ሰዎች ከሃይማኖት እየራቁ ያሉት ለምንድን ነው?
በ19ኛው መቶ ዘመን አጋማሽ ሃይማኖት የለሽ የሆነ አንድም የፕሩሲያ (አሁን ሰሜናዊ ጀርመን) ነዋሪ አልነበረም ማለት ይቻላል። እንዲያውም አባልነቱን ከአንድ ነባር ሃይማኖት በይፋ ተቀባይነት ያገኙ አስተሳሰቦችን ወደማይቀበል ቤተ ክርስቲያን የቀየረ ሰው የፖሊስ ክትትል ይደረግበት ነበር። ጊዜው እንዴት ተለውጧል!
በዛሬው ጊዜ በርካታ ቁጥር ያላቸው ጀርመናውያን ከቤተ ክርስቲያን አባልነት ራሳቸውን እያገለሉ ነው። ከአራት ሰዎች መካከል አንዱ የየትኛውም ሃይማኖት አባል አለመሆኑን እንደሚገልጽ ዘገባዎች ያመለክታሉ። በኦስትሪያና በስዊዘርላንድም ተመሳሳይ የሆነ ዝንባሌ ይታያል። የአንድ ሃይማኖት ሕልውና የተመካው በአባላቱ ቁጥር ከሆነ ጀርመናዊው ጸሐፊ ሪመር ግሮንሚየር እንዳሉት አባላቶቻቸውን እያጡ ያሉት “የአውሮፓ አብያተ ክርስቲያናት ሊሞቱ በማጣጣር ላይ ናቸው።”
ሰዎች ከሃይማኖት የሚርቁበት ምክንያት
ብዙ ሰዎች ነባር ሃይማኖቶችን የሚተዉት ለምንድን ነው? አብዛኛውን ጊዜ ገንዘብ ነክ በሆኑ ምክንያቶች ሲሆን በተለይ ደግሞ አባላቶቹ የቤተ ክርስቲያን ግብር እንዲከፍሉ በሚገደዱባቸው አገሮች ይህ ሁኔታ ይከሰታል። ብዙዎች ‘ላቤን አንጠፍጥፌ ያገኘሁትን ገንዘብ ለቤተ ክርስቲያን የምገብርበት ምክንያት ምንድን ነው?’ ብለው ይጠይቃሉ። አንዳንዶች ደግሞ ቤተ ክርስቲያን ያጋበሰችው ሀብትና ያላት ሥልጣን በጣም ያስከፋቸዋል። እነዚህ ሰዎች በጀርመን የኮሎኝ ካርዲናል የሆኑት ዮአኪም ሚስነር፣ ቤተ ክርስቲያን ያላት ሀብት “በክርስቶስ ላይ እምነት ስለማሳደር በቁም ነገር ከማሰብ ይልቅ” ይበልጥ ትኩረቷን ለቁሳዊ ነገሮች እንድትሰጥ አድርጓታል ሲሉ በተናገሩት ቃል እንደሚስማሙ ግልጽ ነው።
አንዳንዶች ደግሞ ቤተ ክርስቲያናቸውን ትተው የሚሄዱት ትምህርቱ አሰልቺ፣ የማይጥምና መንፈሳዊ ረሃባቸውን የማያረካ ስለሚሆንባቸው ነው። ነቢዩ አሞጽ “የእግዚአብሔርን ቃል ከመስማት እንጂ እንጀራን ከመራብና ውኃን ከመጠማት አይደለም” በማለት አስቀድሞ በተናገረለት ረሃብ እየተጠቁ ነው። (አሞጽ 8:11) ከሃይማኖታቸው ምንም መንፈሳዊ ምግብ ስለማያገኙ ሃይማኖታቸውን ለመተው ይገደዳሉ።
እነዚህ ችግሮች በተጨባጭ የተከሰቱ ቢሆንም ሁሉንም ሃይማኖቶች እስከ ጭራሹ እርግፍ አድርጎ መተው ትክክለኛ እርምጃ ነውን? ለምሳሌ ያህል አንድ የራበው ሰው ዳቦ የሚመስልን ነገር ቢመለከትና ሊበላው ሲል ከሳጋቱራ የተሠራ ነገር ሆኖ ቢያገኘው ምግብ ለመብላትና ረሃቡን ለማስታገሥ የነበረውን ሐሳብ እርግፍ አድርጎ ይተዋልን? በፍጹም፤ ከዚህ ይልቅ ትክክለኛ ምግብ መፈለጉን ይቀጥላል። በተመሳሳይም አንድ ሃይማኖት የአባላቱን መንፈሳዊ ረሃብ ማርካት ሳይችል ቢቀር አባላቱ ሁሉንም ሃይማኖት እርግፍ አድርገው መተው ይኖርባቸዋልን? ወይስ መንፈሳዊ ረሃባቸው የሚረካበትን መንገድ መፈለጋቸው አስተዋይነት ነው? ቀጥሎ እንደምንመለከተው ብዙዎች ያደረጉት ይህንን ነው።