ብልጽግና እምነትህን ሊፈትነው ይችላል
ብልጽግና አካሄዱ ቀና የሆነን ሰው እምነት ሊፈትን ይችላል። በቁሳዊ ሀብት ለመበልጸግ መጣጣር እምነትን ወደ ማጣት ሊያደርስ ይችላል። (1 ጢሞቴዎስ 6:9, 10) ነገር ግን ብልጽግና በሌላ መንገድም እምነትን ሊፈትን ይችላል። አንድ ጻድቅ ሰው እሱ እየተቸገረ ብዙ ኃጢአተኞች ግን በቁሳዊ ሀብት ሲበለጽጉ ሲያይ የኃጢአትን መንገድ ለመከተል ሊፈተን ይችላል። ይህ አንዳንድ የይሖዋ አገልጋዮችን እንኳ ሳይቀር ቀና አካሄድ ስላለው ዋጋ ወደ መጠራጠር አድርሷቸዋል።
ይህ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት የግዛት ዘመን ይኖር በነበረው ሌዋዊ ዘማሪ በአሳፍ ላይም ደርሷል። አሳፍ ለሕዝቡ አምልኮ ያገለገሉ መዝሙሮችን ጽፏል። ከኤማን እና ከኤዶታም ጋር በሙዚቃ ለይሖዋ ምስጋናና ውዳሴ በማቅረብ ትንቢትንም ተናግሯል። (1 ዜና መዋዕል 25:1, 2፤ 2 ዜና መዋዕል 29:30) አሳፍ ይህን ያህል መብት የነበረው ቢሆንም እንኳን መዝሙር 73 እንደሚያሳየው የክፉዎች ቁሳዊ ብልጽግና ለእምነቱ ትልቅ ፈተና ሆኖበት ነበር።
የአሳፍ አደገኛ አስተሳሰብ
“ልባቸው ለቀና [ንጹሕ ለሆነ አዓት] ለእስራኤል እግዚአብሔር እንዴት ቸር [ጥሩ አዓት ] ነው። እኔ ግን እግሮቼ ሊሰናከሉ፣ አረማመዴም ሊወድቅ ትንሽ ቀረ።” (መዝሙር 73:1, 2 ) ይሖዋ ለእስራኤል ሕዝብ ጥሩ መሆኑን አሳፍ በእነዚህ ቃላት ገልጿል። በተለይም ደግሞ ለአምላክ ብቻ የተወሰነ አምልኮ ለመስጠትና ለስሙ መቀደስ የበኩላቸውን ለማድረግ ስለሚመኙ “ንጹሕ ልብ” ላላቸው የበለጠ ጥሩ መሆኑን ገልጿል። የእኛም ሁኔታ እንዲህ ከሆነ በክፉዎች ብልጽግና ወይም በሌላ በማንኛውም ነገር ብንፈተንም እንኳ ስለ እርሱ በጎ በመናገር ይሖዋን እንባርከዋለን። — መዝሙር 145:1, 2
ምንም እንኳን አሳፍ የይሖዋን ጥሩነት ቢያውቅም አረማመዱ ከጽድቅ ጎዳና ሊወጣ ትንሽ ቀርቶት ነበር። ሁኔታው አድካሚ በሆነ የማራቶን ውድድር ወቅት እግሮቹ በበረዶ ላይ እንደሚንሸራተቱበት ያክል ነበር። እምነቱ ይህን ያህል ተዳክሞ የነበረው ለምንድን ነው? ስለዚህ ሲገልጽ እንዲህ አለ:- “ የኃጢአተኞችን ሰላም አይቼ በዓመፀኞች ቀንቼ ነበርና። ለሞታቸው መጣጣር የለውምና፤ ኃይላቸውም ጠንካራ ነው [ገላቸውም የሰባ ነውና የ1879 እትም ] እንደ ሰው በድካም አልሆኑም ከሰውም ጋር አልተገረፉም። [በሰው ድካም አልተገኙም። ከሰውም ጋር አልተሰቃዩም የ1879 እትም ]” — መዝሙር 73:3–5
የዓመፀኛ ሰዎች ቁሳዊ ብልጽግና አሳፍን አስቀንቶት ነበር። ሀብትን ያከማቹት በዓመፅ መንገድ ቢሆንም ሰላም ዕጣ ፈንታቸው ይመስል ነበር። (ከመዝሙር 37:1 ጋር አወዳድር።) ሥራቸው የክፋት ሆኖ እያለ ከውጪ ሲታዩ ግን ስጋት የሌለባቸው ነበሩ። ሕይወታቸው አስደንጋጭ የሞት ጣር ሳያገኛቸው የሚያልፍ ይመስላል። አንዳንድ ጊዜ በራሳቸው ተማምነው ይኸውም የሚጎድሏቸው መንፈሳዊ ነገሮች እንዳሉ ምንም ሳያውቁ በሰላም ይሞታሉ። (ማቴዎስ 5:3) በሌላ በኩል ግን አንዳንድ የአምላክ አገልጋዮች በሕይወታቸው ውስጥ የሚያሠቃይ በሽታና ሞት ይደርስባቸዋል። ነገር ግን አምላክ ደግፎ ያቆማቸዋል፤ እንዲሁም ግሩም የትንሣኤ ተስፋ አላቸው። — መዝሙር 43:1–3፤ ዮሐንስ 5:28, 29
ብዙ ክፉ ሰዎች ያላቸውን የተትረፈረፈ ምግብ እንዳይመገቡ የሚከለክላቸው የጤና ችግር የለባቸውም። “ገላቸውም የሰባ” ቦርጫቸውም ደግሞ የተንዘረጠጠ ነው። ከዚህም በተጨማሪ “በሰው ድካም አልተገኙም” ማለትም እንደተቀረው የሰው ዘር ለሕይወት የሚያስፈልጋቸውን ለማግኘት ቀና ደፋ ለማለት አይገደዱም። አሳፍ ክፉዎች ‘እንደሌላው ሰው አይንገላቱም’ ሲል ደምድሟል። በተለይም የአምላክ ሕዝቦች በክፉው የሰይጣን ዓለም ውስጥ የይሖዋን የጽድቅ ሥርዓት አጥብቀው በመከተላቸው ከሚመጡባቸው መከራዎች ክፉዎች ያመልጣሉ። — 1 ዮሐንስ 5:19
ክፉዎች በመበልጸጋቸው ምክንያት አሳፍ ስለ እነርሱ እንዲህ በማለት ይቀጥላል:- “ ስለዚህ ትዕቢት ያዛቸው፤ [ትዕቢትን እንደ ድሪ አጥልቀዋል የ1980 ትርጉም ] ኃጢአትንና በደልን ተጐናጸፉአት። ዓይናቸው ስብ ስለሆነ ወጣ፤ ልባቸውም ከምኞታቸው ይልቅ አገኘ። አስበው ክፉ ነገርን ተናገሩ፤ ከፍ ከፍ ብለውም በዓመፃ ተናገሩ አፋቸውን በሰማይ አኖሩ፣ አንደበታቸውም በምድር ውስጥ ተመላለሰ።” — መዝሙር 73:6–9
ክፉ አድራጊዎች ክፋትን “እንደ ድሪ” አጥልቀውታል። እንዲሁም የዓመፅ ድርጊታቸው ከመብዛቱ የተነሣ “እንደ ልብስ ተጐናጽፈውታል።” የፈለጉትን ነገር ለመፈጸም ሲሉ በሌሎች ላይ ይደነፋሉ። የክፉዎች ዓይኖች ተገቢውን ምግብ አጥተው አልጎደጐዱም። እንዲያውም ‘ስብ ስለሆኑ አብጠዋል’፤ በሆዳምነታቸው ባተረፉት ቦርጭም ከሌሎች ለየት ብለው ይታያሉ። (ምሳሌ 23:20) ያሰቡት ሁሉ ስለሚሳካ ‘ልባቸው ከምኞታቸው ይልቅ አገኘ።’ ስለ ማጭበርበር ድርጊታቸው ‘ከፍ ከፍ ብለው’ በኩራት ይናገራሉ። እንዲያውም ‘አፋቸውን በሰማይ አኖሩ፤ አንደበታቸውም በምድር ተመላለሰ።’ በሰማይም ሆነ በምድር ለሚኖሩት አክብሮት ስለጐደላቸው አምላክን ይሳደባሉ እንዲሁም ሰውን ያንቋሽሻሉ።
ባየው ነገር የተጐዳው አሳፍ ብቻ አይመስልም። እንዲህ አለ:- “ የእግዚአብሔር ሰዎች እንኳ ሳይቀሩ ወደ እነርሱ ያዘነብላሉ፤ የሚነግሯቸውንም ሁሉ በፍጥነት ይቀበላሉ። ‘ እግዚአብሔር ምንም አያውቅም ልዑል እግዚአብሔር ምንም አያስተውልም’ ይላሉ።” (መዝሙር 73:10, 11 የ1980 ትርጉም። ) የዕብራይስጥ ጽሑፎች ክፉዎች ስለሚበለጽጉ ከአምላክ ሕዝቦች አንዳንዶቹ የተሳሳተ አመለካከት በመያዝ ‘አምላክ ምን እንደሚከናወን አያውቅም በኃጢአትም ላይ አይፈርድም’ በማለት ከኃጢአተኞች ጋር መተባበራቸውን መግለጹ ይሆናል። በሌላ በኩልም ደግሞ መጥፎ ሰዎች ቅጣት ሳይደርስባቸው ኃጢአት ሲፈጽሙ ማየቱ ጻድቃን ‘አምላክ እነዚህን ነገሮች እንዴት ሊታገሥ ቻለ? ምን እንደሚከናወን አያይምን?’ የሚሉትን ጥያቄዎች እንዲያነሡ የሚያደርግ መራራ መድኃኒት የመጠጣትን ያህል ነው።
አሳፍ የራሱን ሁኔታ ከክፉዎች ሁኔታ ጋር በማወዳደር እንዲህ አለ:- “ እነሆ፣ እነዚህ ኃጢአተኞች ይደሰታሉ፣ ሁልጊዜም ባለጠግነታቸውን ያበዛሉ። እንዲህም አልሁ፣ በውኑ ልቤን በከንቱ አጸደቅሁ፣ እጆቼንም በንጽሕና በከንቱ አጠብሁ። ሁልጊዜም የተገረፍሁ ሆንሁ፣ መሰደቤም በማለዳ ነው። [ዕለት ዕለትም የተገረፍሁ ሆንሁ ተግሣጼም ማለዳ ማለዳ ይመለሳል። የ1879 እትም ]” (መዝሙር 73:12–14 ) አሳፍ ትክክለኛ ነገር እየሠሩ መኖር ከንቱ እንደሆነ ተሰማው። ክፉዎች በማጭበርበር መንገድ ‘ሀብታቸውን በማብዛት’ በለጸጉ። በጣም ለከፋው ድርጊታቸው ከቅጣት የሚያመልጡ ይመስሉ ነበር። አሳፍ ግን “ከእንቅልፉ ከተነሳበት ጊዜ ጀምሮ ማታ እስኪተኛ ድረስ” ይገረፋል። ይሖዋ ጠዋት ጠዋት ሁል ጊዜ እንደሚያርመው ሆኖ ተሰማው። ይህም ለአሳፍ ተገቢ ስላልመሰለው እምነቱን ፈትኖበታል።
በአስተሳሰብ ላይ ማስተካከያ ማድረግ
አሳፍ አስተሳሰቡ የተሳሳተ መሆኑን በመገንዘብ በመጨረሻ እንዲህ አለ:- “ እንደዚህ ብዬ ብናገር ኖሮ፣ እነሆ፣ የልጆችህን ትውልድ በበደልሁ ነበር። አውቅም ዘንድ አሰብሁ፣ ይህ ግን በፊቴ ችግር ነበር። ወደ እግዚአብሔር መቅደስ እስክገባ ድረስ፣ ፍጻሜአቸውንም እስካስተውል ድረስ። በድጥ ስፍራ አስቀመጥሃቸው፣ ወደ ጥፋትም ጣልሃቸው። እንዴት ለጥፋት ሆኑ! በድንገት አለቁ ስለ ኃጢአታቸውም ጠፉ። ከሕልም እንደሚነቃ፣ አቤቱ፣ ስትነቃ ምልክታቸውን ታስነውራለህ።” — መዝሙር 73:15–20
አሳፍ የምሬት ቃል አለማሰማቱ መልካም ነበር፤ ምክንያቱም ይሖዋን ማገልገል ከንቱ እንደሆነ በግልጽ ቢናገር ኖሮ የአምልኮ ቤተሰቡን አባላት ተስፋ ሊያስቆርጥ ወይም እምነታቸውን ሊሸረሽርባቸው ይችል ነበር። በትዕግሥት ዝም ማለትና አሳፍ እንዳደረገው ማድረግ ምንኛ የተሻለ ይሆናል! ክፉዎች ከቅጣት ለምን እንደሚያመልጡ ትክክለኛ ነገር የሚያደርጉ ግን ለምን እንደሚሠቃዩ ለመረዳት ወደ አምላክ ቤተ መቅደስ ሄደ። በዚያ ቦታ የሚያየው ሁኔታ አሳፍ ከይሖዋ አምላኪዎች መካከል ሆኖ እንዲያሰላስል አጋጣሚውን ከፈተለት፤ አስተሳሰቡም ተስተካከለ። ስለሆነም ዛሬ በምናየው ነገር ግራ ከተጋባን ራሳችንን በማግለል ፋንታ ከአምላክ ሕዝቦች ጋር በመቀራረብ ለጥያቄዎቻችን መልስ እንፈልግ። — ምሳሌ 18:1
አምላክ ክፉዎችን “በድጥ ስፍራ” እንዳስቀመጣቸው አሳፍ ተገነዘበ። ሕይወታቸው ያተኮረው በቁሳዊ ሀብት ዙሪያ በመሆኑ ድንገተኛ ውድቀት ሊያጋጥማቸው ይችላል። ቢቆይ ቢቆይ በእርጅናቸው ዘመን ሞት ይነጥቃቸዋል፤ በማጭበርበር ያከማቹት ሀብት ዕድሜያቸውን ለማራዘም ዋስትና አይሆናቸውም። (መዝሙር 49:6–12) ብልጽግናቸው ፈጥኖ እንደሚያልፍ ሕልም ይሆናል። ከማርጀታቸውም በፊት እንኳ ፍትሕ ያገኛቸውና የዘሩትን ሊያጭዱ ይችላሉ። (ገላትያ 6:7) ለብቸኛው ረዳታችው ጀርባቸውን ስለሰጡት ረዳት አልባና ተስፋ የለሾች ሆነዋል። ይሖዋ በእነርሱ ላይ እርምጃ ሲወስድባቸው “ምልክታቸውን” ማለትም ያላቸውን ድምቀት እና ደረጃ ከጉዳይ አይጥፈውም።
በነገሮች ግፊት የምታሳዩትን ስሜት ጠብቁ
ባየው ነገር ተገቢውን ስሜት ባለማሳየቱ አሳፍ የሚከተለውን የአመኔታ ቃል ተናግሯል:- “ልቤ ነድዶአልና፣ ኩላሊቴም ቀልጧልና፤ እኔ የተናቅሁ ነኝ አላወቅሁምም፣ በአንተ ዘንድም እንደ እንስሳ ሆንሁ። እኔ ግን ዘወትር ከአንተ ጋር ነኝ፣ ቀኝ እጄንም ያዝከኝ። በአንተ ምክር መራኸኝ፤ ከክብር ጋር ተቀበልከኝ። [እየመከርክ ትመራኛለህ፤ በመጨረሻም በክብር ትቀበለኛለህ። የ1980 ትርጉም ]” — መዝሙር 73:21–24
የክፉዎችን ቁሳዊ ብልጽግናና ቀና አካሄድ ባላቸው ላይ የሚደርሰውን መከራ ማብሰልሰሉ የአንድን ሰው ልብ ሊያሳዝን ወይም እንዲማረር ሊያደርገው ይችላል። አሳፍ በዚህ ጉዳይ ላይ የነበረው ጭንቀት በኩላሊቶቹ ማለትም በውስጡ ሥቃይን አምጥቶበታል። በይሖዋ ዓይን ሲታይ በስሜቱ ተነድቶ እርምጃ እንደሚወስድ የማያስብ እንስሳ ሆኖ ነበር። ይሁንና አሳፍ ‘ዘወትር ቀኝ እጁን ከያዘው አምላክ’ ጋር ነበር። በአስተሳሰባችን ብንሳሳትና ነገር ግን አሳፍ እንዳደረገው የይሖዋን ምክር ለማግኘት ብንጥር እጃችንን ይዞ ይደግፈናል እንዲሁም ይመራናል። (ከኤርምያስ 10:23 ጋር አወዳድር።) አስደሳች ወደሆነ የወደፊት ጊዜ ሊመራን የሚችለው ምክሩን ተግባራዊ ማድረጋችን ብቻ ነው። በጊዜው ውርደትን መቀበል ይኖርብን ይሆናል፤ ነገር ግን ይሖዋ አምላክ እኛን ‘በክብር በመቀበል’ መጨረሻውን ይለውጠዋል።
በይሖዋ ላይ የመመካትን አስፈላጊነት በመገንዘብ አሳፍ እንዲህ ሲል ጨምሮ ተናግሯል:- “ በሰማይ ያለኝ ማን ነው? በምድርስ ውስጥ ከአንተ ዘንድ ምን እሻለሁ? [በሰማይ ከአንተ ሌላ ማን አለኝ? በምድርስ አንተን ካገኘሁ ሌላ ምን እሻለሁ? የ1980 ትርጉም ] የልቤ አምላክ ሆይ ልቤና ሥጋዬ አለቀ እግዚአብሔር ግን ለዘላለም ዕድል ፈንታዬ ነው። እነሆ ከአንተ የሚርቁ ይጠፋሉና፤ ከአንተ ርቀው የሚያመነዝሩትንም ሁሉ አጠፋሃቸው። ለእኔ ግን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ይሻለኛል፤ መታመኛዬ እግዚአብሔር ነው በጽዮን ልጅ በሮች ምስጋናህን ሁሉ እናገር ዘንድ። [ሥራህን ሁሉ እነግር ዘንድ የ1879 ትርጉም ]” — መዝሙር 73:25–28
እንደ አሳፍ ሁሉ ለእውነተኛ የሕይወት ዋስትናና ለመጽናናት ከይሖዋ ሌላ ልንመካበት የምንችል ማንም የለም። (2 ቆሮንቶስ 1:3, 4) ስለዚህ የማንንም ሰው ምድራዊ ሀብት ከመጎምጀት ይልቅ ይሖዋን በማገልገል በሰማይ መዝገብን እንሰብስብ። (ማቴዎስ 6:19, 20) ከማንኛውም ነገር ይበልጥ ሊያስደስተን የሚገባው በይሖዋ ተቀባይነት ያለው አቋም ማግኘታችን ነው። ልባችንና ሥጋችን ቢደክምም እንኳ እሱ ያበረታናል፤ እንዲሁም መከራዎች ቢከቡንም ተስፋና ድፍረት እንዳናጣ ለልባችን መረጋጋትን ይሰጠዋል። ከይሖዋ ጋር በጣም የተቀራረበ ዝምድና መያዝ በዋጋ ሊተመን የማይችል ሀብት ነው። ይህንን ዝምድና ማጣታችን ግን ይሖዋን ከተዉት ሰዎች ሁሉ ጋር መከራ ውስጥ ያስገባናል። እንግዲያው ልክ እንደ አሳፍ ወደ አምላክ ቀርበን የሚያስጨንቀንን ሁሉ በእርሱ ላይ እንጣለው። (1 ጴጥሮስ 5:6, 7) ይህ መንፈሳዊ ደኅንነታችንን ያጠነክርልናል እንዲሁም ለሌሎች ስለ ይሖዋ ድንቅ ሥራዎች እንድንናገር ይገፋፋናል።
በይሖዋ ጎን በታማኝነት ጸንታችሁ ቁሙ
አሳፍ በትውልድ አገሩ በእስራኤል ክፉዎች ሲበለጽጉ በማየቱ ተረብሾ ነበር። ከይሖዋ ታማኝ አገልጋዮች መካከል በትምክህት፣ በትዕቢት፣ በዓመፅ፣ በፌዝና በሽንገላ ኃጢአተኞች የነበሩ እና የሚያደርጉትንም ነገር አምላክ ማወቁን የካዱ “ክፉ ሰዎች” ነበሩ። (መዝሙር 73:1–11) እንዴት ያለ ማስጠንቀቂያ ነው! ይሖዋ አምላክን ለማስደሰት ኩራትን፣ ዓመፅን፣ ፌዝን፣ እና ማጭበርበርን ከመሳሰሉት ባሕርያት መራቅ አለብን። የይሖዋ አገልጋዮች የሆንን ሁላችንም እንደ አሳፍ ከታማኝ አምላኪዎቹ ጋር ዘወትር በመሰብሰብ ‘ወደ ታላቁ የአምላክ ቤተ መቅደስ እንግባ።’ ይሖዋን የሚወዱ ሁሉ ሌሎች ምንም ቢሉ ወይም ቢያደርጉ የከበቧቸውን ችግሮች ለመቋቋም እንዲደግፋቸው እርሱን በመታመን ‘ወደ አምላክ ይቅረቡ።’ — መዝሙር 73:12–28፤ 3 ዮሐንስ 1–10
እውነት ነው የክፉ አድራጊዎች ቁሳዊ ብልጽግና የአሳፍን እምነት እንደፈተነው ሁሉ የእኛንም እምነት ሊፈትነው ይችላል። ይሁን እንጂ ሕይወታችንን በይሖዋ አገልግሎት ላይ እንዲያተኩር ካደረግነው ይህንን ፈተና ልንቋቋመው እንችላለን። ይህንንም በማድረጋችንም ሽልማት እናገኛለን ምክንያቱም አምላክ ‘ያደረግነውን ሥራ ለስሙም ያሳየነውን ፍቅር ይረሳ ዘንድ ዓመፀኛ አይደለምና።’ (ዕብራውያን 6:10) ከሽልማታችን ጋር ሲነጻጸር ፈተናችን ‘ጊዜያዊ እና ቀላል’ ነው። (2 ቆሮንቶስ 4:17) የ70 እና የ80 ዓመታት መከራ እንኳ ቢሆን ይሖዋ ለታማኝ አገልጋዮቹ ሊያመጣ ቃል ከገባላቸው ደስታ የሰፈነበት ዘላለማዊ ሕይወት ጋር ሲነጻጸር ከከንፈራችን እፍ ብሎ እንደሚያልፍ ትንፋሽ ነው። — መዝሙር 90:9, 10
በክፉዎች ቁሳዊ ብልጽግናና እኛ ለጽድቅ ስንል በሚደርስብን መከራ መካከል ያለውን ልዩነት ከአምላክ ቅዱስ መንፈስ ፍሬዎች አንዱ የሆነውን እምነትን ከማሳየት እንዲያግደን ፈጽሞ አንፍቀድለት። (ገላትያ 5:22, 23፤ 1 ጴጥሮስ 3:13, 14) ለሕሊናቸው ደንታ የሌላቸው በመሆናቸው ምክንያት የበለጸጉትን ክፉዎች ብንመስል ሰይጣን ይደሰታል። ከዚህ ይልቅ የጽድቅ ሥርዓቶቹን እንድንተው የሚመጣብንን ፈተና በመቋቋም የይሖዋን ስም እናስከብር። (ሶፎንያስ 2:3) ክፉዎች ስለተሳካላቸው አንጨነቅ፤ ምክንያቱም ግፋ ቢል የሚያገኙት ቁሳዊ ሃብት ብቻ ነው። ይህስ ቢሆን ምን ጥቅም አለው? ይህ ብልጽግና እምነታቸውን በሉዓላዊው ጌታ በይሖዋ ላይ የጣሉ ሰዎች ካገኙት መንፈሳዊ ብልጽግና ጋር ሊወዳደር እንኳ አይችልም።