ሰኔ
ረቡዕ፣ ሰኔ 1
የአምላክን ምሥራች ለማካፈል ብቻ ሳይሆን ራሳችንን ጭምር ለእናንተ ለመስጠት ቆርጠን ነበር።—1 ተሰ. 2:8
አስተማሪዎች ለጥናቶቻቸው ልባዊ አሳቢነት ሊያሳዩአቸው ይገባል። ጥናቶችህን የወደፊት መንፈሳዊ ወንድሞችህ ወይም እህቶችህ እንደሆኑ አድርገህ ተመልከታቸው። የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በዓለም ያሉ ወዳጆቻቸውን መተውና ይሖዋን ለማገልገል አስፈላጊ የሆኑትን ለውጦች ማድረግ ቀላል እንደማይሆንላቸው የታወቀ ነው። ውጤታማ የመጽሐፍ ቅዱስ አስተማሪዎች፣ ጥናቶቻቸው ጥሩ ምሳሌ ከሚሆኗቸው የጉባኤው አስፋፊዎች ጋር እንዲቀራረቡ ያደርጋሉ። ይህም ተማሪዎቹ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር መሆን እንዲያስደስታቸው ያደርጋል፤ እነዚህ ክርስቲያኖች መንፈሳዊ እርዳታ ሊሰጧቸው እንዲሁም ችግር ሲያጋጥማቸው ሊያበረታቷቸው ይችላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን በሙሉ በጉባኤው ውስጥ እንደሚፈለጉና የመንፈሳዊ ቤተሰባችን አካል እንደሆኑ እንዲሰማቸው እንፈልጋለን። እርስ በርሱ ወደሚዋደደው ክርስቲያናዊ የወንድማማች ማኅበራችን እንዲሳቡ እንፈልጋለን። ይህም ጥናቶቻችን፣ ይሖዋን እንዳይወዱ እንቅፋት ከሚሆኑባቸው ሰዎች ጋር ያላቸውን ቅርርብ ማቋረጥ ቀላል እንዲሆንላቸው ያደርጋል። (ምሳሌ 13:20) የቀድሞ ጓደኞቻቸው ቢያገልሏቸውም በይሖዋ ድርጅት ውስጥ እውነተኛ ወዳጆች እንደሚያገኙ ያውቃሉ።—ማር. 10:29, 30፤ 1 ጴጥ. 4:4፤ w20.10 17 አን. 10-11
ሐሙስ፣ ሰኔ 2
ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል።—ማቴ. 28:18
ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና ሊኖረን የሚችለው የኢየሱስ ወዳጆች ከሆንን ብቻ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? እስቲ ሁለት ምክንያቶችን ብቻ እንመልከት። አንደኛ፣ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን “እናንተ እኔን ስለወደዳችሁኝ . . . አብ ራሱ ይወዳችኋል” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 16:27) በተጨማሪም ኢየሱስ “በእኔ በኩል ካልሆነ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 14:6) ከኢየሱስ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ሳይመሠርቱ የይሖዋ ወዳጅ ለመሆን መሞከር በር ሳይጠቀሙ ወደ አንድ ሕንፃ ለመግባት ከመሞከር ተለይቶ አይታይም። ኢየሱስ ተመሳሳይ ምሳሌ በመጠቀም “በጎቹ የሚገቡበት በር እኔ ነኝ” በማለት ስለ ራሱ ተናግሯል። (ዮሐ. 10:7) ሁለተኛ፣ ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መልኩ አንጸባርቋል። ለደቀ መዛሙርቱ “እኔን ያየ ሁሉ አብንም አይቷል” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 14:9) በመሆኑም ስለ ይሖዋ ማወቅ የምንችልበት ዋነኛው መንገድ የኢየሱስን ሕይወት ማጥናት ነው። ስለ ኢየሱስ እየተማርን ስንሄድ ለእሱ ያለን ፍቅር ያድጋል። ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት እየተጠናከረ ሲሄድ ደግሞ ለአባቱ ያለን ፍቅር ይጨምራል። w20.04 21-22 አን. 5-6
ዓርብ፣ ሰኔ 3
በድክመት . . . ደስ እሰኛለሁ፤ ስደክም ያን ጊዜ ብርቱ ነኝና።—2 ቆሮ. 12:10
የአልጋ ቁራኛ ሆነሃል? ወይም የምትንቀሳቀሰው በተሽከርካሪ ወንበር ነው? ጉልበትህ ወይም ዓይንህ ደክሟል? ታዲያ እንዲህ ያለ ሁኔታ ውስጥ ሆነህ ወጣትና ጤናማ ከሆኑት ጋር አብረህ መሮጥ ትችላለህ? አዎ፣ ትችላለህ! በዕድሜ የገፉና የአቅም ገደብ ያለባቸው በርካታ ክርስቲያኖች ወደ ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ እየሮጡ ነው። ይህን ማድረግ የቻሉት በራሳቸው ኃይል አይደለም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ የሚሰጣቸውን ኃይል ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህን የሚያደርጉበት አንዱ መንገድ በስልክ ወይም በቀጥታ የቪዲዮ ስርጭት አማካኝነት ክርስቲያናዊ ስብሰባዎችን መከታተል ነው። በተጨማሪም ለሐኪሞች፣ ለነርሶችና ለዘመዶቻቸው በመመሥከር ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ይካፈላሉ። ባለብህ የአቅም ገደብ የተነሳ በሕይወት መንገድ ላይ ለመሮጥ የሚያስችል አቅም እንደሌለህ በማሰብ ተስፋ አትቁረጥ። ይሖዋ በእሱ ላይ እምነት ስላለህና ቀደም ሲል እሱን ለማገልገል ስትል ብዙ ስለደከምክ ይወድሃል። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ የእሱ እርዳታ የሚያስፈልግህ አሁን ነው፤ እሱም ፈጽሞ አይተውህም። (መዝ. 9:10) እንዲያውም ይበልጥ ወደ አንተ ይቀርባል። w20.04 29 አን. 16-17
ቅዳሜ፣ ሰኔ 4
ምሥራቹን ለሌሎች አካፍል ዘንድ ለምሥራቹ ስል ሁሉን ነገር አደርጋለሁ።—1 ቆሮ. 9:23
ሃይማኖተኛ ከሆነ ሰው ጋር የትኞቹን ጉዳዮች አንስታችሁ መወያየት ትችላላችሁ? በጋራ የሚያስማማችሁን ነገር ፈልጉ። ለምሳሌ፣ ግለሰቡ አንድ አምላክ ብቻ እንዳለ ያምን ይሆናል፤ ኢየሱስን የሰው ዘር አዳኝ አድርጎ ሊቀበል ይችላል፤ ወይም ደግሞ የምንኖርበት የክፋት ዘመን በቅርቡ እንደሚያበቃ ያምን ይሆናል። በጋራ የሚያስማማችሁን ነገር መሠረት በማድረግ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት ግለሰቡን በሚማርክ መንገድ ለመናገር ጥረት አድርጉ። ሰዎች ሃይማኖታቸው የሚያስተምራቸውን እያንዳንዱን ነገር አምነው ላይቀበሉ እንደሚችሉ አስታውሱ። በመሆኑም የአንድን ሰው ሃይማኖት ካወቃችሁ በኋላም እንኳ እሱ በግሉ የሚያምንበትን ነገር ለማወቅ ሞክሩ። አንድ ሚስዮናዊ እንዳስተዋለው አንዳንድ ሰዎች በሥላሴ እንደሚያምኑ ቢናገሩም አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ አንድ አምላክ ናቸው ብለው አያምኑም። ሚስዮናዊው “ይህን ማወቃችን ከግለሰቡ ጋር የሚያስማማንን ነገር ማግኘት ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል” ብሏል። ከዚህ አንጻር ሰዎች በእርግጥ የሚያምኑበትን ነገር ለማወቅ ጥረት አድርጉ። ይህን ካደረጋችሁ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ሁሉንም ነገር” መሆን ትችላላችሁ።—1 ቆሮ. 9:19-22፤ w20.04 10 አን. 9-10
እሁድ፣ ሰኔ 5
በዚያን ወቅት ሕዝብህ ይኸውም በመጽሐፍ ላይ ተጽፎ የተገኘ እያንዳንዱ ሰው ይተርፋል።—ዳን. 12:1
የወደፊቱን ጊዜ በልበ ሙሉነት መጠባበቅ እንችላለን፤ ምክንያቱም ዳንኤልም ሆነ ዮሐንስ፣ ይሖዋንና ኢየሱስን የሚያገለግሉ ሁሉ በታሪክ ውስጥ ሆኖ ከማያውቀው ከዚህ የጭንቀት ጊዜ እንደሚተርፉ ገልጸዋል። ዳንኤል፣ ስማቸው ‘በመጽሐፍ ላይ የተጻፈ’ ሁሉ ከጥፋቱ እንደሚተርፉ ተናግሯል። ታዲያ ስማችን በዚህ መጽሐፍ ላይ እንዲጻፍ ምን ማድረግ አለብን? የአምላክ በግ በሆነው በኢየሱስ ላይ እምነት እንዳለን በግልጽ ማሳየት ይኖርብናል። (ዮሐ. 1:29) ራሳችንን ለአምላክ መወሰናችንን በጥምቀት ማሳየት አለብን። (1 ጴጥ. 3:21) በተጨማሪም ሌሎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩ ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን በማድረግ የአምላክን መንግሥት እንደምንደግፍ ማሳየት ይኖርብናል። በይሖዋና ታማኝ አገልጋዮቹን ባቀፈው ድርጅቱ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር ያለብን አሁን ነው። የአምላክን መንግሥት መደገፍ ያለብንም አሁን ነው። እንዲህ ማድረጋችን የአምላክ መንግሥት የሰሜኑን ንጉሥና የደቡቡን ንጉሥ በሚያጠፋበት ወቅት ለመዳን ያስችለናል። w20.05 16 አን. 18-19
ሰኞ፣ ሰኔ 6
ይሖዋ ሆይ፣ ስምህ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።—መዝ. 135:13
አዳምና ሔዋን የይሖዋን ስም እንዲሁም ከስሙ ባለቤት ጋር በተያያዘ አስፈላጊ የሆኑ እውነቶችን ያውቁ ነበር። ይሖዋ ፈጣሪያቸውና ሕይወት ሰጪያቸው እንደሆነ እንዲሁም ውብ የሆነች ገነት እና ፍጹም የትዳር ጓደኛ የሰጣቸው እሱ እንደሆነ ያውቁ ነበር። (ዘፍ. 1:26-28፤ 2:18) ይሁንና ፍጹም የሆነ አእምሯቸውን ተጠቅመው ይሖዋ ባደረገላቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰላቸውን ይቀጥሉ ይሆን? የስሙ ባለቤት ለሆነው አካል ያላቸው ፍቅርና አድናቆት እያደገ እንዲሄድስ ጥረት ያደርጉ ይሆን? የአምላክ ጠላት ፈተና ሲያቀርብላቸው የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ግልጽ ሆኗል። ሰይጣን በእባብ በመጠቀም ሔዋንን “በእርግጥ አምላክ ‘በአትክልቱ ስፍራ ካለው ከማንኛውም ዛፍ አትብሉ’ ብሏችኋል?” ሲል ጠየቃት። (ዘፍ. 2:16, 17፤ 3:1) ይህ፣ ስውር የሆነ ውሸት ያዘለ መርዛማ ጥያቄ ነው። አምላክ የተናገረው ከአንዱ ዛፍ በቀር ከማንኛውም ዛፍ መብላት እንደሚችሉ ነው። (ዘፍ. 2:9) ሰይጣን፣ አምላክ ለጋስ እንዳልሆነ ለመግለጽ ሞክሯል። ሔዋን ‘አምላክ ያስቀረብን ነገር ይኖር ይሆን እንዴ?’ የሚል ጥያቄ ተፈጥሮባት ሊሆን ይችላል። w20.06 3-4 አን. 8-9
ማክሰኞ፣ ሰኔ 7
እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ።—ቆላ. 3:13
አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች የእምነት ባልንጀራቸው በተናገረው ወይም ባደረገው ነገር ተጎድተዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ፣ በወንድማችን ወይም በእህታችን ‘ቅር እንድንሰኝ’ የሚያደርገን ነገር ሊያጋጥመን እንደሚችል ጠቁሟል። ሌላው ቀርቶ ፍትሕ የጎደለው ነገር ይፈጸምብን ይሆናል። ካልተጠነቀቅን እንዲህ ያለው ነገር በምሬት እንድንዋጥ ሊያደርገን ይችላል። ምሬት ደግሞ አንድን ሰው ቀስ በቀስ ከይሖዋ ሕዝቦች ሊያርቀው ይችላል። በደቡብ አሜሪካ የሚኖረው ፓብሎ በሐሰት ስለተከሰሰ በጉባኤ ውስጥ የነበረውን የአገልግሎት መብት አጣ። ታዲያ ፓብሎ ምን አደረገ? “በጣም ስለተበሳጨሁ ቀስ በቀስ ከጉባኤው እየራቅሁ ሄድኩ” ብሏል። በሌላ በኩል ደግሞ አንድ ሰው ቀደም ሲል የአምላክን ሕግ በመጣሱ ምክንያት ለረጅም ጊዜ በጥፋተኝነት ስሜት ይሠቃይ ይሆናል፤ ግለሰቡ አምላክ ሊወደው እንደማይችል ይሰማው ይሆናል። ይህ ሰው ንስሐ ገብቶ ምሕረት ቢደረግለትም እንኳ ከአምላክ ሕዝቦች እንደ አንዱ ሊቆጠር እንደማይገባው ሊሰማው ይችላል። እስካሁን የተመለከትናቸው ሁኔታዎች ስላጋጠሟቸው ወንድሞችና እህቶች ምን ይሰማሃል? w20.06 19 አን. 6-7
ረቡዕ፣ ሰኔ 8
ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል።—ምሳሌ 22:3
ጉዳት ሊያደርሱብን የሚችሉ ሁኔታዎችን ለይተን የማወቅ ችሎታ ማዳበር እንዲሁም ከአደጋው ለመጠበቅ እርምጃ መውሰድ ይኖርብናል። (ዕብ. 5:14) ለምሳሌ ያህል፣ የምንዝናናበትን ነገር በጥበብ መምረጥ ያስፈልገናል። የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችና ፊልሞች ብዙውን ጊዜ መጥፎ ሥነ ምግባር የሚንጸባረቅበት ነገር ያቀርባሉ። እንዲህ ያለው ምግባር አምላክን የሚያሳዝን ከመሆኑም ሌላ ውሎ አድሮ ጉዳት ማስከተሉ አይቀርም። ስለዚህ ለአምላክ ያለን ፍቅር ቀስ በቀስ እንዲቀዘቅዝ ከሚያደርግ መዝናኛ መራቃችን የተገባ ነው። (ኤፌ. 5:5, 6) ከሃዲዎች የሚያሰራጩት የሐሰት መረጃ አደገኛ መሆኑን ማስተዋልም አለብን፤ ምክንያቱም በወንድሞቻችንና በይሖዋ ድርጅት ላይ ጥርጣሬ እንዲያድርብን ለማድረግ ይሞክራሉ። (1 ጢሞ. 4:1, 7፤ 2 ጢሞ. 2:16) እንዲህ ያለው የተሳሳተ መረጃ እምነታችንን ሊያዳክመው ይችላል። እንደዚህ ባለው ፕሮፓጋንዳ እንዳንታለል መጠንቀቅ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም እንዲህ ያሉት ወሬዎች የሚሰራጩት “አእምሯቸው በተበላሸና እውነትን መረዳት ባቆሙ ሰዎች” ነው። ዓላማቸውም ‘ጭቅጭቅና ክርክር’ ማስነሳት ነው። (1 ጢሞ. 6:4, 5) የወንድሞቻችንን ስም ለማጥፋት የሚያሰራጩትን ውሸት እንድናምንና እነሱን በጥርጣሬ ዓይን ማየት እንድንጀምር ማድረግ ይፈልጋሉ። w20.09 29 አን. 13, 15
ሐሙስ፣ ሰኔ 9
[የራሳችሁን] ጥቅም ሳይሆን የሌላውን ሰው ጥቅም [ፈልጉ]።—1 ቆሮ. 10:24
ባልና ሚስት እርስ በርስ መዋደድና መከባበር አለባቸው። (ኤፌ. 5:33) መጽሐፍ ቅዱስ ከመቀበል ይልቅ በመስጠት ላይ እንድናተኩር ያበረታታናል። (ሥራ 20:35) ባለትዳሮች አንዳቸው ለሌላው ፍቅርና አክብሮት እንዲያሳዩ የሚረዳቸው የትኛው ባሕርይ ነው? ትሕትና ነው። ትሕትና በርካታ ክርስቲያኖች በትዳራቸው ይበልጥ ደስተኛ እንዲሆኑ ረድቷቸዋል። ለምሳሌ ስቲቨን የተባለ አንድ ባል እንዲህ ብሏል፦ “በተለይ ችግር ሲያጋጥማችሁ እንደ አንድ ቡድን ተባብራችሁ መሥራት ይኖርባችኋል። እንዲህ ካደረጋችሁ ‘ለእኔ የሚበጀኝ ምንድን ነው?’ ብላችሁ ከማሰብ ይልቅ ‘ለእኛ የሚበጀን ምንድን ነው?’ ብላችሁ ታስባላችሁ።” ባለቤቱ ስቴፋኒም ተመሳሳይ ስሜት አላት። እንዲህ ብላለች፦ “ሁሌ እየተጨቃጨቀ መኖር የሚፈልግ ሰው እንደሌለ የታወቀ ነው። ግጭት ሲያጋጥመን የችግሩን መንስኤ ለማወቅ እንሞክራለን። ከዚያም እንጸልያለን፣ ምርምር እናደርጋለን እንዲሁም ስለ መፍትሔው እንነጋገራለን። ከመጣላት ይልቅ ችግሩን በመፍታት ላይ እናተኩራለን።” ባለትዳሮች ከሚገባው በላይ ስለ ራሳቸው በማሰብ ራሳቸውን ከፍ አድርገው የማይመለከቱ ከሆነ በትዳራቸው ደስተኛ ይሆናሉ። w20.07 3-4 አን. 5-6
ዓርብ፣ ሰኔ 10
ከወገኖቼ መካከል በእኔ ዕድሜ ካሉት ከብዙዎቹ የበለጠ በአይሁዳውያን ሃይማኖት የላቀ እድገት እያደረግኩ ነበር።—ገላ. 1:14
ይሖዋን ስናገለግል በራሳችን ብርታት ወይም ችሎታ መመካት የለብንም። ሐዋርያው ጳውሎስ የተማረ ሰው ነበር፤ እንዲያውም ያስተማረው በዘመኑ ከነበሩት እጅግ የተከበሩ የአይሁድ ሃይማኖት መሪዎች አንዱ የሆነው ገማልያል ነው። (ሥራ 5:34፤ 22:3) በአንድ ወቅት ጳውሎስ በአይሁዳውያን መካከል ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ሰው ነበር። (ሥራ 26:4) ሆኖም ጳውሎስ በራሱ አልተመካም። ጳውሎስ ከዓለም እይታ አንጻር ኃያል እንዲመስል የሚያደርጉትን ነገሮች ያለምንም ቅሬታ ትቷል። እንዲያውም እነዚህን ነገሮች “እንደ ቆሻሻ” ቆጥሯቸዋል። (ፊልጵ. 3:8 ግርጌ) ጳውሎስ የክርስቶስ ተከታይ ለመሆን ብዙ መሥዋዕት ከፍሏል። የገዛ ወገኖቹ የሆኑት አይሁዳውያን ጠልተውት ነበር። (ሥራ 23:12-14) የአገሩ ዜጎች የሆኑት ሮማውያን ደብድበው እስር ቤት ወርውረውታል። (ሥራ 16:19-24, 37) በተጨማሪም ጳውሎስ ድክመት እንዳለበት ተገንዝቦ ነበር። (ሮም 7:21-25) ሆኖም ተቃዋሚዎቹም ሆኑ የራሱ ድክመት እንዲያሽመደምደው ከመፍቀድ ይልቅ ‘በድክመት ደስ ተሰኝቷል።’ ለምን? ምክንያቱም የአምላክ ኃይል በሕይወቱ ውስጥ ሲሠራ ማየት የቻለው በደከመበት ወቅት ነው።—2 ቆሮ. 4:7፤ 12:10፤ w20.07 16 አን. 7-8
ቅዳሜ፣ ሰኔ 11
በእኔ የሚያምን ሁሉ . . . ከእነዚህ የበለጡ ሥራዎች ይሠራል።—ዮሐ. 14:12
በዛሬው ጊዜ ለመንግሥቱ የስብከት ሥራ ሙሉ ትኩረት መስጠታችን በጣም አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ ይህ ሥራ እየሰፋ እንደሚሄድና እሱ ከሞተ በኋላም ለረጅም ጊዜ እንደሚቀጥል አስቀድሞ ተናግሯል። ከሞት ከተነሳ በኋላ ደቀ መዛሙርቱን በተአምር ብዙ ዓሣ እንዲይዙ ረዳቸው። ከዚያም ይህን አጋጣሚ በመጠቀም፣ ሰው አጥማጆች የመሆን ሥራቸው ከየትኛውም ሥራ ይበልጥ አስፈላጊ እንደሆነ አስገነዘባቸው። (ዮሐ. 21:15-17) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሊያርግ ሲል ደግሞ እሱ የጀመረው የስብከት ሥራ ከእስራኤል ውጭ ርቀው በሚገኙ ቦታዎችም እንደሚከናወን ለደቀ መዛሙርቱ ነገራቸው። (ሥራ 1:6-8) ከበርካታ ዓመታት በኋላ ኢየሱስ ‘በጌታ ቀን’ ስለሚከናወነው ነገር ለሐዋርያው ዮሐንስ ራእይ አሳይቶት ነበር። ዮሐንስ የሚከተለውን አስደናቂ ክንውን በራእይ አይቷል፦ ‘የዘላለሙ ምሥራች’ በመላእክት አመራር ‘ለብሔር፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለሕዝብ ሁሉ’ ይሰበካል። (ራእይ 1:10፤ 14:6) በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ፈቃድ፣ ይህ ታላቅ የስብከት ሥራ እስኪያበቃ ድረስ በሥራው እንድንካፈል ነው። w20.09 9 አን. 5
እሁድ፣ ሰኔ 12
አብርሃም በተፈተነ ጊዜ ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እስከ ማቅረብ ድረስ እምነት አሳይቷል።—ዕብ. 11:17
አብርሃም በቤተሰብ ሕይወቱ ችግሮች አጋጥመውት ነበር። የሚወዳት ሚስቱ ሣራ፣ ልጅ መውለድ አልቻለችም። ለበርካታ አሥርተ ዓመታት፣ ይህን ስሜት የሚጎዳ ሁኔታ ተቋቁመው መኖር ነበረባቸው። ከጊዜ በኋላ ሣራ፣ አገልጋይዋን አጋርን ለአብርሃም ሰጠችው፤ ይህን ያደረገችው ልጆች እንድትወልድላቸው አስባ ነበር። ይሁንና አጋር፣ እስማኤልን ስትፀንስ ሣራን መናቅ ጀመረች። ሣራ ሁኔታው በጣም ስለከበዳት አጋርን እንድትኮበልል አደረገቻት። (ዘፍ. 16:1-6) በመጨረሻም ሣራ ፀነሰችና ወንድ ልጅ ወለደች፤ አብርሃምም ልጁን ይስሐቅ ብሎ ሰየመው። አብርሃም፣ እስማኤልንም ሆነ ይስሐቅን ይወዳቸው ነበር። ይሁን እንጂ እስማኤል በይስሐቅ ላይ ባደረገበት ነገር የተነሳ አብርሃም እስማኤልንና አጋርን ከቤት ለማስወጣት ተገደደ። (ዘፍ. 21:9-14) በኋላ ላይ ደግሞ ይሖዋ፣ ይስሐቅን መሥዋዕት አድርጎ እንዲያቀርብለት አብርሃምን ጠየቀው። (ዘፍ. 22:1, 2፤ ዕብ. 11:17-19) በሁለቱም ወቅቶች አብርሃም፣ ልጆቹን በተመለከተ ይሖዋ የገባውን ቃል መፈጸሙ እንደማይቀር መተማመን አስፈልጎት ነበር። w20.08 4 አን. 9-10
ሰኞ፣ ሰኔ 13
እንደ አምላክ ፈቃድ የተፈጠረውንና ከእውነተኛ ጽድቅና ታማኝነት ጋር የሚስማማውን አዲሱን ስብዕና [ልበሱ]።—ኤፌ. 4:24
ከሞት የተነሱት ሰዎች አሮጌውን ስብዕና አውልቀው በመጣል በአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች መሠረት መኖር ሲጀምሩ ምን ያህል እንደሚደሰቱ አስበው። እንዲህ ያለ ለውጥ የሚያደርጉ ሁሉ ትንሣኤያቸው የሕይወት ትንሣኤ ይሆናል። በተቃራኒው ግን በአምላክ ላይ የሚያምፁ ሰዎች በገነት ውስጥ የሚኖረውን ሰላም እንዲያደፈርሱ አይፈቀድላቸውም። (ኢሳ. 65:20፤ ዮሐ. 5:28, 29) በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር ሁሉም የአምላክ አገልጋዮች በምሳሌ 10:22 ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እውነተኝነት የማየት አጋጣሚ ያገኛሉ፤ ጥቅሱ “የይሖዋ በረከት ባለጸጋ ታደርጋለች፤ እሱም ከበረከቱ ጋር ሥቃይን አይጨምርም” ይላል። የይሖዋ መንፈስ በእነሱ ላይ ስለሚሠራ የአምላክ ሕዝቦች በመንፈሳዊ ባለጸጋ ይሆናሉ፤ ክርስቶስን ይበልጥ እየመሰሉ የሚሄዱ ከመሆኑም ሌላ ደረጃ በደረጃ ወደ ፍጽምና ይደርሳሉ። (ዮሐ. 13:15-17፤ ኤፌ. 4:23) በየዕለቱ አካላዊ ጥንካሬያቸው እየጨመረና የተሻሉ ሰዎች እየሆኑ ይሄዳሉ። በዚያ ወቅት ሕይወት ምንኛ አስደሳች ይሆናል!—ኢዮብ 33:25፤ w20.08 17 አን. 11-12
ማክሰኞ፣ ሰኔ 14
በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ ላለመግባት . . . ተጣጣሩ።—1 ተሰ. 4:11
አንዳንድ ክርስቲያኖች ያላገቡት፣ በነጠላነት ለመኖር ስለመረጡ መሆኑን ልናስታውስ ይገባል። ሌሎች ደግሞ ማግባት ቢፈልጉም የሚሆናቸው ሰው አላገኙም። የትዳር ጓደኛቸውን በሞት ያጡ ክርስቲያኖችም አሉ። ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ በጉባኤ ውስጥ ያሉ ሌሎች እነዚህን ክርስቲያኖች ያላገቡት ለምን እንደሆነ መጠየቃቸው ተገቢ ነው? ወይም ደግሞ የትዳር ጓደኛ በመፈለግ ሊረዷቸው እንደሚችሉ ቢገልጹ ተገቢ ይሆናል? ሳንጠየቅ እንዲህ ያለ ሐሳብ ማቅረባችን ባላገቡ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ላይ ምን ስሜት ሊፈጥር ይችላል? (1 ጢሞ. 5:13) ያላገቡ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን፣ ነጠላ በመሆናቸው እንደምናዝንላቸው ሳይሆን ያሏቸውን ግሩም ባሕርያት ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ስናሳያቸው ደስ ይላቸዋል። የጎደላቸው ነገር እንዳለ ከማሰብ ይልቅ ታማኝነታቸውን ልናደንቅ ይገባል። እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ያላገቡ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን “አንተ አታስፈልገኝም” እንደምንላቸው አይሰማቸውም። (1 ቆሮ. 12:21) ከዚህ ይልቅ እንደምናከብራቸውና በጉባኤው ውስጥ ያላቸውን ቦታ ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ይሰማቸዋል። w20.08 29 አን. 10, 14
ረቡዕ፣ ሰኔ 15
[ክርስቶስ] በአንድ ጊዜ ከ500 ለሚበልጡ ወንድሞች [ታየ]።—1 ቆሮ. 15:6
ከጊዜ በኋላ ኢየሱስ፣ ለሐዋርያው ጳውሎስ ለራሱ ተገልጦለታል። (1 ቆሮ. 15:8) ጳውሎስ (ሳኦል) ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ ሳለ፣ ከሞት የተነሳውን የኢየሱስን ድምፅ ሰማ፤ እንዲሁም በሰማይ ያለውን ኢየሱስን በራእይ ተመለከተው። (ሥራ 9:3-5) ጳውሎስ ያጋጠመው ነገር፣ ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ የሚያረጋግጥ ተጨማሪ ማስረጃ ነው። (ሥራ 26:12-15) በተለይ የጳውሎስ ምሥክርነት የአንዳንዶችን ትኩረት ስቦ መሆን አለበት፤ ምክንያቱም ጳውሎስ በአንድ ወቅት ክርስቲያኖችን ያሳድድ ነበር። ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን አምኖ ከተቀበለ በኋላ ግን ሌሎችም ይህን እንዲያምኑ ለመርዳት በትጋት ሠርቷል። ስለ ኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ የሚገልጸውን እውነት በሚሰብክበት ወቅት ተደብድቧል፣ ታስሯል እንዲሁም የመርከብ መሰበር አደጋ አጋጥሞታል። (1 ቆሮ. 15:9-11፤ 2 ቆሮ. 11:23-27) ጳውሎስ፣ ኢየሱስ ከሞት መነሳቱን እርግጠኛ ከመሆኑ የተነሳ ስለዚህ ጉዳይ ለመስበክ ሲል ለመሞት እንኳ ፈቃደኛ ነበር። የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የሰጡት ይህ ምሥክርነት ኢየሱስ ከሞት እንደተነሳ እርግጠኛ እንድትሆን አያደርግህም? በትንሣኤ ላይ ያለህን እምነትስ አያጠናክረውም? w20.12 3 አን. 8-10
ሐሙስ፣ ሰኔ 16
[ይሖዋን] ብትፈልጉት ይገኝላችኋል።—2 ዜና 15:2
‘በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትሬ እገኛለሁ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቅ እንችላለን። የይሖዋ ድርጅት ባዘጋጃቸው ስብሰባዎች ላይ ስንገኝ እረፍት የሚሰጥ መንፈሳዊ ትምህርት እንዲሁም የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን ማበረታቻ እናገኛለን። (ማቴ. 11:28) በተጨማሪም ‘መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትሬ የማጥናት ልማድ አለኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው። የምትኖረው ከቤተሰብህ ጋር ከሆነ በየሳምንቱ የቤተሰብ አምልኮ ለማድረግ ጊዜ መድባችኋል? የምትኖረው ብቻህን ከሆነ ደግሞ ቤተሰቦች በየሳምንቱ እንደሚያደርጉት የምታጠናበት ጊዜ መድበሃል? በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ አቅምህ በፈቀደው መጠን የተሟላ ተሳትፎ እያደረግክ ነው? ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ ያለብን ለምንድን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ፣ ይሖዋ ሐሳባችንን እና በልባችን ውስጥ ያለውን ነገር እንደሚመረምር ይገልጻል፤ እኛም እንዲህ ማድረግ ይኖርብናል። (1 ዜና 28:9) ግባችንን፣ አስተሳሰባችንን ወይም አመለካከታችንን ማስተካከል እንዳለብን የሚጠቁም ነገር ካስተዋልን እነዚህን ለውጦች ለማድረግ እንዲረዳን ይሖዋን እንለምነው። ወደፊት ለሚመጡት ፈተናዎች ራሳችንን የምናዘጋጅበት ጊዜ አሁን ነው። w20.09 19 አን. 19-20
ዓርብ፣ ሰኔ 17
ከእናንተ መካከል ያለውን ንብረት ሁሉ የማይሰናበት ፈጽሞ ደቀ መዝሙሬ ሊሆን አይችልም።—ሉቃስ 14:33
በአንድ ወቅት ኢየሱስ፣ የእሱ ደቀ መዝሙር መሆን ምን እንደሚጠይቅ በምሳሌ አስረድቶ ነበር። ግንብ ለመገንባት ስለፈለገ ሰው እንዲሁም ወደ ጦርነት ለመዝመት ስላሰበ ንጉሥ ተናግሮ ነበር። ግንብ ለመገንባት የፈለገው ሰው ግንባታውን መጨረስ ይችል እንደሆነ ‘በመጀመሪያ ተቀምጦ ወጪውን ማስላት’ እንዳለበት ኢየሱስ ተናገረ፤ ንጉሡም ቢሆን ሠራዊቱ ድል ማድረግ ይችል እንደሆነ ለማወቅ ‘በቅድሚያ ተቀምጦ መማከር’ እንዳለበት ኢየሱስ ገልጿል። (ሉቃስ 14:27-32) በተመሳሳይም የኢየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን የሚፈልግ ሰው ሁሉ፣ ይህ ውሳኔ ምን እንደሚጠይቅበት በጥንቃቄ መመርመር አለበት። ጥናታችን፣ ደቀ መዝሙር መሆን ምን እንደሚጠይቅ መገንዘብ እንዲችል በየሳምንቱ አብሮን እንዲያጠና ልናበረታታው ይገባል። የመጽሐፍ ቅዱስ አስጠኚው ለእያንዳንዱ የጥናት ክፍለ ጊዜ በሚገባ መዘጋጀት ይኖርበታል። ጥናትህን በአእምሮህ ይዘህ ትምህርቱን ቀላል እና ግልጽ በሆነ መንገድ ማቅረብ የምትችለው እንዴት እንደሆነ አሰላስል፤ ጥናትህ ትምህርቱን መረዳትና ተግባራዊ ማድረግ የሚችለው እንዲህ ካደረግህ ነው።—ነህ. 8:8፤ ምሳሌ 15:28ሀ፤ w20.10 7 አን. 5፤ 8 አን. 7
ቅዳሜ፣ ሰኔ 18
ስለዚህ ሂዱና . . . ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።—ማቴ. 28:19, 20
ኢየሱስ የሰጠው መመሪያ ግልጽ ነው። እሱ ያዘዘውን ነገር ለሰዎች ማስተማር አለብን። ሆኖም ኢየሱስ በሰጠው ትእዛዝ ላይ ልብ ልንለው የሚገባ አንድ አስፈላጊ ነጥብ አለ። ኢየሱስ ‘ያዘዝኳችሁንም ሁሉ አስተምሯቸው’ አላለም። ከዚህ ይልቅ “ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ [አስተምሯቸው]” ብሏል። ይህን መመሪያ ለመታዘዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችንን ማስተማር ብቻ ሳይሆን መምራትም ይኖርብናል። (ሥራ 8:31) ሰዎችን መጽሐፍ ቅዱስ ስናስጠና አምላክ ምን እንደሚጠብቅብን እናስተምራቸዋለን። ይሁን እንጂ ሌላም ማድረግ የሚኖርብን ነገር አለ። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችን የተማሩትን ነገር በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ተግባራዊ እንዲያደርጉ ማስተማር ይኖርብናል። (ዮሐ. 14:15፤ 1 ዮሐ. 2:3) ጥናቶቻችን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶችን በትምህርት ቤት፣ በሥራ ቦታ ወይም በሚዝናኑበት ወቅት እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደሚችሉ ምሳሌ ሆነን እናሳያቸው። ጥናቶቻችን ባሉበት ስንጸልይ ይሖዋ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት እንዲመራቸው እንለምን።—ዮሐ. 16:13፤ w20.11 2-3 አን. 3-5
እሁድ፣ ሰኔ 19
“በመንፈሴ እንጂ፣ በወታደራዊ ኃይል ወይም በጉልበት አይደለም” ይላል የሠራዊት ጌታ ይሖዋ።—ዘካ. 4:6
የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ የቅዱሳን መጻሕፍትን ቅጂዎች እንደ ልብ ማግኘት አይችሉም ነበር። ዛሬ ያሉንን ዓይነት መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የሚረዱ መሣሪያዎች አልነበሯቸውም። በተጨማሪም ደቀ መዛሙርቱ የተለያዩ ቋንቋዎች ለሚናገሩ ሰዎች መስበክ ነበረባቸው። እነዚህ ሁሉ ተፈታታኝ ሁኔታዎች ቢኖሩባቸውም እነዚያ ቀናተኛ ደቀ መዛሙርት ፈጽሞ የማይቻል የሚመስለውን ነገር ማከናወን ችለዋል፤ በጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ምሥራቹን “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ” ሰብከዋል። (ቆላ. 1:6, 23) በዘመናችንም ይሖዋ ለሕዝቡ መመሪያና ብርታት መስጠቱን ቀጥሏል። በዋነኝነት መመሪያ የሚሰጠው በመንፈስ መሪነት በተጻፈው በቃሉ አማካኝነት ነው። በአምላክ ቃል ውስጥ ስለ ኢየሱስ አገልግሎት የሚገልጸውን ዘገባና ኢየሱስ ተከታዮቹ እሱ የጀመረውን ሥራ እንዲቀጥሉ የሰጠውን ትእዛዝ እናገኛለን። (ማቴ. 28:19, 20) ይሖዋ አያዳላም፤ ምሥራቹ “በምድር ላይ ለሚኖር ብሔር፣ ነገድ፣ ቋንቋና ሕዝብ ሁሉ” እንደሚሰበክ አስቀድሞ ተናግሯል። (ራእይ 14:6, 7) ሁሉም ሰው የመንግሥቱን መልእክት የሚሰማበት አጋጣሚ እንዲያገኝ ይፈልጋል። w20.10 21 አን. 6-8
ሰኞ፣ ሰኔ 20
ትሑት የሆኑትን ታድናለህና፤ ዓይኖችህ ግን በትዕቢተኞች ላይ ናቸው።—2 ሳሙ. 22:28
ንጉሥ ዳዊት ‘የይሖዋን ሕግ’ የሚወድ ሰው ነበር። (መዝ. 1:1-3) ይሖዋ ትሑታንን እንደሚያድን፣ ትዕቢተኞችን ግን እንደሚቃወም ዳዊት ያውቅ ነበር። ስለዚህ ዳዊት የአምላክ ሕግ አስተሳሰቡን እንዲያስተካክልለት ፈቅዷል። እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “ምክር የሰጠኝን ይሖዋን አወድሳለሁ። በሌሊትም እንኳ በውስጤ ያለው ሐሳብ ያርመኛል።” (መዝ. 16:7) ትሑት ከሆንን በውስጣችን ያሉ የተሳሳቱ ሐሳቦች ወደ መጥፎ ድርጊት ከማምራታቸው በፊት የአምላክ ቃል አስተሳሰባችንን እንዲያስተካክለው እንፈቅዳለን። የአምላክ ቃል “መንገዱ ይህ ነው። በእሱ ሂድ” በማለት የሚመራን ድምፅ ይሆንልናል። መንገዳችንን ስተን ወደ ቀኝ ወይም ወደ ግራ ስንወጣ ማስጠንቀቂያ ይሰጠናል። (ኢሳ. 30:21) ይሖዋን መስማታችን በብዙ መንገዶች ይጠቅመናል። (ኢሳ. 48:17) ለምሳሌ፣ አንድ ሰው መጥቶ እርማት ሲሰጠን ከሚሰማን የኀፍረት ስሜት ያድነናል። በተጨማሪም ይሖዋ እንደሚወደው ልጁ እንደቆጠረን ስለምንገነዘብ ወደ እሱ ይበልጥ እንቀርባለን።—ዕብ. 12:7፤ w20.11 20 አን. 6-7
ማክሰኞ፣ ሰኔ 21
ስለ ሙታን ትንሣኤ በሰሙ ጊዜ አንዳንዶቹ ያሾፉበት ጀመር።—ሥራ 17:32
ይህ አስተሳሰብ በቆሮንቶስ ባሉ አንዳንድ ክርስቲያኖች ላይ ተጽዕኖ አሳድሮ ሊሆን ይችላል። (1 ቆሮ. 15:12) ሌሎች ደግሞ የትንሣኤ ትምህርት ምሳሌያዊ እንደሆነ አስበው ሊሆን ይችላል፤ በእነሱ አመለካከት አንድ ሰው ክርስቲያን ከመሆኑ በፊት በኃጢአቱ ምክንያት እንደ “ሞተ” ይቆጠር ነበር፤ ክርስቲያን ሲሆን ግን “ሕያው” ሆኗል። እነዚህ ክርስቲያኖች ምክንያታቸው ምንም ይሁን ምን፣ የትንሣኤን ትምህርት ካልተቀበሉ እምነታቸው ከንቱ ነው። አምላክ ኢየሱስን ከሞት ካላስነሳው፣ ቤዛው አልተከፈለም እንዲሁም ማንም ሰው ከኃጢአቱ ይቅርታ አያገኝም ማለት ነው። ከዚህ አንጻር የትንሣኤን ትምህርት መቀበል የማይፈልጉ ሰዎች እርግጠኛ የሆነ ተስፋ ሊኖራቸው አይችልም። (1 ቆሮ. 15:13-19፤ ዕብ. 9:12, 14) ሐዋርያው ጳውሎስ ‘ክርስቶስ ከሞት እንደተነሳ’ በእርግጠኝነት ያውቅ ነበር። የኢየሱስ ትንሣኤ ከዚያ ቀደም ከተከናወኑት ትንሣኤዎች የላቀ ነበር፤ ምክንያቱም ከሞት የተነሱት ሌሎቹ ሰዎች በድጋሚ ሞተዋል። ኢየሱስ “በሞት ካንቀላፉት በኩራት ሆኖ” ከሞት እንደተነሳ ጳውሎስ ተናግሯል። መንፈሳዊ አካል ይዞ ከሞት ለመነሳትም ሆነ ከሞት ከተነሳ በኋላ ወደ ሰማይ ለመሄድ የመጀመሪያው ሰው እሱ ነው።—1 ቆሮ. 15:20፤ ሥራ 26:23፤ 1 ጴጥ. 3:18, 22፤ w20.12 5 አን. 11-12
ረቡዕ፣ ሰኔ 22
ሐዋርያትና ሽማግሌዎች ያስተላለፏቸውን ውሳኔዎች እንዲጠብቁ ጉዳዩን ያሳውቋቸው ነበር።—ሥራ 16:4
በመጀመሪያው መቶ ዘመን በኢየሩሳሌም የነበረው የበላይ አካል በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሥርዓትና ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ አንድ ሆኖ ይሠራ ነበር። (ሥራ 2:42) ለምሳሌ ያህል፣ በ49 ዓ.ም. ገደማ ከግርዘት ጋር በተያያዘ ጥያቄ በተነሳበት ወቅት የበላይ አካሉ በመንፈስ ተመርቶ ጉዳዩን ተመልክቶት ነበር። ጉባኤው በዚህ ጉዳይ የተነሳ እንደተከፋፈለ ቢቀጥል ኖሮ የስብከቱ ሥራ ይስተጓጎል ነበር። ሐዋርያቱና ሽማግሌዎቹ አይሁዳዊ ቢሆኑም የአይሁድ ወግ ወይም ይህን አመለካከት የሚያራምዱ ሰዎች ተጽዕኖ እንዲያደርጉባቸው አልፈቀዱም። ከዚህ ይልቅ የአምላክን ቃልና የመንፈሱን አመራር ለማግኘት ጥረት አድርገዋል። (ሥራ 15:1, 2, 5-20, 28) ታዲያ ምን ውጤት ተገኘ? ይሖዋ ውሳኔያቸውን ባርኮታል፣ ሰላምና አንድነት ሰፍኗል እንዲሁም የስብከቱ ሥራ ይበልጥ መስፋፋቱን ቀጥሏል። (ሥራ 15:30, 31፤ 16:5) በዘመናችንም የይሖዋ ድርጅት በአምላክ ሕዝቦች መካከል ሥርዓትና ሰላም እንዲሰፍን አድርጓል። w20.10 22-23 አን. 11-12
ሐሙስ፣ ሰኔ 23
አምላክ የመረጠው [ልጄ ሰለሞንን] ነው።—1 ዜና 29:1
በዕድሜያችን፣ በጤንነታችን ወይም በሌሎች ምክንያቶች የተነሳ አንድን ቲኦክራሲያዊ ኃላፊነት ማግኘት አንችል ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ካጋጠመን ከንጉሥ ዳዊት ግሩም ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ዳዊት የአምላክን ቤተ መቅደስ ለመገንባት በጣም ጓጉቶ ነበር። ሆኖም ቤተ መቅደሱን ለመገንባት እንዳልተመረጠ በተነገረው ጊዜ ይሖዋ ለዚህ ኃላፊነት ለመረጠው ሰው ሙሉ ድጋፉን ሰጥቷል። እንዲያውም ዳዊት ለሥራው ከፍተኛ መዋጮ አድርጓል። ዳዊት እንዴት ያለ ግሩም አርዓያ ትቶልናል! (2 ሳሙ. 7:12, 13፤ 1 ዜና 29:3-5) ሂዩግ የተባለ በፈረንሳይ የሚኖር አንድ ወንድም በነበረበት የጤና እክል የተነሳ በሽምግልና ማገልገሉን አቆመ፤ ያደረበት ሕመም ቀላል የቤት ውስጥ ሥራዎችን እንኳ እንዳያከናውን እንቅፋት ሆኖበት ነበር። እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “መጀመሪያ አካባቢ በጣም ተስፋ ቆርጬ ነበር፤ እንዲሁም የዋጋ ቢስነት ስሜት አድሮብኝ ነበር። ውሎ አድሮ ግን ያለብኝን የአቅም ገደብ አምኜ መቀበል ያለውን ጥቅም ተገነዘብኩ። በመሆኑም ሁኔታዬ በሚፈቅድልኝ መጠን ይሖዋን በማገልገል ደስታ ማግኘት ችያለሁ። ቢደክማቸውም እንኳ መዋጋታቸውን እንደቀጠሉት እንደ ጌዴዎንና ሦስት መቶዎቹ ሰዎች መታገሌን እቀጥላለሁ!”—መሳ. 8:4፤ w20.12 25 አን. 14-15
ዓርብ፣ ሰኔ 24
እርስ በርስ [መዋደዳችሁን ቀጥሉ]።—1 ዮሐ. 4:7
ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ሕይወት በጻፈው ዘገባ ላይ ሦስቱ የወንጌል ጸሐፊዎች በድምሩ ከጻፉት የበለጠ ስለ ፍቅር በተደጋጋሚ ጠቅሷል። በመንፈስ መሪነት የጻፋቸው መጻሕፍት አንድ ክርስቲያን ማንኛውንም ነገር በፍቅር ማድረግ እንዳለበት ይጠቁማሉ። (1 ዮሐ. 4:10, 11) ዮሐንስ ግን ይህን ለመማር ጊዜ ወስዶበታል። ዮሐንስ ወጣት ሳለ ፍቅር ያላሳየባቸው ጊዜያት ነበሩ። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ወቅት ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ሰማርያን አቋርጠው ወደ ኢየሩሳሌም እየተጓዙ ነበር። የአንዲት የሳምራውያን መንደር ነዋሪዎች ግን በእንግድነት ሊቀበሏቸው ፈቃደኞች አልሆኑም። ዮሐንስ እሳት ከሰማይ ወርዶ የመንደሯን ነዋሪዎች እንዲያጠፋቸው ለማዘዝ ጥያቄ አቀረበ! (ሉቃስ 9:52-56) በሌላ ጊዜ ደግሞ የዮሐንስ እና የያዕቆብ እናት፣ ኢየሱስ በመንግሥቱ ትልቅ ቦታ ለልጆቿ እንዲሰጣቸው ጥያቄ አቅርባ ነበር፤ እናታቸው ይህን ጥያቄ እንድትጠይቅ የገፋፏት እነሱ ራሳቸው ሳይሆኑ አይቀሩም። ሌሎቹ ሐዋርያት፣ ያዕቆብና ዮሐንስ ያደረጉትን ሲያውቁ በጣም ተቆጡ! (ማቴ. 20:20, 21, 24) ዮሐንስ እነዚህ ሁሉ ድክመቶች ቢኖሩበትም ኢየሱስ ይወደው ነበር።—ዮሐ. 21:7፤ w21.01 8-9 አን. 3-4
ቅዳሜ፣ ሰኔ 25
ክርስቶስ . . . ራሱን አላስደሰተም።—ሮም 15:3
ይሖዋ የሚያደርጋቸው ውሳኔዎች ሌሎችን የሚጠቅሙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ ሕይወት ለመፍጠር የተነሳሳው ራሱን ለመጥቀም ሳይሆን ሌሎችም ሕይወት የሚያስገኘውን ደስታ እንዲቀምሱ ሲል ነው። ለኃጢአታችን ሲል ልጁን የሰጠውም ማንም አስገድዶት አይደለም። ለእኛ ጥቅም ሲል እንዲህ ያለውን መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ሆኗል። ኢየሱስ ያደረጋቸው ውሳኔዎችም በዋነኝነት የሌሎችን ጥቅም የሚያስቀድሙ ናቸው። ለምሳሌ ያህል፣ የተሰበሰበውን ሕዝብ ለማስተማር ሲል እረፍት የሚያደርግበትን ጊዜ መሥዋዕት አድርጓል። (ማር. 6:31-34) አንድ የቤተሰብ ራስ ካሉበት ከባድ ኃላፊነቶች አንዱ ቤተሰቡን የሚጠቅም ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ማድረግ እንደሆነ ይረዳል፤ ይህን ኃላፊነቱንም በቁም ነገር ይመለከተዋል። ስለዚህ ሳያስብበት ወይም በስሜት ተነሳስቶ ውሳኔ ከማድረግ ይቆጠባል። ከዚህ ይልቅ ይሖዋ እንዲያሠለጥነው ይፈቅዳል። (ምሳሌ 2:6, 7) በዚህ መንገድ ስለ ራሱ ሳይሆን ስለ ሌሎች ጥቅም እንደሚያስብ ያሳያል። (ፊልጵ. 2:4) አንድ ባል የይሖዋንና የኢየሱስን ምሳሌ ለመከተል ጥረት የሚያደርግ ከሆነ ጥሩ የቤተሰብ ራስ መሆን ይችላል። w21.02 7 አን. 19-21
እሁድ፣ ሰኔ 26
አሳ በአምላኩ በይሖዋ ፊት መልካምና ትክክል የሆነውን ነገር አደረገ።—2 ዜና 14:2
ንጉሥ አሳ በወጣትነቱ ትሑትና ደፋር ነበር። ለምሳሌ በአባቱ በአቢያህ ምትክ ሲነግሥ የጣዖት አምልኮን ለማጥፋት እርምጃ ወስዶ ነበር። በተጨማሪም “የይሁዳ ሰዎች የአባቶቻቸውን አምላክ ይሖዋን እንዲፈልጉ እንዲሁም ሕጉንና ትእዛዙን እንዲያከብሩ” አዟል። (2 ዜና 14:1-7) ኢትዮጵያዊው ዛራ 1,000,000 ወታደሮችን አስከትሎ በይሁዳ ላይ በዘመተበት ጊዜ አሳ የይሖዋን እርዳታ በመጠየቅ የጥበብ እርምጃ ወስዷል። እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ ሆይ፣ የምትረዳው ሕዝብ ብዛት ያለውም ይሁን ደካማ ለአንተ የሚያመጣው ለውጥ የለም። ይሖዋ አምላካችን ሆይ፣ እርዳን፤ በአንተ ታምነናልና።” ይህ ጸሎት አሳ፣ ይሖዋ እሱንም ሆነ ሕዝቡን የማዳን ችሎታ እንዳለው ምን ያህል እንደተማመነ የሚያሳይ ነው። አሳ በሰማይ በሚኖረው አባቱ ተማምኖ ነበር፤ ይሖዋም ‘ኢትዮጵያውያኑን ድል አደረጋቸው።’ (2 ዜና 14:8-12) አንድ ሚሊዮን ወታደሮችን ያቀፈ ሠራዊት መጋፈጥ በጣም አስፈሪ እንደሆነ ምንም ጥርጥር የለውም፤ ሆኖም አሳ በይሖዋ በመታመኑ ድል አድርጓቸዋል። w21.03 5 አን. 12-13
ሰኞ፣ ሰኔ 27
እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ።—ሮም 12:10
መጽሐፍ ቅዱስ ልባዊ ፍቅር ስላሳዩ ፍጹም ያልሆኑ ሰዎች የሚገልጹ ታሪኮችን ይዟል። ዮናታንንና ዳዊትን እንደ ምሳሌ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ “ዮናታንና ዳዊት የጠበቀ ወዳጅነት መሠረቱ፤ ዮናታንም እንደ ራሱ ወደደው” ይላል። (1 ሳሙ. 18:1) ዳዊት በሳኦል ምትክ እንዲነግሥ ተቀብቶ ነበር። ከጊዜ በኋላ ሳኦል በዳዊት ስለቀና ሊገድለው ፈለገ። የሳኦል ልጅ የሆነው ዮናታን ግን አባቱ ዳዊትን ለመግደል በከፈተው ዘመቻ ተባባሪ መሆን አልፈለገም። ዮናታንና ዳዊት ወዳጅነታቸውን ጠብቀው ለመኖርና ምንጊዜም እርስ በርስ ለመደጋገፍ ቃል ተጋብተው ነበር። (1 ሳሙ. 20:42) ዮናታንና ዳዊት ጓደኛሞች እንዳይሆኑ እንቅፋት ሊሆኑባቸው የሚችሉ ነገሮችን ስናስብ እንዲህ ያለ ወዳጅነት መመሥረታቸው ይበልጥ ያስገርመናል። ለምሳሌ ያህል፣ ዮናታን ዳዊትን 30 ዓመት ገደማ ይበልጠው ነበር። ዮናታን በዕድሜም ሆነ በተሞክሮ በጣም ከሚያንሰው ከዚህ ወጣት ጋር ምንም የጋራ ነገር እንደሌላቸው ሊያስብ ይችል ነበር። ያም ቢሆን ዮናታን ዳዊትን ዝቅ አድርጎ አልተመለከተውም። w21.01 21-22 አን. 6-7
ማክሰኞ፣ ሰኔ 28
ወንድሞቼ ሆይ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት።—ያዕ. 1:2
ኢየሱስ ተከታዮቹ እውነተኛ ደስታ እንደሚያገኙ ቃል ገብቷል። ይሁንና የሚወዱት ሰዎች ፈተናዎች እንደሚደርሱባቸውም አስጠንቅቋል። (ማቴ. 10:22, 23፤ ሉቃስ 6:20-23) የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት መሆናችን ደስታ ያስገኝልናል። ሆኖም የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ስንሆን ከቤተሰብ ተቃውሞ ሊያጋጥመን፣ መንግሥታት ስደት ሊያደርሱብን አሊያም አብረውን የሚሠሩ ወይም የሚማሩ ሰዎች ትክክል ያልሆነ ነገር እንድናደርግ ጫና ሊያሳድሩብን ይችላሉ፤ ታዲያ እነዚህ ፈተናዎች ሊደርሱብን እንደሚችሉ ስናውቅ ምን ይሰማናል? ስለ እነዚህ ፈተናዎች ስናስብ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ብንጨነቅ የሚያስገርም አይደለም። ማንም ሰው ቢሆን ስደት ደስታ ያስገኛል ብሎ ላያስብ ይችላል። የአምላክ ቃል ግን ስለ ስደት እንዲህ ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን ይነግረናል። ለምሳሌ ያህል፣ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ፈተና ሲደርስብን በጭንቀት ከመዋጥ ይልቅ እንደ ደስታ እንድንቆጥረው ነግሮናል። (ያዕ. 1:2, 12) ኢየሱስም ቢሆን ስደት ሲደርስብን ልንደሰት እንደሚገባ ተናግሯል። (ማቴ. 5:11) ክርስቲያኖች ፈተናዎች ቢደርሱባቸውም በደስታ መጽናት እንዲችሉ የሚረዷቸውን ጠቃሚ ምክሮች እንዲጽፍ ይሖዋ ያዕቆብን በመንፈሱ መርቶታል። w21.02 26 አን. 1-2፤ 27 አን. 5
ረቡዕ፣ ሰኔ 29
ቅዱስ የሆነውን ነገር ከሚጻረሩ ከንቱ ንግግሮች [ራቅ]።—1 ጢሞ. 6:20
በጢሞቴዎስ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ከአምላክ ጋር የመሥራት መብታቸውን ሳያደንቁ ቀርተዋል። ከእነዚህም መካከል ዴማስ፣ ፊጌሎስ፣ ሄርሞጌኔስ፣ ሄሜኔዎስ፣ እስክንድርና ፊሊጦስ ይገኙበታል። (1 ጢሞ. 1:19, 20፤ 2 ጢሞ. 1:15፤ 2:16-18፤ 4:10) ከሁኔታዎች መረዳት እንደሚቻለው ሁሉም በአንድ ወቅት በመንፈሳዊ ጠንካራ ነበሩ፤ በኋላ ላይ ግን ውድ ለሆኑ ነገሮች የነበራቸውን አድናቆት አጥተዋል። ሰይጣን፣ ይሖዋ በአደራ የሰጠንን ውድ ነገሮች እንድንተው ለማድረግ የሚሞክረው እንዴት ነው? ይህን የሚያደርግባቸውን አንዳንድ ዘዴዎች እስቲ እንመልከት። ሰይጣን የያዝነውን እውነት ቀስ በቀስ እንድንለቅ ሊያደርጉን የሚችሉ የሥነ ምግባር እሴቶችን፣ አመለካከቶችንና ባሕርያትን በመዝናኛው ዓለም እና በመገናኛ ብዙኃን አማካኝነት ያስፋፋል። በእኩዮች ተጽዕኖ ወይም በስደት ተሸብረን መስበካችንን እንድናቆም ለማድረግ ይሞክራል። በተጨማሪም “በውሸት ‘እውቀት’ ተብለው [በሚጠሩ]” የከሃዲዎች ትምህርቶች ተማርከን ከእውነት እንድንወጣ ለማድረግ ይጥራል። ጠንቃቃ ካልሆንን የያዝነውን እውነት ቀስ በቀስ ልንለቀው እንችላለን።—1 ጢሞ. 6: 21፤ w20.09 27 አን. 6-8
ሐሙስ፣ ሰኔ 30
ይሖዋ ሞገስ እንዲያሳየኝ የማቀርበውን ልመና ይሰማል፤ ይሖዋ ጸሎቴን ይቀበላል።—መዝ. 6:9
ጓደኛህ ወይም የቤተሰብህ አባል በሆነ መንገድ ጎድቶሃል? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ ስለ ንጉሥ ዳዊት እና ስለ ልጁ ስለ አቢሴሎም የሚገልጸውን ታሪክ መመርመርህ ሊጠቅምህ ይችላል። (2 ሳሙ. 15:5-14, 31፤ 18:6-14) ዘገባውን በአእምሮህ ይዘህ፣ የደረሰብህ በደል ምን ስሜት እንደፈጠረብህ ለይሖዋ ንገረው። (መዝ. 6:6-8) ቀጥሎ ደግሞ ዳዊት ይሄ ሁሉ ነገር ሲደርስበት ምን ተሰምቶት ሊሆን እንደሚችል በዓይነ ሕሊናህ ሣል። ዳዊት አቢሴሎምን ይወደው፣ አኪጦፌልንም ያምነው ነበር። የሚያሳዝነው ግን ሁለቱም ሰዎች ከዱት። ስሜቱን በጥልቅ መጉዳታቸው ሳያንስ ሊገድሉት ሞክረዋል። ይህ ሁኔታ ዳዊት፣ ሌሎቹ ወዳጆቹም ከአቢሴሎም ጋር እንደተባበሩ በማሰብ በእነሱ ላይ እምነት እንዲያጣ ሊያደርገው ይችል ነበር። አሊያም ደግሞ የራሱን ሕይወት ብቻ ለማትረፍ በማሰብ ብቻውን አገር ጥሎ ለመሸሽ ሊወስን ይችል ነበር። ወይም ደግሞ ተስፋ ቆርጦ ሁሉን ነገር እርግፍ አድርጎ ሊተወው ይችል ነበር። ከዚህ ይልቅ ዳዊት፣ ይሖዋ እንዲረዳው ጸልዮአል። የወዳጆቹንም እርዳታ ጠይቋል። በተጨማሪም ከውሳኔው ጋር የሚስማማ እርምጃ ወዲያውኑ ወስዷል። በይሖዋ መተማመኑን ቀጥሏል፤ በወዳጆቹም ላይ እምነት አላጣም። w21.03 15 አን. 7-8፤ 17 አን. 10-11