ክርስቲያናዊ ወዳጅነት ምን ያህል አስፈላጊ ነው?
1 “ለሰው መድኃኒቱ ሰው ነው።” ይህ አባባል የሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎት የሆነውን ወዳጅነት አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ የተናገረውን ሐሳብ የሚያስተጋባ ነው። (ምሳሌ 18:1) ክርስቲያናዊ ወዳጅነት ይህን ፍላጎታችንን ያሟላልናል። በየትኞቹ ጠቃሚ ዘርፎች?
2 በአገልግሎት:- ከምናገኛቸው ጥቅሞች መካከል የላቀ ግምት የሚሰጠው ወንድሞቻችን በሕዝባዊ አገልግሎት እኛን የሚያበረቱበትና የሚደግፉበት መንገድ ነው። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን እንዲሰብኩ የላካቸው “ሁለት ሁለት” አድርጎ ነው። (ማር. 6:7፤ ሉቃስ 10:1) ይህን ሥርዓት ተከትለን ከሌሎች ጋር በመስክ አገልግሎት ስንሰማራ መክብብ 4:9, 10ን እውነት ሆኖ እናገኘዋለን። አገልግሎታችንን አንድ ላይ በምናከናውንበት ጊዜ አብረውን የሚያገለግሉት ጓደኞቻችን ያላቸው እምነት፣ ታዛዥነትና ፍቅር ድፍረት ይጨምርልናል እንዲሁም ቅንዓታችንን ያቀጣጥልልናል።
3 በግል በምናገኘው እርዳታ:- ክርስቲያናዊ ወንድማማችነታችን ተጽእኖዎችን ለመቋቋምና ተፈታታኝ ችግሮችን ለማሸነፍ የሚያስችል መመሪያ የምናገኝበት ምንጭ ይሆንልናል። ክርስቲያን ወዳጆቻችን በግል የሚያሳስቡንን ችግሮች የሚመለከቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች እንድናስታውስ ይረዱን ይሆናል። እኛ ስለ እነርሱ እንደምንጸልየው ሁሉ እነርሱም ስለ እኛ ሊጸልዩ ይችላሉ። (2 ቆሮ. 1:11) ደግሞም ጥሩ ምሳሌነታቸው ለትክክለኛ ሥራ ያነሳሳናል እንዲሁም ያበረታናል።
4 በስብሰባዎች ላይ:- ክርስቲያናዊ ወዳጅነት የሚያስገኘውን በረከት መቅመስ የምንችለው በጉባኤ ስብሰባዎች ላይ አዘውትረን ስንገኝ ነው። (ዕብ. 10:24, 25) ፕሮግራሙ መንፈሳዊ ትምህርት የተትረፈረፈበት ሲሆን በስብሰባዎቹ ላይ መገኘታችን ከእምነት አጋሮቻችን ጋር ያቀራርበናል። በእነዚህ ስብሰባዎች ላይ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ከመድረክ በሚያቀርቡት ንግግርም ሆነ እንደ አድማጭ በሚያደርጉት ተሳትፎ እምነታቸውን በአንደበታቸው ሲገልጹ የመስማት አጋጣሚ እናገኛለን። (ሮሜ 1:12) ከስብሰባ በፊትና በኋላ ቀርበን ስንጨዋወት ወዳጅነታችን ይጠናከራል። እንዲህ ያለው አጋጣሚ እምነት የሚገነቡ ተሞክሮዎቻችንን ለማካፈል በር ይከፍትልናል። ይሖዋን፣ ቃሉን፣ ሥራዎቹንና ሕዝቡን ከሚወዱ ሰዎች ጋር የሚኖረን እንዲህ ዓይነቱ ግንኙነት ባሕርያችንን በበጎ መልኩ ይቀርጸዋል።—ፊልጵ. 2:1, 2
5 ክርስቲያን ወዳጆቻችን ያስፈልጉናል። ያለ እነርሱ ወደ ዘላለም ሕይወት በሚመራው ጠባብ ጎዳና ላይ የምናደርገው ጉዞ ይበልጥ አስቸጋሪ ይሆናል። ይሁን እንጂ በሚያሳዩን ፍቅርና በሚሰጡን ማበረታቻ አማካኝነት ይሖዋ ወዳዘጋጀው ጽድቅ የሰፈነበት አዲስ ዓለም የምናደርገውን ጉዞ መቀጠል እንችላለን።—ማቴ. 7:14