የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es23 ገጽ 88-97
  • መስከረም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መስከረም
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2023
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ዓርብ፣ መስከረም 1
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 2
  • እሁድ፣ መስከረም 3
  • ሰኞ፣ መስከረም 4
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 5
  • ረቡዕ፣ መስከረም 6
  • ሐሙስ፣ መስከረም 7
  • ዓርብ፣ መስከረም 8
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 9
  • እሁድ፣ መስከረም 10
  • ሰኞ፣ መስከረም 11
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 12
  • ረቡዕ፣ መስከረም 13
  • ሐሙስ፣ መስከረም 14
  • ዓርብ፣ መስከረም 15
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 16
  • እሁድ፣ መስከረም 17
  • ሰኞ፣ መስከረም 18
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 19
  • ረቡዕ፣ መስከረም 20
  • ሐሙስ፣ መስከረም 21
  • ዓርብ፣ መስከረም 22
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 23
  • እሁድ፣ መስከረም 24
  • ሰኞ፣ መስከረም 25
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 26
  • ረቡዕ፣ መስከረም 27
  • ሐሙስ፣ መስከረም 28
  • ዓርብ፣ መስከረም 29
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2023
es23 ገጽ 88-97

መስከረም

ዓርብ፣ መስከረም 1

ከሰማይ ምልክት እንዲያሳያቸው ጠየቁት።—ማቴ. 16:1

በኢየሱስ ዘመን የኖሩ አንዳንድ ሰዎች ግሩም የሆኑ ትምህርቶቹን መስማታቸው ብቻ አላረካቸውም። ተጨማሪ ነገር ፈልገው ነበር። ኢየሱስ የጠየቁትን ምልክት ለማሳየት ፈቃደኛ አለመሆኑ እንዲሰናከሉ አደረጋቸው። (ማቴ. 16:4) ቅዱሳን መጻሕፍት ምን ይላሉ? ነቢዩ ኢሳይያስ ስለ መሲሑ ሲጽፍ “አይጮኽም ወይም ድምፁን ከፍ አያደርግም፤ ድምፁንም በጎዳና ላይ አያሰማም” ብሎ ነበር። (ኢሳ. 42:1, 2) ኢየሱስ አገልግሎቱን ያከናወነው ወደ ራሱ ትኩረት በሚስብ መንገድ አልነበረም። ኢየሱስ ግዙፍ የሆኑ ቤተ መቅደሶችን አልገነባም፤ ለየት ያለ ሃይማኖታዊ ልብስ አልለበሰም፤ ወይም ሰዎች በሃይማኖታዊ የማዕረግ ስሞች እንዲጠሩት አልጠየቀም። ሞት ሊፈረድበት በነበረ ጊዜ እንኳ ኢየሱስ ንጉሥ ሄሮድስን የሚያስደምም ተአምር ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆነም። (ሉቃስ 23:8-11) እርግጥ ኢየሱስ ተአምራት የፈጸመባቸው ጊዜያት አሉ፤ ሆኖም በዋነኝነት ትኩረት ያደረገው ምሥራቹን በመስበኩ ላይ ነበር። ደቀ መዛሙርቱን “የመጣሁት ለዚሁ ነው” ብሏቸዋል።—ማር. 1:38፤ w21.05 4 አን. 9-10

ቅዳሜ፣ መስከረም 2

ብቸኛው እውነተኛ አምላክ የሆንከውን አንተንና የላክኸውን ኢየሱስ ክርስቶስን ማወቅ የዘላለም ሕይወት ነው።—ዮሐ. 17:3

ዓላማችን “ወደ ዘላለም ሕይወት የሚመራ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው” ሰዎችን ማግኘት ነው። (ሥራ 13:48) እነዚህ ሰዎች የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እንዲሆኑ ለመርዳት ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማሩትን ነገር (1) እንዲረዱ፣ (2) እንዲቀበሉ እና (3) በሥራ ላይ እንዲያውሉ ልንረዳቸው ይገባል። (ቆላ. 2:6, 7፤ 1 ተሰ. 2:13) ሁሉም ወንድሞችና እህቶች ለመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶች ፍቅር በማሳየትና በስብሰባ ላይ ሲገኙ እንግድነት እንዳይሰማቸው በማድረግ ጥናቶችን ሊረዷቸው ይችላሉ። (ዮሐ. 13:35) በተጨማሪም አስጠኚው፣ ጥናቱ እንደ “ምሽግ” ጠንካራ የሆኑ እምነቶችንና ልማዶችን እንዲደረምስ ለመርዳት ብዙ ጊዜና ጉልበት ሊጠይቅበት ይችላል። (2 ቆሮ. 10:4, 5) አንድ ሰው እነዚህን እርምጃዎች ወስዶ ወደ ጥምቀት ደረጃ እንዲደርስ ለመርዳት ረጅም ጊዜ ሊያስፈልግ ይችላል። ሆኖም የምናደርገው ጥረት የሚክስ ነው። w21.07 3 አን. 6

እሁድ፣ መስከረም 3

ሁሉንም ነገር መርምሩ፤ መልካም የሆነውን አጥብቃችሁ ያዙ።—1 ተሰ. 5:21

እውነትን እንደምናስተምር እንዲሁም ይሖዋን ተቀባይነት ባለው መንገድ የሚያመልኩት የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ እንደሆኑ እርግጠኞች ነን? ሐዋርያው ጳውሎስ እውነትን እንዳገኘ ሙሉ እምነት ነበረው። (1 ተሰ. 1:5) እምነቱ እንዲሁ በስሜት ላይ ብቻ የተመሠረተ አልነበረም። ጳውሎስ የአምላክን ቃል በትጋት ያጠና ነበር። “ቅዱሳን መጻሕፍት ሁሉ በአምላክ መንፈስ መሪነት የተጻፉ” እንደሆኑ ያምን ነበር። (2 ጢሞ. 3:16) በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ያደረገው ጥናት ምን ድምዳሜ ላይ እንዲደርስ አድርጎታል? ኢየሱስ አስቀድሞ የተነገረለት መሲሕ እንደሆነ የሚያሳይ የማያሻማ ማስረጃ አግኝቷል። የአይሁድ የሃይማኖት መሪዎች ይህን ማስረጃ ችላ ብለውት ነበር። እነዚህ ግብዝ የሃይማኖት መሪዎች አምላክን እንደሚወክሉ ቢናገሩም በሥራቸው ክደውታል። (ቲቶ 1:16) ጳውሎስ ግን ከእነሱ የተለየ አቋም ይዟል፤ የፈለገውን ብቻ ሳይሆን ሙሉውን የአምላክ ቃል ለመቀበል መርጧል። “የአምላክን ፈቃድ ሁሉ” ለማስተማርና ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጁ ነበር።—ሥራ 20:27፤ w21.10 18 አን. 1-2

ሰኞ፣ መስከረም 4

የላከኝ አብ ካልሳበው በቀር ወደ እኔ ሊመጣ የሚችል ሰው የለም።—ዮሐ. 6:44

የምንተክለውና የምናጠጣው እኛ ብንሆንም የሚያሳድገው አምላክ መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። (1 ቆሮ. 3:6, 7) ይሖዋ የሁሉንም ሰው ሕይወት ውድ አድርጎ ይመለከተዋል። የዚህ ሥርዓት መጨረሻ ከመምጣቱ በፊት ከሁሉም ብሔራት ሰዎችን በመሰብሰቡ ሥራ ከልጁ ጋር አብረን የመሥራት መብት ሰጥቶናል። (ሐጌ 2:7) የስብከቱ ሥራችን፣ ሕይወት አድን ሠራተኞች ከሚያከናውኑት ሥራ ጋር ሊመሳሰል ይችላል። አደጋ አጋጥሟቸው ከማዕድን ማውጫ ውስጥ መውጣት ያልቻሉ ሰዎችን ለማዳን ከተሰማሩ ሕይወት አድን ሠራተኞች ጋር እንመሳሰላለን። ከአደጋው በሕይወት የተረፉት ጥቂት ማዕድን አውጪዎች ብቻ ቢሆኑም እንኳ ሁሉም ሕይወት አድን ሠራተኞች ያከናወኑት ሥራ ትልቅ ዋጋ አለው። ከአገልግሎታችን ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ከዚህ በኋላ ከሰይጣን ሥርዓት መትረፍ የሚችሉ ምን ያህል ሰዎች እንዳሉ አናውቅም። ሆኖም ይሖዋ እነዚህን ሰዎች ለመርዳት ማናችንንም ሊጠቀም ይችላል። በቦሊቪያ የሚኖረው አንድሪያስ “አንድ ሰው የመጽሐፍ ቅዱስን እውነቶች ተምሮ እንዲጠመቅ መርዳት የቡድን ሥራ እንደሆነ ይሰማኛል” በማለት ተናግሯል። እኛም ለአገልግሎታችን እንዲህ ያለ አዎንታዊ አመለካከት ሊኖረን ይገባል። እንዲህ ካደረግን ይሖዋ ይባርከናል፤ ከአገልግሎታችንም እውነተኛ ደስታ ማግኘት እንችላለን። w21.05 19 አን. 19-20

ማክሰኞ፣ መስከረም 5

[ከዲያብሎስ] ወጥመድ [ውጡ]።—2 ጢሞ. 2:26

የአዳኞች ዓላማ የሚፈልጉትን እንስሳ መያዝ ወይም መግደል ነው። አንድ አዳኝ የሚፈልገውን እንስሳ ለመያዝ የተለያዩ ወጥመዶችን ሊጠቀም ይችላል፤ ከኢዮብ የውሸት አጽናኞች መካከል አንዱም ይህን ገልጿል። (ኢዮብ 18:8-10) ታዲያ አዳኙ፣ እንስሳው ወደ ወጥመዱ እንዲገባለት የሚያደርገው እንዴት ነው? እንስሳውን በደንብ ያጠናዋል። እንስሳው ብዙ ጊዜ የሚገኘው የት ነው? የሚወደው ነገር ምንድን ነው? ሳያስበው ማጥመድ የሚቻለው እንዴት ነው? ሰይጣንም የሚያደርገው ነገር ከአዳኙ ጋር ይመሳሰላል። በደንብ ያጠናናል። ጊዜ የምናሳልፈው የት እንደሆነ እንዲሁም ምን እንደምንወድ ይከታተላል። ከዚያም ሳናስበው ሊይዘን የሚችል ወጥመድ ይዘረጋል። ሆኖም በሰይጣን ወጥመድ ብንያዝም እንኳ ከወጥመዱ መውጣት እንደምንችል መጽሐፍ ቅዱስ ማረጋገጫ ይሰጠናል። እንዲሁም ቀድሞውንም በወጥመዶቹ ላለመያዝ ምን ማድረግ እንደምንችል ያስተምረናል። በጣም ውጤታማ ከሆኑት የሰይጣን ወጥመዶች መካከል ሁለቱ ኩራት እና ስግብግብነት ናቸው። ሰይጣን እነዚህን መጥፎ ባሕርያት በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ሲጠቀምባቸው ቆይቷል፤ ደግሞም ተሳክቶለታል። ሰይጣን፣ ወጥመድ ወይም መረብ ተጠቅሞ እንደሚያጠምድ ወፍ አዳኝ ነው። (መዝ. 91:3) ሆኖም ከሰይጣን ወጥመዶች ማምለጥ አንችልም ማለት አይደለም። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ሰይጣን የሚጠቀምባቸውን ዘዴዎች ይሖዋ ስላሳወቀን ነው።—2 ቆሮ. 2:11፤ w21.06 14 አን. 1-2

ረቡዕ፣ መስከረም 6

ሽበት በጽድቅ መንገድ ሲገኝ የውበት ዘውድ ነው።—ምሳሌ 16:31

ታማኝ አረጋውያን ውድ ሀብት ናቸው። የአምላክ ቃል የአረጋውያንን ሽበት ከዘውድ ጋር ያመሳስለዋል። (ምሳሌ 20:29) ሆኖም አረጋውያን ውድ ሀብት መሆናቸውን ላናስተውል እንችላለን። አረጋውያን ያላቸውን ዋጋ የሚገነዘቡ ወጣቶች ከቁሳዊ ሀብት የሚበልጥ ውድ ነገር ያገኛሉ። ታማኝ አረጋውያን ለይሖዋ አምላክ ውድ ናቸው። ይሖዋ ውስጣዊ ማንነታቸውን ያያል፤ እንዲሁም ግሩም ባሕርያታቸውን ያደንቃል። አረጋውያን እሱን ለረጅም ዘመን በታማኝነት በማገልገል ያካበቱትን ጥበብ ለወጣቶች ሲያካፍሉ በጣም ይደሰታል። (ኢዮብ 12:12፤ ምሳሌ 1:1-4) በተጨማሪም ይሖዋ አረጋውያን የሚያሳዩትን ጽናት ከፍ አድርጎ ይመለከታል። (ሚል. 3:16) አረጋውያን በሕይወታቸው ውስጥ ብዙ ችግሮች አጋጥመዋቸዋል፤ ሆኖም በይሖዋ ላይ ያላቸው እምነት አልተናወጠም። ስለ ወደፊቱ ጊዜ ያላቸው ተስፋ እውነትን በሰሙበት ጊዜ ከነበረው ይበልጥ ብሩህ ነው። ደግሞም “ባረጁ ጊዜም እንኳ” የይሖዋን ስም ማወጃቸውን ስለቀጠሉ ይሖዋ በጣም ይወዳቸዋል።—መዝ. 92:12-15፤ w21.09 2 አን. 2-3

ሐሙስ፣ መስከረም 7

እያንዳንዱ ሰው የራሱን ተግባር ይመርምር፤ ከዚያም . . . ከራሱ ጋር ብቻ በተያያዘ እጅግ የሚደሰትበት ነገር ያገኛል።—ገላ. 6:4

ውስጣዊ ዝንባሌያችንን አልፎ አልፎ መመርመራችን አስፈላጊ ነው። ራሳችንን እንደሚከተለው እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ለራሴ ጥሩ ግምት የሚኖረኝ ከሌሎች የተሻልኩ እንደሆንኩ ሲሰማኝ ብቻ ነው? አንድን ሥራ ለማከናወን የሚያነሳሳኝ፣ ከሁሉም ሰው ሌላው ቢቀር ከአንድ ወንድም ወይም ከአንዲት እህት በልጬ ለመገኘት ያለኝ ፍላጎት ነው? ወይስ ጠንክሬ የምሠራው ለይሖዋ ምርጤን መስጠት ስለምፈልግ ነው?’ መጽሐፍ ቅዱስ ራሳችንን ከሌሎች ጋር ከማወዳደር እንድንቆጠብ ያሳስበናል። ለምን? ከወንድማችን የተሻልን እንደሆንን ከተሰማን ኩራት ሊያድርብን ይችላል። በሌላ በኩል ደግሞ ራሳችንን ከሌሎች ጋር ስናወዳድር እነሱ የተሻሉ እንደሆኑ ከተሰማን ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። (ሮም 12:3) ይሖዋ ወደ ራሱ የሳበን ቆንጆ፣ አንደበተ ርቱዕ ወይም በሌሎች ዘንድ ተወዳጅ ስለሆንን እንዳልሆነ ልናስታውስ ይገባል፤ ከዚህ ይልቅ ይሖዋ የሳበን እሱን ለመውደድና ልጁን ለመስማት ፈቃደኛ መሆናችንን ስላየ ነው።—ዮሐ. 6:44፤ 1 ቆሮ. 1:26-31፤ w21.07 14-15 አን. 3-4

ዓርብ፣ መስከረም 8

አእምሯችሁን የሚያሠራው ኃይል እየታደሰ ይሂድ።—ኤፌ. 4:23

አእምሯችንን የሚያሠራው ኃይል እንዲታደስ መጸለይ፣ የአምላክን ቃል ማጥናትና ማሰላሰል እንዳለብን የታወቀ ነው። እነዚህን ነገሮች አዘውትረህ አድርግ፤ እንዲሁም ይሖዋ ብርታት እንዲሰጥህ ጠይቀው። የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ራስህን ከሌሎች ጋር የማወዳደር ዝንባሌህን ለማሸነፍ ይረዳሃል። በተጨማሪም በልብህ ውስጥ ምቀኝነት ወይም ተገቢ ያልሆነ ኩራት እያቆጠቆጠ ከሆነ ይሖዋ እነዚህን መጥፎ ዝንባሌዎች ለማስተዋልና ለማስወገድ ይረዳሃል። (2 ዜና 6:29, 30) ይሖዋ ልባችንን ያውቃል። በተጨማሪም ከዓለም መንፈስና ከራሳችን አለፍጽምና ጋር የምናደርገውን ትግል ያውቃል። ይሖዋ እነዚህን አሉታዊ ተጽዕኖዎች ለመቋቋም የምናደርገውን ከፍተኛ ጥረት ሲያይ ለእኛ ያለው ፍቅር ይጨምራል። ይሖዋ ለእኛ ያለውን ፍቅር ለማስረዳት እናት ለሕፃን ልጇ ያላትን ፍቅር እንደ ምሳሌ ተጠቅሟል። (ኢሳ. 49:15) ይሖዋ እሱን በሙሉ ነፍሳችን ለማገልገል የምናደርገውን ከፍተኛ ጥረት ሲያይ ለእኛ እንዲህ ያለ ጥልቅ ፍቅር እንደሚሰማው ማወቃችን በጣም ያጽናናናል! w21.07 24-25 አን. 17-19

ቅዳሜ፣ መስከረም 9

ደስ ከሚላቸው ጋር ደስ ይበላችሁ።—ሮም 12:15

በይሖዋ አገልግሎት በተሰጠን በማንኛውም ሥራ ላይ ትኩረታችንን ሙሉ በሙሉ በማሳረፍ ደስታችንን መጨመር እንችላለን። በስብከቱ ሥራ ‘በእጅጉ ተጠመድ’፤ እንዲሁም በጉባኤ እንቅስቃሴዎች ሙሉ ተሳትፎ አድርግ። (ሥራ 18:5፤ ዕብ. 10:24, 25) በስብሰባዎች ላይ የሚያንጹ ሐሳቦች መስጠት እንድትችል በሚገባ ተዘጋጅ። በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ የተሰጠህን ማንኛውንም የተማሪ ክፍል በቁም ነገር ተመልከተው። በጉባኤ ውስጥ አንድ ሥራ ከተሰጠህ ሥራህን በጊዜው አከናውን፤ እንዲሁም እምነት የሚጣልብህ ሁን። በጉባኤ ውስጥ የተሰጠህን የትኛውንም ሥራ ሳትንቅ ጊዜ ሰጥተህ አከናውን። በተመደብክበት ሥራ ችሎታህን ለማሻሻል ጥረት አድርግ። (ምሳሌ 22:29) በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እና በተሰጡህ ኃላፊነቶች ላይ ትኩረትህ ሙሉ በሙሉ እንዲያርፍ ካደረግህ እድገትህ ይፋጠናል፤ ደስታህም ይጨምራል። (ገላ. 6:4) በተጨማሪም አንተ ለማግኘት የምትመኘውን መብት ሌሎች ሰዎች ቢያገኙ ከእነሱ ጋር አብረህ መደሰት ይበልጥ ቀላል ይሆንልሃል።—ገላ. 5:26፤ w21.08 22 አን. 11

እሁድ፣ መስከረም 10

ከሰማይ የሆነው ጥበብ . . . በመጀመሪያ ንጹሕ ነው፤ ከዚያም ሰላማዊ፣ ምክንያታዊ፣ ለመታዘዝ ዝግጁ የሆነ፣ ምሕረትና መልካም ፍሬዎች የሞሉበት እንዲሁም አድልዎና ግብዝነት የሌለበት ነው።—ያዕ. 3:17

ኩራትን ማስወገድ እንዲሁም ምንጊዜም ለመማር ፈቃደኞች መሆን አለብን። የልባችን የደም ሥሮች እንዲደድሩና ልባችን መምታት እንዲከብደው የሚያደርግ በሽታ አለ፤ ኩራትም ልክ እንደዚህ በሽታ ምሳሌያዊው ልባችን እንዲደነድንና የይሖዋን መመሪያ ለመቀበል አሻፈረኝ እንድንል ሊያደርገን ይችላል። ፈሪሳውያን ልባቸው እንዲደነድን ፈቅደው ነበር፤ ኢየሱስ የአምላክ መንፈስ እንዳለውና የአምላክ ልጅ እንደሆነ የሚያሳየውን ግልጽ ማስረጃ ለመቀበል ፈቃደኛ እንዳይሆኑ ያደረጋቸው ይህ ነው። (ዮሐ. 12:37-40) ይህ አካሄዳቸው አደገኛ ነበር፤ ምክንያቱም የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚያቸውን አሳጥቷቸዋል። (ማቴ. 23:13, 33) እንግዲያው ምንጊዜም የአምላክ ቃል እና መንፈስ ቅዱስ ማንነታችንን እንዲቀርጹት እንዲሁም በአስተሳሰባችን እና በውሳኔያችን ላይ ተጽዕኖ እንዲያሳድሩ መፍቀዳችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! ያዕቆብ ትሑት ስለነበር ከይሖዋ ለመማር ፈቃደኛ ሆኗል። ደግሞም ውጤታማ አስተማሪ መሆን የቻለው ትሑት በመሆኑ ነው። w22.01 10 አን. 7

ሰኞ፣ መስከረም 11

ደጋግማችሁ ለምኑ።—ማቴ. 7:7

‘በጽናት ከጸለይን’ የሰማዩ አባታችን እንደሚሰማንና ጸሎታችንን እንደሚመልስልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ቆላ. 4:2) መልሱ የዘገየ ሆኖ ቢሰማንም እንኳ ይሖዋ ልክ “በሚያስፈልገን ጊዜ” ጸሎታችንን እንደሚመልስልን ቃል ገብቶልናል። (ዕብ. 4:16) አንድ ነገር እኛ በጠበቅነው ጊዜ ሳይፈጸም ቢቀር ይሖዋን ፈጽሞ መውቀስ የሌለብን ለዚህ ነው። ለምሳሌ ያህል ብዙዎች የአምላክ መንግሥት መጥቶ ይህን ሥርዓት እንዲያጠፋ ለዓመታት ሲጸልዩ ቆይተዋል። ኢየሱስም ቢሆን ስለዚህ ጉዳይ መጸለይ እንዳለብን አስተምሯል። (ማቴ. 6:10) ሆኖም አንድ ሰው መጨረሻው ሰዎች በጠበቁት ጊዜ ባለመምጣቱ የተነሳ በአምላክ ላይ ያለው እምነት እንዲዳከም ቢፈቅድ ይህ ምንኛ ሞኝነት ይሆናል! (ዕን. 2:3፤ ማቴ. 24:44) ይሖዋን በትዕግሥት መጠበቃችንና ወደ እሱ በእምነት መጸለያችን የጥበብ እርምጃ ነው። መጨረሻው ልክ በትክክለኛው ጊዜ ይመጣል፤ ምክንያቱም ይሖዋ ‘ቀኑንና ሰዓቱን’ አስቀድሞ ወስኗል። ያ ቀን ሲመጣ፣ ይሖዋ የመረጠው ጊዜ ከሁሉ የተሻለ እንደሆነ ይረጋገጣል።—ማቴ. 24:36፤ 2 ጴጥ. 3:15፤ w21.08 10 አን. 10-11

ማክሰኞ፣ መስከረም 12

ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ።—ፊልጵ. 2:3

ትሑት የሆኑ አረጋውያን ዕድሜያቸው እየገፋ ሲሄድ ቀድሞ ያከናውኑት የነበረውን ያህል ማከናወን እንደማይችሉ ይገነዘባሉ። የወረዳ የበላይ ተመልካቾቻችንን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እነዚህ ወንድሞች 70 ዓመት ሲሆናቸው ሌላ ምድብ ላይ እንዲያገለግሉ ይጋበዛሉ። እርግጥ ይህን ለውጥ ማስተናገድ ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። በወረዳ ሥራ ወንድሞቻቸውን የማገልገል መብታቸውን ከፍ አድርገው ይመለከቱት ነበር። ያም ሆኖ ሥራውን ከእነሱ በዕድሜ የሚያንሱ ወንድሞች ቢያከናውኑት የተሻለ እንደሆነ ይገነዘባሉ። እነዚህ ወንድሞች በጥንቷ እስራኤል የኖሩት ሌዋውያን የነበራቸው ዓይነት አመለካከት ያንጸባርቃሉ፤ ሌዋውያኑ 50 ዓመት ሲሆናቸው በማደሪያ ድንኳኑ የሚያከናውኑትን አገልግሎት ማቆም ነበረባቸው። በዕድሜ የገፉት ሌዋውያን የአገልግሎት ምድባቸው መለወጡ ደስታቸውን አላሳጣቸውም። ማከናወን የሚችሉትን ነገር በቅንዓት የሚያከናውኑ ከመሆኑም ሌላ ወጣቶቹን ሌዋውያን ይረዷቸው ነበር። (ዘኁ. 8:25, 26) በዛሬው ጊዜም የወረዳ የበላይ ተመልካች የነበሩ ወንድሞች እንደ ቀድሞው በርካታ ጉባኤዎችን ባያገለግሉም እንኳ ለጉባኤያቸው ውድ ሀብት ናቸው። w21.09 8-9 አን. 3-4

ረቡዕ፣ መስከረም 13

አባቴ ሆይ፣ በአምላክና በአንተ ላይ በደል ፈጽሜአለሁ። ከእንግዲህ ልጅህ ተብዬ ልጠራ አይገባኝም።—ሉቃስ 15:21

ኢየሱስ በሉቃስ 15:11-32 ላይ ስለ አባካኙ ልጅ የሚገልጸውን ልብ የሚነካ ምሳሌ ተናግሯል። አንድ ወጣት በአባቱ ላይ ዓመፀ፤ ከዚያም ከቤት ወጥቶ “ወደ ሩቅ አገር ተጓዘ።” በዚያም ሥነ ምግባር የጎደለውና ልቅ የሆነ ሕይወት መምራት ጀመረ። ሆኖም ችግር ውስጥ ሲገባ፣ ስለሠራቸው ስህተቶች በጥሞና ማሰብ ጀመረ። በአባቱ ቤት በነበረበት ወቅት ሕይወቱ በጣም የተሻለ እንደነበር ተገነዘበ። ኢየሱስ እንዳለው ወጣቱ ‘ወደ ልቦናው ተመለሰ።’ በመሆኑም ወደ ቤቱ በመመለስ የአባቱን ምሕረት ለመለመን ወሰነ። ወጣቱ፣ ምን ያህል ከባድ ስህተት እንደሠራ መገንዘቡ በጣም አስፈላጊ ነገር ነው። እርምጃ መውሰድ ነበረበት! አባካኙ ልጅ ለሠራው ስህተት ከልቡ ንስሐ መግባቱን አሳይቷል። ይህ ምሳሌ ልብ የሚነካ ታሪክ ብቻ አይደለም። የጉባኤ ሽማግሌዎች ከባድ ኃጢአት የፈጸመ አንድ የእምነት ባልንጀራቸው እውነተኛ ንስሐ መግባት አለመግባቱን በሚገመግሙበት ጊዜ ከዚህ ምሳሌ ለምናገኘው ትምህርት ትኩረት ሊሰጡት ይገባል። w21.10 5 አን. 14-15

ሐሙስ፣ መስከረም 14

ሰማያትን [እና] ምድርን . . . አናውጣለሁ።—ሐጌ 2:6

የማይናወጠው ወይም የማይጠፋው ምንድን ነው? ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “እኛ ሊናወጥ የማይችል መንግሥት ልንቀበል እንደሆነ ስለምናውቅ . . . በአምላካዊ ፍርሃትና በጥልቅ አክብሮት . . . ለአምላክ ቅዱስ አገልግሎት [ማቅረባችንን እንቀጥል]።” (ዕብ. 12:28) ከዚህ የመጨረሻ ታላቅ መናወጥ በኋላ ሳይናወጥ ባለበት የሚቀረው የአምላክ መንግሥት ብቻ ይሆናል። (መዝ. 110:5, 6፤ ዳን. 2:44) የሚባክን ጊዜ የለም! ሰዎች ምርጫ ማድረግ አለባቸው፦ ይህንን ዓለም መደገፋቸውን ለመቀጠል ከመረጡ ጥፋት ይጠብቃቸዋል። በሌላ በኩል ግን ይሖዋን ለማገልገል እንዲሁም የእሱን ፈቃድ ለመፈጸም ሲሉ በሕይወታቸው ውስጥ አስፈላጊውን ለውጥ ለማድረግ ከመረጡ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። (ዕብ. 12:25) የምናከናውነው የስብከት ሥራ ሰዎች በዚህ አስፈላጊ ጉዳይ ላይ ምን ዓይነት ምርጫ እንደሚያደርጉ ለመወሰን ይረዳቸዋል። ጌታችን ኢየሱስ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብም ምንጊዜም እናስታውስ፦ “ይህ የመንግሥቱ ምሥራች ለብሔራት ሁሉ ምሥክር እንዲሆን በመላው ምድር ይሰበካል፤ ከዚያም መጨረሻው ይመጣል።”—ማቴ. 24:14፤ w21.09 19 አን. 18-20

ዓርብ፣ መስከረም 15

ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም።—ዕብ. 13:5

ሽማግሌዎች፣ ይሖዋን የተወ የቤተሰብ አባል ያላቸውን የእምነት ባልንጀሮቻችሁን የማጽናናት ልዩ ኃላፊነት አለባችሁ። (1 ተሰ. 5:14) ከክርስቲያናዊ ስብሰባዎች በፊትና በኋላ እነሱን ለማበረታታት ቅድሚያውን ውሰዱ። ቤታቸው ሄዳችሁ ጠይቋቸው፤ እንዲሁም ጸልዩላቸው። አብራችኋቸው አገልግሉ፤ አልፎ አልፎ ደግሞ በቤተሰብ አምልኳችሁ ላይ ጋብዟቸው። መንፈሳዊ እረኞች በሐዘን ለተዋጡ የይሖዋ በጎች የሚያስፈልጋቸውን ርኅራኄና ፍቅር የማሳየት እንዲሁም ለእነሱ ትኩረት የመስጠት ኃላፊነት አለባቸው። (1 ተሰ. 2:7, 8) ይሖዋ “ሁሉ ለንስሐ እንዲበቃ እንጂ ማንም እንዲጠፋ” አይፈልግም። (2 ጴጥ. 3:9) አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት ቢፈጽምም እንኳ ሕይወቱ በአምላክ ዓይን ውድ ነው። ይሖዋ የኃጢአተኞችን ሕይወት ለማዳን ሲል ምን ያህል ከፍተኛ ዋጋ እንደከፈለ አስቡት፤ የሚወደውን ልጁን ቤዛዊ መሥዋዕት አድርጎ ሰጥቷል። ይሖዋ በርኅራኄ ተነሳስቶ ኃጢአተኞች ወደ እሱ እንዲመለሱ ሊረዳቸው ይጥራል። ኢየሱስ ስለጠፋው ልጅ ከተናገረው ምሳሌ እንደምንማረው ይሖዋ እንዲህ ያሉ ሰዎች ወደ እሱ እንደሚመለሱ ተስፋ ያደርጋል።—ሉቃስ 15:11-32፤ w21.09 30-31 አን. 17-19

ቅዳሜ፣ መስከረም 16

እናንተ የድካማቸው ፍሬ ተካፋዮች ሆናችሁ።—ዮሐ. 4:38

ባጋጠማችሁ የጤና እክል ምክንያት ምሥራቹን በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ የምትፈልጉትን ያህል አስተዋጽኦ ማድረግ ባትችሉስ? ያም ቢሆን በመከሩ ሥራ በምታበረክቱት አስተዋጽኦ ደስተኛ መሆን ትችላላችሁ። ንጉሥ ዳዊትና አብረውት የነበሩት ሰዎች ቤተሰባቸውንና ንብረታቸውን ወረራ ካደረጉባቸው አማሌቃውያን ባስጣሉ ጊዜ የተከናወነውን ነገር እንመልከት። ከሰዎቹ መካከል 200 የሚሆኑት በጣም ከመድከማቸው የተነሳ ወደ ውጊያው ከመሄድ ይልቅ ጓዝ ለመጠበቅ ቀሩ። ወደ ውጊያ የሄዱት ሰዎች ድል አድርገው ሲመለሱ ዳዊት ጓዝ ለመጠበቅ የቀሩትን ሰዎች ጨምሮ ሁሉም ከምርኮው ላይ እኩል እንዲካፈሉ አዘዘ። (1 ሳሙ. 30:21-25) በዓለም ዙሪያ ከሚከናወነው ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። በዚህ ሥራ አቅማቸው የፈቀደውን ያህል የሚያደርጉ ሁሉ አንድ አዲስ ሰው ወደ ዘላለም ሕይወት በሚወስደው መንገድ ላይ መጓዝ ሲጀምር እኩል መደሰት ይችላሉ። ይሖዋ የሚያተኩረው በምናሳየው ትጋትና ፍቅር ላይ ነው፤ ለዚህም ወሮታችንን ይከፍለናል። በተጨማሪም ይሖዋ በመከሩ ሥራ በምናበረክተው አስተዋጽኦ ደስተኛ እንድንሆን ያስተምረናል። (ዮሐ. 14:12) ተስፋ እስካልቆረጥን ድረስ የይሖዋን ሞገስ እንደምናገኝ እርግጠኞች ነን! w21.10 27-28 አን. 15-17

እሁድ፣ መስከረም 17

የወጣቶች ክብር ጉልበታቸው ነው።—ምሳሌ 20:29

ዕድሜያችን እየገፋ ሲሄድ ‘በአንድ ወቅት አደርገው የነበረውን ያህል በይሖዋ አገልግሎት ጠቃሚ አስተዋጽኦ ማበርከት አልችልም’ የሚል ስጋት ያድርብን ይሆናል። የቀድሞውን ያህል ጉልበት እንደማይኖረን ባይካድም ያካበትነውን ጥበብና ተሞክሮ ተጠቅመን ወጣቶች ይሖዋን በተሟላ ሁኔታ እንዲያገለግሉ እንዲሁም ተጨማሪ ኃላፊነቶችን እንዲሸከሙ ልናሠለጥናቸው እንችላለን። አረጋውያን ወጣቶችን መርዳት ከፈለጉ ትሑት መሆን አለባቸው። ትሑት የሆነ ሰው ሌሎች ከእሱ እንደሚበልጡ አድርጎ ያስባል። (ፊልጵ. 2:3, 4) ትሑት የሆኑ አረጋውያን አንድን ነገር ማከናወን የሚቻልባቸው ቅዱስ ጽሑፋዊና ውጤታማ የሆኑ በርካታ መንገዶች እንዳሉ ይገነዘባሉ። በመሆኑም ሁሉም ሰው ነገሮችን እነሱ ድሮ ያከናውኑ በነበረበት መንገድ መሥራት እንዳለበት አይሰማቸውም። (መክ. 7:10) ለወጣቱ ትውልድ ሊያካፍሉ የሚችሉት ብዙ ጠቃሚ ተሞክሮ ቢኖራቸውም “የዚህ ዓለም ትእይንት እየተለዋወጠ” በመሆኑ አዳዲስ አሠራሮችን መልመድ ሊያስፈልጋቸው እንደሚችል ይገነዘባሉ።—1 ቆሮ. 7:31፤ w21.09 8 አን. 1, 3

ሰኞ፣ መስከረም 18

ይሖዋ ሆይ፣ ከአማልክት መካከል እንደ አንተ ያለ ማን ነው? በቅድስናው ኃያል መሆኑን የሚያሳይ እንደ አንተ ያለ ማን ነው?—ዘፀ. 15:11

ይሖዋ፣ አገልጋዮቹ ራሳቸውን በሚያዋርዱ ድርጊቶች እንዲካፈሉ ፈጽሞ አይጠይቃቸውም። ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ቅዱስ ነው። ሊቀ ካህናቱ በሚያደርገው ጥምጥም ላይ በሚቀመጠው ጠፍጣፋ ወርቅ ላይ የተቀረጸው ጽሑፍ ይህን በግልጽ ያሳያል። በወርቁ ላይ “ቅድስና የይሖዋ ነው” የሚል ጽሑፍ ተቀርጾ ነበር። (ዘፀ. 28:36-38) በወርቁ ላይ የተቀረጸውን ጽሑፍ የሚያይ ማንኛውም ሰው፣ ይሖዋ ሙሉ በሙሉ ቅዱስ እንደሆነ መረዳት ይችላል። ሆኖም ወደ ሊቀ ካህናቱ መቅረብ ባለመቻሉ የተነሳ በወርቁ ላይ የተቀረጸውን ጽሑፍ ማየት የማይችል እስራኤላዊስ? ይህን ወሳኝ መረጃ ማግኘት አይችልም ማለት ነው? አይደለም! ሕጉ በወንዶች፣ በሴቶችና በልጆች ፊት ስለሚነበብ ሁሉም እስራኤላውያን ይህን መልእክት መስማት ይችሉ ነበር። (ዘዳ. 31:9-12) እናንተም እዚያ ብትሆኑ ኖሮ የሚከተለው ሐሳብ ሲነበብ ትሰሙ ነበር፦ “እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝና፤ እኔ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም . . . ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል።” “እኔ ይሖዋ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ለእኔ ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል።”—ዘሌ. 11:44, 45፤ 20:7, 26፤ w21.12 3 አን. 6-7

ማክሰኞ፣ መስከረም 19

አትጨነቁ።—ሉቃስ 12:29

አንዳንዶች ስለሚያስፈልጓቸው ነገሮች ይጨነቁ ይሆናል። የሚኖሩት ድሃ አገር ውስጥ ሊሆን ይችላል። ለቤተሰባቸው የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት የሚያስችል ገቢ ማግኘት ከባድ ሊሆንባቸው ይችላል። ወይም ደግሞ ቤተሰቡን የሚያስተዳድረው ሰው ስለሞተ የቤተሰቡ አባላት የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገር ለማግኘት ተቸግረው ይሆናል። ስላሉብን ችግሮች በማሰብ ከመጨነቅ ይልቅ በይሖዋ መተማመን ይኖርብናል። አፍቃሪ የሆነው አባታችን ይሖዋ መንፈሳዊ ነገሮችን ካስቀደምን የሚያስፈልጉንን ቁሳዊ ነገሮች እንደሚያሟላልን ቃል መግባቱን ልናስታውስ ይገባል። (ማቴ. 6:32, 33) ይሖዋ ይህን ቃሉን ሳይጠብቅ የቀረበት ጊዜ የለም። (ዘዳ. 8:4, 15, 16፤ መዝ. 37:25) ይሖዋ ለወፎችና ለአበቦች የሚያስፈልጋቸውን ያሟላላቸዋል፤ ታዲያ እኛስ የምንበላው ወይም የምንለብሰው እናጣለን ብለን መጨነቅ ይኖርብናል? (ማቴ. 6:26-30፤ ፊልጵ. 4:6, 7) ወላጆች ልጆቻቸውን ስለሚወዷቸው የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገር እንደሚያሟሉላቸው የታወቀ ነው፤ በተመሳሳይም የሰማዩ አባታችን ሕዝቦቹን ስለሚወዳቸው የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገር ያሟላላቸዋል። w21.12 17 አን. 4-5፤ 18 አን. 8

ረቡዕ፣ መስከረም 20

ይሖዋ ከዮሴፍ አልተለየም፤ እንደወትሮው ሁሉ ለእሱ ታማኝ ፍቅር ከማሳየት ወደኋላ አላለም።—ዘፍ. 39:21

አንድ ሰው ምናልባትም የእምነት ባልንጀራህ ከባድ በደል ፈጽሞብህ ያውቃል? የገዛ ወንድሞቹ ግፍ የፈጸሙበትን የዮሴፍን ምሳሌ ልብ በል። ዮሴፍ ትኩረት ያደረገው ለይሖዋ በሚያቀርበው አገልግሎት ላይ ነበር፤ በትዕግሥት በመጽናቱ ይሖዋ አትረፍርፎ ባርኮታል። ከጊዜ በኋላ ዮሴፍ ግፍ የፈጸሙበትን ሰዎች ይቅር ማለት እንዲሁም የይሖዋ በረከት እንዳልተለየው ማየት ችሏል። (ዘፍ. 45:5) እንደ ዮሴፍ ሁሉ እኛም ወደ ይሖዋ ስንቀርብና ነገሮችን ለእሱ ስንተው እንጽናናለን። (መዝ. 7:17፤ 73:28) በደረሰብህ ግፍ ወይም በሌላ ምክንያት ተጎድተህ ከሆነ “ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ” እንደሆነ አስታውስ። (መዝ. 34:18) ትዕግሥት በማሳየትህ እንዲሁም ሸክምህን በእሱ ላይ በመጣልህ ይወድሃል። (መዝ. 55:22) ይሖዋ የምድር ሁሉ ዳኛ ነው። ከእሱ እይታ የሚያመልጥ አንድም ነገር የለም። (1 ጴጥ. 3:12) አንተስ መፍታት የማትችለው ችግር ካጋጠመህ እሱን በትዕግሥት ለመጠበቅ ፈቃደኛ ነህ? w21.08 11 አን. 14፤ 12 አን. 16

ሐሙስ፣ መስከረም 21

የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ።—ኤፌ. 5:17

ሕይወታችንን የይሖዋን ሞገስ በሚያስገኝልን መንገድ መጠቀማችን የጥበብ አካሄድ ነው። ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ ነገሮችን መወሰን አለብን። አንዳንዴ ጊዜያችንን በተሻለ መንገድ መጠቀም፣ በራሳቸው ምንም ስህተት ከሌለባቸው ሁለት እንቅስቃሴዎች አንዱን መምረጥ ይጠይቃል። ኢየሱስ ወደ ማርያም እና ወደ ማርታ ቤት እንደሄደ የሚገልጸው በብዙዎች ዘንድ የሚታወቅ ታሪክ ነጥቡን ያጎላልናል። እንግዳ ተቀባይ የሆነችው ማርታ ኢየሱስን የማስተናገድ መብት በማግኘቷ በጣም ተደስታ ትልቅ ድግስ ለማዘጋጀት ጉድ ጉድ ማለት ጀመረች። እህቷ ማርያም ግን ይህን አጋጣሚ ልትጠቀምበት ስለፈለገች ከጌታዋ ጎን ቁጭ ብላ ትምህርቱን ማዳመጥ ጀመረች። ማርታ ኢየሱስን ለማስተናገድ የተነሳችው መልካም አስባ እንደሆነ የታወቀ ነው፤ ኢየሱስ ግን “ማርያም . . . የተሻለውን ድርሻ መርጣለች” ብሏል። (ሉቃስ 10:38-42 ግርጌ) ከጊዜ በኋላ ማርያም በዚያን ዕለት ምን ምግብ እንደቀረበ እንኳ ትዝ አይላት ይሆናል። ከኢየሱስ የተማረችውን ነገር ግን ፈጽሞ እንደማትረሳው የታወቀ ነው። ማርያም ከኢየሱስ ጋር ለምታሳልፈው ጊዜ ትልቅ ቦታ እንደሰጠች ሁሉ እኛም ከይሖዋ ጋር የምናሳልፈውን ጊዜ ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን። w22.01 27 አን. 5-6

ዓርብ፣ መስከረም 22

አክዓብ ስለ እሱ በተናገርኩት ነገር የተነሳ ራሱን እንዴት እንዳዋረደ ተመለከትክ?—1 ነገ. 21:29

አክዓብ ራሱን በይሖዋ ፊት ያዋረደ ቢሆንም በኋላ ያደረገው ነገር ንስሐው እውነተኛ እንዳልነበር ያሳያል። የበዓል አምልኮን ከግዛቱ ለማስወገድ ጥረት አላደረገም። የይሖዋን አምልኮ ለማስፋፋትም አልሞከረም። አክዓብ ከሞተ በኋላ ይሖዋ ስለዚህ ሰው ያለውን አመለካከት ገልጿል። የአምላክ ነቢይ የሆነው ኢዩ፣ አክዓብ “ክፉ ሰው” እንደሆነ ተናግሯል። (2 ዜና 19:1, 2) እስቲ አስበው፦ አክዓብ ከልቡ ንስሐ የገባ ቢሆን ኖሮ ነቢዩ፣ አክዓብ ይሖዋን የሚጠላ ክፉ ሰው እንደሆነ አይገልጽም ነበር። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው አክዓብ በመጠኑ ተጸጽቶ የነበረ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ ንስሐ አልገባም። ከአክዓብ ታሪክ ምን እንማራለን? አክዓብ በቤተሰቡ ላይ ስለሚመጣው ጥፋት ኤልያስ ሲነግረው መጀመሪያ ላይ ራሱን አዋርዶ ነበር። ይህ ጥሩ እርምጃ ነው። ሆኖም ከዚያ በኋላ ያደረጋቸው ነገሮች ከልቡ ንስሐ እንዳልገባ ያሳያሉ። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ንስሐ መግባት ጊዜያዊ የሆነ የጸጸት ስሜት ከማሳየት ያለፈ ነገርን ሊያካትት ይገባል። w21.10 3 አን. 4-5, 7-8

ቅዳሜ፣ መስከረም 23

ይህ የመንግሥቱ ምሥራች . . . ይሰበካል።—ማቴ. 24:14

ኢሳይያስ ነቢይ ነበር። ሚስቱም ‘ነቢዪት’ ተብላለች፤ ስለዚህ እሷም የነቢይነት ሥራ ታከናውን የነበረ ይመስላል። (ኢሳ. 8:1-4) ኢሳይያስ እና ሚስቱ ሕይወታቸው ለይሖዋ በሚያቀርቡት አምልኮ ላይ ያተኮረ ነበር። በዛሬው ጊዜ ያሉ ባለትዳሮችም በይሖዋ አገልግሎት አቅማቸው በፈቀደ መጠን በመካፈል ሕይወታቸው ይሖዋን በማገልገል ላይ ያተኮረ እንዲሆን ማድረግ ይችላሉ። የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች አብረው በማጥናት እንዲሁም ትንቢቶቹ ምንጊዜም ፍጻሜያቸውን እንደሚያገኙ በማስተዋል በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት ማጠናከር ይችላሉ። (ቲቶ 1:2) ከአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ጋር በተያያዘ እነሱም የበኩላቸውን ድርሻ ማበርከት የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ማሰላሰል ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት ምሥራቹ በመላው ምድር እንደሚሰበክ የተናገረው ትንቢት እንዲፈጸም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይችላሉ። ባልና ሚስቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን እያገኙ እንዳለ እርግጠኛ መሆናቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን በይሖዋ አገልግሎት እንዲካፈሉ ይበልጥ ያነሳሳቸዋል። w21.11 16 አን. 9-10

እሁድ፣ መስከረም 24

ደቀ መዝሙሩን “እናትህ ይህችውልህ!” አለው።—ዮሐ. 19:27

ኢየሱስ የእናቱ ጉዳይ በጣም አሳስቦት ነበር፤ በወቅቱ ማርያም መበለት ሳትሆን አትቀርም። ኢየሱስ ለማርያም ባለው ፍቅርና አሳቢነት ተነሳስቶ ለዮሐንስ በአደራ ሰጣት፤ የሚያስፈልጋትን መንፈሳዊ ነገር በሙሉ ዮሐንስ እንደሚያሟላላት ተማምኖ ነበር። ከዚያ ቀን ጀምሮ ዮሐንስ ማርያምን ወደ ቤቱ ወስዶ እንደ እናቱ አድርጎ ተንከባክቧታል። ኢየሱስ ከሕፃንነቱ ጀምሮ ለተንከባከበችውና ሲሞትም ከጎኑ ላልተለየችው ውድ እናቱ ጥልቅ ፍቅር አሳይቷል! ኢየሱስ ከተናገራቸው ቃላት ምን ትምህርት እናገኛለን? ከክርስቲያን ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር ያለን ዝምድና ከቅርብ ቤተሰባችን ጋር ካለን ዝምድና የጠነከረ እንዲሆን ማድረግ እንችላለን። ቤተሰቦቻችን ይቃወሙን ይባስ ብሎም ያገሉን ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ኢየሱስ ቃል በገባው መሠረት ይሖዋን እና ድርጅቱን የሙጥኝ እስካልን ድረስ ያጣነውን ነገር ሁሉ “100 እጥፍ” እናገኛለን። አፍቃሪ የሆኑ ብዙ ልጆች፣ እናቶች ወይም አባቶች እናገኛለን። (ማር. 10:29, 30) ለይሖዋና እርስ በርስ ባላቸው ፍቅር እንዲሁም በእምነት የተሳሰሩ አባላት ያሉት መንፈሳዊ ቤተሰብ ክፍል በመሆንህ ምን ይሰማሃል?—ቆላ. 3:14፤ 1 ጴጥ. 2:17፤ w21.04 9-11 አን. 7-8

ሰኞ፣ መስከረም 25

መልካም ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ።—ዕብ. 13:16

ታማኝ ፍቅር ከሚጠበቅብን አልፈን እንድንሄድ ያነሳሳናል። እንደ ጥንት ጊዜው ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ ብዙ ወንድሞችና እህቶችም በግለሰብ ደረጃ የማያውቋቸውን ጨምሮ ለሁሉም የእምነት ባልንጀሮቻቸው ታማኝ ፍቅር ያሳያሉ። ለምሳሌ በአንድ አካባቢ የተፈጥሮ አደጋ እንደደረሰ ሲሰሙ እርዳታ ማበርከት የሚችሉበትን መንገድ ወዲያውኑ ማሰብ ይጀምራሉ። በጉባኤ ውስጥ ያለ አንድ ሰው የኢኮኖሚ ችግር ሲያጋጥመው ግለሰቡን ለመርዳት በፈቃደኝነት ራሳቸውን ያቀርባሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን እንደኖሩት የመቄዶንያ ክርስቲያኖች ሁሉ እነሱም ከሚጠበቅባቸው በላይ ያደርጋሉ። የተቸገሩ ወንድሞቻቸውን ለመርዳት ሲሉ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ያደርጋሉ፤ “እንዲያውም ከአቅማቸው በላይ” ይሰጣሉ። (2 ቆሮ. 8:3) በዛሬው ጊዜ ያሉ አስተዋይ ሽማግሌዎች፣ በጉባኤያቸው ውስጥ ያሉ ሌሎችን በደግነት የሚረዱ ወንድሞችንና እህቶችን ያመሰግኗቸዋል። እንዲህ ያለው በተገቢው ጊዜ የተሰጠ ልባዊ ምስጋና ወንድሞችና እህቶች መልካም ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ ያበረታታቸዋል።—ኢሳ. 32:1, 2፤ w21.11 11 አን. 14፤ 12 አን. 21

ማክሰኞ፣ መስከረም 26

ጆሮህን አዘንብል፤ የጥበበኞችንም ቃል አዳምጥ።—ምሳሌ 22:17

ሁላችንም ምክር የሚያስፈልገን ጊዜ አለ። አንዳንድ ጊዜ እኛ ራሳችን ቅድሚያውን ወስደን አንድ የምናከብረውን ሰው ምክር እንጠይቃለን። በሌሎች ጊዜያት ደግሞ ሁኔታችን ያሳሰበው አንድ ወንድም፣ በኋላ ላይ የምንጸጸትበትን “የተሳሳተ ጎዳና” ልንከተል እንደሆነ ይጠቁመን ይሆናል። (ገላ. 6:1) ወይም ደግሞ ከባድ ስህተት ሠርተን እርማት ይሰጠን ይሆናል፤ ይህም ምክር የምናገኝበት አንዱ መንገድ ነው። ምክሩ በምንም መልኩ ቢመጣ ልንሰማ ይገባል። ይህን ማድረጋችን የሚበጀን ከመሆኑም ሌላ ሕይወታችንን ሊታደግልን ይችላል! (ምሳሌ 6:23) የዛሬው የዕለት ጥቅሳችን ‘የጥበበኞችን ቃል እንድናዳምጥ’ ያበረታታናል። ሁሉንም ነገር የሚያውቅ ሰው የለም፤ ምንጊዜም ቢሆን ከእኛ የበለጠ እውቀት ወይም ተሞክሮ ያለው ሰው መኖሩ አይቀርም። (ምሳሌ 12:15) ስለዚህ ምክር መስማት የትሕትና አንዱ መገለጫ ነው። ያሉብንን ገደቦች እንደምንረዳና ግባችን ላይ ለመድረስ የሌሎች እርዳታ እንደሚያስፈልገን እንደምንገነዘብ ያሳያል። ጠቢቡ ንጉሥ ሰለሞን ‘የታቀደው ነገር በብዙ አማካሪዎች ይሳካል’ በማለት ጽፏል።—ምሳሌ 15:22፤ w22.02 8 አን. 1-2

ረቡዕ፣ መስከረም 27

የሠራውን በደል የሚሸፋፍን አይሳካለትም፤ የሚናዘዝና የሚተወው ሁሉ ግን ምሕረት ያገኛል።—ምሳሌ 28:13

እውነተኛ ንስሐ መግባት ለፈጸምነው ኃጢአት ይቅርታ ከመጠየቅ ያለፈ ነገርን ያካትታል። አስተሳሰባችንን እና ልባችንን ሙሉ በሙሉ መቀየር ይኖርብናል። ይህም መጥፎ አካሄዳችንን መተውንና ከኃጢአታችን ተመልሰን ይሖዋን የሚያስደስት አካሄድ መከተልን ይጨምራል። (ሕዝ. 33:14-16) አንድ ኃጢአተኛ ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ጉዳይ ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ማስተካከል ነው። አንድ የቅርብ ወዳጃችን ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ብናውቅ ምን ማድረግ ይኖርብናል? የጓደኛችንን ኃጢአት ለመሸፋፈን ብንሞክር እሱን እንጎዳዋለን እንጂ አንጠቅመውም። ደግሞም ይሖዋ ሁሉንም ነገር ስለሚመለከት ኃጢአቱን ለመሸፈን የምናደርገው ጥረት አይሳካም። (ምሳሌ 5:21, 22) ለጓደኛህ ሽማግሌዎች ሊረዱት እንደሚፈልጉ አስታውሰው። ጓደኛህ ኃጢአቱን ለሽማግሌዎች ለመናዘዝ ፈቃደኛ ካልሆነ አንተ ራስህ ጉዳዩን ለሽማግሌዎች መናገር ይኖርብሃል፤ ይህም ጓደኛህን ለመርዳት ከልብህ እንደምትፈልግ ያሳያል። w21.10 7 አን. 19-21

ሐሙስ፣ መስከረም 28

ስለ ራሳችሁ ፍላጎት ብቻ ከማሰብ ይልቅ እያንዳንዳችሁ ለሌሎች ሰዎች ፍላጎትም ትኩረት ስጡ።—ፊልጵ. 2:4

ሁላችንም ኢየሱስ ካሳየው የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ የምንማረው ነገር አለ። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ኢየሱስ ሲናገር “የባሪያን መልክ ያዘ” ይላል። (ፊልጵ. 2:7) የሚወደድ ባሪያ ወይም አገልጋይ ጌታውን ማስደሰት የሚችልበትን አጋጣሚ ይፈልጋል። እኛም የይሖዋ ባሪያና የወንድሞቻችን አገልጋይ እንደመሆናችን መጠን ምኞታችን ለይሖዋም ሆነ ለእምነት ባልንጀሮቻችን ጠቃሚ የሆነ አገልግሎት ማከናወን ነው። ራስህን እንዲህ እያልክ መጠየቅ ትችላለህ፦ ‘ሌሎችን ለመርዳት ስል የራሴን ጥቅም መሥዋዕት ለማድረግ ፈቃደኛ ነኝ? የትላልቅ ስብሰባ አዳራሽ የሚያጸዱ ወይም የስብሰባ አዳራሽ የሚጠግኑ ፈቃደኛ ሠራተኞች ሲያስፈልጉ ወዲያውኑ ራሴን አቀርባለሁ?’ ይሁንና ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ብትገነዘብም አስፈላጊውን ማስተካከያ ለማድረግ ተነሳሽነት ባይኖርህስ? ሁኔታህ እንዲህ ከሆነ ወደ ይሖዋ ከልብህ ጸልይ። ስሜትህን ለይሖዋ ንገረው። ‘ለተግባር የሚያነሳሳ ፍላጎት እንዲያድርብህና ኃይል እንድታገኝ’ ጠይቀው።—ፊልጵ. 2:13፤ w22.02 23 አን. 9-11

ዓርብ፣ መስከረም 29

እኔም እረፍት እሰጣችኋለሁ።—ማቴ. 11:28

ኢየሱስ ሁኔታዎች አስቸጋሪ በሚሆኑበት ጊዜም እንኳ ገርና ምክንያታዊ በመሆን ደግነት አሳይቷል። (ማቴ. 11:29, 30) ለምሳሌ ያህል፣ አንዲት ፊንቄያዊት ሴት ልጇን እንዲፈውስላት ስትለምነው መጀመሪያ ላይ ጥያቄዋን አልተቀበለም ነበር፤ ያላትን ታላቅ እምነት ሲመለከት ግን ልጇን በመፈወስ ደግነት አሳይቷታል። (ማቴ. 15:22-28) ኢየሱስ ደግ ቢሆንም በስሜት የሚመራ ሰው አልነበረም። አንዳንድ ጊዜ፣ ለሚወዳቸው ሰዎች ደግነት ያሳየው ጠንከር በማለት ነው። ለምሳሌ ያህል ጴጥሮስ የይሖዋን ፈቃድ እንዳያደርግ እንቅፋት በሆነበት ወቅት በሌሎቹ ደቀ መዛሙርት ፊት ገሥጾታል። (ማር. 8:32, 33) ኢየሱስ ይህን ያደረገው ጴጥሮስን ለማሸማቀቅ አልነበረም። ከዚህ ይልቅ ጴጥሮስ ከጥፋቱ እንዲማር፣ ሌሎቹ ደቀ መዛሙርትም ቦታቸውን አልፈው በመሄድ ተመሳሳይ ስህተት እንዳይሠሩ ለማስጠንቀቅ ነበር። እርግጥ ነው፣ ጴጥሮስ በተወሰነ መጠንም ቢሆን ተሸማቅቆ ሊሆን ይችላል፤ ያም ቢሆን የተሰጠው ተግሣጽ ጠቅሞታል። እውነተኛ ደግነት ለማሳየት ስንል የምንወዳቸውን ሰዎች በግልጽ ማነጋገር የሚያስፈልገን ጊዜ አለ። እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥምህ ምክርህ በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ እንዲሆን በማድረግ ኢየሱስን ምሰለው። w22.03 11 አን. 12-13

ቅዳሜ፣ መስከረም 30

የውዳሴ መሥዋዕት ዘወትር ለአምላክ እናቅርብ፤ ይህም ስሙን በይፋ የምናውጅበት የከንፈራችን ፍሬ ነው።—ዕብ. 13:15

ይሖዋን ስናወድስ ለእሱ አምልኮ እያቀረብን ነው። (መዝ. 34:1) ለይሖዋ ውዳሴ የምናቀርበው እሱ ስላሉት ግሩም ባሕርያትና ስላከናወናቸው ሥራዎች በአድናቆት በመናገር ነው። ውዳሴ የሚመነጨው ከአመስጋኝ ልብ ነው። ጊዜ ወስደን በይሖዋ ጥሩነት ላይ ማለትም እሱ ባደረገልን ነገሮች ላይ የምናሰላስል ከሆነ እሱን የምናወድስበት ምክንያት አናጣም። የስብከቱ ሥራ “የከንፈራችን ፍሬ” የሆነውን ‘የውዳሴ መሥዋዕት ለአምላክ የምናቀርብበት’ ጥሩ አጋጣሚ ይሰጠናል። ወደ ይሖዋ በጸሎት ከመቅረባችን በፊት ምን እንደምንል ቆም ብለን ማሰብ እንዳለብን ሁሉ በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎችም ምን እንደምንል ቆም ብለን ማሰባችን አስፈላጊ ነው። የምናቀርበው “የውዳሴ መሥዋዕት” ምርጣችን እንዲሆን እንፈልጋለን። ለሌሎች እውነትን በልበ ሙሉነት የምንናገረው ለዚህ ነው። w22.03 21 አን. 8

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ