ታስታውሳለህን?
በቅርቡ የወጡትን የመጠበቂያ ግንብ እትሞች በትኩረት ተከታትለሃልን? የሚከተሉትን መለስ ብሎ ማስታወሱ ጠቃሚ ሆኖ ልታገኘው ትችላለህ፦
◻ ኢየሱስ በማቴዎስ 11:28 ላይ ካቀረበው ግብዣ ጋር በሚስማማ መንገድ አንድ ሰው ‘ወደ እርሱ መሄድ’ የሚችለው እንዴት ነው?
ኢየሱስ “እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፣ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ” ብሏል። (ማቴዎስ 16:24) ስለዚህ ወደ ኢየሱስ መሄድ ለአምላክና ለክርስቶስ ፈቃድ ራስን ማስገዛትንና የተወሰነ ኃላፊነት ያለማቋረጥ መሸከምን ያመለክታል።—8/15፣ ገጽ 17
◻ ኢየሱስ በማቴዎስ 7:13, 14 ላይ የጠቀሰውን ‘ወደ ሕይወት የሚወስደውን ጠባብ መንገድ’ የሚያገኙት “ጥቂቶች” ብቻ የሆኑት ለምንድን ነው?
ጠባቡ መንገድ በአምላክ ሕግጋትና መሠረታዊ ሥርዓቶች የተገደበ ነው። በዚህ የተነሳ ይህ መንገድ የሚያስደስተው ከአምላክ የአቋም ደረጃዎች ጋር ተስማምቶ ለመኖር ልባዊ ፍላጎት ላለው ሰው ብቻ ነው። ‘ጠባቡ መንገድ’ የማያፈናፍን መስሎ ቢታይም እንኳ አንድን ሰው ከማንኛውም ጎጂ ተጽዕኖ ነፃ ያወጣዋል። ወሰኖቹ ‘ነፃ በሚያወጣው ፍጹሙ ሕግ’ የተከለሉ ናቸው። (ያዕቆብ 1:25)—9/1፣ ገጽ 5
◻ ማስተዋል እንዴት ሊዳብር ይችላል?
ማስተዋል ያለጥረት ወይም በተፈጥሮ አይገኝም። ነገር ግን በትዕግሥት፣ በጸሎት፣ ብርቱ ጥረት በማድረግ፣ ከሌሎች ጋር የቀረበ ግንኙነት በማድረግ፣ ጥበበኛ በመሆን፣ መጽሐፍ ቅዱስን በማጥናትና ያጠናነውን በማሰላሰል እንዲሁም በይሖዋ ቅዱስ መንፈስ ላይ በመታመን ማስተዋልን ማዳበር ይቻላል።—9/1፣ ገጽ 21
◻ ቅናት ለመልካም ዓላማ ሊያገለግል የሚችለው እንዴት ነው?
ቅናት አንድ ግለሰብ የሚወደውን ሰው ከመጥፎ ተጽዕኖዎች እንዲጠብቀው ሊገፋፋው ይችላል። ከዚህም በላይ ሰዎች ለይሖዋና ለአምልኮው ተገቢ ቅናት ሊያሳዩ ይችላሉ። (1 ነገሥት 19:10)—9/15፣ ገጽ 8, 9
◻ ዘፍጥረት 50:23 ስለ ዮሴፍ የልጅ ልጆች ሲናገር “በዮሴፍ ጭን ላይ ተወለዱ” ብሎ መግለጹ ምን ያመለክታል?
በአጭሩ ዮሴፍ ልጆቹ የእርሱ የልጅ ልጆች መሆናቸውን መቀበሉን የሚያሳይ ሊሆን ይችላል። በተጨማሪም ጭኑ ላይ በማስቀመጥ ልጆቹን በፍቅር እንደሚያጫውታቸውም ሊያመለክት ይችላል። በዛሬው ጊዜ ያሉ አባቶችም ለልጆቻቸው እንዲህ ያለ የጠበቀ ፍቅር ቢያሳዩአቸው ጥሩ ነው።—9/15፣ ገጽ 21
◻ ለተሳካ ትዳርና የቤተሰብ ኑሮ በጣም የሚያስፈልገው ነገር ምንድን ነው?
የተሳካ ትዳር ለማግኘት ባልና ሚስት ሁልጊዜ የአምላክን ፈቃድ ማስቀደም አለባቸው። እንዲህ የሚያደርጉ ባልና ሚስት አንድ ላይ ሆነው ችግሮቻቸውን የአምላክ ቃል በሚሰጠው ምክር መሠረት ለመፍታት ይጥራሉ። በዚህ መንገድ የአምላክን ፈቃድ ቸል ማለት ከሚያስከትላቸው ከማናቸውም ዓይነት አሳዛኝ ነገሮች ይድናሉ። (መዝሙር 19:7–11)—10/1, ገጽ 11
◻ ስለ ጊዜው አጣዳፊነት ያለን ስሜት እንዳይቀዘቅዝ መጠበቁ በዛሬው ጊዜ ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
አምላካዊ የሆነ ሰው ሊያድርበት የሚገባው የጥድፊያ ስሜት በሙሉ ነፍስ የምናቀርበው አገልግሎት ዋነኛ ክፍል ነው። የጥድፊያ ስሜት የአምላክ አገልጋዮች ‘በነፍሳቸው ዝለው እንዲደክሙ’ ዲያብሎስ የሚያደርገውን ሙከራ ከመከላከሉም በላይ ሙከራውን ለማጨናገፍ ይረዳቸዋል። (ዕብራውያን 12:3) አእምሯቸው ከላይ ባሉት ነገሮች ማለትም ‘በእውነተኛው ሕይወት’ ላይ እንዲያተኩር በማድረግ በዓለምና ዓለም በሚያቀርባቸው አታላይ ቁሳዊ ነገሮች ከመጠን በላይ እንዳይጠላለፉ ይጠብቃቸዋል። (1 ጢሞቴዎስ 6:19)—10/1፣ ገጽ 28
◻ ስለ በጎችና ስለ ፍየሎች በሚናገረው ምሳሌ መሠረት ኢየሱስ በዙፋኑ የተቀመጠው መቼ ነው? ለምንስ?
(ማቴዎስ 25:31–33) ምሳሌው ኢየሱስ ንጉሥ ሆኖ የሚቀመጥበትን ጊዜ ሳይሆን ፈራጅ ሆኖ የሚቀመጥበትን ጊዜ የሚያመለክት ነው። ይህ ፍርድ ለረጅም ዓመታት የሚቀጥል ሳይሆን ኢየሱስ በአሕዛብ ላይ ፍርድ ለመስጠትና ያን ለማስፈጸም ወደፊት የሚቀመጥበትን የተወሰነ ጊዜ ያመለክታል።—10/15፣ ገጽ 22, 23
◻ ኢየሱስ በተደጋጋሚ የጠቀሰው “ትውልድ” ምንድን ነው?
ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” የሚለውን ቃል የተጠቀመበት የአይሁድ ብሔር አባላት የነበሩትን የዘመኑን ሰዎችና ‘ዕውር መሪዎቻቸውን’ ለማመልከት ነበር። (ማቴዎስ 11:16፤ 15:14፤ 24:34)—11/1፣ ገጽ 14
◻ ኢየሱስ በማቴዎስ 24:34–39 ላይ በተናገረው ትንቢት የመጨረሻ ፍጻሜ ላይ “ይህ ትውልድ” የሚለው አገላለጽ ምን ያመለክታል?
ኢየሱስ ያመለከተው የክርስቶስን መገኘት የሚያሳዩ ምልክቶችን አይተው መንገዳቸውን ለማስተካከል አሻፈረኝ ያሉ በምድር ላይ የሚኖሩ ሰዎችን ነው።—11/1፣ ገጽ 19, 31
◻ የመማፀኛ ከተሞች መቋቋማቸውና እዚያ በሚገቡት ሰዎች ላይ አንዳንድ እገዳዎች መጣላቸው በጥንቷ እስራኤል ውስጥ ይኖሩ የነበሩትን ሰዎች የጠቀመው እንዴት ነበር?
እስራኤላውያን ለሰው ሕይወት ጥንቃቄ የማያደርጉ ወይም ግዴለሾች መሆን እንደሌለባቸው አስገንዝቧቸዋል። የምሕረት ዝግጅት አስፈላጊ ሆኖ በሚገኝበት ወቅት ምሕረት የማሳየትንም አስፈላጊነት ያጎላል። (ያዕቆብ 2:13)—11/15፣ ገጽ 14
◻ ታላቁ የመማፀኛ ከተማ ምንድን ነው?
ስለ ደም ቅድስና ያወጣውን ትእዛዝ በመጣሳችን ምክንያት ከሚመጣብን ሞት የሚጠብቀን የአምላክ ዝግጅት ነው። (ዘፍጥረት 9:6)—11/15፣ ገጽ 17
◻ ክርስቲያናዊው የወንድማማች ማኅበር ‘ኃይላችንን ለማደስ’ የሚረዳን እንዴት ነው? (ኢሳይያስ 40:31)
ከወንድሞቻችንና ከእህቶቻችን መካከል ውጣ ውረድ ወይም ፈተና የደረሰባቸውና እኛ የተሰማን ዓይነት ስሜት የተሰማቸው አሉ። (1 ጴጥሮስ 5:9) እየደረሰብን ያለው ነገር በእኛ እንዳልተጀመረ ወይም የሚሰማን ስሜት እንግዳ እንዳልሆነ ማወቃችን የሚያጽናና እና እምነት የሚያጠነክር ነው።—12/1፣ ገጽ 15, 16