የቤተሰብ ሕይወት በአደገኛ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል!
“ከዚያ በኋላ በሰላምና በደስታ ኖሩ።” እንዲህ የሚባልላቸው ትዳሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ ቁጥራቸው እየተመናመነ መጥቷል። አብዛኛውን ጊዜ ‘በደህናውም ይሁን በአስቸጋሪው ጊዜ’ በፍቅር አብሮ ለመኖር የሚገቡት የጋብቻ ቃል ኪዳን እንዲያው ለወጉ ያህል ብቻ የሚደረግ ሆኗል። ደስተኛ ቤተሰብ ማግኘት የማይጨበጥ ሕልም እየሆነ መጥቷል።
ከ1960 እስከ 1990 ባሉት ዓመታት መካከል በኢንዱስትሪ በበለጸጉት በአብዛኞቹ የምዕራብ አገሮች የፍቺ ቁጥር ከእጥፍ በላይ ጨምሯል። በአንዳንድ አገሮች ቁጥሩ በአራት እጥፍ አድጓል። ለምሳሌ ያህል በስዊድን በየዓመቱ ወደ 35,000 የሚጠጉ ጋብቻዎች ይፈጸማሉ። ከእነዚህ ጋብቻዎች ውስጥ ከ45,000 በላይ ልጆች ያሏቸው ግማሽ የሚያህሉት ጋብቻዎች ይፈርሳሉ። ከዚህ የሚበልጥ ቁጥር ያላቸው በሕግ ሳይጋቡ የሚኖሩ ግለሰቦችም የሚለያዩ ሲሆን ይህም በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ልጆችን ችግር ላይ ጥሏል። በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሌሎች አገሮችም ከዚህ ጋር የሚመሳሰል ሁኔታ እየታየ መሆኑን በገጽ 5 ላይ ከሚገኘው ሳጥን መመልከት ይቻላል።
እርግጥ ነው በታሪክ ውስጥ የቤተሰቦች መለያየትና የትዳር መፍረስ አዲስ ነገር አይደለም። በ18ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የነበረው የሃሙራቢ ሕግ በባቢሎን ውስጥ ፍቺ እንዲኖር የሚፈቅዱ ሕጎችን አካቶ ይዟል። ሌላው ቀርቶ በ16ኛው መቶ ዘመን ከዘአበ የተሰጠው የሙሴ ሕግ እንኳ በእስራኤል ውስጥ ፍቺን ይፈቅድ ነበር። (ዘዳግም 24:1) ይሁን እንጂ እንደዚህ እንደ 20ኛው መቶ ዘመን የቤተሰብ ጥምረት የላላበት ጊዜ አልነበረም። ከአሥር ዓመት በፊት የአንድ ጋዜጣ ዓምድ አዘጋጅ “ከሃምሳ ዓመታት በኋላ ባህላዊውን ቤተሰብ ማግኘታችን ያጠራጥራል። ከዚህ ይልቅ የተለያዩ ሰዎች አንድ ላይ በሚኖሩባቸው ቡድኖች ይተኩ ይሆናል” ሲሉ ጽፈዋል። ከዚያ በኋላ የተከሰቱት ሁኔታዎች የአባባላቸውን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡ ሆነው ተገኝተዋል። የቤተሰብ ተቋም በፍጥነት እየፈራረሰ በመሆኑ “ከውድቀት ይድን ይሆን?” የሚለው ጥያቄ ይበልጥ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።
ብዙ ባለ ትዳሮች አንድ ላይ ተጣብቀው መኖርና አንድነት ያለው ቤተሰብ ይዘው መቆየት ያቃታቸው ለምንድን ነው? የጋብቻቸውን የብርና የወርቅ ኢዮቤልዩ በደስታ ያከበሩ ሰዎች ለረዥም ዘመን አንድ ላይ ተጣብቀው ለመኖር የቻሉበት ምስጢር ምንድን ነው? በነገራችን ላይ በቀድሞዋ ሶቭየት ኅብረት በአዘርባጃን ሪፑብሊክ አንድ ባልና ሚስት 100ኛ ዓመት የጋብቻ በዓላቸውን እንዳከበሩ በ1983 ተዘግቧል። በዚያን ጊዜ የባልየው ዕድሜ 126 ሲሆን የሚስትየው ደግሞ 116 ነበር።
አስጊው ሁኔታ ምንድን ነው?
ምንዝር፣ በአእምሮ ወይም በአካል ላይ የሚፈጸም የጭካኔ ድርጊት፣ የትዳር ጓደኛን ጥሎ መሄድ፣ የመጠጥ ሱስ፣ መካንነት፣ የአእምሮ እክል፣ ከአንድ በላይ ማግባትና የአደንዛዥ ዕፅ ሱሰኛ መሆን በብዙ አገሮች ውስጥ ለሕጋዊ ፍቺ መሠረት የሚሆኑ ነገሮች ናቸው። ይሁን እንጂ በአጠቃላይ ሲታይ ዋነኛው ምክንያት በተለይ በእነዚህ የቅርብ አሥርተ ዓመታት ውስጥ ትዳርንና ባህላዊውን ቤተሰብ አስመልክቶ በነበረው መሠረታዊ አስተሳሰብ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ መከሰቱ ነው። ለረዥም ጊዜ ቅዱስ ተደርጎ ይታይ ለነበረው ተቋም የሚሰጠው ክብር ተመናምኗል። የሙዚቃ፣ የተንቀሳቃሽ ፊልሞችና በቴሌቪዥን የሚታዩ ተከታታይ ታሪኮችን የሚያዘጋጁ ስግብግብ ሰዎች እንዲሁም እውቅ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች የፆታ ነፃነት የሚባለውን፣ ብልግናን፣ ልቅ አኗኗርንና ለራስ ጥቅም ሲሉ ብቻ መኖርን ያወድሳሉ። የወጣቶችንም ሆነ በዕድሜ የገፉትን አእምሮና ልብ የመረዘ ልማድ እንዲስፋፋ አድርገዋል።
በ1996 በተሰበሰበ አንድ የሕዝብ አስተያየት ጥናት ላይ 22 በመቶ የሚሆኑ አሜሪካውያን አንዳንድ ጊዜ በትዳር ላይ መወስለት ጥሩ መሆኑን ተናግረዋል። በስዊድን ውስጥ ሰፊ ስርጭት ካላቸው ጋዜጦች መካከል አፍቶንብላዴት የተባለው ጋዜጣ በአንድ ልዩ እትሙ “የተሻለ ነገር ስለሚያስገኝላቸው” ሴቶች ፍቺ እንዲጠይቁ መክሯል። አንዳንድ ታዋቂ የሥነ ልቦና ባለሙያዎችና ስለ ሰው ዘር አመጣጥ የሚያጠኑ ተመራማሪዎች እንኳ ሰዎች በየጥቂት ዓመታቱ የትዳር ጓደኛቸውን እንዲለውጡ ሆነው በዝግመተ ለውጥ “የተሠሩ” መሆናቸውን ገልጸዋል። በሌላ አነጋገር በትዳር ላይ መወስለትም ሆነ ፍቺ ተፈጥሯዊ ናቸው ማለታቸው ነው። ሌላው ቀርቶ ልጆች ወደፊት ከትዳር ጓደኛቸው ጋር ሲፋቱ የሚገጥማቸውን ችግር ለመወጣት እንዲችሉ ሊያዘጋጃቸው ስለሚችል የወላጆች መፋታት ለልጆች ጠቃሚ ሊሆን ይችላል ብለው የሚከራከሩም አሉ!
በርካታ ወጣቶች አባትን፣ እናትንና ልጆችን ያቀፈውን ባህላዊውን የቤተሰብ ሕይወት የመምራት ፍላጎት የላቸውም። “ከአንድ የትዳር ጓደኛ ጋር የሕይወት ዘመኔን በሙሉ ማሳለፍ አይታየኝም” የሚለው አስተሳሰብ ተስፋፍቷል። “ትዳር ልክ እንደ ገና በዓል አፈ ታሪክ ነው። አላምንበትም” ሲል አንድ የ18 ዓመት ዴንማርካዊ ወጣት ተናግሯል። በአየርላንድ በሚገኘው ብሔራዊ የሴቶች ካውንስል ውስጥ አባል የሆኑ ኖሪን በርን የተባሉ ሴት እንዲህ ብለዋል:- “አሁን ያለው አስተሳሰብ ምን አስጨነቀኝና ነው ከወንዶች ጋር እየኖርኩ የቤት ውስጥ ሥራ የምሠራው የሚል ነው። ምንም ዓይነት ቃል ሳትገቡ ከወንዶች ጋር ተዝናኑ። . . . በርካታ ሴቶች ኑሮን ለማሸነፍ የወንዶች ድጋፍ እንደማያስፈልጋቸው ተሰምቷቸዋል።”
በአንድ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ቁጥር እየጨመረ ነው
ይህ አመለካከት በመላው አውሮፓ ውስጥ የነጠላ እናቶችን ቁጥር በፍጥነት እንዲጨምር አድርጓል። ከእነዚህ ነጠላ ወላጆች መካከል ያልተፈለገ እርግዝና ምንም ስህተት የለበትም ብለው የሚያስቡ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ይገኙበታል። አንዳንድ እናቶች ልጃቸውን ለብቻቸው ሆነው ማሳደግ ይፈልጋሉ። ብዙዎቹ እናቶች የማግባት ዓላማ ባይኖራቸውም ከአባትየው ጋር ለተወሰነ ጊዜ ተዳብለው የሚኖሩ ናቸው። ኒውስዊክ መጽሔት በሽፋን ገጹ ላይ “ትዳር እየሞተ ነውን?” በሚል ርዕስ አንድ ዘገባ አቅርቦ ነበር። በአውሮፓ ከጋብቻ ውጪ የሚወለዱ ሕፃናት ቁጥር በመቶኛ ሲሰላ በፍጥነት እየጨመረ ቢሆንም ትኩረት የሰጠው አለመኖሩን ዘግቧል። በስዊድን ከጠቅላላ ሕፃናት መካከል ግማሾቹ የሚወለዱት ከትዳር ውጪ ነው። ስዊድን በዚህ ቁጥር የመጀመሪያውን ቦታ ስትይዝ በዴንማርክና በኖርዌይም እንደዚሁ ወደ ግማሽ የሚጠጉት ሕፃናት የሚወለዱት ከጋብቻ ውጪ ነው። በፈረንሳይና በእንግሊዝ ደግሞ በአማካይ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ሕፃናት የሚወለዱት ከጋብቻ ውጪ ነው።
በዩናይትድ ስቴትስ ባለፉት ጥቂት አሥርተ ዓመታት ውስጥ ሁለት ወላጆች የሚገኙባቸው ቤተሰቦች ቁጥር በሚያስደንቅ ሁኔታ አሽቆልቁሏል። አንድ ዘገባ እንዲህ ይላል:- “በ1960 . . . ከጠቅላላ ልጆች ውስጥ ከነጠላ ወላጃቸው ጋር የሚኖሩ 9 በመቶ ነበሩ። በ1990 ይህ ቁጥር ወደ 25 በመቶ አሻቅቧል። ዛሬ 27.1 በመቶ የሚሆኑት አሜሪካውያን ልጆች የሚወለዱት በነጠላ ወላጆች ቤቶች ውስጥ ሲሆን ይህ ቁጥር ደግሞ እየጨመረ ነው። . . . ከ1970 ወዲህ በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ቁጥር ከእጥፍ በላይ አድጓል። ዛሬ ባህላዊው ቤተሰብ ከፍተኛ አደጋ ላይ በመሆኑ በመጥፊያው ደፍ ላይ ሳይሆን አይቀርም በማለት አንዳንድ ተመራማሪዎች ተናግረዋል።”
የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ያወጣቻቸው የሥነ ምግባር ሕግጋት ወደ ጎን ገሸሽ እየተደረጉ ባሉባቸው አገሮች ውስጥ በነጠላ ወላጅ የሚተዳደሩ ቤተሰቦች ቁጥር እየጨመረ ነው። በኢጣልያ እናት፣ አባትና ልጆች ያሉባቸው ቤተሰቦች ቁጥር ከግማሽ በታች ሲሆን ባህላዊው ቤተሰብ ልጅ በሌላቸው ባለ ትዳሮችና በነጠላ ወላጅ በሚተዳደሩ ቤተሰቦች እየተተካ ነው።
በአንዳንድ አገሮች የሚገኘው የእርዳታ ዝግጅት ሰዎች ሳያገቡ እንዲኖሩ የሚያበረታታ ነው። ከመንግሥት እርዳታ የሚያገኙ ነጠላ እናቶች በሚያገቡበት ጊዜ እርዳታው ይቋረጣል። በዴንማርክ የሚኖሩ ነጠላ እናቶች ልጆቻቸውን ለማሳደግ የሚያስችል ተጨማሪ የገንዘብ እርዳታ የሚያገኙ ሲሆን በአንዳንድ ማኅበረሰቦች ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሚሆናቸው እናቶች ተጨማሪ ገንዘብ ይሰጣቸዋል፤ እንዲሁም የቤት ኪራይ ይከፈልላቸዋል። ስለዚህ ጉዳዩ ከገንዘብ ጋር የተያያዘ ነው። በስዊድን በአንድ ፍቺ ምክንያት ለኪስ ገንዘብ፣ ለቤት ኪራይና ለተለያዩ ድጎማዎች ከ250 ሺህ እስከ 375 ሺህ ዶላር ወጪ እንደሚደረግ አልፍ ቢ ስቬንሰን ተናግረዋል።
የሕዝበ ክርስትና አብያተ ክርስቲያናት ቤተሰቦችን በማውደም ላይ የሚገኘውን ይህን ሁኔታ ለመቀየር ያደረጉት ጥረት ያን ያህል አይደለም ወይም ከነጭራሹ ምንም ነገር አያደርጉም። ብዙ ፓስተሮችና ቀሳውስት በራሳቸው ቤተሰብ ውስጥ ካለው ችግር ጋር እየታገሉ በመሆናቸው ለሌሎች እርዳታ ለመስጠት አልቻሉም። ሌላው ቀርቶ አንዳንዶች ፍቺን የሚደግፉ ይመስላል። አፍቶንብላዴት በሚያዝያ 15, 1996 እትሙ በእንግሊዝ የብራድፎርዱ ፓስተር ስቲቨን አለን በዓይነቱ ልዩ የሆነና በሁሉም የብሪታንያ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ የሚያገለግል ሕጋዊ የፍቺ አገልግሎት ሥነ ሥርዓት ማውጣታቸውን ዘግቧል። “ይህ አገልግሎት ሰዎቹን ከደረሰባቸው ነገር ጋር ራሳቸውን እንዲያስማሙ የሚረዳ ነው። አምላክ አሁንም እንደሚወዳቸውና ችግሮቻቸውን እንዲወጡ እንደሚያስችላቸው እንዲገነዘቡ ይረዳቸዋል።”
ስለዚህ የቤተሰብ ተቋም ወዴት እያመራ ነው? ከውድቀት የመዳን ተስፋ አለውን? እያንዳንዱ ቤተሰብ በዚህ ከባድ አደጋ ውስጥ አንድነቱን ጠብቆ ሊቆይ ይችላልን? እባክዎ የሚቀጥለውን ርዕስ ይመልከቱ።
[በገጽ 5 ላይ የሚገኝ ሰንጠረዥ]
በአንዳንድ አገሮች በዓመት ውስጥ የሚፈጸሙት ጋብቻዎች ከፍቺዎች ጋር ሲነፃፀሩ
አገር ዓመት ጋብቻዎች ፍቺዎች
ማልዲቭስ 1991 4,065 2,659
ስዊድን 1993 34,005 21,673
ቼክ ሪፑብሊክ 1993 66,033 30,227
ኖርዌይ 1993 19,464 10,943
አውስትራሊያ 1993 113,255 48,324
ኢስቶኒያ 1993 7,745 5,757
ኩባ 1992 191,837 63,432
ካናዳ 1992 164,573 77,031
የሩሲያ ፌዴሬሽን 1993 1,106,723 663,282
ዩናይትድ ስቴትስ 1993 2,334,000 1,187,000
ዩናይትድ ኪንግደም 1992 356,013 174,717
ዴንማርክ 1993 31,507 12,991
ጀርመን 1993 442,605 156,425
ጃፓን 1993 792,658 188,297
ፈረንሳይ 1991 280,175 108,086
ፖርቶ ሪኮ 1992 34,222 14,227
(በ1994 ዲሞግራፊክ ይርቡክ ላይ የተመሠረተ፣ የተባበሩት መንግሥታት፣ ኒው ዮርክ 1996)