ሰኔ
ቅዳሜ፣ ሰኔ 1
ሥጋዬ ትልና የአፈር ጓል ለብሷል፤ ቆዳዬ በሙሉ አፈክፍኳል፤ ደግሞም መግል ይዟል።—ኢዮብ 7:5
ኢዮብ ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ወዳጅነት ነበረው። በተጨማሪም ደስታ የሰፈነበት ትልቅ ቤተሰብ ነበረው፤ እጅግ ባለጸጋም ነበር። (ኢዮብ 1:1-5) ሆኖም በአንድ ቀን ውስጥ ሁሉንም ነገር ተነጠቀ። በመጀመሪያ ንብረቱን አጣ። (ኢዮብ 1:13-17) ከዚያም የሚወዳቸው ልጆቹ በሙሉ ሞቱበት። ኢዮብና ሚስቱ አሥሩም ልጆቻቸው እንደሞቱ ሲሰሙ በከፍተኛ ድንጋጤ፣ ሐዘንና ተስፋ መቁረጥ ተውጠው እንደሚሆን ጥያቄ የለውም! ኢዮብ በሐዘን ልብሱን መቅደዱና መሬት ላይ መደፋቱ ምንም አያስገርምም! (ኢዮብ 1:18-20) ቀጥሎም ሰይጣን ከኢዮብ ጤንነቱንና ክብሩን ነጠቀው። (ኢዮብ 2:6-8) በአንድ ወቅት ኢዮብ በማኅበረሰቡ ዘንድ እጅግ የተከበረ ሰው ነበር። ሰዎች መጥተው ምክር ይጠይቁት ነበር። (ኢዮብ 31:18) አሁን ግን ሰዎች ራቁት። የገዛ ወንድሞቹ፣ የቅርብ ወዳጆቹ እና አገልጋዮቹ እንኳ አገለሉት!—ኢዮብ 19:13, 14, 16፤ w22.06 21 አን. 5-6
እሁድ፣ ሰኔ 2
በሁሉም ነገር . . . በፍቅር እንደግ።—ኤፌ. 4:15
እያንዳንዳችን ከተጠመቅን በኋላ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን ለሚገኙ የእምነት ባልንጀሮቹ የሰጣቸውን ምክር መከተል ይኖርብናል። ጳውሎስ የኤፌሶን ክርስቲያኖችን “ሙሉ ሰው” እንዲሆኑ አበረታቷቸዋል። (ኤፌ. 4:13) በሌላ አባባል ‘እድገት ማድረጋችሁን ቀጥሉ’ ብሏቸዋል። አሁንም ይሖዋን በጣም እንደምትወደው ምንም ጥያቄ የለውም። ሆኖም ለእሱ ያለህን ፍቅር ማሳደግ ትችላለህ። እንዴት? ሐዋርያው ጳውሎስ በፊልጵስዩስ 1:9 ላይ አንዱን መንገድ ጠቁሟል። ጳውሎስ የፊልጵስዩስ ክርስቲያኖች ፍቅራቸው “ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲሄድ” ጸልዮአል። ስለዚህ ፍቅራችን እየጨመረ እንዲሄድ ማድረግ እንችላለን ማለት ነው። ይህን ማድረግ የምንችለው “ትክክለኛ እውቀትና ጥልቅ ግንዛቤ” በማግኘት ነው። ይሖዋን ይበልጥ ባወቅነው መጠን ይበልጥ እንወደዋለን፤ እንዲሁም ለባሕርያቱና የተለያዩ ነገሮችን ለሚያከናውንበት መንገድ አድናቆት እናዳብራለን። እሱን ለማስደሰት ያለን ፍላጎት ይጨምራል፤ እሱን የሚያሳዝን ምንም ነገር ማድረግ አንፈልግም። የእሱ ፈቃድ ምን እንደሆነ እንዲሁም ፈቃዱን ማድረግ የምንችለው እንዴት እንደሆነ ለማስተዋል ጥረት እናደርጋለን። w22.08 2-3 አን. 3-4
ሰኞ፣ ሰኔ 3
በቅርብ ጊዜ ውስጥ ሊፈጸሙ የሚገባቸውን ነገሮች ለባሪያዎቹ እንዲያሳይ አምላክ ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠውና እሱ የገለጠው ራእይ ይህ ነው።—ራእይ 1:1
የራእይ መጽሐፍ የተጻፈው በአጠቃላይ ለዓለም ሕዝብ ሳይሆን ለእኛ ማለትም ራሳችንን ለወሰንን የአምላክ አገልጋዮች ነው። የአምላክ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን በዚህ አስደናቂ መጽሐፍ ውስጥ ባሉት ትንቢቶች ፍጻሜ ላይ የእኛም ድርሻ እንዳለበት ብናውቅ ልንገረም አይገባም። አረጋዊው ሐዋርያው ዮሐንስ እነዚህ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን የሚያገኙበትን ጊዜ ነግሮናል። “በመንፈስ ወደ ጌታ ቀን ተወሰድኩ” ብሏል። (ራእይ 1:10) ሐዋርያው ዮሐንስ በ96 ዓ.ም. ይህን ሐሳብ በጻፈበት ወቅት ‘የጌታ ቀን’ ሊጀምር ገና ብዙ ዘመናት ይቀሩት ነበር። (ማቴ. 25:14, 19፤ ሉቃስ 19:12) ሆኖም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንደሚያሳየው በ1914 ኢየሱስ በሰማይ ንጉሥ ሆኖ በተሾመበት ወቅት ይህ ቀን ጀመረ። ከዚህ ዓመት አንስቶ በራእይ መጽሐፍ ላይ የሚገኙት የአምላክን ሕዝቦች የሚመለከቱ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘት ጀመሩ። አዎ፣ ዛሬ የምንኖረው ‘በጌታ ቀን’ ነው!—ራእይ 1:3፤ w22.05 2 አን. 2-3
ማክሰኞ፣ ሰኔ 4
አውሬውም ተያዘ፤ . . . ሐሰተኛው ነቢይም ከእሱ ጋር ተያዘ።—ራእይ 19:20
አውሬውና ሐሰተኛው ነቢይ በሕይወት እንዳሉ በድኝ ወደሚነደው የእሳት ሐይቅ ተወረወሩ። እነዚህ የአምላክ ጠላቶች ጥፋት የሚደርስባቸው ሥልጣን ላይ እንዳሉ ነው፤ ጥፋታቸውም ዘላለማዊ ነው። ይህ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ለአምላክና ለመንግሥቱ ታማኞች መሆን አለብን። (ዮሐ. 18:36) ከዓለም ፖለቲካዊ ጉዳዮች ምንጊዜም ገለልተኛ መሆን ያስፈልገናል። ሆኖም እንዲህ ዓይነት አቋም መያዝ ከባድ የሚሆንበት ጊዜ አለ፤ ምክንያቱም የዓለም መንግሥታት በንግግራችንም ሆነ በተግባራችን ሙሉ ድጋፋችንን እንድንሰጣቸው ይጠብቁብናል። ለሚያሳድሩት ጫና የሚንበረከኩ ሁሉ የአውሬው ምልክት ይደረግባቸዋል። (ራእይ 13:16, 17) ይህ ምልክት የሚደረግበት ማንኛውም ሰው ግን የይሖዋ ቁጣ ይደርስበታል፤ የዘላለም ሕይወትም አያገኝም። (ራእይ 14:9, 10፤ 20:4) የሚደረግብን ጫና ምንም ያህል ከባድ ቢሆን ምንጊዜም የገለልተኝነት አቋም መያዛችን ምንኛ አስፈላጊ ነው። w22.05 10-11 አን. 12-13
ረቡዕ፣ ሰኔ 5
በሥራው የተካነን ሰው አይተሃል? በነገሥታት ፊት ይቆማል፤ ተራ በሆኑ ሰዎች ፊት አይቆምም።—ምሳሌ 22:29
ልታወጣ የምትችለው አንዱ ግብ ጠቃሚ ክህሎቶችን መማር ነው። ክህሎቶቻችንን የምናዳብር ከሆነ ተጨማሪ ኃላፊነቶችን ለመቀበል ብቁ እንሆናለን። የቤቴል ሕንፃዎችን እንዲሁም የትላልቅ እና የጉባኤ ስብሰባ አዳራሾችን ለመገንባት በርካታ ሠራተኞች እንደሚያስፈልጉ አስታውስ። በእነዚህ ሥራዎች ላይ የሚካፈሉ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ክህሎቶቻቸውን ያዳበሩት ልምድ ካላቸው ወንድሞችና እህቶች ጋር በመሥራት ነው። በዛሬው ጊዜ ወንድሞችም ሆኑ እህቶች የትላልቅ እና የጉባኤ ስብሰባ አዳራሾችን ለመንከባከብ የሚያስፈልጉ ክህሎቶችን እየተማሩ ነው። ‘የዘላለሙ ንጉሥ’ ይሖዋ አምላክና “የነገሥታት ንጉሥ” የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ የተካኑ ሠራተኞችን በመጠቀም አስደናቂ ሥራዎችን እያከናወኑ ነው። (1 ጢሞ. 1:17፤ 6:15) ጠንክረን የምንሠራውም ሆነ ክህሎቶቻችንን የምንጠቀመው ይሖዋን እንጂ ራሳችንን ለማስከበር አይደለም።—ዮሐ. 8:54፤ w22.04 24 አን. 7፤ 25 አን. 11
ሐሙስ፣ ሰኔ 6
ገንዘብ ጥበቃ [ያስገኛል]።—መክ. 7:12
ሰለሞን የናጠጠ ሀብታም ነበር፤ የሚኖረውም በቅንጦት ነበር። (1 ነገ. 10:7, 14, 15) በሌላ በኩል ደግሞ ኢየሱስ ብዙም ቁሳዊ ነገር አልነበረውም፤ የራሴ የሚለው ቤት እንኳ አልነበረውም። (ማቴ. 8:20) ሆኖም ሁለቱም ሰዎች ለቁሳዊ ነገር ሚዛናዊ አመለካከት ነበራቸው፤ ምክንያቱም የሁለቱም ጥበብ ምንጭ ይሖዋ ነው። ሰለሞን ገንዘብ ለሕይወት የሚያስፈልጉንን መሠረታዊ ነገሮችና ምናልባትም አንዳንድ ያማሩንን ነገሮች ለመግዛት እንደሚያስችለን ተናግሯል። ሆኖም ያ ሁሉ ሀብት የነበረው ሰለሞንም እንኳ ከገንዘብ ይበልጥ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮች እንዳሉ ተገንዝቦ ነበር። ለምሳሌ “መልካም ስም ከብዙ ሀብት ይመረጣል” ሲል ጽፏል። (ምሳሌ 22:1) በተጨማሪም ሰለሞን ገንዘብ የሚወዱ ሰዎች ብዙውን ጊዜ ባላቸው እንደማይረኩ አስተውሏል። (መክ. 5:10, 12) ከዚህም ሌላ እምነታችንን በገንዘብ ላይ እንዳንጥል አስጠንቅቋል፤ ምክንያቱም ያለን ገንዘብ በቀላሉ ሊጠፋ ይችላል።—ምሳሌ 23:4, 5፤ w22.05 21 አን. 4-5
ዓርብ፣ ሰኔ 7
ይሖዋ ሞገስ ሊያሳያችሁ በትዕግሥት ይጠባበቃል፤ ምሕረት ሊያሳያችሁም ይነሳል። ይሖዋ የፍትሕ አምላክ ነውና። እሱን በተስፋ የሚጠባበቁ ሁሉ ደስተኞች ናቸው።—ኢሳ. 30:18
አሁን ባሉን በረከቶች ላይ ስናሰላስል ከይሖዋ ጋር ያለን ዝምድና ይጠናከራል። ይሖዋ ወደፊት ባዘጋጀልን በረከቶች ላይ ማሰላሰላችን ደግሞ እሱን ለዘላለም ለማገልገል ያለን ተስፋ እውን ሆኖ እንዲታየን ያደርጋል። እነዚህ ነገሮች በሙሉ በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን በማገልገል ደስታ እንድናገኝ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ። ይሖዋ ይህን ክፉ ዓለም በማጥፋት ለእኛ ሲል “ይነሳል።” “የፍትሕ አምላክ” የሆነው ይሖዋ፣ የሰይጣን ዓለም የእሱ የፍትሕ መሥፈርት ከሚጠይቀው በላይ ለአንድ ቀን እንኳ እንዲቆይ እንደማይፈቅድ እርግጠኞች ነን። (ኢሳ. 25:9) ይህ የመዳን ቀን እስኪመጣ ከይሖዋ ጋር በትዕግሥት እንጠብቃለን። እስከዚያው ግን የጸሎት መብታችንን ከፍ አድርገን ለመመልከት፣ የአምላክን ቃል ለማጥናትና በሥራ ላይ ለማዋል እንዲሁም ባሉን በረከቶች ላይ ለማሰላሰል ቁርጥ ውሳኔ አድርገናል። እንዲህ ስናደርግ ይሖዋ እሱን እያመለክን በደስታ እንድንጸና ይረዳናል። w22.11 13 አን. 18-19
ቅዳሜ፣ ሰኔ 8
[የእናትህን] መመሪያ አትተው።—ምሳሌ 1:8, 9
መጽሐፍ ቅዱስ ጢሞቴዎስ ሲጠመቅ የነበረው ሁኔታ ምን ይመስል እንደነበር ባይናገርም እናቱ ኤውንቄ በዚያ ዕለት የተሰማትን ደስታ መገመት አያዳግትም። (ምሳሌ 23:25) ኤውንቄ ልጇ ይሖዋንና ኢየሱስ ክርስቶስን እንዲወድ በማስተማር ረገድ ተሳክቶላታል። ጢሞቴዎስ ያደገው በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ነው። አባቱ ግሪካዊ ነበር፤ እናቱና አያቱ ደግሞ አይሁዳውያን ነበሩ። (ሥራ 16:1) ኤውንቄ እና ሎይድ ክርስትናን ሲቀበሉ ጢሞቴዎስ በአሥራዎቹ ዕድሜ ያለ ወጣት ሳይሆን አይቀርም። አባቱ ግን ክርስትናን አልተቀበለም። ታዲያ ጢሞቴዎስ የትኛውን ጎዳና ይመርጥ ይሆን? በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያን እናቶችም ቤተሰባቸውን ይወዳሉ። ከምንም ነገር በላይ የሚፈልጉት ልጆቻቸው ከይሖዋ ጋር የጠበቀ ዝምድና እንዲኖራቸው መርዳት ነው። አምላካችንም ጥረታቸውን ከፍ አድርጎ ይመለከተዋል። (ምሳሌ 1:8, 9) ይሖዋ ስፍር ቁጥር የሌላቸውን እናቶች ልጆቻቸውን ስለ እሱ እንዲያስተምሩ ረድቷቸዋል። w22.04 16 አን. 1-3
እሁድ፣ ሰኔ 9
አምላክ . . . ሐሳቡን ዳር እንዲያደርሱ . . . ይህን በልባቸው አኑሯል።—ራእይ 17:17
ይሖዋ በቅርቡ ሐሳቡን በእነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች ልብ ውስጥ በማኖር “ሐሳቡን ዳር እንዲያደርሱ” ያደርጋል። ይህስ ምን ውጤት ያስገኛል? እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች ማለትም ‘አሥሩ ነገሥታት’ በሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች ላይ በመነሳት ያጠፏቸዋል። (ራእይ 17:1, 2, 12, 16) ታላቂቱ ባቢሎን መጥፊያዋ እንደቀረበ እንዴት እናውቃለን? ይህን ጥያቄ ለመመለስ አንድ ነገር ማስታወሳችን ጠቃሚ ነው፤ ታላቁ የኤፍራጥስ ወንዝ ለጥንቷ የባቢሎን ከተማ በተወሰነ መጠን ጥበቃ ያደርግላት ነበር። የራእይ መጽሐፍ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩትን የታላቂቱ ባቢሎን ደጋፊዎች ጥበቃ ከሚያደርጉ “ውኃዎች” ጋር አመሳስሏቸዋል። (ራእይ 17:15) ሆኖም የራእይ መጽሐፍ ውኃዎቹ ‘እንደሚደርቁም’ ይናገራል፤ ይህም በዓለም ላይ ያሉ የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶች ብዙዎቹን ደጋፊዎቻቸውን እንደሚያጡ ያመለክታል። (ራእይ 16:12) ይህ ትንቢት በዛሬው ጊዜ ሲፈጸም እየተመለከትን ነው፤ ብዙዎች የሐሰት ሃይማኖት ድርጅቶችን በመተው ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለማግኘት ወደ ሌሎች ምንጮች ዘወር ማለት ጀምረዋል። w22.07 5-6 አን. 14-15
ሰኞ፣ ሰኔ 10
ምሕረት የማያደርግ ሰው ያለምሕረት ይፈረድበታልና። ምሕረት በፍርድ ላይ ድል ይቀዳጃል።—ያዕ. 2:13
ሌሎችን ይቅር ማለት አድናቆት እንዳለን ያሳያል። ኢየሱስ በአንድ ምሳሌ ላይ ይሖዋን የባሪያውን ዕዳ ከሰረዘ ንጉሥ ጋር አመሳስሎታል፤ ይህ ባሪያ ከፍሎ ሊጨርሰው የማይችለው እጅግ ብዙ ዕዳ ነበረበት። ሆኖም ዕዳው የተሰረዘለት ባሪያ ከእሱ በጣም ያነሰ ገንዘብ ለተበደረው ባሪያ ምሕረት ሳያሳይ ቀርቷል። (ማቴ. 18:23-35) ኢየሱስ ይህን ምሳሌ የተናገረው ምን ሊያስተምረን ፈልጎ ነው? ይሖዋ ያሳየንን ታላቅ ምሕረት የምናደንቅ ከሆነ ሌሎችን ይቅር ለማለት እንነሳሳለን። (መዝ. 103:9) አንድ መጠበቂያ ግንብ ከበርካታ ዓመታት በፊት የሚከተለውን ሐሳብ ሰጥቶ ነበር፦ “ሌሎችን ምንም ያህል ጊዜ ይቅር ብንል አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት ካሳየን ምሕረትና ይቅር ባይነት ጋር ጨርሶ ሊተካከል አይችልም።” ሌሎችን ይቅር ካልን ይሖዋ ይቅር ይለናል። ይሖዋ ለመሐሪዎች ምሕረት ያደርጋል። (ማቴ. 5:7) ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዴት እንደሚጸልዩ ባስተማራቸው ወቅት ይህን ግልጽ አድርጓል።—ማቴ. 6:14, 15፤ w22.06 10 አን. 8-9
ማክሰኞ፣ ሰኔ 11
የምድር ብሔራት ሁሉ በዘርህ አማካኝነት ለራሳቸው በረከት ያገኛሉ።—ዘፍ. 22:18
ኢየሱስ ሰው ሆኖ ወደ ምድር መጥቷል። የአባቱንም ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል። (ዮሐ. 14:9) በመሆኑም በእሱ አማካኝነት ይሖዋ አምላክን ማወቅና መውደድ ችለናል። በተጨማሪም ከኢየሱስ ትምህርቶች እንዲሁም በዛሬው ጊዜ ክርስቲያን ጉባኤን ከሚመራበት መንገድ ጥቅም አግኝተናል። የይሖዋን ሞገስ በሚያስገኝ መንገድ መኖር የምንችለው እንዴት እንደሆነ አስተምሮናል። ደግሞም ሁላችንም ከኢየሱስ ሞት ጥቅም ማግኘት እንችላለን። ኢየሱስ ከሞት ሲነሳ የደሙን ዋጋ ‘ከኃጢአት ሁሉ የሚያነጻን’ ፍጹም መሥዋዕት አድርጎ አቅርቦታል። (1 ዮሐ. 1:7) አሁን ግርማ የተላበሰና የማይሞት ሕይወት ያለው ንጉሥ ነው። በቅርቡ ኢየሱስ የእባቡን ራስ ይጨፈልቃል። (ዘፍ. 3:15) ሰይጣን ከሕልውና ውጭ ሲሆን ታማኝ የሰው ልጆች በሙሉ እፎይ ይላሉ! እስከዚያው ድረስ ግን ተስፋ አትቁረጡ። አምላካችን እምነት የሚጣልበት ነው። ‘ለምድር ብሔራት ሁሉ’ የተትረፈረፈ በረከት ያፈስላቸዋል። w22.07 18 አን. 13፤ 19 አን. 19
ረቡዕ፣ ሰኔ 12
እንዲህ ካሉ መከራዎች ማምለጥ [አንችልም]።—1 ተሰ. 3:3
ግብ ስናወጣ እንደ አስፈላጊነቱ ማስተካከያ ለማድረግም ዝግጁ መሆን ይኖርብናል። ለምን? ምክንያቱም በሕይወታችን የሚያጋጥሙንን ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ መቆጣጠር አንችልም። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ በተሰሎንቄ አዲስ ጉባኤ እንዲቋቋም የበኩሉን አስተዋጽኦ አበርክቶ ነበር። ሆኖም ተቃዋሚዎች ጳውሎስ ከተማዋን ለቆ እንዲወጣ አስገደዱት። (ሥራ 17:1-5, 10) ጳውሎስ እዚያ ቢቆይ ኖሮ የወንድሞችን ደህንነት አደጋ ላይ መጣሉ የማይቀር ነበር። ሆኖም ጳውሎስ ተስፋ አልቆረጠም። ከዚህ ይልቅ ሁኔታውን ለማስተናገድ ተገቢውን እርምጃ ወስዷል። ከጊዜ በኋላ፣ በተሰሎንቄ የሚገኙ አዳዲስ ክርስቲያኖችን እንዲረዳ ጢሞቴዎስን ልኮታል። (1 ተሰ. 3:1, 2) የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች ምንኛ ተደስተው ይሆን! ጳውሎስ በተሰሎንቄ ካጋጠመው ተሞክሮ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። አንድ ዓይነት የአገልግሎት መብት ላይ ለመድረስ እየተጣጣርን ነው እንበል። ሆኖም ከቁጥጥራችን ውጭ በሆኑ ሁኔታዎች የተነሳ እዚህ መብት ላይ መድረስ አልቻልንም። (መክ. 9:11) እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ካጋጠመህ፣ ልትደርስበት የምትችለው ሌላ ግብ አውጣ። w22.04 25-26 አን. 14-15
ሐሙስ፣ ሰኔ 13
ፈተናን በጽናት ተቋቁሞ የሚኖር ሰው ደስተኛ ነው።—ያዕ. 1:12
ይሖዋ ለወደፊቱ ጊዜ ተስፋ በመስጠት ያጽናናናል። መከራ ሲያጋጥመን ሊያጽናኑን የሚችሉ ጥቂት የመጽሐፍ ቅዱስ ሐሳቦችን እስቲ እንመልከት። ይሖዋ ከባድ መከራን ጨምሮ ማንኛውም ነገር “[ከእሱ] ፍቅር ሊለየን እንደማይችል” በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ዋስትና ሰጥቶናል። (ሮም 8:38, 39) በተጨማሪም በጸሎት “ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ” እንደሆነ ማረጋገጫ ሰጥቶናል። (መዝ. 145:18) ይሖዋ በእሱ እስከታመንን ድረስ ማንኛውንም ፈተና በጽናት መወጣት፣ አልፎ ተርፎም በመከራ ውስጥ ሆነንም ደስታ ማግኘት እንደምንችል ነግሮናል። (1 ቆሮ. 10:13፤ ያዕ. 1:2) ከዚህም ሌላ የአምላክ ቃል፣ በአሁኑ ጊዜ የሚያጋጥሙን ፈተናዎች አምላክ ወደፊት ከሚሰጠን ዘላለማዊ በረከቶች ጋር ሲወዳደሩ ጊዜያዊና አጭር እንደሆኑ ያስታውሰናል። (2 ቆሮ. 4:16-18) ይሖዋ የችግሮቻችንን ዋነኛ መንስኤ እንደሚያስወግድ፣ ማለትም ሰይጣን ዲያብሎስንና የእሱን የክፋት ጎዳና የሚከተሉትን በሙሉ እንደሚያጠፋ አስተማማኝ ተስፋ ሰጥቶናል። (መዝ. 37:10) ወደፊት የሚያጋጥሙህን ፈተናዎች በጽናት ለመወጣት የሚረዱ አንዳንድ የሚያጽናኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃልህ ይዘሃል? w22.08 11 አን. 11
ዓርብ፣ ሰኔ 14
[እነዚህን ነገሮች] ማሰባችሁን አታቋርጡ።—ፊልጵ. 4:8
ከዕለት ዕለት፣ ከዓመት ዓመት በይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች መመላለስ መቻልህን የምትጠራጠርበት ጊዜ አለ? ይሖዋ ጽድቃችን “እንደ ባሕር ሞገድ” እንደሚሆን ቃል ገብቷል። (ኢሳ. 48:18) በተንጣለለ ባሕር ዳርቻ ላይ ቆመህ የባሕሩ ሞገድ ያለማቋረጥ ተከታትሎ ሲመጣ እያየህ ነው እንበል። በዚህ የተረጋጋ ቦታ ሆነህ ‘እነዚህ ሞገዶች አንድ ቀን መምጣታቸውን ቢያቆሙስ?’ የሚል ስጋት ይፈጠርብሃል? በጭራሽ! ሞገዶቹ መምጣታቸውን እንደሚቀጥሉ እርግጠኛ ነህ። የአንተም ጽድቅ ልክ እንደ ባሕር ሞገድ ሊሆን ይችላል! እንዴት? ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ይሖዋ ምን እንድታደርግ እንደሚፈልግ ቆም ብለህ አስብ። ከዚያም ውሳኔውን ተግባራዊ አድርግ። ውሳኔው ምንም ያህል ከባድ ቢሆን፣ የሚወድህ አባትህ ዕለት ዕለት ያለማቋረጥ ከእሱ የጽድቅ መሥፈርቶች ጋር በሚስማማ መንገድ እንድትመላለስ ከጎንህ ሆኖ ይረዳሃል።—ኢሳ. 40:29-31፤ w22.08 30 አን. 15-17
ቅዳሜ፣ ሰኔ 15
ይህ 1,000 ዓመት እንዳበቃም ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል።—ራእይ 20:7
በ1,000 ዓመቱ መጨረሻ ላይ ሰይጣን ከእስራቱ ይፈታል። ከዚያም ፍጹም የሆኑ ሰዎችን ለማሳሳት ይሞክራል። በዚያ የፈተና ወቅት በምድር ላይ ያሉ ፍጹም የሰው ልጆች በሙሉ ከአምላክ ስምና ከሉዓላዊነቱ ጋር በተያያዘ በተነሳው ጥያቄ ላይ ከየትኛው ወገን እንደሚሰለፉ በግልጽ የሚያሳዩበት አጋጣሚ ያገኛሉ። (ራእይ 20:8-10) ስማቸው በሕይወት መጽሐፍ ላይ በቋሚነት መጻፍ አለመጻፉ የተመካው ለሰይጣን ፈተና በግለሰብ ደረጃ በሚሰጡት ምላሽ ላይ ነው። ቁጥራቸው ያልተጠቀሰ ሰዎች እንደ አዳምና እንደ ሔዋን የይሖዋን አገዛዝ ለመቀበል አሻፈረን ይላሉ። እነዚህ ሰዎች ምን ይደርስባቸዋል? ራእይ 20:15 መልሱን ይሰጠናል፦ “በሕይወት መጽሐፍ ላይ ተጽፎ ያልተገኘ ሁሉ ወደ እሳቱ ሐይቅ ተወረወረ።” አዎ፣ እነዚህ ዓመፀኞች ለዘላለም ሙሉ በሙሉ ይጠፋሉ። ሆኖም አብዛኞቹ ፍጹም ሰዎች ይህን የመጨረሻ ፈተና ያልፋሉ። w22.09 23-24 አን. 15-16
እሁድ፣ ሰኔ 16
በሙሴ ሥርዓት መሠረት ካልተገረዛችሁ በቀር ልትድኑ አትችሉም።—ሥራ 15:1
በመጀመሪያው መቶ ዘመን በነበረው ጉባኤ ውስጥ አንዳንዶች ወደ ክርስትና የመጡ አሕዛብ መገረዝ እንዳለባቸው ይናገሩ ነበር፤ ይህን ያሉት የሌሎችን ትችት ለማስቀረት ብለው ሊሆን ይችላል። (ገላ. 6:12) ሐዋርያው ጳውሎስ ይህን አመለካከት ጨርሶ አልተቀበለውም፤ ሆኖም ‘እኔ ያልኩት ካልሆነ’ ብሎ ድርቅ ከማለት ይልቅ ትሕትና በማሳየት ጉዳዩን በኢየሩሳሌም ወደሚገኙት ሐዋርያትና ሽማግሌዎች መራው። (ሥራ 15:2) ጳውሎስ ጉዳዩን በዚያ መንገድ መያዙ በጉባኤው ውስጥ ሰላምና ደስታ እንዲሰፍን አድርጓል። (ሥራ 15:30, 31) ከባድ አለመግባባት በሚፈጠርበት ጊዜ፣ ይሖዋ ጉባኤውን እንዲንከባከቡ ከሾማቸው አካላት መመሪያ በመፈለግ ሰላም ለማስፈን ጥረት እናደርጋለን። ብዙውን ጊዜ በጽሑፎቻችን ወይም ድርጅቱ በሚያወጣቸው መመሪያዎች ውስጥ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ምክር ማግኘት እንችላለን። የራሳችንን አመለካከት ከማራመድ ይልቅ እነዚህን መመሪያዎች በመከተል ላይ ትኩረት ካደረግን በጉባኤው ውስጥ ሰላም እንዲሰፍን የበኩላችንን አስተዋጽኦ እናበረክታለን። w22.08 22 አን. 8-9
ሰኞ፣ ሰኔ 17
እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው።—ምሳሌ 17:17
አብዛኞቻችን ስሜታችንን አውጥተን ለጓደኞቻችን መናገር የምንፈልግበት ጊዜ ይኖራል። አንዳንድ ጊዜ ግን እንዲህ ማድረግ ሊከብደን ይችላል። ስሜታችንን አውጥተን ለሌሎች መናገር አልለመድን ይሆናል። ጓደኛችን ሚስጥራችንን ለሌላ ሰው እንደተናገረብን ካወቅን ደግሞ በጣም እንደምናዝን ጥያቄ የለውም። በሌላ በኩል ግን ሚስጥር ጠባቂ የሆኑ ጓደኞች ካሉን በጣም አመስጋኝ እንሆናለን! ሚስጥር ጠባቂ በመሆናቸው የሚታወቁ ሽማግሌዎች ለወንድሞቻቸው “ከነፋስ እንደ መከለያ፣ ከውሽንፍር እንደ መሸሸጊያ” ናቸው። (ኢሳ. 32:2) እነዚህ ወንድሞች ሚስጥራችንን እንደሚጠብቁልን በመተማመን በነፃነት ልናነጋግራቸው እንችላለን። በሚስጥር ሊያዙ የሚገባቸውን ነገሮች እንዲነግሩን አንጎተጉታቸውም። በተጨማሪም የሽማግሌ ሚስቶች ከባሎቻቸው ሚስጥራዊ መረጃ ለማወጣጣት ስለማይሞክሩ በጣም እናደንቃቸዋለን። ደግሞም የሽማግሌ ሚስቶች ስለ ወንድሞቻቸውና ስለ እህቶቻቸው ሚስጥራዊ መረጃ አለመስማታቸው ይጠቅማቸዋል። w22.09 11 አን. 10-11
ማክሰኞ፣ ሰኔ 18
እኔ አምላክ [ነኝ]። በብሔራት መካከል ከፍ ከፍ እላለሁ።—መዝ. 46:10
ይሖዋ በመጪው “ታላቅ መከራ” ወቅት ታማኝ አገልጋዮቹን እንደሚያድናቸው እርግጠኞች መሆን እንችላለን። (ማቴ. 24:21፤ ዳን. 12:1) ይህን የሚያደርገው፣ የማጎጉ ጎግ ማለትም ግንባር የፈጠሩ ብሔራት በዓለም ዙሪያ ባሉ ታማኝ የይሖዋ ሕዝቦች ላይ በጭካኔ ጥቃት በሚሰነዝሩበት ወቅት ነው። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል የሆኑት 193 አገራት በሙሉ ግንባር ቢፈጥሩ እንኳ ከሁሉ ከላቀው አምላክና ከሰማያዊ ሠራዊቱ ጋር ሊተካከሉ አይችሉም። ይሖዋ እንዲህ ሲል ቃል ገብቷል፦ “ራሴን ገናና አደርጋለሁ፤ እንዲሁም ራሴን እቀድሳለሁ፤ በብዙ ብሔራትም ፊት ማንነቴ እንዲታወቅ አደርጋለሁ፤ እኔ ይሖዋ እንደሆንኩ ያውቃሉ።” (ሕዝ. 38:14-16, 23) የጎግ ጥቃት ይሖዋ የመጨረሻውን ጦርነት እንዲያካሂድ ያነሳሳዋል። ይሖዋ ‘የዓለምን ነገሥታት ሁሉ’ በአርማጌዶን ያጠፋቸዋል። (ራእይ 16:14, 16፤ 19:19-21) በአንጻሩ “በምድር ላይ የሚኖሩት ቅኖች ብቻ [ይሆናሉ]፤ በእሷም ላይ የሚቀሩት ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ ናቸው።”—ምሳሌ 2:21 ግርጌ፤ w22.10 16-17 አን. 16-17
ረቡዕ፣ ሰኔ 19
[የአምላክ] ፈቃድ ሁሉም ዓይነት ሰዎች እንዲድኑና የእውነትን ትክክለኛ እውቀት እንዲያገኙ ነው።—1 ጢሞ. 2:4
የሰዎችን ልብ ማንበብ አንችልም፤ ‘ውስጣዊ ዓላማን የሚመረምረው’ ይሖዋ ብቻ ነው። (ምሳሌ 16:2) እሱ ባሕልና አስተዳደግ ሳይለይ ሁሉንም ዓይነት ሰዎች ይወዳል። በተጨማሪም ይሖዋ ‘ልባችንን ወለል አድርገን እንድንከፍት’ አበረታቶናል። (2 ቆሮ. 6:13) የመንፈሳዊ ቤተሰባችንን አባላት በሙሉ መውደድ እንጂ በእነሱ ላይ መፍረድ አንፈልግም። ከጉባኤው ውጭ ባሉ ሰዎችም ላይ መፍረድ አይኖርብንም። እምነትህን የማይጋራ አንድ ዘመድህን በተመለከተ “እሱማ መቼም ወደ እውነት አይመጣም” ብለህ ትፈርድበታለህ? ይህ እብሪተኝነትና ተመጻዳቂነት ይሆናል። ይሖዋ “በየቦታው ያሉ ሰዎች ሁሉ ንስሐ እንዲገቡ” አሁንም አጋጣሚ ሰጥቷል። (ሥራ 17:30) ራስን ማመጻደቅ በራሱ ጽድቅ የጎደለው ድርጊት እንደሆነ አትዘንጋ። ለይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ያለን ፍቅር ደስተኛ ያደርገናል፤ እንዲሁም ሌሎች ሰዎች ወደ እኛም ሆነ ወደ አምላካችን እንዲቀርቡ ያነሳሳቸዋል። w22.08 31 አን. 20-22
ሐሙስ፣ ሰኔ 20
በመካከላቸው ነቢይ እንደነበረ በእርግጥ ያውቃሉ።—ሕዝ. 2:5
የስብከቱን ሥራችንን ስናከናውን ተቃውሞ ሊያጋጥመን እንደሚችል እንጠብቃለን። እንዲህ ያለው ተቃውሞ ደግሞ ወደፊት እየጨመረ መሄዱ አይቀርም። (ዳን. 11:44፤ 2 ጢሞ. 3:12፤ ራእይ 16:21) ያም ቢሆን ይሖዋ የሚያስፈልገንን እርዳታ እንደሚሰጠን እርግጠኞች መሆን እንችላለን። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? ጥንትም ሆነ ዛሬ፣ ይሖዋ አገልጋዮቹ በጣም ከባድ የሆኑ ኃላፊነቶችን እንኳ እንዲወጡ ረድቷቸዋል። ለምሳሌ በባቢሎን ለነበሩት አይሁዳውያን ግዞተኞች ይሰብክ የነበረው ነቢዩ ሕዝቅኤል ያጋጠሙትን ነገሮች እንመልከት። ሕዝቅኤል በሚሰብክበት ክልል ውስጥ የሚኖሩት ሰዎች ምን ዓይነት ነበሩ? ይሖዋ እነዚህ ሰዎች “ግትር፣” “ልበ ደንዳና” እና “ዓመፀኛ” እንደሆኑ ተናግሯል። እንደ እሾህ ጎጂ እና እንደ ጊንጥ አደገኛ ነበሩ። ከዚህ አንጻር ይሖዋ ለሕዝቅኤል በተደጋጋሚ “አትፍራ” ያለው መሆኑ አያስገርምም። (ሕዝ. 2:3-6) ያም ቢሆን ሕዝቅኤል የተሰጠውን የስብከት ተልእኮ መወጣት ችሏል። ምክንያቱም (1) የተላከው በይሖዋ ነበር፤ (2) የአምላክ መንፈስ ኃይል ሰጥቶታል፤ እንዲሁም (3) የአምላክ ቃል እንደ ምግብ ሆኖለታል። w22.11 2 አን. 1-2
ዓርብ፣ ሰኔ 21
ከዚህ ዛፍ በበላህ ቀን በእርግጥ ትሞታለህ።—ዘፍ. 2:17
ከሰዎች በስተቀር በምድር ላይ ያሉ ሕያዋን ፍጥረታት በሙሉ የተፈጠሩት ለዘላለም እንዲኖሩ አይደለም። ለሰዎች ግን ይሖዋ ያለመሞት ልዩ መብት ሰጥቷቸው ነበር። ከዚህም ሌላ፣ ይሖዋ የፈጠረን በሕይወት የመቀጠል ከፍተኛ ፍላጎት እንዲኖረን አድርጎ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሰው ልጆች ሲናገር “[አምላክ] ዘላለማዊነትን በልባቸው ውስጥ አኑሯል” ይላል። (መክ. 3:11) ሞትን እንደ ጠላት የምንመለከትበት አንዱ ምክንያት ይህ ነው። (1 ቆሮ. 15:26) በጠና ብንታመም ሁኔታውን ተቀብለን እጃችንን አጣጥፈን እንቀመጣለን? በፍጹም። አብዛኞቻችን ሐኪም ጋ መሄዳችን፣ ምናልባትም ከበሽታው ለመዳን መድኃኒት መውሰዳችን አይቀርም። እንዲያውም ከሞት ለማምለጥ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን። በተጨማሪም የምንወደው ሰው ሲሞት፣ ግለሰቡ ወጣትም ሆነ አረጋዊ ጥልቅ የሆነ የስሜት ሥቃይ ይሰማናል። (ዮሐ. 11:32, 33) በእርግጥም የሚወደን ፈጣሪያችን፣ ሰዎች ለዘላለም እንዲኖሩ ዓላማው ባይሆን ኖሮ ለዘላለም የመኖር ፍላጎትም ሆነ አቅም አይሰጠንም ነበር። w22.12 3 አን. 5፤ 4 አን. 7
ቅዳሜ፣ ሰኔ 22
በዓለም ዙሪያ በመላው የወንድማማች ማኅበር ውስጥ ያሉት ወንድሞቻችሁ ተመሳሳይ መከራ እየደረሰባቸው [ነው]።—1 ጴጥ. 5:9
በዚህ አስቸጋሪ ጊዜ ብዙ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሊታመሙ፣ ፍርሃት ሊያድርባቸው ወይም ብቸኝነት ሊሰማቸው ይችላል። ወንድሞችህንና እህቶችህን ለማግኘት ጥረት አድርግ። ወረርሽኝ ሲከሰት ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር በምንሆንበት ጊዜም ጭምር አካላዊ ርቀት መጠበቅ ሊኖርብን ይችላል። በዚህ ጊዜ እንደ ሐዋርያው ዮሐንስ ዓይነት ስሜት ይሰማህ ይሆናል። ዮሐንስ ወዳጁን ጋይዮስን በአካል ማግኘት ይፈልግ ነበር። (3 ዮሐ. 13, 14) ሆኖም ዮሐንስ ለተወሰነ ጊዜ ያህል ጋይዮስን ሊያገኘው እንደማይችል ተገንዝቧል። በመሆኑም ዮሐንስ ማድረግ የሚችለውን ነገር አደረገ፤ ለጋይዮስ ደብዳቤ ጻፈለት። አንተም ወንድሞችህንና እህቶችህን በአካል ማግኘት ካልቻልክ በሌሎች ዘዴዎች እነሱን ለማነጋገር ጥረት አድርግ። ከእምነት ባልንጀሮችህ ጋር አዘውትረህ መገናኘትህ የሰላምና የደህንነት ስሜት እንዲሰማህ ያደርጋል። ከባድ ጭንቀት ከተሰማህ ሽማግሌዎችን ለማነጋገር ጥረት አድርግ፤ የሚሰጡህን ፍቅራዊ ማበረታቻም ተቀበል።—ኢሳ. 32:1, 2፤ w22.12 17-18 አን. 6-7
እሁድ፣ ሰኔ 23
የዮሴፍ ጌታ ዮሴፍን ወስዶ የንጉሡ እስረኞች የታሰሩበት እስር ቤት አስገባው።—ዘፍ. 39:20
መጽሐፍ ቅዱስ፣ ዮሴፍ ለተወሰነ ጊዜ ያህል እግሮቹ በእግር ብረት እንደታሰሩና አንገቱም ብረት ውስጥ እንደገባ ይገልጻል። (መዝ. 105:17, 18) የዮሴፍ ሁኔታ ከድጡ ወደ ማጡ ሄዶ ነበር። የጌታውን አመኔታ ያተረፈ ባሪያ የነበረው ዮሴፍ አሁን ደግሞ እስረኛ ሆነ። ያለህበትን አስጨናቂ ሁኔታ አስመልክቶ ልባዊ ጸሎት ብታቀርብም እንኳ ሁኔታው ተባብሶ ያውቃል? ይህ ሊያጋጥም ይችላል። የምንኖረው በሰይጣን ዓለም ውስጥ እንደመሆኑ መጠን ይሖዋ ፈተናዎች እንዳይደርሱብን አይከላከልልንም። (1 ዮሐ. 5:19) ያም ቢሆን ስለ አንድ ነገር እርግጠኞች መሆን እንችላለን፦ ይሖዋ የሚያጋጥመንን መከራ በሚገባ ያውቃል፤ እንዲሁም ያስብልናል። (ማቴ. 10:29-31፤ 1 ጴጥ. 5:6, 7) በተጨማሪም “ፈጽሞ አልተውህም፤ በምንም ዓይነት አልጥልህም” የሚል ቃል ገብቶልናል። (ዕብ. 13:5) ያለንበት ሁኔታ ተስፋ አስቆራጭ ቢመስልም እንኳ ይሖዋ ያጋጠመንን ፈተና በጽናት እንድንቋቋም ይረዳናል። w23.01 16 አን. 7-8
ሰኞ፣ ሰኔ 24
አምላካችን . . . ይቅርታው ብዙ ነው።—ኢሳ. 55:7
ቅዱሳን መጻሕፍት አምላካችን ስህተት ስንሠራ እርግፍ አድርጎ እንደማይተወን ማረጋገጫ ይሰጡናል። እስራኤላውያን በተደጋጋሚ ጊዜ በይሖዋ ላይ ኃጢአት ሠርተዋል፤ ከልባቸው ንስሐ ሲገቡ ግን አምላክ ይቅር ብሏቸዋል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ ክርስቲያኖችም አምላክ ምን ያህል አፍቃሪ እንደሆነ የሚያዩበት አጋጣሚ ነበራቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ ከባድ ኃጢአት የሠራን በኋላ ግን ንስሐ የገባን ሰው የእምነት ባልንጀሮቹ ‘ይቅር ሊሉትና ሊያጽናኑት’ እንደሚገባ በመንፈስ መሪነት ማበረታቻ ሰጥቶ ነበር። (2 ቆሮ. 2:6, 7፤ 1 ቆሮ. 5:1-5) ይሖዋ በጥንት ጊዜ የነበሩ አገልጋዮቹን ኃጢአት ስለሠሩ ብቻ እንዳልተዋቸው ማወቅ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ከዚህ ይልቅ በፍቅር ተነሳስቶ ይረዳቸው፣ ያስተካክላቸውና ወደ እሱ እንዲመለሱ ግብዣ ያቀርብላቸው ነበር። በዛሬው ጊዜ ላሉ ንስሐ የሚገቡ ኃጢአተኞችም እንዲሁ እንደሚያደርግ ቃል ገብቷል። (ያዕ. 4:8-10) መጽሐፍ ቅዱስ የአምላክን ጥበብ፣ ፍትሕና ፍቅር ይገልጣል። ይህ መጽሐፍ ይሖዋ እንድናውቀው እንደሚፈልግ ማረጋገጫ ይሰጠናል። ይሖዋ ወዳጆቹ እንድንሆን ይፈልጋል። w23.02 7 አን. 16-17
ማክሰኞ፣ ሰኔ 25
ትኩረት መስጠታችሁ መልካም ነው።—2 ጴጥ. 1:19
በአሁኑ ጊዜ በዓለማችን ላይ እየተከናወኑ ያሉት ነገሮች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም የሚያደርጉት እንዴት እንደሆነ የምንከታተልበት በቂ ምክንያት አለን። ለምሳሌ ያህል፣ ኢየሱስ የሰይጣን ሥርዓት የሚጠፋበት ጊዜ መቃረቡን ለማወቅ የሚረዱንን ዝርዝር ክንውኖች ነግሮናል። (ማቴ. 24:3-14) በተጨማሪም ሐዋርያው ጴጥሮስ እምነታችን ጠንካራ ሆኖ እንዲቀጥል ከፈለግን የትንቢቶችን ፍጻሜ በትኩረት እንድንከታተል አበረታቶናል። (2 ጴጥ. 1:20, 21) የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን ስንመረምር ሚዛናዊ እንድንሆን መክሮናል። ጴጥሮስ ‘የይሖዋን ቀን መምጣት በአእምሯችን አቅርበን እንድንመለከት’ አሳስቦናል። (2 ጴጥ. 3:11-13) ለምን? እንዲህ የምናደርገው ይሖዋ አርማጌዶንን የሚያመጣበትን “ቀንና ሰዓት” ለማስላት አይደለም፤ ከዚህ ይልቅ የቀረንን ጊዜ ‘ቅዱስ ሥነ ምግባር ለመከተልና ለአምላክ ያደርን መሆናችንን የሚያሳዩ ተግባሮች ለመፈጸም’ ልንጠቀምበት ስለምንፈልግ ነው። (ማቴ. 24:36፤ ሉቃስ 12:40) ንጹሕ ምግባር ይዘን መቀጠልና ይሖዋን ለማገልገል የምናደርገው ጥረት ለእሱ ያለንን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳይ መሆኑን ማረጋገጥ እንፈልጋለን። እንዲህ ለማድረግ ደግሞ ለራሳችን ምንጊዜም ትኩረት መስጠት ያስፈልገናል። w23.02 16 አን. 4, 6
ረቡዕ፣ ሰኔ 26
ሌሎች በጎች አሉኝ፤ እነሱንም ማምጣት አለብኝ።—ዮሐ. 10:16
“ሌሎች በጎች” በገነት ውስጥ ለመኖር የሚያስፈልገውን ብቃት ለማሟላት ከአሁኑ ማድረግ ያለባቸው ነገር አለ። ለኢየሱስ ያለንን አድናቆት ማሳየት አለብን። ለምሳሌ በመንፈስ የተቀቡ ወንድሞቹን በምንይዝበት መንገድ ለእሱ ያለንን ፍቅር ማሳየት እንችላለን። ኢየሱስ ለበጎቹ የሚፈርድላቸው ይህን መሠረት አድርጎ እንደሆነ ተናግሯል። (ማቴ. 25:31-40) በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ በቅንዓት በመካፈል እነሱን መደገፍ እንችላለን። (ማቴ. 28:18-20) ይሖዋ በገነት ውስጥ እንዲኖሩ የሚፈልጋቸው ዓይነት ሰዎች ለመሆን እዚያ እስክንገባ መጠበቅ አያስፈልገንም። ከአሁኑ በንግግራችንና በድርጊታችን ሐቀኛ ለመሆን እንዲሁም በልማዳችን ልከኛ ለመሆን ጥረት ማድረግ እንችላለን። ከዚህም ሌላ ለይሖዋ፣ ለትዳር ጓደኛችን እንዲሁም ለእምነት ባልንጀሮቻችን ታማኞች መሆን እንችላለን። በዚህ ክፉ ዓለም ውስጥ እየኖርን የአምላክን መሥፈርቶች በጥብቅ በተከተልን መጠን በገነት ውስጥ በአምላክ መሥፈርቶች መመራት ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል። በተጨማሪም በገነት ውስጥ ለመኖር እየተዘጋጀን እንዳለን ለማሳየት አንዳንድ ክህሎቶችንና ባሕርያትን ማዳበር እንችላለን። w22.12 11-12 አን. 14-16
ሐሙስ፣ ሰኔ 27
እኔን የሚወደኝን ሁሉ . . . አባቴ ይወደዋል።—ዮሐ. 14:21
ኢየሱስ ከማንም የተሻለ ገዢ ስለሆነ ንጉሣችን በመሆኑ ደስተኞች ነን። ኢየሱስን ያሠለጠነውና ገዢ እንዲሆን የሾመው ይሖዋ ነው። (ኢሳ. 50:4, 5) ኢየሱስ ስላሳየው ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ ፍቅርም ለማሰብ ሞክር። (ዮሐ. 13:1) በእርግጥም ንጉሣችን ኢየሱስ ሊወደድ ይገባዋል። ወዳጆቼ ብሎ የሚጠራቸው እሱን ከልባቸው የሚወዱ ሰዎች ትእዛዛቱን በመጠበቅ ፍቅራቸውን እንደሚያሳዩ ተናግሯል። (ዮሐ. 14:15፤ 15:14, 15) የይሖዋ ልጅ ወዳጅ መሆን እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ኢየሱስ ትሑትና የአባቱ ፍጹም ነጸብራቅ እንደሆነ ታውቃለህ። የተራቡትን እንደመገበ፣ ተስፋ የቆረጡትን እንዳጽናና፣ አልፎ ተርፎም የታመሙትን እንደፈወሰ ተምረሃል። (ማቴ. 14:14-21) በዛሬው ጊዜ ጉባኤውን እንዴት እየመራ እንዳለ ተመልክተሃል። (ማቴ. 23:10) ደግሞም የአምላክ መንግሥት ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ወደፊት ከአሁኑ እጅግ የላቁ ነገሮችን እንደሚያከናውን ታምናለህ። ታዲያ ኢየሱስን እንደምትወደው ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? ምሳሌውን በመከተል ነው። ራስህን መወሰንህና መጠመቅህ ይህን ማድረግ ከምትችልባቸው የመጀመሪያዎቹ እርምጃዎች መካከል አንዱ ነው ሊባል ይችላል። w23.03 4 አን. 8, 10
ዓርብ፣ ሰኔ 28
ዓይናችሁን ወደ ሰማይ አንስታችሁ ተመልከቱ። እነዚህን ነገሮች የፈጠረ ማን ነው?—ኢሳ. 40:26
ይሖዋ ሰማያትን ብቻ ሳይሆን ምድርንና ባሕርንም ጭምር አስደናቂ በሆኑ የፍጥረት ሥራዎቹ ሞልቷል፤ እኛም ከእነዚህ የፍጥረት ሥራዎቹ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። (መዝ. 104:24, 25) እስቲ አምላክ እኛን የፈጠረበትን መንገድ እንኳ ለማሰብ ሞክሩ። በተፈጥሮ ላይ የምናያቸውን የሚያማምሩ ነገሮች የማድነቅ ችሎታ በውስጣችን አኑሯል። በተጨማሪም በአምስቱ የስሜት ሕዋሶቻችን ማለትም በማየት፣ በመስማት፣ በመዳሰስ፣ በመቅመስና በማሽተት ችሎታችን ተጠቅመን የተለያዩ ፍጥረታቱን ማድነቅ እንድንችል አድርጎ ፈጥሮናል። መጽሐፍ ቅዱስ ፍጥረትን ለመመርመር የሚያነሳሳንን ሌላ አስፈላጊ ምክንያት ይጠቅሳል። ፍጥረት ስለ ይሖዋ ባሕርያት ያስተምረናል። (ሮም 1:20) ለምሳሌ ያህል፣ በፍጥረት ሥራዎች ላይ በግልጽ የሚታየውን ንድፍ ለማሰብ ሞክሩ። የአምላክን ጥበብ የሚያንጸባርቅ አይደለም? የምንመገባቸውን የተለያዩ ዓይነት ምግቦችም ለማሰብ ሞክሩ። ይህ ለሰው ልጆች ያለውን ፍቅር በግልጽ የሚያሳይ ነው። የይሖዋን የፍጥረት ሥራዎች በማየት ባሕርያቱን ስናስተውል እሱን በደንብ ልናውቀውና ወደ እሱ ይበልጥ ለመቅረብ ልንነሳሳ እንችላለን። w23.03 16 አን. 4-5
ቅዳሜ፣ ሰኔ 29
የቃልህ ፍሬ ነገር እውነት ነው።—መዝ. 119:160
የዓለም ሁኔታ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ ሲሄድ በእውነት ላይ ያለን እምነት መፈተኑ አይቀርም። አንዳንድ ሰዎች ስለ መጽሐፍ ቅዱስ እውነተኝነት ወይም ይሖዋ በዘመናችን አገልጋዮቹን ለመምራት ታማኝና ልባም ባሪያን ስለመሾሙ ጥርጣሬ ሊዘሩብን ይሞክሩ ይሆናል። ሆኖም የይሖዋ ቃል ሁልጊዜም እውነት እንደሆነ እርግጠኞች ከሆንን በእምነታችን ላይ የሚሰነዘሩትን እንዲህ ያሉ ጥቃቶች መመከት እንችላለን። የይሖዋን ‘ሥርዓት በሕይወታችን ዘመን ሁሉ፣ እስከ መጨረሻው ለመጠበቅ’ ቁርጥ ውሳኔ እናደርጋለን። (መዝ. 119:112) ለሌሎች ስለ እውነት መናገር እንዲሁም የመጽሐፍ ቅዱስን ምክር እንዲከተሉ ማበረታታት ‘አያሳፍረንም።’ (መዝ. 119:46) ከዚህም ሌላ ስደትን ጨምሮ ማንኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ቢደርስብን “በትዕግሥትና በደስታ” መጽናት እንችላለን። (ቆላ. 1:11፤ መዝ. 119:143, 157) እውነት ያረጋጋናል፤ ዓላማ ያለው ሕይወት እንዲኖረንና ግልጽ መመሪያ እንድናገኝ ይረዳናል። በአምላክ መንግሥት አገዛዝ ሥር አስደሳች ሕይወት እንደምንመራ ተስፋ ይሰጠናል። w23.01 7 አን. 16-17
እሁድ፣ ሰኔ 30
እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ አዲስ ትእዛዝ እሰጣችኋለሁ፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።—ዮሐ. 13:34
ኢየሱስ ከመሞቱ በፊት በነበረው ምሽት ላይ ስለ ደቀ መዛሙርቱ ረጅም ጸሎት አቅርቧል፤ ‘ከክፉው እንዲጠብቃቸው’ አባቱን ለምኖታል። (ዮሐ. 17:15) ይህ፣ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ያለውን ጥልቅ ፍቅር የሚያሳይ ነው። ኢየሱስ እሱ ራሱ ከፍተኛ መከራ ከፊቱ የሚጠብቀው ቢሆንም ስለ ሐዋርያቱ ደህንነት ተጨንቋል። እኛም የኢየሱስን ምሳሌ በመከተል በራሳችን ፍላጎት ላይ ብቻ ከማተኮር እንቆጠባለን። ከዚህ ይልቅ ስለ ወንድሞቻችንና ስለ እህቶቻችን አዘውትረን እንጸልያለን። እንዲህ ስናደርግ ኢየሱስ እርስ በርስ እንድንዋደድ የሰጠንን ትእዛዝ እንፈጽማለን። እንዲሁም የእምነት ባልንጀሮቻችንን ምን ያህል እንደምንወዳቸው ለይሖዋ እናሳየዋለን። ስለ ወንድሞቻችንና ስለ እህቶቻችን መጸለያችን ለውጥ ያመጣል። የአምላክ ቃል “ጻድቅ ሰው የሚያቀርበው ምልጃ ታላቅ ኃይል አለው” ይላል። (ያዕ. 5:16) የእምነት ባልንጀሮቻችን ብዙ ፈተናዎች ስለሚያጋጥሟቸው የእኛ ጸሎት ያስፈልጋቸዋል። w22.07 23-24 አን. 13-15