ያዘኑትን አጽናኗቸው
1. ሐዘን ላይ የሚገኙ ሰዎች ማጽናኛ የሚያስፈልጋቸው ለምንድን ነው?
1 የሚወዱትን ሰው በሞት ማጣት በተለይ የመንግሥቱን ተስፋ በማያውቁ ሰዎች ላይ ከፍተኛ ሐዘን ያስከትላል። (1 ተሰ. 4:13) ብዙዎች፣ ‘የምንሞተው ለምንድን ነው? ሰዎች ሲሞቱ የሚሄዱት ወዴት ነው? በሞት የተለየኝን ሰው እንደገና አገኘው ይሆን?’ በማለት ይጠይቃሉ። ዘመዳቸውን ወይም ጓደኛቸውን በሞት በማጣታቸው ምክንያት ላዘኑ በአገልግሎት ላይ ለምናገኛቸው ሰዎች ማጽናኛ ለመስጠት የሚረዱ አንዳንድ ሐሳቦች ከዚህ በታች ቀርበዋል።—ኢሳ. 61:2
2. ሐዘን ላይ ያለ ሰው ሲያጋጥመን ብዙውን ጊዜ ምን ብናደርግ የተሻለ ይሆናል?
2 ከቤት ወደ ቤት:- የቤቱ ባለቤት ከቤተሰቡ አባል አንዱ በቅርቡ እንደሞተበት ይነግረን ይሆናል። በግለሰቡ ፊት ላይ ከፍተኛ የሐዘን ስሜት ይነበባል? ሐዘን ላይ የተቀመጡ ዘመድ አዝማድ በቤቱ ውስጥ ይታያሉ? እንዲህ ባሉ ጊዜያት ለመመሥከር ረጅም ሰዓት ባንቆይ የተሻለ ይሆናል። (መክ. 3:1, 7) ምናልባት በሁኔታው ማዘናችንን ከገለጽንለት በኋላ ተስማሚ የሆነ ትራክት፣ መጽሔት አሊያም ብሮሹር በመስጠት ተሰናብተነው ልንሄድ እንችላለን። ከዚያም ከመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጨማሪ ማጽናኛ ለማካፈል ይበልጥ አመቺ በሆነ ጊዜ ላይ ተመልሰን ልንሄድ እንችላለን።
3. ሁኔታው የሚፈቅድልን ከሆነ ሐዘን ላይ ለተቀመጠ ሰው የትኞቹን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ልናሳየው እንችላለን?
3 በሌላ በኩል ግን በመጀመሪያው ቀን ላይ ሰፋ ያለ ውይይት ለማድረግ የሚያስችል አጋጣሚ እንዳለ እናስተውል ይሆናል። ምንም እንኳ ይህ ወቅት የተሳሳተ አመለካከታቸውን የምናርምበት ባይሆንም ትንሣኤን በተመለከተ የሚናገሩ የመጽሐፍ ቅዱስ ተስፋዎች ልናነብላቸው እንችላለን። (ዮሐ. 5:28, 29) ወይም ደግሞ ሙታን ስላሉበት ሁኔታ መጽሐፍ ቅዱስ ምን እንደሚል ልናሳያቸው እንችላለን። (መክ. 9:5, 10) ስለ ትንሣኤ የሚናገር አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባ መንገርም የሚያጽናና ሊሆን ይችላል። (ዮሐ. 11:39-44) ሌላኛው አማራጭ ደግሞ ታማኙ ኢዮብ በይሖዋ ላይ ያለውን እምነት የገለጸባቸውን ቃላት አብረናቸው ማንበብ ነው። (ኢዮብ 14:14, 15) ተሰናብተናቸው ከመሄዳችን በፊት ስንሞት ምን እንሆናለን? እንዲሁም የምትወዱት ሰው ሲሞት የሚሉትን አሊያም ሌላ ተስማሚ ብሮሹር ወይም ትራክት ልንሰጣቸው እንችላለን። ወይም ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የተባለውን መጽሐፍ በመስጠት ምዕራፍ 6 ላይ ያሉትን ሐሳቦች ልናሳያቸው ብሎም በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ መያዝ እንችላለን።
4. ማጽናኛ ለመስጠት የሚያስችሉ ምን ሌሎች አጋጣሚዎች አሉን?
4 ሌሎች አጋጣሚዎች:- የቀብር ንግግር የሚቀርበው ወይም ሟቹን በተመለከተ የሚሰጥ የመታሰቢያ ንግግር የሚደረገው በመንግሥት አዳራሽ ውስጥ ቢሆንና የይሖዋ ምሥክር ያልሆኑ ሰዎች በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሚገኙ ቢሆንስ? ማጽናኛ ሊሰጧቸው የሚችሉ ጽሑፎችን ማግኘት እንዲችሉ ዝግጅት ማድረግ ይቻላል። አንዳንድ ጊዜ በጋዜጣ ላይ የሚወጡ የቀብር ሥነ ሥርዓት ማስታወቂያዎች ሐዘን ለደረሰባቸው የቤተሰቡ አባላት አጠር ያለ አጽናኝ ደብዳቤ ለመጻፍ አጋጣሚ ይከፍታሉ። ሚስቱ የሞተችበት አንድ ሰውና ሴት ልጁ የተወሰኑ ትራክቶችን የያዘ ደብዳቤ ከአንዲት ሴት ደረሳቸው። ከዚያም ደብዳቤውን ወደላከችላቸው አስፋፊ ቤት በመሄድ አባትየው፣ “ይህን ደብዳቤ የጻፋችሁልን እናንተ ናችሁ?” በማለት ከጠየቀ በኋላ “ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የበለጠ ማወቅ እፈልጋለሁ!” አለ። ይህ ሰውና ልጁ መጽሐፍ ቅዱስን ለማጥናት የተስማሙ ሲሆን በጉባኤ ስብሰባዎችም ላይ መገኘት ጀምረዋል።
5. በሐዘን ላይ የሚገኙ ሰዎችን ለማጽናናት የሚያስችሉ አጋጣሚዎችን በመፈለግ ረገድ ንቁዎች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
5 መክብብ 7:2 “ወደ ግብዣ ቤት ከመሄድ፣ ወደ ሐዘን ቤት መሄድ ይሻላል” በማለት ይናገራል። አብዛኛውን ጊዜ በመዝናናት ላይ ካሉ ሰዎች ይልቅ ሐዘንተኞች የአምላክን ቃል ለመስማት ፈቃደኞች ናቸው። ሁላችንም፣ የሚወዱትን ሰው በሞት በማጣት ያዘኑ ሰዎችን ለማጽናናት የሚያስችሉ ጥሩ አጋጣሚዎችን ለማግኘት ንቁዎች መሆን አለብን።