የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es22 ገጽ 88-97
  • መስከረም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መስከረም
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2022
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሐሙስ፣ መስከረም 1
  • ዓርብ፣ መስከረም 2
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 3
  • እሁድ፣ መስከረም 4
  • ሰኞ፣ መስከረም 5
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 6
  • ረቡዕ፣ መስከረም 7
  • ሐሙስ፣ መስከረም 8
  • ዓርብ፣ መስከረም 9
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 10
  • እሁድ፣ መስከረም 11
  • ሰኞ፣ መስከረም 12
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 13
  • ረቡዕ፣ መስከረም 14
  • ሐሙስ፣ መስከረም 15
  • ዓርብ፣ መስከረም 16
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 17
  • እሁድ፣ መስከረም 18
  • ሰኞ፣ መስከረም 19
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 20
  • ረቡዕ፣ መስከረም 21
  • ሐሙስ፣ መስከረም 22
  • ዓርብ፣ መስከረም 23
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 24
  • እሁድ፣ መስከረም 25
  • ሰኞ፣ መስከረም 26
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 27
  • ረቡዕ፣ መስከረም 28
  • ሐሙስ፣ መስከረም 29
  • ዓርብ፣ መስከረም 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2022
es22 ገጽ 88-97

መስከረም

ሐሙስ፣ መስከረም 1

ከዚያ በኋላ በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ መንፈሴን አፈሳለሁ።—ኢዩ. 2:28

ጴጥሮስ የኢዩኤልን ትንቢት ጠቅሶ ሲናገር የተጠቀመባቸው ቃላት ከመጀመሪያው ሐሳብ በተወሰነ መጠን ይለያሉ። (ሥራ 2:16, 17) ጴጥሮስ ሐሳቡን የጀመረው “ከዚያ በኋላ” ብሎ ሳይሆን “በመጨረሻው ቀን” በማለት ነው፤ ጴጥሮስ “በመጨረሻው ቀን” አምላክ መንፈሱን “በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ” እንደሚያፈስስ ተናገረ፤ “በመጨረሻው ቀን” የሚለው ሐረግ በዚህ አገባቡ የአይሁድን ሥርዓት የመጨረሻ ቀን ያመለክታል። ይህም የኢዩኤል ትንቢት ፍጻሜውን ያገኘው ትንቢቱ ከተነገረ ከረጅም ጊዜ በኋላ እንደሆነ ይጠቁማል። የአምላክ መንፈስ በመጀመሪያው መቶ ዘመን አስደናቂ በሆነ መንገድ ከፈሰሰ በኋላ የስብከቱ ሥራ እስከዚያ ድረስ ሆኖ በማያውቅ ስፋት መከናወን ጀመረ። ሐዋርያው ጳውሎስ በ61 ዓ.ም. ገደማ ለቆላስይስ ክርስቲያኖች ደብዳቤ ሲጽፍ ምሥራቹ “ከሰማይ በታች ላለ ፍጥረት ሁሉ” እንደተሰበከ መናገር ችሏል። (ቆላ. 1:23) “ፍጥረት ሁሉ” የሚለው አገላለጽ በወቅቱ የሚታወቀውን ዓለም ያመለክታል። ኃያል በሆነው የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እርዳታ በዛሬው ጊዜ የስብከቱ ሥራ ከዚያ በሚበልጥ ስፋት እየተከናወነ ሲሆን “እስከ ምድር ዳር ድረስ” ተሰብኳል።—ሥራ 13:47፤ w20.04 6-7 አን. 15-16

ዓርብ፣ መስከረም 2

እኔ ራሴ በጎቼን እፈልጋለሁ፤ ደግሞም እንከባከባቸዋለሁ።—ሕዝ. 34:11

ይሖዋ ከመንጋው የባዘኑ አገልጋዮቹን ጨምሮ እያንዳንዳችንን ይወደናል። (ማቴ. 18:12-14) አምላክ፣ የጠፉ በጎቹን እንደሚፈልግና መንፈሳዊ ጤንነታቸውን መልሰው እንዲያገኙ እንደሚረዳቸው ቃል ገብቷል። በተጨማሪም የሚወስዳቸውን እርምጃዎች በዝርዝር ጠቅሷል፤ አንድ እስራኤላዊ እረኛ በጉ ሲጠፋበት እነዚህን እርምጃዎች ይወስድ ነበር። (ሕዝ. 34:12-16) በመጀመሪያ እረኛው በጉን ፍለጋ ይሄዳል፤ ይህም ብዙ ጊዜና ጥረት ሊጠይቅበት ይችላል። የባዘነውን በግ ካገኘው በኋላ ደግሞ ወደ መንጋው መልሶ ያመጣዋል። በጉ ተጎድቶ ወይም ተርቦ ከነበረም ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ይንከባከበዋል፤ የተጎዳ አካሉን በጨርቅ ያስርለታል፣ ይሸከመዋል እንዲሁም ይመግበዋል። ‘የአምላክ መንጋ’ እረኛ ሆነው የሚያገለግሉት ሽማግሌዎችም ከጉባኤ የራቀን ማንኛውንም ሰው ሲረዱ እነዚህን እርምጃዎች መውሰድ ይጠበቅባቸዋል። (1 ጴጥ. 5:2, 3) ሽማግሌዎች እነዚህን ግለሰቦች ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ፤ ወደ መንጋው እንዲመለሱ ይረዷቸዋል እንዲሁም የሚያስፈልጋቸውን መንፈሳዊ እርዳታ በመስጠት ፍቅር ያሳዩአቸዋል። w20.06 20 አን. 10

ቅዳሜ፣ መስከረም 3

አዝመራው [ነጥቷል]።—ዮሐ. 4:35

ኢየሱስ አዝመራው ለአጨዳ እንደደረሰ የተናገረው ብዙ ሰዎች የእሱ ተከታይ እንደሚሆኑ ይጠብቅ ስለነበረ ነው? በፍጹም! በእሱ የሚያምኑት ሰዎች በአንጻራዊ ሁኔታ ሲታይ ቁጥራቸው ጥቂት እንደሚሆን ቅዱሳን መጻሕፍት አስቀድመው ተናግረው ነበር። (ዮሐ. 12:37, 38) በተጨማሪም ኢየሱስ የሰዎችን ልብ የማንበብ ተአምራዊ ችሎታ ነበረው። (ማቴ. 9:4) ኢየሱስ እሱን ለመቀበል ፈቃደኛ የሆኑ ጥቂት ሰዎችን በመርዳት ላይ ትኩረት ቢያደርግም ለሁሉም ሰው በቅንዓት ሰብኳል። የሰዎችን ልብ የማንበብ ችሎታ የሌለን እኛማ በአንድ ክልል ወይም በአንድ ግለሰብ ላይ እንዳንፈርድ መጠንቀቅ እንዳለብን የታወቀ ነው! ከዚህ ይልቅ ሰዎች ለውጥ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ማሰብ አለብን። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የተናገረውን አስታውሱ። አዝመራው ነጥቷል ማለትም ለአጨዳ ደርሷል። ሰዎች ለውጥ አድርገው የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ሊሆኑ ይችላሉ። ይሖዋ ደቀ መዝሙር የመሆን ተስፋ ያላቸውን እነዚህን ሰዎች ‘እንደከበሩ ነገሮች’ አድርጎ ይመለከታቸዋል። (ሐጌ 2:7) ለሰዎች የይሖዋና የኢየሱስ ዓይነት አመለካከት ካለን አስተዳደጋቸውንና ትኩረታቸውን የሚስቡትን ነገሮች ለማወቅ ጥረት እናደርጋለን። እነሱን እንደ ባዕድ ሰው ሳይሆን የወደፊት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን እንደሆኑ አድርገን እንመለከታቸዋለን። w20.04 13 አን. 18-19

እሁድ፣ መስከረም 4

ከአባቴ የሰማሁትን ነገር ሁሉ ስላሳወቅኳችሁ ወዳጆች ብዬ ጠርቻችኋለሁ።—ዮሐ. 15:15

ይሖዋን ማስደሰት ከፈለግን ኢየሱስን መውደድና ይህን ፍቅራችንን ጠብቀን መኖር እንዳለብን የአምላክ ቃል በግልጽ ይናገራል። የኢየሱስ ወዳጅ ለመሆን የሚረዳን አንዱ ነገር እሱን በደንብ ማወቅ ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙትን የማቴዎስ፣ የማርቆስ፣ የሉቃስና የዮሐንስ መጻሕፍት ማንበባችን ለዚህ ይረዳናል። ስለ ኢየሱስ ሕይወት በሚገልጹት የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች ላይ ስናሰላስል ኢየሱስ ሰዎችን እንዴት በደግነት እንደያዛቸው እንገነዘባለን፤ ይህም ለእሱ ያለን ፍቅርና አክብሮት እንዲጨምር ያደርጋል። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ ጌታቸው ቢሆንም እንኳ ደቀ መዛሙርቱን እንደ ባሪያ አልያዛቸውም። ከዚህ ይልቅ የውስጡን ሐሳብና ስሜቱን አካፍሏቸዋል። ኢየሱስ ሐዘናቸውን ተጋርቷል፤ እንዲሁም አብሯቸው አልቅሷል። (ዮሐ. 11:32-36) ተቃዋሚዎቹ እንኳ ኢየሱስ መልእክቱን ለሚቀበሉ ሰዎች ወዳጅ እንደሆነ አምነው ተቀብለዋል። (ማቴ. 11:19) ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን የያዘበትን መንገድ የምንከተል ከሆነ ከሌሎች ጋር ያለን ግንኙነት ይሻሻላል፤ እንዲሁም ደስታችን የሚጨምር ከመሆኑም ሌላ ለክርስቶስ ያለን አድናቆት እያደገ ይሄዳል። w20.04 22 አን. 9-10

ሰኞ፣ መስከረም 5

[የደቡቡ] ንጉሥ እጅግ ታላቅና ኃያል የሆነ ሠራዊት አሰባስቦ ለጦርነቱ ይዘጋጃል።—ዳን. 11:25

በ1870 ብሪታንያ በግዛቷ ስፋትና በወታደራዊ ኃይሏ ብርታት ተወዳዳሪ የሌላት ሆና ነበር። በወቅቱ የነበረው የብሪታንያ መንግሥት ሦስት ቀንዶችን ባሸነፈ አንድ ትንሽ ቀንድ ተመስሏል፤ ሦስቱ ቀንዶች ፈረንሳይ፣ ስፔን እና ኔዘርላንድስ ናቸው። (ዳን. 7:7, 8) አንደኛው የዓለም ጦርነት ከጀመረ በኋላም እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ የደቡቡ ንጉሥ የነበረው የብሪታንያ መንግሥት ነው። በዚሁ ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ በኢኮኖሚ አንደኛውን ቦታ ይዛ የነበረ ሲሆን ከብሪታንያ ጋር የጠበቀ አጋርነት መመሥረት ጀምራ ነበር። በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታንያ ከፍተኛ ኃይል ያለው ወታደራዊ ጥምረት መሠረቱ። በዚህ ጊዜ ብሪታንያና የቀድሞ ቅኝ ግዛቷ የሆነችው ዩናይትድ ስቴትስ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ሆኑ። ዳንኤል በትንቢት እንደተናገረው ይህ ንጉሥ “እጅግ ታላቅና ኃያል የሆነ ሠራዊት” ሰብስቦ ነበር። በመጨረሻዎቹ ቀናት የአንግሎ አሜሪካ ጥምር ኃይል የደቡቡ ንጉሥ ሆኖ ቀጥሏል። w20.05 4 አን. 7-8

ማክሰኞ፣ መስከረም 6

ጅረቶቹ . . . ወደሚነሱበት ወደዚያው ቦታ ተመልሰው ይሄዳሉ።—መክ. 1:7

ውኃ በምድር ላይ በፈሳሽ መልክ ሊገኝ የቻለው ፕላኔታችን ከፀሐይ በትክክለኛው ርቀት ላይ ስለተቀመጠች ነው። ፕላኔታችን ወደ ፀሐይ ትንሽ ቀረብ ብትል ኖሮ በምድር ላይ ያለው ውኃ በሙሉ ተንኖ ያልቅ ነበር፤ በመሆኑም ምድራችን ሕይወት የሌለባት ደረቅ ስፍራ ትሆን ነበር። ምድር ከፀሐይ ትንሽ ራቅ ብትል ኖሮ ደግሞ ውኃው በሙሉ ስለሚረጋ ምድራችን በበረዶ ትሸፈን ነበር። ይሖዋ ምድርን ያስቀመጣት ትክክለኛው ቦታ ላይ ነው፤ በመሆኑም የምድር የውኃ ዑደት ሕይወት እንዲቀጥል አስችሏል። ፀሐይ የምታመነጨው ሙቀት በውቅያኖሶችና በምድር ገጽ ላይ ያለው ውኃ እንዲተን ያደርጋል፤ ከዚያም ደመና ይፈጠራል። በየዓመቱ በፀሐይ ሙቀት የተነሳ የሚተንነው ውኃ 500,000 ኪሎ ሜትር ኩብ ገደማ (በምድር ላይ ባሉት በሁሉም ሐይቆች ውስጥ ካለው ውኃ የሚበልጥ) ይሆናል። የተነነው ውኃ ከባቢ አየር ላይ ለአሥር ቀናት ያህል ከቆየ በኋላ በዝናብ መልክ ይወርዳል። ውሎ አድሮም ውኃው ወደ ውቅያኖሶች ወይም ወደ ሌሎች የውኃ አካላት ይገባል፤ ከዚያም ይኸው ዑደት እንደገና ይደገማል። ይህ ውጤታማና የማይቋረጥ ዑደት ይሖዋ ጥበበኛና ኃያል አምላክ መሆኑን ያረጋግጣል።—ኢዮብ 36:27, 28፤ w20.05 22 አን. 6

ረቡዕ፣ መስከረም 7

መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኃይል ትቀበላላችሁ።—ሥራ 1:8

ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን ለማግኘት አዘውትረን ልመና እንድናቀርብ አሳስቦናል። (ሉቃስ 11:9, 13) ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት ‘ከሰብዓዊ ኃይል በላይ የሆነ ኃይል’ እንኳ ሊሰጠን ይችላል። (2 ቆሮ. 4:7) ምንም ዓይነት ፈተና ቢገጥመን በአምላክ መንፈስ እርዳታ ልንወጣው እንችላለን። በተጨማሪም መንፈስ ቅዱስ አምላክን ስናገለግል የሚሰጡንን ሥራዎች ማከናወን እንዲሁም ያለንን ተሰጥኦ እና ችሎታ ማሻሻል እንድንችል ይረዳናል። በሥራችን ጥሩ ውጤት የምናገኘው በራሳችን ችሎታ ሳይሆን በአምላክ መንፈስ እርዳታ መሆኑን እናውቃለን። የአምላክ ቅዱስ መንፈስ በውስጣችን ያለን ማንኛውንም የተሳሳተ ሐሳብ ወይም ዝንባሌ ለማወቅ እንዲረዳን በመጸለይ የአምላክን መንፈስ እንደ ውድ ሀብት አድርገን እንደምንመለከት ማሳየት እንችላለን። (መዝ. 139:23, 24) እንዲህ ያለውን ልመና ካቀረብን፣ ይሖዋ መንፈሱን በመስጠት በውስጣችን ያለውን የተሳሳተ አስተሳሰብ ወይም ዝንባሌ እንድናስተውል ያደርጋል። ከዚያም አምላክ በመንፈሱ አማካኝነት እንዲህ ያለውን ሐሳብ ወይም ዝንባሌ ለማሸነፍ የሚያስችል ብርታት እንዲሰጠን መጸለይ ይኖርብናል። እንዲህ ማድረጋችን፣ ይሖዋ በመንፈሱ አማካኝነት እንዳይረዳን ሊያደርግ የሚችልን ማንኛውንም ነገር ለማስወገድ ያለንን ቁርጠኝነት ያሳያል።—ኤፌ. 4:30፤ w20.05 28-29 አን. 10-12

ሐሙስ፣ መስከረም 8

ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ።—ዮሐ. 17:26

ለይሖዋ ስም ጥብቅና ስንቆም የኢየሱስ ክርስቶስን ምሳሌ እየተከተልን ነው። ኢየሱስ የአባቱን ስም ያሳወቀው፣ በስሙ በመጠቀም ብቻ ሳይሆን ሰዎች ስለ አባቱ ትክክለኛ ማንነት እንዲያውቁ በማድረግም ነው። ለምሳሌ ይሖዋን ጨካኝ፣ ከፍጥረታቱ ብዙ የሚጠብቅ፣ የማይቀረብና ምሕረት የለሽ አምላክ አድርገው የሚያቀርቡትን ፈሪሳውያን አውግዟቸዋል። አባቱ ምክንያታዊ፣ ትዕግሥተኛ፣ አፍቃሪና ይቅር ባይ አምላክ መሆኑን እንዲያስተውሉ ሰዎችን ረድቷል። ከዚህም በተጨማሪ ኢየሱስ በዕለት ተዕለት ሕይወቱ የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ በማንጸባረቅ ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲያውቁ አድርጓል። (ዮሐ. 14:9) እኛም እንደ ኢየሱስ ስለ ይሖዋ የምናውቀውን ነገር ለሌሎች መናገር ይኸውም ይሖዋ በጣም አፍቃሪና ደግ አምላክ እንደሆነ ሰዎችን ማስተማር እንችላለን። ይህን ስናደርግ ስለ ይሖዋ የሚነገሩትን ውሸቶች እናጋልጣለን። ሰዎች የይሖዋን ስም ቅዱስ አድርገው እንዲመለከቱት በመርዳት ስሙን እንቀድሳለን። በአነጋገራችንና በድርጊታችን ይሖዋ ምን ዓይነት አምላክ እንደሆነ ለሌሎች ማሳየት እንችላለን። ሰዎች ስለ አምላክ ያላቸውን የተሳሳተ አመለካከት እንዲያስተካክሉ ስንረዳ ስሙ ከነቀፋ ነፃ እንዲሆን ወይም ትክክለኛነቱ እንዲረጋገጥ እናደርጋለን። w20.06 6 አን. 17-18

ዓርብ፣ መስከረም 9

በመካከላችን የፉክክር መንፈስ በማነሳሳትና አንዳችን ሌላውን በመመቅኘት በከንቱ አንመካ።—ገላ. 5:26

ማኅበራዊ ሚዲያን ለጥሩ ዓላማ መጠቀም ይቻላል፤ ለምሳሌ ከቤተሰቦቻችንና ከጓደኞቻችን ጋር ለመገናኘት ልንጠቀምበት እንችላለን። ይሁንና ሰዎች ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ አንዳንድ ነገሮችን የሚያወጡት የሌሎችን አድናቆት ለማትረፍ ብቻ እንደሆነ አስተውለሃል? “እዩኝ! እዩኝ!” የሚል መልእክት ማስተላለፍ የፈለጉ ይመስላል። ሌሎች ደግሞ ራሳቸውም ሆኑ ሌሎች ባወጧቸው ፎቶግራፎች ላይ አክብሮት የጎደለው ወይም የብልግና ሐሳብ ይጽፋሉ። ሆኖም ክርስቲያኖች ትሕትናና የሌሎችን ስሜት የመረዳት ባሕርይ እንዲያዳብሩ የተበረታቱ ከመሆኑ አንጻር እንዲህ ማድረጋቸው ተገቢ አይደለም። (1 ጴጥ. 3:8) ማኅበራዊ ሚዲያ የምትጠቀም ከሆነ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘የምጽፋቸው ሐሳቦች ወይም የማወጣቸው ፎቶግራፎችና ቪዲዮዎች ጉራ እየነዛሁ እንዳለ የሚያስመስሉ ናቸው? ሌሎች ሰዎች እንዲቀኑ እያደረግኩ ይሆን?’ ክርስቲያኖች ራሳቸውን ከፍ ከፍ ለማድረግ አይሞክሩም። ከዚህ ይልቅ መጽሐፍ ቅዱስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚሰጠውን ምክር በሥራ ላይ ያውላሉ። ትሕትና ማዳበራችን በዓለም ላይ የሚታየው የኩራትና ራስን ከፍ ከፍ የማድረግ መንፈስ እንዳይጋባብን ይረዳናል።—1 ዮሐ. 2:16፤ w20.07 6 አን. 14-15

ቅዳሜ፣ መስከረም 10

ቀደም ሲል አምላክን የምሳደብ፣ አሳዳጅና እብሪተኛ የነበርኩ ብሆንም . . . ባለማወቅ . . . ስላደረግኩት፣ ምሕረት ተደርጎልኛል።—1 ጢሞ. 1:13

ሐዋርያው ጳውሎስ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር ከመሆኑ በፊት የኢየሱስን ተከታዮች የሚያሳድድ እብሪተኛ ወጣት ነበር። (ሥራ 7:58) ሆኖም ኢየሱስ ራሱ በወቅቱ ሳኦል ተብሎ ይጠራ የነበረው ጳውሎስ የክርስቲያን ጉባኤን ማሳደዱን እንዲያቆም አደረገ። ኢየሱስ ከሰማይ ጳውሎስን ያነጋገረው ከመሆኑም ሌላ ዓይኑን አሳወረው። ጳውሎስ የማየት ችሎታውን መልሶ ለማግኘት ከፈለገ ያሳድዳቸው የነበሩትን ሰዎች እርዳታ መጠየቅ ነበረበት። ጳውሎስ፣ ሐናንያ የተባለ ደቀ መዝሙር ያደረገለትን እርዳታ በትሕትና የተቀበለ ሲሆን ሐናንያም የማየት ችሎታውን መለሰለት። (ሥራ 9:3-9, 17, 18) ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ በጉባኤው ውስጥ ትልቅ ኃላፊነት ያለው ክርስቲያን ሆኗል፤ ያም ቢሆን ወደ ደማስቆ በሚወስደው መንገድ ላይ ኢየሱስ የሰጠውን ትምህርት ፈጽሞ አልረሳም። ጳውሎስ ምንጊዜም ትሑት የነበረ ከመሆኑም ሌላ ወንድሞቹና እህቶቹ ያደረጉለትን እርዳታ በፈቃደኝነት ተቀብሏል። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች “የብርታት ምንጭ” እንደሆኑለት በሐቀኝነት ተናግሯል።—ቆላ. 4:10, 11፤ w20.07 18-19 አን. 16-17

እሁድ፣ መስከረም 11

አባታችሁ መንግሥት ሊሰጣችሁ ወስኗል።—ሉቃስ 12:32

ይሖዋ ሁሉን ቻይ አምላክ ቢሆንም ለሌሎች ኃላፊነት ይሰጣል። ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንዲሆን ኢየሱስን ሾሞታል፤ ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ ገዢዎች ለሚሆኑት 144,000 የሰው ልጆችም በተወሰነ መጠን ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። በእርግጥ ይሖዋ፣ ኢየሱስን ንጉሥና ሊቀ ካህናት መሆን እንዲችል አሠልጥኖታል። (ዕብ. 5:8, 9) ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ ገዢዎች የሚሆኑትን ሰዎችም ያሠለጥናቸዋል፤ አንድ ጊዜ ይህን ኃላፊነት ከሰጣቸው በኋላ ግን ጣልቃ ገብቶ እያንዳንዱን ሥራቸውን አይቆጣጠርም። ከዚህ ይልቅ ፈቃዱን እንደሚያደርጉ ይተማመንባቸዋል። (ራእይ 5:10) የማንም እገዛ የማያስፈልገው የሰማዩ አባታችን ለሌሎች ኃላፊነት የሚሰጥ ከሆነ እኛማ እንዲህ ማድረጋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! የቤተሰብ ራስ ወይም የጉባኤ ሽማግሌ ነህ? ለሌሎች ሥራ በመስጠት እንዲሁም ሥራውን ሲያከናውኑ እያንዳንዱን እርምጃቸውን ባለመቆጣጠር የይሖዋን ምሳሌ ተከተል። የይሖዋን ምሳሌ መከተልህ ሥራው እንዲከናወን የሚያደርግ ከመሆኑም ሌላ ሌሎችን ለማሠልጠንና በራስ የመተማመን ስሜታቸው እንዲጨምር ለመርዳት አጋጣሚ ይሰጥሃል።—ኢሳ. 41:10፤ w20.08 9 አን. 5-6

ሰኞ፣ መስከረም 12

የሰው ልጅ የመጣው የጠፋውን ለመፈለግና ለማዳን ነው።—ሉቃስ 19:10

ይሖዋ ለጠፉት በጎቹ ምን አመለካከት እንዲኖረን ይፈልጋል? ኢየሱስ በዚህ ረገድ ጥሩ ምሳሌ ትቶልናል። ኢየሱስ ሁሉም የይሖዋ በጎች በእሱ ፊት ውድ እንደሆኑ ያውቅ ነበር፤ በመሆኑም ‘ከእስራኤል ቤት የጠፉት በጎች’ ወደ ይሖዋ እንዲመለሱ ለመርዳት የሚችለውን ሁሉ አድርጓል። (ማቴ. 15:24) ከዚህም ሌላ፣ ጥሩ እረኛ የሆነው ኢየሱስ ከይሖዋ በጎች መካከል አንዱም እንኳ እንዳይጠፋበት ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። (ዮሐ. 6:39) ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ጉባኤ የሚገኙ ሽማግሌዎችን የኢየሱስን ምሳሌ እንዲከተሉ አሳስቧቸዋል። እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ደካማ የሆኑትን መርዳት [አለባችሁ]፤ እንዲሁም ‘ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል’ በማለት ጌታ ኢየሱስ ራሱ የተናገረውን ቃል ማስታወስ ይኖርባችኋል።” (ሥራ 20:17, 35) ከዚህ በግልጽ ማየት እንደሚቻለው በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎች በዚህ ረገድ ከባድ ኃላፊነት ተጥሎባቸዋል። በስፔን የሚኖር ሳልቫዶር የተባለ አንድ ሽማግሌ እንዲህ ብሏል፦ ‘ይሖዋ የጠፉ በጎቹን ምን ያህል እንደሚወዳቸው ሳስብ እነሱን ለመርዳት የቻልኩትን ሁሉ ለማድረግ እነሳሳለሁ። ይሖዋ እነሱን እንድንከባከብ እንደሚጠብቅብኝ እገነዘባለሁ።’ w20.06 23 አን. 15-16

ማክሰኞ፣ መስከረም 13

ቀድሞ የነበሩት ነገሮች አልፈዋል።—ራእይ 21:4

ይሖዋ በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ ፍጹም የምንሆንበትን ጊዜ በትዕግሥት ይጠብቃል። ያ ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ኃጢአታችንን ይቅር ለማለት ፈቃደኛ ነው። ከዚህ አንጻር እኛም የሌሎችን መልካም ጎን ልንመለከትና እነሱን በትዕግሥት ልንይዛቸው ይገባል። ምድር በተፈጠረችበት ወቅት ኢየሱስና መላእክት በጣም ተደስተው ነበር። ወደፊት ምድር ይሖዋን በሚወዱና እሱን በሚያገለግሉ ፍጹማን ሰዎች ስትሞላማ ምን ያህል እንደሚደሰቱ መገመት ይቻላል። በሰማይ ከክርስቶስ ጋር እንዲገዙ ከምድር የተዋጁትም፣ የሰው ዘር እነሱ ከሚያከናውኑት ሥራ የሚያገኘውን ጥቅም ሲመለከቱ በጣም እንደሚደሰቱ ጥያቄ የለውም። (ራእይ 4:4, 9-11፤ 5:9, 10) የደስታ እንጂ የሥቃይ እንባ የማናነባበት እንዲሁም ሕመም፣ መከራና ሞት ታሪክ የሚሆኑበት ያ ጊዜ ምን ያህል አስደሳች እንደሚሆን አስበው። እስከዚያ ጊዜ ድረስ ግን አፍቃሪ፣ ጥበበኛና ታጋሽ የሆነውን አባትህን ለመምሰል ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ይህን ካደረግህ ምንም ዓይነት ፈተና ቢያጋጥምህ ደስታህን ጠብቀህ መኖር ትችላለህ። (ያዕ. 1:2-4) በእርግጥም ይሖዋ ሰዎች ‘ከሞት እንደሚነሱ’ ለገባው ቃል ምንኛ አመስጋኞች ነን!—ሥራ 24:15፤ w20.08 19 አን. 18-19

ረቡዕ፣ መስከረም 14

ይህ የመንግሥቱ ምሥራች . . . በመላው ምድር ይሰበካል።—ማቴ. 24:14

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ በፍቅር ተነሳስቶ የሰጠን ስጦታ ነው። ሰማያዊው አባታችን ሰዎችን በመንፈሱ በመምራት መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው ለምድራዊ ልጆቹ በጥልቅ ስለሚያስብ ነው። ይሖዋ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት፣ በጣም አስፈላጊ ለሆኑ ጥያቄዎቻችን መልስ ሰጥቶናል። ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ‘ወደ ሕልውና የመጣነው እንዴት ነው? የሕይወት ዓላማ ምንድን ነው? የወደፊቱ ጊዜ ምን ይዞ ይመጣ ይሆን?’ የሚሉት ይገኙበታል። ይሖዋ ሁሉም ልጆቹ የእነዚህን ጥያቄዎች መልስ እንዲያውቁ ይፈልጋል፤ በመሆኑም ባለፉት በርካታ ዘመናት መጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቋንቋዎች እንዲተረጎም አድርጓል። በአሁኑ ወቅት ሙሉው መጽሐፍ ቅዱስ ወይም የተወሰነው ክፍል ከ3,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች ተተርጉሟል! የመጽሐፍ ቅዱስን ያህል በብዙ ቋንቋዎች የተተረጎመና በስፋት የተሰራጨ መጽሐፍ የለም። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ በማንበብ፣ በመልእክቱ ላይ በማሰላሰል እንዲሁም የተማርነውን ነገር በተግባር ለማዋል የምንችለውን ያህል በመጣር ለመጽሐፍ ቅዱስ አድናቆት እንዳለን ማሳየት እንችላለን። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በተቻለ መጠን ለብዙ ሰዎች በመናገር ለአምላክ ምስጋናችንን መግለጽ እንችላለን።መዝ. 1:1-3፤ ማቴ. 28:19, 20፤ w20.05 24-25 አን. 15-16

ሐሙስ፣ መስከረም 15

የይሖዋ ቃል ቀኑን ሙሉ ስድብና ፌዝ አስከትሎብኛል።—ኤር. 20:8

ነቢዩ ኤርምያስ የተሰጠው የአገልግሎት ምድብ በጣም አስቸጋሪ ነበር። እንዲያውም በአንድ ወቅት በጣም ተስፋ ከመቁረጡ የተነሳ ሥራውን ለማቆም አስቦ ነበር። ሆኖም እንዲህ አላደረገም። ለምን? “የይሖዋ ቃል” በልቡ ውስጥ እንዳለ የሚነድ እሳት ስለሆነበት ቃሉን አፍኖ መያዝ አልቻለም! (ኤር. 20:9) እኛም አእምሯችንን እና ልባችንን በአምላክ ቃል ከሞላነው የኤርምያስ ዓይነት ስሜት ይኖረናል። ይህ መጽሐፍ ቅዱስን በየቀኑ እንድናጠና እና እንድናሰላስልበት የሚያነሳሳ ተጨማሪ ምክንያት ነው። እንዲህ ካደረግን ደስታችን እየጨመረ ይሄዳል፤ እንዲሁም አገልግሎታችን ይበልጥ ፍሬያማ ይሆንልናል። (ኤር. 15:16) ስለዚህ ተስፋ ስትቆርጥ ይሖዋ እንዲረዳህ ምልጃ አቅርብ። ይሖዋ፣ ካለብህ አለፍጽምና፣ ከድክመቶችህ ወይም ካጋጠመህ የጤና እክል ጋር በምታደርገው ትግል እንድታሸንፍ ይረዳሃል። የአገልግሎት መብቶችን በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖርህ ይረዳሃል። እንዲሁም ለአገልግሎትህ አዎንታዊ አመለካከት እንዲኖርህ ይረዳሃል። በተጨማሪም የሚያሳስብህን ነገር በሰማይ ለሚኖረው አባትህ በጸሎት ግለጽለት። ከተስፋ መቁረጥ ጋር የምታደርገውን ትግል በይሖዋ እርዳታ ማሸነፍ ትችላለህ! w20.12 27 አን. 20-21

ዓርብ፣ መስከረም 16

አሮጊቶችን እንደ እናቶች፣ ወጣት ሴቶችን ደግሞ እንደ እህቶች አድርገህ በፍጹም ንጽሕና ያዛቸው።—1 ጢሞ. 5:1, 2

አንዳንድ እህቶች ከእምነት ባልንጀሮቻቸው ጋር መገናኘት የሚችሉበት ዋነኛ አጋጣሚ የጉባኤ ስብሰባ ነው። በመሆኑም በእነዚህ አጋጣሚዎች እህቶቻችንን ሞቅ አድርገን መቀበል፣ እነሱን ማጫወት እንዲሁም እንደምናስብላቸው ማሳየት እንፈልጋለን። እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም ከእህቶች ጋር አብረን የምናሳልፈው ጊዜ መመደብ እንችላለን። (ሉቃስ 10:38-42) ቀለል ያለ ምግብ ሠርተን ልንጋብዛቸው ወይም አብረውን እንዲዝናኑ ልንጠይቃቸው እንችል ይሆናል። ይህን ስናደርግ ጭውውታችን የሚያንጽ እንዲሆን ጥረት እናድርግ። (ሮም 1:11, 12) ሽማግሌዎች የኢየሱስን ዓይነት አመለካከት መያዛቸው አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ ነጠላነት ለአንዳንዶች ተፈታታኝ እንደሚሆን ያውቅ ነበር፤ ሆኖም ዘላቂ ደስታ ለማግኘት ቁልፉ ማግባት ወይም ልጆች መውለድ እንዳልሆነ ግልጽ አድርጓል። (ሉቃስ 11:27, 28) ዘላቂ ደስታ ማግኘት የሚቻለው የይሖዋን አገልግሎት በማስቀደም ነው። (ማቴ. 19:12) በተለይ ሽማግሌዎች ክርስቲያን ሴቶችን እንደ መንፈሳዊ እህቶቻቸውና እናቶቻቸው አድርገው መያዝ ይኖርባቸዋል። ሽማግሌዎች ከስብሰባ በፊት ወይም በኋላ ከእህቶች ጋር ለመጨዋወት ጊዜ መመደብ ያስፈልጋቸዋል። w20.09 21-22 አን. 7-9

ቅዳሜ፣ መስከረም 17

ገበሬ . . . መልካም ፍሬ ይጠባበቃል። እናንተም በትዕግሥት ጠብቁ።—ያዕ. 5:7, 8

በእስራኤል አንድ ገበሬ ዘር የሚዘራው ከፊተኛው ዝናብ በኋላ ሲሆን ሰብሉን የሚሰበስበው ደግሞ ከኋለኛው ዝናብ በኋላ ነበር። (ማር. 4:28) እኛም እንደ ገበሬው ትዕግሥት ማሳየታችን የጥበብ እርምጃ ነው። ሆኖም ይህን ማድረግ ቀላል አይደለም። ፍጹም ያልሆኑት የሰው ልጆች የሥራቸውን ውጤት ቶሎ ማየት ይፈልጋሉ። ይሁን እንጂ ተክል ተክለን ሲያፈራ ማየት ከፈለግን የማያቋርጥ እንክብካቤ ማድረግ ያስፈልገናል፤ ይኸውም መሬቱን መቆፈር፣ መትከል እንዲሁም አረሙን መንቀልና ውኃ ማጠጣት ይኖርብናል። ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራም የማያቋርጥ ጥረት ይጠይቃል። የምናስተምራቸው ሰዎች ጭፍን ጥላቻንና ለሌሎች ግድየለሽ የመሆን ዝንባሌን ከልባቸው ነቅለው እንዲያወጡ መርዳት ጊዜ ይወስዳል። ትዕግሥት ሰዎች መልእክታችንን ለመስማት ፈቃደኛ በማይሆኑበት ጊዜ ተስፋ እንዳንቆርጥ ይረዳናል። በሌላ በኩል ደግሞ ሰዎች ለመልእክታችን ጥሩ ምላሽ በሚሰጡበት ጊዜም ትዕግሥተኛ መሆን ያስፈልገናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን ጠንካራ እምነት እንዲያዳብር ልናስገድደው አንችልም። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም እንኳ እሱ ያስተማራቸውን ነገር ለመረዳት ጊዜ ወስዶባቸው ነበር። (ዮሐ. 14:9) እኛ ብንተክልና ብናጠጣም የሚያሳድገው አምላክ እንደሆነ አንርሳ።—1 ቆሮ. 3:6፤ w20.09 11 አን. 10-11

እሁድ፣ መስከረም 18

ቅኖች በተሰበሰቡበት ማኅበርና በጉባኤ ይሖዋን በሙሉ ልቤ አወድሰዋለሁ።—መዝ. 111:1

ሁላችንም ጥናቶቻችን እድገት አድርገው እንዲጠመቁ እንፈልጋለን። እንዲህ እንዲያደርጉ መርዳት የምንችልበት አንዱ ወሳኝ መንገድ በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ ማበረታታት ነው። በአብዛኛው በስብሰባዎች ላይ ወዲያው መገኘት የጀመሩ ተማሪዎች ፈጣን እድገት ያደርጋሉ። ተማሪዎቹ በጥናታቸው ወቅት የሚማሩትን ያህል በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ በመገኘትም ብዙ እውቀት እንደሚቀስሙ አንዳንድ አስተማሪዎች ለጥናቶቻቸው ይነግሯቸዋል። ከጥናትህ ጋር ዕብራውያን 10:24, 25⁠ን አንብብ፤ ከዚያም በስብሰባዎች ላይ መገኘቱ ምን ጥቅም እንደሚያስገኝለት ከጥቅሱ ላይ አብራራለት። በስብሰባ ላይ የተማርከው ነገር ምን ያህል እንዳስደሰተህ ንገረው። ጉባኤ እንዲመጣ ከመጋበዝ የበለጠ ጥናትህን ስብሰባ ላይ እንዲገኝ ሊያነሳሳው የሚችለው እንዲህ ማድረግህ ነው። ጥናትህ ለመጀመሪያ ጊዜ ስብሰባ ላይ ሲገኝ የሚመለከተው ነገር እስከ ዛሬ ከተገኘባቸው ሃይማኖታዊ ስብሰባዎች ሁሉ እጅግ የላቀ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። (1 ቆሮ. 14:24, 25) ጥሩ ምሳሌ ሊሆኑትና እድገት አድርጎ እንዲጠመቅ ሊረዱት ከሚችሉ ሰዎች ጋር የመተዋወቅ አጋጣሚ ያገኛል። w20.10 10-11 አን. 14-15

ሰኞ፣ መስከረም 19

እንደ [አምላክ] ያለ አስተማሪ ማን ነው?—ኢዮብ 36:22

የአምላክ መንፈስ ከአምላክ ቃል ላይ የምታነበውንና የምታጠናውን ነገር በሕይወትህ ውስጥ ተግባራዊ እንድታደርግ ይረዳሃል። እንደ መዝሙራዊው እንዲህ ብለህ ጸልይ፦ “ይሖዋ ሆይ፣ መንገድህን አስተምረኝ። በእውነትህ እሄዳለሁ። ስምህን እፈራ ዘንድ ልቤን አንድ አድርግልኝ።” (መዝ. 86:11) በተጨማሪም ይሖዋ በቃሉና በድርጅቱ አማካኝነት የሚያቀርበውን መንፈሳዊ ምግብ መመገብህን ቀጥል። እርግጥ ነው፣ ዓላማህ እውቀት መሰብሰብ ብቻ መሆን የለበትም። ከዚህ ይልቅ እውነት ወደ ልብህ ጠልቆ እንዲገባ ማድረግና የተማርካቸውን ነገሮች ተግባር ላይ ማዋል ይኖርብሃል። የይሖዋ መንፈስ እንዲህ እንድታደርግ ይረዳሃል። ከዚህም በተጨማሪ ወንድሞችህንና እህቶችህን ማበረታታት አለብህ። (ዕብ. 10:24, 25) ለምን? ምክንያቱም መንፈሳዊ ቤተሰቦችህ ናቸው። የአምላክ መንፈስ በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ላይ ከልብ የመነጨ ሐሳብ መስጠት እንድትችልና ክፍል ሲሰጥህ አቅምህ በፈቀደ መጠን ጥሩ አድርገህ ማቅረብ እንድትችል እንዲረዳህ ጸልይ። በእነዚህ መንገዶች ውድ ለሆኑት በጎች ፍቅር እንዳለህ ለይሖዋና ለልጁ ማሳየት ትችላለህ። (ዮሐ. 21:15-17) እንግዲያው አምላክ ከሚያዘጋጀው የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ሙሉ ተጠቃሚ በመሆን ታላቁ አስተማሪህን ስማ። w20.10 24-25 አን. 15-17

ማክሰኞ፣ መስከረም 20

ሁሉም ጥለውት ሸሹ።—ማር. 14:50

ኢየሱስ ሐዋርያቱ እምነታቸው ተዳክሞ በነበረበት ወቅት የያዛቸው እንዴት ነው? ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ ብዙም ሳይቆይ ለአንዳንድ ተከታዮቹ ‘አትፍሩ! ሂዱና ለወንድሞቼ፣ እንደተነሳሁ ንገሯቸው’ ብሏቸዋል። (ማቴ. 28:10ሀ) ኢየሱስ በሐዋርያቱ ተስፋ አልቆረጠም። ጥለውት ቢሄዱም እንኳ “ወንድሞቼ” በማለት ጠርቷቸዋል። እንደ ይሖዋ ሁሉ ኢየሱስም መሐሪና ይቅር ባይ መሆኑን አሳይቷል። (2 ነገ. 13:23) እኛም በአገልግሎት መካፈላቸውን ላቆሙ ክርስቲያኖች ከልብ እናስባለን። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስለሆኑ እንወዳቸዋለን። እነዚህ የእምነት ባልንጀሮቻችን ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር ተነሳስተው በትጋት ያከናወኑትን አገልግሎት እናስታውሳለን፤ አንዳንዶቹ ለበርካታ ዓመታት ይሖዋን አገልግለዋል። (ዕብ. 6:10) እንደገና ልናያቸው በጣም እንጓጓለን! (ሉቃስ 15:4-7) እንግዲያው የቀዘቀዙ ክርስቲያኖችን ስብሰባዎች ላይ እንዲገኙ እናበረታታቸው። አንድ የቀዘቀዘ አስፋፊ ወደ ስብሰባ አዳራሹ ሲመጣ ቅድሚያውን ወስደን በደስታ ልንቀበለው ይገባል። w20.11 6 አን. 14-17

ረቡዕ፣ መስከረም 21

ከተጻፈው አትለፍ።—1 ቆሮ. 4:6

ያዕቆብና ዮሐንስ ከእናታቸው ጋር ሆነው በኢየሱስ ሥልጣን ሥር ያልሆነን ነገር እንዲሰጣቸው ኢየሱስን ጠይቀውት ነበር። ኢየሱስ በመንግሥቱ በእሱ ቀኝና ግራ የሚቀመጡትን ሰዎች የሚወስነው የሰማዩ አባቱ ብቻ እንደሆነ ወዲያውኑ ነገራቸው። (ማቴ. 20:20-23) ኢየሱስ፣ ከተሰጠው ቦታ አልፎ እንደማይሄድ አሳይቷል። ልኩን የሚያውቅ ሰው ነበር። ይሖዋ ከሰጠው ሥልጣን አልፎ በመሄድ ምንም ነገር አድርጎ አያውቅም። (ዮሐ. 12:49) እኛስ ኢየሱስ የተወውን ግሩም ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የሚገኘውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር ተግባራዊ በማድረግ፣ ኢየሱስ ልክን በማወቅ ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተል እንችላለን። ስለዚህ ምክር ስንጠየቅ፣ የራሳችንን አመለካከት ከመግለጽ ወይም መጀመሪያ ወደ አእምሯችን የመጣውን ሐሳብ ከመናገር መቆጠብ ይኖርብናል። ከዚህ ይልቅ ምክር የጠየቀን ሰው ትኩረቱን በመጽሐፍ ቅዱስ እና በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎቻችን ላይ እንዲያደርግ መርዳት አለብን። በዚህ መንገድ ቦታችንን እንደምናውቅ እናሳያለን። ልካችንን በማወቅ እንዲህ የምናደርግ ከሆነ ሁሉን ቻይ ለሆነው አምላክ “የጽድቅ ድንጋጌዎች” እውቅና እንሰጣለን።—ራእይ 15:3, 4፤ w20.08 11-12 አን. 14-15

ሐሙስ፣ መስከረም 22

ከልክ በላይ ጻድቅ አትሁን፤ እጅግም ጥበበኛ መስለህ ለመታየት አትሞክር። በራስህ ላይ ለምን ጥፋት ታመጣለህ?—መክ. 7:16

ለአንድ ወዳጅህ ምክር መስጠት እንዳለብህ ከተሰማህ የትኞቹን ነጥቦች ልታስታውስ ይገባል? ወዳጅህን ከማነጋገርህ በፊት ‘“ከልክ በላይ ጻድቅ” እየሆንኩ ይሆን?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ከልክ በላይ ጻድቅ የሆነ ሰው በይሖዋ መሥፈርቶች ሳይሆን የራሱን መሥፈርቶች በማውጣት በሌሎች ላይ ይፈርዳል፤ ይህን በሚያደርግበት ወቅትም ምሕረት ላያሳይ ይችላል። ራስህን ከመረመርክ በኋላም ጓደኛህን ማነጋገር እንዳለብህ ይሰማህ ይሆናል፤ ከሆነ ማስተካከል ያለበትን ችግር ለይተህ ጥቀስ፤ እንዲሁም የአመለካከት ጥያቄዎችን በመጠቀም ስህተቱ እንዲገባው እርዳው። ወዳጅህ ተጠያቂ የሆነው በይሖዋ እንጂ በአንተ ፊት እንዳልሆነ አስታውስ፤ በመሆኑም የምትናገረው ነገር በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ ይሁን። (ሮም 14:10) በአምላክ ቃል ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ ያዘለ ምክር ተጠቀም፤ እንዲሁም ምክር ስትሰጥ እንደ ኢየሱስ ርኅራኄ አሳይ። (ምሳሌ 3:5፤ ማቴ. 12:20) እንዲህ ማድረግህ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ እኛን የሚይዘን ሌሎችን በምንይዝበት መንገድ ነው።—ያዕ. 2:13፤ w20.11 21 አን. 13

ዓርብ፣ መስከረም 23

የሰውን ውጫዊ ገጽታ በማየት አትፍረዱ፤ ከዚህ ይልቅ በጽድቅ ፍረዱ።—ዮሐ. 7:24

ሰዎች የቆዳህን ቀለም፣ መልክህን ወይም ቁመናህን በማየት ብቻ ስለ አንተ አንድ ዓይነት መደምደሚያ ላይ ቢደርሱ ደስ ይልሃል? ደስ እንደማይልህ የታወቀ ነው። ይሖዋ እንደ ሰዎች ከውጭ በሚታይ ነገር ላይ ተመሥርቶ የማይፈርድ መሆኑ ምንኛ ያጽናናል! ለምሳሌ ያህል፣ ሳሙኤል የእሴይን ልጆች የተመለከተው ይሖዋ በሚያይበት መንገድ አልነበረም። ይሖዋ ከእሴይ ልጆች አንዱ የእስራኤል ንጉሥ እንደሚሆን ለሳሙኤል ነግሮት ነበር። ይሁንና ይሖዋ የመረጠው የትኛውን የእሴይ ልጅ ነው? ሳሙኤል፣ የእሴይ የበኩር ልጅ የሆነውን ኤልያብን ሲመለከት “መቼም ይሖዋ የሚቀባው ሰው ይህ መሆን አለበት” አለ። ኤልያብ የንጉሥ ዓይነት አቋም ነበረው። “ሆኖም ይሖዋ ሳሙኤልን እንዲህ አለው፦ ‘እኔ ስላልተቀበልኩት መልኩንና የቁመቱን ርዝማኔ አትይ።’” ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ አክሎ ሲናገር “ሰው የሚያየው ውጫዊ ገጽታን ነው፤ ይሖዋ ግን የሚያየው ልብን ነው” ብሏል። (1 ሳሙ. 16:1, 6, 7) ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር ባለን ግንኙነት ይሖዋን ለመምሰል ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። w20.04 14 አን. 1፤ 15 አን. 3

ቅዳሜ፣ መስከረም 24

ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ።—ዮሐ. 4:35

ኢየሱስ በእህል ማሳ ውስጥ እያለፈ ነው፤ ማሳው የገብስ ቡቃያ ያለበት ሳይሆን አይቀርም። (ዮሐ. 4:3-6) ይህ አዝመራ ከአራት ወር ገደማ በኋላ ለአጨዳ ይደርሳል። ኢየሱስ “ዓይናችሁን ወደ ማሳው አቅንታችሁ አዝመራው እንደነጣ ተመልከቱ” በማለት ለሰሚዎቹ እንግዳ ሊሆን የሚችል ነገር ተናገረ። (ዮሐ. 4:35, 36) ኢየሱስ ምን ማለቱ ነበር? ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው በምሳሌያዊ ሁኔታ ሰዎችን ስለ መሰብሰብ ሳይሆን አይቀርም። እስቲ ኢየሱስ ይህን ከመናገሩ በፊት ምን እንደተከናወነ አስብ። አይሁዳውያን ከሳምራውያን ጋር ምንም ግንኙነት ባይኖራቸውም ኢየሱስ ለአንዲት ሳምራዊት ሴት የሰበከ ሲሆን እሷም መልእክቱን ተቀበለች! እንዲያውም ኢየሱስ “አዝመራው እንደነጣ” በተናገረበት ወቅት ብዙ ሳምራውያን ወደ እሱ እየመጡ ነበር፤ እነዚህ ሰዎች ከሳምራዊቷ ሴት ስለ ኢየሱስ ሰምተው ስለነበር ከእሱ መማር ፈልገው ነበር። (ዮሐ. 4:9, 39-42) አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ማመሳከሪያ ጽሑፍ ስለዚህ ዘገባ ሲገልጽ “ሰዎቹ ጉጉት ስለነበራቸው ለአጨዳ እንደደረሰ አዝመራ ነበሩ” ብሏል። w20.04 8 አን. 1-2

እሁድ፣ መስከረም 25

እርስ በርስ ለፍቅርና ለመልካም ሥራዎች መነቃቃት እንድንችል አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ።—ዕብ. 10:24

ስብሰባዎቻችን የመስበክና የማስተማር ችሎታችንን እንድናሻሽል ስለሚረዱን የውጊያ ክህሎታችንን ያሳድጉልናል ሊባል ይችላል። ለምሳሌ ያህል፣ የማስተማሪያ መሣሪያዎቻችንን ውጤታማ በሆነ መንገድ መጠቀም የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን። እንግዲያው ለጉባኤ ስብሰባዎች በሚገባ ተዘጋጁ። በስብሰባ ወቅት በጥሞና አዳምጡ። ከስብሰባው በኋላ ደግሞ ያገኛችሁትን ሥልጠና በተግባር አውሉ። እንዲህ ካደረጋችሁ “የክርስቶስ ኢየሱስ ምርጥ ወታደር” መሆን ትችላላችሁ። (2 ጢሞ. 2:3) በተጨማሪም እልፍ አእላፋት ኃያላን መላእክት ከጎናችን አሉ። አንድ መልአክ ብቻ እንኳ ምን ያህል ኃይል እንዳለው አስቡት! (ኢሳ. 37:36) እጅግ ብዙ መላእክትን ያቀፈ ሠራዊትማ ምን ያህል ኃይል እንደሚኖረው መገመት አያዳግትም። ከይሖዋ ኃያል ሠራዊት ጋር ሊወዳደር የሚችል ኃይል ያለው ሰውም ሆነ ጋኔን የለም! አንድ ታማኝ ክርስቲያን ይሖዋ ከጎኑ ካለ ከየትኛውም ጭፍራ የሚበልጥ ኃይል ይኖረዋል። (መሳ. 6:16) የሥራ ባልደረባችሁ፣ አብሯችሁ የሚማር ልጅ ወይም የማያምን ዘመዳችሁ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር ሲናገር ወይም ሲያደርግ እነዚህን ነገሮች ማስታወሳችሁ ይረዳችኋል። በዚህ ውጊያ ላይ ብቻችሁን እንዳልሆናችሁ አስታውሱ። የይሖዋን አመራር እየተከተላችሁ ስለሆነ እሱ ይደግፋችኋል። w21.03 29 አን. 13-14

ሰኞ፣ መስከረም 26

ሙታን የማይነሱ ከሆነማ “ነገ ስለምንሞት እንብላ፣ እንጠጣ።”—1 ቆሮ. 15:32

ሐዋርያው ጳውሎስ እስራኤላውያን የነበራቸውን ዝንባሌ የሚገልጸውን ኢሳይያስ 22:13⁠ን እየጠቀሰ ሊሆን ይችላል። እስራኤላውያን ወደ አምላክ ከመቅረብ ይልቅ ተድላን በማሳደድ ላይ ያተኮረ ሕይወት ይመሩ ነበር። በሌላ አባባል እነዚህ እስራኤላውያን “ሺህ ዓመት አይኖር” ያሉ ያህል ነው፤ እንዲህ ያለው አመለካከት ዛሬም በስፋት ይታያል። ይሖዋ ሙታንን እንደሚያስነሳ ማወቃችን በጓደኛ ምርጫችን ላይ ተጽዕኖ ሊያሳድር እንደሚገባ ጥርጥር የለውም። በቆሮንቶስ ይኖሩ የነበሩ ወንድሞች ትንሣኤን ከሚክዱ ሰዎች ጋር ወዳጅነት ላለመመሥረት መጠንቀቅ ነበረባቸው። ከዚህ ግሩም ትምህርት እናገኛለን፤ ለዛሬ ብቻ የሚኖሩ ሰዎችን ጓደኛ አድርገን መምረጣችን ጎጂ ነው። አንድ እውነተኛ ክርስቲያን እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር ብዙ ጊዜ ማሳለፉ በአመለካከቱና በሥነ ምግባሩ ላይ መጥፎ ተጽዕኖ ሊያሳድርበት ይችላል፤ ይባስ ብሎም አምላክ የሚጠላውን ዓይነት ሕይወት እንዲከተል ማለትም በኃጢአት ጎዳና እንዲመላለስ ሊያደርገው ይችላል። በመሆኑም ጳውሎስ “ጽድቅ የሆነውን በማድረግ ወደ ልቦናችሁ ተመለሱ፤ ኃጢአት መሥራትን ልማድ አታድርጉ” የሚል ጠንካራ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።—1 ቆሮ. 15:33, 34፤ w20.12 9 አን. 3, 5-6

ማክሰኞ፣ መስከረም 27

የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ . . . የክርስቶስ ራስ ደግሞ አምላክ [ነው]።—1 ቆሮ. 11:3

ይህ ጥቅስ፣ ይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ ቤተሰቡን እንዴት እንዳደራጀ ይገልጻል። የራስነት ሥርዓት ሁለት ቁልፍ ነገሮችን የያዘ ነው፤ እነሱም ሥልጣንና ተጠያቂነት ናቸው። የሁሉም “ራስ” ወይም የመጨረሻው ባለሥልጣን ይሖዋ ነው፤ ሁሉም ልጆቹ ማለትም መላእክትም ሆኑ የሰው ልጆች በእሱ ፊት ተጠያቂ ናቸው። (ሮም 14:10፤ ኤፌ. 3:14, 15) ይሖዋ ለኢየሱስ በጉባኤው ላይ ሥልጣን ሰጥቶታል፤ ሆኖም ኢየሱስ እኛን የሚይዝበትን መንገድ በተመለከተ በይሖዋ ፊት ተጠያቂ ነው። (1 ቆሮ. 15:27) ይሖዋ ለባልም በሚስቱና በልጆቹ ላይ ሥልጣን ሰጥቶታል። ታዲያ ጥሩ የቤተሰብ ራስ መሆን የሚችለው እንዴት ነው? በመጀመሪያ ይሖዋ የሚጠብቅበትን ማወቅ ይኖርበታል። በተጨማሪም ይሖዋ የራስነት ሥርዓትን ያቋቋመበትን ምክንያት በተለይ ደግሞ ይሖዋና ኢየሱስ የተዉትን ምሳሌ መከተል የሚችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ያስፈልገዋል። እንዲህ ማድረግ የሚጠበቅበት ለምንድን ነው? ምክንያቱም ይሖዋ ለቤተሰብ ራሶች የተወሰነ ሥልጣን ሰጥቷቸዋል፤ እንዲሁም ይህን ሥልጣናቸውን በአግባቡ እንዲጠቀሙበት ይጠብቅባቸዋል።—ሉቃስ 12:48ለ፤ w21.02 2 አን. 1-3

ረቡዕ፣ መስከረም 28

የሚጠቅምህን ነገር የማስተምርህ . . . እኔ ይሖዋ አምላክህ ነኝ።—ኢሳ. 48:17

አንዳንድ ነገሮችን በመርሳት ይሖዋን መምሰላችን ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ይሖዋ ፍጹም የሆነ የማስታወስ ችሎታ ቢኖረውም ለሠራነው ጥፋት ንስሐ ከገባን ስህተታችንን ይቅር ለማለትና ለመርሳት ፈቃደኛ ነው። (መዝ. 25:7፤ 130:3, 4) እኛም የበደሉን ሰዎች በሠሩት ጥፋት ከተጸጸቱ ተመሳሳይ ነገር እንድናደርግ ይሖዋ ይጠብቅብናል። (ማቴ. 6:14፤ ሉቃስ 17:3, 4) አስደናቂ ስጦታ ለሆነው አንጎላችን ያለንን አድናቆት ማሳየት የምንችልበት አንዱ መንገድ ስጦታውን የሰጠንን አካል በሚያስከብር መንገድ አንጎላችንን መጠቀም ነው። አንዳንዶች አንጎላቸውን የሚጠቀሙበት ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ የራሳቸውን መሥፈርት ለማውጣት ነው። ይሁን እንጂ ፈጣሪያችን ይሖዋ ስለሆነ፣ የእሱ መሥፈርቶች እኛ ለራሳችን ከምናወጣቸው ከየትኞቹም መሥፈርቶች የላቁ እንደሆኑ ጥያቄ የለውም። (ሮም 12:1, 2) የይሖዋን መሥፈርቶች ስንከተል ሰላማዊ ሕይወት መምራት እንችላለን። (ኢሳ. 48:18) በተጨማሪም ፈጣሪያችንን እና አባታችንን በሚያስከብርና እሱን በሚያስደስት መንገድ ስለምንኖር ሕይወታችን እውነተኛ ዓላማ ያለው ይሆናል።—ምሳሌ 27:11፤ w20.05 23-24 አን. 13-14

ሐሙስ፣ መስከረም 29

እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ።—ሮም 12:10

ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ልባዊ ፍቅር ማዳበር የምንችለው እንዴት ነው? የእምነት ባልንጀሮቻችንን እያወቅናቸው ስንሄድ እነሱን መረዳትና ከልብ መውደድ ቀላል ይሆንልናል። ዕድሜ ወይም ያለንበት የተለያየ ሁኔታ እንቅፋት ሊሆንብን አይገባም። ዮናታን ዳዊትን 30 ዓመት ገደማ ይበልጠው እንደነበረ አስታውሱ፤ ሆኖም ይህ ከእሱ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት እንዳይመሠርት አላገደውም። እናንተስ በዕድሜ ከሚበልጧችሁ ወይም ከሚያንሷችሁ የእምነት ባልንጀሮቻችሁ ጋር ወዳጅነት መመሥረት ትችሉ ይሆን? እንዲህ በማድረግ “ለመላው የወንድማማች ማኅበር ፍቅር” እንዳላችሁ ታሳያላችሁ። (1 ጴጥ. 2:17) ለእምነት ባልንጀሮቻችን ልባዊ ፍቅር እናሳያለን ሲባል በጉባኤ ውስጥ ካሉ ሁሉም ክርስቲያኖች ጋር እኩል ቀረቤታ ይኖረናል ማለት ነው? እንዲህ ብሎ ማሰብ ከእውነታው የራቀ ነው። በጋራ በሚያመሳስሉን ነገሮች የተነሳ አንዳንዶችን ከሌሎች አስበልጠን መቅረባችን ስህተት አይደለም። ኢየሱስ ሁሉንም ሐዋርያቱን ‘ወዳጆቼ’ ብሎ የጠራቸው ቢሆንም ዮሐንስን አብልጦ ይወደው ነበር። (ዮሐ. 13:23፤ 15:15፤ 20:2) ሆኖም ኢየሱስ ለዮሐንስ አላዳላም።—ማር. 10:35-40፤ w21.01 23 አን. 12-13

ዓርብ፣ መስከረም 30

ከሌሎች ሰዎች ይበልጥ እናንተ አማልክትን እንደምትፈሩ ማየት ችያለሁ።—ሥራ 17:22

ሐዋርያው ጳውሎስ በአቴንስ ላገኛቸው አሕዛብ መልእክቱን የተናገረው፣ በምኩራብ ውስጥ ላገኛቸው አይሁዳውያን በሰበከበት መንገድ አይደለም። በአካባቢው ያሉትን ነገሮችና ሃይማኖታዊ ልማዶቻቸውን በሚገባ አስተውሏል። (ሥራ 17:23) ከዚያም ጳውሎስ እነሱ አምልኳቸውን የሚያካሂዱበትን መንገድና በቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ የሚገኘውን እውነት በጋራ የሚያስማማ ነገር ለማግኘት ጥረት አድርጓል። ይህም ጳውሎስ አቀራረቡን እንደ ሁኔታው ለማስተካከል ፈቃደኛ እንደነበር ያሳያል። እሱ የሚሰብከው መልእክት የመጣው እነሱ ‘የማይታወቅ አምላክ’ በማለት ከሚያመልኩት አምላክ እንደሆነ ለአቴናውያኑ ነግሯቸዋል። እነዚህ አሕዛብ ቅዱሳን መጻሕፍትን ባያውቁም ጳውሎስ ክርስቲያን የመሆን ተስፋ እንደሌላቸው አላሰበም። ከዚህ ይልቅ ለአጨዳ እንደደረሰ አዝመራ አድርጎ የተመለከታቸው ሲሆን ለእነሱ ሲል ምሥራቹን በሚሰብክበት መንገድ ላይ ማስተካከያ አድርጓል። እናንተም እንደ ጳውሎስ አስተዋይ ሁኑ። በክልላችሁ ያሉ ሰዎች ስለሚያምኑባቸው ነገሮች የሚጠቁሙ ምልክቶችን ፈልጉ። የቤቱ ባለቤት ቤቱ ወይም መኪናው ላይ ምን ዓይነት ጌጥ አድርጓል? የግለሰቡ ስም፣ አለባበስ፣ ፀጉር፣ ጢም ሌላው ቀርቶ የሚጠቀምባቸው ቃላት ስለ ሃይማኖቱ ምን ይጠቁማሉ? w20.04 9-10 አን. 7-8

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ