የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es24 ገጽ 47-57
  • ግንቦት

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ግንቦት
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2024
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 1
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 2
  • ዓርብ፣ ግንቦት 3
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 4
  • እሁድ፣ ግንቦት 5
  • ሰኞ፣ ግንቦት 6
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 7
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 8
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 9
  • ዓርብ፣ ግንቦት 10
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 11
  • እሁድ፣ ግንቦት 12
  • ሰኞ፣ ግንቦት 13
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 14
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 15
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 16
  • ዓርብ፣ ግንቦት 17
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 18
  • እሁድ፣ ግንቦት 19
  • ሰኞ፣ ግንቦት 20
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 21
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 22
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 23
  • ዓርብ፣ ግንቦት 24
  • ቅዳሜ፣ ግንቦት 25
  • እሁድ፣ ግንቦት 26
  • ሰኞ፣ ግንቦት 27
  • ማክሰኞ፣ ግንቦት 28
  • ረቡዕ፣ ግንቦት 29
  • ሐሙስ፣ ግንቦት 30
  • ዓርብ፣ ግንቦት 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2024
es24 ገጽ 47-57

ግንቦት

ረቡዕ፣ ግንቦት 1

ከዚህ በኋላ አየሁ፤ . . . ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎች የተውጣጡ አንድም ሰው ሊቆጥራቸው የማይችል እጅግ ብዙ ሕዝብ [ነበሩ]።—ራእይ 7:9

ዮሐንስ የሰማዩን ቡድን ካየ በኋላ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ተመለከተ። ከ144,000ዎቹ በተቃራኒ የእጅግ ብዙ ሕዝብ አባላት ሊቆጠሩ አይችሉም። ስለ እነሱ ምን የምናውቀው ነገር አለ? ዮሐንስ እንዲህ ተብሏል፦ “እነዚህ ታላቁን መከራ አልፈው የመጡ ናቸው፤ ልብሳቸውንም በበጉ ደም አጥበው ነጭ አድርገውታል።” (ራእይ 7:14) የዚህ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” አባላት ከታላቁ መከራ ከተረፉ በኋላ በምድር ላይ ይኖራሉ፤ እንዲሁም አስደናቂ በረከቶችን ያገኛሉ። (መዝ. 37:9-11, 27-29፤ ምሳሌ 2:21, 22፤ ራእይ 7:16, 17) ተስፋችን ወደ ሰማይ መሄድም ሆነ በምድር ላይ መኖር ራእይ ምዕራፍ 7 ላይ ያለው መግለጫ ላይ ራሳችንን ልናገኘው ይገባል። የአምላክን አገልጋዮች ያቀፉት ሁለቱም ቡድኖች እንዴት ያለ አስደናቂ ጊዜ ይጠብቃቸዋል! የይሖዋን አገዛዝ ለመደገፍ በመምረጣችን ያን ጊዜ በጣም እንደምንደሰት የታወቀ ነው። w22.05 16 አን. 6-7

ሐሙስ፣ ግንቦት 2

ይሖዋ ራሱ ጥበብ ይሰጣል።—ምሳሌ 2:6

ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ውሳኔ አድርገህ ታውቃለህ? ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ጥበብ ለማግኘት ጸልየህ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፤ ደግሞም ይህን ማድረግህ ተገቢ ነው። (ያዕ. 1:5) ንጉሥ ሰለሞን “ጥበብ በጣም አስፈላጊ ነገር ናት” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 4:7) እርግጥ ነው፣ ሰለሞን እየተናገረ የነበረው እንዲሁ ስለማንኛውም ዓይነት ጥበብ አይደለም። ከይሖዋ ስለሚገኘው ጥበብ እየተናገረ ነበር። ሆኖም አምላካዊ ጥበብ ዛሬ የሚያጋጥሙንን ችግሮች ለመወጣት ይረዳናል? አዎ ይረዳናል። ጥበበኛ እንድንሆን የሚረዳን አንዱ ነገር በጥበባቸው የተነገረላቸው ሁለት ሰዎች የሰጡትን ምክር ማጥናታችንና ተግባራዊ ማድረጋችን ነው። መጀመሪያ ሰለሞንን እንመልከት። መጽሐፍ ቅዱስ፣ አምላክ “ለሰለሞን እጅግ ታላቅ ጥበብና ማስተዋል” እንደሰጠው ይናገራል። (1 ነገ. 4:29) ሁለተኛ ደግሞ በጥበቡ ተወዳዳሪ የሌለውን ኢየሱስን እንመልከት። (ማቴ. 12:42) ስለ ኢየሱስ እንዲህ የሚል ትንቢት ተነግሯል፦ “[በእሱ] ላይ የይሖዋ መንፈስ፣ የጥበብና የማስተዋል መንፈስ . . . ያርፍበታል።”—ኢሳ. 11:2፤ w22.05 20 አን. 1-2

ዓርብ፣ ግንቦት 3

ለቀጣዩ ትውልድ ስለ ብርታትህ . . . ልናገር።—መዝ. 71:18

ዕድሜያችን ቢገፋም መንፈሳዊ ግብ ማውጣትና ግባችን ላይ መድረስ እንችላለን። ቤቨርሊ የተባሉትን የ75 ዓመት እህት እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እህት ቤቨርሊ ከባድ የጤና እክል ስላለባቸው መራመድ ይከብዳቸዋል። ሆኖም በመታሰቢያው በዓል ዘመቻ ላይ የተሟላ ተሳትፎ ማድረግ ፈልገው ነበር። በመሆኑም ግልጽ የሆነ ግብ አወጡ። እህት ቤቨርሊ ግባቸው ላይ ሲደርሱ በጣም ተደሰቱ። እሳቸው ያደረጉት ጥረት ሌሎችም በአገልግሎት በትጋት እንዲካፈሉ አነሳስቷቸዋል። አረጋዊ የሆኑ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ማድረግ የሚችሉት ነገር የተገደበ ቢሆንም እንኳ ይሖዋ ሥራቸውን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። (መዝ. 71:17) ልትደርስባቸው የምትችላቸውን ግቦች አውጣ። በይሖዋ ዘንድ ተወዳጅነት ለማትረፍ የሚረዱህን ባሕርያት አዳብር። አምላክንም ሆነ ድርጅቱን ይበልጥ ማገልገል እንድትችል የሚረዱህን ክህሎቶች ተማር። ወንድሞችህንና እህቶችህን ይበልጥ ለማገልገል የሚያስችሉህን መንገዶች ፈልግ። አንተም እንደ ጢሞቴዎስ በይሖዋ እርዳታ “እድገትህ በሁሉም ሰዎች ዘንድ በግልጽ” ይታያል።—1 ጢሞ. 4:15፤ w22.04 27 አን. 18-19

ቅዳሜ፣ ግንቦት 4

[ቅዱሳን መጻሕፍትን] ከጨቅላነትህ ጀምሮ አውቀሃል።—2 ጢሞ. 3:15

የቻላችሁትን ሁሉ ጥረት ብታደርጉም ከልጆቻችሁ አንዱ ይሖዋን ማገልገል እንደማይፈልግ ቢገልጽስ? ‘ጥሩ ወላጅ አይደለሁም’ ብላችሁ አትደምድሙ። ይሖዋ ልጃችሁን ጨምሮ ለሁላችንም የመምረጥ ነፃነት ሰጥቶናል፤ ስለዚህ እሱን ለማገልገል ወይም ላለማገልገል መምረጥ እንችላለን። ልጃችሁ አንድ ቀን እንደሚመለስ ተስፋ አድርጉ። የጠፋውን ልጅ ምሳሌ አስታውሱ። (ሉቃስ 15:11-19, 22-24) ይህ ወጣት ከጽድቅ መንገድ በጣም ርቆ ነበር፤ በመጨረሻ ግን ተመልሷል። ወላጆች ታላቅ መብት ተሰጥቷችኋል፤ ይሖዋን የሚያገለግል አዲስ ትውልድ ኮትኩቶ የማሳደግ አደራ ተጥሎባችኋል። (መዝ. 78:4-6) ይህ ቀላል ኃላፊነት አይደለም። ልጆቻችሁ ይሖዋን እንዲወዱ ለመርዳትና በእሱ ተግሣጽና ምክር ለማሳደግ ለምታደርጉት ከፍተኛ ጥረት ከልባችን ልናመሰግናችሁ እንወዳለን። አፍቃሪ የሆነው ሰማያዊ አባታችን እንደሚደሰትባችሁ እርግጠኞች መሆን ትችላላችሁ።—ኤፌ. 6:4፤ w22.05 30-31 አን. 16-18

እሁድ፣ ግንቦት 5

የአካል ክፍሎች ሁሉ . . . እርስ በርስ ተስማምተው ተገጣጥመዋል።—ኤፌ. 4:16

በጉባኤያችን ውስጥ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን እያንዳንዳችን ምርጣችንን መስጠት ይኖርብናል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እነዚህ ክርስቲያኖች የተለያየ ስጦታና የተለያየ የአገልግሎት ምድብ ነበራቸው። (1 ቆሮ. 12:4, 7-11) ሆኖም ይህ ለፉክክርና ለክፍፍል ምክንያት አልሆነም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ፣ እያንዳንዳቸው ‘የክርስቶስን አካል ለመገንባት’ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ አበረታቷቸዋል። ጳውሎስ ለኤፌሶን ክርስቲያኖች “እያንዳንዱ የአካል ክፍል በአግባቡ ሥራውን ማከናወኑ አካሉ ራሱን በፍቅር እያነጸ እንዲያድግ አስተዋጽኦ ያበረክታል” በማለት ጽፎላቸዋል። (ኤፌ. 4:1-3, 11, 12) ይህን ምክር በሥራ ላይ ያዋሉት ክርስቲያኖች ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን አድርገዋል፤ በዛሬው ጊዜ በጉባኤያችን ውስጥ እንዲህ ዓይነት መንፈስ ሰፍኖ እናያለን። ራስህን ከሌሎች ጋር ላለማወዳደር ቁርጥ ውሳኔ አድርግ። ከዚህ ይልቅ ከኢየሱስ ተማር፤ እንዲሁም ባሕርያቱን ለመኮረጅ ጥረት አድርግ። ይሖዋ ‘ሥራህን በመርሳት ፍትሕ እንደማያዛባ’ እርግጠኛ ሁን። (ዕብ. 6:10) እሱን ለማስደሰት በሙሉ ነፍስህ የምታደርገውን ጥረት ያደንቃል። w22.04 14 አን. 15-16

ሰኞ፣ ግንቦት 6

ክርስቶስ ኢየሱስ ኃጢአተኞችን ለማዳን ወደ ዓለም መጣ።—1 ጢሞ. 1:15

ይሖዋ አንድን ኃጢአተኛ ይቅር ይለዋል ወይስ አይለውም የሚለውን መወሰን የእኛ ኃላፊነት አለመሆኑ ትልቅ እፎይታ ነው። ያም ቢሆን የእኛን ውሳኔ የሚጠይቅ ነገር አለ። ምንድን ነው? ምናልባት አንድ ሰው ከባድ በደል አድርሶብን ይሆናል። ከጊዜ በኋላ ግለሰቡ ይቅርታ ሊጠይቀን ይችላል፤ ላይጠይቀንም ይችላል። ያም ቢሆን ግለሰቡን ይቅር ለማለት መምረጥ እንችላለን። ይህም ሲባል በግለሰቡ ላይ ያደረብንን ቅሬታና ብስጭት ለመተው እንመርጣለን ማለት ነው። በተለይ ግለሰቡ ያደረሰብን ጉዳት ከባድ ከሆነ ጉዳዩን መተው ጊዜ እንደሚወስድና ጥረት እንደሚጠይቅብን የታወቀ ነው። የመስከረም 15, 1994 መጠበቂያ ግንብ እንዲህ ይላል፦ “አንድን በደለኛ ይቅር ስትለው በደሉን ተቀብለኸዋል ማለት [አይደለም]። አንድ ክርስቲያን ይቅር አለ ሲባል ጉዳዩን በእምነት ለይሖዋ ተወው ማለት ነው። ይሖዋ የመላው ጽንፈ ዓለም ጻድቅ ፈራጅ ነው፤ ፍትሕንም በተገቢው ጊዜ ላይ ይሰጣል።” w22.06 9 አን. 6-7

ማክሰኞ፣ ግንቦት 7

ይሖዋን ተስፋ አድርግ።—መዝ. 27:14

ይሖዋ በዘመናችን ከሁሉም ብሔራት፣ ነገዶችና ቋንቋዎች የተውጣጡ ሰዎችን በንጹሕ አምልኮ አንድ እንደሚያደርጋቸው ቃል ገብቶ ነበር። ይህ አስደናቂ ቡድን በዛሬው ጊዜ “እጅግ ብዙ ሕዝብ” ተብሎ ይጠራል። (ራእይ 7:9, 10) በዚህ ቡድን ውስጥ ያሉት ሰዎች የተለያየ አስተዳደግ ያላቸው ወንዶች፣ ሴቶችና ልጆች ቢሆኑም ሰላምና አንድነት ያለው ዓለም አቀፋዊ የወንድማማች ማኅበር መሥርተዋል። (መዝ. 133:1፤ ዮሐ. 10:16) ወደፊት የተሻለ ዓለም እንደሚመጣ የሚገልጸውን ተስፋ ሰሚ ጆሮ ላላቸው ሁሉ ለመናገር ምንጊዜም ዝግጁ ናቸው። (ማቴ. 28:19, 20፤ ራእይ 14:6, 7፤ 22:17) አንተም የእጅግ ብዙ ሕዝብ ክፍል ከሆንክ ወደፊት የተሻለ ዓለም እንደሚመጣ የሚገልጸውን ተስፋ ከፍ አድርገህ እንደምትመለከተው ምንም ጥያቄ የለውም። ዲያብሎስ ተስፋህን ሊያጨልምብህ ይፈልጋል። የእሱ ዓላማ ይሖዋ ቃሉን እንደማይጠብቅ እንድታምን ማድረግ ነው። ሰይጣን ተስፋችንን ማጨለም ከቻለ ድፍረት እናጣለን፤ ይባስ ብሎም ይሖዋን ማገልገላችንን ልናቆም እንችላለን። w22.06 20-21 አን. 2-3

ረቡዕ፣ ግንቦት 8

እኛ ለነፍሳችን እንደ መልሕቅ አስተማማኝና ጽኑ የሆነ ይህ ተስፋ አለን።—ዕብ. 6:19

ወደፊት የተሻለ ጊዜ እንደሚመጣ ጽኑ ተስፋ ስላለን አስቸጋሪ ሁኔታዎችን መወጣት እንችላለን። ኢየሱስ ስደት እንደሚደርስብን እንዳስጠነቀቀን አትርሱ። (ዮሐ. 15:20) በመሆኑም ወደፊት በምናገኘው በረከት ላይ ማሰላሰላችን በክርስትና ጎዳና ላይ ጸንተን ለመመላለስ ይረዳናል። ኢየሱስ በአሰቃቂ ሁኔታ እንደሚገደል ቢያውቅም ተስፋው ጽኑ እንዲሆን የረዳው እንዴት እንደሆነ እንመልከት። በ33 ዓ.ም. በዋለው የጴንጤቆስጤ ዕለት ሐዋርያው ጴጥሮስ ከመዝ. መጽሐፍ ላይ አንድ ትንቢት ጠቅሶ ነበር፤ ትንቢቱ ኢየሱስ የነበረውን የመተማመን ስሜት ግሩም አድርጎ የሚገልጽ ነው፤ እንዲህ ይላል፦ “በተስፋ እኖራለሁ፤ ምክንያቱም በመቃብር አትተወኝም፤ ታማኝ አገልጋይህም መበስበስን እንዲያይ አትፈቅድም። . . . በፊትህ በታላቅ ደስታ እንድሞላ ታደርገኛለህ።” (ሥራ 2:25-28፤ መዝ. 16:8-11) ኢየሱስ፣ አምላክ ከሞት እንደሚያስነሳውና ወደ ሰማይ ተመልሶ ከአባቱ ጋር በደስታ እንደሚኖር ጠንካራ ተስፋ ነበረው።—ዕብ. 12:2, 3፤ w22.10 25 አን. 4-5

ሐሙስ፣ ግንቦት 9

ሁላችንም ብዙ ጊዜ እንሰናከላለን።—ያዕ. 3:2

በአንድ ወቅት ከሐዋርያቱ መካከል ሁለቱ ማለትም ያዕቆብና ዮሐንስ ኢየሱስ በመንግሥቱ ከፍ ያለ ቦታ እንዲሰጣቸው በእናታቸው በኩል አስጠይቀውት ነበር። (ማቴ. 20:20, 21) ይህም ያዕቆብና ዮሐንስ ኩራትና የሥልጣን ጥም እንደነበራቸው የሚያሳይ ነው። (ምሳሌ 16:18) በዚያ ወቅት መጥፎ ባሕርይ ያሳዩት ያዕቆብና ዮሐንስ ብቻ አልነበሩም። ሌሎቹ ሐዋርያት ምላሽ የሰጡበትን መንገድ ልብ በሉ፦ “የቀሩት አሥሩ ይህን ሲሰሙ በሁለቱ ወንድማማቾች ላይ ተቆጡ።” (ማቴ. 20:24) በያዕቆብ፣ በዮሐንስና በሌሎቹ ሐዋርያት መካከል የከረረ ጠብ ተነስቶ ሊሆን እንደሚችል እንገምታለን። ኢየሱስ ሁኔታውን የያዘው እንዴት ነው? በሐዋርያቱ ላይ አልተበሳጨባቸውም። እነሱን ትቶ ይበልጥ ትሑት የሆኑና አንዳቸው ለሌላው ሁሌም ፍቅር የሚያሳዩ የተሻሉ ሐዋርያትን እንደሚፈልግ አልተናገረም። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ሐዋርያቱ ልባቸው ቅን እንደሆነ ስለሚያውቅ በትዕግሥት እርማት ሰጥቷቸዋል። (ማቴ. 20:25-28) እነሱን በፍቅር መያዙን ቀጥሏል። w23.03 28-29 አን. 10-13

ዓርብ፣ ግንቦት 10

ልጄ ሆይ፣ ለሚነቅፈኝ መልስ መስጠት እችል ዘንድ ጥበበኛ ሁን፤ ልቤንም ደስ አሰኘው።—ምሳሌ 27:11

እስካሁን ብዙ ነገሮችን አከናውነሃል። መጽሐፍ ቅዱስን በትጋት አጥንተሃል፤ ምናልባትም ያጠናኸው ለበርካታ ዓመታት ሊሆን ይችላል። ማጥናትህ መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክ ቃል እንደሆነ እንድታምን አድርጎሃል። ይህ ብቻ ሳይሆን፣ የዚህ ቅዱስ መጽሐፍ ባለቤት የሆነውን አምላክ ማወቅና መውደድ ችለሃል። ለይሖዋ ያለህ ፍቅር በጣም ስላደገ ራስህን ለእሱ ወስነህ ተጠምቀሃል። ይህ ምንኛ የሚያስደስት ነው! ከመጠመቅህ በፊት እምነትህ በተለያዩ መንገዶች እንደተፈተነ ምንም ጥያቄ የለውም። በመንፈሳዊ ይበልጥ እያደግክ ስትሄድ ደግሞ አዳዲስ ፈተናዎች ያጋጥሙሃል። ሰይጣን ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ለማዳከምና እሱን ማገልገልህን እንድታቆም ለማድረግ ይሞክራል። (ኤፌ. 4:14) ይህ እንዲሆን ፈጽሞ ልትፈቅድ አይገባም። ይሖዋን በታማኝነት ማገልገልህን ለመቀጠልና ራስህን ስትወስን የገባኸውን ቃል ለመጠበቅ ምን ሊረዳህ ይችላል? እድገት ማድረግህን መቀጠል ማለትም ወደ ክርስቲያናዊ ‘ጉልምስና ለመድረስ መጣጣር’ አለብህ።—ዕብ. 6:1፤ w22.08 2 አን. 1-2

ቅዳሜ፣ ግንቦት 11

ዕድሜህ እንዲረዝምና መልካም እንዲሆንልህ አምላክህ ይሖዋ ባዘዘህ መሠረት አባትህንና እናትህን አክብር።—ዘዳ. 5:16

በቤተሰብ ውስጥ እያንዳንዱ ሰው አንዳንድ የቤተሰብ ጉዳዮችን በሚስጥር የመያዝ ኃላፊነት አለበት። ለምሳሌ አንዲት ክርስቲያን ሚስት እንግዳ ልማድ ይኖራት ይሆናል። ባሏ ስለዚህ ጉዳይ ለሌሎች በመናገር ያሳፍራታል? በፍጹም እንደዚህ አያደርግም! ሚስቱን ይወዳታል፤ እሷን የሚጎዳ ምንም ነገር ማድረግ አይፈልግም። (ኤፌ. 5:33) በአሥራዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ወጣቶች በአክብሮት መያዝ ይፈልጋሉ። ወላጆች ይህን መገንዘባቸው ጠቃሚ ነው። ልጆቻቸው የሠሯቸውን ስህተቶች ለሌሎች በመናገር ሊያሳፍሯቸው አይገባም። (ቆላ. 3:21) ልጆችም ሚስጥር ጠባቂነትን መማር አለባቸው፤ የቤተሰባቸውን አባላት ሊያሳፍሩ የሚችሉ ጉዳዮችን ለሌሎች ሰዎች መናገር የለባቸውም። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል የቤተሰቡን ሚስጥር ለመጠበቅ የበኩሉን ድርሻ የሚወጣ ከሆነ በቤተሰቡ መካከል ያለው ጥምረት ይጠናከራል። w22.09 10 አን. 9

እሁድ፣ ግንቦት 12

ኢዮብ ሆይ፣ ይህን ስማ፤ ቆም ብለህ . . . አስብ።—ኢዮብ 37:14

ይሖዋ ኢዮብን በማነጋገር፣ ወደር ስለሌለው ጥበቡ እንዲሁም ለፍጥረታቱ ስለሚያሳየው ፍቅርና አሳቢነት አስታወሰው። ስለተለያዩ አስደናቂ እንስሳት ነገረው። (ኢዮብ 38:1, 2፤ 39:9, 13, 19, 27፤ 40:15፤ 41:1, 2) በተጨማሪም ይሖዋ፣ ኤሊሁ የተባለ አንድ ታማኝ ወጣት ኢዮብን እንዲያጽናናውና እንዲያበረታታው አደረገ። ኤሊሁ፣ ይሖዋ ምንጊዜም አገልጋዮቹን ለጽናታቸው ወሮታ እንደሚከፍላቸው ለኢዮብ አረጋገጠለት። ሆኖም ይሖዋ፣ ኤሊሁ ለኢዮብ ፍቅር የሚንጸባረቅበት እርማት እንዲሰጠውም አነሳስቶታል። ኤሊሁ፣ ኢዮብ የጽንፈ ዓለሙ ፈጣሪ ከሆነው ከይሖዋ አንጻር ያለውን ቦታ እንዲያስታውስ በማድረግ እይታውን እንዲያሰፋ ረድቶታል። ከዚህም ሌላ ይሖዋ ለኢዮብ ኃላፊነት ሰጠው፤ ኃጢአት ለሠሩት ሦስት ጓደኞቹ እንዲጸልይ አዘዘው። (ኢዮብ 42:8-10) በዛሬው ጊዜስ ከባድ ፈተናዎች ሲያጋጥሙን ይሖዋ የሚደግፈን እንዴት ነው? ይሖዋ ለኢዮብ እንዳደረገው እኛን በቀጥታ አያነጋግረንም፤ ሆኖም በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ያነጋግረናል።—ሮም 15:4፤ w22.08 11 አን. 10-11

ሰኞ፣ ግንቦት 13

ወንድምህ የሚሰናከልበት ከሆነ ሥጋ አለመብላት፣ የወይን ጠጅ አለመጠጣት ወይም ማንኛውንም የሚያሰናክል ነገር አለማድረግ የተሻለ ነው።—ሮም 14:21

በሮም በነበረው ጉባኤ ውስጥ ከአይሁዳውያንም ሆነ ከአሕዛብ የተውጣጡ ክርስቲያኖች ነበሩ። የሙሴ ሕግ ሲሻር አንዳንድ ምግቦችን ከመብላት ጋር በተያያዘ የነበሩት ገደቦች ተነሱ። (ማር. 7:19) ከዚያ ጊዜ አንስቶ አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ሁሉንም ዓይነት ምግብ ለመብላት ነፃነት ይሰማቸው ነበር። ሌሎች አይሁዳውያን ክርስቲያኖች ግን ይህን ማድረግ ተገቢ እንደሆነ አልተሰማቸውም። በዚህም የተነሳ በጉባኤው ውስጥ ክፍፍል ተፈጠረ። ሐዋርያው ጳውሎስ የሰላምን አስፈላጊነት ጎላ አድርጎ ገልጿል። በዚህ መንገድ ጳውሎስ፣ እንዲህ ያሉት ግጭቶች ግለሰቦችንም ሆነ መላውን ጉባኤ እንደሚጎዱ የእምነት ባልንጀሮቹን አስገንዝቧቸዋል። (ሮም 14:19, 20) ከዚህም ሌላ ጳውሎስ ሌሎችን ላለማሰናከል ሲል ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ ነበር። (1 ቆሮ. 9:19-22) እኛም በተመሳሳይ ለምርጫ በተተዉ ጉዳዮች ረገድ ድርቅ ባለማለት ሌሎችን ማነጽና ሰላም ማስፈን እንችላለን። w22.08 22 አን. 7

ማክሰኞ፣ ግንቦት 14

ይሖዋ . . . ጽድቅን የሚከታተለውን . . . ይወደዋል።—ምሳሌ 15:9

በይሖዋ አገልግሎት አንድን ግብ እንከታተላለን ሲባል እዚህ ግብ ላይ ለመድረስ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እናደርጋለን ማለት ነው። ጽድቅን ከመከታተል ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይሖዋም እድገት እንድናደርግና በጊዜ ሂደት እያሻሻልን እንድንሄድ ይረዳናል። (መዝ. 84:5, 7) ይሖዋ ጽድቅን መከታተል ከባድ ሸክም እንዳልሆነ የሚገልጽ ፍቅራዊ ማሳሰቢያ ሰጥቶናል። (1 ዮሐ. 5:3) እንዲያውም ጥበቃ ያስገኝልናል፤ እንዲህ ያለው ጥበቃ ደግሞ በየዕለቱ ያስፈልገናል። ሐዋርያው ጳውሎስ የጠቀሰውን መንፈሳዊ የጦር ትጥቅ ወደ አእምሮህ አምጣ። (ኤፌ. 6:14-18) የወታደሩን ልብ የሚጠብቅለት የትኛው የትጥቁ ክፍል ነው? የይሖዋን የጽድቅ መሥፈርቶች የሚያመለክተው ‘የጽድቅ ጥሩር’ ነው። ጥሩር የወታደሩን ልብ እንደሚጠብቅለት ሁሉ የይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶችም ምሳሌያዊ ልባችንን ማለትም ውስጣዊ ማንነታችንን ይጠብቁልናል። እንግዲያው በጦር ትጥቅህ ውስጥ የጽድቅ ጥሩር መካተቱን ምንጊዜም አረጋግጥ!—ምሳሌ 4:23፤ w22.08 29 አን. 13-14

ረቡዕ፣ ግንቦት 15

የአምላካችን ቃል . . . ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል።—ኢሳ. 40:8

የአምላክ ቃል ታማኝ ለሆኑ ወንዶችና ሴቶች በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ጥበብ ያዘለ መመሪያ ሲሰጥ ቆይቷል። ይህ ሊሆን የቻለው እንዴት ነው? ይሖዋ ቅዱስ ጽሑፉ በእጅ እንዲገለበጥ አድርጓል። ገልባጮቹ ፍጹማን ባይሆኑም ሥራቸውን ያከናወኑት በከፍተኛ ጥንቃቄ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አንድ ምሁር የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍትን አስመልክተው እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ “መልእክቱ ይህን ያህል ተጠብቆ የቆየ አንድም ጥንታዊ መጽሐፍ የለም ብንል ማጋነን አይሆንም።” ስለዚህ በዛሬው ጊዜ በመጽሐፍ ቅዱሳችን ላይ የምናነብባቸው ቃላት ያጻፈውን አካል ማለትም የይሖዋን ሐሳብ በትክክል እንደሚያስተላልፉ መተማመን እንችላለን። ይሖዋ ‘የመልካም ስጦታ ሁሉና የፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ’ ምንጭ ነው። (ያዕ. 1:17) ይሖዋ ከሰጠን ግሩም ስጦታዎች መካከል አንዱ መጽሐፍ ቅዱስ ነው። አንድ ስጦታ ሰጪው ስለ እኛም ሆነ ስለሚያስፈልገን ነገር ምን ያህል እንደሚያውቅ ይነግረናል። መጽሐፍ ቅዱስን ከሰጠን አካል ጋር በተያያዘም ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። ይህን ስጦታ ስንመረምር ስለ ይሖዋ ብዙ እንማራለን። እኛንም ሆነ የሚያስፈልጉንን ነገሮች ምን ያህል እንደሚያውቅ እንረዳለን። w23.02 2-3 አን. 3-4

ሐሙስ፣ ግንቦት 16

ምድርም በይሖዋ እውቀት ትሞላለች።—ኢሳ. 11:9

በክርስቶስ የሺህ ዓመት ግዛት በምድር ላይ ትንሣኤ መከናወን የሚጀምርበት ዕለት ምንኛ አስደሳች ይሆናል! የሚወዷቸውን ሰዎች በሞት ያጡ በሙሉ ዳግመኛ ሊያዩአቸው ይናፍቃሉ። ይሖዋም የሚሰማው እንዲህ ነው። (ኢዮብ 14:15) በመላው ምድር የተነፋፈቁ ሰዎች ሲገናኙ ምንኛ ደስታ እንደሚሰፍን እስቲ አስቡት! ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ የተጻፈ “ጻድቃን” “ለሕይወት ትንሣኤ” ይወጣሉ። (ሥራ 24:15፤ ዮሐ. 5:29) ምናልባትም በሞት ካጣናቸው ሰዎች መካከል ብዙዎቹ በምድራዊው ትንሣኤ ወቅት መጀመሪያ ከሚነሱት መካከል ሊሆኑ ይችላሉ። በተጨማሪም “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” ለምሳሌ ከመሞታቸው በፊት ይሖዋን ለማወቅ ወይም እሱን በታማኝነት ለማገልገል በቂ አጋጣሚ ያላገኙ ሰዎች “ለፍርድ ትንሣኤ” ይወጣሉ። ትንሣኤ ያገኙት ሰዎች በሙሉ ትምህርት ያስፈልጋቸዋል። (ኢሳ. 26:9፤ 61:11) በመሆኑም በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ መጠነ ሰፊ የትምህርት መርሐ ግብር መዘርጋት አለበት።—ኢሳ. 11:10፤ w22.09 20 አን. 1-2

ዓርብ፣ ግንቦት 17

እሱ . . . ሕያው አምላክ ነው።—ዳን. 6:26

ይሖዋ ጥምረት ከፈጠሩ መንግሥታት በላይ ኃይል እንዳለው አሳይቷል። ለእስራኤላውያን በመዋጋት የተስፋይቱን ምድር አብዛኛውን ክፍል እንዲቆጣጠሩ አስችሏቸዋል። (ኢያሱ 11:4-6, 20፤ 12:1, 7, 24) ይሖዋ ከሁሉ የላቀ አምላክ መሆኑን በተደጋጋሚ አሳይቷል። የባቢሎኑ ንጉሥ ናቡከደነጾር፣ ውዳሴ የሚገባው ይሖዋ እንደሆነ በትሕትና ከመቀበል ይልቅ ‘ስለ ግርማው ክብር እንዲሁም ስለ ገዛ ብርታቱና ኃይሉ’ ጉራ በነዛበት ጊዜ አምላክ አእምሮውን እንዲስት አድርጎታል። ናቡከደነጾር አእምሮው ከተመለሰለት በኋላ ‘ልዑሉን አምላክ አመሰገነ’፤ እንዲሁም ‘የይሖዋ የመግዛት ሥልጣን ዘላለማዊ እንደሆነ’ አምኖ ተቀበለ። አክሎም “[እሱን] ሊያግደው . . . የሚችል ማንም የለም” ብሏል። (ዳን. 4:30, 33-35) መዝሙራዊው እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ አምላኩ የሆነ ብሔር፣ የራሱ ንብረት አድርጎ የመረጠው ሕዝብ ደስተኛ ነው።” (መዝ. 33:12) በእርግጥም በይሖዋ ፊት ያለንን ንጹሕ አቋም የምንጠብቅበት በቂ ምክንያት አለን። w22.10 15-16 አን. 13-15

ቅዳሜ፣ ግንቦት 18

ቃልህ . . . እውነት ነው።—መዝ. 119:160

እስካሁን ፍጻሜያቸውን ያገኙ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መኖራቸው አምላክ ስለ ወደፊቱ ጊዜ የሰጣቸው ተስፋዎች እንደሚፈጸሙ ይበልጥ እርግጠኛ እንድንሆን ያደርገናል። “ማዳንህን እናፍቃለሁ፤ ቃልህ ተስፋዬ ነውና” በማለት ወደ ይሖዋ የጸለየውን መዝሙራዊ ስሜት እንጋራለን። (መዝ. 119:81) ይሖዋ በደግነት ተነሳስቶ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት “የተሻለ ሕይወትንና ተስፋን” ሰጥቶናል። (ኤር. 29:11) የወደፊት ተስፋችን የተመካው በሰዎች ጥረት ላይ ሳይሆን ይሖዋ በገባቸው ቃሎች ላይ ነው። እንግዲያው የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች በጥንቃቄ በማጥናት በአምላክ ቃል ላይ ያለንን እምነት ማጠናከራችንን እንቀጥል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ እምነት ለመጣል የሚያነሳሳን ሌላው ማስረጃ ሰዎች ምክሩን ሲከተሉ የሚያገኙት ጥቅም ነው። (መዝ. 119:66, 138) ለምሳሌ ሊፋቱ ተቃርበው የነበሩ ባለትዳሮች አሁን በአንድነትና በደስታ እየኖሩ ነው። ልጆቻቸው ሰላምና ፍቅር በሰፈነበት ክርስቲያን ቤተሰብ ውስጥ የማደግ ልዩ አጋጣሚ አግኝተዋል።—ኤፌ. 5:22-29፤ w23.01 5 አን. 12-13

እሁድ፣ ግንቦት 19

በተስፋው ደስ ይበላችሁ።—ሮም 12:12

አምላክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የገባልን ቃል በመፈጸሙ በግለሰብ ደረጃ የተጠቀማችሁት እንዴት እንደሆነ ለማሰብ ሞክሩ። ለምሳሌ ይሖዋ መሠረታዊ ነገሮችን እንደሚሰጠን ኢየሱስ ቃል ገብቶልናል። (ማቴ. 6:32, 33) በተጨማሪም ይሖዋ ስንጠይቀው መንፈስ ቅዱስን እንደሚሰጠን ኢየሱስ ዋስትና ሰጥቶናል። (ሉቃስ 11:13) ይሖዋ የገባውን ቃል ፈጽሟል። ይሖዋ ከእናንተ ጋር በተያያዘ ቃሉን የጠበቀባቸውን ሌሎች መንገዶችም ታስታውሱ ይሆናል። ለምሳሌ ይቅር እንደሚለን፣ እንደሚያጽናናን እንዲሁም በመንፈሳዊ እንደሚመግበን ቃል ገብቶልናል። (ማቴ. 6:14፤ 24:45፤ 2 ቆሮ. 1:3) አምላክ እስካሁን ባደረገላችሁ ነገር ላይ ካሰላሰላችሁ ለወደፊቱ ጊዜ በሰጣችሁ ተስፋ ላይ ያላችሁ እምነት ይጠናከራል። ይሖዋ ምንጊዜም ቃሉን እንደሚጠብቅ እርግጠኞች ነን። መዝሙራዊው እንዲህ ሲል ጽፏል፦ “በአምላኩ በይሖዋ ተስፋ የሚያደርግ ሰው ደስተኛ ነው፤ እሱ . . . ለዘላለም ታማኝ ነው።”—መዝ. 146:5, 6፤ w22.10 27 አን. 15፤ 28 አን. 17

ሰኞ፣ ግንቦት 20

በአንቺ ላይ . . . ይሖዋ ያበራል።—ኢሳ. 60:2

ንጹሕ አምልኮ መልሶ ስለመቋቋሙ የሚገልጸው ትንቢት ከእኛ ጋር በተያያዘ ይሠራል? ምን ጥያቄ አለው! እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ከ1919 ዓ.ም. ወዲህ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች ከታላቂቱ ባቢሎን ግዞት ማለትም በዓለም ላይ ካሉ የሐሰት ሃይማኖቶች ባርነት ነፃ ወጥተዋል። እነዚህ ሰዎች እስራኤላውያን ይኖሩባት ከነበረችው ተስፋይቱ ምድር እጅግ ወደተሻለ ቦታ ማለትም ወደ መንፈሳዊው ገነት ገብተዋል። (ኢሳ. 51:3፤ 66:8) ከ1919 ዓ.ም. ወዲህ ቅቡዓኑ በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ በደስታ እየኖሩ ነው። ውሎ አድሮ ደግሞ፣ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው “ሌሎች በጎች” በዚህ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ መኖር ጀመሩ፤ እነሱም የይሖዋን የተትረፈረፉ በረከቶች እያጨዱ ነው። (ዮሐ. 10:16፤ ኢሳ. 25:6፤ 65:13) እነሱ የሚኖሩበት መንፈሳዊ ገነት የሚገኘው በመላው ዓለም ነው። ስለዚህ በዛሬው ጊዜ የምንኖረው የትም ይሁን የት፣ ንጹሑን አምልኮ በንቃት እስከደገፍን ድረስ በመንፈሳዊው ገነት ውስጥ መኖር እንችላለን። w22.11 11-12 አን. 12-15

ማክሰኞ፣ ግንቦት 21

ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ከዘላለም አንስቶ ያለህ አይደለህም? ቅዱስ የሆንከው አምላኬ ሆይ፣ አንተ አትሞትም።—ዕን. 1:12

ይሖዋ “ከዘላለም እስከ ዘላለም” እንደሚኖር የሚገልጸውን ሐሳብ መረዳት ይከብዳችኋል? (ኢሳ. 40:28) እንዲህ ቢሰማችሁ አያስገርምም። ኤሊሁ ስለ አምላክ ሲናገር “የዘመኑም ቁጥር ከመረዳት ችሎታ በላይ ነው” ብሏል። (ኢዮብ 36:26) ሆኖም አንድን ነገር መረዳት ስላልቻልን ብቻ ያ ነገር ውሸት ነው ማለት አይደለም። ለምሳሌ የብርሃን ምንነት ሙሉ በሙሉ አይገባን ይሆናል። ታዲያ ይህ ሲባል ብርሃን የሚባል ነገር የለም ማለት ነው? በጭራሽ! በተመሳሳይም እኛ የሰው ልጆች፣ ይሖዋ መጀመሪያም ሆነ መጨረሻ እንደሌለው የሚገልጸውን ሐሳብ መቼም ቢሆን ሙሉ በሙሉ መረዳት አንችል ይሆናል። ሆኖም ይህ ሲባል፣ አምላክ ከዘላለም እስከ ዘላለም አይኖርም ማለት አይደለም። የፈጣሪያችን ማንነት በእኛ የመረዳት ችሎታ የተገደበ አይደለም። (ሮም 11:33-36) እሱ እንደ ፀሐይ ያሉ የብርሃን ምንጮችን ጨምሮ ግዑዙ ጽንፈ ዓለም ወደ ሕልውና ከመምጣቱ በፊት ነበር። አዎ፣ ‘ሰማያትን ከመዘርጋቱ’ በፊት እሱ ነበር።—ኤር. 51:15፤ w22.12 2-3 አን. 3-4

ረቡዕ፣ ግንቦት 22

ጸሎቴ በአንተ ፊት እንደተዘጋጀ ዕጣን ይሁን።—መዝ. 141:2

አንዳንድ ጊዜ ሌሎችን ወክለን እንድንጸልይ እንጋበዝ ይሆናል። ለምሳሌ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የምትመራ አንዲት እህት ጥናቱ ላይ የተገኘችን ሌላ እህት እንድትጸልይ ትጋብዛት ይሆናል። ጥናት የተጋበዘችው እህት ስለ ተማሪዋ ብዙም ላታውቅ ስለምትችል በጥናቱ መደምደሚያ ላይ ለመጸለይ ትመርጥ ይሆናል። እንዲህ ማድረጓ የተማሪዋን ሁኔታ ከግምት ያስገባ ጸሎት ለማቅረብ ያስችላታል። አንድ ወንድም በመስክ ስምሪት ስብሰባ ወይም በጉባኤ ስብሰባ ላይ እንዲጸልይ ይጋበዝ ይሆናል። እንዲህ ያለ መብት ያገኙ ወንድሞች የስብሰባውን ዓላማ ሊዘነጉ አይገባም። በተጨማሪም ጉባኤውን ለመምከር ወይም ማስታወቂያ ለመናገር ጸሎትን መጠቀም ተገቢ አይደለም። በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አብዛኛውን ጊዜ ለመዝሙርና ለጸሎት የሚመደበው በድምሩ አምስት ደቂቃ ነው። በመሆኑም ጸሎት የሚያቀርቡ ወንድሞች በተለይም በስብሰባው መጀመሪያ ላይ ‘ቃላት ማብዛት’ የለባቸውም።—ማቴ. 6:7፤ w22.07 24 አን. 17-18

ሐሙስ፣ ግንቦት 23

ጦርነትና የጦርነት ወሬ ትሰማላችሁ። በዚህ ጊዜ እንዳትደናገጡ ተጠንቀቁ፤ ምክንያቱም እነዚህ ነገሮች መፈጸማቸው የግድ ነው፤ ሆኖም ፍጻሜው ገና ነው።—ማቴ. 24:6

ኢየሱስ በመጨረሻዎቹ ቀናት “በተለያየ ስፍራ” ቸነፈር ወይም ወረርሽኝ እንደሚከሰት ትንቢት ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) ይህን ማወቃችን ሰላም የሚሰጠን እንዴት ነው? ወረርሽኝ መከሰቱ አያስደነግጠንም። ኢየሱስ የተናገረው ትንቢት እየተፈጸመ እንዳለ እንገነዘባለን። በመሆኑም ኢየሱስ በመጨረሻው ዘመን ለሚኖሩት ሰዎች “እንዳትደናገጡ ተጠንቀቁ” በማለት የሰጠውን ምክር እንከተላለን። ወረርሽኝ መከሰቱ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴዎችህ ላይ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር ጥያቄ የለውም። ሆኖም የግል ጥናት ከማድረግ ወይም በስብሰባ ላይ ከመገኘት እንዲያግድህ ልትፈቅድ አይገባም። በጽሑፎቻችንና በቪዲዮዎቻችን ላይ የሚወጡት ተሞክሮዎች ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ተመሳሳይ ፈተና ቢያጋጥማቸውም በታማኝነት ይሖዋን እያገለገሉ እንደሆነ ያሳዩናል። w22.12 17 አን. 4, 6

ዓርብ፣ ግንቦት 24

ሁሉም መጥፎ ጊዜ [ያጋጥማቸዋል]።—መክ. 9:11

ያዕቆብ ልጁን ዮሴፍን በጣም ይወደው ነበር። (ዘፍ. 37:3, 4) ትላልቆቹ የያዕቆብ ልጆች ይህን ሲያዩ በወንድማቸው ቀኑበት። ከዚያም አጋጣሚ ሲያገኙ ዮሴፍን ለምድያማውያን ነጋዴዎች ሸጡት። እነዚህ ነጋዴዎች ደግሞ ዮሴፍን በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎ ሜትሮች ርቃ ወደምትገኘው ወደ ግብፅ ወስደው የፈርዖን የዘቦች አለቃ ለሆነው ለጶጢፋር ሸጡት። በአባቱ የተወደደ ልጅ የነበረው ዮሴፍ ሕይወቱ በቅጽበት ተቀይሮ የአንድ ግብፃዊ ባሪያ ሆነ። (ዘፍ. 39:1) አንዳንድ ጊዜ “በሰው ሁሉ ላይ” የሚደርሰው ዓይነት መከራ ያጋጥመናል። (1 ቆሮ. 10:13) ወይም ደግሞ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆናችን ምክንያት ችግር ሊደርስብን ይችላል። ለምሳሌ በእምነታችን ምክንያት ፌዝ፣ ተቃውሞ አልፎ ተርፎም ስደት ሊያጋጥመን ይችላል። (2 ጢሞ. 3:12) ያጋጠመህ ፈተና ምንም ይሁን ምን፣ ይሖዋ ስኬታማ እንድትሆን ሊረዳህ ይችላል። w23.01 15 አን. 3-4

ቅዳሜ፣ ግንቦት 25

እንጨት ከሌለ እሳት ይጠፋል።—ምሳሌ 26:20

አንዳንድ ጊዜ ቅር ያሰኘንን ግለሰብ ማነጋገር እንዳለብን ሊሰማን ይችላል። በቅድሚያ ግን እንደሚከተሉት ያሉ ጥያቄዎችን ራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል፦ ‘ስለ ጉዳዩ በቂ መረጃ አለኝ?’ (ምሳሌ 18:13) ‘ግለሰቡ ያን ነገር ያደረገው ሆን ብሎ ባይሆንስ?’ (መክ. 7:20) ‘እኔስ ተመሳሳይ ስህተት የሠራሁበት ጊዜ የለም?’ (መክ. 7:21, 22) ‘ግለሰቡን ማነጋገሬ ለመፍታት እየሞከርኩ ካለሁት ችግር የከፋ ሌላ ችግር ያስከትል ይሆን?’ እንዲህ ባሉ ጥያቄዎች ላይ ቆም ብለን ካሰብን በኋላ ለወንድማችን ባለን ፍቅር ተነሳስተን በደሉን ችላ ብለን ለማለፍ ልንወስን እንችላለን። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ፍጹማን ባይሆኑም ለእነሱ ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅር ስናሳይ በግለሰብ ደረጃ እውነተኛ የኢየሱስ ተከታዮች እንደሆንን እናሳያለን። ይህም ሌሎች እውነተኛውን ሃይማኖት ለይተው እንዲያውቁና ይሖዋን ከእኛ ጋር አብረው እንዲያመልኩ ለማድረግ ሊረዳ ይችላል። እንግዲያው የእውነተኛ ክርስቲያኖች መለያ የሆነውን ፍቅር ማሳየታችንን ለመቀጠል ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ። w23.03 31 አን. 18-19

እሁድ፣ ግንቦት 26

አምላክ ፍቅር ነው።—1 ዮሐ. 4:8

መጽሐፍ ቅዱስ ከሁሉ የላቀውን የይሖዋን ባሕርይ ማለትም ፍቅሩን ይገልጣል። ይሖዋ ስለሚወደን ከአቅማችን በላይ የሆኑ ዝርዝር መረጃዎችን በማዥጎድጎድ አላስጨነቀንም። (ዮሐ. 21:25) ይሖዋ እኛን እንደሚያከብረን በሚያሳይ መንገድ ሐሳቡን መግለጹም የእሱን ፍቅር ያንጸባርቃል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ብዙ ዝርዝር ሕጎችን በማስፈር እያንዳንዱን የሕይወታችንን ክፍል ለመቆጣጠር አልሞከረም። ከዚህ ይልቅ እውነተኛ ታሪኮችን፣ ስሜት ቀስቃሽ ትንቢቶችንና ጠቃሚ ምክሮችን በመስጠት የማሰብ ችሎታችንን ተጠቅመን እንድንወስን አበረታቶናል። በዚህ መንገድ የአምላክ ቃል ይሖዋን ከልባችን እንድንወደውና እንድንታዘዘው ያነሳሳናል። መጽሐፍ ቅዱስ ይሖዋ በጥልቅ እንደሚያስብልን ያሳያል። እንዴት? ቃሉ እኛ የሰው ልጆች የሚሰሙንን ስሜቶች በሚያንጸባርቁ ዘገባዎች የተሞላ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ባለታሪኮች “እንደ እኛው ዓይነት ስሜት” ያላቸው ስለሆኑ ስሜታቸውን መረዳት አይከብደንም። (ያዕ. 5:17) ከሁሉ በላይ ደግሞ ይሖዋ እንደ እኛው ያሉ ሰዎችን በምን ዓይነት መንገድ እንደያዛቸው ማንበባችን እሱ “እጅግ አፍቃሪና መሐሪ እንደሆነ” በግልጽ ለማየት ያስችለናል።—ያዕ. 5:11፤ w23.02 6 አን. 13-15

ሰኞ፣ ግንቦት 27

የማስተዋል ስሜታችሁን ጠብቁ፤ ንቁ ሆናችሁ ኑሩ!—1 ጴጥ. 5:8

የመጨረሻው የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍም የሚጀምረው በሚከተሉት ቃላት ነው፦ “በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ አምላክ ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውና እሱ የገለጠው ራእይ ይህ ነው።” (ራእይ 1:1) ስለዚህ በዓለማችን ላይ እየተከናወኑ ስላሉት ነገሮች እንዲሁም እነዚህ ክንውኖች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ፍጻሜ እንዲያገኝ ሊያደርጉ የሚችሉት እንዴት እንደሆነ ማወቅ እንፈልጋለን። ከዚህም በላይ ስለ እነዚህ ክንውኖች ከሌሎች ጋር መወያየት ሊያስደስተን ይችላል። ሆኖም ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ከሌሎች ጋር ስንወያይ ግምታዊ ሐሳቦችን ከመሰንዘር መቆጠብ ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም በጉባኤ ውስጥ ክፍፍል እንዲፈጠር የሚያደርግ ምንም ነገር መናገር አንፈልግም። ለምሳሌ ያህል፣ የዓለም መሪዎች እንዴት አንድን ግጭት ፈተው ሰላምና ደህንነት እንደሚያሰፍኑ ሲያወሩ ልንሰማ እንችላለን። እንዲህ ያሉት ንግግሮች በ1 ተሰሎንቄ 5:3 ላይ ያለው ትንቢት እንዲፈጸም የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ ግምታዊ ሐሳብ ከመሰንዘር ይልቅ ይህን ጉዳይ አስመልክቶ የወጣውን ወቅታዊ መረጃ ልንከታተል ይገባል። የይሖዋ ድርጅት ባቀረበው መረጃ ላይ ተመሥርተን ከሌሎች ጋር የምንወያይ ከሆነ ጉባኤው ‘በአስተሳሰብ አንድነት እንዲኖረው’ አስተዋጽኦ እናደርጋለን።—1 ቆሮ. 1:10፤ 4:6፤ w23.02 16 አን. 4-5

ማክሰኞ፣ ግንቦት 28

ፈረስህን እየጋለብክ ለእውነት፣ ለትሕትናና ለጽድቅ ተዋጋ፤ ቀኝ እጅህም የሚያስፈሩ ተግባሮችን ያከናውናል።—መዝ. 45:4

ኢየሱስ ክርስቶስን የምትወደው ለምንድን ነው? ኢየሱስ ለእውነት፣ ለትሕትናና ለጽድቅ ጥብቅና ይቆማል። እውነትንና ጽድቅን የምትወድ ከሆነ ኢየሱስ ክርስቶስንም እንደምትወደው ግልጽ ነው። ኢየሱስ እውነትና ጽድቅ ለሆነው ነገር እንዴት በድፍረት ጥብቅና እንደቆመ ለማሰብ ሞክር። (ዮሐ. 18:37) ሆኖም ኢየሱስ ለትሕትና የሚቆመው እንዴት ነው? ኢየሱስ በሕይወቱ የተወው ምሳሌ ለትሕትና እንደሚቆም ያሳያል። ለምሳሌ ያህል፣ ለራሱ ክብር የሰጠበት አንድም ጊዜ የለም፤ በሁሉም ነገር አባቱ እንዲከበር አድርጓል። (ማር. 10:17, 18፤ ዮሐ. 5:19) የአምላክ ልጅ ስላሳየው ትሕትና ስታስብ ምን ይሰማሃል? እሱን ለመውደድና ምሳሌውን ለመከተል አትነሳሳም? እንደምትነሳሳ ምንም ጥርጥር የለውም። ኢየሱስ ትሑት የሆነው ለምንድን ነው? ትሑት የሆነውን አባቱን ስለሚወደውና የእሱን ምሳሌ ስለሚከተል ነው። (መዝ. 18:35፤ ዕብ. 1:3) ኢየሱስ የይሖዋን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ የሚያንጸባርቅ መሆኑ እሱን ይበልጥ እንድትወደው አያደርግህም? w23.03 3-4 አን. 6-7

ረቡዕ፣ ግንቦት 29

ጻድቃንም ሆኑ ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች ከሞት [ይነሳሉ]።—ሥራ 24:15

መጽሐፍ ቅዱስ ከሞት ተነስተው በምድር ላይ ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ የሚያገኙ ሁለት ቡድኖች እንዳሉ ይናገራል፤ እነሱም “ጻድቃን” እና “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” ናቸው። “ጻድቃን” የተባሉት በሕይወት በነበሩበት ወቅት ይሖዋን በታማኝነት ያገለገሉ ሰዎች ናቸው። “ጻድቃን ያልሆኑ ሰዎች” የተባሉት ግን እንዲህ አላደረጉም። ይሁንና ሁለቱም ቡድኖች ትንሣኤ የሚያገኙ መሆኑ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ እንደተጻፈ የሚጠቁም ነው? “ጻድቃን” የተባሉት ሰዎች ከመሞታቸው በፊት ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ነበር። ታዲያ ሲሞቱ ስማቸው ከዚህ መጽሐፍ ላይ ተሰርዟል? በፍጹም። ምክንያቱም ከይሖዋ አመለካከት አንጻር አሁንም ‘ሕያዋን’ ናቸው። ይሖዋ “የሕያዋን እንጂ የሙታን አምላክ አይደለም፤ በእሱ ፊት ሁሉም ሕያዋን ናቸውና።” (ሉቃስ 20:38) ከዚህ አንጻር ጻድቃን በምድር ላይ ትንሣኤ ሲያገኙ ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ውስጥ እንደተጻፈ ይገኛል። እርግጥ መጀመሪያ ላይ ስማቸው የሚገኘው በምሳሌያዊ ሁኔታ “በእርሳስ” ተጽፎ ነው።—ሉቃስ 14:14፤ w22.09 16 አን. 9-10

ሐሙስ፣ ግንቦት 30

ይሖዋ አምላክ ሰውየውን ወስዶ እንዲያለማውና እንዲንከባከበው በኤደን የአትክልት ስፍራ አስቀመጠው።—ዘፍ. 2:15

ይሖዋ የመጀመሪያው ሰው ፍጥረትን በማየት እንዲደሰት ይፈልግ ነበር። አምላክ አዳምን ከፈጠረው በኋላ ውብ በሆነች ገነት ውስጥ እንዲኖር ያደረገው ሲሆን ገነትን የማልማትና የማስፋፋት ሥራ ሰጥቶታል። (ዘፍ. 2:8, 9) አዳም ዘሮች ሲበቅሉና አበቦች ሲያብቡ ሲመለከት ምን ያህል ተደስቶ ሊሆን እንደሚችል መገመት እንችላለን። አዳም ኤደን ገነትን የመንከባከብ ልዩ መብት አግኝቶ ነበር! በተጨማሪም ይሖዋ ለእንስሳት ስም የማውጣቱን ኃላፊነት ለአዳም ሰጥቶታል። (ዘፍ. 2:19, 20) ይሖዋ ለእያንዳንዱ እንስሳ እሱ ራሱ ስም ማውጣት ይችል ነበር፤ እሱ ግን ይህን ኃላፊነት ለአዳም ሰጠው። አዳም ስም ከማውጣቱ በፊት እንስሳቱን በትኩረት በመመልከት ባሕርያቸውን እንዳጠና ምንም ጥርጥር የለውም። አዳም በዚህ ሥራ በጣም እንደተደሰተ መገመት እንችላለን። የአባቱን ጥበብና የፈጠራ ችሎታ ይበልጥ የሚያስተውልበት አጋጣሚ እንደሰጠው ግልጽ ነው። w23.03 16 አን. 3

ዓርብ፣ ግንቦት 31

እነዚህን መንግሥታት ሁሉ ያደቅቃል፤ ፈጽሞም ያጠፋቸዋል፤ እሱም ብቻውን ለዘላለም ይቆማል።—ዳን. 2:44

በግዙፉ ምስል እግሮች የተወከለው አንግሎ አሜሪካ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት መሠረት የመጨረሻው የዓለም ኃያል መንግሥት ነው። (ዳን. 2:31-33) ከእሱ በኋላ የሚነሳ ሌላ የዓለም ኃያል መንግሥት አይኖርም። ከዚህ ይልቅ የአምላክ መንግሥት በአርማጌዶን እሱንም ሆነ በምድር ላይ ያሉትን ሌሎች መንግሥታት በሙሉ ያደቃቸዋል። (ራእይ 16:13, 14, 16፤ 19:19, 20) ይህ ትንቢት የሚጠቅመን እንዴት ነው? የዳንኤል ትንቢት የምንኖረው በመጨረሻው ዘመን እንደሆነ የሚያሳይ ተጨማሪ ማስረጃ ይሰጠናል። ከ2,500 ዓመታት በፊት ዳንኤል ከባቢሎን በኋላ በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጉልህ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ አራት ሌሎች የዓለም ኃያላን መንግሥታት እንደሚነሱ ተንብዮ ነበር። በተጨማሪም የአንግሎ አሜሪካ የዓለም ኃያል መንግሥት ከእነዚህ መንግሥታት የመጨረሻው እንደሚሆን ገልጿል። ይህም የአምላክ መንግሥት በቅርቡ ሰብዓዊ መንግሥታትን በሙሉ እንደሚደመስስና ምድርን ሙሉ በሙሉ እንደሚቆጣጠር ተስፋ ይሰጠናል፤ ይህ ምንኛ የሚያጽናና ነው! w22.07 4 አን. 9፤ 5 አን. 11-12

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ