የመጠበቂያ ግንብ የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
መጠበቂያ ግንብ
የኢንተርኔት ቤተ መጻሕፍት
አማርኛ
፦
  • ፡
  • መጽሐፍ ቅዱስ
  • የሕትመት ውጤቶች
  • ስብሰባዎች
  • w98 12/1 ገጽ 4-7
  • ወደ እውነተኛ እምነት የሚመራ ስም

በዚህ ክፍል ውስጥ ምንም ቪዲዮ አይገኝም።

ይቅርታ፣ ቪዲዮውን ማጫወት አልተቻለም።

  • ወደ እውነተኛ እምነት የሚመራ ስም
  • የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
  • ንዑስ ርዕሶች
  • ተመሳሳይ ሐሳብ ያለው ርዕስ
  • የኢየሱስ ስም የሚወክለው ነገር
  • በክርስቶስ ማመን ወይስ በቄሣር?
  • የጥንቶቹን ክርስቲያኖች ምሳሌ መከተል
  • በኢየሱስ ስም ማመን ሲባል ምን ማለት ነው?
  • የአምላክን ስም ማወቅ የሚኖርብን ለምንድን ነው?
    ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም
  • የአንባቢያን ጥያቄዎች
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1995
  • የይሖዋ ስም—ልንሰጠው የሚገባው ቦታ
    የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ (የጥናት እትም)—2025
  • የአምላክ ስም
    ንቁ!—2017
ለተጨማሪ መረጃ
የይሖዋን መንግሥት የሚያስታውቅ መጠበቂያ ግንብ—1998
w98 12/1 ገጽ 4-7

ወደ እውነተኛ እምነት የሚመራ ስም

“እናንተ በኢየሱስና በቤዛዊ ደሙ አታምኑም” ስትል አንዲት ሴት ለአንድ የይሖዋ ምሥክር ተናገረች። አንድ ሌላ ሰው ደግሞ “እናንተ የይሖዋ ምሥክሮች ነን ትላላችሁ፣ እኔ ደግሞ የኢየሱስ ምሥክር ነኝ” ሲል ፈርጠም ብሎ ተናግሯል።

የይሖዋ ምሥክሮች በኢየሱስ አያምኑም ወይም ተገቢውን አክብሮት አይሰጡትም የሚለው አመለካከት በጣም የተለመደ ነው። ይሁን እንጂ ሐቁ ምንድን ነው?

እርግጥ ነው፣ የይሖዋ ምሥክሮች ይሖዋ ለሚለው የአምላክ ስም ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣሉ።a በብራዚል የሚኖረው ኢታማር የተባለ የይሖዋ ምሥክር እንዲህ ሲል ያስታውሳል:- “የአምላክን ስም ሳውቅ በሕይወቴ ውስጥ ወሳኝ ለውጥ አደረግሁ። ለመጀመሪያ ጊዜ ስሙን ሳነብ ልክ ከከባድ እንቅልፍ የባነንኩ ያህል ነበር የተሰማኝ። ይሖዋ የሚለው ስም በጥልቅ ነካኝ እንዲሁም ለሥራ አንቀሳቀሰኝ፤ ስሙ በሕይወቴ ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አሳድሯል።” ሆኖም “ለኢየሱስም ከፍተኛ ፍቅር አለኝ” ሲል አክሎ ተናግሯል።

አዎን፣ የይሖዋ ምሥክሮች የዘላለም ሕይወት ለማግኘት “በእግዚአብሔር ልጅ ስም” በኢየሱስ ማመን እንዳለባቸው ይገነዘባሉ። (1 ዮሐንስ 5:​13) ይሁን እንጂ ‘በኢየሱስ ስም’ የሚለው አባባል ምን ትርጉም ይዟል?

የኢየሱስ ስም የሚወክለው ነገር

በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ወይም በ“አዲስ ኪዳን” ውስጥ በሙሉ “በኢየሱስ ስም” የሚሉና ተመሳሳይ የሆኑ አገላለጾች ይገኛሉ። እንዲያውም ኢየሱስ ካለው ሚና ጋር በተያያዘ “ስም” የሚለው ቃል ከ80 ጊዜ በላይ የሚገኝ ሲሆን በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ብቻ ደግሞ ወደ 30 ጊዜ ያህል ይገኛል። የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖች በኢየሱስ ስም አጥምቀዋል፣ በስሙ ፈውሰዋል፣ በስሙ አስተምረዋል፣ በስሙ ተጠርተዋል፣ ለስሙ ሲሉ መከራ ተቀብለዋል እንዲሁም ስሙን ከፍ ከፍ አድርገዋል።​—⁠ሥራ 2:​38፤ 3:​16፤ 5:​28፤ 9:​14, 16፤ 19:​17

በአንድ የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ማብራሪያ መሠረት “ስም” ለሚለው ቃል የገባው የግሪክኛ ቃል በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተደጋጋሚ የተሠራበት “ስም በተዘዋዋሪ መንገድ የሚገልጻቸውን ነገሮች በሙሉ ማለትም ሥልጣንን፣ ባሕርይን፣ ማዕረግን፣ ግርማዊነትን፣ ኃይልን፣ ክብርን፣ ወዘተ በሚያመለክት ሁኔታ ነው።” ይህም በመሆኑ የኢየሱስ ስም ይሖዋ አምላክ የሰጠውን ታላቅና ሰፊ የሆነ የመግዛት ሥልጣኑን የሚያመለክት ነው። ኢየሱስ ራሱ እንዲህ ሲል ገልጿል:- “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ።” (ማቴዎስ 28:​18) ጴጥሮስና ዮሐንስ አንካሳ የነበረን ሰው ከፈወሱ በኋላ የአይሁድ ሃይማኖታዊ መሪዎች “በምን ኃይል ወይስ በማን ስም እናንተ ይህን አደረጋችሁ?” ሲሉ ጠይቀዋቸዋል። በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ይህ ደኅና ሆኖ በፊታችሁ . . . ቆመ” ብሎ ጉዳዩን ሲያሳውቅ የኢየሱስ ስም በሚወክለው ሥልጣንና ኃይል ላይ ያለውን እምነት በድፍረት ገልጿል።​—⁠ሥራ 3:​1–10፤ 4:​5–10

በክርስቶስ ማመን ወይስ በቄሣር?

ሆኖም በኢየሱስ ስም ላይ ይህ ዓይነቱ እምነት እንዳለን መናገሩ ቀላል አይሆንም። ኢየሱስ አስቀድሞ እንደተናገረው ደቀ መዛሙርቱ ‘ስለ ስሙ በአሕዛብ ሁሉ የተጠሉ’ ይሆናሉ። (ማቴዎስ 24:​9) ለምን? የኢየሱስ ስም ብሔራት ባጠቃላይ ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ሊገዙለት የሚገባ በአምላክ የተሾመ የነገሥታት ንጉሥ የሆነው ገዥ መሆኑን ስለሚወክልና ብሔራት ደግሞ ይህን ለማድረግ ዝግጁ ወይም ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ምክንያት ነው።​—⁠መዝሙር 2:​1–7

በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ሃይማኖታዊ መሪዎችም ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ለእሱ መገዛት አልፈለጉም። “ከቄሣር በቀር ሌላ ንጉሥ የለንም” ብለው በተናገሩ ጊዜ የአምላክን ልጅ አንቀበልም ማለታቸው ነበር። (ዮሐንስ 19:​13–15) ከዚህ ይልቅ እምነታቸውን የጣሉት በቄሣርና በንጉሣዊ መንግሥቱ ስም ማለትም በቄሣር ኃይልና ሥልጣን ላይ ነበር። እንዲያውም ያላቸውን ሥልጣንና ማዕረግ ማስከበር እንዲችሉ ኢየሱስ መገደል አለበት ብለው ወስነዋል።​—⁠ዮሐንስ 11:​47–53

ኢየሱስ ከሞተ በኋላ ባሉት ምዕተ ዓመታት የኖሩ ብዙ ክርስቲያን ነን ባዮች የአይሁድ መሪዎች የነበራቸውን ዓይነት አስተሳሰብ ተከትለዋል። እነዚህ ክርስቲያን ነን ባዮች እምነታቸውን የጣሉት መንግሥት ባለው ኃይልና ሥልጣን ላይ ሲሆን ግጭቶች ውስጥ በሚገባበት ጊዜም ተሳትፎ ያደርጋሉ። ለምሳሌ ያህል በ11ኛው መቶ ዘመን ቤተ ክርስቲያን ከውትድርና የተገለሉ ወታደሮችን ሚሊቲያ ክሪስቲ ወይም ታጣቂ ክርስቲያኖች አድርጋ ካደራጀች በኋላ “የጽድቅ ጦርነት የማካሄዱ ኃላፊነት ከሕዝበ ክርስትና የመንግሥት ባለሥልጣናት እጅ ተወስዶ ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ማዕረግ ባላቸው ክርስቲያን ወታደሮች አማካኝነት እንድትቆጣጠረው ተደረገ።” (ዚ ኦክስፎርድ ሂስትሪ ኦቭ ክርስቺያኒቲ) አንዳንድ የሊቃነ ጳጳሳቱ መግለጫዎች አብዛኞቹን የመስቀል ጦርነት ተፋላሚዎች በመስቀል ጦርነት በመካፈል “ከአምላክ ጋር እንደተዋዋሉና በገነት ውስጥ ቦታ ማግኘታቸው የተረጋገጠ እንደሆነ” እንዲያምኑ አድርገዋቸዋል በማለት ዘገባው አክሎ ተናግሯል።

አንዳንዶች በፖለቲካ ጉዳዮችም ሆነ ብሔራት በሚያካሂዷቸው ጦርነቶች እየተሳተፉ ለኢየሱስም ታማኝ መሆን ይቻላል ብለው ይከራከሩ ይሆናል። ከማንኛውም ቦታ ክፋትን ማስወገድ የክርስቲያኖች ግዴታ እንደሆነና ይህ ደግሞ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ጦርነትን እንደ አማራጭ አድርጎ መውሰድን እንደሚጨምር ይሰማቸው ይሆናል። ይሁን እንጂ የቀድሞዎቹ ክርስቲያኖች ይህ ዓይነት አመለካከት ነበራቸውን?

“የጥንቶቹ ክርስቲያኖች በውትድርና ውስጥ ገብተው አላገለገሉም” በማለት ዘ ክርስቺያን ሴንቸሪ በተባለው መጽሔት ላይ የወጣ አንድ ርዕስ ይገልጻል። ከ170–180 እዘአ ድረስ ክርስቲያኖች በውትድርና ስለማገልገላቸው የሚገልጽ አንድም ማስረጃ አለመኖሩን አትቷል። ጽሑፉ በመቀጠል “ክርስቲያኖች ለውትድርና አገልግሎት ያላቸውን ተቃውሞ እየተዉ የመጡት ቀስ በቀስ ነበር” ሲል ይገልጻል።

እንዲህ ማድረጋቸው ምን ውጤት አስከትሏል? “የክርስትና እምነት በጦርነት እንቅስቃሴዋ ክርስቲያን ካልሆኑት ፈጽሞ ያልተሻለ አቋም መውሰድዋ ለክርስትና ስም መጉደፍ ዋናው መንስዔ ሳይሆን አይቀርም” በማለት ዘ ክርስቺያን ሴንቸሪ ዘግቧል። “ክርስቲያኖች በአንድ ወገን ሩኅሩኅ የሆነውን አዳኝ እምነት ሲደግፉ በሌላ ወገን ደግሞ ሃይማኖታዊና ብሔራዊ ጦርነቶችን በጋለ ስሜት መደገፋቸው ሃይማኖቱ ክፉኛ እንዲበላሽ አድርጓል።”

የጥንቶቹን ክርስቲያኖች ምሳሌ መከተል

ዛሬ ያሉ ክርስቲያኖች የጥንቶቹ ክርስቲያኖች የተዉትን ፍጹም ምሳሌ መከተል ይችላሉ? በዚህ መቶ ዘመን ያሉት የይሖዋ ምሥክሮች ይህ እንደሚቻል አሳይተዋል። የሆሎኮስት ኤጁኬሽናል ዳይጀስት አዘጋጅ ስለ እነርሱ የሚከተለውን ተናግረዋል:- “የትኛውም የይሖዋ ምሥክር ምንጊዜም ወደ ጦርነት አይሄድም። . . . በዓለም ዙሪያ በሥልጣን ላይ ያለ እያንዳንዱ ሰው የዚህ እምነት ተከታይ ቢሆን ኖሮ [ሁለተኛው የዓለም ጦርነት] ጭራሽ ባልተከሰተ ነበር።”

ሰሜን አየርላንድን ያመሰውን ግጭት ጨምሮ በቅርቡ ስለተካሄዱት የአካባቢ ግጭቶች ተመሳሳይ ነገር ማለት ይቻላል። ከጥቂት ዓመታት በፊት አንድ የይሖዋ ምሥክር ቤልፋስት ከተማ ውስጥ ፕሮቴስታንቶች በሚኖሩበት አካባቢ ከቤት ወደ ቤት እየሰበከ ነበር። የይሖዋ ምሥክሩ ቀደም ሲል ካቶሊክ እንደነበረ ያወቀ አንድ ሰው “ካቶሊክ በነበርክበት ጊዜ አይ አር ኤን [አይሪሽ ሪፑብሊካን አርሚ] ትደግፍ ነበር?” ሲል ጠየቀው። ሰውየው አንድን ካቶሊክ ለመግደል መሣሪያ ታጥቆ ሲሄድ ተይዞ ከታሰረ በኋላ የተለቀቀው በቅርቡ በመሆኑ ጠብ ሊያነሳ እንደሚችል የይሖዋ ምሥክሩ ተገነዘበ። ስለዚህ ምሥክሩ እንዲህ ሲል መለሰለት:- “አሁን ካቶሊክ ሳይሆን የይሖዋ ምሥክር ነኝ። እውነተኛ ክርስትያን እንደመሆኔ መጠን፣ ለየትኛውም መንግሥት ወይም ለማንኛውም ሰው ስል ማንንም አልገድልም።” በዚህ ጊዜ የቤቱ ባለቤት ከጨበጠው በኋላ እንዲህ አለው:- “ባጠቃላይ ሲታይ መግደል ስህተት ነው። ሥራችሁን አደንቃለሁ፤ ግፉበት።”

በኢየሱስ ስም ማመን ሲባል ምን ማለት ነው?

ሆኖም በኢየሱስ ስም ማመን ሲባል ከጦርነት መራቅ ማለት ብቻ አይደለም። ክርስቶስ የሰጠውን ትእዛዛት በሙሉ ማክበር ማለት ነው። እንዲያውም ኢየሱስ “እኔ ያዘዝኋችሁን ሁሉ ብታደርጉ እናንተ ወዳጆቼ ናችሁ” ብሏል። ከሰጠን ትእዛዛት አንዱ “እርስ በርሳችሁ እንድትዋደዱ” የሚል ነው። (ዮሐንስ 15:​14, 17) ፍቅር ለሌሎች ጥሩ ነገር ለማድረግ ይፈልጋል። ፍቅር በዘር፣ በሃይማኖትና በኑሮ ደረጃ የሚደረገውን ማንኛውንም መድሎ ያስወግዳል። ኢየሱስ ይህ እንዴት ሊሆን እንደሚችል አሳይቷል።

በኢየሱስ ዘመን የነበሩት አይሁዶች ሳምራውያንን በጣም ይጠሏቸው ነበር። በአንጻሩ ኢየሱስ ከአንዲት ሳምራዊት ሴት ጋር የተነጋገረ ሲሆን ከዚህም የተነሳ እሷና ሌሎች ብዙ ሰዎች በስሙ አምነዋል። (ዮሐንስ 4:​39) ከዚህ በተጨማሪም ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱ “በኢየሩሳሌምም በይሁዳም ሁሉ በሰማርያም እስከ ምድር ዳርም ድረስ” ምስክሮቹ እንደሚሆኑ ተናግሯል። (ሥራ 1:​8) ሕይወት አድን የሆነው መልእክቱ ለአይሁዶች ብቻ የተወሰነ አይደለም። በዚህ መሠረት ጴጥሮስ የሮም የጦር አዛዥ ወደሆነው ወደ ቆርኔሌዎስ እንዲሄድ ተነግሮት ነበር። ምንም እንኳ አንድ አይሁዳዊ የሌላ ዘር የሆነ ሰው ጋር እንዲሄድ ሕጉ የማይፈቅድለት ቢሆንም አምላክ ለጴጥሮስ ‘ማንንም ሰው ርኩስና አስጸያፊ እንዳይል’ ነግሮታል።​—⁠ሥራ 10:​28

የይሖዋ ምሥክሮች የኢየሱስን አርአያ በመከተል ሰዎች የትኛውም ዓይነት የዘር፣ የሃይማኖት ወይም የኑሮ ሐረግ ይኑራቸው ሁሉም ሰዎች በኢየሱስ ስም አማካኝነት ስለሚገኘው ደህንነት እንዲያውቁ በፈቃደኝነት ይረዳሉ። በኢየሱስ ስም ላይ ያላቸው እምነት ‘ኢየሱስ ጌታ መሆኑን በግልጽ እንዲመሰክሩ’ ያነሳሳቸዋል። (ሮሜ 10:​8, 9) አንተም በኢየሱስ ስም ላይ እምነት ማሳደር እንድትችል እነሱ የሚሰጡትን እርዳታ እንድትቀበል እናበረታታሃለን።

በእርግጥም የኢየሱስ ስም በውስጣችን የአክብሮት፣ የአድናቆትና የታዛዥነት ስሜት ሊያሳድርብን ይገባል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል ጽፏል:- “ይህም በሰማይና በምድር ከምድርም በታች ያሉት ሁሉ በኢየሱስ ስም ይንበረከኩ ዘንድ፣ መላስም ሁሉ ለእግዚአብሔር አብ ክብር ኢየሱስ ክርስቶስ ጌታ እንደ ሆነ ይመሰክር ዘንድ ነው።” (ፊልጵስዩስ 2:​10, 11) ምንም እንኳ አብዛኛው የምድር ነዋሪ ለኢየሱስ ሥልጣን ለመገዛት ፈቃደኛ ባይሆንም መጽሐፍ ቅዱስ ሰዎች ባጠቃላይ እንዲህ ማድረግ እንዳለባቸውና ይህ ካልሆነ የሚጠፉበት ጊዜ ቅርብ መሆኑን ይገልጻል። (2 ተሰሎንቄ 1:​6–9) ይህም በመሆኑ ትእዛዛቱን ሁሉ በመጠበቅ በኢየሱስ ስም ላይ እምነት ማሳደር የሚቻልበት ጊዜ አሁን ነው።

[የግርጌ ማስታወሻ]

a ተጨማሪ ማብራሪያ ለማግኘት ኒው ዮርክ በሚገኘው የመጠበቂያ ግንብ መጽሐፍ ቅዱስና ትራክት ማኅበር ከታተመው ለዘላለም ጸንቶ የሚኖረው መለኮታዊው ስም ከተባለው ብሮሹር ገጽ 28–31ን ተመልከት።

[በገጽ 6 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

በሚልዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በኢየሱስ ስም ገድለዋል እንዲሁም ተገድለዋል

[በገጽ 7 ላይ የሚገኝ ሥዕል]

ኢየሱስ የዘር ጥላቻ አልነበረውም። አንተስ?

    አማርኛ ጽሑፎች (1991-2025)
    ውጣ
    ግባ
    • አማርኛ
    • አጋራ
    • የግል ምርጫዎች
    • Copyright © 2025 Watch Tower Bible and Tract Society of Pennsylvania
    • የአጠቃቀም ውል
    • ሚስጥር የመጠበቅ ፖሊሲ
    • ሚስጥር የመጠበቅ ማስተካከያ
    • JW.ORG
    • ግባ
    አጋራ