በአምላክ ቃል የሚነግዱ አልነበሩም
“ገንዘብ እያስከፈልን የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ሰጠን።” እነዚህ ቃላት አንድ “በስልክ ጸሎት ያደርጉ የነበሩ ቄስ” በ1991 ማለቂያ አካባቢ በአሜሪካ የቴሌቪዥን ወንጌላውያን የምርመራ ሪፖርት ላይ ቃለ ምልልስ ሲደረግላቸው የተናገሯቸው ነበሩ።
ይህ ፕሮግራም በዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በሚገኙ ሦስት የቴሌቪዥን ወንጌላውያን ላይ ያተኮረ ነበር። ሕዝቦች በእነዚህ ሦስት የቴሌቪዥን ወንጌላውያን ብቻ በየዓመቱ በአሥር ሚልዮኖች የሚቆጠር ገንዘባቸውን እየተገፈፉ እንደሆኑ ይህ ምርመራ ገልጿል። አንዱ “የወንጌል አገልግሎት” “እርዳታ የመሰብሰቢያ ዘመናዊ ዘዴ” እንደሆነ ተደርጎ ተገልጿል። ሦስቱም ወንጌላውያን በበርካታ የማጭበርበር ድርጊቶች ተካፋዮች ናቸው። ይህ ያስደነግጥሃልን?
ሃይማኖት ምርመራ እየተደረገበት ነው
የቴሌቪዥን ወንጌላውያን ብቻ ሳይሆኑ ለአያሌ ክፍለ ዘመናት ተደራጅተው የቆዩ ነባር ሃይማኖቶችም እንኳን በመንግሥትና አባካኝነትን ወይም ሕገ ወጥ ተግባሮችን በሚቆጣጠሩ የግል ድርጅቶች እንዲሁም በጠቅላላው በሕዝቡ የምርመራ ትኩረት እየተደረገባቸው ነው። በአንዳንድ ሁኔታዎች የቤተ ክርስቲያን የአክሲዮን ንግድ ባለቤት መሆን፣ በሃይማኖት ገንዘብ የሚካሄዱ ፖለቲካዊ ዓላማዎችና ከፍተኛ ደመወዝ የሚከፈላቸው ቀሳውስት የተንደላቀቀ ኑሮ መኖራቸው አግባብነት ያለው ስለመሆኑ ጥያቄዎች እያስነሳ ነው።
አንዳንድ ሃይማኖታዊ መሪዎች ሐዋርያው ጳውሎስ ከ2,000 ዓመታት በፊት ስለ ወንጌል አገልግሎት ከሰጠው መግለጫ አንፃር ሲመዘኑ በምን አቋም ላይ ይገኛሉ? “የእግዚአብሔርን ቃል ቀላቅለው እንደሚሸቃቅጡት አይደለንምና፤ በቅንነት ግን ከእግዚአብሔር እንደተላክን በእግዚአብሔር ፊት በክርስቶስ ሆነን እንናገራለን” በማለት ጽፏል። (2 ቆሮንቶስ 2:17) ታዲያ በአሁኑ ጊዜ ይህ መግለጫ ለእነማን ተስማሚ ነው?
ጉዳዮቹን ለማመዛዘን እንድትችል የጳውሎስና የባልደረቦቹ ክርስቲያናዊ አገልግሎት የገንዘብ ድጋፍ የሚያገኘው እንዴት እንደነበረ ቀረብ ብለን እንመልከት። የጳውሎስና የባልደረቦቹ ክርስቲያናዊ አገልግሎት በዘመኑ ከነበሩት ከሌሎቹ ይለይ የነበረው እንዴት ነበር?
የመጀመሪያው መቶ ዘመን ተጓዥ ሰባኪዎች
በተጓዥ ሰባኪነት የሚሠራው ጳውሎስ ብቻ አልነበረም። በዚያ ዘመን ብዙዎች በሃይማኖትና በፍልስፍና ላይ የነበራቸውን አመለካከት ለማስፋፋት ከቦታ ወደ ቦታ ይጓዙ ነበር። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊው ሉቃስ “አጋንንትን እያወጡ ይዞሩ ከነበሩት አይሁድ አንዳንዶቹ” በማለት ተናግሯል። (ሥራ 19:13) ኢየሱስ ክርስቶስ ፈሪሳውያንን ሲያወግዝ “አንድ ሰው ልታሳምኑ በባሕርና በደረቅ ስለምትዞሩ” በማለት ጨምሮ ተናግሯል። (ማቴዎስ 23:15) ኢየሱስ ራሱ ተጓዥ አገልጋይ ነበር። ሐዋርያቱና ደቀ መዛሙርቱ በይሁዳና በሰማርያ ብቻ ሳይሆን “እስከ ምድር ዳርም ድረስ” በመስበኩ እርሱን እንዲመስሉት አሠልጥኖአቸዋል።—ሥራ 1:8
የኢየሱስ ተከታዮች በጉዟቸው ወቅት አይሁዳዊ ያልሆኑ ሰባኪዎችንም አግኝተው ነበር። ጳውሎስ በአቴና ኤፊቆሮሳውያንና ኢስጦኢኮች ከሚባሉ ፈላስፎች ጋር ተጋጭቶ ነበር። (ሥራ 17:18) ሰዎች ሁሉ የራስ ወዳድነት ፀባይ አላቸው ብለው የሚያምኑ በእንግሊዝኛ ሲኒክስ የሚባሉ ሰዎች በሮማ ግዛት በሙሉ ረጅም ንግግር በማድረግ ሐሳባቸውን በኃይል ለማሳመን ይሞክሩ ነበር። የግሪክ ፍልስፍና ተከታዮች ሕዝቦችን እየሰበሰቡ ለማሳመን በሚሞክሩ አይሲስና ሰራፒስ የሚባሉ ደጋፊዎች አማካኝነት ከነፃ ሰዎች ጋር ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ እኩልነት ታገኛላችሁ በሚል ተስፋ ተጽእኖውን በሴቶችና በባሪያዎች ላይ ያስፋፉ ነበር። የምሥራቅ የመዋለድ አምልኮ ተከታዮች ለበርካታ የግሪኮ-ሮማ ዓለም ምስጢራዊ ሃይማኖቶች መንስኤ ሆነዋል። ከኃጢአት ስርየት የማግኘት ተስፋና ከመለኮታዊ ምስጢሮች ተካፋይ የመሆን ፍላጎት ብዙ ተከታዮችን ዲሜትር፣ ዲዮኒሰስና ሲቤሌ ወደተባሉት የሐሰት አማልክት ስቦአል።
ወጪዎች የሚሸፈኑት እንዴት ነበር?
ይሁን እንጂ ጉዞ ብዙ ገንዘብ የሚያስወጣ ነበር። ለጋሪ መጓጓዣ፣ ከኬላ ቀረጥና ከመርከብ ጉዞ ወጪ በተጨማሪ ተጓዦች ምግብ፣ ለአልቤርጎ ኪራይ፣ ማገዶ፣ ልብስና የጤና እንክብካቤ ያስፈልጋቸው ነበር። ሰባኪዎች፣ አስተማሪዎች፣ ፈላስፋዎችና አስማተኞች እነዚህን ፍላጎቶቻቸውን የሚያሟሉት በአምስት ዋና ዋና መንገዶች ነበር፦ (1) ተቀጥረው በማስተማር፣ (2) ዝቅተኛ ሥራዎችን ተቀጥረው በመሥራትና በመነገድ፣ (3) የሚደረግላቸውን መስተንግዶና በፈቃደኝነት የሚሰጡ እርዳታዎችን በመቀበል፣ (4) ወደ ሀብታም በጎ አድራጊዎች በመጠጋት፣ ብዙውን ጊዜም የልጆቻቸው አስተማሪዎች በመሆን እና (5) በመለመን። ዲዮጂነስ የሚባል ታዋቂ ለማኝ ሲኒክ ለምኖ መጽዋች ቢያጣ ለሚሰማው ስሜት ራሱን ለማዘጋጀት ሲል ሕይወት የሌላቸውን ምስሎችም እንኳን ሳይቀር ምጽዋት ለምኗል።
ጳውሎስ ክርስቲያን አገልጋዮች እንደሆኑ የሚናገሩ ነገር ግን እንደ አንዳንዶቹ የግሪክ ፈላስፋዎች ከሀብታሞች ጋር የተወዳጁና ድሆችን የሚዘርፉ አንዳንድ ሰባኪዎችን ያውቅ ነበር። የቆሮንቶሱን ጉባኤ “ማንም ቢበላችሁ፣ ማንም ቢቀማችሁ . . . ትታገሣላችሁና” በማለት ወቅሷቸዋል። (2 ቆሮንቶስ 11:20) ኢየሱስ ክርስቶስ ምንም ነገር ከሰው ወስዶ አያውቅም፣ ጳውሎስና እርሱን መሰል ሰባኪዎችም ቢሆኑ ከሰዎች ምንም ነገር ወስደው አያውቁም። ነገር ግን የቆሮንቶስ ስግብግብ ወንጌላውያን “ውሸተኞች ሐዋርያትና ተንኮለኞች ሠራተኞች” የሆኑ የሰይጣን አገልጋዮች ነበሩ።—2 ቆሮንቶስ 11:13-15
ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጣቸው መመሪያ ተቀጥሮ ማስተማርን የሚከለክል ነበር። “በከንቱ ተቀበላችሁ፣ በከንቱ ስጡ” በማለት መክሮአቸዋል። (ማቴዎስ 10:8) ልመና የተለመደ ነገር ቢሆንም በዚያ ዘመን በንቀት ይታይ ነበር። ኢየሱስ ከሰጣቸው ምሳሌዎች በአንዱ ላይ አንድ መጋቢ “መለመንም አፍራለሁ” እንዳለ ገልጾአል። (ሉቃስ 16:3) ስለዚህ በመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ ውስጥ የኢየሱስ ታማኝ ተከታዮች ገንዘብም ይሁን ሌላ ዕቃ እንደለመኑ የሚናገር ቃል አናገኝም። “ሊሠራ የማይወድ አይብላ” በሚለው መሠረታዊ ሥርዓት እየተመሩ ሠርተዋል።—2 ተሰሎንቄ 3:10
ደቀ መዛሙርቱ የሚያስፈልጋቸውን ነገር በሁለት መንገዶች እንዲያሟሉ ኢየሱስ አበረታቷል። አንደኛ፣ ሐዋርያው ጳውሎስ እንደገለጸው “በወንጌሉ” አማካኝነት በመኖር ነው። እንዴት? በፈቃደኝነት የሚደረግላቸውን መስተንግዶ በመቀበል ነው። (1 ቆሮንቶስ 9:14፤ ሉቃስ 10:7) ሁለተኛ፣ የሚያስፈልጋቸውን ቁሳዊ ነገሮች ሠርተው በማግኘት ነበር።—ሉቃስ 22:36
ጳውሎስ በሥራ ያዋላቸው መሠረታዊ ሥርዓቶች
ጳውሎስ ከላይ የተጠቀሰውን መሠረታዊ ሥርዓት በሥራ ላይ ያዋለው እንዴት ነበር? የሐዋርያውን ሁለተኛ ሚስዮናዊ ጉዞ በሚመለከት ሉቃስ “ከጢሮአዳም ተነስተን በቀጥታ ወደ ሳሞትራቄ በነገውም ወደ ናጱሌ በመርከብ ሄድን፤ ከዚያም ወደ ፊልጵስዩስ ደረስን፤ እርስዋም የመቄዶንያ ከተማ ሆና፣ የወረዳ ዋና ከተማና ቅኝ አገር ናት በዚችም ከተማ አንዳንድ ቀን እንቀመጥ ነበር” በማለት ጽፎአል። በሚያደርጉት ጉዞ ሁሉ መጓጓዣቸውን፣ ቀለባቸውንና ለአልቤርጎ ኪራይ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ ራሳቸው በግል ያሟሉ ነበር።—ሥራ 16:11, 12
በመጨረሻም ልድያ የምትባል ሴት “ጳውሎስ የሚናገረውን [ተቀበለች።] እርስዋም ከቤተ ሰዎችዋ ጋር ከተጠመቀች በኋላ ‘በጌታ የምታምን እንድሆን ከፈረዳችሁልኝ ወደ ቤቴ ገብታችሁ ኑሩ’ ብላ ለመነችን፤ በግድም [አስገባችን።]” (ሥራ 16:13-15) ጳውሎስ በፊልጵስዩስ ለነበሩ መሰል አማኞች “ሁልጊዜ በጸሎቴ ሁሉ ስለ እናንተ ሁሉ በደስታ እየጸለይሁ፣ ከፊተኛው ቀን እስከ ዛሬ ድረስ ወንጌልን በመስበክ አብራችሁ ስለ ሠራችሁ፣ ባሰብኋችሁ ጊዜ ሁሉ አምላኬን አመሰግናለሁ” ብሎ ሊጽፍ የበቃው ቢያንስ በልድያ የእንግድነት አቀባበል ምክንያት ሳይሆን አይቀርም።—ፊልጵስዩስ 1:3-5
ሉቃስ ለእነዚህ ተጓዥ ክርስቲያን ሠራተኞች የእንግድነት አቀባበል ያደረጉ በርካታ ሰዎችን ይጠቅሳል። (ሥራ 16:33, 34፤ 17:7፤ 21:7, 8, 16፤ 28:2, 7, 10, 14) ጳውሎስ በመንፈስ አነሳሽነት በጻፋቸው መልእክቶቹ ውስጥ የተቀበለውን መስተንግዶና ስጦታ ገልጾ ምስጋና አቅርቧል። (ሮሜ 16:23፤ 2 ቆሮንቶስ 11:9፤ ገላትያ 4:13, 14፤ ፊልጵስዩስ 4:15-18) ሆኖም እርሱም ሆነ ጓደኞቹ ስጦታ ወይም ገንዘብ ነክ ድጋፍ እንዲሰጣቸው ለወንድሞች ፍንጭ ሰጥተው አያውቁም። የይሖዋ ምስክሮች ይህ መልካም ዝንባሌ አሁንም በተጓዥ የበላይ ተመልካቾቻቸው ላይ እንደሚታይ ሊናገሩ ይችላሉ።
በሚደረግለት መስተንግዶ ብቻ ተማምኖ የሚኖር አልነበረም
ጳውሎስ ሊደረግለት የሚችለውን መስተንግዶ ተማምኖ የሚኖር አልነበረም። ከባድ ሥራንና ረዥም ሰዓትን የሚጠይቅ ቢሆንም አነስተኛ ገቢ የሚያስገኝ የእጅ ሙያ ተምሮ ነበር። ሐዋርያው ሚስዮናዊ ሆኖ ቆሮንቶስ በደረሰ ጊዜ “አቂላ የሚሉትን አንድ አይሁዳዊ [ከሚስቱ ከጵርስቅላ ጋር] አገኘ፤ . . . ሥራቸውም አንድ ስለነበረ በእነርሱ ዘንድ ተቀምጦ በአንድ ላይ ሠሩ ሥራቸው ድንኳን መስፋት ነበርና።”—ሥራ 18:1-3
በኋላም በኤፌሶን ጳውሎስ በርትቶ ይሠራ ነበር። (ከሥራ 20:34ና ከ1 ቆሮንቶስ 4:11, 12 ጋር አወዳድር።) ከትውልድ ከተማው አካባቢ በሚገኝ ሲሌሲየም በሚባል ሻካራ የፍየል ጠጉር ድንኳን የመሥራትን ጥሩ ችሎታ ሳያዳብር አይቀርም። ጳውሎስ በርጩማ ላይ ተቀምጦ በሚሠራበት ጠረጴዛ ላይ ተጎንብሶ እስኪጨልም ድረስ ሲቆርጥና ሲሰፋ በዓይነ ሕሊናችን ሊታየን ይችላል። ድንኳን ሲሰፋ የሚረብሽ ድምፅ ስለማይኖረው ጳውሎስ በልፋት እየሠራ ለሱቁ ባለቤት፣ ለሠራተኞቹ፣ ለባሪያዎቹ፣ ለደንበኞቹና ለጓደኞቹ ለመመስከር አጋጣሚ ሳይኖረው አይቀርም።—ከ1 ተሰሎንቄ 2:9 ጋር አወዳድር።
ሚስዮናዊው ጳውሎስ አገልግሎቱን መነገጃ ለማድረግ ወይም በምንም መንገድ የአምላክን ቃል የገንዘብ ትርፍ ለማግኘት መጠቀሚያ ለማድረግ አልፈቀደም። ለተሰሎንቄ ሰዎች “እኛን ልትመስሉ እንዴት እንደሚገባችሁ ራሳችሁ ታውቃላችሁና፤ በእናንተ ዘንድ ያለ ሥርዓት አልሄድንምና፤ ከእናንተ ዘንድ በአንዱ ስንኳ እንዳንከብድበት፣ ሌሊትና ቀን በድካምና በጥረት እየሠራን እንኖር ነበር እንጂ ከማንም እንጀራን እንዲያው አልበላንም። ይህም እኛን ልትመስሉ ራሳችንን እንደ ምሳሌ እንሰጣችሁ ዘንድ ነበር እንጂ ያለ ሥልጣን ስለሆንን አይደለም” በማለት ነግሯቸዋል።—2 ተሰሎንቄ 3:7-9
በሃያኛው መቶ ዘመን ያሉ ጳውሎስን የሚመስሉ አገልጋዮች
እስካሁንም ድረስ የይሖዋ ምስክሮች የጳውሎስን መልካም አርአያ ይከተላሉ። ሽማግሌዎችና ዲያቆናት ደመወዝ አይቀበሉም ወይም ከሚያገለግሉአቸው ጉባኤዎች መደጎሚያ እንኳን አይወስዱም። በዚህ ፈንታ ለቤተሰቦቻቸው የሚያስፈልገውን የሚያቀርቡት እንደ ማንኛውም ሰው ወደ ሥራው ዓለም በመግባት ተቀጥረው በመሥራት ነው። የሙሉ ጊዜ አቅኚ አገልጋዮችም ብዙዎቹ መሠረታዊ ፍላጎቶቻቸውን ለማርካት ያህል በመሥራት ራሳቸውን ይረዳሉ። በየዓመቱ አንዳንድ ምስክሮች የምሥራቹ እምብዛም ባልተዳረሰባቸው ሩቅ ቦታዎች ለመስበክ በራሳቸው ወጪ ይጓዛሉ። በአካባቢው የሚኖሩ ቤተሰቦች ከእነርሱ ዘንድ እንዲበሉ ወይም እንዲያርፉ ሲጋብዙአቸው ደስ የሚላቸው ቢሆንም በዚህ የእንግድነት አቀባበል ያለአግባብ አይጠቀሙም።
የይሖዋ ምስክሮች የሚፈጽሙት ስብከትና ማስተማር ሁሉ በፈቃደኛነት የሚደረግ ስለሆነ ለሚሰጡት አገልግሎት አያስከፍሉም። ይሁን እንጂ ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራቸው የሚሰጠው መጠነኛ የሆነ እርዳታ ተቀባይነት በማግኘት ለዚሁ ዓላማ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ይላካል። (ማቴዎስ 24:14) የምስክሮቹ አገልግሎት በሁሉም መንገድ ከንግድ ነፃ የሆነ ነው። እያንዳንዳቸው እንደ ጳውሎስ በእውነተኛነት “የእግዚአብሔርን ወንጌል ያለ ደመወዝ ሰበክሁ” ሊሉ ይችላሉ። (2 ቆሮንቶስ 11:7) የይሖዋ ምስክሮች ‘በአምላክ ቃል የሚነግዱ’ አይደሉም።
[በገጽ 27 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
አንዳንዶች ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ እርዳታ የሚሰጡበት መንገድ
◻ ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ የሚደረግ መዋጮ፦ ብዙዎች “ለማኅበሩ ዓለም አቀፍ ሥራ የሚደረግ መዋጮ—ማቴዎስ 24:14” ተብሎ በተለጠፈባቸው ሣጥኖች ውስጥ የሚያስገቡትን የተወሰነ የገንዘብ መጠን ይመድባሉ ወይም ወጪ ያደርጋሉ። ጉባኤዎች ይህን ገንዘብ በየወሩ በብሩክሊን ኒው ዮርክ ወዳለው ዋና መሥሪያ ቤት ወይም በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ ቅርንጫፍ ቢሮ ይልካሉ።
◻ ስጦታዎች፦ በፈቃደኛነት የሚደረጉ የገንዘብ እርዳታዎች በቀጥታ Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, 25 Columbia Heights, Brooklyn, New York 11201 በሚለው አድራሻ ወይም በአቅራቢያው ወደሚገኝ የማህበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ ሊላክ ይችላል። ጌጣጌጦች ወይም ሌሎች ውድ ዕቃዎችም በእርዳታ ሊሰጡ ይችላሉ። የተላከው ነገር ስጦታ መሆኑን የሚገልጽ አጭር ደብዳቤም አብሮ መላክ ይኖርበታል።
◻ ተመላሽ ሊሆን የሚችል ገንዘብ ለመስጠት የሚያስችል ዝግጅት፦ አንድ ሰው ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የሰጠውን ገንዘቡን ለግሉ ለማዋል በሚፈልገው ጊዜ ሊመለስለት እንዲችል ዝግጅት በማድረግ እስኪሞት ድረስ በአደራ መልክ እንዲይዘው ሊሰጥ ይችላል።
◻ ኢንሹራንስ፦ የመጠበቂያ ግንብ ማኅበር የአንድ ዓመት የሕይወት ዋስትና ኢንሹራንስ ፖሊሲ ወይም የጡረታ ክፍያ ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊዛወርለት ይችላል። እንዲህ ዓይነት ዝግጅት ሲደረግ ለማኅበሩ ማስታወቅ ይገባል።
◻ የባንክ ሒሳብ፦ የባንክ ሒሳቦች፣ ገንዘብ መቀመጡን የሚገልጽ የምስክር ወረቀት ወይም ተናጠል የሆኑ የጡረታ ሒሳቦች የአካባቢው ባንክ በሚፈቅደው መሠረት በአደራ ወይም በሞት ጊዜ የሚከፈል መሆኑ ተገልጾ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር ሊሰጥ ይችላል። ማንኛውም እንዲህ ዓይነቱ ዝግጅት መደረጉን ለማኅበሩ ማስታወቅ ይገባል።
◻ አክሲዮኖችና ቦንዶች፦ አክሲዮኖችና ቦንዶች በይፋ ስጦታነትም ሆነ ወይም ገቢው ለሰጩ በተከታታይ እንዲመለስለት ዝግጅት ተደርጎ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር በእርዳታ ሊሰጥ ይችላል።
◻ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች፦ ሊሸጡ የሚችሉ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች በይፋ ስጦታነት ወይም ሰጪው በሕይወት እስካለ ድረስ በንብረቱ በመተዳደር እንዲቀጥል መብቱን በማስጠበቅ ለማኅበሩ በእርዳታ ሊሰጥ ይችላል። አንድ ሰው ማንኛውንም የማይንቀሳቀስ ንብረት ለማኅበሩ ከማስተላለፉ አስቀድሞ ከማኅበሩ ጋር መገናኘት ይኖርበታል።
◻ ኑዛዜዎችና አደራዎች፦ ለፔንሲልቫኒያው የመጠበቂያ ግንብ የመጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ንብረት ወይም ገንዘብ በሕግ ፊት ተፈጻሚነት ባለው ኑዛዜ አማካኝነት በውርሻ ሊሰጥ ወይም በአደራ የተሰጠው ንብረት ተጠቃሚ እንዲሆን ስም ሊተላለፍለት ይችላል። አንድ የሃይማኖት ድርጅት እንዲጠቀምበት በአደራ የተሰጠ ንብረት በቀረጥ ረገድ አንዳንድ ጥቅሞች አሉት። የኑዛዜው ወይም ንብረት በአደራ የተሰጠበት ስምምነት ቅጂ ለማህበሩ ሊላክ ይገባል።
እንዲህ ዓይነት ጉዳዮችን በተመለከተ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት Treasurer’s Office, Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania, 25 Columbia Heights, Brooklyn, New York 11201 በሚለው አድራሻ ወይም በአቅራቢያው ለሚገኝ የማኅበሩ ቅርንጫፍ ቢሮ መጻፍ ይቻላል።
[በገጽ 29 ላይ የሚገኝ ሣጥን]
ለመርዳት ፈለገች
የአሥራ አንድ ዓመት ልጅ የሆነችው ቲፍኔ በዩናይትድ ስቴትስ ሉዊሲያና ውስጥ በባተን ሩዥ የምትማር ተማሪ ናት። በቅርቡ ይህች ወጣት የይሖዋ ምስክር “ትምህርት በአሜሪካ” በሚል ርዕስ ድርሰት አዘጋጀች። በውጤቱም ምስክሮች የሆኑ ወላጆችዋ ከትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህርት የሚከተለው ደብዳቤ ደረሳቸው፦
“በአሜሪካ የትምህርት ሳምንት ወቅት አንድ ግሩም የሆነ ድርሰት በየክፍሉ ይነበባል። በዚህ ዕለት ጧት የቲፍኔን ድርሰት በማቅረቤ ተደስቻለሁ። በእውነቱ ቲፍኔ የምታስደንቅ ወጣት ልጅ ናት። የእርጋታ መንፈስ ያላት፣ በራሷ የምትተማመን፣ ችሎታ ያላትና ደርባባ ናት። ይህን ያህል ብዙ ጥሩ ባሕርያት አሟልቶ የያዘ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እምብዛም አይቼ አላውቅም። ቲፍኔ ለትምህርት ቤታችን ሀብት ናት።”
ቲፍኔ በድርሰት ውድድሩ የአንደኛነትን ቦታ በማግኘት አሸነፈች። ከዚያ በኋላ ለመጠበቂያ ግንብ ማኅበር እንዲህ ስትል ጻፈች፦ “ውድድሩን ያሸነፍኩት የወጣቶች ጥያቄና ሊሠሩ የሚችሉ መልሶቻቸው በተሰኘው ጽሑፍ ምክንያት ሳይሆን አይቀርም። . . . ስለ ትምህርት በተጻፉት ምዕራፎች ተጠቅሜያለሁ። . . . ይህን ጠቃሚና አንቀሳቃሽ መጽሐፍ በማዘጋጀታችሁ በጣም አመሰግናችኋለሁ። በድርሰት በማሸነፌ ሰባት ዶላር አግኝቻለሁ። ይህን 7 ዶላርና ሌላ 13 ጨምሬበት በጠቅላላው 20 ዶላር ለዓለም አቀፉ የስብከት ሥራ አበርክቼአለሁ። . . . ሳድግ በቤቴል በፈቃደኛነት ለማገልገል ተስፋ አደርጋለሁ።”
[በገጽ 26 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ጳውሎስ አንዳንድ ጊዜ ድንኳን በመስፋት ለመተዳደሪያ የሚሆነውን ገንዘብ ያገኝ ነበር