ሚያዝያ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 1
ተፈትኖ የተረጋገጠው እምነታችሁ ጽናት [ያስገኛል]።—ያዕ. 1:3
ራሳችንን እንዲህ እያልን መጠየቅ እንችላለን፦ ‘ምክር ሲሰጠኝ ምን ዓይነት ምላሽ እሰጣለሁ? ስህተቴን ቶሎ አምኜ እቀበላለሁ? ወይስ ሰበብ አስባብ እደረድራለሁ? ጥፋቴን በሌሎች ላይ አላክካለሁ?’ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ስለተጠቀሱ ታማኝ ወንዶችና ሴቶች ስታነብ እነዚህ ሰዎች እንዲህ ያለ ሁኔታ ሲያጋጥማቸው ጉዳዩን እንዴት እንደያዙት ለማሰብ ሞክር። እያንዳንዱን ምሳሌ ስትመረምር ‘ይህን ታማኝ የይሖዋ አገልጋይ መምሰል የምችለው እንዴት ነው?’ እያልክ ራስህን ጠይቅ። በጉባኤያችን ውስጥ ካሉ ወጣቶችና አረጋውያንም መማር እንችላለን። ለምሳሌ ያህል፣ ያጋጠመውን ፈተና በታማኝነት እየተቋቋመ ያለ ሰው በጉባኤህ ውስጥ አለ? ፈተናው የእኩዮች ተጽዕኖ፣ የቤተሰብ ተቃውሞ ወይም የጤና እክል ሊሆን ይችላል። ይህ ግለሰብ አንተም ማዳበር የምትፈልጋቸው ግሩም ባሕርያት አሉት? የእሱን ምሳሌ በማጤን ያጋጠመህን ፈተና በጽናት ለመቋቋም የሚረዳ ጠቃሚ ትምህርት ታገኝ ይሆናል። እንዲህ ያሉ ግሩም የእምነት ምሳሌዎች በዙሪያችን በመኖራቸው በጣም አመስጋኞች ነን። እጅግ የምንደሰትበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው!—ዕብ. 13:7፤ w22.04 13 አን. 13-14
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 2
ከመቀበል ይልቅ መስጠት የበለጠ ደስታ ያስገኛል።—ሥራ 20:35
በግል ሕይወታችን ከባድ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙን አንድ አሳቢ ሽማግሌ ጊዜ ሰጥቶ ሲያዳምጠንና ሲያጽናናን ደስ ይለናል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በመምራት ረገድ እርዳታ ሲያስፈልገን ተሞክሮ ያለው አንድ አቅኚ አብሮን በማስጠናት ሐሳብ ሲሰጠን አመስጋኝ እንደምንሆን ምንም ጥያቄ የለውም። እነዚህ ወንድሞችና እህቶች እኛን በመርዳታቸው ደስተኞች ናቸው። ወንድሞቻችንን ለማገልገል ራሳችንን ካቀረብን እኛም የዚህ ደስታ ተካፋይ መሆን እንችላለን። በእነዚህ ወይም በሌሎች መንገዶች አገልግሎትህን ለማስፋት ከፈለግክ ግብህ ላይ ለመድረስ ምን ሊረዳህ ይችላል? ግልጽ ያልሆነ ግብ አታውጣ። ለምሳሌ ‘በጉባኤ ውስጥ የማደርገውን እንቅስቃሴ ማሳደግ እፈልጋለሁ’ ብለህ ታስብ ይሆናል። ሆኖም እንዲህ ያለው ግብ ላይ መድረስ የምትችለው እንዴት እንደሆነ ማወቅ ሊከብድህ ይችላል። ግብህ ላይ መድረስህን ማወቅም ከባድ ሊሆንብህ ይችላል። ስለዚህ በግልጽ የተቀመጠ ግብ ይኑርህ። ምናልባትም ግብህንና እዚያ ላይ ለመድረስ ያሰብከው እንዴት እንደሆነ በጽሑፍ ልታሰፍር ትችላለህ። w22.04 25 አን. 12-13
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 3
ባልንጀራህን እንደ ራስህ ውደድ።—ያዕ. 2:8
በአሁኑ ወቅት ይሖዋ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” በመሰብሰብ የመንግሥቱ ተገዢዎች እንዲሆኑ እያሠለጠናቸው ነው። (ራእይ 7:9, 10) በዛሬው ጊዜ ያለው ዓለም በጥላቻና በጦርነት የተከፋፈለ ቢሆንም እንኳ የዚህ ቡድን አባላት ማንኛውንም የብሔር፣ የዘርና የግል ጥላቻ ለማስወገድ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋሉ። አሁንም ቢሆን በምሳሌያዊ ሁኔታ ሰይፋቸውን ቀጥቅጠው ማረሻ እያደረጉ ነው። (ሚክ. 4:3) የብዙዎችን ሕይወት በሚቀጥፈው በጦርነት ከመካፈል ይልቅ ሰዎችን ስለ እውነተኛው አምላክና ስለ ዓላማዎቹ በማስተማር “እውነተኛ የሆነውን ሕይወት” እንዲያገኙ እየረዱ ነው። (1 ጢሞ. 6:19) የቤተሰባቸው አባላት ይቃወሟቸው ይሆናል፤ ወይም ደግሞ የአምላክን መንግሥት በመደገፋቸው የተነሳ የኢኮኖሚ ችግር ሊያጋጥማቸው ይችላል። ያም ቢሆን ይሖዋ ምንጊዜም የሚያስፈልጋቸውን ነገር ይሰጣቸዋል። (ማቴ. 6:25, 30-33፤ ሉቃስ 18:29, 30) እነዚህ ነገሮች የአምላክ መንግሥት እውን እንደሆነና የይሖዋን ዓላማ ማስፈጸሙን እንደሚቀጥል ያረጋግጡልናል። w22.12 5 አን. 13
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 4
አሜን! ጌታ ኢየሱስ፣ ና።—ራእይ 22:20
በሺው ዓመት ማብቂያ ላይ በምድር ላይ የሚኖሩ ሁሉ ፍጹም ይሆናሉ። ከአዳም የወረስነው ኃጢአት ተጽዕኖ የሚያደርግበት ሰው አይኖርም። (ሮም 5:12) የአዳም ኃጢአት ያስከተለው እርግማን ሙሉ በሙሉ ይወገዳል። በሺው ዓመት መጨረሻ ላይ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ፍጹማን ስለሚሆኑ ‘ሕያው ይሆናሉ’ ሊባል ይችላል። (ራእይ 20:5) ኢየሱስ ንጹሕ አቋሙን እንዲያጎድፍ ሰይጣን ላደረገው ጥረት እጅ እንዳልሰጠ እናውቃለን። የሰይጣንን ፈተና በታማኝነት ተወጥቷል። ሆኖም ሰይጣን እንዲፈትናቸው ዕድል ቢሰጠው ፍጹም የሆኑ የሰው ልጆች በሙሉ ታማኝ ይሆናሉ? በሺው ዓመት ማብቂያ ላይ ሰይጣን ከጥልቁ ሲፈታ እያንዳንዳችን ለዚህ የታማኝነት ጥያቄ መልስ ለመስጠት አጋጣሚ እናገኛለን። (ራእይ 20:7) ይህን የመጨረሻ ፈተና በታማኝነት የሚወጡ ሁሉ የዘላለም ሕይወትና እውነተኛ ነፃነት ያገኛሉ። (ሮም 8:21) በይሖዋ ላይ የሚያምፁ ሁሉ ለዘላለም ይጠፋሉ።—ራእይ 20:8-10፤ w22.05 19 አን. 18-19
ዓርብ፣ ሚያዝያ 5
አንተም ተረከዙን ታቆስላለህ።—ዘፍ. 3:15
ሰይጣን አይሁዳውያንን እና ሮማውያንን በማነሳሳት የአምላክን ልጅ እንዲገድሉት ባደረገበት ጊዜ ይህ ትንቢት ተፈጽሟል። (ሉቃስ 23:13, 20-24) የተረከዝ ቁስል አንድን ሰው ለተወሰነ ጊዜ ያህል ከእንቅስቃሴ ውጭ እንደሚያደርገው ሁሉ ኢየሱስም ሞቶ ለሦስት ቀናት ያህል መቃብር ውስጥ መቆየቱ ለጊዜው ከእንቅስቃሴ ውጭ እንዲሆን አድርጎታል። (ማቴ. 16:21) በዘፍጥረት 3:15 ላይ ያለው ትንቢት እንዲፈጸም ከተፈለገ ኢየሱስ መቃብር ውስጥ መቅረት የለበትም። ለምን? ምክንያቱም በትንቢቱ መሠረት የሴቲቱ ዘር የእባቡን ዘር ይጨፈልቃል። ይህ እንዲሆን ኢየሱስ ከተረከዝ ቁስሉ ማገገም አለበት። ደግሞም አገግሟል! ኢየሱስ በሞተ በሦስተኛው ቀን ትንሣኤ አግኝቶ የማይሞት መንፈሳዊ ፍጡር ሆነ። አምላክ የወሰነው ጊዜ ሲደርስ ኢየሱስ ሰይጣንን ጨፍልቆ ከሕልውና ውጭ ያደርገዋል። (ዕብ. 2:14) ክርስቶስና ተባባሪ ገዢዎቹ የእባቡን ዘር ማለትም የአምላክን ጠላቶች በሙሉ ከምድር ገጽ ላይ ጠራርገው ያጠፋሉ።—ራእይ 17:14፤ 20:4, 10፤ w22.07 16 አን. 11-12
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 6
ከጥበበኞች ጋር የሚሄድ ጥበበኛ ይሆናል።—ምሳሌ 13:20
ወላጆች፣ ልጆቻችሁ ጥሩ ወዳጆች እንዲያፈሩ እርዷቸው። የምንመርጣቸው ጓደኞች በጥሩም ሆነ በመጥፎ ተጽዕኖ እንደሚያሳድሩብን የአምላክ ቃል በግልጽ ይናገራል። የልጆቻችሁ ጓደኞች እነማን እንደሆኑ ታውቃላችሁ? ልጆቻችሁ ይሖዋን ከሚወዱ ሰዎች ጋር ጓደኝነት እንዲመሠርቱ ለመርዳት ምን ማድረግ ትችላላችሁ? (1 ቆሮ. 15:33) ጥሩ መንፈሳዊ አቋም ያላቸው አንዳንድ ክርስቲያኖችን ከቤተሰባችሁ ጋር ጊዜ እንዲያሳልፉ በመጋበዝ ልጆቻችሁ ጥሩ ጓደኞች እንዲመርጡ መርዳት ትችላላችሁ። (መዝ. 119:63) ቶኒ የተባለ አባት እንዲህ ብሏል፦ “ልጆቻችንን ባሳደግንባቸው ዓመታት ሁሉ እኔና ባለቤቴ የተለያየ ዕድሜ፣ ባሕልና አስተዳደግ ያላቸው ወንድሞችንና እህቶችን ቤታችን እንጋብዝ ነበር። አብረናቸው ምሳ እንበላለን ወይም የቤተሰብ አምልኮ እናደርጋለን። ይህ ይሖዋን ከሚወዱና እሱን በደስታ ከሚያገለግሉ ሰዎች ጋር ለመተዋወቅ የሚያስችል ግሩም አጋጣሚ ነው። . . . ተሞክሯቸው፣ ቅንዓታቸው እንዲሁም ራሳቸውን ሳይቆጥቡ መስጠታቸው በልጆቻችን ላይ ትልቅ ተጽዕኖ አሳድሯል፤ ወደ ይሖዋ እንዲቀርቡም ረድቷቸዋል።” w22.05 29-30 አን. 14-15
እሁድ፣ ሚያዝያ 7
በምድር የምታስሩት ነገር ሁሉ ቀድሞውኑ በሰማያት የታሰረ ይሆናል።—ማቴ. 18:18
ሽማግሌዎች አንድን ኃጢአተኛ በሚያነጋግሩበት ጊዜ ግባቸው ቀድሞውኑ በሰማይ ከተደረገው ውሳኔ ጋር የሚስማማ ውሳኔ በምድር ላይ ማድረግ ነው። ይህ ዝግጅት ጉባኤውን የሚጠቅመው እንዴት ነው? የይሖዋን ውድ በጎች ሊጎዱ የሚችሉ ንስሐ ያልገቡ ኃጢአተኞች ከጉባኤው እንዲወገዱ ያደርጋል። (1 ቆሮ. 5:6, 7, 11-13፤ ቲቶ 3:10, 11) ኃጢአተኛውም ንስሐ ገብቶ የይሖዋን ይቅርታ እንዲያገኝ ሊረዳው ይችላል። (ሉቃስ 5:32) ግለሰቡ ንስሐ ከገባ ሽማግሌዎች በመንፈሳዊ እንዲያገግም ይሖዋ እንዲረዳው ይጸልዩለታል። (ያዕ. 5:15) ሽማግሌዎች ኃጢአተኛውን በሚያነጋግሩበት ጊዜ ግለሰቡ የንስሐ ፍሬ ባያሳይስ? ሁኔታው እንዲህ ከሆነ ግለሰቡ ከጉባኤ ይወገዳል። ይሁንና ግለሰቡ ከጊዜ በኋላ ወደ ልቦናው ተመልሶ ከልቡ ንስሐ ከገባና ከተለወጠ ይሖዋ ይቅር ሊለው ፈቃደኛ ነው። (ሉቃስ 15:17-24) የፈጸመው ኃጢአት በጣም ከባድ ቢሆንም ይሖዋ ይቅር ይለዋል።—2 ዜና 33:9, 12, 13፤ 1 ጢሞ. 1:15፤ w22.06 9 አን. 5-6
ሰኞ፣ ሚያዝያ 8
የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ፤ ንቁ ሆናችሁ ኑሩ! ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል።—1 ጴጥ. 5:8
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ክርስቲያኖች በይሖዋ እርዳታ ከባድ ፈተናዎችን መቋቋምና ሰይጣንን ስኬታማ በሆነ መንገድ መቃወም ችለዋል። (1 ጴጥ. 5:9) አንተም እንዲህ ማድረግ ትችላለህ። ይሖዋ በቅርቡ ለኢየሱስና አብረውት ለሚገዙት መመሪያ በመስጠት ‘የዲያብሎስን ሥራ እንዲያፈርሱ’ ያደርጋል። (1 ዮሐ. 3:8) ከዚያ በኋላ በምድር ላይ ያሉ የአምላክ አገልጋዮች በሙሉ ‘ምንም ነገር አይፈሩም፤ የሚያሸብራቸውም ነገር አይኖርም።’ (ኢሳ. 54:14፤ ሚክ. 4:4) እስከዚያው ግን ፍርሃታችንን ለማሸነፍ ጥረት ማድረጋችንን መቀጠል ይኖርብናል። ይሖዋ አገልጋዮቹን እንደሚወድና እንደሚጠብቅ ያለንን እምነት ማጠናከር ይኖርብናል። ይሖዋ ከዚህ ቀደም አገልጋዮቹን የጠበቃቸው እንዴት እንደሆነ ማሰላሰላችንና ለሌሎች መናገራችን በዚህ ረገድ ይረዳናል። ከባድ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን እኛን በግለሰብ ደረጃ የረዳን እንዴት እንደሆነም ማስታወስ ይኖርብናል። በይሖዋ እርዳታ ፍርሃታችንን ማሸነፍ እንችላለን!—መዝ. 34:4፤ w22.06 19 አን. 19-20
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 9
ከብረትና ከሸክላ የተሠሩትን የምስሉን እግሮች [መታቸው]።—ዳን. 2:34
‘ከብረትና ከሸክላ በተሠሩት የምስሉ እግሮች’ የተወከለው የዓለም ኃያል መንግሥት በአሁኑ ወቅት በመግዛት ላይ ነው። ወደ ሕልውና የመጣው በመጀመሪያው የዓለም ጦርነት ወቅት ብሪታንያ እና ዩናይትድ ስቴትስ ልዩ ኅብረት በመመሥረት የአንግሎ አሜሪካን ጥምር ኃይል በፈጠሩበት ጊዜ ነው። ናቡከደነጾር በሕልሙ ያየው ምስል፣ ይህንን የዓለም ኃያል መንግሥት ከእሱ በፊት ከተነሱት ሌሎች መንግሥታት የተለየ የሚያደርጉትን ነገሮች ይጠቁማል። በራእዩ ላይ ከተጠቀሱት ከሌሎቹ የዓለም ኃያል መንግሥታት በተለየ መልኩ የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት የተወከለው እንደ ወርቅ ወይም ብር ባለ ንጹሕ ንጥረ ነገር ሳይሆን በብረትና በሸክላ ቅልቅል ነው። ሸክላው ‘የሰውን ዘር’ ማለትም ተራውን ሕዝብ ያመለክታል። (ዳን. 2:43 ግርጌ) በዛሬው ጊዜ በግልጽ እንደሚታየው ሕዝቡ በምርጫ፣ በሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች እንቅስቃሴ፣ በተቃውሞ ሰልፍ እንዲሁም በሠራተኞች ማኅበራት አማካኝነት የሚያሳድረው ተጽዕኖ ይህ የዓለም ኃያል መንግሥት ፖሊሲዎቹን ለማስፈጸም ያለውን ኃይል ያዳክመዋል። w22.07 4 አን. 9-10
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 10
የእኔ ምግብ የላከኝን ፈቃድ ማድረግ . . . ነው።—ዮሐ. 4:34
ለመጠመቅ እያመነታህ ነው? ከሆነ ‘ምን እየጠበቅኩ ነው?’ ብለህ ራስህን መጠየቅህ ጠቃሚ ሊሆን ይችላል። (ሥራ 8:36) ኢየሱስ የአባቱን ፈቃድ ማድረግን ከምግብ ጋር አመሳስሎታል። ለምን? ምግብ መብላታችን ይጠቅመናል። ኢየሱስ፣ ይሖዋ እንድናደርግ የሚያዘን ማንኛውም ነገር ለእኛ ጥቅም እንደሆነ ያውቃል። ይሖዋ ጉዳት ሊያስከትልብን የሚችል ምንም ነገር እንድናደርግ አይፈልግም። ይሖዋ ለአንተ ያለው ፈቃድ መጠመቅን ይጨምራል? አዎ። (ሥራ 2:38) እንግዲያው ይሖዋ እንድትጠመቅ የሰጠህን ትእዛዝ መጠበቅህ አንተኑ እንደሚጠቅምህ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። አንድን ምርጥ የሆነ ምግብ ለመብላት የማታመነታ ከሆነ ለመጠመቅ የምታመነታበት ምን ምክንያት ይኖራል? ምን እየጠበቅክ ነው? ብዙዎች “ገና ዝግጁ አይደለሁም” ብለው ይመልሱ ይሆናል። እርግጥ ራስህን ለይሖዋ ለመወሰንና ለመጠመቅ የምታደርገው ውሳኔ በሕይወትህ ውስጥ ከምታደርጋቸው ውሳኔዎች ሁሉ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ነው። ስለዚህ ዝግጁ ለመሆን ጊዜ ወስዶ በጥንቃቄ ማሰብና ትጋት የተሞላበት ጥረት ማድረግ ይጠይቃል። w23.03 7 አን. 18-20
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 11
ስለ አንድ እንደሚናገር “ለዘርህ” ይላል፤ እሱም ክርስቶስ ነው።—ገላ. 3:16
ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ በተቀባበት ወቅት የሴቲቱ ዘር ዋነኛ ክፍል ሆነ። ኢየሱስ ከሞተና ከተነሳ በኋላ ይሖዋ “የክብርና የሞገስ ዘውድ” ደፋለት፤ እንዲሁም ‘ሥልጣንን ሁሉ በሰማይና በምድር’ ሰጠው። ከተሰጠው ሥልጣን መካከል ‘የዲያብሎስን ሥራ የማፍረስ’ ሥልጣን ይገኝበታል። (ዕብ. 2:7፤ ማቴ. 28:18፤ 1 ዮሐ. 3:8) ይሁንና ይህ ዘር ሁለተኛ ክፍልም አለው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለአይሁዳውያንና ለአሕዛብ ቅቡዓን ክርስቲያኖች የጻፈላቸው ሐሳብ የዘሩን ሁለተኛ ክፍል ማንነት ለማወቅ ይረዳናል፤ እንዲህ ብሏቸዋል፦ “የክርስቶስ ከሆናችሁ በእርግጥም የአብርሃም ዘር ናችሁ፤ በተስፋውም ቃል መሠረት ወራሾች ናችሁ።” (ገላ. 3:28, 29) ይሖዋ አንድን ክርስቲያን በመንፈስ ቅዱስ ሲቀባው ያ ሰው የሴቲቱ ዘር ክፍል ይሆናል። በመሆኑም የሴቲቱ ዘር ኢየሱስን እና አብረውት የሚገዙትን 144,000 ቅቡዓን ያካትታል። (ራእይ 14:1) ሁሉም አባታቸውን ይሖዋ አምላክን ይመስላሉ። w22.07 16 አን. 8-9
ዓርብ፣ ሚያዝያ 12
ሕይወቴን ተጸየፍኳት፤ በሕይወት መቀጠል አልፈልግም።—ኢዮብ 7:16
በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት የተለያዩ ፈተናዎች እንደሚያጋጥሙን እንጠብቃለን። (2 ጢሞ. 3:1) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ሲያጋጥመን በጭንቀት ልንዋጥና ሁኔታው ከአቅማችን በላይ እንደሆነብን ሊሰማን ይችላል። በተለይም ፈተናዎቹ ከተከታተሉብን ወይም በአንድ ጊዜ ተደራርበው ከመጡብን ሁኔታው ይበልጥ ሊከብደን ይችላል። ያም ቢሆን፣ ይሖዋ በትኩረት እንደሚመለከተን እንዲሁም በእሱ እርዳታ የትኛውንም ፈተና በልበ ሙሉነት መጋፈጥ እንደምንችል አትዘንጋ። ይሖዋ ታማኝ ሰው የሆነውን ኢዮብን እንዴት እንደረዳው እንመልከት። ኢዮብ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ከባባድ ፈተናዎች ደርሰውበታል። ኢዮብ ከብቶቹ እንዳለቁ፣ አገልጋዮቹ እንደተገደሉ፣ ይባስ ብሎም የሚወዳቸው ልጆቹ በሙሉ እንደሞቱ በአንድ ቀን ውስጥ ሰማ። (ኢዮብ 1:13-19) ኢዮብ ከደረሰበት መሪር ሐዘን ገና ሳያገግም ከፍተኛ ሥቃይ የሚያስከትልና አካላዊ ገጽታውን የሚያበላሽ ከባድ ሕመም ያዘው። (ኢዮብ 2:7) ይሖዋ ኢዮብን በትኩረት ይመለከተው ነበር። ይሖዋ ኢዮብን ስለሚወደው ያጋጠሙትን ፈተናዎች በጽናት ለመቋቋም የሚያስችል እርዳታ ሰጥቶታል። w22.08 11 አን. 8-10
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 13
ይሖዋ የሚወዳቸውን ይገሥጻል።—ዕብ. 12:6
ተግሣጽ ስሜታችንን ሊጎዳው ይችላል። ተግሣጹ ለእኛ እንደማይሠራና ከመጠን ያለፈ እንደሆነ ልናስብ እንችላለን። ይህ ደግሞ አንድ ውድ ነገር ያሳጣናል፤ ተግሣጹ የይሖዋ ፍቅር መገለጫ እንደሆነ ማየት ይሳነናል። (ዕብ. 12:5, 11) ስለዚህ ተግሣጽን ተቀበል፤ አስፈላጊውን ማስተካከያም አድርግ። ኢየሱስ ለጴጥሮስ በሌሎቹ ሐዋርያት ፊት በተደጋጋሚ እርማት ሰጥቶታል። (ማር. 8:33፤ ሉቃስ 22:31-34) በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ ተሸማቅቆ መሆን አለበት! ያም ቢሆን ጴጥሮስ ለኢየሱስ ታማኝ ሆኖ ቀጥሏል። ተግሣጹን በመቀበል ከስህተቱ ተምሯል። በዚህም የተነሳ ይሖዋ ጴጥሮስን ለታማኝነቱ ክሶታል፤ እንዲሁም በጉባኤው ውስጥ ትላልቅ ኃላፊነቶች ሰጥቶታል። (ዮሐ. 21:15-17፤ ሥራ 10:24-33፤ 1 ጴጥ. 1:1) ተግሣጽ ከሚያሳድርብን የኀፍረት ስሜት አሻግረን ስናይ፣ እርማቱን ስንቀበል እንዲሁም አስፈላጊውን ማስተካከያ ስናደርግ ራሳችንንም ሆነ ሌሎችን እንጠቅማለን። እንዲህ ስናደርግ ለይሖዋና ለወንድሞቻችን ይበልጥ ጠቃሚ እንሆናለን። w22.11 21-22 አን. 6-7
እሁድ፣ ሚያዝያ 14
[ይስሐቅን] የሚቃጠል መባ አድርገህ አቅርበው።—ዘፍ. 22:2
አብርሃም፣ ይሖዋ መቼም ቢሆን ጽድቅ ወይም ፍቅር የጎደለው ነገር እንደማያደርግ ያውቅ ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው አብርሃም፣ ይሖዋ የሚወደውን ልጁን ይስሐቅን ከሞት እንኳ ሳይቀር ሊያስነሳው እንደሚችል ተገንዝቦ ነበር። (ዕብ. 11:17-19) ደግሞም ይሖዋ ከይስሐቅ አንድ ብሔር እንደሚገኝ ቃል ገብቶ ነበር፤ ሆኖም በዚያ ወቅት ይስሐቅ ገና ልጅ አልወለደም። አብርሃም ይሖዋን ይወደው ነበር፤ በመሆኑም አባቱ ጽድቅ የሆነውን ነገር እንደሚያደርግ ተማምኗል። በጣም ከባድ ቢሆንም በእምነት ታዘዘ። (ዘፍ. 22:1-12) የአብርሃምን ምሳሌ መከተል የምንችለው እንዴት ነው? እኛም እንደ እሱ ስለ ይሖዋ መማራችንን መቀጠል ይኖርብናል። እንዲህ ስናደርግ ወደ እሱ ይበልጥ እንቀርባለን፤ ለእሱ ያለን ፍቅርም ያድጋል። (መዝ. 73:28) ሕሊናችን ስለሚሠለጥን የአምላክን አስተሳሰብ ማንጸባረቅ ይጀምራል። (ዕብ. 5:14) በውጤቱም፣ አንድ ሰው መጥፎ ነገር እንድናደርግ ሲፈትነን ፈቃደኛ አንሆንም። አባታችንን የሚያሳዝንና ከእሱ ጋር ያለንን ዝምድና የሚያበላሽ ማንኛውንም ነገር ማድረግ ስናስበው እንኳ ይዘገንነናል። w22.08 28-29 አን. 11-12
ሰኞ፣ ሚያዝያ 15
በሰው ልብ ውስጥ ያለ ጭንቀት ልቡ እንዲዝል ያደርገዋል፤ መልካም ቃል ግን ደስ ያሰኘዋል።—ምሳሌ 12:25
ሐዋርያው ጳውሎስና በርናባስ ልስጥራን፣ ኢቆንዮንን እና አንጾኪያን በድጋሚ በጎበኙበት ወቅት “በየጉባኤው ሽማግሌዎችን ሾሙላቸው።” (ሥራ 14:21-23) እነዚህ ሽማግሌዎች ለጉባኤዎቹ የመጽናኛ ምንጭ እንደሆኑላቸው ምንም ጥያቄ የለውም። በዛሬው ጊዜ ያሉ ሽማግሌዎችም ለወንድሞች የመጽናኛ ምንጭ ናቸው። ሽማግሌዎች፣ የሚያበረታታ “መልካም ቃል” መስማት የሚያስፈልጋቸውን ክርስቲያኖች ለመርዳት ንቁ ሁኑ። ጳውሎስ በይሖዋ እርዳታ ፈተናዎችን መቋቋም የቻለ “ታላቅ የምሥክሮች ደመና” እንዳለ የእምነት ባልንጀሮቹን አስታውሷቸዋል። (ዕብ. 12:1) ጳውሎስ ወንድሞችና እህቶች፣ ባለፉት ዘመናት የተለያዩ ዓይነት ፈተናዎችን በጽናት የተቋቋሙ የአምላክ አገልጋዮችን የሕይወት ታሪክ መስማታቸው ድፍረት እንደሚሰጣቸውና ‘በሕያው አምላክ ከተማ’ ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን እንዲቀጥሉ እንደሚረዳቸው ተገንዝቦ ነበር። (ዕብ. 12:22) በዛሬው ጊዜም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይሖዋ ጌድዮንን፣ ባርቅን፣ ዳዊትን፣ ሳሙኤልንና ሌሎችን እንዴት እንደረዳቸው አንብቦ ያልተበረታታ ማን አለ?—ዕብ. 11:32-35፤ w22.08 21-22 አን. 5-6
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 16
እያንዳንዳቸው እንደየሥራቸው ፍርድ ተሰጣቸው።—ራእይ 20:13
ትንሣኤ ያገኙት ሰዎች “እንደየሥራቸው” ፍርድ ይሰጣቸዋል ሲባል ምን ማለት ነው? የሚፈረድባቸው ከመሞታቸው በፊት በሠሩት ሥራ መሠረት ነው? አይደለም! ሲሞቱ ኃጢአታቸው እንደተሰረዘላቸው አስታውሱ። ከዚህ አንጻር “እንደየሥራቸው” የሚለው ቃል ከመሞታቸው በፊት የሠሩትን ሥራ የሚያመለክት ሊሆን አይችልም። ከዚህ ይልቅ በአዲሱ ሥርዓት ሥልጠና ካገኙ በኋላ የሚሠሩትን ሥራ የሚያመለክት መሆን አለበት። እንደ ኖኅ፣ ሳሙኤል፣ ዳዊትና ዳንኤል ያሉ ታማኝ ሰዎች እንኳ ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ መማርና በእሱ መሥዋዕት ማመን ይኖርባቸዋል። እነዚህ ሰዎች እንኳ ይህን ሁሉ ነገር መማር የሚጠበቅባቸው ከሆነ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎችማ ብዙ ትምህርት እንደሚያስፈልጋቸው ምንም ጥያቄ የለውም! ይህን ግሩም አጋጣሚ የማይቀበሉ ሰዎች ምን ይጠብቃቸዋል? ራእይ 20:15 “በሕይወት መጽሐፍ ላይ ተጽፎ ያልተገኘ ሁሉ ወደ እሳቱ ሐይቅ ተወረወረ” ይላል። አዎ፣ ዘላለማዊ ጥፋት ይደርስባቸዋል። እንግዲያው ስማችን በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ እንዲሰፍርና ሳይሰረዝ እንዲቆይ ማድረጋችን ምንኛ አስፈላጊ ነው! w22.09 19 አን. 17-19
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 17
በአምላክም ሆነ በሰው ፊት ንጹሕ ሕሊና [ያዙ]።—ሥራ 24:16
ከጤናችንና ከምንመርጠው የሕክምና ዓይነት ጋር የተያያዙትን አብዛኞቹን ውሳኔዎች የምናደርገው በመጽሐፍ ቅዱስ የሠለጠነ ሕሊናችንን ተጠቅመን ነው። (1 ጢሞ. 3:9) ውሳኔዎችን ስናደርግና ስላደረግነው ውሳኔ ከሌሎች ጋር ስንነጋገር በፊልጵስዩስ 4:5 ላይ የሚገኘውን “ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን” የሚለውን መሠረታዊ ሥርዓት መከተላችን ተገቢ ነው። ምክንያታዊ ከሆንን ስለ አካላዊ ጤንነታችን ከልክ በላይ አንጨነቅም። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከእኛ የተለየ ውሳኔ ቢያደርጉም እንኳ እንወዳቸዋለን እንዲሁም እናከብራቸዋለን። (ሮም 14:10-12) ሕይወታችንን ከአደጋ በመጠበቅና ለይሖዋ ምርጣችንን በመስጠት የሕይወት ምንጭ ለሆነው ለእሱ አድናቆታችንን እናሳያለን። (ራእይ 4:11) በዚህ ሥርዓት ውስጥ እስካለን ድረስ ከሕመምና ከአደጋ ማምለጥ አንችልም። የፈጣሪያችን ዓላማ ግን በዚህ ዓይነት ሁኔታ እንድንኖር አይደለም። በቅርቡ ሥቃይና ሞት የሌለበት ዘላለማዊ ሕይወት ይሰጠናል። (ራእይ 21:4) እስከዚያው ግን በሕይወት ኖረን አፍቃሪውን አባታችንን ይሖዋን ማገልገላችን እንዴት ያለ ትልቅ መብት ነው! w23.02 25 አን. 17-18
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 18
መንግሥትህ ተከፈለ፤ ለሜዶናውያንና ለፋርሳውያን ተሰጠ።—ዳን. 5:28
ይሖዋ ‘ከበላይ ባለሥልጣናት’ የበለጠ ሥልጣን እንዳለው በግልጽ አሳይቷል። (ሮም 13:1) እስቲ ሦስት ምሳሌዎችን እንመልከት። የግብፁ ፈርዖን የይሖዋን ሕዝቦች በባርነት የገዛ ሲሆን እነሱን ለመልቀቅ ፈቃደኛ እንዳልሆነ በተደጋጋሚ ገልጿል። ሆኖም አምላክ ሕዝቡን ነፃ አውጥቷቸዋል፤ ፈርዖንንም በቀይ ባሕር አስጥሞታል። (ዘፀ. 14:26-28፤ መዝ. 136:15) የባቢሎኑ ንጉሥ ቤልሻዛር ድግስ ባዘጋጀበት ምሽት ‘በሰማያት ጌታ ላይ ታበየ’፤ እንዲሁም ከይሖዋ ይልቅ ‘ከብርና ከወርቅ የተሠሩ አማልክትን አወደሰ።’ (ዳን. 5:22, 23) ይሁን እንጂ አምላክ ይህን ትዕቢተኛ ሰው አዋረደው። “በዚያኑ ሌሊት” ቤልሻዛር ተገደለ። መንግሥቱም ለሜዶናውያንና ለፋርሳውያን ተሰጠ። (ዳን. 5:30, 31) የፓለስቲናው ንጉሥ ቀዳማዊ ሄሮድስ አግሪጳ፣ ሐዋርያው ያዕቆብን ካስገደለ በኋላ ሐዋርያው ጴጥሮስንም ሊገድለው በማሰብ አሰረው። ሆኖም ይሖዋ ሄሮድስ ዕቅዱን እንዲያሳካ አልፈቀደለትም፤ ‘የይሖዋ መልአክ ቀሰፈውና’ ሞተ።—ሥራ 12:1-5, 21-23፤ w22.10 15 አን. 12
ዓርብ፣ ሚያዝያ 19
እሰማችኋለሁ።—ኤር. 29:12
ቃሉን በማንበብና በማሰላሰል ደግሞ አምላክን ማዳመጥ እንችላለን። ይሖዋ የጥንት ታማኞቹን እንዴት እንደተንከባከበ ስናነብ ተስፋችን ይበልጥ ይጠናከራል። “በምናሳየው ጽናትና ከቅዱሳን መጻሕፍት በምናገኘው መጽናኛ ተስፋ ይኖረን ዘንድ [በአምላክ ቃል ውስጥ] የተጻፈው ነገር ሁሉ ለእኛ ትምህርት እንዲሆን ተጽፏልና።” (ሮም 15:4) ይሖዋ ቃሉን እንደጠበቀ በሚገልጹ ዘገባዎች ላይ አሰላስሉ። አምላክ ለአብርሃምና ለሣራ ያደረገላቸውን ነገር እንደ ምሳሌ እንመልከት። ልጅ መውለድ የማይችሉበት ዕድሜ ላይ ደርሰው ነበር። ሆኖም አምላክ ልጅ እንደሚወልዱ ቃል ገባላቸው። (ዘፍ. 18:10) ታዲያ አብርሃም ምን አደረገ? መጽሐፍ ቅዱስ “የብዙ ብሔራት አባት እንደሚሆን በተሰጠው ተስፋ አምኗል” ይላል። (ሮም 4:18) ከሰዎች አመለካከት አንጻር ሁኔታው ተስፋ የሌለው ቢመስልም አብርሃም ይሖዋ ቃሉን እንደሚፈጽም እርግጠኛ ነበር። ይሖዋ ይህን ታማኝ ሰው አላሳፈረውም። (ሮም 4:19-21) እንዲህ ያሉ ዘገባዎች፣ ይሖዋ ምንጊዜም ቃሉን እንደሚጠብቅ ያረጋግጡልናል። w22.10 26-27 አን. 13-14
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 20
በገዛ ዓይኖችህም ታላቁን አስተማሪህን ታያለህ።—ኢሳ. 30:20
አይሁዳውያን ከግዞት ነፃ ሲወጡ ይህ ትንቢት ተፈጽሟል። ይሖዋ ታላቅ አስተማሪ ሆኖላቸዋል፤ በእሱ አመራር ሥር ሕዝቡ ንጹሕ አምልኮን መልሰው ማቋቋም ችለዋል። በዛሬው ጊዜም ይሖዋ ታላቅ አስተማሪ ስለሆነልን አመስጋኞች ነን። ኢሳይያስ እኛ እንደ ተማሪዎች እንደሆንንና ይሖዋ እንደሚያስተምረን ሲገልጽ “በገዛ ዓይኖችህም ታላቁን አስተማሪህን ታያለህ” ብሏል። በዚህ አገላለጽ መሠረት አስተማሪው ከተማሪዎቹ ፊት ቆሟል። በዛሬው ጊዜ ይሖዋ የሚያስተምረን በመሆኑ በእጅጉ ተባርከናል። ለመሆኑ ይሖዋ የሚያስተምረን እንዴት ነው? በድርጅቱ አማካኝነት ነው። ከይሖዋ ድርጅት ለምናገኘው ግልጽ መመሪያ ምንኛ አመስጋኞች ነን! በስብሰባዎች እንዲሁም በጽሑፎቻችን፣ በብሮድካስቶችና በሌሎች መንገዶች የምናገኘው ትምህርት አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመን በደስታ ለመጽናት ይረዳናል። w22.11 10 አን. 8-9
እሁድ፣ ሚያዝያ 21
የዚህ ሥርዓት መደምደሚያ ምልክት . . . ምንድን ነው?—ማቴ. 24:3
ኢየሱስ ስለ አይሁድ ሥርዓት መጨረሻና እኛ ስለምንኖርበት ‘ስለዚህ ሥርዓት መደምደሚያ’ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “ስለዚያ ቀን ወይም ሰዓት ከአብ በቀር በሰማይ ያሉ መላእክትም ሆኑ ወልድ፣ ማንም አያውቅም።” ከዚያም ሁሉም ደቀ መዛሙርቱ ‘ዘወትር ነቅተው መጠበቅ’ እንዳለባቸው አሳሰበ። (ማር. 13:32-37) በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያን የሆኑ ክርስቲያኖች ነቅተው መጠበቅ ነበረባቸው፤ ይህ የሕይወትና የሞት ጉዳይ ነበር። ኢየሱስ ተከታዮቹን እንዲህ ብሏቸዋል፦ “ኢየሩሳሌም በጦር ሠራዊት ተከባ ስታዩ መጥፊያዋ እንደቀረበ እወቁ።” ክርስቲያኖች ልክ ይህን ሲያዩ የኢየሱስን ማስጠንቀቂያ በመስማት “ወደ ተራሮች መሸሽ” ነበረባቸው። (ሉቃስ 21:20, 21) ለዚህ ማስጠንቀቂያ ትኩረት የሰጡ ሰዎች ሮማውያን ኢየሩሳሌምን ባጠፉበት ጊዜ ሕይወታቸውን ማትረፍ ችለዋል። ዛሬ የምንኖረው የዚህ ክፉ ሥርዓት ማብቂያ በተቃረበበት ጊዜ ላይ ነው። ስለዚህ እኛም የማስተዋል ስሜታችንን መጠበቅና ንቁ ሆነን መኖር ያስፈልገናል። w23.02 14 አን. 1-2፤ 16 አን. 3
ሰኞ፣ ሚያዝያ 22
የእውነት አምላክ የሆንከው ይሖዋ።—መዝ. 31:5
ይሖዋ አገልጋዮቹን ሐቀኛና ጻድቅ እንዲሆኑ ያስተምራቸዋል። ይህም ለራሳቸው ይበልጥ አክብሮት እንዲኖራቸውና ውስጣዊ ሰላም እንዲያገኙ ይረዳቸዋል። (ምሳሌ 13:5, 6) አንተ መጽሐፍ ቅዱስን ስታጠና የዚህን እውነተኝነት አልተመለከትክም? የይሖዋ መንገዶች ለሰው ዘር በአጠቃላይም ሆነ ለአንተ በግለሰብ ደረጃ ከሁሉ የተሻሉ እንደሆኑ ተምረሃል። (መዝ. 77:13) ስለዚህ የአምላክን የጽድቅ መሥፈርቶች እንደምትደግፍ ማሳየት ትፈልጋለህ። (ማቴ. 6:33) ለእውነት ጥብቅና የመቆምና በአምላካችን በይሖዋ ላይ የተሰነዘረውን ክስ ውድቅ የማድረግ ፍላጎት አለህ። ታዲያ ይህን ማድረግ የምትችለው እንዴት ነው? የምትመርጠው ሕይወት በተዘዋዋሪ መንገድ እንዲህ እንደምትል የሚያሳይ ሊሆን ይችላል፦ “የሰይጣንን ውሸት እቃወማለሁ፤ ለእውነት ጥብቅና እቆማለሁ። የይሖዋን ሉዓላዊ ገዢነት እቀበላለሁ፤ እንዲሁም እሱ ትክክል ነው የሚለውን ነገር ማድረግ እፈልጋለሁ።” እንዲህ ያለ አቋም እንደያዝክ ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ወደ ይሖዋ በመጸለይና ራስህን ለእሱ በመወሰን ከዚያም በጥምቀት አማካኝነት ይህን ውሳኔህን በሕዝብ ፊት ይፋ በማድረግ ነው። ለእውነትና ለጽድቅ ያለህ ፍቅር እንድትጠመቅ የሚያነሳሳህ አንዱ ጠንካራ ምክንያት ነው። w23.03 3 አን. 4-5
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 23
ልባችሁ አይረበሽ፤ በፍርሃትም አይዋጥ።—ዮሐ. 14:27
ዓለም ጨርሶ የማያውቀው የሰላም ዓይነት አለ። እሱም “የአምላክ ሰላም” ይኸውም ከሰማዩ አባታችን ጋር ውድ ዝምድና በመመሥረት የሚገኝ የመረጋጋት ስሜት ነው። የአምላክ ሰላም ሲኖረን የደህንነት ስሜት ይሰማናል። (ፊልጵ. 4:6, 7) እሱን ከሚወዱ ሰዎች ጋር የቅርብ ወዳጅነት ይኖረናል። እንዲሁም ‘ከሰላም አምላክ’ ጋር የቅርብ ዝምድና እንመሠርታለን። (1 ተሰ. 5:23) አባታችንን የምናውቀው፣ የምንታመንበትና የምንታዘዘው ከሆነ፣ መከራ ሲያጋጥመን የአምላክ ሰላም የተጨነቀውን ልባችንን ያረጋጋልናል። እንደ ወረርሽኝ፣ የተፈጥሮ አደጋ፣ ሕዝባዊ ዓመፅ ወይም ስደት ያለ መከራ ሲያጋጥመን በእርግጥ የአምላክን ሰላም ማግኘት እንችላለን? እነዚህ ችግሮች በፍርሃት እንድንዋጥ ሊያደርጉን ይችላሉ። ደስ የሚለው፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ያለውን የኢየሱስን ምክር ተግባራዊ አድርገዋል። ከባድ መከራ ቢያጋጥማቸውም በይሖዋ እርዳታ ሰላም ማግኘት ችለዋል። w22.12 16 አን. 1-2
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 24
በመንፈስ የምትቃጠሉ ሁኑ። ይሖዋን እንደ ባሪያ አገልግሉ።—ሮም 12:11
በሕይወታችን የሚያጋጥሙንን ነገሮች በሙሉ መቆጣጠር አንችልም። በመሆኑም በይሖዋ ዘንድ ያለንን ዋጋ ባለን የአገልግሎት መብት መለካት አይኖርብንም፤ እንዲሁም ያለንን መብት ሌሎች ካላቸው መብት ጋር ማነጻጸር የለብንም። (ገላ. 6:4) ይበልጥ ማገልገል የምንችልባቸውን መንገዶች መፈለጋችን በጣም አስፈላጊ ነው። ቀላል ሕይወት በመምራትና አላስፈላጊ ዕዳ ውስጥ ባለመግባት አዳዲስ የአገልግሎት መብቶችን ለመቀበል ራስህን ማዘጋጀት ትችላለህ። የረጅም ጊዜ ግብህ ላይ ለመድረስ የሚረዱህን የአጭር ጊዜ ግቦች አውጣ። ለምሳሌ የረጅም ጊዜ ግብህ የዘወትር አቅኚ መሆን ከሆነ አሁን ላልተወሰነ ጊዜ በረዳት አቅኚነት ማገልገል ትችል ይሆን? ወይም ደግሞ ግብህ የጉባኤ አገልጋይ መሆን ከሆነ በመስክ አገልግሎት ላይ ያለህን እንቅስቃሴ ማሳደግ ትችል ይሆን? አሁን ላይ የምታካብተው ተሞክሮ ወደፊት ተጨማሪ የአገልግሎት መብቶችን እንድታገኝ መንገድ ሊከፍትልህ ይችላል። የተሰጠህን ማንኛውንም ኃላፊነት በትጋት ለመወጣት ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። w22.04 26 አን. 16-17
ሐሙስ፣ ሚያዝያ 25
ይሖዋ ድምፄን፣ እርዳታ ለማግኘት የማቀርበውን ልመና ስለሚሰማ እወደዋለሁ።—መዝ. 116:1
ይሖዋ በሕይወታችን ውስጥ የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች እንድንወጣና በቅዱስ አገልግሎታችን ደስታ እንድናገኝ ይረዳናል። የሚያሳስበንን ጉዳይ አስመልክቶ ወደ ይሖዋ ስንጸልይ እሱ የሚያደርግልን የመጀመሪያው ነገር ፈተናውን ለመቋቋም የሚያስችል ኃይል መስጠት ሊሆን ይችላል። የደረሰብን መከራ በጠበቅነው ጊዜ ካላበቃ ደግሞ ይሖዋ ለመጽናት የሚያስችል ኃይል እንዲሰጠን በተደጋጋሚ መጸለይ ሊያስፈልገን ይችላል። ደግሞም እንዲህ እንድናደርግ ይሖዋ ጋብዞናል። ኢሳይያስ “[ለይሖዋ] ምንም እረፍት አትስጡት” ማለቱ ይህን ያሳያል። (ኢሳ. 62:7) ይህ ሐሳብ ምን ትርጉም አለው? ይሖዋን እረፍት እንደነሳነው እስኪቆጠር ድረስ በተደጋጋሚ ልንለምነው ይገባል ማለት ነው። ኢሳይያስ የተጠቀመበት አገላለጽ፣ ኢየሱስ በሉቃስ 11:8-10, 13 ላይ ጸሎትን አስመልክቶ የተናገራቸውን ምሳሌዎች ያስታውሰናል። እዚህ ላይ ኢየሱስ፣ ይሖዋን መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠን ‘ደጋግመን እንድንለምነው’ አበረታቶናል። በተጨማሪም ጥሩ ውሳኔ ለማድረግ የሚረዳ አመራር እንዲሰጠን ይሖዋን ልንለምነው እንችላለን። w22.11 8 አን. 1፤ 9 አን. 6-7
ዓርብ፣ ሚያዝያ 26
በብዙ መከራ አልፈን ወደ አምላክ መንግሥት መግባት አለብን።—ሥራ 14:22
እናንተም ሆናችሁ ቤተሰቦቻችሁ ለስደት ከአሁኑ መዘጋጀት ትችላላችሁ። ሊያጋጥሟችሁ የሚችሉትን መጥፎ ነገሮች እያሰባችሁ አትብሰልሰሉ። ከዚህ ይልቅ ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ወዳጅነት አጠናክሩ፤ ልጆቻችሁም እንደዚያው እንዲያደርጉ እርዷቸው። አልፎ አልፎ ጭንቀት የሚሰማችሁ ከሆነ ልባችሁን በይሖዋ ፊት አፍስሱ። (መዝ. 62:7, 8) በይሖዋ ለመተማመን የሚያነሳሷችሁን ምክንያቶች በቤተሰብ ሆናችሁ ተወያዩ። ለአደጋ አስቀድሞ መዘጋጀት ልጆቻችሁን እንደሚጠቅማቸው ተመልክተናል። ከስደት ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አስቀድማችሁ መዘጋጀታችሁና በይሖዋ መታመናችሁ በስደት ወቅት ልጆቻችሁ ድፍረትና ሰላም እንዲኖራቸው ይረዳቸዋል። የአምላክ ሰላም የደህንነት ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል። (ፊልጵ. 4:6, 7) በአሁኑ ጊዜ በሽታ፣ አደጋ ወይም ስደት ሊደርስብን ቢችልም ይሖዋ በዚህ ሰላም አማካኝነት ልባችንን ያረጋጋልናል። ትጉ የሆኑ ሽማግሌዎችን ተጠቅሞ ይንከባከበናል። በተጨማሪም ለሁላችንም እርስ በርስ የመረዳዳት መብት ሰጥቶናል። በአሁኑ ጊዜ የምናገኘው ሰላም ‘ታላቁን መከራ’ ጨምሮ ወደፊት የሚያጋጥሙንን ከባድ ፈተናዎች ለመጋፈጥ ያዘጋጀናል።—ማቴ. 24:21፤ w22.12 27 አን. 17-18
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 27
እኔ የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ልጠራ ነው።—ማቴ. 9:13
ቀደም ሲል በፈጸምናቸው ከባድ ኃጢአቶች ምክንያት የሚሰማንን የጥፋተኝነት ስሜት ለማስወገድ ጥረት ማድረግ ይኖርብናል። እርግጥ የኢየሱስን ቤዛዊ መሥዋዕት ‘ሆን ብለን በኃጢአት ጎዳና ለመመላለስ’ ሰበብ ልናደርገው እንደማይገባ ግልጽ ነው። (ዕብ. 10:26-31) ሆኖም ለፈጸምነው ከባድ ኃጢአት ከልባችን ንስሐ ከገባን፣ ይሖዋ የሚሰጠውን እርዳታ ለማግኘት ጥረት ካደረግን እንዲሁም ምግባራችንን ካስተካከልን ይቅርታው ብዙ የሆነው አምላካችን ይቅር እንዳለን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ኢሳ. 55:7፤ ሥራ 3:19) የኢየሱስ ቤዛዊ መሥዋዕት ኃጢአታችንን በሙሉ ለመሸፈን የሚያስችል ኃይል አለው፤ በገነት ውስጥ የመኖር ተስፋ እንዲኖረንም አድርጓል። በዚያ ሕይወት በፍጹም አሰልቺ አይሆንም። ሁልጊዜ ደስ ከሚሉ ሰዎች ጋር ጊዜ ማሳለፍ እንዲሁም ትርጉም ያለው ሥራ መሥራት እንችላለን። ከሁሉ በላይ ደግሞ፣ በየቀኑ የሰማዩን አባታችንን ይበልጥ ማወቅ እንዲሁም እሱ ባደረገልን ዝግጅቶች መደሰት እንችላለን። ስለ እሱ የምንማረው ነገር አያልቅም። ስለ ፍጥረታቱም ብዙ የምንማረው ነገር ይኖራል። w22.12 13 አን. 17, 19
እሁድ፣ ሚያዝያ 28
በአንተና በሴቲቱ መካከል . . . ጠላትነት እንዲኖር አደርጋለሁ።—ዘፍ. 3:15
“ሴቲቱ” ሔዋን ልትሆን አትችልም። ትንቢቱ የሴቲቱ ዘር የእባቡን ራስ ‘እንደሚጨፈልቀው’ ይናገራል። እባቡ ሰይጣን ነው። ሰይጣን ደግሞ መንፈሳዊ ፍጡር ስለሆነ የሔዋን ዘር የሆነ ማንኛውም ፍጹም ያልሆነ ሰው እሱን ሊጨፈልቀው አይችልም። ታዲያ ሰይጣን የሚጠፋው እንዴት ነው? በዘፍጥረት 3:15 ላይ የተጠቀሰችው ሴት ማንነት በመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ላይ ተገልጿል። (ራእይ 12:1, 2, 5, 10) ሴቲቱ በምድር ላይ ያለች ሴት አይደለችም። ጨረቃ ከእግሯ ሥር አለች፤ በራሷም ላይ 12 ከዋክብት ያሉት አክሊል አድርጋለች። ሴቲቱ አስደናቂ ልጅ ማለትም የአምላክን መንግሥት ወልዳለች። መንግሥቱ ያለው በሰማይ ነው፤ በመሆኑም ሴቲቱም ያለችው በሰማይ ላይ መሆን አለበት። ሴቲቱ ታማኝ መንፈሳዊ ፍጥረታትን ያቀፈውን የይሖዋን ድርጅት ሰማያዊ ክፍል ታመለክታለች። (ገላ. 4:26) የአምላክ ቃል የሴቲቱ ዘር ዋነኛ ክፍል ማን እንደሆነ ለማወቅም ይረዳናል። የዘሩ ዋነኛ ክፍል የሚመጣው ከአብርሃም የትውልድ መስመር እንደሆነ ተገልጿል።—ዘፍ. 22:15-18፤ w22.07 15-16 አን. 6-8
ሰኞ፣ ሚያዝያ 29
እንደ ሰው ቃል ሳይሆን እንደ አምላክ ቃል አድርጋችሁ ተቀብላችሁታል፤ ደግሞም የአምላክ ቃል ነው።—1 ተሰ. 2:13
ይሖዋ ስጦታ አድርጎ የሰጠን መጽሐፍ ቅዱስ በእሱ ጥበብ የተሞላ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ምክር በሰዎች ላይ በጎ ተጽዕኖ ያሳድራል። መጽሐፍ ቅዱስ የሰዎችን ሕይወት ይለውጣል። ሙሴ የመጀመሪያዎቹን የመጽሐፍ ቅዱስ መጻሕፍት በጻፈበት ወቅት የአምላክ ሕዝቦች ለሆኑት ለእስራኤላውያን “ይህ ቃል ለእናንተ ሕይወታችሁ እንጂ እንዲሁ ባዶ ቃል አይደለም” በማለት ነግሯቸዋል። (ዘዳ. 32:47) ቅዱሳን መጻሕፍት የሚሰጡትን መመሪያ የሚታዘዙ ሰዎች ስኬታማና ደስተኛ ሕይወት መምራት ይችላሉ። (መዝ. 1:2, 3) የአምላክ ቃል ከተጻፈ ረጅም ዘመናት ያለፉ ቢሆንም የሰዎችን ሕይወት የመለወጥ ኃይሉን አላጣም። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኙት ጥበብ ያዘሉ መሠረታዊ ሥርዓቶች ጊዜ የሚሽራቸው አይደሉም፤ በየትኛውም ዘመን ለሚኖሩ ሰዎች ጠቃሚ መሆናቸውም ተረጋግጧል። ይህን ቅዱስ መጽሐፍ ስናነብና ባነበብነው ላይ ስናሰላስል መጽሐፉን ያጻፈው አካል ኃያል የሆነውን ቅዱስ መንፈሱን በመጠቀም ምክሮቹን በሕይወታችን ተግባራዊ ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንድናስተውል ይረዳናል። (መዝ. 119:27፤ ሚል. 3:16፤ ዕብ. 4:12) መጽሐፍ ቅዱስን ያጻፈው ምንጊዜም ሕያው የሆነው አምላክ ሊረዳን ዝግጁ ነው። ይህን ማወቃችን አዘውትረን እንድናነብ አያነሳሳንም? w23.02 3 አን. 5-6
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 30
ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ጥፋት ያደርሳል።—ዳን. 8:24
ራእይ ምዕራፍ 13 እንደሚነግረን ይህ ሰባተኛ ራስ ማለትም የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል በአውሬ ተመስሏል። ይህ አውሬ “እንደ በግ ሁለት ቀንዶች ነበሩት፤ ሆኖም እንደ ዘንዶ መናገር ጀመረ።” ይህ አውሬ “[በሰው ልጆች] ፊት ታላላቅ ምልክቶችን ይፈጽማል፤ እሳትንም እንኳ ከሰማይ ወደ ምድር ያወርዳል።” (ራእይ 13:11-15) ራእይ ምዕራፍ 16 እና ምዕራፍ 19 ላይ ይህ አውሬ “ሐሰተኛው ነቢይ” ተብሎ ተገልጿል። (ራእይ 16:13፤ 19:20) ዳንኤልም ስለ አንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃይል ተመሳሳይ ነገር ገልጿል፤ “አሰቃቂ ጥፋት ያደርሳል” ብሏል። (ዳን. 8:19, 23, 24 ግርጌ) በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት የሆነውም ይህ ነው። ለዚህ ጦርነት ማብቃት ወሳኝ ሚና የተጫወቱት ሁለቱ የአቶሚክ ቦምቦች የብሪታንያና የአሜሪካ ሳይንቲስቶች የሥራ ውጤት ናቸው። የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ‘እሳት ከሰማይ ወደ ምድር ያወረደ’ ያህል ነበር። w22.05 10 አን. 9