ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ መመሥከር
1. በዛሬው ጊዜ ያሉ ክርስቲያኖች የመጀመሪያው መቶ ዘመን ክርስቲያኖችን ምሳሌ በመኮረጅ ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ለመመሥከር ምን ጥረት እያደረጉ ነው? ምንስ ውጤት አግኝተዋል?
1 እንደ ጥንቶቹ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ሁሉ በዛሬው ጊዜ የሚኖሩ ክርስቲያኖችም በየትኛውም ሥፍራ ለሚያገኟቸው ሰዎች ምሥራቹን ለመንገር ጥረት ያደርጋሉ። (ሥራ 16:13፤ 17:17፤ 20:20, 21) ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ለመመሥከር በሚያደርጉት ጥረት ከቤት ወደ ቤት በሚደረገው አገልግሎት ሊገኙ የማይችሉ ፍላጎት ያላቸው ሰዎችን እያገኙ ነው።
2. ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ስንመሠክር አስተዋዮች መሆን ያለብን ለምንድን ነው? የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት ለሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ ማበርከት የምንችለውስ እንዴት ነው?
2 ሕዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች ስንመሠክር አስተዋይ መሆን ይገባናል። ብዙውን ጊዜ እንዲህ ባሉ አካባቢዎች ስናገለግል የሌሎችን ትኩረት እንዳንስብ ጥንቃቄ ማድረጋችን ጥሩ ነው። ለምሳሌ ያህል፣ ብዙ አስፋፊዎች በአንድ አካባቢ የሚመሠክሩ ወይም ለአገልግሎት ወደ አንድ የገበያ አዳራሽ የሚሄዱ ከሆነ አንዳንዶች ሊሰላቹብን ይችላሉ። ይህ ደግሞ ሰዎች ለስብከት ሥራችን ሊኖራቸው የሚገባውን አክብሮት ሊቀንስና ውጤታማ እንዳንሆን ሊያደርገን ይችላል። እንዲህ እንዳይሆን ምን ማድረግ እንችላለን? ሕዝብ በብዛት የሚገኝባቸው በርከት ያሉ ክልሎች ያሏቸው አንዳንድ ጉባኤዎች እነዚህን ቦታዎች በክልል መልክ መሸንሸኑን ጠቃሚ ሆኖ አግኝተውታል። (1 ቆሮ. 14:40) በተጨማሪም የጉባኤው የአገልግሎት ኮሚቴ ሌላ ጉባኤን ለመርዳት ብሎ ልዩ ዝግጅት እስካላደረገ ድረስ በክልላችን ውስጥ ብቻ በማገልገል የተቀናጀ ሥራ ለመሥራት ለሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦ ማበርከት እንችላለን።—የኅዳር 1998 የመንግሥት አገልግሎታችን ገጽ 7 አን. 18-19 ተመልከት
3. አንዳንድ አስፋፊዎች ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች በመመሥከር ረገድ ውጤታማ ሆኖ ያገኙት የትኛውን አቀራረብ ነው?
3 አቀራረባችን:- ኢየሱስ በአንድ የውኃ ጉድጓድ አጠገብ ያገኛትን ሴት ሲያነጋግር ጥቂት አስተያየት በመሰንዘር ከጀመረ በኋላ ፍላጎቷ እየጨመረ በሄደ መጠን ውይይታቸውም ይበልጥ ስፋት እንዲኖረው አድርጎ ነበር። (ዮሐ. 4:7-26) ዛሬም ቢሆን እንዲህ ዓይነቱ አቀራረብ በአንዳንድ ሁኔታዎች ሥር ውጤታማ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ አስፋፊዎች ሰዎች በብዛት በሚገኙባቸው ቦታዎች በተሳካ ሁኔታ ለመመሥከር የመንግሥቱን መልእክት ከመናገራቸው በፊት ጥቂት ደቂቃዎች ወስደው ከሰዎቹ ጋር ሰላምታ መለዋወጣቸውና አሳቢነት ማሳየታቸው ጠቃሚ መሆኑን ተገንዝበዋል። በተጨማሪም የአካባቢውን ትኩረት ስለሳበ አንድ ክንውን አስተያየት ጣል ማድረጋቸው ብዙውን ጊዜ ውይይት ለመጀመር መንገድ ይከፍትላቸዋል። ሰዎቹ ሐሳባቸውን ሲናገሩም በጥሞና ያዳምጣሉ። ከዚያም የአምላክ ቃል የሚሰጠውን ማጽናኛ ያካፍላሉ።—ሮሜ 15:4
4. ለመወያየት ፈቃደኛ የሆኑ ሰዎች ስናገኝ ፍላጎታቸውን እንዴት ማሳደግ እንችላለን?
4 ፍላጎታቸውን ማሳደግ:- ከሰዎች ጋር ጥሩ ውይይት በምናደርግበት ጊዜ ሁሉ ፍላጎታቸውን ለማሳደግ የሚያስችለንን ዝግጅት ለማድረግ መጣር አለብን። ይህን እንዴት ማድረግ እንችላለን? በውይይቱ ማብቂያ ላይ ማስታወሻ ደብተርህን በማውጣት “ባደረግነው ውይይት ተደስቻለሁ። ውይይታችንን ለመቀጠል በሌላ ጊዜ መገናኘት እንችላለን?” ማለት ትችላለህ። ወይም ደግሞ “ይጠቅሞታል ብዬ የማስበው አንድ ጽሑፍ አለኝ፤ አምጥቼልዎት ቢያነብቡት ደስ ይለኛል። ቤትዎ ላምጣልዎት ወይስ መሥሪያ ቤትዎ?” ብለህ መጠየቅ ትችላለህ። አንዳንድ አስፋፊዎች “ስልክ ቁጥርዎን ሊሰጡኝ ይችላሉ?” በማለት በቀጥታ ይጠይቃሉ፤ ይህም ብዙውን ጊዜ ጥሩ ምላሽ ያስገኛል።
5. ሕዝብ በሚበዛባቸው ስፍራዎች ስንመሠክር ግባችን ምን መሆን ይገባዋል?
5 ለመጀመሪያ ጊዜ ሕዝብ በሚበዛባቸው ቦታዎች የተመሠከረላቸው በርካታ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ እንዲያጠኑ የቀረበላቸውን ግብዣ ተቀብለዋል። ጥናቱ በግለሰቡ ቤት፣ በሥራ ቦታው፣ አመቺ በሆኑ ሌሎች ቦታዎች ወይም በስልክ ሊመራ ይችላል። ሕዝብ በሚበዛባቸው ስፍራዎች ውጤታማ በሆነ መንገድ ስንመሠክር ግባችን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማስጀመር ይሁን።