በኬፕ ቨርዴ “የሕይወት ውሃ” ይፈልቃል
“የይሖዋ ምስክሮች አምልኮ ከ1958 ጀምሮ በኬፕ ቨርዴ መኖሩ ሊጠቀስ የሚገባው ሐቅ ነው” በማለት የኬፕ ቨርዴ ሪፑብሊክ የፍትሕ ሚኒስቴር ገለጹ። ይህን የገለጹት ወደቢሮአቸው ተጠርተው ለመጡ ሁለት የይሖዋ ምሥክሮች ነበር። በመጨመርም “የይሖዋ ምሥክሮች ሕጋዊ ዕውቅና ሳያገኙ ይህን ያህል ጊዜ በመቆየታቸው እናዝናለን” ብለዋል።
ህዳር 30 ቀን 1990 የተደረገው ይህ ስብሰባ በኬፕ ቨርዴ በሚኖሩ የይሖዋ ምሥክሮች ዘንድ ሲታወስ የሚኖር ነው። ምክንያቱም ይህ ስብሰባ በዚያ ሀገር ሕጋዊ የሃይማኖት ማህበር ሆነው በይፋ መታወቃቸውን ያበሠረ ነው። ይሁን እንጂ በስብሰባው ላይ ለተገኙት ሁለት ምሥክሮች የግል ትዝታቸውን የሚቀሰቅስ ነበር። ምክንያቱም ሉዊስ አንድራዴ የሚባለው አንደኛው ወንድም በመጠበቂያ ግንብ ማህበር የተዘጋጁ አንዳንድ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጽሑፎችን ያገኘው በ1958 ነበር። ጽሑፎቹን ከዳር እስከዳር ካነበበ በኋላ እውነትን እንዳገኘ አወቀ። ያወቀውንም እውነት የረዥም ጊዜ ወዳጁ ለነበረው ለፍራንሲስኮ ታቫሬዝ በጉጉት አካፈለው። ከዚያ በኋላ በነበሩት ጥቂት ዓመታት ሁለቱም በኮንትራት ያገኙአቸው የነበሩትን መጠበቂያ ግንብና ንቁ! መጽሔቶችን በማንበብ የእውነትን ውሃ መጠጣታቸውን ቀጠሉ። ከአሥር ዓመታት በኋላ በ1968 በኬፕ ቨርዴ ለመጀመሪያ ጊዜ በተደረገው የተጓዥ የበላይ ተመልካች ጉብኝት ወቅት ተጠመቁ።
ወንድም አንድራዴና ወንድም ታቫሬዝ “ና! የሕይወትን ውሃ እንዲያው (በነፃ) ውሰድ” የሚለውን ጥሪ የማሰማት ኃላፊነት እንዳለባቸው ተገነዘቡ። (ራዕይ 22:17) የተበታተነውና አስቸጋሪ የነበረው መስካቸው የተደቀነባቸውን ችግር ለመቀበል ፈቃደኞች ነበሩ። ኬፕ ቨርዴ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ውስጥ ከሴኔጋል ዳካር በስተምዕራብ 560 ኪሎ ሜትር ያህል ርቃ የምትገኝና አሥር ዋና ዋና ደሴቶችንና አንዳንድ ትናንሽ ደሴቶችን የያዘች አገር ናት። ኬፕ ቨርዴ ማለት “አረንጓዴው ኬፕ” ማለት ሲሆን ቀድሞ በአፍሪካ ጠረፍ ላይ የሚገኘውን ባሕረ ገብ መሬት የሚያመለክት ስም ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ደሴቶች የሚያገኙት ዝናብ በጣም አነስተኛ ስለሆነ አረንጓዴ ደሴቶች ናቸው ሊባሉ የሚችሉ አይደሉም። 350,000 የሚያክሉ ነዋሪዎች ኑሮአቸውን ለማሸነፍ ደረቁን መሬት ያርሳሉ።
ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ ሚስዮናውያንና ልዩ አቅኚዎች ለደሴቷ ነዋሪዎች የሕይወትን ውሃ ለማድረስ በሙሉ ጊዜ አገልጋይነት ብዙ ጥረዋል። ይህ ድካማቸው ምን ውጤት አስገኘ? በቅርቡ ከፖርቱጋል የመጣ አንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች በኬፕ ቨርዴ የሚገኙትን ጉባኤዎች ጎብኝቶ ነበር። እስቲ ያጋጠመውን ይንገረን፦
ሳኦ ቪቼንቴ “ንጹሑን ልሳን” ሰማች
በኬፕ ቨርዴ መጀመሪያ ያረፍነው በሳኦ ቪቼንቴ ደሴት በምትገኘው በፖርቶ ግራንዴ ከተማ ነበር። ከአይሮፕላን ጣቢያው ወደ ከተማው ስንሄድ ንፋስ በጠራረገው አሸዋ የተሸፈኑትን አለትማ ኮረብታዎች አየን። የሰሜን አፍሪካ በረሃነት ወደኬፕ ቨርዴ ደሴቶችም ተዳርሷል። ከታህሣስ እስከ የካቲት የሰሀራ ሞቃትና ደረቅ ንፋስ በውቅያኖሱ ላይ አልፎ ደሴቶቹን አሸዋና አቧራ ያለብሳቸዋል። አንዳንድ ጊዜ የአቧራው ደመና በጣም ጥቅጥቅ ያለ ከመሆኑ የተነሣ አይሮፕላኖች መብረር ያቅታቸዋል። ጥቂት ሣርና ቅጠል ቢኖር እንኳአቧራ ያዘለው ደረቅ ንፋስ ሲመጣ ይደርቃል።
ይሁን እንጂ በመንፈሳዊ ረገድ የውሃ ምንጮች እንደልብ ይገኛሉ። የይሖዋ ምሥክሮች በፖርቶ ግራንዴ ሁለት ጉባኤዎችን ስለአቋቋሙ 167 የመንግሥት አስፋፊዎች ለ47,000 የሳኦ ቪቼንቴ ደሴት ነዋሪዎች ሕይወት ሰጪ ውሃዎችን በትጋት ያደርሳሉ። በሳምንቱ የመጨረሻ ቀኖች ላይ በመንግሥት አዳራሹ በሚደረገው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ስብሰባ 400 የሚሆኑ ሰዎች ይገኛሉ።
አንድ ሳምንት በፈጀው ጉብኝት ወቅት በከተማዋ ካሉት ሁሉ በተሻለው የቲያትር ቤት ለሚደረገው “ንጹሕ ልሳን” የወረዳ ስብሰባ የመጨረሻ ዝግጅት እየተደረገ ነበር። (ሶፎንያስ 3:9) ከአካባቢው ነዋሪዎች በተጨማሪ ከሳንቶ አንታኦና ከሳኦ ኒኮላው ደሴቶች የመጡ ልኡካን ስለነበሩ የተሰብሳቢዎቹ ቁጥር 756 ደርሷል። በዚህ ስብሰባ ላይ ሃያ አራት ሰዎች ተጠመቁ። በፕሮግራሙ ላይ በምሥክሮቹ የተዘጋጀ የመጽሐፍ ቅዱስ ድራማ ቀርቧል። አንድ የፊልም ሥራ ድርጅት የልምምድ ዲሬክተር የነበረ ሰው ድራማውን ከተመለከተ በኋላ “ለአንድ ዓመት አሠልጥነን እንኳ ብዙ ችግሮች ያጋጥሙናል። በእናንተ ድራማ የተሳተፉት ግን በሁለት ወር ሥልጠና ብቻ ከእኛዎቹ እጅግ በጣም የተሻለ ሠርተዋል” ብሏል። ስብሰባው በተሳካ ሁኔታ እንዳበቃ በሳኦ ቲያጎ ደሴት ላይ ወደምትገኘው የኬፕ ቨርዴ ሪፑብሊክ ዋና ከተማ ወደሆነችው ወደ ፕራያ ከተማ መሄጃችን ደረሰ።
ታጥቦ የነፃ ሕዝብ
በቅርብ ዓመታት ውስጥ ብዙ የሌሎች ደሴቶች ነዋሪዎች ሥራ ለመፈለግ ወደ ዋና ከተማዋ ጎርፈዋል። በዚህም ምክንያት በከተማዋ ዳርቻ ላይ በሺህ የሚቆጠሩ ጥንታዊ አሠራር ያላቸው ጎጆዎች ስለተቀለሱ የውሃው አቅርቦት የጽዳቱ ዝግጅት በይበልጥ ተዛብቷል። ብዙ ቤተሰቦችም ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት ሲሉ ፍየል፣ አሣማና ዶሮ ያረባሉ። እነዚህ እንስሳት በየመንገዱ ላይ ወዲያና ወዲህ ሲሉ ማየት የተለመደ ነው። ይህም ለበሽታ መስፋፋት ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል።
እንዲህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ቢኖሩም በአሁኑ ጊዜ በፕራያ በድምሩ 130 የመንግሥት አስፋፊዎች ያሏቸው ሁለት ታዳጊ ጉባኤዎች አሉ። እነዚህ ደስተኛ ምሥክሮች ከመጽሐፍ ቅዱስ የተማሩትን በሥራ ላይ በማዋላቸው ‘ራሳቸውን እንደጠቀሙ’ አያጠራጥርም። ወንድሞቻችንና ልጆቻቸው ንጹሕና ቅዱስ ለመሆን ስለሚጥሩ በመንፈሳዊም ሆነ በሥጋዊ የተሻለ ጤንነት አግኝተዋል። ኑሮ ከባድ ቢሆንባቸውም በመንፈሳዊ ግን ባለጠጎች ናቸው።—ኢሳይያስ 48:17፤ 1 ጴጥሮስ 1:15, 16
እንደደረስንም ወንድሞች ለወረዳ ስብሰባው ለመዘጋጀት ይጣደፉ ጀመር። በሳኦ ቲያጎ ያሉ ምሥክሮችና ፍላጎት ያላቸው ሰዎች እንደዚሁም ከሳልና ከፎጎ ደሴቶች የመጡ ሰዎች ስብሰባው ላይ ተገኝተዋል። ይሖዋም 472 ተሰብሳቢዎች እንዲኖሩ በማድረግ ባርኳቸዋል። ሁሉም ሰው፣ የሚያበሩ ፊቶች የነበሯቸው ሕፃናት ጭምር በጣም ተደስተዋል! በጥሞና በሚያዳምጡት ተሰብሳቢዎች መሃል እንደተቀመጥን “የጥቂቱን ነገር ቀን” መናቅ እንደሌለብን በግልጽ ለማየት ችለናል። (ዘካርያስ 4:10) ይህ ሁሉ ዕድገት የተገኘው ከ30 ዓመት በፊት እውነትን ካወቁ ሁለት ሰዎች ተነስቶ ነው!
ደሴቷን ለቅቀን ከመሄዳችን በፊት ከከተማዋ ውጭ የሚገኙ ቪላ አሶማዳና ታራፋል የሚባሉ ሁለት አነስተኛ ቡድኖችን ለመጎብኘት ሄድን። ደሴቷ ኮረብታማ፣ የተራቆተችና ደረቅ ነበረች። ይሁንና አልፎ አልፎ የሣር ቅጠል፣ ቡቃያዎች ያሉባቸው ማሣዎችና የኮኮናት፣ የሙዝ፣ የፓፓያ፣ የማንጎና የመሳሰሉት ዛፎች ያሉባቸው ብዙ ማሳዎች አረንጓዴ ንጣፍ መስለው አየን። ይህም በረሃውና ምድረ በዳው የሚያብብበት ቀን እንደሚመጣ የሚናገረውን የኢሳይያስ ትንቢት አስታወሰን። (ኢሳይያስ 35:1) ሁለቱ የምሥክሮች አነስተኛ ቡድኖች በበረሃ መሃል እንዳለ ገነት በመንፈሳዊ ደረቅ በሆነ ምድር ለሚኖሩት በሺህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች መንፈሳዊ ምግብና መጠጥ በብዛት እያቀረቡ ነው።
እሳታማ ቅንዓት በፎጎ ደሴት
ቀጥለን የጐበኘናት ደሴት ፎጎ ስትሆን የስሙ ትርጉም “እሳት” ማለት ነው። ደሴቷ የተገኘችው ከእሳተ ገሞራ ፍንዳታ ነው። ካኖ ተራራ ጫፍ ላይ አሁንም እሳተ ገሞራ ይፈነዳል። ይህ ተራራ ከባሕር ወለል በላይ 9,300 ጫማ ሾጠጥ ብሎ የወጣ ነው። ደሴቷ ከብዙ ዓመት ድርቅ በኋላ በቂ ዝናብ ያገኘችው በቅርቡ ነበር። በዚህም ምክንያት ሕዝቡ ለሥራ ተነሣስቶ ነበር። የኬፕ ቨርዴ ነዋሪዎች ዋነኛ ምግብ የሆኑትን ባቄላና ማኒዮክ ለመትከል ይጣደፉ ነበር።
ይሁን እንጂ እነዚህ አድናቂ ሰዎች ቆም ብለው ከመጽሐፍ ቅዱስ የሚገኘውን የእውነት ውሃ ለመውሰድ ጊዜ አላጡም። የመኪና እጥረት ስለነበረና ያሉትም ቢሆኑ ያረጁና በደንብ ያልተጠገኑ ስለነበረ የትራንስፖርት ችግር ቢያጋጥመንም ከሦስት የተለያዩ ቡድኖች ጋር ለመገናኘት ችለን ነበር። በደሴቲቱ ላይ የነበሩት የመንግሥት አስፋፊዎች ቁጥር 42 ብቻ ሲሆኑ በጠቅላላው 162 ሰዎች ወደስብሰባው ሲመጡ በጣም ተደሰትን። ይህም በፎጎ ደሴት ለሚገኙት 32,000 ነዋሪዎች የእውነትንና የሕይወትን ምሳሌያዊ ውሃ በማምጣት በየወሩ በአማካይ 15 ሰዓቶች የሚያሳልፉትን የወንድሞችና የእህቶች አነስተኛ ቡድን ቅንዓት የሚያሳይ ነበር።
በካቶሊክ አገር ፍሬ ማግኘት
ገና በሳንቶ አንታኦና በሳኦ ኒኮላው ደሴቶች የሚኖሩ ወንድሞቻችንን መጎብኘት ነበረብን። የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ለአያሌ ምዕተ ዓመታት በደሴቶቹ ላይ ተጽእኖ እንደነበራት ከእነዚህ ስሞች መረዳት ይቻላል። ዋናው የኬፕ ቨርዴ ሃይማኖት አሁንም የካቶሊክ ሃይማኖት ቢሆንም ብዙ ቅን ልብ ያላቸው ሰዎች ጥም አርኪ የሆነውን የእውነት ውሃ ለማግኘት ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ዘወር እያሉ ነው።
በሳንቶ አንታኦ ዳርና ዳር በሚገኙ ሁለት አነስተኛ ጉባኤዎች ያሉት 49 የመንግሥት አስፋፊዎች 44,000 የሚያክሉትን የደሴቲቱን ነዋሪዎች መንፈሳዊ ፍላጎት ለማርካት ተግተው ይሠራሉ። በፖርቶ ኖቮ ጉባኤ በተደረገው ስብሰባ የሕዝብ ንግግሩን ለመስማት 512 ሰዎች በመጡ ጊዜ 32ቱ የመንግሥት አስፋፊዎች በሳንቶ አንታኦ ብዙ በግ መሰል ሰዎች የእውነትን ውሃ እየተጠሙ እንዳሉ በግልጽ ተገነዘቡ።
በሳኦ ኒኮላው ሥራው የጀመረው ከጥቂት ዓመታት በፊት አንዲት ፖርቱጋላዊት አቅኚ እህት በደሴቲቱ ላይ ከሚኖር ቤተሰብ ጋር ደብዳቤ በመጻጻፍ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ስለመራችላቸው ነበር። ከዚያም በ1978 አንድ ሌላ በፖርቱጋል የሚኖር አቅኚ ወንድም የትውልድ አገሩ ወደሆነችው ወደ ሳኦ ኒኮላው ተመልሶ 15,000 ለሚያክሉት ነዋሪዎች የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለማካፈል ወሰነ። በደሴቷ ላይ የመጀመሪያውን የመጽሐፍ ቅዱስ ስብሰባ ሲመራ የተሰብሳቢው ብዛት አንድ ብቻ ነበር፦ በስብሰባው ላይ የተገኘው እሱ ራሱ ብቻ ነበር! ይሁንና በዚያ ስብሰባ ላይ ያቀረበውን ከልብ የመነጨ ጸሎት ይሖዋ መልሶለታል። በጉብኝታችን ወቅት በሦስት ጉባኤዎች የነበሩ 48 አስፋፊዎች በጠቅላላው 335 ሰዎች ወደ ስብሰባው ሲመጡ በማየታቸው በደስታ ፈንድቀዋል።
የመጀመሪያው የክልል ስብሰባ በዚህች ደሴት የተደረገው በእኛ ጉብኝት ወቅት ነበርና በአካባቢው ቲያትር ቤት እንድንሰበሰብ በነፃ ተሰጠን። የከተማው ባለሥልጣኖች ለስብሰባው የሚያገለግሉ ጥሩ ጥሩ መሣሪያዎችና ነፃ መጓጓዣ አቀረቡልን። በአስተናጋጁ ጉባኤ የነበሩት 19 አስፋፊዎች ለ100 ልኡካን ማረፊያና በስብሰባው ለተገኙት 208 ሰዎች ምግብ አዘጋጁ። ወንድሞቻችን በየዕለቱ ብዙ ችግር ቢያጋጥማቸውም ለማህበሩ የመንግሥት አዳራሽ ማሠሪያ መዋጮ ያደርጋሉ።
እዚህች ደሴት ላይ የይሖዋ ምሥክሮች ጥሩ ጠባይ በደንብ የታወቀ ስለሆነ ብዙ አሠሪዎች ሠራተኛ በሚፈልጉበት ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮችን ለመቅጠር ይፈልጋሉ። ለምሳሌ ያህል በደሴቲቱ ላይ የሚገኘው ብቸኛው የነዳጅ ማደያ ጣቢያ ባለቤት ታማኝ ሰው ስለሚፈልግ አንድ የይሖዋ ምሥክር እንዲሠራለት ጠየቀው። ወንድም የራሱ ሥራ ስላለው ሌላ ሰው ካገኘ እንደሚፈልግለት ነገረው። ባለቤቱም “የተጠመቀ ምሥክር ከሆነ ብቻ ነው የምቀበለው” በማለት አሳሰበው። ከሁለት ወራት በኋላ ለወንድማችን “ገንዘብ መያዝ የሚገባቸው የይሖዋ ምሥክሮች ብቻ ናቸው!” ብሎ ነገረው።
የመጨረሻው ጉብኝታችን፤ ሳል ደሴት
በዚህ ጉብኝታችን የመጨረሻ ማረፊያችን የሆነችው የሳል ደሴት ነበረች። የስሟ ትርጓሜ “ጨው” ማለት ሲሆን በዚህች ደሴት ላይ ያለውን ዋነኛ ኢንዱስትሪ ያመለክታል። እዚህ ያለው አነስተኛ ጉባኤ ለ6,500 ነዋሪዎች የመንግሥቱን መልእክት ለማዳረስ ተግተው የሚሠሩ 22 አስፋፊዎች አሉት። ምሥራቹን ለደሴቷ ነዋሪዎች ማካፈል በጣም ያስደስታል፤ ምክንያቱም ወደ እያንዳንዱ ቤት እንድንገባ እንጋበዝና ከቤተሰቡ አባሎች ውስጥ ለሚበዙት መናገር እንችል ነበር።
የሳል ደሴት ጉብኝታችን የጉዞአችን ማብቂያ ነበር። በኬፕ ቨርዴ ካሉ ከእነዚህ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ጋር መሥራት ምንኛ ታላቅ በረከት ነው! አሁን በእነዚህ ደሴቶች ላይ 531 የመንግሥት አስፋፊዎች አሉ። በ1991 በተከበረው የክርስቶስ ሞት መታሰቢያ ላይ የተገኙት 2,567 ሰዎች መንፈሳዊ ዝግጅቶችን መቀበላቸውን ሲቀጥሉ ይህ የአስፋፊዎች ቁጥር እንደሚያድግ አያጠራጥርም። እዚህ ያሉ አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች በቁሳዊ ሀብት ረገድ ድኾች ቢሆኑም በመንፈሳዊ ግን ባለጠጎችና በሚገባ የተቀለቡ ናቸው። ይሖዋ በእነዚህ ደሴቶች ላይ ለስሙ ምስጋና ያመጣለትን የሕይወት ውሃ በብዛት እንዲፈልቅ በማድረጉ ምን ያህል አመስጋኞች ናቸው!
[በገጽ 24 ላይ የሚገኝ ካርታ]
(መልክ ባለው መንገድ የተቀናበረውን ለማየት ጽሑፉን ተመልከት)
ኬፕ ቨርዴ
ሳንቶ አንታኦ
ሳኦ ቪቼንቴ
ሳኦ ኒኮላው
ሳንታ ሉዚያ
ሳል
ቦአ ቪስታ
ማዮ
ሳኦ ቲያጎ
ፎጎ
ብራቫ
ፕራያ
አትላንቲክ ውቅያኖሶች