የመጽሐፍ ቅዱስ መጽሐፍ ቁጥር 2—ዘጸአት
ጸሐፊው፦ ሙሴ
የተጻፈበት ቦታ፦ ምድረ በዳ
ተጽፎ ያለቀው፦ 1512 ከዘአበ
የሸፈነው ጊዜ:-1657-1512 ከዘአበ
ይሖዋ በስሙ የተጠሩትን ሕዝቦቹን ከግብጽ መከራ ነፃ ለማውጣት ስላከናወናቸው ታላላቅ ድንቆችና ተአምራት፣ እስራኤላውያንን እንደ ልዩ ርስቱ አድርጎ በመውሰድ ‘የካህናት መንግሥትና የተቀደሰ ሕዝብ’ እንዲሆኑ ስለማደራጀቱና የቲኦክራሲያዊው ብሔር የእስራኤል አጀማመር የሚናገረው ስሜት ቀስቃሽ ዘገባ የመጽሐፍ ቅዱሱ የዘጸአት መጽሐፍ ጎላ ያሉ ሐሳቦች ናቸው። (ዘጸ. 19:6) በዕብራይስጥ ዌኤልሌህ ሼሞዝ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ትርጉሙም “ስሞቹም እነዚህ ናቸው” ማለት ነው። ወይም ባጭሩ ሼሞዝ ማለትም “ስሞች” የሚል ትርጉም አለው። እነዚህ የመጽሐፉ የመጀመሪያ ቃላት ናቸው። ወደ ላቲን ተቀይሮ ኤክሰደስ (ዘጸአት) የተባለውን ዘመናዊ ስም ያገኘው ኤክሶዶስ ተብሎ ከተጠራበት ከግሪኩ ሴፕቱጀንት ሲሆን “መውጣት” ወይም “ከአንድ ቦታ ለቅቆ መሄድ” የሚል ትርጉም አለው። የዘጸአት መጽሐፍ ከዘፍጥረት ዘገባ የቀጠለ መሆኑን የሚያሳየው [እንደ አዲሲቱ ዓለም ትርጉም] “ም” የሚል ተቀጥያ ባለው ቃል [ወይም በእግሊዝኛ “ናው”፤ ቃል በቃል “እና” ማለት ሊሆን ይችላል] ተጠቅሞ የያዕቆብን ልጆች ስም በመዘርዘር መጀመሩ ነው። ይህም በዘፍጥረት 46:8-27 ላይ ተመዝግቦ ከሚገኘው ሰፊ ዝርዝር የተወሰደ ነው።
2 የዘጸአት መጽሐፍ ይሖዋ የተባለውን ዕጹብ ድንቅ የአምላክ ስም አንጸባራቂ ከሆነው ክብሩና ቅድስናው ጋር ይገልጻል። አምላክ ስሙ ያለውን ጥልቅ ትርጉም ሲያሳይ ሙሴን “መሆን የሚገባኝን እሆናለሁ” ብሎት የነበረ ሲሆን አክሎም “እሆናለሁ” [በዕብራይስጥ:- אהיה፣ ኤዬህ፣ ሃያህ ከተባለው የዕብራይስጥ ግሥ የተገኘ] ወደ እናንተ ላከኝ” ብሎ ለእስራኤላውያን እንዲናገር አዝዞት ነበር። ይሖዋ (יהוה፣ የሐወሐ) የሚለው ስም ተመሳሳይ ሐሳብ ከሚያስተላልፈው ሃዋህ፣ “መሆን” ከሚለው ቃል የተገኘ ሲሆን “እንዲሆን ያደርጋል” የሚል ትርጉም አለው። በእርግጥም ይሖዋ ለሕዝቡ ለእስራኤል ሲል ያደረገው ታላቅና አስፈሪ ነገር ስሙን ከፍ ከፍ በማድረግና አንጸባራቂ የሆነ ክብር በማላበስ “እስከ ልጅ ልጅ” ድረስ መታሰቢያ ሆኖ ለዘላለም ዓለም አክብሮታዊ ፍርሃት እንዲለገሰው አድርጓል። በዚህ ስም ዙሪያ ያለውን ድንቅ ታሪክ ማወቃችንና “እኔ ይሖዋ ነኝ” ብሎ የተናገረውንና እሱ ብቻ እውነተኛ አምላክ የሆነውን ይሖዋን ማምለካችን ከምንም ነገር በላይ እጅግ ጠቃሚ ነው።a—ዘጸ. 3:14, 15 NW፤ 6:6 NW
3 የዘጸአት መጽሐፍ የአምስቱ የኦሪት መጻሕፍት ሁለተኛ ጥራዝ በመሆኑ የመጽሐፉ ጸሐፊ ሙሴ ነው። መጽሐፉ ራሱ ሙሴ በይሖዋ ቀጥተኛ ትእዛዝ የጻፈባቸውን ሦስት ጊዜያት ይጠቅሳል። (17:14፤ 24:4፤ 34:27) ዌስትኮትና ሆርት የተባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ምሁራን እንደገለጹት ከሆነ ኢየሱስና የክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች ጸሐፊዎች ከ100 ጊዜ በላይ ከዘጸአት መጽሐፍ በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ የጠቀሱ ሲሆን ኢየሱስ “ሙሴ ሕግን አልሰጣችሁምን?” ብሎ የተናገረውን በምሳሌነት መጥቀስ ይቻላል። ዘጸአት የተጻፈው በሲና ምድረ በዳ በ1512 ከዘአበ፣ የእስራኤል ልጆች ግብጽን ለቅቀው በወጡ በዓመቱ ነበር። ዮሴፍ ከሞተበት ከ1657 ከዘአበ አንስቶ ለይሖዋ አምልኮ የሚያገለግለው የመገናኛ ድንኳን እስከ ተሠራበት ዓመት እስከ 1512 ከዘአበ ድረስ ያለውን የ145 ዓመታት ጊዜ ይሸፍናል።—ዮሐ. 7:19፤ ዘጸ. 1:6፤ 40:17
4 የዘጸአት መጽሐፍ የሚናገርላቸው ነገሮች የተከናወኑት ከዛሬ 3,500 ዓመታት በፊት ከመሆኑ አንጻር ሲታይ ለዘገባው ትክክለኛነት የሚመሰክሩ አርኪኦሎጂያዊና ሌሎች ውጫዊ ማስረጃዎች በብዛት የሚገኙ መሆናቸው አስገራሚ ነው። በዘጸአት መጽሐፍ ውስጥ ግብጻዊ ስሞች በትክክል የተጻፉ ሲሆን በመጽሐፉ ውስጥ ተጠቅሰው የሚገኙ ማዕረጎችም ተቀርጸው ከተገኙ የግብጻውያን ጽሑፎች ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ግብጻውያን የባዕድ አገር ሰዎች በግብጽ ውስጥ እንዲኖሩ የመፍቀድ ልማድ ቢኖራቸውም ከእነሱ ተለይተው እንዲኖሩ ያደርጉ እንደነበር አርኪኦሎጂ ያሳያል። የአባይ ውኃ ገላን ለመታጠብ ያገለግል የነበረ መሆኑ የፈርዖን ልጅ በዚያ ስለ መታጠቧ የሚናገረውን ታሪክ ያስታውሰናል። በገለባና ያለ ገለባ የተሠሩ ጡቦች ተገኝተዋል። በተጨማሪም ግብጽ ኃያል በነበረችባቸው ጊዜያት አስማተኞች በብዛት ይገኙ ነበር።—ዘጸ. 8:22፤ 2:5፤ 5:6, 7, 18፤ 7:11
5 ፈርዖኖች ሠረገለኞቻቸውን ራሳቸው እየመሩ ወደ ውጊያ ይሄዱ እንደነበር ታሪካዊ ማስረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን ዘጸአትም በሙሴ ዘመን የነበረው ፈርዖን ይህንኑ ልማድ መከተሉን ይጠቁማል። የደረሰበት ውርደት ምን ያህል ታላቅ ነበር! ሆኖም የጥንት ግብጻውያን መዛግብት እስራኤላውያን በአገራቸው ስለ መቀመጣቸው ወይም በግብጽ ላይ ስለወረደው መቅሠፍት ምንም ያልጠቀሱት ለምንድን ነው? አንድ አዲስ ግብጻዊ ሥርወ መንግሥት ሲነሳ ከቀድሞ መዛግብት ውስጥ የሚገኘውን ጥሩ መስሎ ያልታየውን ማንኛውም ነገር ይደመስስ እንደነበር የአርኪኦሎጂ ጥናት ያሳያል። አሳፋሪ ሽንፈቶቻቸውን በፍጹም አይመዘግቡም ነበር። የአባይ አምላክን፣ የእንቁራሪት አምላክንና የፀሐይ አምላክን በመሳሰሉ የግብጽ አማልክት ላይ የደረሱ ታላላቅ ሽንፈቶች እነዚህን የሐሰት አማልክት ያዋረዱና የይሖዋን ታላቅነት ያሳዩ በመሆናቸው በአንድ ኩሩ ብሔር ዜና ታሪክ ውስጥ ቦታ ሊኖራቸው አይችልም።—14:7-10፤ 15:4b
6 ሙሴ የዮቶር እረኛ ሆኖ ለ40 ዓመት ሲያገለግል ከአካባቢው የኑሮ ሁኔታ እንዲሁም ውኃና ምግብ ከሚገኝባቸው ቦታዎች ጋር በደንብ ለመተዋወቅ የቻለ ሲሆን ይህ ደግሞ ከግብጽ የወጣውን ሕዝብ የመምራት ብቃት እንዲኖረው አስችሎታል። በዘገባው ላይ የተገለጹት ቦታዎች በዛሬው ጊዜ የት አካባቢ እንደሚገኙ በትክክል ለማወቅ ስለማይቻል ሕዝቡ የተጓዘበትን መንገድ በእርግጠኝነት ለመናገር አይቻልም። ይሁን እንጂ ቀደም ሲል በሲና ባሕረ ገብ መሬት ላይ ከሰፈሩባቸው የመጀመሪያ ቦታዎች መካከል አንዱ የሆነው ማራ ከዛሬው ስዊዝ ደቡባዊ ምሥራቅ 80 ኪሎ ሜትር ላይ የሚገኘው ‘አይን ሃዋራ’ በመባል የሚታወቀው ቦታ እንደሆነ በሰፊው ይነገራል። ኤሊም የሚባለው ሁለተኛው የሰፈራ ቦታ ዋዲ ጋራንዴል ነው እየተባለ በተለምዶ የሚነገር ሲሆን ከስዊዝ ደቡባዊ ምሥራቅ 88 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል። የሚያስገርመው ዛሬ ይህ ስፍራ ለመጠጥ የሚሆን ውኃ፣ አትክልትና ዘንባባዎች የሚገኙበት ቦታ በመሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ይህም “አሥራ ሁለት የውኃ ምንጮችና ሰባ የዘንባባ ዛፎች” የነበሩባትን የመጽሐፍ ቅዱሷን ኤሊም ያስታውሰናል።c ይሁን እንጂ የሙሴ ዘገባ ትክክለኛነት አርኪኦሎጂስቶች በመንገዱ ላይ ስለነበሩት የተለያዩ ቦታዎች በሚሰጡት ማረጋገጫ ላይ የተመካ አይደለም።—15:23, 27
7 የማደሪያው ድንኳን ከሲና በፊት በነበረው ሜዳ ላይ ስለ መሠራቱ የሚናገረው ታሪክ በአካባቢው ከነበረው ሁኔታ ጋር የሚስማማ ነው። አንድ ምሁር እንዲህ ብለዋል:- “ቅርጹ፣ ይዘቱና ቁሳቁሶቹ የማደሪያው ድንኳን በአጠቃላይ በምድረ በዳ የተሠራ መሆኑን የሚያሳዩ ናቸው። የተሠራበት እንጨት በዚያ ቦታ በብዛት የሚገኝ ነበር።”d በስሞች፣ በልማዶች፣ በሃይማኖት፣ በስፍራዎች፣ በመልከዓ ምድር ሆነ በቁሳቁሶች መስክ የተሰባሰበው ውጫዊ ማስረጃ በአሁኑ ጊዜ ወደ 3,500 ዓመታት የተጠጋው በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፈውን የዘጸአት ዘገባ ትክክለኛነት ያረጋግጣል።
8 ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ከዘጸአት መጽሐፍ በተደጋጋሚ መጥቀሳቸው መጽሐፉ ያለውን ትንቢታዊ ጠቀሜታና ዋጋማነት ያሳያል። ከ900 ከሚበልጡ ዓመታት በኋላ ኤርምያስ ‘ስሙ ታላቅና ኃያል አምላክ የሠራዊት ጌታ ይሖዋ’ “በምልክትና በድንቅ ነገር፣ በብርቱ እጅና በተዘረጋች ክንድ በታላቅም ግርማ” ሕዝቡን እስራኤልን ከግብጽ ምድር እንዳወጣ ጽፏል። (ኤር. 32:18-21) ከ1,500 ዓመታት በኋላ እስጢፋኖስ የሰማዕትነት ሞት ከመሞቱ በፊት የሰጠው ምሥክርነት መሠረት ያደረገው በአብዛኛው በዘጸአት ላይ የሚገኘውን መረጃ ነበር። (ሥራ 7:17-44) በዕብራውያን 11:23-29 ላይ የሙሴ ሕይወት የእምነት ምሳሌ ሆኖ ተጠቅሶልናል፤ እንዲሁም ጳውሎስ በዛሬው ጊዜ ለምንገኘው የሚሆኑ ምሳሌዎችንና ማስጠንቀቂያዎችን በመዘርዘር ከዘጸአት መጽሐፍ በተደጋጋሚ ጠቅሷል። (ሥራ 13:17፤ 1 ቆሮ. 10:1-14, 11, 12፤ 2 ቆሮ. 3:7-16) ይህ ሁሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች እርስ በርሳቸው እንዴት እንደሚዛመዱ እንድንገነዘብ የሚረዳን ሲሆን እያንዳንዱ ክፍል የይሖዋን ዓላማ ጠቃሚ በሆነ መንገድ በማሳወቅ ረገድ የራሱ ድርሻ አለው።
ጠቃሚ የሆነው ለምንድን ነው?
26 የዘጸአት መጽሐፍ ይሖዋ ታላቅ ነፃ አውጪና አደራጅ እንዲሁም አስደናቂ ዓላማዎቹን የሚያስፈጽም መሆኑን አበክሮ የሚገልጽ ሲሆን በእሱ ላይ እምነት እንድናሳድር ያደርጋል። የሕጉ ቃል ኪዳን በርካታ ገጽታዎች ፍጻሜያቸውን ስለማግኘታቸው፣ ትንሣኤ እንደሚኖር ስለተሰጠው ዋስትና፣ ይሖዋ ሕዝቡን ለመደገፍ ስለሚያደርገው ዝግጅት፣ ለክርስቲያናዊ የእርዳታ ተግባራት መቅድም ስለሆኑ ምሳሌዎች፣ ለወላጆች ሊኖር የሚገባውን አመለካከት በተመለከተ የተሰጠውን ምክር፣ ሕይወት ለማግኘት ሊሟሉ ስለሚገባቸው መስፈርቶችና የማካካሻ ቅጣት እንዴት መመልከት እንደሚገባ የሚገልጹትን ከዘጸአት ተወስደው በክርስቲያን ግሪክኛ ቅዱሳን ጽሑፎች የተጠቀሱትን ሐሳቦች ስንመረምር እምነታችን ያድጋል። በመጨረሻም ሕጉ ለአምላክና ለሰዎች ፍቅር ማሳየት በሚሉ ሁለት ትእዛዞች ተጠቃልሏል።—ማቴ. 22:32—ዘጸ. 4:5፤ ዮሐ. 6:31-35ና 2 ቆሮ. 8:15—ዘጸ. 16:4, 18፤ ማቴ. 15:4ና ኤፌ. 6:2—ዘጸ. 20:12፤ ማቴ. 5:26, 38, 39—ዘጸ. 21:24፤ ማቴ. 22:37-40
27 በዕብራውያን 11:23-29 ላይ ሙሴና ወላጆቹ ስለነበራቸው እምነት እናነባለን። ግብጽን ለቅቆ የወጣው በእምነት ነበር፤ የማለፍን በዓል ያከበረው በእምነት ነበር፤ እስራኤልን እየመራ ቀይ ባህርን ያሻገራቸው በእምነት ነበር። እስራኤላውያን ወደ ሙሴ ተጠምቀው መንፈሳዊ መብል በልተዋል፤ እንዲሁም መንፈሳዊ መጠጥ ጠጥተዋል። መንፈሳዊውን ዓለት ወይም ክርስቶስን ይጠባበቁ የነበረ ቢሆንም ጣዖት አምላኪዎች፣ ሴሰኞችና አጉረምራሚዎች በመሆን አምላክን በመፈታተናቸው በአምላክ ዘንድ ተቀባይነት አላገኙም። ጳውሎስ ይህ ነገር በዛሬው ጊዜ በሚገኙ ክርስቲያኖች ላይ እንደሚሠራ አመልክቷል:- “ይህም ሁሉ እንደ ምሳሌ ሆነባቸው፣ እኛንም የዘመናት መጨረሻ የደረሰብንን ሊገሥጸን ተጻፈ። ስለዚህ እንደ ቆመ የሚመስለው እንዳይወድቅ ይጠንቀቅ።”—1 ቆሮ. 10:1-12፤ ዕብራውያን 3:7-13
28 አብዛኛው የዘጸአት መጽሐፍ ያዘለው ጥልቅ መንፈሳዊ ቁም ነገር ከትንቢታዊ ተግባራዊነቱ ጋር በጳውሎስ ደብዳቤዎች ውስጥ በተለይም በዕብራውያን ምዕራፍ 9ና 10 ላይ ተገልጿል። “ሕጉ ሊመጣ ያለው የበጎ ነገር እውነተኛ አምሳል ሳይሆን የነገር ጥላ አለውና፣ ስለዚህም በየዓመቱ ዘወትር በሚያቀርቡት በዚያ መሥዋዕት የሚቀርቡትን ሊፈጽም ከቶ አይችልም።” (ዕብ. 10:1) ከዚህ የተነሣ ይህን ጥላ በማወቅ እውነታውን ለመረዳት እንፈልጋለን። ክርስቶስ “አንድን መሥዋዕት ለዘላለም [አቅርቧል]።” “የእግዚአብሔር በግ” ተብሎም ተገልጿል። በትንቢታዊው ጥላ መሠረት የዚህ “በግ” አንድም አጥንት አልተሰበረም። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ብሏል:- “ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና፤ ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም።”—ዕብ. 10:12፤ ዮሐ. 1:29ና 19:36—ዘጸ. 12:46፤ 1 ቆሮ. 5:7, 8—ዘጸ. 23:15
29 ሙሴ የሕጉ ቃል ኪዳን መካከለኛ እንደነበረ ሁሉ ኢየሱስ ደግሞ የአዲሱ ቃል ኪዳን መካከለኛ ሆኗል። ሐዋርያው ጳውሎስ በእነዚህ ሁለት ቃል ኪዳን መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ ያብራራ ሲሆን ‘በትእዛዛት የተጻፈው የዕዳ ጽሕፈት’ ኢየሱስ በመከራው እንጨት ላይ ሲሞት ከመንገድ እንደተወገደ ተናግሯል። ከሞት የተነሣው ሊቀ ካህናቱ ኢየሱስ “የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፣ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት።” በሕጉ ሥር የነበሩት ካህናት ለሙሴ በተገለጠለት መሠረት ‘ለሰማያዊ ነገር ምሳሌና ጥላ በሆነው ስፍራ ቅዱስ አገልግሎት ያቀርባሉ።’ “አሁን ግን [ኢየሱስ] በሚሻል ተስፋ ቃል በተመሠረተ በሚሻል ኪዳን ደግሞ መካከለኛ እንደሚሆን፣ በዚያ ልክ እጅግ የሚሻል አገልግሎት አግኝቶአል።” አሮጌው ቃል ኪዳን ጊዜ ያለፈበትና ለሞት የሚዳርግ ፊደል በመሆኑ ተወግዷል። ይህን ያልተረዱ አይሁዶች ማስተዋላቸው እንደ ደነዘዘ ሆነው የተገለጹ ሲሆን መንፈሳዊ እስራኤል በአዲስ ቃል ኪዳን ሥር መሆናቸውን የሚያደንቁ አማኞች ግን ብቃት ያላቸው የአምላክ አገልጋዮች በመሆን “በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን [“የይሖዋን፣” NW] ክብር እንደ መስተዋት [ያንጸባርቃሉ]።” እነዚህ ሰዎች ንጹህ ሕሊና ያላቸው በመሆኑ “የምስጋናን መሥዋዕት፣ ማለት ለስሙ የሚመሰክሩ የከንፈሮችን ፍሬ” ለማቅረብ ችለዋል።—ቆላ. 2:14፤ ዕብ. 8:1-6, 13፤ 2 ቆሮ. 3:6-18፤ ዕብ. 13:15፤ ዘጸ. 34:27-35
30 የዘጸአት መጽሐፍ የመንፈሳዊ እስራኤል ክርስቲያናዊ ብሔር ክብራማ ነፃነቱን የሚጎናጸፍበትን ጊዜ በማመልከት የይሖዋን ስምና ሉዓላዊነቱን ከፍ ከፍ የሚያደርግ ሲሆን ስለዚሁ ብሔር እንዲህ ብሏል:- “ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትነግሩ የተመረጠ ትውልድ፣ የንጉሥ ካህናት፣ ቅዱስ ሕዝብ፣ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤ እናንተ ቀድሞ ወገን አልነበራችሁም አሁን ግን የእግዚአብሔር ወገን ናችሁ።” ይሖዋ ስሙን ለማስከበር ሲል መንፈሳዊ እስራኤል የሚሆኑትን ከዓለም በመሰብሰብ ያሳየው ኃይል ከጥንቷ ግብጽ ሕዝቡን ለማውጣት ካሳየው ተአምራዊ ኃይል ምንም አይተናነስም። ይሖዋ ፈርዖንን በሕይወት አቆይቶ ኃይሉ እንዲገለጥበትና ስሙ እንዲታወቅ በማድረግ ወደፊት በክርስቲያን ምሥክሮቹ አማካኝነት የሚከናወን እጅግ ታላቅ የምሥክርነት ሥራ እንደሚኖር አመልክቷል።—1 ጴጥ. 2:9, 10፤ ሮሜ 9:17፤ ራእይ 12:17
31 በመሆኑም ቅዱሳን ጽሑፎች የሚሉትን መሠረት በማድረግ በሙሴ አመራር ሥር የተቋቋመው ብሔር በክርስቶስ አመራር ሥር ለሚቋቋመው አዲስ ብሔርና ፈጽሞ ለማይናወጥ መንግሥት ጥላ ነበር ለማለት እንችላለን። ከዚህ የተነሣ ‘በአክብሮትና በፍርሃት አምላክን እንድናገለግል’ ማበረታቻ ተሰጥቶናል። የይሖዋ መገኘት በምድረ በዳ የነበረውን የማደሪያ ድንኳን እንደሸፈነው ሁሉ አሁንም እሱን ከሚፈሩት ጋር ለዘላለም አብሯቸው እንደሚሆን ተስፋ ሰጥቷል:- “እነሆ፣ የእግዚአብሔር ድንኳን በሰዎች መካከል ነው ከእነርሱም ጋር ያድራል፣ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ እግዚአብሔርም እርሱ ራሱ ከእነርሱ ጋር ሆኖ አምላካቸው ይሆናል። . . . እነዚህ ቃሎች የታመኑና እውነተኛዎች ናቸውና ጻፍ።” በእርግጥም የዘጸአት መጽሐፍ በጣም አስፈላጊና ጠቃሚ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል ነው።—ዘጸ. 19:16-19—ዕብ. 12:18-29፤ ዘጸ. 40:34—ራእይ 21:3, 5
[የግርጌ ማስታወሻዎች]
a ዘጸአት 3:14 የግርጌ ማስታወሻ፤ ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 2 ገጽ 12
b ቅዱሳን ጽሑፎችን ጠለቅ ብሎ ማስተዋል (እንግሊዝኛ) ጥራዝ 1 ገጽ 532, 535፤ አርኪኦሎጂ ኤንድ ባይብል ሂስትሪ 1964 ጄ ፒ ፍሪ ገጽ 98
d ኤክሰደስ 1874፣ ኤፍ ሲ ኩክ ገጽ 247