ሐምሌ
ዓርብ፣ ሐምሌ 1
ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል።—ማቴ. 28:18
ጸሎታችን መልስ የሚያገኘው የኢየሱስ ወዳጆች ከሆንን ብቻ ነው። በመሆኑም በጸሎታችን ላይ ለደንቡ ያህል “በኢየሱስ ስም” ከማለት ያለፈ ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል። ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ ለመስጠት ኢየሱስን የሚጠቀመው እንዴት እንደሆነ መገንዘብ ይኖርብናል። ኢየሱስ ለሐዋርያቱ “በስሜ የምትለምኑትን ሁሉ አደርገዋለሁ” ብሏቸዋል። (ዮሐ. 14:13) ጸሎታችንን የሚሰማውና ለጸሎታችን መልስ የሚሰጠን ይሖዋ ቢሆንም የእሱን ፈቃድ እንዲያስፈጽም ለኢየሱስ ሥልጣን ሰጥቶታል። ከዚህም ሌላ ይሖዋ ለጸሎታችን መልስ ከመስጠቱ በፊት ኢየሱስ የሰጠውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ አለማድረጋችንን ይመለከታል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፦ “የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላችሁ በሰማይ ያለው አባታችሁ ይቅር ይላችኋል፤ እናንተ ግን የበደሏችሁን ሰዎች ይቅር ካላላችሁ አባታችሁም በደላችሁን ይቅር አይላችሁም።” (ማቴ. 6:14, 15) ይሖዋና ኢየሱስ እኛን በደግነት እንደሚይዙን ሁሉ እኛም ሌሎችን በደግነት መያዛችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! w20.04 22 አን. 6
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 2
ምሥራቹን እያወጅንላችሁ ያለነው . . . እነዚህን ከንቱ ነገሮች ትታችሁ . . . ሕያው [የሆነውን] አምላክ እንድታመልኩ ነው።—ሥራ 14:15
ሐዋርያው ጳውሎስ የአድማጮቹን ትኩረት የሚስበውን ነገር ካስተዋለ በኋላ የሚሰብክበትን መንገድ እንደ ሁኔታው ለማስተካከል ጥረት ያደርግ ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ በልስጥራ የመሠከረላቸው ሰዎች ስለ ቅዱሳን መጻሕፍት ቢያውቁ እንኳ እውቀታቸው በጣም ውስን ነበር። በመሆኑም ጳውሎስ እነሱን ለማሳመን የተጠቀመባቸው ነጥቦች ሰዎቹ በሚያውቋቸው ነገሮች ላይ የተመሠረቱ ነበሩ። ለምሳሌ፣ ፍሬያማ ምርት ስለ ማግኘትና ደስተኛ ስለ መሆን ተናግሯል። የተጠቀመባቸው ቃላትና ምሳሌዎች አድማጮቹ በቀላሉ ሊረዷቸው የሚችሉ ነበሩ። በክልላችሁ ያሉ ሰዎችን ትኩረት የሚስበውን ነገር ለማስተዋልና አቀራረባችሁን እንደ ሁኔታው ለማስተካከል ጥረት አድርጉ። ታዲያ አንድን ሰው ከማነጋገራችሁ ወይም አንድን ቤት ከማንኳኳታችሁ በፊት የግለሰቡን ትኩረት የሚስበው ምን እንደሆነ ማወቅ የምትችሉት እንዴት ነው? አስተዋይ ሁኑ። ግለሰቡ አትክልት እየተንከባከበ፣ መጽሐፍ እያነበበ፣ መኪና እየጠገነ ወይም ሌላ ሥራ እየሠራ ሊሆን ይችላል። ታዲያ በሚሠራው ነገር ላይ ተመሥርታችሁ ውይይት መጀመር ትችሉ ይሆን? (ዮሐ. 4:7) ግለሰቡ የለበሰው ልብስ እንኳ ስለ እሱ ለምሳሌ ስለ አገሩ፣ ስለ ሥራው ወይም ስለሚወደው የስፖርት ቡድን የሚጠቁመው ነገር ሊኖር ይችላል። w20.04 11 አን. 11-12
እሁድ፣ ሐምሌ 3
የሚያስጨንቃችሁን . . . ነገር ሁሉ [በአምላክ] ላይ ጣሉ፤ ምክንያቱም እሱ ስለ እናንተ ያስባል።—1 ጴጥ. 5:7
አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ባጋጠማቸው የስሜት ቀውስ የተነሳ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው ከሰዎች ጋር መሆን በጣም ሊያስጨንቃቸውና ሊያስፈራቸው ይችላል። እነዚህ ክርስቲያኖች ብዙ ሰው ባለበት ቦታ መገኘት ቢከብዳቸውም በጉባኤ፣ በወረዳና በክልል ስብሰባዎች ላይ ይገኛሉ። የማያውቁትን ሰው ማነጋገር ቢጨንቃቸውም አገልግሎት ወጥተው ለሰዎች ይመሠክራሉ። አንተም እንዲህ ካለ ተፈታታኝ ሁኔታ ጋር እየታገልክ ከሆነ እንዲህ ያለ ችግር የሚገጥምህ አንተ ብቻ እንዳልሆንክ አትርሳ። ብዙዎች ተመሳሳይ ሁኔታዎችን እየተጋፈጡ ነው። ይሖዋ በሙሉ ነፍስ በምታደርገው ጥረት እንደሚደሰት አስታውስ። ችግሮች ቢኖሩም ተስፋ አለመቁረጥህ በራሱ ይሖዋ እየባረከህና የሚያስፈልግህን ጥንካሬ እየሰጠህ እንዳለ የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (ፊልጵ. 4:6, 7) አካላዊ ወይም ስሜታዊ የጤና እክሎችን ተቋቁመህ ይሖዋን የምታገለግል ክርስቲያን ከሆንክ ይሖዋ በአንተ እንደሚደሰት አትጠራጠር። ብዙዎቻችን አቅማችንን የሚገድቡ ነገሮች እያሉም ሩጫችንን ቀጥለናል። (2 ቆሮ. 4:16) በይሖዋ እርዳታ ሁላችንም ሩጫውን መጨረስ እንችላለን! w20.04 31 አን. 20-21
ሰኞ፣ ሐምሌ 4
የማይታዩት . . . ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።—ሮም 1:20
አምላክ መኖሪያችን የሆነችውን ምድርን የሠራበት መንገድ ጥበበኛ መሆኑን በግልጽ ያሳያል። (ዕብ. 3:4) ምድራችንን ለየት የሚያደርጋት ለሰው ልጆች መኖሪያ ምቹ እንድትሆን የሚያስፈልጉትን ነገሮች በሙሉ አሟልታ የያዘች መሆኗ ነው። ምድር በሕዋ ውስጥ ያለችበት ሁኔታ፣ ሰፊ በሆነ ውቅያኖስ ላይ ከምትንሳፈፍ ጀልባ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። ይሁንና ምድራችን በርካታ ሰዎችን ካሳፈረች ሰው ሠራሽ ጀልባ ጋር ስትነጻጸር ጉልህ ልዩነቶች አሏት። ለምሳሌ ያህል፣ በአንድ ጀልባ ላይ የተሳፈሩ ሰዎች የራሳቸውን ኦክስጅን፣ ምግብና ውኃ ማምረት ቢጠበቅባቸው እንዲሁም ቆሻሻን ወደ ውጭ መጣል ባይችሉ ምን ያህል ጊዜ በሕይወት ሊቆዩ ይችላሉ? በዚያ ጀልባ ላይ የተሳፈሩት ሰዎች ብዙም ሳይቆይ ይሞታሉ። ከዚህ በተለየ መልኩ ምድራችን በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሕያዋን ፍጥረታት የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች ታሟላለች። ምድራችን የሚያስፈልገንን ኦክስጅን፣ ምግብና ውኃ ታመርታለች፤ እንዲሁም ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑት እነዚህ ነገሮች ፈጽሞ አያልቁም። ምድር ቆሻሻዎችንም ወደ ጠፈር አትጥልም፤ ያም ቢሆን ምንጊዜም ውብና ለመኖር አመቺ ናት። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ይሖዋ ምድራችንን የሠራት፣ የሚጣሉ ነገሮችን ወደ ጠቃሚ ነገር ለመቀየር የሚያስችሉ ዑደቶች እንዲኖሯት አድርጎ ነው። w20.05 20 አን. 3-4
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 5
መሞት እንኳ ፈጽሞ አትሞቱም።—ዘፍ. 3:4
ሰይጣን ይህን ሲል፣ ይሖዋ ውሸታም እንደሆነ የገለጸ ያህል ነው። ሰይጣን በዚህ መንገድ፣ ዲያብሎስ ወይም ስም አጥፊ ሆነ። ሔዋንም ተታለለች፤ ሰይጣንን አመነችው። (1 ጢሞ. 2:14) ሔዋን ከይሖዋ ይልቅ በሰይጣን ላይ እምነት ጣለች። ይህም ከሁሉ የከፋ ውሳኔ ወደ ማድረግ መራት። የይሖዋን ትእዛዝ ለመጣስ ወሰነች። ከዚያም ይሖዋ እንዳትበላ የከለከላትን ፍሬ በላች። በኋላም ፍሬውን ለአዳም ሰጠችው። (ዘፍ. 3:6) ሔዋን ለሰይጣን ምን ምላሽ መስጠት ይገባት እንደነበር እስቲ እናስብ። ሔዋን እንዲህ ብላ ልትመልስለት ትችል ነበር፦ “አንተ ማን እንደሆንክ አላውቅም፤ አባቴን ይሖዋን ግን አውቀዋለሁ፣ እወደዋለሁ ደግሞም አምነዋለሁ። ለእኔና ለአዳም ሁሉንም ነገር የሰጠን ይሖዋ ነው። እንዴት ደፍረህ ስሙን ታጠፋለህ? ከፊቴ ዞር በል!” የምትወደው ልጁ እንዲህ ያለ ምላሽ በመስጠት ታማኝነቷን ብታሳይ ኖሮ ይሖዋ ምንኛ ይደሰት ነበር! (ምሳሌ 27:11) ሔዋን ግን ለይሖዋ እንዲህ ያለ ታማኝ ፍቅር አልነበራትም፤ አዳምም ቢሆን ይህ ባሕርይ አልነበረውም። አዳምና ሔዋን ለአባታቸው እንዲህ ዓይነት ፍቅር ስላላዳበሩ ለእሱ ስም ጥብቅና መቆም አልቻሉም። w20.06 4 አን. 10-11
ረቡዕ፣ ሐምሌ 6
ምሥራቹን የሚያውጁ ሴቶች ታላቅ ሠራዊት ናቸው።—መዝ. 68:11
እህቶቻችን በይሖዋ አገልግሎት ለሚያከናውኑት ሥራ ሁሉ ምስጋና ይገባቸዋል። እህቶች ከሚያከናውኗቸው ሥራዎች መካከል ሕንፃዎችን መገንባትና መንከባከብ፣ በሌላ ቋንቋ የሚመሩ ቡድኖችን መደገፍ እንዲሁም በቤቴል በፈቃደኝነት ማገልገል ይገኙበታል። በአደጋ ጊዜ እርዳታ በመስጠቱና ጽሑፎቻችንን በመተርጎሙ ሥራ እገዛ የሚያበረክቱ ሲሆን አቅኚዎችና ሚስዮናውያን ሆነው ያገለግላሉ። በተጨማሪም ሚስቶች፣ ባሎቻቸው በጉባኤ ውስጥም ሆነ በድርጅቱ ውስጥ ያለባቸውን ከባድ ኃላፊነት እንዲወጡ ይረዳሉ። እነዚህ ኃላፊነት ያላቸው ወንድሞች ሚስቶቻቸው ባይረዷቸው ኖሮ ‘ስጦታ’ ሆነው በተሟላ ሁኔታ ማገልገል ይከብዳቸው ነበር። (ኤፌ. 4:8) ጥበበኛ የሆኑ ሽማግሌዎች፣ እህቶች ፈቃደኛ ሠራተኞችን ያቀፈ “ታላቅ ሠራዊት” እንደሆኑና ምሥራቹን በመስበኩ ሥራ ብዙውን ጊዜ የተዋጣላቸው እንደሆኑ ይገነዘባሉ። በተጨማሪም ታማኝ የሆኑና በመንፈሳዊ የጎለመሱ እህቶች፣ ተፈታታኝ ሁኔታዎች የገጠሟቸውን በዕድሜ ከእነሱ የሚያንሱ እህቶች በመርዳት ረገድ ውጤታማ እንደሆኑ ሽማግሌዎች ይገነዘባሉ። (ቲቶ 2:3-5) በእርግጥም እህቶቻችን አድናቆት ሊቸራቸው ይገባል! w20.09 23-24 አን. 13-14
ሐሙስ፣ ሐምሌ 7
በሰማይ ያለው አባቴ ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱም እንኳ እንዲጠፋ አይፈልግም።—ማቴ. 18:14
ይሖዋ በአንድ ወቅት ያገለግሉት የነበሩ አሁን ግን ከሕዝቦቹ ጋር እሱን ማገልገላቸውን ያቆሙ አገልጋዮቹን አይረሳቸውም፤ በእሱ አገልግሎት ያከናወኑትን ሥራም ቢሆን አይዘነጋም። (ዕብ. 6:10) ነቢዩ ኢሳይያስ፣ ይሖዋ ሕዝቡን ምን ያህል እንደሚንከባከብ የሚያሳይ ግሩም ምሳሌ አስፍሮልናል። ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “መንጋውን እንደ እረኛ ይንከባከባል። ግልገሎቹን በክንዱ ይሰበስባል፤ በእቅፉም ይሸከማቸዋል።” (ኢሳ. 40:11) ታዲያ ታላቁ እረኛ ከበጎቹ አንዱ ከመንጋው ሲርቅ ምን ይሰማዋል? ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያቀረበው የሚከተለው ጥያቄ የይሖዋን ስሜት የሚገልጽ ነው፦ “ምን ይመስላችኋል? አንድ ሰው 100 በጎች ቢኖሩትና ከእነሱ አንዷ ብትጠፋ 99ኙን በተራራ ላይ ትቶ የጠፋችውን ለመፈለግ አይሄድም? እውነት እላችኋለሁ፣ የጠፋችውን በግ ካገኛት፣ ካልጠፉት ከ99ኙ ይልቅ በእሷ ይበልጥ ይደሰታል።”—ማቴ. 18:12, 13፤ w20.06 19-20 አን. 8-9
ዓርብ፣ ሐምሌ 8
የበላይ ተመልካች ለመሆን የሚጣጣር ሰው መልካም ሥራን ይመኛል።—1 ጢሞ. 3:1
ይሖዋን በየትኛውም የአገልግሎት መስክ ማገልገል ከፍ ተደርጎ የሚታይ መብት ነው። (መዝ. 27:4፤ 84:10) አንድ ወንድም ለልዩ የአገልግሎት መብት ራሱን ቢያቀርብ ይህ የሚያስመሰግን ነገር ነው። ይሁንና አንድ ወንድም ኃላፊነት ሲሰጠው ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ መመልከት አይኖርበትም። (ሉቃስ 17:7-10) ከዚህ ይልቅ ግቡ በትሕትና ሌሎችን ማገልገል ሊሆን ይገባል። (2 ቆሮ. 12:15) መጽሐፍ ቅዱስ ራሳቸውን ከፍ አድርገው ስለተመለከቱ አንዳንድ ሰዎች ይናገራል። ልኩን የማያውቀው ዲዮጥራጢስ በጉባኤ ውስጥ “የመሪነት ቦታ” ለመያዝ ፈልጎ ነበር። (3 ዮሐ. 9) ኩራተኛው ዖዝያ ይሖዋ ያልፈቀደለትን ሥራ ለማከናወን ሞክሯል። (2 ዜና 26:16-21) መሠሪው አቢሴሎም ንጉሥ መሆን ስለፈለገ ሕዝቡን በማታለል ድጋፋቸውን ለማግኘት ጥረት አድርጓል። (2 ሳሙ. 15:2-6) እነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች በግልጽ እንደሚያሳዩት ይሖዋ የራሳቸውን ክብር በሚሹ ሰዎች አይደሰትም። (ምሳሌ 25:27) ይዋል ይደር እንጂ ኩራትም ሆነ የሥልጣን ጥመኝነት ለውድቀት መዳረጉ አይቀርም።—ምሳሌ 16:18፤ w20.07 4 አን. 7-8
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 9
እያንዳንዱ የራሱን የኃላፊነት ሸክም ይሸከማል።—ገላ. 6:5
አንዳንድ ክርስቲያን ቤተሰቦች አደገኛ ሁኔታን ለመሸሽ ወይም ሥራ ለማግኘት ሲሉ ወደ ሌላ አገር ሄደዋል። ወደ ሌላ አገር ከሄዱ በኋላ ልጆቻቸው ትምህርት ቤት የሚማሩት በአገሪቱ ዋነኛ ቋንቋ ሊሆን ይችላል። ወላጆችም ቢሆኑ ሥራ ለማግኘት ሲሉ የአገሪቱን ቋንቋ መማር ሊያስፈልጋቸው ይችላል። በሄዱበት አገር በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው የሚመራ ጉባኤ ወይም ቡድን ቢኖርስ? ቤተሰቡ ወደ የትኛው ጉባኤ ቢሄድ ይሻላል? በአገሪቱ ዋነኛ ቋንቋ ወደሚመራው ጉባኤ ወይስ በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ወደሚካሄደው ጉባኤ? ቤተሰቡ ወደ የትኛው ጉባኤ እንደሚሄድ መወሰን ያለበት የቤተሰቡ ራስ ነው። የቤተሰቡ ራስ ይህን ውሳኔ ሲያደርግ ለቤተሰቡ የሚበጀውን ነገር ግምት ውስጥ ማስገባት ይኖርበታል። ሌሎቻችን የቤተሰቡ ራስ ያደረገውን ውሳኔ ልናከብር ይገባል። ውሳኔው ምንም ይሁን ምን፣ ወደ ጉባኤያችን ሲመጡ ሞቅ አድርገን በመቀበል ውሳኔያቸውን እንደምናከብር እናሳያቸው።—ሮም 15:7፤ w20.08 30 አን. 17-18
እሁድ፣ ሐምሌ 10
አምላክ . . . የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ።—1 ቆሮ. 1:27
ይሖዋ ኃይል እንዲሰጠን ከፈለግን በእሱ ዘንድ ያለን ዋጋ የሚለካው በአካላዊ ጥንካሬያችን፣ በትምህርት ደረጃችን፣ በዘራችን ወይም በቁሳዊ ሀብታችን ላይ እንዳልሆነ ማስታወስ ይኖርብናል። ይሖዋ የሚጠቀምብን እነዚህን ነገሮች መሠረት አድርጎ አይደለም። እንዲያውም ከይሖዋ ሕዝቦች መካከል ብዙዎቹ ‘በሰብዓዊ አመለካከት ጥበበኞች፣ ኃያላን እንዲሁም ከትልቅ ቤተሰብ የተወለዱ’ አይደሉም። (1 ቆሮ. 1:26) እንግዲያው እንደ ድክመት ሊቆጠሩ የሚችሉ ነገሮች ይሖዋን ከማገልገል እንቅፋት እንዲሆኑባችሁ አትፍቀዱ። ከዚህ ይልቅ የይሖዋ ኃይል በውስጣችሁ ሲሠራ ለማየት የሚያስችሉ አጋጣሚዎች እንደሆኑ አድርጋችሁ ተመልከቷቸው። ለምሳሌ እምነታችሁን እንድትጠራጠሩ ለማድረግ ከሚሞክሩ ሰዎች ጋር መነጋገር የሚያስፈራችሁ ከሆነ ለእምነታችሁ በድፍረት ጥብቅና ለመቆም እንዲረዳችሁ ይሖዋን በጸሎት ጠይቁት። (ኤፌ. 6:19, 20) ከከባድ አእምሯዊ ወይም አካላዊ እክል ጋር እየታገላችሁ ከሆነ በእሱ አገልግሎት የቻላችሁትን ያህል ተሳትፎ ለማድረግ የሚያስፈልጋችሁን ብርታት እንዲሰጣችሁ ይሖዋን ለምኑት። የይሖዋን እርዳታ ባያችሁ ቁጥር እምነታችሁ ያድጋል፤ እናንተም ይበልጥ ጠንካራ ትሆናላችሁ። w20.07 16 አን. 9
ሰኞ፣ ሐምሌ 11
ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት [ፈልጉ]።—ማቴ. 6:33
በሕይወታችን ውስጥ ለአምላክ መንግሥት ቅድሚያ መስጠት ከፈለግን ልክ እንደ አብርሃም መሆን አለብን፤ አብርሃም አምላክን ለማስደሰት ሲል መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ሆኗል። (ማር. 10:28-30፤ ዕብ. 11:8-10) ሕይወታችን ምንም ችግር የሌለበት እንዲሆን አንጠብቅ። መላ ሕይወታቸውን በይሖዋ አገልግሎት ለማሳለፍ የወሰኑ ክርስቲያኖችም እንኳ ችግሮች ያጋጥሟቸዋል። (ያዕ. 1:2፤ 1 ጴጥ. 5:9) ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ዛሬ፣ በወደፊቱ ጊዜ ላይ እንድናተኩር የሚያነሳሳ ምክንያት አለን። የዓለም ሁኔታዎች በግልጽ እንደሚጠቁሙት የምንኖረው በመጨረሻዎቹ ቀናት መጨረሻ ላይ ነው። በመንግሥቱ አገዛዝ ሥር ከምናገኛቸው ብዙ በረከቶች አንዱ የምንወዳቸው ሰዎች ከሞት ሲነሱ ማየት ነው። ያን ጊዜ ይሖዋ፣ አብርሃምንና ቤተሰቡን ከሞት በማስነሳት ይህን ታማኝ አገልጋዩን ላሳየው እምነትና ትዕግሥት ወሮታ ይከፍለዋል። አንተስ በዚያ ጊዜ በሕይወት ኖረህ እነሱን ለመቀበል ትበቃ ይሆን? እንደ አብርሃም ለአምላክ መንግሥት ስትል መሥዋዕት ለመክፈል ፈቃደኛ ከሆንክ፣ ችግሮች እያሉም ጠንካራ እምነት ይዘህ ከኖርክ እንዲሁም ይሖዋን በትዕግሥት ከተጠባበቅህ ለዚያ ጊዜ ትበቃለህ።—ሚክ. 7:7፤ w20.08 5-6 አን. 13-14፤ 7 አን. 17
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 12
እስከ ሞት ድረስ ታማኝነትህን አስመሥክር፤ እኔም የሕይወትን አክሊል እሰጥሃለሁ።—ራእይ 2:10
ጠላቶቻችን ቢገድሉን ይሖዋ ከሞት እንደሚያስነሳን እናውቃለን። ጠላቶቻችን ምንም ቢያደርጉ ከይሖዋ ሊለዩን እንደማይችሉ እርግጠኞች ነን። (ሮም 8:35-39) በእርግጥም ይሖዋ የትንሣኤን ተስፋ መስጠቱ ታላቅ ጥበብ እንዳለው የሚያሳይ ነው! ይህ ተስፋ፣ የሰይጣንን ውጤታማ መሣሪያ የሚያከሽፍ ከመሆኑም ሌላ የማይናወጥ ድፍረት እንዲኖረን ስለሚረዳን ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት ያስችለናል። የይሖዋ ጠላቶች እንደሚገድሉህ ቢዝቱብህ ይሖዋ እንደሚያስነሳህ በመተማመን ሕይወትህን በአደራ ትሰጠዋለህ? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ቢያጋጥምህ በይሖዋ እንደምትተማመን አሁን ማወቅ የምትችለው እንዴት ነው? ‘በየዕለቱ የማደርጋቸው ትናንሽ ውሳኔዎች በይሖዋ እንደምታመን ያሳያሉ?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። (ሉቃስ 16:10) በተጨማሪም ‘አኗኗሬ፣ መንግሥቱን ካስቀደምኩ ይሖዋ የሚያስፈልጉኝን ቁሳዊ ነገሮች እንደሚያሟላልኝ በገባው ቃል እንደምተማመን ያሳያል?’ ብለህ ራስህን መጠየቅህ ይጠቅምሃል። (ማቴ. 6:31-33) ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጠው መልስ ‘አዎ’ የሚል ከሆነ ወደፊት ለሚያጋጥምህ ማንኛውም ዓይነት ፈተና ዝግጁ እንደሆንክ እያሳየህ ነው።—ምሳሌ 3:5, 6፤ w20.08 17-18 አን. 15-16
ረቡዕ፣ ሐምሌ 13
የእውነትን ቃል በአግባቡ በመጠቀም፣ ተቀባይነት ሊያገኝ እንደሚገባውና ምንም የሚያፍርበት ነገር እንደሌለው ሠራተኛ አድርገህ ራስህን በአምላክ ፊት ለማቅረብ የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ።—2 ጢሞ. 2:15
የአምላክን ቃል በምንጠቀምበት መንገድ የተካንን መሆን አለብን። ለዚህ የሚረዱንን አንዳንድ ክህሎቶች በስብሰባዎቻችን ላይ እንማራለን። ሆኖም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘው እውነት ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ለሰዎች አሳማኝ በሆነ መንገድ ማስረዳት እንድንችል መጽሐፍ ቅዱስን በግላችን አዘውትረን ማጥናት ይኖርብናል። የአምላክን ቃል ተጠቅመን እምነታችንን ማጠናከር ያስፈልገናል። ይህ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን ከማንበብ ባለፈ ባነበብነው ነገር ላይ ማሰላሰል ብሎም በጽሑፎቻችን ላይ ምርምር ማድረግ ይጠይቃል፤ ይህም በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የምናነበውን ነገር በትክክል መረዳት እንዲሁም ማብራራት እንድንችል ይረዳናል። (1 ጢሞ. 4:13-15) እንዲህ ካደረግን በአምላክ ቃል ተጠቅመን ሌሎችን ማስተማር እንችላለን። ሰዎችን ስናስተምርም ቢሆን ጥቅስ አውጥተን ከማንበብ ያለፈ ነገር ማድረግ ይጠበቅብናል። የሚያዳምጡን ሰዎች ጥቅሱን እንዲረዱትና ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ እንዲያስተውሉ መርዳት እንፈልጋለን። መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን በግላችን የማጥናት ልማድ ካለን የአምላክን ቃል ለሰዎች የማስተማር ችሎታችን እየተሻሻለ ይሄዳል።—2 ጢሞ. 3:16, 17፤ w20.09 28 አን. 12
ሐሙስ፣ ሐምሌ 14
እንዳትደክሙና ተስፋ እንዳትቆርጡ [ኢየሱስን] በጥሞና አስቡ።—ዕብ. 12:3
ይሖዋ እኛን ለመርዳት ያደረጋቸውን ነገሮች ማሰባችን ምንጊዜም በስብከቱ ሥራ ላይ ትኩረት ለማድረግ ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል፣ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እያቀረበልን ነው፤ ታትመው በሚወጡና በኤሌክትሮኒክ ፎርማት በሚዘጋጁ ጽሑፎች፣ በድምፅና በቪዲዮ በተቀዱ ነገሮች እንዲሁም በኢንተርኔት በሚተላለፉ የብሮድካስት ፕሮግራሞች አማካኝነት ይመግበናል። እስቲ አስበው፦ በሕጋዊ ድረ ገጻችን ላይ ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች የተለያዩ መረጃዎችን ማግኘት ይቻላል። (ማቴ. 24:45-47) በስብከቱ ሥራ ላይ ምንጊዜም ትኩረት ለማድረግ የሚረዳን ሌላው ነገር የኢየሱስን ምሳሌ መከተላችን ነው። ኢየሱስ ምንም ነገር ትኩረቱን እንዲከፋፍልበትና ስለ እውነት ከመመሥከር እንዲያግደው አልፈቀደም። (ዮሐ. 18:37) ሰይጣን “የዓለምን መንግሥታት ሁሉና ክብራቸውን” እንደሚሰጠው ያቀረበለት ግብዣ ኢየሱስን አላጓጓውም፤ ሰዎች ሊያነግሡት በሞከሩበት ወቅትም ቢሆን ይህን ለመቀበል አልተፈተነም። (ማቴ. 4:8, 9፤ ዮሐ. 6:15) ቁሳዊ ሀብት አላማለለውም፤ ለከባድ ተቃውሞም አልተበገረም። (ሉቃስ 9:58፤ ዮሐ. 8:59) እኛም እምነታችንን የሚፈትኑ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ምክር ማስታወሳችን ትኩረታችን እንዳይከፋፈል ይረዳናል። w20.09 9-10 አን. 6-7
ዓርብ፣ ሐምሌ 15
እኔ የክርስቶስን አርዓያ እንደምከተል እናንተም የእኔን አርዓያ ተከተሉ።—1 ቆሮ. 11:1
በጉባኤ ውስጥ በትጋት የሚያገለግሉ እጅግ ብዙ እህቶች ስላሉን ምንኛ አመስጋኞች ነን! እነዚህ እህቶች በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ይሳተፋሉ እንዲሁም በአገልግሎት ይካፈላሉ። አንዳንዶች የስብሰባ አዳራሹን በመንከባከቡ ሥራ አስተዋጽኦ ያበረክታሉ፤ እንዲሁም ለእምነት አጋሮቻቸው በግለሰብ ደረጃ አሳቢነት ያሳያሉ። እርግጥ ነው፣ እነዚህ እህቶች ተፈታታኝ ሁኔታዎች ያጋጥሟቸዋል። አንዳንዶቹ በዕድሜ የገፉ ወላጆቻቸውን ይንከባከባሉ። ሌሎች ደግሞ የቤተሰብ ተቃውሞ ይደርስባቸዋል። ለልጆቻቸው የሚያስፈልገውን ለማቅረብ ብዙ የሚደክሙ ነጠላ እናቶችም አሉ። ለእህቶች ድጋፍ ስለ መስጠት መወያየት ያስፈለገን ለምንድን ነው? ምክንያቱም ብዙውን ጊዜ ይህ ዓለም ለሴቶች የሚገባቸውን ክብር አይሰጣቸውም። ከዚህም ሌላ መጽሐፍ ቅዱስ ሴቶችን እንድንደግፋቸው ያበረታታናል። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ ፌበንን እንዲቀበሏትና ‘የምትፈልገውን እርዳታ ሁሉ እንዲያደርጉላት’ በሮም ጉባኤ ለነበሩ ክርስቲያኖች ጽፎላቸው ነበር። (ሮም 16:1, 2) ጳውሎስ ያደገው ሴቶችን ዝቅ አድርጎ በሚመለከት ማኅበረሰብ ውስጥ ነው። ክርስቲያን ከሆነ በኋላ ግን የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል ሴቶችን በአክብሮትና በደግነት መያዝ ጀመረ። w20.09 20 አን. 1-2
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 16
ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።—ማቴ. 28:20
ጥናታችን ምሥራቹን ለሌሎች የመናገር ፍላጎት እንዲያድርበት ለመርዳት እንዲህ እያልን ልንጠይቀው እንችላለን፦ “የመጽሐፍ ቅዱስን ትምህርት ተግባራዊ ማድረግህ ሕይወትህን ያሻሻለው እንዴት ነው? ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት መስማታቸው እንደሚጠቅማቸው ይሰማሃል? እነሱን ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላለህ?” (ምሳሌ 3:27፤ ማቴ. 9:37, 38) ኢየሱስ፣ ያዘዘውን “ሁሉ እንዲጠብቁ” ሰዎችን እንድናስተምር መመሪያ እንደሰጠን እናስታውስ። ኢየሱስ ካዘዛቸው ነገሮች መካከል፣ ሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት እንደሚገኙበት የታወቀ ነው፤ እነሱም አምላክንና ባልንጀራን መውደድ ናቸው። እነዚህ ትእዛዛት ደግሞ ከስብከቱና ደቀ መዛሙርት ከማድረጉ ሥራ ጋር በጥብቅ የተያያዙ ናቸው። (ማቴ. 22:37-39) እንዲያውም በስብከቱ ሥራ ለመካፈል የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ፍቅር ነው። እርግጥ አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች በስብከቱ ሥራ መካፈል ያስፈራቸው ይሆናል። እንዲህ ላሉት ጥናቶች፣ በይሖዋ እርዳታ ቀስ በቀስ የሰው ፍርሃትን ማሸነፍ እንደሚችሉ ልናረጋግጥላቸው እንችላለን።—መዝ. 18:1-3፤ ምሳሌ 29:25፤ w20.11 3 አን. 6-8
እሁድ፣ ሐምሌ 17
ስለ እናንተ መጸለያችንን . . . አላቋረጥንም።—ቆላ. 1:9
መጽሐፍ ቅዱስን ለማስጠናት ስትዘጋጅ ስለ ተማሪውና ስለሚያስፈልጉት ነገሮች ወደ ይሖዋ ጸልይ። የሰውየውን ልብ በሚነካ መንገድ ከመጽሐፍ ቅዱስ ለማስተማር እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። ዋነኛ ዓላማህ ጥናትህ እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ መርዳት እንደሆነ ምንጊዜም አስታውስ። ጥናቱም ቢሆን ከይሖዋ ጋር መነጋገር ያስፈልገዋል። ይህን ማድረግ የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋን በማዳመጥና በጸሎት ወደ እሱ በመቅረብ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብ አምላክን ማዳመጥ ይችላል። (ኢያሱ 1:8፤ መዝ. 1:1-3) በየዕለቱ በመጸለይ ደግሞ ይሖዋን ያነጋግረዋል። እንግዲያው ጥናታችሁን ከመጀመራችሁ በፊት እንዲሁም ስትደመድሙ ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት አቅርብ፤ በጸሎትህ ላይ ስለ ጥናትህ ጥቀስ። የምታቀርበውን ጸሎት ሲሰማ ከልቡ መጸለይ የሚችለው እንዴት እንደሆነ እንዲሁም በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ወደ ይሖዋ አምላክ መጸለይ እንዳለበት ይማራል። (ማቴ. 6:9፤ ዮሐ. 15:16) በየዕለቱ መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ (ይሖዋን ማዳመጥ) እና መጸለይ (ይሖዋን ማነጋገር) ጥናትህ ወደ ይሖዋ አምላክ ይበልጥ እንዲቀርብ እንደሚረዳው ጥያቄ የለውም!—ያዕ. 4:8፤ w20.10 8 አን. 8፤ 9 አን. 10-11
ሰኞ፣ ሐምሌ 18
አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት [ጠብቁ]።—ኤፌ. 4:3
በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበሩት ክርስቲያኖች መካከል ሥርዓትና ሰላም ሰፍኖ ነበር። የይሖዋ ድርጅት በዛሬው ጊዜም እንዲህ ያለ ሥርዓትና ሰላም እንዲሰፍን ለማድረግ ተግቶ ይሠራል። (ሥራ 16:4, 5) ለምሳሌ ያህል፣ ሌላ ጉባኤ አልፎ ተርፎም ሌላ አገር ሄደህ በመጠበቂያ ግንብ ጥናት ላይ ብትገኝ ጥናቱ እንዴት እንደሚመራም ሆነ የትኛው ርዕስ እንደሚጠና ታውቃለህ። ምንም የእንግድነት ስሜት አይሰማህም! ይህን የመሰለ አስገራሚ አንድነት በአምላክ መንፈስ እርዳታ ካልሆነ ሌላ በምን ሊገኝ ይችላል? (ሶፎ. 3:9 ግርጌ) አንተ ለዚህ አንድነት አስተዋጽኦ ማበርከት የምትችለው እንዴት ነው? ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘በጉባኤው ውስጥ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ጥረት አደርጋለሁ? አመራር ለሚሰጡት ወንድሞች እታዘዛለሁ? በተለይ በጉባኤው ውስጥ ኃላፊነት ካለኝ ሌሎች እምነት የሚጥሉብኝ ዓይነት ሰው ነኝ? ሰዓት አክባሪ፣ ተባባሪና ሌሎችን ለማገልገል ፈቃደኛ ነኝ?’ (ያዕ. 3:17) በዚህ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንዳለብህ ከተሰማህ መንፈስ ቅዱስ ለማግኘት ጸልይ። መንፈስ ቅዱስ ማንነትህንና ድርጊትህን እንዲቀርጸው በፈቀድክ መጠን ወንድሞችና እህቶች ይበልጥ የሚወዱህ ከመሆኑም ሌላ የምታከናውነውን አስተዋጽኦ ከፍ አድርገው ይመለከታሉ። w20.10 23 አን. 12-13
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 19
ቃሉን የምታደርጉ ሁኑ እንጂ . . . ሰሚዎች ብቻ አትሁኑ።—ያዕ. 1:22
የአምላክ ቃል እንደ መስተዋት ሊሆንልን ይችላል። (ያዕ. 1:23-25) አብዛኞቻችን ጠዋት ከቤት ከመውጣታችን በፊት መስተዋት እናያለን። ይህን የምናደርገው ከሰዎች ጋር ከመገናኘታችን በፊት፣ የሚያስፈልገንን ማስተካከያ ለማድረግ ነው። በተመሳሳይም መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ ስናነብ ከአስተሳሰባችን እና ከዝንባሌያችን ጋር በተያያዘ ማስተካከያ ልናደርግባቸው የሚገቡ አቅጣጫዎችን እንመለከታለን። ብዙዎች ጠዋት ከቤት ከመውጣታቸው በፊት የዕለቱን ጥቅስ ማንበብ ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። በሚያነቡት ነገር ላይ ተመሥርተው አስተሳሰባቸውን ያርማሉ። ከዚያም በቀኑ ውስጥ፣ ከአምላክ ቃል ያገኙትን ምክር ተግባራዊ ማድረግ የሚችሉባቸውን መንገዶች ይፈልጋሉ። በተጨማሪም በየቀኑ የአምላክን ቃል የምናነብበትና ባነበብነው ላይ የምናሰላስልበት ፕሮግራም ሊኖረን ይገባል። ይህ ቀላል ነገር ቢመስልም ወደ ሕይወት ከሚወስደው ቀጭን መንገድ ሳንወጣ ለመጓዝ ከሚረዱን በጣም አስፈላጊ ነገሮች አንዱ ነው። እንደ ራጅ መሣሪያ ሁሉ የአምላክ ቃልም በውስጣችን ያለውን ለማየት ያስችለናል። ሆኖም ከመጽሐፍ ቅዱስ ወይም ከአምላክ ወኪሎች የምናገኘውን ምክር ተግባራዊ በማድረግ ጥቅም ማግኘት ከፈለግን ትሑቶች መሆን ያስፈልገናል። w20.11 18 አን. 3፤ 20 አን. 8
ረቡዕ፣ ሐምሌ 20
ጉባኤዎቹ . . . በእምነት እየጠነከሩና ከዕለት ወደ ዕለት በቁጥር እየጨመሩ ሄዱ።—ሥራ 16:5
በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ ስደት ይደርስባቸው የነበረ ቢሆንም ሰላም ያገኙባቸው ወቅቶችም ነበሩ። ታዲያ ደቀ መዛሙርቱ እነዚህን ወቅቶች እንዴት ተጠቀሙባቸው? እነዚህ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ምሥራቹን ያለማሰለስ ሰብከዋል። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ላይ የሚገኘው ዘገባ “ይሖዋን በመፍራት” ይኖሩ እንደነበር ይገልጻል። ምሥራቹን መስበካቸውን በመቀጠላቸው ‘በቁጥር እየበዙ ሄዱ።’ እነዚህ ክርስቲያኖች በሰላሙ ጊዜ በቅንዓት ያከናወኑትን የስብከት ሥራ ይሖዋ እንደባረከላቸው አያጠራጥርም። (ሥራ 9:26-31) የመጀመሪያው መቶ ዘመን ደቀ መዛሙርት ምሥራቹን ለመስበክ የሚያስችላቸውን አጋጣሚ ሁሉ ተጠቅመውበታል። አንድ ምሳሌ እንውሰድ፤ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ሳለ ትልቅ የሥራ በር እንደተከፈተለት ተገንዝቦ ነበር፤ በመሆኑም ይህን አጋጣሚ በዚያች ከተማ ለመስበክና ደቀ መዛሙርት ለማፍራት ተጠቅሞበታል። (1 ቆሮ. 16:8, 9) ደቀ መዛሙርቱ “ምሥራቹን ይኸውም የይሖዋን ቃል” ለማወጅ በትጋት ሠርተዋል። (ሥራ 15:30-35) ውጤቱ ምን ሆነ? የዛሬው የዕለት ጥቅስ መልሱን ይሰጠናል። w20.09 16 አን. 6-8
ሐሙስ፣ ሐምሌ 21
ሞት የመጣው በአንድ ሰው በኩል [ነው]።—1 ቆሮ. 15:21
አዳም ኃጢአት በመሥራቱ በራሱም ሆነ በዘሮቹ ላይ ሞት አምጥቷል። የእሱ አለመታዘዝ ያስከተለው መዘዝ አሁንም አልለቀቀንም። አምላክ ልጁን ከሞት ማስነሳቱ ያስገኘው ውጤት ግን ከዚህ ምንኛ የተለየ ነው! ሐዋርያው ጳውሎስ “የሙታን ትንሣኤም በአንድ ሰው [በኢየሱስ] በኩል ነው። ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉና” የሚል አሳማኝ ነጥብ አቅርቧል። (1 ቆሮ. 15: 22) ጳውሎስ ‘ሁሉም በአዳም ይሞታሉ’ ሲል ምን ማለቱ ነበር? ስለ አዳም ዘሮች መናገሩ ነበር፤ ሁሉም የአዳም ዘሮች ኃጢአትንና አለፍጽምናን ከአዳም ስለወረሱ እንደሚሞቱ ገልጿል። (ሮም 5:12) አዳም ‘ሕያው ከሚሆኑት’ መካከል አይካተትም። አዳም ከክርስቶስ ቤዛ ጥቅም አያገኝም፤ ምክንያቱም አዳም ፍጹም ሰው የነበረ ቢሆንም ሆን ብሎ በአምላክ ላይ ዓምጿል። የአዳም ዕጣ ፈንታ፣ ኢየሱስ ‘ፍየሎች’ እንደሆኑ ከሚፈርድባቸው ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ነው፤ የሁሉም ፍርድ ‘የዘላለም ጥፋት’ ነው።—ማቴ. 25:31-33, 46፤ ዕብ. 5:9፤ w20.12 5 አን. 13-14
ዓርብ፣ ሐምሌ 22
ይሖዋ . . . ትሑት የሆነውን ሰው ይመለከታል።—መዝ. 138:6
የምንፈልገውን የአገልግሎት መብት ካላገኘን ታማኝ መላእክት የተዉልንን ምሳሌ ማሰባችን ይጠቅመናል። ንጉሥ አክዓብ ሥልጣን ላይ በነበረበት ወቅት፣ ይሖዋ ይህን ክፉ ንጉሥ ማሞኘት ስለሚቻልበት መንገድ ሐሳብ እንዲሰጡ መላእክቱን ጋብዟቸው ነበር። አንዳንዶቹ መላእክት ሐሳብ አመነጩ። ይሖዋን የአንዱን መልአክ ሐሳብ በመቀበል እንደሚሳካለት ነገረው። (1 ነገ. 22:19-22) ታዲያ ሌሎቹ ታማኝ መላእክት በዚህ ተስፋ ቆርጠው ‘መጀመሪያውኑ ቢቀርብኝ ኖሮስ?’ ብለው አስበው ይሆን? እንደዚያ ብለው እንዳሰቡ የሚያሳይ ምንም ፍንጭ አናገኝም። መላእክት በጣም ትሑት ስለሆኑ የሚያሳስባቸው ለይሖዋ ክብር መሰጠቱ ነው። (መሳ. 13:16-18፤ ራእይ 19:10) ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መብት የይሖዋን ስም መሸከምና መንግሥቱን ማሳወቅ እንደሆነ አትርሱ። በይሖዋ ፊት ውድ የሚያደርገን ያለን ቲኦክራሲያዊ መብት አይደለም። በይሖዋም ሆነ በወንድሞቻችን ዘንድ ተወዳጅ የሚያደርገን፣ ትሑት መሆናችን እና ልካችንን ማወቃችን ነው። ስለዚህ ምንጊዜም ትሑት ለመሆን እንዲረዳችሁ ይሖዋን በጸሎት ለምኑት። በትሕትና እና ልክን በማወቅ ረገድ ግሩም አርዓያ በሚሆኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች ላይ አሰላስሉ። አቅማችሁ በሚፈቅደው በማንኛውም መንገድ ወንድሞቻችሁን በደስታ አገልግሉ።—1 ጴጥ. 5:5፤ w20.12 26 አን. 16-17
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 23
የመዳንን የራስ ቁር አድርጉ፤ እንዲሁም የመንፈስን ሰይፍ ይኸውም የአምላክን ቃል ያዙ።—ኤፌ. 6:17
የመዳን የራስ ቁር ይሖዋ የሰጠንን ተስፋ ያመለክታል፤ ይህ ተስፋ ይሖዋ ከሞት እንደሚታደገንና ፈቃዱን ለሚያደርጉ ሰዎች ሁሉ ወሮታ እንደሚከፍላቸው የሚገልጽ ነው። (1 ተሰ. 5:8፤ 1 ጢሞ. 4:10፤ ቲቶ 1:1, 2) የመዳን ተስፋችን የማሰብ ችሎታችንን ይጠብቅልናል። አምላክ ቃል በገባቸው ነገሮች ላይ ምንጊዜም እንድናተኩርና ለሚደርሱብን ችግሮች ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። ይህን የራስ ቁር ማጥለቅ የምንችለው አስተሳሰባችን ምንጊዜም ከአምላክ አስተሳሰብ ጋር የሚስማማ እንዲሆን በማድረግ ነው። ለምሳሌ ተስፋችንን አስተማማኝነት በሌለው ሀብት ላይ ሳይሆን በአምላክ ላይ እንጥላለን። (መዝ. 26:2፤ 104:34፤ 1 ጢሞ. 6:17) የመንፈስ ሰይፍ የአምላክ ቃል የሆነው መጽሐፍ ቅዱስ ነው። እንደ ሰይፍ የሆነው የአምላክ ቃል ማታለያዎችን የማጋለጥ እንዲሁም በሐሰት ትምህርቶችና ጎጂ በሆኑ ልማዶች የተተበተቡ ሰዎችን ነፃ የማውጣት ኃይል አለው። (2 ቆሮ. 10:4, 5፤ 2 ጢሞ. 3:16, 17፤ ዕብ. 4:12) በግል ጥናት እንዲሁም ከአምላክ ድርጅት በምናገኘው ሥልጠና አማካኝነት፣ ይህን ሰይፍ በአግባቡ መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን።—2 ጢሞ. 2:15፤ w21.03 27 አን. 4፤ 29 አን. 10-11
እሁድ፣ ሐምሌ 24
እኔ . . . ስለ አምላክ በመናገሬና ስለ ኢየሱስ በመመሥከሬ ጳጥሞስ በምትባል ደሴት ነበርኩ።—ራእይ 1:9
ሐዋርያው ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ በመስበኩ የተነሳ ታስሮ በነበረበት ወቅትም እንኳ ለሌሎች ያለውን ፍቅር በተግባር አሳይቷል። ለምሳሌ ያህል፣ የተመለከተውን ራእይ በጽሑፍ በማስፈር ለጉባኤዎቹ ልኮላቸዋል፤ ይህን ያደረገው ጉባኤዎቹ “በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን” ነገሮች እንዲያውቁ ለመርዳት ነበር። (ራእይ 1:1) ከዚያም ከጳጥሞስ ደሴት ከእስር ከተለቀቀ በኋላ ሳይሆን አይቀርም፣ ዮሐንስ ስለ ኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት የሚተርከውን የወንጌል ዘገባ በጽሑፍ አስፍሯል። በተጨማሪም ወንድሞቹንና እህቶቹን ለማበረታታትና ለማጠናከር ሦስት ደብዳቤዎችን ጽፏል። እናንተም የራስን ጥቅም መሥዋዕት ማድረግ የሚጠይቅ ሕይወት በመምራት ረገድ ዮሐንስ የተወውን ምሳሌ መከተልና በምትመርጡት የሕይወት ጎዳና ለሰዎች ያላችሁን ፍቅር ማሳየት ትችላላችሁ። የሰይጣን ሥርዓት ስለ ራሳችሁ ጥቅም ብቻ እንድታስቡ ይኸውም ጊዜያችሁንና ጉልበታችሁን ሁሉ ገንዘብ ወይም ዝና በማሳደድ ላይ እንድታውሉ ይፈልጋል። በዓለም ዙሪያ የሚገኙ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርጉ የመንግሥቱ አስፋፊዎች ግን በተቻለ መጠን ጊዜያቸውንና ጉልበታቸውን የሚያውሉት ምሥራቹን ለመስበክና ሰዎች ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡ ለመርዳት ነው። w21.01 10 አን. 9-10
ሰኞ፣ ሐምሌ 25
ዮናታን . . . እንደ ራሱ ወደደው።—1 ሳሙ. 18:1
ዮናታን በዳዊት ላይ ቅናት ሊያድርበት ይችል ነበር። የንጉሥ ሳኦል ልጅ እንደመሆኑ መጠን ዮናታን ‘ዙፋኑ የሚገባው ለእኔ ነው’ የሚል ጥያቄ ሊያነሳ ይችል ነበር። (1 ሳሙ. 20:31) ዮናታን ግን ትሑት ከመሆኑም ሌላ ለይሖዋ ታማኝ ነበር። በመሆኑም ዳዊት ቀጣዩ ንጉሥ እንዲሆን ይሖዋ ያደረገውን ውሳኔ በሙሉ ልቡ ደግፏል። ዮናታን ለዳዊትም ታማኝ ነበር፤ ይህ ሳኦልን ቢያስቆጣውም እንዲህ ከማድረግ ወደኋላ አላለም። (1 ሳሙ. 20:32-34) ዮናታን ዳዊትን ከልቡ ይወደው ስለነበር ተቀናቃኙ አድርጎ አልተመለከተውም። ዮናታን የተዋጣለት ቀስተኛና ጀግና ተዋጊ ነበር። እሱና አባቱ ሳኦል “ከንስር ይልቅ ፈጣኖች፣ ከአንበሳም ይልቅ ብርቱዎች” የሚል ስም አትርፈው ነበር። (2 ሳሙ. 1:22, 23) በመሆኑም ዮናታን በጦርነት ስላከናወናቸው ጀብዱዎች ጉራውን ሊነዛ ይችል ነበር። ዮናታን ግን የፉክክር ወይም የቅናት መንፈስ አልነበረበትም። ከዚህ ይልቅ ዳዊትን በድፍረቱና በይሖዋ ላይ ባለው እምነት አድንቆታል። እንዲያውም ዮናታን ዳዊትን እንደ ራሱ አድርጎ የወደደው፣ ዳዊት ጎልያድን ከገደለው በኋላ ነው። w21.01 21 አን. 6፤ 22 አን. 8-9
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 26
የሴት . . . ራስ ወንድ [ነው]።—1 ቆሮ. 11:3
ሁሉም ክርስቲያኖች በኢየሱስ ክርስቶስ የራስነት ሥልጣን ሥር ናቸው፤ እሱ ደግሞ ፍጹም የሆነ ራስ ነው። ሆኖም አንዲት ክርስቲያን ትዳር ስትመሠርት ራሷ የሚሆነው ፍጹም ያልሆነ ወንድ ነው። ይህ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ አንድን ወንድም ለማግባት ስታስብ እንዲህ ብላ ራሷን መጠየቋ ጠቃሚ ነው፦ ‘ይህ ወንድም ጥሩ የቤተሰብ ራስ ሊሆን እንደሚችል የሚያሳዩ ነገሮች አሉ? በሕይወቱ ወስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ይሰጣል? ካልሆነ ከተጋባን በኋላ ጥሩ መንፈሳዊ የቤተሰብ ራስ ይሆናል ብዬ እንዳስብ የሚያደርግ ምን ምክንያት አለኝ?’ በእርግጥ አንዲት እህት እንዲህ ብላ ራሷን መጠየቋም ተገቢ ነው፦ ‘እኔ ራሴ ለትዳር ሕይወት የሚጠቅሙ ምን ባሕርያት አሉኝ? ታጋሽና ደግ ነኝ? ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና መሥርቼያለሁ?’ (መክ. 4:9, 12) አንዲት ሚስት በትዳሯ ደስተኛ መሆኗ በተወሰነ መጠንም ቢሆን የተመካው ከማግባቷ በፊት በምታደርጋቸው ውሳኔዎች ላይ ነው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ክርስቲያን እህቶች ለባሎቻቸው በመገዛት ረገድ ግሩም ምሳሌ ይሆናሉ። ለዚህም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል! ከእነዚህ ታማኝ ሴቶች ጋር ይሖዋን ማገልገል በጣም ያስደስተናል! w21.02 8 አን. 1-2
ረቡዕ፣ ሐምሌ 27
ወደ መቄዶንያ ተሻገርና እርዳን።—ሥራ 16:9
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ አስፋፊዎች አገልግሎታቸውን ለማስፋትና አስፋፊዎች ይበልጥ በሚያስፈልጉበት ጉባኤ ውስጥ ለማገልገል ሲሉ ሌላ ቋንቋ እየተማሩ ነው። እነዚህ ክርስቲያኖች ይህን ውሳኔ ያደረጉት በይሖዋ አገልግሎት ይበልጥ መካፈል ስለፈለጉ ነው። አዲሱን ቋንቋ በደንብ ለመልመድ ዓመታት ሊወስድባቸው ቢችልም ጉባኤውን በብዙ መንገድ ይጠቅማሉ። ያሏቸው ግሩም ባሕርያትና ያካበቱት ተሞክሮ ጉባኤውን ያጠናክረዋል። የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ያደረጉትን እነዚህን ወንድሞችና እህቶች እናደንቃቸዋለን! አንድ ወንድም ጉባኤው የሚመራበትን ቋንቋ አቀላጥፎ መናገር ስላልቻለ ብቻ የሽማግሌዎች አካል፣ ይህ ወንድም የጉባኤ ሽማግሌ ወይም አገልጋይ እንዲሆን የድጋፍ ሐሳብ ከማቅረብ ወደኋላ ማለት የለበትም። ሽማግሌዎች አንድን ወንድም ሲገመግሙ ከግምት የሚያስገቡት፣ ከሽማግሌዎችና ከአገልጋዮች የሚጠበቁ ቅዱስ ጽሑፋዊ ብቃቶችን ማሟላቱን እንጂ ጉባኤው የሚካሄድበትን ቋንቋ በደንብ መቻል አለመቻሉን አይደለም።—1 ጢሞ. 3:1-10, 12, 13፤ ቲቶ 1:5-9፤ w20.08 30 አን. 15-16
ሐሙስ፣ ሐምሌ 28
ወንድሞቼ ሆይ፣ ልዩ ልዩ ፈተና ሲደርስባችሁ እንደ ሙሉ ደስታ ቁጠሩት።—ያዕ. 1:2
ሰዎች ደስተኛ የሚሆኑት ጥሩ ጤና፣ ብዙ ገንዘብ ወይም ሰላማዊ የቤተሰብ ሕይወት ሲኖራቸው እንደሆነ ሊሰማቸው ይችላል። ያዕቆብ የጻፈው ግን የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታ ስለሆነው ደስታ ሲሆን ይህ ደስታ ግለሰቡ ባለበት ሁኔታ ላይ የተመካ አይደለም። (ገላ. 5:22) ለአንድ ክርስቲያን ደስታ ወይም ጥልቅ እርካታ የሚያስገኝለት ይሖዋን እያስደሰተና የኢየሱስን ምሳሌ እየተከተለ እንዳለ ማወቁ ነው። (ሉቃስ 6:22, 23፤ ቆላ. 1:10, 11) በአንድ ክርስቲያን ልብ ውስጥ ያለው ደስታ ከፋኖስ ብርሃን ጋር ሊመሳሰል ይችላል፤ የፋኖስ ብርሃን መከለያ ስላለው በቀላሉ አይጠፋም። በተመሳሳይም አንድ ክርስቲያን ጤንነቱ ቢቃወስ ወይም ገንዘብ ቢያጣም እንኳ ውስጣዊ ደስታው አይጠፋም። ከቤተሰቡ አባላት ወይም ከሌሎች የሚደርስበት ፌዝና ተቃውሞም ደስታውን አያጨልመውም። ተቃዋሚዎች ደስታውን ለማጥፋት የሚያደርጉት ጥረት ደስታውን አያደበዝዘውም፤ እንዲያውም ይበልጥ ደምቆ እንዲበራ ያደርገዋል። በእምነታችን ምክንያት የሚደርሱብን ፈተናዎች እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት እንደሆንን ያረጋግጣሉ። (ማቴ. 10:22፤ 24:9፤ ዮሐ. 15:20) ያዕቆብ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ የጻፈው በዚህ የተነሳ ነው። w21.02 28 አን. 6
ዓርብ፣ ሐምሌ 29
መልካም ቃል [ልብን] ደስ [ያሰኛል]።—ምሳሌ 12:25
መጽሐፍ ቅዱስ ስታነብብ፣ ሳይረበሹ በይሖዋ ታምኖ መኖር ያለውን አስፈላጊነት የሚያጎላ ጥቅስ ካገኘህ ጥቅሱን በቃልህ ለመያዝ ጥረት አድርግ። የጥቅሱን ሐሳብ ጮክ ብሎ ማንበብ ወይም ጥቅሱን ከጻፍከው በኋላ አልፎ አልፎ መለስ ብሎ ማየት ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። ኢያሱ ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን ከፈለገ የሕጉን መጽሐፍ አዘውትሮ በለሆሳስ ማንበብ እንዳለበት ተነግሮት ነበር። እንዲህ ማድረጉ በፍርሃት ከመሸነፍ ይልቅ የተሰጠውን ኃላፊነት በድፍረት እንዲወጣ ረድቶታል። (ኢያሱ 1:8, 9) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኙ በርካታ ጥቅሶች እንድትጨነቁ ወይም እንድትፈሩ የሚያደርጉ ሁኔታዎች ሲያጋጥሟችሁ አእምሯችሁና ልባችሁ እንዲረጋጋ ይረዷችኋል። (መዝ. 27:1-3፤ ምሳሌ 3:25, 26) በስብሰባዎች ላይ ስንገኝ ከመድረክ የሚተላለፈው ትምህርት፣ አድማጮች የሚሰጧቸው ሐሳቦች እንዲሁም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር የምናደርጋቸው የሚያንጹ ጭውውቶች በጣም ይጠቅሙናል። (ዕብ. 10:24, 25) በጉባኤ ውስጥ ላሉ የምንቀርባቸው ወዳጆቻችን ስሜታችንን አውጥተን መናገራችንም በእጅጉ ሊያበረታታን ይችላል። w21.01 6 አን. 15-16
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 30
ታማኞች ለሆኑት . . . አርዓያ ሁን።—1 ጢሞ. 4:12
ስትጠመቁ ጠንካራ እምነት እንዳላችሁና በይሖዋ እንደምትተማመኑ አሳይታችኋል። ይሖዋም የቤተሰቡ አባል የመሆን መብት በመስጠት አክብሯችኋል። ከዚህ በኋላም በይሖዋ መታመናችሁን መቀጠል ይኖርባችኋል። በሕይወታችሁ ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጡ ውሳኔዎችን ስታደርጉ በይሖዋ መታመን ቀላል ሊሆንላችሁ ይችላል። ይሁንና በሌሎች ጊዜያትስ? ከመዝናኛ ምርጫ፣ ከሰብዓዊ ሥራ እንዲሁም ከምታወጡት ግብ ጋር በተያያዘ ውሳኔዎች ስታደርጉ በይሖዋ መታመናችሁ ምንኛ አስፈላጊ ነው! በራሳችሁ ጥበብ አትመኩ። ከዚህ ይልቅ ከእናንተ ሁኔታ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ፈልጉ፤ ከዚያም በእነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ተመሩ። (ምሳሌ 3:5, 6) እንዲህ ካደረጋችሁ የይሖዋን ልብ ታስደስታላችሁ እንዲሁም በጉባኤ ያሉ ወንድሞችና እህቶችን አክብሮት ታተርፋላችሁ። እንደ ማንኛውም ሰው ሁሉ እናንተም ፍጹማን ስላልሆናችሁ አልፎ አልፎ ስህተት መሥራታችሁ አይቀርም። ሆኖም ይህ ሁኔታ በይሖዋ አገልግሎት አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ ከማድረግ ሊያግዳችሁ አይገባም። w21.03 6 አን. 14-15
እሁድ፣ ሐምሌ 31
ከአንበሳ አፍ . . . ዳንኩ።—2 ጢሞ. 4:17
ከቤተሰብህ አባላት ተቃውሞ እየደረሰብህ ነው? ወይም ደግሞ የምትኖረው በይሖዋ ሕዝቦች እንቅስቃሴ ላይ ገደብ በተጣለበት አሊያም ሥራችን ጨርሶ በታገደበት አገር ውስጥ ነው? ከሆነ 2 ጢሞቴዎስ 1:12-16ን እና 4:6-11, 17-22ን ማንበብህ ሊያበረታታህ ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የጻፈው እስር ቤት ሆኖ ነው። እነዚህን ጥቅሶች ማንበብ ከመጀመርህ በፊት፣ ስላጋጠመህ ችግርና ችግሩ ስለፈጠረብህ ስሜት ለይሖዋ ንገረው። ስሜትህን ግልጥልጥ አድርገህ ወደ ይሖዋ ጸልይ። ከዚያም ጳውሎስ ስለደረሰበት ፈተና ከሚገልጸው ታሪክ ውስጥ፣ አንተ ያጋጠመህን ፈተና ለመቋቋም የሚረዱ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማግኘት እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። ጳውሎስ ክርስቲያን በመሆኑ ስደት እንደሚደርስበት ይሖዋ አስቀድሞ ነግሮት ነበር። (ሥራ 21:11-13) ታዲያ ይሖዋ ጳውሎስን የረዳው እንዴት ነው? ይሖዋ ጸሎቱን የመለሰለት ከመሆኑም ሌላ ከጊዜ በኋላ ኃይል ሰጥቶታል። ጳውሎስ ብዙ የለፋለትን ሽልማት እንደሚያገኝ ማረጋገጫ ተሰጥቶታል። በተጨማሪም ይሖዋ የጳውሎስን ታማኝ ወዳጆች በተለያዩ መንገዶች ጳውሎስን እንዲረዱት አነሳስቷቸዋል። w21.03 17-18 አን. 14-15, 19