ግንቦት
እሁድ፣ ግንቦት 1
እንደ ወትሮውም ይገዛላቸው ነበር።—ሉቃስ 2:51
ኢየሱስ ልጅ ሳለ ለወላጆቹ ለመገዛት መርጧል። ከእነሱ የተሻለ እውቀት እንዳለው በማሰብ የወላጆቹን መመሪያ ችላ አላለም። ኢየሱስ የቤቱ የመጀመሪያ ልጅ መሆኑ ያስከተለበትን ኃላፊነት በቁም ነገር ይመለከት እንደነበር ጥርጥር የለውም። በቁሳዊ ረገድ ለቤተሰቡ የተወሰነ ድጋፍ ለማድረግ ሲል የአሳዳጊ አባቱን ሙያ በትጋት ይማር ነበር። ኢየሱስ፣ ተአምራዊ በሆነ መንገድ እንደተወለደና የአምላክ መልእክተኞች ስለ እሱ ምን እንደተናገሩ ከወላጆቹ ሳይሰማ አልቀረም። (ሉቃስ 2:8-19, 25-38) ሆኖም ከወላጆቹ በሰማው ነገር ብቻ ረክቶ አልተቀመጠም፤ ከዚህ ይልቅ ቅዱሳን መጻሕፍትን በግሉ ያጠና ነበር። ኢየሱስ የአምላክን ቃል በትጋት ያጠና እንደነበር እንዴት እናውቃለን? ምክንያቱም ኢየሱስ ገና ልጅ እያለ በኢየሩሳሌም የነበሩት አስተማሪዎች “በመረዳት ችሎታውና በመልሱ ተደንቀው” እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገራል። (ሉቃስ 2:46, 47) በተጨማሪም ኢየሱስ ገና የ12 ዓመት ልጅ እያለ የአምላክን ቃል በሚገባ በመመርመር ይሖዋ አባቱ እንደሆነ በእርግጠኝነት ማወቅ ችሎ ነበር።—ሉቃስ 2:42, 43, 49፤ w20.10 29-30 አን. 13-14
ሰኞ፣ ግንቦት 2
ክርስቶስ ከሞት [ተነስቷል]።—1 ቆሮ. 15:12
ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን ማመን፣ በትንሣኤ ተስፋ ለማመን መሠረት ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ ትንሣኤ የሰጠውን ማብራሪያ ሲጀምር ሦስት እውነታዎችን ገልጿል። (1) “ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ።” (2) “ተቀበረ።” (3) “ቅዱሳን መጻሕፍት [እንደሚሉት] በሦስተኛው ቀን ተነሳ።” (1 ቆሮ. 15:3, 4) የኢየሱስ መሞት፣ መቀበርና መነሳት ለእኛ ምን ትርጉም አለው? ነቢዩ ኢሳይያስ፣ መሲሑ ‘ከሕያዋን ምድር እንደሚወገድ’ እና ‘የመቃብር ቦታው ከክፉዎች ጋር እንደሚሆን’ በትንቢት ተናግሯል። ግን በዚህ ብቻ አያበቃም። ኢሳይያስ አክሎም መሲሑ ‘የብዙ ሰዎችን ኃጢአት እንደሚሸከም’ ገልጿል። ኢየሱስ ይህን ያደረገው ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ በመስጠት ነው። (ኢሳ. 53:8, 9, 12፤ ማቴ. 20:28፤ ሮም 5:8) በመሆኑም የኢየሱስ መሞት፣ መቀበርና መነሳት ከኃጢአትና ከሞት ነፃ እንደምንወጣ እንዲሁም በሞት ካጣናቸው ሰዎች ጋር መልሰን እንደምንገናኝ ላለን ተስፋ ጠንካራ መሠረት ይሆናል። w20.12 2-3 አን. 4-6፤ 5 አን. 11
ማክሰኞ፣ ግንቦት 3
በሥጋ የምመካበት ነገር አለኝ የሚል ማንም ቢኖር ያ ሰው እኔ ነኝ። በሥጋ የሚመካበት ነገር እንዳለው አድርጎ የሚያስብ ሌላ ማንም ሰው ቢኖር እኔ እበልጣለሁ።—ፊልጵ. 3:4
ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙ ጊዜ በአይሁዳውያን ምኩራቦች ውስጥ ይሰብክ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በተሰሎንቄ ባለ ምኩራብ ውስጥ ‘ለሦስት ሰንበት ከቅዱሳን መጻሕፍት እየጠቀሰ ከአይሁዳውያን ጋር ተወያይቶ’ ነበር። (ሥራ 17:1, 2) ጳውሎስ በምኩራብ ውስጥ መስበክ ይቀለው የነበረ ይመስላል። ምክንያቱም አይሁዳዊ ነበር። (ሥራ 26:4, 5) ጳውሎስ አይሁዳውያን የሚያምኑበትን ነገር በሚገባ ስለሚያውቅ ለእነሱ የሚሰብከው በልበ ሙሉነት ነበር። (ፊልጵ. 3:5) ጳውሎስ አሳዳጆቹ ባደረሱበት ጥቃት የተነሳ በመጀመሪያ ከተሰሎንቄ ከዚያም ከቤርያ ከወጣ በኋላ ወደ አቴንስ ሄደ። በዚያም “በምኩራብ ከአይሁዳውያንና አምላክን ከሚያመልኩ ሌሎች ሰዎች ጋር” መወያየት ጀመረ። (ሥራ 17:17) በገበያ ስፍራ በሚሰብክበት ወቅት ግን የተለየ እምነት ያላቸው ሰዎች አገኘ። ከእነዚህ ሰዎች መካከል የጳውሎስ መልእክት “አዲስ ትምህርት” የሆነባቸው ፈላስፎችና ከአሕዛብ ወገን የሆኑ ሌሎች ሰዎች ይገኙበታል። እነሱም “ለጆሯችን እንግዳ የሆነ ነገር እያሰማኸን ነው” አሉት።—ሥራ 17:18-20፤ w20.04 9 አን. 5-6
ረቡዕ፣ ግንቦት 4
ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ ስፈልግ ከእኔ ጋር ያለው ግን መጥፎ ነገር ነው።—ሮም 7:21
ካለብህ ድክመት ጋር እየታገልክ ከሆነ ራስህን አትኮንን። ማናችንም ብንሆን በራሳችን ሥራ በይሖዋ ዘንድ ጻድቅ ሆነን ልንቆጠር እንደማንችል ማስታወስ ይኖርብናል። ሁላችንም በቤዛው በኩል የተገለጸው የአምላክ ጸጋ ያስፈልገናል። (ኤፌ. 1:7፤ 1 ዮሐ. 4:10) በተጨማሪም ከመንፈሳዊ ቤተሰባችን ማበረታቻ ማግኘት እንችላለን! ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ ማውራት ስንፈልግ ጆሮ ሰጥተው ሊያዳምጡን እንዲሁም የሚያጽናና እና የሚያበረታታ ሐሳብ ሊያካፍሉን ይችላሉ። (ምሳሌ 12:25፤ 1 ተሰ. 5:14) ከተስፋ መቁረጥ ስሜት ጋር ስትታገል የኖረች ጆይ የተባለች በናይጄሪያ የምትኖር እህት እንዲህ ብላለች፦ “ወንድሞቼ ባይኖሩልኝ ኖሮ ምን ይውጠኝ ነበር? ወንድሞቼና እህቶቼ የሚሰጡኝ ማበረታቻ ይሖዋ ጸሎቴን እንደመለሰልኝ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። እንዲያውም ከራሴ አልፌ፣ ተስፋ የቆረጡ ሌሎች ሰዎችን ማጽናናት የምችለው እንዴት እንደሆነ ከእነሱ ተምሬያለሁ።” እርግጥ ነው፣ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን መቼ ማበረታቻ እንደሚያስፈልገን ላያውቁ እንደሚችሉ ማስታወስ ይኖርብናል። ስለዚህ እርዳታ ሲያስፈልገን ወደ አንድ የጎለመሰ ክርስቲያን ቀርበን የውስጣችንን አውጥተን መናገር ሊያስፈልገን ይችላል። w20.12 23-24 አን. 7-8
ሐሙስ፣ ግንቦት 5
ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ።—ዮሐ. 15:15
ብዙውን ጊዜ ከአንድ ሰው ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችለን የመጀመሪያው እርምጃ ከግለሰቡ ጋር አብረን ጊዜ ማሳለፍ ነው። እርስ በርስ ስንጨዋወት ይኸውም ስሜታችንን እና ያጋጠሙንን ነገሮች አንዳችን ለሌላው ስናካፍል ወዳጅነታችን እየጠበቀ ይሄዳል። ከኢየሱስ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ከመመሥረት ጋር በተያያዘ ግን አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሙናል። አንዱ ተፈታታኝ ሁኔታ፣ ኢየሱስን አግኝተነው የማናውቅ መሆኑ ነው። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ በርካታ ክርስቲያኖችም ተመሳሳይ ሁኔታ አጋጥሟቸዋል። ያም ቢሆን ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ ብሏል፦ “እሱን አይታችሁት ባታውቁም ትወዱታላችሁ። አሁን ባታዩትም እንኳ በእሱ ላይ እምነት እያሳያችሁ . . . ነው።” (1 ጴጥ. 1:8) ከዚህ መመልከት እንደሚቻለው ከኢየሱስ ጋር ተገናኝተን ባናውቅም ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት እንችላለን። ሌላው ፈታኝ ሁኔታ፣ ኢየሱስን በቀጥታ ማነጋገር አለመቻላችን ነው። በምንጸልይበት ወቅት በቀጥታ የምናነጋግረው ይሖዋን ነው። በእርግጥ የምንጸልየው በኢየሱስ ስም ነው፤ ሆኖም እሱን በቀጥታ አናነጋግረውም። ኢየሱስም ቢሆን ወደ እሱ እንድንጸልይ አይፈልግም። ለምን? ምክንያቱም ጸሎት የአምልኮ ክፍል ነው፤ ሊመለክ የሚገባው ደግሞ ይሖዋ ብቻ ነው። (ማቴ. 4:10) ያም ቢሆን ለኢየሱስ ያለንን ፍቅር ማሳየት የምንችልባቸው መንገዶች አሉ። w20.04 20 አን. 1-3
ዓርብ፣ ግንቦት 6
[አምላክ] ጽኑ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል፤ ደግሞም ያጠነክራችኋል።—1 ጴጥ. 5:10
በግሪክ ይካሄዱ በነበሩ ውድድሮች ላይ የሚሳተፉ ሯጮች እንደ ድካም ወይም ሕመም ያሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም ነበረባቸው። ሩጫውን በጽናት ለመጨረስ የሚረዳቸው ያገኙት ሥልጠናና አካላዊ ጥንካሬያቸው ብቻ ነበር። እኛም እንደነዚህ ሯጮች ሁሉ እንዴት መሮጥ እንዳለብን ሥልጠና እናገኛለን። ሆኖም ከእነዚህ ሯጮች በተሻለ ሁኔታ ላይ እንገኛለን። የማይነጥፍ የኃይል ምንጭ ባለቤት የሆነው አምላካችን ኃይል ይሰጠናል። ይሖዋ በእሱ የምንታመን ከሆነ ሥልጠና እንደሚሰጠን ብቻ ሳይሆን እንደሚያጠነክረንም ቃል ገብቶልናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በርካታ ተፈታታኝ ሁኔታዎችን መቋቋም ነበረበት። ከሚደርስበት ፌዝና ስደት በተጨማሪ ድካም የሚሰማው ጊዜ ነበር፤ እንዲሁም “ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ” ብሎ ከጠራው ነገር ጋር መታገል ነበረበት። (2 ቆሮ. 12:7) ይሁንና እነዚህ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ተስፋ እንዲያስቆርጡት ከመፍቀድ ይልቅ በይሖዋ ለመታመን እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርጎ ተመልክቷቸዋል። (2 ቆሮ. 12:9, 10) ጳውሎስ እንዲህ ዓይነት አመለካከት ስለነበረው ያጋጠሙትን ችግሮች ሁሉ እንዲቋቋም ይሖዋ ረድቶታል። w20.04 29 አን. 13-14
ቅዳሜ፣ ግንቦት 7
አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም።—ዮሐ. 6:44
ከይሖዋ እና ከድርጅቱ ሰማያዊ ክፍል ጋር “አብረን የምንሠራ” መሆናችን በዓይን የማይታይ ውድ ሀብት ነው። (2 ቆሮ. 6:1) ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ስንካፈል እንዲህ ያለ አጋጣሚ እናገኛለን። ጳውሎስ ራሱንና በዚህ ሥራ የሚካፈሉትን ሰዎች በተመለከተ “ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ ነን” ብሏል። (1 ቆሮ. 3:9) በክርስቲያናዊው አገልግሎት ስንካፈል የኢየሱስም የሥራ ባልደረቦች እንሆናለን። ኢየሱስ ለተከታዮቹ “ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ” የሚል ትእዛዝ ከሰጠ በኋላ “እኔ . . . ከእናንተ ጋር ነኝ” እንዳለ አስታውስ። (ማቴ. 28:19, 20) ስለ መላእክትስ ምን ማለት ይቻላል? ‘በምድር ላይ ለሚኖሩ ሁሉ የዘላለም ምሥራች ለማብሰር’ በምናከናውነው ሥራ መላእክት ይመሩናል፤ ይህ እንዴት ያለ በረከት ነው! (ራእይ 14:6) ከሰማይ እንዲህ ያለ ድጋፍ በማግኘታችን ምን ውጤት ሊገኝ ችሏል? የመንግሥቱን ዘር ስንዘራ አንዳንድ ዘሮች በጥሩ ልብ ላይ አርፈው ያድጋሉ። (ማቴ. 13:18, 23) ታዲያ እነዚህ የእውነት ዘሮች እንዲያድጉና ፍሬ እንዲያፈሩ የሚያደርጋቸው ማን ነው? በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘው ኢየሱስ የተናገረው ሐሳብ የዚህን ጥያቄ መልስ ይዟል። w20.05 30 አን. 14-15
እሁድ፣ ግንቦት 8
ይህ ሥርዓት እንዲቀርጻችሁ አትፍቀዱ።—ሮም 12:2
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ቤተሰቦች በፍቺ ምክንያት ሲፈርሱ እየተመለከትን ነው። የቤተሰብ አባላት፣ በአንድ ጣሪያ ሥር ቢኖሩም እንኳ የሚኖሩት እንደ ደባል ሊሆን ይችላል። አንድ የቤተሰብ አማካሪ እንዲህ ብለዋል፦ “አባት፣ እናትና ልጆች እርስ በርስ ያላቸው ግንኙነት ተቋርጧል፤ አሁን ግንኙነታቸው ከኮምፒውተራቸው፣ ከታብሌታቸው፣ ከስልካቸው ወይም ከቪዲዮ ጌማቸው ጋር ነው። እነዚህ ቤተሰቦች፣ በአንድ ጣሪያ ሥር እየኖሩም ጭራሽ አይተዋወቁም ሊባል ይችላል።” ፍቅር የሌለው ይህ ዓለም እንዲቀርጸን አንፈልግም። ከዚህ ይልቅ ለቤተሰባችን አባላት ብቻ ሳይሆን በእምነት ለሚዛመዱን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም ልባዊ ፍቅር ማዳበር ያስፈልገናል። (ሮም 12:10) ታዲያ ከልብ መዋደድ ሲባል ምን ማለት ነው? ከልብ መዋደድ ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል በቅርብ የቤተሰብ አባላት መካከል ያለውን የጠበቀ ፍቅር ያመለክታል። ለመንፈሳዊ ቤተሰባችን አባላት ማለትም ለክርስቲያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችንም እንዲህ ዓይነት ፍቅር ማዳበር ይኖርብናል። ልባዊ ፍቅር ስናሳይ በመካከላችን ያለው አንድነት እንዲጠበቅ እናደርጋለን፤ አንድነት ደግሞ ለእውነተኛው አምልኮ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው።—ሚክ. 2:12፤ w21.01 20 አን. 1-2
ሰኞ፣ ግንቦት 9
ስምህን እፈራ ዘንድ ልቤን አንድ አድርግልኝ።—መዝ. 86:11
አንድነት ያለው የስፖርት ቡድን አንድነት ከሌለው የስፖርት ቡድን ይልቅ የማሸነፍ አጋጣሚው ሰፊ ነው። አንተም ልብህ እንደዚህ ስኬታማ የስፖርት ቡድን እንዲሆን ማድረግ ትችላለህ፤ ይህ የሚሆነው ሐሳብህን፣ ምኞትህንና ስሜትህን አንድ በማድረግ ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር ካስማማኸው ነው። ሰይጣን ልብህን መክፈል እንደሚያስደስተው አትርሳ። ሐሳብህ፣ ምኞትህና ስሜትህ አንድ እንዳይሆኑ እንዲሁም ከይሖዋ መሥፈርቶች ጋር እንዲጋጩ ማድረግ ይፈልጋል። አንተ ግን ይሖዋን ለማገልገል ልብህ ሙሉ መሆን እንዳለበት ታውቃለህ። (ማቴ. 22:36-38) እንግዲያው ሰይጣን ልብህን እንዲከፋፍለው ፈጽሞ አትፍቀድለት! አንተም እንደ ዳዊት “ስምህን እፈራ ዘንድ ልቤን አንድ አድርግልኝ” ብለህ ይሖዋን ለምነው። ከዚህ ጸሎት ጋር በሚስማማ መንገድ የመኖር ግብ ይኑርህ። ትንሽም ይሁን ትልቅ በየዕለቱ በምታደርጋቸው ውሳኔዎች ለይሖዋ ቅዱስ ስም ያለህን ጥልቅ አክብሮት ለማሳየት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። እንዲህ ስታደርግ እንደ አንድ የይሖዋ ምሥክር መጠን የይሖዋን ስም ማስከበር ትችላለህ። (ምሳሌ 27:11) ሁላችንም “በአምላካችን በይሖዋ ስም ለዘላለም እንሄዳለን” ብሎ የተናገረውን የነቢዩ ሚክያስ ሐሳብ እንደምንጋራ ማሳየት እንችላለን።—ሚክ. 4:5፤ w20.06 13 አን. 17-18
ማክሰኞ፣ ግንቦት 10
ለማጥፋትና ብዙዎችን ለመደምሰስ በታላቅ ቁጣ ይወጣል።—ዳን. 11:44
የሰሜኑ ንጉሥ ከሌሎቹ የዓለም መንግሥታት ጋር በመሆን የሚሰነዝረው ይህ ጥቃት ሁሉን ቻይ የሆነውን አምላክ ቁጣ ይቀሰቅሰዋል፤ ከዚያም የአርማጌዶን ጦርነት ይጀምራል። (ራእይ 16:14, 16) በዚያን ጊዜ የሰሜኑ ንጉሥም ሆነ ሌሎቹ የማጎጉ ጎግ አባላት ወደ ፍጻሜያቸው ይመጣሉ፤ የሰሜኑን ንጉሥ “የሚረዳውም አይኖርም።” (ዳን. 11:45) ዳንኤል በጻፈው ዘገባ ላይ የሚገኘው ቀጣዩ ሐሳብ፣ የሰሜኑ ንጉሥና አጋሮቹ ወደ ፍጻሜያቸው የሚመጡበትንና መዳን የምናገኝበትን መንገድ በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ይሰጠናል። (ዳን. 12:1) በዚህ ጥቅስ ላይ የሚገኘው ሐሳብ ምን ትርጉም አለው? ሚካኤል፣ የንጉሣችን የክርስቶስ ኢየሱስ ሌላ ስም ነው። ሚካኤል ለአምላክ ሕዝቦች ‘መቆም’ የጀመረው መንግሥቱ በ1914 በሰማይ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ነው። በቅርቡ በአርማጌዶን ጦርነት ወቅት ደግሞ “ይነሳል” ማለትም ወሳኝ እርምጃ ይወስዳል። ይህ ጦርነት፣ ዳንኤል ከዚህ በፊት ሆኖ የማያውቅ “የጭንቀት ጊዜ” በማለት የጠራው ወቅት የመጨረሻ ክንውን ይሆናል።—ራእይ 6:2፤ 7:14፤ w20.05 15-16 አን. 15-17
ረቡዕ፣ ግንቦት 11
ዮሴፍ . . . ወደ ግብፅ ተወሰደ።—ዘፍ. 39:1
ዮሴፍ ባሪያ እያለም ሆነ እስረኛ በነበረበት ወቅት ሁኔታውን መቀየር የሚችልበት ምንም መንገድ አልነበረም። ታዲያ ዮሴፍ አዎንታዊ አመለካከት ይዞ መቀጠል የቻለው እንዴት ነው? ማድረግ በማይችለው ነገር ላይ ከማተኮር ይልቅ የተሰጠውን ሥራ በትጋት ይሠራ ነበር። ዮሴፍ ምንጊዜም ይሖዋን ለማስደሰት ጥረት ያደርግ ነበር። ይሖዋም ዮሴፍ የሠራውን ሥራ ሁሉ ባርኮለታል። (ዘፍ. 39:21-23) የዮሴፍ ታሪክ የምንኖርበት ዓለም ጨካኝ እንደሆነ እና ሰዎች ግፍ ሊያደርሱብን እንደሚችሉ ያስታውሰናል። የእምነት ባልንጀራችን እንኳ ሊጎዳን ይችላል። ሆኖም ይሖዋን እንደ ዓለታችን ወይም እንደ መጠጊያችን አድርገን ከተመለከትነው ተስፋ አንቆርጥም አሊያም እሱን ማገልገላችንን አናቆምም። (መዝ. 62:6, 7፤ 1 ጴጥ. 5:10) ከዚህም ሌላ ይሖዋ ለዮሴፍ ልዩ ትኩረት በሰጠበት ወቅት ዮሴፍ ገና 17 ዓመቱ ገደማ እንደነበር ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው። ይሖዋ በወጣት አገልጋዮቹ እንደሚተማመን ከዚህ በግልጽ መመልከት እንችላለን። በዛሬው ጊዜም እንደ ዮሴፍ ያሉ በርካታ ወጣቶች አሉ። ልክ እንደ እሱ በይሖዋ ላይ እምነት አላቸው። እንዲያውም አንዳንዶቹ ለይሖዋ ያላቸውን ታማኝነት ለማላላት ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ታስረዋል።—መዝ. 110:3፤ w20.12 16 አን. 3፤ 17 አን. 5, 7
ሐሙስ፣ ግንቦት 12
ሐዋርያትን . . . ጠርተው ገረፏቸው፤ ከዚያም በኢየሱስ ስም መናገራቸውን እንዲያቆሙ [አዘዟቸው]።—ሥራ 5:40
ጴጥሮስና ዮሐንስ ኢየሱስን በመከተላቸውና ስለ እሱ ሌሎችን በማስተማራቸው ምክንያት ስደት ሲደርስባቸው እንደ ክብር ቆጥረውታል። (ሥራ 4:18-21፤ 5:27-29, 41, 42) የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የሚያፍሩበት ምንም ምክንያት አልነበራቸውም። በወቅቱ የነበረው ማኅበረሰብ ለክርስቲያኖች አክብሮት ባይኖረውም እነዚህ ክርስቲያኖች ከተቃዋሚዎቻቸው ይበልጥ የሰው ልጆችን የሚጠቅም ነገር አድርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ከእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል አንዳንዶቹ በመንፈስ መሪነት የጻፏቸው መጻሕፍት አሁንም ድረስ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች የእርዳታና የተስፋ ምንጭ ናቸው። እንዲሁም እነሱ ይሰብኩት የነበረው መንግሥት በአሁኑ ወቅት ተቋቁሟል፤ በቅርቡ ደግሞ የሰውን ዘር በሙሉ ይገዛል። (ማቴ. 24:14) በአንጻሩ ግን ክርስቲያኖችን ያሳድድ የነበረው ኃያል መንግሥት ተንኮታኩቶ ከወደቀ ዘመናት ተቆጥረዋል። በተጨማሪም እነዚያ ታማኝ ክርስቲያኖች በአሁኑ ወቅት በሰማይ ነገሥታት ሆነው እየገዙ ነው። ተቃዋሚዎቻቸው ግን በሕይወት የሉም፤ ወደፊት ከሞት ቢነሱ እንኳ ይጠሏቸው የነበሩት ክርስቲያኖች ይሰብኩት በነበረው መንግሥት ለመገዛት ይገደዳሉ።—ራእይ 5:10፤ w20.07 15 አን. 4
ዓርብ፣ ግንቦት 13
[አብርሃም] አምላክ ንድፍ ያወጣላትንና የገነባትን፣ እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር።—ዕብ. 11:10
አብርሃም፣ አምላክ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ በጣም ጠንካራ እምነት ነበረው፤ በመሆኑም የአምላክ መንግሥት ንጉሥ የሚሆነውን መሲሕ ያየው ያህል ነበር። በዚህም ምክንያት ኢየሱስ በዘመኑ የነበሩትን አይሁዳውያን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “አባታችሁ አብርሃም ቀኔን እንደሚያይ ተስፋ በማድረግ እጅግ ተደሰተ፤ አይቶትም ደስ ተሰኘ።” (ዮሐ. 8:56) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አብርሃም፣ ዘሮቹ ይሖዋ የሚያቋቁመው መንግሥት ክፍል እንደሚሆኑ ያውቅ ነበር፤ በመሆኑም ይሖዋ የገባው ይህ ቃል የሚፈጽምበትን ጊዜ ለመጠባበቅ ፈቃደኛ ነበር። አብርሃም፣ አምላክ ንድፍ ያወጣላትን ከተማ ወይም መንግሥት ይጠባበቅ እንደነበር ያሳየው እንዴት ነው? አንደኛ፣ የየትኛውም ምድራዊ መንግሥት ዜጋ አልሆነም። በአንድ ቦታ ላይ ሰፍሮ ከመኖርና ለየትኛውም ሰብዓዊ ንጉሥ ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ ከቦታ ቦታ እየተዘዋወረ ይኖር ነበር። ከዚህም ሌላ አብርሃም የራሱን መንግሥት ለማቋቋም አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ይሖዋን ይታዘዝና እሱ የገባለትን ቃል እስኪፈጽም ይጠባበቅ ነበር። አብርሃም ይህን ማድረጉ በይሖዋ ላይ አስደናቂ እምነት እንደነበረው ያሳያል። w20.08 3 አን. 4-5
ቅዳሜ፣ ግንቦት 14
የሞተ ከኃጢአቱ ነፃ ወጥቷል።—ሮም 6:7
በክርስቶስ አገዛዝ ሥር የሚኖር ማንኛውም ሰው “ታምሜአለሁ” እንደማይል ይሖዋ ቃል ገብቷል። (ኢሳ. 33:24) በመሆኑም ሙታን የሚነሱት ጤናማ አካል ይዘው ነው። ይሁንና ወዲያውኑ ፍጽምና ደረጃ ላይ ይደርሳሉ ማለት አይደለም። እንዲህ ቢሆን፣ ቤተሰቦቻቸውና ወዳጆቻቸው እነሱን መለየት ሊከብዳቸው ይችላል። ሁሉም የሰው ዘር በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ቀስ በቀስ ወደ ፍጽምና ደረጃ የሚደርስ ይመስላል። ኢየሱስ መንግሥቱን ለአባቱ መልሶ የሚያስረክበው በሺው ዓመት ግዛት መጨረሻ ላይ ነው። በዚያን ጊዜ፣ መንግሥቱ የተቋቋመበትን ዓላማ ዳር ያደርሳል፤ ከሚያጠናቅቃቸው ሥራዎች መካከል ደግሞ የሰውን ዘር ወደ ፍጽምና ማድረስ ይገኝበታል። (1 ቆሮ. 15:24-28፤ ራእይ 20:1-3) በሞት የተለዩህን የምትወዳቸውን ሰዎች እንደገና ስታገኝ ምን እንደሚሰማህ እስቲ አስበው። በሳቅ ትፍለቀለቅ ወይም የደስታ እንባ ታነባ ይሆን? ወይስ ለይሖዋ ከልብ የመነጨ የውዳሴ መዝሙር ለመዘመር ትነሳሳለህ? እርግጠኛ የምንሆንበት አንድ ነገር አለ፤ አሳቢ የሆነው አባታችን እና አፍቃሪ የሆነው ልጁ አስደናቂ የሆነውን የትንሣኤ ስጦታ እንድናገኝ አጋጣሚ ስለከፈቱልን ለእነሱ ያለን ፍቅር በእጅጉ መጨመሩ አይቀርም። w20.08 16-17 አን. 9-10
እሁድ፣ ግንቦት 15
እያንዳንዱ ሰው ከአምላክ ያገኘው የራሱ ስጦታ አለው፤ አንዱ አንድ ዓይነት ስጦታ ሲኖረው ሌላው ደግሞ ሌላ ዓይነት ስጦታ አለው።—1 ቆሮ. 7:7
ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ይሖዋን በነጠላነት ማገልገል ይችሉ እንደሆነ እንዲያስቡበት ክርስቲያኖችን አበረታቷል። (1 ቆሮ. 7:8, 9) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ጳውሎስ ያላገቡ ክርስቲያኖችን ዝቅ አድርጎ አልተመለከታቸውም። እንዲያውም ነጠላ የነበረውን ወጣቱን ጢሞቴዎስን ከባድ ኃላፊነት እንዲሸከም መርጦታል። (ፊልጵ. 2:19-22) የአንድን ወንድም ብቃት፣ በማግባቱ ወይም ባለማግባቱ መመዘን ስህተት እንደሆነ ከዚህ በግልጽ ማየት ይቻላል። (1 ቆሮ. 7:32-35, 38) ኢየሱስም ሆነ ጳውሎስ፣ ማግባት ወይም በነጠላነት መቆየት ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ መሥፈርት እንደሆነ አላስተማሩም። ታዲያ ስለ ትዳርና ስለ ነጠላነት ምን አመለካከት ሊኖረን ይገባል? የጥቅምት 1, 2012 መጠበቂያ ግንብ እንደሚከተለው በማለት ነጥቡን ግሩም አድርጎ አስቀምጦታል፦ “ጋብቻም ሆነ ነጠላነት ከአምላክ የተገኙ ስጦታዎች ናቸው ሊባል ይችላል። . . . ይሖዋ ነጠላነትን ለኃፍረት ወይም ለሐዘን እንደሚዳርግ ነገር አድርጎ አይመለከተውም።” ይህን በመገንዘብ በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ነጠላ ወንድሞችንና እህቶችን ልናከብራቸው ይገባል። w20.08 28 አን. 8-9
ሰኞ፣ ግንቦት 16
ስለዚያ ቀንና ሰዓት ከአብ ብቻ በቀር . . . ማንም አያውቅም።—ማቴ. 24:36
በአንዳንድ አገሮች ያሉ ሰዎች ምሥራቹ ሲሰበክላቸው በጉጉት ያዳምጣሉ! ሲፈልጉት የቆዩትን እውነት እንዳገኙ ይሰማቸዋል። በሌሎች አገሮች ግን ብዙ ሰዎች ስለ አምላክም ሆነ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የማወቅ ፍላጎት የላቸውም። አንተ በምትኖርበት አካባቢ አብዛኞቹ ሰዎች ለምሥራቹ የሚሰጡት ምላሽ ምንድን ነው? የሰዎች ምላሽ ምንም ይሁን ምን ይሖዋ ሥራው አብቅቷል እስኪለን ድረስ መስበካችንን እንድንቀጥል ይጠብቅብናል። ይሖዋ በወሰነው ጊዜ የስብከቱ ሥራ ያበቃል፤ ከዚያም “መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴ. 24:14) ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን በዓለም ላይ የሚፈጸሙ ክንውኖችንና በሰዎች ባሕርይ ላይ የሚታየውን ለውጥ ለደቀ መዛሙርቱ አስቀድሞ ተናግሯል፤ እነዚህ ሁኔታዎች ተከታዮቹ በስብከቱ ሥራ ላይ ትኩረት እንዳያደርጉ እንቅፋት ሊሆኑባቸው እንደሚችሉ ያውቅ ነበር። በመሆኑም ደቀ መዛሙርቱን “ምንጊዜም ነቅታችሁ ጠብቁ” ሲል መክሯቸዋል። (ማቴ. 24:42) በኖኅ ዘመን ሰዎች፣ ኖኅ ለሚሰብከው ማስጠንቀቂያ ትኩረት እንዳይሰጡ ያደረጓቸው ነገሮች ነበሩ፤ በዛሬው ጊዜም እነዚህ ነገሮች ትኩረታችንን ሊከፋፍሉብን ይችላሉ። (ማቴ. 24:37-39፤ 2 ጴጥ. 2:5) እንግዲያው ይሖዋ በሰጠን ሥራ ላይ ምንጊዜም ትኩረት ለማድረግ እንጣር። w20.09 8 አን. 1-2, 4
ማክሰኞ፣ ግንቦት 17
የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል።—2 ጢሞ. 3:12
ሰይጣን ‘በታላቅ ቁጣ ተሞልቷል’፤ ስለዚህ የእሱን ቁጣ በሆነ መንገድ ማምለጥ እንደምንችል ማሰብ ሞኝነት ነው። (ራእይ 12:12) በቅርቡ ሁላችንም ንጹሕ አቋማችንን የሚፈትን ነገር እንደሚገጥመን የታወቀ ነው። ብዙም ሳይቆይ፣ “ከዓለም መጀመሪያ አንስቶ እስካሁን ድረስ ሆኖ የማያውቅ ዳግመኛም የማይሆን ታላቅ መከራ” ይመጣል። (ማቴ. 24:21) በዚያ ወቅት የቤተሰባችን አባላት ይነሱብን እንዲሁም ሥራችን ይታገድ ይሆናል። (ማቴ. 10:35, 36) ታዲያ እያንዳንዳችን እንደ ንጉሥ አሳ ይሖዋ እንደሚረዳንና እንደሚጠብቀን እንተማመናለን? (2 ዜና 14:11) ይሖዋ መንፈሳዊነታችንን እንድናጠናክር በመርዳት ወደፊት ለሚመጣው ነገር ሲያዘጋጀን ቆይቷል። ‘ታማኝና ልባም ባሪያን’ በመጠቀም በአምልኳችን ለመጽናት የሚያስፈልገንን ገንቢ መንፈሳዊ ምግብ “በተገቢው ጊዜ” እያቀረበልን ነው። (ማቴ. 24:45) ሆኖም እኛም በይሖዋ ላይ የማይናወጥ እምነት ለማዳበር ጥረት በማድረግ የራሳችንን ድርሻ መወጣት አለብን።—ዕብ. 10:38, 39፤ w20.09 18 አን. 16-18
ረቡዕ፣ ግንቦት 18
የንጉሥ ልብ በይሖዋ እጅ እንዳለ ጅረት ነው። እሱ ደስ ወዳሰኘው አቅጣጫ ሁሉ ይመራዋል።—ምሳሌ 21:1
ይሖዋ ከዓላማው ጋር የሚስማማ በሚሆንበት ወቅት፣ በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች የእሱን ፈቃድ እንዲፈጽሙ ሊያደርግ ይችላል፤ ይህን የሚያደርገው ኃያል ቅዱስ መንፈሱን ተጠቅሞ ነው። ሰዎች አንድ ጅረት ወደፈለጉት አቅጣጫ እንዲፈስ ለማድረግ ቦይ ይቆፍራሉ። በተመሳሳይም ይሖዋ መንፈሱን ተጠቅሞ በሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ሐሳብ ሊመራ ይችላል፤ ይህን የሚያደርገው ከእሱ ዓላማ ጋር የሚስማማ ነገር እንዲያከናውኑ ሲል ነው። ይሖዋ ይህን በሚያደርግበት ወቅት ባለሥልጣናቱ የአምላክን ሕዝቦች የሚጠቅም ውሳኔ ለማድረግ ይነሳሳሉ። (ከዕዝራ 7:21, 25, 26 ጋር አወዳድር።) ምን ማድረግ እንችላለን? ‘ነገሥታትና በሥልጣን ላይ ያሉ’ ሰዎች፣ አምልኳችንን እና አገልግሎታችንን የሚነካ ውሳኔ በሚያደርጉበት ወቅት እነሱን በተመለከተ ልንጸልይ እንችላለን። (1 ጢሞ. 2:1, 2፤ ነህ. 1:11) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖች እንዳደረጉት ሁሉ እኛም በእስር ላይ ስላሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ወደ አምላክ አጥብቀን እንጸልያለን።—ሥራ 12:5፤ ዕብ. 13:3፤ w20.11 15 አን. 13-14
ሐሙስ፣ ግንቦት 19
ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን ደቀ መዛሙርት አድርጉ፤ [አጥምቋቸው]።—ማቴ. 28:19
ያስጠናኸው ሰው ሲጠመቅ ማየት በጣም እንደሚያስደስትህ የታወቀ ነው! (1 ተሰ. 2:19, 20) አዲስ ተጠማቂዎች፣ ላስጠኗቸው ክርስቲያኖች ብቻ ሳይሆን ለመላው ጉባኤ ግሩም “የምሥክር ወረቀት” ናቸው። (2 ቆሮ. 3:1-3) ለአራት ዓመታት ያህል በዓለም ዙሪያ በየወሩ በአማካይ 10,000,000 ገደማ የሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች እንደተመሩ ሪፖርት ተደርጓል፤ ይህም በጣም የሚያስደስት ነው። በእነዚሁ ዓመታት ውስጥ በየዓመቱ በአማካይ ከ280,000 የሚበልጡ ሰዎች ተጠምቀው የይሖዋ ምሥክሮችና የኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሆነዋል። ታዲያ በሚሊዮኖች ከሚቆጠሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች መካከል ተጨማሪ ሰዎች እንዲጠመቁ መርዳት የምንችለው እንዴት ነው? ይሖዋ ታጋሽ በመሆን፣ ሰዎች የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆን የሚችሉበት ጊዜና አጋጣሚ ሰጥቷል፤ ይህ ጊዜ እስካለ ድረስ እነዚህ ሰዎች ፈጣን እድገት አድርገው እንዲጠመቁ ለመርዳት አቅማችን የሚፈቅደውን ሁሉ ማድረግ እንፈልጋለን። የቀረው ጊዜ በጣም አጭር ነው!—1 ቆሮ. 7:29ሀ፤ 1 ጴጥ. 4:7፤ w20.10 6 አን. 1-2
ዓርብ፣ ግንቦት 20
አምላክ ትዕቢተኞችን ይቃወማል፤ ለትሑታን ግን ጸጋን ይሰጣል።—ያዕ. 4:6
ንጉሥ ሳኦል ይሖዋን አልታዘዘም። ነቢዩ ሳሙኤል ስለ ጉዳዩ ሲያነጋግረው ደግሞ ሳኦል ስህተቱን አምኖ አልተቀበለም። ከዚህ ይልቅ ስህተቱን በማቃለልና ጥፋቱን በሌሎች ላይ በማላከክ ድርጊቱን ለማስተባበል ሞከረ። (1 ሳሙ. 15:13-24) ሳኦል ከዚህ በፊትም ተመሳሳይ ዝንባሌ አሳይቷል። (1 ሳሙ. 13:10-14) ልቡ እንዲታበይ መፍቀዱ የሚያሳዝን ነው። አስተሳሰቡን አላስተካከለም፤ በመሆኑም ይሖዋ ተግሣጽ የሰጠው ከመሆኑም ሌላ የእሱን ንግሥና አልተቀበለውም። እንደ ሳኦል ዓይነት ስህተት ላለመሥራት ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘በአምላክ ቃል ላይ የሚገኝን ምክር ሳነብ ምክሩን ተግባራዊ ላለማድረግ ሰበብ አስባብ እፈጥራለሁ? ድርጊቴ ያን ያህል መጥፎ እንዳልሆነ ራሴን ለማሳመን እሞክራለሁ? ጥፋቴን በሌሎች ላይ አላክካለሁ?’ ከእነዚህ ጥያቄዎች ለአንዱም እንኳ የምንሰጠው መልስ ‘አዎ’ ከሆነ አስተሳሰባችንን እና ዝንባሌያችንን ማስተካከል ይኖርብናል። እንዲህ ካላደረግን ልባችን እየታበየ ይሄዳል፤ ትዕቢተኛ ከሆንን ደግሞ ይሖዋ እንደ ወዳጆቹ አድርጎ አይቀበለንም። w20.11 20 አን. 4-5
ቅዳሜ፣ ግንቦት 21
አስጨናቂ የሆኑት ዘመናት ከመምጣታቸው እንዲሁም “ደስ አያሰኙኝም” የምትላቸው ዓመታት ከመድረሳቸው በፊት በወጣትነትህ ጊዜ ታላቁን ፈጣሪህን አስብ።—መክ. 12:1
ወጣቶች፣ ማንን እንደምታገለግሉ ምረጡ። ይሖዋ ማን እንደሆነ፣ ዓላማው ምን እንደሆነና የእሱ ፈቃድ ከእናንተ ሕይወት ጋር የሚገናኘው እንዴት እንደሆነ ለራሳችሁ ማረጋገጥ አለባችሁ። (ሮም 12:2) እንዲህ ካደረጋችሁ በሕይወታችሁ ውስጥ ከሁሉ የላቀውን ውሳኔ ማድረግ ማለትም ይሖዋን ለማገልገል መምረጥ ትችላላችሁ። (ኢያሱ 24:15) መጽሐፍ ቅዱስን የምታነቡበትና የምታጠኑበት ቋሚ ፕሮግራም ካላችሁ ለይሖዋ ያላችሁ ፍቅር እያደገ ይሄዳል፤ እንዲሁም እምነታችሁ ይበልጥ ይጠናከራል። በሕይወታችሁ ውስጥ የይሖዋን ፈቃድ ለማስቀደም ምረጡ። የሰይጣን ዓለም ተሰጥኦዋችሁን የራሳችሁን ፍላጎት ለማሟላት ከተጠቀማችሁበት ደስተኛ እንደምትሆኑ ሊያሳምናችሁ ይሞክራል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን፣ ቁሳዊ ሀብት በማካበት ላይ ያተኮረ ሕይወት የሚመሩ ሰዎች “ሁለንተናቸውን በብዙ ሥቃይ” ይወጋሉ። (1 ጢሞ. 6:9, 10) በሌላ በኩል ይሖዋን የምትሰሙና የእሱን ፈቃድ ለማስቀደም የምትመርጡ ከሆነ ሕይወታችሁ ስኬታማ ይሆናል፤ እንዲሁም ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን ትችላላችሁ።—ኢያሱ 1:8፤ w20.10 30-31 አን. 17-18
እሁድ፣ ግንቦት 22
የአምላክን መንግሥት ምሥራች ማወጅ አለብኝ፤ ምክንያቱም የተላክሁት ለዚህ ዓላማ ነው።—ሉቃስ 4:43
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ኢየሱስ የሰበከው መልእክት ለመላው የሰው ዘር ተስፋ የሚፈነጥቅ ነበር። (ሉቃስ 4:43) ተከታዮቹም “እስከ ምድር ዳር ድረስ” በመመሥከር እሱ የጀመረውን ሥራ እንዲቀጥሉ አዟቸዋል። (ሥራ 1:8) እርግጥ ነው፣ በራሳቸው ኃይል ይህን ሥራ ማከናወን አይችሉም። ኢየሱስ ቃል የገባላቸው “ረዳት” ማለትም የመንፈስ ቅዱስ እርዳታ ያስፈልጋቸው ነበር። (ዮሐ. 14:26፤ ዘካ. 4:6) የኢየሱስ ተከታዮች በ33 ዓ.ም. የጴንጤቆስጤ ዕለት መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ። በዚህ መንፈስ እርዳታ ወዲያውኑ የስብከቱን ሥራቸውን ጀመሩ። በአጭር ጊዜ ውስጥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ምሥራቹን ተቀበሉ። (ሥራ 2:41፤ 4:4) ተቃውሞ ባጋጠማቸው ወቅት ደቀ መዛሙርቱ በፍርሃት አልተሸነፉም፤ ከዚህ ይልቅ የአምላክን እርዳታ ጠየቁ። “[ባሪያዎችህ] ቃልህን በፍጹም ድፍረት መናገራቸውን እንዲቀጥሉ እርዳቸው” በማለት ጸለዩ። ከዚያም በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ሲሆን ‘የአምላክን ቃል በድፍረት መናገራቸውን’ ቀጠሉ።—ሥራ 4:18-20, 29, 31፤ w20.10 21 አን. 4-5
ሰኞ፣ ግንቦት 23
ቅዱሳን መጻሕፍት እንደሚሉት ክርስቶስ ስለ ኃጢአታችን ሞተ፤ ደግሞም . . . ተነሳ።—1 ቆሮ. 15:3, 4
ይሖዋ ኢየሱስን ከሞት እንዳስነሳው እርግጠኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን የመሠከሩ ብዙ የዓይን ምሥክሮች ነበሩ። (1 ቆሮ. 15:5-7) ሐዋርያው ጳውሎስ መጀመሪያ ላይ የጠቀሰው ምሥክር፣ ሐዋርያው ጴጥሮስ (ኬፋ) ነው። ጴጥሮስ ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን እንዳየው ሌሎች ደቀ መዛሙርትም መሥክረዋል። (ሉቃስ 24:33, 34) በተጨማሪም “አሥራ ሁለቱ” ማለትም ሐዋርያቱ፣ ኢየሱስን ከሞት ከተነሳ በኋላ አይተውታል። ከዚያም ክርስቶስ “በአንድ ጊዜ ከ500 ለሚበልጡ ወንድሞች” ታየ፤ ይህ የሆነው በማቴዎስ 28:16-20 ላይ በተገለጸውና በገሊላ በተከናወነው አስደሳች ስብሰባ ወቅት ሊሆን ይችላል። ኢየሱስ ‘ለያዕቆብም ታይቷል’፤ እዚህ ላይ የተጠቀሰው ያዕቆብ የኢየሱስ ወንድም መሆን አለበት። ያዕቆብ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ቀደም ሲል አላመነም ነበር። (ዮሐ. 7:5) ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን ካየ በኋላ ግን በእሱ አመነ። በ55 ዓ.ም. ገደማ ማለትም ጳውሎስ ይህን ደብዳቤ በጻፈበት ወቅት፣ ለኢየሱስ ትንሣኤ የዓይን ምሥክር ከነበሩት ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በሕይወት የነበሩ መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል። ስለዚህ ጥርጣሬ ያደረበት ማንኛውም ሰው፣ በወቅቱ በሕይወት የነበሩትን እምነት የሚጣልባቸው የዓይን ምሥክሮች ማነጋገር ይችል ነበር። w20.12 3 አን. 5, 7-8
ማክሰኞ፣ ግንቦት 24
ታሞ በአልጋ ላይ ተኝቶ ሳለ ይሖዋ ይደግፈዋል።—መዝ. 41:3
ጤንነታችን ጥሩ በማይሆንበት ጊዜ በተለይ ደግሞ ከማይድን በሽታ ጋር በምንታገልበት ወቅት አዎንታዊ አመለካከት መያዝ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። በመሆኑም የይሖዋን እርዳታ መጠየቅ ያስፈልገናል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ በአሁኑ ጊዜ በተአምር አይፈውሰንም፤ ሆኖም ያጽናናናል እንዲሁም ለመጽናት የሚያስፈልገንን ብርታት ይሰጠናል። (መዝ. 94:19) ለምሳሌ የቤት ውስጥ ሥራዎችን በማከናወን ረገድ እርዳታ ካስፈለገን የእምነት አጋሮቻችን እንዲያግዙን ሊያነሳሳቸው ይችላል። ወንድሞቻችን አብረውን እንዲጸልዩም ሊያነሳሳቸው ይችላል። አሊያም ደግሞ በቃሉ ውስጥ የሚገኙ የሚያጽናኑ ሐሳቦችን እንድናስታውስ ሊረዳን ይችላል፤ ለምሳሌ፣ ሕመምና ሥቃይ በሌለበት አዲስ ዓለም ስለሚኖረን ፍጹም ሕይወት እንድናስብ ሊያደርገን ይችላል። (ሮም 15:4) ሆኖም በአገልግሎት ማከናወን የምንችለው ነገር በጣም ውስን እንደሆነ ሊሰማን ይችላል። ሎረል የተባለች እህት እንደ ሳንባ ሆኖ በሚያገለግል ማሽን ውስጥ ለ37 ዓመታት ኖራለች። በካንሰር ትሠቃይ ነበር፤ ከባድ ቀዶ ሕክምናዎችን አድርጋለች እንዲሁም አስከፊ የቆዳ በሽታ ነበረባት። ሆኖም ይህ ሁኔታ መስበኳን እንድታቆም አላደረጓትም። ወደ ቤቷ ለሚመጡ ነርሶች እና ሌሎች የሕክምና ባለሙያዎች ትመሠክር የነበረ ከመሆኑም ሌላ ቢያንስ 17 ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ረድታለች! w20.12 24 አን. 9፤ 25 አን. 12
ረቡዕ፣ ግንቦት 25
ይሖዋ ከጎኔ ነው፤ አልፈራም። ሰው ምን ሊያደርገኝ ይችላል?—መዝ. 118:6
ሐዋርያው ጳውሎስ እርዳታ ያስፈልገው ነበር። በ56 ዓ.ም. ገደማ ተቃዋሚዎቹ በኢየሩሳሌም ካለው ቤተ መቅደስ እየጎተቱ ካወጡት በኋላ ሊገድሉት ሞክረው ነበር። በቀጣዩ ቀን ጳውሎስ በሳንሄድሪን ሸንጎ ፊት በቀረበበት ወቅት ጠላቶቹ ሊገነጣጥሉት ደርሰው ነበር። (ሥራ 21:30-32፤ 22:30፤ 23:6-10) በዚህ ጊዜ ጳውሎስ ‘በዚህ ሁኔታ የምዘልቀው እስከ መቼ ድረስ ነው?’ የሚል ስሜት ተፈጥሮበት ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ ምን እርዳታ አግኝቷል? ጳውሎስ ከተያዘ በኋላ ሌሊት ላይ “ጌታ” ማለትም ኢየሱስ አጠገቡ ቆሞ እንዲህ አለው፦ “አይዞህ፣ አትፍራ! ምክንያቱም በኢየሩሳሌም ስለ እኔ በሚገባ እንደመሠከርክ ሁሉ በሮምም ልትመሠክርልኝ ይገባል።” (ሥራ 23:11) ጳውሎስ ይህን ሲሰማ እንዴት ተበረታቶ ይሆን! ኢየሱስ ጳውሎስን በኢየሩሳሌም ለሰጠው ምሥክርነት አመስግኖታል። ከዚያም በሰላም ሮም እንደሚደርስና በዚያ ተጨማሪ ምሥክርነት እንደሚሰጥ አረጋግጦለታል። ጳውሎስ ይህን ማረጋገጫ መስማቱ በአባቱ እቅፍ እንዳለ ልጅ የመረጋጋት ስሜት እንዲያድርበት አድርጎ መሆን አለበት። w20.11 12 አን. 1, 3፤ 13 አን. 4
ሐሙስ፣ ግንቦት 26
አስተማማኝና ጽኑ የሆነ ይህ ተስፋ አለን።—ዕብ. 6:19
የመንግሥቱ ተስፋ “ለነፍሳችን እንደ መልሕቅ” ነው፤ ከባድ ችግሮች ወይም የሚያስጨንቁ ሐሳቦች ሲያጋጥሙን እንዳንናወጥ ይረዳናል። ወደፊት ይሖዋ የገባው ቃል በሚፈጸምበት ወቅት ስለሚኖረን ሕይወት አሰላስሉ፤ በዚያን ጊዜ ምንም ዓይነት መጥፎ ሐሳብ ወደ አእምሯችን አይመጣም። (ኢሳ. 65:17) የሚያስጨንቁ ነገሮች በሌሉበት ሰላማዊ ዓለም ውስጥ ስትኖሩ ይታያችሁ። (ሚክ. 4:4) ተስፋችሁ እውን ሆኖ እንዲታያችሁ ማድረግ የምትችሉበት ሌላው መንገድ ደግሞ ስለ ተስፋችሁ ለሌሎች መናገር ነው። በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ አድርጉ። እንዲህ በማድረግ “ሙሉ በሙሉ አስተማማኝ የሆነውን ተስፋ እስከ መጨረሻው መያዝ” ትችላላችሁ። (ዕብ. 6:11) ይህ ሥርዓት ወደ ፍጻሜው እየተቃረበ ሲሄድ ጭንቀት የሚፈጥሩ ተጨማሪ ችግሮች ሊያጋጥሙን እንደሚችሉ እንጠብቃለን። በራሳችን ብርታት ሳይሆን በይሖዋ በመታመን እነዚህን ችግሮች ሳንረበሽ መጋፈጥ እንችላለን። እንግዲያው ይሖዋ እንደሚከተለው በማለት በገባው ቃል ላይ እምነት እንዳለን በተግባር እናሳይ፦ “ሳትረበሹ፣ ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ።”—ኢሳ. 30:15፤ w21.01 7 አን. 17-18
ዓርብ፣ ግንቦት 27
ይሖዋ እጅግ አፍቃሪ [ነው]።—ያዕ. 5:11
ያዕቆብ 5:11 ይሖዋ አፍቃሪ ስለመሆኑ ከተናገረ በኋላ ስለ መሐሪነቱ ይገልጻል፤ ምሕረት ይሖዋን እንድንወደው የሚያነሳሳን ሌላው ባሕርይ ነው። (ዘፀ. 34:6) ይሖዋ ለእኛ ምሕረት የሚያሳይበት አንዱ መንገድ ስህተቶቻችንን ይቅር ማለት ነው። (መዝ. 51:1) ምሕረት የሚለው ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ አገባቡ ከይቅር ባይነት ያለፈ ሰፊ ትርጉም አለው። ምሕረት፣ አንድ የተቸገረ ሰው ስናይ እንድናዝንለትና እሱን ለመርዳት እርምጃ እንድንወስድ የሚያነሳሳ ጥልቅ ስሜት ነው። ይሖዋ፣ እሱ እኛን ለመርዳት እንዲነሳሳ የሚያደርገው ጥልቅ ስሜት፣ እናት ለልጇ ካላት ስሜትም እንኳ እንደሚበልጥ ገልጿል። (ኢሳ. 49:15) ችግር ላይ ስንወድቅ፣ ይሖዋ እኛን ለመርዳት የሚያነሳሳው ምሕረቱ ነው። (መዝ. 37:39፤ 1 ቆሮ. 10:13) እኛም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ቅር ሲያሰኙን ይቅር በማለትና ቂም ባለመያዝ ምሕረት ማሳየት እንችላለን። (ኤፌ. 4:32) ምሕረት የምናሳይበት ሌላው ዋነኛ መንገድ ግን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ችግር ላይ ሲወድቁ መርዳት ነው። እንዲህ ስናደርግ ልባዊ ፍቅር በማሳየት ረገድ ተወዳዳሪ የሌለውን ይሖዋን እንመስለዋለን።—ኤፌ. 5:1፤ w21.01 21 አን. 5
ቅዳሜ፣ ግንቦት 28
ክርስቶስ . . . የእሱን ፈለግ በጥብቅ እንድትከተሉ አርዓያ [ትቶላችኋል]።—1 ጴጥ. 2:21
አንድ የቤተሰብ ራስ ሚዛኑን መጠበቅ ይኖርበታል። ቤተሰቡን ለማስተዳደር ሲል በሰብዓዊ ሥራ ከልክ በላይ ከመጠመዱ የተነሳ የቤተሰቡን መንፈሳዊና ስሜታዊ ፍላጎት ከማሟላት እንዲሁም ሥልጠና ከመስጠት ወደኋላ ማለት የለበትም። ይሖዋ ለራሳችን ጥቅም ሲል ሥልጠናና ተግሣጽ ይሰጠናል። (ዕብ. 12:7-9) ኢየሱስም ልክ እንደ አባቱ በእሱ ሥልጣን ሥር ያሉትን ሰዎች ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ያሠለጥናቸዋል። (ዮሐ. 15:14, 15) ጠንከር ያለ ምክር መስጠት የሚያስፈልገው ጊዜ ቢኖርም ይህን የሚያደርገው በደግነት ነው። (ማቴ. 20:24-28) ፍጹማን እንዳልሆንንና ስህተት መሥራት እንደሚቀናን ይረዳል። (ማቴ. 26:41) የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ የሚከተል የቤተሰብ ራስ፣ የቤተሰቡ አባላት ፍጹማን እንዳልሆኑ አይዘነጋም። በሚስቱ ወይም በልጆቹ ላይ ‘መራራ ቁጣ አይቆጣም።’ (ቆላ. 3:19) ከዚህ ይልቅ እሱ ራሱ ፍጹም እንዳልሆነ በማስታወስ ገላትያ 6:1 እንደሚለው “በገርነት መንፈስ” ሊያስተካክላቸው ይሞክራል። ኢየሱስ እንዳደረገው፣ ከሁሉ የተሻለው የማስተማሪያ ዘዴ ምሳሌ ሆኖ መገኘት እንደሆነ ይገነዘባል። w21.02 6-7 አን. 16-18
እሁድ፣ ግንቦት 29
እስትንፋስ ያለው ሁሉ ያህን ያወድስ።—መዝ. 150:6
ይሖዋ በጉባኤው ውስጥ ያለውን የእያንዳንዱን ክርስቲያን ሕይወት የዋጀው በቤዛው አማካኝነት ነው። (ማር. 10:45፤ ሥራ 20:28፤ 1 ቆሮ. 15:21, 22) ከዚህ አንጻር ሕይወቱን ቤዛ አድርጎ የሰጠውን ኢየሱስን የጉባኤው ራስ አድርጎ መሾሙ የተገባ ነው። ኢየሱስ ራሳችን እንደመሆኑ መጠን ግለሰቦች፣ ቤተሰቦችና መላው ጉባኤ የሚመሩባቸውን ደንቦች የማውጣትና የማስፈጸም ሥልጣን አለው። (ገላ. 6:2) ሆኖም ኢየሱስ ደንብ በማውጣት ብቻ አይወሰንም። እያንዳንዳችንን ይመግበናል እንዲሁም በፍቅር ይንከባከበናል። (ኤፌ. 5:29) እህቶች እነሱን እንዲንከባከቡ የተሾሙ ወንዶች የሚሰጡትን መመሪያ በመከተል ክርስቶስን እንደሚያከብሩ ያሳያሉ። ወንድሞች፣ እህቶችን በማክበር ስለ ራስነት ሥርዓት ትክክለኛው ግንዛቤ እንዳላቸው ያሳያሉ። በጉባኤው ውስጥ ያለን ሁላችን ስለ ራስነት ሥርዓት ትክክለኛው ግንዛቤ ካለንና ለዚህ ዝግጅት አክብሮት የምናሳይ ከሆነ በጉባኤው ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን አስተዋጽኦ እናደርጋለን። ከሁሉም በላይ ደግሞ በሰማይ ላለው አፍቃሪ አባታችን ለይሖዋ ውዳሴ እናመጣለን። w21.02 18-19 አን. 14-17
ሰኞ፣ ግንቦት 30
ዳዊት . . . ይሖዋን ጠየቀ።—1 ሳሙ. 30:8
ዳዊትና ሰዎቹ በስደት ይኖሩ በነበረበት ወቅት ቤተሰቦቻቸውን ትተው ለውጊያ ዘምተው ነበር። ወንዶቹ በሌሉበት በዚህ ወቅት የጠላት ሠራዊት ጥቃት በመሰንዘር ቤተሰቦቻቸውን በምርኮ ወሰደ። ዳዊት ልምድ ያለው ተዋጊ እንደመሆኑ መጠን በምርኮ የተያዙትን ለማስመለስ ውጤታማ የሆነ ስልት መቀየስ እንደማይከብደው ሊያስብ ይችል ነበር። ዳዊት ግን የይሖዋን እርዳታ ጠይቋል። ይሖዋን “ይህን ወራሪ ቡድን ላሳደው?” ብሎ ጠየቀ። ይሖዋም ዳዊት ወራሪውን ቡድን እንዲያሳድድ የነገረው ሲሆን ውጤታማ እንደሚሆንም አረጋገጠለት። (1 ሳሙ. 30:7-10) ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት ታገኛላችሁ? ውሳኔ ከማድረጋችሁ በፊት የሌሎችን ምክር ጠይቁ። ወጣቶች፣ ወላጆቻችሁን አማክሩ። ተሞክሮ ካላቸው የጉባኤ ሽማግሌዎችም ጥሩ ምክር ማግኘት ትችላላችሁ። ይሖዋ እነዚህን የተሾሙ ወንዶች ይተማመንባቸዋል፤ እናንተም ልትተማመኑባቸው ትችላላችሁ። ይሖዋ የሚመለከታቸው ለጉባኤው እንደተሰጡ ‘ስጦታዎች’ አድርጎ ነው። (ኤፌ. 4:8) እነሱን በእምነታቸው መምሰላችሁና የሚሰጧችሁን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር ማዳመጣችሁ ይጠቅማችኋል። w21.03 4-5 አን. 10-11
ማክሰኞ፣ ግንቦት 31
ማንኛውም [ነገር ከአምላክ] ፍቅር ሊለየን [አይችልም]።—ሮም 8:38, 39
ኢየሱስ የተማረውን ነገር በተግባር የማያውል ሰው፣ ቤቱን በአሸዋ ላይ ከሠራ ሰው ጋር እንደሚመሳሰል ተናግሯል። ይህ ሰው ቤቱን ለመገንባት ተግቶ ቢሠራም ልፋቱ ከንቱ ነው። ለምን? ምክንያቱም ጎርፍ ሲጎርፍና ነፋስ ሲነፍስ ቤቱ ይደረመሳል። (ማቴ. 7:24-27) እኛም በተመሳሳይ፣ ያገኘነውን ትምህርት በተግባር እስካላዋልን ድረስ ጥረታችን ከንቱ ነው። ፈተና ወይም ስደት ሲያጋጥመን ለመጽናት የሚያስችል ጠንካራ እምነት አይኖረንም። በሌላ በኩል ግን መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና እና የተማርነውን ነገር በተግባር ስናውል የተሻለ ውሳኔ እናደርጋለን፣ ውስጣዊ ሰላም ይኖረናል እንዲሁም እምነታችን ይበልጥ ይጠናከራል። (ኢሳ. 48:17, 18) በፈተና ውስጥ ታማኝነታችንን መጠበቅ እንድንችል፣ አዘውትረን በመጸለይ በይሖዋ እንደምንተማመን ማሳየት እንዲሁም ጥሩ የግል ጥናት ልማድ ማዳበር አለብን። ከሁሉ በላይ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነገር ለይሖዋ ክብር ማምጣት እንደሆነም ምንጊዜም ማስታወስ አለብን። ይሖዋ ፈጽሞ እንደማይተወንና ከይሖዋ ፍቅር ማንም ሊለየን እንደማይችል እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ዕብ. 13:5, 6፤ w21.03 15 አን. 6፤ 18 አን. 20