የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es24 ገጽ 67-77
  • ሐምሌ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ሐምሌ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2024
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 1
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 2
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 3
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 4
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 5
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 6
  • እሁድ፣ ሐምሌ 7
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 8
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 9
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 10
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 11
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 12
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 13
  • እሁድ፣ ሐምሌ 14
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 15
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 16
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 17
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 18
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 19
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 20
  • እሁድ፣ ሐምሌ 21
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 22
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 23
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 24
  • ሐሙስ፣ ሐምሌ 25
  • ዓርብ፣ ሐምሌ 26
  • ቅዳሜ፣ ሐምሌ 27
  • እሁድ፣ ሐምሌ 28
  • ሰኞ፣ ሐምሌ 29
  • ማክሰኞ፣ ሐምሌ 30
  • ረቡዕ፣ ሐምሌ 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2024
es24 ገጽ 67-77

ሐምሌ

ሰኞ፣ ሐምሌ 1

ታማኞች ለሆኑት በንግግር . . . አርዓያ ሁን።—1 ጢሞ. 4:12

የመናገር ችሎታችን ከአፍቃሪው አምላካችን ያገኘነው ስጦታ ነው። የሚያሳዝነው ግን ይህ ልዩ ስጦታ አላግባብ ጥቅም ላይ ዋለ። ሰይጣን ዲያብሎስ ሔዋንን ዋሻት፤ ይህ ውሸት ደግሞ በሰው ልጆች ላይ ኃጢአትንና አለፍጽምናን አስከተለ። (ዘፍ. 3:1-4) አዳም የራሱን ጥፋት በሔዋን ይባስ ብሎም በይሖዋ ላይ በማላከክ አንደበቱን አላግባብ ተጠቀመበት። (ዘፍ. 3:12) ቃየን ወንድሙን አቤልን ከገደለው በኋላ ለይሖዋ ውሸት ተናገረ። (ዘፍ. 4:9) በዛሬው ጊዜ ስድብ ወይም የብልግና ንግግር የሌለበት ፊልም አለ ማለት ይከብዳል። ተማሪዎች በትምህርት ቤት፣ አዋቂዎች ደግሞ በሥራ ቦታቸው ስድብና ነውረኛ ንግግር ይሰማሉ። ጠንቃቃ ካልሆንን እንዲህ ዓይነቱን አነጋገር ከመልመዳችን የተነሳ እኛ ራሳችን እንደዚያ ማውራት ልንጀምር እንችላለን። ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ይሖዋን ማስደሰት እንፈልጋለን፤ ስለዚህ ነውረኛ ከሆነ ንግግር እንደምንርቅ የታወቀ ነው። ሆኖም ከዚህ ባለፈ ይህን አስደናቂ ስጦታ በትክክለኛው መንገድ ይኸውም አምላካችንን ለማወደስ ልንጠቀምበት ይገባል። w22.04 4 አን. 1-3

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 2

ለአምላክም ለሀብትም በአንድነት መገዛት አትችሉም።—ማቴ. 6:24

ኢየሱስ ለቁሳዊ ነገሮች ሚዛናዊ አመለካከት ነበረው፤ ምግብና መጠጥ የሚያስገኙትን ደስታም ያውቃል። (ሉቃስ 19:2, 6, 7) በአንድ ወቅት ምርጥ የወይን ጠጅ ሠርቷል፤ ይህ የመጀመሪያው ተአምር ነበር። (ዮሐ. 2:10, 11) በሞተበት ቀንም የለበሰው ውድ ልብስ ነበር። (ዮሐ. 19:23, 24) ሆኖም ኢየሱስ ቁሳዊ ነገሮች በሕይወቱ ውስጥ ትልቅ ቦታ እንዲይዙ አልፈቀደም። ኢየሱስ የአምላክን መንግሥት እስካስቀደምን ድረስ ይሖዋ የሚያስፈልገንን ነገር እንደሚያሟላልን አስተምሯል። (ማቴ. 6:31-33) ብዙዎች ከገንዘብ ጋር በተያያዘ መለኮታዊውን ጥበብ ተግባራዊ በማድረጋቸው ተጠቅመዋል። ዳንኤል የተባለን አንድ ያላገባ ወንድም እንደ ምሳሌ እንውሰድ። እንዲህ ብሏል፦ “በአሥራዎቹ ዕድሜ ውስጥ ሳለሁ በሕይወቴ ውስጥ ለመንፈሳዊ ነገሮች ቅድሚያ ለመስጠት ወሰንኩ።” ዳንኤል አኗኗሩን ቀላል ማድረጉ ጊዜውንና ችሎታውን በብዙ ቲኦክራሲያዊ ፕሮጀክቶች ላይ ለማዋል አስችሎታል። አክሎም እንዲህ ብሏል፦ “ምንም ያህል ገንዘብ ባገኝ ይሖዋ ከሰጠኝ በረከት ጋር ሊወዳደር አይችልም።” w22.05 21-22 አን. 6-7

ረቡዕ፣ ሐምሌ 3

[ይሖዋ] ከጨለማ ወደ አስደናቂ ብርሃኑ [ጠራችሁ]።—1 ጴጥ. 2:9

መጽሐፍ ቅዱስንና መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን አዘውትረን በማጥናት እውነትን እንደምንወድ ማሳየት እንችላለን። ደግሞም እውነት ውስጥ የቆየንበት ጊዜ ምንም ያህል ረጅም ቢሆን ሁሌም የምንማረው ነገር አለ። ጥናት ጥረት እንደሚጠይቅ የታወቀ ነው፤ ሆኖም የምናደርገው ጥረት የሚክስ ነው። እርግጥ ማንበብና ማጥናት የምንወደው ሁላችንም አይደለንም። ሆኖም ይሖዋ ስለ እውነት ጥልቅ ግንዛቤ ለማግኘት ‘ተግተን እንድንፈልግ’ እንዲሁም ‘አጥብቀን እንድንሻ’ ጋብዞናል። (ምሳሌ 2:4-6) እንዲህ ያለውን ጥረት ስናደርግ ሁሌም እንጠቀማለን። ኮሪ መጽሐፍ ቅዱስን ስለሚያነብበት መንገድ ሲናገር በእያንዳንዷ ጥቅስ ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ተናግሯል። እንዲህ ብሏል፦ “ሁሉንም የግርጌ ማስታወሻዎች አነብባለሁ፤ ሁሉንም የኅዳግ ማጣቀሻዎች እመለከታለሁ፤ እንዲሁም ተጨማሪ ምርምር አደርጋለሁ። . . . ይህን ዘዴ በመጠቀሜ ከመጽሐፍ ቅዱስ ንባቤ ብዙ ጥቅም አግኝቻለሁ!” እኛም የምንጠቀመው ዘዴ ይህም ሆነ ሌላ፣ እውነትን ለማጥናት ጊዜና ጥረት የምናውል ከሆነ ለእውነት ያለንን አድናቆት እናሳያለን።—መዝ. 1:1-3፤ w22.08 17 አን. 13፤ 18 አን. 15-16

ሐሙስ፣ ሐምሌ 4

በዚያን ወቅት የተዋጣለት ሠራተኛ ሆኜ ከጎኑ ነበርኩ። በየዕለቱ በእኔ የተነሳ ልዩ ደስታ ይሰማው ነበር፤ እኔም በፊቱ ሁልጊዜ ሐሴት አደርግ ነበር።—ምሳሌ 8:30

ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ጊዜ ደቀ መዛሙርቱን ስለ አባቱ ለማስተማር ፍጥረትን ተጠቅሟል። እስቲ ኢየሱስ ካስተማራቸው ትምህርቶች ውስጥ አንዱን እንመልከት። ይሖዋ ለሁሉም ሰዎች ፍቅር ያሳያል። ኢየሱስ በተራራው ስብከቱ ላይ ብዙዎች እምብዛም ትኩረት ስለማይሰጧቸው ሁለት የፍጥረት ሥራዎች ተናግሯል፤ እነሱም ፀሐይና ዝናብ ናቸው። ሁለቱም ለሕይወት የግድ አስፈላጊ ናቸው። ይሖዋ እሱን የማያገለግሉ ሰዎች ፀሐይና ዝናብ እንዳያገኙ መከልከል ይችል ነበር። እሱ ግን በፍቅር ተነሳስቶ ለሁሉም ሰዎች ፀሐይንና ዝናብን ሰጥቷል። (ማቴ. 5:43-45) ኢየሱስ ይህን ምሳሌ በመጠቀም ይሖዋ ለሁሉም ሰዎች ፍቅር እንድናሳይ እንደሚፈልግ ለደቀ መዛሙርቱ አስተምሯል። ፀሐይ ስትጠልቅ ያለውን ማራኪ እይታም ሆነ መንፈስን የሚያድስ ዝናብ ስንመለከት ይሖዋ ስላሳየው ከአድልዎ ነፃ የሆነ ፍቅር ማሰብ እንችላለን። እሱ የተወልን ምሳሌ ለሁሉም ዓይነት ሰዎች በመስበክ ተመሳሳይ ፍቅር እንድናሳይ ያነሳሳናል። w23.03 17 አን. 9-10

ዓርብ፣ ሐምሌ 5

እጅግ ተደነቅኩ።—ራእይ 17:6

ሐዋርያው ዮሐንስን ያስደነቀው ምን ይሆን? አንዲት ሴት አንድ ደማቅ ቀይ አውሬ ላይ ስትጋልብ ተመለከተ። ይህች ሴት “ታላቂቱ አመንዝራ” እንዲሁም “ታላቂቱ ባቢሎን” ተብላ ተገልጻለች። ‘ከምድር ነገሥታት ጋር ምንዝር’ ትፈጽማለች። (ራእይ 17:1-5) “ታላቂቱ ባቢሎን” ማን ናት? ይህች ሴት የፖለቲካ ድርጅት ልትሆን አትችልም፤ ምክንያቱም ከዚህ ዓለም የፖለቲካ መሪዎች ጋር ምንዝር እንደምትፈጽም ተገልጿል። (ራእይ 18:9) እንዲያውም እንደምትጋልባቸው ስለተገለጸ እነዚህን መሪዎች ልትቆጣጠራቸው ትሞክራለች። የሰይጣንን ዓለም ስግብግብ የንግድ ሥርዓትም ልታመለክት አትችልም። የንግዱ ሥርዓት “የምድር ነጋዴዎች” በሚለው መግለጫ ለብቻው ተገልጿል። (ራእይ 18:11, 15, 16) የጥንቷ ባቢሎን የሐሰት አምልኮ ማዕከል ነበረች። ስለዚህ ታላቂቱ ባቢሎን የሐሰት አምልኮዎችን በሙሉ የምትወክል መሆን አለባት። እንዲያውም በዓለም ዙሪያ ያሉ የሐሰት ሃይማኖቶችን ያቀፈች ናት።—ራእይ 17:5, 18፤ w22.05 11 አን. 14-16

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 6

ጠላታችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይንጎራደዳል።—1 ጴጥ. 5:8

እናቶች ‘ልጆቻችን ይሖዋን ለማገልገል ይመርጣሉ ወይስ አይመርጡም?’ የሚለው ጉዳይ ሊያሳስባቸው ይችላል። ምክንያቱም ልጆች በሰይጣን ዓለም ውስጥ ምን ያህል ፈተና እንደሚያጋጥማቸው ወላጆች በሚገባ ያውቃሉ። በተጨማሪም ብዙ እናቶች ልጆቻቸውን የሚያሳድጉት ያለአባት ወይም ይሖዋን ከማያገለግል አባት ጋር ነው። ተፈታታኝ ሁኔታ የሚያጋጥመው በሃይማኖት በተከፋፈሉ ቤተሰቦች ውስጥ ብቻ አይደለም። ሁለቱም ወላጆች እውነት ውስጥ ቢሆኑም እንኳ የወጣቶችን ልብ መንካትና ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች እንዲሆኑ መርዳት አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል። ሁኔታችሁ ምንም ይሁን ምን ከልክ በላይ አትጨነቁ። ይሖዋ ይረዳችኋል። ያሉንን መሣሪያዎች ለቤተሰብ አምልኳችሁ መጠቀም የምትችሉት እንዴት እንደሆነ ጠቃሚ ምክር እንዲሰጧችሁ ተሞክሮ ያላቸውን ወላጆች ለምን አታማክሩም? (ምሳሌ 11:14) በተጨማሪም ከልጆቻችሁ ጋር ጥሩ የሐሳብ ግንኙነት እንዲኖራችሁ ይሖዋ ይረዳችኋል። በአእምሯቸውና በልባቸው ውስጥ ያለውን ለማወቅ እንዲረዳችሁ ይሖዋን ጠይቁት።—ምሳሌ 20:5፤ w22.04 17 አን. 4, 7፤ 18 አን. 9

እሁድ፣ ሐምሌ 7

ፍቅራችሁ ከአምላክ ፈቃድ ትክክለኛ እውቀትና ጥልቅ ግንዛቤ ጋር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንዲሄድ መጸለዬን እቀጥላለሁ።—ፊልጵ. 1:9

ኢየሱስ የአባቱን ባሕርያት ፍጹም በሆነ መንገድ አንጸባርቋል፤ በመሆኑም ስለ ኢየሱስ ይበልጥ በማወቅ ለይሖዋ ያለንን ፍቅር ማሳደግ እንችላለን። (ዕብ. 1:3) ኢየሱስን ማወቅ የምንችልበት ከሁሉ የተሻለው ዘዴ አራቱን ወንጌሎች ማጥናት ነው። መጽሐፍ ቅዱስን በየዕለቱ የማንበብ ልማድ እስካሁን ካላዳበርክ ለምን አሁን አትጀምርም? ስለ ኢየሱስ የሚናገሩትን ዘገባዎች ስታነብ በባሕርያቱ ላይ ትኩረት አድርግ። ኢየሱስ በቀላሉ የሚቀረብ ሰው ነበር፤ ትናንሽ ልጆችን ፍቅር በሚንጸባረቅበት መንገድ አቅፏቸዋል። (ማር. 10:13-16) ደቀ መዛሙርቱ ነፃነት እንዲሰማቸው ያደርግ ነበር፤ እሱ ባለበት የፈለጉትን ነገር መናገር አይከብዳቸውም። (ማቴ. 16:22) በዚህ ረገድ ኢየሱስ የአባቱን ምሳሌ ተከትሏል። ይሖዋም በቀላሉ የሚቀረብ አምላክ ነው። ወደ እሱ መጸለይ እንችላለን። በምንጸልይበት ጊዜም ልባችንን በፊቱ ማፍሰስ እንችላለን። እንደማይኮንነን እርግጠኞች ነን። በጣም ይወደናል፤ ያስብልናል።—1 ጴጥ. 5:7፤ w22.08 3 አን. 4-5

ሰኞ፣ ሐምሌ 8

ይሖዋ ሆይ፣ አንተ ጥሩ ነህና፤ ይቅር ለማለትም ዝግጁ ነህ።—መዝ. 86:5

ይሖዋ ፈጣሪያችን ስለሆነ ስለ እኛ ሁሉንም ነገር ያውቃል። እስቲ አስበው! በምድር ላይ ስላለው ስለ እያንዳንዱ ሰው እያንዳንዷን ዝርዝር ነገር ያውቃል። (መዝ. 139:15-17) ስለዚህ ከወላጆቻችን የወረስነውን አለፍጽምና በሙሉ ማየት ይችላል። በተጨማሪም በሕይወታችን ውስጥ ያጋጠሙን ነገሮች ባሕርያችንን የቀረጹት እንዴት እንደሆነ ያውቃል። ይሖዋ የሰው ልጆችን እንዲህ በጥልቀት ማወቁ ምን እንዲያደርግ ያነሳሳዋል? በምሕረት እንዲይዘን ያነሳሳዋል። (መዝ. 78:39፤ 103:13, 14) ይሖዋ ይቅር ለማለት እንደሚጓጓ በተግባር አሳይቷል። የመጀመሪያው ሰው አዳም በሠራው ኃጢአት የተነሳ ሁላችንም በኃጢአትና በሞት እርግማን ሥር እንደወደቅን ያውቃል። (ሮም 5:12) ራሳችንንም ሆነ ሌላ ማንኛውንም ሰው ከዚህ እርግማን ማላቀቅ የምንችልበት ምንም መንገድ አልነበረም። (መዝ. 49:7-9) ያም ቢሆን አፍቃሪ የሆነው አምላካችን ነፃ የምንወጣበትን መንገድ በማዘጋጀት ርኅራኄ አሳይቶናል። ዮሐንስ 3:16 እንደሚገልጸው ይሖዋ አንድያ ልጁን ለእኛ ሲል እንዲሞት ላከልን።—ማቴ. 20:28፤ ሮም 5:19፤ w22.06 3 አን. 5-6

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 9

ደግ ሰው ራሱን ይጠቅማል።—ምሳሌ 11:17

ይሖዋ ለአገልጋዩ ለኢዮብ የነገረው ነገር ሌሎችን ይቅር ካልን ይሖዋ ይቅር እንደሚለን ያስተምረናል። ይህ ታማኝ ሰው ኤሊፋዝ፣ በልዳዶስና ሶፋር የተባሉ ሦስት ሰዎች በተናገሩት ጎጂ ንግግር ስሜቱ እጅግ ተጎድቶ ነበር። ሆኖም ይሖዋ ኢዮብን ለእነዚህ ሰዎች እንዲጸልይላቸው አዘዘው። ይሖዋ ኢዮብን የባረከው እንዲህ ካደረገ በኋላ ነው። (ኢዮብ 42:8-10) ቂም መያዝ ራሳችንን ይጎዳናል። ቂም ከባድ ሸክም ነው፤ ይሖዋ ይህን ሸክም ከላያችን አውርደን እፎይ እንድንል ይፈልጋል። (ኤፌ. 4:31, 32) “ከቁጣ ተቆጠብ፤ ንዴትንም ተው” የሚል ምክር ሰጥቶናል። (መዝ. 37:8) ይህን ምክር መከተል በጣም ጠቃሚ ነው። ቂም መያዝ አካላዊም ሆነ አእምሯዊ ጤንነታችንን ሊጎዳው ይችላል። (ምሳሌ 14:30) ደግሞም ቂም ይዘን የበደለን ሰው እንዲጎዳ መጠበቅ እኛ መርዝ እየጠጣን የበደለን ሰው እንዲጎዳ ከመጠበቅ ተለይቶ አይታይም። ሌሎችን ይቅር ስንል ለራሳችን ስጦታ እየሰጠን ነው ሊባል ይችላል። አእምሯችንና ልባችን ሰላም ያገኛል፤ እንዲሁም በይሖዋ አገልግሎት ወደፊት መግፋት እንችላለን። w22.06 10 አን. 9-10

ረቡዕ፣ ሐምሌ 10

የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር እንልበስ፤ የመዳንንም ተስፋ እንደ ራስ ቁር እንድፋ።—1 ተሰ. 5:8

ተስፋችን እንደ ራስ ቁር በመሆን አስተሳሰባችንን ይጠብቅልናል፤ በተጨማሪም ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና የሚያበላሽ የራስ ወዳድነት ሕይወት እንዳንመራ ይረዳናል። (1 ቆሮ. 15:33, 34) እንደ ራስ ቁር የሆነው ተስፋችን ‘ይሖዋን ለማስደሰት መሞከር ዋጋ የለውም’ ከሚለው አስተሳሰብ እንድንጠበቅ ይረዳናል። የኢዮብ የውሸት አጽናኝ የሆነው ኤሊፋዝም ተመሳሳይ ሐሳብ እንደተናገረ አስታውሱ። ኤሊፋዝ “ንጹሕ ይሆን ዘንድ ሟች የሆነ ሰው ምንድን ነው?” ብሏል። አክሎም ስለ አምላክ ሲናገር “እነሆ፣ በቅዱሳኑ ላይ እምነት የለውም፤ ሰማያትም እንኳ በፊቱ ንጹሐን አይደሉም” ብሏል። (ኢዮብ 15:14, 15) ይህ ዓይን ያወጣ ውሸት ነው! እንዲህ ያለው አስተሳሰብ የሚመነጨው ከሰይጣን ነው። ሰይጣን እንዲህ ባሉ ሐሳቦች ላይ ካውጠነጠናችሁ ተስፋችሁ እንደሚደበዝዝ ያውቃል። በመሆኑም እንዲህ ያሉ ውሸቶችን ከአእምሯችሁ አውጡ። ይሖዋ ለዘላለም እንድትኖሩ እንደሚፈልግና እዚያ ግብ ላይ እንድትደርሱ እንደሚረዳችሁ አትጠራጠሩ።—1 ጢሞ. 2:3, 4፤ w22.10 25-26 አን. 8-10

ሐሙስ፣ ሐምሌ 11

ኢዮብ . . . በከንፈሩ አልበደለም።—ኢዮብ 2:10

ሰይጣን፣ ኢዮብ መከራ የደረሰበት የይሖዋን ሞገስ ስላጣ እንደሆነ እንዲያስብ ፈልጎ ነበር። ለምሳሌ ሰይጣን አሥሩም የኢዮብ ልጆች አንድ ላይ እየተመገቡ በነበረበት ወቅት ኃይለኛ ነፋስ አምጥቶ ቤቱን አፈረሰው። (ኢዮብ 1:18, 19) በተጨማሪም ከሰማይ እሳት አውርዶ የኢዮብን መንጎችና መንጎቹን እየጠበቁ የነበሩትን አገልጋዮቹን ገደላቸው። (ኢዮብ 1:16) ነፋሱና እሳቱ የመጡት ከሰብዓዊ ምንጭ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ስለዚህ ኢዮብ የእነዚህ አደጋዎች ምንጭ ይሖዋ አምላክ እንደሆነ ደመደመ። በመሆኑም ኢዮብ ይሖዋ በሆነ ምክንያት እንዳዘነበት አሰበ። ያም ቢሆን ኢዮብ የሰማዩን አባቱን ለመርገም ፈቃደኛ አልሆነም። ኢዮብ ላለፉት ዓመታት ከይሖዋ ብዙ መልካም ነገሮችን እንደተቀበለ ያውቃል። ስለዚህ ከይሖዋ መልካም ነገሮችን ከተቀበለ ክፉውንም ለመቀበል ፈቃደኛ መሆን እንዳለበት ተናገረ። በመሆኑም “የይሖዋ ስም ምንጊዜም ይወደስ” አለ።—ኢዮብ 1:20, 21፤ w22.06 21 አን. 7

ዓርብ፣ ሐምሌ 12

በስሜ [የተነሳ] ሰዎች ሁሉ ይጠሏችኋል። እስከ መጨረሻው የጸና ግን ይድናል።—ማር. 13:13

ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል፤ ይህ ማስጠንቀቂያ በዮሐንስ 17:14 ላይ ተመዝግቦ ይገኛል። በተለይ ባለፉት 100 ዓመታት ይህ ትንቢት ሲፈጸም በግልጽ ተመልክተናል። እንዴት? ኢየሱስ በ1914 መሲሐዊ ንጉሥ ሆኖ መግዛት ከጀመረ ብዙም ሳይቆይ ሰይጣን ከሰማይ ተባረረ። አሁን እንቅስቃሴው በምድር አካባቢ ተገድቦ መጥፊያውን እየተጠባበቀ ነው። (ራእይ 12:9, 12) ሆኖም የሚጠብቀው እጁን አጣጥፎ አይደለም። ሰይጣን መጥፊያው መቅረቡን ስላወቀ በከፍተኛ ቁጣ ተሞልቷል፤ ቁጣውንም በአምላክ ሕዝቦች ላይ እየተወጣ ነው። (ራእይ 12:13, 17) በመሆኑም ዓለም ለአምላክ ሕዝቦች ያለው ጥላቻ ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ ጨምሯል። ሆኖም ሰይጣንን እና ተከታዮቹን የምንፈራበት ምንም ምክንያት የለም። ከዚህ ይልቅ እንደ ሐዋርያው ጳውሎስ “አምላክ ከእኛ ጋር ከሆነ ማን ሊቃወመን ይችላል?” ብለን በልበ ሙሉነት መናገር እንችላለን። (ሮም 8:31) በይሖዋ ሙሉ በሙሉ መታመን እንችላለን። w22.07 18 አን. 14-15

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 13

ይህ የመንግሥቱ ምሥራች . . . በመላው ምድር ይሰበካል።—ማቴ. 24:14

ኢየሱስ በሥርዓቱ መደምደሚያ ላይ የሠራተኞች እጥረት ይኖራል የሚል ስጋት አላደረበትም። ምክንያቱም መዝሙራዊው የተናገረው የሚከተለው ትንቢት እንደሚፈጸም ያውቅ ነበር፦ “ወደ ጦርነት በምትዘምትበት ቀን ሕዝብህ በገዛ ፈቃዱ ራሱን ያቀርባል።” (መዝ. 110:3) በስብከቱ ሥራ የምትካፈል ከሆነ ኢየሱስንና ታማኙን ባሪያ እየደገፍክ እንዲሁም ለዚህ ትንቢት ፍጻሜ የበኩልህን አስተዋጽኦ እያበረከትክ ነው። ሥራው ወደፊት እየገሰገሰ ነው፤ ሆኖም አንዳንድ ተፈታታኝ ሁኔታዎች አሉ። የመንግሥቱ ሰባኪዎች የሚያጋጥማቸው አንዱ ተፈታታኝ ሁኔታ ተቃውሞ ነው። ከሃዲዎች፣ የሃይማኖት መሪዎችና ፖለቲከኞች ብዙ ሰዎች ስለ ሥራችን የተሳሳተ አመለካከት እንዲኖራቸው አድርገዋል። ዘመዶቻችን፣ የምናውቃቸው ሰዎችና የሥራ ባልደረቦቻችን በዚህ ፕሮፓጋንዳ ተታለው ይሖዋን ማገልገላችንን እና መስበካችንን እንድናቆም ጫና ሊያሳድሩብን ይችላሉ። በአንዳንድ አገሮች ውስጥ ጠላቶቻችን ወንድሞቻችንን ያስፈራሯቸዋል፤ ጥቃት ይሰነዝሩባቸዋል፤ አልፎ ተርፎም እስር ቤት ያስገቧቸዋል። w22.07 8 አን. 1፤ 9 አን. 5-6

እሁድ፣ ሐምሌ 14

በብዙ መከራ አልፈን ወደ አምላክ መንግሥት መግባት አለብን።—ሥራ 14:22

ይሖዋ መጽሐፍ ቅዱስን አዘውትረን ለማንበብና ባነበብነው ነገር ላይ በጥልቀት ለማሰብ ጊዜ እንድንመድብ ይጠብቅብናል። የተማርነውን ነገር በሥራ ላይ ስናውል እምነታችን ይጠናከራል፤ ወደ ሰማዩ አባታችንም ይበልጥ እንቀርባለን። ይህ ደግሞ የሚያጋጥሙንን ፈተናዎች በጽናት ለመቋቋም ብርታት ይሰጠናል። በተጨማሪም ይሖዋ በቃሉ ለሚመሩ ሰዎች ቅዱስ መንፈሱን ይሰጣቸዋል። ይህ መንፈስ ደግሞ የትኛውንም ፈተና በጽናት መቋቋም እንድንችል “ከሰብዓዊ ኃይል በላይ [የሆነ] ኃይል” ይሰጠናል። (2 ቆሮ. 4:7-10) በይሖዋ እርዳታ “ታማኝና ልባም ባሪያ” ጠንካራ እምነት ለመገንባትና በመንፈሳዊ ንቁ ሆነን ለመኖር የሚረዱ ጽሑፎችን፣ ቪዲዮዎችንና ሙዚቃዎችን አትረፍርፎ ያዘጋጅልናል። (ማቴ. 24:45) ይሖዋ በአስጨናቂ ጊዜያት ሕዝቦቹ እርስ በርስ እንዲዋደዱና አንዳቸው ሌላውን እንዲያጽናኑ አሠልጥኗቸዋል። (2 ቆሮ. 1:3, 4፤ 1 ተሰ. 4:9) ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አስቸጋሪ ሁኔታ ሲያጋጥመን በታማኝነት እንድንጸና እኛን ለመርዳት ዝግጁ ናቸው። w22.08 12 አን. 12-14

ሰኞ፣ ሐምሌ 15

አንድ ላይ በሚያስተሳስረው የሰላም ማሰሪያ የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ ልባዊ ጥረት አድርጉ።—ኤፌ. 4:3

ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ስላሏቸው መልካም ባሕርያት አዘውትረን ስንናገር እርስ በርስ ይበልጥ እንዲቀራረቡ እንረዳቸዋለን፤ ይህ ደግሞ ጉባኤው በፍቅር እንዲታነጽ ያደርጋል። አንዳንድ ጊዜ በጎለመሱ ክርስቲያኖች መካከልም እንኳ አለመግባባት ወይም ጭቅጭቅ ሊያጋጥም ይችላል። በሐዋርያው ጳውሎስና የቅርብ ጓደኛው በሆነው በበርናባስ መካከል እንዲህ ዓይነት ሁኔታ ተፈጥሮ ነበር። ሁለቱ ሰዎች በቀጣዩ የሚስዮናዊ ጉዟቸው ላይ ማርቆስን ከመውሰድ ጋር በተያያዘ አለመግባባት አጋጥሟቸው ነበር። “በመካከላቸው ኃይለኛ ጭቅጭቅ ስለተፈጠረ ተለያዩ።” (ሥራ 15:37-39) ሆኖም ጳውሎስ፣ በርናባስና ማርቆስ በመካከላቸው የተፈጠረውን ግጭት ፈትተዋል። ከጊዜ በኋላ ጳውሎስ ስለ በርናባስና ስለ ማርቆስ አዎንታዊ ነገር ተናግሯል። (1 ቆሮ. 9:6፤ ቆላ. 4:10) እኛም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር አለመግባባት ሲፈጠር ችግሩን ወዲያውኑ ፈትተን በመልካም ጎናቸው ላይ ማተኮራችንን መቀጠል ይኖርብናል። እንዲህ ካደረግን ሰላምና አንድነት እናሰፍናለን። w22.08 23 አን. 10-11

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 16

እንዳይፈረድባችሁ በሌሎች ላይ አትፍረዱ።—ማቴ. 7:1

በይሖዋ የጽድቅ መሥፈርቶች ለመመራት አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ብናደርግም በሌሎች ላይ ከመፍረድና ራሳችንን ከማመጻደቅ መቆጠብ ይኖርብናል። ይሖዋ “የምድር ሁሉ ዳኛ” መሆኑን ማስታወስ ይኖርብናል። (ዘፍ. 18:25) ይሖዋ የመፍረድ ሥልጣኑን ለእኛ አሳልፎ አልሰጠንም። የጻድቁን ዮሴፍን ምሳሌ እንመልከት። ዮሴፍ የበደሉትን ሰዎች ጨምሮ በሌሎች ላይ ከመፍረድ ተቆጥቧል። የገዛ ወንድሞቹ አንገላተውታል፤ ለባርነት ሸጠውታል፤ አልፎ ተርፎም ‘ዮሴፍ ሞቷል’ ብለው ለአባታቸው ነግረውታል። ከበርካታ ዓመታት በኋላ ዮሴፍ ከቤተሰቡ ጋር መልሶ ተገናኘ። በወቅቱ ዮሴፍ ከፍተኛ ባለሥልጣን ስለነበር በወንድሞቹ ላይ በጭካኔ ሊፈርድባቸውና ሊበቀላቸው ይችል ነበር። የዮሴፍ ወንድሞች ለሠሩት በደል ከልባቸው የተጸጸቱ ቢሆንም ዮሴፍ ሊበቀላቸው እንደሚችል ፈርተው ነበር። ሆኖም ዮሴፍ “አይዟችሁ አትፍሩ። ለመሆኑ እኔን በአምላክ ቦታ ያስቀመጠኝ ማን ነው?” በማለት አረጋጋቸው። (ዘፍ. 37:18-20, 27, 28, 31-35፤ 50:15-21) ዮሴፍ በትሕትና ፍርዱን ለይሖዋ ትቷል። w22.08 30 አን. 18-19

ረቡዕ፣ ሐምሌ 17

ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችል አቅም ካለህ ለሚገባቸው መልካም ነገር ከማድረግ ወደኋላ አትበል።—ምሳሌ 3:27

ይሖዋ አገልጋዮቹ ያቀረቡትን ልባዊ ጸሎት ለመመለስ በአንተ ሊጠቀም እንደሚችል ታውቃለህ? የጉባኤ ሽማግሌም ሆንክ አገልጋይ፣ አቅኚም ሆንክ አስፋፊ ሊጠቀምብህ ይችላል። አረጋውያንም ሆኑ ወጣቶች፣ ወንዶችም ሆኑ ሴቶች ይሖዋ ሊጠቀምባቸው ይችላል። ይሖዋን የሚወድ አንድ ሰው እርዳታ ለማግኘት ወደ እሱ ሲጮኽ፣ አምላካችን ብዙውን ጊዜ ሽማግሌዎችና ሌሎች ታማኝ አገልጋዮቹ ለዚያ ሰው “የብርታት ምንጭ” እንዲሆኑለት ያደርጋል። (ቆላ. 4:11) ይሖዋንና ወንድሞቻችንን በዚህ መንገድ ማገልገል እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ወረርሽኝ፣ አደጋ ወይም ስደት በሚያጋጥምበት ጊዜ ወንድሞቻችንን መርዳት እንችላለን። ሌሎችን መርዳት ብንፈልግም የእኛም ቤተሰቦች ችግር ውስጥ ከሆኑ እንዲህ ማድረግ ከባድ ሊሆንብን ይችላል። ያም ቢሆን ወንድሞቻችንን መርዳት እንፈልጋለን፤ ይሖዋም እነሱን ለመርዳት አቅማችን የፈቀደውን ስናደርግ ይደሰታል።—ምሳሌ 19:17፤ w22.12 22 አን. 1-2

ሐሙስ፣ ሐምሌ 18

ትእዛዜ ይህ ነው፤ እኔ እንደወደድኳችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ።—ዮሐ. 15:12

የመተማመን መሠረቱ ፍቅር ነው። ኢየሱስ ከሁሉ የሚበልጡት ሁለት ትእዛዛት ይሖዋን መውደድና ባልንጀራችንን መውደድ እንደሆኑ ተናግሯል። (ማቴ. 22:37-39) ለይሖዋ ያለን ፍቅር እምነት የሚጣልበት በመሆን ረገድ የተወልንን ፍጹም ምሳሌ እንድንከተል ያነሳሳናል። ለወንድሞቻችንና ለእህቶቻችን ያለን ፍቅር የግል ጉዳያቸውን በሚስጥር እንድንይዝ ይገፋፋናል። ሊጎዳቸው፣ ሊያሳፍራቸው ወይም ሊያሳዝናቸው የሚችል መረጃ ማውጣት አንፈልግም። ትሕትናም እምነት የሚጣልብን ለመሆን ይረዳናል። ትሑት የሆነ ክርስቲያን አንድን መረጃ ለመናገር የመጀመሪያው ሰው በመሆን ሌሎችን ለማስደመም አይሞክርም። (ፊልጵ. 2:3) ወይም ደግሞ ለሌሎች መናገር የማይችለው መረጃ እንዳለው በመጠቆም በጣም ተፈላጊ ሰው መስሎ ለመታየት አይሞክርም። በተጨማሪም ትሕትና በመጽሐፍ ቅዱስ ወይም በመጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎች ውስጥ ማብራሪያ ስላልተሰጠባቸው ጉዳዮች ግምታዊ ሐሳብ ከማሰራጨት እንድንቆጠብ ያነሳሳናል። w22.09 12 አን. 12-13

ዓርብ፣ ሐምሌ 19

እውነተኛው እውቀትም ይበዛል።—ዳን. 12:4

አንድ መልአክ ለዳንኤል የአምላክ ሕዝቦች በእሱ መጽሐፍ ውስጥ ያሉትን ትንቢቶች ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ እንደሚረዱት ሆኖም “ከክፉዎች መካከል አንዳቸውም [እንደማይረዱት]” ነግሮታል። (ዳን. 12:10) ከክፉዎች መካከል እንደማንመደብ የምናስመሠክርበት ጊዜ አሁን ነው። (ሚል. 3:16-18) ይሖዋ እንደ “ልዩ ንብረት” ወይም እንደ ውድ ሀብት የሚመለከታቸውን ሰዎች እየሰበሰበ ነው። እኛም ከእነሱ መካከል መገኘት እንደምንፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም። በእርግጥም የምንኖረው እጅግ አስደናቂ ጊዜ ላይ ነው። በቅርቡ ደግሞ ይበልጥ አስደናቂ የሆኑ ክንውኖች ይጠብቁናል። ክፋት ሁሉ ሲጠፋ የምናይበት ጊዜ ሩቅ አይደለም። ከዚያ በኋላ፣ ይሖዋ ለዳንኤል “በዘመኑ ፍጻሜ ዕጣ ፋንታህን ለመቀበል ትነሳለህ” በማለት የገባለት ቃል ሲፈጸም እንመለከታለን። (ዳን. 12:13) ዳንኤል እና በሞት ያጣችኋቸው የምትወዷቸው ሰዎች የሚነሱበትን ቀን አትናፍቁም? ከሆነ፣ ከአሁኑ ታማኝ ለመሆን አቅማችሁ የፈቀደውን ሁሉ አድርጉ። እንዲህ ካደረጋችሁ ስማችሁ በይሖዋ የሕይወት መጽሐፍ ውስጥ ሳይጠፋ እንደሚኖር እርግጠኛ መሆን ትችላላችሁ! w22.09 24 አን. 17፤ 25 አን. 19-20

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 20

እልክሃለሁ።—ሕዝ. 2:3

ይህ ቃል ሕዝቅኤልን አበረታቶት መሆን አለበት። ለምን? ይሖዋ ለሙሴና ለኢሳይያስ የነቢይነት ተልእኮ ሲሰጣቸው ይህንኑ ቃል እንደተጠቀመ ሕዝቅኤል አስታውሶ መሆን አለበት። (ዘፀ. 3:10፤ ኢሳ. 6:8) በተጨማሪም ሕዝቅኤል፣ ይሖዋ እነዚህ ሁለት ነቢያት የተሰጣቸውን ከባድ ኃላፊነት እንዲወጡ እንደረዳቸው ያውቃል። በመሆኑም ይሖዋ ለሕዝቅኤል ሁለት ጊዜ “እልክሃለሁ” ሲለው ነቢዩ ይሖዋ እንደሚረዳው የሚተማመንበት በቂ ምክንያት ነበረው። ከዚህም ሌላ በሕዝቅኤል መጽሐፍ ውስጥ “የይሖዋ ቃል ወደ እኔ መጣ” የሚለውን አገላለጽ በተደጋጋሚ እናገኛለን። (ሕዝ. 3:16) “የይሖዋ ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ” የሚለው አገላለጽም በመጽሐፉ ውስጥ ብዙ ጊዜ ይገኛል። (ሕዝ. 6:1) በእርግጥም ሕዝቅኤል፣ የላከው ይሖዋ እንደሆነ ምንም አልተጠራጠረም። በተጨማሪም ሕዝቅኤል የካህን ልጅ ስለነበር አባቱ፣ ይሖዋ በታሪክ ዘመናት ሁሉ ነቢያቱን እንደሚደግፋቸው ዋስትና እንደሰጣቸው አስተምሮት መሆን አለበት። ይሖዋ ለይስሐቅ፣ ለያዕቆብና ለኤርምያስ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝ” ብሏቸዋል።—ዘፍ. 26:24፤ 28:15፤ ኤር. 1:8፤ w22.11 2 አን. 3

እሁድ፣ ሐምሌ 21

[ይህ] የዘላለም ሕይወት ነው።—ዮሐ. 17:3

አዳምና ሔዋን ኃጢአት በመሥራት በልጆቻቸው ላይ ሞት ቢያመጡም እንኳ ይሖዋ ለሰዎች ያለውን ዓላማ አልቀየረም። (ኢሳ. 55:11) አሁንም ቢሆን ዓላማው ታማኝ ሰዎች ለዘላለም እንዲኖሩ ነው። ይሖዋ ዓላማውን ለመፈጸም ሲል የተናገራቸውንና ያደረጋቸውን ነገሮች እናስብ። ይሖዋ ሙታንን እንደሚያስነሳና ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንደሚሰጣቸው ቃል ገብቷል። (ሥራ 24:15፤ ቲቶ 1:1, 2) ታማኙ ኢዮብ፣ ይሖዋ የሞቱትን ለማስነሳት እንደሚናፍቅ እርግጠኛ ነበር። (ኢዮብ 14:14, 15) ነቢዩ ዳንኤል፣ ሰዎች ከሞት ተነስተው የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ እንደሚኖራቸው ያውቅ ነበር። (መዝ. 37:29፤ ዳን. 12:2, 13) በኢየሱስ ዘመን የነበሩት አይሁዳውያንም፣ ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ “የዘላለም ሕይወት” እንደሚሰጣቸው ያውቁ ነበር። (ሉቃስ 10:25፤ 18:18) ኢየሱስ ስለዚህ ተስፋ በተደጋጋሚ ተናግሯል፤ እሱንም ቢሆን አባቱ ከሞት አስነስቶታል።—ማቴ. 19:29፤ 22:31, 32፤ ሉቃስ 18:30፤ ዮሐ. 11:25፤ w22.12 4-5 አን. 8-9

ሰኞ፣ ሐምሌ 22

ይሖዋ ሆይ፣ . . . በአንተ እታመናለሁ።—መዝ. 31:14

ይሖዋ ወደ እሱ እንድንቀርብ ጋብዞናል። (ያዕ. 4:8) አምላካችን፣ አባታችንና ወዳጃችን መሆን ይፈልጋል። ይሖዋ ጸሎታችንን ይመልስልናል፤ እንዲሁም ፈተና ሲያጋጥመን ይረዳናል። በተጨማሪም ድርጅቱን በመጠቀም ያስተምረናል እንዲሁም ይጠብቀናል። ወደ ይሖዋ ለመቅረብ ወደ እሱ መጸለይ እንዲሁም ቃሉን ማንበብና ማሰላሰል ይኖርብናል። ይህን ስናደርግ ልባችን ለእሱ ባለን ፍቅርና አድናቆት ይሞላል። ለእሱ የሚገባውን ውዳሴ ልንሰጠውና ልንታዘዘው እንነሳሳለን። (ራእይ 4:11) ይሖዋን ይበልጥ ባወቅነው መጠን በእሱም ሆነ እኛን ለመርዳት ባቋቋመው ድርጅት ይበልጥ እንተማመናለን። ይሁንና ዲያብሎስ፣ በይሖዋና በድርጅቱ ላይ ያለንን እምነት ቀስ በቀስ ለመሸርሸር ይሞክራል። ሆኖም እሱ የሚሸርባቸውን ሴራዎች ማክሸፍ እንችላለን። በይሖዋ ላይ ያለን እምነት ጠንካራና የማይናወጥ ከሆነ አምላካችንንና ድርጅቱን በፍጹም አንተውም።—መዝ. 31:13, 14፤ w22.11 14 አን. 1-3

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 23

የራሳቸውን አምላክ ትተው ሌላ አምላክ ከማገልገል ወይም ከማምለክ ይልቅ ሞትን መርጠዋል።—ዳን. 3:28

በርካታ እውነተኛ ክርስቲያኖች ሉዓላዊ ገዢያቸው ለሆነው ለይሖዋ ባላቸው ፍቅር የተነሳ ነፃነታቸውን አልፎ ተርፎም ሕይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለዋል። እነዚህ እውነተኛ ክርስቲያኖች በይሖዋ ፊት ያላቸውን ንጹሕ አቋም ለመጠበቅ ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። አቋማቸው ከሁሉ ለላቀው አምላክ ታማኝነታቸውን ለመጠበቅ ሲሉ ወደ እቶን እሳት ቢጣሉም በሕይወት ከተረፉት ሦስት ዕብራውያን ጋር ተመሳሳይ ነው። መዝሙራዊው ዳዊት በአምላክ ፊት ንጹሕ አቋምን መጠበቅ ያለውን አስፈላጊነት ሲጽፍ እንዲህ ብሏል፦ “ይሖዋ በሕዝቦች ላይ ፍርድ ያስተላልፋል። ይሖዋ ሆይ፣ እንደ ጽድቄ፣ እንደ ንጹሕ አቋሜም ፍረድልኝ።” (መዝ. 7:8) በሌላ ቦታ ላይ ደግሞ ዳዊት “ንጹሕ አቋሜና ቅንነቴ ይጠብቁኝ” በማለት ጽፏል። (መዝ. 25:21) ከሁሉ የተሻለው የሕይወት ጎዳና፣ ምንጊዜም ለይሖዋ ያለንን ታማኝነት መጠበቅ ነው። እንዲህ ካደረግን እንደ መዝሙራዊው ዓይነት ስሜት ይኖረናል፤ መዝሙራዊው “ንጹሕ አቋማቸውን የሚጠብቁ፣ በይሖዋ ሕግ የሚመላለሱ ሰዎች ደስተኞች ናቸው” ብሏል።—መዝ. 119:1 ግርጌ፤ w22.10 17 አን. 18-19

ረቡዕ፣ ሐምሌ 24

የማይታዩ . . . ባሕርያቱን ከተሠሩት ነገሮች ማስተዋል ይቻላል።—ሮም 1:20

ኢዮብ በሕይወቱ ሁሉ ካደረጋቸው ውይይቶች መካከል በተለይ አንዱን ፈጽሞ እንደማይረሳው መገመት እንችላለን፤ ይህም ከይሖዋ አምላክ ጋር ያደረገው ውይይት ነው። በዚህ ውይይት ላይ ይሖዋ ለኢዮብ አንዳንድ አስደናቂ የፍጥረት ሥራዎቹን እንዲመለከት ነግሮታል፤ ይህም ኢዮብ፣ ይሖዋ ምን ያህል ጥበበኛ እንደሆነ እንዲያይና ለአገልጋዮቹ የሚያስፈልጋቸውን ነገር የማቅረብ ችሎታ እንዳለው እንዲተማመን ያደርገዋል። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክ ለእንስሳት የሚያስፈልጋቸውን ነገር እንደሚያቀርብላቸው ለኢዮብ በማስታወስ እሱንም እንደሚንከባከበው አረጋግጦለታል። (ኢዮብ 38:39-41፤ 39:1, 5, 13-16) ኢዮብ አንዳንድ የፍጥረት ሥራዎችን በመመልከት ስለ አምላኩ ባሕርይ ብዙ ትምህርት ማግኘት ችሏል። እኛም የአምላክን የፍጥረት ሥራዎች በመመርመር ስለ አምላካችን ይበልጥ ማወቅ እንችላለን። ሆኖም እንዲህ ማድረግ ቀላል ላይሆንልን ይችላል። የምንኖረው ከተማ ውስጥ ከሆነ በዕለት ተዕለት ሕይወታችን ተፈጥሮን የምናይበት አጋጣሚ አነስተኛ ሊሆን ይችላል። ተፈጥሮን ማየት የሚቻልበት አካባቢ ብንኖርም እንኳ ቆም ብለን በደንብ ለመመልከት ጊዜ እንደሌለን ይሰማን ይሆናል። ሆኖም ተፈጥሮን ለመመልከት ጊዜ መመደባችንና ጥረት ማድረጋችን አስፈላጊ ነው። w23.03 15 አን. 1-2

ሐሙስ፣ ሐምሌ 25

ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል።—ምሳሌ 22:3

ኢየሱስ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት “ታላላቅ የምድር ነውጦች” እና ሌሎች አደጋዎች እንደሚከሰቱ ተናግሯል። (ሉቃስ 21:11) በተጨማሪም “ሕገ ወጥነት እየበዛ” እንደሚሄድ ተናግሯል፤ በአሁኑ ጊዜ የሚታየው ወንጀል፣ ዓመፅና የሽብርተኝነት ጥቃት ይህን ያሳያል። (ማቴ. 24:12 ግርጌ) ኢየሱስ እነዚህ አደጋዎች የሚደርሱት የይሖዋን ሞገስ ያጡ ሰዎች ላይ ብቻ እንደሆነ አልተናገረም። እንዲያውም በርካታ የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች አደጋ ደርሶባቸዋል። (ኢሳ. 57:1፤ 2 ቆሮ. 11:25) ይሖዋ በተአምራዊ መንገድ ከሁሉም አደጋዎች ባይታደገንም ለመረጋጋትና ሰላም ለማግኘት የሚያስፈልገንን ነገር ሁሉ ይሰጠናል። አደጋ ሲደርስ ምን እንደምናደርግ አስቀድመን ካቀድን መረጋጋት ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል። ይሁንና አስቀድመን መዘጋጀታችን በይሖዋ ላይ እምነት እንደሌለን የሚያሳይ ነው? በጭራሽ። እንዲያውም ለአደጋ መዘጋጀታችን ይሖዋ እኛን ለመንከባከብ ችሎታው እንዳለው እንደምናምን ያሳያል። እንዴት? የአምላክ ቃል፣ ሊያጋጥሙ ለሚችሉ አደጋዎች እንድንዘጋጅ ይመክረናል። w22.12 18 አን. 9-10

ዓርብ፣ ሐምሌ 26

አምላክ ከእናንተ አስቀድሞ የላከኝ ሕይወት ለማዳን ሲል ነው።—ዘፍ. 45:5

ዮሴፍ እስር ቤት በነበረበት ወቅት ይሖዋ የግብፅ ንጉሥ ሁለት አስጨናቂ ሕልሞችን እንዲያይ አደረገ። ፈርዖን፣ ዮሴፍ ሕልም የመተርጎም ችሎታ እንዳለው ሲሰማ ሰው ልኮ አስጠራው። በይሖዋ እርዳታ ዮሴፍ ሕልሞቹን ፈታ፤ እንዲሁም ጠቃሚ ምክር በመስጠት ፈርዖንን አስደመመው። ፈርዖን፣ ይሖዋ ከዮሴፍ ጋር እንዳለ ስለተገነዘበ የምግብ አቅርቦቱን እንዲቆጣጠር በመላው የግብፅ ምድር ላይ አስተዳዳሪ አድርጎ ሾመው። (ዘፍ. 41:38, 41-44) ከጊዜ በኋላ ከባድ ረሃብ ተከሰተ፤ ረሃቡ የተከሰተው በግብፅ ብቻ ሳይሆን የዮሴፍ ቤተሰቦች በሚኖሩበት በከነአንም ጭምር ነበር። አሁን ዮሴፍ የቤተሰቡን ሕይወት መታደግ እንዲሁም መሲሑ የሚመጣበትን የትውልድ መስመር ጠብቆ ማቆየት ቻለ። ዮሴፍ ያደረገውን ነገር ሁሉ ያሳካለት ይሖዋ እንደሆነ በግልጽ ማየት ይቻላል። በእርግጥም ይሖዋ የዮሴፍ ወንድሞች በጭካኔ የሸረቡትን ሴራ ተጠቅሞ በስተ መጨረሻ ዓላማውን ማስፈጸም ችሏል። w23.01 17 አን. 11-12

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 27

ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።—ሉቃስ 21:34

ለራሱ የሚጠነቀቅ ወይም ትኩረት የሚሰጥ ሰው ከይሖዋ ጋር ያለውን ዝምድና ሊያበላሹበት የሚችሉ አደጋዎችን በንቃት ይከታተላል፤ ከእነዚህ አደጋዎች ለመራቅም አስፈላጊውን እርምጃ ይወስዳል። እንዲህ በማድረግ ከአምላክ ፍቅር ሳይወጣ መኖር ይችላል። (ምሳሌ 22:3፤ ይሁዳ 20, 21) ሐዋርያው ጳውሎስም ክርስቲያኖችን ለራሳቸው ትኩረት እንዲሰጡ አሳስቧቸዋል። ለምሳሌ በኤፌሶን ያሉትን ክርስቲያኖች እንዲህ ብሏቸዋል፦ “የምትመላለሱት ጥበብ እንደጎደላቸው ሳይሆን እንደ ጥበበኛ ሰዎች መሆኑን ምንጊዜም በጥንቃቄ አስተውሉ።” (ኤፌ. 5:15, 16) ሰይጣን በመንፈሳዊነታችን ላይ የማያባራ ጥቃት ይሰነዝራል፤ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰነዘርብንን ማንኛውንም ጥቃት መቋቋም እንድንችል “የይሖዋ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ” የሚል ምክር የሚሰጠን ለዚህ ነው። (ኤፌ. 5:17) ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ ‘የይሖዋን ፈቃድ’ ማስተዋል ይኖርብናል። ይህን ማድረግ የምንችለው የአምላክን ቃል አዘውትረን በማንበብና ባነበብነው ላይ በማሰላሰል ነው። የይሖዋን ፈቃድ ይበልጥ በተረዳንና ‘የክርስቶስን አስተሳሰብ’ ባዳበርን መጠን ‘እንደ ጥበበኛ ሰዎች መመላለስ’ ይበልጥ ቀላል ይሆንልናል፤ ምን ማድረግ እንዳለብን የሚገልጽ ቀጥተኛ ሕግ ባይኖርም እንኳ ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ እናደርጋለን።—1 ቆሮ. 2:14-16፤ w23.02 16-17 አን. 7-9

እሁድ፣ ሐምሌ 28

ጥሩ የሆነውን፣ ተቀባይነት ያለውንና ፍጹም የሆነውን የአምላክ ፈቃድ መርምራችሁ ማረጋገጥ ትችሉ ዘንድ አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።—ሮም 12:2

ቤትህን የምታጸዳው በየስንት ጊዜው ነው? በዚህ ቤት መኖር ከመጀመርህ በፊት ቤቱን በደንብ እንዳጸዳኸው ምንም ጥያቄ የለውም። ይሁንና ከዚያ በኋላ ችላ ብትለውስ? ወዲያውኑ መልሶ መቆሸሹ አይቀርም። ቤትህ ምንጊዜም እንዳማረበት እንዲቆይ አዘውትረህ ማጽዳት ይኖርብሃል። ከአስተሳሰባችንና ከባሕርያችን ጋር በተያያዘም ቀጣይነት ያለው ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። ከመጠመቃችን በፊት “ሥጋንና መንፈስን ከሚያረክስ ነገር ሁሉ ራሳችንን [ለማንጻት]” ስንል በሕይወታችን ውስጥ አስፈላጊውን ለውጥ እንዳደረግን ምንም ጥያቄ የለውም። (2 ቆሮ. 7:1) ሆኖም አሁንም ቢሆን፣ ሐዋርያው ጳውሎስ ‘እየታደስን እንድንሄድ’ የሰጠውን ምክር መከተል ይኖርብናል። (ኤፌ. 4:23) የዚህ ዓለም ቆሻሻ ወዲያውኑ ሊበክለን ይችላል። በይሖዋ ፊት እንዳማረብን ለመኖር ከፈለግን አስተሳሰባችንን፣ ባሕርያችንንና ምኞታችንን አዘውትረን መመርመር ይኖርብናል። w23.01 8 አን. 1-2

ሰኞ፣ ሐምሌ 29

የአምላክም መንፈስ በእሱ ላይ እንደ ርግብ ሲወርድ አየ።—ማቴ. 3:16

ኢየሱስ ሲያስተምር ማዳመጥ ምን ሊመስል እንደሚችል እስቲ አስቡት። ቅዱሳን መጻሕፍትን በተደጋጋሚ በቃሉ ይጠቅስ ነበር! በተጠመቀበትና በመንፈስ ቅዱስ በተቀባበት ወቅት ሰው ሆኖ ከመምጣቱ በፊት ስለነበረው ሕይወት ማስታወስ እንደቻለ ከሁኔታዎች መረዳት ይቻላል። ከተጠመቀ በኋላ የተናገራቸው ተመዝግበው የሚገኙት የመጀመሪያዎቹ ቃላትም ሆኑ ልክ ከመሞቱ በፊት ከተናገራቸው የመጨረሻ ቃላት መካከል አንዳንዶቹ ከቅዱሳን መጻሕፍት የተወሰዱ ነበሩ። (ዘዳ. 8:3፤ መዝ. 31:5፤ ሉቃስ 4:4፤ 23:46) በእነዚህ ሁለት ክንውኖች መካከል ባሉት ሦስት ዓመት ተኩል ጊዜያት ውስጥ ደግሞ በሕዝብ ፊት በተደጋጋሚ ቅዱሳን መጻሕፍትን አንብቧል፣ ጠቅሷል እንዲሁም አብራርቷል። (ማቴ. 5:17, 18, 21, 22, 27, 28፤ ሉቃስ 4:16-20) ኢየሱስ አገልግሎቱን ከመጀመሩ በፊት ባሉት ዓመታት የአምላክን ቃል በተደጋጋሚ ያነብና ያዳምጥ ነበር። ቤት ውስጥ ማርያምና ዮሴፍ ከቅዱሳን መጻሕፍት ላይ ሲጠቅሱ እንደሰማ ምንም ጥርጥር የለውም። (ዘዳ. 6:6, 7) በተጨማሪም ኢየሱስ በየሰንበቱ ከቤተሰቡ ጋር በምኩራብ ይገኝ ነበር። (ሉቃስ 4:16) እዚያ በሚገኝበት ወቅት ቅዱሳን መጻሕፍት ሲነበቡ በጥንቃቄ ያዳምጥ እንደነበር ግልጽ ነው። w23.02 8 አን. 1-2

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 30

አምላክህን ይሖዋን . . . ውደድ።—ማር. 12:30

ይሖዋን እንድትወደው የሚያደርጉህ በጣም ብዙ ምክንያቶች አሉህ። ለምሳሌ እሱ “የሕይወት ምንጭ” እንደሆነ እንዲሁም “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ” የሚገኘው ከእሱ እንደሆነ ተምረሃል። (መዝ. 36:9፤ ያዕ. 1:17) በሕይወትህ ደስተኛ እንድትሆን የሚያደርጉህ ነገሮች ሁሉ ምንጭ ለጋስና አፍቃሪ የሆነው አምላክ ነው። ቤዛው ይሖዋ የሰጠን እጅግ አስደናቂ ስጦታ ነው። እንዲህ የምንለው ለምንድን ነው? በይሖዋና በልጁ መካከል ያለውን የጠበቀ ዝምድና ለማሰብ ሞክር። ኢየሱስ “አብ ይወደኛል” እንዲሁም ‘እኔ አብን እወደዋለሁ’ በማለት ተናግሯል። (ዮሐ. 10:17፤ 14:31) በቢሊዮኖች ለሚቆጠሩ ዓመታት አብረው ስለኖሩ በመካከላቸው ያለው ዝምድና በጣም ጠንካራ ነው። (ምሳሌ 8:22, 23, 30) ከዚህ አንጻር አምላክ ልጁ ተሠቃይቶ እንዲሞት ሲፈቅድ ምን ያህል አዝኖ ሊሆን እንደሚችል አስበው። ይሖዋ አንተን ጨምሮ ለመላው የሰው ዘር ካለው ጥልቅ ፍቅር የተነሳ አንተም ሆንክ ሌሎች ሰዎች ለዘላለም መኖር እንድትችሉ ሲል የሚወደው ልጁ መሥዋዕት እንዲሆን ፈቅዷል። (ዮሐ. 3:16፤ ገላ. 2:20) አምላክን ለመውደድ የሚያነሳሳ ከዚህ የበለጠ ምን ምክንያት ሊኖር ይችላል? w23.03 4-5 አን. 11-13

ረቡዕ፣ ሐምሌ 31

ያላችሁን አጥብቃችሁ ያዙ።—ራእይ 2:25

ከከሃዲዎች ትምህርት መራቅ ይኖርብናል። ኢየሱስ በጴርጋሞን ጉባኤ ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችን ክፍፍልና ኑፋቄ እንዲኖር በማድረጋቸው ወቅሷቸዋል። (ራእይ 2:14-16) በትያጥሮን ያሉ አንዳንድ ክርስቲያኖችን ደግሞ ‘ከሰይጣን ጥልቅ ነገሮች’ በመራቃቸው አመስግኗቸዋል፤ እንዲሁም እውነትን ‘አጥብቀው እንዲይዙ’ አሳስቧቸዋል። (ራእይ 2:24-26) በዚህ ጉባኤ ያሉ በሐሰት ትምህርት የተታለሉ አንዳንድ ደካማ ክርስቲያኖች ንስሐ መግባት ያስፈልጋቸው ነበር። በዛሬው ጊዜስ? ከይሖዋ አስተሳሰብ ጋር ከሚጻረር ማንኛውም ትምህርት መራቅ አለብን። ከሃዲዎች “ለአምላክ ያደሩ መስለው” ይታዩ ይሆናል፤ “በሥራቸው ግን ኃይሉን ይክዳሉ።” (2 ጢሞ. 3:5) የአምላክን ቃል በትጋት የምናጠና ከሆነ የሐሰት ትምህርቶችን መለየትና ከዚያ መራቅ ቀላል ይሆንልናል። (2 ጢሞ. 3:14-17፤ ይሁዳ 3, 4) የምናቀርበው አምልኮ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ያለው መሆኑን ማረጋገጣችን በጣም አስፈላጊ ነው። አምልኳችን ተቀባይነት እንዲያጣ የሚያደርግ ነገር እያደረግን ከሆነ ሁኔታውን ለማስተካከል በአፋጣኝ እርምጃ መውሰድ አለብን።—ራእይ 2:5, 16፤ 3:3, 16፤ w22.05 4 አን. 9፤ 5 አን. 11

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ