የይሖዋ መንፈስ ሕዝቡን ይመራል
“ቅዱስ መንፈስህም [መንፈስህ ጥሩ ነውና አዓት] በጽድቅ ምድር ይምራኝ።”—መዝሙር 143:10
1, 2. የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች የሚያስጨንቃቸው ነገር ምን ሊሆን ይችላል?
‘በጣም ተክዣለሁ! ማን ሊያጽናናኝ ይችላል? አምላክ ትቶኝ ይሆን?’ እንደዚህ ዓይነት ስሜት ተሰምቶህ ያውቃልን? ከሆነ እንዲህ ያለው ስሜት የሚሰማህ አንተ ብቻ አይደለህም። የይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች በበለጸገ መንፈሳዊ ገነት ውስጥ የሚኖሩ ቢሆኑም አንዳንድ ጊዜ የሚያሳዝኑ ችግሮች፣ መከራዎችና በሰው ልጆች ላይ የሚደርሱት ፈተናዎች ያጋጥሟቸዋል።—1 ቆሮንቶስ 10:13
2 ምናልባት በአንድ ዓይነት መከራ ወይም ከፍተኛ ጭንቀት በሚያስከትል ሁኔታ ረዘም ላለ ጊዜ ተቸግረህ ይሆናል። የምትወደው ሰው ስለሞተብህ ኀዘንና ከፍተኛ ብቸኝነት ተሰምቶህ ይሆናል። ወይም በምትወደው ወዳጅህ ሕመም ምክንያት ልብህ ተጨንቆ ይሆናል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታዎች ደስታና ሰላም ሊያሳጡና እምነትህንም ሳይቀር አስጊ ሁኔታ ላይ ሊጥሉብህ ይችላሉ። ታዲያ ምን ማድረግ ይኖርብሃል?
አምላክ መንፈሱን እንዲሰጥህ ለምነው
3. እንደ ሰላምና ደስታ የመሳሰሉትን ባሕሪያት የሚያሳጣችሁ ነገር ካጋጠማችሁ ምን ማድረግ ጥበብ ይሆናል?
3 ሰላምህን፣ ደስታህን ወይም ሌሎቹን አምላካዊ ባሕርያት የሚያሳጣህ ሁኔታ ካጋጠመህ የአምላክን መንፈስ ቅዱስ ወይም አንቀሳቃሽ ኃይል እንድታገኝ መጸለይ ጥበብ ይሆናል። ለምን? ምክንያቱም የይሖዋ መንፈስ አንድ ክርስቲያን ችግሮችን፣ መከራዎችንና ፈተናዎችን እንዲቋቋም የሚረዱትን መልካም ፍሬዎች ስለሚያፈራ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ ስለ “ሥጋ ሥራዎች” ካስጠነቀቀ በኋላ “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግስት፣ ቸርነት [ደግነት አዓት]፣ በጎነት [ጥሩነት አዓት]፣ እምነት፣ የውሃት [የዋህነት አዓት]፣ ራስን መግዛት ነው። እንደዚህ ያሉትን የሚከለክል ሕግ የለም” በማለት ጽፏል።—ገላትያ 5:19-23
4. አንድ ሰው አንድ ዓይነት ችግር ወይም ፈተና ሲያጋጥመው ችግሩን ለይቶ በጸሎት መግለጹ ተገቢ የሚሆነው ለምንድን ነው?
4 ባጋጠመህ ችግር ምክንያት የዋህነትህን ወይም ለስለስ ያለ የገርነት ጠባይህን ልታጣ እንደተቃረብህ ልትገነዘብ ትችላለህ። እንዲህ ከሆነ ይሖዋ አምላክ የየዋህነትን መንፈስ እንዲሰጥህ ለይተህ በመጸለይ ለምነው። አንድ ዓይነት ፈተና አጋጥሞህ ከሆነ በተለይ የሚያስፈልግህ ራስን የመግዛት ባሕርይ ነው። በእርግጥ እንዲህ ዓይነቱን ፈተና ለመቋቋም እንዲያስችልህና ከሰይጣን እንዲያስጥልህ፣ እንዲሁም ፈተናውን ለመታገሥ የሚያስፈልገውን ጥበብ እንዲሰጥህ መለኮታዊ እርዳታ እንድታገኝ መጸለይ ተገቢ ነው።—ማቴዎስ 6:13፤ ያዕቆብ 1:5, 6
5. በጸሎትህ ላይ የትኛውን የመንፈስ ፍሬ እንደምትለምን እስከማታውቅ ድረስ ሁኔታዎች በጣም አስጨናቂ ከሆኑ ምን ማድረግ ይቻላል?
5 ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ ሁኔታዎች በጣም የሚያሳዝኑ ወይም ግራ የሚያጋቡ ከመሆናቸው የተነሳ የትኛው የመንፈስ ፍሬ እንደሚያስፈልግህ አታውቅ ይሆናል። እንዲያውም ደስታ፣ ሰላም፣ የዋህነትና ሌሎቹም አምላካዊ ባሕርያት በአደጋ ላይ ሊወድቁ ይችላሉ። ታዲያ ምን ማድረግ አለብህ? መንፈስ ቅዱሱን ራሱን እንዲሰጥህና ይህም መንፈስ የሚያስፈልጉህን ፍሬዎች እንዲያበዛልህ አምላክን ለምነው። የሚያስፈልጉህ ፍሬዎች ፍቅር ወይም ደስታ ወይም ሰላም ወይም የእነዚህ የመንፈስ ፍሬዎች ጥምር ሊሆን ይችላል። አምላክ ሕዝቡን ለመምራት የሚጠቀመው በመንፈሱ ስለሆነ የመንፈሱን አመራር እንድትቀበል እንዲረዳህ ጸልይ።
ይሖዋ ለመርዳት ፈቃደኛ ነው
6. ኢየሱስ ሳያቋርጡ የመጸለይን አስፈላጊነት አጥብቆ ለተከታዮቹ ያሳሰባቸው እንዴት ነበር?
6 ኢየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርቱ ስለ ጸሎት እንዲያስተምራቸው በጠየቁት ጊዜ አጥብቆ ካሳሰባቸው ነገሮች አንዱ የአምላክ መንፈስ እንዲሰጣቸው እንዲጸልዩ ነበር። ኢየሱስ በመጀመሪያ ሳያቋርጡ እንዲጸልዩ የሚገፋፋቸው ምሳሌ ነገራቸው። “ከእናንተ ማናቸውም ወዳጅ ያለው ሰው በእኩል ሌሊትስ ወደ እርሱ ሄዶ፦ ወዳጄ ሆይ፣ ሦስት እንጀራ አበድረኝ፣ አንድ ወዳጄ ከመንገድ ወደ እኔ መጥቶ የማቀርብለት የለኝምና ይላልን? ያም ከውስጥ መልሶ፦ አታድክመኝ አሁን ደጁ ተቆልፎአል ልጆቼም ከእኔ ጋር በአልጋ ላይ አሉ ተነሥቼ ልሰጥህ አልችልም ይላልን? እላችኋለሁ፣ ወዳጅ ስለሆነ ተነሥቶ ባይሰጠው እንኳ ስለ ንዝነዛው ተነሥቶ የሚፈልገውን ሁሉ ይሰጠዋል” በማለት ነገራቸው።—ሉቃስ 11:5-8
7. በሉቃስ 11:11-13 ላይ ያሉት የኢየሱስ ቃላት ትርጉም ምንድን ነው? ስለ አምላክና ስለ መንፈሱ ምን ማረጋገጫ ይሰጡናል?
7 ይሖዋ ማንኛውንም ራሱን የወሰነ ታማኝ አገልጋይ ለመርዳት ፈቃደኛ ነው፣ ስለዚህም ልመናቸውን ይሰማል። ይሁን እንጂ እንዲህ ዓይነቱ ሰው ‘ሳያቋርጥ ከለመነ’ የሚለምነውን ነገር ከልብ እንደሚፈልገው ከማመልከቱም በላይ እምነት እንዳለው ያሳያል። (ሉቃስ 11:9, 10) ቀጥሎም ክርስቶስ “አባት ከሆናችሁ ከእናንተ ከማንኛችሁም ልጁ እንጀራ ቢለምነው እርሱም ድንጋይ ይሰጠዋልን? ዓሣ ደግሞ ቢለምነው በዓሣ ፈንታ እባብ ይሰጠዋልን? ወይስ እንቁላል ቢለምነው ጊንጥ ይሰጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠት ካወቃችሁ በሰማይ ያለው አባት ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መንፈስ ቅዱሱን ይሰጣቸው?” ብሏል። (ሉቃስ 11:11-13) አንድ ምድራዊ ወላጅ በወረሰው አለፍጽምና ምክንያት ይብዛም ይነስ ክፉ ቢሆንም ለልጆቹ መልካም ነገሮችን የሚሰጥ ከሆነ ሰማያዊ አባታችን መንፈስ ቅዱሱን እንዲሰጠው በትሕትና ለሚለምን ታማኝ አገልጋዩ እንደሚሰጥ ጥርጥር የለውም።
8. መዝሙር 143:10 በዳዊት፣ በኢየሱስና በአምላክ ዘመናዊ አገልጋዮች ላይ የሚሠራው እንዴት ነው?
8 ከአምላክ መንፈስ ተጠቃሚዎች ለመሆን ከፈለግን ዳዊት እንዳደረገው የመንፈሱን አመራር ለመከተል ፈቃደኞች መሆን አለብን። ዳዊት እንዲህ በማለት ጸልዮ ነበር፦ “አንተ አምላኬ ነህና ፈቃድህን ለማድረግ አስተምረኝ፤ ቅዱስ መንፈስህም [መንፈስህ ጥሩ ነውና አዓት] በጽድቅ መንገድ ይምራኝ።” (መዝሙር 143:10) የእሥራኤላውያን ንጉሥ በነበረው በሳኦል እንደ ሽፍታ ይታደን የነበረው ዳዊት አካሄዱ የቀና እንዲሆንለት የአምላክ መንፈስ እንዲመራው ፈልጎ ነበር። አብያታር አምላክን ለመጠየቅ የሚያገለግለውን የካህናት ኤፉድ ይዞ መጣለት። አብያታር የአምላክ ካህናዊ ወኪል ስለነበረ ይሖዋን ለማስደሰት ከፈለገ ሊሄድበት ስለሚገባው መንገድ ለዳዊት አስተምሮታል። (1 ሳሙኤል 22:17 እስከ 23:12፤ 30:6-8) ኢየሱስም እንደ ዳዊት በይሖዋ መንፈስ ይመራ ነበር። የክርስቶስ ቅቡዓን ተከታዮችም እንደዚሁ በአምላክ መንፈስ ተመርተዋል። እነዚህ ቅቡዓን ተከታዮቹ ከ1918-19 በነበረው ጊዜ ከሰው ልጅ ኅብረተሰብ ውጭ እንደሆኑ ተደርገው ታይተው ነበር፣ ሃይማኖታዊ ጠላቶቻቸውም ሊያጠፏቸው የሚችሉ መስሎአቸው ነበር። ቅቡዓኑ በመንፈሳዊ ሙት ከነበሩበት ሁኔታ እንዲወጡ ጸለዩና በ1919 አምላክ ለጸሎታቸው መልስ በመስጠት ታደጋቸው፣ በአገልግሎቱም እንደገና አነቃቃቸው። (መዝሙር 143:7-9) በእርግጥም የይሖዋ መንፈስ እስከ ዛሬ እያደረገ እንዳለው በዚያን ጊዜም ሕዝቡን ይረዳና ይመራ ነበር።
መንፈሱ የሚረዳው እንዴት ነው?
9. (ሀ) መንፈስ ቅዱስ “አጽናኝ [ረዳት አዓት]” በመሆን የሚያገለግለው እንዴት ነው? (ለ) መንፈስ ቅዱስ አካል እንዳልሆነ እንዴት እናውቃለን? (የግርጌ ማስታወሻውን ተመልከቱ።)
9 ኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ቅዱስን “አጽናኝ [ረዳት አዓት]” ብሎ ጠርቶታል። ለምሳሌ ያህል ለተከታዮቹ እንደሚከተለው ብሏቸው ነበር፦ “እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ [ረዳት አዓት] ይሰጣችኋል፤ እርሱም ዓለም የማያየውና የማያውቀው ስለሆነ ሊቀበለው የማይቻለው የእውነት መንፈስ ነው ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ ስለሚኖር በውስጣችሁም ስለሚሆን እናንተ ታውቃላችሁ።” ክርስቶስ “አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ [ረዳት አዓት] እርሱ ሁሉን ያስተምራችኋል እኔም የነገርኳችሁን ሁሉ ያሳስባችኋል” በማለት ቃል ስለገባ ይህ “አጽናኝ [ረዳት አዓት]” ከሚያደርጋቸው ብዙ ነገሮች አንዱ አስተማሪ መሆን ነው። በተጨማሪም መንፈሱ ስለ ክርስቶስ ይመሰክራል። ክርስቶስም ለደቀ መዛሙርቱ “እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል። እኔ ባልሄድ አጽናኙ [ረዳቱ አዓት] ወደ እናንተ አይመጣም፤ እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ” በማለት አረጋግጦላቸዋል።—ዮሐንስ 14:16, 17, 26፤ 15:26፤ 16:7a
10. መንፈስ ቅዱስ አጽናኝ ወይም ረዳት መሆኑ የታየው በምን መንገድ ነው?
10 ኢየሱስ በ33 እዘአ በዋለው የጰንጠቆስጤ ዕለት ቃል የገባውን መንፈስ ቅዱስ በተከታዮቹ ላይ አፈሰሰ። (ሥራ 1:4, 5፤ 2:1-11) መንፈስ ቅዱስ ረዳት እንደመሆኑ መጠን ስለ አምላክ ፈቃድና ዓላማ እየጨመረ የሚሄድ ዕውቀትና ማስተዋል ሰጣቸው፣ እንዲሁም ትንቢታዊ ቃሉን ከፈተላቸው። (1 ቆሮንቶስ 2:10-16፤ ቆላስይስ 1:9, 10፤ ዕብራውያን 9:8-10) ይህ ረዳት ወይም አጋዥ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት በምድር ሁሉ ምሥክሮቹ እንዲሆኑ የሚያስችላቸውን ኃይል ሰጥቷቸዋል። (ሉቃስ 24:49፤ ሥራ 1:8፤ ኤፌሶን 3:5, 6) በዛሬው ጊዜም አንድ ውስን ክርስቲያን አምላክ “በታማኝና ልባም ባሪያ” በኩል በሚያቀርባቸው መንፈሳዊ ዝግጅቶች ከተጠቀመ መንፈስ ቅዱስ በእውቀት እንዲያድግ ሊረዳው ይችላል። (ማቴዎስ 24:45-47) የአምላክ መንፈስ አንድ የይሖዋ አገልጋይ ምስክርነት ለመስጠት የሚያስፈልጉትን ብርታትና ጥንካሬ በመስጠት ሊረዳው ይችላል። (ማቴዎስ 10:19, 20፤ ሥራ 4:29-31) ይሁን እንጂ መንፈስ ቅዱስ የአምላክን ሕዝቦች በሌሎች መንገዶችም ይረዳል።
“በማይነገር መቃተት”
11. አንድ ክርስቲያን ያጋጠመው ችግር ሊወጣው የማይቻል መስሎ ከታየው ማድረግ የሚኖርበት ምንድን ነው?
11 አንድ ክርስቲያን ሊወጣው የማይችል መስሎ በሚታይ ችግር ከተዋጠ ምን ማድረግ ይኖርበታል? መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጠው መጸለይና መንፈሱም ሥራውን እንዲሠራ መፍቀድ ይኖርበታል። ጳውሎስ “እንዲሁም መንፈስ ደግሞ ድካማችንን ያግዛል፤ እንዴት እንድንጸልይ አናውቅምና፣ ነገር ግን መንፈስ ራሱ በማይነገር መቃተት ይማልድልናል፤ ልብንም የሚመረምረው የመንፈስ አሳብ ምን እንደሆነ ያውቃል፣ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ስለ ቅዱሳን ይማልዳልና” ብሏል።—ሮሜ 8:26, 27
12, 13. (ሀ) ሮሜ 8:26, 27 በተለይ በጣም ፈታኝ በሆኑ ሁኔታዎች ላይ የሚሠራው እንዴት ነው? (ለ) ጳውሎስና ባልደረቦቹ በእስያ አውራጃዎች በከፍተኛ ጭንቀት ላይ ሳሉ ምን አደረጉ?
12 የአምላክ መንፈስ የሚማልድላቸው እነዚህ ቅዱሳን ሰማያዊ ተስፋ ያላቸው የኢየሱስ ቅቡዓን ተከታዮች ናቸው። ነገር ግን ሰማያዊ ጥሪ ያለህም ሆንክ ምድራዊ ውርሻ፣ ክርስቲያን እንደመሆንህ መጠን የአምላክን መንፈስ ቅዱስ እርዳታ ልታገኝ ትችላለህ። አንዳንድ ጊዜ ይሖዋ ለአንድ የተወሰነ ልመና ቀጥተኛ መልስ ይሰጣል። ይሁን እንጂ አንዳንድ ጊዜ በጣም ከመጨነቅህ የተነሳ ስሜቶችህን በቃላት ለመግለጽ የማትችል ትሆንና እንዲሁ ብቻ በማይነገር መቃተት ይሖዋን ትማጸን ይሆናል። እንዲያውም መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥህ ካልጸለይክ በቀር ለአንተ ከሁሉ የተሻለው ነገር ምን እንደሆነ ሳታውቅ ያልሆነ ነገር እንዲደረግልህ ትለምን ይሆናል። የአምላክ ፈቃድ እንዲሆን እንደምትፈልግ አምላክ ያውቃል፣ በእርግጥ የሚያስፈልግህ ነገር ምን እንደሆነም ያውቃል። ከዚህም በላይ በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት በፈታኝ ሁኔታዎች ወቅት የሚቀርቡ ብዙ ጸሎቶች በቃሉ ውስጥ እንዲመዘገቡ አድርጓል። (2 ጢሞቴዎስ 3:16, 17፤ 2 ጴጥሮስ 1:21) ስለዚህ አንተም ከይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች አንዱ እንደመሆንህ መጠን ልትገልጽ የፈለግኸው እንዲህ በመሰሉት በመንፈስ መሪነት የተጻፉ ጸሎቶች ላይ የተገለጹትን ስሜቶች እንደሆነ ተመልክቶ መልስ ሊሰጥህ ይችላል።
13 ጳውሎስና ባልደረቦቹ በእስያ አውራጃዎች መከራ ሲደርስባቸው ሳሉ ምን እንደሚለምኑ አላወቁ ሊሆን ይችላል። ‘ከአቅማቸው በላይ በሆነ ጭንቀት ላይ ሳሉ በውስጣቸው የሞት ፍርድ የተቀበሉ መስሎ ተሰምቷቸው ነበር።’ ይሁን እንጂ ሌሎች ስለ እነርሱ እንዲጸልዩላቸው ፈልገው ነበር፣ ሙታንን ለማስነሳት በሚቻለው አምላክም ተማምነው ነበር፤ እርሱም በእርግጥ አድኗቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 1:8-11) ይሖዋ አምላክ የታማኝ አገልጋዮቹን ጸሎቶች የሚሰማና መልስም የሚሰጥ መሆኑ እንዴት የሚያጽናና ነው!
14. ይሖዋ አንድ ችግር ለጥቂት ጊዜ እንዲቀጥል ቢፈቅድ ምን ጥሩ ውጤት ሊገኝ ይችላል?
14 የአምላክ ሕዝቦች ብዙውን ጊዜ በድርጅት ደረጃ ፈታኝ ሁኔታዎች ይደርሱባቸዋል። ቀደም ሲል እንደተገለጸው በአንደኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ስደት ደርሶባቸው ነበር። በዚያን ጊዜ ሁኔታቸውን በግልጽ ያልተረዱና ምን መለመን እንደነበረባቸው በትክክል የማያውቁ ቢሆኑም ይሖዋ ምላሽ የሰጣቸው ትንቢታዊ ጸሎቶች በቃሉ ውስጥ ይገኙ ነበር። (መዝሙር 69, 102, 126፤ ኢሳይያስ ምዕራፍ 12) ይሁን እንጂ ይሖዋ አንድን ፈተና ለጥቂት ጊዜ እንዲቀጥል ቢፈቅድስ? ይህ ሁኔታ ምስክርነቱ እንዲዳረስ ሊያደርግ፣ አንዳንድ ሰዎች እውነትን እንዲቀበሉ ሊያነሳሳቸውና ክርስቲያኖች መከራ የሚደርስባቸውን የእምነት ባልደረቦች በጸሎትም ሆነ በሌላ መንገድ በመርዳት የወንድማማች ፍቅር እንዲያሳዩ የሚያስችላቸው አጋጣሚ የሚሰጣቸው ሊሆን ይችላል። (ዮሐንስ 13:34, 35፤ 2 ቆሮንቶስ 1:11) ይሖዋ ሕዝቡን በመንፈስ ቅዱሱ አማካኝነት እንደሚመራ፣ ለእነርሱም ከሁሉ የተሻለውን ነገር እንደሚያደርግና ሁልጊዜ ቅዱስ ስሙን በሚያስከብርና በሚያስቀድስ መንገድ ነገሮችን እንደሚያሳካ አስታውስ።—ዘጸአት 9:16፤ ማቴዎስ 6:9
መንፈሱን ፈጽሞ አታሳዝኑ
15. ክርስቲያኖች የይሖዋ መንፈስ ስለ እነርሱ ሆኖ ምን እንዲያደርግላቸው ሊተማመኑበት ይችላሉ?
15 የይሖዋ አገልጋይ ከሆንክና በችግርና በሌላም ጊዜ መንፈስ ቅዱሱን እንዲሰጥህ ለምነው። ከዚያም ጳውሎስ “ለቤዛም ቀን የታተማችሁበትን ቅዱሱን የእግዚአብሔርን መንፈስ አታሳዝኑ” በማለት ስለጻፈ አመራሩን ለመከተል አታወላውል። (ኤፌሶን 4:30) የአምላክ መንፈስ ለታማኝ ቅቡዓን ክርስቲያኖች ‘ለሚመጣው ነገር [ማለትም የማይሞት ሰማያዊ ሕይወት] እንደ መያዣ የሚያገለግል’ ማህተም ነበር፣ ዛሬም ነው። (2 ቆሮንቶስ 1:22፤ ሮሜ 8:15፤ 1 ቆሮንቶስ 15:50-57፤ ራእይ 2:10) ቅቡዓን ክርስቲያኖችም ሆኑ ምድራዊ ተስፋ ያላቸው ክርስቲያኖች ስለ እነርሱ ሆኖ ብዙ ሊሠራላቸው እንደሚችል በይሖዋ መንፈስ ሊተማመኑ ይችላሉ። በታማኝነት መንገድ ሊመራቸውና የአምላክን ሞገስና ቅዱስ መንፈሱን ወደማጣትና እንዲሁም የዘላለምን ሕይወት እንዳያገኙ ወደማድረግ ከሚያደርሱ የኃጢአተኝነት ሥራዎች እንዲርቁ ሊረዳቸው ይችላል።—ገላትያ 5:19-21
16, 17. አንድ ክርስቲያን መንፈስ ቅዱስን ሊያሳዝን የሚችለው እንዴት ሊሆን ይችላል?
16 ታዲያ አንድ ክርስቲያን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ መንፈሱን ሊያሳዝን የሚችለው እንዴት ነው? ይሖዋ መንፈሱን በጉባኤ ውስጥ አንድነት ለማስፈንና ኃላፊነት የሚወስዱ ሰዎችን ለመሾም ይጠቀምበታል። ስለዚህ አንድ የጉባኤ አባል በተሾሙት ሽማግሌዎች ላይ የሚያጉረመርም፣ የስም አጥፊነት ሐሜት የሚያስፋፋና የመሳሰሉትን የሚያደርግ ከሆነ ወደ ሰላምና አንድነት የሚያደርሰውን የአምላክን መንፈስ አመራሮች እየተከተለ አይደለም። ጠቅለል ባለ አነጋገር የአምላክን መንፈስ የሚያሳዝን ይሆናል።—1 ቆሮንቶስ 1:10፤ 3:1-4, 16, 17፤ 1 ተሰሎንቄ 5:12, 13፤ ይሁዳ 16
17 ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበሩ ክርስቲያኖች ሲጽፍላቸው ሐሰትን ከመናገር፣ ከቂም፣ ከስርቆት፣ ከክፉ ቃል፣ ዝሙትን ከመመኘት፣ ከሚያሳፍር ጠባይና ከነውረኛ ቀልድ እንዲርቁ አስጠንቅቋል። አንድ ክርስቲያን ወደ እነዚህ ነገሮች የሚያዘነብል ከሆነ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ካለው በመንፈስ መሪነት የተጻፈ ምክር ጋር በሚቃረን መንገድ መሄድ ይሆንበታል። (ኤፌሶን 4:17-29፤ 5:1-5) አዎ፣ በዚያው ልክ የአምላክን መንፈስ ማሳዘን ይሆንበታል።
18. አንድ ክርስቲያን በአምላክ መንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን ቃል ምክር ችላ ማለት ቢጀምር ምን ሊደርስበት ይችላል?
18 እንደ እውነቱ ከሆነ በይሖዋ መንፈስ መሪነት በተጻፈው ቃሉ ውስጥ ያለውን ምክር ችላ ማለት የሚጀምር ማንኛውም ክርስቲያን ሆን ተብሎ ወደሚደረግ ኃጢአትና መለኮታዊውን ሞገስ ወደ ማጣት የሚያደርሱ ዝንባሌዎችን ወይም ጠባዮችን ማሳደግ ሊጀምር ይችላል። ለጊዜው ኃጢአት እየሠራ ባይሆንም ወደዚያው አቅጣጫ እያመራ ሊሆን ይችላል። ከመንፈሱ አመራር በመቃረን የሚሄድ እንዲህ ዓይነቱ ክርስቲያን መንፈሱን ያሳዝናል። እንዲህ በማድረጉም የመንፈስ ቅዱስ ምንጭ የሆነውን ይሖዋን የሚቃወምና የሚያሳዝን ይሆናል። አምላክን የሚወድ ሰው ደግሞ እንዲህ ያለውን ድርጊት ሊፈጽም አይፈልግም!
መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጣችሁ መጸለያችሁን ቀጥሉ
19. የይሖዋ ሕዝቦች በተለይ ዛሬ መንፈሱ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
19 የይሖዋ አገልጋይ ከሆንክ መንፈስ ቅዱስ እንዲሰጥህ ሳታቋርጥ ጸልይ። በተለይም መኖር አስጨናቂ በሆነባቸው በእነዚህ “የመጨረሻ ቀኖች” ክርስቲያኖች የአምላክ መንፈስ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል። (2 ጢሞቴዎስ 3:1-5) በአሁኑ ጊዜ ከሰማይ ወደ ምድር ተወርውረው የተጣሉት ሰይጣንና አጋንንቱ በይሖዋ ድርጅት ላይ በቁጣ ተነስተዋል። ስለዚህ ዛሬ የአምላክ ሕዝቦች ከመቼውም ጊዜ ይበልጥ እንዲመራቸውና መከራዎችንና ስደትን እንዲታገሡ እንዲያስችላቸው የአምላክ መንፈስ ያስፈልጋቸዋል።—ራእይ 12:7-12
20, 21. የይሖዋን ቃል፣ መንፈስና ድርጅት አመራር መከተል አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
20 ይሖዋ አምላክ በቅዱስ መንፈሱ አማካኝነት ለሚሰጠው እርዳታ ምንጊዜም አድናቆት አሳይ። በመንፈሱ መሪነት የተጻፈው ቃሉ መጽሐፍ ቅዱስ የሚሰጠውን መመሪያ ተከተል። በመንፈስ ከሚመራው የአምላክ ምድራዊ ድርጅት ጋር ሙሉ በሙሉ ተባበር። መንፈስ ቅዱስን ማሳዘን በመጨረሻው ከመንፈሱ መውጣትንና ብሎም መንፈሳዊ ጥፋትን ስለሚያደርስ ሐሳባችሁ ቅዱስ መንፈሱን ወደሚያሳዝን ቅዱስ ጽሑፋዊ ያልሆነ አካሄድ ዘወር እንዲል ፈጽሞ አትፍቀዱ።—መዝሙር 51:11
21 ይሖዋን ለማስደሰትና ሰላማዊና ደስተኛ ሕይወት ለመኖር የሚቻለው በይሖዋ መንፈስ በመመራት ብቻ ነው። በተጨማሪም ኢየሱስ መንፈስ ቅዱስን “አጽናኝ” ወይም “አጋዥ” ብሎ እንደጠራው አስታውሱ። (ዮሐንስ 14:16, የግርጌ ማስታወሻ) በእርሱም አማካኝነት አምላክ ክርስቲያኖችን ያጽናናል ችግሮቻቸውንም ሁሉ እንዲቋቋሙ ያጠነክራቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) የአምላክ መንፈስ የይሖዋ ሕዝቦች የምሥራቹን እንዲሰብኩና ጥሩ ምስክርነት ለመስጠት የሚያስፈልጉትን ቅዱስ ጽሑፋዊ ቁም ነገሮች እንዲያስታውሱ ኃይል ይሰጣቸዋል። (ሉቃስ 12:11, 12፤ ዮሐንስ 14:25, 26፤ ሥራ 1:4-8፤ 5:32) ክርስቲያኖች በጸሎትና በመንፈሱ አመራር አማካኝነት የእምነት ፈተናዎችን በሰማያዊ ጥበብ ሊወጧቸው ይችላሉ። ስለዚህ በሁሉም የሕይወት ገጽታዎች የአምላክን ቅዱስ መንፈስ ለማግኘት መጸለያቸውን ይቀጥላሉ። በዚህም ምክንያት የአምላክ ሕዝቦች በይሖዋ መንፈስ ይመራሉ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a መንፈስ ቅዱስ “አጽናኝ [ረዳት አዓት]” በመባል ስብዕና ቢሰጠውም በግሪክኛው የተሰጠው ፆታ የግዑዝ ፆታ ወይም አነስታይ ወይም ተባዕታይ መሆኑን የማያመለክት ስለሆነ መንፈስ ቅዱስ ስብዕና ያለው አካል አይደለም። በተመሳሳይም ለጥበብ አነስታይ ተውላጠ ስም ተሰጥቶት ስብዕና እንዳለው ተደርጎ ተገልጾአል። (ምሳሌ 1:20-33፤ 8:1-36) ከዚህም በላይ መንፈስ ቅዱስ “ፈሰሰ” ተብሎ ስለተገለጸ አካል ቢሆን ኖሮ ሊፈስ አይችልም ነበር።—ሥራ 2:33
ምን ብላችሁ ትመልሳላችሁ?
◻ የይሖዋ ቅዱስ መንፈስ እንዲሰጠን መጸለይ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
◻ መንፈስ ቅዱስ አጽናኝ ወይም ረዳት የሆነው እንዴት ነው?
◻ መንፈስን ማሳዘን ማለት ምን ማለት ነው? ይህን ከማድረግ ልንርቅ የምንችለውስ እንዴት ነው?
◻ የአምላክ መንፈስ እንዲሰጠን ሳናቋርጥ መጸለይና አመራሩን መከተል ያለብን ለምንድን ነው?
[በገጽ 15 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
አንድ አፍቃሪ አባት ለልጁ ጥሩ ነገሮችን እንደሚሰጥ ይሖዋም መንፈስ ቅዱሱን እንዲሰጣቸው ለሚለምኑት አገልጋዮቹ ይሰጣቸዋል
[በገጽ 17 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
የአምላክ መንፈስ ለሚጸልዩ ክርስቲያኖች እንዴት እንደሚማልድላቸው ታውቃለህ?