ጊዜያችሁ የተያዘው በሞቱ ሥራዎች ነው ወይስ በይሖዋ አገልግሎት?
“ይቅርታ፣ ጊዜ የለኝም።” ይህ አነጋገር የይሖዋ ምሥክሮች የመንግሥቱን ምስራች ለሕዝብ በሚሰብኩበት ጊዜ የሚያጋጥማቸው ነው። (ማቴዎስ 24:14) አንዳንድ ጊዜ “ጊዜ የለኝም” የሚሉት ምሥራቹን ላለመስማት ቀላል ሰበብ ሆኖ ስለሚያገኙት ሊሆን ይችላል። ቢሆንም ብዙ ሰዎች ሥራ ስለሚበዛባቸው ጊዜ ያንሳቸዋል። በእርግጥም ኑሮን ለማሸነፍ፣ የመብራት፣ የስልክ፣ የውኃና የመሳሰሉትን ወጪዎች መክፈል፣ ወደ ሥራ መሄድና ከሥራ መምጣት፣ ልጆችን ማሳደግ፣ ቤትን፣ መኪናንና ሌሎች ንብረቶችን መንከባከብና የመሳሰሉት ነገሮች ባስከተሉባቸው ተጽእኖዎች ምክንያት “በዚህ የነገሮች ሥርዓት ጭንቀት” ይዋጣሉ።—ማቴዎስ 13:22
ይሁን እንጂ ብዙ ሰዎች በእርግጥም ጊዜ የሌላቸው ቢሆኑም ፍሬያማ ወይም ውጤታማ በሆኑ ሥራዎች ላይ የተሠማሩት ጥቂቶች ናቸው። ይህም አንድ ጊዜ ጠቢቡ ሰለሞን እንደጻፈው ነው፦ “ከፀሐይ በታች በደከመበት ድካም ሁሉና በልቡ አሳብ የሰው ጥቅም ምንድር ነው? ዘመኑ ሁሉ ኀዘን፣ ጥረትም ትካዜ ነው፤ ልቡም በሌሊት አይተኛም ይህም ደግሞ ከንቱ ነው።”—መክብብ 2:22, 23
መጽሐፍ ቅዱስም ይህን ፍሬ ቢስ የሆነ ሥራ “የሞተ ሥራ” ብሎ ይጠራዋል። (ዕብራውያን 9:14) ሕይወትህ ያተኮረው በእነዚህ የሞቱ ሥራዎች ላይ ነውን? አምላክ “ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው መጠን ስለሚከፍል” ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን ይህ ጉዳይ በጣም ሊያሳስብህ ይገባል። (መዝሙር 62:12) በተለይም ‘ዘመኑ አጭር ስለሆነ’ የሞቱ ሥራዎችን በመሥራት ጊዜ እንዳናባክን ልዩ ትኩረት መስጠት ይኖርብናል። (1 ቆሮንቶስ 7:29) ይሁን እንጂ የሞቱ ሥራዎች ምንድን ናቸው? እነሱንስ እንዴት መመልከት ይኖርብናል? ዋጋ ባላቸው ሥራዎችስ እንደተጠመድን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?
የሞቱ ሥራዎችን ለይቶ ማወቅ
ጳውሎስ በዕብራውያን 6:1, 2 ላይ “እንግዲህ ስለ ክርስቶስ የተሰጠውን የመጀመሪያ ትምህርት ትተን፣ ፍጹም ወደሆነው ትምህርት እንለፍ፤ ከሞተ ሥራ ንስሐ የመግባትንና በእግዚአብሔር የማመንን መሠረት እንደገና አንመሥርት፤ እንዲሁም የጥምቀትን፣ የእጅ መጫንን፣ ከሞት መነሣትን፣ የዘላለም ፍርድን ትምህርት እንደገና አንመሥርት” ሲል ጽፏል። (የ1980 እትም) እንግዲህ የመጀመሪያው ትምህርት ‘ከሞተ ሥራ ንስሐ መግባትን’ እንደሚጨምር ልብ በሉ። ጳውሎስ የጻፈላቸው ሰዎች ክርስቲያን እንደመሆናቸው መጠን ከሞቱ ሥራዎች ንስሐ የገቡ ነበሩ። እንዴት?
በመጀመሪያው መቶ ዘመን ይኖሩ ከነበሩት ክርስቲያኖች አንዳንዶች ክርስቶስን ከማወቃቸው በፊት በሞቱ “የሥጋ ሥራዎች” ተሰማርተው ነበር። እነዚህም የሥጋ ሥራዎች ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ምዋርትና” ሌሎች መጥፎ ተግባሮች ናቸው። (ገላትያ 5:19-21) እነዚህን ሥራዎች ባይተዉአቸው ኖሮ ወደ መንፈሳዊ ሞት ያደርሷቸው ነበር። ይሁን እንጂ እነዚህ ክርስቲያኖች በአምላክ ምህረት ከጥፋት መንገዳቸው ተመልሰውና ንስሐ ገብተው ‘ታጥበው ነጽተዋል።’ ስለዚህ በይሖዋ ዘንድ ንጹህ አቋም ለማግኘት ችለዋል።—1 ቆሮንቶስ 6:9-11
ይሁን እንጂ ሁሉም ክርስቲያኖች ከክፉ ሥራ ወይም ከሥነ ምግባር ውጭ ከሆኑ ድርጊቶች ንስሐ መግባት አያስፈልጋቸውም ነበር። የጳውሎስ ደብዳቤ በመጀመሪያ ደረጃ የተጻፈው ክርስቶስን ከመቀበላቸው በፊት የሙሴን ሕግ በጥብቅ ይከተሉ ለነበሩ አይሁዳውያን አማኞች ነው። ታዲያ እነዚህ ሰዎች ከምን የሞቱ ሥራዎች ነው ንስሐ የገቡት? ሕጉ እንዲጠብቁ ያዝዛቸው የነበረውን የአምልኮና የአመጋገብ ሥርዓት መጠበቃቸው ምንም ዓይነት ጉድለት እንደሌላቸው ግልጽ ነው። ሕጉ ‘ቅዱስና ጻድቅ በጐም’ አይደለምን? (ሮሜ 7:12) አዎ ነው፤ ይሁን እንጂ ጳውሎስ በሮሜ 10:2, 3 ላይ አይሁዶችን በሚመለከት እንዲህ ብሏል፦ “በእውቀት አይቅኑ እንጂ ለእግዚአብሔር እንዲቀኑ እመሰክርላቸዋለሁና። የእግዚአብሔርን ጽድቅ ሳያውቁ የራሳቸውንም ጽድቅ ሊያቆሙ ሲፈልጉ፣ ለእግዚአብሔር ጽድቅ አልተገዙም።”
አዎ፣ አይሁዶች ሕጉን በጥንቃቄ በመጠበቅ ደህንነት ለማግኘት እንደሚችሉ ያምኑ ነበር። ይሁን እንጂ ጳውሎስ አንድ ሰው “ሰው በኢየሱስ ክርስቶስ በማመን እንዲጸድቅ እንጂ በሕግ ሥራ” አይጸድቅም ሲል አብራርቶአል። (ገላትያ 2:16) የሕግ ሥራዎች የቱንም ያህል ጻድቅ ወይም የተከበሩ መስለው ቢታዩ የክርስቶስ ቤዛ ከቀረበ በኋላ የሞቱ ሥራዎች ሆነዋል። መዳንም ሊያስገኙ አይችሉም። ስለዚህ ትክክለኛ የልብ ዝንባሌ ያላቸው አይሁዶች ከእነዚህ የሞቱ ሥራዎች ንስሐ በመግባት የአምላክን ሞገስ ለማግኘት ፈልገዋል። ንስሐ መግባታቸውን ለማሳየትም ተጠምቀዋል።—ሥራ 2:38
ከዚህ ምን እንማራለን? የሞቱ ሥራዎች መጥፎ ወይም ከሥነ ምግባር ውጭ በሆኑ ተግባሮች የተወሰኑ አይደሉም። በመንፈሳዊ ሙት፣ ከንቱ፣ ወይም ፍሬ ቢስ የሆኑ ድርጊቶችን ይጨምራሉ። ይሁን እንጂ ሁሉም ክርስቲያኖች ከመጠመቃቸው በፊት ከእነዚህ የሞቱ ሥራዎች ንስሐ ይገቡ የለምን? አዎ፣ ይገባሉ። ሆኖም በመጀመሪያው መቶ ዘመን የነበሩ አንዳንድ ክርስቲያኖች ቆየት ብለው ወደ መጥፎ ሥነ ምግባር አኗኗር ተመልሰዋል። (1 ቆሮንቶስ 5:1) እንዲሁም አይሁዳውያን ክርስቲያኖች የሞቱትን የሙሴ ሕግ ሥራዎች ወደ መጠበቅ ዞር ማለት ጀምረው ነበር። ጳውሎስ እነዚህን አይሁዶች ወደ እነዚህ የሞቱ ሥራዎች እንዳይመለሱ ማሳሰብ ነበረበት።—ገላትያ 4:21፤ 5:1
ራስን ከሞቱ ሥራዎች መጠበቅ
በዘመናችን ያሉ የይሖዋ ሕዝቦችም ተመልሰው በሞቱ ሥራዎች ወጥመድ እንዳይያዙ መጠንቀቅ ይገባቸዋል። ሥነ ምግባር የጎደለው ድርጊት እንድንፈጽም፣ ታማኞች እንዳንሆንና የጾታ ብልግና እንድንፈጽም የሚያደርጉ ተጽእኖዎች ከየአቅጣጫው ይመጡብናል። በየዓመቱ በሺህ የሚቆጠሩ ክርስቲያኖች በእነዚህ ተጽእኖዎች መሸነፋቸው የሚያሳዝን ነው። ንስሐ ካልገቡ ደግሞ ከክርስቲያን ጉባኤ ይወገዳሉ። ስለዚህ አንድ ክርስቲያን ከምንጊዜውም ይበልጥ በኤፌሶን 4:22-24 ላይ ያለውን የጳውሎስ ምክር መከተል ያለበት አሁን ነው። “ፊተኛ ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ። በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፣ ለእውነትም በሚሆን ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።”
እርግጥ ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈላቸው የኤፌሶን ክርስቲያኖች በአብዛኛው አዲሱን ሰው ቀደም ሲሉ የለበሱ ናቸው። ይሁን እንጂ ጳውሎስ አዲሱን ሰው መልበሳቸው የማያቋርጥ ሂደት መሆኑን እንዲገነዘቡ ረድቷቸዋል። ክርስቲያኖች የማያቋርጥ ጥረት ካላደረጉ በስተቀር በውስጣቸው በሚፈጠሩ አጥፊ የሆኑ አሳሳች ፍላጎቶች ተሸንፈው ወደ ሞቱ ሥራዎች ሊመለሱ ይችሉ ነበር። በዘመናችንም ቢሆን ሁኔታው ተመሳሳይ ነው። አዲሱ ሰው በአሮጌው የአኗኗር ልማዳችን እንዳይበከል ለመከላከል አዲሱን ሰው ለመልበስ የማያቋርጥ ጥረት ማድረግ አለብን። ከማንኛውም ዓይነት ክፉ የሆኑ የሥጋ ሥራዎች ሁሉ መራቅና እነዚህን ነገሮች መጥላት አለብን። መዝሙራዊው “[ይሖዋን አዓት] የምትወዱ ክፋትን ጥሉ” በማለት ይመክረናል።—መዝሙር 97:10
አብዛኞቹ የይሖዋ ምሥክሮች ይህን ምክር ስለሚከተሉና የሥነ ምግባር ንጽሕናቸውን ጠብቀው ስለሚኖሩ የሚመሰገኑ ናቸው። ይሁን እንጂ አንዳንድ ክርስቲያኖች በባሕርያቸው መጥፎዎች ባይሆኑም የመጨረሻ ውጤታቸው ግብ ዋጋ ቢስ ወይም ፍሬ ቢስ በሆኑ ሥራዎች ተጠምደዋል። ለምሳሌ አንዳንዶች ገንዘብ ወይም ቁሳዊ ሀብት ለማግኘት በሚያደርጉት መሯሯጥ ተውጠዋል። ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ “ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ” በማለት ያስጠነቅቃል። (1 ጢሞቴዎስ 6:9) ሌሎች ደግሞ ዓለማዊ ትምህርት ወጥመድ ሆኖባቸዋል። እርግጥ ነው፣ ሥራ ለማግኘት እስከተወሰነ ደረጃ ዓለማዊ ትምህርትም መከታተል ሊያስፈልግ ይችላል። ይሁን እንጂ አንዳንዶች ብዙ ጊዜ የሚጨርሰውን ከፍተኛ ዓለማዊ ትምህርት ለመከታተል ሲሉ ራሳቸውን በመንፈሳዊ ጎድተዋል።
አዎ፣ ብዙ ሥራዎች ከሥነ ምግባር አንፃር ሲታዩ ስህተት ላይሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ በሕይወታችን ላይ የሚጨምሩት ነገር ከሌለ ወይም የይሖዋ አምላክን ሞገስ የሚያስገኙልን ካልሆኑ የሞቱ ሥራዎች ናቸው። እንደነዚህ ዓይነት ሥራዎች ጊዜንና ኃይልን ይጨርሳሉ እንጂ መንፈሳዊ ጥቅምም ሆነ ዘላቂ ደስታ አያስገኙም።—ከመክብብ 2:11 ጋር አወዳድር።
ጠቃሚ የሆኑ መንፈሳዊ ሥራዎችን ለመሥራት ከፍተኛ ጥረት እያደረጋችሁ እንዳላችሁ ምንም አያጠራጥርም። ይሁን እንጂ ዘወትር ራሳችንን ብንመረምር እንጠቀማለን። በየጊዜው ራሳችሁን እንደዚህ እያላችሁ ልትጠይቁ ትችላላችሁ፦ ‘አስፈላጊ ባልሆነ ዓለማዊ ሥራ በመጠመዴ ምክንያት የአገልግሎትና የስብሰባዎች ተሳትፎዬ እየቀነሰ ነውን?’ ‘ብዙ ጊዜ በመዝናናት እያጠፋሁ ለግልና ለቤተሰብ ጥናት ጊዜ አጣለሁን?’ ‘ቁሳዊ ሀብት ለማግኘትና ለመጠበቅ ብዙ ጊዜና ኃይል እያጠፋሁ በጉባኤ ውስጥ ያሉትን ችግረኞች ማለትም የታመሙትንና በዕድሜ የገፉትን መርዳት ያቅተኛልን?’ ለእነዚህ ጥያቄዎች የምትሰጡት መልስ ለመንፈሳዊ ሥራዎች ትልቅ ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ መሆኑን ሊያስገነዝባችሁ ይችላል።
ጊዜያችሁን በይሖዋ አገልግሎት አስይዙት
1 ቆሮንቶስ 15:58 “የጌታም ሥራ ሁልጊዜ የሚበዛላችሁ ሁኑ” ይላል። ከእነዚህም ሥራዎች የመጀመሪያውን ደረጃ የሚይዙት የመንግሥቱ ስብከትና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ናቸው። ጳውሎስ በ2 ጢሞቴዎስ 4:5 ላይ “ምሥራቹን መስበክን የመላ ሕይወትህ ሥራ አድርገው። አገልግሎትህንም በትጋት ፈጽም” ሲል አበረታቷል። (ጀሩሳሌም ባይብል) በተጨማሪም ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ለመንጋው ፍላጎት በማሰብ የሚሠሩአቸው ብዙ ሥራዎች አሉ። (1 ጢሞቴዎስ 3:1, 5, 13፤ 1 ጴጥሮስ 5:2) የቤተሰብ ራሶች በተለይም አለአባት ወይም አለእናት ልጆቻቸውን የሚያሳድጉ ወላጆች ቤተሰባቸውን የመንከባከብና ልጆቻቸው ከይሖዋ ጋር ጥሩ ዝምድና መሥርተው እንዲያድጉ የመርዳት ከባድ ኃላፊነት አለባቸው። እነዚህ ሥራዎች አድካሚ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ የሚያበሳጩ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሁን እንጂ የሞቱ ሥራዎች ሳይሆኑ እውነተኛ እርካታ የሚያመጡ ናቸው።
ችግሩ ግን አንድ ሰው እነዚህን ሁሉ አስፈላጊ ሥራዎች የሚያከናውንበት ጊዜ እንዴት ሊያገኝ ይችላል? ራስን መገሰጽና የተደራጀ ኑሮ መኖር በጣም አስፈላጊዎች ናቸው። ጳውሎስ በ1 ቆሮንቶስ 9:26, 27 ላይ “ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም፣ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም፤ ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጎሰምሁ አስገዛዋለሁ” ሲል ጽፏል። የዚህን ጥቅስ መሠረተ ሐሳብ በሥራ ላይ የምናውልበት አንዱ መንገድ ዕለታዊ ተግባራችንንና የአኗኗር ዘይቤአችንን በየጊዜው መመርመር ነው። እንዲህ ካደረጋችሁ ልታስወግዷቸው የምትችሉአቸውን ጊዜአችሁንና ጉልበታችሁን የሚያባክኑ አስፈላጊ ያልሆኑ ብዙ ነገሮችን በሚገባ መለየት ትችላላችሁ።
ለምሳሌ አብዛኛው ጉልበታችሁና ጊዜአችሁ የሚያልቀው ቴሌቪዥን በመመልከት፣ በመዝናናት፣ ዓለማዊ ጽሑፎችን በማንበብ ወይም ለመዝናኛ ተብለው በሚሠሩ የትርፍ ጊዜ ሥራዎች ነውን? ዘ ኒው ዮርክ ታይምስ ላይ የወጣ አንድ ጽሑፍ እንደሚለው በዩናይትድ ስቴትስ የሚኖር አንድ ሙሉ ሰው በአማካይ “በሳምንት ከ30 ሰዓት በላይ ቴሌቪዥን በመመልከት ያሳልፋል።” ቴሌቪዥን በመመልከት የምናሳልፈውን ጊዜ ለተሻለ ነገር ልንጠቀምበት አንችልምን? የአንድ ተጓዥ የበላይ ተመልካች ሚስት “ጊዜዬን የሚያባክኑብኝን እንደ ቴሌቪዥን መመልከት የመሳሰሉትን ነገሮች ሙሉ በሙሉ አስወገድኩ” ስትል ተናግራለች። ታዲያ ምን ውጤት አገኘች? በሁለት ጥራዝ የተዘጋጀውን ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል የተባለውን የመጽሐፍ ቅዱስ ኢንሳይክሎፒዲያ ሙሉ በሙሉ አንብባ ለመጨረስ ችላለች!
በተጨማሪም አኗኗራችሁን እስከምን ድረስ ቀላል ለማድረግ እንደምትችሉ ማሰብ ሊያስፈልጋችሁ ይችላል። ሰለሞን እንዲህ ብሏል፦ “እጅግ ወይም ጥቂት ቢበላ የሠራተኛ እንቅልፍ ጣፋጭ ነው፣ የባለጠጋ ጥጋብ ግን እንቅልፍን ይከለክለዋል።” (መክብብ 5:12) አብዛኛውን ጊዜአችሁንና ጉልበታችሁን የምታውሉት አስፈላጊ ያልሆኑ ቁሳዊ ሀብቶችን ለማግኘትና ለመንከባከብ ነውን? ብዙ ነገሮች በኖሩን መጠን የምንጠብቃቸው፣ የምንጠግናቸውና ኢንሹራንስ የምናስገባቸው ነገሮች ይበዛሉ። አንዳንድ ነገሮችን ማስወገድ ሊጠቅማችሁ ይችል ይሆንን?
ጊዜአችሁን በተሻለ ሁኔታ ለመጠቀም የሚያስችላችሁ ሌላው መንገድ በሚገባ የታሰበበት ምክንያታዊ ፕሮግራም ማውጣት ነው። እንዲህ ዓይነት ፕሮግራም በሚወጣበት ጊዜ ለመዝናኛም የሚሆን ጊዜ መመደብ ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ ለመንፈሳዊ ጉዳዮች ቅድሚያ መስጠት አስፈላጊ ነው። በሁሉም የጉባኤ ስብሰባዎች አለማሰለስ ለመገኘት ጊዜ መመደብ ይኖርበታል። በተጨማሪም የትኞቹ ቀኖች ወይም ምሽቶች ለወንጌላዊነቱ ሥራ ሊውሉ እንደሚችሉ አስቀድማችሁ ልትወስኑ ትችላላችሁ። ፕሮግራማችሁን በጥንቃቄ በማውጣት በአገልግሎት ያላችሁን ድርሻ ከፍ ልታደርጉ ትችላላችሁ። ምናልባትም በየጊዜው ረዳት አቅኚ ሆናችሁ ለማገልገል ትችሉ ይሆናል። ይሁን እንጂ ለግልና ለቤተሰብ ጥናት እንዲሁም ለስብሰባዎች ዝግጅት ጊዜ መመደባችሁን አረጋግጡ። በሚገባ ከተዘጋጃችሁ ራሳችሁ ከስብሰባዎች ብዙ ጥቅም ለማግኘት ከመቻላችሁም በላይ በምትሰጡት ሐሳብ አማካኝነት ሌሎችን በተሻለ ሁኔታ “ለፍቅርና ለመልካም ሥራ ልታነቃቁ” ትችላላችሁ።—ዕብራውያን 10:24
ለጥናት በቂ ጊዜ ለማግኘት አንዳንድ ነገሮችን መሥዋዕት ማድረግ ሊያስፈልግ ይችላል። ለምሳሌ በዓለም ዙሪያ ያሉ የቤቴል ቤተሰቦች በዕለት ጥቅሱ ላይ ለመወያየት ሲሉ ማልደው ይነሳሉ። እናንተስ ማለዳ በመነሳት ለግል ጥናታችሁ ጥቂት ጊዜ ልትገዙ ትችላላችሁን? መዝሙራዊው “ለእርዳታ ወደ አንተ ለመጮህ እንድችል ገና ሳይነጋ በማለዳ ተነሳሁ፤ ቃሎችህን እጠብቅ ነበርና” ብሎአል። (መዝሙር 119:147) እርግጥ ማለዳ ለመነሳትና የሚቀጥለውንም ቀን በሚገባ አርፎ ለመጀመር የምትተኙበትን ጊዜ መወሰን ይኖርባችኋል።
ጊዜአችን በይሖዋ አገልግሎት የተያዘ መሆኑ የሚያስገኛቸው ጥቅሞች
‘የጌታ ሥራ የበዛልን’ ለመሆን ዕቅድ ማውጣት፣ ራስን መገሰጽና መስዋዕት ማድረግ ያስፈልጋል። ይሁን እንጂ በውጤቱ እጅግ ብዙ ጥቅሞችን ታገኛላችሁ። ስለዚህ ጊዜአችሁ የባዶነት ስሜትና ሥቃይ ብቻ በሚያስከትሉት የሞቱ ሥራዎች ሳይሆን በይሖዋ አገልግሎት ይያዝ። እምነታችንን ለማሳየት፣ የአምላክን ሞገስ ለማግኘትና በመጨረሻም የዘላለም ሕይወት ሽልማት ለመቀበል የምንችለው በእነዚህ ሥራዎች ነው!
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ምክንያታዊ የሆነ ፕሮግራም ማውጣት አንድ ክርስቲያን ጊዜውን ይበልጥ በጥበብ እንዲጠቀምበት ይረዳዋል