ከአምላክ የሚሰጠው ነፃነት ደስታ ያመጣል
“የይሖዋ ደስታ አምባችሁ ነው።”—ነህምያ 8:10
1. ደስታ ምንድን ነው? ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሰዎች ይህን ደስታ ሊያገኙ የሚችሉት ለምንድን ነው?
ይሖዋ የሕዝቡን ልብ በደስታ ይሞላል። ይህ ዓይነቱ ከፍተኛ ደስታ ጥሩ ነገር ከማግኘት ወይም ለማግኘት ከመጠባበቅ የሚገኝ ነው። ደስታ የአምላክ መንፈስ ቅዱስ ወይም ሠራተኛ የሆነው ኃይሉ ፍሬ ስለሆነ ራሳቸውን ለአምላክ የወሰኑ ሰዎች ይህን ደስታ ሊያገኙ ይችላሉ። (ገላትያ 5:22, 23) ስለዚህ የሚያስጨንቅ ፈተና ቢያዋክበንም እንኳን በመንፈሱ የምንመራ የይሖዋ አገልጋዮች በመሆናችን ደስተኞች ልንሆን እንችላለን።
2. አይሁዳውያን በዕዝራ ዘመን በአንድ ልዩ በዓል ላይ የተደሰቱት ለምን ነበር?
2 አይሁድ በአምስተኛው መቶ ዘመን ከዘአበ በአንድ ልዩ ወቅት ከአምላክ የተሰጣቸውን ነፃነት በኢየሩሳሌም አስደሳች የዳስ በዓል ለማክበር ተጠቅመውበት ነበር። ዕዝራና ሌሎችም ሌዋውያን የአምላክን ሕግ ካነበቡላቸው በኋላ “ሕዝቡም ሁሉ የተነገረላቸውን ቃል አስተውለዋልና ሊበሉና ሊጠጡ እድል ፈንታም ሊሰድዱ ደስታም ሊያደርጉ ሄዱ።”—ነህምያ 8:5-12
የይሖዋ ደስታ አምባችን ነው
3. “የይሖዋ ደስታ” ኃይላችን ወይም አምባችን ሊሆንልን የሚችለው በምን ሁኔታዎች ሥር ነው?
3 አይሁዳውያን ይህን በዓል ባከበሩበት ወቅት “የይሖዋ ደስታ ኃይላችሁ [አምባችሁ (አዓት)] ነው” የሚሉትን ቃላት እውነተኛነት ተገንዝበው ነበር። (ነህምያ 8:10) እኛም ራሳችንን የወሰንንና የተጠመቅን የይሖዋ ምሥክሮች በመሆን አምላክ በሰጠን ነፃነት ጸንተን ከቆምን ይህ ደስታ ለእኛም አምባችን ይሆንልናል። ጥቂቶቻችን በመንፈስ ቅዱስ ተቀብተን በሰማይ ከክርስቶስ ጋር ተባባሪ ገዢዎች ለመሆን እንድንችል የአምላክ ቤተሰብ አባሎች የመሆን ተስፋ አግኝተናል። (ሮሜ 8:15-23) አብዛኞቻችን ደግሞ በምድራዊ ገነት የመኖር ተስፋ አለን። (ሉቃስ 23:43) ይህ ተስፋ በጣም ሊያስደስተን ይገባል።
4. ክርስቲያኖች ስቃይንና ስደትን ሊታገሡ የሚችሉት ለምንድን ነው?
4 ግሩም ተስፋ የሚጠብቀን ብንሆንም ስቃይና ስደት ታግሦ ማሳለፍ ቀላል አይደለም። ይሁን እንጂ አምላክ ቅዱስ መንፈሱን ስለሚሰጠን ልንታገስ እንችላለን። መንፈስ ቅዱስ ደስታና ተስፋችንንም ሆነ የአምላክን ፍቅር ሊቀማን የሚችል ምንም ነገር እንደሌለ ጽኑ እምነት እንዲኖረን ያስችለናል። ከዚህም በላይ ይሖዋን በሙሉ ልባችን፣ ነፍሳችን፣ ኃይላችንና ሐሳባችን እስከወደድነው ድረስ አምባችን እንደሚሆንልን እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን።—ሉቃስ 10:27
5. ለመደሰት የሚያስችሉን ምክንያቶች ልናገኝ የምንችለው የት ሊሆን ይችላል?
5 የይሖዋ ሕዝቦች ብዙ በረከቶችን ከማግኘታቸውም በላይ ብዙ የሚደሰቱባቸው ምክንያቶች አሏቸው። አንዳንዶቹ ምክንያቶች ጳውሎስ ለገላትያ ክርስቲያኖች በጻፈላቸው ደብዳቤ ላይ ተገልጸዋል። ሌሎቹ ደግሞ በሌሎች የቅዱሳን ጽሑፎች ክፍሎች ተመልክተዋል። እነዚህን አስደሳች በረከቶች ብናሰላስል መንፈሳችን ይነቃቃል።
ከአምላክ ለሚሰጠው ነፃነት ከፍ ያለ ዋጋ ስጡት
6. ጳውሎስ የገላትያ ክርስቲያኖችን ጸንተው እንዲቆሙ አጥብቆ ያሳሰባቸው ለምን ነበር?
6 ክርስቲያኖች እንደመሆናችን መጠን ከአምላክ ጋር ተቀባይነት ያለው አቋም የማግኘት አስደሳች በረከት አለን። ክርስቶስ ተከታዮቹን ከሙሴ ሕግ ነፃ ስላወጣቸው የገላትያ ሰዎች ጸንተው እንዲቆሙና በዚህ “የባርነት ቀንበር” እንዳይታሰሩ ጥብቅ ማሳሰቢያም ተሰጥቷቸዋል። እኛስ? ሕጉን በመጠበቅ ለመጽደቅ ጥረት እናደርግ ከነበረ ከክርስቶስ ተለይተን ነበር ማለት ነው። በአምላክ መንፈስ እየታገዝን ከአካላዊ መገረዝ ወይም ከሌላ የሕግ ሥራ የሚገኘውን ጽድቅ ሳይሆን በፍቅር በኩል ከሚሠራ እምነት የሚገኘውን ጽድቅ እንጠባበቃለን።—ገላትያ 5:1-6
7. ለይሖዋ የምናቀርበውን ቅዱስ አገልግሎት የምንመለከተው እንዴት መሆን ይኖርበታል?
7 ከአምላክ የተሰጠንን ነፃነት “ይሖዋን በደስታ ለማገልገል” መጠቀም ታላቅ በረከት ነው። (መዝሙር 100:2 አዓት) በእርግጥም ‘የዘላለም ንጉሥና ሁሉን ቻይ ለሆነው ለይሖዋ አምላክ’ ቅዱስ አገልግሎት ማቅረብ ታላቅ መብት ነው! (ራዕይ 15:3 አዓት) የዝቅተኛነት ስሜት የሚያስቸግርህ ከሆነ አምላክ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ወደራሱ እንደሳበህና ‘ቅዱስ በሆነው የአምላክ ምሥራች ሥራ’ የመካፈል መብት እንደሰጠህ መገንዘብ ሊረዳህ ይችላል። (ሮሜ 15:16 አዓት፤ ዮሐንስ 6:44፤ 14:6) ይህም የምንደሰትበትና አምላክን የምናመሰግንበት ትልቅ ምክንያት ነው።
8. የአምላክ ሕዝቦች ታላቂቱ ባቢሎንን በሚመለከት ምን የሚደሰቱበት ምክንያት አላቸው?
8 ደስተኞች የምንሆንበት ሌላው ምክንያት አምላክ የዓለም የሐሰት ሃይማኖት ግዛት ከሆነችው ከታላቂቱ ባቢሎን የሰጠን ነፃነት ነው። (ራዕይ 18:2, 4, 5) ይህች ሃይማኖታዊ አመንዝራ በምሳሌያዊ ሁኔታ “በብዙ ውሃዎች ላይ” ማለትም “ወገኖች፣ ብዙ ሰዎች፣ አሕዛብም፣ ቋንቋዎችም ላይ የተቀመጠች” ብትሆንም በይሖዋ አገልጋዮች ላይ አትቀመጥም ወይም በእነሱ ላይ ሃይማኖታዊ ተጽእኖና ቁጥጥር አታደርግም። (ራዕይ 17:1, 15) የታላቂቱ ባቢሎን ደጋፊዎች በመንፈሳዊ ጨለማ ሲደናበሩ እኛ ግን በአምላክ አስደናቂ ብርሃን እንደሰታለን። (1 ጴጥሮስ 2:9) እርግጥ ነው፣ አንዳንድ ጊዜ “የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር” መረዳት አስቸጋሪ ሊሆንብን ይችላል። (1 ቆሮንቶስ 2:10) ቢሆንም በመንፈስ ቅዱስ አማካኝነት ጥበብና እርዳታ እንዲሰጠን ብንጸልይ ለሰዎች መንፈሳዊ ነፃነት የሚሰጠውን ቅዱስ ጽሑፋዊ እውነት ለመረዳት እንችላለን።—ዮሐንስ 8:31, 32፤ ያዕቆብ 1:5-8
9. ከሃይማኖታዊ ስህተት ነፃ በመውጣታችን የማያቋርጥ በረከት ለማግኘት ከፈለግን ምን ማድረግ አለብን?
9 ከሃይማኖታዊ ስህተት ነፃ በመውጣታችን ብዙ በረከቶችን አግኝተናል። ይሁን እንጂ ይህን ነፃነት ጠብቀን ለመኖር ከፈለግን ከክህደት መራቅ አለብን። የገላትያ ሰዎች የክርስትናን ሩጫ በመልካም ይሮጡ ነበር፤ ይሁን እንጂ አንዳንድ ሰዎች ለእውነት እንዳይታዘዙ እንቅፋት ሆነውባቸው ነበር። ይህ ክፉ ማግባባት ወይም ማባበል ግን ከአምላክ የመጣ ስላልነበረ ሊቃወሙት ይገባ ነበር። ጥቂት እርሾ ሊጡን ሁሉ እንደሚያቦካ ሁሉ የሐሰት አስተማሪዎች ወይም የክህደት ዝንባሌ ያላቸው ሰዎች መላውን ጉባኤ ሊበክሉ ይችሉ ነበር። ጳውሎስ የክርስቲያኖችን እምነት ሊገለብጡ ይፈልጉ የነበሩትን የግዝረት ጠበቃዎች እንዲገረዙ ብቻ ሳይሆን ብልታቸው ፈጽሞ እንዲቆረጥ ተመኝቷል። በእርግጥም ኃይለኛ አነጋገር ነበር! እኛም ከአምላክ የተሰጠንን ነፃነት ከሃይማኖታዊ ስህተት ለመጠበቅ ከፈለግን ክህደትን በመቃወም ረገድ ይህን የመሰለ ጽናትና የማያወላውል አቋም ሊኖረን ይገባል።—ገላትያ 5:7-12
እርስ በርሳችሁ በፍቅር ተገዙ
10. የክርስቲያናዊ ወንድማማችነት ክፍል በመሆን ረገድ ያለብን ሐላፊነት ምንድን ነው?
10 ከአምላክ የሚሰጠው ነፃነት እርስ በርሳቸው ከሚዋደዱ ወንድማማቾች ጋር አስተባብሮናል። ቢሆንም እኛም በበኩላችን ፍቅር ለማሳየት መጣር አለብን። የገላትያ ሰዎች ነፃነታቸውን ‘ለሥጋ ማመካኛ’ ወይም ፍቅር ለጎደለው የራስ ወዳድነት ባሕርይ ማሳበቢያ ማድረግ አይገባቸውም ነበር። በፍቅር ተነሳስተው አንዳቸው ሌላውን እንደ ባሪያ ማገልገል ነበረባቸው። (ዘሌዋውያን 19:18፤ ዮሐንስ 13:35) እኛም እርስ በርሳችን እንድንጠፋፋ ሊያደርገን የሚችለውን መተማማትና ጥላቻ ማስወገድ አለብን። የወንድማማች ፍቅር የምናሳይ ከሆነ እንዲህ ያለው ነገር አይደርስብንም።—ገላትያ 5:13-15
11. ለሌሎች ሰዎች በረከት ልንሆን የምንችለው እንዴት ነው? እነሱስ የሚባርኩን እንዴት ነው?
11 ከአምላክ የተሰጠንን ነፃነት ከአምላክ መንፈስ አመራር ጋር በሚስማማ መንገድ ከተጠቀምንበት ለሰዎች ፍቅር ስለምናሳይ ለሌሎች በረከት ልንሆን እንችላለን። ራሳችንን ለመንፈስ ቅዱስ ቁጥጥርና አመራር የማስገዛት ልማድ ሊኖረን ይገባል። እንዲህ ካደረግን ‘ምኞቱ ከመንፈስ ጋር የሚዋጋውን’ የኃጢአተኛ ሥጋችንን ፍላጎት ፍቅር በጎደለው መንገድ ወደ ማርካት አናዘነብልም። በአምላክ መንፈስ ከተመራን ፍቅራዊ የሆነውን ነገር የምናደርገው ትእዛዝ የመፈጸም ግዴታ ስላለብን ወይም ሳንፈጽም ብንቀር ቅጣት ስለሚደርስብን አይሆንም። ለምሳሌ ያህል ሌሎችን እንዳናማና ስማቸውን እንዳናጠፋ የሚጠብቀን ሕግ ሳይሆን ፍቅር ነው። (ዘሌዋውያን 19:16) ፍቅር ደግ የሆነውን እንድንናገርና እንድናደርግ ይገፋፋናል። የመንፈስ ፍሬ የሆነውን የፍቅር ባሕርይ ስለምናሳይ ሌሎች ይባርኩናል ወይም ስለ እኛ መልካም ይናገራሉ። (ምሳሌ 10:6) ከዚህም በላይ ከእኛ ጋር መሆን በረከት ያስገኝላቸዋል።—ገላትያ 5:16-18
ፍሬዎችን ማነፃፀር
12. ኃጢአተኛውን “የሥጋ ሥራ” ከማስወገድ ጋር የሚገኙ አንዳንድ በረከቶች ምንድን ናቸው?
12 አምላክ ከሰጠን ነፃነት ጋር ግንኙነት ያላቸው ብዙ በረከቶች ኃጢአት የሆኑትን “የሥጋ ፍሬዎች” ከማስወገድ የተገኙ ናቸው። የአምላክ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ምንዝርን፣ እርኩሰትንና ስድ የሆኑ ተግባራትን ስለማንፈጽም ከብዙ ጭንቀት ድነናል። ከጣኦት አምልኮ ስለራቅን በዚህ ረገድ ይሖዋን ከማስደሰት የሚገኘው ደስታ አለን። (1 ዮሐንስ 5:21) የመናፍስትነት ሥራ ስለማንፈጽም በአጋንንት ከመገዛት ነፃ ሆነናል። ክርስቲያናዊ ወንድማማችነታችን በጥላቻ፣ በጠብ፣ በቅናት፣ በቁጣ ግንፋሎት፣ በክርክር፣ በመከፋፈል፣ በኑፋቄና በምቀኝነት አልተበላሸም ወይም አልጐደፈም። ደስታችን በስካርና በፈንጠዝያ አልባከነም። ጳውሎስ የሥጋ ፍሬዎችን የሚፈጽሙ ሰዎች የአምላክን መንግሥት እንደማይወርሱ አስጠንቅቋል። እኛ ግን የእርሱን ቃል ስለምንቀበልና ስለምንፈጽም አስደሳቹን የመንግሥት ተስፋ አጥብቀን ልንይዝ እንችላለን።—ገላትያ 5:19-21
13. የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ምን ፍሬዎችን ያፈራል?
13 ክርስቲያኖች የይሖዋን መንፈስ ፍሬ ስለሚያፈሩ ከአምላክ የሚሰጠው ነፃነት ደስታ አምጥቶልናል። ጳውሎስ ለገላትያ ሰዎች ከጻፈላቸው ቃላት የኃጢአተኛው ሥጋ ሥራ ካፈሩት የመንፈስ ፍሬዎች ማለትም ከፍቅር፣ ከደስታ፣ ከሰላም፣ ከትዕግስት፣ ከደግነት፣ ከጥሩነት፣ ከእምነት፣ ከየዋህነትና ራስን ከመግዛት ጋር ሲነጻጸሩ እንደ እሾህ የሚዋጉ መሆናቸውን ለመገንዘብ አያዳግትም። ከኃጢአተኛው ሥጋችን ምኞት በሚቃረን መንገድ ለመኖር ቁርጥ ውሳኔ በማድረግ በአምላክ መንፈስ ለመመራትና በመንፈሱ ለመኖር እንፈልጋለን። መንፈስም “ራስ ወዳዶች፣ እርስ በርስ የምንነሣሣና የምንቀናና” እንድንሆን ሳይሆን ትሑቶችና ሰላማውያን እንድንሆን ያደርገናል። የመንፈስን ፍሬ ከሚያሳዩ ሰዎች ጋር መተባበርና መወዳጀት የሚያስደስት መሆኑ አያስደንቅም።—ገላትያ 5:22-26
ለመደሰት የሚያስችሉን ሌሎች ምክንያቶች
14. ከክፉ መናፍስት ኃይሎች ጋር ለመዋጋት ምን የጦር ዕቃዎች ያስፈልጉናል?
14 ከአምላክ ከሚሰጠን ነፃነት ከሚገኙት በረከቶች አንዱ ከሰይጣንና ከአጋንንቱ ጥበቃ ማግኘት ነው። ከክፉ መንፈሳውያን ኃይሎች ጋር የምናደርገው ውጊያ እንዲሳካልን ከፈለግን “የእግዚአብሔርን ዕቃ ጦር ሁሉ” መልበስ አለብን። የእውነት መታጠቂያና የጽድቅ ጥሩር ያስፈልገናል። እግሮቻችን የሰላምን ወንጌል መጫማት አለባቸው። የክፉውን የሚንበለበሉ ፍላጻዎች የምናጠፋበት ትልቅ የእምነት ጋሻም ያስፈልገናል። የመዳንን ራስ ቁር መልበስና የአምላክ ቃል የሆነውን “የመንፈስ ሰይፍ” መያዝ አለብን። “ዘወትር በመንፈስ እንጸልይ።” (ኤፌሶን 6:11-18) መንፈሳዊውን የጦር ዕቃ ከለበስንና ከአጋንንታዊ ሥራዎች ከራቅን ደፋሮችና ደስተኞች እንሆናለን።—ከሥራ 19:18-20 ጋር አወዳድር
15. ራሳችንን ከአምላክ ቃል ጋር አስማምተን በመኖራችን ምን አስደሳች በረከቶች እናገኛለን?
15 ጠባያችን ከአምላክ ቃል ጋር ስለሚስማማ ደስተኞች ነን፤ ብዙ ክፉ አድራጊዎችን ከሚያሰቃየው የህሊና ቁስል ነፃ ነን። ‘በአምላክና በሰው ፊት ሁልጊዜ ነውር የሌለበት ሕሊና ትኖረን ዘንድ’ እንተጋለን። (ሥራ 24:16) በመሆኑም ሆን ብለው ኃጢአት በሚሠሩና ንስሐ በማይገቡ ኃጢአተኞች ላይ የሚወርደው መለኮታዊ ቅጣት ያገኘናል ብለን መፍራት አያስፈልገንም። (ማቴዎስ 12:22-32፤ ዕብራውያን 10:26-31) የምሳሌ 3:21-26ን ምክር በሥራ ላይ ስናውል “ልጄ ሆይ፣ እነዚህ ከዓይኖችህ አይራቁ፤ መልካም ጥበብንና ጥንቃቄን ጠብቅ። ለነፍስህም ሕይወት ይሆናሉ፣ ለአንገትህም ሞገስ (ጌጥ)። የዚያን ጊዜ መንገድህን ተማምነህ ትሄዳለህ፣ እግርህም አይሰናከልም። በተኛህ ጊዜ አትፈራም፤ ትተኛለህ፣ እንቅልፍህም የጣፈጠ ይሆንልሃል። ድንገት ከሚያስፈራ ነገር ከሚመጣውም የኀጥአን ጥፋት አትፈራም፤ እግዚአብሔር መታመኛህ ይሆናልና፣ እግርህም እንዳይጠመድ ይጠብቅሃልና” የሚሉት ቃላት ለእኛም ይፈጸሙልናል።
16. ጸሎት ለደስታ ምክንያት የሆነው እንዴት ነው? በዚህ ረገድ የይሖዋ መንፈስ ምን ድርሻ ያበረክታል?
16 ለመደሰት ምክንያት የሚሆነን ሌላው ነገር እንደምንደመጥ በመተማመን በጸሎት ወደ ይሖዋ ለመቅረብ የሚያስችል ነፃነት ያለን መሆናችን ነው። አዎን፣ አክብሮት የተመላበት “የይሖዋ ፍርሃት” ስላለን ጸሎታችን መልስ ያገኛል። (ምሳሌ 1:7) ከዚህም በላይ “በመንፈስ ቅዱስ በመጸለይ” ራሳችንን በአምላክ ፍቅር ጠብቀን ለማኖር እንታገዛለን። (ይሁዳ 20,21) ይህንንም የምናደርገው በይሖዋ ፊት ተቀባይነት ያለው የልብ ዝንባሌ በማሳየትና እንዴት እንደምንጸልይና በጸሎታችንም ምን መጠየቅ እንደምንችል በሚያሳየን በመንፈሱ መሪነት ከፈቃዱና ከቃሉ ጋር የሚስማማ ጸሎት በማቅረብ ነው። (1 ዮሐንስ 5:13-15) በጣም ከባድ ፈተና ቢያጋጥመንና ምን እንደምንለምን ካላወቅን ‘መንፈስ ድካማችንን ያግዛል፤ . . . በማይነገር መቃተት ይማልድልናል።’ አምላክም እንደዚህ ያሉትን ጸሎቶች ይመልሳል። (ሮሜ 8:26, 27) መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠን እንጸልይ። መንፈሱም ፍሬዎቹን በተለይም አንድ ዓይነት ፈተና ለመቋቋም የሚያስፈልጉትን ፍሬዎች በውስጣችን እንዲያፈራ እንፍቀድለት። (ሉቃስ 11:13) አምላክ በመንፈሱ መሪነት ያስጻፈውን ቃሉንና በመንፈሱ አመራር አማካኝነት የሚዘጋጁትን ክርስቲያናዊ ጽሑፎች በጸሎትና በትጋት ካጠናን ደስታችንን እንጨምራለን።
በተፈለገው ጊዜ በሚገኘው ዕርዳታ መባረክ
17. የሙሴ ተሞክሮና የዳዊት ቃላት ይሖዋ ከሕዝቡ ጋር መሆኑን የሚያመለክቱት እንዴት ነው?
17 ከአምላክ የተሰጠንን ነፃነት በትክክል ስንጠቀም ይሖዋ ከእኛ ጋር እንደሆነ ስለምናውቅ እንደሰታለን። ሙሴ ባጋጠሙት መጥፎ ሁኔታዎች ምክንያት ከግብፅ እንዲወጣ በተገደደበት ጊዜ “የማይታየውን እንደሚያየው አድርጎ የጸናው” በእምነት ነበር። (ዕብራውያን 11:27) ሙሴ ይሖዋ ከእርሱ ጋር እንደነበረ ያውቅ ስለነበር ብቻውን አልነበረም። በተመሳሳይም የቆሬ ልጆች “አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን፣ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው። ስለዚህ ምድር ብትነዋወጥ፣ ተራሮችም ወደ ባሕር ልብ ቢወሰዱ አንፈራም። ውኆቻቸው ጮኹ ተናወጡም፣ ተራሮችም ከኃይሉ የተነሣ ተናወጡ” በማለት ዘምረዋል። (መዝሙር 46:1-3) በአምላክ ላይ ይህን የመሰለ እምነት ካለህ ፈጽሞ አይተውህም። ዳዊት “እናቴና አባቴ ቢተዉኝም እንኳን ይሖዋ ግን ይቀበለኛል” ብሏል። (መዝሙር 27:10(አዓት)) አምላክ ለአገልጋዮቹ ይህን ያህል እንደሚያስብ ማወቅ ምንኛ ያስደስታል!—1 ጴጥሮስ 5:6, 7
18. የይሖዋ ደስታ ያላቸው ሰዎች በጭንቀት ከመዋጥ የሚያድነው ከአምላክ የተሰጠ ነፃነት የሚኖራቸው ለምንድን ነው?
18 የይሖዋ ደስታ ስላለን በጭንቀት ከመዋጥ የሚያድን ከአምላክ የተሰጠ ነፃነት አለን። “በነገር ሁሉ በጸሎትና በምልጃ ከምስጋና ጋር በእግዚአብሔር ዘንድ ልመናችሁን አስታውቁ እንጂ በአንዳች አትጨነቁ” ብሏል ጳውሎስ። “አእምሮንም ሁሉ የሚያልፍ የእግዚአብሔር ሰላም ልባችሁንና አሳባችሁን በክርስቶስ ኢየሱስ ይጠብቃል።” (ፊልጵስዩስ 4:6, 7) የአምላክ ሰላም እጅግ በጣም ፈታኝ በሆነ ሁኔታ ሥር እንኳን ተወዳዳሪ የማይገኝለት የመንፈስ እርጋታ ያስገኛል። በዚህ ሰላም አማካኝነት ልባችን ይረጋጋል። ይህም መንፈሳዊ፣ ስሜታዊና ለአካላዊ ጤናችን ይጠቅመናል። (ምሳሌ 14:30) አምላክ የሚፈቅደው ማንኛውም ነገር ዘላቂ ጉዳት እንደማያስከትልብን ስለምናውቅ የአእምሮአችንን ሚዛን እንድንጠብቅ ይረዳናል። (ማቴዎስ 10:28) ለይሖዋ የተወሰንን ስለሆንንና ሰላምንና ደስታን የመሳሰሉትን ፍሬዎች ለሚያፈራው ለመንፈሱ አመራር ስለምንገዛ በክርስቶስ አማካኝነት ከአምላክ ጋር ጥብቅ ዝምድና ከመመሥረት የሚገኘው ይህ ሰላም ይኖረናል።
19. ደስተኞች ለመሆን የምንችለው ልባችን በምን ላይ እንዲያተኩር ብናደርግ ነው?
19 ልባችን ከአምላክ በተሰጠን ነፃነትና በመንግሥቱ ተስፋ ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ደስተኞች እንድንሆን ይረዳናል። ለምሳሌ ያህል አንዳንድ ጊዜ ልንታመምና ከበሽታችን ለመዳን የምናደርገው ነገር እናጣ ይሆናል። ይሁን እንጂ ይህን ችግር ለመቋቋም የሚያስችለን ጥበብና ጥንካሬ እንድናገኝ ልንጸልይ እንችላለን። አሁን ስላገኘነው መንፈሳዊ ጤንነትና ወደፊት በመንግሥቲቱ አገዛዝ ሥር ስለምናገኘው አካላዊ ፈውስ ማሰባችንም ሊያጽናናንና ሊያበረታን ይችላል። (መዝሙር 41:1-3፤ ኢሳይያስ 33:24) ባሁኑ ጊዜ የምግብና የልብስ ችግሮችን መቋቋም ቢኖርብንም በቅርቡ በምትመጣው በገነቲቱ ምድር ላይ ለሕይወት አስፈላጊ ከሆኑት ነገሮች ምንም ነገር አናጣም። (መዝሙር 72:14, 16፤ ኢሳይያስ 65:21-23) አዎን፣ ሰማያዊው አባታችን አሁን የሚያስፈልገንን ያሟላልናል፤ በኋላም ደስታችንን ፍጹም ያደርግልናል።—መዝሙር 145:14-21
ከአምላክ የተሰጠህን ነፃነት ተንከባከበው
20. በመዝሙር 100:1-5 መሠረት ራሳችንን በይሖዋ ፊት ማቅረብ ያለብን እንዴት መሆን ይኖርበታል?
20 የይሖዋ ሕዝቦች እንደመሆናችን መጠን ይህን ሁሉ ደስታና በረከት ያመጣልንን ከአምላክ የተሰጠ ነፃነት መንከባከብ እንደሚገባን አያጠራጥርም። መዝሙር 100:1-5 ወደ አምላክ ፊት “በእልልታ እንድንገባ” መጋበዙ አያስደንቅም። ይሖዋ የራሱ ገንዘብ ስላደረገን እንደ አፍቃሪ እረኛ ያስብልናል። አዎን፣ “እኛ ሕዝቡ የማሰማሪያውም በጎች ነን።” ፈጣሪነቱና አስደናቂ ባሕርያቱ ወደ መቅደሱ አደባባይ በውዳሴና በምስጋና እንድንገባ ይገፋፋናል። “ስሙን ለመባረክ”ና ስለ ይሖዋ አምላክ መልካም ነገር ለመናገር እንገፋፋለን። በተጨማሪም ምንጊዜም ለእኛ ባለው ፍቅራዊ ደግነቱ ወይም ርኅራኄ በተሞላበት አያያዙ ልንመካ እንችላለን። ይሖዋ “ለልጅ ልጅ” ማለትም ከትውልድ እስከ ትውልድ ታማኝ ከመሆኑም ሌላ ፈቃዱን ለሚያደርጉ ሰዎች ፍቅር ከማሳየት ወደኋላ አይልም።
21. በዚህ መጽሔት የመጀመሪያ እትም ላይ ምን ማበረታቻ ቀርቦ ነበር? ከአምላክ ስለተሰጠን ነፃነትስ ምን ማድረግ ይኖርብናል?
21 ፍጽምና የሌለን ሰዎች እንደመሆናችን መጠን ከሁሉም ፈተናዎች ልናመልጥ አንችልም። ይሁን እንጂ በመለኮታዊ እርዳታ የይሖዋ ደስተኛ ምሥክሮች ልንሆን እንችላለን። በዚህ ረገድ በዚህ መጽሔት የመጀመሪያ እትም (ሐምሌ 1879) ላይ የተጻፉት ቃላት ሊጠቀሱ የሚገባቸው ናቸው፦ “በጠባቡ መንገድ ላይ በዛለ እርምጃ ለመሮጥ የምትፈልጉ ክርስቲያን ወንድሞችና እህቶች ሆይ፣ በርቱ። . . . የመንገዱን ወጣ ገባነት አትመልከቱ። ይህ መንገድ በጌታ የተባረኩ እግሮች የተቀደሰ ነው። እያንዳንዱን እሾህ እንደ አበባ በመንገዳችሁ ላይ የሚያጋጥማችሁን እያንዳንዱን ሹል ድንጋይ ወደ ግባችሁ እንደሚያዘልላችሁ ድንጋይ አድርጋችሁ ቁጠሩ። ዓይናችሁን በሽልማቱ ላይ ትከሉ” የሚል ነበር። ዛሬ ይሖዋን እያገለገሉ ያሉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ዓይናቸውን በሽልማቱ ላይ ስለተከሉ ደፋሮች የሚሆኑበትና የሚደሰቱበት ብዙ ምክንያት አግኝተናል። አንተም ከእነሱ ጋር ሆነህ ከአምላክ ለተሰጠህ ነፃነት ጸንተህ ቁም። የዚህን ነፃነት ዓላማ አትሳት። የይሖዋ ደስታ ምንጊዜም ኃይልህ ወይም አምባህ ይሁንልህ።
እንዴት ብለህ ትመልሳለህ?
◻ “የይሖዋ ደስታ” ኃይላችን ወይም አምባችን ሊሆን የሚችለው እንዴት ነው?
◻ በሃይማኖታዊ አባባል ከአምላክ የተሰጠ ነፃነት ለይሖዋ ሕዝቦች ምን በረከቶችን አምጥቶላቸዋል?
◻ እርስ በርሳችን በፍቅር እንደ ባሪያዎች መገዛት ያለብን ለምንድን ነው?
◻ ከአምላክ ከተሰጠ ነፃነት ጋር አብረው የሚገኙ አንዳንድ በረከቶች ምንድን ናቸው?
◻ የአምላክ ሕዝቦች ደስተኞች ሆነው ሊኖሩ የሚችሉት እንዴት ነው?
[በገጽ 23 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
“እያንዳንዱን እሾህ እንደ አበባ በመንገዳችሁ ላይ የሚያጋጥማችሁን እያንዳንዱን ሹል ድንጋይ ወደ ግባችሁ እንደሚያዘልላችሁ ድንጋይ አድርጋችሁ ቁጠሩ”