“ይሖዋን ለማክበር አሁን ከምታደርገው የበለጠ መሥራት ትችላለህን?
1 ይህ ሁላችንም ልናስብበት የሚገባን በጣም አስፈላጊ ጥያቄ ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመምሰል በታማኝነት የምንጥር ሰዎች እንደመሆናችን መጠን የአምላካችንን ስም ለሕዝብ በመግለጽ እርሱን እናከብራለን። የአምላክን ሞገስ ለማግኘት የምንፈልግ ከሆነ ይህ ልንወጣው የሚገባን ኃላፊነት ነው። (ማር. 13:10፤ ሉቃስ 4:18፤ ሥራ 4:20፤ ዕብ. 13:15) አዎን፤ ይህንን ምሥራች ወደፊት የይሖዋ ጽንፈ ዓለማዊ በረት ክፍል ሊሆኑ ወደሚችሉ ቀሪ “በጎች” ማድረስ በቃላት መግለጽ የማይቻል እንዴት ያለ መብትና ክብር ነው! — ዮሐ. 10:16
2 በአገልግሎቱ የምታደርጉትን እንቅስቃሴ በመጨመር አንተና ልጆችህ ከአሁኑ የበለጠ ይሖዋን ለማስከበር ትችላላችሁን? እየጨመረ የሚሄድ ቁጥር ያላቸው በዓለም ዙሪያ ያሉ ወንድሞችህና እህቶችህ ወደ አቅኚነት አገልግሎት እየገቡ ናቸው። በምሥራቅ አፍሪካ በሚያዝያ ወር 1992 በጠቅላላው 5,651 የሚሆኑ ወንድሞችና እህቶች በልዩ፣ በዘወትር ወይም በረዳት አቅኚነት አገልግሎት ውስጥ ነበሩ። አቅኚነትን በሚመለከት በግልህ በቁም ነገር አስበህበት ታውቃለህን? ልጆችህ የሙሉ ጊዜ አገልጋይነትን እንደ ቋሚ ሥራቸው አድርገው እንዲከታተሉ ታበረታታቸዋለህን?
3 ለአቅኚነቱ አገልግሎት ያለህን የግል ስሜት ለምን አትመረምርም? ጉዳዩ በተነሳበት ጊዜ ሁሉ ያለህበት ሁኔታ አቅኚ ሆነህ ለማገልግል እንደማያስችልህ አድርገህ ብቻ በቶሎ ትደመድማለህን? ሁሉም ሰው አቅኚ ሊሆን የሚችል አለመሆኑ እውነት ነው። መንፈሳዊ ኃላፊነቶችና ሌሎች ዕንቅፋቶች ብዙዎች የሙሉ ጊዜ አገልጋይ እንዳይሆኑ ያግዷቸዋል። (1 ጢሞ. 5:8) ነገር ግን በቅርቡ ጉዳዩን በጸሎት አስበህበታልን? ከቤተሰባችሁ ቢያንስ አንዱ አቅኚ ሊሆን ይችል እንደሆነ ነገሩን በቤተሰብ ደረጃ ተወያይታችሁበታልን? የኅዳር 15, 1982 የመጠበቂያ ግንብ እትም በገጽ 23 ላይ እንዲህ የሚል አእምሮን የሚቀሰቅስ ሐሳብ ገልጾ ነበር:- “በእርግጥ እያንዳንዱ ክርስቲያን አገልጋይ አቅኚ መሆን ይችል ወይም አይችል እንደሆነ በጸሎት ሊያስብበት ይገባል። ለአሥራ አምስት ዓመታት በአቅኚነት ያገለገሉ ደቡብ አፍሪካውያን ባልና ሚስት እንዲህ አሉ:- ‘በአቅኚነት የምናገለግለው ለምንድን ነው? አቅኚ ባንሆን ኖሮ በይሖዋ ፊት በቂ ምክንያት ለማቅረብ እንችል ነበርን?’ አቅኚዎች ያልሆኑ ብዙ ክርስቲያኖች ‘በእርግጥ አቅኚ ላለመሆኔ በይሖዋ ፊት ትክክለኛ ምክንያት ማቅረብ እችላለሁን?’ ብለው ከዚህ ጋር ተቀራራቢ የሆነ ጥያቄ ሊጠይቁ ይችላሉ።”
4 በዚህ ጉዳይ ላይ የቀረበ ሌላ የመጠበቂያ ግንብ ርዕሰ ትምህርት ቀጥሎ ያለውን ኃይለኛ ነጥብ አቅርቦ ነበር:- “እያንዳንዳችን ለራሳችን እውነተኞች መሆን ይኖርብናል። ‘መንፈስስ ፈቃደኛ ነው፣ ሥጋ ግን ደካማ ነው’ ትላላችሁን? ግን መንፈሱ በእርግጥ ፈቃደኛ ነውን? የሥጋን ድካም ለመንፈሱ ፈቃደኛ አለመሆን ሽፋን አድርገን አንጠቀምበት።” — የእንግሊዝኛ መግ 78 8/15 ገጽ 23
5 ልጆቻቸው የተሳካላቸው እንዲሆኑ የሚፈልጉ ወላጆች፦ ምሳሌ 15:20 “ጠቢብ ልጅ አባቱን ደስ ያሰኛል” በማለት ያረጋግጥልናል። አምላካዊ የሆኑ ወላጆች ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸው ጉልበታቸውን ለይሖዋ አምላክ አገልግሎት ወስነው ሲጓዙ በማየት እንደሚደሰቱ አያጠያይቅም። ይሁን እንጂ ልጆቻችሁ በደመ ነፍስ የጥበብን መንገድ አይመርጡም። ይህ ዓለም ስሜትን የሚስብባቸው ነገሮች በጣም ኃይለኞች ናቸው። ልጆቻችሁ ለነገሮች የሚሰጡት ግምት የሚቀረጸው በአብዛኛው በእናንተ በወላጆች ሁኔታ ነው። ስለ ሙሉ ጊዜ አገልግሎት ጥቅሞች ሁልጊዜ አዎንታዊ ሐሳብ የምትናገሩ ከሆናችሁ፣ ወጣት ልጆቻችሁ ከታማኝ አቅኚዎች ጋር እንዲቀራረቡ የምታበረታቷቸው ከሆነ እንዲሁም ልጆቻችሁ ሊይዟቸው ከሚችሏቸው ሥራዎች ሁሉ የበለጠ ክብር ያለው ሥራ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መሆኑን ከልብ የምታምኑበት ከሆነ፣ ይህ ዓይነቱ ይሆናል የሚል አመለካከት በልጆቻችሁ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንደሚኖረው ምንም አያጠራጥርም። በሰው ዘንድ ሳይሆን በይሖዋ ዘንድ መልካም ስም የማትረፍን ዋጋማነት ከፍ አድርገው እንዲመለከቱት እርዷቸው።
6 ወጣቶች ሆይ፤ ምሳሌ 22:1 “መልካም ስም ከብዙ ባለጠግነት ይሻላል፣ መልካምም ሞገስ ከብርና ከወርቅ ይበልጣል” በማለት እናንተ ልትወስዱት የሚገባችሁን ምርጫ ያጎላል። ለራሳችሁ ምን ዓይነት ስም ታስመዘግቡ ይሆን? ጉልበታቸውን ለአምላክ አገልግሎት በመወሰን በአምላክ ዘንድ ጥሩ ስም ያተረፉትን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ታሪካቸውን የምናነባቸውን ወንዶችና ሴቶች አስቡ። ተወዳጁ ሐኪም ሉቃስ እንዲሁም ከእውነተኛው አምላክ ጋር የሄደው ሄኖክ አሉ። ሳሙኤልም ገና በለጋ ዕድሜው በይሖዋ ቤተ መቅደስ ውስጥ ማገልገል በመጀመሩ ተወዳዳሪ የማይገኝለትን ሥልጠና አግኝቷል። እነዚህ ታማኝ አገልጋዮች ባደረጉት ምርጫ ተቆጭተው ያውቃሉ ብላችሁ ታስባላችሁ? ለምን ይቆጫሉ? ሁሉም ደስተኛ፣ ውጤታማና ስሜትን የሚቀሰቅስ ሕይወት አሳልፈዋል። በይሖዋም ዘንድ ዘላቂ ሞገስ አግኝተዋል! — መዝ. 110:3 አዓት፤ 148:12, 13፤ ምሳሌ 20:29፤ 1 ጢሞ. 4:8
7 ልጆች ሕይወታቸው የተሳካ መሥመር ሲይዝ ወላጆቻቸው ኩራት ይሰማቸዋል። እነዚህን ‘ከይሖዋ የተገኙ ውርሻዎች’ ለማሰልጠን፣ ለመገሠጽና ለማስተማር ያወጡት ወጪ ብዙ ጊዜ እጥፍ ሆኖ ይመለስላቸዋል። (መዝ. 127:3) ይሖዋን ለማክበር የተቻለውን ወይም የተቻላትን ሁሉ ከሚያደርግ ወይም ከምታደርግ ልጅ የበለጠ ማንኛውንም ወላጅ የሚያኮራ ምን ነገር ሊኖር ይችላል? አንድ ደብዳቤ እንደሚያሳየው በዘመናችን ያሉ ብዙ ወጣቶች የሉቃስን፣ የሄኖክንና የሳሙኤልን ፈለግ በመከተል ላይ ናቸው። “16 ዓመቴ ነው። ከተጠመቅሁ ከዘጠኝ ወራት በኋላ . . . የዘወትር አቅኚነት አገልግሎትን ጀመርኩ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ከይሖዋ ብዙ በረከቶችን በማግኘት ላይ ነኝ። . . . አቅኚነት በትምህርት ቤትም ጭምር የሚረዳ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በፊት ምስክር በመሆኔ ምክንያት የክፍል ጓደኞቼ ያሾፉብኝ ነበር። አሁን በጣም ብዙ የግል ጥናት ስለማደርግ ‘ለሚሰድቡኝ መልስ ለመስጠት’ ችያለሁ።”
8 አንድን ሰው በአገልግሎቱ ለማስታጠቅ የሚረዳ ትምህርት፦ በዚህ ነጥብ ላይ የዓለማዊ ትምህርትን ጉዳይ ልንመለከት እንችላለን። ይህ ጉዳይ ሚዛናዊ አመለካከት ይበልጥ የሚያስፈልግበት ነው። የኅዳር 1, 1992 መጠበቂያ ግንብ “ትምህርትን በዓላማ መከታተል” የሚል ርዕሰ ትምህርት አውጥቶ ነበር። “በቂ ትምህርት ማግኘት” በሚለው ንዑስ ርዕስ ሥር እንዲህ የሚል ነጥብ ነበረው:- “ክርስቲያኖች የሙሉ ጊዜ አቅኚ አገልጋዮች ቢሆኑም እንኳን ራሳቸውን ችለው ለመኖር መቻል አለባቸው። (2 ተሰሎንቄ 3:10–12) . . . አንድ ወጣት ክርስቲያን እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ሥርዓቶች ለማክበርና ክርስቲያናዊ ግዴታዎቹን ለመወጣት እንዲችል እስከምን ድረስ መማር ያስፈልገዋል? . . . የምሥራቹ አቅኚ አገልጋዮች ለመሆን ለሚፈልጉት “አጥጋቢ” የሚባለው [ደሞዝ] ምን ያህል ነው? . . . እንዲህ ያሉት በአጠቃላይ በወንድሞቻቸው ወይም በቤተሰባቸው ላይ “እንዳይከብዱባቸው” የትርፍ ሰዓት ሥራ ያስፈልጋቸዋል። — 1 ተሰሎንቄ 2:9”
9 ወደፊት አቅኚ ለመሆን በመዘጋጀት ላይ ያለው ሰው የሙሉ ጊዜ አገልግሎትን ለመከታተል እንዲረዳው ተጨማሪ ትምህርት ማግኘቱ አስፈላጊ መስሎ ከታየ የኅዳር 1, 1992 መጠበቂያ ግንብ እንደሚከተለው በማለት ሐሳብ ያቀርባል:- “አንድ ወጣት ምስክር . . . የተለመደ ክርስቲያናዊ የጥናት ልማዱን፣ በስብሰባዎች መካፈልና የስብከት ሥራውን ለማከናወን ይችል ዘንድ ከቤተሰቦቹ ሳይለይ ቢከታተለው የተሻለ ይሆናል።”
10 ምንም እንኳን ልቡ በአቅኚነት አገልግሎት ላይ ቢሆንም ወደ አንድ የንግድ ሞያ ትምህርት ቤት መግባት ስላስፈለገው የ22 ዓመት ወጣት የሚገልጽ አንድ ተሞክሮ ከአፍሪካ መጥቷል። ወጣቱ በንግድ ሞያ ትምህርት ቤት ውስጥ እያለ ረዳት አቅኚ ሆነ። የዕድሜ እኩዮቹ ፈተናውን እንደሚወድቅ የተረጋገጠ ነገር ነው እያሉ ይስቁበት ነበር። የእርሱ መልስ ግን ሁልጊዜ “አስቀድማችሁ የእግዚአብሔርን መንግሥት ጽድቁንም ፈልጉ” የሚል ነበር። ራስን መገሠጽን በመልመድ በየዕለቱ በማለዳ ይነሳና ለሁለት ሰዓት ያህል ለትምህርቱ ዝግጅት ያደርጋል። ከዚያም ከሰዓት በኋላ ትምህርት ሲያበቃ በመስክ አገልግሎቱ ይካፈላል። ትምህርት ቤቱ በሚያዘጋጀው ልዩ የሽልማት ዝግጅት ላይ የሚቀርቡ ሦስት ተማሪዎችን ለመምረጥ ሲባል በቀረበው ልዩ ፈተና እርሱ የሦስተኝነትን ደረጃ ሲይዝ ተማሪዎቹ በሙሉ ክው አሉ። ሁለተኛ የወጣው ልጅ ከአቅኚው ወንድማችን ጋር ትምህርት ቤት ውስጥ መጽሐፍ ቅዱስን የሚያጠና ፍላጎት ያሳየ ልጅ ነበር። አንደኛ የወጣው ደግሞ በትምህርት ቤት ውስጥ ያለ ሌላ ቀናተኛ ምስክር ነበር።
11 ሽማግሌዎች ድርሻቸውን ያበረክታሉ፦ አቅኚዎች በሚሠሩት ሥራ ኩራት የሚሰማቸው የጉባኤ ሽማግሌዎች ቀናተኛ ለሆኑት ለእነዚህ አገልጋዮች ትልቅ ማበረታቻ ይሰጧቸዋል። ሽማግሌዎች እንደዚህ የሚያደርጉት ጠንክረው የሚሠሩ ውጤታማ አቅኚዎች ለጉባኤው በረከት እንደሆኑ ስለሚያውቁ ነው። በዘወትር አቅኚነት አገልግሎት አንድ ዓመት ወይም ከዚያ በላይ ካሳለፉ በኋላ በአቅኚነት አገልግሎት ትምህርት ቤት ውስጥ ተጨማሪ ሥልጠና ለማግኘት ብቁዎች ይሆናሉ። ኮርሱ የአቅኚዎችን ውጤታማነት ለማሻሻል ጠቃሚ መሣሪያ መሆኑን አስመስክሯል። ምንም እንኳን አቅኚዎች በሥራው ግንባር ቀደም ሆነው ቢሰለፉም ፍቅራዊ ማበረታቻ ያስፈልጋቸዋል። ሽማግሌዎች ደግሞ ይህንን አስፈላጊ ነገር ለማሟላት ንቁ መሆን ይኖርባቸዋል። — 1 ጴጥ. 5:1–3
12 ሽማግሌዎች ለአቅኚነቱ ሥራ ማነቃቂያ ሊሰጡ የሚችሉት እንዴት ነው? እዚህ መብት ላይ ለመድረስ የሚችሉት እነማን መሆናቸውን በየወቅቱ መገምገም ጥሩ መነሻ ይሆናል። ሽማግሌዎች አቅኚ ለመሆን አመቺ ሁኔታ ያላቸው የሚመስሉትን ለምሳሌ ረዳት አቅኚ ሆነው አዘውትረው የሚያገለግሉትን፣ ጡረታ የወጡ ሰዎችን፣ የቤት እመቤቶችንና ተማሪዎችን በግል ቀርበው ማነጋገር ይችላሉ። ማንም ሰው አቅኚ እንዲሆን እንደተገደደ እንዲሰማው ሊደረግ አይገባም። ነገር ግን አቅኚ ለመሆን ፍላጎቱ እያላቸው በማመንታት ላይ ያሉት ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ትንሽ ማበረታቻ ቢያገኙ አቅኚነት ሊደርሱበት የሚችሉት ነገር እንደሆነ ሊታያቸው ይችላል።
13 ሽማግሌዎች ለአቅኚነት አገልግሎት ሊያመለክቱ ለሚፈልጉ ሰዎች ማበረታቻ በሚሰጡበት ጊዜ አመልካቹ የዘወትር አቅኚ ለመሆን ከመመዝገቡ በፊት በረዳት አቅኚነት ሥራ በርካታ ወራት ማሳለፍ እንደማያስፈልገው በአእምሮአቸው መያዝ ይኖርባቸዋል። (የመአ 9–68 አባሪ አንቀጽ 24–26) እርግጥ ሽማግሌዎች አመልካቹ የሚፈለግበትን ሰዓት ለማሟላት በሚችልበት ሁኔታ ላይ መሆኑን ለማረጋገጥ ምክንያታዊ ግምት መውሰዳቸው አይቀርም።
14 ማመልከቻው በጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ ውይይት ከተደረገበትና ጥያቄዎቹ በሙሉ መመለሳቸውን ለማረጋገጥ ሲባል በጸሐፊው አማካኝነት በጥንቃቄ ከተጣራ በኋላ ወዲያውኑ ለማኅበር መላክ ይገባዋል።
15 አቅኚዎቹ ማንኛውም ችግር አጋጥሟቸው ከሆነ ጸሐፊው ለሽማግሌዎች ዘወትር ማሳወቅ ይኖርበታል። በተለይ ብዙ አቅኚዎች ባሏቸው ጉባኤዎች ውስጥ ይህን ማድረጉ በጣም አስፈላጊ ነው። በጉባኤዎች አናሊስስ ሪፖርት (S-10-AM) ላይ እንደሚጠየቀው ጸሐፊው በአገልግሎቱ ዓመት ማብቂያ ላይ የአቅኚዎችን አገልግሎት ከመመርመሩም በተጨማሪ የሚፈለግበትን ሰዓት ለማሟላት ሳይችል የቀረው እንዲሁም በግል ትኩረት ሊሰጠው የሚያስፈልገው ማን እንደሆነ አብረው ለማየት እንዲችሉ በመጋቢት መጀመሪያ ላይ የአገልግሎት የበላይ ተመልካቹ ከእርሱ ጋር እንዲገናኝ መጠየቅ ይኖርበታል። (በየካቲት 1993 የመንግሥት አገልግሎታችን ላይ የወጡትን ማስታወቂያዎች ተመልከት።) ሳይዘገይ እርዳታ ከተደረገለት አቅኚው የአገልግሎቱን ዓመት በተሳካ ሁኔታ ለመጨረስ ይችል ይሆናል።
16 ከአዲሶቹ አቅኚዎች መካከል በዕድሜ ወጣቶች የሆኑና ከሌሎቹ አንፃር ሲታዩ በእውነት ውስጥ አዲሶች የሆኑት ቁጥራቸው ከፍተኛ ነው። የፈቃደኝነት መንፈሳቸው በእርግጥም ደስ ያሰኘናል! እነዚህ አዲሶች ግን ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው ሥራ ችሎታ እንዲያዳብሩ፣ ውጤታማ ተመላልሶ መጠየቆችን እንዲያደርጉና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን በትክክል ለማስተማር እንዲችሉ አሁንም ቢሆን ሥልጠና ያስፈልጋቸዋል። ይህን ሥልጠና ካላገኙ አዲሶቹ አቅኚዎች ከአንድ ዓመት ወይም ከዚያ ትንሽ በለጥ ከሚል ጊዜ በኋላ በአገልግሎታቸው ጥሩ ውጤት ባለማግኘታቸው ምክንያት ተስፋ ቆርጠው በመጨረሻው የአቅኝነት አገልግሎታቸውን ሊያቋርጡ ይችላሉ። ንቁ የሆኑ ሽማግሌዎች አቅኚዎች ላይ ጥቃቅን ችግሮችን ለማየት ወይም በእንቅስቃሴያቸው የሚያሳዩትን ድካም ለመከታተል መቻል ይኖርባቸው ይሆናል። አቅኚው ወዲያውኑ ትኩረት ተሰጥቶት እርዳታ ከተደረገለት ውጤታማ አገልግሎት ያለባቸውን ብዙ ዓመታት በደስታ ሊያሳልፍ ይችላል።
17 ራቅ ባሉ ውኃዎች ውስጥ ዓሣ ልታጠምድ ትችላለህን? አንዳንዶቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ዓሣ አጥማጆች ነበሩ። አንዳንድ ጊዜ ሌሊቱን ሙሉ ሲያጠምዱ አድረው መረባቸው ባዶውን ይመለስ ነበር። (ዮሐ. 21:3) በአንዳንድ አካባቢዎች ‘ሰዎችን ማጥመዱ’ ከዓመታት በፊት የጀመረ በመሆኑ አንዳንድ አቅኚዎች በጉባኤያቸው “ውኃ” ውስጥ የቀሩ “ዓሦች” እምብዛም አይኖሩም ብለው ደምድመው ይሆናል። (ማቴ. 4:19) በተቃራኒው ግን አስፋፊዎችና አቅኚዎች ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቶችን ከሚመሩባቸው አካባቢዎች የመጡ ሪፖርቶችን ስናነብ በጣም አንደሰትምን? በነዚህ አገሮች ያሉ አቅኚዎችና ሚስዮናውያን ያላቸው ደስታ በግልጽ የሚታይ ነው። (መግ 92 9/1 ገጽ 20 አን. 15) ስለዚህ አንዳንድ ጠንክረው የሚሠሩ አቅኚዎች ይበልጥ አስፈላጊ ወደ ሆነ ክልል ለመዛወር በሚያስችላቸው ሁኔታ ላይ የሚገኙ ከሆነ ከመዛወራቸው በፊት ይህንን ሁኔታ ከቅርንጫፍ ቢሮው ወይም ከክልል የበላይ ተመልካቹ ጋር ሊነጋገሩበት ይገባል።
18 በመጀመሪያ ላይ አንዳንዶች አቅኚነትን የጀመሩት ሊያደርጉት የሚገባቸው ትክክለኛ ነገር እንደሆነ ስለሚያውቁ ነው። ነገር ግን አቅኚነት ባይሳካልንስ ብለው ያስባሉ። አቅኚ ለመሆን ያመለከቱት እየተጠራጠሩና እያመነቱ ሊሆን ይችላል። በመጀመሪያ ላይ በመስክ አገልግሎት ያገኙት ውጤት አነስተኛ ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ከጊዜ በኋላ ችሎታቸው ዳብሮ በሥራቸው ላይ የይሖዋ በረከት እንዳለበት የሚያሳዩ ማስረጃዎች ሊታዩ ይችላሉ። በዚህም ምክንያት ደስታቸውና በራሳቸው ላይ ያላቸው እምነት ከፍ አለ። አቅኚነት ለአንዳንዶች ወደ ቤቴል አገልግሎት፣ የጊልያድ ሥልጠናና የሚስዮናዊነት ሥራ፣ የአገልጋዮች ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት እንዲሁም ወደ ተጓዥነት ሥራ ለመግባት መሸጋገሪያ ሆኖላቸዋል።
19 ወደ ሌላ አገር ለመሄድ ወይም ከጊልያድ ሥልጠና ጥቅም ለማግኘት አትችል ይሆናል። ነገር ግን በተለይ አሁን ያለው ክልልህ ውጤታማ ካልሆነ ወይም ወደ ሌላ ቦታ ለመዛወር በምትችልበት ሁኔታ ላይ ከሆንክ በአገርህ ውስጥ በሌላ ውኃ ላይ ለማጥመድ የምትችልበት አጋጣሚ አሁንም ቢሆን አለህ። ይህ ዓይነቱ ውሳኔ በአኗኗርህ ላይ ለውጥ እንድታደርግ ይጠይቅብህ ይሆናል። ሆኖም በአጸፋው የምታገኘው መንፈሳዊ ዋጋ በእርግጥም ከፍተኛ ነው። — ማቴ. 6:19–21
20 ወይም ሁኔታዎች የሚፈቅዱልህ ሆነ በክልልህ ውስጥ በአቅራቢያህ ባለ ጉባኤ እርዳታ ልታደርግ ትችል ይሆናል። የሚፈለጉትን ብቃቶች የምታሟላ ከሆነ የክልል የበላይ ተመልካቹ ሌላ አቅኚ ቢመጣላቸው ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ የሚላቸው በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ጉባኤዎች የትኞቹ እንደሆኑ በደስታ ሐሳብ ያቀርብልሃል።
21 አንዳንድ አቅኚዎችና አስፋፊዎች መኖሪያቸውን ሳይለቁ ለአካባቢያቸው የሚያስፈልገውን ነገር ለማሟላት ችለዋል። ምናልባት ሌላ ቋንቋ መናገር ይችሉ ይሆናል። በክልልህ ውስጥ ሌላ ቋንቋ የሚናገሩ በርከት ያሉ ሰዎች ይገኛሉን? የምልክት ቋንቋ መናገር የሚችል ሰው የመንግሥቱን መልእክት እንዲያስተላልፍላቸው የሚፈልጉ ሰዎች አሉን? ሌላ ቋንቋ የሚያውቁ ሰዎች የመንግሥቱን መልእክት ለሁሉም ዓይነት ሰዎች ለማድረስ ትልቅ እርዳታ ሊያደርጉ ይችላሉ። ምንም እንኳን ይህ በእርግጥ ፈታኝ ሁኔታ ሊሆን ቢችልም መልሶ የሚክስ መሆኑንም አስመስክሯል። — 1 ጢሞ. 2:4፤ ቲቶ 2:11
22 በአሁኑ ጊዜ ይሖዋን ለማስከበር የምትችለውን ሁሉ እያደረግህ ከሆነ ባሉህ የአገልግሎት መብቶች ተደሰት። ይበልጥ ልትሠራ እንደምትችል ከተሰማህ ነገሩን በጸሎት ወደ ይሖዋ አቅርበው። ከሐቁ ሳትሸሽ ሁኔታህ ምን ምን ለውጦችን ለማድረግ እንደሚያስችልህ መርምረው። የአቅኚነት መንፈስ ካለው ሌላ ሽማግሌ ጋር ወይም ከክልል የበላይ ተመልካች ጋር ዕቅድህን ተወያይበት። ጸሎት የሞላበት ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ውሳኔ ካደረግህ ይሖዋ የሚያከብሩትን እንደሚያከብር በገባው ቃል እምነት ኖሮህ ወዲያውኑ ውሳኔህን ተግባራዊ አድርግ። — ዕብ. 13:5, 6፤ 1 ሳሙ. 2:30