የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es23 ገጽ 77-87
  • ነሐሴ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ነሐሴ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2023
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 1
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 2
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 3
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 4
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 5
  • እሁድ፣ ነሐሴ 6
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 7
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 8
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 9
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 10
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 11
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 12
  • እሁድ፣ ነሐሴ 13
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 14
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 15
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 16
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 17
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 18
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 19
  • እሁድ፣ ነሐሴ 20
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 21
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 22
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 23
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 24
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 25
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 26
  • እሁድ፣ ነሐሴ 27
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 28
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 29
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 30
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2023
es23 ገጽ 77-87

ነሐሴ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 1

አባት ሆይ፣ . . . ይቅር በላቸው።—ሉቃስ 23:34

ኢየሱስ እየተናገረ ያለው እጆቹንና እግሮቹን በሚስማር ስለቸነከሩት ሮማውያን ወታደሮች ሳይሆን አይቀርም። ኢየሱስ ግፍ ቢደርስበትም በሁኔታው አልተማረረም፤ ቂምም አልያዘም። (1 ጴጥ. 2:23) እንደ ኢየሱስ ሁሉ እኛም ሌሎችን ይቅር ለማለት ፈቃደኞች መሆን ይኖርብናል። (ቆላ. 3:13) ቤተሰቦቻችንን ጨምሮ አንዳንዶች እምነታችንን እና ሕይወታችንን የምንመራበትን መንገድ መረዳት ስለሚከብዳቸው ሊቃወሙን ይችላሉ። ስለ እኛ ውሸት ይናገሩ፣ በሰዎች ፊት ያዋርዱን፣ ጽሑፎቻችንን ይቀዳድዱ አልፎ ተርፎም አካላዊ ጥቃት እንደሚሰነዝሩብን ይዝቱ ይሆናል። እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥመን ቂም ከመያዝ ይልቅ ይሖዋ የሚቃወሙንን ሰዎች ዓይናቸውን እንዲከፍትላቸውና እውነትን ለመቀበል እንዲረዳቸው መጸለይ እንችላለን። (ማቴ. 5:44, 45) እርግጥ አንዳንድ ጊዜ ሌሎችን ይቅር ማለት ቀላል ላይሆን ይችላል፤ በተለይ ደግሞ ከባድ በደል ተፈጽሞብን ከሆነ እንዲህ ማድረግ ሊከብደን ይችላል። ይሁንና ቂምና ምሬት በልባችን ውስጥ ሥር እንዲሰድ ከፈቀድን የምንጎዳው እኛው ነን። (መዝ. 37:8) ይቅር ለማለት ስንወስን በደረሰብን በደል ምክንያት በምሬት ላለመዋጥ መርጠናል ማለት ነው።—ኤፌ. 4:31, 32፤ w21.04 8 አን. 3-4

ረቡዕ፣ ነሐሴ 2

ብዙ ጊዜ ስሜቱን ጎዱት!—መዝ. 78:40

ከቤተሰባችሁ አባላት አንዱ ከጉባኤ ተወግዷል? ይህ ሁኔታ ልብ እንደሚሰብር ምንም ጥያቄ የለውም። ይሖዋ የቤተሰቡ አባላት የነበሩት መላእክት ጀርባቸውን ሲሰጡት ምን ያህል አዝኖ እንደሚሆን እስቲ አስቡት! (ይሁዳ 6) በተጨማሪም የሚወዳቸው ሕዝቦቹ የነበሩት እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ሲያምፁበት ስሜቱ ምን ያህል ተጎድቶ እንደሚሆን አስቡት። (መዝ. 78:41) አፍቃሪው የሰማዩ አባታችን የእናንተም ቤተሰብ አባል እሱን ሲተወው በጣም እንደሚያዝን አትጠራጠሩ። ይሖዋ የሚሰማችሁን ሐዘን ይረዳል። እንዲሁም የሚያስፈልጋችሁን ማበረታቻና ድጋፍ በርኅራኄ ይሰጣችኋል። ወላጆች የሚወዱት ልጃቸው ይሖዋን ሲተው ‘እንዲህ ባደርግ ኖሮ ልጄ ከእውነት አይወጣም ነበር’ በማለት ራሳቸውን ይወቅሱ ይሆናል። አንድ ወንድም እንዲህ ብሏል፦ “ራሴን እወቅስ ነበር። ጉዳዩ ሌሊት እንኳ ያቃዠኝ ነበር።” ተመሳሳይ ሁኔታ ያጋጠማት እህትም እንዲህ ብላለች፦ “‘የእናትነት ኃላፊነቴን በሚገባ አልተወጣሁ ይሆን?’ ብዬ አስብ ነበር። በልጄ ልብ ውስጥ እውነትን ለመትከል ማድረግ ያለብኝን ያህል እንዳላደረግኩ ተሰማኝ።” w21.09 26 አን. 1-2, 4

ሐሙስ፣ ነሐሴ 3

ያልተማሩና ተራ ሰዎች መሆናቸውን [ተረዱ]።—ሥራ 4:13

አንዳንዶች፣ የአምላክ ሕዝቦች ስመ ጥር ከሆኑ የሃይማኖት ትምህርት ቤቶች ስላልተመረቁ መጽሐፍ ቅዱስን ለማስተማር ብቁ እንዳልሆኑ ይሰማቸዋል። ሆኖም መረጃዎቹን መመርመራቸው አስፈላጊ ነው። የወንጌል ጸሐፊ የሆነው ሉቃስ ይህን ለማድረግ ጥረት አድርጎ ነበር። “ሁሉንም ነገር ከመጀመሪያው አንስቶ በጥንቃቄ” መርምሯል። ወንጌሉን የሚያነቡ ሰዎች ስለ ኢየሱስ የሰሟቸው ነገሮች “እርግጠኛ መሆናቸውን በሚገባ” እንዲያውቁ ፈልጎ ነበር። (ሉቃስ 1:1-4) በጥንቷ ቤርያ የነበሩት አይሁዳውያንም እንደ ሉቃስ አድርገዋል። ስለ ኢየሱስ የሚገልጸውን ምሥራች መጀመሪያ በሰሙበት ወቅት፣ የሰሙት ነገር ትክክል መሆኑን ለማረጋገጥ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን መርምረዋል። (ሥራ 17:11) በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎችም በተመሳሳይ መረጃዎቹን መመርመር ያስፈልጋቸዋል። የአምላክ ሕዝቦች ያስተማሯቸውን ነገር በቅዱሳን መጻሕፍት ውስጥ ከሚገኘው ነገር ጋር ማወዳደር ይኖርባቸዋል። በተጨማሪም በዘመናችን ያሉ የይሖዋ ሕዝቦች ያስመዘገቡትን ታሪክ ማጥናት ያስፈልጋቸዋል። መረጃዎቹን በጥንቃቄ ከመረመሩ መሠረተ ቢስ ጥላቻ ወይም አሉባልታ እንዲያሳውራቸው አይፈቅዱም። w21.05 3 አን. 7-8

ዓርብ፣ ነሐሴ 4

ልባችሁን ወለል አድርጋችሁ ክፈቱ።—2 ቆሮ. 6:13

በጉባኤያችሁ ውስጥ ካሉ ወንድሞችና እህቶች መካከል ማንን መጋበዝ ትችላላችሁ? ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አብረን ጊዜ ማሳለፋችን ይበልጥ አስፈላጊ የሚሆንበት ጊዜ ይኖራል። አንዳንዶች በበዓላት ወቅት ከማያምኑ ቤተሰቦቻቸው ጋር መሆን ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። ሌሎች ደግሞ በአንዳንድ ቀናት ለምሳሌ በየዓመቱ፣ የቤተሰባቸው አባል የሞተበት ቀን ሲደርስ ይበልጥ ብቸኝነት ይሰማቸዋል። እንዲህ ባለ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ካሉ ወንድሞችና እህቶች ጋር ጊዜ ለማሳለፍ ስንጥር ‘ከልብ እንደምንጨነቅላቸው’ እናሳያለን። (ፊልጵ. 2:20) አንድ ክርስቲያን አልፎ አልፎ ብቸኝነት እንዲሰማው ሊያደርጉ የሚችሉ ብዙ ምክንያቶች አሉ። ይሁንና ይሖዋ ስሜታችንን ሙሉ በሙሉ እንደሚረዳልን ፈጽሞ ልንዘነጋ አይገባም። የሚያስፈልገንን እርዳታ ሁሉ ይሰጠናል፤ አብዛኛውን ጊዜ ይህን የሚያደርገው በእምነት አጋሮቻችን አማካኝነት ነው። (ማቴ. 12:48-50) እኛ ደግሞ መንፈሳዊ ቤተሰባችንን ለመደገፍ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ስናደርግ ይሖዋ ላደረገልን ፍቅራዊ ዝግጅት ያለንን አድናቆት እናሳያለን። አንዳንድ ጊዜ ብቸኝነት ቢሰማንም እንኳ መቼም ቢሆን ብቻችንን አይደለንም፤ ምክንያቱም ይሖዋ ምንጊዜም ከጎናችን ነው! w21.06 12-13 አን. 18-20

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 5

ክፉ አድራጊዎች እንደሆናችሁ አድርገው ሲከሷችሁ መልካም ሥራችሁን በዓይናቸው ማየት እንዲችሉ ብሎም [አምላክን] እንዲያከብሩ በዓለም ባሉ ሰዎች መካከል መልካም ምግባር ይኑራችሁ።—1 ጴጥ. 2:12

ኢየሱስ አንዳንዶች ለመልእክቱ ግድየለሽ ቢሆኑም እንኳ አዎንታዊ አመለካከት ይዞ መስበኩን ቀጥሏል። ለምን? ሰዎች እውነትን መስማት ምን ያህል እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝቦ ነበር፤ እንዲሁም በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት የመቀበል አጋጣሚ እንዲያገኙ ፈልጓል። ከዚህም ሌላ መጀመሪያ ላይ ለመልእክቱ ግድየለሽ የነበሩ ሰዎች ከጊዜ በኋላ መልእክቱን እንደሚቀበሉ ተገንዝቦ ነበር። በራሱ ቤተሰብ ውስጥ ያጋጠመውን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት። ለሦስት ዓመት ተኩል በዘለቀው አገልግሎቱ ወቅት ከወንድሞቹ መካከል አንዳቸውም ደቀ መዝሙሩ አልሆኑም ነበር። (ዮሐ. 7:5) ከሞት ከተነሳ በኋላ ግን ክርስቲያኖች ሆነዋል። (ሥራ 1:14) የምናስተምረውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ማን መቼ እንደሚቀበል አናውቅም። አንዳንዶች መልእክታችንን ለመቀበል ረጅም ጊዜ ሊወስድባቸው ይችላል። መልእክታችንን ለማዳመጥ ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎችም እንኳ መልካም ምግባራችንን እና አዎንታዊ አመለካከታችንን ሲመለከቱ ከጊዜ በኋላ ‘አምላክን ማክበር’ ሊጀምሩ ይችላሉ። w21.05 18-19 አን. 17-18

እሁድ፣ ነሐሴ 6

በምትሄዱበት ጊዜም “መንግሥተ ሰማያት ቀርቧል” ብላችሁ ስበኩ።—ማቴ. 10:7

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ለተከታዮቹ ድርብ ተልእኮ ሰጥቷቸዋል። የመንግሥቱን ምሥራች እንዲሰብኩ የነገራቸው ሲሆን ይህን ማድረግ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ አሳይቷቸዋል። (ሉቃስ 8:1) ለምሳሌ ሰዎች ለመንግሥቱ መልእክት አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ ምላሽ ሲሰጡ ምን ማድረግ እንዳለባቸው ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። (ሉቃስ 9:2-5) ምሥራቹ ምን ያህል በስፋት እንደሚሰበክም ገልጾላቸዋል፤ ተከታዮቹ “ለብሔራት ሁሉ” ምሥክርነት እንደሚሰጡ ተናግሯል። (ማቴ. 24:14፤ ሥራ 1:8) በተጨማሪም ተከታዮቹ የእሱ ደቀ መዛሙርት ለሚሆኑ ሰዎች እሱ ያዘዘውን ነገር ሁሉ እንዲጠብቁ ማስተማር እንዳለባቸው ነግሯቸዋል። ኢየሱስ ይህ ወሳኝ ሥራ “እስከ ሥርዓቱ መደምደሚያ” ማለትም አሁን እስከምንኖርበት ዘመን ድረስ እንደሚቀጥል አመልክቷል። (ማቴ. 28:18-20) በተጨማሪም ኢየሱስ ለዮሐንስ ባሳየው ራእይ ላይ ሁሉም ደቀ መዛሙርቱ ሰዎች ስለ ይሖዋ እንዲማሩ የመርዳት ኃላፊነት እንዳለባቸው በማያሻማ መንገድ ጠቁሟል።—ራእይ 22:17፤ w21.07 2-3 አን. 3-4

ሰኞ፣ ነሐሴ 7

በመካከላችን የፉክክር መንፈስ በማነሳሳትና አንዳችን ሌላውን በመመቅኘት በከንቱ አንመካ።—ገላ. 5:26

በዛሬው ጊዜ ራስ ወዳድነትና የፉክክር መንፈስ በብዙዎች ዘንድ ይታያል። ለምሳሌ፣ አንድ ነጋዴ ከተፎካካሪዎቹ ይበልጥ ትርፋማ ለመሆን ሲል ሌሎችን የሚጎዳ ነገር ከማድረግ ላይመለስ ይችላል። አንድ ስፖርተኛ በውድድሩ ለማሸነፍ ሲል በተቃራኒው ቡድን ያለውን ተጫዋች ሆን ብሎ ይጎዳው ይሆናል። ወይም ደግሞ ታዋቂ ወደሆነ ዩኒቨርሲቲ ለመግባት እየተወዳደረ ያለ ተማሪ የመግቢያውን ፈተና ለማለፍ ያጭበረብር ይሆናል። እኛ ክርስቲያኖች እንዲህ ያሉት ድርጊቶች ስህተት እንደሆኑና “የሥጋ ሥራዎች” ከተባሉት መካከል እንደሚመደቡ እናውቃለን። (ገላ. 5:19-21) ይሁንና አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮች ሳያውቁት በጉባኤው ውስጥ የፉክክር መንፈስ ሊያነሳሱ ይችሉ ይሆን? የፉክክር መንፈስ የወንድማማች ማኅበራችንን አንድነት ስለሚያናጋ ይህን ጥያቄ ልናስብበት ይገባል። እንግዲያው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተጠቀሱ ለፉክክር መንፈስ እጅ ያልሰጡ ታማኝ ወንዶችንና ሴቶችን ምሳሌ መመልከታችን ጠቃሚ ነው። w21.07 14 አን. 1-2

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 8

ለተቸገረ ሰው የሚያስብ ደስተኛ ነው፤ በመከራ ቀን ይሖዋ ይታደገዋል።—መዝ. 41:1

ታማኝ ፍቅር ያዘኑ ወይም ተስፋ የቆረጡ ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንድንረዳቸው ያነሳሳናል። በዛሬው ጊዜ ያሉ አሳቢ ወንድሞችና እህቶች በጉባኤያቸው ካሉ ያዘኑ ወይም የተጨነቁ ክርስቲያኖች ጎን ይቆማሉ። ወንድሞቻቸውን እና እህቶቻቸውን ይወዷቸዋል፤ ስለዚህ እነሱን ለመርዳት የቻሉትን ሁሉ ለማድረግ ይጓጓሉ። (ምሳሌ 12:25 ግርጌ፤ 24:10) ሐዋርያው ጳውሎስም እንዲህ እንድናደርግ አሳስቦናል፦ “የተጨነቁትን አጽናኗቸው፤ ደካሞችን ደግፏቸው፤ ሁሉንም በትዕግሥት ያዙ” ብሏል። (1 ተሰ. 5:14) ብዙውን ጊዜ፣ ተስፋ የቆረጡ ወንድሞችን ወይም እህቶችን መርዳት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ እነሱን ማዳመጥ እንዲሁም እንደምንወዳቸው መግለጽ ነው። ይሖዋ ውድ ለሆኑት በጎቹ የምታሳዩትን አሳቢነት በትኩረት ይመለከታል። ምሳሌ 19:17 እንዲህ ይላል፦ “ለችግረኛ ሞገስ የሚያሳይ ለይሖዋ ያበድራል፤ ላደረገውም ነገር ብድራት ይከፍለዋል።” w21.11 10 አን. 11-12

ረቡዕ፣ ነሐሴ 9

ይሖዋ ጥሩ መሆኑን ቅመሱ፤ እዩም፤ እሱን መጠጊያ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው።—መዝ. 34:8

ለወደፊቱ ጊዜ ከአሁኑ መዘጋጀት የምንችለው እንዴት ነው? ባለን ነገር መርካት እንዲሁም ከሁሉ በላቀው ሀብታችን ይኸውም ከይሖዋ ጋር ባለን ዝምድና መደሰት ይኖርብናል። አምላካችንን ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ፣ የማጎጉ ጎግ ጥቃት በሚሰነዝርበት ወቅት እኛን ለመጠበቅ ችሎታ እንዳለው ያለን እምነት ይበልጥ ይጠናከራል። በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለው ሐሳብ ዳዊት፣ ይሖዋ እንደሚደግፈው የተማመነው ለምን እንደሆነ ይጠቁመናል። ዳዊት ሁልጊዜም በይሖዋ ይታመን ነበር፤ አምላክም አሳፍሮት አያውቅም። ዳዊት ወጣት እያለ ግዙፉን ፍልስጤማዊ ጎልያድን ገጥሞት ነበር፤ ይህን ኃያል ተዋጊ “ዛሬ ይሖዋ አንተን በእጄ አሳልፎ ይሰጥሃል” ብሎታል። (1 ሳሙ. 17:46) ከጊዜ በኋላ ደግሞ ዳዊት ንጉሥ ሳኦልን በሚያገለግልበት ወቅት ሳኦል እሱን ለመግደል ብዙ ጊዜ ሙከራ አድርጓል፤ ይሖዋ ግን ‘ከዳዊት ጋር ነበር።’ (1 ሳሙ. 18:12) ዳዊት ቀደም ሲል ካጋጠሙት ሁኔታዎች ጋር በተያያዘ የይሖዋን እጅ ስላየ አሁን የሚያጋጥሙትን ፈተናዎች ለመወጣትም እንደሚረዳው ተማምኖ ነበር። w22.01 6 አን. 14-15

ሐሙስ፣ ነሐሴ 10

የአምላክ . . . ልጆች ሁሉ በደስታ [ጮኹ]።—ኢዮብ 38:7

ይሖዋ ማንኛውንም ነገር የሚያከናውነው ሳይጣደፍ በቂ ጊዜ ወስዶ ነው። እንዲህ የሚያደርገው ለስሙ ክብር እንዲሁም ለሌሎች ጥቅም ሲል ነው። ለምሳሌ ይሖዋ ምድርን ለሰው ልጆች መኖሪያ እንድትሆን ቀስ በቀስ ያዘጋጃት እንዴት እንደሆነ እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ ስለዚህ ሲናገር ‘መለኪያዎቿን እንደወሰነ፣’ ‘ምሰሶዎቿን እንደተከለ’ እንዲሁም ‘የማዕዘኗን ድንጋይ እንዳኖረ’ ይገልጻል። (ኢዮብ 38:5, 6) ይሖዋ የሠራውን ሥራ መለስ ብሎ ለማየትም ጊዜ ወስዷል። (ዘፍ. 1:10, 12) መላእክት የይሖዋ የፍጥረት ሥራ ቀስ በቀስ መልክ እየያዘ ሲሄድ ሲያዩ ምን ተሰምቷቸው እንደሚሆን መገመት ትችላለህ? በጣም ተደንቀው መሆን አለበት! እንዲያውም ‘በደስታ እንደጮኹ’ ተገልጿል። ከዚህ ምን እንማራለን? ይሖዋ የፍጥረት ሥራውን ለማከናወን ብዙ ሺህ ዓመታት ወስዶበታል፤ ደግሞም በጥንቃቄ የፈጠረውን ሁሉ ከተመለከተ በኋላ “እጅግ መልካም” እንደሆነ ተናግሯል።—ዘፍ. 1:31፤ w21.08 9 አን. 6-7

ዓርብ፣ ነሐሴ 11

ጎበዝ፣ አንተ ጥሩና ታማኝ ባሪያ!—ማቴ. 25:23

ኢየሱስ በተናገረው ምሳሌ ላይ አንድ ሰው ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ተነሳ። ከመሄዱ በፊት ባሪያዎቹን ጠርቶ ለእያንዳንዳቸው የሚነግዱበት ታላንት ሰጣቸው። ሰውየው የባሪያዎቹን ችሎታ ግምት ውስጥ በማስገባት ለአንዱ ባሪያ አምስት ታላንት፣ ለሌላኛው ባሪያ ሁለት ታላንት፣ ለሦስተኛው ደግሞ አንድ ታላንት ሰጣቸው። ሁለቱ ባሪያዎች ለጌታቸው ትርፍ ለማስገኘት በትጋት ሠሩ። ሦስተኛው ባሪያ ግን ለጌታው ትርፍ ለማምጣት ምንም ያደረገው ነገር የለም፤ በዚህም ምክንያት ከሥራው ተባረረ። የመጀመሪያውና ሁለተኛው ባሪያ የተሰጣቸውን ኃላፊነት በቁም ነገር ተመልክተውታል፤ እንዲሁም ጌታቸውን ለማገልገል አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ አድርገዋል። በመሆኑም የጌታቸውን ታላንት በእጥፍ ማሳደግ ችለዋል። እነዚህ ባሪያዎች በትጋት በመሥራታቸው በሚገባ ተክሰዋል። ጌታቸው የተደሰተባቸው ከመሆኑም ሌላ እነዚህን ባሪያዎች ተጨማሪ ኃላፊነት ለመቀበል ብቁ እንደሆኑ አድርጎ ቆጥሯቸዋል! w21.08 21 አን. 7፤ 22 አን. 9-10

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 12

እንደገና [ሰማያትንና] ምድርን . . . አናውጣለሁ።—ሐጌ 2:6

ይሖዋ በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ታላቅ ትዕግሥት አሳይቷል። ይሖዋ ማንም ሰው እንዲጠፋ አይፈልግም። (2 ጴጥ. 3:9) በመሆኑም ሁሉም ሰው ንስሐ መግባት እንዲችል አጋጣሚ ሰጥቷል። ይሁንና የይሖዋ ትዕግሥት ገደብ አለው። ይሖዋ በሰጣቸው አጋጣሚ ለመጠቀም ፈቃደኛ ያልሆኑ ሰዎች የፈርዖን ዕጣ ይደርስባቸዋል። ይሖዋ በሙሴ ዘመን ለኖረው ፈርዖን እንዲህ ብሎት ነበር፦ “እስካሁን እጄን ዘርግቼ አንተንም ሆነ ሕዝብህን አጥፊ በሆነ መቅሰፍት በመታኋችሁ ነበር፤ አንተም ከምድር ገጽ ተጠራርገህ በጠፋህ ነበር። ሆኖም ኃይሌን እንዳሳይህና ስሜ በመላው ምድር እንዲታወጅ ስል በሕይወት አቆይቼሃለሁ።” (ዘፀ. 9:15, 16) ይዋል ይደር እንጂ፣ ብሔራት ሁሉ ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ይሖዋ መሆኑን ለማወቅ ይገደዳሉ። (ሕዝ. 38:23) በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ የተገለጸው ነውጥ፣ እንደ ፈርዖን የይሖዋን የመግዛት መብት የማይቀበሉ ሰዎች የሚደርስባቸውን ዘላለማዊ ጥፋት ያመለክታል። w21.09 18-19 አን. 17-18

እሁድ፣ ነሐሴ 13

ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ፤ ከሚያለቅሱ ጋር አልቅሱ።—ሮም 12:15

የምትወዱት ሰው ከጉባኤ በመወገዱ ልባችሁ ተሰብሯል? ይባስ ብሎ ደግሞ በጉባኤ ውስጥ ያሉ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች ይባስ እንዲከፋችሁ የሚያደርግ ነገር ቢናገሩስ? ሁሉም ሰው ሁልጊዜ ትክክለኛውን ነገር ይናገራል ብለን መጠበቅ አንችልም። (ያዕ. 3:2) ሁላችንም ፍጹማን አይደለንም፤ በመሆኑም አንዳንዶች ምን ማለት እንዳለባቸው ግራ ቢገባቸው ይባስ ብሎም የሚጎዳችሁን ነገር ሳያስቡት ቢናገሩ ልትገረሙ አይገባም። ሐዋርያው ጳውሎስ “አንዱ በሌላው ላይ ቅር የተሰኘበት ነገር ቢኖረው እንኳ እርስ በርስ መቻቻላችሁንና በነፃ ይቅር መባባላችሁን ቀጥሉ” በማለት የሰጠውን ምክር አስታውሱ። (ቆላ. 3:13) ታማኝ የሆኑትን የቤተሰብ አባላት ማበረታታታችሁን አታቋርጡ። ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ በዚህ ወቅት የእናንተ ፍቅርና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። (ዕብ. 10:24, 25) የቤተሰባቸው አባል የተወገደባቸው አንዳንድ ክርስቲያኖች ጉባኤው እነሱንም ጭምር እንዳገለላቸው የተሰማቸው ጊዜ አለ። እነዚህ ክርስቲያኖች እንዲህ እንዲሰማቸው ልናደርግ አይገባም። በተለይም እውነትን የተዉ ወላጆች ያሏቸው ወጣቶች ምስጋናና ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። w21.09 29 አን. 13-14፤ 30 አን. 16

ሰኞ፣ ነሐሴ 14

ጥበበኛ ሰው ያዳምጣል፤ ደግሞም ተጨማሪ ትምህርት ይቀስማል።—ምሳሌ 1:5

ወጣቶችና አረጋውያን እርስ በርስ መጨዋወታቸው ሁለቱንም ይጠቅማቸዋል። (ሮም 1:12) እንዲህ ያለው ጭውውት፣ ወጣቶቹ ይሖዋ ታማኝ አገልጋዮቹን ምንጊዜም እንደማይጥል እንዲተማመኑ ያደርጋቸዋል፤ አረጋውያኑን ደግሞ እንደሚወደዱ እንዲሰማቸው ያደርጋል። አረጋውያን በሕይወታቸው ውስጥ የይሖዋን በረከት ያዩት እንዴት እንደሆነ መናገር ያስደስታቸዋል። ውጫዊ ውበት በአብዛኛው ዕድሜ ሲጨምር እየደበዘዘ ይሄዳል፤ ለይሖዋ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ግን ዓመታት እያለፉ ሲሄዱ በይሖዋ ዓይን ይበልጥ ውብ ይሆናሉ። (1 ተሰ. 1:2, 3) ይህ የሚሆነው ለምንድን ነው? ምክንያቱም በይሖዋ አገልግሎት ባሳለፏቸው ዓመታት የአምላክ መንፈስ እንዲቀርጻቸውና እንዲያጠራቸው ፈቅደዋል። ታማኝ የሆኑ አረጋውያን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይበልጥ ባወቅናቸው፣ ባከበርናቸውና ከእነሱ በተማርን መጠን እንደ ውድ ሀብት አድርገን እንመለከታቸዋለን! ጉባኤው እንዲጠናከር የሚያደርገው ወጣቶች አረጋውያንን ውድ አድርገው መመልከታቸው ብቻ አይደለም፤ አረጋውያንም ወጣቶችን ከፍ አድርገው መመልከት አለባቸው። w21.09 7 አን. 15-18

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 15

እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ አትፍረዱ፤ በምትፈርዱት ፍርድ ይፈረድባችኋል።—ማቴ. 7:1, 2

ምሕረት የለሽ እንዳንሆን እንጠንቀቅ፤ ከዚህ ይልቅ “ምሕረቱ ብዙ” የሆነውን አምላካችንን ለመምሰል ጥረት እናድርግ። (ኤፌ. 2:4) ምሕረት ማሳየት ሲባል ለሌሎች ማዘን ማለት ብቻ አይደለም። እንዲያውም ምሕረት “በተግባር የተደገፈ ርኅራኄ” የሚል ፍቺ ተሰጥቶታል። እንግዲያው ሁላችንም በቤተሰባችን፣ በጉባኤያችን ወይም በአካባቢያችን ውስጥ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ይኖሩ እንደሆነ በንቃት መከታተል እንችላለን። ምሕረት ማሳየት የምንችልባቸው ብዙ አጋጣሚዎች አሉ። ማጽናኛ የሚያስፈልገው ሰው አለ? ምግብ ልንወስድለት ወይም በሌላ ተግባራዊ መንገድ ልንረዳው የምንችለው ሰው ይኖር ይሆን? ውገዳ የተነሳለትን ክርስቲያን ማበረታታትና አብረነው ጊዜ ማሳለፍ እንችል ይሆን? አጽናኝ የሆነውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሥራች ለሌሎች ማካፈልም እንችላለን። (ኢዮብ 29:12, 13፤ ሮም 10:14, 15፤ ያዕ. 1:27) ንቁ ከሆንን ምሕረት ለማሳየት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን ሁልጊዜ እናገኛለን። ምሕረት ስናሳይ “ምሕረቱ ብዙ” የሆነውን የሰማዩን አባታችንን በእጅጉ እናስደስተዋለን! w21.10 12-13 አን. 20-22

ረቡዕ፣ ነሐሴ 16

ይሖዋ እረኛዬ ነው። የሚጎድልብኝ ነገር የለም።—መዝ. 23:1

በመዝሙር 23 ላይ ዳዊት እውነተኛና ዘላቂ ዋጋ ያላቸውን ነገሮች ጠቅሷል፤ እነሱም ይሖዋን እንደ እረኛው አድርጎ በመቀበሉ ያገኛቸው የተትረፈረፉ መንፈሳዊ በረከቶች ናቸው። ይሖዋ ዳዊትን “በጽድቅ መንገድ [ይመራዋል]” እንዲሁም በክፉም ሆነ በደጉ ጊዜ በታማኝነት ይደግፈዋል። ዳዊት ‘በለመለመው የይሖዋ መስክ’ ላይ ቢሰማራም ሕይወቱ አልጋ በአልጋ እንደማይሆን ያውቅ ነበር። አንዳንድ ጊዜ፣ “ድቅድቅ ጨለማ በዋጠው ሸለቆ ውስጥ” የሚሄድ ያህል ተስፋ ይቆርጥ ይሆናል፤ ጠላቶችም ይኖሩታል። ሆኖም ዳዊት ይሖዋ እረኛው ስለሆነ ‘ጉዳት ይደርስብኛል ብሎ አይፈራም።’ ዳዊት ‘መልካም ነገር አልጎደለበትም’ ሊባል የሚችለው ከምን አንጻር ነው? በመንፈሳዊ ረገድ የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ተሟልቶለታል። ደስተኛ መሆኑ በቁሳዊ ነገሮች ላይ የተመካ አልነበረም። ዳዊት ይሖዋ በሰጠው ነገር ረክቶ ይኖር ነበር። ከምንም በላይ ትልቅ ቦታ የሰጠው ከአምላክ ለሚያገኘው በረከትና ጥበቃ ነበር። ዳዊት የተናገረው ነገር ለቁሳዊ ነገሮች ተገቢውን አመለካከት መያዛችን ምን ያህል አስፈላጊ መሆኑን እንድንገነዘብ ያደርገናል። w22.01 3-4 አን. 5-7

ሐሙስ፣ ነሐሴ 17

እያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የራሱን ወሮታ ይቀበላል።—1 ቆሮ. 3:8

በጥንት ጊዜ የነበሩት የይሖዋ አገልጋዮች ከአምላክ የተቀበሉትን መልእክት ሲሰብኩ ጥሩ ምላሽ የማይሰጡ ሰዎች አጋጥመዋቸዋል። ለምሳሌ ያህል፣ ኖኅ “የጽድቅ ሰባኪ” ነበር፤ ምናልባትም ለአሥርተ ዓመታት ያህል በዚህ ሥራ ቀጥሏል። (2 ጴጥ. 2:5) ይህን ሥራ ሲያከናውን ሰዎች ለመልእክቱ ጥሩ ምላሽ እንደሚሰጡ ተስፋ አድርጎ መሆን አለበት፤ ይሖዋ ግን ይህን የሚጠቁም ምንም ሐሳብ አልነገረውም። ከዚህ ይልቅ መርከቡን እንዲሠራ ትእዛዝ ሲሰጠው እንዲህ ብሎታል፦ “አንተም ወደ መርከቡ መግባት አለብህ፤ አንተ፣ ከአንተም ጋር ወንዶች ልጆችህ፣ ሚስትህና የልጆችህ ሚስቶች ወደ መርከቡ መግባት ይኖርባችኋል።” (ዘፍ. 6:18) ደግሞም ኖኅ፣ አምላክ እንዲገነባ የነገረውን መርከብ መጠንና የመያዝ አቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ለስብከቱ ምላሽ የሚሰጡት ሰዎች ቁጥር ውስን እንደሚሆን ገምቶ ሊሆን ይችላል። (ዘፍ. 6:15) በኋላ እንደታየው በወቅቱ ከነበሩት ዓመፀኞች መካከል ለኖኅ ስብከት ምላሽ የሰጠ አንድም ሰው አልነበረም። (ዘፍ. 7:7) ታዲያ ኖኅ ያከናወነው ሥራ በይሖዋ ፊት ከንቱ ነበር? በፍጹም! በይሖዋ ዓይን ኖኅ ውጤታማ ሰባኪ ነበር፤ ምክንያቱም የታዘዘውን ሁሉ በታማኝነት ፈጽሟል።—ዘፍ. 6:22፤ w21.10 26 አን. 10-11

ዓርብ፣ ነሐሴ 18

ከዚህ ስወጣ ሙሉ ነበርኩ፤ ይሖዋ ግን ባዶ እጄን እንድመለስ አደረገኝ።—ሩት 1:21

ናኦሚ ይህን ስትናገር ሩት ምን ተሰምቷት ሊሆን እንደሚችል እስቲ አስቡት! ሩት ናኦሚን ለመርዳት ስትል ብዙ መሥዋዕት ከፍላለች። አብራት አልቅሳለች፣ አጽናንታታለች እንዲሁም ለበርካታ ቀናት አብራት ተጉዛለች። ሩት ይህን ሁሉ ብታደርግላትም ናኦሚ “ይሖዋ . . . ባዶ እጄን እንድመለስ አደረገኝ” ብላለች። የናኦሚ ንግግር አጠገቧ የቆመችው ሩት ያደረገችላትን ድጋፍ ከቁብ ያልቆጠረችው ያስመስልባታል። ሩት ይህን ስትሰማ ስሜቷ ምንኛ ተጎድቶ ይሆን! ያም ቢሆን ከናኦሚ ላለመለየት የሙጥኝ ብላለች። (ሩት 1:3-18) በዛሬው ጊዜ አንዲትን የተጨነቀች እህት ለማጽናናት ብዙ ጥረት ብናደርግም መጀመሪያ ላይ እህታችን የሚያስከፋ ነገር ትናገረን ይሆናል። ሆኖም በተናገረችው ነገር ቅር ላለመሰኘት ጥረት እናደርጋለን። እርዳታ ከሚያስፈልጋት እህታችን ጋር የሙጥኝ እንላለን፤ እንዲሁም ይሖዋ እሷን ለማጽናናት የሚያስችል መንገድ እንዲጠቁመን በጸሎት እንጠይቀዋለን። (ምሳሌ 17:17) እገዛ የሚያስፈልጋት አንዲት እህት መጀመሪያ ላይ እርዳታችንን ለመቀበል ፈቃደኛ ላትሆን ትችላለች። ያም ቢሆን ታማኝ ፍቅር፣ እሷን ለመርዳት ጥረት ማድረጋችንን እንድንቀጥል ያነሳሳናል።—ገላ. 6:2፤ w21.11 11 አን. 17-19

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 19

በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።—1 ጴጥ. 1:15

በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “ቅዱስ” እና “ቅድስና” የሚሉት ቃላት በሥነ ምግባር ወይም በአምልኮ ንጹሕ መሆንን ያመለክታሉ። ለይሖዋ አገልግሎት የተለዩ መሆንንም ሊያመለክቱ ይችላሉ። በሌላ አባባል፣ በሥነ ምግባር ንጹሕ ከሆንን፣ ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ ካመለክነው እንዲሁም ከእሱ ጋር በግለሰብ ደረጃ የቀረበ ዝምድና ከመሠረትን ቅዱስ ልንባል እንችላለን። ፍጹማን ካለመሆናችን አንጻር፣ ቅዱስ ከሆነው አምላካችን ጋር በግለሰብ ደረጃ ወዳጅነት መመሥረት መቻላችን በራሱ፣ ለማሰብ እንኳ የሚከብድ ልዩ መብት ነው። ይሖዋ በሁሉም መንገድ ንጹሕ እና ቅዱስ ነው። ሱራፌል የተባሉት በይሖዋ ዙፋን አቅራቢያ የሚያገለግሉ መላእክት ይሖዋን ከገለጹበት መንገድ ይህን እንማራለን። ሱራፌል “የሠራዊት ጌታ ይሖዋ ቅዱስ፣ ቅዱስ፣ ቅዱስ ነው” በማለት አውጀዋል። (ኢሳ. 6:3) እርግጥ ነው፣ ቅዱስ ከሆነው አምላካቸው ጋር የቀረበ ዝምድና መመሥረት እንዲችሉ መላእክት ራሳቸው ቅዱሳን መሆን አለባቸው፤ ደግሞም ቅዱሳን ናቸው። w21.12 3 አን. 4-5

እሁድ፣ ነሐሴ 20

የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ፤ . . . ጊዜያችሁን በተሻለ መንገድ ተጠቀሙበት።—ኤፌ. 5:15, 16

ወጣቶች ‘የትኛውን የሕይወት ጎዳና ልምረጥ?’ የሚለው ጉዳይ ብዙ ጊዜ ያሳስባቸዋል። በአንድ በኩል የትምህርት ቤት አማካሪዎችና የማያምኑ የቤተሰብ አባላት፣ በዓለም ላይ አንቱ የሚያስብል ሥራ ለማግኘት ከፍተኛ ትምህርት እንዲከታተሉ ይገፋፏቸው ይሆናል። ይህ አካሄድ በአብዛኛው ጊዜያቸውን ሙሉ በሙሉ ይወስድባቸዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ወላጆቻቸውና በጉባኤ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች ሕይወታቸውን ይሖዋን ለማገልገል እንዲጠቀሙበት ያበረታቷቸው ይሆናል። ታዲያ ይሖዋን የሚወድ አንድ ወጣት ከሁሉ የተሻለውን ውሳኔ ለማድረግ ምን ይረዳዋል? ኤፌሶን 5:15-17⁠ን ማንበቡና በዚያ ላይ ማሰላሰሉ ይጠቅመዋል። አንድ ወጣት ይህን ጥቅስ ካነበበ በኋላ እንደሚከተለው ብሎ ራሱን ሊጠይቅ ይችላል፦ ‘“የይሖዋ ፈቃድ” ምንድን ነው? እሱ የሚደሰተው ምን ዓይነት ውሳኔ ባደርግ ነው? ጊዜዬን ከሁሉ በተሻለ መንገድ መጠቀም የምችለው የትኛውን ጎዳና ብከተል ነው?’ “ቀኖቹ ክፉዎች” እንደሆኑና በሰይጣን የሚመራው ይህ ሥርዓት በቅርቡ እንደሚጠፋ አስታውሱ። w22.01 27 አን. 5

ሰኞ፣ ነሐሴ 21

ወንድሞቹም ቢሆኑ አላመኑበትም ነበር።—ዮሐ. 7:5

ያዕቆብ የኢየሱስ ታማኝ ተከታይ የሆነው መቼ ነው? ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ “ለያዕቆብ ታየ፤ ቀጥሎም ለሐዋርያቱ በሙሉ ታየ።” (1 ቆሮ. 15:7) ያዕቆብ ከኢየሱስ ጋር የተገናኘበት ይህ አጋጣሚ በሕይወቱ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል። በኋላ ላይ ሐዋርያቱ ኢየሩሳሌም ባለ አንድ ደርብ ላይ ሆነው ቃል የተገባላቸውን መንፈስ ቅዱስ ይጠባበቁ በነበረበት ወቅት ያዕቆብ አብሯቸው ነበር። (ሥራ 1:13, 14) ከጊዜ በኋላ ያዕቆብ በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የበላይ አካል አባል ሆኖ የማገልገል መብት አግኝቷል። (ሥራ 15:6, 13-22፤ ገላ. 2:9) ከ62 ዓ.ም. ገደማ በፊት ደግሞ በመንፈስ መሪነት ለቅቡዓን ክርስቲያኖች ደብዳቤ ጽፏል። ተስፋችን ሰማያዊም ይሁን ምድራዊ ይህ ደብዳቤ በዛሬው ጊዜ ያለነውን ሁሉ ይጠቅመናል። (ያዕ. 1:1) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የኖረው ታሪክ ጸሐፊ ጆሴፈስ እንደዘገበው ያዕቆብ የአይሁድ ሊቀ ካህናት የሆነው ሐናንያ (የሐና ልጅ) ባስተላለፈው ትእዛዝ ተገድሏል። ያዕቆብ ምድራዊ ሕይወቱን እስካጠናቀቀበት ጊዜ ድረስ ይሖዋን በታማኝነት አገልግሏል። w22.01 8 አን. 3፤ 9 አን. 5

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 22

አምላኬ፣ አምላኬ ለምን ተውከኝ?—ማቴ. 27:46

በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ካለው ሐሳብ የምናገኘው አንዱ ትምህርት ይሖዋ ከእምነት ፈተናዎች ከለላ እንዲያደርግልን መጠበቅ እንደሌለብን ነው። ኢየሱስ እስከ መጨረሻ ድረስ እንደተፈተነ ሁሉ እኛም አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ እስከ ሞት ድረስ ታማኝነታችንን ለማስመሥከር ዝግጁ መሆን ይኖርብናል። (ማቴ. 16:24, 25) ይሁን እንጂ አምላክ ልንሸከመው ከምንችለው በላይ ፈተና እንዲደርስብን እንደማይፈቅድ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (1 ቆሮ. 10:13) ኢየሱስ ከተናገረው ሐሳብ ሌላስ ምን እንማራለን? እንደ ኢየሱስ ግፍ ሊደርስብን ይችላል። (1 ጴጥ. 2:19, 20) ተቃዋሚዎቻችን ስደት የሚያደርሱብን የዓለም ክፍል ባለመሆናችን እና ስለ እውነት በመመሥከራችን ነው እንጂ የሠራነው ጥፋት ስላለ አይደለም። (ዮሐ. 17:14፤ 1 ጴጥ. 4:15, 16) ኢየሱስ፣ መከራ እንዲደርስበት ይሖዋ የፈቀደው ለምን እንደሆነ ያውቅ ነበር። በአንጻሩ ግን መከራ የደረሰባቸው አንዳንድ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች፣ ይሖዋ መከራ እንዲደርስባቸው የፈቀደው ለምን እንደሆነ ግልጽ አልሆነላቸውም። (ዕን. 1:3) መሐሪና ታጋሽ የሆነው አምላካችን እነዚህ አገልጋዮቹ እንዲህ የተሰማቸው እምነት በማጣታቸው እንዳልሆነ ያውቃል፤ እነዚህ የይሖዋ ሕዝቦች እሱ ብቻ ሊሰጣቸው የሚችለው ማጽናኛ ያስፈልጋቸዋል።—2 ቆሮ. 1:3, 4፤ w21.04 11 አን. 9-10

ረቡዕ፣ ነሐሴ 23

ጸሎቴ በአንተ ፊት እንደተዘጋጀ ዕጣን ይሁን።—መዝ. 141:2

ይሖዋ አምልኳችንን እንዲቀበልልን ከፈለግን አምልኮውን ያቀረብነው ከዓላማው ጋር በሚስማማ መልኩ እንዲሁም ፍቅርና አክብሮት በሚንጸባረቅበት መንገድ መሆን ይኖርበታል። ይሖዋ አምልኮ ሊቀርብለት እንደሚገባ እናውቃለን፤ በተጨማሪም በተቻለን መጠን ጥራት ያለው አምልኮ ልናቀርብለት እንፈልጋለን። ለይሖዋ አምልኮ የምናቀርብበት አንዱ መንገድ ወደ እሱ መጸለይ ነው። ቅዱሳን መጻሕፍት ጸሎታችንን መጀመሪያ ላይ በማደሪያው ድንኳን በኋላም በቤተ መቅደሱ ይቀርብ ከነበረው በጥንቃቄ የተዘጋጀ ዕጣን ጋር ያመሳስሉታል። እንዲህ ያለው ዕጣን አምላክን ያስደስተው ነበር። በተመሳሳይም በጣም ቀላል የሆኑ ቃላትን እንኳ ተጠቅመን የምናቀርበው ከልብ የመነጨ ጸሎት አምላክን “ደስ ያሰኘዋል።” (ምሳሌ 15:8፤ ዘዳ. 33:10) ይሖዋ ለእሱ ያለንን ፍቅርና አመስጋኝነት ስንገልጽ መስማት ያስደስተዋል። ያሳሰበንን፣ ተስፋ የምናደርገውንና የምንመኘውን ነገር ለእሱ እንድንነግረው ይፈልጋል። ወደ ይሖዋ በጸሎት ከመቅረብህ በፊት በጸሎትህ ላይ ልታካትታቸው ስለምትችላቸው ነገሮች ለምን ቆም ብለህ አታስብም? እንዲህ ማድረግህ በሰማይ ላለው አባትህ ምርጥ “ዕጣን” ለማቅረብ ያስችልሃል። w22.03 20 አን. 2፤ 21 አን. 7

ሐሙስ፣ ነሐሴ 24

መከራን የምትቀበሉት እናንተ . . . ጌታ ኢየሱስ ከኃያላን መላእክቱ ጋር ከሰማይ በሚገለጥበት ጊዜ ከእኛ ጋር እረፍት ይሰጣችኋል።—2 ተሰ. 1:7

በአርማጌዶን ወቅት የይሖዋ ምሕረት የሚገባው ይሄ ነው ወይስ ያ የሚለውን መወሰን የእኛ ቦታ አይደለም። (ማቴ. 25:34, 41, 46) ታዲያ ይሖዋ ያኔ በሚሰጠው ፍርድ እንተማመናለን? ወይስ ማሰናከያ ይሆንብን ይሆን? በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ወደፊት ሙሉ በሙሉ በይሖዋ መታመን እንድንችል ከአሁኑ በእሱ ላይ ያለንን እምነት ማጠናከራችን በጣም አስፈላጊ ነው። በአዲሱ ዓለም ውስጥ ምን እንደሚሰማን አስቡት። የሐሰት ሃይማኖት አይኖርም፤ በታሪክ ዘመናት ሁሉ የሰው ልጆች እንዲማቅቁና ይህ ነው የማይባል ሥቃይ እንዲደርስባቸው ያደረገው ስግብግብ የንግድ ሥርዓትና የፖለቲካው ሥርዓትም ተጠራርገው ጠፍተዋል። በጤና ችግር፣ በእርጅና ወይም የምንወደውን ሰው በሞት በማጣታችን ምክንያት በየቀኑ አንደቆስም። ሰይጣንና አጋንንቱ ለአንድ ሺህ ዓመት ይታሰራሉ። ዓመፃቸው ያስከተለው ጉዳት ሙሉ በሙሉ ይወገዳል። (ራእይ 20:2, 3) በይሖዋ አሠራር በመታመናችን ያን ጊዜ ምን ያህል አመስጋኝ እንደምንሆን አስቡት! w22.02 6 አን. 16-17

ዓርብ፣ ነሐሴ 25

ሰላም ፈጣሪዎች ደስተኞች ናቸው።—ማቴ. 5:9

ኢየሱስ ቅድሚያውን ወስዶ ሰላም ለመፍጠር ጥረት አድርጓል፤ እንዲሁም አለመግባባቶችን እንዲፈቱ ሌሎችን አበረታቷል። ተከታዮቹ ይሖዋ አምልኳቸውን እንዲቀበል ከፈለጉ ከወንድማቸው ጋር ሰላም መፍጠር እንዳለባቸው አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 5:23, 24) በተጨማሪም በሐዋርያቱ መካከል ‘ማነው ታላቅ?’ የሚል ክርክር በሚነሳበት ወቅት በተደጋጋሚ ጊዜ ጉዳዩን እንዲፈቱ ረድቷቸዋል። (ሉቃስ 9:46-48፤ 22:24-27) ሰላም ፈጣሪ መሆን ላለመጋጨት ከመጠንቀቅ ያለፈ ነገርን ይጠይቃል። ቅድሚያውን ወስደን ሰላም መፍጠር ይኖርብናል፤ እንዲሁም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አለመግባባቶችን እንዲፈቱ ማበረታታት አለብን። (ፊልጵ. 4:2, 3፤ ያዕ. 3:17, 18) ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቃችን ጠቃሚ ነው፦ ‘ከሌሎች ጋር ሰላም ለመፍጠር ምን ያህል መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኛ ነኝ? አንድ ወንድም ወይም አንዲት እህት ስሜቴን ሲጎዱት ቂም እይዛለሁ? ሌላኛው ሰው ቅድሚያውን ወስዶ እስኪያናግረኝ ድረስ እጠብቃለሁ? ወይስ የችግሩ መንስኤ ግለሰቡ እንደሆነ በሚሰማኝ ጊዜም እንኳ ቅድሚያውን ለመውሰድ ፈቃደኛ ነኝ?’ w22.03 10 አን. 10-11

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 26

ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።—ሥራ 20:35

ከብዙ ዘመናት በፊት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተነገረ አንድ ትንቢት አለ፤ ትንቢቱ የአምላክ ሕዝቦች በኢየሱስ አመራር ሥር ሆነው ይሖዋን ለማገልገል ‘በገዛ ፈቃዳቸው ራሳቸውን እንደሚያቀርቡ’ ይናገራል። (መዝ. 110:3) ይህ ትንቢት በዛሬው ጊዜ በሚገባ እየተፈጸመ ነው። ቀናተኛ የሆኑ የይሖዋ አገልጋዮች በስብከቱ ሥራ ላይ በየዓመቱ በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዓታት ያሳልፋሉ። ይህን የሚያደርጉት በገዛ ፈቃዳቸውና መሥዋዕትነት እየከፈሉ ጭምር ነው። ከዚህም በተጨማሪ ለእምነት ባልንጀሮቻቸው አካላዊ፣ ስሜታዊና መንፈሳዊ ድጋፍ ለማድረግ ጊዜያቸውን ይሰጣሉ። የተሾሙ ወንድሞች የስብሰባ ክፍሎችን በመዘጋጀትና ለእምነት ባልንጀሮቻቸው እረኝነት በማድረግ ብዙ ሰዓታት ያሳልፋሉ። ይህን ሁሉ እንዲያከናውኑ የሚያነሳሳቸው ምንድን ነው? ፍቅር ነው፤ ለይሖዋና ለባልንጀሮቻቸው ያላቸው ፍቅር። (ማቴ. 22:37-39) ኢየሱስ ከራሱ ይልቅ የሌሎችን ፍላጎት በማስቀደም ግሩም ምሳሌ ትቷል። እኛም የእሱን አርዓያ ለመከተል የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። (ሮም 15:1-3) የእሱን ምሳሌ የሚከተሉ ሁሉ ብዙ ጥቅም ያገኛሉ። w22.02 20 አን. 1-2

እሁድ፣ ነሐሴ 27

የቅጥር ሠራተኛውን ደሞዝ ሳትከፍል አታሳድር።—ዘሌ. 19:13

በግብርና በሚተዳደረው የእስራኤል ማኅበረሰብ ውስጥ ቅጥር ሠራተኞች ደሞዛቸው የሚከፈላቸው በእያንዳንዱ ቀን ማብቂያ ላይ ነበር። በመሆኑም አንድ አሠሪ ለቅጥር ሠራተኛው ደሞዙን ሳይከፍለው ቢቀር ይህ ሠራተኛ በዚያ ዕለት ቤተሰቡን ለመመገብ የሚያስፈልገው ገንዘብ አይኖረውም። ይሖዋ እንዲህ ብሏል፦ “ችግረኛ በመሆኑና ሕይወቱ የተመካው በደሞዙ ላይ ስለሆነ ፀሐይ ከመጥለቋ በፊት ስጠው።” (ዘዳ. 24:14, 15፤ ማቴ. 20:8) በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ቅጥር ሠራተኞች የሚከፈላቸው በየቀኑ ሳይሆን በየወሩ ወይም በየሁለት ሳምንቱ ነው። ያም ቢሆን በዘሌዋውያን 19:13 ላይ የሚገኘው መሠረታዊ ሥርዓት ዛሬም ይሠራል። አንዳንድ ቀጣሪዎች ለሠራተኞቻቸው ከሚገባቸው በጣም ያነሰ ደሞዝ በመክፈል መጠቀሚያ ያደርጓቸዋል። አሠሪዎቹ ይህን የሚያደርጉት ሠራተኞቹ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸውና የሚከፈላቸው ደሞዝ እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉ ስለሚያውቁ ነው። እንዲህ ያሉት አሠሪዎች “የቅጥር ሠራተኛውን ደሞዝ [አልከፈሉም]” ሊባል ይችላል። ሌሎችን ቀጥሮ የሚያሠራ አንድ ክርስቲያን ሠራተኞቹን በተገቢው መንገድ ለመያዝ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል። w21.12 10 አን. 9-10

ሰኞ፣ ነሐሴ 28

ተጠማሁ።—ዮሐ. 19:28

ኢየሱስ ብዙ መከራ ደርሶበታል፤ ስለዚህ በጣም ተጠምቶ መሆን አለበት። ጥሙን ለማርካት እርዳታ ያስፈልገው ነበር። ኢየሱስ፣ ስሜቱን መናገር የድክመት ምልክት እንደሆነ አልተሰማውም፤ እኛም እንደዚህ ሊሰማን አይገባም። አንዳንዶቻችን የሌሎችን እርዳታ መጠየቅ ይከብደን ይሆናል። ሆኖም የሌሎች እገዛ የሚያስፈልገን ከሆነ እርዳታ ከመጠየቅ ወደኋላ ማለት የለብንም። ለምሳሌ ዕድሜያችን ከገፋ ወይም የአቅም ገደብ ካለብን፣ ገበያ አሊያም ሐኪም ቤት ለመሄድ የወዳጆቻችንን እርዳታ መጠየቅ ሊያስፈልገን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ስሜታችን ከተደቆሰ ወይም የተስፋ መቁረጥ ስሜት ከተሰማን ለአንድ የጉባኤ ሽማግሌ ወይም የጎለመሰ ክርስቲያን ስሜታችንን አውጥተን ልንነግረው እንችላለን። በተጨማሪም የሚያበረታታ “መልካም ቃል” እንዲያካፍለን ልንጠይቀው እንችላለን። (ምሳሌ 12:25) ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ይወዱናል፤ እንዲሁም ‘በመከራ ቀን’ ሊረዱን ይፈልጋሉ። (ምሳሌ 17:17) ይሁንና በልባችን ውስጥ ያለውን ነገር ማንበብ አይችሉም። እኛ ራሳችን እስካልነገርናቸው ድረስ እርዳታ እንደሚያስፈልገን ላያውቁ ይችላሉ። w21.04 11-12 አን. 11-12

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 29

በመከራ ቀን ተስፋ የምትቆርጥ ከሆነ ጉልበትህ እጅግ ይዳከማል።—ምሳሌ 24:10

አብዛኞቻችን ለውጥን ማስተናገድ ይከብደናል። በአንድ ዓይነት የልዩ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ዘርፍ ለረጅም ጊዜ ያገለገሉ አንዳንድ ወንድሞችና እህቶች የአገልግሎት ምድብ ለውጥ አጋጥሟቸዋል። ሌሎች ደግሞ በዕድሜያቸው ምክንያት የሚወዱትን የአገልግሎት መብት ለመተው ተገደዋል። እንዲህ ያለ ለውጥ ሲያጋጥመን ብናዝን የሚያስገርም አይደለም። የይሖዋ ዓይነት አመለካከት ማዳበራችን ያጋጠመንን ለውጥ በተሻለ ሁኔታ ለማስተናገድ ይረዳናል። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ አስደናቂ ነገሮችን እያከናወነ ነው፤ እኛም ከእሱ ጋር አብረን የመሥራት ልዩ መብት አግኝተናል። (1 ቆሮ. 3:9) ይሖዋ ለእኛ ያለው ፍቅር ፈጽሞ አይቀየርም። እንግዲያው በድርጅቱ ውስጥ የተደረገ ለውጥ እናንተን በግለሰብ ደረጃ ከነካችሁ ለውጡ የተደረገባቸውን ምክንያቶች በማሰብ አትብሰልሰሉ። ‘የቀድሞውን ዘመን’ ከመናፈቅ ተቆጠቡ፤ ከዚህ ይልቅ ለውጡ ያስገኛቸውን መልካም ነገሮች ለማስተዋል እንዲረዳችሁ ወደ ይሖዋ ጸልዩ። (መክ. 7:10) ምንጊዜም አዎንታዊ አመለካከት ይኑራችሁ። አዎንታዊ አመለካከት መያዛችሁ ደስታችሁን እንዳታጡና ታማኝ እንድትሆኑ ይረዳችኋል። w22.03 17 አን. 11-12

ረቡዕ፣ ነሐሴ 30

ይሖዋ፣ ይሖዋ . . . ታማኝ ፍቅርን ለሺዎች የሚያሳይ [አምላክ]።—ዘፀ. 34:6, 7

ይሖዋ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው ለእነማን ነው? መጽሐፍ ቅዱስ ለተለያዩ ነገሮች ፍቅር ሊኖረን እንደሚችል ይናገራል። ለምሳሌ ‘ግብርናን፣’ ‘የወይን ጠጅንና ዘይትን፣’ “ተግሣጽን፣” “እውቀትን፣” እንዲሁም “ጥበብን” ልንወድ እንደምንችል ይናገራል። (2 ዜና 26:10፤ ምሳሌ 12:1፤ 21:17፤ 29:3) ታማኝ ፍቅርን ግን ለግዑዝ ነገሮች ወይም ለጽንሰ ሐሳቦች ማሳየት አይቻልም። ይሖዋ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው ማሰብ ለሚችሉ ፍጥረታት ብቻ ነው። ሆኖም ይሖዋ ታማኝ ፍቅር የሚያሳየው ለሁሉም ሰው አይደለም። እንዲህ ዓይነት ፍቅር የሚያሳየው ከእሱ ጋር ልዩ የሆነ ዝምድና ላላቸው ሰዎች ነው። አምላካችን ለወዳጆቹ ታማኝ ነው። ለእነሱ አስደናቂ ዓላማ አለው፤ እንዲሁም መቼም ቢሆን እነሱን መውደዱን አያቆምም። ይሖዋ ለሰው ልጆች በሙሉ ፍቅር አሳይቷል። ኢየሱስ ለኒቆዲሞስ እንዲህ ብሎታል፦ “አምላክ ዓለምን [ማለትም ሁሉንም ሰው] እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።”—ዮሐ. 3:1, 16፤ ማቴ. 5:44, 45፤ w21.11 2 አን. 3፤ 3 አን. 6-7

ሐሙስ፣ ነሐሴ 31

ከጸናችሁ ሕይወታችሁን ታተርፋላችሁ።—ሉቃስ 21:19

በዚህ ሥርዓት ውስጥ ሕይወት በጣም ከባድ ነው፤ ወደፊት ደግሞ ይበልጥ ከባድ ሊሆን እንደሚችል እንጠብቃለን። (ማቴ. 24:21) ይህ ሁሉ መከራ ያለፈ ታሪክ የሚሆንበትንና ጨርሶ የማይታወስበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን! (ኢሳ. 65:16, 17) በመሆኑም ለመጽናት የሚያስችል አቋም እንዲኖረን ከአሁኑ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም ኢየሱስ “ከጸናችሁ ሕይወታችሁን ታተርፋላችሁ” ብሏል። (ሉቃስ 21:19) ከእኛ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ፈተና ያጋጠማቸው ሰዎች እንዴት እንደጸኑ ማሰባችን እኛም በጽናት እንድንቀጥል ይረዳናል። ጽናት በማሳየት ረገድ ከሁሉ የላቀው ምሳሌ ማን ነው? ይሖዋ አምላክ ነው። ይህ ሐሳብ ያስገርምህ ይሆናል። ግን እስቲ አስበው። ይህ ዓለም በዲያብሎስ ቁጥጥር ሥር በመሆኑ በብዙ ችግሮች የተሞላ ነው። ይሖዋ እነዚህን ችግሮች በቅጽበት ለማጥፋት ኃይሉ አለው፤ ግን ይህን ለማድረግ ጊዜው እስኪደርስ በትዕግሥት እየጠበቀ ነው። (ሮም 9:22) አምላካችን፣ የቀጠረው ጊዜ እስኪደርስ ድረስ ይጸናል። w21.07 8 አን. 2-4

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ