ጥቅምት
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 1
“ያስተምረው ዘንድ የይሖዋን አስተሳሰብ ያወቀ ማን ነው?” . . . እኛ ግን የክርስቶስ አስተሳሰብ አለን።—1 ቆሮ. 2:16
ኢየሱስን ስናውቀው በአስተሳሰቡና በድርጊቱ እንመስለዋለን። ኢየሱስን ባወቅነውና የእሱ ዓይነት አስተሳሰብ ለመያዝ ጥረት ባደረግን መጠን ደግሞ ከእሱ ጋር ያለን ወዳጅነት እየተጠናከረ ይሄዳል። ታዲያ ኢየሱስን በየትኞቹ መንገዶች መምሰል እንችላለን? እስቲ አንድ ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስን ይበልጥ የሚያሳስበው ሌሎችን መርዳት እንጂ ራሱን ማስደሰት አልነበረም። (ማቴ. 20:28፤ ሮም 15:1-3) ኢየሱስ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ ስለነበረው የራሱን ጥቅም መሥዋዕት የሚያደርግና ይቅር ባይ ሰው ነበር። ሰዎች ስለ እሱ በሚናገሩት ነገር ቶሎ አይበሳጭም ነበር። (ዮሐ. 1:46, 47) በተጨማሪም ቀደም ሲል ስህተት የሠሩ ሰዎች ለውጥ ሊያደርጉ እንደማይችሉ አያስብም ነበር። (1 ጢሞ. 1:12-14) ኢየሱስ ለሌሎች የነበረውን አመለካከት ማንጸባረቃችን አስፈላጊ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ “እርስ በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ ሰዎች ሁሉ ደቀ መዛሙርቴ እንደሆናችሁ በዚህ ያውቃሉ” ብሏል። (ዮሐ. 13:35) እንግዲያው ‘ከወንድሞቼና ከእህቶቼ ጋር በሰላም ለመኖር ስል የምችለውን ሁሉ በማድረግ የኢየሱስን ምሳሌ እየተከተልኩ ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። w20.04 24 አን. 11
እሁድ፣ ጥቅምት 2
ስሜን ይቀድሳሉ።—ኢሳ. 29:23
የምንኖረው የይሖዋን ስም የሚያጠፉና የሚሳደቡ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ቢሆንም ከይሖዋ ጎን በመቆም እውነቱን መናገር ትችላለህ፤ ይሖዋ ቅዱስ፣ ጻድቅ፣ ጥሩና አፍቃሪ አምላክ መሆኑን መናገር ትችላለህ። በተጨማሪም የይሖዋን አገዛዝ መደገፍ ትችላለህ። በጽድቅ ላይ የተመሠረተው እንዲሁም ለፍጥረታት ሁሉ ሰላምና ደስታ የሚያስገኘው የይሖዋ አገዛዝ ብቻ እንደሆነ መግለጽ ትችላለህ። (መዝ. 37:9, 37፤ 146:5, 6, 10) ለሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ስናስተምር ብዙ ጊዜ ጎላ አድርገን የምንገልጸው የአምላክን ሉዓላዊነት ይኸውም ይሖዋ አጽናፈ ዓለምን የመግዛት መብት ያለው መሆኑን ነው፤ ደግሞም ይህ እውነት ነው። ሰዎችን ስለ አምላክ ሕግጋት ማስተማራችን አስፈላጊ ቢሆንም ዋናው ዓላማችን ሰዎች አባታችንን ይሖዋን እንዲወዱትና ለእሱ ታማኝ እንዲሆኑ መርዳት ነው። ለዚህ ሲባል የይሖዋን ተወዳጅ ባሕርያት ጎላ አድርገን መግለጽ ያስፈልገናል፤ ይሖዋ በሚለው ስም የሚጠራውን አምላክ ማንነት እንዲያውቁ መርዳት ይኖርብናል። (ኢሳ. 63:7) በዚህ መንገድ ስናስተምር ሰዎች፣ ይሖዋን እንዲወዱትና ለእሱ ባላቸው ታማኝነት ተነሳስተው እሱን እንዲታዘዙት መርዳት እንችላለን። w20.06 6 አን. 16፤ 7 አን. 19
ሰኞ፣ ጥቅምት 3
ለሰው አፍ የፈጠረለት ማን ነው? . . . እኔ ይሖዋ አይደለሁም?—ዘፀ. 4:11
አንጎላችን አስደናቂ ንድፍ የተንጸባረቀበት የአካላችን ክፍል ነው። በእናትህ ማህፀን ውስጥ በነበርክበት ወቅት፣ አንጎልህ አስቀድሞ የተቀመጠለትን ንድፍ ተከትሎ ተሠርቷል፤ በየደቂቃው በሺዎች የሚቆጠሩ አዳዲስ የአንጎል ሴሎች ይሠሩ ነበር! የአንድ አዋቂ ሰው አንጎል፣ ኒውሮን ተብለው የሚጠሩ 100 ቢሊዮን ገደማ የሚሆኑ ሴሎች እንዳሉት ተመራማሪዎች ይገምታሉ። ወደ 1.5 ኪሎ ግራም ገደማ ክብደት ያለው አንጎላችን የተገነባው በእነዚህ ሴሎች ነው። አንጎላችን ካሉት አስደናቂ ችሎታዎች መካከል አንዱ የመናገር ችሎታችን ነው። በምንናገርበት ወቅት ምን እንደሚከናወን እስቲ ለአንድ አፍታ አስብ። እያንዳንዱን ቃል ስትጠራ አንጎልህ በምላስህ፣ በጉሮሮህ፣ በከንፈሮችህ፣ በመንገጭላህ እና በደረትህ ላይ የሚገኙ ወደ 100 የሚጠጉ ጡንቻዎችን እንቅስቃሴ ማቀናጀት ያስፈልገዋል። የምትናገራቸው ቃላት ጥርት ብለው መሰማት እንዲችሉ እነዚህ ጡንቻዎች ትክክለኛውን ቅደም ተከተል ጠብቀው መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል። በ2019 የወጣ አንድ ጥናት እንደሚጠቁመው አራስ ሕፃናት ቃላትን ነጥለው የማወቅ ችሎታ አላቸው። ይህ ግኝት፣ ስንወለድ ጀምሮ ቋንቋን ለይተን የማወቅና የመማር ችሎታ እንዳለን የሚያሳይ ነው። በእርግጥም የመናገር ችሎታችን ከአምላክ ያገኘነው ስጦታ ነው። w20.05 22-23 አን. 8-9
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 4
አምላክ ንድፍ ያወጣላትንና የገነባትን፣ እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ ይጠባበቅ ነበር።—ዕብ. 11:10
አብርሃም በዑር ከተማ የነበረውን የተደላደለ ሕይወት ትቶ ለመውጣት ፈቃደኛ ሆኗል። ለምን? “እውነተኛ መሠረት ያላትን ከተማ” ይጠባበቅ ስለነበር ነው። (ዕብ. 11:8-10, 16) አብርሃም ይጠባበቃት የነበረችው ከተማ የአምላክን መንግሥት ታመለክታለች። ይህ መንግሥት በኢየሱስ ክርስቶስና በ144,000 ቅቡዓን ክርስቲያኖች የተዋቀረ ነው። ጳውሎስ ይህን መንግሥት ‘የሕያው አምላክ ከተማ የሆነችው ሰማያዊቱ ኢየሩሳሌም’ በማለት ጠርቶታል። (ዕብ. 12:22፤ ራእይ 5:8-10፤ 14:1) ኢየሱስ “መንግሥትህ ይምጣ” ብለው እንዲጸልዩ ደቀ መዛሙርቱን አስተምሯቸዋል፤ እንዲህ ብለው ሲጸልዩ የአምላክ ፈቃድ በሰማይ እየተፈጸመ እንዳለ ሁሉ በምድርም ላይ እንዲፈጸም መጠየቃቸው ነው። (ማቴ. 6:10) አብርሃም የአምላክ መንግሥት ስለሚዋቀርበት መንገድ ዝርዝር ነገሮችን ያውቅ ነበር? አያውቅም ነበር። እነዚህ ነገሮች ለበርካታ መቶ ዘመናት “ቅዱስ ሚስጥር” ነበሩ። (ኤፌ. 1:8-10፤ ቆላ. 1:26, 27) ሆኖም አብርሃም የእሱ ዘር የሆኑ አንዳንዶች፣ ነገሥታት እንደሚሆኑ ያውቅ ነበር። ይሖዋ ይህ እንደሚሆን ቃል ገብቶለት ነበር።—ዘፍ. 17:1, 2, 6፤ w20.08 2-3 አን. 2-4
ረቡዕ፣ ጥቅምት 5
[ከጌታ] ጋር በአንድነት መመላለሳችሁን ቀጥሉ፤ . . . በእሱ ላይ ሥር ሰዳችሁና ታንጻችሁ ኑሩ፤ እንዲሁም በእምነት ጸንታችሁ መኖራችሁን ቀጥሉ።—ቆላ. 2:6, 7
የከሃዲዎችን ትምህርት መቃወም አለብን። የክርስቲያን ጉባኤ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ ዲያብሎስ በርካታ አታላይ ሰዎችን በመጠቀም በአምላክ ታማኝ አገልጋዮች አእምሮ ውስጥ ጥርጣሬ ለመዝራት ሲሞክር ቆይቷል። በመሆኑም እውነቱን ከውሸቱ የመለየት ችሎታ ልናዳብር ይገባል። ጠላቶቻችን በኢንተርኔት ወይም በማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቅመው በይሖዋ ላይ ያለንን እምነትና ለወንድሞቻችን ያለንን ፍቅር ለማዳከም ሊሞክሩ ይችላሉ። እንዲህ ካለው ፕሮፓጋንዳ በስተ ጀርባ ያለው ማን እንደሆነ በማስታወስ አጥብቃችሁ ተቃወሙት! (1 ዮሐ. 4:1, 6፤ ራእይ 12:9) የሰይጣንን ጥቃቶች ለመቋቋም በኢየሱስና እሱ በአምላክ ዓላማ ውስጥ በሚጫወተው ሚና ላይ ያለንን እምነት ማጠናከር ይኖርብናል። በተጨማሪም ይሖዋ በዚህ ዘመን ድርጅቱን ለመምራት በሚጠቀምበት ብቸኛ መስመር ላይ እምነት ማሳደር አለብን። (ማቴ. 24:45-47) የአምላክን ቃል አዘውትረን በማጥናት እምነታችንን ማጠናከር እንችላለን። እንዲህ ስናደርግ እምነታችን ሥሩን መሬት ውስጥ በጥልቀት እንደሰደደ ዛፍ ይሆናል። ሐዋርያው ጳውሎስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን መልእክት በጻፈበት ወቅት ተመሳሳይ ሐሳብ ተናግሯል። w20.07 23-24 አን. 11-12
ሐሙስ፣ ጥቅምት 6
ሰው የሚያየው ውጫዊ ገጽታን ነው፤ ይሖዋ ግን የሚያየው ልብን ነው።—1 ሳሙ. 16:7
ፍጹማን ባለመሆናችን ሁላችንም የሰዎችን ውጫዊ ገጽታ ተመልክተን መፍረድ ይቀናናል። (ዮሐ. 7:24) ሆኖም ከውጭ በሚታየው ነገር ብቻ ስለ አንድ ሰው ልናውቅ የምንችለው ነገር በጣም ውስን ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ጥሩ ችሎታ ያለውና ተሞክሮ ያካበተ ሐኪምም እንኳ ታካሚውን ከውጭ በመመልከት ብቻ ሊያውቅ የሚችለው ነገር ጥቂት ነው። የታካሚውን የሕክምና ታሪክ፣ ያለበት ሁኔታ ያሳደረበትን ስሜት ወይም በእሱ ላይ ስለሚታዩት የበሽታ ምልክቶች ሊያውቅ የሚችለው ታካሚውን በጥሞና ካዳመጠው ነው። እንዲያውም ሐኪሙ፣ የታካሚውን ውስጣዊ የሰውነት ክፍሎች ለማየት ምርመራ ያዝለት ይሆናል። አለዚያ ግን ሐኪሙ የግለሰቡን ሕመም በተመለከተ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ሊደርስ ይችላል። እኛም በተመሳሳይ የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን ውጫዊ ገጽታ በመመልከት ብቻ ስለ እነሱ በሚገባ ማወቅ አንችልም። ከውጭ ከሚታየው ነገር አልፈን ውስጣዊ ማንነታቸውን ለማወቅ መጣር ይኖርብናል። በእርግጥ የሰዎችን ልብ ማንበብ አንችልም። ሆኖም ይሖዋን ለመምሰል የቻልነውን ያህል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ይሖዋ አገልጋዮቹን ያዳምጣቸዋል። በማንነታቸው ላይ ተጽዕኖ ያሳደሩ ነገሮችንና ያሉበትን ሁኔታ ግምት ውስጥ ያስገባል። እንዲሁም ርኅራኄ ያሳያቸዋል። w20.04 14-15 አን. 1-3
ዓርብ፣ ጥቅምት 7
ጤናማ አስተሳሰብ [እንዳላችሁ] በሚያሳይ መንገድ [አስቡ]።—ሮም 12:3
ትሕትና ማዳበር የሚያስፈልገን ኩራተኛ የሆኑ ሰዎች “ጤናማ አስተሳሰብ” ስለሌላቸው ነው። ኩራተኛ የሆኑ ሰዎች ጠበኛና ትምክህተኛ ናቸው። አብዛኛውን ጊዜ አስተሳሰባቸውና ድርጊታቸው ራሳቸውንም ሆነ ሌሎችን ይጎዳል። አስተሳሰባቸውን ካላስተካከሉ ሰይጣን አእምሯቸውን ያሳውረዋል እንዲሁም ያበላሸዋል። (2 ቆሮ. 4:4፤ 11:3) ትሑት ሰው ጤናማ አስተሳሰብ አለው። ሌሎች በብዙ መንገዶች ከእሱ እንደሚበልጡ ስለሚገነዘብ ለራሱ ሚዛናዊና ምክንያታዊ የሆነ አመለካከት አለው። (ፊልጵ. 2:3) በተጨማሪም ‘አምላክ ትዕቢተኞችን እንደሚቃወምና ለትሑታን ጸጋን እንደሚሰጥ’ ያውቃል። (1 ጴጥ. 5:5) ጤናማ አስተሳሰብ ያለው ሰው የይሖዋ ጠላት መሆን አይፈልግም። ምንጊዜም ትሑት ለመሆን ከፈለግን “አሮጌውን ስብዕና ከነልማዶቹ ገፋችሁ ጣሉ፤ እንዲሁም . . . አዲሱን ስብዕና ልበሱ” የሚለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሥራ ላይ ማዋል አለብን። ኢየሱስ የተወውን ምሳሌ መመርመርና አቅማችን በፈቀደ መጠን ምሳሌውን ለመከተል ጥረት ማድረግ ይኖርብናል።—ቆላ. 3:9, 10፤ 1 ጴጥ. 2:21፤ w20.07 7 አን. 16-17
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 8
አካል አንድ ቢሆንም ብዙ የአካል ክፍሎች [አሉት]።—1 ቆሮ. 12:12
በይሖዋ ጉባኤ ውስጥ መታቀፍ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! የምንኖረው ሰላማዊና ደስተኛ ሰዎች በሞሉበት መንፈሳዊ ገነት ውስጥ ነው። ታዲያ አንተ በጉባኤው ውስጥ ያለህ ቦታ ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ ጉባኤውን ከሰው አካል ጋር አነጻጽሮታል። በጉባኤው ውስጥ ያሉትን ሰዎች ደግሞ ከሰው አካል ክፍሎች ጋር አመሳስሏቸዋል። (ሮም 12:4-8፤ 1 ቆሮ. 12:12-27፤ ኤፌ. 4:16) ከጳውሎስ ምሳሌ የምናገኘው አንዱ ትምህርት፣ እያንዳንዳችን በይሖዋ ቤተሰብ ውስጥ አስፈላጊ ድርሻ ያለን መሆኑን ነው። ጳውሎስ ምሳሌውን የጀመረው እንዲህ በማለት ነው፦ “በአንድ አካል ላይ ብዙ የአካል ክፍሎች አሉን፤ ደግሞም ሁሉም የአካል ክፍሎች አንድ ዓይነት ተግባር አያከናውኑም፤ ልክ እንደዚሁ እኛም ብዙ ብንሆንም እንኳ ከክርስቶስ ጋር ባለን አንድነት አንድ አካል ነን፤ ደግሞም አንዳችን የሌላው የአካል ክፍል ነን።” (ሮም 12:4, 5) ጳውሎስ ምን ማለቱ ነበር? እያንዳንዳችን በጉባኤው ውስጥ የተለያየ ድርሻ ቢኖረንም ሁላችንም ጠቃሚ ቦታ እንዳለን መግለጹ ነበር። w20.08 20 አን. 1-2, 4
እሁድ፣ ጥቅምት 9
ይሖዋም “እንዴት አድርገህ?” አለው።—1 ነገ. 22:21
ወላጆች ይሖዋ በትሕትና ረገድ የተወውን ምሳሌ መከተል የምትችሉት እንዴት ነው? ተገቢ በሚሆንበት ጊዜ፣ አንድ ሥራ የሚከናወንበትን መንገድ በተመለከተ ሐሳብ እንዲሰጡ ልጆቻችሁን ጠይቋቸው። የሚቻል ከሆነም፣ የሚሰጡትን ሐሳብ ተግባራዊ አድርጉት። በተጨማሪም ይሖዋ አገልጋዮቹ ውሳኔውን በተመለከተ ጥያቄ በሚያነሱበት ጊዜም እንኳ ትዕግሥት በማሳየት ምሳሌ ትቷል። ሰዶምንና ገሞራን ለማጥፋት በወሰነበት ወቅት አብርሃም ይህን በተመለከተ ያሳሰበውን ነገር ሲገልጽ አምላክ አዳምጦታል። (ዘፍ. 18:22-33) ይሖዋ የአብርሃም ሚስት የሆነችውን ሣራን የያዘበትን መንገድም እናስታውስ። ሣራ በስተርጅናዋ እንደምትፀንስ ይሖዋ በገባው ቃል ስቃ ነበር፤ ይሖዋ ግን በዚህ ቅር አልተሰኘም ወይም አልተቆጣም። (ዘፍ. 18:10-14) እንዲያውም ሣራን በአክብሮት ይዟታል። ወላጆች እና ሽማግሌዎች፣ ከይሖዋ ምሳሌ ምን መማር ትችላላችሁ? ልጆቻችሁ ወይም በጉባኤው ውስጥ ያሉ አንዳንዶች፣ በውሳኔያችሁ ላይ ጥያቄ ሲያነሱ ምን ምላሽ እንደምትሰጡ ለማሰብ ሞክሩ። ወዲያውኑ እነሱን ለማረም ትሞክራላችሁ? ወይስ አመለካከታቸውን ለመረዳት ትጥራላችሁ? ኃላፊነት ያላቸው ሰዎች ይሖዋን የሚመስሉ ከሆነ ቤተሰቦችም ሆኑ ጉባኤዎች በእጅጉ ይጠቀማሉ። w20.08 10 አን. 7-9
ሰኞ፣ ጥቅምት 10
ኃይሌ ፍጹም የሚሆነው በምትደክምበት ጊዜ ነው።—2 ቆሮ. 12:9
እውነትን በሰማንበት ወቅት በመንፈሳዊ ሕፃናት እንደሆንንና የምንማራቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ ስለምንገነዘብ የሌሎችን እርዳታ ለመቀበል እንጓጓ ነበር። (1 ቆሮ. 3:1, 2) አሁንስ? በይሖዋ አገልግሎት በርካታ ዓመታት ካሳለፍንና ብዙ ተሞክሮ ካካበትን እንደ ቀድሞው የሌሎችን እርዳታ መቀበል ላይቀለን ይችላል፤ በተለይ እርዳታ የሚሰጠን ሰው የእኛን ያህል እውነት ውስጥ ካልቆየ እርዳታውን መቀበል ሊከብደን ይችላል። ይሁንና ይሖዋ አብዛኛውን ጊዜ እኛን ለማበረታታት በወንድሞቻችንና በእህቶቻችን ይጠቀማል። (ሮም 1:11, 12) ይሖዋ የሚሰጠውን ኃይል ማግኘት ከፈለግን ይህን እውነታ አምነን መቀበል ይኖርብናል። አንድ ሰው ስኬት ማግኘቱ የተመካው በአካላዊ ጥንካሬው፣ በትምህርት ደረጃው፣ በሀብቱ ወይም በማኅበረሰቡ ውስጥ ባለው ቦታ ላይ ሳይሆን በትሕትናውና በይሖዋ በመመካቱ ላይ ነው። ሁላችንም (1) በይሖዋ በመመካት፣ (2) ከመጽሐፍ ቅዱስ ምሳሌዎች በመማር እንዲሁም (3) የእምነት ባልንጀሮቻችንን እርዳታ በመቀበል ወደፊት እንግፋ። እንዲህ ካደረግን በጣም ደካማ እንደሆንን ቢሰማንም እንኳ ይሖዋ ብርቱ ያደርገናል! w20.07 14 አን. 2፤ 19 አን. 18-19
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 11
እያንዳንዳችሁ ያንኑ ትጋት [አሳዩ]፤ ይህም አምላክ ቃል የገባቸውን ነገሮች በእምነትና በትዕግሥት የሚወርሱትን እንድትመስሉ እንጂ ዳተኞች እንዳትሆኑ ነው።—ዕብ. 6:11, 12
ትዕግሥት ማሳየት ከባድ እንዲሆንብን ከሚያደርጉ ሁኔታዎች አንዱ ለማያምኑ የቤተሰባችን አባላት መመሥከር ነው። በዚህ ረገድ በመክብብ 3:7 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ይጠቅመናል። ጥቅሱ “ዝም ለማለት ጊዜ አለው፤ ለመናገርም ጊዜ አለው” ይላል። በምናሳየው መልካም ምግባር፣ ያለቃል ግሩም ምሥክርነት መስጠት እንችላለን፤ ሆኖም እውነትን ለመናገር የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች በንቃት መከታተል የለብንም ማለት አይደለም። (1 ጴጥ. 3:1, 2) ምሥራቹን በቅንዓት ስንሰብክና ስናስተምር የቤተሰባችንን አባላት ጨምሮ ሁሉንም ሰው በትዕግሥት ለመያዝ እንጥራለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከተጠቀሱም ሆነ በዘመናችን ካሉ ታማኝ ሰዎች ስለ ትዕግሥት መማር እንችላለን። ዕንባቆም ክፋት የሚወገድበትን ጊዜ ለማየት ይጓጓ ነበር፤ ያም ቢሆን “በንቃት እጠባበቃለሁ” በማለት ያን ጊዜ በትዕግሥት እንደሚጠባበቅ አሳይቷል። (ዕን. 2:1) ሐዋርያው ጳውሎስ አገልግሎቱን ‘ለማጠናቀቅ’ ከልቡ እንደሚፈልግ ገልጿል። ይሁንና ታጋሽ በመሆን ‘ምሥራቹን በተሟላ ሁኔታ መመሥከሩን’ ቀጥሏል።—ሥራ 20:24፤ w20.09 11-12 አን. 12-14
ረቡዕ፣ ጥቅምት 12
[ኢየሱስ] የሥልጣን ቦታን ለመቀማት ማለትም ከአምላክ ጋር እኩል ለመሆን አላሰበም።—ፊልጵ. 2:6
ኢየሱስ ከይሖዋ ቀጥሎ ያለውን ሥልጣን የያዘ ቢሆንም ከሚገባው በላይ ስለ ራሱ በማሰብ ራሱን ከፍ አድርጎ አልተመለከተም። ትሑት የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ የሆነው ፍቅር እንዲሰፍን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ያበረክታሉ። (ሉቃስ 9:48፤ ዮሐ. 13:35) በጉባኤህ ውስጥ ተገቢው መፍትሔ ያልተሰጠው ችግር እንዳለ ቢሰማህስ? ከማጉረምረም ይልቅ አመራር የሚሰጡትን ወንድሞች በመደገፍ ትሕትና ማሳየት ትችላለህ። (ዕብ. 13:17) ለዚህ እንዲረዳህ እንደሚከተለው በማለት ራስህን ጠይቅ፦ ‘በእርግጥ ጉዳዩ መፍትሔ የሚያሻው አሳሳቢ ችግር ነው? ችግሩን ለማስተካከል ጊዜው አሁን ነው? ችግሩን ማስተካከል የእኔ ኃላፊነት ነው? በእርግጥ ያሳሰበኝ በጉባኤው ውስጥ አንድነት የመስፈኑ ጉዳይ ነው ወይስ ራሴን ከፍ ከፍ ለማድረግ እየሞከርኩ ነው?’ ይሖዋ ከችሎታ ይልቅ ለትሕትና፣ ከቅልጥፍና ይልቅ ደግሞ ለአንድነት ቦታ ይሰጣል። በመሆኑም ይሖዋን በትሕትና ለማገልገል የተቻለህን ጥረት አድርግ። እንዲህ ካደረግክ በጉባኤው ውስጥ አንድነት እንዲሰፍን አስተዋጽኦ ታበረክታለህ።—ኤፌ. 4:2, 3፤ w20.07 4-5 አን. 9-11
ሐሙስ፣ ጥቅምት 13
ኢየሱስ “አትፍሩ! ሂዱና [ለወንድሞቼ ንገሯቸው]” አላቸው።—ማቴ. 28:10
ኢየሱስ ‘በንብረታቸው ያገለግሉት’ የነበሩ ታማኝ ሴቶች የሚያደርጉለትን እርዳታ ያደንቅ ነበር። (ሉቃስ 8:1-3) ለእነዚህ ሴቶች ጥልቅ መንፈሳዊ እውነቶችን አካፍሏቸዋል። ለምሳሌ፣ እንደሚሞትና ከሞት እንደሚነሳ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 24:5-8) ለሐዋርያቱ እንዳደረገው ሁሉ እነዚህን ሴቶችም ወደፊት ለሚጠብቃቸው ፈተና አዘጋጅቷቸዋል። (ማር. 9:30-32፤ 10:32-34) ኢየሱስን ያገለግሉ ከነበሩት ከእነዚህ ሴቶች አንዳንዶቹ በመከራ እንጨት ላይ ተሰቅሎ በነበረበት ወቅት ከጎኑ አለመለየታቸው ትኩረት የሚስብ ነው፤ ምክንያቱም ኢየሱስ በተያዘበት ወቅት ሐዋርያቱ ጥለውት ሸሽተው ነበር። (ማቴ. 26:56፤ ማር. 15:40, 41) የኢየሱስ ትንሣኤ የመጀመሪያዎቹ ምሥክሮች አምላክን የሚፈሩ ሴቶች ነበሩ። ኢየሱስ፣ ከሞት መነሳቱን ለሐዋርያቱ እንዲነግሩ እነዚህን ሴቶች ልኳቸዋል። (ማቴ. 28:5, 9, 10) በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ በዓል ላይ መንፈስ ቅዱስ በፈሰሰበት ወቅት በቦታው ሴቶች ተገኝተው ሊሆን ይችላል። በዚያ የተገኙ ሁሉ ደግሞ በሌሎች ቋንቋዎች የመናገር ተአምራዊ ችሎታ የተሰጣቸው ከመሆኑም ሌላ “ስለ አምላክ ታላቅ ሥራ” ለሰዎች የመመሥከር አጋጣሚ አግኝተዋል።—ሥራ 1:14፤ 2:2-4, 11፤ w20.09 23 አን. 11-12
ዓርብ፣ ጥቅምት 14
ለራስህና ለምታስተምረው ትምህርት ምንጊዜም ትኩረት ስጥ።—1 ጢሞ. 4:16
ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ሥራ ሕይወት አድን ነው! ይህን እንዴት እናውቃለን? ኢየሱስ በማቴዎስ 28:19, 20 ላይ የሚገኘውን ትእዛዝ ሲሰጥ ‘ሂዱና ሰዎችን እያጠመቃችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ ብሎ ነበር። ጥምቀት ምን ያህል አስፈላጊ ነው? መዳን ለማግኘት የሚያስፈልግ ብቃት ነው። እጩ ተጠማቂው፣ የመዳን በር የተከፈተው ኢየሱስ መሥዋዕታዊ ሞት በመሞቱና ከሞት በመነሳቱ መሆኑን ሊያምን ይገባል። ሐዋርያው ጴጥሮስ የእምነት አጋሮቹን “ጥምቀት በኢየሱስ ክርስቶስ ትንሣኤ አማካኝነት እናንተን እያዳናችሁ ነው” ያላቸው ለዚህ ነው። (1 ጴጥ. 3:21) በመሆኑም አንድ ሰው ሲጠመቅ መዳን የማግኘት አጋጣሚ ይከፈትለታል። ሰዎችን ደቀ መዛሙርት ለማድረግ ‘የማስተማር ጥበብ’ ማዳበር ይኖርብናል። (2 ጢሞ. 4:1, 2) ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ ያዘዘን ‘ሂዱና ሰዎችን እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው’ በማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስም በዚህ ሥራ ‘መጽናት’ እንደሚያስፈልግ ተናግሯል፤ ምክንያቱም ‘ይህን በማድረግ ራሳችንንም ሆነ የሚሰሙንን እናድናለን።’ w20.10 14 አን. 1-2
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 15
ከአሁን ጀምሮ ሰውን የምታጠምድ ትሆናለህ።—ሉቃስ 5:10
ደቀ መዝሙሩ ጴጥሮስ፣ ሰው የማጥመድ ሥራውን ወዶታል። ደግሞም በይሖዋ እርዳታ ጴጥሮስ በዚህ ሥራ ውጤታማ መሆን ችሏል። (ሥራ 2:14, 41) የምንሰብከው ይሖዋን ስለምንወደው ነው፤ በዚህ ሥራ ለመካፈል የሚያነሳሳን ዋነኛው ምክንያት ይህ ነው። ለይሖዋ ያለን ፍቅር ‘ብቃት የለኝም’ የሚለውን ስሜት ለማሸነፍ ይረዳናል። ኢየሱስ ጴጥሮስን ሰው አጥማጅ እንዲሆን በጋበዘው ወቅት “አይዞህ አትፍራ” ብሎት ነበር። (ሉቃስ 5:8-11) ጴጥሮስን ያስፈራው ‘ደቀ መዝሙር ብሆን ምን ያጋጥመኛል?’ የሚለው ስጋት አልነበረም። ኢየሱስ፣ እሱንና የሥራ ባልደረቦቹን ብዙ ዓሣ እንዲይዙ በተአምር በረዳቸው ወቅት ጴጥሮስ በጣም ተደንቆ ነበር፤ በመሆኑም እንዲህ ያለ ተአምር ከፈጸመው ከኢየሱስ ጋር መሥራት የሚገባው ሰው እንደሆነ አልተሰማውም። በሌላ በኩል ግን አንተን የሚያስፈራህ፣ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆን ምን ነገሮችን እንደሚጨምር መገንዘብህ ሊሆን ይችላል። ከሆነ ለይሖዋ፣ ለኢየሱስና ለባልንጀራህ ያለህ ፍቅር እንዲጨምር ጥረት አድርግ፤ ይህን ስታደርግ ኢየሱስ ሰው አጥማጅ እንድትሆን ያቀረበልህን ግብዣ ለመቀበል ትነሳሳለህ።—ማቴ. 22:37, 39፤ ዮሐ. 14:15፤ w20.09 3 አን. 4-5
እሁድ፣ ጥቅምት 16
ሂዱና . . . እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው።—ማቴ. 28:19, 20
“ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎችን ለመፈለግ ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እና ንብረታችንን በደስታ እንሰጣለን። (ሥራ 13:48) እንዲህ በማድረግ የኢየሱስን ምሳሌ እንከተላለን። ኢየሱስ “የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግና እንዳከናውነው የሰጠኝን ሥራ መፈጸም ነው” ብሏል። (ዮሐ. 4:34፤ 17:4) የእኛም ልባዊ ምኞት ይህ ነው። በአደራ የተሰጠንን ሥራ ማጠናቀቅ እንፈልጋለን። (ዮሐ. 20:21) በተጨማሪም የቀዘቀዙ አስፋፊዎችን ጨምሮ ሌሎችም በዚህ ሥራ አብረውን እንዲጸኑ እንፈልጋለን። (ማቴ. 24:13) ኢየሱስ የሰጠንን ታላቅ ተልእኮ መፈጸም ቀላል እንዳልሆነ የታወቀ ነው። ሆኖም ይህንን ሥራ የምንሠራው ብቻችንን አይደለም። ኢየሱስ አብሮን እንደሚሆን ቃል ገብቷል። ደቀ መዛሙርት የማድረጉ ተልእኮ “ከአምላክ ጋር አብረን [የምንሠራው]” ሥራ ነው፤ በተጨማሪም ይህ “ከክርስቶስ ጋር በመተባበር” የምናከናውነው ሥራ ነው። (1 ቆሮ. 3:9፤ 2 ቆሮ. 2:17) በመሆኑም ሊሳካልን ይችላል። ይህን ተልእኮ መፈጸም እና ሌሎችም እንዲህ እንዲያደርጉ መርዳት እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው፤ ደግሞም ታላቅ ደስታ ያስገኛል!—ፊልጵ. 4:13፤ w20.11 7 አን. 19-20
ሰኞ፣ ጥቅምት 17
ኢየሱስም በአካልና በጥበብ እያደገ እንዲሁም በአምላክና በሰው ፊት ይበልጥ ሞገስ እያገኘ ሄደ።—ሉቃስ 2:52
አብዛኛውን ጊዜ ወላጆች የሚያደርጉት ምርጫ በልጆቻቸው ላይ ለረጅም ጊዜ የሚዘልቅ ተጽዕኖ ያሳድራል። ወላጆች መጥፎ ምርጫ ካደረጉ ልጆቻቸው ለችግር ሊዳረጉ ይችላሉ። ጥሩ ምርጫ ካደረጉ ግን ልጆቻቸው ደስተኛና አርኪ ሕይወት የሚኖሩበት ከሁሉ የተሻለ አጋጣሚ ያገኛሉ። እርግጥ ነው፣ ልጆችም ጥሩ ውሳኔዎች ማድረግ ይኖርባቸዋል። አንድ ሰው ሊያደርገው የሚችለው ከሁሉ የተሻለ ውሳኔ አፍቃሪ አባታችን የሆነውን ይሖዋን ማገልገል ነው። (መዝ. 73:28) የኢየሱስ ወላጆች፣ ልጆቻቸው ይሖዋን እንዲያገለግሉ ለመርዳት ቁርጥ ውሳኔ አድርገው ነበር፤ ያደረጓቸው ምርጫዎች በሕይወታቸው ውስጥ ዋነኛው ግባቸው ይህ እንደነበር ይጠቁማሉ። (ሉቃስ 2:40, 41, 52) ኢየሱስም ቢሆን በይሖዋ ዓላማ ውስጥ ያለውን ድርሻ ለመወጣት የሚረዱትን ጥሩ ምርጫዎች አድርጓል። (ማቴ. 4:1-10) ኢየሱስ አድጎ ደግ፣ ታማኝና ደፋር ሰው ሆኗል፤ ፈሪሃ አምላክ ያለው ማንኛውም ወላጅ እንዲህ ያለ ልጅ ቢኖረው እንደሚኮራና እንደሚደሰት የታወቀ ነው። w20.10 26 አን. 1-2
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 18
ዓይኖችህ በቀጥታ ይዩ።—ምሳሌ 4:25
እስቲ ስለሚከተሉት ሁኔታዎች አስብ። አንዲት አረጋዊት እህት ያሳለፉትን አስደሳች ሕይወት በትዝታ ያስታውሳሉ። በአሁኑ ወቅት ሕይወት ከባድ ቢሆንባቸውም ይሖዋን ለማገልገል የሚችሉትን ሁሉ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል። (1 ቆሮ. 15:58) ከወዳጆቻቸውና ከቤተሰባቸው ጋር በአዲሱ ዓለም ውስጥ ሲኖሩ በየቀኑ በዓይነ ሕሊናቸው ይታያቸዋል። አንዲት ሌላ እህት በአንድ የእምነት ባልንጀራዋ የተጎዳችበትን ወቅት ጨርሶ ባትረሳውም ቂም ላለመያዝ መርጣለች። (ቆላ. 3:13) አንድ ወንድም ደግሞ ቀደም ሲል የፈጸማቸውን ስህተቶች ባይረሳቸውም ከዚህ በኋላ ባለው ሕይወቱ ታማኝ ለመሆን ማድረግ በሚችለው ነገር ላይ ያተኩራል። (መዝ. 51:10) እነዚህን ሦስት ክርስቲያኖች የሚያመሳስላቸው ነገር ምንድን ነው? ሦስቱም ቀደም ሲል የገጠማቸውን ነገር አልረሱትም፤ ሆኖም ስለዚያ ነገር እያሰቡ አይብሰለሰሉም። ከዚህ ይልቅ የወደፊቱን ጊዜ ‘በትኩረት ይመለከታሉ።’ እንዲህ ማድረግ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? አንድ ሰው አሥር ጊዜ ወደ ኋላ እየተመለከተ ወደ ፊት ቀጥ ብሎ መራመድ አይችልም፤ እኛም በተመሳሳይ ስላሳለፍነው ሕይወት ነጋ ጠባ የምናስብ ከሆነ በይሖዋ አገልግሎት ወደ ፊት መግፋት አንችልም።—ሉቃስ 9:62፤ w20.11 24 አን. 1-3
ረቡዕ፣ ጥቅምት 19
ትኩር ብሎ ሲያየው . . . ናቀው።—1 ሳሙ. 17:42
ኃያል ተዋጊ የሆነው ጎልያድ ዳዊትን እንደ ደካማ አድርጎ ተመልክቶት ነበር። ደግሞም ጎልያድ ግዙፍ እንዲሁም በሚገባ የታጠቀና ጥሩ ሥልጠና ያገኘ ጦረኛ ነበር። ዳዊት ግን የጦርነት ልምድ የሌለውና የጦር ትጥቅ ያልለበሰ ትንሽ ልጅ ነው። ይሁንና ዳዊት በይሖዋ ኃይል በመታመን ጠላቱን ድል አድርጓል። (1 ሳሙ. 17:41-45, 50) ዳዊት ደካማና አቅመ ቢስ እንደሆነ እንዲሰማው ሊያደርግ የሚችል ሌላም ፈታኝ ሁኔታ አጋጥሞት ነበር። ዳዊት ይሖዋ የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ የሾመውን ሳኦልን በታማኝነት ያገለግል ነበር። ንጉሥ ሳኦል መጀመሪያ ላይ ለዳዊት አክብሮት ነበረው። ከጊዜ በኋላ ግን ሳኦል ኩራት ስለተጠናወተው በዳዊት ቀና። በመሆኑም ሳኦል በዳዊት ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀመረ፤ እንዲያውም ሊገድለው ሞክሮ ነበር። (1 ሳሙ. 18:6-9, 29፤ 19:9-11) ንጉሥ ሳኦል ዳዊትን ቢበድለውም ዳዊት ይሖዋ ለቀባው ንጉሥ አክብሮት ማሳየቱን ቀጥሏል። (1 ሳሙ. 24:6) ዳዊት ይሖዋ ያንን ፈታኝ ሁኔታ ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል እንደሚሰጠው ተማምኗል።—መዝ. 18:1 አናት ላይ ያለው መግለጫ፤ w20.07 17 አን. 11-13
ሐሙስ፣ ጥቅምት 20
በፍጻሜው ዘመን የደቡቡ ንጉሥ ከእሱ [ከሰሜኑ ንጉሥ] ጋር ይጋፋል።—ዳን. 11:40
ስለ ሰሜኑ ንጉሥና ስለ ደቡቡ ንጉሥ የሚናገረው ትንቢት አብዛኛው ክፍል ፍጻሜውን አግኝቷል፤ በመሆኑም የቀረው የትንቢቱ ክፍልም እንደሚፈጸም መተማመን እንችላለን። በዳንኤል ምዕራፍ 11 ላይ የሚገኘውን ትንቢት ለመረዳት፣ ትንቢቱ የሚገልጸው ከአምላክ ሕዝቦች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ስላላቸው ገዢዎችና መንግሥታት ብቻ እንደሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል። ደግሞም የአምላክ አገልጋዮች ከዓለም ሕዝብ አንጻር ሲታዩ ቁጥራቸው በጣም አነስተኛ ቢሆንም ብዙውን ጊዜ በዓለም ላይ የሚፈጸሙት ወሳኝ ክንውኖች በእጅጉ ይነኳቸዋል። ለምን? ምክንያቱም የሰይጣንና በእሱ ቁጥጥር ሥር ያለው ሥርዓት ዋነኛ ዓላማ፣ የይሖዋንና የኢየሱስን አገልጋዮች ድል መንሳት ነው። (ዘፍ. 3:15፤ ራእይ 11:7፤ 12:17) ይህን የዳንኤል ትንቢት ስንመረምር ግምት ውስጥ ማስገባት ያለብን ሌላው ነገር፣ ትንቢቱ በአምላክ ቃል ውስጥ ከሚገኙ ሌሎች ትንቢቶች ጋር መስማማት ያለበት መሆኑን ነው። ደግሞም የዳንኤልን ትንቢት በትክክል መረዳት የምንችለው ከሌሎች የቅዱሳን መጻሕፍት ክፍሎች ጋር አያይዘን ካየነው ብቻ ነው። w20.05 2 አን. 1-2
ዓርብ፣ ጥቅምት 21
ሙታን የሚነሱት እንዴት ነው? ከሞት የሚነሱትስ ምን ዓይነት አካል ይዘው ነው?—1 ቆሮ. 15:35
ብዙ ሰዎች ከሞት በኋላ ስላለው ሕይወት የተለያየ አመለካከት አላቸው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል? ሰው ሲሞት፣ አካሉ ይበሰብሳል። ይሁን እንጂ ጽንፈ ዓለምን ከምንም የፈጠረው አምላክ፣ ሰውየውን ከሞት አስነስቶ ተስማሚ አካል ሊሰጠው ይችላል። (ዘፍ. 1:1፤ 2:7) አምላክ ያንኑ አካል መልሶ ማስነሳት እንደማያስፈልገው ለማስረዳት ሐዋርያው ጳውሎስ ግሩም ምሳሌ ተጠቅሟል። አንድን “ዘር” ወደ አእምሯችን እናምጣ። መሬት ላይ የተዘራ ዘር ሲበቅል አዲስ ተክል ይሆናል። አዲሱ ተክል፣ ከተዘራው ዘር ሙሉ በሙሉ የተለየ ነው። ጳውሎስ ይህን ንጽጽር የተጠቀመው፣ ፈጣሪ “የፈለገውን አካል” መስጠት እንደሚችል ለማስረዳት ነው። በተጨማሪም ጳውሎስ “ሰማያዊ አካላት አሉ፤ ምድራዊ አካላትም አሉ” በማለት ጽፏል። ምን ማለቱ ነበር? በምድር ላይ ያለነው ሥጋዊ አካል አለን፤ በሰማይ ያሉት ደግሞ ልክ እንደ መላእክት መንፈሳዊ አካል አላቸው።—1 ቆሮ. 15:36-41፤ w20.12 10 አን. 7-9
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 22
ልቤ በየዕለቱ በሐዘን እየተደቆሰ፣ በጭንቀት ተውጬ የምኖረው እስከ መቼ ነው?—መዝ. 13:2
ሁላችንም ምንም የሚረብሸን ነገር ሳይኖር በሰላም ብንኖር ደስ ይለናል። መጨነቅ የሚወድ ሰው የለም። ሆኖም በጭንቀት የምንዋጥባቸውና ንጉሥ ዳዊት በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የጠየቀው ዓይነት ጥያቄ የምንጠይቅባቸው ጊዜያት አሉ። እንድንጨነቅ የሚያደርጉን አንዳንዶቹ ነገሮች ከእኛ ቁጥጥር ውጭ ሊሆኑ ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል የምግብ፣ የልብስና የቤት ኪራይ ዋጋ እንዳይወደድ ማድረግ አንችልም፤ ወይም ደግሞ አብረውን የሚሠሩ ወይም አብረውን የሚማሩ ሰዎች ሐቀኝነታችንን እንድናጎድል ወይም ሥነ ምግባር የጎደለው ነገር እንድንፈጽም ይፈትኑን ይሆናል፤ የእነሱን ድርጊት መቆጣጠርም አንችልም። በተጨማሪም በአካባቢያችን ወንጀል እንዳይፈጸም ማድረግ አንችልም። እነዚህ ሁሉ ችግሮች የሚያጋጥሙን የመጽሐፍ ቅዱስን መመሪያዎች የማይከተሉ ሰዎች በሞሉበት ዓለም ውስጥ ስለምንኖር ነው። የዚህ ዓለም አምላክ የሆነው ሰይጣን፣ “የዚህ ሥርዓት ጭንቀት” አንዳንድ ሰዎችን ይሖዋን ከማገልገል ወደኋላ እንዲሉ እንደሚያደርጋቸው ያውቃል። (ማቴ. 13:22፤ 1 ዮሐ. 5:19) ከዚህ አንጻር ዓለማችን በሚያስጨንቁ ነገሮች የተሞላ መሆኑ አያስገርመንም። w21.01 2 አን. 1, 3
እሁድ፣ ጥቅምት 23
ወንድሙን የሚጠላ ሁሉ ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳይ የሆነ ሁሉ ደግሞ የዘላለም ሕይወት እንደሌለው ታውቃላችሁ።—1 ዮሐ. 3:15
ሐዋርያው ዮሐንስ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንዳንጠላ ማሳሰቢያ ሰጥቶናል። ይህን ማሳሰቢያ ችላ ካልን ሰይጣን እንዲጠቀምብን ዕድል እንሰጠዋለን። (1 ዮሐ. 2:11) በመጀመሪያው መቶ ዘመን መገባደጃ ላይ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች እንዲህ ዓይነት ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። ሰይጣን በአምላክ ሕዝቦች መካከል ጥላቻና ክፍፍል ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት አድርጓል። ዮሐንስ ደብዳቤዎቹን በጻፈበት ወቅት የሰይጣን ዓይነት መንፈስ ያላቸው ሰዎች ወደ ጉባኤው ሾልከው ገብተው ነበር። ለምሳሌ ያህል፣ ዲዮጥራጢስ በአንድ ጉባኤ ውስጥ ከፍተኛ ክፍፍል ፈጥሮ ነበር። (3 ዮሐ. 9, 10) ከበላይ አካሉ ተልከው ለሚመጡ ወንድሞች አክብሮት አልነበረውም። ሌላው ቀርቶ እሱ የሚጠላቸውን ሰዎች በእንግድነት የተቀበሉ ክርስቲያኖችን ከጉባኤው ለማባረር ጥረት አድርጓል። እንዴት ያለ እብሪተኝነት ነው! ሰይጣን ዛሬም ቢሆን የአምላክን ሕዝቦች ለመከፋፈል የማይፈነቅለው ድንጋይ የለም። እንግዲያው ጥላቻ በመካከላችን ክፍፍል እንዲፈጥር ፈጽሞ አንፍቀድ። w21.01 11 አን. 14
ሰኞ፣ ጥቅምት 24
የምሥክርነት ሥራቸውን ባጠናቀቁ ጊዜ፣ [አውሬው] ውጊያ ይከፍትባቸዋል፤ ድል ይነሳቸዋል፤ እንዲሁም ይገድላቸዋል።—ራእይ 11:7
በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የጀርመን መንግሥትም ሆነ የብሪታንያ መንግሥት፣ በጦርነቱ ሰው ለመግደል ፈቃደኛ ያልሆኑ የአምላክ አገልጋዮችን አሳድደዋል። የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥትም ቢሆን የስብከቱን ሥራ የሚመሩት ወንድሞች እስር ቤት እንዲጣሉ አድርጓል። ይህም በራእይ 11:7-10 ላይ የሚገኘው ትንቢት ፍጻሜ ነው። ከዚያም በ1930ዎቹ ዓመታት፣ በተለይም በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሰሜኑ ንጉሥ የአምላክን ሕዝቦች ያለምንም ርኅራኄ አሳድዷል። ሂትለርና ተከታዮቹ በአምላክ ሕዝቦች ሥራ ላይ እገዳ ጥለዋል። ተቃዋሚዎች፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ የይሖዋ አገልጋዮችን ገድለዋል፤ እንዲሁም በሺዎች የሚቆጠሩትን ወደ ማጎሪያ ካምፖች ልከዋል። የሰሜኑ ንጉሥ፣ የአምላክ አገልጋዮች ይሖዋን በሕዝብ ፊት ለማወደስ በሚያከናውኑት ሥራ ላይ ከፍተኛ ገደብ በመጣሉ ‘መቅደሱን አርክሷል’ እንዲሁም ‘የዘወትሩን መሥዋዕት አስቀርቷል።’ (ዳን. 11:30ለ, 31ሀ) እንዲያውም የጀርመን መሪ የነበረው ሂትለር የአምላክ ሕዝቦችን ከአገሪቱ ጠራርጎ እንደሚያጠፋ ዝቶ ነበር። w20.05 6 አን. 12-13
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 25
በወንድማማች ፍቅር እርስ በርሳችሁ ከልብ ተዋደዱ። አንዳችሁ ሌላውን ለማክበር ቀዳሚ ሁኑ።—ሮም 12:10
አንዳችን ለሌላው ልባዊ ፍቅር የምናሳይ ከሆነ በጉባኤው ውስጥ የፉክክር መንፈስ እንዳይፈጠር አስተዋጽኦ እናደርጋለን። እንደምናስታውሰው፣ ዮናታን የፉክክር መንፈስ አልነበረውም፤ ዳዊትን ዙፋኑን እንደሚነጥቅ ተቀናቃኝ አድርጎ አልተመለከተውም። (1 ሳሙ. 20:42) ዮናታን ለሁላችንም ግሩም ምሳሌ ትቶልናል። የእምነት ባልንጀሮቻችሁን ባሏቸው ችሎታዎች የተነሳ እንደ ተቀናቃኝ አድርጋችሁ አትመልከቷቸው፤ ከዚህ ይልቅ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ።” (ፊልጵ. 2:3) እያንዳንዱ ክርስቲያን በጉባኤው ውስጥ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ እንዳለ አትርሱ። በትሕትና ለራሳችን ትክክለኛውን አመለካከት ከያዝን የወንድሞቻችንንና የእህቶቻችንን መልካም ጎን ማየት እንዲሁም ከእነሱ ግሩም ምሳሌ ትምህርት ማግኘት ቀላል ይሆንልናል። (1 ቆሮ. 12:21-25) እርስ በርስ ከልብ ስንዋደድ በአምላክ ሕዝቦች መካከል ያለው አንድነት እንዲጠናከር አስተዋጽኦ እናደርጋለን። የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንደሆንን እናሳያለን፤ ይህ ደግሞ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ወደ እውነተኛው አምልኮ እንዲሳቡ ያደርጋል። ከሁሉ በላይ ግን “የምሕረት አባትና የመጽናናት ሁሉ አምላክ” የሆነውን ይሖዋን እናስደስተዋለን።—2 ቆሮ. 1:3፤ w21.01 23 አን. 14፤ 25 አን. 16
ረቡዕ፣ ጥቅምት 26
የዓለም ክፍል ስላልሆናችሁ . . . ዓለም ይጠላችኋል።—ዮሐ. 15:19
በዛሬው ጊዜ ያለን የይሖዋ ሕዝቦችም እንደ ሞኝና እንደ ደካማ ተቆጥረን የምንናቅበትና የምንሰደብበት ጊዜ አለ። ለምን? በዙሪያችን ካሉት ሰዎች የተለየ አመለካከት ስላለን ነው። ትሑት፣ የዋህና ታዛዥ ለመሆን እንጥራለን። በአንጻሩ ግን ይህ ዓለም ኩሩ፣ ግትርና ዓመፀኛ ለሆኑ ሰዎች ከፍተኛ ቦታ ይሰጣል። በተጨማሪም ፖለቲካ ውስጥ አንገባም፤ የየትኛውንም አገር ወታደራዊ ኃይልም አንቀላቀልም። በዚህ ሥርዓት ለመቀረጽ ፈቃደኛ ስላልሆንን ሌሎች ዝቅ አድርገው ይመለከቱናል። (ሮም 12:2) ዓለም እንደ ደካማ አድርጎ ቢመለከተንም ይሖዋ በእኛ አማካኝነት አስደናቂ ነገሮችን እያከናወነ ነው። ይሖዋ በሰው ዘር ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ ሰፊ የስብከት ሥራ እንዲከናወን አድርጓል። አገልጋዮቹ በትርጉምና በስርጭት ረገድ ተወዳዳሪ የሌላቸውን መጽሔቶች እያዘጋጁ ነው፤ በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስን በመጠቀም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን እንዲያሻሽሉ እየረዱ ነው። ለእነዚህ አስደናቂ ነገሮች ምስጋና የሚገባው ይሖዋ ነው። w20.07 15 አን. 5-6
ሐሙስ፣ ጥቅምት 27
አብ ባዘዘኝ መሠረት እየሠራሁ ነው።—ዮሐ. 14:31
ኢየሱስ ለይሖዋ ይገዛል፤ ይህን የሚያደርገው ግን የማሰብ ችሎታው ወይም ክህሎቱ ዝቅተኛ ስለሆነ አይደለም። ኢየሱስ በጣም ቀላልና ግልጽ በሆነ መንገድ ማስተማሩ በራሱ ከፍተኛ የማሰብ ችሎታ እንዳለው ያሳያል። (ዮሐ. 7:45, 46) ይሖዋ ጽንፈ ዓለምን በፈጠረበት ወቅት ኢየሱስ አብሮት እንዲሠራ የፈቀደለት ከፍተኛ ችሎታ እንዳለው ስለሚያውቅ ነው። (ምሳሌ 8:30፤ ዕብ. 1:2-4) ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላም ይሖዋ ‘በሰማይና በምድር ሁሉ ላይ ሥልጣን ሰጥቶታል።’ (ማቴ. 28:18) ኢየሱስ ከፍተኛ ችሎታ ቢኖረውም ከይሖዋ መመሪያ ይጠይቃል። ለምን? ምክንያቱም አባቱን ይወደዋል። ባሎች ይሖዋ ሚስቶች ለባሎቻቸው እንዲገዙ ያዘዘው ሴቶችን ከወንዶች ዝቅ አድርጎ ስለሚመለከት እንዳልሆነ መገንዘብ አለባቸው። ይሖዋ ከኢየሱስ ጋር ተባባሪ ገዢዎች እንዲሆኑ ወንዶችን ብቻ ሳይሆን ሴቶችንም መምረጡ በራሱ ይህን ሐቅ ያረጋግጣል። (ገላ. 3:26-29) ይሖዋ ለልጁ ሥልጣን በመስጠት እንደሚተማመንበት አሳይቷል። በተመሳሳይም ጥበበኛ የሆነ አንድ ባል ለሚስቱ አንዳንድ ኃላፊነቶች ይሰጣል። w21.02 11 አን. 13-14
ዓርብ፣ ጥቅምት 28
የጸኑትን ደስተኞች እንደሆኑ አድርገን እንቆጥራቸዋለን።—ያዕ. 5:11
የአምላክ ቃል እንደ መስታወት ነው፤ ልናስተካክለው የሚገባንን ነገር ለማስተዋልና ማስተካከያ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማወቅ ይረዳናል። (ያዕ. 1:23-25) ለምሳሌ ያህል፣ የአምላክን ቃል ስናጠና ቁጣችንን መቆጣጠር እንደሚያስፈልገን እንገነዘብ ይሆናል። መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ የሚያስቆጡ ሰዎች ወይም ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን ገር መሆን የምንችለው እንዴት እንደሆነ ይሖዋ ያስተምረናል። ይህም በትክክል ማሰብና የተሻለ ውሳኔ ማድረግ እንድንችል ይረዳናል። (ያዕ. 3:13) እንግዲያው መጽሐፍ ቅዱስን በደንብ ማወቃችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! አንዳንድ ጊዜ አንድ ነገር ማድረግ እንደሌለብን የምንማረው ስህተት ከሠራን በኋላ ነው። ጥበብ ለማግኘት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ከሌሎች ስኬትና ከሠሯቸው ስህተቶች መማር ነው። ያዕቆብ እንደ አብርሃም፣ ረዓብ፣ ኢዮብና ኤልያስ ያሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ሰዎች የተዉትን ምሳሌ እንድንመረምር ያበረታታን ለዚህ ነው። (ያዕ. 2:21-26፤ 5:10, 11, 17, 18) እነዚህ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ደስታቸውን ሊያሳጧቸው የሚችሉ ፈተናዎችን በጽናት መቋቋም ችለዋል። ጽናት በማሳየት ረገድ የተዉት ምሳሌ እኛም በይሖዋ እርዳታ ተመሳሳይ ነገር ማድረግ እንደምንችል ይጠቁማል። w21.02 29-30 አን. 12-13
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 29
መመካከር ሲኖር የታቀደው ነገር ይሳካል፤ ለውጊያም ስትወጣ ጥበብ ያለበት አመራር ተቀበል።—ምሳሌ 20:18
በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ወቅት ተማሪው የአምላክን ቃል እንዲረዳ ማድረግ በዋነኝነት የአስጠኚው ኃላፊነት ነው። አስጠኚው ጥናት ሲመራ እንድትገኝ ከጋበዘህ የእሱ ረዳት መሆንህን ማስታወስ ይኖርብሃል። የአንተ ሚና እሱን ማገዝ ነው። (መክ. 4:9, 10) ታዲያ በጥናቱ ወቅት ጥሩ ረዳት መሆን የምትችለው እንዴት ነው? ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ተዘጋጅ። በመጀመሪያ አስጠኚው ስለ ተማሪው አንዳንድ ነገሮችን እንዲነግርህ ጠይቀው። ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ምን ማወቅ ያለብህ ነገር አለ? የምታጠኑት ስለ ምንድን ነው? በዛሬው ጥናት ማስጨበጥ የሚኖርብህ የትኛውን ነጥብ ነው? በጥናቱ ወቅት ማድረግ ወይም መናገር ያለብህ አሊያም የሌለብህ ነገር አለ? ጥናቱ እድገት እንዲያደርግ ለማበረታታት ምን ማድረግ ትችላለህ? እርግጥ አስጠኚው የጥናቱን ሚስጥር አይነግርህም። ሆኖም ጠቃሚ የሆኑ ነጥቦችን ሊነግርህ ይችላል። ጆይ የተባለች ሚስዮናዊት እንዲህ ብላለች፦ “እንዲህ ያለውን ውይይት ማድረጌ ጥናት የምጋብዘው ሰው ጥናቴን ለመርዳት እንዲነሳሳና በጥናቱ ወቅት ምን ማለት እንዳለበት እንዲያውቅ ይረዳዋል።” w21.03 9 አን. 5-6
እሁድ፣ ጥቅምት 30
ዓለም ቢጠላችሁ፣ እናንተን ከመጥላቱ በፊት እኔን እንደጠላኝ ታውቃላችሁ።—ዮሐ. 15:18
በዓለም እንድንጠላ የሚያደርገን አንዱ ምክንያት በአምላክ የጽድቅ መሥፈርቶች የምንመራ መሆኑ ነው። በእነዚህ መሥፈርቶችና ዓለም በሚከተለው ያዘቀጠ የሥነ ምግባር መሥፈርት መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ሰዶምንና ገሞራን ለማጥፋት እንዲነሳሳ ያደረጉትን አስጸያፊ የብልግና ድርጊቶች በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ሰዎች በይፋ ይደግፋሉ። (ይሁዳ 7) ከእንደነዚህ ዓይነት ድርጊቶች ጋር በተያያዘ የመጽሐፍ ቅዱስን መሥፈርቶች በመከተላችን ብዙ ሰዎች ያፌዙብናል እንዲሁም ጠባብ አስተሳሰብ እንዳለን ይናገራሉ። (1 ጴጥ. 4:3, 4) የሰዎችን ጥላቻና ስድብ ለመቋቋም የሚረዳን ምንድን ነው? ይህን ለማድረግ የሚያስችለን ይሖዋ እንደሚረዳን ያለን ጠንካራ እምነት ነው። እምነታችን እንደ ጋሻ በመሆን “የሚንበለበሉትን የክፉውን ፍላጻዎች ሁሉ ማምከን” እንድንችል ይረዳናል። (ኤፌ. 6:16) ሆኖም የሚያስፈልገን እምነት ብቻ አይደለም። ፍቅርም ያስፈልገናል። ለምን? ምክንያቱም ፍቅር “በቀላሉ አይበሳጭም።” የሚጎዱ ነገሮችን ሁሉ ችሎ ያልፋል እንዲሁም በጽናት ይቋቋማል። (1 ቆሮ. 13:4-7, 13) ለይሖዋና ለእምነት ባልንጀሮቻችን ሌላው ቀርቶ ለጠላቶቻችን እንኳ ያለን ፍቅር ጥላቻን እንድንቋቋም ይረዳናል። w21.03 21 አን. 3-4
ሰኞ፣ ጥቅምት 31
የሞኞች ቁጣ በጉያቸው ውስጥ ስለሆነ ለቁጣ አትቸኩል።—መክ. 7:9
አንዳንድ ጊዜ ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለንን ፍቅር የምናሳየው አንዳንድ ነገሮችን ባለማድረግ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ በሚናገሩት ነገር ቶሎ ቅር አንሰኝም። ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ የተከሰተን አንድ ሁኔታ እንደ ምሳሌ እንመልከት። ኢየሱስ ሥጋውን ካልበሉና ደሙን ካልጠጡ ሕይወት እንደማያገኙ ለደቀ መዛሙርቱ ተናገረ። (ዮሐ. 6:53-57) ብዙዎቹ ደቀ መዛሙርቱ ይህን ሲሰሙ በጣም ስለሰቀጠጣቸው ትተውት ሄዱ፤ እውነተኛ ወዳጆቹ ግን ይህን አላደረጉም። በታማኝነት ከእሱ ጋር ጸንተዋል። እነሱም ቢሆኑ ኢየሱስ የተናገረው ነገር አልገባቸውም፤ ምናልባትም የተናገረው ነገር አስደንግጧቸው ሊሆን ይችላል። ሆኖም እነዚህ ታማኝ ወዳጆቹ ኢየሱስ የተሳሳተ ነገር እንደተናገረ አላሰቡም፤ እንዲሁም ቅር አልተሰኙም። ከዚህ ይልቅ እውነቱን እንደሚናገር ስለሚያውቁ አምነውታል። (ዮሐ. 6:60, 66-69) እንግዲያው ወዳጆቻችን በሚናገሩት ነገር ቶሎ ቅር አለመሰኘታችን ምንኛ ተገቢ ነው! የተናገሩት ነገር ካልገባን እስኪያስረዱን ድረስ እንታገሣለን።—ምሳሌ 18:13፤ w21.01 11 አን. 13