ማአቅኚዎች እንዲያሟሉ በሚጠበቅባቸው ሰዓት ላይ የተደረገ ማሻሻያ
1 ሁላችንም በጉባኤያችን ውስጥ ተግተው የሚሠሩ የዘወትርና ረዳት አቅኚዎች በመኖራቸው ደስ ይለናል። አነስተኛና በተደጋጋሚ ተጣርቶ የተሸፈነ የአገልግሎት ክልል ባለባቸው ቦታዎችም እንኳ አቅኚዎች ቅንዓት በተሞላበት የመንግሥቱ አገልግሎታቸው ጥሩ ምሳሌ ይሆናሉ። ‘ለዘላለም ሕይወት የተዘጋጁትን’ ሰዎች በመፈለጉ ሥራ እንዲቀጥሉ ለሁሉም አስፋፊዎች ማበረታቻ ሆነዋል።—ሥራ 13:48
2 ማኅበሩ አቅኚዎች የሚገጥሟቸውን ከፍተኛ ችግሮች፣ በተለይ ደግሞ በሙሉ ጊዜ አገልግሎታቸው መቀጠል እንዲችሉ በግል የሚያስፈልጓቸውን ነገሮች በበቂ መጠን ማሟላት የሚያስችላቸውን የትርፍ ሰዓት ሥራ በማግኘት ረገድ የሚገጥማቸውን ችግር ተገንዝቧል። በአሁኑ ጊዜ በብዙ አገሮች ውስጥ ያለው የኢኮኖሚ ሁኔታም አንዳንዶች አቅኚ የመሆን ልባዊ ፍላጎት ቢኖራቸውም እንኳ የአቅኚነት አገልግሎት እንዳይጀምሩ ይበልጥ አዳጋች አድርጎባቸዋል። ከቅርብ ወራት ወዲህ እነዚህም ሆኑ ሌሎች ነገሮች በጥንቃቄ ተገምግመዋል።
3 ስለዚህ ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ግምት ውስጥ በማስገባት ማኅበሩ የዘወትርም ሆነ የረዳት አቅኚዎች እንዲያሟሉ የሚጠበቅባቸውን የሰዓት ግብ ቀንሷል። ከጥር 1999 ጀምሮ የዘወትር አቅኚዎች በየወሩ እንዲመልሱ የሚጠበቅባቸው ሰዓት 70 ሲሆን በዓመት ውስጥ በድምሩ የሚጠበቅባቸው ሰዓት 840 ይሆናል። ረዳት አቅኚዎች ደግሞ በወር ውስጥ እንዲመልሱ የሚጠበቅባቸው 50 ሰዓት ይሆናል። ማኅበሩ የሚያስፈልጓቸውን መሠረታዊ የሆኑ ቁሳዊ ነገሮች ለማሟላት የሚያስችላቸውን ዝግጅት ስለሚያደርግ ልዩ አቅኚዎችና ሚስዮናውያን እንዲያሟሉ የሚጠበቅባቸው ሰዓት እንዳለ ይቀጥላል። ይህም በስብከቱና ደቀ መዛሙርት በማድረጉ ሥራ ይበልጥ በተሟላ ትኩረት እንዲሳተፉ የሚያስችላቸው ነው።
4 ይህ የሰዓት ግብ ማሻሻያ ብዙ አቅኚዎች ይህን ውድ የአገልግሎት መብት የሙጥኝ ብለው እንዲቀጥሉ እንደሚረዳ ተስፋ እናደርጋለን። እንዲሁም ብዙ ተጨማሪ አስፋፊዎች ወደ ዘወትርና ረዳት አቅኚነት እንዲገቡ መንገድ የሚከፍት ይሆናል። ይህ ማሻሻያ በጉባኤ ውስጥ ላለ ለእያንዳንዱ ሰው ምንኛ በረከት የሚያስገኝ ይሆናል!