ለማንኛውም መልካም ሥራ ራሳችንን በፈቃደኝነት ማቅረብ
1 “የይሖዋ ምሥክሮችን ያህል ለሃይማኖታቸው ጠንክረው የሚሠሩ የሌላ ቡድን አባላት ማግኘት ያስቸግራል” በማለት አንድ ዓለማዊ ጽሑፍ ስለ ይሖዋ ምሥክሮች ተናግሯል። የይሖዋ ምሥክሮች በትጋትና እንዲህ ባለው የፈቃደኝነት መንፈስ የሚሠሩት ለምንድን ነው?
2 አንዱ ምክንያት በጥድፊያ ስሜት የተሞሉ ስለሆኑ ነው። ኢየሱስ በምድር ላይ የሚያከናውነውን ሥራ ለማጠናቀቅ ያለው ጊዜ የተወሰነ እንደነበረ ተገንዝቦ ነበር። (ዮሐ. 9:4) ክብራማው የአምላክ ልጅ በጠላቶቹ መካከል እየገዛ ባለበት በአሁኑ ጊዜ የይሖዋ ምሥክሮች ሥራቸውን ለማከናወን ያላቸው ጊዜ ውስን እንደሆነ ይገነዘባሉ። ስለዚህ ምንጊዜም በፈቃደኝነት ራሳቸውን ለቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ። (መዝ. 110:1–3 አዓት) ለመከሩ ሥራ ብዙ ሠራተኞች በሚያስፈልጉበት በዛሬው ጊዜ በትጋት ከመሥራት ወደኋላ ሊሉ አይችሉም። (ማቴ. 9:37, 38) በመሆኑም በሥራው ፍጹም የሆነ የፈቃደኝነትና የታታሪነት ምሳሌ የተወውን ኢየሱስን ለመምሰል ይጥራሉ።— ዮሐ. 5:17
3 የይሖዋ ምሥክሮች ለይሖዋ እንደሚሠሩ አድርገው በሙሉ ነፍሳቸው የሚሠሩበት ሌላው ምክንያት ዓለም አቀፋዊው ድርጅታቸው ከሌላ ከማንኛውም ቡድን የተለየ ስለሆነ ነው። ዓለማዊ የሃይማኖት ድርጅቶች ከተከታዮቻቸው የሚፈልጉት ጊዜና ጥረት አነስተኛ ነው። የሚያምኑት ነገር በዕለታዊ ሕይወታቸው፣ ከሌሎች ጋር ባላቸው ግንኙነት ወይም በሕይወታቸው ውስጥ ቅድሚያ በሚሰጡት ነገር ላይ የሚያመጣው ለውጥ አነስተኛ ነው፤ ወይም ደግሞ ጭራሹኑ ለውጥ አያመጣም። የእውነተኛው እምነት አንቀሳቃሽ ኃይል ስለሌላቸው ያደረጉት የይስሙላ ጥረት በቂ እንደሆነ በማረጋገጥ እረኞቻቸው ‘ለስላሳ የሆነውን ነገር እንዲነግሯቸው ’ አጥብቀው ይጠይቃሉ። (ኢሳ. 30:10 የ1980 ትርጉም) ቄሶቻቸው ግዴለሽነትንና መንፈሳዊ ስንፍናን ቀስ በቀስ በውስጣቸው በመትከል ‘እነርሱ የሚወድዱትን ይነግሯቸዋል።’— 2 ጢሞ. 4:3 የ1980 ትርጉም
4 ከይሖዋ ሕዝቦች ምንኛ የተለዩ ናቸው! የትኛውም የአምልኳችን ክፍል ጥረት፣ ልፋትና ድካም ይጠይቃል። በየትኛውም ቀንና በምንሠራው ማንኛውም ሥራ የምናምንበትን ነገር በተግባር እናውላለን። እውነት ከፍተኛ ደስታ ቢያስገኝልንም የሚጠይቅብንን ነገር ለማሟላት “ብዙ ገድል” ይፈለግብናል። (ከ1 ተሰሎንቄ 2:2 ጋር አወዳድር።) ዕለታዊው ኑሮ የሚያስከትልባቸውን ኃላፊነቶች ለመወጣት የሚያደርጉት ጥረት ብቻ ብዙዎቹን ሰዎች በሥራ እንዲወጠሩ ያደርጋቸዋል። እኛ ግን እነዚህ ሁኔታዎች ለመንግሥቱ ጉዳዮች የመጀመሪያ ቦታ ከመስጠት እንዲያግዱን አንፈቅድም።— ማቴ. 6:33
5 በይሖዋ አገልግሎት ውስጥ እንድንሠራ የተሰጠን ሥራ በጣም ጠቃሚና አጣዳፊ ስለሆነ ከሌሎች ጉዳዮች ጊዜ ‘ለመዋጀትና’ የተሻለ ጥቅም ለሚያስገኙት መንፈሳዊ ጉዳዮች ለማዋል ተገፋፍተናል። (ኤፌ. 5:16) ለአምላክ ማደራችንና የፈቃደኝነት መንፈሳችን ይሖዋን እንደሚያስደስተው ማወቃችን በተያያዝነው ከባድ ሥራ እንድንቀጥል የሚያስችል ታላቅ ማበረታቻ ነው። በአሁኑ ጊዜ የተትረፈረፉ በረከቶች ስለምንቀበልና ወደፊት ሕይወት እንደምናገኝ ተስፋ ስለምናደርግ ለመንግሥቱ ጉዳዮች ‘እየታገልንና እየደከምን’ በውሳኔያችን እንቀጥላለን።— 1 ጢሞ. 4:10 የ1980 ትርጉም
6 ለአምላክ ያደሩ መሆንና ራስን መሥዋዕት የማድረግ መንፈስ፦ በዛሬው ጊዜ አብዛኞቹ ሰዎች ከማንኛውም ነገር ይልቅ ለቁሳዊ ፍላጎቶችና ጥቅሞች ቅድሚያ ይሰጣሉ። በሚበሉት በሚጠጡት ወይም በሚለብሱት ነገር ላይ ማተኮር ሙሉ በሙሉ ተገቢ እንደሆነ ይሰማቸዋል። (ማቴ. 6:31) ለሕይወት በሚያስፈልጋቸው ነገር ከመርካት ይልቅ በአሁኑ ጊዜ የተደላደለ ኑሮ የመኖርና ‘ለመዝናናት፣ ለመብላት፣ ለመጠጣትና ለመደሰት እንዲችሉ ለብዙ ጊዜ የሚሆኑ አያሌ ጥሩ ነገሮችን የማጠራቀም’ ግብ ከፊታቸው አስቀምጠው ይህን ግባቸውን ዳር ለማድረስ ጠንክረው ይሠራሉ። (ሉቃስ 12:19) አዘውታሪ የቤተ ክርስቲያን ተሳላሚ የሆነ ሰው ሃይማኖቱ የሚፈልግበት ማንኛውም የግል ጥረት መብቶቹን የሚጋፋበት ይመስለዋል። ቁሳዊ ነገሮችን ከማሳደድ ለመታቀብ ሌላው ቀርቶ ለዚያ የሚያውለውን ጊዜ ለመቀነስ ወይም ደግሞ ደስታ የሚያስገኙ ነገሮችን ለመተው አይስማማም። አስተሳሰቡ በራሱ ላይ ያተኮረ ስለሆነ ራስን የመሠዋት መንፈስ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም።
7 እኛ ይህንን የምንመለከተው በተለየ መንገድ ነው። የአምላክ ቃል አመለካከታችንን ስላሳደገልን የሰው ሳይሆን የአምላክ ዓይነት አስተሳሰብ አለን። (ኢሳ. 55:8, 9) በሕይወታችን ውስጥ ሥጋዊ ነገሮችን ከማሳደድ የሚበልጡ ግቦች አሉን። የይሖዋ ሉዓላዊነት መረጋገጥና የስሙ መቀደስ በመላው አጽናፈ ዓለም ውስጥ የላቀ ቦታ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ናቸው። እነዚህ ጉዳዮች ትልቅ ስፋት ስላላቸው አሕዛብ ከእነዚህ አከራካሪ ጉዳዮች ጋር ሲወዳደሩ በይሖዋ ‘ፊት እንዳሉ እንኳ የሚቆጠሩ አይደሉም።’ (ኢሳ. 40:17 የ1980 ትርጉም) የአምላክን ፈቃድ ችላ ብለን ሕይወታችንን ለመግፋት የምናደርገው ማንኛውም ሙከራ እንደ ሞኝነት መታየት አለበት።— 1 ቆሮ. 3:19
8 የመንግሥቱ እንቅስቃሴዎቻችንን ከግቡ ለማድረስ አንዳንዶቹ ቁሳዊ ነገሮች አስፈላጊ ሲሆኑ ሌሎቹ ደግሞ ጠቃሚ ናቸው፤ ቢሆንም እነዚህ ነገሮች ‘ይበልጥ የተሻሉ ነገሮች’ እንዳልሆኑ እንገነዘባለን። (ፊልጵ. 1:10) ለቁሳዊ ነገሮች የምናውለውን ጊዜ በመቀነስና ልባችን ‘በማይታየውና ዘላለማዊ በሆነው’ ነገር ላይ እንዲያተኩር ጥበብ የተሞላበት ጥረት በማድረግ 1 ጢሞቴዎስ 6:8 የሚሰጠውን ሐሳብ በሥራ እናውላለን።— 2 ቆሮ. 4:18
9 ስለ አምላካዊ ነገሮች ይበልጥ ባሰብን መጠን ለቁሳዊ ነገሮች ያለን ጉጉት ይቀንሳል። ይሖዋ ከዚህ ቀደም ያደረገልንንና ለወደፊቱ ቃል የገባልንን አስደናቂ በረከቶች ስናሰላስል የሚጠይቅብንን ማንኛውንም መሥዋዕትነት ለመክፈል ፈቃደኞች እንሆናለን። (ማር. 10:29, 30) መላ ሕይወታችንን ለእርሱ እናቀርባለን። በመሐሪነቱና በፍቅሩ ባይሆን ኖሮ አሁንም ሆነ ወደፊት በሕይወታችን ደስታ አናገኝም ነበር። በይሖዋ አገልግሎት የምናደርገው ማንኛውም ነገር ‘ልናደርገው የሚገባን’ ስለሆነ ራሳችንን ዝግጁ አድርገን ማቅረብ እንዳለብን ይሰማናል። (ሉቃስ 17:10) ‘በበረከት እንደምናጭድ’ ስለምናውቅ ለይሖዋ መልሰን እንድንሰጥ የተጠየቅነውን ማንኛውንም ነገር በደስታ እንሰጣለን።— 2 ቆሮ. 9:6, 7
10 በአሁኑ ጊዜ ፈቃደኛ ሠራተኞች ያስፈልጋሉ፦ የክርስቲያን ጉባኤ ከመጀመሪያው አንስቶ በሥራ ተወጥሮ ነበር። ኢየሩሳሌም በ70 እዘአ ከመውደቋ በፊት የተሟላ ምሥክርነት መሰጠት ነበረበት። በዚያን ወቅት የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ‘ለቃሉ ይተጉ’ ነበር። (ሥራ 18:5) ፈጣን እድገት ስለነበረ ተጨማሪ ወንጌላውያንንና ብቃት ያላቸው እረኞችን ማሰልጠንና እርዳታ እንዲያበረክቱ ማድረግ አስፈልጎ ነበር። የሚሰበሰቡትንና የሚታደሉትን ቁሳዊ ነገሮች በበላይነት ለመቆጣጠር የሚችሉ ዓለማዊ ባለ ሥልጣኖችን በማነጋገር ረገድ ልምድ ያላቸውና ብቁ የሆኑ ወንዶች አስፈልገው ነበር። (ሥራ 6:1–6፤ ኤፌ. 4:11) ጥቂቶቹ በአገልግሎታቸው ጎላ ብለው ቢታዩም አብዛኞቹ ግን እምብዛም አይታወቁም። ነገር ግን ሁሉም አንድ ላይ ሆነው በሙሉ ልባቸው በመሥራት ሥራውን ለማከናወን ‘ተጋድለዋል።’— ሉቃስ 13:24
11 ከእነዚህ ጊዜያት በኋላ በነበሩት መቶ ዘመናት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጠንክሮ የመሥራቱ አስፈላጊነት በአንፃራዊነት ሲታይ ይህን ያህል የነበረ ቢሆንም ኢየሱስ በ1914 መንግሥታዊ ሥልጣኑን ሲቀበል የመንግሥቱ እንቅስቃሴ በከፍተኛ ደረጃ አንሰራራ። የመንግሥቱን ሥራዎች የሚያከናውኑ ብዙ ሠራተኞች የሚያስፈልጉበት ጊዜ እንደሚመጣና ይህም በምድር ዙሪያ የሚገኙ በሚልዮን የሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሰዎችን እርዳታ እንደሚጠይቅ ከመጀመሪያው የተገነዘቡት ጥቂቶች ነበሩ።
12 በዛሬው ጊዜ ድርጅቱ ብዛት ያላቸው የተለያዩ ሥራዎችን እያካሄደ ነው፤ እነዚህ ሥራዎች ኃይላችንንና ጥሪታችንን የሚጠይቁ ናቸው። የመንግሥቱ ሥራ በከፍተኛ ደረጃ ወደ ፊት እየገፋ ነው። ያለንበት ጊዜ አጣዳፊ መሆን ከፍተኛ ጥረት እንድናደርግና በእጃችን ያለውን ጥሪት መሠራት የሚያስፈልገውን ሥራ ለማከናወን እንድንጠቀምበት ይገፋፋናል። ይህ ክፉ የነገሮች ሥርዓት ሙሉ በሙሉ የሚያከትምበት ጊዜ በጣም እየቀረበ ስለሆነ በፊታችን ባሉት ጊዜያት ከዚህም የበለጠ ከፍተኛ ሥራ እንደምናከናውን እንጠብቃለን። እያንዳንዱ ራሱን የወሰነ የይሖዋ አገልጋይ አጣዳፊ በሆነው የመሰብሰቡ ሥራ በፈቃደኝነት እንዲካፈል ተጋብዟል።
13 መሠራት የሚገባው ነገር ምንድን ነው?፦ ‘ብዙ የጌታ ሥራ’ እንዳለ አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን። (1 ቆሮ. 15:58) በብዙ የአገልግሎት ክልሎች ውስጥ መከሩ ቢደርስም ሠራተኞቹ ግን ጥቂቶች ናቸው። የራሳችንን የአገልግሎት ክልል ሙሉ በሙሉ በመሸፈን ብቻ ሳንወሰን የምሥራቹ ሰባኪዎች ይበልጥ ወደሚያስፈልጉበት ቦታዎች ሄዶ ማገልገል የሚያስከትለውን ፈታኝ ሁኔታ በመቅመስ የድርሻችንን እንድንወጣ ተጋብዘናል።
14 በሁሉም የምድር ክፍሎች ያሉ የይሖዋ ምሥክሮች ለሌሎች ሥራዎችም ራሳቸውን በፈቃደኝነት ሲያቀርቡ ማየቱ የሚያስደስት ነው። ይህም የአምልኮ ቦታ ሲሠራ በፈቃደኝነት መካፈል፣ በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ማገልገልና ጉዳት ለደረሰባቸው የእርዳታ ቁሳቁስ ማድረስ እንዲሁም የጉባኤውን የመንግሥት አዳራሽ ሁልጊዜ ማጽዳትን ያጠቃልላል። መጨረሻ የተጠቀሰው ሥራ ከእያንዳንዱ ስብሰባ በኋላ የመንግሥት አዳራሹ ንጹሕና ሥርዓታማ መሆኑን ማረጋገጥን ያጠቃልላል። ዝቅተኛ እንደሆኑ ተደርገው የሚታዩ ሥራዎችን ማከናወን በሉቃስ 16:10 ላይ የተጠቀሱትን “ከሁሉ በሚያንስ የታመነ በብዙ ደግሞ የታመነ ነው፣ ከሁሉ በሚያንስም የሚያምፅ በብዙ ደግሞ ዓመፀኛ ነው” የሚሉትን የኢየሱስ ቃላት በሚገባ እንደተገነዘብናቸው ያሳያል።
■ የጉባኤውን እንቅስቃሴዎች ማገዝ፦ የእያንዳንዱ ጉባኤ እንቅስቃሴ የጠቅላላው ድርጅት ክፍል ከመሆኑም በተጨማሪ መመሪያዎችን “ከታማኝና ልባም ባሪያ” የሚቀበል ቢሆንም ጉባኤው በእያንዳንዱ የመንግሥቱ አስፋፊዎች የተገነባ ነው። (ማቴ. 24:45) የጉባኤው ሥራ ይበልጡኑ የተመካው እያንዳንዱ የይሖዋ ምሥክር ለመሥራት ፈቃደኛና ብቁ በመሆኑ ላይ ነው። ጉባኤው የሚያተኩረው ምሥራቹን በክልሉ ውስጥ በመስበክ፣ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት በማፍራትና ከዚያም በመንፈሳዊ በማጠናከር ላይ ነው። እያንዳንዳችን በዚህ ሥራ ላይ የበኩላችንን ድርሻ ማበርከት እንችላለን። በተጨማሪም ለግል ጥናት፣ በስብሰባዎች ላይ ትርጉም ያለው ተሳትፎ ለማድረግና በጉባኤው ውስጥ እርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ለመርዳት የራሳችንን ግቦች ማውጣት እንችላለን። እነዚህ እንቅስቃሴዎች መልካም ፈቃደኝነታችንን እንድናሳይ የሚያስችሉ ብዙ ጥሩ አጋጣሚዎች ይፈጥሩልናል።
■ የበላይ ተመልካች ሆኖ ማገልገል፦ ይሖዋ እያንዳንዱን ጉባኤ በበላይነት የመቆጣጠሩን ኃላፊነት ለጉባኤው የተሾሙ ሽማግሌዎች ሰጥቷል። (ሥራ 20:28 አዓት) እነዚህ ሰዎች ይህንን መብት ለማግኘት ጥረት ያደረጉ ወንዶች ናቸው። (1 ጢሞ. 3:1) በጉባኤ ውስጥ የሚገኙ ወንድሞች የተሻሉ ኃላፊነቶች ላይ መድረስ ይችላሉ። ብዙ ወንድሞች በመንፈሳዊነታቸው ገና በማደግ ላይ ስለሆኑ በጉባኤ ሽማግሌዎች አመራርና ፍቅራዊ እርዳታ አማካኝነት እድገታቸውን መቀጠል ያስፈልጋቸዋል። እነዚህ ወንዶች መጽሐፍ ቅዱስንና ጽሑፎቻችንን በትጋት የሚያጠኑ መሆን አለባቸው። በመንፈስ ለተሾሙት ሽማግሌዎች በመገዛት፣ እምነታቸውን በመምሰልና ከበላይ ተመልካቾች የሚፈለገውን ባሕርይ በመኮትኮት ፈቃደኛ መሆናቸውን ሊያሳዩ ይችላሉ።— ዕብ. 13:7, 17
■ የሙሉ ጊዜ አገልግሎት መጀመር፦ የጉባኤው ዋነኛ ተግባር ምሥራቹን መስበክ ነው። (ማቴ. 24:14) ቀናተኛ የሆኑ ወንድሞችና እህቶች አቅኚ በመሆን ጥረታቸውን ሲያጠናክሩ እንዴት ያለ በረከት ነው! ይህም ብዙውን ጊዜ በሕይወታቸው ውስጥ ማስተካከያዎችን ማድረግ ይጠይቅባቸዋል። በዚህ ልዩ የአገልግሎት መስክ መቀጠሉ ደግሞ ተጨማሪ ማስተካከያዎች ማድረግ ሊጠይቅባቸው ይችላል። ነገር ግን በአንዳንድ ጊዜያዊ የሆኑ ተስፋ የሚያስቆርጡ ነገሮች የተነሳ ከአንድ ወይም ከሁለት ዓመታት በኋላ አቅኚነታቸውን ሳያቆሙ ይህንን መብት አጥብቀው የያዙ ወንድሞችና እህቶች የይሖዋን የተትረፈረፈ በረከት እንደሚያገኙ አያጠራጥርም። አፍቃሪ ሽማግሌዎችና ሌሎች የጎለመሱ ክርስቲያኖች አቅኚዎችን በቃልና በተግባር በማበረታታት በያዙት የአገልግሎት መስክ ስኬታማ እንዲሆኑ አስተዋጽኦ ሊያደርጉ ይችላሉ። ትምህርታቸውን እንደጨረሱ በቀጥታ የአቅኚነት ሥራ የጀመሩ ወጣቶች እንዴት ያለ ግሩም መንፈስ አሳይተዋል! ዓለማዊ ሥራቸው ቀለል እንዳለላቸው የዘወትር አቅኚዎች የሆኑ በዕድሜ የጎለመሱ ሰዎችም እንዲሁ አድርገዋል። ራሱን የወሰነ አንድ ክርስቲያን በዚህ መንገድ ይሖዋ እያፋጠነው ባለው የመሰብሰቡ ሥራ ሲካፈል እንዴት ያለ እርካታ ያገኛል!— ኢሳ. 60:22
■ የስብሰባ ቦታዎችን በመገንባቱና በማደሱ ሥራ መካፈል፦ በጣም ብዙ የሆኑ ዘመናዊ የመንግሥት አዳራሾችና አያሌ የትልልቅ ስብሰባ አዳራሾች ተሠርተዋል። የሚያስገርመው ይህ ሁሉ ሥራ የተከናወነው ጊዜያቸውንና ችሎታቸውን በፈቃደኝነት ባበረከቱ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን አማካኝነት ነው። (1 ዜና 28:21) በሺህ የሚቆጠሩ ፈቃደኛ ሠራተኞች የሚጠበቅባቸውን ማንኛውንም ሥራ በማከናወን እነዚህን የስብሰባ አዳራሾች እድሳት ያደርጉላቸዋል። (2 ዜና 34:8) ይህ ሥራ የቅዱስ አገልግሎት አንዱ ክፍል ስለሆነ ራሳቸውን በፈቃደኝነት በማቅረብ እርዳታ የሚያበረክቱ ወንድሞች ከቤት ወደ ቤት እየሄዱ ሲሰብኩ፣ በጉባኤ የሕዝብ ንግግር ሲሰጡ አለበለዚያም በትልልቅ ስብሰባዎች ላይ ሲሠሩ ገንዘብ እንዲከፈላቸው እንደማይጠይቁ ሁሉ በዚህ ረገድ ለሚያበረክቱት አገልግሎትም ክፍያ አይጠይቁም። እነዚህ ፈቃደኛ ሠራተኞች ለይሖዋ ውዳሴ የሚያመጡ የአምልኮ ቦታዎችን ፕላን በማውጣትም ሆነ በመገንባት ነፃ አገልግሎት ያበረክታሉ። ሕጋዊ ሰነዶችን በማስፈጸም፣ የሒሳብ መዝገቦችን በመያዝ፣ የዕቃ ግዢ በማከናወን፣ የሚያስፈልጉትን ቁሳቁሶች መጠን በማስላትና በመሳሰሉት ነገሮች በቅንዓት እገዛ ያደርጋሉ። እነዚህ ታማኝ የይሖዋ አገልጋዮች ያላቸው ችሎታና ጥሪት በሙሉ ለይሖዋ የተወሰነ ስለሆነ ለሥራ ወጪ ካደረጉት ገንዘብ በላይ አይጠይቁም ወይም በማንኛውም መንገድ ከሚያበረክቱት አገልግሎት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ቁሳዊ ትርፍ ለማግኘት አይፈልጉም። (የየካቲት 1992 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 4 አንቀጽ 10 ተመልከት።) ይህ ሥራ ‘ለይሖዋ እንደሚሠሩት እያሰቡ በሙሉ ነፍሳቸው’ አገልግሎታቸውን የሚያከናውኑ ታታሪ ሠራተኞችን ይጠይቃል።— ቆላ. 3:23 አዓት
15 የይሖዋ ሕዝቦችን የፈቃደኝነት መንፈስ ልዩ የሚያደርገው ምንድን ነው? የመስጠት መንፈስ ያላቸው መሆኑ ነው። በልግስና የሚሰጡት ገንዘብ ወይም ቁሳዊ ነገሮችን ብቻ ሳይሆን “በፈቃዳቸው ራሳቸውን ያቀርባሉ።” (መዝ. 110:3 አዓት) ራሳችንን ለይሖዋ የመወሰናችን ትርጉምም ይኸው ነው። ልዩ በሆነ መንገድ ተክሰናል። የምናደርገው ነገር መልሰው በሚሰጡን ሌሎች ሰዎች ስለሚደነቅ ‘የላቀ ደስታ’ ከማግኘታችንም በላይ ‘በበረከት እናጭዳለን።’ (ሥራ 20:35፤ 2 ቆሮ. 9:6፤ ሉቃስ 6:38) ከሁሉ በላይ የሚሰጠን ‘በደስታ የሚሰጡትን የሚወደው’ ሰማያዊ አባታችን ይሖዋ ነው። (2 ቆሮ. 9:7) ዘላለማዊ በረከቶችን በመስጠት መቶ እጥፍ ይከፍለናል። (ሚል. 3:10፤ ሮሜ 6:23) ስለዚህ በይሖዋ አገልግሎት የተለያዩ መብቶች ሲቀርቡልህ ራስህን በፈቃደኝነት በማቅረብ ልክ እንደ ኢሳይያስ “እነሆኝ፣ እኔን ላከኝ” በማለት መልስ ትሰጣለህን?— ኢሳ. 6:8