ቤተሰብ ለሰው ልጅ የግድ አስፈላጊ ነው!
ሰብዓዊው ኅብረተሰብ የሚበለጽገው በውስጡ ያሉት ቤተሰቦች ጠንካራ ሲሆኑ ነው ተብሎ ይታመናል። ታሪክ እንደሚያሳየው የቤተሰብ ዝግጅት ሲቆረቁዝ የማኅበረሰቦችና የመንግሥታት ጥንካሬ ይዳከማል። በጥንቷ ግሪክ የሞራል ውድቀት ቤተሰቦችን ሲያፈራርስ ሥልጣኔዋ በመፈረካከሱ በሮማውያን ድል ልትደረግ ችላለች። የሮማውያኑ ግዛት ጠንካራ ሆኖ የቆየው ቤተሰቦች ጠንካራ ሆነው እስከቆዩ ድረስ ነበር። ይሁን እንጂ ዓመታት ባለፉ ቁጥር የቤተሰብ ሕይወት በመዳከሙ የግዛቱ ጥንካሬም ዋዠቀ። የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ቻርለስ ደብልዩ ኤልዮት “የቤተሰብ ሕይወትን ደኅንነትና የኑሮ ደረጃ ከፍ ማድረግ የሥልጣኔና የኢንዱስትሪ ዋነኛ ዓላማ ነው” ብለዋል።
አዎን፣ ቤተሰብ ለሰው ልጅ የግድ አስፈላጊ ነው። የኅብረተሰብን መረጋጋት፣ የልጆችን ደህንነት እንዲሁም የወደፊቱን ትውልድ በቀጥታ ይነካል። እጅግ ብዙ ቁጥር ያላቸው ነጠላ እናቶች ጥሩ ሥነ ምግባር ያላቸውን ልጆች ለማሳደግ ጠንክረው እንደሚሠሩ ምንም ጥርጥር የለውም። ትጉህ ሠራተኞች በመሆናቸውም ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። ይሁን እንጂ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ለልጆች ይበልጥ የሚሻለው ሁለቱም ወላጆች ባሉበት ቤተሰብ ውስጥ መኖር ነው።
በአውስትራሊያ በ2,100 ወጣቶች ላይ የተደረገ ጥናት እንዳሳየው “ችግር ባለባቸው ቤተሰቦች ውስጥ ያደጉ በአሥራዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙ ልጆች አንድነት ባላቸው ቤተሰቦች ውስጥ ካደጉ ልጆች ይልቅ በአጠቃላይ ሲታይ የጤና እክል አለባቸው፤ የስሜት ችግሮች እንዳሉባቸው የሚያሳዩ ምልክቶች ይታዩባቸዋል፤ እንዲሁም ወሲባዊ ፍላጎታቸው ከፍተኛ ነው።” በዩ ኤስ ናሽናል ኢንስቲትዩትስ ኦቭ ሄልዝ ስታትስቲክስ የተደረገ ጥናት እንዳመለከተው በተከፋፈለ ቤተሰብ ውስጥ ከሚኖሩ ልጆች መካከል “ከ20-30 በመቶ የሚሆኑት ለአደጋ የተጋለጡ ናቸው፤ ከ40-75 በመቶ የሚሆኑት ክፍል ይደግሙ ይሆናል፤ እንዲሁም 70 በመቶ የሚሆኑት ከትምህርት ቤት የመባረር አጋጣሚያቸው ሰፊ ነው።” በተጨማሪም አንድ የፖሊሲ ተንታኝ “በነጠላ ወላጆች በሚተዳደሩ ቤቶች ውስጥ የሚኖሩ ልጆች በባሕላዊው ቤተሰብ ውስጥ ካደጉት ልጆች ይልቅ በወንጀል ተካፋዮች ይሆናሉ” የሚል ዘገባ አቅርበዋል።
ቤት ማረፊያ ነው
የቤተሰብ ዝግጅት ቤትን አስደሳች፣ ገንቢና ማራኪ ያደርገዋል። አንድ ስዊድናዊ ባለ ሥልጣን “ከሁሉ የበለጠው የደስታና የደኅንነት ምንጭ ቋሚ ሥራ፣ ንብረት፣ በትርፍ ጊዜ የምንሠራው የምንወደው ሥራ ወይም ጓደኛ ሳይሆን ቤተሰብ ነው” ብለዋል።
መጽሐፍ ቅዱስ እያንዳንዱ ቤተሰብ መጠሪያውን ያገኘው ከታላቁ የቤተሰቦች ፈጣሪ ከይሖዋ አምላክ መሆኑንና በዚህም ምክንያት የቤተሰብን ዝግጅት ያቋቋመው እሱ መሆኑን ይገልጻል። (ዘፍጥረት 1:27, 28፤ 2:23, 24፤ ኤፌሶን 3:14, 15) ይሁን እንጂ በመንፈስ አነሳሽነት በተጻፉት ቅዱሳን ጽሑፎች ውስጥ ከክርስቲያን ጉባኤ ውጪ ባለው ሥነ ምግባርና ሰብዓዊ ኅብረተሰብ ላይ ውድቀትን የሚያስከትል በተንኮል የተሞላ ጥቃት በቤተሰብ ላይ እንደሚሰነዘር ሐዋርያው ጳውሎስ ገልጿል። ጳውሎስ ‘የመጨረሻዎቹ ቀናት’ ‘የአምልኮ መልክ ባላቸው’ ሰዎች ዘንድ እንኳ ታማኝነትና ‘የተፈጥሮ ፍቅር’ የጠፋባቸው እንዲሁም ልጆች ለወላጆቻቸው የማይታዘዙባቸው ጊዜያት በመሆናቸው ተለይተው እንደሚታወቁ ተናግሯል። ክርስቲያኖችን ከእንደዚህ ዓይነት ሰዎች እንዲርቁ አጥብቆ መክሯል። ኢየሱስ የአምላክን እውነት ባለመቀበላቸው ምክንያት ቤተሰቦች እንደሚለያዩ አስቀድሞ ተናግሯል።—2 ጢሞቴዎስ 3:1-5፤ ማቴዎስ 10:32-37
ቢሆንም አምላክ ያለ እርዳታ አልተወንም። የቤተሰብን ግንኙነት አስመልክቶ የተሰጡ በርካታ መመሪያዎች በቃሉ ውስጥ ይገኛሉ። የተሳካ ቤተሰብ ለመመሥረትና ቤታችንን ደስታ የሰፈነበት ቦታ ለማድረግ እንዴት እንደምንችል ይነግረናል። በእንዲህ ዓይነት ቤተሰብ ውስጥ እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ለሌሎቹ አባላት ጥቅም ሲል ማሟላት የሚገባው ኃላፊነት ይኖረዋል።a—ኤፌሶን 5:33፤ 6:1-4
ቤተሰብ በከፍተኛ አደጋ ላይ በሚገኝበት በዚህ ጊዜ ይህን የመሰለውን አስደሳች ግንኙነት ለመመሥረት ይቻላልን? አዎን፣ ይቻላል! በዚህ መጥፎና በረሃ መሰል ዓለም ውስጥ ቤተሰብህን አስደሳችና በበረሃ መሃል የሚገኝ መንፈስን የሚያረካ ገነት ልታደርገው ትችላለህ። ይሁን እንጂ በቤተሰብ ክልል ውስጥ ከሚገኘው ከእያንዳንዱ የሚፈለግ ነገር አለ። ከዚህ ቀጥሎ አንዳንድ ሐሳቦች ቀርበዋል።
ቤተሰብህ ከወድቀት እንዲድን መርዳት
ቤተሰብ አንድነቱን ጠብቆ ሊቆይ ከሚችልባቸው መንገዶች አንዱ አብሮ ጊዜ ማሳለፍ ነው። ሁሉም አባላት ትርፍ ጊዜያቸውን አብረው ለማሳለፍ ጥረት ሊያደርጉ ይገባል። ይህ መሥዋዕትነት መክፈል ይጠይቅ ይሆናል። ለምሳሌ ያህል እናንተ ወጣቶች አንዳንድ የምትወዷቸውን የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች፣ የስፖርት ግጥሚያዎች ወይም ከጓደኞቻችሁ ጋር አብራችሁ የምታሳልፉትን ጊዜ መሥዋዕት ማድረግ ይጠይቅባችሁ ይሆናል። አብዛኛውን ጊዜ ለቤተሰቡ የገቢ ምንጭ የምታስገኙት እናንተ አባቶች ትርፍ ጊዜያችሁን በጣም የምትወዷቸውን ሥራዎች ለመሥራት ወይም የግል ጉዳዮቻችሁን ለማከናወን ብቻ አትጠቀሙ። ከቤተሰባችሁ ጋር አንድ ላይ ለመሆን፣ ምናልባትም የሳምንቱን የመጨረሻ ቀናት ወይም የእረፍት ጊዜያችሁን አንድ ላይ እንዴት ልታሳልፉ እንደምትችሉ እቅድ ልታወጡ ትችላላችሁ። እርግጥ የምታወጡት እቅድ ሁሉም የሚደሰትበትና የሚጓጓለት ሊሆን ይገባል።
ከልጆች ጋር በየጊዜው ግማሽ ሰዓት ያህል ብቻ ማሳለፍ በቂ ነው የሚለው ፈሊጥ አይሠራም። ልጆች ሰፊ ጊዜ ይፈልጋሉ። በስዊድን የሚታተም የአንድ ዕለታዊ ጋዜጣ አምድ አዘጋጅ እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል:- “ዜና ዘጋቢ ሆኜ ባሳለፍኳቸው 15 ዓመታት ውስጥ ብዙ ጊዜ ከወጣት ጥፋተኞች ጋር ተገናኝቻለሁ። . . . ሁሉም ‘ወላጆቼ ጊዜ አልነበራቸውም።’ ‘በጭራሽ አያዳምጡም።’ ‘አባቴ ሁልጊዜ ይጓዝ ነበር’ እንደሚሉ ያሉት አባባሎች የተለመዱ ናቸው። እነዚህ አባባሎች ወላጆች ከእነሱ ጋር ያሳለፉት ጊዜ ምን ያህል አነስተኛ እንደነበረ ያሳያሉ። . . . ወላጅ እንደመሆንህ መጠን ከልጆችህ ጋር የምታሳልፈውን ጊዜ የመወሰኑ መብት ምንጊዜም ያንተ ነው። ያደረግኸው ምርጫ የሚመዘነው ከ15 ዓመታት በኋላ በተፈጠረ አንድ ጨካኝ የ15 ዓመት ልጅ ነው።”
ለገንዘብ ትክክለኛ አመለካከት መያዝ
ሁሉም አባላት ለገንዘብ ትክክለኛ አመለካከት ማዳበር ይኖርባቸዋል። ሁሉም የቤተሰቡን የጋራ ወጪዎች ለመሸፈን ገንዘብ ለማዋጣት ዝግጁ መሆን ይገባቸዋል። ብዙ ሴቶች ቤተሰባቸውን ለመደገፍ ሲሉ ተቀጥረው መሥራት ቢኖርባቸውም እናንተ ሚስቶች ግን ለሚያጋጥሟችሁ አደጋዎችና ፈተናዎች ንቁ መሆን ይገባችኋል። ይህ ዓለም “በችሎታዎቻችሁ እንድትጠቀሙ” እና “ማድረግ የምትፈልጉትን” ሁሉ እንድታደርጉ አጥብቆ ያሳስባችኋል። ይህ ደግሞ በራሳችሁ ሐሳብ የምትመሩና አምላክ በሰጣችሁ የእናትነትና ቤትን የማስተዳደር ሥራ እንዳትደሰቱ ሊያደርጋችሁ ይችላል።—ቲቶ 2:4, 5
እናንተ እናቶች በቤት እየሠራችሁ ለልጆቻችሁ መሪና ጓደኛ ብትሆኗቸው በደህናውም ይሁን በአስቸጋሪው ጊዜ ቤተሰባችሁ አንድነት እንዲኖረው የሚያስችል ጠንካራ ጥምረት ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት የተረጋገጠ ነው። አንዲት ሴት አንድን ቤት አስደሳች፣ የተረጋጋና የተሟላ እንዲሆን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ልታደርግ ትችላለች። አንድ የ19ኛው መቶ ዘመን የፖለቲካ ሰው “አንድ ካምፕ ለማቋቋም አንድ መቶ ሰዎች ያስፈልጋሉ። ቤትን ለማዘጋጀት ግን አንድ ሴት ትበቃለች” በማለት ተናግረዋል።
የቤተሰቡ አባላት በሙሉ በቤተሰቡ አቅም መሠረት ለመኖር ቢተባበሩ ቤተሰቡን ከብዙ ችግሮች ይጠብቀዋል። ባልና ሚስት ቀላል ኑሮ ለመኖርና መንፈሳዊ ነገሮችን ለማስቀደም ሊስማሙ ይገባል። ልጆች ከቤተሰቡ ባጀት ጋር የማይመጣጠኑ ነገሮችን ከመጠየቅ ይልቅ ባላቸው ነገር መርካትን መማር ይኖርባቸዋል። ለዓይናችሁ ፍላጎት ጥንቃቄ አድርጉ! ብዙ ቤተሰቦች አቅማቸው የማይፈቅድላቸውን ነገር ለመግዛት ሲሉ ብድር ውስጥ በመግባታቸው ለውድቀት ተዳርገዋል። መንፈስን የሚያድስ ጉዞ ለማድረግ፣ ለቤቱ ጠቃሚና አስደሳች የሆነ ዕቃ ለመግዛት ወይም የክርስቲያን ጉባኤን ለመደገፍ የሚያስችል መዋጮ ለማድረግ ሁሉም ከገቢው በማዋጣት በኅብረት መሥራቱ ለቤተሰቡ አንድነት ጠቃሚ ይሆናል።
ቤተሰብ ደስተኛ መንፈስ እንዲኖረው “አስተዋጽኦ” የሚያደርገው ሌላው ነገር ሁሉም የቤተሰቡ አባል በጽዳትና በጥገና ሥራ እንዲሁም ለቤቱ፣ ለአትክልት ቦታው፣ ለመኪናውና ለሌሎችም ነገሮች እንክብካቤ በማድረጉ ሥራ ተካፋይ መሆኑ ነው። እያንዳንዱ የቤተሰብ አባል ሌላው ቀርቶ ትንንሽ ልጆች እንኳ የሥራ ምድብ ሊኖራቸው ይችላል። እናንተ ልጆች ጊዜያችሁን ላለማባከን ጣሩ። ከዚህ ይልቅ የመተጋገዝንና የትብብር መንፈስን አዳብሩ። ይህ እውነተኛ ወዳጅነትንና ኅብረትን ስለሚፈጥር አንድነት ያለው ቤተሰብ ለመገንባት ያስችላል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት ያለው ጥቅም
በተጨማሪም አንድነት ያለው የክርስቲያን ቤተሰብ ዘወትር ለሚደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ልዩ ትኩረት ይሰጣል። በየቀኑ በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ የሚደረግ ውይይትና በየሳምንቱ በቅዱሳን ጽሑፎች ላይ የሚደረግ ጥናት ለቤተሰብ አንድነት መሠረት ነው። መሠረታዊ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶችና መሠረታዊ ሥርዓቶች የሁሉንም የቤተሰብ አባላት ልብ በሚነካ መንገድ ውይይት ሊደረግባቸው ይገባል።
እነዚህ የቤተሰብ ጥናቶች ትምህርት ሰጪ ብቻ ሳይሆን አስደሳችና አበረታች ጊዜያትም ሊሆኑ ይገባል። በሰሜን ስዊድን የሚገኝ አንድ ቤተሰብ ልጆች በሳምንቱ ቀናት ውስጥ ወደ አእምሯቸው የሚመጡ ጥያቄዎችን እንዲጽፉ የማድረግ ልማድ ነበረው። ከዚያም እነዚህ ጥያቄዎች በሳምንታዊው የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ላይ ውይይት ይደረግባቸዋል። ብዙውን ጊዜ ጥያቄዎቹ ጥልቀት ያላቸውና የሚያመራምሩ እንዲሁም የልጆቹን የማሰብ ችሎታና ለመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርቶች ያላቸውን አድናቆት የሚያንጸባርቁ ነበሩ። አንዳንዶቹ ጥያቄዎች እንደሚከተሉት ያሉት ናቸው:- “ይሖዋ እያንዳንዱን ተክል እየተከታተለ እንዲበቅል ያደርገዋል ወይስ አንድ ጊዜ ብቻ እንዲበቅል አድርጎ ይተወዋል?” “አምላክ ሰው አይደለም። ታዲያ አምላክ ሰውን ‘በመልኩ’ እንደፈጠረ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ለምንድን ነው?” “አዳምና ሔዋን በገነት ውስጥ ራቁታቸውን ስለነበሩና ጫማ ስላልነበራቸው የክረምቱ ብርድ አላቆራመዳቸውም?” “ጨለማ መሆን ሲገባው በሌሊት ጨረቃ የምትወጣው ለምንድን ነው?” አሁን እነዚህ ልጆች አድገው የሙሉ ጊዜ አገልጋዮች ሆነው አምላክን እያገለገሉ ናቸው።
እናንተ ወላጆች ስለ ቤተሰቡ ችግሮች በምትወያዩበት ጊዜ አዎንታዊ አመለካከት ለመያዝና ደስተኛ ለመሆን ጣሩ። አሳቢዎችና አዲስ ሐሳብ ለመቀበል የማታስቸግሩ ሁኑ። አስፈላጊ የሆኑ መመሪያዎች ማክበርን የሚመለከት ጉዳይ በሚሆንበት ጊዜ ግን ጥብቅ ሁኑ። ምንጊዜም ውሳኔዎቻችሁ የተመረኮዙት ለአምላክና ለትክክለኛ መመሪያዎቹ ባላችሁ ፍቅር ላይ መሆኑን ልጆቻችሁ እንዲመለከቱ አድርጉ። አብዛኛውን ጊዜ ልጆች የትምህርት ቤት ውሏቸው ውጥረትና ጭንቀት ስለሚፈጥርባቸው እንዲህ ያለውን ተጽእኖ ለመቋቋም እንዲችሉ ወላጆች ብዙ ማበረታቻ ሊሰጧቸው ይገባል።
ወላጆች ፍጹም መስላችሁ ለመቅረብ አትሞክሩ። ስህተታችሁን አምናችሁ ተቀበሉ፤ እንዲሁም አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ ልጆቻችሁን ይቅርታ ጠይቁ። ወጣቶች፣ አባባና እማማ ስህተታቸውን አምነው ሲቀበሉ ይበልጥ ልትወዷቸው ይገባል።—መክብብ 7:16
አዎን፣ አንድነት ያለው ቤተሰብ ሰላም፣ ደኅንነት እንዲሁም ደስታ ያለበት ቤት ያስገኛል። የጀርመኑ ባለቅኔ ጎቴ በአንድ ወቅት እንዲህ ብሎ ነበር:- “አንድ ሰው ንጉሥ ይሁን ገበሬ፣ እጅግ በጣም ደስተኛ ነው ሊባል የሚችለው በቤተሰቡ ደስተኛ ሲሆን ነው።” አድናቂ ለሆኑ ወላጆችና ልጆች ቤትን የመሰለ ሌላ ቦታ የትም ሊኖር አይችልም።
አዎን፣ የምንኖርበት ዓለም በሚያመጣቸው ተጽእኖዎች ምክንያት ቤተሰብ በዛሬው ጊዜ በከፍተኛ አደጋ ላይ ወድቋል። ይሁን እንጂ ቤተሰብን የመሠረተው አምላክ ስለሆነ ከውድቀት ይድናል። አምላክ ለደስተኛ ቤተሰብ ያወጣቸውን የጽድቅ መመሪያዎች ከተከተልህ አንተም ሆንክ ቤተሰብህ ከውድቀት ትድናላችሁ።
[የግርጌ ማስታወሻ]
a በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር የታተመውን ለቤተሰብ ደስታ ቁልፉ ምንድን ነው? (የእንግሊዝኛ) የተባለውን ባለ 192 ገጽ መጽሐፍ ተመልከት።