መጋቢት
ዓርብ፣ መጋቢት 1
የምትኩራራው ለምንድን ነው?—1 ቆሮ. 4:7
ሐዋርያው ጴጥሮስ ወንድሞቹ ያላቸውን ስጦታና ችሎታ ተጠቅመው የእምነት ባልንጀሮቻቸውን እንዲያንጹ አበረታቷቸዋል። ጴጥሮስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የአምላክ ጸጋ መልካም መጋቢዎች እንደመሆናችሁ መጠን፣ እያንዳንዳችሁ በተቀበላችሁት ስጦታ መሠረት የተሰጣችሁን ስጦታ አንዳችሁ ሌላውን ለማገልገል ተጠቀሙበት።” (1 ጴጥ. 4:10) ሌሎች በእኛ ምክንያት ይቀናሉ ወይም ተስፋ ይቆርጣሉ ብለን በመስጋት ስጦታችንን በተሟላ ሁኔታ ከመጠቀም ወደኋላ ማለት የለብንም። ሆኖም በስጦታዎቻችን መኩራራት የለብንም። (1 ቆሮ. 4:6) በተፈጥሮ ያገኘናቸው ተሰጥኦዎች በሙሉ የአምላክ ስጦታዎች እንደሆኑ ማስታወስ ይኖርብናል። እነዚህን ስጦታዎች ራሳችንን ከፍ ከፍ ለማድረግ ሳይሆን ጉባኤውን ለማነጽ ልንጠቀምባቸው ይገባል። (ፊልጵ. 2:3) ጉልበታችንን እና ችሎታችንን የአምላክን ፈቃድ ለማድረግ ስንጠቀምበት እጅግ የምንደሰትበት ነገር እናገኛለን፤ የምንደሰተው ከሌሎች በልጠን ስለተገኘን ሳይሆን ስጦታችንን ተጠቅመን ለይሖዋ ውዳሴ ስላመጣን ነው። w22.04 11-12 አን. 7-9
ቅዳሜ፣ መጋቢት 2
በሕግህ ውስጥ ያሉትን አስደናቂ ነገሮች አጥርቼ እንዳይ ዓይኖቼን ክፈት።—መዝ. 119:18
ኢየሱስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ይወድ ነበር። ይህ ስሜቱ መዝሙር 40:8 ላይ በትንቢት ተነግሯል፤ ጥቅሱ “አምላኬ ሆይ፣ ፈቃድህን ማድረግ ያስደስተኛል፤ ሕግህም በልቤ ውስጥ ነው” ይላል። በዚህም የተነሳ በይሖዋ አገልግሎት ደስተኛና ስኬታማ ሊሆን ችሏል። እኛም የአምላክ ቃል ወደ ልባችን ዘልቆ እንዲገባ የምንፈቅድ ከሆነ ደስተኛና ስኬታማ መሆን እንችላለን። (መዝ. 1:1-3) ኢየሱስ ከተናገራቸው ቃላትና ከተወው ምሳሌ ጋር በሚስማማ መልኩ የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ ችሎታችንን እናሻሽል። በመጸለይ፣ ረጋ ብለን በማንበብ፣ ጥያቄዎችን በመጠየቅና አጫጭር ማስታወሻዎችን በመያዝ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎችን የመረዳት ችሎታችንን ማሳደግ እንችላለን። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎቻችንን ተጠቅመን የምናነበውን ነገር በጥንቃቄ እናመዛዝን፤ ይህም በማስተዋል ለማንበብ ያስችለናል። በተጨማሪም በትክክለኛው የልብ ዝንባሌ በማንበብ የአምላክ ቃል እንዲቀርጸን እንፍቀድ። በእነዚህ አቅጣጫዎች የቻልነውን ሁሉ ካደረግን ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባባችን የተሟላ ጥቅም እናገኛለን፤ እንዲሁም ከምንጊዜውም ይበልጥ ወደ ይሖዋ እንቀርባለን።—መዝ. 119:17፤ ያዕ. 4:8፤ w23.02 13 አን. 15-16
እሁድ፣ መጋቢት 3
የትጉ ሰው ዕቅድ ለስኬት ያበቃዋል።—ምሳሌ 21:5
ግልጽ የሆነ ግብ አውጣ። ከዚያም ግብህ ላይ ለመድረስ የሚረዱህን ተግባራዊ እርምጃዎች ውሰድ። ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የማስተማር ችሎታህን ለማሻሻል ግብ አወጣህ እንበል። ለማንበብ እና ለማስተማር የተቻለህን ሁሉ ጥረት አድርግ የተባለውን ብሮሹር በጥንቃቄ ልታጠና ትችላለህ። በሳምንቱ መሃል ስብሰባ ላይ ክፍል ሲሰጥህ ብቃት ያለውን አንድ ወንድም ከስብሰባው በፊት ክፍልህን አዳምጦ ምክር እንዲሰጥህ ልትጠይቀው ትችላለህ። በችሎታህ ብቻ ሳይሆን ትጉና እምነት የሚጣልብህ በመሆን ረገድም መልካም ስም አትርፍ። (2 ቆሮ. 8:22) ያወጣኸው ግብ በጣም የሚከብድህን ነገር ማድረግ የሚጠይቅብህ ቢሆንስ? ተስፋ አትቁረጥ! ጢሞቴዎስ አንደበተ ርቱዕ ተናጋሪ ወይም ግሩም አስተማሪ መሆን ችሎ ነበር? መጽሐፍ ቅዱስ ይህን በተመለከተ የሚናገረው ነገር የለም። ሆኖም ጢሞቴዎስ የጳውሎስን ምክር በመከተሉ የተሰጠውን ኃላፊነት በጊዜ ሂደት ውጤታማ በሆነ መንገድ መወጣት እንደቻለ ምንም ጥያቄ የለውም።—2 ጢሞ. 3:10፤ w22.04 24-25 አን. 8-11
ሰኞ፣ መጋቢት 4
አሥር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ያሉት አንድ አውሬ ከባሕር ሲወጣ አየሁ።—ራእይ 13:1
ሰባት ራሶች ያሉት አውሬ ማን ነው? ይህ አውሬ በጥቅሉ ሲታይ ነብር ይመስላል፤ እግሮቹ ግን የድብ፣ አፉ ደግሞ የአንበሳ አፍ ነው፤ አሥር ቀንዶችም አሉት። እነዚህን ገጽታዎች በሙሉ በዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይ የተገለጹት አራት አራዊት ላይም እናያቸዋለን። በራእይ መጽሐፍ ላይ ግን እነዚህ ገጽታዎች በሙሉ የሚታዩት በአንድ አውሬ ላይ እንጂ በአራት የተለያዩ አራዊት ላይ አይደለም። ይህ አውሬ አንድን መንግሥት ወይም የዓለም ኃይል ብቻ የሚያመለክት አይደለም። አውሬው “በነገድ፣ በሕዝብ፣ በቋንቋና በብሔር ሁሉ ላይ ሥልጣን” እንዳለው ተገልጿል። ስለዚህ አንድን መንግሥት ብቻ ሊያመለክት አይችልም። (ራእይ 13:7) እንግዲያው ይህ አውሬ የሚያመለክተው እስከ ዛሬ የሰው ልጆችን ሲያስተዳድሩ የቆዩ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች መሆን አለበት። (መክ. 8:9) ይህን የሚጠቁመው ሌላው ነገር አሥር ቁጥር ብዙውን ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሙላትን ለማመልከት የሚሠራበት መሆኑ ነው። w22.05 9 አን. 6
ማክሰኞ፣ መጋቢት 5
እንባን ሁሉ ከዓይናቸው ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም፤ ሐዘንም ሆነ ጩኸት እንዲሁም ሥቃይ ከእንግዲህ ወዲህ አይኖርም።—ራእይ 21:4
እነዚህን አስደናቂ በረከቶች የሚያገኙት እነማን ናቸው? የመጀመሪያ ተጠቃሚ የሚሆኑት ከአርማጌዶን በሕይወት የሚተርፉት እጅግ ብዙ ሕዝብና በአዲሱ ዓለም የሚወልዷቸው ልጆች ናቸው። ሆኖም ራእይ ምዕራፍ 20 ሙታን እንደሚነሱም ይናገራል። (ራእይ 20:11-13) በሞት ያንቀላፉ “ጻድቃንም ሆኑ ዓመፀኞች” ተነስተው በምድር ላይ ይኖራሉ፤ “ዓመፀኞች” የተባሉት ስለ ይሖዋ ለማወቅ በቂ አጋጣሚ ሳያገኙ የሞቱ ሰዎች ናቸው። (ሥራ 24:15፤ ዮሐ. 5:28, 29) ይህ ሲባል ታዲያ በሺው ዓመት ግዛት ወቅት ሁሉም ሰው ከሞት ይነሳል ማለት ነው? አይደለም። ይሖዋን ለማገልገል የሚያስችል አጋጣሚ አግኝተው ሆን ብለው ሳይጠቀሙበት የቀሩ ሰዎች ከሞት አይነሱም። እነዚህ ሰዎች በቂ አጋጣሚ አግኝተው ስላልተጠቀሙበት ገነት በምትሆነው ምድር ላይ ሕይወት ለማግኘት ብቁ አይሆኑም።—ማቴ. 25:46፤ 2 ተሰ. 1:9፤ ራእይ 17:8፤ 20:15፤ w22.05 18 አን. 16-17
ረቡዕ፣ መጋቢት 6
ወደ ማን እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ።—ዮሐ. 6:68
ኢየሱስ ‘በታማኝና ልባም ባሪያ’ አማካኝነት በምድር ላይ ንጹሕ አምልኮን የሚያስፋፋ አስደናቂ ድርጅት አቋቁሟል። (ማቴ. 24:45) ስለዚህ ድርጅት ምን ይሰማሃል? ምናልባት እንደ ሐዋርያው ጴጥሮስ ዓይነት ስሜት ይሰማህ ይሆናል፤ ጴጥሮስ ለኢየሱስ በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን ሐሳብ ነግሮት ነበር። ማናችንስ ብንሆን ከይሖዋ ድርጅት ጋር ባንተዋወቅ ኖሮ ዛሬ የት እንገኝ ነበር? ክርስቶስ በዚህ ድርጅት አማካኝነት የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እንድናገኝ ያደርጋል። በተጨማሪም አገልግሎታችንን ውጤታማ በሆነ መንገድ እንድናከናውን ያሠለጥነናል። ከዚህም ሌላ ይሖዋን ለማስደሰት የሚያስችለንን “አዲሱን ስብዕና” እንድንለብስ ይረዳናል። (ኤፌ. 4:24) ኢየሱስ በአስቸጋሪ ጊዜ ጥበብ የሚንጸባረቅበት መመሪያ ይሰጠናል። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት እንዲህ ያለው መመሪያ ምን ያህል ጠቃሚ እንደሆነ ተመልክተናል። በዓለም ላይ ያሉ ብዙ ሰዎች ምን ማድረግ እንዳለባቸው ግራ በተጋቡበት ወቅት ኢየሱስ ደህንነታችንን ለመጠበቅ የሚረዳን ግልጽ መመሪያ እንድናገኝ አድርጓል። w22.07 12 አን. 13-14
ሐሙስ፣ መጋቢት 7
ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ለይታችሁ [እወቁ]።—ፊልጵ. 1:10
ይሖዋ የጥንቶቹን እስራኤላውያን ልጆቻቸውን ስለ እሱ አዘውትረው እንዲያስተምሯቸው አዟቸው ነበር። (ዘዳ. 6:6, 7) እነዚህ ወላጆች በየቀኑ ከልጆቻቸው ጋር ማውራትና ለይሖዋ ፍቅር እንዲያድርባቸው መርዳት የሚችሉባቸው በርካታ አጋጣሚዎች ነበሯቸው። ለምሳሌ አንድ እስራኤላዊ ልጅ በእርሻ ወይም በመከር ወቅት አባቱን እያገዘ ብዙ ሰዓታት ሊያሳልፍ ይችላል። እህቱም ብትሆን ልብስ በመስፋት፣ በመሸመንና ሌሎች የቤት ውስጥ ሥራዎችን በማከናወን እናቷን ስታግዝ ትውላለች። ወላጆችና ልጆች አብረው ሲሠሩ ስለ ብዙ ጉዳዮች ማውራት ይችላሉ። ለምሳሌ ስለ ይሖዋ ጥሩነትና ቤተሰባቸውን እንዴት እንደረዳው የማውራት አጋጣሚ ያገኛሉ። በብዙ አገሮች ውስጥ ወላጆችና ልጆች በቀን ውስጥ አብረው የሚያሳልፉት ሰፋ ያለ ጊዜ ማግኘት አይችሉም። ወላጆች ሥራ ቦታ፣ ልጆች ደግሞ ትምህርት ቤት ይውላሉ። ስለዚህ ወላጆች ከልጆቻቸው ጋር ለማውራት የሚያስችሏቸውን አጋጣሚዎች በንቃት መፈለግ አለባቸው።—ኤፌ. 5:15, 16፤ w22.05 28 አን. 10-11
ዓርብ፣ መጋቢት 8
ዓመፀኞች የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ አታውቁም?—1 ቆሮ. 6:9
ከባድ ኃጢአት የሚባለው ከአምላክ ሕግ ጋር በእጅጉ የሚቃረን ድርጊት ነው። አንድ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ኃጢአት ከፈጸመ ወደ ይሖዋ በመጸለይ ይቅርታ መጠየቅ አለበት፤ እንዲሁም የጉባኤውን ሽማግሌዎች ሊያነጋግር ይገባል። (መዝ. 32:5፤ ያዕ. 5:14) የሽማግሌዎች ሚና ምንድን ነው? ኃጢአትን ሙሉ በሙሉ ይቅር የማለት ሥልጣን ያለው ይሖዋ ብቻ ነው፤ ይህን የሚያደርገው ደግሞ የኢየሱስን ቤዛዊ መሥዋዕት መሠረት በማድረግ ነው። ሆኖም ‘ኃጢአተኛው በጉባኤው ውስጥ ይቀጥል ወይ’ የሚለውን ጉዳይ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት አድርገው እንዲወስኑ ይሖዋ ለሽማግሌዎች ሥልጣን ሰጥቷቸዋል። (1 ቆሮ. 5:12) ሽማግሌዎች ይህን ጉዳይ በሚወስኑበት ጊዜ የሚከተሉትን ጥያቄዎች ለመመለስ ጥረት ያደርጋሉ፦ ግለሰቡ ኃጢአት የሠራው አስቀድሞ አሲሮ ነው? ኃጢአቱን ከሌሎች ለመደበቅ ሞክሯል? ኃጢአቱን ረዘም ላለ ጊዜ ሲፈጽም ቆይቷል? በዋነኝነት ደግሞ፣ ኃጢአተኛው ከልቡ ንስሐ እንደገባ የሚያሳይ ማስረጃ አለ? ይሖዋ ይቅር እንዳለው የሚጠቁም ነገር አለ?—ሥራ 3:19፤ w22.06 9 አን. 4
ቅዳሜ፣ መጋቢት 9
እውነትን . . . ውደዱ።—ዘካ. 8:19
ኢየሱስ ተከታዮቹን ጽድቅን እንዲከተሉ አበረታቷቸዋል። (ማቴ. 5:6) ይህ ሲባል በአምላክ ዓይን ትክክል፣ መልካምና ንጹሕ የሆነውን ነገር ለማድረግ ጠንካራ ፍላጎት ሊኖረን ይገባል ማለት ነው። እውነትንና ጽድቅን ትወዳለህ? እንደምትወድ እርግጠኞች ነን። ለውሸት እንዲሁም መጥፎና ክፉ ለሆኑ ነገሮች ጥላቻ አለህ። (መዝ. 119:128, 163) ውሸት የዚህ ዓለም ገዢ የሆነው የሰይጣን መለያ ነው። (ዮሐ. 8:44፤ 12:31) አንዱ የሰይጣን ዓላማ የይሖዋ አምላክን ቅዱስ ስም ማጉደፍ ነው። ሰይጣን በኤደን ዓመፅ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ አንስቶ ስለ አምላካችን ውሸት ሲያናፍስ ቆይቷል። ይሖዋን ከሰው ልጆች መልካም ነገርን የሚነፍግ፣ ራስ ወዳድና ውሸታም ገዢ እንደሆነ አድርጎ ገልጾታል። (ዘፍ. 3:1, 4, 5) ሰይጣን ስለ ይሖዋ የሚያናፍሳቸው ውሸቶች የሰዎችን አእምሮና ልብ መመረዛቸውን ቀጥለዋል። ሰዎች ‘እውነትን ለመውደድ’ የማይመርጡ ከሆነ ሰይጣን ከጽድቅ ወደራቁና በክፋት ወደተሞሉ የተለያዩ ዓይነት ድርጊቶች ሊመራቸው ይችላል።—ሮም 1:25-31፤ w23.03 2 አን. 3
እሁድ፣ መጋቢት 10
[የይሖዋ ፍቅር] ለዘላለም . . . ጸንቶ ይኖራል።—መዝ. 100:5
አንድን መጥፎ ልማድ ለማስወገድ ጥረት ብታደርግም አልፎ አልፎ ይህ ልማድ ሊያገረሽብህ ይችላል። አሊያም ደግሞ ግብህ ፈጽሞ ሊደረስበት የማይችል እንደሆነ በማሰብ ትዕግሥትህ ሊሟጠጥና ተስፋ ልትቆርጥ ትችላለህ። ታዲያ ለመጽናት የሚረዳህ ምንድን ነው? በዚህ ረገድ የሚረዳህ ወሳኝ ባሕርይ ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ነው። ሊኖሩህ ከሚችሉት ባሕርያት ሁሉ እጅግ የላቀው ለይሖዋ ያለህ ፍቅር ነው። (ምሳሌ 3:3-6) ለአምላክ ያለህ ጥልቅ ፍቅር በሕይወትህ ውስጥ የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች በተሳካ መንገድ እንድትወጣ ይረዳሃል። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ ለአገልጋዮቹ ስላለው ታማኝ ፍቅር በተደጋጋሚ ይናገራል። ታማኝ ፍቅር ከሚወዱት አካል ጋር እስከ መጨረሻው መጣበቅን የሚጠይቅ ጠንካራ ባሕርይ ነው። የተፈጠርከው በአምላክ መልክ ነው። (ዘፍ. 1:26) ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን ፍቅር ማንጸባረቅ የምትችለው እንዴት ነው? በቅድሚያ አመስጋኝ ልትሆን ይገባል። (1 ተሰ. 5:18) በየዕለቱ ‘ይሖዋ ፍቅር ያሳየኝ እንዴት ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። ከዚያም ይሖዋ ያደረገልህን ነገር ለይተህ በመጥቀስ በጸሎትህ ላይ እሱን ማመስገንህን አትርሳ። የይሖዋን የፍቅር መግለጫዎች ለአንተ በግለሰብ ደረጃ እንደተደረጉልህ አድርገህ ተመልከታቸው። w23.03 12 አን. 17-19
ሰኞ፣ መጋቢት 11
[ኢየሱስ] በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ [ነበር]።—ዮሐ. 2:25
ኢየሱስ ለ12ቱም ሐዋርያት ደግነትና ፍቅር አሳይቷቸዋል። ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ዋናው ነገር ሰዎች የሚያደርጉት ነገር ብቻ ሳይሆን እኛ ለስህተታቸው ወይም ለድክመታቸው ምላሽ የምንሰጥበት መንገድ ነው። አንድ የእምነት ባልንጀራችን ሲያበሳጨን ራሳችንን እንዲህ ብለን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ያደረገው ነገር ይህን ያህል ቅር ያሰኘኝ ለምንድን ነው? እንዲህ የተሰማኝ መሆኑ ማስተካከል ያለብኝ መጥፎ ባሕርይ እንዳለ የሚጠቁም ይሆን? ያበሳጨኝ ሰው እንደዚያ ያደረገው ከባድ ሁኔታ ውስጥ ስለነበረ ነው? መበሳጨቴ ተገቢ እንደሆነ ቢሰማኝ እንኳ ጉዳዩን ችላ ብዬ በማለፍ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ማሳየት እችላለሁ?’ ሌሎችን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ ለመያዝ ይበልጥ ጥረት ባደረግን ቁጥር የኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች መሆናችንን እናረጋግጣለን። ኢየሱስ የተወልን ምሳሌ የእምነት ባልንጀሮቻችንን ለመረዳት ጥረት ማድረግ እንዳለብንም ያስተምረናል። (ምሳሌ 20:5) እርግጥ ነው፣ ኢየሱስ የሰዎችን ልብ ማንበብ ይችላል። እኛ ግን አንችልም። ሆኖም ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስህተት ሊሠሩ እንደሚችሉ በመጠበቅ እነሱን በትዕግሥት ለመያዝ ጥረት ማድረግ እንችላለን። (ኤፌ. 4:1, 2፤ 1 ጴጥ. 3:8) እነሱን በደንብ ለማወቅ መሞከራችን እንዲህ ማድረግ ይበልጥ ቀላል እንዲሆንልን ያደርጋል። w23.03 30 አን. 14-16
ማክሰኞ፣ መጋቢት 12
እሱ የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም።—ሉቃስ 20:38
ሰይጣን፣ ያለብንን ከባድ የጤና እክል ተጠቅሞ አቋማችንን እንድናላላ ለማድረግ ይሞክራል። ሐኪሞች ወይም የማያምኑ ቤተሰቦቻችን ደም እንድንወስድ ይገፋፉን ይሆናል፤ ደም መውሰድ ደግሞ የአምላክን ሕግ መጣስ ነው። አንዳንዶች ደግሞ ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጋር የሚጋጭ ሕክምና እንድንከታተል ሊያግባቡን ይሞክሩ ይሆናል። መሞት እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ሆኖም ብንሞትም እንኳ ይሖዋ እኛን መውደዱን እንደማያቆም ማስታወስ ይኖርብናል። (ሮም 8:37-39) ይሖዋ ወዳጆቹ ቢሞቱም እንኳ በሕይወት ያሉ ያህል ያስታውሳቸዋል። (ሉቃስ 20:37) በትንሣኤ ሊያስነሳቸው ይናፍቃል። (ኢዮብ 14:15) ይሖዋ ‘የዘላለም ሕይወት እንዲኖረን’ ሲል ውድ ዋጋ ከፍሏል። (ዮሐ. 3:16) ይሖዋ በጣም እንደሚወደንና እንደሚያስብልን እናውቃለን። ስለዚህ ስንታመም ወይም ከሞት ጋር ስንፋጠጥ ይሖዋን ከመተው ይልቅ ማጽናኛ፣ ጥበብና ብርታት እንዲሰጠን ወደ እሱ መቅረብ ይኖርብናል።—መዝ. 41:3፤ w22.06 18 አን. 16-17
ረቡዕ፣ መጋቢት 13
እውነተኛ ጥበብ በጎዳና ላይ ትጮኻለች።—ምሳሌ 1:20
መጽሐፍ ቅዱስ “የጥበብ መጀመሪያ ይሖዋን መፍራት ነው፤ እጅግ ቅዱስ ስለሆነው አምላክ ማወቅም ማስተዋል ነው” ይላል። (ምሳሌ 9:10) እንግዲያው ከባድ ውሳኔ በምናደርግበት ጊዜ ውሳኔያችን በይሖዋ አስተሳሰብ ማለትም ‘እጅግ ቅዱስ ስለሆነው አምላክ ባለን እውቀት’ ላይ የተመሠረተ መሆን ይኖርበታል። መጽሐፍ ቅዱስንና በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተመሠረቱ ጽሑፎችን በመመርመር እንዲህ ያለ ውሳኔ ማድረግ እንችላለን። እንዲህ ስናደርግ እውነተኛ ጥበብ እንዳለን እናሳያለን። (ምሳሌ 2:5-7) እውነተኛ ጥበብ ሊሰጠን የሚችለው ይሖዋ ብቻ ነው። (ሮም 16:27) የጥበብ ምንጭ ይሖዋ ነው የምንለው ለምንድን ነው? አንደኛ፣ ፈጣሪ እንደመሆኑ መጠን ስለ ፍጥረታቱ ገደብ የለሽ እውቀት አለው። (መዝ. 104:24) ሁለተኛ፣ ይሖዋ የሚያደርገው ነገር ሁሉ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ነው። (ሮም 11:33) ሦስተኛ፣ ጥበብ የሚንጸባረቅበትን የይሖዋን ምክር የሚከተሉ ሰዎች ሁልጊዜ ጥቅም ያገኛሉ። (ምሳሌ 2:10-12) እውነተኛ ጥበብ ማግኘት ከፈለግን እነዚህን መሠረታዊ እውነታዎች መቀበል እንዲሁም ውሳኔ ከማድረጋችን ወይም አንድን እርምጃ ከመውሰዳችን በፊት እነዚህን እውነታዎች ከግምት ማስገባት አለብን። w22.10 19 አን. 3-4
ሐሙስ፣ መጋቢት 14
በሰማይም ጦርነት ተነሳ፦ ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም ተዋጓቸው፤ ነገር ግን አልቻሏቸውም፤ ከዚያ በኋላም በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም።—ራእይ 12:7, 8
በራእይ ምዕራፍ 12 ላይ አስቀድሞ በተነገረው ጦርነት ሰይጣን ተሸነፈ፤ እሱና አጋንንቱም ወደ ምድር ተወረወሩ። በቁጣ የተሞላው ሰይጣን ንዴቱን በሰው ልጆች ላይ መወጣት ጀመረ፤ ይህም ‘በምድር ላይ ወዮታ’ አስከትሏል። (ራእይ 12:9-12) እነዚህ ትንቢቶች የሚጠቅሙን እንዴት ነው? በዓለም ላይ የሚታዩ ክንውኖችና በሰዎች ባሕርይ ላይ የሚታየው ለውጥ ኢየሱስ ንጉሥ መሆኑን ለማስተዋል ይረዳናል። በመሆኑም ሰዎች ራስ ወዳድና ጨካኝ መሆናቸውን ስናይ ከመበሳጨት ይልቅ ምግባራቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ እንደሆነ እናስታውሳለን። አዎ፣ መንግሥቱ ተቋቁሟል! (መዝ. 37:1) ደግሞም ወደ አርማጌዶን በተቃረብን መጠን በዓለም ላይ የሚታየው መከራ እየተባባሰ እንደሚሄድ እንጠብቃለን። (ማር. 13:8፤ 2 ጢሞ. 3:13) በእርግጥም አፍቃሪ የሆነው የሰማዩ አባታችን፣ ዓለማችን ትርምስምሱ የወጣው ለምን እንደሆነ እንድናውቅ ስለረዳን በጣም እናመሰግነዋለን። w22.07 3-4 አን. 7-8
ዓርብ፣ መጋቢት 15
ጻድቅ ሰው የሚያቀርበው ምልጃ ታላቅ ኃይል አለው።—ያዕ. 5:16
የእምነት ባልንጀሮቻችን ሕመምን፣ የተፈጥሮ አደጋን፣ የእርስ በርስ ጦርነትን፣ ስደትን ወይም ሌሎች ፈተናዎችን እንዲቋቋሙ ልንጸልይላቸው እንችላለን። በተጨማሪም የተቸገሩትን ለመርዳት ሲሉ የራሳቸውን ጥቅም መሥዋዕት ለሚያደርጉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መጸለይ እንችላለን። እንዲህ ዓይነት ፈተና ያጋጠማቸውን ወንድሞችና እህቶች በግል ታውቁ ይሆናል። ታዲያ ለምን ስማቸውን ጠቅሳችሁ አትጸልዩላቸውም? ይሖዋ መጽናት እንዲችሉ እንዲረዳቸው በመጸለይ እውነተኛ የወንድማማች ፍቅር እንዳለን እናሳያለን። በጉባኤ ውስጥ አመራር የሚሰጡ ወንዶች ስንጸልይላቸው ደስ ይላቸዋል፤ ደግሞም ጸሎታችን በእጅጉ ይጠቅማቸዋል። ከሐዋርያው ጳውሎስ ጋር በተያያዘ ይህ እውነት መሆኑ ታይቷል። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “የምሥራቹን ቅዱስ ሚስጥር በድፍረት ለሌሎች ማሳወቅ እንድችል አፌን በምከፍትበት ጊዜ የምናገረው ቃል እንዲሰጠኝ ለእኔም ጸልዩልኝ።” (ኤፌ. 6:19) በዛሬው ጊዜም በመካከላችን ሆነው አመራር የሚሰጡ በርካታ ትጉ ወንድሞች አሉ። ይሖዋ ሥራቸውን እንዲባርክላቸው በመጸለይ ለእነሱ ያለንን ፍቅር እናሳያለን። w22.07 23-24 አን. 14-16
ቅዳሜ፣ መጋቢት 16
የመዳንን . . . ተስፋ እንደ ራስ ቁር እንድፋ።—1 ተሰ. 5:8
ወታደሮች የራስ ቁር የሚያደርጉት ጭንቅላታቸውን ከጥቃት ለመከላከል ነው። እኛም በምናደርገው መንፈሳዊ ውጊያ ላይ አእምሯችንን ከሰይጣን ጥቃቶች መከላከል ይጠበቅብናል። ሰይጣን አስተሳሰባችንን የሚመርዙ ሐሳቦችንና ፈተናዎችን ያዥጎደጉድብናል። የራስ ቁር የአንድን ወታደር ጭንቅላት እንደሚጠብቅለት ሁሉ ተስፋችን ለይሖዋ ታማኝ መሆን እንድንችል አስተሳሰባችንን ይጠብቅልናል። ተስፋችን ከደበዘዘና ሥጋዊ አስተሳሰብ አእምሯችንን እንዲቆጣጠረው ከፈቀድን የዘላለም ሕይወት ተስፋችንን ልንረሳው እንችላለን። በጥንቷ ቆሮንቶስ ይኖሩ የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ወሳኝ በሆነው የትንሣኤ ተስፋ ላይ እምነት አጥተው ነበር። (1 ቆሮ. 15:12) ጳውሎስ፣ ለወደፊቱ ጊዜ ተስፋ የሌላቸው ሰዎች የሚኖሩት ለዛሬ ብቻ እንደሆነ ተናግሯል። (1 ቆሮ. 15:32) በዛሬው ጊዜም አምላክ በሰጣቸው ተስፋዎች ላይ እምነት የሌላቸው ብዙ ሰዎች የሚኖሩት ለዕለቱ ብቻ ነው፤ የሚያሳስባቸው የአሁኑን ሕይወታቸውን አስደሳች የማድረጉ ጉዳይ ብቻ ነው። እኛ ግን አምላክ በሰጠን የወደፊት ተስፋ ላይ እምነት አለን። w22.10 25-26 አን. 8-9
እሁድ፣ መጋቢት 17
ዘወትር ጸልዩ።—1 ተሰ. 5:17
ይሖዋ ወደ እሱ እንድትጸልይ ጋብዞሃል። የሚያጋጥሙህን ችግሮች ያያል፤ እንዲሁም በማንኛውም ጊዜ ጸሎትህን እንደሚሰማ ዋስትና ሰጥቶሃል። ይሖዋ አገልጋዮቹን መስማት ደስ ያሰኘዋል። (ምሳሌ 15:8) ይሁንና ብቻህን እንደሆንክ ሲሰማህ ምን ብለህ መጸለይ ትችላለህ? ልብህን በይሖዋ ፊት አፍስስ። (መዝ. 62:8) ስለሚያሳስቡህ ነገሮች እንዲሁም እነዚህ ነገሮች ስለፈጠሩብህ ስሜት ንገረው። ይሖዋ አሉታዊ ስሜቶችን ለማሸነፍ እንዲረዳህ እንዲሁም እምነትህን ለመግለጽ የሚያስችል ድፍረት እንዲሰጥህ ለምነው። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ስለ እምነትህ በዘዴ ለማስረዳት የሚያስችል ጥበብ እንዲሰጥህ መጠየቅ ትችላለህ። (ሉቃስ 21:14, 15) ከአሉታዊ ስሜቶች ጋር እየታገልክ ከሆነ ከአንድ ጎልማሳ ክርስቲያን ጋር ስለ ጉዳዩ ለመነጋገር እንዲረዳህ ይሖዋን ጠይቀው። የምታነጋግረው ሰው ስሜትህን መረዳት እንዲችል እንዲያግዘውም ይሖዋን መጠየቅ ትችላለህ። ይሖዋ ለጸሎትህ የሚሰጠውን ምላሽ ተመልከት፤ እንዲሁም የሌሎችን እርዳታ ተቀበል። እንዲህ ካደረግክ የሚሰማህ የብቸኝነት ስሜት ይቀንሳል። w22.08 10 አን. 6
ሰኞ፣ መጋቢት 18
እነዚህ . . . ሰዎች . . . የቄሳርን ሕግ የሚቃረን ነገር ያደርጋሉ።—ሥራ 17:7
በተሰሎንቄ የተቋቋመው አዲስ ጉባኤ ከባድ ተቃውሞ አጋጠመው። በቁጣ የተሞሉ ተቃዋሚዎች “አንዳንድ ወንድሞችን እየጎተቱ ወስደው የከተማዋ ገዢዎች ፊት” አቀረቧቸው። (ሥራ 17:6) አዲሶቹ ክርስቲያኖች ምን ያህል ተደናግጠው ይሆን! ሁኔታው የአገልግሎት ቅንዓታቸውን ሊያቀዘቅዝባቸው ይችል ነበር፤ ሆኖም ሐዋርያው ጳውሎስ ይህ እንዲሆን አልፈለገም። አዲሱ ጉባኤ አስፈላጊውን እንክብካቤ እንዲያገኝ አድርጓል። ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “እምነታችሁ ይጠነክር ዘንድ እንዲያጸናችሁ እንዲሁም እንዲያበረታታችሁ ጢሞቴዎስን ላክንላችሁ፤ . . . የላክነውም ማንም በእነዚህ መከራዎች እንዳይናወጥ ነው።” (1 ተሰ. 3:2, 3) ጢሞቴዎስ፣ ጳውሎስ በልስጥራ ያሉትን ክርስቲያኖች እንዴት እንዳበረታታቸው ተመልክቷል። በተጨማሪም ጢሞቴዎስ፣ ይሖዋ የልስጥራን ክርስቲያኖች እንዴት እንደባረካቸው አይቷል፤ በመሆኑም ይሖዋ እነሱንም እንደሚረዳቸውና እንደሚባርካቸው በመግለጽ አዲሶቹን ክርስቲያኖች ሊያበረታታቸው ይችላል።—ሥራ 14:8, 19-22፤ ዕብ. 12:2፤ w22.08 21 አን. 4
ማክሰኞ፣ መጋቢት 19
በእሱ አማካኝነት ሕይወት [እናገኛለን]።—1 ዮሐ. 4:9
በ19ኛው መቶ ዘመን ማብቂያ አካባቢ የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች በቻርልስ ቴዝ ራስል አመራር ሥር ሆነው ቅዱሳን መጻሕፍትን በጥልቀት ማጥናት ጀመሩ። እነዚህ ሰዎች የኢየሱስ መሥዋዕት ስላለው ዋጋ እንዲሁም የሞቱ መታሰቢያ እንዴት ሊከበር እንደሚገባ እውነቱን ማወቅ ፈልገው ነበር። እነሱ ያደረጉት ምርምር በዛሬው ጊዜ ያለነውንም ጠቅሞናል። እንዴት? ስለ ኢየሱስ መሥዋዕት እንዲሁም ስለሚያስገኘው ጥቅም እውነቱ በርቶልናል። (1 ዮሐ. 2:1, 2) በተጨማሪም አምላክን ለሚያስደስቱ ሰዎች ስለተዘረጉላቸው ሁለት ተስፋዎች ከመጽሐፍ ቅዱስ ተምረናል፤ አንዳንዶች በሰማይ የማይሞት ሕይወት፣ ሌሎች ደግሞ በምድር ላይ የዘላለም ሕይወት እንደሚያገኙ አውቀናል። ይሖዋ ምን ያህል እንደሚወደንና የኢየሱስ መሥዋዕት ምን ያህል እንደሚጠቅመን መረዳታችን ወደ ይሖዋ ይበልጥ ለመቅረብ ረድቶናል። (1 ጴጥ. 3:18) በመሆኑም እነዚያ ታማኝ ወንድሞች ያኔ እንዳደረጉት በዓሉን ኢየሱስ ባሳየው መንገድ በምናከብርበት ወቅት ሌሎችም አብረውን እንዲገኙ እንጋብዛለን። w23.01 21 አን. 6-7
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 9) ማርቆስ 14:3-9
ረቡዕ፣ መጋቢት 20
በሕይወት ያሉትም ከእንግዲህ ለራሳቸው ከመኖር ይልቅ ለእነሱ ለሞተውና ለተነሳው እንዲኖሩ እሱ ለሁሉም ሞቷል።—2 ቆሮ. 5:15
ኢየሱስ የአምላክ መንግሥት ስለሚያመጣቸው በረከቶች ለሰዎች አስተምሯል። ቤዛው ከይሖዋና ከኢየሱስ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ለመመሥረት አጋጣሚ ከፍቶልናል፤ ለዚህም አመስጋኞች ነን። በተጨማሪም በኢየሱስ የሚያምኑ ሁሉ ለዘላለም የመኖር እንዲሁም በሞት ያጧቸውን የሚወዷቸውን ሰዎች ዳግም የማየት ተስፋ ተዘርግቶላቸዋል። (ዮሐ. 5:28, 29፤ ሮም 6:23) እነዚህ በረከቶች ይገባናል የምንላቸው አይደሉም፤ ምንም ብናደርግ አምላክና ክርስቶስ የዋሉልንን ውለታ መክፈልም አንችልም። (ሮም 5:8, 20, 21) ሆኖም የአመስጋኝነታችንን ጥልቀት ልናሳያቸው እንችላለን። እንዴት? ያሉንን ነገሮች ተጠቅመን የመንግሥቱን ሥራ በመደገፍ ነው። ለምሳሌ ለንጹሕ አምልኮ የሚሆኑ ሕንፃዎችን በመገንባቱና በመንከባከቡ ሥራ ለማገዝ ራሳችንን ማቅረብ እንችላለን። w23.01 26 አን. 3፤ 28 አን. 5
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 9) ማርቆስ 11:1-11
ሐሙስ፣ መጋቢት 21
አየሁ፤ . . . በጉ [እና 144,000ዎቹ] ነበሩ።—ራእይ 14:1
በአምላክ መንግሥት ውስጥ ሥልጣን የሚኖራቸው ገዢዎች በመላው ዓለም የሚኖሩ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን ያስተዳድራሉ። እንደ ኢየሱስ ሁሉ 144,000ዎቹም ነገሥታትና ካህናት ሆነው ያገለግላሉ። (ራእይ 5:10) በሙሴ ሕግ ሥር የካህናቱ ዋነኛ ኃላፊነት የሕዝቡን አካላዊም ሆነ መንፈሳዊ ጤንነት ማስጠበቅ ነበር። ሕጉ “ወደፊት ለሚመጡት መልካም ነገሮች ጥላ” ነው፤ በመሆኑም የኢየሱስ ተባባሪ ገዢዎች የአምላክ ሕዝቦች ያሏቸውን ሥጋዊና መንፈሳዊ ፍላጎቶች በማሟላት ረገድ ልዩ ሚና ይኖራቸዋል ብሎ መደምደም ምክንያታዊ ነው። (ዕብ. 10:1) እነዚህ ነገሥታትና ካህናት፣ በምድር ላይ ካሉት የመንግሥቱ ተገዢዎች ጋር የሐሳብ ግንኙነት የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ ወደፊት የምናየው ይሆናል። ወደፊት በሚመጣው ገነት ውስጥ በምድር ላይ ያሉ ሰዎች የሚያስፈልጋቸውን መመሪያ እንደሚያገኙ እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ራእይ 21:3, 4፤ w22.12 11 አን. 11-13
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 10) ማርቆስ 11:12-19
ዓርብ፣ መጋቢት 22
ጌታ እስከሚመጣ ድረስ ሞቱን ታውጃላችሁ።—1 ቆሮ. 11:26
ሰዎችን ወደ መታሰቢያው በዓል የምንጋብዝበት አንዱ ምክንያት አዲሶች ይሖዋና ኢየሱስ ለሁላችንም ስላደረጉልን ነገር እንዲማሩ ስለምንፈልግ ነው። (ዮሐ. 3:16) በመታሰቢያው በዓል ላይ የሚያዩትና የሚሰሙት ነገር ስለ ይሖዋ ይበልጥ ለመማርና የእሱ አገልጋይ ለመሆን ያነሳሳቸዋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን። ይሖዋን ማገልገላቸውን ያቆሙ ሰዎችንም ወደ በዓሉ እንጋብዛለን። ይህን የምናደርገው አምላክ አሁንም ቢሆን እንደሚወዳቸው ለማስታወስ ነው። ብዙዎች ግብዣችንን ተቀብለው በበዓሉ ላይ ይገኛሉ፤ እኛም በደስታ እንቀበላቸዋለን። በመታሰቢያው በዓል ላይ መገኘታቸው ቀደም ሲል ይሖዋን ሲያገለግሉ የነበራቸውን ደስታ ይቀሰቅስባቸዋል። (መዝ. 103:1-4) ሰዎች ግብዣውን ተቀበሉም አልተቀበሉ በትጋት መጋበዛችንን እንቀጥላለን፤ ምክንያቱም ይሖዋ ለግለሰቦቹ ትኩረት እንደሚሰጥ እርግጠኞች ነን።—ሉቃስ 15:7፤ 1 ጢሞ. 2:3, 4፤ w23.01 20 አን. 1፤ 22-23 አን. 9-11
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 11) ማርቆስ 11:20–12:27, 41-44
ቅዳሜ፣ መጋቢት 23
የይሖዋ ዓይን የሚፈሩትን . . . በትኩረት ይመለከታል።—መዝ. 33:18
ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ለሰማዩ አባቱ ልዩ ልመና አቅርቧል። ተከታዮቹን እንዲጠብቃቸው ይሖዋን ጠይቆታል። (ዮሐ. 17:15, 20) ይሖዋ ከጥንትም ጀምሮ ሕዝቡን በትኩረት ሲመለከት፣ ሲንከባከብና ሲጠብቅ ቆይቷል። ሆኖም ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ ከሰይጣን ይህ ነው የማይባል ተቃውሞ እንደሚደርስባቸው ጠብቆ ነበር። በተጨማሪም ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ የዲያብሎስን መሠሪ ዘዴዎች እንዲቋቋሙ የይሖዋ እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ተገንዝቦ ነበር። በዛሬው ጊዜ የሰይጣን ሥርዓት በእውነተኛ ክርስቲያኖች ላይ ከፍተኛ ጫና ያሳድራል። ተስፋ ሊያስቆርጡን አልፎ ተርፎም ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት ሊፈትኑ የሚችሉ መከራዎች ያጋጥሙናል። ሆኖም የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። ይሖዋ በትኩረት ይመለከተናል። የሚያጋጥሙንን ችግሮች ያያል፤ እንዲሁም ችግሮቹን እንድንቋቋም ለመርዳት ምንጊዜም ዝግጁ ነው። አዎ፣ ይሖዋ ‘የሚፈሩትን በትኩረት ይመለከታል።’—መዝ. 33:18-20፤ w22.08 8 አን. 1-2
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 12) ማርቆስ 14:1, 2, 10, 11፤ ማቴዎስ 26:1-5, 14-16
የመታሰቢያው በዓል የሚከበርበት ዕለት
ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ
እሁድ፣ መጋቢት 24
ይህን ሁልጊዜ ለመታሰቢያዬ አድርጉት።—ሉቃስ 22:19
በየዓመቱ በመታሰቢያው በዓል ሰሞን፣ ኢየሱስ ላደረገልን ነገር አድናቆታችንን ለማሳየት አጋጣሚ እናገኛለን። በዚህ ወቅት የእሱ ሞት ስላስገኘልን ጥቅም ጊዜ ወስደን በጸሎት እናስብበታለን። በተቻለን መጠን ብዙዎች በዚህ ልዩ በዓል ላይ እንዲገኙም እንጋብዛለን። ደግሞም ምንም ነገር በበዓሉ ላይ እንዳንገኝ እንቅፋት እንዲሆንብን አንፈቅድም። በመታሰቢያው በዓል ላይ የሰው ልጆች ቤዛ ያስፈለጋቸው ለምን እንደሆነና የአንድ ሰው ሞት የብዙዎችን ኃጢአት የሚያስተሰርየው እንዴት እንደሆነ እንማራለን። ቂጣውና የወይን ጠጁ ምን እንደሚወክሉ እንዲሁም ከዚያ መካፈል የሚችሉት እነማን እንደሆኑ ማብራሪያ ይሰጣል። (ሉቃስ 22:19, 20) በተጨማሪም ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ሰዎች ስለሚያገኟቸው በረከቶች የምናሰላስልበት አጋጣሚ እናገኛለን። (ኢሳ. 35:5, 6፤ 65:17, 21-23) እነዚህን እውነቶች እንደ ቀላል ነገር ልንመለከታቸው አይገባም። w23.01 20 አን. 2, 4
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 13) ማርቆስ 14:12-16፤ ማቴዎስ 26:17-19 (ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 14) ማርቆስ 14:17-72
ሰኞ፣ መጋቢት 25
አምላክ ዓለምን እጅግ ከመውደዱ የተነሳ በልጁ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው . . . ሲል አንድያ ልጁን ሰጥቷል።—ዮሐ. 3:16
አምላክ ልጁን ኃጢአታችንን የሚሸፍን ቤዛ አድርጎ በመስጠት የዘላለም ሕይወት ማግኘት የምንችልበት በር ከፍቶልናል። (ማቴ. 20:28) ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፦ “ሞት የመጣው በአንድ ሰው በኩል ስለሆነ የሙታን ትንሣኤም በአንድ ሰው በኩል ነው። ሁሉም በአዳም እንደሚሞቱ ሁሉም በክርስቶስ ሕያው ይሆናሉና።” (1 ቆሮ. 15:21, 22) ኢየሱስ፣ ተከታዮቹ የአምላክ መንግሥት እንዲመጣና የአምላክ ፈቃድ በምድር ላይ እንዲፈጸም እንዲጸልዩ አስተምሯቸዋል። (ማቴ. 6:9, 10) የአምላክ ዓላማ አንዱ ክፍል፣ ሰዎች በምድር ላይ ለዘላለም እንዲኖሩ ነው። ይሖዋ ይህን ዓላማውን ለማስፈጸም ልጁን የመሲሐዊው መንግሥት ንጉሥ አድርጎ ሾሞታል። አምላክ ፈቃዱን ለማስፈጸም ከኢየሱስ ጋር የሚሠሩ 144,000 ሰዎችን ከምድር ሲሰበስብ ቆይቷል።—ራእይ 5:9, 10፤ w22.12 5 አን. 11-12
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 14) ማርቆስ 15:1-47
ማክሰኞ፣ መጋቢት 26
በሕይወት ያሉትም ከእንግዲህ ለራሳቸው [እንዳይኖሩ] ክርስቶስ ያለው ፍቅር ግድ ይለናል።—2 ቆሮ. 5:14, 15
የምንወደውን ሰው በሞት ስናጣ ናፍቆቱ በጣም ከባድ ይሆንብናል። መጀመሪያ አካባቢ ውስጣችንን ያመናል፤ በተለይ አሟሟቱ ሥቃይ ከነበረው። እያደር ግን ሐዘኑ እየቀነሰ ይሄዳል። ግለሰቡ ያስተማረንን ነገር እናስታውሳለን፤ ምን ብሎ ወይም ምን አድርጎ ያበረታታን ወይም ያስቀን እንደነበረም ትዝ ይለናል። እነዚህ ትዝታዎች በኋላ ላይ ደስታ የሚያስገኙልን ነገር ይሆናሉ። በተመሳሳይም ኢየሱስ ስለደረሰበት መከራና ስለ አሟሟቱ ስናስብ በጣም እናዝናለን። በመታሰቢያው በዓል ሰሞን ቤዛው ስላለው ዋጋ ጊዜ ወስደን እንደምናስብ የታወቀ ነው። (1 ቆሮ. 11:24, 25) ያም ቢሆን በጥቅሉ ኢየሱስ ምድር ላይ ሳለ ስለተናገራቸውና ስላከናወናቸው ነገሮች ማሰባችን ላቅ ያለ ደስታ ያስገኝልናል። በአሁኑ ጊዜ ምን እያደረገ እንዳለና ወደፊት ምን እንደሚያደርግልን ማሰባችንም በጣም ያበረታታናል። w23.01 26 አን. 1-2
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 15) ማቴዎስ 27:62-66 (ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 16) ማርቆስ 16:1
ረቡዕ፣ መጋቢት 27
ከሁሉ አስቀድማችሁ የአምላክን መንግሥት . . . ፈልጉ።—ማቴ. 6:33
ኢየሱስ ሲሞት ደቀ መዛሙርቱ በጣም አዝነው ነበር። የሚወዱትን ወዳጃቸውን ብቻ አይደለም የተነጠቁት፤ ተስፋቸው እንደ ጉም በንኖ እንደጠፋም ተሰምቷቸው መሆን አለበት። (ሉቃስ 24:17-21) ሆኖም ኢየሱስ ተገለጠላቸውና ከመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ጋር በተያያዘ ያለውን ድርሻ ጊዜ ወስዶ አብራራላቸው። በተጨማሪም አንድ አስፈላጊ ሥራ ሰጣቸው። (ሉቃስ 24:26, 27, 45-48) ኢየሱስ ወደ ሰማይ ባረገበት ወቅት የደቀ መዛሙርቱ ሐዘን ወደ ደስታ ተቀይሮ ነበር። ጌታቸው ሕያው እንደሆነና አዲሱን ተልእኳቸውን እንዲወጡ እንደሚረዳቸው ማወቃቸው ደስተኛ አድርጓቸዋል። ይህ ደስታ ደግሞ ይሖዋን ያለማሰለስ እንዲያወድሱ አነሳስቷቸዋል። (ሉቃስ 24:52, 53፤ ሥራ 5:42) የኢየሱስን ደቀ መዛሙርት ለመምሰል በሕይወታችን ውስጥ ለአምላክ መንግሥት ቅድሚያ መስጠት ይኖርብናል። እርግጥ ነው፣ ይሖዋን ያለማሰለስ ማገልገል ጽናት ይጠይቃል፤ ሆኖም እንዲህ ካደረግን ይሖዋ እንደሚባርከን ቃል ገብቶልናል።—ምሳሌ 10:22፤ w23.01 30-31 አን. 15-16
የመታሰቢያው በዓል የመጽሐፍ ቅዱስ ንባብ፦ (ቀን ላይ የተከናወኑ ነገሮች፦ ኒሳን 16) ማርቆስ 16:2-8
ሐሙስ፣ መጋቢት 28
ወደ አፈር ትመለሳለህ።—ዘፍ. 3:19
አዳምና ሔዋን የሠሩትን ዓይነት ስህተት መሥራት እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ስለ ይሖዋ መማራችንን፣ ባሕርያቱን ማድነቃችንን እንዲሁም አስተሳሰቡን ለመረዳት ጥረት ማድረጋችንን ከቀጠልን እንዲህ ያለውን ስህተት ከመሥራት እንጠበቃለን። እንዲህ ስናደርግ ለይሖዋ ያለን ፍቅር ያድጋል። የአብርሃምን ምሳሌ እንመልከት። አብርሃም ይሖዋን በጣም ይወደው ነበር። ይሖዋ ያደረጋቸውን አንዳንድ ውሳኔዎች መረዳት በከበደው ጊዜም እንኳ አብርሃም አላመፀም። ከዚህ ይልቅ ይሖዋን ይበልጥ ለማወቅ ጥረት አድርጓል። ለምሳሌ ይሖዋ ሰዶምንና ገሞራን ለማጥፋት መወሰኑን ሲያውቅ አብርሃም መጀመሪያ ላይ “የምድር ሁሉ ዳኛ” ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አብሮ እንዳያጠፋ ሰግቶ ነበር። አብርሃም ይህ ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር እንደሆነ ተሰምቶት ነበር፤ በመሆኑም ይሖዋን በትሕትና የተለያዩ ጥያቄዎችን ጠየቀው። ይሖዋም በትዕግሥት መለሰለት። በመጨረሻም አብርሃም፣ ይሖዋ የሁሉንም ሰው ልብ እንደሚመረምርና መቼም ቢሆን ጻድቁን ከኃጢአተኛው ጋር አብሮ እንደማይቀጣ ተገነዘበ።—ዘፍ. 18:20-32፤ w22.08 28 አን. 9-10
ዓርብ፣ መጋቢት 29
እምነት የሚጣልበት ሰው . . . ሚስጥር ይጠብቃል።—ምሳሌ 11:13
በ455 ዓ.ዓ. ገዢው ነህምያ የኢየሩሳሌምን ቅጥሮች መልሶ ከገነባ በኋላ ከተማዋን በሚገባ የሚንከባከቡ እምነት የሚጣልባቸው ሰዎችን ማግኘት ፈልጎ ነበር። ነህምያ ከመረጣቸው ሰዎች መካከል የምሽጉ አለቃ የሆነው ሃናንያህ ይገኝበታል። መጽሐፍ ቅዱስ ሃናንያህ “እምነት የሚጣልበትና ከሌሎቹ ሁሉ ይበልጥ እውነተኛውን አምላክ የሚፈራ ሰው” እንደሆነ ይገልጻል። (ነህ. 7:2) ሃናንያህ ለይሖዋ ፍቅር የነበረው ከመሆኑም ሌላ እሱን ማሳዘን ያስፈራው ነበር፤ ይህም የተሰጠውን ማንኛውንም ኃላፊነት በቁም ነገር እንዲመለከት አነሳስቶታል። እኛም እነዚህን ባሕርያት ማዳበራችን ለአምላክ በምናቀርበው አገልግሎት እምነት የሚጣልብን እንድንሆን ይረዳናል። እምነት የሚጣልበት የጳውሎስ ወዳጅ የሆነውን ቲኪቆስን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። ጳውሎስ በቲኪቆስ ላይ ይተማመን ነበር፤ “ታማኝ አገልጋይ” በማለት ጠርቶታል። (ኤፌ. 6:21, 22) ጳውሎስ በኤፌሶንና በቆላስይስ ላሉ ወንድሞች ደብዳቤ እንዲያደርስ ብቻ ሳይሆን እነሱን እንዲያበረታታና እንዲያጽናናም አደራ ጥሎበታል። ቲኪቆስ በዛሬው ጊዜ መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ለማሟላት ተግተው የሚሠሩትን ታማኝና እምነት የሚጣልባቸው ወንድሞች ያስታውሰናል።—ቆላ. 4:7-9፤ w22.09 9-10 አን. 5-6
ቅዳሜ፣ መጋቢት 30
ፍቅር የኃጢአትን ብዛት ይሸፍናል።—1 ጴጥ. 4:8
ዮሴፍ ለ13 ዓመት ያህል ከባድ መከራ ደርሶበታል። ዮሴፍ ይሖዋ በእርግጥ የሚወደው መሆኑን ሊጠራጠር ይችል ነበር። በተጨማሪም እርዳታ በጣም በሚያስፈልገው ጊዜ ይሖዋ እንደተወው ሊሰማው ይችል ነበር። ሆኖም ዮሴፍ አልተመረረም። ከዚህ ይልቅ በመረጋጋት የማስተዋል ስሜቱን ጠብቋል። ወንድሞቹን ለመበቀል አጋጣሚ ባገኘ ጊዜ እንዲህ ከማድረግ ተቆጥቧል፤ ከዚህ ይልቅ ፍቅር አሳይቷቸዋል፤ እንዲሁም ይቅር ብሏቸዋል። (ዘፍ. 45:4, 5) ዮሴፍ እንዲህ ያደረገው ቆም ብሎ ማሰብ ስለቻለ ነው። በራሱ ችግሮች ላይ ከማተኮር ይልቅ እይታውን በማስፋት በይሖዋ ዓላማ ላይ ትኩረት አድርጓል። (ዘፍ. 50:19-21) ታዲያ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? በደል ሲፈጸምብህ በይሖዋ አትመረር፤ ወይም ‘እሱ ትቶኛል’ ብለህ አታስብ። ከዚህ ይልቅ ፈተናውን እንድትወጣ እየረዳህ ያለው እንዴት እንደሆነ አሰላስል። በተጨማሪም ሌሎች ሲበድሉህ ድክመታቸውን በፍቅር ለመሸፈን ሞክር። w22.11 21 አን. 4
እሁድ፣ መጋቢት 31
መንግሥታትም ሁሉ ያገለግሏቸዋል፤ ደግሞም ይታዘዟቸዋል።—ዳን. 7:27
ነቢዩ ዳንኤል፣ ይሖዋ ከሁሉም መንግሥታት የላቀ ሥልጣን እንዳለው የሚያሳይ ራእይ ተመልክቷል። በመጀመሪያ ዳንኤል ጥንትም ሆነ ዛሬ ያሉ የዓለም ኃያላን መንግሥታትን የሚወክሉ አራት ትላልቅ አውሬዎችን ተመለከተ፤ እነዚህ መንግሥታት ባቢሎን፣ ሜዶ ፋርስ፣ ግሪክ፣ ሮም እና በዘመናችን ሥልጣን ላይ ያለው አንግሎ አሜሪካ ናቸው። (ዳን. 7:1-3, 17) ከዚያም ዳንኤል፣ ይሖዋ አምላክ በሰማያዊ ችሎቱ በዙፋን ላይ ተቀምጦ ተመለከተ። (ዳን. 7:9, 10) አምላክ የሁሉንም መንግሥታት ሥልጣን ወስዶ ብቃቱን ለሚያሟሉና ይበልጥ ኃያላን ለሆኑ አካላት ይሰጠዋል። እነሱ እነማን ናቸው? ‘የሰው ልጅ የሚመስለው’ ኢየሱስ ክርስቶስና ‘ከሁሉ የላቀው አምላክ ቅዱሳን የሆኑት ሰዎች’ ማለትም “ለዘላለም ዓለም” የሚነግሡት 144,000ዎች ናቸው። (ዳን. 7:13, 14, 18) በእርግጥም ይሖዋ ‘ከሁሉ የላቀ አምላክ’ ነው። ዳንኤል ያየው ራእይ ከዚያ ቀደም ከተናገረው ሐሳብ ጋር የሚስማማ ነው። ዳንኤል “[የሰማይ አምላክ] ነገሥታትን ያስወግዳል፤ ደግሞም ያስቀምጣል” ብሏል።—ዳን. 2:19-21፤ w22.10 14-15 አን. 9-11