ነሐሴ
ዓርብ፣ ነሐሴ 1
የጻድቅ ሰው መከራ ብዙ ነው፤ ይሖዋ ግን ከመከራው ሁሉ ይታደገዋል።—መዝ. 34:19
በዚህ መዝሙር ላይ የተጠቀሱትን ሁለት አስፈላጊ ነጥቦች ልብ በል። (1) ጻድቅ የሆኑ ሰዎች መከራ ይደርስባቸዋል። (2) ይሖዋ ከሚያጋጥመን መከራ ይታደገናል። ይሖዋ የሚታደገን እንዴት ነው? አንዱ መንገድ፣ በዚህ ሥርዓት ውስጥ ያለንን ሕይወት በተመለከተ ሚዛናዊ አመለካከት እንዲኖረን በመርዳት ነው። ይሖዋ እሱን በማገልገል ደስታ እንደምናገኝ ቃል ቢገባልንም በአሁኑ ዘመን ከችግር ነፃ የሆነ ሕይወት እንደምንመራ ዋስትና አልሰጠንም። (ኢሳ. 66:14) እሱ እንድንኖር የሚፈልገውን ሕይወት ለዘላለም በምናጣጥምበት በወደፊቱ ጊዜ ላይ እንድናተኩር ያበረታታናል። (2 ቆሮ. 4:16-18) እስከዚያው ግን ለእያንዳንዱ ቀን የሚያስፈልገንን እርዳታ ይሰጠናል። (ሰቆ. 3:22-24) በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመንም ሆነ በዘመናችን የኖሩ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ከተዉት ምሳሌ ምን ትምህርት እናገኛለን? ሁላችንም ያልተጠበቁ ችግሮች ሊያጋጥሙን ይችላሉ። ሆኖም በይሖዋ ከታመንን እሱ ምንጊዜም ይደግፈናል።—መዝ. 55:22፤ w23.04 14-15 አን. 3-4
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 2
ለበላይ ባለሥልጣናት [ተገዙ]።—ሮም 13:1
አመቺ ባልሆነ ጊዜ ጭምር ለበላይ ባለሥልጣናት በመታዘዝ ረገድ ከዮሴፍና ከማርያም ምሳሌ ትምህርት ማግኘት እንችላለን። (ሉቃስ 2:1-6) ማርያም የዘጠኝ ወር እርጉዝ ሳለች እሷና ዮሴፍ የታዛዥነት ፈተና አጋጠማቸው። የሮም ገዢ የሆነው አውግስጦስ የሕዝብ ቆጠራ እንዲካሄድ አዘዘ። ማርያምና ዮሴፍ ዳገት ቁልቁለት አቋርጠው 150 ኪሎ ሜትር በመጓዝ ቤተልሔም መሄድ ነበረባቸው። ይህ ጉዞ በተለይ ለማርያም የሚያንገላታ እንደሚሆን ጥርጥር የለውም። የማርያምና የፅንሱ ደህንነት አሳስቧቸው ሊሆን ይችላል። መንገድ ላይ ሳለች ምጧ ቢመጣስ? በማህፀኗ የተሸከመችው ተስፋ የተሰጠበትን መሲሕ ነው። እነዚህ ነገሮች መንግሥትን ላለመታዘዝ ምክንያት ሊሆኑ ይችላሉ? ዮሴፍና ማርያም እነዚህ ምክንያቶች የመንግሥትን ሕግ ከመታዘዝ ወደኋላ እንዲሉ እንዲያደርጓቸው አልፈቀዱም። ይሖዋም ለታዛዥነታቸው ባርኳቸዋል። ማርያም ወደ ቤተልሔም በሰላም ደረሰች። በዚያም ጤናማ ልጅ ተገላገለች። በተጨማሪም የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት እንዲፈጸም አድርጋለች።—ሚክ. 5:2፤ w23.10 8 አን. 9፤ 9 አን. 11-12
እሁድ፣ ነሐሴ 3
እርስ በርስ እንበረታታ።—ዕብ. 10:25
በስብሰባ ላይ ሐሳብ ስለመስጠት ስታስቡ እንኳ በጣም የሚያስፈራችሁ ከሆነስ? በደንብ መዘጋጀታችሁ ሊረዳችሁ ይችላል። (ምሳሌ 21:5) ትምህርቱን ከራሳችሁ ጋር ይበልጥ ባዋሃዳችሁት መጠን ሐሳብ መስጠት ይበልጥ ይቀላችኋል። በተጨማሪም አጭር መልስ ለመመለስ ሞክሩ። (ምሳሌ 15:23፤ 17:27) መልሳችሁ አጭር ከሆነ ያን ያህል አያስፈራችሁም። በራሳችሁ አባባል አጭር መልስ መመለሳችሁ በደንብ እንደተዘጋጃችሁና ትምህርቱን በሚገባ እንደተረዳችሁት ያሳያል። እነዚህን ምክሮች ተግባራዊ ለማድረግ ጥረት ብታደርጉም ከአንዴ ወይም ከሁለቴ በላይ ሐሳብ መስጠት የሚያስፈራችሁ ቢሆንስ? አቅማችሁ የፈቀደውን ነገር ለማድረግ የምታደርጉትን ጥረት ይሖዋ ከፍ አድርጎ እንደሚመለከተው እርግጠኛ ሁኑ። (ሉቃስ 21:1-4) ምርጣችንን መስጠት ማለት ከአቅማችን በላይ መጣጣር ማለት አይደለም። (ፊልጵ. 4:5) ምን ማድረግ እንደምትችሉ አስቡ፤ ግብ አውጡ፤ እንዲሁም መረጋጋት እንድትችሉ ጸልዩ። መጀመሪያ ላይ፣ አንድ አጭር መልስ ብቻ ለመመለስ ግብ ማውጣታችሁ በቂ ሊሆን ይችላል። w23.04 21 አን. 6-8
ሰኞ፣ ነሐሴ 4
ጥሩር እንልበስ፤ . . . ራስ ቁር እንድፋ።—1 ተሰ. 5:8
ሐዋርያው ጳውሎስ ዝግጁ ከሆኑና የጦር ትጥቅ ከለበሱ ወታደሮች ጋር አመሳስሎናል። አንድ ወታደር በማንኛውም ጊዜ ለጦርነት ዝግጁ እንዲሆን ይጠበቅበታል። የእኛም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው። የእምነትንና የፍቅርን ጥሩር በመልበስ እንዲሁም ተስፋን እንደ ራስ ቁር በመድፋት የይሖዋን ቀን ዝግጁ ሆነን መጠበቅ እንችላለን። ጥሩር የአንድን ወታደር ልብ ከጉዳት ይጠብቅለታል። እምነትና ፍቅርም ምሳሌያዊ ልባችንን ይጠብቁልናል። አምላክን ማገልገላችንንና ኢየሱስን መከተላችንን እንድንቀጥል ይረዱናል። እምነት ካለን ይሖዋ እሱን በሙሉ ልባችን በመፈለጋችን ወሮታ እንደሚከፍለን እርግጠኞች እንሆናለን። (ዕብ. 11:6) እምነት፣ መከራ ቢደርስብንም እንኳ ለመሪያችን ለኢየሱስ ምንጊዜም ታማኝ እንድንሆን ያነሳሳናል። ስደት ወይም የኢኮኖሚ ችግር ቢያጋጥማቸውም ንጹሕ አቋማቸውን ከጠበቁ በዘመናችን ያሉ ታማኝ የአምላክ አገልጋዮች በመማር የሚያጋጥሙንን ተፈታታኝ ሁኔታዎች ለመቋቋም የሚያስችል እምነት መገንባት እንችላለን። በተጨማሪም መንግሥቱን ለማስቀደም ሲሉ አኗኗራቸውን ቀላል ያደረጉ ክርስቲያኖችን ምሳሌ በመከተል ከፍቅረ ነዋይ ወጥመድ መራቅ እንችላለን። w23.06 10 አን. 8-9
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 5
ነፋስን የሚጠባበቅ አይዘራም።—መክ. 11:4
ራስን መግዛት፣ ስሜትንና ድርጊትን የመቆጣጠር ችሎታ ነው። ግባችን ላይ ለመድረስ ራስን መግዛት ያስፈልገናል። በተለይ እዚያ ግብ ላይ መድረስ ከባድ ከሆነ ወይም ተነሳሽነት ካጣን ራሳችንን መግዛታችን አስፈላጊ ነው። ራስን መግዛት የአምላክ መንፈስ ፍሬ ገጽታ እንደሆነ አትዘንጋ። በመሆኑም ይህን አስፈላጊ ባሕርይ ማዳበር እንድትችል መንፈስ ቅዱስን እንዲሰጥህ ይሖዋን ጠይቀው። (ሉቃስ 11:13፤ ገላ. 5:22, 23) ሁኔታዎች ሙሉ በሙሉ እስኪስተካከሉ አትጠብቅ። በዚህ ዓለም ውስጥ ሁሉ ነገር ሊስተካከልልን እንደማይችል የታወቀ ነው። ሁሉ ነገር እስኪስተካከል ከጠበቅን ግባችን ላይ ፈጽሞ ላንደርስ እንችላለን። ግባችን ላይ መድረስ በጣም አስቸጋሪ እንደሆነ ከተሰማን ተነሳሽነታችን ሊጠፋ ይችላል። የአንተም ሁኔታ እንደዚያ ከሆነ ግብህን በትንሽ በትንሹ ልትከፋፍለው ትችል ይሆን? ለምሳሌ ግብህ አንድ ክርስቲያናዊ ባሕርይ ማዳበር ከሆነ መጀመሪያ ላይ ይህን ባሕርይ በትናንሽ መንገዶች ለማንጸባረቅ ለምን አትሞክርም? ግብህ መጽሐፍ ቅዱስን አንብቦ መጨረስ ከሆነ ደግሞ ለጥቂት ደቂቃዎች ብቻ በማንበብ ለምን አትጀምርም? w23.05 29 አን. 11-13
ረቡዕ፣ ነሐሴ 6
የጻድቃን መንገድ . . . ፍንትው ብሎ እንደሚወጣ የማለዳ ብርሃን ነው፤ እንደ ቀትር ብርሃን ቦግ ብሎ እስኪበራም ድረስ እየደመቀ ይሄዳል።—ምሳሌ 4:18
በእነዚህ የመጨረሻ ቀናት ይሖዋ ድርጅቱን በመጠቀም ‘በቅድስና ጎዳና’ ላይ ሁላችንም መጓዛችንን እንድንቀጥል የሚረዳ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ምግብ ያለማቋረጥ እያቀረበልን ነው። (ኢሳ. 35:8፤ 48:17፤ 60:17) አንድ ሰው መጽሐፍ ቅዱስን ማጥናት ሲጀምር ‘በቅድስና ጎዳና’ ላይ ለመጓዝ አጋጣሚ ተከፈተለት ሊባል ይችላል። አንዳንዶች ጥቂት መንገድ ብቻ ተጉዘው ከአውራ ጎዳናው ይወጣሉ። ሌሎች ደግሞ እስከ መዳረሻቸው ድረስ ከመንገዱ ላለመውጣት ቁርጥ ውሳኔ አድርገዋል። ይሁንና መዳረሻቸው የት ነው? “የቅድስና ጎዳና” ሰማያዊ ተስፋ ያላቸውን ክርስቲያኖች በሰማይ ወዳለው ‘የአምላክ ገነት’ ይወስዳቸዋል። (ራእይ 2:7) ምድራዊ ተስፋ ያላቸውን ክርስቲያኖች ደግሞ ሁሉም ሰው ፍጹም ወደሚሆንበት የክርስቶስ ሺህ ዓመት ግዛት መጨረሻ ያደርሳቸዋል። በዚህ አውራ ጎዳና ላይ መጓዝ ጀምረህ ከሆነ እባክህ ወደ ኋላ አትመልከት። በተጨማሪም አዲሱ ዓለም ውስጥ እስክትገባ ድረስ ከዚህ መንገድ አትውጣ። w23.05 17 አን. 15፤ 19 አን. 16-18
ሐሙስ፣ ነሐሴ 7
እሱ አስቀድሞ ስለወደደን እኛም ፍቅር እናሳያለን።—1 ዮሐ. 4:19
ይሖዋ ስለሰጠህ ስጦታዎች በሙሉ ስታስብ ራስህን ለእሱ ለመወሰን መነሳሳትህ አይቀርም። (መዝ. 116:12-14) መጽሐፍ ቅዱስ “መልካም ስጦታ ሁሉና ፍጹም ገጸ በረከት ሁሉ” የሚመጣው ከይሖዋ እንደሆነ ይናገራል፤ ደግሞም እንዲህ ማለቱ ተገቢ ነው። (ያዕ. 1:17) ከእነዚህ ስጦታዎች ሁሉ የላቀው የልጁ የኢየሱስ መሥዋዕት ነው። እስቲ አስበው! ቤዛው ከይሖዋ ጋር የቀረበ ወዳጅነት እንድትመሠርት መንገድ ከፍቶልሃል። በተጨማሪም ለዘላለም የመኖር አጋጣሚ ሰጥቶሃል። (1 ዮሐ. 4:9, 10) ከሁሉ ለላቀው ለዚህ የይሖዋ ፍቅር መግለጫ እንዲሁም ይሖዋ ለሰጠህ ሌሎች በረከቶች ሁሉ አድናቆትህን ማሳየት የምትችልበት አንዱ መንገድ ራስህን ለይሖዋ መወሰን ነው።—ዘዳ. 16:17፤ 2 ቆሮ. 5:15፤ w24.03 5 አን. 8
ዓርብ፣ ነሐሴ 8
አካሄዱ ቅን የሆነ ሰው ይሖዋን ይፈራል።—ምሳሌ 14:2
በዛሬው ጊዜ ዓለም የሚከተለውን የሥነ ምግባር መሥፈርት ስናይ እንደ ጻድቁ ሎጥ ዓይነት ስሜት ይሰማናል። ሎጥ የሰማዩ አባታችን መጥፎ ምግባርን እንደሚጠላ ስለሚያውቅ “ለሕግ የማይገዙ ሰዎች በማንአለብኝነት በሚፈጽሙት ድርጊት እጅግ እየተሳቀቀ” ይኖር ነበር። (2 ጴጥ. 2:7, 8) ሎጥ ለአምላክ ያለው ፍርሃትና ፍቅር በዙሪያው የሚኖሩት ሰዎች ከነበራቸው ያዘቀጠ ሥነ ምግባር እንዲርቅ ረድቶታል። እኛም ለይሖዋ የሥነ ምግባር መሥፈርቶች አክብሮት በሌላቸው ሰዎች ተከበናል። ያም ቢሆን ለአምላክ ፍቅርና ጤናማ ፍርሃት ካዳበርን የሥነ ምግባር ንጽሕናችንን መጠበቅ እንችላለን። ይሖዋ በዚህ ረገድ እኛን ለመርዳት ሲል በምሳሌ መጽሐፍ ውስጥ ጠቃሚ ማበረታቻ አስፍሮልናል። ወንድ፣ ሴት፣ ወጣት፣ አረጋዊ ሳይል ሁሉም ክርስቲያኖች በዚህ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኘውን ጥበብ የሚንጸባረቅበት ምክር መመርመራቸው ይጠቅማቸዋል። ይሖዋን የምንፈራው ከሆነ መጥፎ ምግባር ከሚፈጽሙ ሰዎች ጋር ወዳጅነት አንመሠርትም። w23.06 20 አን. 1-2፤ 21 አን. 5
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 9
ሊከተለኝ የሚፈልግ ማንም ቢኖር ራሱን ይካድ፤ የራሱን የመከራ እንጨት በየዕለቱ ይሸከም፤ ያለማቋረጥም ይከተለኝ።—ሉቃስ 9:23
ቤተሰቦችህ ይቃወሙህ ይሆናል፤ ወይም ደግሞ የአምላክን መንግሥት ለማስቀደም ስትል አንዳንድ ቁሳዊ ነገሮችን መሥዋዕት አድርገህ ሊሆን ይችላል። (ማቴ. 6:33) ከሆነ፣ ይሖዋ በታማኝነት ያከናወንከውን ሥራ እንደተመለከተ እርግጠኛ መሆን ትችላለህ። (ዕብ. 6:10) ኢየሱስ የተናገረውን የሚከተለውን ሐሳብ በሕይወትህ ተመልክተህ ይሆናል፦ “ስለ እኔና ስለ ምሥራቹ ሲል ቤትን ወይም ወንድሞችን ወይም እህቶችን ወይም እናትን ወይም አባትን ወይም ልጆችን ወይም እርሻን የተወ ሁሉ፣ አሁን በዚህ ዘመን ከስደት ጋር ቤቶችን፣ ወንድሞችን፣ እህቶችን፣ እናቶችን፣ ልጆችንና እርሻን 100 እጥፍ፣ በሚመጣው ሥርዓት ደግሞ የዘላለም ሕይወት ያገኛል።” (ማር. 10:29, 30) ያገኘሃቸው በረከቶች መሥዋዕት ካደረግካቸው ነገሮች በእጅጉ እንደሚበልጡ ምንም ጥያቄ የለውም።—መዝ. 37:4፤ w24.03 9 አን. 5
እሁድ፣ ነሐሴ 10
እውነተኛ ወዳጅ ምንጊዜም አፍቃሪ ነው፤ ደግሞም ለመከራ ቀን የተወለደ ወንድም ነው።—ምሳሌ 17:17
በይሁዳ ታላቅ ረሃብ ተከስቶ ክርስቲያኖች በተቸገሩበት ወቅት በአንጾኪያ ያሉ ክርስቲያኖች “እያንዳንዳቸው አቅማቸው በፈቀደ መጠን አዋጥተው በይሁዳ ለሚኖሩ ወንድሞች እርዳታ ለመላክ ወሰኑ።” (ሥራ 11:27-30) በረሃብ የተጎዱት ወንድሞቻቸው የሚኖሩት ርቀው ቢሆንም የአንጾኪያ ክርስቲያኖች እነሱን ለመርዳት ቆርጠው ነበር። (1 ዮሐ. 3:17, 18) እኛም የእምነት አጋሮቻችን በአደጋ እንደተጎዱ ስንሰማ ርኅራኄ ማሳየት እንችላለን። ቶሎ ልንደርስላቸው እንፈልጋለን፤ ለምሳሌ በእርዳታ እንቅስቃሴው መካፈል እንችል እንደሆነ ሽማግሌዎችን መጠየቅ፣ ለዓለም አቀፉ ሥራ መዋጮ ማድረግ ወይም በአደጋው ለተጎዱት መጸለይ እንችላለን። ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መሠረታዊ ነገሮችን እንኳ ለማግኘት እገዛ ሊያስፈልጋቸው ይችላል። ንጉሣችን ክርስቶስ ኢየሱስ ለፍርድ ሲመጣ ርኅራኄ ስናሳይ እንዲያገኘን እንፈልጋለን፤ ምኞታችን ‘መንግሥቱን እንዲወርሱ’ ከሚጋብዛቸው ሰዎች መካከል መሆን ነው።—ማቴ. 25:34-40፤ w23.07 4 አን. 9-10፤ 6 አን. 12
ሰኞ፣ ነሐሴ 11
ምክንያታዊነታችሁ በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ይሁን።—ፊልጵ. 4:5
ኢየሱስ እንደ ይሖዋ ምክንያታዊ መሆኑን አሳይቷል። ወደ ምድር የተላከው “ከእስራኤል ቤት ለጠፉት በጎች” ለመስበክ ነው። ሆኖም ይህን ኃላፊነቱን ሲወጣ ምክንያታዊነት አሳይቷል። በአንድ ወቅት፣ እስራኤላዊት ያልሆነች አንዲት ሴት ‘ጋኔን ክፉኛ የሚያሠቃያትን’ ልጇን እንዲፈውስላት ለመነችው። ኢየሱስ ለሴትየዋ ስለራራላት ጥያቄዋን ተቀብሎ ልጇን ፈወሰላት። (ማቴ. 15:21-28) ሌላ ምሳሌ ደግሞ እንመልከት። ኢየሱስ “የሚክደኝን ሁሉ [እኔም] እክደዋለሁ” ብሎ ነበር። (ማቴ. 10:33) ታዲያ ሦስት ጊዜ የካደውን ጴጥሮስን ክዶታል? በፍጹም። ኢየሱስ፣ ጴጥሮስ ከልቡ መጸጸቱንና ለእሱ ያለውን ታማኝነት አይቷል። ኢየሱስ ከሞት ከተነሳ በኋላ ለጴጥሮስ ተገልጦለታል፤ በዚህ አጋጣሚ ይቅር እንዳለውና እንደሚወደው አረጋግጦለት መሆን አለበት። (ሉቃስ 24:33, 34) ይሖዋ አምላክም ሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ምክንያታዊ ናቸው። እኛስ? ይሖዋ ምክንያታዊ እንድንሆን ይጠብቅብናል። w23.07 21 አን. 6-7
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 12
ከእንግዲህ ወዲህ ሞት አይኖርም።—ራእይ 21:4
አምላክ ገነትን አስመልክቶ የገባውን ቃል ለሚጠራጠሩ ሰዎች የትኞቹን ዋስትናዎች ልንነግራቸው እንችላለን? አንደኛ፣ ይህን ቃል የገባልን ይሖዋ ራሱ ነው። የራእይ መጽሐፍ “በዙፋኑም ላይ የተቀመጠው ‘እነሆ፣ ሁሉንም ነገር አዲስ አደርጋለሁ’ አለ” ይላል። እሱ ቃሉን ለመፈጸም የሚያስችል ጥበብ፣ ኃይልና ፍላጎት አለው። ሁለተኛ፣ ይህ ተስፋ መፈጸሙ የተረጋገጠ ከመሆኑ የተነሳ በይሖዋ ዓይን ያኔም እንደተፈጸመ ሊቆጠር ይችላል። ይሖዋ “እነዚህ ቃላት አስተማማኝና እውነት [ናቸው]፤ እነዚህ ነገሮች ተፈጽመዋል!” ያለው ለዚህ ነው። ሦስተኛ፣ ይሖዋ አንድ ነገር ከጀመረ በተሳካ ሁኔታ ዳር ያደርሰዋል። “እኔ አልፋና ኦሜጋ . . . ነኝ” የሚለው አገላለጽ ይህን ያረጋግጣል። (ራእይ 21:6) ይሖዋ፣ ሰይጣን ውሸታም እንደሆነና ዓላማውን ከመፈጸም ሊያግደው እንደማይችል በማያሻማ ሁኔታ ያሳያል። እንግዲያው አንድ ሰው “ይህማ የሕልም እንጀራ ነው” ቢልህ ራእይ 21:5, 6ን አንብበህ አብራራለት። ይሖዋ በምሳሌያዊ ሁኔታ የራሱን ፊርማ በማስፈር ይህ ተስፋ እንደሚፈጸም ዋስትና እንደሰጠን አሳየው።—ኢሳ. 65:16፤ w23.11 7 አን. 18-19
ረቡዕ፣ ነሐሴ 13
ታላቅ ብሔር አደርግሃለሁ።—ዘፍ. 12:2
ይሖዋ ለአብርሃም ይህን ቃል ሲገባለት አብርሃም ገና ልጅ አልወለደም ነበር፤ እንዲሁም 75 ዓመቱ ነበር። ታዲያ አብርሃም ይህ ቃል ሲፈጸም ተመልክቷል? በመጠኑ። ኤፍራጥስ ወንዝን ከተሻገረና 25 ዓመት ከጠበቀ በኋላ በተአምራዊ መንገድ ይስሐቅን ወለደ፤ ከ60 ዓመት ገደማ በኋላ ደግሞ የልጅ ልጆቹ የሆኑት ኤሳውና ያዕቆብ ሲወለዱ ተመልክቷል። (ዕብ. 6:15) ሆኖም አብርሃም ዘሮቹ ታላቅ ብሔር ሲሆኑና ተስፋይቱን ምድር ሲወርሱ አልተመለከተም። ያም ቢሆን ይህ ታማኝ ሰው ከፈጣሪው ጋር የቀረበ ወዳጅነት መመሥረት ችሏል። (ያዕ. 2:23) ወደፊት አብርሃም ከሞት ሲነሳ ደግሞ እምነትና ትዕግሥት ማሳየቱ ለሁሉም ብሔራት በረከት ያስገኘው እንዴት እንደሆነ ሲገነዘብ በጣም መደሰቱ አይቀርም። (ዘፍ. 22:18) እኛስ ከዚህ ምን ትምህርት እናገኛለን? ይሖዋ ቃል የገባቸው ነገሮች በሙሉ ሲፈጸሙ በዚህ ዘመን አናይ ይሆናል። ያም ቢሆን እንደ አብርሃም ትዕግሥት ካሳየን ይሖዋ በአሁኑ ወቅት ወሮታችንን እንደሚከፍለን፣ አዲሱ ዓለም ሲመጣ ደግሞ የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያፈስልን እርግጠኞች መሆን እንችላለን።—ማር. 10:29, 30፤ w23.08 24 አን. 14
ሐሙስ፣ ነሐሴ 14
ይሖዋን ይፈልግ በነበረበት ዘመን እውነተኛው አምላክ አበለጸገው።—2 ዜና 26:5
ንጉሥ ዖዝያ ወጣት ሳለ ትሑት ነበር። “እውነተኛውን አምላክ መፍራት” ተምሯል። ዖዝያ 68 ዓመት የኖረ ሲሆን በአብዛኛው የሕይወቱ ክፍል ይሖዋ ባርኮታል። (2 ዜና 26:1-4) ብዙዎቹን የይሁዳ ጠላቶች ድል ያደረገ ከመሆኑም ሌላ የኢየሩሳሌምን መከላከያዎች አጠናክሯል። (2 ዜና 26:6-15) ዖዝያ በአምላክ እርዳታ ባከናወናቸው ነገሮች በጣም እንደተደሰተ ምንም ጥያቄ የለውም። (መክ. 3:12, 13) ንጉሥ እንደመሆኑ መጠን ሁልጊዜ ለሌሎች ትእዛዝ ያስተላልፍ ነበር። ይህ መሆኑ፣ የፈለገውን ነገር ሁሉ ማድረግ እንደሚችል እንዲሰማው አድርጎት ይሆን? አንድ ቀን ዖዝያ በትዕቢት ወደ ይሖዋ ቤተ መቅደስ ገብቶ በመሠዊያው ላይ ዕጣን ለማጠን ሞከረ፤ ነገሥታት ይህን ማድረግ አይፈቀድላቸውም ነበር። (2 ዜና 26:16-18) ሊቀ ካህናቱ አዛርያስ ሊያስቆመው ሞክሮ ነበር፤ ዖዝያ ግን በጣም ተበሳጨ። የሚያሳዝነው፣ ዖዝያ ያስመዘገበውን የታማኝነት ታሪክ አበላሸ፤ ይሖዋም በሥጋ ደዌ መታው። (2 ዜና 26:19-21) እስከ መጨረሻው ትሑት ሆኖ ቢኖር ኖሮ ሕይወቱ ምንኛ የተሻለ ይሆን ነበር! w23.09 10 አን. 9-10
ዓርብ፣ ነሐሴ 15
ከተገረዙት ወገን የሆኑትን በመፍራት . . . ራሱን ከአሕዛብ አገለለ።—ገላ. 2:12
ሐዋርያው ጴጥሮስ በመንፈስ ከተቀባ በኋላም እንኳ ከድክመቶቹ ጋር መታገል ነበረበት። በ36 ዓ.ም. ካልተገረዙ አሕዛብ ወገን የሆነው ቆርኔሌዎስ በመንፈስ ቅዱስ በተቀባበት ጊዜ ጴጥሮስ እዚያ ነበር። ይህ አጋጣሚ “አምላክ እንደማያዳላ” እና አሕዛብም የክርስቲያን ጉባኤ አባል መሆን እንደሚችሉ በግልጽ አሳይቷል። (ሥራ 10:34, 44, 45) ከዚያ ጊዜ በኋላ ጴጥሮስ ከአሕዛብ ጋር አብሮ መብላት ጀመረ፤ በፊት ቢሆን ይህን ፈጽሞ አያደርግም ነበር። ነገር ግን አንዳንድ አይሁዳውያን ክርስቲያኖች፣ አይሁዳውያንና አሕዛብ አብረው መብላት እንደሌለባቸው ይሰማቸው ነበር። እንዲህ ያለ አመለካከት ያላቸው ሰዎች ወደ አንጾኪያ ሲመጡ ጴጥሮስ ከአሕዛብ ወንድሞቹ ጋር መብላቱን አቆመ፤ ይህን ያደረገው አይሁዳውያን ክርስቲያኖችን እንዳያስቀይም ፈርቶ ሳይሆን አይቀርም። ሐዋርያው ጳውሎስ የጴጥሮስን ግብዝነት ሲመለከት በሁሉም ፊት ገሠጸው። (ገላ. 2:13, 14) ጴጥሮስ እንዲህ ያለ ስህተት ቢሠራም በጽናት ቀጥሏል። w23.09 22 አን. 8
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 16
አጽንቶም ያቆማችኋል።—1 ጴጥ. 5:10
ራሳችሁን በሐቀኝነት ስትመረምሩ በአንዳንድ አቅጣጫዎች ማሻሻያ ማድረግ እንደሚያስፈልጋችሁ ትገነዘቡ ይሆናል። ያም ቢሆን ተስፋ አትቁረጡ። “ጌታ ደግ” ነው፤ ማሻሻያ እንድታደርጉ ይረዳችኋል። (1 ጴጥ. 2:3) ሐዋርያው ጴጥሮስ እንዲህ የሚል ዋስትና ሰጥቶናል፦ “አምላክ . . . ራሱ ሥልጠናችሁ እንዲጠናቀቅ ያደርጋል። ጽኑ እንድትሆኑ ያደርጋችኋል።” ጴጥሮስ በአንድ ወቅት ከአምላክ ልጅ አጠገብ መቆም እንኳ እንደማይገባው ተሰምቶት ነበር። (ሉቃስ 5:8) ሆኖም ይሖዋና ኢየሱስ ባደረጉለት ፍቅራዊ ድጋፍ ጴጥሮስ የክርስቶስ ተከታይ ሆኖ መጽናት ችሏል። በመሆኑም ጴጥሮስ “ጌታችንና አዳኛችን ወደሆነው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ዘላለማዊ መንግሥት” ለመግባት ብቁ ሆኗል። (2 ጴጥ. 1:11) ይህ እንዴት ያለ ግሩም ሽልማት ነው! እናንተም እንደ ጴጥሮስ ከጸናችሁና ይሖዋ እንዲያሠለጥናችሁ ከፈቀዳችሁ የዘላለም ሕይወት ሽልማት ታገኛላችሁ። “የእምነታችሁ ግብ ላይ” መድረስ ይኸውም ‘ራሳችሁን ማዳን’ ትችላላችሁ።—1 ጴጥ. 1:9፤ w23.09 31 አን. 16-17
እሁድ፣ ነሐሴ 17
ሰማይን [እና] ምድርን . . . የሠራውን አምልኩ።—ራእይ 14:7
የጥንቱ የማደሪያ ድንኳን፣ ካህናቱ ሥራቸውን የሚያከናውኑበት በአጥር የተከለለ አንድ ግቢ ነበረው። የሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርብበት ትልቁ የመዳብ መሠዊያ የሚገኘው በግቢው ውስጥ ነበር። ካህናቱ ቅዱስ የሆኑ ሥራዎቻቸውን ከማከናወናቸው በፊት ለመታጠብ የሚጠቀሙበት ከመዳብ የተሠራው የውኃ ገንዳም የሚገኘው እዚያው ነው። (ዘፀ. 30:17-20፤ 40:6-8) በዛሬው ጊዜ በምድር ላይ ያሉት የክርስቶስ ቅቡዓን ወንድሞች በመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ውስጠኛ ግቢ ውስጥ በታማኝነት ያገለግላሉ። ትልቅ የውኃ ገንዳ መኖሩ ሥነ ምግባራዊና መንፈሳዊ ንጽሕናቸውን መጠበቃቸው በጣም አስፈላጊ መሆኑን ያስታውሳቸዋል፤ እርግጥ ይህ ማሳሰቢያ ለሁሉም ክርስቲያኖች አስፈላጊ ነው። ይሁንና “እጅግ ብዙ ሕዝብ” አምልኮ የሚያቀርቡት የት ነው? ሐዋርያው ዮሐንስ ‘በአምላክ ዙፋን ፊት ሆነው በቤተ መቅደሱ ቀንና ሌሊት ቅዱስ አገልግሎት ሲያቀርቡ’ ተመልክቷል፤ እጅግ ብዙ ሕዝብ ይህን የሚያደርጉት በምድር ላይ በመንፈሳዊ ቤተ መቅደሱ ውጨኛ ግቢ ውስጥ ሆነው ነው። (ራእይ 7:9, 13-15) ይሖዋ ለንጹሕ አምልኮ ባደረገው ዝግጅት ውስጥ ቦታ ያለን በመሆኑ ምንኛ አመስጋኞች ነን! w23.10 28 አን. 15-16
ሰኞ፣ ነሐሴ 18
አምላክ ከሰጠው የተስፋ ቃል የተነሳ . . . በእምነት በረታ።—ሮም 4:20
ይሖዋ ለእኛ ኃይል የሚሰጥበት አንዱ መንገድ በሽማግሌዎች አማካኝነት ነው። (ኢሳ. 32:1, 2) እንግዲያው በጭንቀት ስትዋጥ ያሳሰበህን ነገር ለሽማግሌዎች ንገራቸው። ሊረዱህ ሲሞክሩ እርዳታቸውን በአመስጋኝነት ተቀበል። ይሖዋ በእነሱ አማካኝነት ሊያጠነክርህ ይችላል። ገነት በሆነችው ምድር ላይ ወይም በሰማያዊው መንግሥት ውስጥ ለዘላለም የመኖር ተስፋችንም ጥንካሬ ሊሰጠን ይችላል። (ሮም 4:3, 18, 19) ተስፋችን ፈተናዎችን በጽናት እንድንቋቋም፣ ምሥራቹን እንድንሰብክ እንዲሁም በጉባኤ ውስጥ ያሉንን የተለያዩ ኃላፊነቶች እንድንወጣ ጥንካሬ ይሰጠናል። (1 ተሰ. 1:3) ሐዋርያው ጳውሎስንም ያጠነከረው ይኸው ተስፋ ነው። ‘ተደቁሶ፣ ግራ ተጋብቶ፣ ስደት ደርሶበት እንዲሁም በጭንቀት ተውጦ’ ነበር። ይባስ ብሎም ሕይወቱ አደጋ ላይ ወድቋል። (2 ቆሮ. 4:8-10) ጳውሎስ በተስፋው ላይ ትኩረት ማድረጉ ለመጽናት የሚያስችል ጥንካሬ ሰጥቶታል። (2 ቆሮ. 4:16-18) ጳውሎስ በሰማይ ላይ የዘላለም ሕይወት በማግኘት ተስፋው ላይ አተኩሯል። በዚህ ተስፋ ላይ አሰላስሏል። ይህም “ከቀን ወደ ቀን እየታደሰ” እንዲሄድ ረድቶታል። w23.10 15-16 አን. 14-17
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 19
ይሖዋ ለሕዝቡ ብርታት ይሰጣል። ይሖዋ ሰላም በመስጠት ሕዝቡን ይባርካል።—መዝ. 29:11
በምትጸልዩበት ጊዜ ይሖዋ ጥያቄያችሁን የሚመልስበት ጊዜ አሁን መሆን አለመሆኑን አስቡ። ጸሎታችን ወዲያውኑ መመለስ እንዳለበት ይሰማን ይሆናል። ሆኖም መልስ ለመስጠት ከሁሉ የተሻለውን ጊዜ የሚያውቀው ይሖዋ ነው። (ዕብ. 4:16) የጠየቅነውን ነገር ወዲያውኑ ካላገኘን ይሖዋ ‘አይሆንም’ እንዳለን ሊሰማን ይችላል። እንደ እውነቱ ከሆነ ግን የይሖዋ መልስ ‘ትንሽ ጠብቅ’ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ አንድ ወጣት ወንድም ከበሽታው ለመዳን ጸለየ እንበል። ሆኖም የጤንነቱ ሁኔታ አልተሻሻለም። ይሖዋ በተአምር ቢፈውሰው፣ ሰይጣን ይህ ወንድም ይሖዋን ማገልገሉን የቀጠለው ስለተፈወሰ እንደሆነ ይናገር ይሆናል። (ኢዮብ 1:9-11፤ 2:4) በዚያ ላይ ደግሞ ይሖዋ ሁሉንም በሽታ የሚያስወግድበትን ጊዜ ቀጥሯል። (ኢሳ. 33:24፤ ራእይ 21:3, 4) እስከዚያ ግን ተአምራዊ ፈውስ እንደምናገኝ ልንጠብቅ አንችልም። በመሆኑም ይህ ወንድም በሽታውን በጽናት መቋቋምና አምላክን በታማኝነት ማገልገሉን መቀጠል እንዲችል ጥንካሬና የአእምሮ ሰላም ለማግኘት ሊጠይቅ ይችላል። w23.11 24 አን. 13
ረቡዕ፣ ነሐሴ 20
እንደ ኃጢአታችን አላደረገብንም፤ ለበደላችን የሚገባውንም ብድራት አልከፈለንም።—መዝ. 103:10
ሳምሶን ከባድ ስህተት ቢሠራም ተስፋ አልቆረጠም። አምላክ ፍልስጤማውያንን እንዲወጋ የሰጠውን ተልእኮ ለመፈጸም የሚያስችል አጋጣሚ ፈልጓል። (መሳ. 16:28-30) ሳምሶን “እባክህ . . . ፍልስጤማውያንን ልበቀላቸው” በማለት ይሖዋን ለመነው። እውነተኛው አምላክ የሳምሶንን ልመና በመስማት ተአምራዊ በሆነ መንገድ ጥንካሬውን መለሰለት። በመሆኑም ሳምሶን በዚያ ዕለት፣ ከዚያ በፊት ከገደለው ይበልጥ ብዙ ፍልስጤማውያንን መግደል ቻለ። ሳምሶን የሠራው ስህተት ከባድ መዘዝ ቢያስከትልበትም የይሖዋን ፈቃድ ለማድረግ መሞከሩን አላቆመም። እኛም በሠራነው ስህተት የተነሳ ወቀሳ ቢሰጠን ወይም ያለንን መብት ብናጣም እንኳ ተስፋ መቁረጥ አይኖርብንም። ይሖዋ ተስፋ እንደማይቆርጥብን ማስታወስ ይኖርብናል። (መዝ. 103:8, 9) እንደ ሳምሶን ሁሉ እኛም ስህተት ብንሠራም እንኳ ይሖዋ ሊጠቀምብን ይችላል። w23.09 6 አን. 15-16
ሐሙስ፣ ነሐሴ 21
[ጽናት] በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንድናገኝ ያስችለናል፤ ተቀባይነት ማግኘት ደግሞ ተስፋን ያጎናጽፋል።—ሮም 5:4
ከጸናህ በይሖዋ ዘንድ ተቀባይነት ታገኛለህ። ይህ ሲባል ግን ይሖዋ ፈተና ወይም ችግር ስላጋጠመህ ይደሰታል ማለት አይደለም። ይሖዋ የሚደሰተው በአንተ ነው። መጽናታችን የይሖዋን ልብ እንደሚያስደስተው ማወቃችን በጣም የሚያበረታታ ነው! (መዝ. 5:12) አብርሃም ፈተናን በጽናት በመቋቋሙ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘ አስታውስ። ይሖዋ እንደ ወዳጁ አድርጎ ተመልክቶታል፤ ጻድቅ አድርጎም ቆጥሮታል። (ዘፍ. 15:6፤ ሮም 4:13, 22) እኛም እንዲሁ ሊባልልን ይችላል። አምላክ ሞገሱን የሚያሳየን በእሱ አገልግሎት ያከናወንነውን ሥራ ወይም ያለንን መብት መሠረት አድርጎ አይደለም። ሞገስ የሚያሳየን በታማኝነት በመጽናታችን ነው። ደግሞም ዕድሜያችን፣ ያለንበት ሁኔታ ወይም ችሎታችን ምንም ይሁን ምን ሁላችንም መጽናት እንችላለን። በአሁኑ ጊዜ እየደረሰብህ ያለውን መከራ በጽናት እየተቋቋምክ ነው? ከሆነ በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘህ ማወቅህ ሊያጽናናህ ይችላል። በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት እንዳገኘን ማወቃችን ተስፋችንን ሊያጠናክርልን ይችላል። w23.12 11 አን. 13-14
ዓርብ፣ ነሐሴ 22
ወንድ ሁን።—1 ነገ. 2:2
ክርስቲያን ወንዶች ከሌሎች ጋር የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ጥሩ ችሎታ ሊያዳብሩ ይገባል። የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታ ያለው ወንድም ሌሎች ሐሳባቸውንና ስሜታቸውን ሲገልጹ በሚገባ ያዳምጣል፤ ስሜታቸውንም ይረዳላቸዋል። (ምሳሌ 20:5) ሌሎች ሲናገሩ የድምፃቸውን ቃና፣ የፊታቸውን ገጽታ እንዲሁም አካላዊ መግለጫቸውን ማስተዋል ይችላል። ይህን ችሎታ ማዳበር የምትችሉት ከሌሎች ጋር ጊዜ የምታሳልፉ ከሆነ ብቻ ነው። የሐሳብ ልውውጥ የምታደርጉት እንደ ኢሜይል እና የጽሑፍ መልእክት ባሉት የኤሌክትሮኒክ መልእክት መላላኪያ ዘዴዎች ብቻ ከሆነ በአካል የሐሳብ ልውውጥ የማድረግ ችሎታችሁ እየቀነሰ ሊሄድ ይችላል። ስለዚህ ከሌሎች ጋር በአካል ተገናኝታችሁ ማውራት የምትችሉባቸውን አጋጣሚዎች ለመፍጠር ሞክሩ። (2 ዮሐ. 12) የጎለመሰ ክርስቲያን ወንድም ራሱንም ሆነ ቤተሰቡን የማስተዳደር ችሎታም ሊኖረው ይገባል። (1 ጢሞ. 5:8) ሥራ ለማግኘት የሚረዳችሁን ክህሎት ማዳበራችሁ ጠቃሚ ነው። (ሥራ 18:2, 3፤ 20:34፤ ኤፌ. 4:28) በትጋት በመሥራት እንዲሁም የጀመራችሁትን ሥራ በመጨረስ ረገድ ጥሩ ስም ለማትረፍ ጥረት አድርጉ። እንዲህ ካደረጋችሁ ሥራ የማግኘታችሁና ሥራችሁን ይዛችሁ የመቀጠላችሁ አጋጣሚ ሰፊ ይሆናል። w23.12 27 አን. 12-13
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 23
የይሖዋ ቀን የሚመጣው ሌባ በሌሊት በሚመጣበት መንገድ [ነው]።—1 ተሰ. 5:2
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ “የይሖዋ ቀን” የሚለው አገላለጽ ይሖዋ ጠላቶቹ ላይ የሚፈርድበትንና ለሕዝቦቹ መዳን የሚያመጣበትን ወቅት ያመለክታል። በጥንት ዘመን ይሖዋ የፍርድ እርምጃ የወሰደባቸው ጊዜያት ነበሩ። (ኢሳ. 13:1, 6፤ ሕዝ. 13:5፤ ሶፎ. 1:8) በዘመናችን “የይሖዋ ቀን” የሚጀምረው በታላቂቱ ባቢሎን ላይ በሚሰነዘረው ጥቃት ሲሆን የሚደመደመው ደግሞ በአርማጌዶን ጦርነት ነው። ከዚያ “ቀን” ለመትረፍ ከአሁኑ ዝግጅት ማድረግ ይኖርብናል። ኢየሱስ ‘ለታላቁ መከራ’ እንድንዘጋጅ ብቻ ሳይሆን ‘ዝግጁ ሆነን እንድንጠብቅም’ አስተምሮናል። (ማቴ. 24:21፤ ሉቃስ 12:40) ሐዋርያው ጳውሎስ በመንፈስ መሪነት ለተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በጻፈው የመጀመሪያ ደብዳቤ ላይ ክርስቲያኖች ታላቁን የይሖዋን የፍርድ ቀን ዝግጁ ሆነው እንዲጠብቁ ለመርዳት በርካታ ምሳሌዎችን ተጠቅሟል። ጳውሎስ የይሖዋ ቀን ወዲያውኑ እንደማይመጣ ያውቅ ነበር። (2 ተሰ. 2:1-3) ያም ቢሆን ወንድሞቹ የይሖዋ ቀን ነገ የሚመጣ ያህል ተዘጋጅተው እንዲጠብቁ አበረታቷቸዋል። እኛም ይህን ምክር ተግባራዊ ማድረግ እንችላለን። w23.06 8 አን. 1-2
እሁድ፣ ነሐሴ 24
የተወደዳችሁ ወንድሞቼ፣ ጸንታችሁ ቁሙ፤ አትነቃነቁ።—1 ቆሮ. 15:58
በ1970ዎቹ መጨረሻ ቶኪዮ፣ ጃፓን ውስጥ ባለ 60 ፎቅ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ተገነባ። ሕንፃው በከተማዋ ውስጥ በተደጋጋሚ የሚከሰተውን ርዕደ መሬት መቋቋም መቻሉን የተጠራጠሩ ታዛቢዎች ነበሩ። ታዲያ ጸንቶ ለመቆሙ ሚስጥሩ ምንድን ነው? መሐንዲሶች ሕንፃውን የገነቡት ጠንካራ ሆኖም ንዝረትን ውጦ ለማስቀረት የሚያስችል የመለመጥ ባሕርይ እንዲኖረው አድርገው ነው። ክርስቲያኖች ከዚህ ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ ጋር ሊመሳሰሉ ይችላሉ። እንዴት? እንደ ክርስቲያን መጠን ፍንክች አለማለትም ሆነ እንደአስፈላጊነቱ ሐሳብን መቀየር የሚያስፈልገን ጊዜ ይኖራል፤ በዚህ ረገድ ሚዛናችንን መጠበቅ አለብን። አንድ ክርስቲያን የይሖዋን ሕጎችና መሥፈርቶች ከመጠበቅ ጋር በተያያዘ ጽኑና የማይነቃነቅ አቋም ሊኖረው ይገባል። “ለመታዘዝ ዝግጁ” ነው፤ እንዲሁም አቋሙን ለድርድር አያቀርብም። በሌላ በኩል ደግሞ የሚቻል ወይም አስፈላጊ በሚሆንበት ወቅት “ምክንያታዊ” ወይም ለውጥ ለማድረግ ፈቃደኛ መሆን አለበት። (ያዕ. 3:17) በዚህ ረገድ ሚዛኑን መጠበቅን የተማረ ክርስቲያን ወደ የትኛውም ጽንፍ አይሄድም፤ ከልክ በላይ ጥብቅም ልልም አይሆንም። w23.07 14 አን. 1-2
ሰኞ፣ ነሐሴ 25
እሱን አይታችሁት ባታውቁም ትወዱታላችሁ።—1 ጴጥ. 1:8
ኢየሱስ ሰይጣን ዲያብሎስ ያደረሰበትን ፈተና መቋቋም ነበረበት። ሰይጣን፣ ኢየሱስ ለአምላክ ያለውን ታማኝነት እንዲያጓድል ለማድረግ ቀጥተኛ ጥቃት ሰንዝሮበታል። (ማቴ. 4:1-11) ሰይጣን፣ ኢየሱስ ቤዛውን መክፈል እንዳይችል ለማድረግ ሲል ኃጢአት ሊያሠራው ቆርጦ ተነስቶ ነበር። ኢየሱስ ምድራዊ አገልግሎቱን ባከናወነበት ወቅት ሌሎች ፈተናዎችንም በጽናት ተቋቁሟል። ስደት ደርሶበታል፤ ሕይወቱ አደጋ ላይ የወደቀባቸው ጊዜያትም ነበሩ። (ሉቃስ 4:28, 29፤ 13:31) የተከታዮቹን አለፍጽምና መቻል ነበረበት። (ማር. 9:33, 34) ለፍርድ በቀረበበት ወቅት ከፍተኛ ሥቃይና ፌዝ ደርሶበታል። ከዚያም እጅግ በሚያሠቃይና በሚያዋርድ መንገድ ተገደለ። (ዕብ. 12:1-3) የመጨረሻውን ፈተና የተቋቋመው ደግሞ ያለይሖዋ ጥበቃ ብቻውን ነው። (ማቴ. 27:46) በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ ቤዛው ኢየሱስን ትልቅ ዋጋ አስከፍሎታል። ኢየሱስ ለእኛ ሲል ይህን ሁሉ መሥዋዕት በፈቃደኝነት እንደከፈለልን ስናስብ ልባችን ለእሱ ባለን ፍቅር አይሞላም? w24.01 10-11 አን. 7-9
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 26
ችኩሎች ሁሉ . . . ለድህነት ይዳረጋሉ።—ምሳሌ 21:5
ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት ረገድ ትዕግሥት ይረዳናል። ሌሎች በሚናገሩበት ጊዜ በጥሞና እንድናዳምጥ ያግዘናል። (ያዕ. 1:19) በተጨማሪም ትዕግሥት ሰላም ለማስፈን ይረዳናል። ውጥረት ውስጥ በምንሆንበት ጊዜ በችኮላ ምላሽ ከመስጠትና ደግነት የጎደለው ነገር ከመናገር ይጠብቀናል። በተጨማሪም ትዕግሥተኛ ከሆንን አንድ ሰው ስሜታችንን ሲጎዳን ለቁጣ የዘገየን እንሆናለን። አጸፋ ከመመለስ ይልቅ ‘እርስ በርስ መቻቻላችንንና በነፃ ይቅር መባባላችንን እንቀጥላለን።’ (ቆላ. 3:12, 13) ትዕግሥት ጥሩ ውሳኔ ለማድረግም ይረዳናል። በችኮላ ወይም በስሜት ተነድተን ከመወሰን ይልቅ ያሉንን አማራጮች በተመለከተ ጊዜ ወስደን ምርምር እናደርጋለን፤ እንዲሁም የተሻለው አማራጭ የትኛው እንደሆነ እንገመግማለን። ለምሳሌ ሥራ እየፈለግን ከሆነ ያገኘነውን የመጀመሪያ ሥራ ለመቀጠር እንፈተን ይሆናል። ትዕግሥተኛ ከሆንን ግን ሥራው በቤተሰባችንና በመንፈሳዊነታችን ላይ ስለሚያሳድረው ተጽዕኖ ጊዜ ወስደን እናስባለን። ትዕግሥተኛ መሆናችን መጥፎ ውሳኔ ከማድረግ ሊጠብቀን ይችላል። w23.08 22 አን. 8-9
ረቡዕ፣ ነሐሴ 27
በሰውነቴ ውስጥ . . . ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በሰውነቴ ውስጥ ላለው የኃጢአት ሕግ ምርኮኛ አድርጎ የሚሰጠኝን ሌላ ሕግ አያለሁ።—ሮም 7:23
የኃጢአት ዝንባሌ ያለህ መሆኑ ተስፋ ካስቆረጠህ ራስህን ለይሖዋ በወሰንክበት ወቅት ለእሱ በገባኸው ቃል ላይ ማሰላሰልህ ፈተናን ለመቋቋም ያለህን ቁርጠኝነት ያጠናክረዋል። እንዴት? ራስህን ለይሖዋ ስትወስን ራስህን ትክዳለህ። ይህም ሲባል ይሖዋን የሚያሳዝኑ ፍላጎቶችንና ምኞቶችን እንቢ ትላለህ ማለት ነው። (ማቴ. 16:24) ስለዚህ ፈተና ሲያጋጥምህ ‘ምን ላድርግ?’ የሚለውን ለመወሰን ብዙ ጊዜ ማጥፋት አያስፈልግህም። ያለው አማራጭ አንድና አንድ ብቻ፣ ይኸውም ለይሖዋ ያለህን ታማኝነት መጠበቅ እንደሆነ አስቀድመህ ወስነሃል። ይሖዋን ለማስደሰት ያደረግከውን ቁርጥ ውሳኔ ይዘህ ትቀጥላለህ። እንደ ኢዮብ ትሆናለህ ሊባል ይችላል። ኢዮብ በጣም ከባድ መከራ ቢደርስበትም “ንጹሕ አቋሜን አላጎድፍም!” በማለት ቁርጥ አቋሙን ገልጿል።—ኢዮብ 27:5፤ w24.03 9 አን. 6-7
ሐሙስ፣ ነሐሴ 28
ይሖዋ ለሚጠሩት ሁሉ፣ በእውነት ለሚጠሩት ሁሉ ቅርብ ነው።—መዝ. 145:18
‘የፍቅር አምላክ’ የሆነው ይሖዋ ከእኛ ጋር ነው! (2 ቆሮ. 13:11) በግለሰብ ደረጃ ትኩረት ይሰጠናል። ‘ታማኝ ፍቅሩ እንደከበበን’ እርግጠኞች ነን። (መዝ. 32:10) ይሖዋ ፍቅሩን ያሳየን እንዴት እንደሆነ ይበልጥ ባሰላሰልን መጠን እሱ ይበልጥ እውን ይሆንልናል፤ እንዲሁም ይበልጥ ወደ እሱ እንቀርባለን። በነፃነት ልናነጋግረውና ፍቅሩ ምን ያህል እንደሚያስፈልገን ልንነግረው እንችላለን። ይሖዋ ስሜታችንን እንደሚረዳልንና ሊረዳን እንደሚጓጓ በመተማመን የሚያሳስበንን ነገር ሁሉ ልናካፍለው እንችላለን። (መዝ. 145:19) ብርድ በሆነ ቀን የተቀጣጠለ እሳት እንደሚስበን ሁሉ የይሖዋ ፍቅርም ወደ እሱ እንድንቀርብ ያነሳሳናል። የይሖዋ ፍቅር ታላቅና ማራኪ ነው። እንግዲያው የይሖዋን ፍቅር አጣጥም። ሁላችንም ‘ይሖዋን እወደዋለሁ’ በማለት ለፍቅሩ ምላሽ እንስጥ!—መዝ. 116:1፤ w24.01 31 አን. 19-20
ዓርብ፣ ነሐሴ 29
ስምህን አሳውቄአቸዋለሁ።—ዮሐ. 17:26
ኢየሱስ ለሰዎች የአምላክ ስም ይሖዋ መሆኑን ከማሳወቅ ያለፈ ነገር አድርጓል። ኢየሱስ ያስተማራቸው አይሁዳውያን ቀድሞውንም የአምላክን ስም ያውቃሉ። ሆኖም ኢየሱስ ግንባር ቀደም ሆኖ ስለ እሱ ‘ገልጿል።’ (ዮሐ. 1:17, 18) ለምሳሌ የዕብራይስጥ ቅዱሳን መጻሕፍት ይሖዋ መሐሪና ሩኅሩኅ እንደሆነ ይናገራሉ። (ዘፀ. 34:5-7) ኢየሱስ ስለ አባካኙ ልጅና ስለ አባቱ የሚገልጸውን ምሳሌ በተናገረበት ወቅት ይህንን እውነት ይበልጥ ግልጽ አድርጎታል። አባትየው ንስሐ የገባውን ልጁን ‘ገና ሩቅ ሳለ እንዳየው፣’ ሮጦ ሄዶ እንደተቀበለው፣ እንዳቀፈው እንዲሁም በሙሉ ልቡ ይቅር እንዳለው ስናነብ የይሖዋ ምሕረትና ርኅራኄ ግልጽ ሆኖ ይታየናል። (ሉቃስ 15:11-32) በእርግጥም ኢየሱስ የአባቱን እውነተኛ ማንነት ገልጦልናል። w24.02 10 አን. 8-9
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 30
ከአምላክ በምናገኘው መጽናኛ [ሰዎችን እናጽናና]።—2 ቆሮ. 1:4
ይሖዋ የተጨነቁ ሰዎችን ያጽናናል። ለሌሎች በመራራትና እነሱን በማጽናናት ይሖዋን መምሰል የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ የምንችልበት አንዱ መንገድ ማጽናኛ ለመስጠት የሚያነሳሱ ባሕርያትን በልባችን ውስጥ በማዳበር ነው። ከእነዚህ ባሕርያት መካከል አንዳንዶቹ የትኞቹ ናቸው? ‘ሁልጊዜ እርስ በርስ ለመጽናናት’ የሚያነሳሳ ፍቅር እንዲኖረን ምን ይረዳናል? (1 ተሰ. 4:18) የሌላውን ስሜት መረዳት እንዲሁም የወንድማማች መዋደድንና ደግነትን የመሳሰሉ ባሕርያትን ማዳበር ይኖርብናል። (ቆላ. 3:12፤ 1 ጴጥ. 3:8) እነዚህ ባሕርያት የሚረዱን እንዴት ነው? ርኅራኄ እና ተመሳሳይ ባሕርያት የማንነታችን ክፍል ከሆኑ የተጨነቁ ሰዎችን እንድናጽናና ውስጣችን ይገፋፋናል። ኢየሱስ እንዳለው “አንደበት የሚናገረው በልብ ውስጥ የሞላውን ነውና። ጥሩ ሰው በልቡ ካከማቸው መልካም ነገር ጥሩ ነገር ያወጣል።” (ማቴ. 12:34, 35) በእርግጥም እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ወንድሞቻችንን እና እህቶቻችንን ማጽናናት ለእነሱ ያለንን ፍቅር የምንገልጽበት ወሳኝ መንገድ ነው። w23.11 10 አን. 10-11
እሁድ፣ ነሐሴ 31
ጥልቅ ማስተዋል ያላቸው . . . ይረዱታል።—ዳን. 12:10
የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች መረዳት ከፈለግን እርዳታ መጠየቅ ይኖርብናል። አንድ ምሳሌ እንመልከት። ጨርሶ የማታውቀውን ቦታ ለመጎብኘት አስበሃል እንበል። ሆኖም አብሮህ የሚጓዘው ጓደኛህ አካባቢውን በደንብ ያውቀዋል። የት እንዳላችሁ እንዲሁም እያንዳንዱ መንገድ ወዴት እንደሚያመራ ጠንቅቆ ያውቃል። ጓደኛህ አብሮህ ለመምጣት በመስማማቱ በጣም እንደምትደሰት ጥያቄ የለውም። በተመሳሳይም ይሖዋ በጊዜ ሰሌዳ ላይ የቱ ጋ እንዳለን እንዲሁም ወደፊት ምን እንደሚጠብቀን ያውቃል። በመሆኑም የመጽሐፍ ቅዱስን ትንቢቶች መረዳት ከፈለግን ይሖዋ እንዲረዳን በትሕትና ልንጠይቀው ይገባል። (ዳን. 2:28፤ 2 ጴጥ. 1:19, 20) እንደ ማንኛውም ጥሩ ወላጅ፣ ይሖዋ ልጆቹ ወደፊት ደስተኛ ሕይወት እንዲመሩ ይፈልጋል። (ኤር. 29:11) ሆኖም ከሰብዓዊ ወላጆች በተለየ መልኩ ይሖዋ ስለ ወደፊቱ ጊዜ በትክክል ትንቢት መናገር ይችላል። ወሳኝ የሆኑ ክንውኖች ከመከሰታቸው በፊት እንድናውቅ ሲል ትንቢቶች በቃሉ ውስጥ እንዲሰፍሩ አድርጓል።—ኢሳ. 46:10፤ w23.08 8 አን. 3-4