ባለጸጋ መሆን ትችላለህ!
1. ዘወትር አቅኚ ለመሆን ማሰብ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?
1 በሕይወትህ ውስጥ የበለጠ ደስታና እርካታ ማግኘት ትፈልጋለህ? ሌሎችን መርዳት ያስደስትሃል? ይሖዋን የበለጠ ለማገልገል ትመኛለህ? ከእነዚህ ጥያቄዎች መካከል ለአንዱ እንኳ አዎን የሚል መልስ ከሰጠህ የዘወትር አቅኚ ለመሆን በቁም ነገር ልታስብ ይገባል። እርግጥ ነው፣ የቤተሰብ ኃላፊነትና ሌሎች ቅዱስ ጽሑፋዊ ግዴታዎች እንዲሁም የጤና ሁኔታና የአቅም ውስንነት ግምት ውስጥ መግባት ይኖርባቸዋል።
2. የዘወትር አቅኚዎች ከሚያገኟቸው መንፈሳዊ ብልጽግናዎች አንዳንዶቹን ጥቀስ።
2 ሰሎሞን በመንፈስ አነሳሽነት በጻፈው መጽሐፍ ላይ የይሖዋን በረከት ከቁሳዊ ብልጽግና ጋር አያይዞ ጠቅሶታል። (ምሳሌ 10:22) በዛሬው ጊዜ የይሖዋ በረከት የሚያስገኘው ውጤት በዋነኝነት መንፈሳዊ ብልጽግና ነው። የዘወትር አቅኚዎች እንዲህ ያለውን የተትረፈረፈ ብልጽግና ማግኘት ይችላሉ። ለምሳሌ ያህል፣ የዘወትር አቅኚዎች ከግል ጉዳዮቻቸው ላይ ጊዜ ‘በመዋጀት’ ሌሎችን በመርዳታቸው የበለጠ ደስታ ማግኘት ችለዋል። (ቈላ. 4:5 የ1954 ትርጉም፤ ሥራ 20:35) ይሖዋም የሚያከናውኑትን ከፍቅር የመነጨ ሥራ ይመለከታል እንዲሁም ያደንቃል። እንዲህ ያለው ‘በሰማይ የተከማቸ ሀብት’ ፈጽሞ አይጠፋም። (ማቴ. 6:20፤ ዕብ. 6:10) ከዚህም በላይ አቅኚዎች ‘ጤናማ ዓይን’ በመያዝ ለሕይወት አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን እንደሚሰጣቸው በይሖዋ እንደሚታመኑ ስለሚያሳዩ ከእሱ ጋር ያላቸው ዝምድና የበለጠ እየጠነከረ ይሄዳል።—ማቴ. 6:22, 25, 32፤ ዕብ. 13:5, 6
3. በመንፈሳዊ ለመበልጸግ ጥረት በማድረግና ሀብት በማሳደድ መካከል ምን ልዩነት አለ?
3 ቁሳዊ ሀብትን ማሳደድ በአብዛኛው “ወደ ብዙ ከንቱና ክፉ ምኞት” ይመራል። (1 ጢሞ. 6:9, 10፤ ያዕ. 5:1-3) የይሖዋ በረከት ግን ከዚህ ፍጹም ተቃራኒ ነው። የዘወትር አቅኚዎች አብዛኛውን ጊዜያቸውን በአገልግሎት ማሳለፋቸው መንፈሳዊ ሚዛናቸውን እንዲጠብቁና ከሁሉ የሚሻለውን ነገር ለይተው እንዲያውቁ ይረዳቸዋል። (ፊልጵ. 1:10) አንድ ወንድም፣ አቅኚ ለመሆን ሲል ጊዜውን ይሻማበት የነበረውን የምህንድስና ሥራውን አቆመ። ይህ ወንድም እንዲህ በማለት ተናግሯል:- “ሥራዬ ከፍተኛ ውጥረት ፈጥሮብኝ ነበር። አቅኚነትን ግን ከዚህ የተለየ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። ሰዎች እውነትን እንዲያውቁ መርዳት ከምንም በላይ አርኪና አስደሳች ሥራ ነው።”
4. የዘወትር አቅኚዎች ለሌሎች በረከት መሆናቸው መልሶ የሚክሳቸው እንዴት ነው?
4 ለሌሎች በረከት መሆን:- ሁላችንም የምንኖረው ‘በሚያስጨንቅ ጊዜ’ ውስጥ ነው። (2 ጢሞ. 3:1) በመሆኑም በየትኛውም አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች፣ ተስፋ የሚፈነጥቅላቸው ነገር በእጅጉ ያስፈልጋቸዋል። የመንግሥቱ አዋጅ ነጋሪዎች፣ ተስፋ ቆርጠው የነበሩ ሰዎች ለምሥራቹ ምላሽ በመስጠት ብሩሕ አመለካከት ሲይዙ መመልከት በጣም ያስደስታቸዋል። ሕይወት አድን በሆነው በዚህ ሥራ በየዓመቱ ከ800 ሰዓት በላይ የሚያሳልፉት የዘወትር አቅኚዎች ደግሞ ምንኛ የላቀ ደስታ ያገኙ ይሆን!—1 ጢሞ. 4:16
5, 6. የዘወትር አቅኚ ለመሆን ምን ሊረዳህ ይችላል?
5 የዘወትር አቅኚ ለመሆን በቁም ነገር አስበህ ታውቃለህ? እንዲህ ማድረግ እምብዛም አስፈላጊ ካልሆኑ ነገሮች ላይ ‘ጊዜ መዋጀትን’ ይጠይቃል። (ኤፌ. 5:15, 16) ይህን ለማድረግ ብዙዎች አኗኗራቸውን ቀላል አድርገዋል፤ ይህ ደግሞ ከመንግሥቱ ጋር ለተያያዙ ጉዳዮች ጊዜ ለማግኘት ሲሉ በሰብዓዊ ሥራ ላይ የሚያሳልፉትን ጊዜ ለመቀነስ ረድቷቸዋል። አንተስ፣ አቅኚ ለመሆን ሁኔታዎችህን ማመቻቸት ትችል ይሆን?
6 ተግባራዊ ሊሆን የሚችል ፕሮግራም ማውጣት እንድትችል ይሖዋን ጥበብ እንዲሰጥህ ጠይቀው። (ያዕ. 1:5) አቅኚ ብትሆን ምን በረከት የምታገኝ ይመስልሃል? የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ብልጽግና ታገኛለህ! ይሖዋ የሚያስፈልግህን ቁሳዊ ነገር በመስጠትም ይባርክሃል። (ማቴ. 6:33) በዚህ ረገድ ይሖዋን የሚፈትኑ ሁሉ ‘ማስቀመጫ እስኪያጡ ድረስ የተትረፈረፈ በረከት’ ያገኛሉ።—ሚል. 3:10