በሕይወትህ ውስጥ ያሉ ገደቦች ተስፋ ያስቆርጡሃልን?
በሕይወት ውስጥ ያሉ ገደቦችን ማንም ሰው አይወድም፤ ይሁን እንጂ ሁላችንም ብንሆን ቢያንስ እስከተወሰነ ደረጃም እንኳ ቢሆን ሳናንገራግር ልንቀበላቸው ይገባናል። ሆኖም አንዳንድ ጊዜ ሕይወትህ በጣም የተገደበ መስሎህ ተስፋ ትቆርጣለህን? አመለካከትህን ብትቀይር ምናልባት የተሻለ ስሜት ይኖርህ ይሆናል። ልታደርገው የማትችለውን ነገር እያሰብክ ከመነጫነጭ ይልቅ ባለህ ነፃነት ለምን ሙሉ በሙሉ አትጠቀምም?
ለምሳሌ ያህል በኢኮኖሚ ድሀ የሆኑ ብዙ ሰዎች ሀብታም ለመሆን ይመኛሉ። ይሁን እንጂ ድህነት በዚህ የነገሮች ሥርዓት ልናደርግ የምንችለውን ነገር ቢገድብብንም እንኳ በሕይወት ውስጥ በጣም አስፈላጊ የሆኑትን ነገሮች ሁሉም ሰዎች ሊያገኟቸው ይችላሉ። ድሆችም ሆኑ ሀብታሞች ፍቅር ሊይዛቸው፣ ሊያገቡ፣ ልጆችን ወልደው ሊያሳድጉ፣ ከሌሎች ጋር ወዳጅነት ሊመሥርቱና የመሳሰሉትን ሊያደርጉ ይችላሉ። ከሁሉም በላይ ደግሞ ድሆችም ሆኑ ሀብታሞች ይሖዋን ያውቃሉ፤ እንዲሁም ተስፋ የተሰጠውን አዲስ ዓለም በጉጉት ይጠባበቃሉ። ድሆችም ሆኑ ሀብታሞች ከቁሳዊ ሀብት የበለጠ ዋጋ ባለው ክርስቲያናዊ ጥበብና እውቀት ሊያድጉ ይችላሉ። (ምሳሌ 2:1–9፤ መክብብ 7:12) ሁሉም ማለትም ድሆችም ሆኑ ሀብታሞች በይሖዋ ዘንድ መልካም ስም ሊያተርፉ ይችላሉ። (መክብብ 7:1) በጳውሎስ ዘመን የክርስቲያን ጉባኤ በአብዛኛው ከዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ በመጡ ሰዎች የተገነባ ነበር። እንዲያውም አንዳንዶች ባሪያዎች ነበሩ። ነገር ግን ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸውን ማንኛውንም ነፃነታቸውን በጥበብ ይጠቀሙበት ነበር።—1 ቆሮንቶስ 1:26–29
ቅዱስ ጽሑፋዊ ራስነት
በክርስቲያን ጋብቻ ውስጥ ሚስት ለባሏ ትገዛለች፤ ይህም መላውን ቤተሰብ ለመጥቀም ሲባል የወጣ ዝግጅት ነው። (ኤፌሶን 5:22–24) በዚህ ምክንያት አንዲት ሚስት ዝቅ እንደተደረገች ሊሰማት ይገባልን? በፍጹም ሊሰማት አይገባም። ባልና ሚስት እንደ አንድ ቡድን በመሆን ተባብረው የሚሠሩ ናቸው። የወንድ ራስነት ክርስቶስ ራስነቱን በተጠቀመበት መንገድ ከተሠራበት ባል በሚስቱ ላይ ብዙ ገደቦች አያደርግም፤ እንዲሁም ሚስቱ ያሏትን ችሎታዎችና ተሰጥዎች በሚገባ እንድትጠቀምባቸው ብዙ አጋጣሚዎችን ይሰጣታል። (ኤፌሶን 5:25, 31) በምሳሌ ምዕራፍ 31 ላይ የተጠቀሰችው “ልባም ሴት” በብዙ አስደሳች እንዲሁም ልዩ ሙያና ቆራጥነት በሚጠይቁ ሥራዎች የተጠመደች ነበረች። ይህች ሴት ለባሏ መገዛቷ ተስፋ እንዳላስቆረጣት ግልጽ ነው።—ምሳሌ 31:10–29
በተመሳሳይም አንዲት ሴት በጉባኤ ውስጥ ባሉ ብቃት ባላቸው ወንዶች ላይ እንድትሠለጥን የሚፈቅድ ምንም ዝግጅት የለም። (1 ቆሮንቶስ 14:34፤ 1 ጢሞቴዎስ 2:11, 12) ክርስቲያን ሴቶች በዚህ ገደብ ሥር በመሆናቸው ቅር ሊሰኙ ይገባቸዋልን? በፍጹም አይገባቸውም። ብዙዎቹ ክርስቲያን ሴቶች ይህ ክርስቲያናዊ አገልግሎት በቲኦክራሲያዊ መንገድ ሲከናወን በመመልከታቸው አመስጋኞች ናቸው። የተሾሙ ሽማግሌዎች ከሚያከናውኑት የእረኝነትና የማስተማር ሥራ ተጠቃሚ ስለሚሆኑ ደስተኞች ናቸው። እንዲሁም በጣም አስፈላጊ በሆነው የመስበክና ደቀ መዛሙርት የማድረግ ሥራ ላይ ያተኩራሉ። (ማቴዎስ 24:14፤ 28:19, 20) ክርስቲያን ሴቶች በዚህ መስክ ከፍተኛ አስተዋጽዖ ያበረክታሉ። ይህም በይሖዋ አምላክ ፊት ክብር ያመጣላቸዋል።—መዝሙር 68:11፤ ምሳሌ 3:35
በወጣቶች ላይ የተጣሉ ገደቦች
ወጣቶችም አንዳንድ ጊዜ እንደ ልባችን እንዳንሆን ታፍነናል በማለት ያማርራሉ። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ያለውን ምሬት የሚያሰሙት በወላጆቻቸው ሥልጣን ሥር በመሆናቸው ነው። ይሁን እንጂ ይህ ቅዱስ ጽሑፋዊ ድጋፍ ያለው ዝግጅት ነው። (ኤፌሶን 6:1) ጥበበኛ የሆኑ ክርስቲያን ወጣቶች ግን ወላጆቻቸው በእነሱ ላይ በሚያደርጉባቸው ገደቦች ከመበሳጨት ይልቅ አብዛኛውን ጊዜ ከባድ ከሆኑ ኃላፊነቶች ጭምር ነፃ መሆናቸውን በማሰብ በዚህ ነፃነታቸው ይደሰታሉ። በዚህ መንገድ የወጣትነት ጥንካሬያቸውንና ያላቸውን አጋጣሚ ትልቅ ሰው ሲሆኑ ለሚያጋጥማቸው ሕይወት ራሳቸውን ለማዘጋጀት ሊጠቀሙበት ይችላሉ።
በብራዚል የሚገኝ አንድ የቀድሞ የክልል የበላይ ተመልካች ገለልተኛ በሆነ አካባቢ በሚገኝ በአንድ አነስተኛ የአስፋፊዎች ቡድን ውስጥ ማድረግ በሚችላቸው ነገሮች ረገድ ገደብ የነበረበትን አንድ የ12 ዓመት ልጅ ዘወትር ያስታውሳል። የጉባኤውን መዝገብ የሚይዘው ወንድም በዓለማዊ ሥራ የተወጠረ ስለነበረ ለቡድኑ ብዙ ትኩረት ለመስጠት አይችልም ነበር። ስለዚህ ይህ ወጣት ልጅ እንዲረዳው አደረገ። የጉባኤው ቅጾች በሙሉ የት እንደሚቀመጡ አወቀ። ስለዚህ ዘወትር አጠገቡ ሆኖ ይረዳው ነበር። ይህ ወጣት የነበረው የሥራ ፍላጎት የሚያበረታታ ነበር። በመስክ አገልግሎትም ዘወትር ከሌሎች ጋር አብሮ ይሄዳል። ይህ ወጣት በአሁኑ ጊዜ የተሾመ ሽማግሌ ነው።
የአንድን ሰው ነፃነት ሊገድቡ የሚችሉ በርካታ ሁኔታዎች አሉ። አንዳንዶች በበሽታ ምክንያት ነፃነታቸው ተገድቧል። አንዳንዶች በሃይማኖት በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ይኖራሉ። የማያምነው የትዳር ጓደኛ እንዲደረጉለት የሚጠይቃቸው ነገሮች ነፃነታቸውን ይገድቡባቸዋል። ምንም እንኳን ገደብ ያለባቸው ሰዎች ገደቡ ባይኖር ኖሮ ብለው ቢመኙም ገደቡ እያለም ቢሆን አርኪ የሆነ ኑሮ መኖር ይችላሉ። ይህ መጽሔት በይሖዋ ላይ በመመካትና ሁኔታቸው የሚፈቅድላቸውን አጋጣሚ በተሻለ መንገድ በመጠቀም ረገድ ሌሎችን በጣም የሚያበረታቱ የብዙ ሰዎችን ታሪኮች ይዞ ወጥቷል።
ጳውሎስ በራሱ ዘመን ስለነበረ አንድ ሁኔታ ሲናገር እንዲህ ብሏል፦ “እግዚአብሔር በጠራህ ጊዜ ባሪያ ነበርህን? ብትሆንም ግድ የለም፣ አትጨነቅበት፤ ነፃ የመውጣት ዕድል ብታገኝ ግን ይህ ዕድል አያምልጥህ።” (1 ቆሮንቶስ 7:21 የ1980 ትርጉም) ምንኛ ሚዛናዊ የሆነ አመለካከት ነው! አንዳንዶቹ ሁኔታዎች ይለወጣሉ። ወጣቶች ትልቅ ሰው ይሆናሉ። ተቃዋሚ የነበሩ የትዳር ጓደኞችም አንዳንድ ጊዜ እውነትን ይቀበላሉ። የኢኮኖሚ ሁኔታዎችም እንደሚሻሻሉ የተረጋገጠ ነው። የታመሙ ሰዎችም ሊድኑ ይችላሉ። አንዳንድ ሁኔታዎች ግን የይሖዋ አዲስ ዓለም እስከሚመጣ ድረስ ላይለወጡ ይችላሉ። አንድ ሰው ሌሎች ሊያደርጉት የሚችሉትን እሱ ሊያደርገው ባለመቻሉ ቢበሳጭ ምን ጥቅም ያገኛል?
ወፎች ከምድር በጣም ከፍ ብለው በሰማይ ላይ ሲበሩ አይተህ ውበታቸውንና እንደልብ ለመንቀሳቀስ ያላቸውን ነፃነት አድንቀህ ታውቃለህ? ምናልባት ምነው እኔም እንደነሱ መብረር ብችል ብለህ ተመኝተህ ይሆናል። አሁንም ሆነ ወደፊት በፍጹም እንደ ወፍ ልትበር አትችልም! ቢሆንም በዚህ እንደማታማርር የታወቀ ነው። ከዚህ ይልቅ አምላክ በሰጠህ ልዩ ልዩ ችሎታዎች ትደሰታለህ። ምንም እንኳን በምድር ላይ የምትሄድ ብትሆንም በተሳካ ሁኔታ ልትኖር ትችላለህ። በተመሳሳይም የኑሮ ሁኔታችን ምንም ዓይነት ይሁን ማድረግ ስለማንችለው ነገር ከመጨነቅ ይልቅ ማድረግ በምንችለው ነገር ላይ ካተኮርን ሕይወት አርኪ ይሆንልናል፤ እንዲሁም በይሖዋ አገልግሎት እንደሰታለን።—መዝሙር 126:5, 6
[በገጽ 28 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
ወላጆችህ ከመጠን በላይ ጥብቅ ቁጥጥር የሚያደርጉብህ ሆኖ ይሰማሃልን?