የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es22 ገጽ 77-87
  • ነሐሴ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ነሐሴ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2022
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 1
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 2
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 3
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 4
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 5
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 6
  • እሁድ፣ ነሐሴ 7
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 8
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 9
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 10
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 11
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 12
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 13
  • እሁድ፣ ነሐሴ 14
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 15
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 16
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 17
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 18
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 19
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 20
  • እሁድ፣ ነሐሴ 21
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 22
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 23
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 24
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 25
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 26
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 27
  • እሁድ፣ ነሐሴ 28
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 29
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 30
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2022
es22 ገጽ 77-87

ነሐሴ

ሰኞ፣ ነሐሴ 1

ከእኔ ተለይታችሁ ምንም ነገር ልታደርጉ አትችሉም።—ዮሐ. 15:5

ከቤዛው ጥቅም ማግኘት የሚችሉት ከኢየሱስ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ያላቸው ሰዎች ብቻ ናቸው። ኢየሱስ ‘ሕይወቱን ለወዳጆቹ ሲል አሳልፎ እንደሚሰጥ’ ተናግሯል። (ዮሐ. 15:13) ኢየሱስ ወደ ምድር ከመምጣቱ በፊት የኖሩ ታማኝ ሰዎች ወደፊት ስለ እሱ መማርና ለእሱ ፍቅር ማዳበር ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሰዎች ወደፊት ከሞት ይነሳሉ፤ ሆኖም እነዚህ ጻድቅ የይሖዋ አገልጋዮችም እንኳ የዘላለም ሕይወት ማግኘት የሚችሉት ከኢየሱስ ጋር ወዳጅነት ከመሠረቱ ብቻ ነው። (ዮሐ. 17:3፤ ሥራ 24:15፤ ዕብ. 11:8-12, 24-26, 31) በዛሬው ጊዜ፣ የመንግሥቱን ምሥራች በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ ከኢየሱስ ጋር የመሥራት መብት አግኝተናል። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት አስተማሪ ነበር። ወደ ሰማይ ከተመለሰ በኋላም የጉባኤው ራስ እንደመሆኑ መጠን የስብከቱንና የማስተማሩን ሥራ መምራቱን ቀጥሏል። በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች ስለ እሱና ስለ አባቱ እንዲያውቁ የምናደርገውን ጥረት ያያል፤ እንዲሁም ከፍ አድርጎ ይመለከታል። ደግሞም ይህን ሥራ ማከናወን የምንችለው ይሖዋና ኢየሱስ ከረዱን ብቻ ነው።—ዮሐ. 15:4፤ w20.04 22 አን. 7-8

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 2

እነዚህ ሁለት ነገሥታት . . . በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው እርስ በርስ ውሸት ይነጋገራሉ።—ዳን. 11:27

‘የሰሜኑ ንጉሥ’ እና “የደቡቡ ንጉሥ” የሚሉት መጠሪያዎች መጀመሪያ ላይ የሚያመለክቱት ከእስራኤል ምድር በስተ ሰሜንና በስተ ደቡብ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎችን ነበር። (ዳን. 10:14) በ33 ዓ.ም. እስከተከበረው የጴንጤቆስጤ በዓል ድረስ የአምላክ ሕዝብ የነበረው የእስራኤል ብሔር ነው። ከዚያ ወዲህ ግን ይሖዋ፣ ሕዝቡ አድርጎ የመረጠው የኢየሱስን ታማኝ ደቀ መዛሙርት እንደሆነ ግልጽ አደረገ። በመሆኑም በዳንኤል ምዕራፍ 11 ላይ የሚገኘው ትንቢት አብዛኛው ክፍል የሚገልጸው ስለ እስራኤል ብሔር ሳይሆን ስለ ክርስቶስ ተከታዮች ነው። (ሥራ 2:1-4፤ ሮም 9:6-8፤ ገላ. 6:15, 16) በተጨማሪም የሰሜኑ ንጉሥና የደቡቡ ንጉሥ ማንነት ሲለዋወጥ ቆይቷል። ያም ቢሆን ሁሉንም የሚያመሳስሏቸው ነገሮች አሉ። አንደኛ፣ ነገሥታቱ ከአምላክ ሕዝብ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ነበራቸው። ሁለተኛ፣ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ያደረሱት ነገር እውነተኛውን አምላክ ይሖዋን እንደሚጠሉ ያሳያል። ሦስተኛ፣ በሁለቱ ነገሥታት መካከል የበላይ ለመሆን የሚደረግ ሽኩቻ ነበር። w20.05 3 አን. 3-4

ረቡዕ፣ ነሐሴ 3

መሆን የምፈልገውን እሆናለሁ።—ዘፀ. 3:14

ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ በመሆን፣ የሚፈልገው እንዲሆን ያደርጋል። በተጨማሪም ይሖዋ፣ ፍጹማን ያልሆኑ ሰብዓዊ አገልጋዮቹ እሱን ለማገልገልና ዓላማውን ለመፈጸም የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንዲሆኑ ማድረግ ይችላል። (ኢሳ. 64:8) ይሖዋ በእነዚህ መንገዶች ፈቃዱ እንዲፈጸም ያደርጋል። ዓላማውን እንዳይፈጽም ሊያግደው የሚችል ምንም ነገር የለም። (ኢሳ. 46:10, 11) የሰማዩ አባታችን ባደረጋቸውና እኛም እንድናደርግ ባስቻለን ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን ለእሱ ያለን አድናቆት እንዲጨምር ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል፣ አስደናቂ በሆኑት የፍጥረት ሥራዎች ላይ ስናሰላስል ይሖዋ ባከናወናቸው ይኸውም ወደ ሕልውና እንዲመጡ ባደረጋቸው ነገሮች መደመማችን አይቀርም። (መዝ. 8:3, 4) ከዚህም ሌላ ይሖዋ የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም የሚያስፈልገንን እንድንሆን ባደረጋቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰላችን ለእሱ ጥልቅ አክብሮት እንዲያድርብን ያደርጋል። በእርግጥም ይሖዋ የሚለው ስም አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲያድርብን የሚያደርግ ነው! የአምላክ ስም ትርጉም፣ የአባታችንን አጠቃላይ ማንነት እንዲሁም እስከ ዛሬ ያደረጋቸውንና ወደፊት የሚያደርጋቸውን ነገሮች በሙሉ ያካትታል።—መዝ. 89: 7, 8፤ w20.06 9-10 አን. 6-7

ሐሙስ፣ ነሐሴ 4

ሕይወትንና እስትንፋስን . . . ለሰው ሁሉ የሚሰጠው [አምላክ ነው]።—ሥራ 17:24, 25

ኦክስጅን እኛን ጨምሮ አንዳንድ ሕያዋን ፍጥረታት በሕይወት ለመኖር የሚያስፈልጋቸው ጋዝ ነው። ሕያዋን ፍጥረታት በየዓመቱ ወደ ሰውነታቸው የሚያስገቡት ኦክስጅን መጠን መቶ ቢሊዮን ቶን እንደሚሆን ይገመታል። እነዚህ ፍጥረታት ካርቦንዳይኦክሳይድ የተባለ ጋዝ ያስወጣሉ። ሆኖም እነዚህ ፍጥረታት በምድር ላይ ያለውን ኦክስጅን አይጨርሱትም፤ እንዲሁም ከባቢ አየሩ እነሱ በሚያስወጡት ካርቦንዳይኦክሳይድ አይሞላም። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ ከትንሹ አልጌ አንስቶ እስከ ትላልቅ ዛፎች ያሉ ዕፀዋትን ፈጥሯል፤ እነዚህ ዕፀዋት ካርቦንዳይኦክሳይድን ወደ ውስጥ አስገብተው ኦክስጅንን ያስወጣሉ። በእርግጥም የኦክስጅን ዑደት በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን ሐሳብ እውነተኝነት የሚያረጋግጥ ነው። አስደናቂ ለሆነችው ፕላኔታችን እና ከእሷ ለምናገኛቸው ነገሮች አድናቆት ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? (መዝ. 115:16) ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ይሖዋ በፈጠራቸው ነገሮች ላይ ማሰላሰል ነው። ይህም ይሖዋ ለሚሰጠን መልካም ነገሮች በየዕለቱ እሱን እንድናመሰግነው ያነሳሳናል። ከዚህም ሌላ የምንኖርበትን አካባቢ በንጽሕና ለመያዝ የተቻለንን ሁሉ በማድረግ ለምድር ያለንን አድናቆት እናሳያለን። w20.05 22 አን. 5, 7

ዓርብ፣ ነሐሴ 5

በብሔራት መካከል የረከሰውን . . . ታላቅ ስሜን በእርግጥ እቀድሰዋለሁ።—ሕዝ. 36:23

ይሖዋ፣ ሰይጣን ለሰነዘረበት ነቀፋ ምላሽ የሰጠው ጥበብ፣ ትዕግሥትና ፍትሕ በሚንጸባረቅበት መንገድ ነው። ከዚህም ሌላ ገደብ የለሽ ኃይሉን በብዙ መንገዶች አሳይቷል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ያደረጋቸው ነገሮች በሙሉ ፍቅሩን የሚያሳዩ ናቸው። (1 ዮሐ. 4:8) ይሖዋ ስሙን ለመቀደስ የሚያስፈልገውን እርምጃ መውሰዱን አላቆመም። ሰይጣን በዛሬው ጊዜም የይሖዋን ስም እያጠፋ ነው። አምላክ ኃያል፣ ፍትሐዊ፣ ጥበበኛና አፍቃሪ መሆኑን እንዲጠራጠሩ በማድረግ ሰዎችን ያታልላቸዋል። ለምሳሌ ሰይጣን፣ ይሖዋ ፈጣሪ እንዳልሆነ ሰዎችን ለማሳመን ይጥራል። በአምላክ መኖር የሚያምኑ ሰዎችን ደግሞ አምላክም ሆነ መሥፈርቶቹ ከልክ በላይ ጥብቅና ምክንያታዊነት የጎደላቸው እንደሆኑ ለማሳመን ይሞክራል። ይባስ ብሎም፣ ይሖዋ ሰዎችን በገሃነመ እሳት የሚያቃጥል ጨካኝና ርኅራኄ የሌለው አምላክ እንደሆነ ሰይጣን ያስተምራል። ሰዎች እንዲህ ያለውን ውሸት ማመናቸው ቀጣዩን እርምጃ ወደ መውሰድ ይኸውም በይሖዋ የጽድቅ አገዛዝ ላይ ወደ ማመፅ ይመራቸዋል። ሰይጣን ሙሉ በሙሉ ድል እስኪደረግ ድረስ አንተንም በአምላክ ላይ እንድታምፅ ለማድረግ መሞከሩ አይቀርም። ታዲያ ይሳካለት ይሆን? w20.06 5 አን. 13-15

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 6

ግሪካዊ ወይም አይሁዳዊ፣ የተገረዘ ወይም ያልተገረዘ፣ የባዕድ አገር ሰው፣ እስኩቴስ፣ ባሪያ ወይም ነፃ ሰው ብሎ ልዩነት የለም፤ ነገር ግን ክርስቶስ ሁሉም ነገር ነው፤ እንዲሁም በሁሉም ነው።—ቆላ. 3:11

በብዙ ጉባኤዎች ውስጥ አዲስ ቋንቋ ለመማር እየታገሉ ያሉ ወንድሞችና እህቶች ይኖራሉ። እነዚህ ክርስቲያኖች ሐሳባቸውን መግለጽ ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። ያም ቢሆን ከቋንቋ ችሎታቸው ባሻገር ለመመልከት ጥረት ካደረግን ለይሖዋ ያላቸውን ፍቅርና እሱን ለማገልገል ያላቸውን ፍላጎት ማስተዋል እንችላለን። እነዚህን ግሩም ባሕርያት ካስተዋልን ደግሞ ለእነሱ ያለን ፍቅርና አክብሮት ይጨምራል። የእኛን ቋንቋ በደንብ ስለማይችሉ ብቻ “አንተ አታስፈልገኝም” አንላቸውም። (1 ቆሮ. 12:21) ይሖዋ በጉባኤው ውስጥ ቦታ እንዲኖረን በማድረግ ግሩም መብት ሰጥቶናል። ወንዶችም ሆንን ሴቶች፣ ያገባንም ሆንን ያላገባን፣ ወጣትም ሆንን አረጋዊ እንዲሁም አንድን ቋንቋ አቀላጥፈን መናገር ቻልንም አልቻልን ሁላችንም በይሖዋ ዘንድ ውድ ነን፤ አንዳችን በሌላው ዘንድም ዋጋ አለን። (ሮም 12:4, 5፤ ቆላ. 3:10) በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ እኛም ሆንን ሌሎች ያላቸውን ቦታ ከፍ አድርገን እንደምንመለከት ማሳየት የምንችልባቸውን መንገዶች መፈለጋችንን እንቀጥል። w20.08 31 አን. 20-22

እሁድ፣ ነሐሴ 7

አንዳንድ ሰዎች . . . ከእሱ ጋር በመተባበር አማኞች ሆኑ።—ሥራ 17:34

የአቴንስ ከተማ በጣዖት አምልኮ፣ በፆታ ብልግናና በአረማዊ ፍልስፍና የተሞላች ብትሆንም ሐዋርያው ጳውሎስ፣ አቴናውያኑ ደቀ መዝሙር ሊሆኑ እንደማይችሉ አላሰበም፤ የሰዎቹ ስድብም ቢሆን ተስፋ እንዲያስቆርጠው አልፈቀደም። ጳውሎስ ራሱ ‘አምላክን የሚሳደብ፣ አሳዳጅና እብሪተኛ የነበረ’ ቢሆንም በኋላ ላይ ክርስቲያን ሊሆን ችሏል። (1 ጢሞ. 1:13) ኢየሱስ፣ ጳውሎስ ወደፊት የእሱ ተከታይ ሊሆን እንደሚችል እንደተሰማው ሁሉ ጳውሎስም ለአቴናውያኑ ተመሳሳይ አመለካከት ነበረው። ደግሞም ውጤቱ እንደሚያሳየው ጳውሎስ በእነሱ ላይ እንዲህ ያለ እምነት መጣሉ ተገቢ ነበር። (ሥራ 9:13-15) በመጀመሪያው መቶ ዘመን ሁሉም ዓይነት ሰዎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሆነው ነበር። ጳውሎስ የግሪካውያን ከተማ በሆነችው በቆሮንቶስ ለሚኖሩ ክርስቲያኖች በጻፈው ደብዳቤ ላይ አንዳንድ የጉባኤው አባላት ቀደም ሲል ወንጀለኞች እንደነበሩ ወይም በሥነ ምግባር ረገድ ያዘቀጠ ሕይወት እንደነበራቸው ገልጿል። ከዚያም “አንዳንዶቻችሁም እንደዚህ ነበራችሁ። ሆኖም . . . ታጥባችሁ ነጽታችኋል” ብሏቸዋል። (1 ቆሮ. 6:9-11) እናንተ ብትሆኑ ኖሮ እነዚህ ሰዎች ተለውጠው ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ ይችላሉ ብላችሁ ታስቡ ነበር? w20.04 12 አን. 15-16

ሰኞ፣ ነሐሴ 8

አሁንስ በቅቶኛል! . . . ሕይወቴን ውሰዳት።—1 ነገ. 19:4

ሽማግሌዎች ይሖዋን ማገልገል ጠቃሚ ስለ መሆኑ ጥርጣሬ ባደረባቸው ክርስቲያኖች ላይ ለመፍረድ መቸኮል የለባቸውም። ሽማግሌዎች እነዚህን ግለሰቦች ከመንቀፍ ይልቅ ይህን አካሄድ ለመከተል ምክንያት የሆናቸውን ነገር ለመረዳት ጥረት ማድረግ አለባቸው። ሽማግሌዎች ግለሰቦቹ የሚያስፈልጋቸውን ቅዱስ ጽሑፋዊ ማበረታቻ መስጠት የሚችሉት እንዲህ ካደረጉ ብቻ ነው። ነቢዩ ኤልያስ ከንግሥት ኤልዛቤል ሸሽቶ ነበር። (1 ነገ. 19:1-3) ኤልያስ ያከናወነው ሥራ ከንቱ እንደሆነ ተሰምቶት የነበረ ከመሆኑም ሌላ ሞትን ተመኝቶ ነበር። (1 ነገ. 19:10) ይሖዋ ግን ኤልያስን ከመውቀስ ይልቅ ብቻውን እንዳልሆነ፣ በአምላክ ኃይል መተማመን እንደሚችል እንዲሁም ገና ብዙ የሚያከናውነው ሥራ እንዳለ አረጋግጦለታል። ኤልያስ የሚያሳስበውን ነገር ሲናገር ይሖዋ በደግነት ያዳመጠው ሲሆን ሌሎች ኃላፊነቶችም ሰጥቶታል። (1 ነገ. 19:11-16, 18) ከዚህ ዘገባ ምን እንማራለን? ሁላችንም በተለይ ደግሞ ሽማግሌዎች የይሖዋን በጎች በደግነት ልንይዝ ይገባል። አንድ ሰው ምሬቱን ቢገልጽ ወይም የይሖዋ ምሕረት የማይገባው ሰው እንደሆነ ቢሰማውም እንኳ ግለሰቡ የልቡን አውጥቶ ሲናገር ሽማግሌዎች ያዳምጡታል። ከዚያም በይሖዋ ፊት የላቀ ዋጋ እንዳለው በመግለጽ የጠፋውን በግ ያጽናኑታል። w20.06 22 አን. 13-14

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 9

እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው።—ምሳሌ 17:17

ይሖዋ ከጓደኞቻችንና ከቤተሰቦቻችን ጋር ጥሩ ጊዜ በማሳለፍ እንድንደሰት ይፈልጋል። (መዝ. 133:1) ኢየሱስም ጥሩ ጓደኞች ነበሩት። (ዮሐ. 15:15) መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኛ ጓደኞች ማፍራት ያለውን ጥቅም ይገልጻል። (ምሳሌ 18:24) በተጨማሪም ራስን ማግለል ጎጂ እንደሆነ ይናገራል። (ምሳሌ 18:1) ብዙዎች ማኅበራዊ ሚዲያ መጠቀም ብዙ ጓደኞች ለማግኘትና የብቸኝነት ስሜትን ለማስወገድ እንደሚረዳ ይሰማቸዋል። ይሁንና ከማኅበራዊ ሚዲያ አጠቃቀማችን ጋር በተያያዘ ጠንቃቆች መሆን ይኖርብናል። በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የወጡ ነገሮችን በማየት ብዙ ጊዜ የሚያሳልፉ ሰዎች ለብቸኝነትና ለመንፈስ ጭንቀት ሊዳረጉ እንደሚችሉ አንዳንድ ጥናቶች ያሳያሉ። ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? አንዱ ምክንያት ብዙ ሰዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ የሚያወጡት፣ ለየት ያሉ የሕይወት እንቅስቃሴዎቻቸውን የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ስለሆነ ነው፤ የራሳቸውንና የጓደኞቻቸውን ቆንጆ ፎቶግራፍ ወይም የጎበኟቸውን አስገራሚ ቦታዎች የሚያሳዩ ፎቶግራፎችን ብቻ መርጠው ያወጣሉ። እነዚህን ፎቶግራፎች የሚያይ ሰው የእሱ ሕይወት ከእነዚህ ሰዎች ሕይወት ጋር ሲነጻጸር አስደሳች እንዳልሆነ እንዲያውም አሰልቺ እንደሆነ ሊሰማው ይችላል። w20.07 5-6 አን. 12-13

ረቡዕ፣ ነሐሴ 10

ሐዋርያትና ሽማግሌዎችም ይህን ጉዳይ ለመመርመር ተሰበሰቡ።—ሥራ 15:6

የጥቅምት 1, 1988 መጠበቂያ ግንብ (እንግሊዝኛ) እንዲህ የሚል ሐሳብ ይዟል፦ “ክርስቶስ በመንፈስ ቅዱስ ተጠቅሞ፣ በሽማግሌዎች አካል ውስጥ የሚገኝን ማንኛውንም ሽማግሌ ለአንድ ሁኔታ መፍትሔ የሚሆን ወይም አንድ አስፈላጊ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳ የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓት እንዲመጣለት ሊያደርግ እንደሚችል ሽማግሌዎች ይገነዘባሉ። (ሥራ 15:7-15) መንፈስ ቅዱስ የሚያግዘው በሽማግሌዎች አካል ውስጥ ያሉትን ሁሉንም ሽማግሌዎች እንጂ አንድን ሽማግሌ ብቻ አይደለም።” አብረውት የሚያገለግሉትን ሽማግሌዎች የሚያከብር አንድ ሽማግሌ፣ በሽማግሌዎች ስብሰባ ላይ ሁልጊዜ መጀመሪያ ለመናገር አይሞክርም። በውይይቱ ላይ እሱ ብቻ ተናጋሪ ከመሆን ይቆጠባል፤ እንዲሁም የእሱ አመለካከት ምንጊዜም ቢሆን ትክክል እንደሆነ አያስብም። ከዚህ ይልቅ ሐሳቡን የሚገልጸው በትሕትና እና ልኩን እንደሚያውቅ በሚያሳይ መንገድ ነው። ሌሎች ሽማግሌዎች የሚሰጡትን ሐሳብ በትኩረት ያዳምጣል። ከሁሉ በላይ ደግሞ ቅዱስ ጽሑፋዊ መሠረታዊ ሥርዓቶችን ለማካፈል እንዲሁም “ታማኝና ልባም ባሪያ” የሰጠውን መመሪያ ለመከተል ይጥራል። (ማቴ. 24:45-47) ሽማግሌዎች ስብሰባቸውን የሚያደርጉት ፍቅርና አክብሮት በሰፈነበት መንገድ ከሆነ የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በመካከላቸው ይኖራል፤ ይህ መንፈስ ደግሞ ትክክለኛ ውሳኔዎችን ለማድረግ ይረዳቸዋል።—ያዕ. 3:17, 18፤ w20.08 27 አን. 5-6

ሐሙስ፣ ነሐሴ 11

ምንጊዜም ክፉውን በመልካም አሸንፍ።—ሮም 12:21

የሐዋርያው ጳውሎስ ጠላቶች ከእሱ ይልቅ እጅግ ኃያላን ነበሩ። በተደጋጋሚ አስደብድበውታል እንዲሁም እስር ቤት ወርውረውታል። በተጨማሪም ጳውሎስ ወዳጆቹ ሊሆኑ በሚገባቸው ሰዎች በደል ደርሶበታል። በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩ አንዳንድ ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ተቃውመውታል። (2 ቆሮ. 12:11፤ ፊልጵ. 3:18) ሆኖም ጳውሎስ ተቃዋሚዎቹን በሙሉ ድል አድርጓል። እንዴት? ተቃውሞ ቢደርስበትም መስበኩን አላቆመም። ወንድሞቹና እህቶቹ ቢያሳዝኑትም እንኳ ለእነሱ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። ከሁሉ በላይ ደግሞ እስከ ሕይወቱ ፍጻሜ ድረስ ለአምላክ ታማኝ ሆኗል። (2 ጢሞ. 4:8) ይህን ሁሉ ማድረግ የቻለው በራሱ ብርታት ሳይሆን በይሖዋ በመታመኑ ነው። እናንተስ ስድብና ስደት ይደርስባችኋል? ዓላማችሁ በሌሎች ልብና አእምሮ ውስጥ የአምላክን ቃል ማስረጽ ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ተጠቅማችሁ የሰዎችን ጥያቄ በመመለስ፣ በደል የሚያደርሱባችሁን ሰዎች በአክብሮትና በደግነት በመያዝ እንዲሁም ጠላቶቻችሁን ጨምሮ ለሁሉም ሰው መልካም በማድረግ ይህን ግብ ማሳካት ትችላላችሁ።—ማቴ. 5:44፤ 1 ጴጥ. 3:15-17፤ w20.07 17-18 አን. 14-15

ዓርብ፣ ነሐሴ 12

ትሕትናህ . . . ታላቅ ያደርገኛል።—2 ሳሙ. 22:36

ይሖዋ ትሑት እንደሆነ መናገር እንችላለን? አዎን። ዳዊትም በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ይህን ሐሳብ ተናግሯል። (መዝ. 18:35) ዳዊት ይህን ሲጽፍ፣ ነቢዩ ሳሙኤል የእስራኤል ንጉሥ የሚሆነውን ሰው ለመቀባት ወደ ቤታቸው የመጣበትን ቀን አስታውሶ ሊሆን ይችላል። ዳዊት ከስምንት ወንዶች ልጆች የመጨረሻው ነበር፤ ሆኖም በንጉሥ ሳኦል ቦታ እንዲነግሥ ይሖዋ የቀባው እሱን ነበር። (1 ሳሙ. 16:1, 10-13) አንድ መዝሙራዊ ስለ ይሖዋ እንዲህ ሲል ዘምሯል፦ “ሰማይንና ምድርን ለማየት ወደ ታች ያጎነብሳል፤ ችግረኛውን ከአፈር ያነሳል። ድሃውን . . . ብድግ ያደርገዋል፤ ይህም ከታላላቅ ሰዎች . . . ጋር ያስቀምጠው ዘንድ ነው።” ዳዊት ከዚህ መዝሙራዊ ጋር እንደሚስማማ ጥርጥር የለውም። (መዝ. 113:6-8) ይሖዋ ፍጹማን ያልሆኑ ሰብዓዊ አገልጋዮቹን የያዘበት መንገድ ትሑት መሆኑን ያረጋግጣል። እሱን እንድናመልከው መፍቀድ ብቻ ሳይሆን ወዳጆቹ አድርጎም ይመለከተናል። (መዝ. 25:14) ይሖዋ ቅድሚያውን ወስዶ፣ ከእሱ ጋር ወዳጅነት ለመመሥረት የሚያስችለንን መንገድ ከፍቷል፤ ይህን ያደረገው ለኃጢአታችን መሥዋዕት እንዲሆን ልጁን በመስጠት ነው። ይሖዋ ያሳየን ምሕረትና ርኅራኄ እንዴት ታላቅ ነው! w20.08 8 አን. 1-3

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 13

[ይሖዋ] ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ [አይፈልግም]።—2 ጴጥ. 3:9

ይሖዋ ይህንን አሮጌ ሥርዓት የሚያጠፋበትን ቀንና ሰዓት ወስኗል። (ማቴ. 24:36) ይህ ጊዜ ከመድረሱ በፊት ትዕግሥቱ አልቆ እርምጃ አይወስድም። ሙታንን ለማስነሳት ቢናፍቅም ይታገሣል። (ኢዮብ 14:14, 15) እነሱን ለማስነሳት የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ እየጠበቀ ነው። (ዮሐ. 5:28) ለይሖዋ ትዕግሥት አመስጋኝ እንድንሆን የሚያነሳሱን ምክንያቶች አሉ። እስቲ አስበው፦ እኛን ጨምሮ ብዙ ሰዎች ‘ለንስሐ ለመብቃት’ የሚያስችል ጊዜ ያገኙት ይሖዋ ታጋሽ ስለሆነ ነው። ይሖዋ፣ በተቻለ መጠን በርካታ ሰዎች የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ እንዲከፈትላቸው ይፈልጋል። እንግዲያው እኛም የእሱን ትዕግሥት እንደምናደንቅ እናሳይ። እንዴት? “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ” ያላቸውን ሰዎች በትጋት በመፈለግ እንዲሁም ይሖዋን እንዲወዱትና እንዲያገለግሉት በመርዳት ነው። (ሥራ 13:48) በዚህ መንገድ እነሱም እንደ እኛ ከይሖዋ ትዕግሥት ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንረዳቸዋለን። w20.08 18 አን. 17

እሁድ፣ ነሐሴ 14

ይሖዋ ሆይ፣ መንገድህን አሳውቀኝ፤ ጎዳናህንም አስተምረኝ።—መዝ. 25:4

አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪ በጥናቱ ላይ የሚማረው ነገር የጭንቅላት እውቀት ከመሆን ባለፈ ልቡን ሊነካው ይገባል። ለምን? ምክንያቱም ለተግባር የሚያነሳሳን ልባችን ነው፤ ልባችን ምኞታችንን፣ ስሜታችንን እና ዝንባሌያችንን ያካትታል። ኢየሱስ የሰዎችን ግንዛቤ በሚያሰፋ መንገድ ያስተምር ነበር። ሰዎች እሱን የተከተሉት ግን ያስተማራቸው ነገር ልባቸውን ስለነካው ነው። (ሉቃስ 24:15, 27, 32) ጥናትህ ይሖዋ እውን እንዲሆንለት፣ ከእሱ ጋር ዝምድና መመሥረት እንደሚችል እንዲሰማው እንዲሁም እሱን አባቱ፣ አምላኩና ወዳጁ አድርጎ እንዲያየው ልትረዳው ይገባል። (መዝ. 25:5) በምታጠኑበት ወቅት የአምላክ ባሕርያት ጎልተው እንዲወጡ አድርግ። (ዘፀ. 34:5, 6፤ 1 ጴጥ. 5:6, 7) የምትወያዩት በየትኛውም ርዕሰ ጉዳይ ላይ ቢሆን በይሖዋ ማንነት ላይ ትኩረት አድርግ። ተማሪው ስለ ይሖዋ ግሩም ባሕርያት እንዲያውቅ ይኸውም ፍቅሩን፣ ደግነቱን እና ርኅራኄውን እንዲገነዘብ እርዳው። ኢየሱስ ‘ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ ይሖዋን መውደድ’ እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴ. 22:37, 38) እንግዲያው ጥናትህ ይሖዋን ከልቡ እንዲወደው ለመርዳት ጥረት አድርግ። w20.10 10 አን. 12

ሰኞ፣ ነሐሴ 15

ኢየሱስ ማርታንና እህቷን እንዲሁም አልዓዛርን ይወዳቸው ነበር።—ዮሐ. 11:5

ኢየሱስ ሁሉንም ሴቶች በአክብሮት ይይዝ ነበር። (ዮሐ. 4:27) በተለይ ደግሞ የአባቱን ፈቃድ ለሚያደርጉ ሴቶች ልዩ አክብሮት ነበረው። እንደ እህቶቹ አድርጎ ይመለከታቸው የነበረ ከመሆኑም ሌላ የመንፈሳዊ ቤተሰቡ አባላት አድርጎ ከሚቆጥራቸው ወንዶች ጋር አብሮ ጠቅሷቸዋል። (ማቴ. 12:50) በተጨማሪም ኢየሱስ እውነተኛ ወዳጅ ሆኖላቸዋል። ከማርያምና ከማርታ ጋር የነበረውን ወዳጅነት እንደ ምሳሌ እንመልከት፤ ሁለቱም ነጠላ የነበሩ ይመስላል። (ሉቃስ 10:38-42) ኢየሱስ በንግግሩም ሆነ በድርጊቱ ነፃነት ተሰምቷቸው እንዲቀርቡት አድርጓቸው መሆን አለበት። ማርያም አንድ ደቀ መዝሙር እንደሚያደርገው ሳትፈራ እግሩ ሥር ተቀምጣለች። ማርታም ብትሆን ማርያም ስላላገዘቻት በተበሳጨችበት ወቅት፣ ስሜቷን ለኢየሱስ በነፃነት ነግራዋለች። በዚህ ግብዣ ላይ ኢየሱስ ሁለቱንም ሴቶች በመንፈሳዊ ለመርዳት አጋጣሚውን ተጠቅሞበታል። በተጨማሪም እነዚህን ሴቶችም ሆነ ወንድማቸውን አልዓዛርን በሌሎች አጋጣሚዎችም ሄዶ በመጠየቅ እንደሚያስብላቸው አሳይቷል። (ዮሐ. 12:1-3) አልዓዛር በጠና በታመመበት ወቅት ማርያምና ማርታ የኢየሱስን እርዳታ ለመጠየቅ ያልተሳቀቁት ለዚህ ነው።—ዮሐ. 11:3፤ w20.09 20 አን. 3፤ 21 አን. 6

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 16

የአምላክ መንግሥት ወዲያውኑ የሚገለጥ [መሰላቸው]።—ሉቃስ 19:11

የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የአምላክ መንግሥት ‘ወዲያውኑ እንደሚገለጥ’ እና ከሮም ጭቆና ነፃ እንደሚያወጣቸው ተስፋ አድርገው ነበር። እኛ ደግሞ የአምላክ መንግሥት ክፋትን አስወግዶ ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም የሚያመጣበትን ጊዜ እንናፍቃለን። (2 ጴጥ. 3:13) ይሁንና ትዕግሥት ማዳበርና ይሖዋ የወሰነው ጊዜ እስኪደርስ መጠበቅ ይኖርብናል። ይሖዋ፣ ኖኅ መርከቡን ለመገንባትና “የጽድቅ ሰባኪ” ሆኖ ለማገልገል የሚያስችል በቂ ጊዜ እንዲያገኝ አድርጓል። (2 ጴጥ. 2:5፤ 1 ጴጥ. 3:20) ክፉ የሆኑትን የሰዶምና ገሞራ ነዋሪዎች ለማጥፋት ስላደረገው ውሳኔ አብርሃም በተደጋጋሚ ጥያቄ ሲያቀርብለት ይሖዋ አዳምጦታል። (ዘፍ. 18:20-33) ይሖዋ ዓመፀኛ የሆነውን የእስራኤል ብሔር ለበርካታ ዘመናት ብዙ ታግሦታል። (ነህ. 9:30, 31) ዛሬም ይሖዋ ወደ ራሱ የሚስባቸው ሰዎች ሁሉ ‘ለንስሐ እንዲበቁ’ ጊዜ መስጠቱ ትዕግሥቱን ያሳያል። (2 ጴጥ. 3:9፤ ዮሐ. 6:44፤ 1 ጢሞ. 2:3, 4) ይሖዋ የተወው ምሳሌ እኛም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ስንካፈል ትዕግሥት ማሳየታችንን እንድንቀጥል ያነሳሳናል። w20.09 10 አን. 8-9

ረቡዕ፣ ነሐሴ 17

ከሞት [ይነሳሉ]።—ሥራ 24:15

ይሖዋ ሰዎችን ከሞት ሲያስነሳ አእምሯቸው ውስጥ ያሉትን መረጃዎች እና የማንነታቸው መለያ የሆኑትን ነገሮች ይዘው እንዲነሱ ያደርጋል። ይህ ምን ማለት እንደሆነ እስቲ አስበው። ይሖዋ በጣም ስለሚወድህ የምታስበውን፣ የሚሰማህን፣ የምትናገረውንና የምታደርገውን እያንዳንዱን ነገር ያስተውላል እንዲሁም ያስታውሳል። በመሆኑም አንተም በትንሣኤ ከሚነሱት ሰዎች መካከል ብትሆን አእምሮህ ውስጥ ያሉትን መረጃዎች፣ አመለካከትህንና የማንነትህ መለያ የሆኑትን ነገሮች በሙሉ ይዘህ እንድትነሳ ማድረግ አይከብደውም። ንጉሥ ዳዊት፣ ይሖዋ እያንዳንዳችንን ምን ያህል በጥልቀት እንደሚያውቀን ተገንዝቦ ነበር። (መዝ. 139:1-4) ታዲያ ይሖዋ ምን ያህል እንደሚያውቀን መገንዘባችን በአሁኑ ወቅት ምን ስሜት ይፈጥርብናል? ይሖዋ ምን ያህል እንደሚያውቀን ማሰላሰላችን ሊያስጨንቀን አይገባም። ለምን? ይሖዋ በጥልቅ እንደሚያስብልን እናስታውስ። እያንዳንዳችንን ልዩ እንደሆንን አድርጎ ይመለከተናል። ማንነታችንን የሚቀርጹ የሕይወት ገጠመኞቻችንን በሚገባ ያስተውላል። ይህን ማወቃችን ምንኛ የሚያጽናና ነው! መቼም ቢሆን ብቻችንን እንደሆንን ሊሰማን አይገባም። በእያንዳንዱ ቀንና ሴኮንድ ይሖዋ አብሮን ነው፤ ምንጊዜም እኛን ለመርዳት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ይፈልጋል።—2 ዜና 16:9፤ w20.08 17 አን. 13-14

ሐሙስ፣ ነሐሴ 18

ጥልቅ ማስተዋል እሰጥሃለሁ፤ ልትሄድበት የሚገባውንም መንገድ አስተምርሃለሁ።—መዝ. 32:8

ይሖዋ ሕዝቡን ማስተማር ያስደስተዋል። እሱን እንዲያውቁት፣ እንዲወዱትና የተወደዱ ልጆቹ ሆነው ለዘላለም እንዲኖሩ ይፈልጋል። ይሖዋ ሕዝቡን ባያስተምር ኖሮ እነዚህ ነገሮች እውን ሊሆኑ አይችሉም ነበር። (ዮሐ. 17:3) ይሖዋ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረውን የክርስቲያን ጉባኤ ሕዝቡን ለማስተማር ተጠቅሞበታል። (ቆላ. 1:9, 10) ኢየሱስ ቃል የገባው “ረዳት” ማለትም መንፈስ ቅዱስ በዚህ ረገድ ትልቅ ሚና ተጫውቷል። (ዮሐ. 14:16) ደቀ መዛሙርቱ የአምላክን ቃል ይበልጥ ማስተዋል እንዲችሉ እንዲሁም ኢየሱስ የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን በርካታ ነገሮች እንዲያስታውሱ ረድቷቸዋል። ከጊዜ በኋላም እነዚህን ነገሮች በወንጌል ዘገባዎች ላይ አስፍረዋቸዋል። በዚህ መልኩ የተገኘው እውቀት በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩትን ክርስቲያኖች እምነት ለማጠናከር እንዲሁም ለአምላክ፣ ለልጁ ብሎም አንዳቸው ለሌላው ያላቸውን ፍቅር ለማሳደግ አስችሏል። ይሖዋ “በዘመኑ መጨረሻ” ላይ ከብሔራት ሁሉ የተውጣጡ ሰዎች ስለ መንገዶቹ ለመማር ወደ እሱ ምሳሌያዊ ተራራ እንደሚጎርፉ አስቀድሞ ተናግሯል። (ኢሳ. 2:2, 3) በዛሬው ጊዜ ይህ ትንቢት ፍጻሜውን ሲያገኝ እያየን ነው። w20.10 24 አን. 14-15

ዓርብ፣ ነሐሴ 19

ማስተዋል ያለው ሰው . . . ጥበብ ያለበትን መመሪያ ይቀበላል።—ምሳሌ 1:5

አንድ ሰው ከሚወደው ወዳጁ የሚሰጠውን ጥሩ ምክር እንዳይቀበል እንቅፋት የሚሆንበት አንዱ ነገር ምንድን ነው? ኩራት ነው። ኩሩ ሰዎች መስማት የሚፈልጉት ‘ጆሯቸውን የሚኮረኩርላቸውን’ ነገር ነው። “እውነትን ከመስማት ጆሯቸውን ይመልሳሉ።” (2 ጢሞ. 4:3, 4) ለራሳቸው አመለካከት ትልቅ ቦታ ይሰጣሉ፤ ከሌሎች የተሻሉ እንደሆኑም ያስባሉ። ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ “አንድ ሰው ምንም ሳይሆን ራሱን ከፍ አድርጎ የሚመለከት ከሆነ ራሱን እያታለለ ነው” ሲል ጽፏል። (ገላ. 6:3) ንጉሥ ሰለሞንም ነጥቡን ጥሩ አድርጎ አስቀምጦታል፤ እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “የተሰጠውን ማስጠንቀቂያ ተግባራዊ እንዳያደርግ ማስተዋል ከጎደለው በዕድሜ የገፋ ሞኝ ንጉሥ ይልቅ ድሃ የሆነ ጥበበኛ ልጅ ይሻላል።” (መክ. 4:13) እስቲ ሐዋርያው ጴጥሮስ የተወውን ምሳሌ እንመልከት፤ በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ በሰዎች ፊት ለጴጥሮስ እርማት ሰጥቶት ነበር። (ገላ. 2:11-14) ጴጥሮስ ትኩረት ያደረገው እርማቱ በተሰጠበት መንገድ ወይም በሰው ፊት በመሰጠቱ ላይ ቢሆን ኖሮ ጳውሎስ በተናገረው ነገር ቅር ሊሰኝ ይችል ነበር። ሆኖም ጴጥሮስ ጥበበኛ ነበር። ምክሩን ተቀብሏል፤ በጳውሎስ ላይም ቂም አልያዘም። እንዲያውም ከጊዜ በኋላ ስለ ጳውሎስ ሲናገር “የተወደደው ወንድማችን” በማለት ጠርቶታል።—2 ጴጥ. 3:15፤ w20.11 21 አን. 9, 11-12

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 20

እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።—ማቴ. 28:20

የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክተው ምንድን ነው? በክርስቲያናዊ ስብሰባዎቻችን ላይ መገኘታቸው ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በስብሰባዎቻችን ላይ የሚያገኙት ቅዱስ ጽሑፋዊ ትምህርት እውቀታቸው እንዲያድግ፣ እምነታቸው እንዲጠነክር እንዲሁም ለአምላክ ያላቸው ፍቅር እንዲጨምር ያደርጋል። (ሥራ 15:30-32) በተጨማሪም አስፋፊዎች ለይሖዋ ያላቸው ፍቅር እያደገ መሄዱ ትእዛዛቱን ለመጠበቅ እንዴት እንደረዳቸው ለተማሪዎች ሊነግሯቸው ይችላሉ። (2 ቆሮ. 7:1፤ ፊልጵ. 4:13) ከዚህም ሌላ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ወደ ስብሰባ ሲመጡ የተለያየ ሁኔታ ካላቸው ታማኝ አስፋፊዎች ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚ ያገኛሉ፤ የእነሱን ምሳሌ መመልከታቸው፣ አምላክንና ባልንጀራችንን እንድንወድ ክርስቶስ የሰጠውን ትእዛዝ መጠበቅ ምን እንደሚጠይቅ ለመማር ያስችላቸዋል። (ዮሐ. 13:35፤ 1 ጢሞ. 4:12) እንደ እነሱ ዓይነት ተፈታታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁመው ያሉ አስፋፊዎች እንዳሉና የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ለመሆን የሚያስፈልጉትን ማስተካከያዎች ማድረግ ከአቅማቸው በላይ እንዳልሆነ ይማራሉ። (ዘዳ. 30:11) በእርግጥም በጉባኤ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ክርስቲያን፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች መንፈሳዊ እድገት እንዲያደርጉ በተለያዩ መንገዶች አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላል።—ማቴ. 5:16፤ w20.11 5 አን. 10-12

እሁድ፣ ነሐሴ 21

በኤፌሶን ከአውሬዎች ጋር [ታግያለሁ]።—1 ቆሮ. 15:32

ሐዋርያው ጳውሎስ ምናልባት በኤፌሶን በሚገኝ ስታዲየም ውስጥ ቃል በቃል ከእንስሳት ጋር እንደታገለ መግለጹ ሊሆን ይችላል። (2 ቆሮ. 1:8፤ 4:10፤ 11:23) ወይም ደግሞ እንደ “አውሬ” ጨካኝ የሆኑ አይሁዳውያን ወይም ሌሎች ሰዎች ያደረሱበትን ተቃውሞ እየገለጸ ሊሆን ይችላል። (ሥራ 19:26-34፤ 1 ቆሮ. 16:9) ሁኔታው ምንም ይሁን ምን፣ ጳውሎስ ከባድ መከራዎችን ተጋፍጧል፤ ይሁን እንጂ ስለ ወደፊቱ ጊዜ አዎንታዊ አመለካከት ይዞ ቀጥሏል። (1 ቆሮ. 15:30, 31፤ 2 ቆሮ. 4:16-18) የምንኖረው አደገኛ በሆነ ዘመን ውስጥ ነው። አንዳንድ ወንድሞቻችን የወንጀል ሰለባ ሆነዋል። በጦርነት በሚታመስ አካባቢ የሚኖሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ሕይወታቸው ሁልጊዜ አደጋ ላይ ነው። ሌሎች ደግሞ የሚኖሩት በስብከቱ ሥራችን ላይ አንዳንድ ገደቦች በተጣሉባቸው አልፎ ተርፎም ሥራችን ጨርሶ በታገደባቸው አገሮች ውስጥ ነው። በዚህም የተነሳ ይሖዋን የሚያገለግሉት ሕይወታቸውን ወይም ነፃነታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ነው። ያም ቢሆን እነዚህ ወንድሞችና እህቶች በሙሉ በጽናት ይሖዋን ማምለካቸውን ቀጥለዋል፤ በዚህም ግሩም ምሳሌ ሆነውልናል። በዚህ ሥርዓት ሕይወታቸውን ቢያጡም እንኳ ይሖዋ ወደፊት የላቀ ነገር እንደሚሰጣቸው ስለሚያውቁ አይፈሩም። w20.12 9 አን. 3-4

ሰኞ፣ ነሐሴ 22

እኛ ከአምላክ ጋር አብረን የምንሠራ [ነን]። እናንተ በመልማት ላይ ያለ የአምላክ እርሻ ናችሁ፤ የአምላክ ሕንፃ ናችሁ።—1 ቆሮ. 3:9

የምታገለግልበት ክልል ፍሬያማ እንዳልሆነ ስለተሰማህ ወይም ሰዎችን ቤታቸው ማግኘት ባለመቻልህ ምክንያት ተስፋ የቆረጥክበት ጊዜ አለ? እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን ደስታችንን ጠብቀን ለመቀጠል አልፎ ተርፎም ይበልጥ ደስተኛ ለመሆን ምን ሊረዳን ይችላል? ለአገልግሎት ተገቢውን አመለካከት መያዝ ጠቃሚ ነው። ይህ ምን ማለት ነው? የስብከታችን ዋነኛ ዓላማ የአምላክን ስም እና መንግሥቱን ማሳወቅ እንደሆነ አንዘንጋ። ኢየሱስ የሕይወትን መንገድ የሚያገኙት በአንጻራዊ ሁኔታ ጥቂት ሰዎች እንደሆኑ በግልጽ ተናግሯል። (ማቴ. 7:13, 14) አገልግሎት ስንወጣ ከይሖዋ፣ ከኢየሱስ እንዲሁም ከመላእክት ጋር አብሮ የመሥራት መብት እናገኛለን። (ማቴ. 28:19, 20፤ ራእይ 14:6, 7) ይሖዋ የዘላለም ሕይወት የሚገባቸውን ሰዎች ወደ ራሱ ይስባል። (ዮሐ. 6:44) ስለዚህ አንድ ሰው ስናነጋግረው ለመልእክታችን ጥሩ ምላሽ ባይሰጥም እንኳ በሌላ ጊዜ ስንሄድ ጆሮ ሊሰጠን ይችላል። ዲቦራ የተባለች እህት “ተስፋ መቁረጥ ሰይጣን የሚጠቀምበት ኃይለኛ መሣሪያ ነው” በማለት ተናግራለች። ሆኖም አምላካችን ይሖዋ፣ ሰይጣን ከሚጠቀምበት ከማንኛውም መሣሪያ የሚበልጥ ኃይል አለው። w20.12 26 አን. 18-19፤ 27 አን. 21

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 23

እርስ በርስ መዋደዳችንን እንቀጥል፤ ምክንያቱም ፍቅር ከአምላክ ነው።—1 ዮሐ. 4:7

ብዙ ታማኝ ክርስቲያኖች ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን ለማስተዳደር የሙሉ ጊዜ ሥራ መሥራት ያስፈልጋቸዋል። ያም ቢሆን እነዚህ ታማኝ አስፋፊዎች በቻሉት ሁሉ የአምላክን ድርጅት ለመደገፍ ጥረት ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንዶች በእርዳታ ሥራ እንዲሁም በግንባታ ፕሮጀክቶች ላይ እገዛ ያበረክታሉ፤ እንዲሁም ሁሉም አስፋፊዎች ለዓለም አቀፉ ሥራ የገንዘብ መዋጮ ማድረግ ይችላሉ። እንዲህ እንዲያደርጉ የሚያነሳሳቸው ለአምላክና ለባልንጀራቸው ያላቸው ፍቅር ነው። ሁላችንም በየሳምንቱ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘትና ተሳትፎ በማድረግ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለንን ፍቅር በተግባር እናሳያለን። ድካም ቢሰማንም ከስብሰባ አንቀርም። በስብሰባ ላይ ሐሳብ መስጠት ቢያስፈራንም እንዲህ ከማድረግ ወደኋላ አንልም። እንዲሁም ሁላችንም የየራሳችን ችግሮች ያሉብን ቢሆንም ከስብሰባ በፊት ወይም በኋላ ሌሎችን ለማበረታታት ጥረት እናደርጋለን። (ዕብ. 10:24, 25) ውድ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ለሚያከናውኑት ሥራ ምንኛ አመስጋኞች ነን! w21.01 10 አን. 11

ረቡዕ፣ ነሐሴ 24

በከንቱ አንመካ።—ገላ. 5:26

ኩሩ የሆኑ ሰዎች እነሱ ራሳቸው እንዲመሰገኑ ስለሚፈልጉ ሌሎችን ማመስገን ይተናነቃቸዋል። ብዙውን ጊዜ ራሳቸውን ከሌሎች ጋር ስለሚያወዳድሩ የፉክክር መንፈስ እንዲፈጠር ያደርጋሉ። ሌሎችን ከማሠልጠንና ለእነሱ ኃላፊነት ከመስጠት ይልቅ ‘አንድ ሥራ በትክክል እንዲሠራ እኔው ራሴ ባከናውነው ይሻላል’ የሚል አመለካከት አላቸው፤ ትክክለኛ መንገድ ብለው የሚያስቡት ደግሞ እነሱ የሚፈልጉትን መንገድ ነው። ኩሩ የሆነ ሰው በአብዛኛው ከሌሎች ልቆ መታየት የሚፈልግ ሲሆን ቅናተኛ ነው። በውስጣችን ኩራት እንዳለ ካስተዋልን ‘አእምሯችንን በማደስ ለመለወጥ’ እንዲረዳን አጥብቀን ይሖዋን እንለምነው፤ እንዲህ ማድረጋችን ይህን ጎጂ ባሕርይ በውስጣችን ሥር ሳይሰድድ ለማስወገድ ያስችለናል። (ሮም 12:2) ይሖዋ ለተወልን ግሩም ምሳሌ ምንኛ አመስጋኞች ነን! (መዝ. 18:35) አገልጋዮቹን የሚይዝበት መንገድ ትሑት እንደሆነ ያሳያል፤ እኛም የእሱን ምሳሌ መከተል እንፈልጋለን። በተጨማሪም ልካቸውን አውቀው ከአምላክ ጋር የሄዱ ሰዎች ግሩም ምሳሌ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሰፍሮልናል፤ የእነሱን ምሳሌም መከተል እንፈልጋለን። እንግዲያው ለይሖዋ የሚገባውን ግርማና ክብር ምንጊዜም እንስጠው።—ራእይ 4:11፤ w20.08 13 አን. 19-20

ሐሙስ፣ ነሐሴ 25

የሚያገቡ ሰዎች በሥጋቸው ላይ መከራ ይደርስባቸዋል።—1 ቆሮ. 7:28

ትዳር ፍጹም የሆነ የአምላክ ስጦታ ነው፤ ሰዎች ግን ፍጹማን አይደሉም። (1 ዮሐ. 1:8) የአምላክ ቃል፣ ባለትዳሮች ‘በሥጋቸው ላይ መከራ እንደሚደርስባቸው’ በመግለጽ ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንደሚገጥሟቸው የሚያስጠነቅቃቸው ለዚህ ነው። ይሖዋ፣ ክርስቲያን ባሎች የቤተሰቡን መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና ቁሳዊ ፍላጎት እንዲያሟሉ ይጠብቅባቸዋል። (1 ጢሞ. 5:8) ሆኖም ያገቡ እህቶች በየቀኑ የአምላክን ቃል ለማንበብና ባነበቡት ነገር ላይ ለማሰላሰል እንዲሁም ወደ ይሖዋ ልባዊ ጸሎት ለማቅረብ ከተጣበበው ፕሮግራማቸው ላይ የተወሰነ ጊዜ መመደብ ይኖርባቸዋል። ይህ ተፈታታኝ ሊሆን ይችላል። ሚስቶች ሥራ ቢበዛባቸውም ጊዜ መድበው እንዲህ ማድረጋቸው የግድ አስፈላጊ ነው። ለምን? ምክንያቱም ይሖዋ እያንዳንዳችን ከእሱ ጋር በግለሰብ ደረጃ ወዳጅነት እንድንመሠርትና ይህን ወዳጅነት ጠብቀን እንድንኖር ይፈልጋል። (ሥራ 17:27) አንዲት ሚስት ፍጹም ላልሆነው ባሏ መገዛት ብዙ ጥረት ቢጠይቅባት የሚያስገርም አይደለም። ይሁንና ለባሏ እንድትገዛ የሚያነሳሷትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ምክንያቶች ማወቋና አምና መቀበሏ ይሖዋ የሰጣትን ድርሻ መወጣት ቀላል እንዲሆንላት ያደርጋል። w21.02 9 አን. 3, 6-7

ዓርብ፣ ነሐሴ 26

ተፈትኖ የተረጋገጠው እምነታችሁ ጽናት [ያስገኛል]።—ያዕ. 1:3

ፈተናዎች ብረት ቀጥቃጮች ብረትን ለማጠንከር ከሚጠቀሙበት ሂደት ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። ብረት ቀጥቃጮች ብረቱን እሳት ውስጥ ከትተው ካጋሉት በኋላ አውጥተው ያቀዘቅዙታል፤ ይህ ሂደት ብረቱ እየጠነከረ እንዲሄድ ያደርጋል። በተመሳሳይም በፈተና ውስጥ ስናልፍ እምነታችን ይጠናከራል። ያዕቆብ “በሁሉም ረገድ . . . ፍጹማንና እንከን የለሽ እንድትሆኑ ጽናት ሥራውን ሙሉ በሙሉ ይፈጽም” በማለት የጻፈው ለዚህ ነው። (ያዕ. 1:4) የሚያጋጥሙን ፈተናዎች እምነታችንን እንደሚያጠነክሩት ስናይ በደስታ መጽናት ቀላል ይሆንልናል። ያዕቆብ ደስታችንን ሊያሳጡን የሚችሉ አንዳንድ ነገሮችንም በደብዳቤው ላይ ጠቅሷል። አንዱ ተፈታታኝ ሁኔታ ምን ማድረግ እንዳለብን አለማወቅ ነው። ፈተና ሲደርስብን ይሖዋን የሚያስደስት፣ ወንድሞቻችንንና እህቶቻችንን የሚጠቅም እንዲሁም ንጹሕ አቋማችንን ለመጠበቅ የሚረዳ ውሳኔ ማድረግ እንፈልጋለን፤ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ለማድረግ ግን የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል። (ኤር. 10:23) ምን ማድረግ እንዳለብንና ለተቃዋሚዎቻችን ምን መልስ እንደምንሰጥ ለማወቅ ጥበብ ያስፈልገናል። ምን ማድረግ እንዳለብን ካላወቅን ሁኔታው ከአቅማችን በላይ እንደሆነ ሊሰማን ይችላል፤ ይህ ደግሞ ደስታችንን ሊያሳጣን ይችላል። w21.02 28 አን. 7-9

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 27

እርስ በርሳችሁ አጥብቃችሁ ከልብ ተዋደዱ።—1 ጴጥ. 1:22

ይሖዋ ምሳሌ ትቶልናል። እሱ ለእኛ ያለው ፍቅር በጣም ጥልቅ ነው፤ እኛ ታማኝነታችንን እስከጠበቅን ድረስ እሱ ለእኛ ያለውን ፍቅር ሊበጥሰው የሚችል ነገር የለም። (ሮም 8:38, 39) “አጥብቃችሁ” ተብሎ የተተረጎመው ግሪክኛ ቃል “በኃይል መንጠራራት” የሚል ሐሳብ በውስጡ ይዟል። የእምነት ባልንጀራችንን ከልብ ለመውደድ በኃይል መንጠራራት የሚያስፈልገን ጊዜ ሊኖር ይችላል። ሌሎች ቅር ሲያሰኙን ‘እርስ በርሳችን በፍቅር መቻቻልና’ “አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት” ማድረግ ያስፈልገናል። (ኤፌ. 4:1-3) በወንድሞቻችን ድክመቶች ላይ ትኩረት አናደርግም፤ እንዲሁም ወንድሞቻችንን በይሖዋ ዓይን ለማየት የቻልነውን ሁሉ ጥረት እናደርጋለን። (1 ሳሙ. 16:7፤ መዝ. 130:3) ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ልባዊ ፍቅር ማሳየት ሁልጊዜ ቀላል ነው ማለት አይደለም፤ በተለይ ድክመቶቻቸውን የምናውቅ ከሆነ እንዲህ ማድረግ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን ለነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ይህ ተፈታታኝ ሳይሆንባቸው አልቀረም፤ ኤዎድያንንና ሲንጤኪን እንደ ምሳሌ መውሰድ እንችላለን። ስለዚህ “በጌታ አንድ ዓይነት አስተሳሰብ እንዲኖራቸው” ሐዋርያው ጳውሎስ መክሯቸዋል።—ፊልጵ. 4:2, 3፤ w21.01 22-23 አን. 10-11

እሁድ፣ ነሐሴ 28

እናንተ ወጣት ወንዶች፣ የምጽፍላችሁ ጠንካሮች ስለሆናችሁ፣ የአምላክ ቃል በልባችሁ ስለሚኖርና ክፉውን ስላሸነፋችሁት ነው።—1 ዮሐ. 2:14

እናንት ወጣት ወንድሞች፣ በዕድሜ የሚበልጧችሁ ክርስቲያኖች ከእነሱ ጋር ‘እጅ ለእጅ ተያይዛችሁ’ ይሖዋን በማገልገላችሁ ከልብ ያደንቋችኋል። (ሶፎ. 3:9) ቅንዓታችሁን እንዲሁም የተሰጣችሁን ሥራ ለማከናወን ያላችሁን ተነሳሽነት በጣም ያደንቃሉ። በእነሱ ዘንድ ሞገስ አግኝታችኋል። ወጣት ወንድሞች፣ ይሖዋ እንደሚወዳችሁና እንደሚተማመንባችሁ ፈጽሞ አትዘንጉ። ይሖዋ በመጨረሻዎቹ ቀናት በገዛ ፈቃዱ ራሱን የሚያቀርብ የወጣት ወንዶች ሠራዊት እንደሚኖር ትንቢት አስነግሯል። (መዝ. 110:1-3) ይሖዋ እንደምትወዱትና አቅማችሁ በፈቀደ መጠን ልታገለግሉት እንደምትፈልጉ ያውቃል። ስለዚህ ከራሳችሁም ሆነ ከሌሎች ጋር በተያያዘ ታጋሾች ሁኑ። ስህተት ስትሠሩ የሚሰጣችሁን ምክር እና ተግሣጽ ከይሖዋ እንደመጣ አድርጋችሁ ተቀበሉት። (ዕብ. 12:6) የሚሰጣችሁን ማንኛውንም ኃላፊነት በትጋት ተወጡ። ከሁሉ በላይ ደግሞ በምታደርጉት ነገር ሁሉ የሰማዩ አባታችሁ የሚኮራባችሁ ሰዎች ለመሆን ጥረት አድርጉ።—ምሳሌ 27:11፤ w21.03 7 አን. 17-18

ሰኞ፣ ነሐሴ 29

በችግር ጊዜ ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል።—ምሳሌ 24:10 ግርጌ

ተስፋ እንድንቆርጥ የሚያደርጉ ብዙ ምክንያቶች አሉ፤ አንዳንዶቹ ውስጣዊ፣ ሌሎቹ ደግሞ ውጫዊ ናቸው። ተስፋ ከሚያስቆርጡን ሁኔታዎች መካከል አለፍጽምናችን፣ ያሉብን ድክመቶች እንዲሁም የጤና እክል ይገኙበታል። በሌላ በኩል ደግሞ በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ የምንፈልገውን መብት ባለማግኘታችን ምክንያት ወይም የአገልግሎት ክልላችን ፍሬያማ እንዳልሆነ ስለተሰማን ተስፋ እንቆርጥ ይሆናል። አለፍጽምናችንን ወይም ድክመቶቻችንን በተመለከተ ሚዛናዊ ያልሆነ አመለካከት ሊያድርብን ይችላል። ባሉብን ድክመቶችን የተነሳ ይሖዋ ፈጽሞ ወደ አዲሱ ዓለም እንደማያስገባን ይሰማን ይሆናል። እንዲህ ያለው አመለካከት ጎጂ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ሁሉም ሰዎች “ኃጢአት” እንደሠሩ ይናገራል። (ሮም 3:23) ሆኖም ይሖዋ ስህተታችን ላይ አያተኩርም፤ እንዲሁም ፍጹም እንድንሆን አይጠብቅብንም። ከዚህ ይልቅ እኛን ለመርዳት የሚፈልግ አፍቃሪ አባት ነው። ይሖዋ ታጋሽም ነው። ድክመቶቻችንን ለማሸነፍ እንዲሁም ራሳችንን ከልክ በላይ ላለመኮነን መታገል እንደሚያስፈልገን ያውቃል፤ ሊረዳንም ይፈልጋል።—ሮም 7:18, 19፤ w20.12 22 አን. 1-3

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 30

በተረፈ ወንድሞች፣ [መደሰታችሁንና] መስተካከላችሁን ቀጥሉ።—2 ቆሮ. 13:11

ሁላችንም በጉዞ ላይ ነን። የጉዟችን መዳረሻ ወይም ግባችን አፍቃሪ የሆነው ይሖዋ በሚያስተዳድረው አዲስ ዓለም ውስጥ መኖር ነው። ወደ ሕይወት በሚወስደው ጎዳና ላይ ለመጓዝ በየዕለቱ ጥረት እናደርጋለን። ሆኖም ኢየሱስ እንዳለው ይህ መንገድ ቀጭን ነው፤ አንዳንድ ጊዜም በዚህ መንገድ ላይ መጓዝ አስቸጋሪ ነው። (ማቴ. 7:13, 14) ፍጹማን ስላልሆንን በቀላሉ ከዚህ ጎዳና ስተን ልንወጣ እንችላለን። (ገላ. 6:1) ወደ ሕይወት በሚወስደው ቀጭን መንገድ ላይ መጓዛችንን መቀጠል ከፈለግን አስተሳሰባችንን፣ ዝንባሌያችንን እና ምግባራችንን ለማስተካከል ፈቃደኞች መሆን አለብን። ሐዋርያው ጳውሎስ ‘መስተካከላችሁን ቀጥሉ’ በማለት አበረታቶናል። የራሳችንን አስተሳሰብና ስሜት ለመመርመር ጥረት ስናደርግ አንድ ተፈታታኝ ሁኔታ ይገጥመናል። ልባችን ከዳተኛ ስለሆነ ወዴት እየመራን እንዳለ በትክክል ማወቅ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። (ኤር. 17:9) “የውሸት ምክንያት” እያቀረብን ሳይታወቀን ራሳችንን ልናታልል እንችላለን። (ያዕ. 1:22) እንግዲያው ራሳችንን ለመመርመር የአምላክን ቃል መጠቀም ያስፈልገናል። የአምላክ ቃል ውስጣዊ ማንነታችንን ይኸውም የልባችንን “ሐሳብና ዓላማ” ግልጽልጽ አድርጎ ያሳየናል።—ዕብ. 4:12, 13፤ w20.11 18 አን. 1-3

ረቡዕ፣ ነሐሴ 31

አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።—ሮም 12:10

ትሑቶችና ልካችንን የምናውቅ ከሆንን ይበልጥ ደስተኞች እንሆናለን። ለምን? አቅማችን ውስን መሆኑን የምንገነዘብ ከሆነ ሌሎች የሚሰጡንን ማንኛውም እርዳታ በደስታና በአመስጋኝነት እንቀበላለን። ኢየሱስ አሥር የሥጋ ደዌ ሕመምተኞችን በፈወሰበት ወቅት የተፈጠረውን ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ከዚህ አስከፊ በሽታ ስለፈወሰው ኢየሱስን ሊያመሰግነው የተመለሰው አንደኛው ብቻ ነው፤ ሰውየው በራሱ ችሎታ ከዚህ በሽታ መንጻት እንደማይችል ተገንዝቦ ነበር። ትሑት የሆነውና ልኩን የሚያውቀው ይህ ሰው ለተደረገለት ነገር አመስጋኝ ነበር፤ ለአምላክም ክብር ሰጥቷል። (ሉቃስ 17:11-19) ትሑት የሆኑና ልካቸውን የሚያውቁ ሰዎች ከሌሎች ጋር ተስማምተው መኖርና የጠበቀ ወዳጅነት መመሥረት ቀላል ይሆንላቸዋል። ለምን? ምክንያቱም ሌሎች ሰዎች ግሩም ባሕርያት እንዳሏቸው መቀበል አይከብዳቸውም፤ እንዲሁም በሌሎች እንደሚተማመኑ ያሳያሉ። ትሑት የሆኑና ልካቸውን የሚያውቁ ግለሰቦች፣ ሌሎች ሰዎች የተሰጣቸውን የትኛውንም ኃላፊነት በመወጣት ረገድ ሲሳካላቸው ይደሰታሉ፤ እነሱን ከማመስገንና ከማክበርም ወደኋላ አይሉም። w20.08 12 አን. 17-18

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ