ፈላስፋ፣ ክርስትናን ደግፎ የጻፈና ሰማዕት የነበረው ጀስቲን
“በክርስቲያኖች ላይ የተሠነዘሩት ክሶች እንዲመረመሩና በማስረጃ ከተረጋገጡ የሚገባቸውን ቅጣት እንዲቀበሉ እንጠይቃለን። . . . ስለ ምንም ጉዳይ ወንጀለኛ መሆናችንን የሚያረጋግጥ ማንም ከሌለ ግን በመጥፎ ሐሜት ተነሳስታችሁ ነቀፌታ የማይገኝባቸውን ሰዎች እንዳትበድሉ ትክክለኛ አስተሳሰብ ሊያግዳችሁ ይገባል። . . . ምክንያቱም እውነቱን እያወቃችሁ ትክክልና ፍትሕ የሆነውን ነገር ባታደርጉ በአምላክ ፊት የምታመካኙበት ነገር አይኖራችሁም።”
በሁለተኛው መቶ ዘመን እዘአ የኖረው ክርስቲያን ነኝ ባዩና ሰማዕቱ ጀስቲን ለሮማው ንጉሠ ነገሥት ለአንቶኒየስ ፓየስ አቤቱታ ያቀረበው ከላይ በተጠቀሱት ቃላት ነበር። ጀስቲን የክርስቲያን ነን ባዮች ኑሮና እምነት ሚዛናዊ በሆነና በረጋ አእምሮ እንዲመረመር ጠየቀ። ይህ የፍትሕ ጥያቄ የቀረበው አስደናቂ አስተዳደግና ፍልስፍና ካለው ሰው ነበር።
የልጅነት ሕይወቱና ያገኘው ትምህርት
ጀስቲን የተወለደው በ110 እዘአ ገደማ በሰማርያ ሲሆን በዘመናችን ናብሉስ ተብላ በምትጠራውና ቀድሞ ግን ፍላቪያ ኒያፖሊስ ትባል በነበረችው ከተማ ነበር። አባቱና የወንድ አያቱ ሮማውያን ወይም ግሪኮች ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ቢታመንም እሱ ግን ራሱን ሳምራዊ ብሎ ይጠራ ነበር። በአረማዊ ልማድ ውስጥ ተወልዶ በማደጉ ላይ ለእውነት የነበረው ጥማት ስለታከለበት ፍልስፍናን በትጋት ወደ መማር አዘንብሏል። ከኢስጦኢኮች፣ ከፐሪፓተቲኮችና ከፓይታጎራውያን እውነትን ለማግኘት ባደረገው ሙከራ ስላልረካ የፕላቶን አስተሳሰብ ተከተለ።
ጀስቲን ከጽሑፎቹ በአንዱ ከፈላስፎች ጋር ለመነጋገር የነበረውን ፍላጎት ሲገልጽ እንዲህ ብሏል፦ “ለአንድ ኢስጦኢክ እጄን ሰጥቼ ነበር፤ ከእሱ ጋር ረዥም ጊዜ ካሳለፍኩ በኋላ ስለ አምላክ ምንም ተጨማሪ እውቀት ላገኝ ስላልቻልኩ (ራሱም ቢሆን ብዙ የሚያውቀው ነገር ስላልነበረ) . . . እሱን ተውኩና ወደ ሌላ ሄድኩ።”—ፈላስፋውና ሰማዕቱ ጀስቲን ትሪፎ ከሚባል አይሁድ ጋር ያደረገው ውይይት
ቀጥሎም ጀስቲን ከእውነት ይልቅ ለገንዘብ አጥብቆ ያስብ ወደነበረ አንድ ፐሪፓተቲክ ዘንድ ሄደ። “ይህ ሰው ለመጀመሪያዎቹ ጥቂት ቀናት ካስተናገደኝ በኋላ” ይላል ጀስቲን “ግንኙነታችን ምንም ትርፍ የሌለው እንዳይሆን በቅድሚያ ገንዘብ እንድከፍል ጠየቀኝ። እሱንም በዚህ ምክንያት ጭራሹኑ ፈላስፋ እንዳልሆነ በማመን ተውኩት።”
ጀስቲን “ምርጥ ፍልስፍናን” ለመማር በመጓጓት ስለ ራሱ ጥበበኛነት ብዙ ይመካ ወደነበረ አንድ ዝነኛ ፓይታጎራዊ ሰው መጣ። ጀስቲን እንዲህ ይላል፦ “የእሱ ተማሪና ደቀመዝሙር ለመሆን ፈቃደኛ ሆኜ ከእሱ ጋር ቃለ ምልልስ ሳደርግ ‘ታዲያ ሙዚቃ፣ አስትሮኖሚ (የከዋክብት ጥናት)ና ጂኦሜትሪ ታውቃለህ? [ስለነዚህ] ነገሮች በቅድሚያ ያላወቅህ ከሆነ ለደስተኛ ኑሮ የሚረዱህን ሌሎች [አምላካዊ] ነገሮች ለመረዳት እንዴት ታስባለህ?’ አለኝ። . . . እኔም ምንም የማላውቅ መሆኔን ስነግረው አሰናበተኝ።”
ጀስቲን ተስፋ ቢቆርጥም ዕውቅ ወደሆኑ የፕላቶን ፍልስፍና ይከተሉ ወደ ነበሩ ፈላስፋዎች ዘወር በማለት እውነትን መፈለጉን ቀጠለ። እንዲህ በማለት ይናገራል፦ “በፕላቶናውያን መሃል ከፍተኛ ደረጃ ካለውና በቅርቡም በከተማችን መኖር ከጀመረው አንድ ብልህ ሰው ጋር የቻልኩትን ያህል አብዛኛውን ጊዜዬን ካሳለፍኩ በኋላ ብዙ ዕድገት አደረግሁ። በየቀኑም ከፍተኛ መሻሻል ስላደረግሁ . . . ከጥቂት ጊዜ በኋላ ጠቢብ የሆንኩ መሰለኝ።” ጀስቲን ሲደመድም “ትልቁ ድንቁርናዬ ጠቢብ እንደሆንኩ ማሰቤ ነበር” ብሏል።
ጀስቲን ከፈላስፎች ጋር በመገናኘት እውነትን ለማግኘት ያደረገው ፍለጋ ከንቱ ሆነ። ይሁንና አንድ ቀን በባሕር ዳር ተቀምጦ ሲያሰላስል ከአንድ በዕድሜ የገፋ ክርስቲያን ጋር፣ በራሱ አገላለጽ “ቁመናው ፈጽሞ የማይናቅ፣ ትሑትና የሚያስከብር አቀራረብ ያለው አንድ አረጋዊ ሰው” ጋር ተገናኘ። ያደረጉት ጭውውት ጀስቲንን ስለ አምላክ ትክክለኛ እውቀት በሚያስገኙት የመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ ትምህርቶች ላይ እንዲያተኩር አደረገው።—ሮሜ 10:2, 3
ስሙ ያልተጠቀሰው ክርስቲያን ለጀስቲን “ከዚህ ዘመን በፊት፣ ፈላስፎች ተብለው ከሚከበሩት ሰዎች ሁሉ በፊት ጻድቃንና በአምላክ የተወደዱ የነበሩ . . . ገና ወደፊት የሚሆነውንና አሁንም እየሆነ ያለውን ነገር የተነበዩ አንዳንድ ሰዎች ነበሩ። እነሱም ነቢያት ተብለው ይጠራሉ። በመንፈስ ቅዱስ በመመራት እውነትን ያገኙና ለሰዎችም ያሳወቁ እነሱ ብቻ ናቸው።” ክርስቲያኑም “የእነሱ ጽሑፎች አሁንም ስለሚገኙ የሚያነባቸው ሰው ስለ ነገሮች መጀመሪያና መጨረሻ ለማወቅ ብዙ እርዳታ ያገኛል” በማለት የጀስቲንን ፍላጐት አረካ። (ማቴዎስ 5:6፤ ሥራ 3:18) ደግነት የተላበሰው ይህ ክቡር ሰው ጀስቲንን እንዳበረታታው ቅዱሳን ጽሑፎችን በትጋት የመረመረ ይመስላል ከጽሑፍ ሥራዎቹ መገንዘብ እንደሚቻለው ስለ ቅዱሳን ጽሑፎችና ስለ መጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች መጠነኛ ግንዛቤ አግኝቷል።
የጀስቲንን ጽሑፎች ጠጋ ብሎ መመርመር
ጀስቲን ክርስቲያኖች ሞት ሲደቀንባቸው እንኳ በሚያሳዩት ድፍረት በጣም ተደንቋል። የዕብራይስጥ ቅዱሳን ጽሑፎችንም እውነተኛ ትምህርቶች ያደንቅ ነበር። ጀስቲን ከትሪፎ ጋር ባደረገው ውይይት ለመከራከሪያ ነጥቦቹ ድጋፍ እንዲሆኑት ከዘፍጥረት፣ ከዘጸአት፣ ከዘሌዋውያን፣ ከዘዳግም፣ ከ2 ሳሙኤል፣ ከ1 ነገሥት፣ ከመዝሙራት፣ ከኢሳይያስ፣ ከኤርምያስ፣ ከሕዝቅኤል፣ ከዳንኤል፣ ከሆሴዕ፣ ከኢዩኤል፣ ከአሞጽ፣ ከዮናስ፣ ከሚክያስ፣ ከዘካርያስና ከሚልክያስ እንዲሁም ከወንጌሎች ጠቅሷል። ጀስቲን በመሲሕ ስለሚያምነው የአይሁድ እምነት ከትሪፎ ጋር ባደረገው ውይይት ስለ እነዚህ ቅዱሳን መጻሕፍት ጥሩ ግንዛቤ እንደነበረው መመልከት ይቻላል።
ጀስቲን ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ የምሥራቹን የሚያውጅ ወንጌላዊ እንደነበረ ይነገርለታል። ብዙ ሳይጓዝም አልቀረም። አብዛኛውን ዘመኑን ያሳለፈው በኤፌሶን ሲሆን በሮምም ለብዙ ጊዜ ሳይቀመጥ አልቀረም።
የጀስቲን የጽሑፍ ሥራዎች ክርስትናን በመደገፍ የጻፋቸውን ጽሑፎች ይጨምራሉ። በመጀመሪያው አፖሎጂ (ክርስትናን በመደገፍ በጻፈው የመጀመሪያው ጽሑፍ) ላይ በቅዱሳን ጽሑፎች ብርሃን አማካኝነት ከፍተኛውን የአረማዊ ፍልስፍና ጨለማ ለመበታተን ሞክሯል። ከክርስቶስ ኃይለኛ ቃላትና ሥራዎች አንፃር ሲታይ የፈላስፎች ጥበብ ሐሰትና ባዶ መሆኑን ተናግሯል። (ከቆላስይስ 2:8 ጋር አወዳድር) ጀስቲን ራሱን ከተናቁት ክርስቲያኖች ጋር አንድ አድርጎ ያይ ስለነበር ስለ ክርስቲያኖች አቤቱታ አቅርቧል። ወደ ክርስትና ከተለወጠ በኋላም ብቸኛውን እውነተኛ ፍልስፍና እንዳገኘ ይናገርና የፈላስፎችን ልብስ ይለብስ ነበር።
የሁለተኛው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች አረማዊ አማልክትን ለማምለክ እምቢ በማለታቸው እንደ አምላክ የለሾች ይቆጠሩ ነበር። ጀስቲን አረማውያን ስለ ክርስቲያኖች የነበራቸውን ይህን አመለካከት በመቃወም “የጽንፈ ዓለሙን ሠሪ ስለምናመልክ አምላክ የለሾች አይደለንም። . . . እነዚህን ነገሮች ያስተማረን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። . . . እሱ የእውነተኛው አምላክ ልጅ ነው” ብሏል። ጣኦት አምልኮትን በተመለከተ ጀስቲን እንዲህ ብሏል፦ “አምላክ ብለው የሚጠሩትን ነገር የሚሠሩት አረማውያን ራሳቸው ናቸው። እኛ ይህን የምንቆጥረው እንደ ሞኝነት ብቻ ሳይሆን አምላክን እንደ መስደብ ነው። . . . ወራዳ ሰዎች የምታመልኩትን አምላክ ይሥሩ ማለት እንዴት ያለ መነሁለል ነው!”—ኢሳይያስ 44:14-20
ጀስቲን ከክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ብዙ በመጥቀስ በትንሣኤ፣ በክርስቲያናዊ ሥነ ምግባር፣ በጥምቀት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት (በተለይም ክርስቶስን በተመለከተ)ና በኢየሱስ ትምህርቶች ላይ የነበረውን እምነት ገልጿል። የአምላክን መንግሥት በሚመለከትም ጀስቲን ኢሳይያስን በመጥቀስ “መንግሥቱም [በክርስቶስ] ጫንቃ ላይ ይሆናል” ብሏል። ጀስቲን ጨምሮም “ሰብአዊ መንግሥትን ተስፋ የምናደርግ ከሆነ ክርስቶሳችንን መካድ አለብን” ብሏል። ለአምላክ ተገቢ የሆነ አገልግሎት ለአምላክ ለማቅረብ የአምላክን ፈቃድ ማድረግ እንደሚያስፈልግ በመግለጽ በክርስቲያኖች ላይ ስለሚደርሰው ፈተናና ግዴታ ይናገራል። በተጨማሪም “እነዚህን ነገሮች ለማስታወቅ አምላክ ሰዎችን ወደ ሁሉም ብሔራት እንደሚልካቸው” ተናግሯል።
የመጀመሪያው አፖሎጂ ተከታይ ወይም ቅጥያ እንደሆነ የሚታመነው ሁለተኛው የጀስቲን አፖሎጂ (ክርስትናን በመደገፍ የጻፈው ሁለተኛው ጽሑፍ) የተጻፈው ለሮማው የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት ነበር። ጀስቲን ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ ትክክለኛ እውቀት በማግኘታቸው ምክንያት ስደት የደረሰባቸውን ክርስቲያኖች ተሞክሮ በማውሳት ለሮማውያን አቤቱታ ያቀርባል። በክርስቲያን ዜጎች ጠባይ ላይ የተንፀባረቁት የኢየሱስ ትምህርቶች ያላቸው የሥነ ምግባር ብልጫ በሮማውያን ባለሥልጣኖች ዘንድ ምንም ዋጋ የተሰጠው አይመስልም ነበር። የኢየሱስ ደቀ መዝሙር ነኝ ማለት ብቻ ሞት ሊያስከትል የሚችል ወንጀል ሆኖ ነበር። ጀስቲን ቀደም ሲል ይኖር ስለነበረ የክርስትና መሠረተ ትምህርት አስተማሪ “አመንዝራ ወይም ዘማዊ ወይም ነፍሰ ገዳይ ወይም ነጣቂ ያልሆነውን ወይም የምንም ዓይነት ወንጀል ክስ ያልቀረበበትን ይህን ሰው ክርስቲያን ነኝ ብሎ ስለተናገረ ብቻ ለምን ቀጣችሁት?” ብሎ የጠየቀውን ሉሲየስ የተባለ ግለሰብ ጠቅሶ ተናግሯል።
በዚያ ዘመን ክርስቲያኖች ነን በሚሉ ላይ ይደርስ የነበረው አግባብ የሌለው ጥላቻ በሚቀጥለው የጀስቲን አነጋገር ላይ ተገልጿል፦ “እንግዲያውስ እኔም ስማቸውን በጠቀስኩት በአንዳንዶች ወይም ጀብደኝነትና ጉራ ወዳድ በሆነው በክሬሰንስ እንደሚሴርብኝና በእንጨት ላይ እንደምቸነከር እጠብቃለሁ። በዕብሪት የተሞሉትን ረብሸኞች ሞገስ ለማግኘትና እነሱን ለማስደሰት ብሎ ክርስቲያኖች አምላክ የለሾችና ሃይማኖት የለሾች ናቸው እያለ በማያውቀው ነገር በሕዝብ ፊት የሚመሠክርብን ይህ ሰው ፈላስፋ ሊባል የሚበቃ አይደለም። የክርስቶስን ትምህርት ሳያነብ እኛን ቢያጠቃን በጣም ነውረኛና ካልተማሩ ሰዎች የከፋ ሰው መሆኑ ነው። ያልተማሩ ሰዎች እንኳ አብዛኛውን ጊዜ ስለማያውቁት ነገር የሐሰት ምሥክርነት ከመስጠት ይቆጠባሉ።”
የጀስቲን አሟሟት
ጀስቲን በክሬሰንስ ወይም ሲኒክስ በሚባሉ ፈላስፎች ሰላም አደፍራሽ ነው ተብሎ ተከሶ በሮማ ከፍተኛ ባለሥልጣን ፊት ቀርቦ የሞት ፍርድ ተፈረደበት። በ165 አካባቢ በሮማ ከተማ ራሱ ተቆረጠና “ሰማዕት” ሆነ (ሰማዕት ማለት “ምሥክር” ማለት ነው።) በመሆኑም ጀስቲን ሰማዕቱ ወይም ምሥክሩ ጀስቲን ተብሎ ተጠራ።
የጀስቲን የአጻጻፍ ስልት በእሱ ዘመን ከነበሩት ከሌሎች የተማሩ ሰዎች ጽሑፎች ጋር ሲነፃፀር ውበትና ብልሃት ይጎድለው ይሆናል። ቢሆንም ለእውነትና ለጽድቅ የነበረው ሐቀኛ ቅንዓት በግልጽ ሊታይ ይችላል። ከቅዱሳን ጽሑፎችና ከኢየሱስ ትምህርቶች ጋር የቱን ያህል ተስማምቶ እንደኖረ በእርግጠኝነት መናገር አይቻልም። ሆኖም የጀስቲን ጽሑፎች ታሪካዊ ይዘታቸውና በብዛት ከቅዱሳን ጽሑፎች የተጠቀሱት ሐሳቦች ዋጋ ያላቸው ናቸው። በሁለተኛው መቶ ዘመን ይኖሩ የነበሩ ክርስቲያኖች ነን ባዮች ሕይወትና ተሞክሮ እንዴት እንደነበር እንድናስተውል ያስችሉናል።
ጀስቲን በክርስቲያኖች ላይ የሚሰነዘርባቸው ስደት ፍትሕ የጎደለው መሆኑን ለንጉሠ ነገሥቱ ለማሳየት መጣሩ የሚደነቅ ነው። ጀስቲን የአምላክን ቃል ትክክለኛ እውቀት ለማግኘት ሲል አረማዊ ሃይማኖትንና ፍልስፍናን የተወ መሆኑ ጳውሎስ በአቴና ለኤፊቆሮሳውያንና ለኢስጦኢኮች ስለ እውነተኛው አምላክና ከሙታን ስለተነሣው ስለ ኢየሱስ ክርስቶስ በድፍረት የተናገረውን ቃል ያስታውሰናል።—ሥራ 17:18-34
ጀስቲን ራሱም በሺህ ዓመት ግዛት ስለሚሆነው የሙታን ትንሣኤ መጠነኛ እውቀት ነበረው። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተገለጸው እውነተኛ የትንሣኤ ተስፋ እምነት ያጠነክራል። ክርስቲያኖችን በስደት ጊዜ አጽናንቶአቸዋል። ከፍተኛ መከራ፣ ሞትንም እንኳ ሳይቀር ታግሠው እንዲጸኑ አስችሎአቸዋል።—ዮሐንስ 5:28, 29፤ 1 ቆሮንቶስ 15:16-19፤ ራእይ 2:10፤ 20:4, 12, 13፤ 21:2-4
ስለዚህ ጀስቲን እውነትን ፈልጎ የግሪኮችን ፍልስፍና ትቷል። ክርስትናን ደግፎ በመጻፍም ክርስቲያን ነን ባዮች ያስተምሩ ለነበረው ትምህርትና ምግባር ጥብቅና ቆሟል። ራሱም ክርስቲያን ነኝ በማለቱ የሰማዕትነት ሞት ደርሶበታል። በተለይ የሚደነቀው ጀስቲን ለእውነት የነበረው አድናቆትና ስደት የሚደርስበት ቢሆንም እንኳ በድፍረት ምሥክርነት መስጠቱ ነበር፤ ምክንያቱም እነዚህ ባሕርያት የሚገኙት በኢየሱስ እውነተኛ ተከታዮች ዘንድ ብቻ ነው።—ምሳሌ 2:4-6፤ ዮሐንስ 10:1-4፤ ሥራ 4:29፤ 3 ዮሐንስ 4