ጥቅምት
እሁድ፣ ጥቅምት 1
በእኔ ምክንያት የማይሰናከል ደስተኛ ነው።—ማቴ. 11:6
ትምህርታችንና እምነታችን የተመሠረተው በአምላክ ቃል ላይ ነው። ያም ቢሆን ብዙዎች አምልኳችን የሚያስደምም ሃይማኖታዊ ሥርዓት የሌለው መሆኑ ያሰናክላቸዋል፤ በዚያ ላይ ደግሞ ትምህርታችን እነሱ መስማት ከሚፈልጉት ነገር ጋር አይስማማም። እንዳንሰናከል ምን ይረዳናል? ሐዋርያው ጳውሎስ በሮም የሚገኙትን ክርስቲያኖች “እምነት የሚገኘው ቃሉን ከመስማት ነው። ቃሉን መስማት የሚቻለው ደግሞ ስለ ክርስቶስ የሚናገር ሰው ሲኖር ነው” ብሏቸው ነበር። (ሮም 10:17) ስለሆነም እምነታችንን የምንገነባው ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጥናት እንጂ ለዓይን በሚስቡ ሆኖም ቅዱስ ጽሑፋዊ ባልሆኑ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች በመካፈል አይደለም። በትክክለኛ እውቀት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ እምነት ማዳበር ይኖርብናል፤ ምክንያቱም “ያለእምነት አምላክን በሚገባ ደስ ማሰኘት አይቻልም።” (ዕብ. 11:1, 6) እንግዲያው እውነትን ማግኘታችንን ለማረጋገጥ ከሰማይ አስደናቂ ምልክት ማየት አያስፈልገንም። እውነትን እንዳገኘን እርግጠኞች ለመሆን እንዲሁም ማንኛውንም ጥርጣሬ ለማስወገድ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን እምነት የሚያጠናክር ትምህርት በጥንቃቄ መመርመራችን ብቻ በቂ ነው። w21.05 4-5 አን. 11-12
ሰኞ፣ ጥቅምት 2
እኔ ያጋጠመኝ ሁኔታ ምሥራቹ ይበልጥ እንዲስፋፋ አስተዋጽኦ [አድርጓል]።—ፊልጵ. 1:12
ሐዋርያው ጳውሎስ ብዙ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አጋጥመውታል። በተለይ ደግሞ በተደበደበበት፣ በድንጋይ በተወገረበት እንዲሁም በታሰረበት ጊዜ ብርታት አስፈልጎታል። (2 ቆሮ. 11:23-25) ጳውሎስ አንዳንድ ጊዜ ከአሉታዊ ስሜቶች ጋር መታገል እንዳስፈለገውም ሳይሸሽግ ተናግሯል። (ሮም 7:18, 19, 24) በተጨማሪም “ሥጋዬን የሚወጋ እሾህ” በማለት የጠራው የጤና እክል ነበረበት፤ አምላክ ይህን ችግር እንዲያስወግድለት በተደጋጋሚ ለምኖ ነበር። (2 ቆሮ. 12:7, 8) ጳውሎስ ብዙ ችግሮች ቢያጋጥሙትም አገልግሎቱን እንዲፈጽም ይሖዋ ብርታት ሰጥቶታል። ጳውሎስ ምን እንዳከናወነ ለማሰብ ሞክሩ። ለምሳሌ ሮም ውስጥ የቁም እስረኛ በነበረበት ጊዜ በአይሁድ መሪዎችና በመንግሥት ባለሥልጣናት ፊት ለምሥራቹ በቅንዓት ተሟግቷል። (ሥራ 28:17፤ ፊልጵ. 4:21, 22) ከዚህም በተጨማሪ በንጉሠ ነገሥቱ የክብር ዘብ ውስጥ ለነበሩ ብዙ ሰዎች እንዲሁም ሊጠይቁት ለመጡ ሰዎች ሁሉ መሥክሯል። (ሥራ 28:30, 31፤ ፊልጵ. 1:13) በዚያው ወቅት ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ደብዳቤዎችን ጽፏል፤ እነዚህ ደብዳቤዎች በዘመናችን ላሉ እውነተኛ ክርስቲያኖችም ጠቃሚ ናቸው። w21.05 21 አን. 4-5
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 3
እንዳትታበዩ . . . “ከተጻፈው አትለፍ” የሚለውን ደንብ [ተማሩ]።—1 ቆሮ. 4:6
የይሁዳ ንጉሥ የሆነው ዖዝያ ኩራተኛ መሆኑ የተሰጠውን ምክር እንዳይቀበልና የማይገባውን ድርጊት እንዲፈጽም አድርጎታል። ዖዝያ ጥሩ ችሎታ ያለው ሰው ነበር። በወታደራዊ ዘመቻዎች፣ በግንባታ ፕሮጀክቶችና በግብርና ረገድ ብዙ ስኬት ያስመዘገበ ሰው ነው። መጽሐፍ ቅዱስም “እውነተኛው አምላክ አበለጸገው” ይላል። (2 ዜና 26:3-7, 10) “ይሁን እንጂ ዖዝያ በበረታ ጊዜ ለጥፋት እስኪዳረግ ድረስ ልቡ ታበየ።” ይሖዋ በቤተ መቅደሱ ውስጥ ዕጣን ማጠን የሚፈቀድላቸው ካህናቱ ብቻ እንደሆኑ ተናግሮ ነበር። ንጉሥ ዖዝያ ግን በእብሪት ስለተሞላ ዕጣን ለማጠን ወደ ቤተ መቅደሱ ገባ። ይሖዋ በዚህ በጣም ስላዘነ ይህን ኩራተኛ ሰው በሥጋ ደዌ መታው። (2 ዜና 26:16-21) እኛስ እንደ ዖዝያ በኩራት ወጥመድ እንያዝ ይሆን? ራሳችንን ከፍ አድርገን የምንመለከት ከሆነ በዚህ ወጥመድ ልንያዝ እንችላለን። ያሉን ተሰጥኦዎችና በጉባኤ ውስጥ የምንቀበላቸው መብቶች በሙሉ ከይሖዋ የተገኙ መሆናቸውን መዘንጋት አይኖርብንም። (1 ቆሮ. 4:7) ኩራተኛ ከሆንን ይሖዋ አይጠቀምብንም። w21.06 16 አን. 7-8
ረቡዕ፣ ጥቅምት 4
መናፍስት ስለተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ፤ ከዚህ ይልቅ ስማችሁ በሰማያት ስለተጻፈ ደስ ይበላችሁ።—ሉቃስ 10:20
ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ በአገልግሎታቸው አስደሳች ተሞክሮዎችን የሚያገኙት ሁልጊዜ እንዳልሆነ ያውቃል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ መጀመሪያ ላይ የደቀ መዛሙርቱን መልእክት ከሰሙት ሰዎች መካከል ምን ያህሎቹ አማኞች እንደሆኑ አናውቅም። ደቀ መዛሙርቱ መደሰት ያለባቸው ባገኙት ውጤት ብቻ እንዳልሆነ መገንዘብ ነበረባቸው፤ ከሁሉ በላይ ሊያስደስታቸው የሚገባው ይሖዋ ባደረጉት ትጋት የተሞላበት ጥረት እንደተደሰተ ማወቃቸው ነው። በአገልግሎታችን የምንጸና ከሆነ የዘላለም ሕይወት እናገኛለን። የመንግሥቱን እውነት በሙሉ ልብ ስንዘራና ለማሳደግ ጥረት ስናደርግ የአምላክ መንፈስ በሕይወታችን ውስጥ በነፃነት እንዲሠራ በመፍቀድ ‘ለመንፈስ ብለን እንዘራለን።’ ‘ተስፋ ካልቆረጥን’ ወይም “ካልታከትን” ይሖዋ የዘላለም ሕይወት እንደምናጭድ አረጋግጦልናል፤ አንድ አዲስ ደቀ መዝሙር ራሱን ለይሖዋ እንዲወስን መርዳት አለመርዳታችን በዚህ ላይ የሚያመጣው ለውጥ አይኖርም።—ገላ. 6:7-9፤ w21.10 26 አን. 8-9
ሐሙስ፣ ጥቅምት 5
በጣም አዘነላቸው። ብዙ ነገርም ያስተምራቸው ጀመር።—ማር. 6:34
በአንድ ወቅት ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ለረጅም ሰዓት ሲሰብኩ ከቆዩ በኋላ በጣም ደክሟቸው ነበር። ስለዚህ ለማረፍ ወደ ሌላ ቦታ ሄዱ፤ ሆኖም እጅግ ብዙ ሕዝብ ተከተላቸው። ኢየሱስ ለሰዎቹ በጣም ስላዘነላቸው “ብዙ ነገር” ያስተምራቸው ጀመር። ኢየሱስ ራሱን በሰዎቹ ቦታ አስቀምጦ ነበር። እነዚህ ሰዎች ብዙ መከራ እንደደረሰባቸውና ተስፋ በጣም እንደሚያስፈልጋቸው ተመልክቶ ነበር፤ ስለዚህ ሊረዳቸው ፈልጓል። በዛሬው ጊዜ ያሉ ሰዎች የሚገኙበት ሁኔታም በኢየሱስ ዘመን ከነበሩት ሰዎች ጋር ተመሳሳይ ነው። ከውጭ ሲታዩ ደስተኛ ቢመስሉም ብዙ ችግሮች አሉባቸው፤ እንዲሁም ተስፋ ያስፈልጋቸዋል። የሚመራቸው እረኛ እንደሌላቸው በጎች እየተቅበዘበዙ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ያሉት ሰዎች “ያለተስፋና ያለአምላክ” እንደሆኑ ገልጿል። (ኤፌ. 2:12) በክልላችን ውስጥ ያሉ ሰዎች ስለሚገኙበት መንፈሳዊ ሁኔታ ማሰባችን እንድንወዳቸውና እንድናዝንላቸው ያደርገናል፤ ይህም እነሱን ለመርዳት ያነሳሳናል። እነሱን መርዳት የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው መንገድ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱስን እንዲያጠኑ መጋበዝ ነው። w21.07 5 አን. 8
ዓርብ፣ ጥቅምት 6
አንዳችን ሌላውን በመመቅኘት በከንቱ አንመካ።—ገላ. 5:26
ትምክህተኛ የሆነ ሰው ኩሩና ራስ ወዳድ ነው። ምቀኛ የሆነ ሰው ሌሎች ያሏቸውን ነገሮች ከመመኘት ባለፈ ሰዎቹ እነዚያን ነገሮች እንዲያጡ ይፈልጋል። እንደ እውነቱ ከሆነ ምቀኝነት የጥላቻ መገለጫ ነው። ትምክህተኝነትና ምቀኝነት የአውሮፕላንን ነዳጅ ከሚበክሉ ባዕድ ነገሮች ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። አውሮፕላኑ ከመሬት መነሳትና መብረር ይችል ይሆናል፤ ሆኖም እነዚህ ባዕድ ነገሮች የነዳጅ ማስተላለፊያ መስመሮቹን ስለሚዘጓቸው አውሮፕላኑ ሊከሰከስ ይችላል። በተመሳሳይም ትምክህተኛና ምቀኛ የሆነ ሰው ለተወሰነ ጊዜ ይሖዋን ማገልገል ይችል ይሆናል። ሆኖም ውሎ አድሮ ለጥፋት መዳረጉ አይቀርም። (ምሳሌ 16:18) ይሖዋን ማገልገሉን ያቆማል፤ እንዲሁም በራሱም ሆነ በሌሎች ላይ ጉዳት ያስከትላል። ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጠውን የሚከተለውን ምክር በተግባር ማዋላችን ትምክህተኝነትን ለማሸነፍ ይረዳናል፦ “ሌሎች ከእናንተ እንደሚበልጡ በትሕትና አስቡ እንጂ በጠበኝነት መንፈስ ወይም በትምክህተኝነት ምንም ነገር አታድርጉ።”—ፊልጵ. 2:3፤ w21.07 15-16 አን. 6-8
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 7
የሰበክንላችሁ ምሥራች ወደ እናንተ የመጣው በቃል ብቻ ሳይሆን በኃይልና በመንፈስ ቅዱስ እንዲሁም በጠንካራ እምነት ነው።—1 ተሰ. 1:5
አንዳንዶች እውነተኛው ሃይማኖት መጽሐፍ ቅዱስ በቀጥታ የማይመልሳቸውን ጨምሮ ሁሉንም ጥያቄዎቻቸውን ሊመልስላቸው እንደሚገባ ይሰማቸዋል። ሆኖም እንዲህ ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ ነው? እስቲ የሐዋርያው ጳውሎስን ምሳሌ እንመልከት። ጳውሎስ የእምነት ባልንጀሮቹን “ሁሉንም ነገር [እንዲመረምሩ]” አበረታቷቸዋል፤ ሆኖም እሱ ራሱ ያልተረዳቸው ብዙ ነገሮች እንዳሉ አምኖ ተቀብሏል። (1 ተሰ. 5:21) “እውቀታችን ከፊል ነው” እንዲሁም “በብረት መስተዋት ብዥ ያለ ምስል ይታየናል” በማለት ጽፏል። (1 ቆሮ. 13:9, 12) ጳውሎስ ያልተረዳቸው ነገሮች እንደነበሩ ሁሉ እኛም የማንረዳቸው ነገሮች ይኖራሉ። ይሁንና ጳውሎስ የይሖዋን ዓላማ በተመለከተ መሠረታዊ የሆኑትን እውነቶች ተረድቶ ነበር። እውነትን እንዳገኘ እርግጠኛ ለመሆን የሚያስችል በቂ እውቀት ነበረው! እውነትን እንዳገኘን እርግጠኛ እንድንሆን የሚረዳን አንዱ ነገር በዛሬው ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች የሚያደርጉትን ነገር ኢየሱስ ከተወው የአምልኮ ሥርዓት ጋር ማነጻጸር ነው። w21.10 18-19 አን. 2-4
እሁድ፣ ጥቅምት 8
ዕድሜው 50 ዓመት ከሞላ . . . ጡረታ ይወጣል።—ዘኁ. 8:25
እናንት ውድ አረጋውያን፣ በሙሉ ጊዜ አገልግሎት ውስጥ ሆናችሁም አልሆናችሁ ሌሎችን መርዳት የምትችሉባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። ይህን ማድረግ የምትችሉት እንዴት ነው? ከአዲሱ ሁኔታችሁ ጋር ተላመዱ፤ አዳዲስ ግቦችን አውጡ፤ እንዲሁም ማድረግ በማትችሉት ነገር ላይ ሳይሆን ማድረግ በምትችሉት ነገር ላይ አተኩሩ። ንጉሥ ዳዊት ለይሖዋ ቤተ መቅደስ ለመሥራት በጣም ጓጉቶ ነበር። ይሁንና ይሖዋ ቤተ መቅደሱን የመሥራት መብት የሰጠው ለወጣቱ ሰለሞን እንደሆነ ለዳዊት ሲነግረው ዳዊት የይሖዋን ውሳኔ በመቀበል ሥራውን በሙሉ ልቡ ደግፏል። (1 ዜና 17:4፤ 22:5) ዳዊት፣ ሰለሞን ‘ገና ወጣት እና ተሞክሮ የሌለው’ በመሆኑ ይህን ሥራ በተሻለ መንገድ ማከናወን የሚችለው እሱ ራሱ እንደሆነ አልተሰማውም። (1 ዜና 29:1) ዳዊት የግንባታው ሥራ ስኬታማ መሆኑ የተመካው በይሖዋ በረከት እንጂ ሥራውን በሚያከናውኑት ሰዎች ዕድሜ ወይም ተሞክሮ ላይ እንዳልሆነ ተገንዝቦ ነበር። እንደ ዳዊት ሁሉ በዛሬው ጊዜ ያሉ አረጋውያንም የነበራቸው ኃላፊነት ቢለወጥም በይሖዋ አገልግሎት በትጋት መካፈላቸውን ይቀጥላሉ። ደግሞም እነሱ በአንድ ወቅት ያከናውኑ የነበረውን ሥራ አሁን የሚሠሩትን ወጣቶች ይሖዋ እንደሚባርካቸው ያውቃሉ። w21.09 9 አን. 4፤ 10 አን. 5, 8
ሰኞ፣ ጥቅምት 9
የዋሆችን በትክክለኛ መንገድ ይመራቸዋል፤ እንዲሁም ለየዋሆች መንገዱን ያስተምራል።—መዝ. 25:9
መንፈሳዊ ግቦች ሕይወታችን አቅጣጫ እንዲይዝና ዓላማ እንዲኖረው ይረዱናል። ሆኖም ግብ ማውጣት ያለብን ሌሎችን በማየት ሳይሆን የራሳችንን ችሎታና ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ነው። እንዲህ ማድረጋችን ከሐዘንና ተስፋ ከመቁረጥ ይጠብቀናል። (ሉቃስ 14:28) የይሖዋ አገልጋይ በመሆንህ ልዩና ውድ የሆንክ የቤተሰቡ አባል ነህ። ይሖዋ ወደ ራሱ የሳበህ ከሌሎች ሰዎች የተሻልክ ስለሆንክ አይደለም። ወደ ራሱ የሳበህ ልብህን ስለመረመረና ትሑት እንዲሁም ለመማርና ለመቀረጽ ፈቃደኛ ሰው እንደሆንክ ስላየ ነው። እሱን ለማገልገል አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ ስታደርግ በጣም እንደሚደሰት እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። የምታሳየው ጽናትና ታማኝነት ‘መልካምና ጥሩ ልብ’ እንዳለህ ያሳያል። (ሉቃስ 8:15) እንግዲያው ለይሖዋ ምርጥህን መስጠትህን ቀጥል። እንዲህ ካደረግክ ‘ከራስህ ጋር ብቻ በተያያዘ’ የምትደሰትበት ነገር ታገኛለህ።—ገላ. 6:4፤ w21.07 24 አን. 15፤ 25 አን. 20
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 10
ኃጢአተኛን ከስህተት ጎዳናው የሚመልስ ማንኛውም ሰው ኃጢአተኛውን [ያድነዋል]።—ያዕ. 5:20
ፍትሕ የጎደለው ድርጊት ቢፈጸም አብዛኛውን ጊዜ ነገሩ እስኪስተካከል ድረስ በትዕግሥት መጠበቅ ይኖርብናል። ለምሳሌ ሽማግሌዎች በጉባኤው ውስጥ ከባድ ኃጢአት እንደተፈጸመ ሲያውቁ ‘ከሰማይ የሆነውን ጥበብ’ ለማግኘት ወደ ይሖዋ ይጸልያሉ፤ ይህም ጉዳዩን ከይሖዋ አመለካከት አንጻር ለማየት ይረዳቸዋል። (ያዕ. 3:17) ዓላማቸው፣ የሚቻል ከሆነ ኃጢአት የፈጸመው ግለሰብ ‘ከስህተት ጎዳናው እንዲመለስ’ መርዳት ነው። (ያዕ. 5:19, 20) በተጨማሪም ጉባኤውን ለመጠበቅና በተፈጸመው ድርጊት የተጎዱትን ወንድሞችና እህቶች ለማጽናናት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ይፈልጋሉ። (2 ቆሮ. 1:3, 4) ደግሞም ሽማግሌዎች አንድ ሰው ከባድ ኃጢአት እንደፈጸመ ሲሰሙ በመጀመሪያ ስለ ጉዳዩ የተሟላ መረጃ ለማግኘት ጥረት ያደርጋሉ፤ ይህ ደግሞ ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ከዚያም ኃጢአት ለፈጸመው ግለሰብ በቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ተመሥርተው ምክር ይሰጣሉ፤ እንዲሁም “በተገቢው መጠን” እርማት ይሰጡታል። (ኤር. 30:11) ሽማግሌዎች ፍርድ ለማሳለፍ አይቸኩሉም። ጉዳዩ በተገቢው መንገድ ሲያዝ መላው ጉባኤ ይጠቀማል። w21.08 11 አን. 12-13
ረቡዕ፣ ጥቅምት 11
ወደምትሄጂበት እሄዳለሁ፤ . . . ሕዝብሽ ሕዝቤ፣ አምላክሽም አምላኬ ይሆናል።—ሩት 1:16
በእስራኤል ምድር ረሃብ በመከሰቱ ናኦሚ፣ ባሏና ሁለት ልጆቿ ወደ ሞዓብ ተሰደዱ። እዚያ እያሉ የናኦሚ ባል ሞተ። ሁለቱ ልጆቿ ትዳር መሥርተው ነበር፤ የሚያሳዝነው ግን እነሱም ሞቱ። (ሩት 1:3-5) እነዚህ አስከፊ መከራዎች ናኦሚ በተስፋ መቁረጥ ስሜት እንድትዋጥ አደረጓት። በሐዘን ከመዋጧ የተነሳ ይሖዋ እየተቃወማት እንዳለ ተሰምቷት ነበር። ስሜቷን እንዴት ብላ እንደገለጸች ልብ በሉ፦ “የይሖዋ እጅ በእኔ ላይ [ተነስቷል]።” “ሁሉን ቻይ የሆነው አምላክ ሕይወቴን መራራ አድርጎታል።” በተጨማሪም እንዲህ ብላለች፦ ‘ይሖዋ ተቃውሞኛል፤ ሁሉን የሚችለው አምላክ መከራ አምጥቶብኛል።’ (ሩት 1:13, 20, 21) ይሖዋ “ግፍ ጥበበኛውን ሊያሳብደው [እንደሚችል]” ያውቃል። (መክ. 7:7) ለናኦሚ ታማኝ ፍቅር እንድታሳይ ሩትን አነሳስቷታል። ሩት፣ አማቷ ስሜታዊ እንዳትሆንና መንፈሳዊ ሚዛኗን እንድትጠብቅ በደግነትና በፈቃደኝነት ረድታታለች። w21.11 9 አን. 9፤ 10 አን. 10, 13
ሐሙስ፣ ጥቅምት 12
አምላክን ያለማሰለስ [ለምኑ]።—ያዕ. 1:5
አሁን ባሉን መብቶች ላይ ትኩረት እናደርጋለን ሲባል ለይሖዋ የምናቀርበውን አገልግሎት ለማስፋት የሚያስችሉንን አጋጣሚዎች መፈለግ እናቆማለን ማለት ነው? በፍጹም! በአገልግሎታችን ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን እንዲሁም ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ይበልጥ ለመርዳት የሚያስችሉንን መንፈሳዊ ግቦች ማውጣት እንችላለን፤ እንዲህ ማድረግም ይኖርብናል። ልካችንን በማወቅ በራሳችን ላይ ሳይሆን ሌሎችን በማገልገል ላይ ትኩረት ማድረጋችን የጥበብ እርምጃ ከመሆኑም ሌላ ግቦቻችን ላይ ለመድረስ ይረዳናል። (ምሳሌ 11:2፤ ሥራ 20:35) የትኞቹን ግቦች ማውጣት ትችላለህ? ልትደርስባቸው የምትችላቸውን ግቦች ለማስተዋል እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። (ምሳሌ 16:3) ረዳት ወይም የዘወትር አቅኚ ለመሆን፣ በቤቴል ለማገልገል ወይም በቲኦክራሲያዊ ሕንፃዎች ግንባታ ለመካፈል ግብ ማውጣት ትችል ይሆን? አሊያም ደግሞ ምሥራቹን ለማስፋፋት አልፎ ተርፎም በሌላ አገር ለማገልገል አዲስ ቋንቋ መማር ትችል ይሆናል። w21.08 23 አን. 14-15
ዓርብ፣ ጥቅምት 13
[የይሖዋ ታማኝ ፍቅር] ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።—መዝ. 136:1
ይሖዋ ታማኝ ፍቅር ያስደስተዋል። (ሆሴዕ 6:6) አምላካችን ‘ታማኝ ፍቅርን እንድንወድ’ በነቢዩ ሚክያስ አማካኝነት አበረታቶናል። (ሚክ. 6:8 ግርጌ) እንዲህ ማድረግ እንድንችል ግን ታማኝ ፍቅር ራሱ ምን እንደሆነ ማወቅ ይኖርብናል። ታማኝ ፍቅር ምንድን ነው? “ታማኝ ፍቅር” የሚለው አገላለጽ በአዲስ ዓለም ትርጉም መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ 230 ጊዜ ገደማ ይገኛል። ይሁንና ታማኝ ፍቅር ምንድን ነው? በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ውስጥ የሚገኘው “የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መፍቻ” እንደሚገልጸው ታማኝ ፍቅር “በከፍተኛ ቅንዓት፣ በጽኑ አቋም፣ በታማኝነትና ከልብ በመነጨ የመውደድ ስሜት ተነሳስቶ ፍቅር ማሳየትን ያመለክታል። ብዙውን ጊዜ አምላክ ለሰዎች ያለውን ፍቅር ለማመልከት የተሠራበት ቢሆንም በሰዎች መካከል ያለውንም ፍቅር ሊያመለክት ይችላል።” ይሖዋ ታማኝ ፍቅር በማሳየት ረገድ ወደር የሌለው ምሳሌ ነው። ከዚህ አንጻር ንጉሥ ዳዊት እንዲህ ብሎ መዘመሩ የሚያስገርም አይደለም፦ “ይሖዋ ሆይ፣ ታማኝ ፍቅርህ እስከ ሰማያት፣ . . . ይደርሳል። አምላክ ሆይ፣ ታማኝ ፍቅርህ ምንኛ ክቡር ነው!” (መዝ. 36:5, 7) እኛስ እንደ ዳዊት የይሖዋን ታማኝ ፍቅር ከፍ አድርገን እንመለከተዋለን? w21.11 2 አን. 1-2፤ 3 አን. 4
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 14
እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ።”—ማቴ. 6:9
የይሖዋን አምላኪዎች ያቀፈው ቤተሰብ “የፍጥረት ሁሉ በኩር” የሆነውን ኢየሱስን እና ስፍር ቁጥር የሌላቸውን መላእክት ያካትታል። (ቆላ. 1:15፤ መዝ. 103:20) ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት ታማኝ ሰዎች ይሖዋን እንደ አባታቸው አድርገው መመልከት እንደሚችሉ ጠቁሟል። ለደቀ መዛሙርቱ በላከው መልእክት ላይ ይሖዋን ‘አባቴና አባታችሁ’ በማለት ጠርቶታል። (ዮሐ. 20:17) በተጨማሪም ራሳችንን ለይሖዋ ወስነን ስንጠመቅ አፍቃሪ የሆኑ ወንድሞችንና እህቶችን ያቀፈ ቤተሰብ ክፍል እንሆናለን። (ማር. 10:29, 30) ይሖዋ አፍቃሪ አባት ነው። ኢየሱስ፣ እሱ ለይሖዋ ያለው ዓይነት አመለካከት እንዲኖረን ይፈልጋል፤ በሌላ አባባል ይሖዋን እንደ አስፈሪ ገዢ ሳይሆን በየትኛውም ጊዜ ልናነጋግረው እንደምንችል አፍቃሪ አባታችን አድርገን እንድንመለከተው ይፈልጋል። በጸሎቱ ናሙና ላይ ይሖዋን “አባታችን” ብለን እንድንጠራው ነግሮናል። ኢየሱስ ይሖዋን “ሁሉን ቻይ፣” “ፈጣሪ” ወይም ‘የዘላለም ንጉሥ’ ብለን እንድንጠራው ሊነግረን ይችል ነበር፤ ምክንያቱም ሁሉም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙ የይሖዋ የማዕረግ ስሞች ናቸው። (ዘፍ. 49:25፤ ኢሳ. 40:28፤ 1 ጢሞ. 1:17) ሆኖም ኢየሱስ “አባታችን” የሚለውን ፍቅር የሚንጸባረቅበት መጠሪያ እንድንጠቀም አስተምሮናል። w21.09 20 አን. 1, 3
እሁድ፣ ጥቅምት 15
ምናሴ፣ ይሖዋ እውነተኛ አምላክ እንደሆነ አወቀ።—2 ዜና 33:13
ንጉሥ ምናሴ ልቡን በማደንደን ይሖዋ በነቢያቱ አማካኝነት የሰጠውን ማስጠንቀቂያ ለመስማት ፈቃደኛ አልሆነም። በመጨረሻም “ይሖዋ [በይሁዳ ሕዝብ ላይ] የአሦርን ንጉሥ ሠራዊት አለቆች አመጣባቸው፤ እነሱም ምናሴን በመንጠቆ ያዙት፤ ከመዳብ በተሠሩ ሁለት የእግር ብረቶች አስረው ወደ ባቢሎን ወሰዱት።” ምናሴ በባዕድ አገር ታስሮ በነበረበት ወቅት፣ ስለፈጸማቸው ኃጢአቶች ቆም ብሎ ማሰብ ጀመረ። “በአባቶቹም አምላክ ፊት ራሱን እጅግ አዋረደ።” ግን በዚህ ብቻ አልተወሰነም። “ሞገስ እንዲያሳየው አምላኩን ይሖዋን ለመነ።” እንዲያውም “ወደ እሱ አጥብቆ ጸለየ።” (2 ዜና 33:10-12) ከጊዜ በኋላ ይሖዋ የምናሴን ጸሎት መለሰለት። ይሖዋ የምናሴ ልብ መለወጡን ካቀረባቸው ጸሎቶች ተመልክቷል። በመሆኑም ይሖዋ፣ ምናሴ ምሕረት ለማግኘት ያቀረበውን ጸሎት በመስማት ወደ ዙፋኑ መለሰው። ምናሴም እውነተኛ ንስሐ መግባቱን ለማሳየት አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ አደረገ። w21.10 4 አን. 10-11
ሰኞ፣ ጥቅምት 16
አንድ ከመሆን ሁለት መሆን ይሻላል፤ ምክንያቱም ሁለት ሆነው የሚያከናውኑት ሥራ ጥሩ ውጤት ያስገኝላቸዋል።—መክ. 4:9
አቂላ እና ጵርስቅላ የለመዱትን አካባቢ ለቀው መሄድ፣ ቤት ማግኘት እንዲሁም የድንኳን ሥራቸውን በአዲስ አካባቢ መጀመር ነበረባቸው። ሆኖም በአዲሱ መኖሪያቸው በቆሮንቶስ የሚገኘውን ጉባኤ መርዳት ጀመሩ፤ እንዲሁም ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር ሆነው በዚያ ያሉትን ወንድሞች ለማበረታታት ጥረት ያደርጉ ነበር። ከጊዜ በኋላም ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉባቸው ሌሎች ከተሞች ሄደው አገልግለዋል። (ሥራ 18:18-21፤ ሮም 16:3-5) በእርግጥም በትዳር አብረው ያሳለፉት ሕይወት ትርጉም ያለውና አስደሳች ነበር! በዛሬው ጊዜ ያሉ ባለትዳሮችም መንግሥቱን በማስቀደም የጵርስቅላን እና የአቂላን ምሳሌ መከተል ይችላሉ። ጥንዶቹ ስለ ግቦቻቸው መነጋገር የሚችሉበት ከሁሉ የተሻለው ጊዜ እየተጠናኑ ያሉበት ወቅት ነው። ባለትዳሮች አብረው መንፈሳዊ ግብ የሚያወጡና ግቦቻቸው ላይ ለመድረስ ጥረት የሚያደርጉ ከሆነ የይሖዋን መንፈስ በሕይወታቸው ውስጥ ማየት የሚችሉበት ተጨማሪ አጋጣሚ ይኖራቸዋል።—መክ. 4:12፤ w21.11 17 አን. 11-12
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 17
ከእናንተ እያንዳንዱ እናቱንና አባቱን ያክብር፤ . . . እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ነኝ።—ዘሌ. 19:3
አምላክ ወላጆቻችንን እንድናከብር የሰጠንን መመሪያ መታዘዝ እንዳለብን ግልጽ ነው። በዘሌዋውያን 19:3 ላይ የሚገኘው “ከእናንተ እያንዳንዱ እናቱንና አባቱን ያክብር” የሚለው መመሪያ “እኔ አምላካችሁ ይሖዋ ቅዱስ ስለሆንኩ እናንተም ቅዱስ ልትሆኑ ይገባል” የሚለውን ትእዛዝ ተከትሎ እንደሚመጣ ልብ እንበል። (ዘሌ. 19:2) ይሖዋ ወላጆቻችንን እንድናከብር የሰጠንን መመሪያ ስናስብ ‘እኔስ በዚህ ረገድ እንዴት ነኝ?’ ብለን ራሳችንን መጠየቃችን ተገቢ ነው። እስካሁን ድረስ ይህን መመሪያ በበቂ መጠን እንዳልታዘዛችሁ ከተሰማችሁ ከዚህ በኋላ ማስተካከያ ለማድረግ ልትወስኑ ትችላላችሁ። ያለፈውን መቀየር አትችሉም፤ ሆኖም ከዚህ በኋላ ወላጆቻችሁን ለማክበር አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ ማድረግ ትችላላችሁ። ምናልባት ከእነሱ ጋር ተጨማሪ ጊዜ ማሳለፍ ትችሉ ይሆናል። አሊያም ደግሞ ለእነሱ ቁሳዊ፣ መንፈሳዊ ወይም ስሜታዊ ድጋፍ በመስጠት ረገድ ተጨማሪ ነገር ማድረግ ትችላላችሁ። እንዲህ ካደረጋችሁ በዘሌዋውያን 19:3 ላይ ያለውን ትእዛዝ ታከብራላችሁ። w21.12 4-5 አን. 10-12
ረቡዕ፣ ጥቅምት 18
በሌሎች ላይ አትፍረዱ።—ማቴ. 7:1
ንጉሥ ዳዊት ከባድ ስህተቶችን ሠርቷል፤ ለምሳሌ ከቤርሳቤህ ጋር ምንዝር ፈጽሟል፤ ይባስ ብሎም ባሏን አስገድሎታል። (2 ሳሙ. 11:2-4, 14, 15, 24) ዳዊት እንዲህ ያለ ድርጊት በመፈጸሙ የጎዳው ራሱን ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሚስቶቹንና መላውን ቤተሰቡን ጭምር ነው። (2 ሳሙ. 12:10, 11) በሌላ ጊዜ ደግሞ ዳዊት ይሖዋ ሳያዘው የእስራኤልን ሠራዊት በማስቆጠር በአምላኩ ሳይታመን ቀርቷል። ታዲያ ይህን ማድረጉ ምን አስከተለ? ሰባ ሺህ የሚያህሉ እስራኤላውያን በመቅሰፍት ሞቱ! (2 ሳሙ. 24:1-4, 10-15) እናንተ ብትሆኑ ዳዊት የይሖዋን ምሕረት ማግኘት አይገባውም ብላችሁ ትፈርዱበታላችሁ? ይሖዋ እንዲህ አልተሰማውም። ይሖዋ ትኩረት ያደረገው ዳዊት በመላ ሕይወቱ ታማኝ በመሆኑና ከልቡ ንስሐ በመግባቱ ላይ ነው። በመሆኑም ዳዊት እነዚህን ከባድ ኃጢአቶች ቢፈጽምም ይሖዋ ይቅር ብሎታል። ይሖዋ ዳዊት ከልቡ እንደሚወደውና ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ እንደሚፈልግ ያውቅ ነበር። እኛም ይሖዋ በመልካም ጎናችን ላይ የሚያተኩር በመሆኑ አመስጋኞች ነን!—1 ነገ. 9:4፤ 1 ዜና 29:10, 17፤ w21.12 19 አን. 11-13
ሐሙስ፣ ጥቅምት 19
ወዲያውም የዓይኑ ብርሃን ተመለሰለት፤ አምላክን እያመሰገነም ይከተለው ጀመር።—ሉቃስ 18:43
ኢየሱስ ለአካል ጉዳተኞች ርኅራኄ አሳይቷል። ለመጥምቁ ዮሐንስ የላከውን መልእክት እናስታውስ፦ “ዓይነ ስውሮች እያዩ ነው፤ አንካሶች እየተራመዱ ነው፤ የሥጋ ደዌ የያዛቸው እየነጹ ነው፤ መስማት የተሳናቸው እየሰሙ ነው፤ [እንዲሁም] ሙታን እየተነሱ ነው” ብሎት ነበር። “ሕዝቡም ሁሉ” ኢየሱስ የፈጸማቸውን ተአምራት ሲያዩ “አምላክን አወደሱ።” (ሉቃስ 7:20-22) ክርስቲያኖች ለአካል ጉዳተኞች ርኅራኄ በማሳየት ኢየሱስን መምሰል ይፈልጋሉ። በመሆኑም እንዲህ ላሉ ሰዎች ደግነት፣ አሳቢነትና ትዕግሥት እናሳያለን። እርግጥ ነው፣ ይሖዋ ተአምራት የመፈጸም ኃይል አልሰጠንም። ያም ቢሆን ቃል በቃልም ሆነ በመንፈሳዊ ሁኔታ ለታወሩ ሰዎች ምሥራች የመናገር መብት ተሰጥቶናል፤ ይህ ምሥራች፣ ሁሉም ሰው የተሟላ አካላዊና መንፈሳዊ ጤንነት የሚያገኝበት ገነት እንደሚመጣ የሚገልጽ ነው። (ሉቃስ 4:18) ምሥራቹ በአሁኑ ጊዜም ብዙዎች አምላክን እንዲያወድሱ እያነሳሳቸው ነው። w21.12 9 አን. 5
ዓርብ፣ ጥቅምት 20
ስለ ኢዮብ ጽናት ሰምታችኋል፤ በውጤቱም ይሖዋ ያደረገለትን አይታችኋል።—ያዕ. 5:11
ያዕቆብ ለትምህርቱ ዋና መሠረት አድርጎ የተጠቀመው ቅዱሳን መጻሕፍትን ነው። የአምላክን ቃል ተጠቅሞ፣ ይሖዋ እንደ ኢዮብ ያሉ ለእሱ ታማኝ የሆኑ ሰዎችን ምንጊዜም እንደሚባርክ አንባቢዎቹን አስገንዝቧቸዋል። ያዕቆብ ቀላል ቃላትና ለመረዳት የማይከብድ ማብራሪያ በመጠቀም ነጥቡን አስተላልፏል። በመሆኑም የአንባቢዎቹ ትኩረት እንዲያርፍ ያደረገው በእሱ ላይ ሳይሆን በይሖዋ ላይ ነው። የምናገኘው ትምህርት፦ መልእክታችሁ ቀላል እንዲሆን አድርጉ፤ እንዲሁም ከአምላክ ቃል አስተምሩ። ግባችን በእውቀታችን ሌሎችን ማስደመም መሆን የለበትም፤ ከዚህ ይልቅ የምናስተምራቸው ሰዎች ይሖዋ ባለው ጥልቅ እውቀት እንዲሁም ለእነሱ ባለው አሳቢነት ልባቸው እንዲነካ እንፈልጋለን። (ሮም 11:33) ምንጊዜም ከቅዱሳን መጻሕፍት የምናስተምር ከሆነ ይህንን ግባችንን ማሳካት እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶቻችንን እኛ በእነሱ ቦታ ብንሆን ኖሮ ምን እንደምናደርግ ልንነግራቸው አይገባም። ከዚህ ይልቅ እነሱ ራሳቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሉ ምሳሌዎችን እንዲያስቡባቸው እንዲሁም የይሖዋ አስተሳሰብ እና ስሜት ምን እንደሆነ ለማስተዋል እንዲጥሩ ልንረዳቸው ይገባል። እንዲህ ካደረግን እርምጃ ለመውሰድ የሚያነሳሳቸው እኛን ሳይሆን ይሖዋን ለማስደሰት ያላቸው ፍላጎት ይሆናል። w22.01 10-11 አን. 9-10
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 21
ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።—ዘሌ. 19:18
አምላክ የሚጠብቅብን ሌሎችን ከመጉዳት እንድንቆጠብ ብቻ አይደለም። አንድ ክርስቲያን አምላክን ማስደሰት ከፈለገ ባልንጀራውን እንደ ራሱ መውደዱ የግድ አስፈላጊ ነው። ኢየሱስ በዘሌዋውያን 19:18 ላይ የሚገኘው ትእዛዝ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን የጠቆመው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። በአንድ ወቅት አንድ ፈሪሳዊ ኢየሱስን “ከሕጉ ውስጥ ከሁሉ የሚበልጠው ትእዛዝ የትኛው ነው?” በማለት ጠይቆት ነበር። ኢየሱስም “ከሁሉ የሚበልጠውና የመጀመሪያው ትእዛዝ” ይሖዋን በሙሉ ልባችን፣ በሙሉ ነፍሳችንና በሙሉ አእምሯችን መውደድ እንደሆነ ነገረው። ከዚያም ኢየሱስ ዘሌዋውያን 19:18ን በመጥቀስ “ሁለተኛውም ይህንኑ የሚመስል ሲሆን ‘ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ’ ይላል” አለው። (ማቴ. 22:35-40) ባልንጀራችንን እንደምንወድ ማሳየት የምንችልባቸው ብዙ መንገዶች አሉ። አንዱ መንገድ በዘሌዋውያን 19:18 ላይ የሚገኘውን ምክር ተግባራዊ ማድረግ ነው። ጥቅሱ “አትበቀል፤ . . . ቂም አትያዝ” ይላል። w21.12 10-11 አን. 11-13
እሁድ፣ ጥቅምት 22
አውሎ ነፋሱን ሲያይ ፈራ። መስጠም ሲጀምርም “ጌታ ሆይ፣ አድነኝ!” ብሎ ጮኸ።—ማቴ. 14:30
ኢየሱስ እጁን ዘርግቶ በመያዝ ሐዋርያው ጴጥሮስን አዳነው። ጴጥሮስ ትኩረቱን በኢየሱስ ላይ ባደረገበት ወቅት በማዕበል በሚናወጠው ባሕር ላይ መራመድ ችሎ ነበር። አውሎ ነፋሱን ማየት ሲጀምር ግን ፍርሃትና ጥርጣሬ ስላደረበት መስጠም ጀመረ። (ማቴ. 14:24-31) ከጴጥሮስ ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። ጴጥሮስ ከጀልባው ወርዶ በባሕሩ ላይ መጓዝ ሲጀምር ማዕበሉን ፈርቶ መስጠም እንደሚጀምር አልጠበቀም ነበር። በውኃው ላይ እየተራመደ ጌታው ጋ ለመድረስ ፈልጎ ነበር። ሆኖም ትኩረቱን በጌታው ላይ ከማድረግ ይልቅ ማዕበሉን ማየት ጀመረ። እኛ በውኃ ላይ መሄድ እንደማንችል የታወቀ ነው፤ ይሁንና እምነታችንን የሚፈትኑ ነገሮች ያጋጥሙናል። በይሖዋ እና እሱ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ ትኩረት ካላደረግን በመንፈሳዊ ሁኔታ ልንሰጥም እንችላለን። በሕይወታችን ውስጥ እንደ ማዕበል ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎች ቢያጋጥሙንም በይሖዋና እኛን ለመርዳት ባለው ችሎታ ልንተማመን ይገባል። w21.12 17-18 አን. 6-7
ሰኞ፣ ጥቅምት 23
ታላቅ ከሆነው ታማኝ ፍቅርህ የተነሳ ወደ ቤትህ እገባለሁ።—መዝ. 5:7
ጸሎት፣ ጥናትና ማሰላሰል የአምልኳችን ክፍል ናቸው። ስንጸልይ በጣም ከሚወደን የሰማዩ አባታችን ጋር እየተነጋገርን ነው። መጽሐፍ ቅዱስን ስናጠና የጥበብ ሁሉ ምንጭ የሆነውን ‘የአምላክን እውቀት’ እየቀሰምን ነው። (ምሳሌ 2:1-5) ስናሰላስል ደግሞ ይሖዋ ስላሉት ማራኪ ባሕርያት እንዲሁም ለፍጥረታቱ ስላለው አስደናቂ ዓላማና እኛ በዚህ ዓላማ ውስጥ ስላለን ቦታ እናስባለን። ታዲያ ከዚህ የተሻለ ጊዜያችንን ልንጠቀምበት የምንችልበት መንገድ አለ? ይሁንና ለይሖዋ ልናውል አስበን የወሰንነውን ጊዜ ውጤታማ በሆነ መንገድ ልንጠቀምበት የምንችለው እንዴት ነው? የሚቻል ከሆነ ጸጥ ያለ ቦታ ምረጥ። ኢየሱስ ያደረገውን እንደ ምሳሌ እንመልከት። ምድራዊ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት 40 ቀናት በምድረ በዳ አሳልፏል። (ሉቃስ 4:1, 2) እንዲህ ባለ ጸጥ ያለ ስፍራ ኢየሱስ ወደ ይሖዋ መጸለይና አባቱ ለእሱ ስላለው ፈቃድ ማሰላሰል የሚችልበት ጥሩ አጋጣሚ ነበረው። ኢየሱስ እንዲህ ማድረጉ ከፊቱ ለሚጠብቀው ፈተና አዘጋጅቶት እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። w22.01 27-28 አን. 7-8
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 24
በብዙ አማካሪዎች . . . ይሳካል።—ምሳሌ 15:22
አንድ የጉባኤ ሽማግሌ ወይም የጎለመሰ ወንድም ማስተካከል ያለብንን ነገር ይነግረን ይሆናል። አንድ ሰው ለእኛ ባለው ፍቅር ተነሳስቶ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረተ ምክር ከሰጠን፣ ምክሩን ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል። እውነታውን ካየን፣ ብዙ ጊዜ መቀበል የሚከብደን ቀጥተኛ የሆነን ምክር ነው። እንዲያውም እንበሳጭ ይሆናል። ለምን? ፍጹም አለመሆናችንን መቀበል ባይከብደንም አንድ ሰው ድክመታችንን ለይቶ ሲነግረን፣ ብዙውን ጊዜ ምክሩን መቀበል ይተናነቀናል። (መክ. 7:9) ሰበብ አስባብ እንደረድር ይሆናል። ምክሩን በሰጠን ግለሰብ ዝንባሌ ላይ ጥያቄ ልናነሳ እንችላለን፤ ወይም ደግሞ ምክሩን በሰጠበት መንገድ እንከፋ ይሆናል። ሌላው ቀርቶ ምክር በሰጠን ሰው ላይ እንከን ወደመፈላለግ ልንሄድ እንችላለን፤ ‘እሱ ማን ሆኖ ነው እንዲህ የሚለኝ? እሱ ራሱ ስንት ነገር ያጠፋ የለ!’ እንል ይሆናል። የተሰጠንን ምክር ካልወደድነው ደግሞ ምክሩን ችላ ልንለው ወይም ሌላ የሚስማማንን ምክር ፍለጋ ልንሄድ እንችላለን። w22.02 8-9 አን. 2-4
ረቡዕ፣ ጥቅምት 25
ሳትረበሹ፣ ተማምናችሁ በመኖር ብርቱ መሆናችሁን ታሳያላችሁ።—ኢሳ. 30:15
በአዲሱ ዓለም ውስጥ በይሖዋ አሠራር ላይ ያለንን እምነት የሚፈትኑ ሁኔታዎች ያጋጥሙን ይሆን? እስራኤላውያን ከግብፅ ባርነት ነፃ ከወጡ ብዙም ሳይቆይ ያጋጠማቸውን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት። አንዳንዶች በግብፅ ይበሉት የነበረው ምግብ ስለናፈቃቸው ማጉረምረም ጀመሩ፤ ይባስ ብሎም ይሖዋ የሰጣቸውን መና ጠሉት። (ዘኁ. 11:4-6፤ 21:5) እኛስ ታላቁ መከራ ካበቃ በኋላ እንዲህ ዓይነት ስሜት ይመጣብን ይሆን? ምድርን ማጽዳትና ወደ ገነትነት መቀየር ምን ያህል ሥራ እንደሚጠይቅ አናውቅም። ብዙ ሥራ እንደሚጠብቀንና መጀመሪያ አካባቢ አንዳንድ አመቺ ያልሆኑ ነገሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ግን እንጠብቃለን። ታዲያ ይሖዋ በዚያ ጊዜ በሚያደርግልን ዝግጅት ላይ ለማማረር እንፈተን ይሆን? አንድ ነገር በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፦ በአሁኑ ጊዜ ለይሖዋ ዝግጅቶች አድናቆት ካለን ያን ጊዜ ደግሞ ይበልጥ አመስጋኞች እንሆናለን። w22.02 7 አን. 18-19
ሐሙስ፣ ጥቅምት 26
የአንድን አይሁዳዊ ልብስ አጥብቀው በመያዝ “. . . ከእናንተ ጋር እንሄዳለን” ይላሉ።—ዘካ. 8:23
በዘካርያስ 8:23 ላይ በሚገኘው ትንቢት ላይ የተጠቀሱት “አይሁዳዊ” እና “እናንተ” የሚሉት ቃላት የሚያመለክቱት ቅቡዓን ቀሪዎችን ነው። (ሮም 2:28, 29) “ከብሔራት ቋንቋዎች ሁሉ [የተውጣጡት] አሥር ሰዎች” ሌሎች በጎችን ያመለክታሉ። እነዚህ ሰዎች ቅቡዓኑን ‘አጥብቀው ይይዛሉ’ ወይም በታማኝነት ከእነሱ ጋር ይጣበቃሉ። ይህም በንጹሕ አምልኮ ከእነሱ ጋር እንደሚተባበሩ የሚያሳይ ነው። በተመሳሳይም ሕዝቅኤል 37:15-19, 24, 25 ላይ በሚገኘው ትንቢት ፍጻሜ መሠረት ይሖዋ በቅቡዓኑ እና በሌሎች በጎች መካከል የማይሰበር አንድነት እንዲኖር አድርጓል። በትንቢቱ ላይ ሁለት በትሮች ተጠቅሰዋል። ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች “ለይሁዳ” (የእስራኤል ነገሥታት የሚመረጡበት ነገድ ነው) እንደተባለው በትር ናቸው። ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ደግሞ እንደ “ኤፍሬም” በትር ናቸው። ይሖዋ ሁለቱን ቡድኖች አንድ ስለሚያደርጋቸው “አንድ በትር” ይሆናሉ። ይህም በአንድ ንጉሥ በኢየሱስ ክርስቶስ አመራር ሥር በአንድነት እንደሚያገለግሉ ያመለክታል።—ዮሐ. 10:16፤ w22.01 22 አን. 9-10
ዓርብ፣ ጥቅምት 27
ሰዎች እንዲያዩላችሁ ብላችሁ የጽድቅ ሥራችሁን በእነሱ ፊት እንዳታደርጉ ተጠንቀቁ።—ማቴ. 6:1
ኢየሱስ ሌሎች እንዲያዩላቸው ብለው ለድሆች ምጽዋት ስለሚሰጡ ሰዎች ተናግሮ ነበር። እነዚህ ሰዎች መልካም ያደረጉ ቢመስላቸውም በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት የለውም። (ማቴ. 6:2-4) እውነተኛ ጥሩነት ማሳየት የምንችለው ከራስ ወዳድነት ነፃ በሆነ ዝንባሌ ተነሳስተን ትክክለኛውን ነገር ስናደርግ ነው። እስቲ ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘ማድረግ ያለብኝን ትክክለኛ ነገር ማወቅ ብቻ ሳይሆን አደርገዋለሁ? ለሌሎች ጥሩ ነገር የማደርገው በምን ዓይነት ዝንባሌ ተነሳስቼ ነው?’ ይሖዋ የተግባር አምላክ ነው፤ መንፈሱም በሥራ ላይ ያለ ኃይል ነው። (ዘፍ. 1:2) በመሆኑም እያንዳንዱ የመንፈሱ ፍሬ ገጽታ ለተግባር ያነሳሳል። ለምሳሌ ደቀ መዝሙሩ ያዕቆብ ‘እምነት ያለሥራ የሞተ ነው’ ሲል ጽፏል። (ያዕ. 2:26) ከሌሎች የመንፈስ ፍሬ ገጽታዎች ጋር በተያያዘም ይህ እውነት ነው። እነዚህን ባሕርያት ስናንጸባርቅ መንፈሱ በውስጣችን እየሠራ እንደሆነ እናሳያለን። w22.03 11 አን. 14-16
ቅዳሜ፣ ጥቅምት 28
የጠራችሁ ቅዱስ አምላክ፣ ቅዱስ እንደሆነ ሁሉ እናንተም በምግባራችሁ ሁሉ ቅዱሳን ሁኑ።—1 ጴጥ. 1:15
በተለያዩ መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች እንካፈል እንዲሁም በርካታ መልካም ሥራዎችን እናከናውን ይሆናል። ሆኖም ሐዋርያው ጴጥሮስ ክርስቲያኖች በዋነኝነት ሊያከናውኑት የሚገባ አንድ ሥራ እንዳለ ገልጿል፤ በምግባራችን ሁሉ ቅዱሳን እንድንሆን ከማበረታታቱ አስቀድሞ “አእምሯችሁን ዝግጁ በማድረግ ለሥራ ታጠቁ” ብሎ ነበር። (1 ጴጥ. 1:13) ይህ ሥራ ምንድን ነው? ጴጥሮስ የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች ‘የጠራቸውን የእሱን ድንቅ ባሕርያት በየቦታው እንደሚያውጁ’ ተናግሯል። (1 ጴጥ. 2:9) በዛሬው ጊዜ የሚገኙ ክርስቲያኖች በሙሉ በዚህ በጣም አስፈላጊ ሥራ የመካፈል መብት ተሰጥቷቸዋል። ይህ ሥራ ከሁሉ የላቀ ጥቅም ያስገኛል። ቅዱስ የሆኑት የአምላክ ሕዝቦች በስብከቱ እና በማስተማሩ ሥራ አዘውትረው በቅንዓት የመካፈል ልዩ መብት ተሰጥቷቸዋል! (ማር. 13:10) አቅማችን በፈቀደው መጠን በዚህ ሥራ ስንካፈል አምላካችንንም ሆነ ባልንጀራችንን እንደምንወድ እናሳያለን። እንዲሁም ‘በምግባራችን ሁሉ ቅዱሳን መሆን’ እንደምንፈልግ በግልጽ ይታያል። w21.12 13 አን. 18
እሁድ፣ ጥቅምት 29
እናንተ ይቅር ያላችሁትን ማንኛውንም ሰው እኔም ይቅር እለዋለሁ።—2 ቆሮ. 2:10
ሐዋርያው ጳውሎስ ለወንድሞቹና ለእህቶቹ አዎንታዊ አመለካከት ነበረው። አንድ ሰው መጥፎ ነገር ስላደረገ ግለሰቡ መጥፎ ሰው ነው ብሎ መደምደም ተገቢ እንዳልሆነ ያውቅ ነበር። ለወንድሞቹ ፍቅር የነበረው ሲሆን በመልካም ጎናቸው ላይ አተኩሯል። ትክክል የሆነውን ነገር ማድረግ በሚከብዳቸው ጊዜ ውስጣዊ ዝንባሌያቸውን ከመጠራጠር ይልቅ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ያስብ ነበር። ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ጉባኤ የነበሩ ሁለት እህቶችን እንዴት እንደረዳቸው እንመልከት። (ፊልጵ. 4:1-3) ኤዎድያን እና ሲንጤኪ በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት የተነሳ ተቀያይመው ነበር። ጳውሎስ ደግነት የጎደለው ነገር ከመናገር ወይም ከመንቀፍ ይልቅ በመልካም ባሕርያቸው ላይ አተኩሯል። ሁለቱም መልካም ስም ያተረፉ ታማኝ እህቶች ናቸው። ይሖዋ እንደሚወዳቸው ጳውሎስ ያውቅ ነበር። ጳውሎስ ለእነዚህ እህቶች አዎንታዊ አመለካከት መያዙ ቅራኔያቸውን እንዲፈቱ ማበረታቻ ለመስጠት አነሳስቶታል። በተጨማሪም እንዲህ ያለ አመለካከት መያዙ ደስታውን እንዳያጣና በዚያ ጉባኤ ካሉ ወንድሞች ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ይዞ እንዲቀጥል አስችሎታል። w22.03 30 አን. 16-18
ሰኞ፣ ጥቅምት 30
ይሖዋ ልባቸው ለተሰበረ ቅርብ ነው፤ መንፈሳቸው የተደቆሰባቸውንም ያድናል።—መዝ. 34:18
ከይሖዋ የምናገኘው ሰላም ልባችንን ያረጋጋልናል፤ አስተሳሰባችንንም ያስተካክልልናል። ሉዝ የተባለች እህት ይህን በሕይወቷ ተመልክታለች፤ እንዲህ ብላለች፦ “የብቸኝነት ስሜት በጣም ያስቸግረኛል። በዚህ የተነሳ አንዳንዴ ‘ይሖዋ አይወደኝም’ ብዬ አስባለሁ። እንዲህ ሲሰማኝ ግን ወዲያውኑ ለይሖዋ ስሜቴን እነግረዋለሁ። ጸሎት ስሜቴን መቆጣጠር እንድችል ይረዳኛል።” የሉዝ ተሞክሮ እንደሚያሳየው ጸሎት ሰላም እንድናገኝ ይረዳናል። (ፊልጵ. 4:6, 7) ሐዘን ሲደርስብን ይሖዋ እና ኢየሱስ እንደሚደግፉን እናውቃለን። ይሖዋ አምላክ እና ኢየሱስ ክርስቶስን በመምሰል በርኅራኄ ተነሳስተን መስበክና ማስተማር አለብን። ይሖዋ እና ውድ ልጁ ድካማችንን እንደሚረዱልን ብሎም ለመጽናት የሚያስፈልገንን ድጋፍ ሊያደርጉልን እንደሚፈልጉ ማወቃችንም ያጽናናናል። ይሖዋ ‘እንባን ሁሉ ከዓይናችን እንደሚያብስ’ የሰጠው አስደሳች ተስፋ የሚፈጸምበትን ጊዜ በጉጉት እንጠብቃለን።—ራእይ 21:4፤ w22.01 16 አን. 7፤ 19 አን. 19-20
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 31
በጠባቡ በር ግቡ፤ ምክንያቱም ወደ ጥፋት የሚወስደው በር ትልቅ፣ መንገዱም ሰፊ ነው፤ በዚያ የሚሄዱም ብዙዎች ናቸው።—ማቴ. 7:13
ኢየሱስ ወደ ሁለት መንገዶች የሚመሩ ሁለት በሮችን ጠቅሷል፤ አንደኛው መንገድ “ሰፊ” ነው፤ ሌላኛው ደግሞ “ቀጭን” ነው። (ማቴ. 7:14) ሦስተኛ መንገድ የለም። በየትኛው መንገድ እንደምንጓዝ መምረጥ ያለብን እኛ ራሳችን ነን። በሕይወታችን ውስጥ የምናደርገው ትልቁ ውሳኔ ይህ ነው፤ ምክንያቱም የዘላለም ሕይወት ማግኘታችን የተመካው በምናደርገው ምርጫ ላይ ነው። ‘ሰፊው’ መንገድ በብዙዎች ዘንድ ተመራጭ ነው፤ ምክንያቱም መንገዱ ምቹ ነው። የሚያሳዝነው ብዙዎች በዚህ መንገድ ላይ መጓዛቸውን እና ብዙኃኑን መከተላቸውን ለመቀጠል መርጠዋል። በዚህ መንገድ ላይ ሰዎች እንዲጓዙ የሚፈልገው ሰይጣን ዲያብሎስ እንደሆነና ይህ መንገድ ወደ ጥፋት እንደሚወስድ አይገነዘቡም። (1 ቆሮ. 6:9, 10፤ 1 ዮሐ. 5:19) ‘ከሰፊው’ መንገድ በተቃራኒ ሌላኛው መንገድ “ቀጭን” ነው፤ ኢየሱስ ይህን መንገድ የሚያገኙት ጥቂቶች እንደሆኑ ገልጿል። ይህ የሆነው ለምንድን ነው? ኢየሱስ በቀጣዩ ቁጥር ላይ ከሐሰተኛ ነቢያት እንድንጠነቀቅ ማሳሰቢያ እንደሰጠ ልብ በሉ።—ማቴ. 7:15፤ w21.12 22-23 አን. 3-5