የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es24 ገጽ 78-88
  • ነሐሴ

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ነሐሴ
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2024
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 1
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 2
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 3
  • እሁድ፣ ነሐሴ 4
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 5
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 6
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 7
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 8
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 9
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 10
  • እሁድ፣ ነሐሴ 11
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 12
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 13
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 14
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 15
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 16
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 17
  • እሁድ፣ ነሐሴ 18
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 19
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 20
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 21
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 22
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 23
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 24
  • እሁድ፣ ነሐሴ 25
  • ሰኞ፣ ነሐሴ 26
  • ማክሰኞ፣ ነሐሴ 27
  • ረቡዕ፣ ነሐሴ 28
  • ሐሙስ፣ ነሐሴ 29
  • ዓርብ፣ ነሐሴ 30
  • ቅዳሜ፣ ነሐሴ 31
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2024
es24 ገጽ 78-88

ነሐሴ

ሐሙስ፣ ነሐሴ 1

[ይሖዋን] ለሚፈሩና በስሙ ላይ ለሚያሰላስሉ በፊቱ የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ።—ሚል. 3:16

ይሖዋ እሱን እንደሚፈሩና በስሙ ላይ እንደሚያሰላስሉ በንግግራቸው የሚያሳዩ ሰዎችን ‘በመታሰቢያ መጽሐፉ’ ላይ የሚጽፈው ለምን ይመስልሃል? ንግግራችን በልባችን ውስጥ ያለውን ነገር ቁልጭ አድርጎ ያሳያል። ኢየሱስ “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነው” ብሏል። (ማቴ. 12:34) ይሖዋ እሱን የሚወዱ ሰዎች በአዲሱ ዓለም ውስጥ ለዘላለም በደስታ እንዲኖሩ ይፈልጋል። አነጋገራችን አምልኳችን በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት እንዲያገኝ ወይም እንዲያጣ ሊያደርግ ይችላል። (ያዕ. 1:26) አምላክን የማይወዱ አንዳንድ ሰዎች ሲናገሩ ይቆጣሉ፣ ሌሎችን ያመናጭቃሉ እንዲሁም ጉራ ይነዛሉ። (2 ጢሞ. 3:1-5) እንደ እነሱ መሆን አንፈልግም። ፍላጎታችን ይሖዋን በንግግራችን ማስደሰት ነው። ይሁንና በክርስቲያናዊ ስብሰባዎች ወይም በአገልግሎት ላይ የምናገኛቸውን ሰዎች በአክብሮትና በደግነት እያነጋገርን ቤት ገብተን የቤተሰባችንን አባላት የምናመናጭቅ ከሆነ ይሖዋ ሊደሰትብን ይችላል?—1 ጴጥ. 3:7፤ w22.04 5 አን. 4-5

ዓርብ፣ ነሐሴ 2

አመንዝራዋን ይጠሏታል፤ ከዚያም ይበዘብዟታል፤ ራቁቷንም ያስቀሯታል፤ እንዲሁም ሥጋዋን ይበላሉ፤ ሙሉ በሙሉም በእሳት ያቃጥሏታል።—ራእይ 17:16

አምላክ በአሥሩ ቀንዶችና በአውሬው ልብ ውስጥ ሐሳቡን በማስገባት ታላቂቱ ባቢሎንን እንዲያጠፉ ያደርጋቸዋል። ይሖዋ ብሔራትን በዓለም የሐሰት ሃይማኖቶች ላይ እንዲነሱና ሙሉ በሙሉ እንዲያጠፏቸው ያነሳሳቸዋል። ብሔራት ይህን የሚያደርጉት ደማቁን ቀይ አውሬ ማለትም የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ተጠቅመው ነው። (ራእይ 18:21-24) ይህ ለእኛ ምን ትርጉም አለው? አምልኳችን ምንጊዜም “በአምላካችንና በአባታችን ዓይን ንጹሕና ያልረከሰ” ሊሆን ይገባል። (ያዕ. 1:27) የታላቂቱ ባቢሎን የሐሰት ትምህርቶች፣ አረማዊ በዓላቷ፣ ልል የሆኑት የሥነ ምግባር መሥፈርቶቿ እንዲሁም መናፍስታዊ ድርጊቶቿ ተጽዕኖ እንዲያደርጉብን ፈጽሞ አንፍቀድ። በተጨማሪም ሰዎች የኃጢአቷ ተካፋይ እንዳይሆኑ “ከእሷ ውጡ” የሚለውን ጥሪ ማሰማታችንን መቀጠል አለብን።—ራእይ 18:4፤ w22.05 11 አን. 17-18

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 3

የይሖዋን የታማኝ ፍቅር መግለጫዎች . . . እናገራለሁ።—ኢሳ. 63:7

ወላጆች፣ ልጆቻችሁን ስለ ይሖዋ ለማስተማር አጋጣሚ ፍጠሩ። ስለ ይሖዋና እሱ ስላደረገላችሁ ብዙ መልካም ነገሮች ተናገሩ። (ዘዳ. 6:6, 7) በተለይም ቤተሰባችሁ በሃይማኖት የተከፋፈለ በመሆኑ ልጆቻችሁን በቋሚነት ማስጠናት የማትችሉ ከሆነ እንዲህ ማድረጋችሁ በጣም አስፈላጊ ነው። ክርስቲን የተባለች እህት እንዲህ ብላለች፦ “መንፈሳዊ ነገሮችን ለመወያየት ብዙም አጋጣሚ ስለማላገኝ ያገኘሁትን ማንኛውንም አጋጣሚ ጥሩ አድርጌ ለመጠቀም እሞክር ነበር።” በተጨማሪም ስለ ይሖዋ ድርጅት እንዲሁም ስለ ወንድሞችና እህቶች አዎንታዊ ነገር ተናገሩ። ሽማግሌዎችን አትተቹ። ስለ ሽማግሌዎች የምትናገሩት ነገር ልጆቻችሁ እርዳታ በሚያስፈልጋቸው ጊዜ ወደ እነሱ ዞር እንዳይሉ እንቅፋት ሊሆን ይችላል። በቤት ውስጥ ሰላም አስፍኑ። ለትዳር ጓደኛችሁና ለልጆቻችሁ ያላችሁን ፍቅር አዘውትራችሁ ግለጹ። ስለ ባላችሁ በደግነትና በአክብሮት ተናገሩ፤ ልጆቻችሁም እንዲሁ እንዲያደርጉ አሠልጥኗቸው። እንዲህ ስታደርጉ ስለ ይሖዋ ለመማር የሚያመች ሰላማዊ መንፈስ እንዲሰፍን ታደርጋላችሁ።—ያዕ. 3:18፤ w22.04 18 አን. 10-11

እሁድ፣ ነሐሴ 4

ሥራህን አውቃለሁ።—ራእይ 3:1

ኢየሱስ ለኤፌሶን ጉባኤ የጻፈው መልእክት እንደሚያሳየው እነዚህ ክርስቲያኖች የተለያዩ ፈተናዎች ቢያጋጥሟቸውም ጸንተዋል፤ እንዲሁም ሳይታክቱ ይሖዋን ማገልገላቸውን ቀጥለዋል። ይሁንና መጀመሪያ ላይ የነበራቸውን ፍቅር ትተው ነበር። ይህን ፍቅራቸውን መልሰው ማቀጣጠል ያስፈልጋቸው ነበር፤ አለዚያ አምልኳቸው ተቀባይነት አይኖረውም። በዛሬው ጊዜም መጽናታችን ብቻውን በቂ አይደለም። እንድንጸና የሚያነሳሳን ምክንያትም ትክክለኛ መሆን ይኖርበታል። አምላካችን ምን እናደርጋለን የሚለው ብቻ ሳይሆን ለምን እናደርጋለን የሚለውም ያሳስበዋል። አንድን ነገር ለማድረግ ለተነሳሳንበት ዝንባሌ ትኩረት ይሰጣል፤ ምክንያቱም እንድናመልከው የሚፈልገው ለእሱ ባለን ጥልቅ ፍቅርና አድናቆት ተነሳስተን ነው። (ምሳሌ 16:2፤ ማር. 12:29, 30) ምንጊዜም ንቁ መሆን ይኖርብናል። የሰርዴስ ጉባኤ ክርስቲያኖች የነበረባቸው ችግር ደግሞ የተለየ ነው። ቀደም ሲል በመንፈሳዊ ሥራ የተጠመዱ ነበሩ፤ በኋላ ላይ ግን ለአምላክ ከሚያቀርቡት አገልግሎት ጋር በተያያዘ ቸልተኞች መሆን ጀምረው ነበር። ኢየሱስ “ንቃ” ብሏቸዋል። (ራእይ 3:1-3) እውነት ነው፣ ይሖዋ ያከናወንነውን ሥራ ፈጽሞ አይረሳም።—ዕብ. 6:10፤ w22.05 3 አን. 6-7

ሰኞ፣ ነሐሴ 5

በትጋት ያከናወኑት ነገር ሁሉ ጥቅም ያስገኛል።—ምሳሌ 14:23

ሰለሞን ተግቶ መሥራት የሚያስገኘውን ደስታ “የአምላክ ስጦታ” ሲል ገልጾታል። (መክ. 5:18, 19) “በትጋት ያከናወኑት ነገር ሁሉ ጥቅም ያስገኛል” በማለት ጽፏል። ሰለሞን ይህን ከራሱ ሕይወት ተነስቶ መናገር ይችላል። ትጉ ሠራተኛ ነበር! ቤቶችን ሠርቷል፤ ወይን ተክሏል፤ የአትክልት ስፍራዎችንና የውኃ ማጠራቀሚያዎችንም ሠርቷል። ከዚህም በተጨማሪ ከተሞችን ገንብቷል። (1 ነገ. 9:19፤ መክ. 2:4-6) ይህ ትጋት የሚጠይቅ ሥራ ነበር፤ በተወሰነ መጠንም ቢሆን እርካታ አስገኝቶለት እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። ይሁንና ሰለሞን እንዲህ ያሉ ሥራዎችን ማከናወን ብቻውን እውነተኛ ደስታ እንደማያስገኝ ተገንዝቦ ነበር። በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችም ተካፍሏል። ለምሳሌ ለይሖዋ አምልኮ የሚሆን አስደናቂ ቤተ መቅደስ በተገነባበት ወቅት ሥራውን በበላይነት ይከታተል ነበር፤ ይህ የግንባታ ሥራ ሰባት ዓመት ፈጅቷል! (1 ነገ. 6:38፤ 9:1) በዓለማዊም ሆነ በመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች መካፈል ምን እንደሚመስል የሚያውቀው ሰለሞን መንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ከሌሎች ሥራዎች እጅግ የላቁ እንደሆኑ ተገንዝቧል። “ሁሉ ነገር ከተሰማ በኋላ መደምደሚያው ይህ ነው፦ እውነተኛውን አምላክ ፍራ፤ ትእዛዛቱንም ጠብቅ” ሲል ጽፏል።—መክ. 12:13፤ w22.05 22 አን. 8

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 6

አምላክ በክርስቶስ አማካኝነት በነፃ ይቅር [ብሏችኋል]።—ኤፌ. 4:32

ይሖዋ በነፃ ይቅር ያላቸው በርካታ ሰዎች ታሪክ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይገኛል። የማንን ታሪክ ታስታውሳለህ? ንጉሥ ምናሴን ታስታውስ ይሆናል። ይህ ክፉ ሰው ዘግናኝ ኃጢአቶችን በመሥራት ይሖዋን አሳዝኗል። የሐሰት አምልኮን አስፋፍቷል። የገዛ ልጆቹን እንኳ ለሐሰት አማልክት መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል። ይባስ ብሎም ቅዱስ በሆነው የይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ጣዖት አቁሟል። መጽሐፍ ቅዱስ ስለ እሱ ሲናገር “ይሖዋን ያስቆጣው ዘንድ በእሱ ፊት በጣም ብዙ መጥፎ ነገሮችን ሠራ” ይላል። (2 ዜና 33:2-7) ሆኖም ምናሴ ከልቡ ንስሐ ስለገባ ይሖዋ በነፃ ይቅር ብሎታል። (2 ዜና 33:12, 13) ምናልባት የንጉሥ ዳዊትን ታሪክም ታስታውስ ይሆናል። ንጉሥ ዳዊት እንደ ምንዝርና ነፍስ ግድያ ያሉ ከባድ ኃጢአቶችን በመሥራት ይሖዋን አሳዝኗል። ሆኖም ዳዊት ኃጢአቱን አምኖ ተቀብሎ ከልቡ ንስሐ ስለገባ ይሖዋ በነፃ ይቅር ብሎታል። (2 ሳሙ. 12:9, 10, 13, 14) በእርግጥም ይሖዋ ይቅር ለማለት እንደሚጓጓ መተማመን እንችላለን። w22.06 3 አን. 7

ረቡዕ፣ ነሐሴ 7

በትዕግሥት ጠብቁ፤ . . . ልባችሁን አጽኑ።—ያዕ. 5:8

ተስፋችን እንዳይደበዝዝ ማድረግ ሁልጊዜ ቀላል አይደለም። አምላክ ቃሉን የሚፈጽምበትን ጊዜ ስንጠባበቅ ትዕግሥት ልናጣ እንችላለን። ሆኖም ይሖዋ ዘላለማዊ አምላክ ነው፤ በመሆኑም እሱ ለጊዜ ያለው አመለካከት ከእኛ የተለየ ነው። (2 ጴጥ. 3:8, 9) ዓላማውን የሚፈጽመው ከሁሉ በተሻለው መንገድ ነው፤ ሆኖም እርምጃ የሚወስደው እኛ በጠበቅነው ጊዜ ላይሆን ይችላል። ታዲያ አምላካችን ቃሉን እስኪፈጽም በትዕግሥት በምንጠባበቅበት ጊዜ ተስፋችን እንዳይደበዝዝ ምን ይረዳናል? (ያዕ. 5:7) ለተስፋችን ዋስትና የሰጠንን ይሖዋን የሙጥኝ እንበል። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ተስፋን ይሖዋ ስለመኖሩ እንዲሁም ‘ከልብ ለሚፈልጉት ወሮታ ከፋይ ስለመሆኑ’ ካለን እምነት ጋር ያያይዘዋል። (ዕብ. 11:1, 6) ይሖዋ ይበልጥ እውን በሆነልን መጠን ቃል የገባውን ነገር ሁሉ እንደሚፈጽም ይበልጥ እንተማመናለን። ተስፋችን እንዳይደበዝዝ ለማድረግ ወደ ይሖዋ መጸለይና ቃሉን ማንበብ አለብን። ይሖዋን ማየት ባንችልም ወደ እሱ መቅረብ እንችላለን። እንደሚሰማን እርግጠኞች ሆነን በጸሎት ልናነጋግረው እንችላለን።—ኤር. 29:11, 12፤ w22.10 26 አን. 11-13

ሐሙስ፣ ነሐሴ 8

ኢዮብ መናገርና የተወለደበትን ቀን መርገም ጀመረ።—ኢዮብ 3:1

እስቲ ሁኔታውን በዓይነ ሕሊናህ ለመሣል ሞክር። ኢዮብ አመድ ላይ ተቀምጧል፤ ሕመሙ በኃይል እያሠቃየው ነው። (ኢዮብ 2:8) ሦስቱ ወዳጅ ተብዬዎች የማያባራ ክስ እየሰነዘሩበትና ስሙን ለማጠልሸት እየሞከሩ ነው። የደረሰበት መከራ እንደ ከባድ ሸክም ተጭኖታል፤ ልጆቹን ማጣቱ ያስከተለበት ሐዘን ውስጥ ውስጡን እየበላው ነው። መጀመሪያ ላይ ኢዮብ ምንም አልተናገረም። (ኢዮብ 2:13) ወዳጅ ተብዬዎቹ የኢዮብ ዝምታ ለፈጣሪው ጀርባውን እንደሰጠ የሚያሳይ እንደሆነ ከተሰማቸው በእጅጉ ተሳስተዋል። በአንድ ወቅት ኢዮብ፣ ሦስቱን ሰዎች ቀና ብሎ ዓይን ዓይናቸውን እያየ ሳይሆን አይቀርም “እስክሞት ድረስ ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!” አላቸው። (ኢዮብ 27:5) ኢዮብ ይህ ሁሉ መከራ ቢደርስበትም ደፋርና ብርቱ እንዲሆን የረዳው ምንድን ነው? በሐዘን በተዋጠበት ጊዜም እንኳ፣ የሚወደው አባቱ ይዋል ይደር እንጂ ከሥቃዩ እንደሚገላግለው ተስፋ ያደርግ ነበር። ቢሞት እንኳ ይሖዋ እንደሚያስነሳው ያውቅ ነበር።—ኢዮብ 14:13-15፤ w22.06 22 አን. 9

ዓርብ፣ ነሐሴ 9

እንግዲያው እናንተ በዚህ መንገድ ጸልዩ፦ “በሰማያት የምትኖር አባታችን ሆይ፣ ስምህ ይቀደስ። መንግሥትህ ይምጣ። ፈቃድህ . . . ይፈጸም።”—ማቴ. 6:9, 10

የሰማይና የምድር ፈጣሪ ወደሆነው አምላክ በጸሎት የመቅረብ አስደናቂ መብት አግኝተናል። በማንኛውም ሰዓት፣ ማንኛውንም ቋንቋ ተጠቅመን ልባችንን ለይሖዋ ማፍሰስ እንችላለን። የሆስፒታል አልጋ ላይም እንሁን እስር ቤት ውስጥ፣ የሚወደን አባታችን እንደሚሰማን ተማምነን ወደ እሱ መጸለይ እንችላለን። ይህን መብት በፍጹም አቅልለን አንመለከተውም። ንጉሥ ዳዊት የጸሎት መብቱን ከፍ አድርጎ ይመለከተው ነበር። “ጸሎቴ በአንተ ፊት እንደተዘጋጀ ዕጣን ይሁን” በማለት ለይሖዋ ዘምሯል። (መዝ. 141:1, 2) በዳዊት ዘመን ካህናቱ ለእውነተኛው አምልኮ የሚጠቀሙበት ቅዱስ ዕጣን የሚዘጋጀው በከፍተኛ ጥንቃቄ ነበር። (ዘፀ. 30:34, 35) ዳዊት ስለ ዕጣን መጥቀሱ ወደ ሰማዩ አባቱ ሲጸልይ ምን እንደሚል አስቀድሞ በጥንቃቄ እንደሚያስብበት ያመለክታል። የእኛም ልባዊ ፍላጎት ይኸው ነው። ጸሎታችን ይሖዋን የሚያስደስት እንዲሆን እንፈልጋለን። w22.07 20 አን. 1-2፤ 21 አን. 4

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 10

“በቀል የእኔ ነው፤ እኔ ብድራትን እመልሳለሁ” ይላል ይሖዋ።—ሮም 12:19

በቀል የይሖዋ ነው። ይሖዋ የበደሉንን እንድንበቀል አልፈቀደልንም። (ሮም 12:20, 21) እይታችን የተዛባና የተገደበ ስለሆነ እንደ አምላክ ትክክለኛ ፍርድ ማስተላለፍ አንችልም። (ዕብ. 4:13) ደግሞም አንዳንድ ጊዜ ስሜታችን የማመዛዘን ችሎታችንን ይጋርደዋል። ያዕቆብ በይሖዋ መንፈስ ተመርቶ “የሰው ቁጣ የአምላክ ጽድቅ እንዲፈጸም አያደርግም” በማለት ጽፏል። (ያዕ. 1:20) ይሖዋ ትክክለኛውን ነገር እንደሚያደርግና ፍትሕን ፍጹም በሆነ መንገድ እንደሚያስፈጽም እርግጠኛ መሆን እንችላለን። ይቅር ማለታችን በይሖዋ ፍትሕ እንደምንተማመን ያሳያል። ጉዳዩን በይሖዋ እጅ ስንተወው ይሖዋ ኃጢአት ያስከተለውን ጉዳት በሙሉ እንደሚያስተካክል እምነት እንዳለን እናሳያለን። አምላክ እንደሚያመጣ ቃል በገባው አዲስ ዓለም ውስጥ፣ የስሜት ቁስል ያስከተሉብን ነገሮች ጨርሶ “አይታሰቡም፤ ወደ ልብም አይገቡም።”—ኢሳ. 65:17፤ w22.06 10-11 አን. 11-12

እሁድ፣ ነሐሴ 11

በስሜ ምክንያት በሕዝቦች ሁሉ ዘንድ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ።—ማቴ. 24:9

ሰዎች የሚጠሉን መሆኑ ራሱ የይሖዋ ሞገስ እንዳለን የሚያሳይ ማስረጃ ነው። (ማቴ. 5:11, 12) ከዚህ ተቃውሞ በስተ ጀርባ ያለው ዲያብሎስ ነው። ሆኖም የኢየሱስ ኃይል ከዲያብሎስ በእጅጉ ይበልጣል! በኢየሱስ እርዳታ ምሥራቹ ለሁሉም ብሔራት እየተዳረሰ ነው። ይህን የሚያሳዩ ማስረጃዎች አሉ። ምሥራቹን ስንሰብክ የሚያጋጥመን ሌላው ተፈታታኝ ሁኔታ የቋንቋ ልዩነት ነው። ኢየሱስ ለሐዋርያው ዮሐንስ ባሳየው ራእይ ላይ በዘመናችን ምሥራቹ ይህን እንቅፋት እንደሚያሸንፍ ተንብዮአል። (ራእይ 14:6, 7) ይህ ትንቢት እየተፈጸመ ያለው እንዴት ነው? በተቻለ መጠን ብዙ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት እንዲሰሙ አጋጣሚ እየሰጠናቸው ነው። በዛሬው ጊዜ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ሰዎች jw.org በተባለው ድረ ገጻችን ላይ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ማንበብ ይችላሉ፤ ምክንያቱም በድረ ገጹ ላይ ከ1,000 በሚበልጡ ቋንቋዎች መረጃ ማግኘት ይቻላል! ደቀ መዛሙርት ለማድረግ የምንጠቀምበት ዋነኛ የማስተማሪያ መሣሪያ የሆነው ለዘላለም በደስታ ኑር! የተባለው መጽሐፍ ከ700 በሚበልጡ ቋንቋዎች እንዲተረጎም ፈቃድ ተሰጥቷል! w22.07 9 አን. 6-7

ሰኞ፣ ነሐሴ 12

ብዙ አማካሪዎች ባሉበት . . . ስኬት ይገኛል።—ምሳሌ 11:14

ኢየሱስ ለሰዎች ይራራ ነበር። ሐዋርያው ማቴዎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፦ “ሕዝቡንም ባየ ጊዜ እረኛ እንደሌላቸው በጎች ተገፈውና ተጥለው ስለነበር እጅግ አዘነላቸው።” (ማቴ. 9:36) ይሖዋስ ምን ይሰማዋል? ኢየሱስ “በሰማይ ያለው አባቴ ከእነዚህ ከትናንሾቹ መካከል አንዱም እንኳ እንዲጠፋ አይፈልግም” ብሏል። (ማቴ. 18:14) ይህ ምንኛ የሚያጽናና ነው! ኢየሱስን ይበልጥ እያወቅነው ስንሄድ ለይሖዋ ያለን ፍቅር ያድጋል። በጉባኤህ ውስጥ ካሉ የጎለመሱ ወንድሞችና እህቶች ጋር መቀራረብህም ይሖዋን ይበልጥ ለመውደድና መንፈሳዊ እድገት ለማድረግ ይረዳሃል። ምን ያህል ደስተኛ እንደሆኑ ልብ ብለህ ተመልከት። ይሖዋን ለማገልገል በመወሰናቸው ቅንጣት ታክል አይቆጩም። በይሖዋ አገልግሎት ሲካፈሉ ያገኟቸውን አንዳንድ ተሞክሮዎች እንዲነግሩህ ለምን አትጠይቃቸውም? አስፈላጊ ውሳኔ ከማድረግህ በፊት ምክር ጠይቃቸው። ደግሞም “ብዙ አማካሪዎች ባሉበት” ስኬት እንደሚገኝ አትርሳ። w22.08 3 አን. 6-7

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 13

የይሖዋ ዓይኖች ጻድቃንን ይመለከታሉ።—1 ጴጥ. 3:12

ሁላችንም በተለያየ መልኩ ፈተና ያጋጥመናል። ይሁንና መቼም ቢሆን ፈተናውን ብቻችንን መጋፈጥ አያስፈልገንም። ይሖዋ ልክ እንደ አንድ አፍቃሪ አባት ሁልጊዜ በትኩረት ይመለከተናል። እሱ ከጎናችን ነው፤ እርዳታ ለማግኘት የምናሰማውን ጩኸት ለማዳመጥ እንዲሁም እኛን ለመደገፍ ሁሌም ዝግጁ ነው። (ኢሳ. 43:2) ለመጽናት የሚያስፈልጉንን ነገሮች በሙሉ አትረፍርፎ ስለሰጠን ማንኛውንም መከራ መቋቋም እንደምንችል እርግጠኞች ነን። የጸሎት መብት፣ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ እንዲሁም እርዳታ ሲያስፈልገን የሚደርስልን አፍቃሪ የወንድማማች ማኅበር ሰጥቶናል። በትኩረት የሚመለከተን ሰማያዊ አባት ስላለን ምንኛ አመስጋኞች ነን! “ልባችን በእሱ ሐሴት ያደርጋል።” (መዝ. 33:21) ይሖዋ እኛን ለመርዳት ባደረጋቸው ዝግጅቶች በሙሉ በመጠቀም የእሱን ፍቅራዊ እንክብካቤ እንደምናደንቅ እናሳያለን። በተጨማሪም በአምላክ እንክብካቤ ውስጥ ለመኖር የበኩላችንን ድርሻ መወጣት ያስፈልገናል። በሌላ አነጋገር፣ ይሖዋን ለመታዘዝና በእሱ ዓይን ትክክል የሆነውን ነገር ለማድረግ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ ማድረጋችንን ከቀጠልን እሱ ለዘላለም በትኩረት ይመለከተናል! w22.08 13 አን. 15-16

ረቡዕ፣ ነሐሴ 14

የቃልህ ፍሬ ነገር እውነት ነው።—መዝ. 119:160

በዛሬው ጊዜ ብዙ ሰዎች ማንን እንደሚያምኑ ግራ ገብቷቸዋል። የሚያከብሯቸው ሰዎች ለምሳሌ ፖለቲከኞች፣ ሳይንቲስቶችና በንግዱ ዓለም ያሉ ሰዎች ለእነሱ ጥቅም የሚያስቡ መሆኑን ይጠራጠራሉ። በተጨማሪም ለሕዝበ ክርስትና ቀሳውስት አክብሮት የላቸውም። በመሆኑም እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ‘እንመራበታለን’ የሚሉትን መጽሐፍ ቅዱስን በጥርጣሬ ዓይን ማየታቸው አያስገርምም። እኛ የይሖዋ አገልጋዮች፣ እሱ “የእውነት አምላክ” እንደሆነና ምንጊዜም ለእኛ ጥቅም እንደሚያስብ እርግጠኞች ነን። (መዝ. 31:5፤ ኢሳ. 48:17) በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ያለውን ሐሳብ ልንተማመንበት እንደምንችል እናውቃለን። አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁር በጻፉት ሐሳብ እንስማማለን፤ እንዲህ ብለዋል፦ “አምላክ የተናገረው ማንኛውም ነገር ውሸት ሊሆን ወይም ሊከሽፍ የሚችልበት ምንም መንገድ የለም። የአምላክ ሕዝቦች አምላክን ስለሚያምኑት እሱ በተናገረው ነገር መተማመን ይችላሉ።” w23.01 2 አን. 1-2

ሐሙስ፣ ነሐሴ 15

አንዳችን ለሌላው ትኩረት እንስጥ።—ዕብ. 10:24

ወንድሞቻችንና እህቶቻችን በይሖዋ ላይ ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩ በመርዳት እነሱን ማነጽ እንችላለን። አንዳንዶች ከማያምኑ ሰዎች ፌዝ ይደርስባቸዋል። ሌሎች ከከባድ የጤና እክል ጋር ይታገላሉ፤ የስሜት መጎዳት ያጋጠማቸውም አሉ። ሌሎች ደግሞ የዚህን ሥርዓት መጨረሻ ለረጅም ዘመን ሲጠብቁ ቆይተዋል። እነዚህ ሁኔታዎች በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖችን እምነት ሊፈትኑ ይችላሉ። በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበረው የክርስቲያን ጉባኤ አባላትም ተመሳሳይ ፈተናዎች አጋጥመዋቸዋል። ሐዋርያው ጳውሎስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ተጠቅሞ የወንድሞቹንና የእህቶቹን እምነት አጠናክሯል። ለምሳሌ ያህል፣ አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የማያምኑ ቤተሰቦቻቸው የአይሁድ እምነት ከክርስትና እምነት የተሻለ እንደሆነ በመግለጽ ይተቿቸው ይሆናል፤ ምን ብለው እንደሚመልሱላቸውም ግራ ሊገባቸው ይችላል። ጳውሎስ ለዕብራውያን የጻፈላቸው ደብዳቤ እነዚህን ክርስቲያኖች አበረታቷቸው እንደሚሆን ምንም ጥያቄ የለውም። (ዕብ. 1:5, 6፤ 2:2, 3፤ 9:24, 25) ጳውሎስ የተጠቀመባቸውን ጠንካራ የመከራከሪያ ነጥቦች በመጠቀም የተቃዋሚዎቻቸውን አፍ ማዘጋት ይችላሉ። w22.08 23-24 አን. 12-14

ዓርብ፣ ነሐሴ 16

በይሖዋ የሚታመን . . . ሰው የተባረከ ነው።—ኤር. 17:7

በሰይጣን ዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች ማንን ማመን እንደሚችሉ ግራ ይገባቸዋል። በንግዱ ዓለም ውስጥ ያሉ ሰዎች፣ ፖለቲከኞች እንዲሁም የሃይማኖት መሪዎች በሚያደርጉት ነገር ብዙ ጊዜ ቅር ይሰኛሉ። እንዲያውም ብዙዎች ጓደኞቻቸውን፣ ጎረቤቶቻቸውን አልፎ ተርፎም የቤተሰባቸውን አባላት ማመን እንደማይችሉ ይሰማቸዋል። እርግጥ ይህ መሆኑ አያስገርመንም። መጽሐፍ ቅዱስ ‘በመጨረሻዎቹ ቀናት ሰዎች ታማኝ ያልሆኑ፣ ስም አጥፊዎችና ከዳተኞች’ እንደሚሆኑ ይናገራል። በሌላ አባባል፣ ሰዎች የዚህ ዓለም አምላክ የሆነውን የሰይጣንን ባሕርይ ያንጸባርቃሉ፤ ሰይጣን ደግሞ ጨርሶ እምነት የሚጣልበት አይደለም። (2 ጢሞ. 3:1-4፤ 2 ቆሮ. 4:4) እኛ ክርስቲያኖች ግን በይሖዋ ላይ ሙሉ በሙሉ መተማመን እንደምንችል እናውቃለን። እሱ እንደሚወደንና ወዳጆቹን ‘ፈጽሞ እንደማይተዋቸው’ እርግጠኞች ነን። (መዝ. 9:10) ክርስቶስ ኢየሱስንም ማመን እንችላለን፤ ምክንያቱም ለእኛ ሲል ሕይወቱን ሰጥቷል። (1 ጴጥ. 3:18) በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ አስተማማኝ መመሪያ እንደያዘ በሕይወታችን ተመልክተናል።—2 ጢሞ. 3:16, 17፤ w22.09 2 አን. 1-2

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 17

ይሖዋን የሚፈሩ፣ በመንገዱም የሚሄዱ ሁሉ ደስተኞች ናቸው።—መዝ. 128:1

እውነተኛ ደስታ የሚያመለክተው ጊዜያዊ የሆነን የደስታ ስሜት ብቻ አይደለም። በመላው ሕይወታችን እውነተኛ ደስታ ማግኘት እንችላለን። እንዴት? ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “ለመንፈሳዊ ፍላጎታቸው ንቁ የሆኑ ደስተኞች ናቸው” ብሏል። (ማቴ. 5:3 ግርጌ) ኢየሱስ ሰዎች ሲፈጠሩ ጀምሮ ፈጣሪያቸውን ይሖዋ አምላክን የማወቅና የማምለክ ልባዊ ፍላጎት እንዳላቸው ያውቃል። ‘መንፈሳዊ ፍላጎት’ ማለት ይህ ነው። ደግሞም ይሖዋ ‘ደስተኛ አምላክ’ ስለሆነ እሱን የሚያመልኩ ሰዎችም ደስተኛ መሆን ይችላሉ። (1 ጢሞ. 1:11) ደስተኛ መሆን የምንችለው ሕይወታችን አልጋ በአልጋ ከሆነልን ብቻ ነው? አይደለም። ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይ “የሚያዝኑ” እንኳ ደስተኞች ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግሯል። ኢየሱስ “ለጽድቅ ሲሉ ስደት የሚደርስባቸው” ሰዎችም ደስተኞች እንደሆኑ ተናግሯል። (ማቴ. 5:4, 10, 11) ኢየሱስ ደስታ የሚያስገኝልን የተመቻቸ ሕይወት መምራታችን ሳይሆን መንፈሳዊ ፍላጎታችንን ማሟላታችንና ወደ አምላክ መቅረባችን መሆኑን ሊያስተምረን ፈልጓል።—ያዕ. 4:8፤ w22.10 6 አን. 1-3

እሁድ፣ ነሐሴ 18

ጥልቅ ግንዛቤ ያለው ሰው . . . ዝም ይላል።—ምሳሌ 11:12

ማስተዋል አንድ ክርስቲያን ‘መቼ ዝም ማለት፣ መቼ ደግሞ መናገር’ እንዳለበት ለይቶ እንዲያውቅ ይረዳዋል። (መክ. 3:7) “ዝምታ ወርቅ ነው፤ መናገር ብር ነው” ሲባል እንሰማለን። ይህም ሲባል ከመናገር ይልቅ ዝም ማለት የሚሻልበት ጊዜ አለ ማለት ነው። አንድ ምሳሌ እንመልከት። ተሞክሮ ያለው አንድ ሽማግሌ፣ ሌሎች ጉባኤዎች ውስብስብ ችግሮች ሲያጋጥሟቸው እንዲረዳ ብዙ ጊዜ ይጠየቃል። አብሮት የሚያገለግል አንድ ሽማግሌ ስለዚህ ወንድም ሲናገር “ስለ ሌሎች ጉባኤዎች ሚስጥራዊ መረጃ ላለማውጣት ሁሌም ይጠነቀቃል” ብሏል። ይህ ወንድም አስተዋይ መሆኑ በጉባኤው ውስጥ አብረውት የሚያገለግሉትን ሽማግሌዎች አክብሮት እንዲያተርፍ ረድቶታል። እነዚህ ወንድሞች የእነሱን ሚስጥራዊ መረጃ ለሌሎች እንደማይናገርባቸው እርግጠኞች ናቸው። እምነት የሚጣልብን ለመሆን የሚረዳን ሌላው ባሕርይ ሐቀኝነት ነው። ሐቀኛ ሰው ሁልጊዜ እውነቱን እንደሚናገር ስለምናውቅ እናምነዋለን።—ኤፌ. 4:25፤ ዕብ. 13:18፤ w22.09 12 አን. 14-15

ሰኞ፣ ነሐሴ 19

ይሖዋን የሚጻረር ጥበብ፣ ማስተዋልም ሆነ ምክር ከንቱ ነው።—ምሳሌ 21:30

እውነተኛ ጥበብ ‘መንገድ ላይ ስትጮኽ’ ብዙዎች ጥሪዋን ለመስማት አሻፈረኝ ይላሉ። (ምሳሌ 1:20) መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ጥበብን የሚቃወሙ ሦስት ዓይነት ሰዎች አሉ፤ እነሱም “አላዋቂዎች፣” “ፌዘኞች” እና “ሞኞች” ናቸው። (ምሳሌ 1:22-25) “አላዋቂዎች” ወይም ተሞክሮ የሌላቸው ሰዎች ተላላ፣ የሰሙትን ሁሉ የሚያምኑ እንዲሁም በቀላሉ የሚታለሉ ናቸው። (ምሳሌ 14:15 ግርጌ) ለምሳሌ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎች በሃይማኖታዊ ወይም በፖለቲካዊ መሪዎች እየተታለሉ ነው። አንዳንዶች በእነዚህ መሪዎች ሲታለሉ መኖራቸውን ሲያውቁ በጣም ይደነግጣሉ። በምሳሌ 1:22 ላይ የተጠቀሱት ሰዎች ግን ወደውና ፈቅደው አላዋቂዎች ለመሆን ይመርጣሉ። (ኤር. 5:31) መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል መማር ወይም በመሥፈርቶቹ መመራት አይፈልጉም። ሆን ብለው በአላዋቂነት የሚቀጥሉ ሰዎችን መምሰል እንደማንፈልግ ምንም ጥያቄ የለውም!—ምሳሌ 1:32፤ 27:12፤ w22.10 19 አን. 5-7

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 20

ለሰብዓዊ ሥልጣን ሁሉ ተገዙ።—1 ጴጥ. 2:13

የአምላክ ድርጅት ጉዳት እንዳያገኘን የሚረዳ መመሪያ ይሰጠናል። ሽማግሌዎች አደጋ በሚደርስበት ጊዜ እንዲያገኙን ወቅታዊ አድራሻችንን እንድንሰጣቸው በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ይሰጠናል። ከዚህም ሌላ ቤታችን ከመቆየት፣ አካባቢውን ለቆ ከመሄድ እንዲሁም የእርዳታ ቁሳቁሶችን ከማግኘት ጋር የተያያዘ መመሪያ ሊሰጠን ይችላል። ሌሎችን መርዳት የምንችለው እንዴትና መቼ እንደሆነም ይነገረናል። መመሪያውን ሳንታዘዝ ከቀረን የእኛንም ሆነ ‘ተግተው የሚጠብቁንን’ ሽማግሌዎች ሕይወት አደጋ ላይ ልንጥል እንችላለን። (ዕብ. 13:17) በተፈጥሮ አደጋ ወይም በሕዝባዊ ዓመፅ ምክንያት ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ በርካታ ወንድሞችና እህቶች ከአዲሱ ሁኔታቸው ጋር ለመላመድ ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤ በተጨማሪም ወዲያውኑ በቲኦክራሲያዊ እንቅስቃሴዎች መካፈላቸውን ቀጥለዋል። በደረሰባቸው ስደት ምክንያት ወደተለያየ አካባቢ እንደተበተኑት የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች ሁሉ እነሱም ‘የአምላክን ቃል ምሥራች መስበካቸውን’ ቀጥለዋል። (ሥራ 8:4) እንዲህ ማድረጋቸው፣ ባሉበት አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ሳይሆን በመንግሥቱ ላይ እንዲያተኩሩ ረድቷቸዋል። በዚህም የተነሳ ደስታቸውንና ሰላማቸውን መጠበቅ ችለዋል። w22.12 19 አን. 12-13

ረቡዕ፣ ነሐሴ 21

ይሖዋ ከጎኔ ነው፤ አልፈራም።—መዝ. 118:6

ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ከፍ አድርጎ ይመለከተናል። ኢየሱስ ሐዋርያቱን ለስብከት ከመላኩ በፊት ተቃውሞን እንዳይፈሩ አዘጋጅቷቸዋል። (ማቴ. 10:29-31) እንዲህ ያደረገው በእስራኤል ውስጥ ካሉ በጣም የተለመዱ ወፎች መካከል አንዷ የሆነችውን ድንቢጥን እንደ ምሳሌ በመጠቀም ነው። ድንቢጦች በኢየሱስ ዘመን በጣም አነስተኛ ዋጋ ያላቸው ወፎች ነበሩ። ሆኖም ኢየሱስ “ከእነሱ አንዷም እንኳ አባታችሁ ሳያውቅ መሬት ላይ አትወድቅም” በማለት ለደቀ መዛሙርቱ ነግሯቸዋል። አክሎም “እናንተ ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ” ብሏቸዋል። በዚህ መንገድ ኢየሱስ፣ ይሖዋ እያንዳንዳቸውን በግለሰብ ደረጃ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታቸው ለደቀ መዛሙርቱ አረጋግጦላቸዋል፤ ስለዚህ ስደትን የሚፈሩበት ምንም ምክንያት የለም። ደቀ መዛሙርቱ በከተማዎችና በመንደሮች ውስጥ እየሰበኩ ባሉበት ወቅት ድንቢጦችን ሲያዩ ኢየሱስ የነገራቸውን ነገር አስታውሰው መሆን አለበት። ትናንሽ ወፎችን ስትመለከቱ ይሖዋ በግለሰብ ደረጃ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከታችሁ አስታውሱ፤ ምክንያቱም እናንተም “ከብዙ ድንቢጦች የላቀ ዋጋ አላችሁ።” በይሖዋ እርዳታ ተቃውሞን በድፍረት መጋፈጥ ትችላላችሁ። w23.03 18 አን. 12

ሐሙስ፣ ነሐሴ 22

በፈርዖንና በአገልጋዮቹ ፊት እንድንጠላ [አደረጋችሁን]፤ እንዲገድሉን በእጃቸው ሰይፍ [ሰጣችኋቸው]።—ዘፀ. 5:21

አንዳንድ ጊዜ እንደ ቤተሰብ ተቃውሞ ወይም ሥራ ማጣት ያሉ ችግሮች ያጋጥሙናል። ረዘም ላለ ጊዜ ችግሮች ሲያጋጥሙን ቅስማችን ሊሰበርና ተስፋ ልንቆርጥ እንችላለን። ሰይጣን ደግሞ እንዲህ ያሉ አጋጣሚዎችን ተጠቅሞ ይሖዋ የሚወደን መሆኑን እንድንጠራጠር ለማድረግ ይሞክራል። ዲያብሎስ ለሚደርስብን ችግር ተጠያቂው ይሖዋ ወይም ድርጅቱ እንደሆነ እንድናስብ ይፈልጋል። በግብፅ የነበሩት አንዳንድ እስራኤላውያንም እንዲህ ያለ ሁኔታ አጋጥሟቸው ነበር። መጀመሪያ ላይ፣ ይሖዋ እነሱን ከባርነት ለማውጣት ሙሴንና አሮንን እንደሾመላቸው አምነው ነበር። (ዘፀ. 4:29-31) በኋላ ግን ፈርዖን ሕይወታቸውን ከባድ ሲያደርግባቸው፣ ላጋጠማቸው ችግር ሙሴንና አሮንን ተጠያቂ አደረጉ። (ዘፀ. 5:19, 20) የአምላክን ታማኝ አገልጋዮች ወቀሱ። እንዴት ያሳዝናል! እናንተም ለረጅም ጊዜ የዘለቀ ችግር ከደረሰባችሁ በጸሎት ልባችሁን ለይሖዋ አፍስሱ፤ እንዲሁም እርዳታውን ፈልጉ። w22.11 15 አን. 5-6

ዓርብ፣ ነሐሴ 23

እውነት እውነት እላችኋለሁ፣ ሙታን የአምላክን ልጅ ድምፅ የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ ያም ሰዓት አሁን ነው፤ የሚሰሙትም በሕይወት ይኖራሉ።—ዮሐ. 5:25

የሕይወት ምንጭ የሆነው ይሖዋ ሰዎችን ከሞት የማስነሳት ኃይል አለው። ነቢዩ ኤልያስ የሰራፕታዋን መበለት ልጅ ከሞት እንዲያስነሳ ኃይል ሰጥቶታል። (1 ነገ. 17:21-23) ከጊዜ በኋላም ነቢዩ ኤልሳዕ በአምላክ እርዳታ የሱናማዊቷን ልጅ ከሞት አስነስቶታል። (2 ነገ. 4:18-20, 34-37) እነዚህና ሌሎች ትንሣኤዎች፣ ይሖዋ ሰዎችን ከሞት የማስነሳት ኃይል እንዳለው ያረጋግጣሉ። ኢየሱስ ምድር ላይ በነበረበት ወቅት አባቱ እንዲህ ያለ ኃይል እንደሰጠው አሳይቷል። (ዮሐ. 11:23-25, 43, 44) አሁን ኢየሱስ በሰማይ ላይ ሲሆን “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር” ተሰጥቶታል። በመሆኑም “በመታሰቢያ መቃብር ያሉ ሁሉ” እንደሚነሱና ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ እንደሚያገኙ የገባውን ቃል ለመፈጸም የሚያስችል ሥልጣን አለው።—ማቴ. 28:18፤ ዮሐ. 5:26-29፤ w22.12 5 አን. 10

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 24

የእስራኤል ቤት ግን ሊሰሙህ አይፈልጉም፤ እኔን መስማት አይፈልጉምና።—ሕዝ. 3:7

ሕዝቡ ሕዝቅኤልን ባለመቀበል ይሖዋን እንደማይቀበሉ አሳይተዋል። በዛሬው የዕለት ጥቅስ ላይ ይሖዋ የተናገረው ሐሳብ፣ ሕዝቡ ሕዝቅኤልን አለመቀበላቸው ሕዝቅኤል የነቢይነት ተልእኮውን በአግባቡ እንዳልተወጣ የሚያሳይ እንዳልሆነ አረጋግጦለታል። ከዚህም ሌላ ሕዝቅኤል የተናገረው የፍርድ መልእክት ሲፈጸም ሕዝቡ “በመካከላቸው ነቢይ እንደነበረ በእርግጥ [እንደሚያውቁ]” ይሖዋ ለሕዝቅኤል ገልጾለታል። (ሕዝ. 2:5፤ 33:33) እነዚህ አጽናኝ ሐሳቦች፣ ሕዝቅኤል አገልግሎቱን ለመፈጸም የሚያስፈልገውን ብርታት እንደሰጡት ምንም ጥርጥር የለውም። እኛም ይሖዋ እንደላከን ማወቃችን ብርታት ይሰጠናል። ይሖዋ “ምሥክሮቼ” ብሎ በመጥራት አክብሮናል። (ኢሳ. 43:10) ይህ እንዴት ያለ ታላቅ መብት ነው! ይሖዋ ሕዝቅኤልን “አትፍራ” እንዳለው ሁሉ እኛንም “ስጋት አይደርባችሁ” ብሎናል። (ሕዝ. 2:6) ተቃዋሚዎቻችንን ልንፈራ የማይገባው ለምንድን ነው? እንደ ሕዝቅኤል ሁሉ እኛንም የላከን ይሖዋ ነው፤ ደግሞም እሱ ይደግፈናል።—ኢሳ. 44:8፤ w22.11 3-4 አን. 4-5

እሁድ፣ ነሐሴ 25

እምነት የሚጣልበት ሰው . . . ሚስጥር ይጠብቃል።—ምሳሌ 11:13

በዛሬው ጊዜ እምነት የሚጣልባቸው ሽማግሌዎችና የጉባኤ አገልጋዮች ስላሉን በጣም አመስጋኞች ነን። እነዚህ ታማኝ ወንድሞች በደንብ ይንከባከቡናል። እነሱን ስለሰጠን ይሖዋን እናመሰግነዋለን! ይሁንና እምነት የሚጣልብን መሆናችንን ማስመሥከር የምንችለው በየትኞቹ መንገዶች ነው? ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን እንወዳቸዋለን፤ ያሉበት ሁኔታም ያሳስበናል። ሆኖም ሚዛናዊ መሆንና በግል ጉዳያቸው ላለመግባት መጠንቀቅ ይኖርብናል። በመጀመሪያው መቶ ዘመን በክርስቲያን ጉባኤ ውስጥ የነበሩ አንዳንዶች “ማውራት ስለማይገባቸው ነገሮች እያወሩ ሐሜተኞችና በሌሎች ሰዎች ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡ” ነበሩ። (1 ጢሞ. 5:13) እንደ እነሱ መሆን እንደማንፈልግ የታወቀ ነው። ይሁንና አንድ ሰው ሌሎች እንዲያውቁት የማይፈልገውን የግል ጉዳዩን ነገረን እንበል። ለምሳሌ አንዲት እህት ስላጋጠማት የጤና እክል ወይም ስለደረሰባት አንድ ፈተና ከነገረችን በኋላ ጉዳዩን በሚስጥር እንድንይዘው ትጠይቀን ይሆናል። በዚህ ጊዜ ሚስጥሯን ልንጠብቅላት ይገባል። w22.09 10 አን. 7-8

ሰኞ፣ ነሐሴ 26

አእምሯችሁን በማደስ ተለወጡ።—ሮም 12:2

አንድን ቤት ማደስ ሲባል በቤቱ ውስጥ አንዳንድ ጌጣጌጦችን ማስቀመጥ ማለት አይደለም። በተመሳሳይም ‘አእምሯችንን ማደስ’ ማለት ጥቂት መልካም ነገሮችን በመሥራት ሕይወታችንን ማስጌጥ ማለት አይደለም። ከዚህ ይልቅ ውስጣዊ ማንነታችንን በጥልቀት መመርመር እንዲሁም የይሖዋን መሥፈርቶች በተቻለ መጠን በጥብቅ ለመከተል አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ይኖርብናል። ይህን ማድረግ ያለብን አንዴ ብቻ ሳይሆን በቀጣይነት ነው። ፍጹማን ስንሆን በምናደርገው ነገር ሁሉ ምንጊዜም ይሖዋን ማስደሰት እንችላለን። እስከዚያው ድረስ ግን ይሖዋን ለማስደሰት ከፍተኛ ጥረት ማድረግ ያስፈልገናል። በሮም 12:2 ላይ ጳውሎስ፣ አእምሯችንን በማደስና የአምላክን ፈቃድ መርምሮ በማረጋገጥ መካከል ያለውን ግንኙነት እንዴት እንደገለጸው ልብ በል። እጃችንን አጣጥፈን ይህ ሥርዓት እንዲቀርጸን ከመፍቀድ ይልቅ እንደሚከተለው እያልን ራሳችንን መመርመር ይኖርብናል፦ ‘ከዓለም አስተሳሰብ ይልቅ የአምላክ አስተሳሰብ በግቦቼና በውሳኔዎቼ ላይ ተጽዕኖ እንዲያደርግ እየፈቀድኩ ነው?’ w23.01 8-9 አን. 3-4

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 27

ሸክምህን በይሖዋ ላይ ጣል፤ እሱም ይደግፍሃል። ጻድቁ እንዲወድቅ ፈጽሞ አይፈቅድም።—መዝ. 55:22

ይሖዋ በሕይወታችን በሚያጋጥሙን ነገሮች ሁሉ ላይ ጣልቃ ይገባል? የሚያጋጥመንን እያንዳንዱን ነገር በመቆጣጠር፣ የሚደርሱብን ነገሮች ሁሉ ለበጎ እንዲሆኑ ያደርጋል? መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ብሎ አያስተምርም። (መክ. 8:9፤ 9:11) ሆኖም የምናውቀው አንድ ነገር አለ፦ ፈተና ሲያጋጥመን ይሖዋ ሁኔታችንን ይረዳልናል፤ እንዲሁም እርዳታ ለማግኘት የምናሰማውን ጩኸት ያዳምጣል። (መዝ. 34:15፤ ኢሳ. 59:1) ይህ ብቻ ሳይሆን፣ ይሖዋ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በተሳካ ሁኔታ እንድንወጣ ይረዳናል። እንዴት? ይሖዋ እኛን የሚረዳበት አንዱ መንገድ ማጽናኛና ማበረታቻ በመስጠት ነው፤ በአብዛኛው ይህን የሚያደርገው ልክ በሚያስፈልገን ጊዜ ነው። (2 ቆሮ. 1:3, 4) ይሖዋ ልክ በሚያስፈልግህ ወቅት ማጽናኛና ማበረታቻ በመስጠት የረዳህን ጊዜ ታስታውሳለህ? ብዙውን ጊዜ፣ ይሖዋ አንድን ችግር ለመቋቋም እንዴት እንደረዳን የምናስተውለው ችግሩ ካለፈ በኋላ ነው። w23.01 17-18 አን. 13-15

ረቡዕ፣ ነሐሴ 28

ከዚህ በፊት የነበረው፣ አሁን ግን የሌለው አውሬ . . . ወደ ጥፋት ይሄዳል።—ራእይ 17:11

ይህ አውሬ ሰባት ራሶች ካሉት አውሬ ጋር በጣም ይመሳሰላል፤ የሚለየው በደማቅ ቀይ ቀለሙ ብቻ ነው። “የአውሬው ምስል” ተብሎ የተጠራ ሲሆን “ስምንተኛ ንጉሥ” ተብሏል። (ራእይ 13:14, 15፤ 17:3, 8) ይህ “ንጉሥ” ቀደም ሲል በሕይወት እንደነበረ፣ በኋላ ላይ ከሕልውና ውጭ እንደሚሆን ከዚያም ዳግም ሕያው እንደሚሆን ተገልጿል። ይህ መግለጫ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን በሚገባ ይገልጸዋል። ይህ ድርጅት በዓለም ዙሪያ ያሉ መንግሥታትን ፍላጎት እንደሚያራምድ ይታወቃል። ድርጅቱ መጀመሪያ የተቋቋመው የመንግሥታት ቃል ኪዳን ማኅበር ተብሎ ነው። በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከሕልውና ውጭ ሆነ። በኋላ ላይ ደግሞ ዛሬ ያለውን መልክ ይዞ ብቅ አለ። አራዊቱ ፕሮፓጋንዳ በመንዛት በይሖዋና በሕዝቡ ላይ ተቃውሞ ይቀሰቅሳሉ። በምሳሌያዊ ሁኔታ ‘የዓለምን ነገሥታት ሁሉ’ ወደ አርማጌዶን ጦርነት ይሰበስቧቸዋል፤ ይህ ጦርነት “ሁሉን ቻይ [የሆነው] አምላክ ታላቅ ቀን” ነው።—ራእይ 16:13, 14, 16፤ w22.05 10 አን. 10-11

ሐሙስ፣ ነሐሴ 29

ምን ትረዳለህ?—ሉቃስ 10:26

ኢየሱስ ቅዱሳን መጻሕፍትን ራሱ ማንበብ ሲችል ቅዱሳን መጻሕፍትን ከማወቅ ባለፈ ሊወዳቸውና ሕይወቱን በእነሱ መሠረት ሊመራ ችሏል። ለምሳሌ ኢየሱስ ገና የ12 ዓመት ልጅ ሳለ በቤተ መቅደሱ የተከናወነውን ነገር ማስታወስ እንችላለን። የሙሴን ሕግ ጠንቅቀው ያውቁ የነበሩት መምህራን በኢየሱስ ‘የመረዳት ችሎታና በመልሱ ተደንቀው’ ነበር። (ሉቃስ 2:46, 47, 52) እኛም ቅዱሳን መጻሕፍትን አዘውትረን የምናነብ ከሆነ የአምላክን ቃል ልናውቀውና ልንወደው እንችላለን። በዚህ ረገድ ኢየሱስ ጸሐፍትን፣ ፈሪሳውያንንና ሰዱቃውያንን ጨምሮ ሕጉን ያውቁ ለነበሩት ሰዎች ከተናገረው ነገር ትምህርት ማግኘት እንችላለን። እነዚህ የሃይማኖት መሪዎች ቅዱሳን መጻሕፍትን ደጋግመው ያነቡ ነበር፤ ሆኖም ከሚያነቡት ነገር ጥቅም ማግኘት አልቻሉም። ኢየሱስ እነዚህ ሰዎች ከቅዱሳን መጻሕፍት ጥቅም ማግኘት ከፈለጉ ሊያደርጓቸው የሚገቡ ሦስት ነገሮችን ጠቁሟል። ለእነሱ የተናገረው ሐሳብ (1) የምናነበውን ነገር በመረዳት፣ (2) ውድ የሆኑ መንፈሳዊ እውነቶችን በማግኘት እንዲሁም (3) የአምላክ ቃል እንዲቀርጸን በመፍቀድ ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንድንችል ይረዳናል። w23.02 8-9 አን. 2-3

ዓርብ፣ ነሐሴ 30

ብልህ ሰው አደጋ ሲያይ ይሸሸጋል።—ምሳሌ 22:3

ልንርቃቸው ከሚገቡ አደጋዎች መካከል ማሽኮርመም፣ ከልክ በላይ መብላትና መጠጣት እንዲሁም ጎጂ ንግግር ይገኙበታል፤ ዓመፅ የሚንጸባረቅባቸውን መዝናኛዎች፣ የብልግና ምስሎችንና የመሳሰሉትን ማየትም በዚህ ውስጥ ይካተታል። (መዝ. 101:3) ዲያብሎስ ከይሖዋ ጋር ያለንን ዝምድና ለማበላሸት የሚያስችሉትን አጋጣሚዎች በንቃት ይከታተላል። (1 ጴጥ. 5:8) ንቁ ካልሆንን ሰይጣን በአእምሯችንና በልባችን ውስጥ የምቀኝነት፣ የውሸት፣ የስግብግብነት፣ የጥላቻ፣ የኩራትና የምሬት ዘር ሊዘራ ይችላል። (ገላ. 5:19-21) ከሥራቸው ነቅለን ለመጣል አፋጣኝ እርምጃ ካልወሰድን እንደ መርዛማ ተክል ማደጋቸውን ሊቀጥሉና ችግር ላይ ሊጥሉን ይችላሉ። (ያዕ. 1:14, 15) ስውር ከሆኑት አደጋዎች መካከል አንዱ መጥፎ ባልንጀርነት ነው። አብረናቸው ጊዜ የምናሳልፋቸው ሰዎች ትልቅ ተጽዕኖ ሊያሳድሩብን እንደሚችሉ መዘንጋት አይኖርብንም። (1 ቆሮ. 15:33) ለራሳችን የምንጠነቀቅ ወይም ትኩረት የምንሰጥ ከሆነ በይሖዋ መሥፈርቶች ከማይመሩ ሰዎች ጋር አላስፈላጊ ቅርርብ ከመፍጠር እንርቃለን። (ሉቃስ 21:34፤ 2 ቆሮ. 6:15) አደጋውን አስቀድመን አይተን ከዚያ እንሸሻለን። w23.02 16 አን. 7፤ 17 አን. 10-11

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 31

አምላክን መውደድ ማለት ትእዛዛቱን መጠበቅ ማለት ነው።—1 ዮሐ. 5:3

ስለ ይሖዋ ይበልጥ እያወቅክ ስትሄድ ለእሱ ያለህ ፍቅርም ይበልጥ እየጨመረ እንደሄደ ግልጽ ነው። አሁንም ሆነ ለዘላለም ወደ እሱ ይበልጥ መቅረብ እንደምትፈልግ ጥርጥር የለውም። ደግሞም ትችላለህ። ይሖዋ ልቡን ደስ እንድታሰኘው በደግነት ግብዣ አቅርቦልሃል። (ምሳሌ 23:15, 16) ይህን ማድረግ የምትችለው በቃል ብቻ ሳይሆን በድርጊት ጭምር ነው። ይሖዋን ከልብህ እንደምትወደው በሚያሳይ መንገድ ሕይወትህን መምራት ትችላለህ። በሕይወትህ ውስጥ ልታወጣ የምትችለው ከሁሉ የተሻለ ግብ ይህ ነው። ለይሖዋ ያለህን ፍቅር ማሳየት የምትችለው እንዴት ነው? በቅድሚያ ልባዊ ጸሎት በማቅረብ ራስህን ብቸኛው እውነተኛ አምላክ ለሆነው ለይሖዋ ትወስናለህ። (መዝ. 40:8) ከዚያም በሰዎች ፊት በመጠመቅ በግልህ ያደረግከውን ውሳኔ ይፋ ታደርጋለህ። ይህ በሕይወትህ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ የሚከፍት አስደሳች እርምጃ ይሆናል። ለራስህ ሳይሆን ለይሖዋ የምትኖረውን አዲስ ሕይወት ትጀምራለህ። (ሮም 14:8፤ 1 ጴጥ. 4:1, 2) ይህ በጣም ከባድ እርምጃ ሊመስል ይችላል፤ ደግሞም ነው። ሆኖም ከሁሉ የተሻለ ሕይወት መምራት የምትችልበትን አጋጣሚ ይከፍትልሃል። w23.03 5-6 አን. 14-15

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ