የመጨረሻውን ገጽ ተጠቅማችሁበት ታውቃላችሁ?
ሰዎች አንድ መጽሔት ሲደርሳቸው ብዙውን ጊዜ የፊት ለፊቱን ገጽ ከተመለከቱ በኋላ በደመ ነፍስ ገልብጠው የመጨረሻውን ገጽ ያዩታል። የሚበረከተው የመጠበቂያ ግንብ እትም የመጨረሻ ገጽ የሰዎችን የማወቅ ፍላጎት የሚቀሰቅሱ ጥያቄዎችንና ሐሳቦችን እንዲሁም ሐሳቦቹ የሚገኙባቸውን ገጾች ይዞ ይወጣል።
ይህን ገጽ ውይይት ለመጀመር የሚያስችሉ ግሩም የሆኑ የመግቢያ ሐሳቦችን ለማግኘት ልንጠቀምበት እንችላለን። የአገልግሎት ክልላችንን በተደጋጋሚ የምንሸፍን ከሆነ በወሩ ውስጥ የተለያዩ ጥያቄዎችን በመጠቀም መግቢያዎቻችንን መለዋወጥ እንችላለን። የቤቱ ባለቤት ሥራ ላይ ከሆነ በመጨረሻው ገጽ ላይ ከሚገኙት ጥያቄዎች አንዱን አንስተን “የዚህን ጥያቄ መልስ ማወቅ ከፈለጉ እነዚህን መጽሔቶች ትቼልዎት ልሄድና ጊዜ ሲኖርዎት ተጨማሪ ውይይት ልናደርግ እንችላለን” በማለት መግቢያችንን አጠር አድርገን ማቅረብ እንችላለን። አንዳንድ አስፋፊዎች ደግሞ ለቤቱ ባለቤት የመጨረሻውን ገጽ አሳይተው የሚፈልገውን ጥያቄ እንዲመርጥ በመጋበዝ ውይይቱን መጀመር ይፈልጉ ይሆናል። ከዚያም መልሱ የሚያገኝበትን ገጽ በማውጣት አስቀድመው የመረጡትን አንድ ጥቅስ ያነቡለታል። ምናልባት አንተም የመጠበቂያ ግንብን የመጨረሻ ገጽ ተጠቅመህ የሰዎችን የማወቅ ፍላጎት መቀስቀስ የምትችልባቸው ሌሎች መንገዶች ይኖሩህ ይሆናል።