የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • es24 ገጽ 88-98
  • መስከረም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • መስከረም
  • ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2024
  • ንዑስ ርዕሶች
  • እሁድ፣ መስከረም 1
  • ሰኞ፣ መስከረም 2
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 3
  • ረቡዕ፣ መስከረም 4
  • ሐሙስ፣ መስከረም 5
  • ዓርብ፣ መስከረም 6
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 7
  • እሁድ፣ መስከረም 8
  • ሰኞ፣ መስከረም 9
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 10
  • ረቡዕ፣ መስከረም 11
  • ሐሙስ፣ መስከረም 12
  • ዓርብ፣ መስከረም 13
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 14
  • እሁድ፣ መስከረም 15
  • ሰኞ፣ መስከረም 16
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 17
  • ረቡዕ፣ መስከረም 18
  • ሐሙስ፣ መስከረም 19
  • ዓርብ፣ መስከረም 20
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 21
  • እሁድ፣ መስከረም 22
  • ሰኞ፣ መስከረም 23
  • ማክሰኞ፣ መስከረም 24
  • ረቡዕ፣ መስከረም 25
  • ሐሙስ፣ መስከረም 26
  • ዓርብ፣ መስከረም 27
  • ቅዳሜ፣ መስከረም 28
  • እሁድ፣ መስከረም 29
  • ሰኞ፣ መስከረም 30
ቅዱሳን መጻሕፍትን በየዕለቱ መመርመር—2024
es24 ገጽ 88-98

መስከረም

እሁድ፣ መስከረም 1

አንድ ሰው አምላክን እያመለከ እንዳለ ቢያስብም እንኳ አንደበቱን የማይገታ ከሆነ ይህ ሰው የገዛ ልቡን ያታልላል፤ አምልኮውም ከንቱ ነው።—ያዕ. 1:26

አንደበታችንን በአግባቡ መጠቀማችን ሰዎች የይሖዋ አገልጋዮች መሆናችንን ለይተው እንዲያውቁ ይረዳቸዋል። እንዲህ ስናደርግ የሚያዩን ሰዎች “አምላክን በሚያገለግለውና በማያገለግለው ሰው መካከል ያለውን ልዩነት” በግልጽ ማስተዋል ይችላሉ። (ሚል. 3:18) ኪምበርሊ የተባለች እህት ያጋጠማት ነገር የዚህን እውነተኝነት ያረጋግጣል። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሳለች አብራት ከምትማር አንዲት ልጅ ጋር በአንድ ፕሮጀክት ላይ እንዲሠሩ ተመደቡ። ፕሮጀክቱን አብረው ሲሠሩ ኪምበርሊ ከሌሎቹ ተማሪዎች የተለየች እንደሆነች ልጅቷ አስተዋለች። ኪምበርሊ ሌሎችን አታማም፣ ሰዎችን የምታነጋግረው በደግነት ነው እንዲሁም አትሳደብም። ልጅቷ ይህ በጣም ስላስገረማት ከጊዜ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስ ለማጥናት ተስማማች። አነጋገራችን ሰዎችን ወደ እውነት የሚስብ ከሆነ ይሖዋ በጣም ይደሰታል! ሁላችንም አነጋገራችን ይሖዋን የሚያስከብርና ከወንድሞቻችን ጋር ጥሩ ግንኙነት እንዲኖረን የሚያደርግ እንዲሆን እንፈልጋለን። w22.04 5-6 አን. 5-7

ሰኞ፣ መስከረም 2

ብዙ ሴቶች . . . በንብረታቸው ያገለግሏቸው ነበር።—ሉቃስ 8:3

ኢየሱስ መግደላዊቷን ማርያምን ካደሩባት ሰባት አጋንንት ነፃ አውጥቷታል! አመስጋኝነቷ የኢየሱስ ተከታይ እንድትሆን እንዲሁም እሱን እንድታገለግል አነሳስቷታል። (ሉቃስ 8:1-3) ማርያም ኢየሱስ በግሏ ላደረገላት ነገር ጥልቅ አድናቆት እንደነበራት ግልጽ ነው፤ በኋላ ላይ ከዚህም እጅግ የላቀ ነገር እንደሚያደርግ ግን በወቅቱ አልተገነዘበች ይሆናል። “[በእሱ] የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው” ሲል ሕይወቱን ይሰጣል። (ዮሐ. 3:16) ማርያም ለኢየሱስ ታማኝ በመሆን አድናቆቷን አሳይታለች። ኢየሱስ በእንጨት ላይ ተሰቅሎ በነበረበት ወቅት ማርያም በቦታው ተገኝታለች። በዚህ መንገድ እሱን እንደምትደግፍ አሳይታለች፣ ሌሎቹንም አጽናንታለች። (ዮሐ. 19:25) ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ማርያምና ሌሎች ሁለት ሴቶች ቅመሞች ይዘው ወደ መቃብሩ ሄደው ነበር። (ማር. 16:1, 2) ማርያም ከሞት የተነሳውን ኢየሱስን ስታገኝና ስታነጋግር ምን ያህል ተደስታ ይሆን! ይህ አብዛኞቹ ደቀ መዛሙርት ያላገኙት መብት ነው።—ዮሐ. 20:11-18፤ w23.01 27 አን. 4

ማክሰኞ፣ መስከረም 3

ቀዝቃዛ ወይም ደግሞ ትኩስ ብትሆን ደስ ባለኝ ነበር።—ራእይ 3:15

ቀደም ሲል በይሖዋ አገልግሎት ባከናወንነው ነገር ብቻ ረክተን ልንቀመጥ አይገባም። እርግጥ ነው፣ አሁን የአቅም ገደቦች ይኖሩብን ይሆናል፤ ያም ቢሆን ‘በጌታ ሥራ’ በመጠመድ እስከ መጨረሻው ንቁ መሆን ያስፈልገናል። (1 ቆሮ. 15:58፤ ማቴ. 24:13፤ ማር. 13:33) አምልኳችንን በቅንዓትና በሙሉ ልብ ማከናወን አለብን። ኢየሱስ ለሎዶቅያ ጉባኤ በላከው መልእክት ላይ እነዚህ ክርስቲያኖች የነበረባቸውን የተለየ ችግር አንስቷል። ከአምልኳቸው ጋር በተያያዘ “ለብ” ያሉ ነበሩ። በግድ የለሽነታቸው የተነሳ ኢየሱስ “ጎስቋላ” እና “ምስኪን” እንደሆኑ ነግሯቸዋል። ለይሖዋና ለአምልኮው እንደ እሳት የሚነድ ቅንዓት ማሳየት ያስፈልጋቸው ነበር። (ራእይ 3:16, 17, 19) ይህ ለእኛ ምን ትምህርት ይዞልናል? ቅንዓታችን በተወሰነ መጠንም ቢሆን ቀዝቅዞ ከሆነ ለመንፈሳዊ ሀብታችን ያለንን አድናቆት ማቀጣጠል አለብን። (ራእይ 3:18) የተመቻቸ ሕይወት ለመምራት የምናደርገው ጥረት ትኩረታችንን እንዲከፋፍለው አንፍቀድ፤ ይህ አካሄድ ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎች ሁለተኛ ቦታ እንድንሰጥ ስለሚያደርገን ልንጠነቀቅ ይገባል። w22.05 3-4 አን. 7-8

ረቡዕ፣ መስከረም 4

ይሖዋንም ለሚፈሩ . . . በፊቱ የመታሰቢያ መጽሐፍ ተጻፈ።—ሚል. 3:16

በሺዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ይሖዋ አንድ ልዩ መጽሐፍ ሲጽፍ ቆይቷል። ይህ መጽሐፍ የስም ዝርዝር ይዟል። በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ስሙ የተጻፈው የመጀመሪያ ሰው፣ የመጀመሪያው ታማኝ ምሥክር የሆነው አቤል ነው። (ሉቃስ 11:50, 51) ከዚያ ጊዜ አንስቶ ይሖዋ በመጽሐፉ ውስጥ ተጨማሪ ስሞችን ሲያሰፍር ቆይቷል። በዛሬው ጊዜ ይህ መጽሐፍ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ስሞችን ይዟል። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ይህ መጽሐፍ “የመታሰቢያ መጽሐፍ፣” “የሕይወት መጽሐፍ” እንዲሁም “የሕይወት መጽሐፍ ጥቅልል” ተብሎ ተጠርቷል። በዚህ ርዕስ ውስጥ “የሕይወት መጽሐፍ” የሚለውን አጠራር እንጠቀማለን። (ሚል. 3:16፤ ራእይ 3:5፤ 17:8) ይህ ልዩ መጽሐፍ ይሖዋን በፍርሃት ወይም በጥልቅ አክብሮት የሚያመልኩ እንዲሁም ስሙን ከፍ አድርገው የሚመለከቱ ሰዎችን ስም በሙሉ ይዟል። እነዚህ ሰዎች የዘላለም ሕይወት የማግኘት አጋጣሚ አላቸው። በዛሬው ጊዜ በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛዊ መሥዋዕት አማካኝነት ከይሖዋ ጋር የቀረበ ዝምድና ከመሠረትን ስማችን በዚህ መጽሐፍ ላይ ሊጻፍ ይችላል። (ዮሐ. 3:16, 36) ተስፋችን ወደ ሰማይ መሄድም ይሁን በምድር ላይ መኖር ሁላችንም ስማችን በዚህ መጽሐፍ ውስጥ እንዲገኝ እንፈልጋለን። w22.09 14 አን. 1-2

ሐሙስ፣ መስከረም 5

ሲያሳስታቸው የነበረው ዲያብሎስ . . . ወደ እሳቱና ወደ ድኙ ሐይቅ ተወረወረ።—ራእይ 20:10

የራእይ መጽሐፍ “ደማቅ ቀይ ቀለም” ስላለው “ታላቅ ዘንዶ” ይናገራል። (ራእይ 12:3) ይህ ዘንዶ ከኢየሱስና ከመላእክቱ ጋር ይዋጋል። (ራእይ 12:7-9) በአምላክ ሕዝቦች ላይ ጥቃት ይሰነዝራል፤ እንዲሁም ለአራዊቱ ሥልጣን ይሰጣል። (ራእይ 12:17፤ 13:4) ይህ ዘንዶ ማን ነው? “ዲያብሎስና ሰይጣን ተብሎ የሚጠራው የጥንቱ እባብ” ነው። (ራእይ 12:9፤ 20:2) ሌሎቹን የይሖዋ ጠላቶች በሙሉ የሚቆጣጠራቸው እሱ ነው። ዘንዶው ምን ይደርስበታል? ራእይ 20:1-3 እንደሚገልጸው አንድ መልአክ ሰይጣንን ወደ ጥልቁ ይወረውረዋል፤ ይህም እንደ እስር ባለ ሁኔታ ውስጥ እንደሚሆን ያመለክታል። ሰይጣን በዚህ ሁኔታ ውስጥ በሚሆንበት ወቅት ለ1,000 ዓመት ‘ሕዝቦችን ማሳሳት’ አይችልም። በመጨረሻም ሰይጣንና አጋንንቱ “ወደ እሳቱና ወደ ድኙ ሐይቅ” ይጣላሉ፤ ወይም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይጠፋሉ። ሰይጣንና አጋንንቱ የሌሉበት ዓለም ምን ሊመስል እንደሚችል እስቲ አስበው። ያ ጊዜ እንዴት አስደናቂ ይሆናል! w22.05 14 አን. 19-20

ዓርብ፣ መስከረም 6

ለተቸገረ ሰው የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው በእጆቹ መልካም ተግባር እያከናወነ በትጋት ይሥራ።—ኤፌ. 4:28

ኢየሱስ ታታሪ ሠራተኛ ነበር። ወጣት እያለ በአናጺነት ሠርቷል። (ማር. 6:3) ያደገው ትልቅ ቤተሰብ ውስጥ እንደመሆኑ መጠን ኑሮን ለማሸነፍ ደፋ ቀና የሚሉት ወላጆቹ የእሱን ድጋፍ በማግኘታቸው አመስጋኝ እንደነበሩ ጥርጥር የለውም። ደግሞም ፍጹም ሰው ስለነበር የእሱ ምርቶች ተፈላጊ ቢሆኑ የሚያስገርም አይደለም። ኢየሱስ ሥራውን ይወደው እንደነበረም መገመት እንችላለን። ያም ቢሆን ኢየሱስ ከሥራው ጎን ለጎን ለመንፈሳዊ እንቅስቃሴዎችም ጊዜ ይመድብ ነበር። (ዮሐ. 7:15) በኋላም የሙሉ ጊዜ ሰባኪ በነበረበት ወቅት አድማጮቹን እንዲህ ሲል መክሯቸዋል፦ “ለሚጠፋ ምግብ ሳይሆን . . . ዘላቂ ለሆነውና የዘላለም ሕይወት ለሚያስገኘው ምግብ ሥሩ።” (ዮሐ. 6:27) ኢየሱስ በተራራ ስብከቱ ላይም “በሰማይ ለራሳችሁ ሀብት አከማቹ” ብሏል። (ማቴ. 6:20) አምላካዊ ጥበብ ለሥራችን ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን ይረዳናል። ክርስቲያኖች “መልካም ተግባር” እንድናከናውንና ‘በትጋት እንድንሠራ’ ተመክረናል። w22.05 22 አን. 9-10

ቅዳሜ፣ መስከረም 7

እናትህ ሐሴት [ታደርጋለች]።—ምሳሌ 23:25

ኤውንቄ ለጢሞቴዎስ ጥሩ ምሳሌ ሆናለታለች። ጢሞቴዎስ እናቱ ማንኛውንም ነገር የምታደርገው ለይሖዋ ባላት ጠንካራ ፍቅር ተነሳስታ እንደሆነና ይሖዋን ማገልገሏ ደስታ እንዳስገኘላት አስተውሎ መሆን አለበት። በተመሳሳይም በአሁኑ ጊዜ ብዙ እናቶች “ያለቃል” የቤተሰባቸውን አባሎች ልብ መንካት ችለዋል። (1 ጴጥ. 3:1, 2) እናንተም እንዲሁ ማድረግ ትችላላችሁ። እንዴት? ከይሖዋ ጋር ላላችሁ ዝምድና ቅድሚያ ስጡ። (ዘዳ. 6:5, 6) እንደ አብዛኞቹ እናቶች እናንተም ብዙ መሥዋዕት ትከፍላላችሁ። የልጆቻችሁን አካላዊ ፍላጎት ለማሟላት ጊዜያችሁን፣ ገንዘባችሁን፣ እንቅልፋችሁን እንዲሁም ሌሎች ነገሮችን መሥዋዕት ታደርጋላችሁ። ይሁንና ቤተሰባችሁን በመንከባከብ ከመጠመዳችሁ የተነሳ ከይሖዋ ጋር ያላችሁን ዝምድና መሥዋዕት እንዳታደርጉ መጠንቀቅ ይኖርባችኋል። ብቻችሁን ለመጸለይ፣ መጽሐፍ ቅዱስን በግላችሁ ለማጥናት እንዲሁም በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ ለመገኘት አዘውትራችሁ ጊዜ መድቡ። እንዲህ ካደረጋችሁ የራሳችሁን መንፈሳዊነት ታጠናክራላችሁ፤ እንዲሁም ለቤተሰባችሁ አልፎ ተርፎም ለሌሎች ጥሩ ምሳሌ ትሆናላችሁ። w22.04 16 አን. 1፤ 19 አን. 12-13

እሁድ፣ መስከረም 8

ክፉውን ጥፋተኛ በማለትና እንደ ሥራው በመመለስ፣ ጻድቁንም ንጹሕ መሆኑን በማሳወቅና እንደ ጽድቁ ወሮታውን በመክፈል እርምጃ ውሰድ።—1 ነገ. 8:32

ሰዎች ምን ዓይነት ፍርድ ሊፈረድባቸው እንደሚገባ መወሰን የእኛ ኃላፊነት አለመሆኑ ትልቅ እፎይታ ነው! ይህን ወሳኝ ሥራ ማከናወን የጽንፈ ዓለሙ ሉዓላዊ ዳኛ የሆነው የይሖዋ ኃላፊነት ነው። (ሮም 14:10-12) ይሖዋ ምንጊዜም ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ ካወጣው ፍጹም መሥፈርት ጋር የሚስማማ ፍርድ እንደሚያስተላልፍ መተማመን እንችላለን። (ዘፍ. 18:25) ይሖዋ መቼም ቢሆን ፍትሕ አያዛባም! ይሖዋ አለፍጽምና እና ኃጢአት ያስከተሏቸውን መጥፎ ውጤቶች በሙሉ የሚያስተካክልበትን ጊዜ በጉጉት እንጠባበቃለን። በዚያ ጊዜ ያሉብን አካላዊም ሆነ ስሜታዊ ቁስሎች በሙሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይሻራሉ። (መዝ. 72:12-14፤ ራእይ 21:3, 4) ጨርሶ አይታወሱም። ያ አስደሳች ጊዜ እስኪመጣ በምንጠባበቅበት ወቅት ይሖዋ በይቅር ባይነት ረገድ እሱን የመምሰል ችሎታ ስለሰጠን በጣም አመስጋኞች ነን። w22.06 13 አን. 18-19

ሰኞ፣ መስከረም 9

የምድር ሁሉ ዳኛ ትክክል የሆነውን ነገር አያደርግም?—ዘፍ. 18:25

አንድ ጥሩ ዳኛ ሕጉን ጠንቅቆ ማወቅ ይጠበቅበታል። ትክክልና ስህተት የሆነውን ነገር በተመለከተ ጥልቅ እውቀት ሊኖረው ይገባል። ከአንድ ጥሩ ዳኛ ሌላስ ምን ይጠበቃል? ብይን ከማስተላለፉ በፊት ከጉዳዩ ጋር የተያያዙ መረጃዎችን በሙሉ ከግምት ማስገባት አለበት። በዚህ ረገድ ይሖዋን የሚተካከለው ዳኛ የለም። ከሰብዓዊ ዳኞች በተለየ መልኩ ይሖዋ ከየትኛውም ጉዳይ ጋር በተያያዘ የተሟላ መረጃ አለው። (ዘፍ. 18:20, 21፤ መዝ. 90:8) የእሱ ፍርድ በዓይን በሚታየው ወይም በጆሮ በሚሰማው ነገር ብቻ የተገደበ አይደለም። አንድ ሰው በዘር የወረሰው ነገር፣ አስተዳደጉ፣ ማኅበረሰቡ እንዲሁም ስሜታዊና አእምሯዊ ጤንነቱ በድርጊቱ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድረው እንዴት እንደሆነ ሙሉ በሙሉ ይረዳል። ከዚህም በተጨማሪ ይሖዋ የሰዎችን ልብ ያነብባል። የእያንዳንዱን ሰው ውስጣዊ ግፊት፣ የልብ ዝንባሌና ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ይረዳል። ከይሖዋ ዓይን ሊሰወር የሚችል አንድም ነገር የለም። (ዕብ. 4:13) በመሆኑም ይሖዋ ይቅር የሚለው ከጉዳዩ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ነገሮች በሙሉ ስለሚያውቅ ነው። w22.06 4 አን. 8-9

ማክሰኞ፣ መስከረም 10

[ሰው] ለሕይወቱ ሲል ያለውን ነገር ሁሉ ይሰጣል።—ኢዮብ 2:4

ሰይጣን ኢዮብን ለማጥቃት የተጠቀመባቸውን ዘዴዎች ልብ ልንላቸው ይገባል። ምክንያቱም ሰይጣን በዛሬው ጊዜም እኛን ለማጥቃት ተመሳሳይ ዘዴዎችን ይጠቀማል። ሰይጣን፣ ይሖዋ አምላክን ከልባችን እንደማንወደው እንዲሁም ሕይወታችንን ለማትረፍ ስንል እሱን እንደምንተወው ተናግሯል። በተጨማሪም ሰይጣን፣ አምላክ እንደማይወደን እንዲሁም እሱን ለማስደሰት የምናደርገውን ጥረት ከቁብ እንደማይቆጥረው ገልጿል። ይሖዋን ተስፋ የሚያደርጉ ሰዎች የሰይጣንን መሠሪ ዘዴዎች ስለሚያውቁ በእሱ ውሸቶች አይታለሉም። የሚደርሱብንን መከራዎች ስለ ራሳችን ይበልጥ ለማወቅ እንደሚያስችሉ አጋጣሚዎች አድርገን ልንመለከታቸው ይገባል። ኢዮብ የደረሰበት መከራ ያለበትን ድክመት ለማወቅና ለማስተካከል አጋጣሚ ሰጥቶታል። ለምሳሌ ይበልጥ ትሕትና ማዳበር እንደሚያስፈልገው ተገንዝቧል። (ኢዮብ 42:3) እኛም መከራ ሲደርስብን ስለ ራሳችን ብዙ ነገር ማወቅ እንችላለን። ድክመቶቻችንን ለይተን ካወቅን በኋላ ደግሞ ለማስተካከል ጥረት ማድረግ እንችላለን። w22.06 23 አን. 13-14

ረቡዕ፣ መስከረም 11

“እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ” ይላል ይሖዋ፤ “አዎ፣ የመረጥኩት አገልጋዬ ናችሁ።”—ኢሳ. 43:10

ይሖዋ እንደሚደግፈን ቃል ገብቶልናል። ለምሳሌ “እናንተ ምሥክሮቼ ናችሁ” ከማለቱ በፊት እንዲህ ብሏል፦ “በውኃዎች መካከል ስታልፍ እኔ ከአንተ ጋር እሆናለሁ፤ በወንዞችም መካከል ስትሻገር አያሰምጡህም። በእሳት መካከል ስትሄድ አትቃጠልም፤ ነበልባሉም አይፈጅህም።” (ኢሳ. 43:2) አገልግሎታችንን ስናከናውን አንዳንድ ጊዜ እንደ ወንዝ ያሉ እንቅፋቶችና እንደ እሳት ያሉ ፈተናዎች ያጋጥሙናል። ያም ቢሆን በይሖዋ እርዳታ መስበካችንን እንቀጥላለን። (ኢሳ. 41:13) ዛሬ አብዛኞቹ ሰዎች መልእክታችንን አይቀበሉም። ሆኖም እነሱ መልእክቱን አለመቀበላቸው የስብከቱን ሥራ በአግባቡ እንዳላከናወንን የሚያሳይ እንዳልሆነ እንገነዘባለን። መልእክቱን በታማኝነት ማወጃችንን እስከቀጠልን ድረስ ይሖዋ እንደሚደሰት ማወቃችን ያጽናናናል እንዲሁም ያበረታታናል። ሐዋርያው ጳውሎስ “እያንዳንዱ ሰው እንደ ሥራው መጠን የራሱን ወሮታ ይቀበላል” ብሏል።—1 ቆሮ. 3:8፤ 4:1, 2፤ w22.11 4 አን. 5-6

ሐሙስ፣ መስከረም 12

በዓለም ባሉ ሰዎች መካከል መልካም ምግባር ይኑራችሁ።—1 ጴጥ. 2:12

ዛሬ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ሲፈጸሙ እየተመለከትን ነው። “ከብሔራት ቋንቋዎች ሁሉ የተውጣጡ” ሰዎች ‘ንጹሑን ቋንቋ’ ማለትም የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት እየተማሩ ነው። (ዘካ. 8:23፤ ሶፎ. 3:9) በ240 አገሮች የሚገኙ ከ8,000,000 የሚበልጡ ሰዎች በይሖዋ ድርጅት ውስጥ ታቅፈዋል፤ በየዓመቱ ደግሞ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ይጠመቃሉ! ከቁጥሩ ይበልጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ግን እነዚህ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት “አዲሱን ስብዕና” መልበሳቸው ማለትም ግሩም መንፈሳዊ ባሕርያትን ማዳበራቸው ነው። (ቆላ. 3:8-10) ብዙዎች የሥነ ምግባር ብልግናን፣ ዓመፅን፣ ጭፍን ጥላቻንና ብሔራዊ ስሜትን አስወግደዋል። በኢሳይያስ 2:4 ላይ የሚገኘው “ከእንግዲህ ወዲህ ጦርነት አይማሩም” የሚለው ትንቢት እየተፈጸመ ነው። አዲሱን ስብዕና ለመልበስ ጥረት ስናደርግ ሰዎች ወደ አምላክ ድርጅት እንዲሳቡ እናደርጋለን፤ እንዲሁም መሪያችንን ክርስቶስ ኢየሱስን እንደምንከተል እናሳያለን። (ዮሐ. 13:35) ይህ ሁሉ የሆነው በአጋጣሚ አይደለም። ኢየሱስ የሚያስፈልገንን እርዳታ ስለሚሰጠን ነው። w22.07 9 አን. 7-8

ዓርብ፣ መስከረም 13

ጸሎቴ በአንተ ፊት እንደተዘጋጀ ዕጣን ይሁን።—መዝ. 141:2

ወደ ይሖዋ ስንጸልይ አክብሮት በጎደለው መንገድ እንዳንናገር መጠንቀቅ ይኖርብናል። ከዚህ ይልቅ ምንጊዜም ወደ ይሖዋ የምንቀርበው በጥልቅ አክብሮት ሊሆን ይገባል። እስቲ ኢሳይያስ፣ ሕዝቅኤል፣ ዳንኤልና ዮሐንስ ያዩአቸውን አስደናቂ ራእዮች ለማሰብ ሞክሩ። በሁሉም ራእዮች ላይ ይሖዋ የተገለጸው ግርማ ሞገስ የተላበሰ ንጉሥ ተደርጎ ነው። ኢሳይያስ፣ ይሖዋ “በረጅምና ከፍ ባለ ዙፋን ላይ ተቀምጦ” ተመልክቷል። (ኢሳ. 6:1-3) ሕዝቅኤል፣ ይሖዋ ‘እንደ ቀስተ ደመና ባለ ደማቅ ብርሃን ተከቦ’ በሰማያዊ ሠረገላው ላይ ተቀምጦ አይቷል። (ሕዝ. 1:26-28) ዳንኤል “ከዘመናት በፊት የነበረው” ነጭ ልብስ እንደለበሰና ከዙፋኑ የእሳት ነበልባል ይወጣ እንደነበር ተመልክቷል። (ዳን. 7:9, 10) ዮሐንስ ደግሞ ይሖዋ መረግድ በሚመስል ውብ ቀስተ ደመና በተከበበ ዙፋን ላይ ተቀምጦ ተመልክቷል። (ራእይ 4:2-4) ወደር በሌለው የይሖዋ ክብር ላይ ስናሰላስል ወደ እሱ በጸሎት መቅረብ አስደናቂ መብት እንደሆነ እናስታውሳለን፤ እንዲሁም ወደ እሱ ስንጸልይ ጥልቅ አክብሮት ሊኖረን እንደሚገባ እንገነዘባለን። w22.07 20 አን. 3

ቅዳሜ፣ መስከረም 14

[ከሰዎች] የማታለያ ዘዴ [ተጠንቀቁ]።—ኤፌ. 4:14

ሰይጣን ወጣቶች መንፈሳዊ እድገት እንዳያደርጉ ለማገድ ይሞክራል። ለዚህ የሚጠቀምበት አንዱ ዘዴ አንዳንዶቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች በተመለከተ ጥርጣሬ እንዲፈጠርብህ ማድረግ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ አምላክን የሚያቃልል ትምህርት ስለሆነው ስለ ዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሐሳብ መማርህ አይቀርም። ልጅ እያለህ ስለዚህ ርዕሰ ጉዳይ እምብዛም አስበህበት አታውቅ ይሆናል። አሁን ግን ዕድሜህ ከፍ ስላለ ትምህርት ቤት ውስጥ ስለ ዝግመተ ለውጥ ትማር ይሆናል። አስተማሪዎችህ ዝግመተ ለውጥን ለመደገፍ የሚጠቅሷቸው ማስረጃዎች አሳማኝና ምክንያታዊ መስለው ሊታዩህ ይችላሉ። ሆኖም አስተማሪዎችህ ፈጣሪ መኖሩን ስለሚያሳየው ማስረጃ በቁም ነገር አስበውበት እንኳ አያውቁ ይሆናል። ምሳሌ 18:17 ላይ የሚገኘውን መሠረታዊ ሥርዓት አስታውስ፤ ጥቅሱ “ክሱን አስቀድሞ ያሰማ ትክክለኛ ይመስላል፤ ይህም ሌላው ወገን መጥቶ እስኪመረምረው ድረስ ነው” ይላል። በትምህርት ቤት የምትማራቸውን ነገሮች በጭፍን ከማመን ይልቅ የአምላክ ቃል በሆነው በመጽሐፍ ቅዱስና በጽሑፎቻችን ውስጥ የሚገኙትን እውነቶች በጥንቃቄ መርምር። w22.08 2 አን. 2፤ 4 አን. 8

እሁድ፣ መስከረም 15

የተጻፈውንም በጥንቃቄ [ፈጽም]፤ እንዲህ ካደረግክ መንገድህ ይቃናልሃል፤ እንዲሁም ማንኛውንም ነገር በጥበብ ማከናወን ትችላለህ።—ኢያሱ 1:8

በአምላክ ቃል ውስጥ የምናነበውን ነገር ትርጉም መረዳት እንፈልጋለን። አለዚያ ከምናነበው ነገር ሙሉ ጥቅም ላናገኝ እንችላለን። ኢየሱስ ‘ከአንድ ሕግ አዋቂ’ ጋር ያደረገውን ውይይት እንደ ምሳሌ እንመልከት። (ሉቃስ 10:25-29) ሰውየው የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ምን ማድረግ እንዳለበት ሲጠይቀው ኢየሱስ “በሕጉ ላይ የተጻፈው ምንድን ነው? አንተስ ምን ትረዳለህ?” በማለት ወደ አምላክ ቃል መራው። ሰውየው አምላክንና ባልንጀራን ስለመውደድ የሚናገሩትን ጥቅሶች በመጥቀስ ትክክለኛውን መልስ መስጠት ችሏል። (ዘሌ. 19:18፤ ዘዳ. 6:5) ግን ቀጥሎ ምን እንዳለ ልብ በሉ፤ “ለመሆኑ ባልንጀራዬ ማን ነው?” በማለት ጠይቋል። ይህ ጥያቄው እንደሚጠቁመው ሰውየው ያነበበውን ነገር በደንብ አልተረዳውም። በዚህም የተነሳ ጥቅሶቹን በሕይወቱ ውስጥ እንዴት ተግባራዊ እንደሚያደርጋቸው አላወቀም። ቅዱሳን መጻሕፍትን ለመረዳት የይሖዋ እርዳታ ያስፈልገናል። ስለዚህ ትኩረታችሁን ለመሰብሰብ እንዲረዳችሁ ይሖዋ ቅዱስ መንፈሱን እንዲሰጣችሁ ጠይቁት። ከዚያም ያነበባችሁትን ነገር ተግባር ላይ ለማዋል እንዲረዳችሁ ለምኑት። w23.02 9 አን. 4-5

ሰኞ፣ መስከረም 16

በእውነት ውስጥ ተመላለሱ።—3 ዮሐ. 4

“እውነትን የሰማኸው እንዴት ነው?” ይህን ጥያቄ ብዙ ጊዜ መልሰህ እንደምታውቅ ጥርጥር የለውም። ከአንድ የይሖዋ ምሥክር ጋር ስንተዋወቅ ከምናነሳቸው የመጀመሪያ ጥያቄዎች መካከል አንዱ ይህ ነው። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይሖዋን ማወቅና መውደድ የቻሉት እንዴት እንደሆነ መስማት እንዲሁም ለእውነት ምን ያህል ፍቅር እንዳለን መናገር ያስደስተናል። (ሮም 1:11) እንዲህ ያሉ ጭውውቶችን ማድረጋችን እውነት ምን ያህል ውድ እንደሆነ ያስታውሰናል። በተጨማሪም ‘በእውነት ውስጥ ለመመላለስ’ ማለትም የይሖዋን በረከትና ሞገስ በሚያስገኝ መንገድ መኖራችንን ለመቀጠል ያለንን ቁርጠኝነት ያጠናክረዋል። እውነትን ለመውደድ የሚያነሳሱን ብዙ ምክንያቶች አሉ። ዋነኛው ምክንያት የእውነት ምንጭ የሆነውን ይሖዋ አምላክን ስለምንወደው ነው። ይሖዋ ሰማይንና ምድርን የፈጠረ ሁሉን ቻይ አምላክ መሆኑን ብቻ ሳይሆን በርኅራኄ የሚንከባከበን አፍቃሪ የሰማዩ አባታችን መሆኑንም በቃሉ በመጽሐፍ ቅዱስ አማካኝነት ተምረናል።—1 ጴጥ. 5:7፤ w22.08 14 አን. 1, 3

ማክሰኞ፣ መስከረም 17

ድሆችን ማሰባችንን [አናቋርጥ]።—ገላ. 2:10

ሐዋርያው ጳውሎስ ወንድሞቹና እህቶቹ ‘በመልካም ሥራዎች’ አማካኝነት ፍቅር እንዲያሳዩ አበረታቷቸዋል። (ዕብ. 10:24) ወንድሞቹንና እህቶቹን በንግግሩ ብቻ ሳይሆን በተግባሩም ረድቷቸዋል። ለምሳሌ በይሁዳ ያሉ ክርስቲያኖች ረሃብ ባጋጠማቸው ወቅት ጳውሎስ ለእነሱ እርዳታ በማከፋፈሉ ሥራ ተካፍሏል። (ሥራ 11:27-30) እንዲያውም ጳውሎስ በመስበኩና በማስተማሩ ሥራ የተጠመደ ቢሆንም ቁሳዊ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ክርስቲያኖች ለመርዳት ሁልጊዜ አጋጣሚ ይፈልግ ነበር። እንዲህ በማድረግ፣ የእምነት ባልንጀሮቹ ይሖዋ እንደሚንከባከባቸው ያላቸውን እምነት እንዲያጠናክሩ ረድቷቸዋል። በዛሬው ጊዜም በአደጋ ጊዜ እርዳታ ሥራ ለመካፈል ጊዜያችንን፣ ጉልበታችንን እና ችሎታችንን ስናውል የወንድሞቻችንን እና የእህቶቻችንን እምነት እናጠናክራለን። ለዓለም አቀፉ ሥራ አዘውትረን መዋጮ ማድረጋችንም ተመሳሳይ ውጤት ያስገኛል። በእነዚህና በሌሎችም መንገዶች፣ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ይሖዋ መቼም ቢሆን እንደማይተዋቸው እንዲተማመኑ እንረዳቸዋለን። w22.08 24 አን. 14

ረቡዕ፣ መስከረም 18

መቼም ቢሆን ትንቢት በሰው ፈቃድ አልመጣምና፤ ከዚህ ይልቅ ሰዎች ከአምላክ የተቀበሉትን ትንቢት በመንፈስ ቅዱስ ተገፋፍተው ተናገሩ።—2 ጴጥ. 1:21

መጽሐፍ ቅዱስ ፍጻሜያቸውን ያገኙ በርካታ ትንቢቶችን ይዟል። እንዲያውም አንዳንዶቹ የተፈጸሙት ከተጻፉ በመቶዎች ከሚቆጠሩ ዓመታት በኋላ ነው። እነዚህ ትንቢቶች መፈጸማቸውን ታሪክ ይመሠክራል። ይህ መሆኑ አያስገርመንም፤ ምክንያቱም የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች ያስጻፈው ይሖዋ መሆኑን እናውቃለን። የጥንቷን የባቢሎን ከተማ አወዳደቅ በተመለከተ የተነገሩትን ትንቢቶች እንደ ምሳሌ እንውሰድ። በስምንተኛው መቶ ዘመን ዓ.ዓ. ነቢዩ ኢሳይያስ፣ በወቅቱ ኃያል ከተማ የነበረችው ባቢሎን ድል እንደምትደረግ በመንፈስ ተመርቶ ትንቢት ተናግሯል። ድል የሚያደርጋት ቂሮስ የተባለ ሰው እንደሆነም ጭምር ተናግሯል፤ በተጨማሪም ከተማዋ ድል የምትደረገው እንዴት እንደሆነ በዝርዝር ገልጿል። (ኢሳ. 44:27–45:2) ከዚህም ሌላ ኢሳይያስ፣ ባቢሎን ከጊዜ በኋላ እንደምትደመሰስ እንዲሁም ሙሉ በሙሉ ባድማ እንደምትሆን ተናግሯል። (ኢሳ. 13:19, 20) ባቢሎን በ539 ዓ.ዓ. በሜዶናውያንና በፋርሳውያን እጅ ወደቀች። ይህች ታላቅ ከተማ ትገኝበት የነበረው ቦታ አሁን የፍርስራሽ ክምር ሆኗል። w23.01 4 አን. 10

ሐሙስ፣ መስከረም 19

እርስ በርስ ተበረታቱ።—1 ተሰ. 5:11

ይሖዋ አገልጋዮቹን ያቀፈው ዓለም አቀፋዊ ቤተሰብ አባል እንድንሆን መርጦናል። ይህ ልዩ መብት ነው፤ ብዙ በረከቶችንም ያስገኛል! (ማር. 10:29, 30) በዓለም ዙሪያ እንደ እኛ ይሖዋን የሚወዱና በእሱ መሥፈርቶች ለመመራት አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ የሚያደርጉ ወንድሞችና እህቶች አሉን። ቋንቋችን፣ ባሕላችንና አለባበሳችን የተለያየ ቢሆንም ለመጀመሪያ ጊዜ ስናገኛቸው እንኳ በደንብ እንደምናውቃቸው ይሰማናል። በተለይ አብረናቸው ሆነን የሚወደንን ሰማያዊ አባታችንን ስናወድስና ስናመልክ በጣም ደስ ይለናል። ከእነሱ ጋር ያለንን አንድነት መጠበቅ ያስፈልገናል። (መዝ. 133:1) አንዳንድ ጊዜ ወንድሞቻችን ሸክማችንን ለመሸከም ያግዙናል። (ሮም 15:1፤ ገላ. 6:2) በተጨማሪም ይሖዋን በቅንዓት ማገልገላችንን እንድንቀጥልና በመንፈሳዊ ጠንካራ እንድንሆን ያበረታቱናል። (ዕብ. 10:23-25) የጋራ ጠላቶቻችን የሆኑትን ሰይጣን ዲያብሎስንና በሥሩ ያለውን ክፉ ዓለም ለመቋቋም የጉባኤው ጥበቃ ባይኖረን ኖሮ ምን ይውጠን ነበር! w22.09 2-3 አን. 3-4

ዓርብ፣ መስከረም 20

ከንፈሩን የሚገታ . . . ልባም ሰው ነው።—ምሳሌ 10:19

ማኅበራዊ ሚዲያ በምንጠቀምበት ጊዜ ራስን የመግዛት ባሕርያችን ሊፈተን ይችላል። ካልተጠነቀቅን ሳናስበው ሚስጥራዊ የሆኑ መረጃዎችን ለብዙ ሰዎች ልናሰራጭ እንችላለን። አንድን መረጃ ኢንተርኔት ላይ ካወጣነው በኋላ መረጃው በምን መልኩ ጥቅም ላይ እንደሚውል ወይም ምን ያህል ጉዳት እንደሚያደርስ መቆጣጠር አንችልም። ከዚህም ሌላ ራስን መግዛት ተቃዋሚዎች ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን አደጋ ላይ የሚጥል መረጃ ለማወጣጣት በሚሞክሩበት ወቅት ዝም እንድንል ይረዳናል። በሥራችን ላይ እገዳ ወይም ገደብ በተጣለባቸው አገሮች ውስጥ ፖሊሶች ምርመራ ሲያደርጉብን እንዲህ ያለ ሁኔታ ሊያጋጥመን ይችላል። በእነዚህም ሆነ በሌሎች ሁኔታዎች ውስጥ ስንሆን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚለው ‘አፋችንን ለመጠበቅ ልጓም ማስገባት’ ይኖርብናል። (መዝ. 39:1) ከቤተሰቦቻችን፣ ከጓደኞቻችን፣ ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን እንዲሁም ከሌላ ከማንኛውም ሰው ጋር ባለን ግንኙነት እምነት የሚጣልብን መሆን ይኖርብናል። እምነት የሚጣልብን ለመሆን ደግሞ ራሳችንን መግዛት ያስፈልገናል። w22.09 13 አን. 16

ቅዳሜ፣ መስከረም 21

በይሖዋ ሕግ ደስ [የሚለው ሰው ደስተኛ ነው]፤ ሕጉንም በቀንና በሌሊት በለሆሳስ ያነበዋል።—መዝ. 1:1, 2

እውነተኛ ደስታ ለማግኘት መንፈሳዊ ምግብ መመገብ አለብን። ደግሞም መንፈሳዊ ምግብ ያስፈልገናል። ኢየሱስ “ሰው ከይሖዋ አፍ በሚወጣ ቃል ሁሉ እንጂ በምግብ ብቻ አይኖርም” ያለው ለዚህ ነው። (ማቴ. 4:4) በመሆኑም የአምላክ ውድ ቃል ከሆነው ከመጽሐፍ ቅዱስ መንፈሳዊ ምግብ ሳንመገብ አንድም ቀን እንዲያልፍብን መፍቀድ የለብንም። ይሖዋ ስለሚወደን ደስተኛ ሕይወት መምራት የምንችልበትን መንገድ በተመለከተ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ወሳኝ መረጃ ሰጥቶናል። የሕይወታችን ዓላማ ምን እንደሆነ እንማራለን። ወደ አምላክ መቅረብና ለኃጢአታችን ይቅርታ ማግኘት የምንችለው እንዴት እንደሆነ እንማራለን። በተጨማሪም የወደፊቱን ጊዜ አስመልክቶ ስለሰጠን ግሩም ተስፋ እንማራለን። (ኤር. 29:11) ከመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የምንማራቸው እነዚህ እውነቶች ልባችን በደስታ እንዲሞላ ያደርጋሉ። ባጋጠሟችሁ ችግሮች ምክንያት ተስፋ በምትቆርጡበት ጊዜ የይሖዋን ቃል ለማንበብና ለማሰላሰል ተጨማሪ ጊዜ መድቡ። w22.10 7 አን. 4-6

እሁድ፣ መስከረም 22

በማስተዋል ችሎታችሁ . . . የጎለመሳችሁ ሁኑ።—1 ቆሮ. 14:20

መጽሐፍ ቅዱስ፣ አላዋቂዎች ሆነን እንዳንኖር ያበረታታናል። የመጽሐፍ ቅዱስን መሠረታዊ ሥርዓቶች በሕይወታችን ተግባራዊ በማድረግ ጥበብ ማግኘት እንችላለን። እንዲህ ካደረግን እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ከችግር ለመራቅና ጥበብ የሚንጸባረቅበት ውሳኔ ለማድረግ እንደሚረዱን በሕይወታችን እናያለን። በዚህ ረገድ የምናደርገውን እድገት መገምገማችን ጠቃሚ ነው። ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናትና በስብሰባዎች ላይ መገኘት ከጀመርክ ረዘም ያለ ጊዜ ቢያልፍም ሕይወትህን ለይሖዋ ወስነህ ካልተጠመቅክ ‘እስካሁን እዚህ ግብ ላይ ያልደረስኩት ለምንድን ነው?’ ብለህ ራስህን ጠይቅ። የተጠመቅክ ክርስቲያን ከሆንክ ደግሞ ምሥራቹን በመስበክና በማስተማር ረገድ ማሻሻያ እያደረግክ ነው? የምታደርጋቸው ውሳኔዎች በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች እንደምትመራ ያሳያሉ? ከሌሎች ጋር ባለህ ግንኙነት ክርስቲያናዊ ባሕርያትን ታንጸባርቃለህ? በእነዚህ ጉዳዮች ረገድ ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልግህ ከተገነዘብክ በይሖዋ ማሳሰቢያዎች ላይ አሰላስል፤ ምክንያቱም የይሖዋ ማሳሰቢያ “ተሞክሮ የሌለውን ጥበበኛ ያደርጋል።”—መዝ. 19:7፤ w22.10 20 አን. 8

ሰኞ፣ መስከረም 23

መንፈሱ ወደመራቸው አቅጣጫ . . . ሁሉ ይሄዳሉ።—ሕዝ. 1:20

ሕዝቅኤል የአምላክ መንፈስ ምን ያህል ኃያል እንደሆነ ተመልክቷል። ሕዝቅኤል፣ መንፈስ ቅዱስ ኃያል በሆኑት መንፈሳዊ ፍጥረታት ላይ ሲሠራ እንዲሁም የሰማያዊውን ሠረገላ ግዙፍ መንኮራኩሮች ሲያንቀሳቅስ በራእይ አይቷል። (ሕዝ. 1:21) ታዲያ በዚህ ጊዜ ምን አደረገ? “እኔም ባየሁት ጊዜ በግንባሬ ተደፋሁ” ብሏል። ሕዝቅኤል በድንጋጤ ተውጦ መሬት ላይ ወደቀ። (ሕዝ. 1:28) ሕዝቅኤል ይህን አስደናቂ ራእይ ባስታወሰ ቁጥር፣ በአምላክ መንፈስ እርዳታ አገልግሎቱን ማከናወን እንደሚችል ያለው እምነት ይበልጥ እንደሚጠናከር ጥያቄ የለውም። ይሖዋ ሕዝቅኤልን “የሰው ልጅ ሆይ፣ ተነስተህ በእግርህ ቁም፤ እኔም አናግርሃለሁ” በማለት አዘዘው። ይህ ትእዛዝ ከአምላክ መንፈስ ጋር ተደምሮ፣ ለሕዝቅኤል ከመሬት ለመነሳት የሚያስፈልገውን ጥንካሬ ሰጥቶታል። (ሕዝ. 2:1, 2) ከጊዜ በኋላም ሕዝቅኤል አገልግሎቱን ባከናወነበት ዘመን ሁሉ የአምላክ “እጅ” ማለትም የአምላክ ቅዱስ መንፈስ መርቶታል።—ሕዝ. 3:22፤ 8:1፤ 33:22፤ 37:1፤ 40:1፤ w22.11 4 አን. 7-8

ማክሰኞ፣ መስከረም 24

ጆሮህ ከኋላህ . . . ድምፅ ይሰማል።—ኢሳ. 30:21

ነቢዩ ኢሳይያስ እዚህ ላይ ይሖዋን ከተማሪዎቹ ኋላ ኋላ እየሄደ አቅጣጫ እንደሚጠቁም ንቁ አስተማሪ አድርጎ ገልጾታል። በዛሬው ጊዜ የአምላክን ድምፅ ከኋላችን እንሰማለን። እንዴት? አምላክ በመንፈስ መሪነት መጽሐፍ ቅዱስን ያስጻፈው ከረጅም ጊዜ በፊት ነው፤ ከኋላችን ሊባል ይችላል። በመሆኑም መጽሐፍ ቅዱስን ስናነብ የአምላክን ድምፅ ከኋላችን የምንሰማ ያህል ነው። (ኢሳ. 51:4) ይሖዋ ከሚሰጠው አመራር የተሟላ ጥቅም ማግኘት የምንችለው እንዴት ነው? ኢሳይያስ ሁለት ነገሮችን እንደጠቀሰ ልብ በሉ። አንደኛ፣ “መንገዱ ይህ ነው።” ሁለተኛ፣ “በእሱ ሂድ።” ስለዚህ ‘መንገዱን’ ማወቅ ብቻ በቂ አይደለም። ‘በእሱ ልንሄድም’ ይገባል። በይሖዋ ቃልና ድርጅቱ በሚሰጠው ማብራሪያ አማካኝነት ይሖዋ ምን እንደሚጠብቅብን እንማራለን። የተማርነውን እንዴት ተግባራዊ ማድረግ እንደምንችልም እንማራለን። ለይሖዋ በምናቀርበው አገልግሎት በደስታ ለመጽናት ከፈለግን ሁለቱንም እርምጃዎች መውሰድ ይጠበቅብናል። ይሖዋ እንደሚባርከን እርግጠኞች መሆን የምንችለው ይህን ካደረግን ብቻ ነው። w22.11 10-11 አን. 10-11

ረቡዕ፣ መስከረም 25

እኔ ከሄድኩ በኋላ ጨካኝ ተኩላዎች በመካከላችሁ [ይገባሉ]።—ሥራ 20:29

አብዛኞቹ የኢየሱስ ሐዋርያት ከሞቱ ብዙም ሳይቆይ አስመሳይ ክርስቲያኖች ወደ ጉባኤው ሰርገው ገቡ። (ማቴ. 13:24-27, 37-39) “ደቀ መዛሙርቱን ወደ ራሳቸው ለመሳብ ጠማማ ነገር” መናገር ጀመሩ። (ሥራ 20:30) እነዚህ አስመሳይ ክርስቲያኖች ካመጧቸው ‘ጠማማ ነገሮች’ አንዱ ኢየሱስ “የብዙዎችን ኃጢአት ለመሸከም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መሥዋዕት” እንደሆነ ከሚገልጸው የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ጋር የሚጋጭ ነው፤ መሥዋዕቱ ደጋግሞ መቅረብ እንዳለበት ማስተማር ጀመሩ። (ዕብ. 9:27, 28) በዛሬው ጊዜ በዚህ የሐሰት ትምህርት የሚያምኑ ብዙ ቅን ሰዎች አሉ። “ቅዱስ ቁርባን” ተብሎ የሚጠራውን ሥርዓት ለማክበር ሲሉ አዘውትረው አንዳንዴም በየቀኑ ወደ ቤተ ክርስቲያን ይሄዳሉ። አንዳንድ የሃይማኖት ድርጅቶች ደግሞ የኢየሱስን ሞት መታሰቢያ ያን ያህል ደጋግመው አያከብሩም፤ ሆኖም አብዛኞቹ አባሎቻቸው የኢየሱስ መሥዋዕት ስለሚያስገኘው ጥቅም እምብዛም የሚያውቁት ነገር የለም። w23.01 21 አን. 5

ሐሙስ፣ መስከረም 26

መልካም ማድረግንና ያላችሁን ነገር ለሌሎች ማካፈልን አትርሱ።—ዕብ. 13:16

በኢየሱስ የሺህ ዓመት ግዛት ወቅት ሙታን ይነሳሉ፤ እንዲሁም ታዛዥ የሆኑ የሰው ልጆች ወደ ፍጽምና ደረጃ ይደርሳሉ። ይሖዋ ‘ጻድቃን ናቸው’ ብሎ የሚፈርድላቸው ሰዎች “ምድርን ይወርሳሉ፤ በእሷም ላይ ለዘላለም ይኖራሉ።” (መዝ. 37:10, 11, 29) በጣም ደስ የሚለው ደግሞ “የመጨረሻው ጠላት፣ ሞት ይደመሰሳል።” (1 ቆሮ. 15:26) የዘላለም ሕይወት ተስፋችን በአምላክ ቃል ላይ የተመሠረተ አስተማማኝ ተስፋ ነው። ይህ ተስፋ በእነዚህ አስጨናቂ የመጨረሻ ቀናት ታማኝነታችንን እንድንጠብቅ ይረዳናል። ይሁንና ይሖዋን ማስደሰት ከፈለግን፣ እሱን ለማገልገል የሚያነሳሳን ዋነኛ ምክንያት የዘላለም ሕይወት ለማግኘት ያለን ፍላጎት ሊሆን አይገባም። ለይሖዋና ለኢየሱስ ታማኝ እንድንሆን የሚያነሳሳን ለእነሱ ያለን ጥልቅ ፍቅር ነው። (2 ቆሮ. 5:14, 15) እንዲህ ያለው ፍቅር፣ እነሱን ለመምሰልና ስለ ተስፋችን ለሌሎች ለመናገር ያነሳሳናል። (ሮም 10:13-15) ከራስ ወዳድነት ነፃ ስንሆንና ልግስናን ስናዳብር ይሖዋ ለዘላለም ወዳጆቹ እንዲሆኑ የሚፈልጋቸው ዓይነት ሰዎች እንሆናለን። w22.12 6-7 አን. 15-16

ዓርብ፣ መስከረም 27

የክርስቶስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በመሆን ለአምላክ ያደሩ ሆነው መኖር የሚፈልጉ ሁሉ ስደት ይደርስባቸዋል።—2 ጢሞ. 3:12

ስደት ሰላም የሚያስገኙልንን የተለያዩ ነገሮች ሊያሳጣን ይችላል። ‘ነገ ምን ይደርስብን ይሆን’ ብለን በመስጋት ልንጨነቅ እንችላለን። እንዲህ ቢሰማን አያስገርምም። ያም ቢሆን መጠንቀቅ ይኖርብናል። ኢየሱስ፣ ስደት ተከታዮቹን ሊያሰናክላቸው እንደሚችል ተናግሯል። (ዮሐ. 16:1, 2) ኢየሱስ ስደት እንደሚደርስብን ቢናገርም ታማኝነታችንን መጠበቅ እንደምንችልም ዋስትና ሰጥቶናል። (ዮሐ. 15:20፤ 16:33) በሥራችን ላይ እገዳ ወይም ከፍተኛ ገደብ በሚጣልበት ወቅት ከቅርንጫፍ ቢሮው ወይም ከሽማግሌዎች መመሪያ ሊሰጠን ይችላል። የእነዚህ መመሪያዎች ዓላማ እኛን ከጉዳት መጠበቅ፣ መንፈሳዊ ምግብ ማግኘታችንን እንድንቀጥል ማድረግ እንዲሁም ሁኔታው በሚፈቅደው መጠን መስበካችንን እንድንቀጥል መርዳት ነው። የተሰጠህን መመሪያ ለመታዘዝ አቅምህ የፈቀደውን ሁሉ አድርግ። (ያዕ. 3:17) በተጨማሪም ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ማወቅ ለማይገባቸው ሰዎች እንዳትናገር ተጠንቀቅ።—መክ. 3:7፤ w22.12 20-21 አን. 14-16

ቅዳሜ፣ መስከረም 28

ያንኑ ትጋት [አሳዩ]።—ዕብ. 6:11

ኢየሱስ በመላው ምድር ላይ ስለ አምላክ መንግሥት ለሚሰብኩ ደቀ መዛሙርቱ መመሪያ መስጠቱን ቀጥሏል። እሱ የበኩሉን አድርጓል። በይሖዋ ድርጅት አማካኝነት እንዴት እንደምንሰብክ ያሠለጥነናል፤ እንዲሁም ምሥራቹን ለማስፋፋት የሚያስፈልጉንን መሣሪያዎች ያቀርብልናል። (ማቴ. 28:18-20) እኛም በስብከቱና በማስተማሩ ሥራ ትጉ በመሆን እንዲሁም ይሖዋ ይህን ሥርዓት የሚያጠፋበትን ጊዜ በንቃት በመጠባበቅ የበኩላችንን ማድረግ ይኖርብናል። በዕብራውያን 6:11, 12 ላይ በሚገኘው ምክር መሠረት ተስፋችንን “እስከ መጨረሻው” አጥብቀን እንይዛለን። ይሖዋ የሰይጣንን ሥርዓት የሚያጠፋበትን ቀንና ሰዓት ወስኗል። ያ ጊዜ ሲመጣ ይሖዋ በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍሩ ያደረጋቸው ትንቢቶች በሙሉ ያለአንዳች ጥርጥር እንዲፈጸሙ ያደርጋል። እርግጥ አንዳንድ ጊዜ የሥርዓቱ ፍጻሜ እንደዘገየ ሊሰማን ይችላል። ሆኖም የይሖዋ ቀን “አይዘገይም!” (ዕን. 2:3) እንግዲያው ‘የሚያድነንን አምላክ በትዕግሥት’ እንዲሁም ‘በጉጉት ለመጠባበቅ’ ቁርጥ ውሳኔ እናድርግ።—ሚክ. 7:7፤ w23.02 19 አን. 15-16

እሁድ፣ መስከረም 29

ከአንተ ጋር ሊወዳደር የሚችል ማንም የለም።—መዝ. 40:5

ተራራ የሚወጣ ሰው ዋነኛ ግቡ የተራራው ጫፍ ላይ መድረስ ነው። ይሁንና በመንገዱ ላይ ቆም እያለ የአካባቢውን መልክዓ ምድር ማድነቅ የሚችልበት ብዙ አጋጣሚ ይኖረዋል። አንተም በተመሳሳይ በመከራ ውስጥ ብትሆንም እንኳ ይሖዋ ስኬታማ እንድትሆን እየረዳህ ያለው እንዴት እንደሆነ አልፎ አልፎ ቆም እያልክ አስብ። በእያንዳንዱ ቀን መጨረሻ ላይ እንዲህ እያልክ ራስህን ጠይቅ፦ ‘ዛሬ የይሖዋን በረከት ያየሁት በምን መንገድ ነው? የደረሰብኝ ፈተና ገና ባያበቃም ይሖዋ ለመጽናት እየረዳኝ ያለው እንዴት ነው?’ ይሖዋ ስኬታማ እንድትሆን ለመርዳት ያደረገልህን ቢያንስ አንድ ነገር ለማስተዋል ሞክር። እርግጥ ፈተናው እንዲያበቃ እየጸለይክ ሊሆን ይችላል። (ፊልጵ. 4:6) ሆኖም አሁን ያሉህን በረከቶችም ማስተዋል ይኖርብሃል። ደግሞም ይሖዋ ቃል የገባልን ብርታት እንደሚሰጠንና ለመጽናት እንደሚረዳን ነው። ስለዚህ ይሖዋ እያደረገልህ ላለው ድጋፍ ምንጊዜም አመስጋኝ ሁን። እንዲህ ካደረግክ፣ በፈተና ውስጥ ብትሆንም እንኳ ይሖዋ ስኬታማ እንድትሆን እየረዳህ ያለው እንዴት እንደሆነ ማየት ትችላለህ።—ዘፍ. 41:51, 52፤ w23.01 19 አን. 17-18

ሰኞ፣ መስከረም 30

የይሖዋን ቀን መምጣት . . . በአእምሯችሁ አቅርባችሁ እየተመለከታችሁ ልትኖሩ ይገባል!—2 ጴጥ. 3:12

ራስህን እንዲህ እያልክ ጠይቅ፦ ‘አኗኗሬ የዚህ ሥርዓት መጨረሻ ምን ያህል እንደቀረበ እንደተገነዘብኩ የሚያሳይ ነው? ከትምህርትና ከሥራ ጋር በተያያዘ የማደርጋቸው ውሳኔዎች በሕይወቴ ውስጥ ትልቁን ቦታ የምሰጠው ለይሖዋ አገልግሎት እንደሆነ ያሳያሉ? ይሖዋ ለእኔም ሆነ ለቤተሰቤ የሚያስፈልገንን ነገር እንደሚያሟላልን እተማመናለሁ?’ ይሖዋ ሕይወታችንን ከእሱ ፈቃድ ጋር ለማስማማት ጥረት ስናደርግ ምን ያህል እንደሚደሰት እስቲ አስበው። (ማቴ. 6:25-27, 33፤ ፊልጵ. 4:12, 13) አስተሳሰባችንን አዘውትረን በመገምገም አስፈላጊውን ማስተካከያ ማድረግ ይኖርብናል። ጳውሎስ “በእምነት ውስጥ መሆናችሁን ለማረጋገጥ ዘወትር ራሳችሁን ፈትሹ፤ ማንነታችሁን ለማወቅ ዘወትር ራሳችሁን መርምሩ” በማለት የቆሮንቶስ ክርስቲያኖችን መክሯቸዋል። (2 ቆሮ. 13:5) በመሆኑም የአምላክን ቃል በማንበብ፣ የይሖዋን አስተሳሰብ ለማዳበር ጥረት በማድረግ እንዲሁም ሕይወታችንን ከእሱ ፈቃድ ጋር ለማስማማት አስፈላጊውን ማስተካከያ ሁሉ በማድረግ አእምሯችንን ማደሳችንን መቀጠል ይኖርብናል።—1 ቆሮ. 2:14-16፤ w23.01 9 አን. 5-6

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ