምንችለው እንዲህ ካደረግን ብቻ ነው። (ዮሐ. 17:3) እውነትን ማግኘታችንን እርግጠኛ መሆን የምንችለውም በዚህ መንገድ ብቻ ነው። w20.07 21 አን. 4-5

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 5

በአንድ ወንድም ፊት የሚያደናቅፍ . . . ነገር ላለማስቀመጥ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ሮም 14:13

አብረውን የሚሮጡትን ሰዎች ‘እንዳናደናቅፍ’ መጠንቀቅ የምንችልበት አንዱ መንገድ፣ እኔ ያልኩት ካልሆነ ብለን ሌሎችን ከመጫን ይልቅ የሚቻል በሚሆንበት ጊዜ ሁሉ የእነሱን ምርጫ ማክበር ነው። (ሮም 14:19-21፤ 1 ቆሮ. 8:9, 13) በዚህ ረገድ ቃል በቃል በውድድር ላይ ከሚሳተፍ ሯጭ እንለያለን። ይህ ሯጭ ከሌሎች ሯጮች ጋር በመፎካከር ሽልማቱን የግሉ ለማድረግ ይጥራል። እንዲህ ያሉ ሯጮች በዋነኝነት የሚያስቡት ስለ ራሳቸው ብቻ ነው። ስለዚህ ሌሎቹን ተወዳዳሪዎች ገፍተውም ቢሆን ከፊት ለመገኘት ጥረት ያደርጋሉ። እኛ ግን እርስ በርስ አንፎካከርም። (ገላ. 5:26፤ 6:4) ግባችን በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች አብረውን የመጨረሻውን መስመር አልፈው የሕይወትን ሽልማት እንዲያገኙ መርዳት ነው። በመሆኑም “ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ” የሚለውን በመንፈስ መሪነት የተሰጠ ምክር ተግባራዊ ለማድረግ እንጥራለን። (ፊልጵ. 2:4) ይሖዋ፣ እኛ የምንካፈልበትን ሩጫ ለሚያጠናቅቁ ሕዝቦቹ በደግነት ተነሳስቶ አስተማማኝ ሽልማት አዘጋጅቶላቸዋል፤ ይህም በሰማይ ወይም ገነት በምትሆነው ምድር ላይ የምናገኘው የዘላለም ሕይወት ነው። w20.04 28 አን. 10፤ 29 አን. 12

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 6

እነዚህ ታላቁን መከራ አልፈው የመጡ ናቸው።—ራእይ 7:14

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሌሎች ክርስቲያን ወንዶችና ሴቶች ወደ አዲሱ ዓለም ይገባሉ። እነዚህ ሰዎች ሞት በሌላ መንገድ ድል ሲነሳ ይኸውም በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ቀደም ሲል የሞቱ ሰዎች ትንሣኤ ሲያገኙ ይመለከታሉ። ይህን አስደናቂ ድል ስንመለከት ምን ያህል እንደምንደሰት እስቲ አስበው! (ሥራ 24:15) ለይሖዋ ሙሉ በሙሉ ታማኝ የሚሆኑ ሁሉ ከአዳም በወረሱት ሞት ላይም ጭምር ድል ይቀዳጃሉ። ለዘላለም መኖር ይችላሉ። በዛሬው ጊዜ በሕይወት ያሉ ክርስቲያኖች በሙሉ ጳውሎስ የትንሣኤ ተስፋን አስመልክቶ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ለጻፈላቸው የሚያበረታታ መልእክት አመስጋኞች መሆን አለባቸው። ጳውሎስ ‘በጌታ ሥራ’ እንድንጠመድ የሰጠንን ማሳሰቢያ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያነሳሳ በቂ ምክንያት አለን። (1 ቆሮ. 15:58) በዚህ ሥራ በታማኝነትና በትጋት ከተካፈልን፣ ወደፊት አስደሳች የሆነ ሕይወት ይጠብቀናል። ይህ ሕይወት ልናስብ ከምንችለው ከማንኛውም ነገር የላቀ ይሆናል። ይህን ሕይወት ስናገኝ፣ ከጌታ ጋር በተያያዘ በትጋት ያከናወንነው ሥራ ከንቱ አለመሆኑን እርግጠኛ እንሆናለን። w20.12 13 አን. 16-17

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 7

ሠራዊታቸው በፈረሱ ላይ ከተቀመጠውና ከሠራዊቱ ጋር ለመዋጋት ተሰብስበው አየሁ።—ራእይ 19:19

በሕዝቅኤል 38:10-23፣ በዳንኤል 2:43-45፤ 11:44 እስከ 12:1 እንዲሁም በራእይ 16:13-16, 21 ላይ የሚገኙት ትንቢቶች የሚናገሩት ስለ ተመሳሳይ ጊዜ እና ክንውኖች ይመስላል፤ ይህ እውነት ከሆነ፣ የሚከተሉት ነገሮች ይፈጸማሉ ብለን መጠበቅ እንችላለን። ታላቁ መከራ ከጀመረ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ‘የዓለም ነገሥታት’ ጥምረት ይፈጥራሉ። (ራእይ 16:13, 14) ይህን ጥምረት፣ ቅዱሳን መጻሕፍት ‘በማጎግ ምድር የሚገኘው ጎግ’ ብለው ይጠሩታል። (ሕዝ. 38:2) ጥምረት የፈጠሩት ብሔራት፣ የአምላክን ሕዝቦች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመደምሰስ ጥቃት ይሰነዝራሉ። ሐዋርያው ዮሐንስ በዚህ ጊዜ ስለሚፈጸመው ነገር ሲናገር እጅግ ታላቅ የበረዶ ድንጋይ በአምላክ ጠላቶች ላይ እንደሚወርድ ገልጿል። ይህ ምሳሌያዊ በረዶ፣ የማጎጉ ጎግን በማስቆጣት የአምላክን ሕዝቦች ከምድር ገጽ ለማጥፋት እንዲነሳሳ የሚያደርገውን የይሖዋ ሕዝቦች የሚያውጁትን ከባድ የፍርድ መልእክት የሚያመለክት ሊሆን ይችላል።—ራእይ 16:21፤ w20.05 15 አን. 13-14

ዓርብ፣ ሚያዝያ 8

እናንተ ክፉዎች ሆናችሁ ሳለ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባትማ ለሚለምኑት መንፈስ ቅዱስን እንዴት አብልጦ አይሰጣቸው!—ሉቃስ 11:13

የአምላክን ቅዱስ መንፈስ እንደ ውድ ሀብት ልንመለከተው ይገባል። መንፈስ ቅዱስ በዛሬው ጊዜ እያከናወናቸው ባሉት ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን ለዚህ መንፈስ ያለንን አድናቆት ለማሳደግ ይረዳናል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ከመሄዱ በፊት ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ ብሏቸው ነበር፦ “መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ፤ . . . እስከ ምድር ዳር ድረስ ምሥክሮቼ ትሆናላችሁ።” (ሥራ 1:8) ስምንት ሚሊዮን ተኩል የሚሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች በአምላክ መንፈስ እርዳታ ከመላው ምድር ሊሰበሰቡ ችለዋል። በተጨማሪም የምንኖረው በመንፈሳዊ ገነት ውስጥ ነው፤ ይህም የሆነው የአምላክ መንፈስ እንደ ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ደግነት፣ ጥሩነት፣ እምነት፣ ገርነትና ራስን መግዛት ያሉ ግሩም ባሕርያት እንድናዳብር ስለረዳን ነው። እነዚህ ባሕርያት “የመንፈስ ፍሬ” ገጽታዎች ናቸው። (ገላ. 5:22, 23) በእርግጥም መንፈስ ቅዱስ ውድ ስጦታ ነው! w20.05 28 አን. 10፤ 29 አን. 13

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 9

ሞት የመጣው በአንድ ሰው በኩል ስለሆነ የሙታን ትንሣኤም በአንድ ሰው በኩል ነው።—1 ቆሮ. 15:21

ከሞት የሚነሱ ቤተሰቦቻችንን እና ወዳጆቻችንን መለየት እንችላለን እንድንል የሚያደርጉን ምክንያቶች አሉ። ከዚህ በፊት ከተከናወኑ ትንሣኤዎች እንደምንመለከተው ይሖዋ የሞቱ ሰዎችን ሲያስነሳ ልክ ከመሞታቸው በፊት የነበራቸውን ገጽታ፣ አነጋገርና አስተሳሰብ ይዘው እንዲነሱ የሚያደርግ ይመስላል። ኢየሱስ ሞትን ከእንቅልፍ፣ ትንሣኤን ደግሞ ከእንቅልፍ ከመነሳት ጋር እንዳመሳሰለው እናስታውስ። (ማቴ. 9:18, 24፤ ዮሐ. 11:11-13) እንቅልፍ የወሰዳቸው ሰዎች ሲነቁ መልካቸውም ሆነ አነጋገራቸው አይቀየርም፤ ከመተኛታቸው በፊት አእምሯቸው ውስጥ የነበረው መረጃም አይጠፋም። አልዓዛርን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። አልዓዛር ከሞተ አራት ቀናት ስለሆነው ሰውነቱ መበስበስ ጀምሮ ነበር። ሆኖም ኢየሱስ ከሞት ሲያስነሳው እህቶቹ ወዲያውኑ አውቀውታል፤ አልዓዛርም ቢሆን እህቶቹን እንዳወቃቸው ግልጽ ነው።—ዮሐ. 11:38-44፤ 12:1, 2፤ w20.08 14 አን. 3፤ 16 አን. 8

እሁድ፣ ሚያዝያ 10

መዳን ያገኘነው በዙፋኑ ላይ ከተቀመጠው ከአምላካችን እንዲሁም ከበጉ ነው።—ራእይ 7:10

በአምላክ ዘንድ ካላቸው ቦታ አንጻር በቅቡዓኑና በሌሎች በጎች መካከል ምንም ልዩነት የለም። ሁለቱም ቡድኖች በይሖዋ ዘንድ እኩል ዋጋ አላቸው። ደግሞም ይሖዋ፣ ቅቡዓኑንም ሆነ ሌሎች በጎችን ለመዋጀት የከፈለው የውድ ልጁን ሕይወት ነው። በሁለቱ ቡድኖች መካከል ያለው ልዩነት ተስፋቸው ነው። ሁለቱም ቡድኖች ለአምላክና ለክርስቶስ ታማኝ ሆነው መኖር ይጠበቅባቸዋል። (መዝ. 31:23) በተጨማሪም የአምላክ መንፈስ በሁላችንም ላይ በእኩል ደረጃ እንደሚሠራ አንዘንጋ። ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን የሚሰጠው እያንዳንዱ ግለሰብ የሚያስፈልገውን ነገር ግምት ውስጥ በማስገባት እንጂ ተስፋውን መሠረት በማድረግ አይደለም። ይሖዋ ራሳቸውን ለወሰኑ አገልጋዮቹ በሙሉ አስደናቂ ተስፋ ሰጥቷቸዋል። (ኤር. 29:11) አምላክና ክርስቶስ የዘላለም ሕይወት እንድናገኝ ላደረጉልን ነገር አመስጋኝ ነን፤ የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ፣ ሁላችንም አምላክንና ክርስቶስን በማወደስ አመስጋኝነታችንን የምንገልጽበት ጥሩ አጋጣሚ ይሰጠናል። የመታሰቢያው በዓል፣ እውነተኛ ክርስቲያኖች ከሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ስብሰባ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም። w21.01 18 አን. 16፤ 19 አን. 19

ሰኞ፣ ሚያዝያ 11

ይህን ሁልጊዜ . . . አድርጉት።—1 ቆሮ. 11:25

በመታሰቢያው በዓል ላይ ከሚገኙት መካከል አብዛኞቹ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ናቸው። ታዲያ በዚህ በዓል ላይ የሚገኙት ለምንድን ነው? ይህን የሚያደርጉበት ምክንያት፣ ሰዎች በወዳጃቸው የሠርግ ሥነ ሥርዓት ላይ ከሚገኙበት ምክንያት ጋር ይመሳሰላል። በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚገኙት ጋብቻቸውን ለሚፈጽሙት ጥንዶች ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ እንዲሁም ከጎናቸው እንደሆኑ ለማሳየት ነው። በተመሳሳይም የሌሎች በጎች አባላት በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙት ለክርስቶስና ለቅቡዓኑ ያላቸውን ፍቅር ለመግለጽ እንዲሁም ከጎናቸው እንደሆኑ ለማሳየት ነው። የሌሎች በጎች አባላት በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚገኙበት ሌላው ምክንያት ደግሞ ለተከፈለላቸው መሥዋዕት ያላቸውን አድናቆት ለማሳየት ነው፤ ምክንያቱም ይህ መሥዋዕት በምድር ላይ ለዘላለም መኖር የሚችሉበትን አጋጣሚ እንደከፈተላቸው ያውቃሉ። ከዚህም በተጨማሪ የሌሎች በጎች አባላት፣ ኢየሱስ የሰጠውን ትእዛዝ ለማክበር ሲሉ በመታሰቢያው በዓል ላይ ይገኛሉ። ኢየሱስ ከታማኝ ሐዋርያቱ ጋር ሆኖ የጌታ ራት በዓልን ባቋቋመበት ወቅት “ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት” ብሏቸው ነበር። (1 ቆሮ. 11:23-26) በመሆኑም ቅቡዓን ቀሪዎች በምድር ላይ እስካሉ ድረስ ይህ በዓል መከበሩን ይቀጥላል፤ የሌሎች በጎች አባላትም በበዓሉ ላይ ይገኛሉ። w21.01 17-18 አን. 13-14

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 9) ዮሐንስ 12:12-19፤ ማርቆስ 11:1-11

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 12

የአምላክ ፍቅር ከእኛ ሁኔታ ጋር በተያያዘ በዚህ መንገድ ተገልጧል፤ እኛ በእሱ አማካኝነት ሕይወት ማግኘት እንድንችል አምላክ አንድያ ልጁን ወደ ዓለም ልኮታል።—1 ዮሐ. 4:9

እውነተኛ ፍቅር በተግባር የተደገፈ ሊሆን ይገባል። (ከያዕቆብ 2:17, 26 ጋር አወዳድር።) ለምሳሌ ይሖዋ ይወደናል። (1 ዮሐ. 4:19) ፍቅሩን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባስጻፋቸው ግሩም ቃላት ገልጾልናል። (መዝ. 25:10፤ ሮም 8:38, 39) እንደሚወደን ያሳመነን ግን የተናገረው ነገር ብቻ ሳይሆን ያደረገልንም ነገር ነው። ይሖዋ የሚወደው ልጁ ለእኛ ሲል እንዲሠቃይና እንዲሞት ፈቅዷል። (ዮሐ. 3:16) ታዲያ ይሖዋ እንደሚወደን የምንጠራጠርበት ምን ምክንያት አለ? ይሖዋን እና ኢየሱስን እንደምንወዳቸው የምናሳየው እነሱን በመታዘዝ ነው። (ዮሐ. 14:15፤ 1 ዮሐ. 5:3) ኢየሱስ ደግሞ እርስ በርስ እንድንዋደድ ቀጥተኛ ትእዛዝ ሰጥቶናል። (ዮሐ. 13:34, 35) ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን እንደምንወዳቸው በቃል መግለጽ ብቻ ሳይሆን በተግባር ልናሳይም ይገባል።—1 ዮሐ. 3:18፤ w21.01 9 አን. 6፤ 10 አን. 8

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 10) ዮሐንስ 12:20-50

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 13

ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ።—ዮሐ. 15:15

በመንፈስ ቅዱስ የተቀቡ ክርስቲያኖች ከኢየሱስ ጋር ለዘላለም አብረው የመሆን ተስፋ አላቸው፤ የአምላክ መንግሥት ወራሾች በመሆን አብረውት ይገዛሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች ቃል በቃል ከክርስቶስ ጋር የመሆን ይኸውም እሱን ፊት ለፊት የማየት፣ ከእሱ ጋር የመነጋገርና አብረው ጊዜ የማሳለፍ መብት ያገኛሉ። (ዮሐ. 14:2, 3) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖችም የኢየሱስን ፍቅርና እንክብካቤ ያገኛሉ። ኢየሱስን ፊት ለፊት የማየት አጋጣሚ ባያገኙም ይሖዋና ኢየሱስ የሰጧቸውን አስደሳች ሕይወት ስለሚያጣጥሙ ከኢየሱስ ጋር ያላቸው ዝምድና ይበልጥ ይጠናከራል። (ኢሳ. 9:6, 7) ኢየሱስ የእሱ ወዳጆች እንድንሆን ያቀረበልንን ግብዣ መቀበላችን ብዙ በረከቶች ያስገኝልናል። ለምሳሌ ያህል፣ በአሁኑ ጊዜ የእሱን ፍቅርና ድጋፍ እናገኛለን። ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ተዘርግቶልናል። ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ ከኢየሱስ ጋር የመሠረትነው ወዳጅነት የኢየሱስ አባት ከሆነው ከይሖዋ ጋር በግለሰብ ደረጃ የጠበቀ ዝምድና ለመመሥረት ያስችለናል፤ ይህ ደግሞ እጅግ የላቀ ሀብት ነው። በእርግጥም የኢየሱስ ወዳጅ ተብለን መጠራታችን ትልቅ መብት ነው! w20.04 25 አን. 15-16

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 11) ሉቃስ 21:1-36

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 14

ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉ።—1 ቆሮ. 15:22

ሐዋርያው ጳውሎስ ደብዳቤውን የጻፈው በቆሮንቶስ ለሚኖሩ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ሲሆን እነዚህ ክርስቲያኖች ደግሞ ተስፋቸው ትንሣኤ አግኝተው ወደ ሰማይ መሄድ ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ‘ከክርስቶስ ኢየሱስ ጋር ባላቸው አንድነት የተቀደሱ እና ቅዱሳን ለመሆን የተጠሩ’ ናቸው። እንዲሁም ጳውሎስ “ከክርስቶስ ጋር አንድነት ኖሯቸው በሞት [ስላንቀላፉ]” ሰዎች ተናግሯል። (1 ቆሮ. 1:2፤ 15:18፤ 2 ቆሮ. 5:17) ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት በጻፈው ሌላ ደብዳቤ ላይ፣ ‘ሞቱን በሚመስል ሞት ከኢየሱስ ጋር አንድ የሆኑ ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ ደግሞ ከእሱ ጋር አንድ እንደሚሆኑ’ ገልጿል። (ሮም 6:3-5) ኢየሱስ መንፈስ ሆኖ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ ሰማይ ሄዷል። ስለዚህ “ከክርስቶስ ጋር አንድነት” ያላቸው ሁሉ ማለትም ሁሉም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ ይሄዳሉ። ጳውሎስ “ክርስቶስ በሞት ካንቀላፉት በኩራት ሆኖ ከሞት ተነስቷል” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 15:20) መንፈስ ሆኖ ከሞት ለመነሳትና የዘላለም ሕይወት ለማግኘት የመጀመሪያው ሰው ኢየሱስ ነበር። w20.12 5-6 አን. 15-16

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 12) ማቴዎስ 26:1-5, 14-16፤ ሉቃስ 22:1-6

የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ዕለት
ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ
ዓርብ፣ ሚያዝያ 15

ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን።—1 ተሰ. 4:17

በዛሬው ጊዜ ምድራዊ ሕይወታቸውን የሚያጠናቅቁ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ወዲያውኑ ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ ይሄዳሉ። ሐዋርያው ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 15:51, 52 ላይ የተናገረው ሐሳብ ይህን ያረጋግጥልናል። እነዚህ የክርስቶስ ወንድሞች ከሞት ከተነሱ በኋላ የተሟላ ደስታ ይኖራቸዋል። “በቅጽበተ ዓይን” የሚለወጡት ሰዎች ሰማይ ሄደው ምን እንደሚያከናውኑ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል። ኢየሱስ እንዲህ ይላቸዋል፦ “ድል ለሚነሳና በሥራዬ እስከ መጨረሻ ለሚጸና በብሔራት ላይ ሥልጣን እሰጠዋለሁ፤ ይህም ከአባቴ የተቀበልኩት ዓይነት ሥልጣን ነው። ድል የነሳውም ሕዝቦችን እንደ ሸክላ ዕቃ እንዲደቅቁ በብረት በትር ይገዛቸዋል።”—ራእይ 2:26, 27፤ w20.12 12 አን. 14-15

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 13) ማቴዎስ 26:17-19፤ ማርቆስ 14:12-16፤ ሉቃስ 22:7-13 (ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 14) ዮሐንስ 13:1-5፤ 14:1-3

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 16

ክርስቶስ . . . ከሞት ተነስቷል።—1 ቆሮ. 15:20

ሐዋርያው ጳውሎስ ኢየሱስን “በኩራት” ብሎ መጥራቱ ከእሱ በኋላ ሌሎች ሰዎችም ከሞት ተነስተው ሰማያዊ ሕይወት እንደሚያገኙ ይጠቁማል። ሐዋርያትን ጨምሮ ‘ከክርስቶስ ጋር አንድነት ያላቸው’ ሌሎች ሰዎች ከጊዜ በኋላ የኢየሱስ ዓይነት ትንሣኤ ያገኛሉ። (1 ቆሮ. 15:18) ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ክርስቲያኖች ደብዳቤውን በጻፈበት ወቅት ‘ከክርስቶስ ጋር አንድነት ያላቸው’ ክርስቲያኖች የሚያገኙት ሰማያዊ ትንሣኤ አልጀመረም ነበር። ጳውሎስ ይህ ትንሣኤ የሚከናወነው ወደፊት እንደሆነ ጠቁሟል። እንዲህ ብሏል፦ “እያንዳንዱ በራሱ ተራ ይሆናል፦ ክርስቶስ በኩራት ነው፤ በመቀጠል ደግሞ ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ የእሱ የሆኑት ሕያዋን ይሆናሉ።” (1 ቆሮ. 15:23፤ 1 ተሰ. 4:15, 16) አሁን የምንኖረው ጳውሎስ “ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ” ብሎ በጠቀሰው ዘመን ውስጥ ነው። ሐዋርያትም ሆኑ በሞት ያንቀላፉ ሌሎች በመንፈስ የተቀቡ ክርስቲያኖች፣ ሰማያዊ ሽልማታቸውን ለማግኘትና ‘የኢየሱስን ትንሣኤ በሚመስል ትንሣኤ ከእሱ ጋር አንድ ለመሆን’ ‘የክርስቶስ መገኘት’ እስኪጀምር ድረስ መጠበቅ ነበረባቸው።—ሮም 6:5፤ w20.12 5 አን. 12፤ 6 አን. 16-17

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 14) ዮሐንስ 19:1-42

እሁድ፣ ሚያዝያ 17

የሚዘራው የሚበሰብስ ነው፤ የሚነሳው የማይበሰብስ ነው።—1 ቆሮ. 15:42

ሐዋርያው ጳውሎስ ሰማያዊ አካል ወይም “መንፈሳዊ አካል” ይዘው ስለሚነሱ ሰዎች እየተናገረ ነበር። (1 ቆሮ. 15:43, 44) ኢየሱስ ምድር ላይ በኖረበት ጊዜ ሥጋዊ አካል ነበረው፤ ትንሣኤ ካገኘ በኋላ ግን “ሕይወት የሚሰጥ መንፈስ” ሆኖ ወደ ሰማይ ተመለሰ። በተመሳሳይም ቅቡዓን ክርስቲያኖች ከሞት የሚነሱት መንፈሳዊ አካል ይዘው ነው። ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ከአፈር የተሠራውን ሰው መልክ እንደመሰልን ሁሉ የሰማያዊውንም መልክ እንመስላለን።” (1 ቆሮ. 15:45-49) ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ የሰጠውን ማብራሪያ እየደመደመ ነበር። ኢየሱስ ሥጋዊ አካል ይዞ እንዳልተነሳ እናስታውስ። ጳውሎስ “ሥጋና ደም የአምላክን መንግሥት አይወርስም” በማለት በግልጽ ተናግሯል። (1 ቆሮ. 15:50) ሐዋርያትም ሆኑ ሌሎች ቅቡዓን ክርስቲያኖች፣ ወደ ሰማይ የሚሄዱት ሥጋና ደም ይኸውም የሚበሰብስ አካል ይዘው አይደለም። w20.12 11 አን. 10-12

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 15) ማቴዎስ 27:62-66 (ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 16) ዮሐንስ 20:1

ሰኞ፣ ሚያዝያ 18

ሞት ሆይ፣ ድል አድራጊነትህ የት አለ? ሞት ሆይ፣ መንደፊያህ የት አለ?—1 ቆሮ. 15:55

በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስለ ሰማያዊው ትንሣኤ እንዲጽፉ አምላክ በመንፈሱ መርቷቸዋል። ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “እኛ አሁን የአምላክ ልጆች ነን፤ ሆኖም ወደፊት ምን እንደምንሆን ገና አልተገለጠም። እሱ በሚገለጥበት ጊዜ እንደ እሱ እንደምንሆን እናውቃለን።” (1 ዮሐ. 3:2) ስለዚህ ቅቡዓን ክርስቲያኖች መንፈሳዊ አካል ይዘው ከሞት ሲነሱ በሰማይ ምን ዓይነት ሕይወት እንደሚኖራቸው አያውቁም። ሆኖም ሽልማታቸውን ሲያገኙ ይሖዋን ያዩታል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ የተወሰነ መረጃ ሰጥቶናል። ክርስቶስ “ማንኛውንም መስተዳድር እንዲሁም ሥልጣንን ሁሉና ኃይልን” በሚያጠፋበት ጊዜ ቅቡዓኑ ከእሱ ጋር ይሆናሉ። ከሚጠፉት ነገሮች መካከል “የመጨረሻው ጠላት፣ ሞት” ይገኝበታል። በመጨረሻም ኢየሱስና ተባባሪ ገዢዎቹ ራሳቸውን እንዲሁም ሁሉንም ነገር ለይሖዋ ያስገዛሉ። (1 ቆሮ. 15:24-28) እንዴት ያለ አስደሳች ጊዜ ይሆናል! w20.12 8 አን. 2

የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 16) ዮሐንስ 20:2-18

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 19

ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች ከሞት እንደሚነሱ በአምላክ ተስፋ አለኝ።—ሥራ 24:15

ከክርስቶስ ጋር በሰማይ የመኖር ተስፋ የሌላቸው ታማኝ ክርስቲያኖችም ትንሣኤ የማግኘት ተስፋ አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ሐዋርያው ጳውሎስና ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሌሎች ክርስቲያኖች “መጀመሪያ ላይ ትንሣኤ ከሚያገኙት መካከል” እንደሚሆኑ ይናገራል። (ፊልጵ. 3:11) ይህ ሐሳብ ከዚያ በኋላ ሌላ ትንሣኤ እንደሚከናወስን የሚጠቁም አይደለም? ይህ መደምደሚያ ኢዮብ ስለ ተስፋው ከተናገረው ሐሳብ ጋር ይስማማል። (ኢዮብ 14:15) “ክርስቶስ በሚገኝበት ጊዜ የእሱ የሆኑት” ቅቡዓን፣ ኢየሱስ ማንኛውንም መስተዳድር እንዲሁም ሥልጣንን ሁሉና ኃይልን በሚያጠፋበት ጊዜ ከእሱ ጋር በሰማይ ላይ ይሆናሉ። “የመጨረሻው ጠላት፣ ሞት” እንኳ ይደመሰሳል። ከሞት ተነስተው ወደ ሰማይ የሚሄዱ ሰዎች ዳግመኛ እንደማይሞቱ ግልጽ ነው። (1 ቆሮ. 15:23-26) ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ከሚገኘው ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ ተስፋ ማግኘት ይችላሉ። ዓመፀኞች ወደ ሰማይ እንደማይሄዱ ግልጽ ነው፤ ስለዚህ ጳውሎስ የተናገረው ሐሳብ ወደፊት በምድር ላይ ትንሣኤ እንደሚኖር ይጠቁማል። w20.12 6-7 አን. 18-19

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 20

የምኖረው በወደደኝና ለእኔ ሲል ራሱን አሳልፎ በሰጠው [በክርስቶስ] ነው።—ገላ. 2:20

‘ይሖዋ በእኔ ተስፋ እንዳልቆረጠ እንዴት አውቃለሁ?’ ብለን እናስብ ይሆናል። ይህን ጥያቄ ማንሳታችን በራሱ የይሖዋን ይቅርታ ልናገኝ እንደምንችል ያሳያል። ከበርካታ ዓመታት በፊት መጠበቂያ ግንብ ላይ እንዲህ የሚል ሐሳብ ወጥቶ ነበር፦ “በቀድሞ ሕይወትህ የነበረህ አንድ መጥፎ ልማድ፣ ካሰብከው የበለጠ ሥር ከመስደዱ የተነሳ በተደጋጋሚ እያገረሸ ያስቸግርህ [ይሆናል]። . . . ይቅር የማይባል ኃጢአት እንደፈጸምክ አታስብ። እንዲህ ብለህ እንድታስብ የሚፈልገው ሰይጣን ነው። በጥፋትህ መጸጸትህና ማዘንህ በራሱ ብዙ እንዳልራቅህ የሚጠቁም ነው። በትሕትና እና ከልብ በመነጨ ስሜት የአምላክን እርዳታ መጠየቅህን አታቋርጥ፤ ይቅር እንዲልህ፣ እንዲያነጻህ እና እንዲረዳህ አምላክን ለምነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት ከባድ ኃጢአቶች ሠርቷል። ጳውሎስ የፈጸማቸውን ስህተቶች አልረሳቸውም። (1 ጢሞ. 1:12-15) ሆኖም ቤዛውን ለእሱ በግሉ እንደተሰጠው ስጦታ አድርጎ ቆጥሮታል። በመሆኑም ጳውሎስ ከልክ ያለፈ የጥፋተኝነት ስሜት ወጥመድ እንዲሆንበት አልፈቀደም። ትኩረት ያደረገው፣ ከዚያ በኋላ ለይሖዋ መስጠት በሚችለው ነገር ላይ ነው። w20.11 27 አን. 14፤ 29 አን. 17

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 21

ከእናንተ መካከል ጥበብ የጎደለው ሰው ካለ አምላክን ያለማሰለስ ይለምን፤ አምላክ ማንንም ሳይነቅፍ ለሁሉም በልግስና ይሰጣልና፤ ይህም ሰው ይሰጠዋል።—ያዕ. 1:5

ሰይጣን ብዙ ነገሮችን በመጠቀም መጥፎ ነገር እንድንፈጽም ይፈትነናል። ታዲያ እንዲህ ዓይነት ፈተና ሲያጋጥመን ምን እናደርጋለን? በዚህ ጊዜ ሰበብ መደርደር ይቀናን ይሆናል። ለምሳሌ ያህል፣ ‘ይህን ባደርግ ከጉባኤ አልወገድም፤ ያን ያህል ከባድ ኃጢአት ባይሆን ነው’ ብለን እናስብ ይሆናል። እንዲህ ያለው አስተሳሰብ በጣም የተሳሳተ ነው። ከዚህ በተቃራኒ ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ሰይጣን በዚህ ፈተና ተጠቅሞ ልቤን ለመክፈል እየሞከረ ነው? በመጥፎ ምኞቶች መሸነፌ በይሖዋ ስም ላይ ነቀፋ ያመጣ ይሆን? እንዲህ ማድረጌ ወደ አምላኬ ይበልጥ ያቀርበኛል ወይስ ከእሱ ያርቀኛል?’ በእነዚህ ጥያቄዎች ላይ አሰላስል። ራስህን ሳታታልል በሐቀኝነት መልስ መስጠት እንድትችል ይሖዋ ጥበብ እንዲሰጥህ ጸልይ። እንዲህ ማድረግህ ትልቅ ጥበቃ ይሆንልሃል። በተጨማሪም ከሰይጣን የሚቀርብልህን ፈተና እንደ ኢየሱስ አጥብቀህ እንድትቃወም ይረዳሃል፤ ኢየሱስ “አንተ ሰይጣን፣ ከፊቴ ራቅ” ብሎት ነበር። (ማቴ. 4:10) የተከፋፈለ ልብ ምንም እንደማይጠቅም አስታውስ። w20.06 12-13 አን. 16-17

ዓርብ፣ ሚያዝያ 22

እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት፤ ከዚህ ይልቅ . . . ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለው በሚያሳይ መንገድ እንዲያስብ፣ በመካከላችሁ ያለውን እያንዳንዱን ሰው . . . እመክራለሁ።—ሮም 12:3

ይሖዋ ለእኛ ከሁሉ የተሻለው ምን እንደሆነ እንደሚያውቅ ስለምንገነዘብ በትሕትና ለእሱ መሥፈርቶች እንገዛለን። (ኤፌ. 4:22-24) ትሕትና ከራሳችን ይልቅ የይሖዋን ፈቃድ እንድናስቀድምና ሌሎች ከእኛ እንደሚበልጡ እንድናስብ ያነሳሳናል። ይህ ደግሞ ከይሖዋም ሆነ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር ጥሩ ዝምድና እንዲኖረን ይረዳናል። (ፊልጵ. 2:3) ይሁን እንጂ ካልተጠነቀቅን በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያሉ ኩራተኛና ራስ ወዳድ ሰዎች ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን ይችላሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ዓ.ም. እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሞ የነበረ ይመስላል፤ ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም ለነበሩት ክርስቲያኖች የሚከተለውን ምክር የሰጣቸው ለዚህ ሊሆን ይችላል፤ “እያንዳንዱ ሰው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አይመልከት፤ ከዚህ ይልቅ . . . ጤናማ አስተሳሰብ እንዳለው በሚያሳይ መንገድ እንዲያስብ፣ በመካከላችሁ ያለውን እያንዳንዱን ሰው . . . እመክራለሁ” በማለት ጽፏል። ጳውሎስ በተወሰነ መጠን ለራሳችን አክብሮት ሊኖረን እንደሚገባ ጠቁሟል። ሆኖም ትሕትና ለራሳችን ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን እንዲሁም ከሚገባው በላይ ስለ ራሳችን በማሰብ ራሳችንን ከፍ አድርገን ከመመልክት እንድንቆጠብ ይረዳናል። w20.07 2 አን. 1-2

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 23

ምድሪቱ እረፍት አግኝታ ስለነበር . . . በእሱ ላይ ጦርነት የከፈተ አልነበረም።—2 ዜና 14:6

በንጉሥ አሳ ዘመን የነበረው የሰላም ጊዜ ውሎ አድሮ አበቃ። አንድ ሚሊዮን ወታደሮችን ያቀፈ ታላቅ ሠራዊት ከኢትዮጵያ መጣባቸው። የሠራዊቱ አዛዥ የሆነው ዛራ ይሁዳን ድል እንደሚያደርግ ተማምኖ ነበር። ንጉሥ አሳ የተማመነው ግን በሠራዊቱ ብዛት ሳይሆን በአምላኩ በይሖዋ ነበር። አሳ “ይሖዋ አምላካችን ሆይ፣ እርዳን፤ በአንተ ታምነናልና፤ በስምህ ይህን ታላቅ ሠራዊት ለመግጠም ወጥተናል” በማለት ጸለየ። (2 ዜና 14:11) የኢትዮጵያውያን ወታደሮች ብዛት ከይሁዳ ሠራዊት በእጥፍ ያህል የሚበልጥ ቢሆንም ይሖዋ ሕዝቡን ለማዳን የሚያስችል ኃይልና ችሎታ እንዳለው አሳ ተናግሯል። ይሖዋም ቢሆን አላሳፈረውም፤ የኢትዮጵያውያን ሠራዊት ሽንፈት እንዲከናነብ አደረገ። (2 ዜና 14:8-13) ወደፊት በግለሰብ ደረጃ የሚገጥመንን እያንዳንዱን ነገር አናውቅም፤ የምናውቀው ነገር ቢኖር ዛሬ የአምላክ ሕዝቦች ያገኙት ሰላም ጊዜያዊ እንደሆነ ነው። ኢየሱስ ስለ መጨረሻዎቹ ቀናት ለደቀ መዛሙርቱ ሲናገር “በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ” ማለቱን አስታውስ።—ማቴ. 24:9፤ w20.09 17-18 አን. 14-16

እሁድ፣ ሚያዝያ 24

በስድብ . . . ደስ እሰኛለሁ።—2 ቆሮ. 12:10

ማናችንም ብንሆን መሰደብ እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ሆኖም ጠላቶቻችን ሲሰድቡን ስሜታችን እንዲጎዳ የምንፈቅድ ከሆነ ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። (ምሳሌ 24:10) ታዲያ ተቃዋሚዎች ለሚሰነዝሩት ስድብ ምን ዓይነት አመለካከት ሊኖረን ይገባል? እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ስንሰደብ ደስ መሰኘት’ እንችላለን። ለምን? ምክንያቱም ስድብና ተቃውሞ እውነተኛ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደሆንን የሚያሳዩ ምልክቶች ናቸው። (1 ጴጥ. 4:14) ኢየሱስ ተከታዮቹ ስደት እንደሚደርስባቸው ተናግሯል። (ዮሐ. 15:18-20) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች እንዲህ ያለው ሁኔታ ደርሶባቸዋል። በወቅቱ በግሪካውያን ባሕል ተጽዕኖ ሥር የነበሩ ሰዎች ክርስቲያኖችን ሞኝና ደካማ አድርገው ይመለከቷቸው ነበር። አይሁዳውያን ደግሞ እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስና ዮሐንስ ያሉ ክርስቲያኖችን “ያልተማሩና ተራ ሰዎች” አድርገው ይቆጥሯቸው ነበር። (ሥራ 4:13) ክርስቲያኖች ደካማ መስለው ይታዩ ነበር፤ ምክንያቱም ፖለቲካዊ ሥልጣንም ሆነ ወታደራዊ ኃይል አልነበራቸውም፤ በማኅበረሰቡ ዘንድም ተቀባይነት አልነበራቸውም። ታዲያ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች የተቃዋሚዎቻቸው አሉታዊ አመለካከት እንቅፋት እንዲፈጥርባቸው ፈቅደዋል? በፍጹም። w20.07 14-15 አን. 3-4

ሰኞ፣ ሚያዝያ 25

እርስ በርስ መዋደዳችንን እንቀጥል፤ ምክንያቱም ፍቅር ከአምላክ ነው፤ ፍቅር የሚያሳይ ሁሉ ከአምላክ የተወለደ ሲሆን አምላክን ያውቃል።—1 ዮሐ. 4:7

ሐዋርያው ዮሐንስ ለወንድሞቹ ፍቅር ስለነበረው ለመንፈሳዊ ደህንነታቸው ከልቡ ያስብ ነበር፤ በመንፈስ መሪነት በጻፋቸው ሦስት ደብዳቤዎች ላይ የሰጠው ምክር ይህን በግልጽ ያሳያል። እንደ እሱ ያሉ ወንዶችና ሴቶች ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ገዢዎች ለመሆን እንደተቀቡ ማወቅ ምንኛ የሚያበረታታ ነው! (1 ዮሐ. 2:27) እሱ የሰጣቸውን ምክሮች በተግባር ማዋል ይኖርብናል። በሁሉም የሕይወታችን ዘርፎች ይሖዋን በመታዘዝ በእውነት ውስጥ ለመመላለስ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። የአምላክን ቃል አንብቡ፤ እንዲሁም በቃሉ ተማመኑ። በኢየሱስ ላይ ጠንካራ እምነት አዳብሩ። ዓለማዊ ፍልስፍናዎችንና የከሃዲዎችን ትምህርት ተቃወሙ። ሁለት ዓይነት ሕይወት ከመምራትና በኃጢአት ከመውደቅ ተቆጠቡ። ይሖዋ ባወጣቸው ላቅ ያሉ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች ተመሩ። እንዲሁም የበደሉንን ይቅር በማለትና እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ድጋፍ በማበርከት ወንድሞቻችን ጸንተው እንዲኖሩ እንርዳቸው። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም በእውነት ውስጥ መመላለሳችንን መቀጠል እንችላለን። w20.07 24-25 አን. 15-17

ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 26

አምላክ እያንዳንዱን የአካል ክፍል እሱ በፈለገው ቦታ መድቦታል።—1 ቆሮ. 12:18

ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ስለሚወዳቸው እያንዳንዳቸው በጉባኤው ውስጥ ቦታ እንዲኖራቸው አድርጓል። የምናበረክተው ድርሻ የተለያየ ቢሆንም ሁላችንም ጠቃሚ ቦታ አለን፤ እንዲሁም አንዳችን ለሌላው እናስፈልጋለን። ሐዋርያው ጳውሎስ ጎላ አድርጎ እንደገለጸው ማንኛችንም ብንሆን አንድን የይሖዋ አገልጋይ “አንተ አታስፈልገኝም” ልንለው አንችልም። (1 ቆሮ. 12:21) በጉባኤው ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን አንዳችን ሌላውን ከፍ አድርገን መመልከትና ተባብረን መሥራት ይኖርብናል። (ኤፌ. 4:16) እርስ በርስ ተባብረን የምንሠራ ከሆነ ጉባኤው ይጠናከራል እንዲሁም በፍቅር ይታነጻል። ሁሉም የጉባኤ ሽማግሌዎች የተሾሙት በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ነው። ያም ቢሆን እያንዳንዳቸው ያላቸው ስጦታና ችሎታ የተለያየ ነው። (1 ቆሮ. 12:17) አንዳንዶቹ ሽማግሌዎች በቅርቡ የተሾሙና በአንጻራዊ ሁኔታ ብዙም ተሞክሮ የሌላቸው ሊሆኑ ይችላሉ። ሌሎቹ ደግሞ በዕድሜ መግፋት ወይም በጤና እክል የተነሳ ማከናወን የሚችሉት ነገር ውስን ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ማንኛውም ሽማግሌ፣ አብሮት ለሚያገለግል ለየትኛውም ሽማግሌ “አንተ አታስፈልገኝም” የሚል አመለካከት ሊኖረው አይገባም። ከዚህ ይልቅ እያንዳንዱ ሽማግሌ ጳውሎስ በሮም 12:10 ላይ የሰጠውን ምክር መከተል ይኖርበታል። w20.08 26 አን. 1-2፤ 27 አን. 4

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 27

የዚህ ዓለም ትእይንት እየተለዋወጠ ነው።—1 ቆሮ. 7:31

ይሖዋ ወደ ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ እንድንጓዝ እኛን ለመምራት በድርጅቱ ምድራዊ ክፍል ይጠቀማል። ከመሠረተ ትምህርት ወይም ከሥነ ምግባር ደንቦች ጋር በተያያዘ ድርጅቱ የሚሰጠውን በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ መመሪያ መከተል እንደማይከብደን የታወቀ ነው። ሆኖም የአምላክ ድርጅት ሌሎች የሕይወታችንን ዘርፎች የሚነካ ለውጥ በሚያደርግበት ጊዜ፣ ለምሳሌ የምንሰበሰብበትን አዳራሽ እንደ መሸጥ ያሉ ውሳኔዎችን ሲያደርግ ምን ምላሽ እንሰጣለን? የምንሠራው ለይሖዋ እንደሆነና እሱ ድርጅቱን እየመራ እንዳለ ካስታወስን ደስታችንን አናጣም። (ቆላ. 3:23, 24) ንጉሥ ዳዊት ለቤተ መቅደሱ ግንባታ የሚሆን ገንዘብ በሰጠበት ወቅት የተናገረው ነገር ጥሩ ምሳሌ ይሆነናል። እንዲህ ብሏል፦ “በፈቃደኝነት ተነሳስተን እንዲህ ያለ መባ ማቅረብ እንችል ዘንድ እኔም ሆንኩ ሕዝቤ ማን ነን? ሁሉም ነገር የተገኘው ከአንተ ነውና፤ የሰጠንህም ከገዛ እጅህ የተቀበልነውን ነው።” (1 ዜና 29:14) እኛም የገንዘብ መዋጮ ስናደርግ ከይሖዋ እጅ የተቀበልነውን ነገር መልሰን እየሰጠነው ነው። ያም ቢሆን ይሖዋ የእሱን ሥራ ለመደገፍ የምንሰጠውን ጊዜ፣ ጉልበት እና ንብረት ከፍ አድርጎ ይመለከታል።—2 ቆሮ. 9:7፤ w20.11 22-23 አን. 14-16

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 28

[ደመናትን] የሚመለከት አያጭድም።—መክ. 11:4

እኛ የይሖዋ ምሥክሮች ስኬታማነታችንን የምንለካው ወደ አምላክ ድርጅት ባመጣናቸው ሰዎች ብዛት አይደለም። (ሉቃስ 8:11-15) ምሥራቹን በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ ከጸናን ይሖዋ ስኬታማ አድርጎ ይቆጥረናል። ለምን? እሱንና ልጁን ስለታዘዝን ነው። (ማር. 13:10፤ ሥራ 5:28, 29) በአሁኑ ወቅት እንድንሰብክ የሚያነሳሳን ተጨማሪ ምክንያት አለን፦ ይህም የዚህ ሥርዓት መጨረሻ በጣም መቅረቡ ነው! በዚህ ሕይወት አድን ሥራ ለመካፈል ያለን ጊዜ በጣም አጭር ነው። እንግዲያው አትዘግይ፤ በዚህ አስፈላጊ ሥራ ለመካፈል ሁኔታዎች ሁሉ እስኪመቻቹልህም አትጠብቅ። ተነሳሽነትህ እንዲጨምር ለማድረግ፣ የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀትህን ለማሳደግ እንዲሁም ድፍረትና ራስህን የመገሠጽ ችሎታ ለማዳበር አሁኑኑ እርምጃ ውሰድ። ከስምንት ሚሊዮን ከሚበልጡት ሰው አጥማጆች ጋር ተባብረህ ለመሥራት መወሰንህ የይሖዋን ደስታ ለመቅመስ ያስችልሃል። (ነህ. 8:10፤ ሉቃስ 5:10) በዚህ ሥራ የተሟላ ተሳትፎ ለማድረግና ሥራው እስከሚጠናቀቅበት ጊዜ ድረስ ለመጽናት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። w20.09 7 አን. 18-20

ዓርብ፣ ሚያዝያ 29

በአደራ የተሰጠህን ነገር ጠብቅ።—1 ጢሞ. 6:20

ተጨማሪ ቁሳዊ ነገሮች የማግኘት ምኞት ትኩረታችንን እንዲከፋፍለው መፍቀድ አይኖርብንም። “ሀብት ያለው የማታለል ኃይል” ለይሖዋ ያለንን ፍቅር፣ ለአምላክ ቃል ያለንን አድናቆት እንዲሁም ይህን እውነት ለሌሎች የማስተማር ፍላጎታችንን ሊያንቀው ይችላል። (ማቴ. 13:22) ይሖዋ በአደራ የሰጠንን ነገሮች መጠበቅ እንድንችል፣ አደጋ ስናይ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። ኢንተርኔት ስንጠቀምና ፊልም ወይም የቴሌቪዥን ፕሮግራም ስንመለከት፣ የጭካኔ ድርጊትና ብልግና የሚታይበት ምስል ወይም ከሃዲዎች የሚያቀርቡት መረጃ በድንገት ብቅ ቢል ምን ማድረግ እንዳለብን አስቀድመን መዘጋጀት ይኖርብናል። ሊያጋጥመን ለሚችለው ነገር አስቀድመን ከተዘጋጀን መንፈሳዊ ጉዳት ከሚያስከትልብን ነገር ቶሎ ማምለጥ እንዲሁም በይሖዋ ዓይን ንጹሕ ሆነን መኖር እንችላለን። (መዝ. 101:3፤ 1 ጢሞ. 4:12) ይሖዋ የሰጠንን ውድ ነገሮች ይኸውም ውድ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችና እነዚህን እውነቶች ለሌሎች የማስተማር መብታችንን ልንጠብቃቸው ይገባል። ይህን ስናደርግ ንጹሕ ሕሊና፣ ትርጉም ያለው ሕይወት እንዲሁም ሌሎች ይሖዋን እንዲያውቁ መርዳት የሚያስገኘው ደስታ ይኖረናል። w20.09 30 አን. 16-19

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 30

በገዛ ዓይኖችህ . . . ታላቁን አስተማሪህን ታያለህ።—ኢሳ. 30:20

የተጠመቅክ የይሖዋ ምሥክር ነህ? ከሆንክ በይሖዋ ላይ እምነት እንዳለህና ከድርጅቱ ጋር ተባብረህ ለመሥራት ፈቃደኛ እንደሆንክ በይፋ አሳውቀሃል። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ ድርጅቱን የሚመራው ባሕርይውን፣ ዓላማውንና መሥፈርቱን በሚያንጸባርቅ መንገድ ነው። በድርጅቱ ላይ ተንጸባርቀው የምናያቸውን ሦስት የይሖዋ ባሕርያት እንመልከት። አንደኛ፣ ‘አምላክ አያዳላም።’ (ሥራ 10:34) አምላክ በፍቅሩ ተነሳስቶ ልጁን ‘ለሁሉም ሰው’ ቤዛ አድርጎ ሰጥቷል። (1 ጢሞ. 2:6፤ ዮሐ. 3:16) ይሖዋ ሕዝቦቹ ለመስማት ፈቃደኛ ለሆኑ ሰዎች ሁሉ ምሥራቹን እንዲሰብኩ አድርጓል። ይህም በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ከቤዛው ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏል። ሁለተኛ፣ ይሖዋ የሥርዓትና የሰላም አምላክ ነው። (1 ቆሮ. 14:33, 40) ከዚህ አንጻር፣ አገልጋዮቹም ሥርዓታማና ሰላማዊ በሆነ መንገድ ተደራጅተው እንደሚያገለግሉት መጠበቃችን ምክንያታዊ ነው። ሦስተኛ፣ ይሖዋ ‘ታላቅ አስተማሪ’ ነው። (ኢሳ. 30:21) ድርጅቱ በጉባኤም ሆነ በመስክ አገልግሎት ላይ በእሱ መንፈስ መሪነት የተጻፈውን የአምላክን ቃል በማስተማር ላይ የሚያተኩረው ለዚህ ነው። w20.10 20 አን. 1-3

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ