በፍቅርና በብጥብጥ የምትታወቀው ሱነም
በደቡብ ገሊላ በኢይዝራኤል ሸለቆ ምሥራቃዊ ዳርቻ የሱነም ከተማ ትገኛለች። ይህች ትንሽ ከተማ የምትታወቀው በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ውስጥ የጎላ ትርጉም ያላቸው ሁለት ፍልሚያዎችን በማስተናገድ ብቻ ሳይሆን ለታማኝ ፍቅር አርአያ በሚሆኑ ሁለት ሴቶች የትውልድ ስፍራነት ጭምር ነው።
ከሱነም በስተጀርባ የሞሬ ኮረብታ ነው ተብሎ የሚገመተው ቦታ የሚገኝ ሲሆን ለጥ ካለው ሜዳ ባሻገር ስምንት ኪሎ ሜትር ያህል ርቆ ደግሞ የጊልቦዓ ተራራ ይገኛል። በእነዚህ ሁለት ኮረብታዎች መካከል የሚገኘው መሬት በእስራኤል ምድር ውስጥ ውኃ በደንብ ከሚያገኙትና ፍሬያማ ከሆኑት ለም ቦታዎች አንዱ ነበረ።
በሱነም ዙሪያ የሚገኘው ይህ ለምለም ገጠር እስከ ዛሬ ከተነገሩት በጣም አስደሳች የፍቅር ታሪኮች መካከል አንዱ የሆነውና በመኃልየ መኃልይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጸው ታሪክ የተፈጸመበት ቦታ ነበር። ይህ መኃልይ ንጉሥ ሰሎሞን ከሚስቶቹ መካከል አንዷ እንድትሆን ያቀረበላትን ግብዣ ከመቀበል ይልቅ እረኛ የሆነውን ጓደኛዋን ማግባት ስለመረጠች አንዲት ውብ የገጠር ልጃገረድ ይተርካል። ሰሎሞን ልቧን ለመማረክ ጥበቡንና ሀብቱን በሙሉ ተጠቅሟል። “ይህች እንደ ማለዳ ብርሃን የምትጎበኝ፣ እንደ ጨረቃ የተዋበች እንደ ፀሐይም የጠራች . . . ማን ናት?” እያለ በተደጋጋሚ ጊዜያት አወድሷታል። አለ ብላ የምታስበውን ጌጣጌጥ ሁሉ ሊሰጣት ቃል ገብቶላት ነበር።—መኃልየ መኃልይ 1:11፤ 6:10
የንጉሥ ቤት ኑሮ ምን እንደሚመስል እንድታየው ሲል ሰሎሞን በ60 የክብር ዘቦች ታጅቦ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ አብረውት ከነበሩት ሰዎች መካከል እንድትሆን አድርጓት ነበር። (መኃልየ መኃልይ 3:6-11) በቤተ መንግሥቱ እንድትቀመጥ አደረገ። ይህ ቤተ መንግሥት በጣም አስደናቂ ከመሆኑ የተነሣ የሳባ ንግሥት ባየችው ጊዜ ‘መንፈስ አልቀረላትም።’—1 ነገሥት 10:4, 5
ይሁን እንጂ ሱነማይቷ ልጃገረድ እረኛ ለሆነው ጓደኛዋ ታማኝ ነበረች። “በዱር እንዳለ እንኮይ፣ እንዲሁ ውዴ ነው” ብላለች። (መኃልየ መኃልይ 2:3) ሰሎሞን በሺህ በሚቆጠሩት የወይን ተክሎቹ ሊደሰት ይችላል። ለእሷ ግን አንድ የወይን ተክል ከፍቅረኛዋ ጋር በቂዋ ነበር። ፍቅሯ የጸና ነበር።—መኃልየ መኃልይ 8:11, 12
ሌላም ውብ ሴት በሱነም ትኖር ነበር። ስለ አካላዊ ገጽታዋ ምንም ባናውቅም የልብ ውበት እንደነበራት እርግጠኞች ልንሆን እንችላለን። መጽሐፍ ቅዱስ ይህች ሴት ነቢዩ ኤልሳዕን ዘወትር ለመመገብና ለእሱ የሚሆን የማረፊያ ቦታ ለመስጠት ስትል ‘እንዳሰበች’ ወይም መሥዋዕትነት እንደከፈለች ይናገራል።—2 ነገሥት 4:8-13
ኤልሳዕ ረዥምና አድካሚ ጉዞ ካደረገ በኋላ እሷና ባሏ ወዳዘጋጁለት፣ ሰገነት ላይ ወደምትገኘው ትንሽ ቤት በአመስጋኝነት ሲመለስ በዓይነ ሕሊናችን ልንመለከተው እንችላለን። አገልግሎቱ ለ60 ዓመታት የቆየ ስለነበረ ቤታቸውን ለብዙ ጊዜ ጎብኝቶት መሆን አለበት። ይህች ሱነማዊት ሴት ኤልሳዕ በዚያ በኩል በሚያልፍበት ጊዜ ሁሉ ቤታቸው እንዲያርፍ የፈለገችው ለምንድን ነው? ምክንያቱም የኤልሳዕ ሥራ ጠቃሚ መሆኑን ተገንዝባ ስለነበር ነው። ይህ ትሑት የሆነና የራሱን ሳይሆን የሌሎች ሰዎችን ጥቅም የሚያስቀድም ነቢይ ነገሥታት፣ ካህናትና ሌሎች ሰዎችም ይሖዋን የማገልገል ግዴታቸውን እንዲፈጽሙ በማሳሰብ የሕዝቡ ሕሊና ሆኖ አገልግሏል።
ኢየሱስ “ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል” ብሎ ሲናገር በአእምሮው ውስጥ ከነበሩት ሰዎች መካከል አንዷ ሱነማይቱ ሴት እንደምትሆን ምንም ጥርጥር የለውም። (ማቴዎስ 10:41) ይሖዋ ለዚህች አምላካዊ ፍርሃት ለነበራት ሴት ወሮታውን ከፍሏታል። ለብዙ ዓመታት መካን ሆና ብትኖርም ወንድ ልጅ ልትወልድ ችላለች። ከዓመታት በኋላም የሰባት ዓመት ረሃብ ምድሪቱን ባጠቃት ጊዜ መለኮታዊ እርዳታ አግኝታለች። ይህ ስሜትን የሚነካ ታሪክ የሰማዩ አባታችን ለአምላክ አገልጋዮች የምናሳየውን ደግነት በፍጹም እንደማይረሳ ያስታውሰናል።—2 ነገሥት 4:13-37፤ 8:1-6፤ ዕብራውያን 6:10
ሁለት ወሳኝ ፍልሚያዎች
ሱነም በእነዚህ ሁለት ታማኝ ሴቶች መኖሪያነት ብቻ ሳይሆን የእስራኤላውያንን የታሪክ ሒደት በቀየሩ ሁለት ፍልሚያዎች ጭምር ትታወሳለች። በከተማይቱ አቅራቢያ በሞሬና በጊልቦዓ ተራሮች መካከል የሚገኘው ሸለቆ ተስማሚ የጦር ሜዳ ነበረ። በመጽሐፍ ቅዱስ ዘመን የነበሩ ወታደራዊ አዛዦች ሁልጊዜ በቂ የውኃ አቅርቦት፣ ለጥበቃ የሚያመች ከፍ ያለ መሬት፣ ከተቻለም ደግሞ ሠራዊቱን፣ ፈረሶችንና ሠረገላዎችን ሊይዝ የሚችልና በሸለቆ ውስጥ የሚገኝን ደረቅ ሜዳ በደንብ ለማየት የሚያስችል ከፍ ያለ ቦታን ይመርጡ ነበር። ሱነምና ጊልቦዓ እነዚህን የመሰሉ ጥቅሞች ነበሯቸው።
በመሳፍንት ዘመን 135,000 ምድያማውያን፣ አማሌቃውያንና ሌሎች ሰዎችን የያዘ ሠራዊት በሞሬ ፊት ለፊት በሚገኘው ሸለቆ ሰፍሮ ነበር። “የግመሎቻቸውም ብዛት በባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ነበረ።” (መሳፍንት 7:12) ከእነሱ ፊት ለፊት ከሸለቆው ባሻገር በሐሮድ ምንጭ አጠገብ በጊልቦዓ ተራራ ግርጌ 32,000 ወታደሮችን ብቻ ያቀፈው የእስራኤላውያን ሠራዊት በመስፍኑ ጌዴዎን አመራር ስር በመሆን ሰፍሮ ነበር።
አንድ ፍልሚያ ከመጀመሩ በፊት በነበሩት ቀናት ተዋጊዎቹ አንዱ ወገን የሌላውን ወገን ወኔ ለመስለብ ይጥር ነበር። ፉከራና ቀረርቶ የሚያሰሙት ወታደሮች ብዛት፣ በጦር ግንባሩ የተሰለፉት ግመሎች፣ ሰረገሎችና ፈረሶች የእግረኛ ወታደሮቹን ልብ ሊያርዱት ይችላሉ። ቦታቸውን በመያዝ ዝግጁ ሆነው ይጠባበቁ የነበሩት ምድያማውያን ገና በመሰባሰብ ላይ ለነበሩት እስራኤላውያን አስፈሪ ትዕይንት ሆነውባቸው እንደነበር አያጠራጥርም። ጌዴዎን “የፈራና የደነገጠ” ማን ነው? ብሎ ሲጠይቅ ሁለት ሦስተኛ የሚሆነው ሠራዊት የጦር አውድማውን ትቶ ወጣ።—መሳፍንት 7:1-3
የቀሩት 10,000 የሚያክሉ እስራኤላውያን ወታደሮች ከሸለቆው ባሻገር በሚገኙት 135,000 የጠላት ወታደሮች ላይ አፍጥጠው ሳሉ ብዙም ሳይቆይ ይሖዋ የእስራኤላውያንን ወታደሮች ቁጥር በማሳነስ ወደ 300 አወረደው። በእስራኤላውያን ልማድ መሠረት ይህ ትንሽ ቡድን በሦስት ተከፈለ። ጨለማን ተገን በማድረግ በጠላት ሰፈር በሦስት አቅጣጫ ሆነው ቦታ ቦታቸውን ያዙ። ከዚያም በጌዴዎን ትእዛዝ 300ዎቹ ወታደሮች ችቦዎቹ ተሸሽገውባቸው የነበሩትን ማሰሮዎች ሰባበሩ፣ ችቦዎቻቸውን ከፍ አድርገው ያዙ፣ እንዲሁም “የእግዚአብሔርና የጌዴዎን ሰይፍ!” በማለት ጮኹ። መለከቶቻቸውን ለረዥም ጊዜ ነፉ። በዚያ ጨለማ የደነበሩት ከተለያዩ ብሔራት የተውጣጡ ወታደሮች እነዚያ 300 ሰዎች ጥቃት የሰነዘሩባቸው መሰላቸው። ይሖዋ እያንዳንዱ ሰው በሌላው ላይ እንዲነሳ ስላደረገ “ሠራዊቱም ሁሉ ሮጠ፣ ጮኸ፣ ሸሸም።”—መሳፍንት 7:15-22፤ 8:10
በንጉሥ ሳውል ዘመን በሱነም አቅራቢያ ሁለተኛ ፍልሚያ ተካሄዶ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስ ‘ፍልስጥኤማውያን ተሰብስበው በመምጣት በሱነም እንደሰፈሩና’ ልክ የጌዴዎን ሠራዊት ከዓመታት በፊት እንዳደረገው ‘ሳኦልም እስራኤልን ሁሉ ሰብስቦ በጊልቦዓ እንደሰፈረ’ ይገልጻል። ይሁን እንጂ ሳኦል ከጌዴዎን በተለየ መልኩ በይሖዋ ላይ እምነት ስላልነበረው በዓይንዶር የምትገኝ መናፍስት ጠሪ ለማማከር መረጠ። የፍልስጥኤማውያንን ሰፈር በሚያይበት ጊዜ “ፈራ፣ ልቡም እጅግ ተንቀጠቀጠ።” ከጥቂት ጊዜ በኋላ በተደረገው ውጊያ እስራኤላውያን ሸሹ፣ ከፍተኛ ሽንፈትም ደረሰባቸው። ሳኦልና ዮናታን ሁለቱም ሕይወታቸውን አጡ።—1 ሳሙኤል 28:4-7፤ 31:1-6
ስለዚህ የሱነም ታሪክ ፍቅርና ብጥብጥ የታየባት እንዲሁም በይሖዋ መታመን ያስከተለው ውጤትና በአጋንንት መመካት ያስከተለው ውድቀት የተንጸባረቀባት ሆናለች። በዚህች ሸለቋማ ሥፍራ ሁለት ሴቶች በፍቅርና እንግዳ ተቀባይ በመሆን ትጋትን ሲያሳዩ ሁለት እስራኤላውያን መሪዎች ደግሞ ወሳኝ ፍልሚያዎችን አድርገዋል። አራቱም ምሳሌዎች አገልጋዮቹን በሚክሰው በይሖዋ ላይ የመታመንን አስፈላጊነት ያሳያሉ።
[በገጽ 31 ላይ የሚገኝ ሥዕል]
በጥንቷ የሱነም ከተማ የሚገኝ ዘመናዊ የሱላም መንደርና ከበስተኋላ ጉብ ብሎ የሚታየው የሞሬ ተራራ
[ምንጭ]
Pictorial Archive (Near Eastern History) Est.