የመጨረሻው ፍርድ
“ስትሞት ነፍስህ ብቻዋን ትሰቃያለች። ለሷ ሲኦሏ ያ ነው። ይሁን እንጂ በፍርድ ቀን ሰውነትህ ከነፍስህ ጋር ትገናኝና ያኔ እጥፍ ሲኦል ያገኝሃል። ነፍስህን የደም ነጠብጣብ ሲያልባት ሰውነትህ ደግሞ በጭንቀትና ስቃይ ይዋጣል።”
የ19ኛው መቶ ዘመን ሰባኪ የነበሩት ሲ ኤች እስፕርጀን ቀሳውስት ስለ ፍርድ ቀንና የተኰነኑ ሰዎች ስለሚደርስባቸው ስቃይ ያላቸውን አመለካከት የገለጹት ከላይ እንደተጠቀሰው በማለት ነበር። ጣሊያናዊው ሰዓሊ ማይክል አንጀሎም በሮም ውስጥ በሲስቲን ጸሎት ቤት ግድግዳ ላይ በተሳለው (በከፊል እዚህ ገጽ ላይ የሚታየው) ሥዕል ላይ እንደሚታየው ተመሳሳይ የሆነ አስፈሪ እምነት ነበረው። ዘ ኒው ኢንሳይክሎፔዲያ ብሪታኒካ ስለዚህ ሥዕል ሲያትት እንዲህ ይላል፦ “በፍርድ ላይ የሚቀመጠው ክርስቶስ ክርስቲያናዊ መድኃኒት (አዳኝ) ሳይሆን በነጐድጓድ ዓይነት ድምጽ የሚናገር ኃያል አምላክና የተባረኩ ወይም የጸደቁ ነፍሳትን ወደሰማይ ከመጋበዝ ይልቅ የሰው ዘሮችን ስለ መኮነን ይበልጥ አጥብቆ የሚያስብ ነው።”
የሕዝበ ክርስትና መሠረተ ትምህርት
ባለፉት መቶ ዓመታት የፍርድ ቀንና የሲኦል እሳት ተወዳጅ የስብከት ርዕሶች ሆነው ቆይተዋል። እንደ ሲ ኤች እስፐርጀን ያሉት ሰባኪዎች ከስብከት መድረኰቻቸው ላይ በመሆን ኃጢአተኞችን ስለሚጠብቃቸው አሰቃቂ ሥቃይ እንደ ነጎድጓድ እየጮሁ ይናገሩ ነበር። በዛሬው ጊዜ ያን ዓይነት ስብከት የሚሰማው አልፎ አልፎ ብቻ ነው። ይሁን እንጂ አሁንም ቢሆን የሲኦል እሳትና የመጨረሻው ፍርድ ብዙዎቹ አብያተ ክርስቲያናት በይፋ የሚያስተምሩአቸው ትምህርቶች ናቸው።
አብዛኞቹ የሕዝበ ክርስትና ሃይማኖቶች ይብዛ ይነስ እንጂ የአምላክ ፍርዶች በሁለት ደረጃዎች እንደሚፈጸሙ ከምታስተምረው ከሮማ ካቶሊክ ቤተክርስቲያን ትምህርት ጋር ይስማማሉ። የመጀመሪያው ደረጃ “ውስን ፍርድ” ነው። ሰውዬው በሚሞትበት ጊዜ የማትሞት ናት የምትባለው ነፍሱ ወዲያውኑ ትፈረድና በሲኦል ውስጥ ወይም በሰማይ ተወስና ለዘላለም እንድትኖር ትደረጋለች።a ከዚህ በኋላ ደግሞ በዘመኑ ፍጻሜ የሙታኑ ሰውነቶች ተነስተው ከማይሞቱ ነፍሶቻቸው ጋር የሚዋሃዱበት የመጨረሻው ወይም አጠቃላዩ ፍርድ ይመጣል።
በዚህ የፍርድ ቀን በሰማይ ያሉ ነፍሳት እዚያው ይቆዩና ያለመሞትን ባሕርይ ከወረሱት አካሎቻቸው ጋር ይዋሃዳሉ። በሲኦል የሚሰቃዩትም ነፍሳት እዚያው ይቆዩና በተመሳሳይ ያለመሞት ባሕርይ ከተሰጣቸው ሥጋዎቻቸው ጋር ይዋሃዳሉ። አንዳንዶች እንደሚሉት ይህ (የነፍስና የሥጋ መዋሃድ) ሥቃያቸውን ይበልጥ ያባብሰዋል። እስከ መጨረሻው ፍርድ ቀን ድረስ በሕይወት የሚቆዩት አይሞቱም። በሕይወት እንዳሉ ይፈረዱና “ሥጋቸውም ሆነ ነፍሳቸው” በአንድነት በቀጥታ ወደ ሰማይ ወይም ወደ ሲኦል ይወሰዳል።
በሲኦል እሳት ውስጥ ሊገለጽ የማይቻል ሥቃይ ያጋጥማል የሚለው እምነት በኢየሱስ ክርስቶስ እጅ የሚደረገውን መላውን የመጨረሻ ፍርድ ርዕሰ ጉዳይ ለማሰብ የሚያስፈራ ጉዳይ አድርጎታል። ይሁን እንጂ የአምላክ ፍርድ ከዚህ የተለየና በአብዛኛው የሚያስደስት የፍርድ ቀንም ቢሆን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ከታዩት ጊዜያት ሁሉ ይበልጥ እጅግ አስደሳች ጊዜ እንደሚሆን ብታውቅ በጣም ይገርምህ ይሆናል። ይሁን እንጂ እንዴት እንዲህ ሊሆን ይችላል?
[የግርጌ ማስታወሻ]
a (የሮማ ካቶሊኮች ሦስተኛ አማራጭ ማለትም ነፍስ በመጨረሻ ወደ ሰማይ ከመግባቷ በፊት ጊዜያዊ ቅጣት የምታሳልፍበት መንጽሔ የሚባል ቦታም አለ ብለው ያምናሉ)
[በገጽ 3 ላይ የሚገኝ የሥዕል ምንጭ]
Random/Sipa Icono